የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት
    የመንግሥት አገልግሎት—2004 | ሚያዝያ
    • ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት

      1 ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግ ለእርሱ በመሥዋዕትነት የሚቀርብ እንስሳ ‘እንከን የሌለበት’ እንዲሆን ይደነግግ ነበር። ጉድለት ያለበት እንስሳ ተቀባይነት አልነበረውም። (ዘሌ. 22:18-20፤ ሚል. 1:6-9) በተጨማሪም መሥዋዕት ሲቀርብ ለይሖዋ የሚሰጠው ስቡ ማለትም ምርጥ የሆነው ክፍል ነበር። (ዘሌ. 3:14-16) ይሖዋ የእስራኤል አባትና ጌታ እንደመሆኑ መጠን ምርጥ የሆነው ሊሰጠው ይገባ ነበር።

      2 እንደ ጥንቱ ሁሉ ዛሬም አምላክ ለምናቀርብለት መሥዋዕት ጥራት ትኩረት ይሰጣል። አገልግሎታችን ለይሖዋ ተገቢ አክብሮት እንዳለን የሚያሳይ መሆን አለበት። እርግጥ ነው፣ ሁኔታችን ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። ቢሆንም ለይሖዋ የምንሰጠው ምርጣችንን እንደሆነና እንዳልሆነ ራሳችንን መመርመራችን ተገቢ ነው።​—⁠ኤፌ. 5:10

      3 በሙሉ ልብ የሚቀርብ አገልግሎት፦ አገልግሎታችን ይሖዋን የሚያስከብርና የአድማጮቻችንን ልብ የሚነካ እንዲሆን በዘልማድ የሚደረግ መሆን የለበትም። ስለ ይሖዋና ስለ ታላላቅ ዓላማዎቹ የምንናገረው መልእክት በአድናቆት ከተሞላ ልብ የመነጨ መሆን ይኖርበታል። (መዝ. 145:7) ይህ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና የግል ጥናት ፕሮግራማችንን በቋሚነት የመጠበቅን አስፈላጊነት ያጎላል።​—⁠ምሳሌ 15:28

      4 ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት እርሱ ለሰዎች ያለውን ፍቅር መኮረጅንም ይጨምራል። (ኤፌ. 5:1, 2) ለሰዎች ያለን ፍቅር ሕይወት አድን የሆነውን የእውነት መልእክት በተቻለን መጠን ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ ጥረት እንድናደርግ ያነሳሳናል። (ማር. 6:34) እንዲሁም ለምናነጋግራቸው ሰዎች ልባዊ አሳቢነት እንድናሳይ ይገፋፋናል። ከመጀመሪያው ውይይታችን በኋላ ስለ እነርሱ እንድናስብና ብዙም ሳንቆይ ተመልሰን እንድንሄድ ያደርገናል። በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ አቅማችን በፈቀደው መጠን እንድንረዳቸው ይገፋፋናል።​—⁠ሥራ 20:24፤ 26:28, 29

      5 ‘የምስጋና መሥዋዕት’፦ ለይሖዋ ምርጣችንን የምንሰጥበት ሌላው መንገድ አገልግሎታችንን በትጋት በማከናወን ነው። አስቀድመን በሚገባ ከተዘጋጀንና ሙሉ ትኩረታችንን በአገልግሎታችን ላይ ካደረግን ጊዜያችንን ውጤታማ በሆነ መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን። (1 ጢ⁠ሞ. 4:10) ጥሩ ዝግጅት መልእክታችንን ግልጽና አሳማኝ በሆነ መንገድ ለማቅረብ ስለሚያስችለን የምናነጋግራቸው ሰዎች ለመልእክታችን ጥሩ ምላሽ እንዲሰጡ ሊያደርጋቸው ይችላል። (ምሳሌ 16:21) ለሌሎች ምሥራቹን የምንናገረው ከልብ በመነጨ መንፈስ ከሆነ በእርግጥም ‘የምስጋና መሥዋዕት’ ሊባልልን ይችላል።​—⁠ዕብ. 13:15

  • ወጣቶች—የአምላክን ቃል አንብቡ!
    የመንግሥት አገልግሎት—2004 | ሚያዝያ
    • ወጣቶች​—⁠የአምላክን ቃል አንብቡ!

      1 ወጣትነት ፈተናዎች የሚያጋጥሙበትና ከባድ ውሳኔዎች የሚደረጉበት ወቅት ነው። ብዙ ወጣት ክርስቲያኖች በየዕለቱ የአምላክን የሥነ ምግባር መስፈርቶች እንዲጥሱ ተጽዕኖዎች ይደረጉባቸዋል። ከትምህርት፣ ከሥራና ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ማንኛውንም ውሳኔ ከማድረጋችሁ በፊት መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣት ይኖርባችኋል። ሌሎች ውሳኔዎቻችሁ በቀሪው ሕይወታችሁ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዲኖራቸው ማድረግ የምትችሉት በዚህ መንገድ ብቻ ነው። በግልጽ የተቀመጡ መንፈሳዊ ግቦች ያሏችሁ መሆኑ በማስተዋል እርምጃ እንድትወስዱና መንገዳችሁ የተቃና እንዲሆን ይረዳችኋል። የአምላክን ቃል ዘወትር የምታነብቡና የምታሰላስሉ ከሆነ በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው ምክሩ ጋር ተስማምታችሁ እንድትኖሩ የሚገፋፋችሁ ከመሆኑም በላይ የምታደርጓቸው መልካም ጥረቶች ይሳኩላችኋል።​—⁠ኢያሱ 1:8፤ መዝ. 1:2, 3

      2 መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችሁ የሚጠቅማችሁ እንዴት ነው? የሰይጣን ዓለም መጥፎ ድርጊቶችን እንድንፈጽም በሚገፋፉ ማባበያዎች የተሞላ ነው። (1 ዮሐ. 2:15, 16) እናንተም ከክፍላችሁ ተማሪዎች ወይም በእናንተ ዕድሜ ካሉ ልጆች መካከል በእኩዮቻቸው ግፊት በመሸነፋቸው ምክንያት ለችግር የተዳረጉ ወጣቶችን ታውቁ ይሆናል። የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በጥብቅ መከተላችሁ ኃጢአት ከመሥራት እንድትቆጠቡ የሚያስችል ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ጥንካሬ ይሰጣችኋል። ከዚህም በላይ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ምክር በሰይጣን ስውር ወጥመድ እንዳትያዙ ሊረዳችሁ ይችላል። (2 ቆ⁠ሮ. 2:11፤ ዕብ. 5:14) በአምላክ መንገድ መሄድ እውነተኛ ደስታ እንድታገኙ ወይም እርካታ ያለው ሕይወት እንድትመሩ ያስችላችኋል።​—⁠መዝ. 119:1, 9, 11

      3 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት ጊዜ የማይሽራቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ከሰብዓዊ ጥበብ እጅግ የላቁ ናቸው። (መዝ. 119:98-100) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚገባ ማወቃችሁና በይሖዋ ዓላማዎች ላይ ማሰላሰላችሁ እንዲሁም ልባዊ ጸሎት ማቅረባችሁ በጥበቡ አቻ ከሌለው የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ጋር የቀረበ ወዳጅነት እንድትመሠርቱ ሊረዳችሁ ይችላል። እርሱ “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ” በማለት ቃል ገብቷል።​—⁠መዝ. 32:8

      4 ለማንበብ ጊዜ መድቡ:- አንዲት ወጣት ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ለማንበብ ግብ ያወጣች ሲሆን በአንድ ዓመት ውስጥ አንብባ ጨረሰች። ምን ጥቅም አገኘች? እንዲህ ትላለች:- “ስለ ይሖዋ ብዙ ነገሮችን ተምሬያለሁ። እነዚህ ነገሮች ወደ እርሱ ይበልጥ እንድቀርብ እንዲሁም በቀሪው ሕይወቴ እርሱን እንድፈራ የሚያደርጉ ናቸው።” (ያዕ. 4:8) እናንተስ መጽሐፍ ቅዱስን አንብባችሁ ጨርሳችኋል? ካልሆነ ለምን ግብ አታወጡም? ይሖዋ ጥረታችሁን የሚባርክ ከመሆኑም በላይ ታላላቅ በረከቶችን ታጭዳላችሁ።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ