የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 64—3 ዮሐንስ
ጸሐፊው:- ሐዋርያው ዮሐንስ
የተጻፈበት ቦታ:- በኤፌሶን ወይም በአቅራቢያው
ተጽፎ ያለቀው:- በ98 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
ይህ ደብዳቤ የተጻፈው ዮሐንስ ከልቡ ይወደው ለነበረውና ታማኝ ክርስቲያን ለሆነው ለጋይዮስ ነው። ጋይዮስ የሚለው ስም በጥንቱ ጉባኤ ውስጥ የተለመደ ነበር። በሌሎች የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥም አራት ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኝ ሲሆን ቢያንስ ሦስት ምናልባትም አራት የተለያዩ ሰዎችን ያመለክታል። (ሥራ 19:29፤ 20:4፤ ሮሜ 16:23፤ 1 ቆሮ. 1:14) ዮሐንስ መልእክቱን የጻፈው ለየትኛው ጋይዮስ መሆኑን የሚጠቁም መረጃ የለም። ስለ ጋይዮስ የምናውቀው ነገር ቢኖር የክርስቲያን ጉባኤ አባልና የዮሐንስ የቅርብ ወዳጅ መሆኑን እንዲሁም ደብዳቤው በቀጥታ ለእሱ መጻፉን ነው። መልእክቱ በቀጥታ ለእሱ እንደተጻፈ የሚጠቁመን፣ “አንተ” የሚለውን ነጠላ ተውላጠ ስም በተደጋጋሚ መጠቀሙ ነው።
2 የመክፈቻውና የመደምደሚያው ሰላምታ ከሁለተኛ ዮሐንስ መልእክት ጋር መመሳሰሉ እንዲሁም ጸሐፊው በድጋሚ ራሱን “ሽማግሌው” ብሎ መጥራቱ መልእክቱን ሐዋርያው ዮሐንስ እንደጻፈው በማያሻማ ሁኔታ ያሳያል። (2 ዮሐ. 1) የጽሑፉ ይዘትና የአጻጻፍ ስልቱ መመሳሰል፣ እንደ ሌሎቹ ሁለት መልእክቶች ሁሉ ይህም ደብዳቤ በ98 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ በኤፌሶን ወይም በዚያ አቅራቢያ እንደተጻፈ ይጠቁማል። መልእክቱ አጭር በመሆኑ የጥንት ጸሐፊዎች እምብዛም ከእሱ ላይ ጠቅሰው አልጻፉም። ይሁን እንጂ በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ጥንታዊ ዝርዝር ውስጥ ከሁለተኛው የዮሐንስ መልእክት ጋር አብሮ ተጠቅሶ እናገኘዋለን።
3 ዮሐንስ በመልእክቱ ላይ፣ ጋይዮስ ለተጓዥ ወንድሞች ያሳየውን የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ካደነቀ በኋላ ዲዮጥራጢስ ከሚባለው የሥልጣን ጥም ከተጠናወተው ሰው ጋር በተያያዘ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ጠቅሷል። ዮሐንስ ይህንን መልእክት ለጋይዮስ እንዲያደርስለት የላከው ስሙ በመልእክቱ ውስጥ ተጠቅሶ የሚገኘውን ድሜጥሮስን ሳይሆን አይቀርም። በመሆኑም ጋይዮስ ይህንንም ሰው በእንግድነት መቀበል ነበረበት። ደብዳቤውም የሚያበረታታው ይኽንኑ መንፈስ ነው። ልክ እንደ ጋይዮስ፣ ስለ ዲዮጥራጢስም ሆነ ስለ ድሜጥሮስ በመልእክቱ ውስጥ ከሰፈረው መረጃ ያለፈ ምንም የምናውቀው ነገር የለም። ይሁን እንጂ፣ መልእክቱ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ምን ያህል የጠበቀ የወንድማማች ኅብረት እንደነበራቸው ጥሩ ፍንጭ ይሰጠናል። ይህ ደግሞ የማያውቋቸው ቢሆኑም እንኳ “ስለ ስሙ” ሲሉ የሚጓዙትን ወንድሞች በእንግድነት መቀበልን ያካትት ነበር።—ቁጥር 7
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
5 ሐዋርያው ዮሐንስ ጉባኤውን ከሚበክሉ ተጽዕኖዎች ለመጠበቅ ሲባል ቅንዓት በማሳየት ረገድ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን የበላይ ተመልካች መሆኑን አስመሥክሯል። በጉባኤው ውስጥ ሰፍኖ የነበረው የፍቅርና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ የሚያስመሰግን ሲሆን የአካባቢው ወንድሞችም ሆኑ ወደ እነሱ የሚመጡት “እንግዶች” (እንግዳ ተቀባዩ ክርስቲያን ከዚያ በፊት የማያውቃቸው ሰዎች) ‘በእውነት አብረው መሥራት’ ይችሉ ዘንድ ይህን አስደሳች መንፈስ ጠብቀው ማቆየት ነበረባቸው። (ቁጥር 5, 8) ዲዮጥራጢስ ግን ትዕቢተኛ ዓይን ነበረው፤ ይሖዋ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱን ነገር ይጸየፈዋል። ከዚህም ሌላ፣ ይህ ሰው ስለ ሐዋርያው ዮሐንስ ሳይቀር ክፉ ነገር መናገሩ ለቲኦክራሲያዊው ሥልጣን አክብሮት እንዳልነበረው ያሳያል። (ምሳሌ 6:16, 17) ጉባኤው ክርስቲያናዊ የሆነ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዳያሳይ እንቅፋት ሆኖ ነበር። ሐዋርያው ዮሐንስ ይህንን ክፉ ድርጊት በግልጽ በመቃወም በጉባኤው ውስጥ የነበረውን እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር ማድነቁ ምንም አያስገርምም። እኛም በዛሬው ጊዜ፣ ዮሐንስ ‘መልካም የሆነውን የሚያደርግ ሁሉ ከአምላክ ነው፤ ክፉ የሚያደርግ ግን አምላክን አላየውም’ ሲል ከገለጸው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በሚስማማ መንገድ፣ ትሕትናን ለማሳየትና በእውነት ለመመላለስ እንዲሁም አምላካዊ ፍቅር ለማንጸባረቅና ለጋስ ለመሆን መትጋት ይገባናል።—3 ዮሐ. 11