የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • kr ምዕ. 17 ገጽ 182-191
  • የመንግሥቱን አገልጋዮች ማሠልጠን

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመንግሥቱን አገልጋዮች ማሠልጠን
  • የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ” ነው
  • ወንጌላዊ የሚሆኑ አገልጋዮችን ማሠልጠን
  • ወንድሞች ለየት ያሉ ኃላፊነቶችን እንዲወጡ ማሠልጠን
  • የይሖዋ ፍቅር መገለጫ የሆኑት ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎታቸውን ለማከናወን የሚሠለጥኑት እንዴት ነው?
    ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች
  • ከይሖዋ የምትችለውን ያህል ትምህርት እየቀሰምክ ነው?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2011
  • አቅኚዎች ምን ዓይነት የትምህርት አጋጣሚዎች ተከፍተውላቸዋል?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
ለተጨማሪ መረጃ
የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
kr ምዕ. 17 ገጽ 182-191

ምዕራፍ 17

የመንግሥቱን አገልጋዮች ማሠልጠን

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች የመንግሥቱ አገልጋዮች ተልእኳቸውን እንዲወጡ የሚያዘጋጁበት መንገድ

1-3. ኢየሱስ የስብከቱ ሥራ በስፋት እንዲከናወን ሁኔታዎችን ያመቻቸው እንዴት ነው? ይህስ የትኞቹን ጥያቄዎች ያስነሳል?

ኢየሱስ ለሁለት ዓመት ያህል በመላው ገሊላ ሲሰብክ ቆይቷል። (ማቴዎስ 9:35-38⁠ን አንብብ።) ወደተለያዩ ከተሞችና መንደሮች በመሄድ በምኩራቦች አስተምሯል፤ እንዲሁም የመንግሥቱን ምሥራች ሰብኳል። በሚሰብክባቸው ቦታዎች ሁሉ ብዙ ሕዝብ ይከተለው ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ “አዝመራው ብዙ ነው” በማለት ተጨማሪ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ ጠቁሟል።

2 ኢየሱስ የስብከቱ ሥራ በስፋት እንዲከናወን ሁኔታዎችን አመቻችቷል። እንዴት? “የአምላክን መንግሥት እንዲሰብኩ” 12 ሐዋርያቱን በመላክ ነው። (ሉቃስ 9:1, 2) ሐዋርያቱ ይህን ሥራ እንዴት ማከናወን እንደሚችሉ ጥያቄ ተፈጥሮባቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ ሐዋርያቱን ከመላኩ በፊት፣ በሰማይ ያለው አባቱ ለእሱ የሰጠውን ነገር ይኸውም ሥልጠና በመስጠት እንደሚወድዳቸው አሳይቷል።

3 ከዚህ ጋር በተያያዘ በርካታ ጥያቄዎች ወደ አእምሯችን ይመጡ ይሆናል፦ ኢየሱስ ከአባቱ ምን ዓይነት ሥልጠና አግኝቷል? ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የሰጣቸው ምን ዓይነት ሥልጠና ነው? በዛሬው ጊዜስ መሲሐዊው ንጉሥ፣ ተከታዮቹ አገልግሎታቸውን እንዲያከናውኑ የሚያስችላቸው ሥልጠና እየሰጣቸው ነው? ከሆነስ እንዴት?

“የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ” ነው

4. ኢየሱስ ከአባቱ የተማረው መቼና የት ነው?

4 ኢየሱስ፣ አባቱ እንዳስተማረው በግልጽ ተናግሯል። አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ወቅት “እነዚህን ነገሮች የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ [ነው]” ብሏል። (ዮሐ. 8:28) ኢየሱስ ትምህርት ያገኘው መቼና የት ነው? ሥልጠናውን የጀመረው የአምላክ የበኩር ልጅ ሆኖ ከተፈጠረ ብዙም ሳይቆይ መሆን አለበት። (ቆላ. 1:15) ወልድ፣ በሰማይ ካለው አባቱ ጋር ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት ሲኖር ታላቁን “አስተማሪ” ያዳምጥና የሚያደርገውን ይመለከት ነበር። (ኢሳ. 30:20) በመሆኑም ወልድ ስለ አባቱ ባሕርያት፣ ሥራዎችና ዓላማዎች ከማንም የበለጠ እውቀት ቀስሟል።

5. ወልድ ምድር ላይ ከሚያከናውነው አገልግሎት ጋር በተያያዘ አብ ምን ዓይነት ሥልጠና ሰጥቶታል?

5 ወልድ በምድር ላይ ስለሚያከናውነው አገልግሎት ጊዜው ሲደርስ ይሖዋ አስተምሮታል። በታላቁ አስተማሪና በበኩር ልጁ መካከል ስላለው ግንኙነት የተነገረ አንድ ትንቢት እንመልከት። (ኢሳይያስ 50:4, 5⁠ን አንብብ።) ይሖዋ፣ ልጁን “በየማለዳው” እንደሚያነቃው ትንቢቱ ይገልጻል። ይህ ምሳሌያዊ አገላለጽ፣ ተማሪውን ለማሠልጠን ሲል በማለዳ የሚቀሰቅሰውን አስተማሪ እንድናስብ ያደርገናል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ . . . አገልጋዩን ልክ እንደ አንድ ተማሪ በምሳሌያዊ መንገድ ትምህርት ቤት ወስዶ ምን እና እንዴት እንደሚሰብክ ያስተምረዋል።” ይሖዋ በሰማይ ባለው በዚያ “ትምህርት ቤት” ልጁን ‘ምን እንደሚልና ምን እንደሚናገር’ አስተምሮታል። (ዮሐ. 12:49) በተጨማሪም ወልድ እንዴት ማስተማር እንዳለበት አብ አሠልጥኖታል።a ኢየሱስ ያገኘውን ሥልጠና፣ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት አገልግሎቱን ለማከናወን ብቻ ሳይሆን ተከታዮቹ አገልግሎታቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ ለማሠልጠንም ጭምር ተጠቅሞበታል።

6, 7. (ሀ) ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ምን ዓይነት ሥልጠና ሰጥቷቸዋል? ሥልጠናውስ ምን እንዲያደርጉ አስታጥቋቸዋል? (ለ) ኢየሱስ በዘመናችን ያሉ ተከታዮቹ ምን ዓይነት ሥልጠና እንዲያገኙ አድርጓል?

6 በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው፣ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የሰጣቸው ሥልጠና ምንድን ነው? በማቴዎስ ምዕራፍ 10 ላይ እንደተገለጸው ለአገልግሎት የሚያስፈልጓቸውን ዝርዝር መመሪያዎች ሰጥቷቸዋል፤ ለምሳሌ፣ የት መስበክ እንዳለባቸው (ቁጥር 5, 6)፣ ምን እንደሚሰብኩ (ቁጥር 7)፣ በይሖዋ የመታመንን አስፈላጊነት (ቁጥር 9, 10)፣ ሰዎችን እንዴት ማነጋገር እንደሚችሉ (ከቁጥር 11-13)፣ ሰዎች ባይቀበሏቸው ምን እንደሚያደርጉ (ቁጥር 14, 15) እንዲሁም ስደት ሲደርስባቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው (ከቁጥር 16-23) አሠልጥኗቸዋል።b ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የሰጣቸው ግልጽ ሥልጠና በመጀመሪያው መቶ ዘመን ምሥራቹን የመስበኩን ሥራ ቅድሚያውን ወስደው እንዲያከናውኑ አስታጥቋቸዋል።

7 ስለ ዘመናችንስ ምን ማለት ይቻላል? የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ፣ ለተከታዮቹ ከሁሉ በላይ ትልቅ ቦታ ያለው ሥራ ሰጥቷቸዋል፤ ሥራው “የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር” መስበክ ነው። (ማቴ. 24:14) ታዲያ ንጉሡ ይህንን በጣም አስፈላጊ ሥራ ማከናወን እንድንችል አሠልጥኖናል? በሚገባ! ንጉሡ ከሰማይ ሆኖ፣ ተከታዮቹ ከጉባኤ ውጭ ላሉ ሰዎች ለመስበክና በጉባኤ ውስጥ ያሏቸውን ለየት ያሉ ኃላፊነቶች ለመወጣት የሚያስችላቸው ሥልጠና እንዲያገኙ አድርጓል።

ወንጌላዊ የሚሆኑ አገልጋዮችን ማሠልጠን

8, 9. (ሀ) የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ዋነኛ ዓላማ ምን ነበር? (ለ) በሳምንቱ መካከል የሚደረገው ስብሰባ በአገልግሎትህ ይበልጥ ውጤታማ እንድትሆን የረዳህ እንዴት ነው?

8 ቀደም ካሉት ዓመታት ጀምሮ የይሖዋ ድርጅት፣ የአምላክን ሕዝቦች ለአገልግሎት ለማሠልጠን በትላልቅ ስብሰባዎች እንዲሁም እንደ አገልግሎት ስብሰባ ባሉ የጉባኤ ስብሰባዎች ሲጠቀም ቆይቷል። ከ1940ዎቹ ዓመታት ወዲህ ግን በዋናው መሥሪያ ቤት ሆነው ሥራውን በኃላፊነት የሚመሩት ወንድሞች የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም ሥልጠና እንዲሰጥ ዝግጅት ማድረግ ጀመሩ።

9 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት። ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው ይህ ትምህርት ቤት የጀመረው በ1943 ነው። የትምህርት ቤቱ ዓላማ ተማሪዎቹ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ጥሩ ክፍሎችን እንዲያቀርቡ ማሠልጠን ብቻ ነበር? አይደለም። ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የትምህርት ቤቱ ዋነኛ ዓላማ የአምላክ ሕዝቦች የመናገር ስጦታቸውን ይሖዋን በአገልግሎት ለማወደስ እንዲጠቀሙበት ማሠልጠን ነበር። (መዝ. 150:6) በትምህርት ቤቱ የሚካፈሉ ወንድሞችና እህቶች ሁሉ ይበልጥ ውጤታማ የመንግሥቱ አገልጋዮች እንዲሆኑ የሚያስችል ሥልጠና አግኝተዋል። አሁን እንዲህ ዓይነት ሥልጠና የምናገኘው በሳምንቱ መካከል በምናደርገው ስብሰባ አማካኝነት ነው።

10, 11. በአሁኑ ጊዜ በጊልያድ ትምህርት ቤት መካፈል የሚችሉት እነማን ናቸው? የሥልጠናው ዓላማስ ምንድን ነው?

10 ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት። በአሁኑ ጊዜ ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተብሎ የሚጠራው ትምህርት ቤት የተቋቋመው ሰኞ፣ የካቲት 1, 1943 ነው። መጀመሪያ ላይ ትምህርት ቤቱ የተቋቋመበት ዓላማ አቅኚዎችንና ሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሚስዮናዊ ሆነው እንዲያገለግሉ ማሠልጠን ነበር። ከጥቅምት 2011 ወዲህ ግን በትምህርት ቤቱ መሠልጠን የሚችሉት በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማሩ ክርስቲያኖች ይኸውም ልዩ አቅኚዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው፣ ቤቴላውያን እንዲሁም በትምህርት ቤቱ ያልተካፈሉ ሚስዮናውያን ብቻ ናቸው።

11 በጊልያድ ትምህርት ቤት የሚሠጠው ሥልጠና ዓላማ ምንድን ነው? በትምህርት ቤቱ አስተማሪ ሆኖ ለረጅም ጊዜ ያገለገለ አንድ ወንድም እንዲህ በማለት መልስ ሰጥቷል፦ “ተማሪዎቹ የአምላክን ቃል ጥልቀት ባለው መንገድ እንዲያጠኑ በማድረግ እምነታቸውን ማጠናከር ብሎም በምድባቸው ላይ የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት የሚያስችሏቸውን መንፈሳዊ ባሕርያት እንዲያዳብሩ መርዳት ነው። በተጨማሪም የሚሰጠው ሥልጠና መሠረታዊ ዓላማ፣ ተማሪዎቹ በወንጌላዊነቱ ሥራ ለመካፈል ይበልጥ ጉጉት እንዲያድርባቸው መርዳት ነው።”—ኤፌ. 4:11

12, 13. በጊልያድ ትምህርት ቤት የሚሰጠው ሥልጠና በዓለም ዙሪያ ከሚከናወነው የስብከት ሥራ ጋር በተያያዘ ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል? ምሳሌ ስጥ።

12 በጊልያድ ትምህርት ቤት የሚሰጠው ሥልጠና በዓለም ዙሪያ ከሚከናወነው የስብከት ሥራ ጋር በተያያዘ ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል? ከ1943 ጀምሮ ከ8,500 በላይ የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች በዚህ ትምህርት ቤት ሠልጥነዋል፤c እነዚህ ሚስዮናውያንም በዓለም ዙሪያ ከ170 ወደሚበልጡ አገሮች ተልከዋል። ሚስዮናውያኑ በቅንዓት በአገልግሎት በመካፈል ግሩም ምሳሌ የተዉ ከመሆኑም በላይ ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ አሠልጥነዋል፤ በዚህ መንገድ፣ ያገኙትን ሥልጠና ጥሩ አድርገው ተጠቅመውበታል። አብዛኛውን ጊዜ፣ ጥቂት ወይም ምንም የመንግሥቱ አስፋፊዎች በሌሉባቸው አካባቢዎች ሥራው እንዲስፋፋ አድርገዋል።

13 ጃፓንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት፣ በጃፓን በተደራጀ መልክ የሚከናወነው የስብከት እንቅስቃሴ የቆመ ያህል ሆኖ ነበር። በነሐሴ 1949 በአገሪቱ የነበሩት ጃፓናውያን አስፋፊዎች አሥር አይሞሉም። በዚያ ዓመት መጨረሻ አካባቢ ግን በጊልያድ የሠለጠኑ 13 ሚስዮናውያን በጃፓን በስብከቱ ሥራ ተጠምደው ነበር። ከዚያ በኋላም ተጨማሪ ሚስዮናውያን ወደ አገሪቱ ገቡ። መጀመሪያ ላይ መላው ትኩረታቸውን ያደረጉት በትላልቅ ከተሞች ላይ ነበር፤ ውሎ አድሮ ደግሞ ወደ ሌሎች ከተሞች መሄድ ጀመሩ። ሚስዮናውያኑ ተማሪዎቻቸውንም ሆነ ሌሎችን በአቅኚነት አገልግሎት እንዲካፈሉ በጣም ያበረታቷቸው ነበር። ሚስዮናውያኑ በቅንዓት ማገልገላቸው ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል። በአሁኑ ጊዜ በጃፓን ከ216,000 በላይ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ወደ 40 በመቶ የሚሆኑት አቅኚዎች ናቸው!d

14. ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች ምን ያረጋግጣሉ? (“የመንግሥቱን አገልጋዮች የሚያሠለጥኑ ትምህርት ቤቶች” የሚለውን በገጽ 188 ላይ የሚገኝ ሣጥንም ተመልከት።)

14 ሌሎች ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች። የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት፣ ለባለትዳሮች የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እና ለነጠላ ወንድሞች የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተማሪዎቹ መንፈሳዊነታቸው እንዲጠነክርና በወንጌላዊነቱ ሥራ ግንባር ቀደም ሆነው በቅንዓት እንዲካፈሉ እየረዷቸው ነው።e እነዚህ ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች በሙሉ፣ ንጉሣችን ተከታዮቹ አገልግሎታቸውን መፈጸም እንዲችሉ ሙሉ በሙሉ እንደሚያስታጥቃቸው ያረጋግጣሉ።—2 ጢሞ. 4:5

ወንድሞች ለየት ያሉ ኃላፊነቶችን እንዲወጡ ማሠልጠን

15. በኃላፊነት ቦታ የሚያገለግሉ ወንዶች በየትኛው አቅጣጫ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ይፈልጋሉ?

15 ኢየሱስ ከአምላክ እንደተማረ የሚገልጸውን የኢሳይያስ ትንቢት አስታውስ። በሰማይ በሚገኘው በዚያ “ትምህርት ቤት” ወልድ “ለደከመው ትክክለኛ ቃል በመናገር እንዴት መልስ መስጠት [እንደሚችል]” ተምሯል። (ኢሳ. 50:4) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት፣ ‘ለደከሙና ሸክም ለከበዳቸው’ ሰዎች እረፍት በመስጠት በሰማይ ያገኘውን ትምህርት ተግባራዊ አድርጓል። (ማቴ. 11:28-30) በኃላፊነት ቦታ የሚያገለግሉ ወንዶች፣ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው የእረፍት ምንጭ መሆን ይፈልጋሉ። በመሆኑም ብቃት ያላቸው ወንድሞች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በማገልገል ረገድ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ለመርዳት ሲባል የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተቋቁመዋል።

16, 17. የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ዓላማ ምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

16 የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት። ይህ ትምህርት ቤት የጀመረው መጋቢት 9, 1959 በሳውዝ ላንሲንግ፣ ኒው ዮርክ ነው። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች (በአሁኑ ጊዜ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪዎች ይባላሉ) አንድ ወር በሚፈጀው ኮርስ እንዲካፈሉ ተጋብዘው ነበር። ከጊዜ በኋላ በትምህርት ቤቱ የሚሠጠው ትምህርት ከእንግሊዝኛ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች የተተረጎመ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ወንድሞች መሰጠት ጀመረ።f

ወንድም ሎይድ ባሪ በጃፓን የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ሥልጠና ሲሰጥ፣ 1970

ወንድም ሎይድ ባሪ በጃፓን የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ሥልጠና ሲሰጥ፣ 1970

17 የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤትን ዓላማ አስመልክቶ የ1962 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “ብዙዎች ፕሮግራማቸው በጣም በተጣበበበት በዚህ ዓለም በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግል የበላይ ተመልካች የራሱን ሕይወት በተደራጀ መልክ የሚመራ መሆን አለበት፤ እንዲህ ካደረገ በጉባኤው ውስጥ ላሉት ሁሉ ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንዲሁም ለጉባኤው በረከት መሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ጉባኤውን ለመርዳት ሲል የራሱን ቤተሰብ ችላ ማለት አይኖርበትም፤ ከዚህ ይልቅ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ሊሆን ይገባል። በዓለም ዙሪያ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ የጉባኤ አገልጋዮች (የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪዎች) በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት በመካፈል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ የበላይ ተመልካች ሊያከናውነው እንደሚገባ የሚናገረውን ሥራ ለመፈጸም የሚያስችል ሥልጠና ማግኘት መቻላቸው እንዴት ያለ ግሩም አጋጣሚ ነው!”—1 ጢሞ. 3:1-7፤ ቲቶ 1:5-9

18. ሁሉም የአምላክ ሕዝቦች በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ጥቅም የሚያገኙት እንዴት ነው?

18 የአምላክ ሕዝቦች በሙሉ ከመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ጥቅም እያገኙ ነው። እንዴት? ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች በትምህርት ቤቱ የተማሩትን ተግባራዊ ሲያደርጉ ልክ እንደ ኢየሱስ ለእምነት አጋሮቻቸው የእረፍት ምንጭ ይሆናሉ። አሳቢ የሆነ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ በደግነት ሲያናግርህ፣ ጆሮ ሰጥቶ ሲያዳምጥህ ወይም መጥቶ ሲያበረታታህ ደስ አይልህም? (1 ተሰ. 5:11) ብቃት ያላቸው እንዲህ ያሉ ወንድሞች በእርግጥም ለጉባኤዎቻቸው በረከት ናቸው!

19. የትምህርት ኮሚቴ የትኞቹን ሌሎች ትምህርት ቤቶች በበላይነት ይከታተላል? የእነዚህ ትምህርት ቤቶች ዓላማስ ምንድን ነው?

19 ሌሎች ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች። የበላይ አካሉ የትምህርት ኮሚቴ፣ በድርጅቱ ውስጥ ኃላፊነት ላላቸው ወንድሞች ሥልጠና የሚሰጡ ሌሎች ትምህርት ቤቶችን በበላይነት ይከታተላል። እነዚህ ትምህርት ቤቶች የተዘጋጁት ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ይኸውም የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ያሏቸውን በርካታ ኃላፊነቶች ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲወጡ ለመርዳት ታስቦ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ሥልጠና፣ ወንድሞች የራሳቸውን መንፈሳዊነት እንዲጠብቁ እንዲሁም ይሖዋ በአደራ የሰጣቸውን ውድ በጎች ሲንከባከቡ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ያበረታታቸዋል።—1 ጴጥ. 5:1-3

በማላዊ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት፣ 2007

በማላዊ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት፣ 2007

20. ኢየሱስ እኛን በተመለከተ “ሁሉም ከይሖዋ የተማሩ [ናቸው]” ብሎ መናገር የሚችለው ለምንድን ነው? ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

20 መሲሐዊው ንጉሥ፣ ተከታዮቹ ጥሩ ሥልጠና እንዲያገኙ እያደረገ እንደሆነ ግልጽ ነው። ሁሉም ሥልጠናዎች የመጡት በተዋረድ ነው፦ ይሖዋ ወልድን አሠልጥኖታል፤ ወልድ ደግሞ ተከታዮቹን አሠልጥኗቸዋል። በመሆኑም ኢየሱስ እኛን በተመለከተ “ሁሉም ከይሖዋ የተማሩ [ናቸው]” ብሎ መናገር ይችላል። (ዮሐ. 6:45፤ ኢሳ. 54:13) ንጉሣችን ከሚያቀርብልን ሥልጠና ሙሉ ጥቅም ለማግኘት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ይህ ሁሉ ሥልጠና የሚሰጥበት ዋነኛ ዓላማ የራሳችንን መንፈሳዊነት ለማጠናከር እንድንችል መሆኑን ምንጊዜም አንዘንጋ፤ ይህም አገልግሎታችንን በተሟላ መንገድ ለማከናወን ያስችለናል።

a ወልድ እንዴት ማስተማር እንዳለበት አብ እንዳሠለጠነው በምን እናውቃለን? እስቲ ይህን አስብ፦ ኢየሱስ በሚያስተምርበት ወቅት በርካታ ምሳሌዎችን መጠቀሙ እሱ ከመወለዱ ከብዙ ዘመናት በፊት የተጻፈ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል። (መዝ. 78:2፤ ማቴ. 13:34, 35) ከዚህ መመልከት እንደምንችለው ይህንን ትንቢት ያስነገረው ይሖዋ፣ ልጁ በምሳሌዎች ተጠቅሞ እንደሚያስተምር ከረጅም ጊዜ በፊት ያውቅ ነበር። —2 ጢሞ. 3:16, 17

b ከወራት በኋላ ኢየሱስ ‘ሌሎች 70 ሰዎችን በመሾም’ “ሁለት ሁለት አድርጎ” እንዲሰብኩ ላካቸው። ለእነዚህ ሰዎችም ሥልጠና ሰጥቷቸው ነበር።—ሉቃስ 10:1-16

c አንዳንድ ተማሪዎች በጊልያድ ትምህርት ቤት ከአንድ ጊዜ በላይ ተካፍለዋል።

d በጊልያድ የሠለጠኑ ሚስዮናውያን በዓለም ዙሪያ ያከናወኑትን ሥራ በተመለከተ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 23 ተመልከት።

e ለባለትዳሮች በተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እና ለነጠላ ወንድሞች በተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ምትክ የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተቋቁሟል።

f አሁን በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት የሚካፈሉት ሁሉም ሽማግሌዎች ናቸው፤ ሥልጠናው በየተወሰነ ዓመት የሚሰጥ ሲሆን የሚፈጀው ጊዜም እንደየሁኔታው ይለያያል። ከ1984 ወዲህ የጉባኤ አገልጋዮችም በዚህ ትምህርት ቤት መሠልጠን ጀምረዋል።

የአምላክ መንግሥት ለአንተ ምን ያህል እውን ነው?

  • ኢየሱስ ከአባቱ ምን ዓይነት ሥልጠና አግኝቷል?

  • ንጉሡ፣ ተከታዮቹን ወንጌላዊ እንዲሆኑ ያሠለጠናቸው እንዴት ነው?

  • ብቃት ያላቸው ወንድሞች ኃላፊነቶቻቸውን ለመወጣት የሚያስችል ሥልጠና ያገኙት እንዴት ነው?

  • ንጉሡ የሚሰጠውን ሥልጠና እንደምታደንቅ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

የመንግሥቱን አገልጋዮች የሚያሠለጥኑ ትምህርት ቤቶች

ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን

ዓላማው፦ አስፋፊዎች ምሥራቹን ውጤታማ በሆነ መንገድ መስበክና ማስተማር እንዲችሉ ማሠልጠን።

የሚፈጀው ጊዜ፦ ሁልጊዜ የሚሰጥ።

ቦታ፦ በየአካባቢው በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ።

ምዝገባ፦ አዘውትሮ በጉባኤ የሚገኝ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት አምኖ የሚቀበልና አኗኗሩ ከክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ማንኛውም ሰው መመዝገብ ይችላል። በዚህ ትምህርት ቤት ለመካፈል የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ የበላይ ተመልካቹን አነጋግረው።

ጥቅም፦ በሳምንቱ መሃል የሚደረገው ስብሰባ፣ ምርምር ማድረግና መረጃውን አሳማኝ በሆነ መንገድ ማቅረብ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያሠለጥነናል። በተጨማሪም ሌሎችን ማዳመጥን እንማራለን፤ እንዲሁም ስለ ራሳችን ብቻ ሳይሆን ስለ እነሱም መንፈሳዊነት እንድናስብ ሥልጠና እናገኛለን።

ለረጅም ጊዜ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ያገለገለው አርኒ እንዲህ ብሏል፦ “ከልጅነቴ ጀምሮ የመንተባተብ ችግር አለብኝ፤ ሌሎችን ፊት ለፊት ማየትም ያስፈራኝ ነበር። ይህ [ስብሰባ] በራሴ እንድተማመን ረድቶኛል። ይሖዋ በዚህ ትምህርት ቤት አማካኝነት ሥልጠና ስለሰጠኝ ትንፋሼን መቆጣጠርና ትኩረቴን መሰብሰብ የምችልባቸውን ዘዴዎች ተምሬያለሁ። አምላክን በጉባኤ መካከል እንዲሁም በአገልግሎት ላይ ማወደስ በመቻሌ በጣም አመስጋኝ ነኝ።”

አስፋፊ የሆነ አንድ ትንሽ ልጅ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ሲያቀርብ

የጉባኤ ሽማግሌዎች ትምህርት ቤትg

ዓላማው፦ ሽማግሌዎች መንፈሳዊነታቸውን እንዲያጎለብቱና በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነቶቻቸውን እንዲወጡ መርዳት።

የሚፈጀው ጊዜ፦ አምስት ቀናት።

ቦታ፦ ቅርንጫፍ ቢሮው በወሰነው ቦታ፤ ብዙውን ጊዜ በመንግሥት አዳራሽ ወይም በትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ።

ምዝገባ፦ ቅርንጫፍ ቢሮው ሽማግሌዎችን ይጋብዛል።

ጥቅም፦ በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በትምህርት ቤቱ 92ኛ ክፍል የሠለጠኑ ተማሪዎች የሰጧቸውን አንዳንድ አስተያየቶች ተመልከት፦

“ትምህርት ቤቱ ራሴን በደንብ እንድፈትሽ ስላደረገኝና የይሖዋን በጎች እንዴት መንከባከብ እንዳለብኝ ስላስገነዘበኝ በጣም ጠቅሞኛል።”

“ይህን ሥልጠና በሕይወቴ ሙሉ እጠቀምበታለሁ።”

የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት

ዓላማው፦ አቅኚዎች ‘አገልግሎታቸውን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም’ እንዲችሉ መርዳት።—2 ጢሞ. 4:5

የሚፈጀው ጊዜ፦ ስድስት ቀናት።

ቦታ፦ ቅርንጫፍ ቢሮው በወሰነው ቦታ፤ ብዙውን ጊዜ በቅርብ በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ።

ምዝገባ፦ ቢያንስ ለአንድ ዓመት የዘወትር አቅኚ ሆነው ያገለገሉ ክርስቲያኖች ሁሉ በትምህርት ቤቱ መካፈል እንደሚችሉ በወረዳ የበላይ ተመልካቹ አማካኝነት ይነገራቸዋል። ሥልጠናውን ካገኙ ከአምስት ዓመት በላይ የሆናቸው ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ አንዳንድ አቅኚዎች በድጋሚ እንዲካፈሉ ሊጋበዙ ይችላሉ።

ጥቅም፦ ሊሊ እንዲህ ብላለች፦ “ትምህርት ቤቱ በአገልግሎት ላይ አልፎ ተርፎም በሕይወቴ የሚያጋጥሙኝን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት ረድቶኛል። የማጠናበት፣ የማስተምርበትና መጽሐፍ ቅዱስን የምጠቀምበት መንገድ በጣም ተሻሽሏል። ሌሎችን ለመርዳት፣ ከሽማግሌዎች ጋር ተባብሬ ለመሥራት እንዲሁም ለጉባኤው እድገት አስተዋጽኦ ለማበርከት እንድችል ትምህርት ቤቱ የበለጠ አዘጋጅቶኛል።”

በትምህርት ቤቱ ለሁለተኛ ጊዜ የተካፈለችው ብሬንዳ እንዲህ ብላለች፦ “ሥልጠናው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ሙሉ በሙሉ ትኩረት እንዳደርግ፣ ሕሊናዬን ይበልጥ እንዳሠለጥንና ሌሎችን በመርዳት ላይ እንዳተኩር አስችሎኛል። በእርግጥም ይሖዋ ደግ ነው!”

ለአዲስ ቤቴላውያን የተዘጋጀ ትምህርት ቤት

ዓላማው፦ አዳዲስ ቤቴላውያን፣ በቤቴል አገልግሎታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ መርዳት።

የሚፈጀው ጊዜ፦ አራት ቀናት ሲሆን በየቀኑ ለአራት ሰዓታት ይካሄዳል።

ቦታ፦ ቤቴል።

ምዝገባ፦ የቤቴል ቤተሰብ ቋሚ አባል አሊያም ለአንድ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ጊዜያዊ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆኖ በቤቴል እንዲያገለግል የተጠራ መሆን አለበት።

ጥቅም፦ በ1980ዎቹ ዓመታት በዚህ ትምህርት ቤት የተካፈለው ዲሜትሪየስ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ሥልጠና የጥናት ልማዴን እንዳሻሽል የረዳኝ ከመሆኑም በላይ ረጅም ዓመት በቤቴል እንዳገለግል አዘጋጅቶኛል። አስተማሪዎቹ፣ ኮርሱና በዚያ ያገኘሁት ጠቃሚ ምክር ይሖዋ ከልቡ እንደሚያስብልኝና በቤቴል አገልግሎቴ ውጤታማ እንድሆን እንደሚፈልግ አረጋግጠውልኛል።”

የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤትh

ዓላማው፦ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን (ባለትዳሮችም ሆኑ ነጠላ ወንድሞችና እህቶች) ይሖዋና ድርጅቱ ይበልጥ ሊጠቀሙባቸው እንዲችሉ ልዩ ሥልጠና መስጠት። አብዛኞቹ ተመራቂዎች በሚኖሩበት አገር ውስጥ ይበልጥ እርዳታ በሚያስፈልግበት ቦታ ይመደባሉ። ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች የሆኑ ተመራቂዎች ገለልተኛና ሩቅ በሆኑ አካባቢዎች እንዲሰብኩና ሥራውን እንዲያስፋፉ ጊዜያዊ ልዩ አቅኚ ሆነው ይመደባሉ።

የሚፈጀው ጊዜ፦ ሁለት ወራት።

ቦታ፦ ቅርንጫፍ ቢሮው በወሰነው ቦታ፤ ብዙውን ጊዜ በመንግሥት አዳራሽ ወይም በትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ።

አንዲት እህት አገልግሎት ላይ

ወንድሞችም ሆኑ እህቶች ከቲኦክራሲያዊ ሥልጠናዎች ይጠቀማሉ

ምዝገባ፦ ከ23 እስከ 65 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ፣ ጥሩ ጤንነት ያላቸው እንዲሁም ይበልጥ እርዳታ በሚያስፈልግበት በማንኛውም ቦታ ለማገልገል የሚችሉና “እነሆኝ! እኔን ላከኝ!” በማለት ራሳቸውን የሚያቀርቡ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች መመዝገብ ይችላሉ። (ኢሳ. 6:8) በትምህርት ቤቱ የሚካፈሉ ሁሉ ማለትም ነጠላ ወንድሞችና እህቶችም ሆኑ ባለትዳሮች፣ ቢያንስ ለሁለት ዓመት ያለማቋረጥ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተካፈሉ መሆን አለባቸው። ባለትዳሮች ደግሞ ቢያንስ ለሁለት ዓመት ተጋብተው የቆዩ መሆን አለባቸው። ወንድሞች ቢያንስ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆነው እያገለገሉ ያሉ መሆን ይኖርባቸዋል። የምትኖርበትን አካባቢ በበላይነት በሚከታተለው ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ይህ ትምህርት ቤት የሚካሄድ ከሆነ በክልል ስብሰባ ወቅት ይህን ትምህርት ቤት በተመለከተ ለአመልካቾች መረጃ ለመስጠት ስብሰባ ይካሄዳል።

ጥቅም፦ ለነጠላ ወንድሞች በተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እና ለባለትዳሮች በተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የተካፈሉ ክርስቲያኖች ስላገኟቸው ጥቅሞች ብዙ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። በ2013 የበላይ አካሉ እነዚህ ሁለት ትምህርት ቤቶች አንድ ላይ እንዲዋሃዱና የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት እንዲባሉ ፈቃድ ሰጥቷል። ነጠላ እህቶችን ጨምሮ በርካታ ታማኝ አቅኚዎች ከዚህ ትምህርት ቤት ጥቅም ማግኘት ይችላሉ።

ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት

ዓላማው፦ ተመራቂዎቹ፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ወይም ሚስዮናውያን አሊያም ቤቴላውያን ሆነው እንዲያገለግሉ ሊመደቡ ይችላሉ። ተመራቂዎቹ ያገኙትን ሥልጠና በመጠቀም የመስኩን እንዲሁም የቅርንጫፍ ቢሮዎችን ሥራ መደገፍና ማደራጀት ይችላሉ።

የሚፈጀው ጊዜ፦ አምስት ወራት።

ቦታ፦ ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል።

የጊልያድ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ አስተማሪያቸውን እያዳመጡ

የጊልያድ ተማሪዎች—ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ

ምዝገባ፦ በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማሩ ባለትዳሮች እንዲሁም ነጠላ ወንድሞችና እህቶች መካፈል ይችላሉ። በጊልያድ ያልሠለጠኑ በመስክ የሚያገለግሉ ሚስዮናውያንን፣ ልዩ አቅኚዎችን፣ ቤቴላውያንን ወይም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችንና ሚስቶቻቸውን ለዚህ ትምህርት ቤት እንዲያመለክቱ ቅርንጫፍ ኮሚቴው ሊጋብዝ ይችላል። አመልካቾች እንግሊዝኛ መናገርና መጻፍ መቻል ይኖርባቸዋል።

ጥቅም፦ በዩናይትድ ስቴትስ ይኖሩ የነበሩት ላዲ እና ሞኒክ የተባሉ ባልና ሚስት በምድባቸው ለረጅም ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፤ እንዲህ ብለዋል፦

“የጊልያድ ትምህርት ቤት በየትኛውም የዓለም ክፍል ብንመደብ ለመሄድና ከውድ ወንድሞቻችን ጋር ለመሥራት ራሳችንን እንድናዘጋጅ አድርጎናል” በማለት ላዲ ተናግሯል።

ሞኒክ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ከአምላክ ቃል የተማርኩትን ተግባራዊ ለማድረግ ስጥር በተመደብኩበት ቦታ ይበልጥ ደስታ አገኛለሁ። ይህም ይሖዋ እንደሚወደኝ ማረጋገጫ ሆኖልኛል።”

የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት

ዓላማው፦ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ ሽማግሌዎች እና የጉባኤ አገልጋዮች ሥራቸውንና ድርጅታዊ ኃላፊነቶቻቸውን እንዲወጡ ማሠልጠን። (ሥራ 20:28) ትምህርት ቤቱ፣ በጉባኤዎች ውስጥ ትኩረት ሊሰጣቸው በሚገቡ ወቅታዊ ሁኔታዎች፣ እየታዩ ባሉ አዝማሚያዎች ወይም አስቸኳይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል። ይህ ትምህርት ቤት የበላይ አካሉ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት በየተወሰነ ዓመት ይካሄዳል።

የሚፈጀው ጊዜ፦ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህ ትምህርት ቤት የሚወስደው ጊዜ እንደየሁኔታው የተለያየ እንዲሆን ተደርጓል።

ቦታ፦ ብዙውን ጊዜ በቅርብ በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ወይም የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ።

ምዝገባ፦ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ሽማግሌዎችን እና የጉባኤ አገልጋዮችን ይጋብዛል። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን የሚጋብዘው ቅርንጫፍ ቢሮው ነው።

ጥቅም፦ “ትምህርቱ የሚሰጠው ለአጭር ጊዜ ቢሆንም በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስሳል፤ ሽማግሌዎች በይሖዋ አገልግሎት እንዲደሰቱና ‘ወንድ እንዲሆኑ’ ይረዳቸዋል። አዲሶችም ሆኑ ነባር ሽማግሌዎች፣ ውጤታማ የሆነ እረኝነት እንዴት ማድረግ እንደሚችሉ እንዲሁም ‘በዓላማ ፍጹም አንድነት’ እንዲኖራቸው ይሠለጥናሉ።”—ክዊን

“ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የቀረበው ሥልጠና ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለንን አድናቆት አሳድጎልናል፤ ስለሚያጋጥሙን አደጋዎች አስጠንቅቆናል፤ በተጨማሪም መንጋውን ለመንከባከብ የሚረዱ ጠቃሚ ሐሳቦችን አግኝተንበታል።”—ማይክል

ለወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀ ትምህርት ቤትi

ዓላማው፦ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጉባኤዎችን በማገልገል ረገድ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ፣ “በመናገርና በማስተማር ተግተው [እንዲሠሩ]” እንዲሁም በአደራ የተሰጣቸውን መንጋ እንዲጠብቁ መርዳት።—1 ጢሞ. 5:17፤ 1 ጴጥ. 5:2, 3

የሚፈጀው ጊዜ፦ አንድ ወር።

ቦታ፦ ቅርንጫፍ ቢሮው በወሰነው ቦታ።

ምዝገባ፦ ቅርንጫፍ ቢሮው የወረዳ የበላይ ተመልካቾችን እንዲሁም ሚስቶቻቸውን ይጋብዛል።

ጥቅም፦ “ኢየሱስ ድርጅቱን ስለሚመራበት መንገድ ያለን አድናቆት ጨምሯል። የምናገለግላቸውን ወንድሞች ማበረታታትና የእያንዳንዱን ጉባኤ አንድነት ማጠናከር እንዳለብን ተገንዝበናል። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ምክር፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እርማት ቢሰጡም ዋነኛ ዓላማቸው ወንድሞች ይሖዋ እንደሚወዳቸው እንዲሰማቸው መርዳት እንደሆነ በማይረሳ መንገድ ትምህርት ቤቱ አስገንዝቦናል።”—ጆኤል እና ከኒ፣ አንደኛው ክፍል፣ 1999

ለቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀ ትምህርት ቤት

ዓላማው፦ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ሆነው የሚያገለግሉ ወንድሞች የቤቴል ቤቶችን የመምራት፣ ጉባኤዎችን የሚመለከቱ የአገልግሎት ጉዳዮችን የመከታተል እንዲሁም በክልላቸው ውስጥ ያሉ ወረዳዎችን በበላይነት የመምራት ኃላፊነታቸውን በተሻለ መንገድ እንዲወጡ መርዳት።—ሉቃስ 12:48ለ

የሚፈጀው ጊዜ፦ ሁለት ወራት።

ቦታ፦ ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል።

ምዝገባ፦ የበላይ አካሉ የአገልግሎት ኮሚቴ፣ የቅርንጫፍ ወይም የአገር ኮሚቴ አባላትንና ሚስቶቻቸውን ይጋብዛል።

ጥቅም፦ ሎዌል እና ካራ በ25ኛው ክፍል ተካፍለዋል። በአሁኑ ጊዜ በናይጄሪያ እያገለገሉ ነው።

ሎዌል “ምንም ያህል ሥራ ቢበዛብኝ ወይም የትኛውም ዓይነት ሥራ ቢሰጠኝ ይሖዋን ለማስደሰት ቁልፉ መንፈሳዊነትን መጠበቅ እንደሆነ ተረድቻለሁ” ብሏል።

ካራ ከትምህርት ቤቱ የማትረሳው ትምህርት እንዳገኘች ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “አንድን ትምህርት ቀለል ባለ መንገድ መግለጽ ካልቻልኩ ሌሎችን ከማስተማሬ በፊት በጉዳዩ ላይ ምርምር ማድረግ እንዳለብኝ ተምሬያለሁ።”

g ይህ ትምህርት ቤት ያልተጀመረባቸው አገሮች አሉ።

h ይህ ትምህርት ቤት ያልተጀመረባቸው አገሮች አሉ።

i ይህ ትምህርት ቤት ያልተጀመረባቸው አገሮች አሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ