በመንፈሳዊ በደንብ ትመገባለህ?
“የተመጣጠነ ምግብ የሰው ልጅ ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች አንዱ ነው። . . . በቂ ምግብ ካልተመገብን እንሞታለን።”— ፉድ ኤንድ ኒውትሪሽን (እንግሊዝኛ)
ይህን ከሁሉ “የላቀ የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎት” ተነፍገው ሰውነታቸው እየመነመነ በመሄድ ላይ ያሉ ረሃብ ያጠቃቸው ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ሁኔታ ይህን መሠረታዊ ሐቅ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። አንዳንዶች ይህ መሠረታዊ ፍላጎት በመጠኑ ቢሟላላቸውም የተመጣጠነ ምግብ በጣም ያስፈልጋቸዋል። እንደልብ ምግብ ማግኘት የሚችሉ ብዙዎች ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ምንም ገንቢነት በሌለው አሸር ባሸር ምግብ ሆዳቸውን ይሞላሉ። ሄልዚ ኢይቲንግ የተባለው መጽሐፍ “ካሉን ነገሮች ሁሉ አለአግባብ የምንጠቀምበት ምግብን ሳይሆን አይቀርም” በማለት ይናገራል።
መንፈሳዊ ምግብን ማለትም የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አንዳንድ ሰዎች ሌላው ቀርቶ መሠረታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ አያገኙም፤ በመንፈሳዊ ይራባሉ። ሌሎች ደግሞ የሚቀርብላቸውን መንፈሳዊ ምግብ ከመመገብ ቸል ይላሉ። በዚህ ረገድ አንተ እንዴት ነህ? በግለሰብ ደረጃ በመንፈሳዊ በደንብ ትመገባለህ? ወይስ ራስህን መንፈሳዊ ምግብ እየነፈግክ ነው? መንፈሳዊ ምግብ ከሰብዓዊ ምግብም እንኳ የበለጠ ስለሚያስፈልገን በዚህ ረገድ ራሳችንን ማታለል የለብንም።— ማቴዎስ 4:4
ለመንፈሳዊ እድገት የሚረዳ ምግብ
የተስተካከለ አመጋገብ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያብራራው ፉድ ኤንድ ኒውትሪሽን የተባለው የመማሪያ መጽሐፍ በደንብ መመገብ አስፈላጊ የሆነባቸውን ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች ይሰጠናል። ምግብ የሚያስፈልገን አንደኛው ምክንያት “እድገትን ለማፋጠንና በየጊዜው የሚሞቱትን የሰውነታችን ሴሎች ለመተካት” ነው። በየዕለቱ በትሪሊዮን የሚቆጠሩ የሰውነትህ ሴሎች እንደሚሞቱና እነዚህ ሴሎች ደግሞ መተካት እንደሚያስፈልጋቸው ታውቃለህን? ተገቢውን እድገት ለማድረግና ሰውነታችንን ለመጠገን የተመጣጠነ ምግብ ያስፈልጋል።
በመንፈሳዊም ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለሚገኘው ጉባኤ ሲጽፍ ‘ወደ ሙሉ ሰውነት’ ለመድረስ እያንዳንዱ ክርስቲያን የተመጣጠነ መንፈሳዊ ምግብ እንደሚያስፈልገው ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (ኤፌሶን 4:11-13) ገንቢ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ በደንብ አድርገን ራሳችንን የምንመግብ ከሆነ ምንም አቅም እንደሌላቸውና ራሳቸውን መከላከል እንደማይችሉ ሕፃናት ለማንኛውም አደጋ የተጋለጥን ደካማ ፍጥረታት አንሆንም። (ኤፌሶን 4:14) ከዚህ ይልቅ ‘የእምነትን ቃል በመመገባችን’ ከፍተኛ የእምነት ተጋድሎ ማድረግ የምንችል ጠንካራና የጎለመስን ሰዎች እንሆናለን።— 1 ጢሞቴዎስ 4:6
አንተ እንዲህ እያደረግህ ነውን? በመንፈሳዊ ጎልምሰሃልን? ወይስ አሁንም በመንፈሳዊ ገና ሕፃን ማለትም ራስህን ከአደጋ የመከላከል አቅም የሌለህ፣ ሙሉ በሙሉ በሌሎች ጥገኛ የሆንክና ሙሉ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶችን መሸከም የማትችል ነህ? በመንፈሳዊ ሕፃናት መሆናችንን ያለ ማንገራገር የምንቀበል ጥቂቶች እንደምንሆን የታወቀ ነው፤ ሆኖም በሐቀኝነት ራስን መመርመር ተገቢ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ሕፃናት ነበሩ። ምንም እንኳ እነሱ ራሳቸው የአምላክ ቃል የሚናገረውን ለሌሎች ማስተማር የሚችሉና ፈቃደኛ “አስተማሪዎች” መሆን ይገባቸው የነበሩ ቢሆንም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነት ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም።” በመንፈሳዊ ለማደግ የምትፈልግ ከሆነ ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ የመመገብ ፍላጎት አዳብር። በመንፈሳዊ ሕፃናት የሆኑ ሰዎች በሚመገቡት መንፈሳዊ ምግብ ብቻ አትርካ!— ዕብራውያን 5:12
በተጨማሪም ጠላት በሆነ ዓለም ውስጥ ዕለት ተዕለት በሚያጋጥሙን ፈተናዎች የሚደርስብንን ማንኛውም ዓይነት ጉዳት ለመጠገን ጠንካራ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልገናል። እነዚህ ፈተናዎች መንፈሳዊ ኃይላችንን ሊያሟጥጡ ይችላሉ። ሆኖም አምላክ ኃይላችንን ሊያድስልን ይችላል። ጳውሎስ “አንታክትም፣ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 4:16) ‘ዕለት ዕለት የምንታደሰው’ እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ቅዱሳን ጽሑፎችንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በግልና በቡድን በማጥናት ከአምላክ ቃል ዘወትር መመገብ ነው።
መንፈሳዊ ኃይል ለማግኘት የሚረዳ ምግብ
በተጨማሪም ምግብ የሚያስፈልገው “ሙቀትና ኃይል ለማመንጨት” ነው። ሰውነታችን በሚገባ እንዲሠራ የሚያደርገውን ኃይል የሚያገኘው ከምግብ ነው። በደንብ ካልተመገብን ኃይል ያንሰናል። ምግባችን የብረት ማዕድን ከሌለው ድካም ድካም ሊለንና አቅመ ቢሶች ልንሆን እንችላለን። መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ይሰማሃልን? ከክርስቲያንነትህ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ግዴታዎችን መወጣት ያዳግትሃልን? የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ነን የሚሉ አንዳንዶች መልካም ለመሥራት ይታክታሉ፤ እንዲሁም ለክርስቲያናዊ ሥራዎች አቅም ያንሳቸዋል። (ያዕቆብ 2:17, 26) እንዲህ ዓይነት ችግር ካለብህ ትልቁ መፍትሄ የመንፈሳዊ ምግብህን ጥራት ማሻሻል ወይም መጠኑን መጨመር ነው።— ኢሳይያስ 40:29-31፤ ገላትያ 6:9
የተሳሳተ መንፈሳዊ የአመጋገብ ልማድ በማዳበር አትታለል። ሰይጣን ለብዙ መቶ ዘመናት ሲጠቀምበት የኖረው ትልቁ የማታለያ ዘዴ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና በውስጡ የያዘውን ትክክለኛ እውቀት ማግኘት እንደማያስፈልጋቸው ማሳመን ነው። ሰይጣን የሚጠቀምበት ዘዴ ጥንት ወራሪ ሠራዊት የጠላትን ከተሞች በቁጥጥሩ ሥር ለማዋል የሚገለገልበት ዓይነት ዘዴ ማለት ከተማውን በመክበብ ነዋሪዎቹ ምግብ እንዳያገኙና በረሀብ ተጎሳቁለው እጃቸውን እንዲሰጡ ማድረግ ነው። ሆኖም ሰይጣን ይህን ዘዴ ትንሽ ረቀቅ ባለ ሁኔታ ይጠቀምበታል። ጤናማ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ሞልቶ ተትረፍርፎ እያለ ከዚህ መንፈሳዊ ምግብ መብላት ተስኗቸው እንዲራቡ በማድረግ ሰይጣን “የከበባቸውን” ሰዎች ያታልላቸዋል። ብዙዎች ለእሱ ጥቃት የተጋለጡ መሆናቸው ምንም አያስደንቅም!— ኤፌሶን 6:10-18
ለመንፈሳዊ ጤንነት የሚረዳ ምግብ
ምግብ አስፈላጊ የሆነበት ሦስተኛው ምክንያት ይላል ፉድ ኤንድ ኒውትሪሽን የተባለው መጽሐፍ “ጤንነትን ለመጠበቅና . . . በሽታን ለመከላከል” ነው። የተመጣጠነ ምግብ ከጤና አኳያ ያለው ጠቀሜታ ወዲያው የሚታይ አይደለም። የተመጣጠነ ምግብ በልተን እንደጨረስን ‘ለልቤ (ወይም ለኩላሊቴ ወይም ለጡንቻዎቼ እና ለመሳሰሉት) ይጠቅመኛል’ ብለን ብዙውን ጊዜ አናስብም። ሆኖም ረዘም ላለ ጊዜ ምግብ ለመተው ብትሞክር በጤንነትህ ላይ የሚያስከትለው ውጤት ግልጽ እየሆነ ይመጣል። ውጤቱ ምንድን ነው? “የተመጣጠነ ምግብ እጦት የሚያስከትለው የተለመደ ውጤት ጎጂ እንደሆነ ማለትም መጫጫት፣ በቀላሉ ለበሽታ የተጋለጡ መሆን፣ የኃይል ወይም የአቅም ማጣት እንደሚያስከትል” አንድ ጥናታዊ የሕክምና ጽሑፍ ይናገራል። ባንድ ወቅት በጥንት እስራኤላውያን ላይ ተመሳሳይ የሆነ የመንፈሳዊ ጤንነት መቃወስ ደርሶ ነበር። ነቢዩ ኢሳይያስ እነሱን በተመለከተ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ራስ ሁሉ ለሕመም ልብም ሁሉ ለድካም ሆኖአል። ከእግር ጫማ አንሥቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም።”— ኢሳይያስ 1:5, 6
የተመጣጠነ መንፈሳዊ ምግብ እንዲህ ዓይነቱን መንፈሳዊ ልፍስፍስነትና ይህ የሚያመጣውን መንፈሳዊ በሽታ ለመቋቋም የሚረዳንን ኃይል ይሰጠናል። አምላክ የሚሰጠውን እውቀት የምንመገብ ከሆነ በመንፈሳዊ ዘወትር ጤናሞች ሆነን ለመቀጠል እንችላለን! ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች የቀድሞ አባቶቻቸው በመንፈሳዊ በደንብ በመመገብ ረገድ ያሳዩት ቸልተኝነት ትምህርት እንዳልሆናቸው አስተያየት ሰጥቷል። በዘመኑ የነበሩት ሰዎች እሱ ከሚያስተምረው እውነት ለመመገብ አሻፈረን ብለዋል። ይህስ ምን ውጤት አስከተለባቸው? ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “በዓይናቸው እንዳያዩ፣ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፣ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፣ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጀሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል።” (ማቴዎስ 13:15) አብዛኞቹ የአምላክ ቃል ካለው የመፈወስ ኃይል ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። በመንፈሳዊ በሽተኞች እንደሆኑ ቀጥለዋል። ሌላው ቀርቶ አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንኳ ‘ደካማና በሽተኛ’ ሆነው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 11:30) አምላክ የሚያቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ ፈጽሞ መናቅ የለብንም።— መዝሙር 107:20
መንፈሳዊ ብክለት
በመንፈሳዊ እንዳንራብ ከመስጋት በተጨማሪ ልንጠነቀቅ የሚገባን ሌላ አደጋም አለ፤ የምንመገበው ምግብ ራሱ የተበከለ ሊሆን ይችላል። በጀርም ወይም በመርዝ የተበከለ ሰብዓዊ ምግብ መመገብ በቀላሉ ሊመርዘን እንደሚችል ሁሉ አደገኛ በሆኑ አጋንንታዊ ሐሳቦች የተበከለ ትምህርት መመገብም ሊመርዘን ይችላል። (ቆላስይስ 2:8) የተመረዘ ምግብ መለየት ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ነው። “አንዳንድ ጊዜ ምግብ በሽታ የሚያመጡ ባክቴሪያዎች እያሉበት ምንም ጎጂ ነገር የሌለበትና ለጤና የሚስማማ መስሎ ሊታይ ይችላል” ሲሉ አንድ ጠበብት ተናግረዋል። ስለዚህ ከሃዲዎች እንደሚያዘጋጁአቸው ባሉ መጥፎ ጽሑፎች አማካኝነት ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ትምህርቶችና ፍልስፍናዎች ሊበከል ስለሚችል የምሳሌያዊ ምግባችን ምንጭ ምን እንደሆነ መመርመራችን ጥበብ ነው። እንዲያውም አንዳንድ የምግብ አምራቾች የምርታቸውን ይዘት በተመለከተ ደንበኞቻቸውን የሚያሳስት ነገር ምግቡ በሚታሸግበት ዕቃ ላይ ይለጥፋሉ። ቀንደኛው አታላይ ሰይጣንም ተመሳሳይ ነገር እንደሚያደርግ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ስለዚህ ‘በእምነት ጤናማ’ ሆነህ ለመቀጠል ምሳሌያዊ ምግብህን ሊታመን ከሚችል ምንጭ ማግኘት ይኖርብሃል።— ቲቶ 1:9, 13
ቶማስ አዳምስ የተባሉ አንድ የ17ኛው መቶ ዘመን ሰባኪ በእሳቸው ዘመን የነበሩትን ሰዎች በተመለከተ “በጥርሳቸው የገዛ መቃብራቸውን ቆፍረዋል” ሲሉ ተናግረው ነበር። በሌላ አባባል የገደላቸው የበሉት ነገር ነበር። በመንፈሳዊ የምትመገበው ነገር የማይገድልህ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብሃል። ጥሩ የመንፈሳዊ ምግብ አቅርቦት ለማግኘት ጣር። ሕዝቦቹ እንደሆኑ ይናገሩ የነበሩት ሰዎች ወደ ሐሰት አስተማሪዎችና ነቢያት ዞር ባሉበት ጊዜ ይሖዋ አምላክ “ገንዘብን እንጀራ ላይደለ . . . ነገር ለምን ትመዝናላችሁ?” ሲል ጠይቆ ነበር። “አድምጡኝ፣ በረከትንም ብሉ፣ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ፤ ስሙ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች።”— ኢሳይያስ 55:2, 3፤ ከኤርምያስ 2:8, 13 ጋር አወዳድር።
የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ
የተመጣጠነ መንፈሳዊ ምግብ እጥረት በፍጹም የለም። ኢየሱስ ክርስቶስ በትንቢት እንደተናገረው በአሁኑ ጊዜ ለሚፈልግ ለማንኛውም ሰው ‘በተገቢው ጊዜ ምግብ’ በማቅረብ ተግቶ የሚሠራ የታማኝና ልባም ባሪያ ቡድን አለው። (ማቴዎስ 24:45) ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት “እነሆ፣ ባሪያዎቼ ይበላሉ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ . . . እነሆ፣ ባሪያዎቼ ከልባቸው ደስታ የተነሳ ይዘምራሉ” ሲል ቃል ገብቷል። እንዲያውም መብላት ለሚፈልጉ ሁሉ የሰባ ግብዣ እንደሚያዘጋጅ ተስፋ ሰጥቷል። “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝብ ሁሉ . . . ታላቅ የሰባ ግብዣ፣ ያረጀ የወይን ጠጅ፣ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፣ . . . ግብዣ ያደርጋል።”— ኢሳይያስ 25:6፤ 65:13, 14
መንፈሳዊ ምግብ ሞልቶ ተትረፍርፎ እያለ በረሀብ ልንጠቃ እንደምንችል እዚህ ላይ ልብ በል! የተትረፈረፈ ምግብ አጠገባችን ቢኖርም አንስተን በደንብ ካልተመገብን በረሀብ ልንጠቃ እንችላለን። ምሳሌ 26:15 (የ1980 ትርጉም) “አንዳንድ ሰዎች በጣም ሰነፎች ናቸው፤ ሌላው ቀርቶ በወጥ ያጠቀሱትን እንጀራ መጉረስ ያታክታቸዋል” በማለት ይህን ቃል በቃል ይገልጻል። እንዴት የሚያሳዝን ነው! እኛም በተመሳሳይ መንፈሳዊ ምግብ እንድንመገብ በተዘጋጀልን በአምላክ ቃልና መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆኑ ጽሑፎች ላይ የግል ጥናት በማድረግ ረገድ በጣም ሰነፎች ልንሆን እንችላለን። ወይም በጣም ከመታከታችን የተነሳ ለክርስቲያን ጉባኤ ስብሰባዎች ሳንዘጋጅና ተሳትፎ ሳናደርግ እንቀር ይሆናል።
ጥሩ የአመጋገብ ልማድ
እንግዲያው ጥሩ የአመጋገብ ልማድ እንድናዳብር የሚገፋፉን ብዙ ምክንያቶች አሉ። ሐቁ ግን ብዙዎች መንፈሳዊ ምግብ በደንብ አይመገቡም፤ እንዲያውም አንዳንዶች ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለመንፈሳዊ ረሀብ አጋልጠዋል። የኋላ ኋላ በሕይወታቸው ላይ የሚያስከትለውን ችግር እስኪቀምሱ ድረስ ሰብዓዊ ምግብ በደንብ መመገብ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንደማይገነዘቡ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ሄልዚ ኢቲንግ የተባለው መጽሐፍ ጥሩ አድርጎ መመገብ ለሕይወት የግድ አስፈላጊ መሆኑን ብናውቅም እንኳ በአመጋገብ ልማዳችን ረገድ ግዴለሾች ልንሆን የምንችልባቸውን እነዚህን ምክንያቶች ይሰጠናል:- “ችግሩ [በደንብ አለመመገብ የሚያስከትለው ውጤት] በግዴለሽነት መንገድ ማቋረጥ እንደሚያስከትለው አደጋ ሁሉ በጤና ላይ የሚያስከትለው ውጤት በቅጽበት የሚታይ አለመሆኑ ነው። ከዚህ ይልቅ አንድ ሰው ጤንነቱ ቀስ በቀስ፣ ሳይታወቀው እያሽቆለቆለ ሊሄድና በቀላሉ ለበሽታ ሊጋለጥ፣ አጥንቶቹ ደካማ ሊሆኑ፣ ቁስል ቢኖረው ወይም ቢታመም ለመዳን ረጅም ጊዜ ሊወስድበት ይችላል።”
ክብደት እጨምራለሁ ብላ በመፍራት የተሳሳተ የአመጋገብ ልማድ የምታዳብር ወጣት ከሚደርስባት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነገር አንድ ሰው ሊያጋጥመው ይችላል። ምንም እንኳ ሰውነቷ እየመነመ ቢሄድም በጣም ደህና እንደሆነችና ብዙ መብላት እንደማያስፈልጋት ራሷን ታሳምናለች። በመጨረሻ ሙሉ በሙሉ የምግብ ፍላጎቷ ይጠፋል። አንድ ጥናታዊ የሕክምና ጽሑፍ “ይህ በጣም አደገኛ ነው” ይላል። ለምን? “ምንም እንኳ ረሀቡ ብዙውን ጊዜ በሽተኛዋን ለሞት ባያደርሳትም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሊያጋጥማትና በቀላሉ ለበሽታ የተጋለጠች ልትሆን ትችላለች።”
አንዲት ክርስቲያን “ዘወትር ለስብሰባ የመዘጋጀትንና የግል ጥናት የማድረግን አስፈላጊነት እያወቅሁ ነገር ግን ፈጽሞ ይህን ማድረግ ሳልችል ለብዙ ዓመታት ትግል አድርጌያለሁ” ስትል አምናለች። በመጨረሻ ለውጥ አድርጋ ትጉ የአምላክ ቃል ተማሪ ሆነች፤ ሆኖም ይህን እርምጃ የወሰደችው አደገኛ ሁኔታ ላይ እንደደረሰች ሙሉ በሙሉ ከተገነዘበች በኋላ ነው።
እንግዲያው ሐዋርያው ጴጥሮስ የሰጠውን ምክር ልብ በል። “ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኮል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።” (1 ጴጥሮስ 2:2) አዎን፣ አምላክ በሚሰጠው እውቀት አእምሮህንና ልብህን ለመሙላት ‘ምኞት’ ማለትም ጠንካራ ፍላጎት አዳብር። በመንፈሳዊ የጎለመሱም ሰዎች ይህን ጉጉት ማሳደግ ያስፈልጋቸዋል። መንፈሳዊ ምግብ ‘ካሉህ ነገሮች ሁሉ አለአግባብ የምትጠቀምበት ነገር’ እንዲሆን አታድርግ። በመንፈሳዊ በደንብ በመመገብ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ‘ጤናማ ቃል’ ሙሉ በሙሉ ተጠቀም።—2 ጢሞቴዎስ 1:13, 14
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአመጋገብ ልማድህን ማሻሻል ያስፈልግህ ይሆን?