የማንን ትኩረት ሊስቡ ይችላሉ?
1. መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ስናነብ ምን ነገር ማሰብ ይኖርብናል? ለምንስ?
1 መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! የሚዘጋጁት በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። በመሆኑም መጽሔቶቹ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስሳሉ። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ላይ የሚወጣውን እያንዳንዱን ርዕስ ስናነብ በተለይ የእነማንን ትኩረት ሊስብ እንደሚችል በቁም ነገር ማሰባችንና መጽሔቶቹን ለእነሱ ለማበርከት ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው።
2. በመጽሔቶቻችን ላይ የሚወጡ የትኞቹ ርዕሰ ጉዳዮች የሰዎችን ትኩረት ሊስቡ ይችላሉ?
2 በቅርቡ የደረሰን መጠበቂያ ግንብ ከሥራ ባልደረባችሁ ጋር ከዚህ ቀደም የተወያያችሁበትን ርዕሰ ጉዳይ የያዘ ነው? አሊያም ዘመዳችሁን ሊጠቅም የሚችል ስለ ቤተሰብ ሕይወት የሚናገር ርዕስ አለው? በንቁ! መጽሔት ላይ ዘገባ ወደቀረበለት አንድ አገር ለመሄድ ያሰበ የምታውቁት ሰው አለ? በመጽሔቶቻችን ላይ የወጣው ሐሳብ ትኩረታቸውን ሊስብ የሚችሉ የንግድ ድርጅቶች ወይም መሥሪያ ቤቶች በክልላችሁ ውስጥ አሉ? ለምሳሌ በቅርቡ የወጣው መጽሔት አረጋውያን ስለሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች የሚያወሳ ከሆነ አረጋውያንን የሚንከባከቡ ተቋማት ውስጥ ብናበረክተው ትኩረታቸው ሊሳብ ይችላል። ሕግ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ደግሞ ስለ ወንጀል የሚናገሩ መጽሔቶች ቀልባቸውን ሊስቡ ይችላሉ።
3. ለየት ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን የያዙ መጽሔቶች በሚወጡበት ጊዜ ትኩረታቸውን ሊስቡ ለሚችሉ ሰዎች ማበርከት ምን ጥቅም እንዳለው የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።
3 ውጤት፦ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት “ልጆችን ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ አድርጎ ማሳደግ” የሚል ርዕስ ያለው የጥቅምት 2011 ንቁ! ሲደርሳቸው በጉባኤያቸው ክልል ውስጥ ወደሚገኙ 25 ትምህርት ቤቶች ስልክ ደወሉ። ከእነዚህ መካከል 22ቱ ጽሑፎቹን ወስደው ለተማሪዎቹ አከፋፈሏቸው። በዚያው አገር የሚኖሩ ሌላ ባልና ሚስትም ተመሳሳይ ነገር በማድረግ መጽሔቱን በክልላቸው ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች አሰራጩ። እንዲያውም በአንደኛው ትምህርት ቤት ውስጥ የሚሠሩት አስተማሪዎች መጽሔቱን በሳምንታዊ የትምህርትና የንባብ ክፍለ ጊዜያቸው ላይ ተጠቅመውበታል። እነዚህ ባልና ሚስት ተሞክሯቸውን ለአንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ነገሩት፤ ከዚያ እሱም በወረዳው ውስጥ የሚገኙ ጉባኤዎች በትምህርት ቤቶች እንዲሰብኩ አበረታታቸው። በዚህም የተነሳ ተጨማሪ መጽሔቶች በብዛት ስለታዘዙ ቅርንጫፍ ቢሮው ይህ ቅጂ በድጋሚ እንዲታተም ማድረግ ነበረበት።
4. መጽሔቶቻችን ሰፊ ስርጭት እንዲኖራቸው የምንፈልገው ለምንድን ነው?
4 መጽሔቶቻችን ከወቅታዊ ሁኔታዎች በስተ ጀርባ ያለውን እውነተኛ ትርጉም የሚያብራሩ ከመሆኑም ሌላ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስና በአምላክ መንግሥት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ያበረታታሉ። በዓለም ላይ ካሉት መጽሔቶች “ድነትን የሚያውጁ” እነሱ ብቻ ናቸው። (ኢሳ. 52:7) በመሆኑም ሰፊ ስርጭት እንዲያገኙ እንፈልጋለን። እንዲህ ለማድረግ የሚያስችለን አንዱ መንገድ ‘ይህ መጽሔት የማንን ትኩረት ሊስብ ይችላል?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ነው።