ምሥራቹ የሚገባቸውን ሰዎች ፈልጉ
1. ላገኘነው የአገልግሎት መብት አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
1 ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ለሰዎች የሚያጽናና ምሥራች ለመንገር ያልተጓዘበት ቦታ የለም ማለት ይቻላል። (ኢሳ. 61:1, 2) እኛም የክርስቶስ አምባሳደሮችና መልእክተኞች እንደመሆናችን መጠን በክልላችን ውስጥ ምሥራቹ የሚገባቸውን ሰዎች ሁሉ ሳናሰልስ በመፈለግ ለአገልግሎታችን አድናቆት እንዳለን ማሳየት እንችላለን።—ማቴ. 10:11፤ 2 ቆሮ. 5:20
2. ጳውሎስ ዘዴኛ እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው? በዚህስ ምን ውጤት አግኝቷል?
2 ዘዴኞች ሁኑ፦ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ለአይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት ለተለወጡ ሰዎች ለመመሥከር በመጀመሪያ ወደ ምኩራብ የመሄድ ልማድ ነበረው። (ሥራ 14:1) እሱና ሲላስ ወደ ፊልጵስዩስ በሄዱ ጊዜ ሰዎችን ለመፈለግ ‘የጸሎት ስፍራ ይገኝበታል ብለው ወዳሰቡት’ ቦታ ሄደው ነበር። በዚያም ተሰብስበው ለነበሩት ሴቶች መመሥከር የጀመሩ ሲሆን ከሴቶቹ መካከል ሊዲያ የተባለች አንዲት ሴት ወዲያውኑ እውነትን ተቀበለች።—ሥራ 16:12-15
3. ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ከማገልገል በተጨማሪ ለመመሥከር የሚያስችሉ ምን ሌሎች አጋጣሚዎች አሉ?
3 ከቤት ወደ ቤት እየሄዳችሁ ከማገልገል በተጨማሪ በአውቶቡስ ፌርማታዎች፣ በመናፈሻ ቦታዎች፣ በመሥሪያ ቤቶች፣ ሰው በሚበዛባቸው ጎዳናዎች፣ በገበያ ቦታዎችና በንግድ ማዕከሎች ለምታገኟቸው ሰዎች መመሥከር ትችሉ ይሆን? በቀላሉ መግባት በማይቻልባቸው ግቢዎችና ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግባቸው ሕንጻዎች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች በደብዳቤ አሊያም በስልክ መመሥከር ትችሉ ይሆናል። አስተዋዮችና አቀራረባችሁን እንደ ክልሉ ሁኔታ የምትለዋውጡ መሆናችሁ “የጌታ ሥራ የበዛላችሁ” እንድትሆኑ ያስችላችኋል።—1 ቆሮ. 15:58
4. የጉባኤያችን ክልል ሰፊ ካልሆነ ለመመሥከር የትኞቹን አጋጣሚዎች መጠቀም እንችላለን?
4 በርካታ አስፋፊዎች በአገራቸው ወደሚገኝ ሌላ ጉባኤ ወይም ክልል በመዛወር አገልግሎታቸውን ማስፋት ችለዋል። አንዳንዶች ደግሞ ከሌሎች አገሮች ለመጡ ሰዎች ለመመሥከር ሌላ ቋንቋ ተምረዋል።
5. ስለምንኖርበት ጊዜ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ቁርጥ ውሳኔያችንስ ምን መሆን ይኖርበታል?
5 ሁላችንም “እርሻው ዓለም” እንደሆነ ምንጊዜም መዘንጋት አይኖርብንም። (ማቴ. 9:37፤ 13:38) የዚህ ክፉ ሥርዓት መደምደሚያ እየቀረበ እንደመሆኑ መጠን እያንዳንዳችን አገልግሎታችንን ለማስፋት የሚያስችል ምን ሁኔታ፣ ተሰጥኦ አሊያም አጋጣሚ እንዳለን በቁም ነገር ልናስብበት ይገባል። ይሖዋ መንግሥቱን እስካስቀደምን ድረስ አገልግሎታችንን ለማስፋት የምናደርገውን ልባዊ ጥረት እንደሚባርክልን ማረጋገጫ ሰጥቶናል።—ማቴ. 6:33