-
“ጅረቱ በሚፈስበት ቦታ ያለው ነገር ሁሉ በሕይወት ይኖራል”የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ!
-
-
ምዕራፍ 19
“ጅረቱ በሚፈስበት ቦታ ያለው ነገር ሁሉ በሕይወት ይኖራል”
ፍሬ ሐሳብ፦ ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ስለሚፈሰው ወንዝ የሚገልጸው ራእይ በጥንት ዘመንና በአሁኑ ጊዜ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? ወደፊትስ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?
1, 2. በሕዝቅኤል 47:1-12 ላይ እንደተገለጸው ሕዝቅኤል ምን ተመለከተ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ባየው ራእይ ላይ ሌላ አስደናቂ ነገር ተመለከተ፦ አንድ ጅረት ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ይፈስሳል። ሕዝቅኤል ይህን ኩልል ያለ ውኃ ተከትሎ ሲሄድ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። (ሕዝቅኤል 47:1-12ን አንብብ።) ውኃው የሚመነጨው ከመቅደሱ ደፍ ሥር ነው፤ ከዚያም ቀስ ብሎ እየፈሰሰ በምሥራቁ በር አቅራቢያ ከቤተ መቅደሱ ግቢ ይወጣል። ሕዝቅኤልን የሚያስጎበኘው መልአክ ሕዝቅኤልን እየመራ ከቤተ መቅደሱ ውጭ ወሰደው፤ በሚሄዱበት ጊዜም ርቀቱን ይለካ ነበር። መልአኩ ሕዝቅኤልን በተደጋጋሚ በውኃው መካከል እንዲያልፍ አደረገው። ነቢዩም የውኃው ጥልቀት በፍጥነት እየጨመረ እንደሄደ አስተዋለ፤ ብዙም ሳይቆይ ውኃው በዋና ካልሆነ በስተቀር በእግር ሊሻገሩት የማይቻል ትልቅ ወንዝ ሆነ!
2 ሕዝቅኤል ወንዙ ወደ ሙት ባሕር እንደሚፈስ ተገነዘበ፤ የወንዙ ውኃ በደረሰበት ቦታ ሁሉ በሙት ባሕር ውስጥ ያለውን ሕይወት አልባና ጨዋማ የሆነ ውኃ በመፈወስ በዓሣዎች እንዲሞላ ያደርጋል። በወንዙ ዳርና ዳር ደግሞ ብዙ ዓይነት ዛፎች ይበቅላሉ። ዛፎቹ ለመብል የሚሆን አዲስ ፍሬ በየወሩ ይሰጣሉ፤ ቅጠላቸውም ለመድኃኒት ይሆናል። ሕዝቅኤል ይህን ሁሉ ሲመለከት ልቡ በሰላምና በተስፋ ተሞልቶ መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ይህ የራእዩ ገጽታ ለእሱና በግዞት ላይ ላሉ ወገኖቹ ምን መልእክት ይዟል? በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛስ ምን መልእክት ያስተላልፋል?
በራእይ የታየው ወንዝ ለግዞተኞቹ ምን መልእክት ይዟል?
3. የጥንቶቹ አይሁዳውያን በራእይ የታየው ወንዝ እውነተኛ ወንዝ ነው ብለው እንዳላሰቡ እንዴት እናውቃለን?
3 የጥንቶቹ አይሁዳውያን በራእይ የታየው ወንዝ እውነተኛ ወንዝ ነው ብለው እንዳላሰቡ ጥያቄ የለውም። ከዚህ ይልቅ ይህ ራእይ ነቢዩ ኢዩኤል ሁለት መቶ ዓመታት ገደማ አስቀድሞ የጻፈውን፣ ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋም የሚገልጽ ሌላ ትንቢት አስታውሷቸው ይሆናል። (ኢዩኤል 3:18ን አንብብ።) ግዞተኞቹ አይሁዳውያን በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የኢዩኤል ትንቢት ሲያነቡ ተራሮቹ ቃል በቃል “ጣፋጭ የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ” ወይም “ኮረብቶቹ ወተት ያፈሳሉ” ብለው እንዳልጠበቁ የታወቀ ነው፤ ልክ እንደዚሁ “ከይሖዋም ቤት ምንጭ ይፈልቃል” ብለው አልጠበቁም። በተመሳሳይም እነዚህ አይሁዳውያን ነቢዩ ሕዝቅኤል ያየው ራእይ ስለ እውነተኛ ወንዝ የሚገልጽ እንዳልሆነ ሳይገነዘቡ አይቀሩም።a ታዲያ ይሖዋ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት ምን ነበር? ቅዱሳን መጻሕፍት የዚህን ራእይ አንዳንድ ገጽታዎች ትርጉም እንድንረዳ የሚያስችሉ ፍንጮች ይሰጡናል። በጥቅሉ ሲታይ ግን ይህ ትንቢታዊ መግለጫ የይሖዋን ፍቅር የሚያሳዩ ሦስት ዋስትናዎች ይሰጠናል። እስቲ እነዚህን ዋስትናዎች እንመልከት።
4. (ሀ) ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ወንዝ አይሁዳውያን የትኞቹን በረከቶች እንደሚያገኙ አረጋግጦላቸው መሆን አለበት? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ “ወንዝ” እና “ውኃ” የሚሉትን ቃላት የሚጠቀምበት መንገድ ይሖዋ ሕዝቦቹን እንደሚባርክ የሚያረጋግጥልን እንዴት ነው? (“የይሖዋን በረከት የሚያስገኙ ወንዞች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
4 በረከት የሚያስገኝ ወንዝ። አብዛኛውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወንዝና ውኃ፣ ሕይወት ሰጪ የሆኑት የይሖዋ በረከቶች መፍሰሳቸውን ለማመልከት እንደ ምሳሌ ሆነው ያገለግላሉ። ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ወንዝ ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ይፈስ ነበር፤ በመሆኑም ይህ ራእይ የአምላክ ሕዝቦች ከንጹሕ አምልኮ እስካልራቁ ድረስ ሕይወት ሰጪ የሆኑት የይሖዋ መንፈሳዊ በረከቶች ወደ እነሱ መፍሰሳቸውን እንደማያቆሙ አረጋግጦላቸው መሆን አለበት። እነዚህ በረከቶች ምን ነገሮችን ያካትታሉ? የአምላክ ሕዝቦች እንደ ቀድሞው ከካህናቱ መንፈሳዊ መመሪያ ያገኛሉ። በተጨማሪም በቤተ መቅደሱ ውስጥ መሥዋዕቶች ስለሚቀርቡ ኃጢአታቸው እንደሚሰረይላቸው መተማመን ይችላሉ። (ሕዝ. 44:15, 23፤ 45:17) በዚህ መንገድ ከቤተ መቅደሱ በሚወጣው ንጹሕ ውኃ የታጠቡ ያህል ዳግመኛ ንጹሕ ይሆናሉ።
5. በራእዩ ላይ የታየው ወንዝ ምንጊዜም ለሁሉም የሚበቃ በረከት እንደሚኖር የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?
5 ይሁንና ምንጊዜም ለሁሉም የሚበቃ በረከት ይኖራል? ራእዩ፣ ቀስ እያለ የሚፈሰው ውኃ በአስደናቂ ሁኔታ እየጨመረ ሄዶ ሁለት ኪሎ ሜትር በማይሞላ ርቀት ውስጥ ትልቅ ወንዝ እንደሚሆን ስለሚገልጽ በዚህ ረገድ የሚያሳስብ ነገር አይኖርም። (ሕዝ. 47:3-5) አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ የሕዝቡ ቁጥር እያደገ ይሄድ ይሆናል፤ ያም ቢሆን የይሖዋ በረከት እየጨመረ ስለሚሄድ የሁሉንም ፍላጎት ማሟላት ይችላል። በራእዩ ላይ የታየው ወንዝ የተትረፈረፈ በረከት እንደሚኖር ያመለክታል።
6. (ሀ) ራእዩ ምን አጽናኝ ተስፋ ይዟል? (ለ) ራእዩ ምን ማስጠንቀቂያ ያስተላልፋል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
6 ሕይወት ሰጪ ውኃ። በሕዝቅኤል ራእይ ላይ ወንዙ ወደ ሙት ባሕር ገብቶ አብዛኛውን የባሕሩን ክፍል እንደፈወሰው ተገልጿል። የሙት ባሕር ውኃ ተፈውሶ እንደ ታላቁ ባሕር ማለትም እንደ ሜድትራንያን ባሕር ብዙ ዓይነት ዓሣዎች የሚርመሰመሱበት ሆኗል። እንዲያውም በሙት ባሕር ዳርቻ “ከኤንገዲ እስከ ኤንዔግላይም ድረስ” ብዙዎች ዓሣ በማጥመድ ሥራ ተሰማርተዋል፤ እነዚህ ከተሞች ተራርቀው የሚገኙ ከተሞች ሳይሆኑ አይቀሩም። መልአኩ “ጅረቱ በሚፈስበት ቦታ ያለው ነገር ሁሉ በሕይወት ይኖራል” ብሏል። ይህ ሲባል ታዲያ ከይሖዋ ቤት የወጣው ወንዝ ሙት ባሕርን ሙሉ በሙሉ ያዳርሳል ማለት ነው? አይደለም። መልአኩ ሕይወት ሰጪ የሆነው ውኃ የማይደርስባቸው ረግረጋማ የሆኑ አንዳንድ ቦታዎች እንዳሉ ገልጿል። እነዚህ ቦታዎች “ጨዋማ እንደሆኑ ይቀራሉ።”b (ሕዝ. 47:8-11) ራእዩ፣ ንጹሕ አምልኮ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ሕያው እንዲሆኑና ጥሩ ሕይወት እንዲመሩ እንደሚያስችላቸው የሚገልጽ አጽናኝ ተስፋ ይዟል። ይሁን እንጂ ራእዩ የሚያስተላልፈው ማስጠንቀቂያም አለ፦ የይሖዋን በረከት የሚቀበሉትም ሆነ ፈውስ የሚያገኙት ሁሉም አይደሉም።
7. በወንዙ ዳርና ዳር ስለበቀሉት ዛፎች የሚናገረው መግለጫ ለግዞተኞቹ አይሁዳውያን ምን ዋስትና ሰጥቷቸዋል?
7 ለመብልና ለመድኃኒት የሚሆኑ ዛፎች። በወንዙ ዳርና ዳር ስላሉት ዛፎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ዛፎች ለራእዩ ውበት ከመስጠት ባለፈ የሚያስተላልፉት መልእክትም አለ። ሕዝቅኤልና ወገኖቹ እነዚህ ዛፎች በየወሩ ስለሚሰጡት ጣፋጭ ፍሬ ማሰባቸው ብቻ እንኳ እንደሚያስደስታቸው የታወቀ ነው። ይህ አስደሳች መግለጫ ይሖዋ በመንፈሳዊ እንደሚመግባቸው ተጨማሪ ዋስትና ሰጥቷቸዋል። ከዚህም ሌላ የዛፎቹ ቅጠል “ለመድኃኒት” እንደሚሆን ልብ በል። (ሕዝ. 47:12) ይሖዋ ከግዞት የሚመለሱት አይሁዳውያን ከሁሉ ይበልጥ የሚያስፈልጋቸው መንፈሳዊ ፈውስ እንደሆነ ያውቃል፤ በመሆኑም በመንፈሳዊ ሁኔታ እንደሚፈውሳቸው ተስፋ ሰጥቷቸዋል። ይህ ተስፋ የሚፈጸመው እንዴት እንደሆነ ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋም በሚገልጹ ሌሎች ትንቢቶች ላይ ተብራርቷል፤ በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ላይ ይህን ሐሳብ ተመልክተን ነበር።
8. የሕዝቅኤል ራእይ በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ የሚጠቁመው ምንድን ነው?
8 ይሁን እንጂ በምዕራፍ 9 ላይ እንደተብራራው እነዚህ ትንቢቶች ከግዞት ከተመለሱት አይሁዳውያን ጋር በተያያዘ ፍጻሜያቸውን ያገኙት ውስን በሆነ መንገድ ብቻ ነው። እርግጥ ትንቢቶቹ ውስን በሆነ መንገድ የተፈጸሙት በሕዝቡ ምክንያት ነው። ሕዝቡ በተደጋጋሚ ወደ መጥፎ ጎዳናቸው ይመለሱ፣ በአምላክ ላይ ያምፁ እንዲሁም ንጹሕ አምልኮን ችላ ይሉ ስለነበር ይሖዋ እንዴት በተሟላ ሁኔታ ሊባርካቸው ይችላል? ታማኝ የሆኑት አይሁዳውያን የወገኖቻቸው ምግባር በጣም አሳዝኗቸው መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ታማኞቹ የይሖዋ አገልጋዮች ይሖዋ የገባው ቃል በምንም ዓይነት ሳይፈጸም እንደማይቀር ያውቁ ነበር። (ኢያሱ 23:14ን አንብብ።) ስለዚህ የሕዝቅኤል ራእይ በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን ማግኘቱ አይቀርም። ታዲያ ይህ የሚሆነው መቼ ነው?
ወንዙ በዛሬው ጊዜም እየፈሰሰ ነው!
9. ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ያየው ራእይ በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ ነው?
9 በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 14 ላይ እንደተመለከትነው ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ያየው ራእይ በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን የሚያገኘው ንጹሕ አምልኮ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ከፍ ከፍ በሚልበት “በዘመኑ መጨረሻ” ነው። (ኢሳ. 2:2) ታዲያ ስለ ወንዙ የሚገልጸው የራእዩ ክፍል በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ ያለው በምን መንገድ ነው?
10, 11. (ሀ) በዛሬው ጊዜ እንደ ወንዝ እየፈሰሱልን ያሉት የትኞቹ በረከቶች ናቸው? (ለ) የይሖዋ በረከት ቁጥራቸው እያደገ የሄደውን ሰዎች ፍላጎት ማርካት በሚያስችል መጠን እየፈሰሰ ያለው እንዴት ነው?
10 በረከት የሚያስገኝ ወንዝ። ከይሖዋ ቤት ስለሚፈሰው ውኃ የሚገልጸው ዘገባ በዘመናችን የትኞቹን በረከቶች ያስታውሰናል? በመንፈሳዊ እንድንመገብና መንፈሳዊ ጤንነታችን እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን ነገሮች በሙሉ ያስታውሰናል። ከእነዚህ መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው ለኃጢአታችን ይቅርታ እንድናገኝና እንድንነጻ የሚያስችለን የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ንጹሕ እውነትም ሕይወት ሰጪ በሆነና በሚያነጻ ውኃ ተመስሏል። (ኤፌ. 5:25-27) እነዚህ በረከቶች በዘመናችን የፈሰሱት እንዴት ነው?
11 በ1919 በጥቂት ሺዎች ብቻ የሚቆጠሩ የይሖዋ አገልጋዮች የነበሩ ሲሆን እነዚህ ክርስቲያኖች የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ምግብ ማግኘት በመቻላቸው እጅግ ተደስተው ነበር። ከዚያ በኋላ በነበሩት አሥርተ ዓመታት ግን ቁጥራቸው በጣም ጨምሯል። በዛሬው ጊዜ ያሉት የአምላክ ሕዝቦች ቁጥራቸው ከስምንት ሚሊዮን ይበልጣል። ታዲያ ንጹሕ የሆነው የእውነት ውኃ የእነሱን ፍላጎት ማሟላት በሚያስችል መጠን እየፈሰሰ ነው? አዎ! መንፈሳዊ እውነት በተትረፈረፈ ሁኔታ እየቀረበልን ነው። ባለፈው መቶ ዘመን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶች፣ መጻሕፍት፣ ብሮሹሮችና ትራክቶች ተዘጋጅተዋል። ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው ወንዝ መጠኑ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ እንደሄደ ሁሉ ንጹሕ የሆነው የእውነት ውኃም በመላው ዓለም ቁጥራቸው እያደገ የሄደውን በመንፈሳዊ የተጠሙ ሰዎች ፍላጎት ማርካት በሚያስችል መጠን በብዛት እየፈሰሰ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ለበርካታ ዓመታት ሲታተሙ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ jw.org በተባለው ድረ ገጽ አማካኝነት መንፈሳዊ ትምህርት ከ900 በሚበልጡ ቋንቋዎች በመቅረብ ላይ ይገኛል። ይህ የእውነት ውኃ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ላላቸው ሰዎች ምን ጥቅም አስገኝቷል?
12. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሰዎችን የጠቀማቸው እንዴት ነው? (ለ) ራእዩ ምን ማስጠንቀቂያ ይዞልናል? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
12 ሕይወት ሰጪ ውኃ። ሕዝቅኤል “ጅረቱ በሚፈስበት ቦታ ያለው ነገር ሁሉ በሕይወት” እንደሚኖር ተነግሮታል። የእውነት ውኃ ወደ መንፈሳዊው ገነት ለመጡ ሁሉ እንዴት እንደፈሰሰላቸው ለማሰብ ሞክር። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በመንፈሳዊ ሁኔታ ሕያውና ጤናማ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ይሁን እንጂ ራእዩ፣ ለዚህ እውነት ምላሽ መስጠታቸውን የሚቀጥሉት ሁሉም ሰዎች እንዳልሆኑ የሚያሳይ ማስጠንቀቂያም ይዟል። በሕዝቅኤል ራእይ ላይ በሙት ባሕር ውስጥ ወንዙ ያልፈወሳቸው ረግረጋማና ውኃ ያቆሩ ቦታዎች እንዳሉ ተገልጾ ነበር፤ ከዚህ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ አንዳንድ ሰዎች የሆነ ወቅት ላይ ልባቸው በመደንደኑ ለእውነት በጎ ምላሽ መስጠታቸውን አቁመዋል።c ይህ ሁኔታ ፈጽሞ እኛ ላይ እንዲደርስ አንፈልግም!—ዘዳግም 10:16-18ን አንብብ።
13. በወንዙ ዳርና ዳር ስለሚገኙት ዛፎች የሚገልጸው ዘገባ ምን ትምህርት ይዞልናል?
13 ለመብልና ለመድኃኒት የሚሆኑ ዛፎች። በወንዙ ዳርና ዳር ስለሚገኙት ዛፎች የሚገልጸው ዘገባ ምን የሚያበረታታ ትምህርት ይዞልናል? ዛፎቹ በየወሩ አዲስ ጣፋጭ ፍሬ እንደሚሰጡ፣ ቅጠላቸው ደግሞ ለመድኃኒት እንደሚሆን መገለጹን ልብ በል። (ሕዝ. 47:12) ይህም የምናገለግለው አምላክ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እንደሚሰጠንና ከሁሉ በላቀው መንገድ ማለትም በመንፈሳዊ ሁኔታ እንደሚፈውሰን ያስታውሰናል። የምንኖርበት ዓለም በመንፈሳዊ ሁኔታ ረሃብተኛና ታማሚ ነው። በተቃራኒው ግን ይሖዋ ሕዝቦቹን እንዴት እንደሚንከባከባቸው ለማሰብ ሞክር። በጽሑፎቻችን ላይ የወጣ አንድ ርዕስ አንብበህ ስትጨርስ፣ በትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኝተህ የመደምደሚያውን መዝሙር ስትዘምር አሊያም አንድ ቪዲዮ ወይም የብሮድካስት ፕሮግራም አይተህ ስታጠናቅቅ ባገኘኸው መንፈሳዊ ምግብ እጅግ እንደምትደሰት ጥያቄ የለውም። በእርግጥም ይሖዋ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርብልናል። (ኢሳ. 65:13, 14) መንፈሳዊ ምግብ መመገባችን በመንፈሳዊ ጤናማ እንድንሆን ይረዳናል። በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ምክር ማግኘታችን እንደ ፆታ ብልግና፣ ስግብግብነትና እምነት ማጣት ያሉትን ለመንፈሳዊነታችን ጠንቅ የሆኑ ነገሮች እንድንዋጋ ይረዳናል። በተጨማሪም ይሖዋ ከባድ ኃጢአት በመፈጸማቸው ምክንያት በመንፈሳዊ የታመሙ ክርስቲያኖች ከሕመማቸው እንዲያገግሙ ለመርዳት የሚያስችል ዝግጅት አድርጓል። (ያዕቆብ 5:14ን አንብብ።) በእርግጥም ሕዝቅኤል ስለ ዛፎቹ ያየው ራእይ እንደሚያመለክተው በእጅጉ ተባርከናል።
14, 15. (ሀ) በወንዙ ስላልተፈወሱት ረግረጋማ ቦታዎች ከሚገልጸው ሐሳብ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ወንዝ በዛሬው ጊዜ እየፈሰሰ ያለው በምን መንገድ ነው?
14 በወንዙ ስላልተፈወሱት ረግረጋማ ቦታዎች ከሚገልጸው ሐሳብም የምናገኘው ትምህርት አለ። የይሖዋን በረከት እንዳናገኝ እንቅፋት የሚሆን ነገር ፈጽሞ ማድረግ አንፈልግም። በመንፈሳዊ ሁኔታ ታማሚ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ እንዳሉት ብዙ ሰዎች ሳንፈወስ ብንቀር በጣም አሳዛኝ ይሆናል። (ማቴ. 13:15) በራእዩ ላይ ከተገለጸው በረከት የሚያስገኝ ወንዝ ተጠቃሚ በመሆናችን በእጅጉ ደስተኞች ነን። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ንጹሕ የእውነት ውኃ ስንጠጣ፣ በስብከቱ ሥራ አማካኝነት ይህን እውነት ለሌሎች ስናካፍል እንዲሁም ታማኙ ባሪያ ሥልጠና ከሰጣቸው ሽማግሌዎች ፍቅራዊ መመሪያ፣ ማጽናኛና እርዳታ ስናገኝ ሕዝቅኤል በራእይ ያየውን ሕይወት ሰጪና ፈዋሽ የሆነ ወንዝ ማስታወሳችን አይቀርም።
15 ስለ ወንዙ የሚገልጸው ራእይ ወደፊትስ ተጨማሪ ፍጻሜ ይኖረው ይሆን? እንዴታ! ቀጥለን እንደምንመለከተው ወንዙ በመጪው ገነት ውስጥ ከአሁኑ እጅግ በላቀ መጠን መፍሰሱን ይቀጥላል።
ራእዩ በገነት ውስጥ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?
16, 17. ወንዙ በገነት ውስጥ ምን በረከቶችን ያስገኛል? ምሳሌ ስጥ።
16 በገነት ውስጥ በወዳጆችህና በቤተሰብህ ተከብበህ አስደሳች ሕይወት ስትመራ ይታይሃል? ሕዝቅኤል በራእይ ስላየው ወንዝ የሚገልጸውን ዘገባ መመርመርህ ይህ ተስፋ ይበልጥ እውን ሆኖ እንዲታይህ ይረዳሃል። እንዴት? የይሖዋን ፍቅር የሚያሳዩትን የራእዩን ሦስት ገጽታዎች እስቲ በድጋሚ እንመልከት።
17 በረከት የሚያስገኝ ወንዝ። ምሳሌያዊው ወንዝ በገነት ውስጥ ከአሁኑ እጅግ በላቀ መጠን ይፈስሳል፤ ምክንያቱም ወንዙ በገነት ውስጥ መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን አካላዊም ጥቅም ያስገኛል። በኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት የአምላክ መንግሥት፣ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ከቤዛው ሙሉ ጥቅም እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። እነዚህ ሰዎች ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና ደረጃ ይደርሳሉ! በዚያ ወቅት በሽታ፣ ሐኪም፣ ነርስ፣ ሆስፒታል ወይም የጤና መድን የሚባል ነገር አይኖርም! “ታላቁን መከራ” በሕይወት አልፈው ወደ አዲሱ ዓለም ለሚገቡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የሕይወት ውኃ ይፈስላቸዋል። (ራእይ 7:9, 14) ይህ ወንዝ በአዲሱ ዓለም መጀመሪያ ላይ በከፍተኛ መጠን የሚፈስ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ከሚመጣው በረከት ጋር ሲነጻጸር ጭል ጭል እንደሚል ውኃ ሊቆጠር ይችላል። በሕዝቅኤል ራእይ ላይ እንደታየው፣ ይህ ወንዝ እየተስፋፋ ሄዶ ተጨማሪ በረከቶችን ያስገኛል።
በረከት የሚያስገኘው ወንዝ በገነት ውስጥ ሁሉም ሰው ወጣትና ጤናማ እንዲሆን ያደርጋል (አንቀጽ 17ን ተመልከት)
18. በሺው ዓመት የክርስቶስ ግዛት ወቅት “የሕይወት ውኃ ወንዝ” ትልቅ ወንዝ የሚሆነው ከምን አንጻር ነው?
18 ሕይወት ሰጪ ውኃ። በሺው ዓመት የክርስቶስ ግዛት ወቅት “የሕይወት ውኃ ወንዝ” ትልቅ ወንዝ ይሆናል። (ራእይ 22:1) በብዙ ሚሊዮኖች እንዲያውም በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት ተነስተው በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ያገኛሉ! ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት የሚያፈሰው በረከት፣ ለብዙ ዘመናት አፈር ለብሰው የቆዩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሙታን ዳግመኛ ሕያው እንዲሆኑ ማድረግን ይጨምራል። (ኢሳ. 26:19) ይሁን እንጂ ከሞት የሚነሱት ሰዎች በሙሉ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ?
19. (ሀ) በገነት ውስጥ የሚገለጡ አዳዲስ መንፈሳዊ መመሪያዎች እንደሚኖሩ የሚያመለክተው ምንድን ነው? (ለ) አንዳንድ ሰዎች ‘ጨዋማ እንደሆኑ የሚቀሩት’ በምን መንገድ ነው?
19 እያንዳንዱ ሰው የራሱን ምርጫ ማድረግ ይኖርበታል። በዚያ ወቅት አዳዲስ የመጽሐፍ ጥቅልሎች ይከፈታሉ። ስለዚህ ከይሖዋ የሚመጣው አርኪ የሆነ ውኃ በዚያን ጊዜ የሚገለጡ እውነቶችን ይኸውም አዳዲስ መንፈሳዊ መመሪያዎችን የሚያካትት ይሆናል። ይህ ተስፋ እጅግ አስደሳች አይደለም? ሆኖም አንዳንዶች እነዚህን መመሪያዎች ለመቀበል እምቢተኞች በመሆን በይሖዋ ላይ ያምፃሉ። በሺው ዓመት የክርስቶስ ግዛት ወቅት የሚያምፁ ሰዎች የገነትን ሰላም እንዲያውኩ አይፈቀድላቸውም። (ኢሳ. 65:20) የእነዚህ ሰዎች ሁኔታ በሕዝቅኤል ራእይ ላይ የተጠቀሱትን ‘ጨዋማ እንደሆኑ የሚቀሩ’ ረግረጋማ ቦታዎች ያስታውሰን ይሆናል። ውድ ከሆነው የሕይወት ውኃ ለመጠጣት አሻፈረን ማለታቸው እንዴት ያለ ሞኝነት ነው! ከሺው ዓመት ግዛት በኋላም ከሰይጣን ጎን ተሰልፈው የሚያምፁ ሰዎች ይኖራሉ። ጻድቅ የሆነውን የይሖዋ አገዛዝ የማይቀበሉ ሁሉ የሚጠብቃቸው ዕጣ ዘላለማዊ ሞት ነው።—ራእይ 20:7-12
20. ሕዝቅኤል በራእይ ያያቸውን ዛፎች የሚያስታውሰን በሺው ዓመት ወቅት የሚኖረው የትኛው ዝግጅት ነው?
20 ለመብልና ለመድኃኒት የሚሆኑ ዛፎች። ይሖዋ በገነት ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው የዘላለም ሕይወት እንዲያጣ አይፈልግም። በመሆኑም በሺው ዓመት ግዛት ወቅት፣ ይህን አጋጣሚ እንድናገኝ የሚያስችል ዝግጅት ያደርግልናል፤ ይህ ዝግጅት ሕዝቅኤል በራእይ ያያቸውን ዛፎች ያስታውሰናል። ይሁን እንጂ በገነት ውስጥ ከይሖዋ የምናገኘው በረከት መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን አካላዊ ጥቅሞችንም የሚያካትት ይሆናል። ኢየሱስ ክርስቶስና አብረውት የሚገዙት 144,000 ቅቡዓን በሰማይ ለሺህ ዓመት ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ። በተጨማሪም 144,000ዎቹ፣ ካህናት እንደመሆናቸው መጠን ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች ከክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሙሉ ጥቅም እንዲያገኙና ወደ ፍጽምና ደረጃ እንዲደርሱ ይረዳሉ። (ራእይ 20:6) ሕዝቅኤል በወንዙ ዳርና ዳር ስላሉት ለመብል የሚሆን ፍሬ የሚያፈሩና ለመድኃኒት የሚሆን ቅጠል የሚያወጡ ዛፎች ያየው ራእይ ሐዋርያው ዮሐንስ ከመዘገበው ሌላ አስደናቂ ትንቢት ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል። (ራእይ 22:1, 2ን አንብብ።) ዮሐንስ የተመለከታቸው ዛፎች “ሕዝቦችን ለመፈወስ የሚያገለግሉ” ቅጠሎች አሏቸው። በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ታማኝ የሰው ልጆች 144,000ዎቹ ከሚሰጡት የክህነት አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ።
21. (ሀ) ሕዝቅኤል በራእይ ስላየው ወንዝ ስታሰላስል ምን ይሰማሃል? (“ቀስ እያለ የሚፈሰው ውኃ ትልቅ ወንዝ ሆነ!” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመለከታለን?
21 ሕዝቅኤል በራእይ ስላየው ወንዝ ስታሰላስል ልብህ በሰላምና በተስፋ አይሞላም? በእርግጥም ከፊታችን እጅግ አስደሳች ጊዜ ይጠብቀናል! ይሖዋ በገነት ውስጥ የሚኖረው ሕይወት ምን እንደሚመስል በዓይነ ሕሊናችን መሣል እንድንችል ሲል በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በርካታ ትንቢቶችን አስነግሯል። በተጨማሪም እነዚህ ትንቢቶች በላቀ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ማየት እንድንችል በትዕግሥት ግብዣ ሲያቀርብ ቆይቷል። ይሁንና ‘በእርግጥ በገነት ውስጥ መኖር እችል ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። የሕዝቅኤል ትንቢት የመጨረሻ ምዕራፎች ማረጋገጫ የሚሰጡን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
a በተጨማሪም ግዞተኞቹ አይሁዳውያን ከትውልድ አገራቸው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ይህ ወንዝ እውነተኛ ወንዝ እንዳልሆነ ሳይገነዘቡ አይቀሩም፤ ምክንያቱም ወንዙ የሚፈሰው በትልቅ ተራራ ላይ ከሚገኝ ቤተ መቅደስ ተነስቶ ነው፤ ይህ ቤተ መቅደስ ደግሞ በተጠቀሰው ቦታ ላይ አይገኝም። ከዚህም ሌላ ራእዩ፣ ወንዙ ምንም ነገር ሳያግደው በቀጥታ ወደ ሙት ባሕር እንደፈሰሰ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል፤ ይህም ቢሆን ከአካባቢው መልክዓ ምድር አንጻር ሊሆን የሚችል ነገር አይደለም።
b አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች፣ ይህ አገላለጽ አዎንታዊ ሐሳብ እንደሚያስተላልፍ ይናገራሉ፤ ምክንያቱም ምግብ ሳይበላሽ እንዲቆይ ለማድረግ የሚያገለግል ጨው ማምረት በሙት ባሕር አካባቢ ለረጅም ዘመን የቆየ አትራፊ ሥራ ነው። ይሁን እንጂ ጥቅሱ “እነዚህ ቦታዎች አይፈወሱም” በማለት በቀጥታ እንደሚናገር ልብ በል። እነዚህ ቦታዎች ከይሖዋ ቤት የሚመነጨው ሕይወት ሰጪ ውኃ ስለማይደርስባቸው ሳይፈወሱ ሕይወት አልባ እንደሆኑ ይቀራሉ። ስለዚህ በዚህ ራእይ ላይ የተጠቀሱት ረግረጋማ ቦታዎች ጨዋማ ሆነው መቅረታቸው አሉታዊ የሆነ ትርጉም የሚያስተላልፍ ሳይሆን አይቀርም።—መዝ. 107:33, 34፤ ኤር. 17:6
c ኢየሱስ ስለ መረቡ የተናገረው ምሳሌም ተመሳሳይ መልእክት ይዟል። መረቡ ብዙ ዓሣዎችን ቢሰበስብም “ጥሩ” ሆነው የተገኙት ግን ሁሉም ዓሣዎች አይደሉም። በምሳሌው ላይ እንደተገለጸው መጥፎ መጥፎዎቹ ዓሣዎች ይጣላሉ። በዚህ መንገድ፣ ኢየሱስ ወደ ይሖዋ ድርጅት ከሚመጡት ሰዎች መካከል ጥቂት የማይባሉት ከጊዜ በኋላ ታማኝነታቸውን ሊያጓድሉ እንደሚችሉ ገልጿል።—ማቴ. 13:47-50፤ 2 ጢሞ. 2:20, 21
-
-
‘ምድሪቱን ርስት አድርጋችሁ ተከፋፈሉ’የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ!
-
-
ምዕራፍ 20
‘ምድሪቱን ርስት አድርጋችሁ ተከፋፈሉ’
ፍሬ ሐሳብ፦ የምድሪቱ መከፋፈል ምን ትርጉም አለው?
1, 2. (ሀ) ይሖዋ ለሕዝቅኤል ምን መመሪያ ሰጠው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመለከታለን?
ሕዝቅኤል አሁን ያየው ራእይ ከ900 ዓመት ገደማ በፊት ይኖሩ በነበሩት በሙሴና በኢያሱ ዘመን የነበረውን ሁኔታ እንዲያስታውስ አድርጎት መሆን አለበት። በዚያ ወቅት ይሖዋ የተስፋይቱን ምድር ወሰኖች ለሙሴ የነገረው ሲሆን ቆየት ብሎ ደግሞ ምድሪቱ ለእስራኤል ነገዶች እንዴት መከፋፈል እንዳለባት ለኢያሱ ነግሮት ነበር። (ዘኁ. 34:1-15፤ ኢያሱ 13:7፤ 22:4, 9) አሁን ደግሞ በ593 ዓ.ዓ. ይሖዋ ሕዝቅኤልንና ግዞተኛ ወገኖቹን ተስፋይቱን ምድር ዳግመኛ ለእስራኤል ነገዶች እንዲያከፋፍሉ ነገራቸው።—ሕዝ. 45:1፤ 47:14፤ 48:29
2 ይህ ራእይ ለሕዝቅኤልና ለግዞተኛ ወገኖቹ ምን መልእክት ይዟል? ዛሬ ለሚኖሩት የአምላክ ሕዝቦችስ የብርታት ምንጭ የሚሆነው እንዴት ነው? ይህ ራእይ ወደፊት በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን ያገኝ ይሆን?
አራት ዋስትናዎችን የያዘ ራእይ
3, 4. (ሀ) የሕዝቅኤል የመጨረሻ ራእይ ለግዞተኞቹ የትኞቹን አራት ዋስትናዎች ሰጥቷል? (ለ) በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የትኛውን ዋስትና እንመረምራለን?
3 ሕዝቅኤል ያየው የመጨረሻ ራእይ በመጽሐፉ የመጨረሻ ዘጠኝ ምዕራፎች ላይ ተገልጿል። (ሕዝ. 40:1 እስከ 48:35) ይህ ራእይ የእስራኤልን ብሔር መልሶ መቋቋም በተመለከተ የተነገሩ አራት አጽናኝ ዋስትናዎችን ይዟል። እነዚህ ዋስትናዎች ምንድን ናቸው? አንደኛ፣ ንጹሕ አምልኮ በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ መልሶ ይቋቋማል። ሁለተኛ፣ ጻድቅ የሆኑ ካህናትና እረኞች ተመልሶ ለተቋቋመው ብሔር አመራር ይሰጣሉ። ሦስተኛ፣ ወደ እስራኤል የሚመለሱ ሁሉ ርስት ያገኛሉ። አራተኛ፣ ይሖዋ በድጋሚ ከእነሱ ጋር ይሆናል፤ አብሯቸውም ይኖራል።
4 በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 13 እና 14 ላይ ስለ መጀመሪያዎቹ ሁለት ዋስትናዎች፣ ማለትም ስለ እውነተኛው አምልኮ መልሶ መቋቋም እንዲሁም ጻድቅ የሆኑ እረኞች ስለሚሰጡት አመራር የሚገልጹት ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙበት መንገድ ተብራርቷል። በዚህ ምዕራፍ ላይ፣ ምድሪቱ ርስት ሆና እንደምትከፋፈል በሚገልጸው በሦስተኛው ዋስትና ላይ ትኩረት እናደርጋለን። የሚቀጥለው ምዕራፍ ደግሞ ይሖዋ ከሕዝቦቹ ጋር እንደሚሆን ስለሚገልጸው ተስፋ የሚያብራራ ይሆናል።—ሕዝ. 47:13-21፤ 48:1-7, 23-29
“ይህች ምድር ርስት ሆና ተሰጥታችኋለች”
5, 6. (ሀ) ለነገዶቹ የሚከፋፈለው ክልል የትኛው ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ስለ ርስት ክፍፍል የሚገልጸው ራእይ ዓላማ ምንድን ነው?
5 ሕዝቅኤል 47:14ን አንብብ። ይሖዋ በራእይ አማካኝነት ሕዝቅኤል ትኩረቱን “እንደ ኤደን የአትክልት ሥፍራ” በምትሆነው ምድር ላይ እንዲያሳርፍ አደረገ። (ሕዝ. 36:35) ከዚያም ይሖዋ “ለ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ርስት አድርጋችሁ የምታከፋፍሏት ክልል ይህች ናት” አለው። (ሕዝ. 47:13) ለነገዶቹ የሚከፋፈለው “ክልል” ግዞተኞቹ ተመልሰው የሚኖሩበት የእስራኤል ምድር ነው። ቀጥሎም በሕዝቅኤል 47:15-21 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ይሖዋ የምድሪቱን ውጫዊ ወሰኖች በዝርዝር ገለጸ።
6 ስለ ርስት ክፍፍል የሚገልጸው የዚህ ራእይ ዓላማ ምንድን ነው? የወሰኖቹ ልክ በዝርዝር መገለጹ ሕዝቅኤልና ግዞተኛ ወገኖቹ የሚወዷት አገራቸው ተመልሳ እንደምትቋቋም እርግጠኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ዝርዝር መግለጫ በመጠቀም የሰጣቸው ዋስትና ግዞተኞቹን ምን ያህል አስደስቷቸው እንደሚሆን መገመት እንችላለን። ታዲያ የጥንቶቹ የአምላክ ሕዝቦች በእርግጥ በምድሪቱ ላይ ርስት ተሰጥቷቸዋል? አዎ፣ ተሰጥቷቸዋል።
7. (ሀ) በ537 ዓ.ዓ. የትኛው ክንውን መፈጸም ጀመረ? ይህስ ምን ያስታውሰናል? (ለ) በመጀመሪያ የትኛውን ጥያቄ እንመለከታለን?
7 ሕዝቅኤል ራእዩን ካየ ከ56 ዓመት ገደማ በኋላ በ537 ዓ.ዓ. በሺዎች የሚቆጠሩ ግዞተኞች ወደ እስራኤል ምድር ተመልሰው ምድሪቱን መውረስ ጀመሩ። ጥንት የተፈጸመው ይህ አስደናቂ ክንውን በዘመናችን በአምላክ ሕዝቦች መካከል የተፈጸመውን ተመሳሳይ ክንውን ያስታውሰናል። በዘመናችን ያሉ የአምላክ ሕዝቦችም ርስት ተሰጥቷቸዋል ሊባል ይችላል። እንዴት? ይሖዋ አገልጋዮቹ ወደ አንድ መንፈሳዊ “ምድር” እንዲገቡና ርስታቸው አድርገው እንዲወርሱት ፈቅዶላቸዋል። በመሆኑም በጥንት ዘመን የነበረችው ተስፋይቱ ምድር መልሳ እንደምትቋቋም የሚገልጸው ትንቢት፣ በዘመናችን የአምላክ ሕዝቦች የሚኖሩበት መንፈሳዊ “ምድር” መልሶ ስለተቋቋመበት ሁኔታ ጥሩ ትምህርት ይሰጠናል። ይሁን እንጂ የምናገኘውን ትምህርት ከመመርመራችን በፊት “በዛሬው ጊዜ መንፈሳዊ ‘ምድር’ አለ የሚል መደምደሚያ ላይ የደረስነው ለምንድን ነው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት እንሞክር።
8. (ሀ) ይሖዋ የሥጋዊ እስራኤላውያንን ብሔር በየትኛው ብሔር ተክቶታል? (ለ) መንፈሳዊው “ምድር” ወይም መንፈሳዊው ገነት ምንድን ነው? (ሐ) መንፈሳዊው ገነት ወደ ሕልውና የመጣው መቼ ነው? በዚያ የሚኖሩትስ እነማን ናቸው?
8 ይሖዋ ቀደም ሲል ለሕዝቅኤል ባሳየው ራእይ ላይ፣ እስራኤል መልሳ እንደምትቋቋም የሚናገሩት ትንቢቶች በላቀ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት ‘አገልጋዩ ዳዊት’ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ከጀመረ በኋላ እንደሆነ አመልክቷል። (ሕዝ. 37:24) ይህ የሆነው በ1914 ዓ.ም. ነው። በዚህ ወቅት የሥጋዊ እስራኤላውያን ብሔር የአምላክ ሕዝብ መሆኑ ቀርቶ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችን ባቀፈው የመንፈሳዊ እስራኤል ብሔር ከተተካ ብዙ ዘመን አልፏል። (ማቴዎስ 21:43፤ 1 ጴጥሮስ 2:9ን አንብብ።) ይሁን እንጂ ይሖዋ የሥጋዊ እስራኤላውያንን ብሔር በመንፈሳዊ ብሔር በመተካት ብቻ አልተወሰነም፤ ግዑዙን የእስራኤል አገርም በመንፈሳዊ “ምድር” ማለትም በመንፈሳዊው ገነት ተክቶታል። (ኢሳ. 66:8) በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 17 ላይ እንደተመለከትነው መንፈሳዊው ገነት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከ1919 ጀምሮ ይሖዋን ሲያመልኩ የቆዩበትን ከስጋት ነፃ የሆነ መንፈሳዊ ሁኔታ ወይም የእንቅስቃሴ ቀጠና ያመለክታል። (“በ1919 ነው የምንለው ለምንድን ነው?” የሚለውን ሣጥን 9ለን ተመልከት።) ከጊዜ በኋላ፣ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ‘ሌሎች በጎችም’ በዚህ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ መኖር ጀምረዋል። (ዮሐ. 10:16) መንፈሳዊው ገነት በዛሬው ጊዜም በማደግና በመስፋፋት ላይ ቢሆንም ይህ ገነት የሚያስገኛቸውን በረከቶች ሙሉ በሙሉ ማጣጣም የሚቻለው ገና ከአርማጌዶን በኋላ ነው።
ምድሪቱን እኩል ማከፋፈል
9. ይሖዋ የምድሪቱን አከፋፈል በተመለከተ ምን ዝርዝር መመሪያ ሰጥቷል?
9 ሕዝቅኤል 48:1, 28ን አንብብ። ይሖዋ የምድሪቱን ወሰኖች ከገለጸ በኋላ ምድሪቱ መከፋፈል ያለባት እንዴት እንደሆነ በዝርዝር ተናገረ። ይሖዋ ምድሪቱ ለዳን ነገድ ከተሰጠው ሰሜናዊ ወሰን አንስቶ ለጋድ ነገድ እስከተሰጠው ደቡባዊ ወሰን ድረስ ለ12ቱ ነገዶች እኩል ቦታ መከፋፈል እንዳለባት ገለጸ። አሥራ ሁለቱም ነገዶች በስተ ምሥራቅ ከሚገኘው የምድሪቱ ምሥራቃዊ ወሰን አንስቶ በስተ ምዕራብ እስከሚገኘው ታላቁ ባሕር ወይም ሜድትራንያን ባሕር ድረስ ወደ ጎን የተዘረጋ ርስት ተሰጥቷቸዋል።—ሕዝ. 47:20
10. ይህ ራእይ ለግዞተኞቹ ምን ዋስትና ሰጥቷቸው ሊሆን ይችላል?
10 ይህ ራእይ ለግዞተኞቹ ምን ዋስትና ሰጥቷቸው ሊሆን ይችላል? ሕዝቅኤል ስለ ምድሪቱ አከፋፈል የሰጠው ዝርዝር መግለጫ፣ ግዞተኞቹ ምድሪቱን የማከፋፈሉ ሥራ በተደራጀ መንገድ እንደሚከናወን እርግጠኞች እንዲሆኑ አድርጓቸው መሆን አለበት። ከዚህም ሌላ ምድሪቱ ለ12ቱ ነገዶች በትክክል መከፋፈሏ ከግዞት የሚመለሱት እስራኤላውያን በሙሉ መልሶ በተቋቋመው ምድር ላይ ርስት ማግኘታቸው የተረጋገጠ እንደሆነ ያሳያል። ከግዞት ከሚመለሱት መካከል ቤት ወይም መሬት የማያገኝ ሰው አይኖርም።
11. ስለ ምድሪቱ መከፋፈል ከሚገልጸው ትንቢታዊ ራእይ ምን ትምህርት እናገኛለን? (“የምድሪቱ አከፋፈል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
11 ዛሬስ ከዚህ ራእይ ምን የሚያበረታታ ትምህርት እናገኛለን? ተመልሳ የተቋቋመችው ተስፋይቱ ምድር ለካህናቱ፣ ለሌዋውያኑና ለአለቆቹ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የ12ቱ ነገዶች አባላት የሚበቃ ቦታ ነበራት። (ሕዝ. 45:4, 5, 7, 8) ዛሬም በተመሳሳይ ቅቡዓን ቀሪዎችና ‘ከእጅግ ብዙ ሕዝብ’ መካከል አመራር የመስጠት ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ብቻ ሳይሆኑ የቀሩት የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላትም በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ቦታ አላቸው።a (ራእይ 7:9) በድርጅቱ ውስጥ የምናበረክተው አስተዋጽኦ ምንም ያህል አነስተኛ ቢሆን፣ በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ የተረጋገጠ ቦታና ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው የሥራ ድርሻ አለን። ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ዋስትና ነው!
በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያለን ኃላፊነት ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል (አንቀጽ 11ን ተመልከት)
ሁለት ጉልህ ልዩነቶች
12, 13. ይሖዋ ምድሪቱ ለ12ቱ ነገዶች የምትከፋፈልበትን መንገድ በተመለከተ ምን መመሪያ ሰጥቷል?
12 ይሖዋ የምድሪቱን አከፋፈል በተመለከተ ለሕዝቅኤል የሰጣቸው አንዳንድ መመሪያዎች ለሙሴ ከሰጣቸው መመሪያዎች የተለዩ በመሆናቸው ሕዝቅኤል ግራ ሳይጋባ አይቀርም። ከእነዚህ ልዩነቶች መካከል ሁለቱን እንመልከት። አንደኛው ከምድሪቱ አከፋፈል ጋር የተያያዘ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከምድሪቱ ነዋሪዎች ጋር የተያያዘ ነው።
13 አንደኛ፣ የምድሪቱ አከፋፈል። ሙሴ ብዙ ሕዝብ ላላቸው ነገዶች በዛ ያለ ርስት፣ አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ላላቸው ነገዶች ደግሞ አነስ ያለ ርስት እንዲሰጥ ተነግሮት ነበር። (ዘኁ. 26:52-54) ሆኖም ሕዝቅኤል ባየው ራእይ ላይ፣ ይሖዋ ለሁሉም ነገዶች “እኩል ድርሻ [“እያንዳንዱም እንደ ወንድሙ” ግርጌ]” እንዲከፋፈል መመሪያ ሰጥቷል። (ሕዝ. 47:14) በመሆኑም የ12ቱም ነገዶች ርስት ከሰሜን ወሰኑ እስከ ደቡብ ወሰኑ ድረስ ያለው ርቀት እኩል መሆን ነበረበት። የየትኛውም ነገድ አባል የሆኑ እስራኤላውያን፣ ለምለም የሆነችው ተስፋይቱ ምድር ከምታስገኘው የተትረፈረፈ ምርት በእኩል መጠን ተጠቃሚዎች ይሆናሉ።
14. ይሖዋ ስለ ባዕድ አገር ሰዎች ለሕዝቅኤል የሰጠው መመሪያ በሙሴ ሕግ ውስጥ ከተገለጸው የሚለየው በምን መንገድ ነው?
14 ሁለተኛ፣ የምድሪቱ ነዋሪዎች። የሙሴ ሕግ ለባዕድ አገር ሰዎች ጥበቃ ያደርግ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በይሖዋ አምልኮ እንዲካፈሉ ይፈቅድላቸው ነበር፤ ሆኖም የባዕድ አገር ሰዎች ርስት አያገኙም ነበር። (ዘሌ. 19:33, 34) ይሖዋ ለሕዝቅኤል የሰጠው መመሪያ ግን በሕጉ ውስጥ ከሰፈረው የተለየ ነበር። ይሖዋ “ከባዕድ አገር ለመጣው ሰው በሚኖርበት ነገድ ክልል ውስጥ ርስት ልትሰጡት ይገባል” የሚል መመሪያ ሰጥቷል። ይሖዋ በዚህ ትእዛዝ አማካኝነት ‘የአገሪቱ ተወላጆች በሆኑት እስራኤላውያን’ እና በምድሪቱ በሚኖሩት የባዕድ አገር ሰዎች መካከል የነበረውን መሠረታዊ ልዩነት አስወግዷል። (ሕዝ. 47:22, 23) ሕዝቅኤል በራእይ በተመለከታት ተመልሳ የተቋቋመች ምድር ውስጥ በነዋሪዎቹ መካከል እኩልነትና የአምልኮ አንድነት ሰፍኖ ነበር።—ዘሌ. 25:23
15. ይሖዋ ስለ ምድሪቱ አከፋፈልና ስለ ነዋሪዎቿ የሰጣቸው መመሪያዎች እሱን በተመለከተ የትኛውን የማይለወጥ እውነታ ጎላ አድርገው ያሳያሉ?
15 ይሖዋ የምድሪቱን አከፋፈልና ነዋሪዎቿን በተመለከተ የሰጣቸው እነዚህ ሁለት አስደናቂ መመሪያዎች ግዞተኞቹን አበረታተዋቸው መሆን አለበት። የእስራኤል ተወላጆችም ሆኑ ይሖዋን የሚያመልኩ የባዕድ አገር ሰዎች፣ ይሖዋ ለእያንዳንዳቸው እኩል ቦታ እንደሚሰጣቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። (ዕዝራ 8:20፤ ነህ. 3:26፤ 7:6, 25፤ ኢሳ. 56:3, 8) በተጨማሪም እነዚህ መመሪያዎች የሚከተለውን አበረታች የሆነና የማይለወጥ እውነታ ጎላ አድርገው ያሳያሉ፦ ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች በእሱ ፊት በእኩል ደረጃ ውድ ናቸው። (ሐጌ 2:7ን አንብብ።) በዚህ ዘመን የምንኖር የይሖዋ አገልጋዮችም፣ ተስፋችን ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ይህን እውነት ማወቃችን በጣም ያስደስተናል።
16, 17. (ሀ) የምድሪቱን አከፋፈልና ነዋሪዎቿን በተመለከተ የተሰጡትን ዝርዝር መግለጫዎች መመርመራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንመለከታለን?
16 የምድሪቱን አከፋፈልና ነዋሪዎቿን በተመለከተ የተሰጡትን እነዚህን ዝርዝር መግለጫዎች መመርመራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? በዛሬው ጊዜ ያለው ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ዋነኛ ገጽታ እኩልነትና አንድነት መሆን እንዳለበት ያስገነዝበናል። ይሖዋ አያዳላም። በመሆኑም እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘አድልዎ ባለማድረግ የይሖዋን ባሕርይ አንጸባርቃለሁ? ዘራቸውም ሆነ የኑሮ ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን ለሁሉም የእምነት ባልንጀሮቼ ልባዊ አክብሮት አሳያለሁ?’ (ሮም 12:10) ይሖዋ በሙሉ ልባችን ቅዱስ አገልግሎት ከምናቀርብበትና የእሱን በረከቶች ከምናገኝበት መንፈሳዊ ገነት ሁላችንም በእኩል ደረጃ ተጠቃሚዎች እንድንሆን ስላስቻለን በጣም ደስተኞች ነን።—ገላ. 3:26-29፤ ራእይ 7:9
አድልዎ ባለማድረግና ለሌሎች ልባዊ አክብሮት በማሳየት የይሖዋን ባሕርይ እናንጸባርቃለን? (አንቀጽ 15, 16ን ተመልከት)
17 አሁን ደግሞ ሕዝቅኤል ባየው የመጨረሻ ራእይ የመደምደሚያ ክፍል ላይ የምናገኘውን አራተኛ ዋስትና ይኸውም ይሖዋ ከግዞተኞቹ ጋር እንደሚሆን የሰጠውን ተስፋ እንመልከት። ከዚህ ተስፋ ምን ትምህርት እናገኛለን? የዚህን ጥያቄ መልስ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ እንመለከታለን።
-
-
“ከተማዋ ‘ይሖዋ በዚያ አለ’ ተብላ ትጠራለች”የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ!
-
-
ምዕራፍ 21
“ከተማዋ ‘ይሖዋ በዚያ አለ’ ተብላ ትጠራለች”
ፍሬ ሐሳብ፦ ከተማዋና በመዋጮ የተሰጠው መሬት ያላቸው ትርጉም
1, 2. (ሀ) የተወሰነው የምድሪቱ ክፍል ተለይቶ የተቀመጠው ለምንድን ነው? (በመጽሐፉ ሽፋን ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ራእዩ ለግዞተኞቹ ምን ዋስትና ይሰጣቸዋል?
ሕዝቅኤል ባየው የመጨረሻ ራእይ ላይ ለአንድ ልዩ ዓላማ ተለይቶ የተቀመጠን መሬት በተመለከተ መግለጫ ተሰጠው። ይህ የምድሪቱ ክፍል ተለይቶ የተቀመጠው ለእስራኤል ነገዶች በርስትነት እንዲሰጥ ሳይሆን ለይሖዋ መዋጮ ሆኖ እንዲሰጥ ነው። በተጨማሪም ሕዝቅኤል አስገራሚ ስያሜ ስለተሰጣት አንዲት ከተማ ተነገረው። ይሄኛው የራእዩ ክፍል ለግዞተኞቹ በጣም አስፈላጊ የሆነ ዋስትና ይሰጣቸዋል፦ ወደሚወዷት የትውልድ አገራቸው ሲመለሱ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ይሆናል።
2 ሕዝቅኤል ለይሖዋ በመዋጮ የተሰጠውን መሬት በተመለከተ ዝርዝር መግለጫ አስፍሮልናል። በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው የይሖዋ አምላኪዎች ትልቅ ትርጉም የያዘውን ይህን ዘገባ እስቲ እንመርምር።
‘መዋጮ ሆኖ የተሰጠው ቅዱስ ስፍራና ከተማዋ’
3. መዋጮ ሆኖ የተሰጠው መሬት የትኞቹ አምስት ክፍሎች ነበሩት? እነዚህ ክፍሎች ለምን ዓላማ የሚያገለግሉ ነበሩ? (“መዋጮ አድርጋችሁ ለመስጠት የምትለዩት መሬት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
3 ተለይቶ በተቀመጠው የምድሪቱ ክፍል ውስጥ ከሰሜን እስከ ደቡብ 25,000 ክንድ (13 ኪሎ ሜትር) እንዲሁም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ 25,000 ክንድ ርዝመት ያለው መሬት አለ። አራቱም ጎኖቹ እኩል የሆኑት ይህ አራት ማዕዘን መሬት “በመዋጮ የተሰጠው መሬት በአጠቃላይ” ተብሎ ተገልጿል። መሬቱ ሦስት ቦታ ተከፍሏል። የላይኛው ክፍል ለሌዋውያን፣ መካከለኛው ክፍል ደግሞ ለቤተ መቅደሱና ለካህናቱ የተመደበ ነበር። እነዚህ ሁለት ክፍሎች በጋራ “መዋጮ ሆኖ የተሰጠ ቅዱስ ስፍራ” ተብለው ተጠርተዋል። “የቀረው ቦታ” ማለትም አነስ ያለው የታችኛው የመሬቱ ክፍል ቅዱስ ለሆነ አገልግሎት የተለየ አይደለም። ለከተማዋ የተመደበ ነው።—ሕዝ. 48:15, 20
4. ለይሖዋ መዋጮ ሆኖ ስለሚሰጠው መሬት ከሚገልጸው ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?
4 ለይሖዋ መዋጮ ሆኖ ስለሚሰጠው መሬት ከሚገልጸው ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ በመጀመሪያ መዋጮ ሆኖ የሚሰጠውን መሬት ከለየ በኋላ ለየነገዶቹ የሚከፋፈለውን መሬት በመመደብ ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው ለዚህ መንፈሳዊ ማዕከል እንደሆነ አመልክቷል። (ሕዝ. 45:1) መሬቱ በዚህ ቅደም ተከተል መከፋፈሉ፣ በግዞት የነበሩትን እስራኤላውያን በሕይወታቸው ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ መስጠት ያለባቸው ለይሖዋ አምልኮ እንደሆነ አስተምሯቸው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ዛሬም በተመሳሳይ የአምላክን ቃል ማጥናትን፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትንና በስብከቱ ሥራ መካፈልን ለመሳሰሉት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባን እንገነዘባለን። ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ነገር በማስቀደም ረገድ ይሖዋ የተወውን ምሳሌ የምንከተል ከሆነ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ለእሱ በምናቀርበው አምልኮ ላይ ያተኮረ ይሆናል።
“ከተማዋ በመካከሉ ትሆናለች”
5, 6. (ሀ) የከተማዋ ባለቤት ማን ነው? (ለ) ይህች ከተማ ምን ልታመለክት አትችልም? ለምንስ?
5 ሕዝቅኤል 48:15ን አንብብ። ‘ከተማዋም’ ሆነች በከተማዋ ዙሪያ ያለው መሬት ምን ያመለክታሉ? (ሕዝ. 48:16-18) በራእዩ ላይ ይሖዋ ለሕዝቅኤል “የከተማዋ ርስት” ባለቤት ‘የእስራኤል ቤት ሁሉ’ እንደሚሆን ነግሮታል። (ሕዝ. 45:6, 7) በመሆኑም ከተማዋና በዙሪያዋ ያለው መሬት ‘ለይሖዋ የተለየው’ “መዋጮ ሆኖ የተሰጠ ቅዱስ ስፍራ” ክፍል አይደለም። (ሕዝ. 48:9, 20) ይህን በአእምሯችን ይዘን፣ ስለዚህች ከተማ የተሰጠው መግለጫ ለእኛ ምን ትምህርት እንደያዘ እንመልከት።
6 ሆኖም ስለ ከተማዋ ከተሰጠው መግለጫ ምን ትምህርት እንደምናገኝ ከመመልከታችን በፊት ይህች ከተማ ምን ልታመለክት እንደማትችል ማወቅ ያስፈልገናል። ቤተ መቅደሱ የሚገኝባትን ዳግመኛ የተገነባችውን የኢየሩሳሌም ከተማ ልታመለክት አትችልም። ለምን? ምክንያቱም ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከታት ከተማ በውስጧ ቤተ መቅደስ አይኖራትም። በተጨማሪም ከተማዋ ዳግመኛ በተቋቋመው የእስራኤል ምድር ውስጥ የሚገኝን የትኛውንም ከተማ አታመለክትም። ለምን? ምክንያቱም ከግዞት የተመለሱት እስራኤላውያንም ሆኑ ዘሮቻቸው በራእዩ ውስጥ የተገለጸችውን ዓይነት ከተማ ገንብተው አያውቁም። ከዚህም ሌላ ከተማዋ በሰማይ ላይ ያለችን ከተማ ልታመለክት አትችልም። ለምን? ምክንያቱም ለቅዱስ አምልኮ ብቻ ተለይቶ በተመደበ ቦታ ላይ ከተገነቡ ሕንፃዎች በተለየ መልኩ ይህች ከተማ የተገነባችው ‘ቅዱስ ላልሆነ’ ወይም ተራ ለሆነ አገልግሎት በተመደበ ቦታ ላይ ነው።—ሕዝ. 42:20
7. ሕዝቅኤል በራእይ ያያት ከተማ የምታመለክተው ምንን መሆን አለበት? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
7 ታዲያ ሕዝቅኤል በራእይ ያያት ከተማ ምን ታመለክታለች? ሕዝቅኤል ከተማዋን ያየው ስለ ምድሪቱ ባየው ራእይ ላይ እንደሆነ ልብ በል። (ሕዝ. 40:2፤ 45:1, 6) ምድሪቱ የምታመለክተው ምሳሌያዊ የሆነን “ምድር” እንደሆነ የአምላክ ቃል ይጠቁማል፤ በመሆኑም ከተማዋም የምታመለክተው ምሳሌያዊ የሆነን ከተማ መሆን አለበት። “ከተማ” የሚለው ቃል በአብዛኛው ምን ሐሳብ ያስተላልፋል? ይህ ቃል፣ በርካታ ሰዎች ተደራጅተውና አንድ ዓይነት መዋቅር ፈጥረው አብረው የሚኖሩበትን ቦታ ያመለክታል። በመሆኑም ሕዝቅኤል የተመለከታት አራቱም ጎኗ እኩል የሆነው ከተማ፣ በሚገባ የተደራጀን መስተዳድር የምታመለክት ይመስላል።
8. የዚህ መስተዳድር የግዛት ክልል ምንድን ነው? እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
8 የዚህ መስተዳድር የግዛት ክልል ምንድን ነው? የሕዝቅኤል ራእይ ከተማዋ የምትገኘው በምሳሌያዊው ምድር ውስጥ እንደሆነ ይገልጻል። በመሆኑም ይህ መስተዳድር በዛሬው ጊዜ ሥራውን የሚያከናውነው የአምላክ ሕዝቦች የእንቅስቃሴ ቀጠና በሆነው በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ነው። ከተማዋ የተገነባችው ቅዱስ ባልሆነ ወይም ለተራ አገልግሎት በሚውል መሬት ላይ መሆኑስ ምን ይጠቁማል? ከተማዋ የምታመለክተው ሰማያዊ የሆነን መስተዳድር ሳይሆን በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ጥቅም ሲባል የተቋቋመውን ምድራዊ መስተዳድር መሆኑን ያስታውሰናል።
9. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ይህ ምድራዊ መስተዳድር እነማንን ያቀፈ ነው? (ለ) ኢየሱስ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት ምን ያደርጋል?
9 ይህ ምድራዊ መስተዳድር እነማንን ያቀፈ ነው? በሕዝቅኤል ራእይ ላይ፣ በከተማዋ መስተዳድር ውስጥ ግንባር ቀደም ኃላፊነት ያለው ሰው “አለቃው” ተብሎ ተጠርቷል። (ሕዝ. 45:7) “አለቃው” በሕዝቡ መካከል የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግል ቢሆንም ካህን ወይም ሌዋዊ አይደለም። ይህ አለቃ በዛሬው ጊዜ የጉባኤ የበላይ ተመልካቾች ሆነው የሚያገለግሉትን፣ በተለይም ቅቡዓን ያልሆኑትን ሽማግሌዎች ያስታውሰናል። ‘ከሌሎች በጎች’ የተውጣጡት እነዚህ አሳቢ የሆኑ መንፈሳዊ እረኞች በክርስቶስ ሰማያዊ መስተዳድር ሥር የሚሠሩ ትሑት ምድራዊ አገልጋዮች ናቸው። (ዮሐ. 10:16) ኢየሱስ በመጪው የሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት፣ ብቃት ያላቸውን ሽማግሌዎች “በምድር ሁሉ ላይ መኳንንት” አድርጎ ይሾማቸዋል። (መዝ. 45:16) እነሱም በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት በሰማያዊው መንግሥት አመራር ሥር ሆነው የአምላክን ሕዝቦች ያገለግላሉ።
“ይሖዋ በዚያ አለ”
10. የከተማዋ ስም ማን ነው? ይህ ስያሜ ምን ዋስትና ይሰጣል?
10 ሕዝቅኤል 48:35ን አንብብ። የከተማዋ ስም “ይሖዋ በዚያ አለ” የሚል ነው። ይህ ስያሜ ይሖዋ በከተማዋ ውስጥ እንደሚገኝ የሚያሳይ ዋስትና ነው። ይሖዋ በማዕከላዊ ቦታ ላይ የምትገኘውን ይህችን ከተማ ለሕዝቅኤል ሲያሳየው፣ ለግዞተኞቹ ‘ዳግመኛ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ!’ የሚል መተማመኛ የሰጣቸው ያህል ነበር። እንዴት ያለ አስደሳች ዋስትና ነው!
11. ሕዝቅኤል ስለ ከተማዋም ሆነ ስለ ከተማዋ ስም ከተመለከተው ራእይ ምን ትምህርት እናገኛለን?
11 ይህ የሕዝቅኤል ትንቢት ምን ትምህርት ይሰጠናል? የከተማዋ ስም ይሖዋ አሁንም ሆነ ለዘላለም፣ ምድር ላይ ካሉት ታማኝ አገልጋዮቹ ጋር እንደሚኖር ማረጋገጫ ይሰጠናል። በተጨማሪም ትልቅ ትርጉም ያዘለው ይህ ስም አንድን ወሳኝ እውነታ አጉልቶ ያሳያል፤ ከተማዋ የተቋቋመችው ለየትኛውም ሰው ሥልጣን ለመስጠት ሳይሆን ፍቅራዊና ምክንያታዊ የሆኑትን የይሖዋ መንገዶች ለማስፈጸም ነው። ለምሳሌ ይሖዋ፣ መስተዳድሩ በሰብዓዊ አመለካከት ላይ ተመሥርቶ ምድሪቱን እንዲያከፋፍል ሥልጣን አልሰጠውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ፣ ዝቅ ተደርገው የሚታዩትን ጨምሮ ለአገልጋዮቹ በሙሉ የሰጠውን ድርሻ ወይም ቦታ አስተዳዳሪዎቹ እንዲያከብሩ ይፈልጋል።—ሕዝ. 46:18፤ 48:29
12. (ሀ) የዚህች ከተማ አንዱ አስደናቂ ገጽታ ምንድን ነው? ይህስ ምን ያመለክታል? (ለ) ይህ ገጽታ ለክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ምን አስፈላጊ ማሳሰቢያ ያስተላልፋል?
12 “ይሖዋ በዚያ አለ” የተባለችው ከተማ ያላት ሌላ አስደናቂ ገጽታ ምንድን ነው? በጥንት ዘመን የነበሩ ከተሞች ለመከላከያነት የሚያገለግሉ ቅጥሮች የነበሯቸው ሲሆን ቅጥሮቹ ጥቂት በሮች ብቻ ነበሯቸው። ይህች ከተማ ግን 12 በሮች አሏት። (ሕዝ. 48:30-34) በሮቹ ብዙ መሆናቸው (በአራቱም ጎን ሦስት ሦስት በሮች አሉ) የዚህች ከተማ አስተዳዳሪዎች ለአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ተደራሽና በቀላሉ የሚቀረቡ መሆናቸውን ያመለክታል። ከዚህም ሌላ ከተማዋ 12 በሮች ያሏት መሆኑ ለሁሉም፣ ማለትም “ለእስራኤል ቤት ሁሉ” ክፍት መሆኗን ያሳያል። (ሕዝ. 45:6) ወደ ከተማዋ በቀላሉ መግባት የሚቻል መሆኑ ለክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች አንድ አስፈላጊ የሆነ ማሳሰቢያ ያስተላልፋል። ይሖዋ፣ የበላይ ተመልካቾች በመንፈሳዊው ገነት ለሚኖሩ ሁሉ ጊዜ እንዲሰጡና በቀላሉ የሚቀረቡ እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል።
ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ለሌሎች ጊዜ የሚሰጡና በቀላሉ የሚቀረቡ ናቸው (አንቀጽ 12ን ተመልከት)
የአምላክ ሕዝቦች “የአምልኮ ሥርዓት ለመፈጸም” ይመጣሉ፣ ‘ከተማዋንም ያገለግላሉ’
13. ይሖዋ ሕዝቦቹ የሚካፈሉባቸውን የተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች በተመለከተ ምን ገልጿል?
13 እስቲ ወደ ሕዝቅኤል ዘመን መለስ እንበልና ስለ ምድሪቱ አከፋፈል ያየውን ራእይ አስመልክቶ ምን ተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮችን እንደመዘገበ እንመልከት። ይሖዋ ሕዝቦቹ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች እንደሚካፈሉ ተናግሯል። ‘በመቅደሱ የሚያገለግሉት’ ካህናት መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ እንዲሁም ይሖዋን ለማገልገል ወደ እሱ ይቀርባሉ። “በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚያገለግሉት ሌዋውያን” ደግሞ “በውስጡ የሚካሄደውን አገልግሎትና መሠራት ያለበትን ሥራ ሁሉ” ያከናውናሉ። (ሕዝ. 44:14-16፤ 45:4, 5) በተጨማሪም በከተማዋ አቅራቢያ የሚሠሩ ሠራተኞች አሉ። እነዚህ ሠራተኞች እነማን ናቸው?
14. በከተማዋ አቅራቢያ የሚሠሩት ሠራተኞች ምን ያስታውሱናል?
14 በከተማዋ አቅራቢያ የሚሠሩት ሠራተኞች “ከሁሉም የእስራኤል ነገዶች የተውጣጡ ሰዎች” ናቸው። የእነዚህ ሰዎች የሥራ ድርሻ ድጋፍ መስጠት ነው። “ከተማዋን ለሚያገለግሉ ምግብ” የሚሆን እህል የማምረት ሥራ ተሰጥቷቸዋል። (ሕዝ. 48:18, 19) ይህ ዝግጅት እኛ ያለንን የትኛውን አጋጣሚ ያስታውሰናል? በዛሬው ጊዜ በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች የሚሰጡትን አገልግሎት እንዲሁም ‘ከእጅግ ብዙ ሕዝብ’ መካከል ግንባር ቀደም ሆነው አመራር የመስጠት ኃላፊነት ያለባቸው ወንድሞች የሚያከናውኑትን አገልግሎት የመደገፍ አጋጣሚ አላቸው። (ራእይ 7:9, 10) እንዲህ ያለውን ድጋፍ መስጠት የምንችልበት ዋነኛው መንገድ ታማኙ ባሪያ የሚሰጠውን መመሪያ በፈቃደኝነት መቀበል ነው።
15, 16. (ሀ) የሕዝቅኤል ራእይ ምን ሌላ ዝርዝር መረጃ ይዟል? (ለ) እኛስ በተመሳሳይ የትኞቹን ነገሮች የማከናወን አጋጣሚ አለን?
15 በሕዝቅኤል ራእይ ላይ የተጠቀሰው ሌላ ዝርዝር መረጃ ደግሞ አገልግሎታችንን በተመለከተ ጥሩ ትምህርት ይሰጠናል። ይሖዋ ከሌዊ ነገድ ውጭ ያሉት 12 ነገዶች በሁለት ቦታዎች፣ ማለትም በቤተ መቅደሱ ግቢና በከተማዋ የግጦሽ መሬት ላይ የሚያከናውኑት ነገር እንደሚኖር ተናግሯል። በእነዚህ ቦታዎች ላይ የሚያከናውኑት ነገር ምንድን ነው? በቤተ መቅደሱ ግቢ ውስጥ ሁሉም ነገዶች ለይሖዋ መሥዋዕት በማቅረብ “የአምልኮ ሥርዓት” ይፈጽማሉ። (ሕዝ. 46:9, 24) ከዚህም ሌላ የሁሉም ነገዶች አባላት መሬቱን በማረስ ለከተማዋ ድጋፍ ይሰጣሉ። እነዚህ ሠራተኞች ከሚያከናውኑት ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን?
16 በዛሬው ጊዜ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት በሕዝቅኤል ራእይ ላይ ከተጠቀሱት ነገሮች ጋር የሚመሳሰል ነገር የማከናወን አጋጣሚ አላቸው። አንደኛ፣ የውዳሴ መሥዋዕት በማቅረብ ይሖዋን “በቤተ መቅደሱ” ያመልካሉ። (ራእይ 7:9-15) ይህን የሚያደርጉት በስብከቱ ሥራ በመካፈልና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እምነታቸውን በይፋ በመግለጽ ነው። ተቀዳሚ ኃላፊነታቸው፣ በዚህ መንገድ ለይሖዋ አምልኮ ማቅረብ እንደሆነ ይገነዘባሉ። (1 ዜና 16:29) በተጨማሪም ብዙዎቹ የአምላክ ሕዝቦች በተለያዩ መንገዶች ለአምላክ ድርጅት ድጋፍ ይሰጣሉ። ለምሳሌ የስብሰባ አዳራሾችንና የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎችን በመገንባትና በመጠገን እንዲሁም የይሖዋ ድርጅት በሚያካሂዳቸው ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶች በመካፈል እርዳታ ያበረክታሉ። ሌሎች ደግሞ የገንዘብ መዋጮ በማድረግ እነዚህን ፕሮጀክቶች ይደግፋሉ። ይህን ሁሉ ሥራ በማከናወን በምሳሌያዊ ሁኔታ መሬቱን የሚያርሱት “ለአምላክ ክብር” ማምጣት ስለሚፈልጉ ነው። (1 ቆሮ. 10:31) ይሖዋ ‘እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ እንደሚደሰት’ ስለሚያውቁ ሥራቸውን በቅንዓትና በደስታ ያከናውናሉ። (ዕብ. 13:16) አንተስ በእነዚህ አጋጣሚዎች ሙሉ በሙሉ እየተጠቀምክ ነው?
ሕዝቅኤል በከተማዋ ውስጥና በበሮቿ አቅራቢያ ይከናወኑ ስለነበሩት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ከሰጠው መግለጫ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ከአንቀጽ 14-16ን ተመልከት)
“አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን”
17. (ሀ) ወደፊት የሕዝቅኤል ራእይ በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው? (ለ) በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት በከተማ ከተመሰለው መስተዳድር ጥቅም የሚያገኙት እነማን ናቸው?
17 ሕዝቅኤል በመዋጮ ስለተሰጠው መሬት ያየው ራእይ ወደፊት በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን ያገኝ ይሆን? አዎ! ሕዝቅኤል “የይሖዋ መቅደስ” የሚገኝበት “መዋጮ ሆኖ የተሰጠ ቅዱስ ስፍራ” የተባለው የመሬቱ ክፍል የሚገኘው በምድሪቱ እምብርት ላይ እንደሆነ መግለጹን ልብ በል። (ሕዝ. 48:10) ይህም ከአርማጌዶን በኋላ በየትኛውም የምድር ክፍል ብንኖር ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደሚኖር ዋስትና ይሆነናል። (ራእይ 21:3) በምድር ላይ የአምላክን ሕዝቦች ለማገልገል የሚሾሙትን ሰዎች የሚያመለክተው በከተማ የተመሰለው መስተዳድር፣ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ‘የአዲሱ ምድር’ ማለትም የአዲሱ ኅብረተሰብ አባላት ለሚሆኑ ሁሉ ፍቅራዊ አመራር በመስጠት የግዛት አድማሱን በመላው ምድር ላይ ያስፋፋል።—2 ጴጥ. 3:13
18. (ሀ) በከተማ የተመሰለው መስተዳድር ከአምላክ አገዛዝ ጋር እንደሚስማማ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) የከተማዋ ስም ምን ያረጋግጥልናል?
18 በከተማ የተመሰለው መስተዳድር ከአምላክ አገዛዝ ጋር ሙሉ በሙሉ እንደሚስማማ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? የአምላክ ቃል እንደሚያሳየው 12 በሮች ያሏት ምድራዊቷ ከተማ፣ 12 በሮች ያሏት ሰማያዊ ከተማ ነጸብራቅ ነች፤ ይህች ሰማያዊ ከተማ ከክርስቶስ ጋር የሚገዙትን 144,000 ቅቡዓን ያቀፈችው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ነች። (ራእይ 21:2, 12, 21-27) ይህም ምድራዊው መስተዳድር በሰማይ ያለው የአምላክ መንግሥት ከሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ጋር ሙሉ በሙሉ እንደሚስማማና እነዚህን ውሳኔዎች በጥንቃቄ እንደሚያስፈጽም ያመለክታል። አዎ፣ “ይሖዋ በዚያ አለ” የሚለው የከተማዋ ስም ንጹሕ አምልኮ በገነት ውስጥ ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር ያረጋግጥልናል። ወደፊት የሚጠብቀን ጊዜ ምንኛ አስደሳች ነው!
-