-
ማርቆስ 9:17-29አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
17 ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “መምህር፣ ልጄ ዱዳ የሚያደርግ መንፈስ ስላደረበት ወደ አንተ አመጣሁት።+ 18 በያዘው ስፍራ ሁሉ መሬት ላይ ይጥለዋል፤ ከዚያም አፉ አረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱን ያፋጫል እንዲሁም ይዝለፈለፋል። ደቀ መዛሙርትህ እንዲያስወጡት ጠየቅኳቸው፤ እነሱ ግን ሊያስወጡት አልቻሉም።” 19 እሱም መልሶ “እምነት የለሽ ትውልድ ሆይ፣+ ከእናንተ ጋር እስከ መቼ መቆየት ሊኖርብኝ ነው? እስከ መቼስ እናንተን መታገሥ ሊኖርብኝ ነው? ልጁን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው።+ 20 ልጁንም ወደ እሱ አመጡት፤ ልጁን የያዘው መንፈስም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ወዲያውኑ ልጁን አንዘፈዘፈው። ልጁም መሬት ላይ ከወደቀ በኋላ አፉ አረፋ እየደፈቀ ይንከባለል ጀመር። 21 ከዚያም ኢየሱስ አባትየውን “እንዲህ ማድረግ ከጀመረው ምን ያህል ጊዜ ሆነው?” ሲል ጠየቀው። አባትየውም እንዲህ አለው፦ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ 22 ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳት ውስጥና ውኃ ውስጥ ይጥለዋል። ማድረግ የምትችለው ነገር ካለ እዘንልንና እርዳን።” 23 ኢየሱስም “‘የምትችለው ነገር ካለ’ አልክ? እምነት ላለው ሰው፣ ሁሉ ነገር ይቻላል” አለው።+ 24 ወዲያውም የልጁ አባት “እምነት አለኝ! እምነቴ እንዲጠነክር ደግሞ አንተ እርዳኝ!”+ በማለት ጮክ ብሎ ተናገረ።
25 ኢየሱስ ሕዝቡ ወደ እነሱ ግር ብሎ እየሮጠ በመምጣት ላይ መሆኑን ሲያይ ርኩሱን መንፈስ “አንተ ዱዳና ደንቆሮ የምታደርግ መንፈስ ከእሱ ውጣ፤ ዳግመኛም ወደ እሱ እንዳትገባ አዝሃለሁ!” ሲል ገሠጸው።+ 26 ርኩሱ መንፈስ በኃይል ከጮኸና ብዙ ካንዘፈዘፈው በኋላ ወጣ፤ ልጁም የሞተ ያህል ሆነ፤ በዚህ ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች “ሞቷል!” ይሉ ጀመር። 27 ይሁን እንጂ ኢየሱስ እጁን ይዞ አስነሳው፤ ልጁም ተነስቶ ቆመ። 28 ከዚያም ወደ ቤት ከገባ በኋላ ብቻውን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።+ 29 እሱም “እንዲህ ዓይነቱ በጸሎት ካልሆነ በቀር ሊወጣ አይችልም” አላቸው።
-
-
ሉቃስ 9:38-42አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
38 እነሆም ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “መምህር፣ ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ፤ ምክንያቱም ያለኝ ልጅ አንድ እሱ ብቻ ነው።+ 39 እነሆም፣ ርኩስ መንፈስ ይይዘውና በድንገት ይጮኻል፤ ጥሎም በአፉ አረፋ እያስደፈቀ ያንፈራግጠዋል፤ ጉዳት ካደረሰበትም በኋላ በስንት መከራ ይለቀዋል። 40 ደቀ መዛሙርትህ እንዲያስወጡት ለመንኳቸው፤ እነሱ ግን አልቻሉም።” 41 ኢየሱስም መልሶ “እምነት የለሽና ጠማማ ትውልድ ሆይ፣+ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር መቆየትና እናንተን መታገሥ ሊኖርብኝ ነው? እስቲ ልጅህን ወደዚህ አምጣው” አለ።+ 42 ሆኖም ወደ እሱ እየመጣ ሳለ ጋኔኑ መሬት ላይ ጥሎ በኃይል አንፈራገጠው። ይሁንና ኢየሱስ ርኩሱን መንፈስ ገሠጸውና ልጁን ፈወሰው፤ ከዚያም ለአባቱ መልሶ ሰጠው።
-