ትምህርት 2
አምላክ ከማንም የሚበልጥ ወዳጅ ነው
የአምላክ ወዳጅ መሆን ልታገኝ ከምትችለው ነገር ሁሉ የሚበልጥ ነው። አምላክ ደስተኛና የተረጋጋ ሕይወት እንዴት መምራት እንደምትችል ያስተምርሃል። ከተሳሳቱ እምነቶችና ከጎጂ ልማዶች ነፃ ያደርግሃል። የምታቀርበውን ጸሎት ይሰማል። ውስጣዊ ሰላምና ትምክህት እንዲኖርህ ይረዳሃል። (መዝሙር 71:5፤ 73:28) አምላክ በመከራ ጊዜ ይደግፍሃል። (መዝሙር 18:18) እንዲሁም የዘላለም ሕይወት ስጦታ ይሰጥሃል።—ሮሜ 6:23
ወደ አምላክ ይበልጥ እየቀረብክ በሄድክ መጠን ከአምላክ ወዳጆች ጋርም እንደዚያው እየተቀራረብህ ትሄዳለህ። እነርሱም የአንተ ወዳጆች ይሆናሉ። እንዲያውም እንደ ወንድሞችህና እህቶችህ ይሆኑልሃል። አንተን ስለ አምላክ ለማስተማር፣ ለመርዳትና ለማበረታታት ደስተኞች ናቸው።
ከአምላክ ጋር እኩል አይደለንም። የአምላክ ወዳጅ ለመሆን በምትፈልግበት ጊዜ አንድ አስፈላጊ ሃቅ መገንዘብ አለብህ። ከአምላክ ጋር ወዳጅ መሆን እኩያ በሆኑ ሁለት አካላት መካከል ከሚኖረው ወዳጅነት ጋር አንድ ዓይነት አይደለም። እርሱ ከእኛ ይልቅ ብዙ ዕድሜ ያለው ከመሆኑም በላይ ከእኛ የላቀ ጥበብና ኃይል አለው። እርሱ ገዥያችን ለመሆን መብት ያለው ነው። ስለዚህ የእርሱ ወዳጆች መሆን ከፈለግን እርሱን ማዳመጥና እንድናደርግ የሚያስተምረንን ሁሉ በተግባር ማዋል አለብን። እንዲህ ማድረጋችን ምንጊዜም ጥቅም ያስገኝልናል።—ኢሳይያስ 48:18