ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን እውነት በቅንዓት አውጁ
ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን እውነት ለሌሎች ማካፈል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ማወቃችን ቅንዓታችን እንዲጨምር ያደርጋል። ኢየሱስ እውነተኛው እምነት የተገነባበት ዋናው የመሠረት ድንጋይ ነው። (ኤፌ. 2:20) የዘላለም ሕይወት ተስፋ ያገኘነው በእሱ አማካኝነት ነው። (ሥራ 4:12) በመሆኑም ሁሉም ሰው ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ያለውን ቦታ ማወቁ አስፈላጊ ነው። ብዙዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ትምህርቶች ተታልለዋል። አምላክ በኢየሱስ ለሚያምኑ ሰዎች የገባላቸውን በረከቶች እንዳያገኙ የሚያደርግ እንቅፋት የተጋረጠባቸው መሆኑ ያሳዝናል። ለእውነት ያለን ቅንዓት ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ማንነት ማለትም ከአምላክ ጋር ስላለው ግንኙነትና በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስላለው ሚና ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ለመርዳት ያነሳሳናል። በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን እውነት በቅንዓት ለማወጅ ተዘጋጅታችኋል?