12 ከዚያም ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦
2 “በእርግጥ አዋቂዎች እናንተ ናችኋ!
ጥበብም ከእናንተ ጋር ትሞታለቻ!
3 እኔም እኮ ማስተዋል አለኝ።
ከእናንተ አላንስም።
እነዚህን ነገሮች የማያውቅ ማን ነው?
4 ወደ አምላክ ተጣርቼ መልስ የምጠብቅ፣+
የባልንጀሮቼ መሳለቂያ ሆኛለሁ።+
ጻድቅና ነቀፋ የሌለበት ሰው፣ የሰዎች መሳለቂያ ነው።
5 የደላው ሰው ‘መከራ የሚደርሰው
እግራቸው በሚብረከረክ ሰዎች ላይ ብቻ ነው’ ብሎ በማሰብ መከራን ይንቃል።
6 የዘራፊዎች ድንኳን ሰላም አለው፤+
አምላክን የሚያስቆጡ ሰዎችም፣
አምላካቸውን በእጃቸው እንደያዙ ሰዎች የደህንነት ስሜት ይሰማቸዋል።+
7 ይሁን እንጂ እስቲ እንስሳትን ጠይቅ፤ እነሱም ያስተምሩሃል፤
በሰማያት የሚበርሩ ወፎችንም ጠይቅ፤ እነሱም ይነግሩሃል።
8 ወይም በምድር ላይ ትኩረትህን አድርግ፤ እሷም ታስተምርሃለች፤
የባሕር ዓሣም ያሳውቅሃል።
9 የይሖዋ እጅ ይህን ማድረጉን፣
ከእነዚህ ሁሉ መካከል የማያውቅ ማን ነው?
10 የሕያው ነገር ሁሉ ሕይወት፣
የሰውም ሁሉ መንፈስ በእሱ እጅ ነው።+
11 ምላስ የምግብን ጣዕም እንደሚለይ ሁሉ፣
ጆሮስ ቃላትን አያመዛዝንም?+
12 በዕድሜ በገፉት መካከል ጥበብ፣
ከረጅም ዕድሜስ ጋር ማስተዋል አይገኝም?+
13 በእሱ ዘንድ ጥበብና ኃይል አለ፤+
ምክርና ማስተዋልም አለው።+
14 እሱ ያፈረሰውን ነገር መልሶ መገንባት አይቻልም፤+
እሱ የዘጋውን ማንም ሰው ሊከፍት አይችልም።
15 ውኃዎችን ሲከለክል ሁሉም ነገር ይደርቃል፤+
ሲልካቸውም ምድርን ያጥለቀልቃሉ።+
16 ብርታትና ጥበብ በእሱ ዘንድ ናቸው፤+
መንገድ የሚስተውም ሆነ የሚያስተው የእሱ ናቸው፤
17 አማካሪዎችን ባዶ እግራቸውን ያስኬዳቸዋል፤
ፈራጆችንም ያሞኛቸዋል።+
18 ነገሥታት ያሰሩትን ይፈታል፤+
በወገባቸውም ዙሪያ መታጠቂያ ያስራል።
19 ካህናትን ባዶ እግራቸውን ያስኬዳቸዋል፤+
በሥልጣን ላይ ተደላድለው የተቀመጡትንም ይገለብጣል፤+
20 የታመኑ አማካሪዎችን የሚሉትን ነገር ያሳጣቸዋል፤
ሽማግሌዎችንም ማስተዋል ይነሳል፤
21 በታላላቅ ሰዎች ላይ የውርደት መዓት ያዘንባል፤+
ብርቱዎችንም ደካማ ያደርጋል፤
22 ጥልቅ የሆኑ ነገሮችን ከጨለማ ውስጥ ይገልጣል፤+
በድቅድቅ ጨለማ ላይ ብርሃን ይፈነጥቃል፤
23 ያጠፋቸው ዘንድ ብሔራትን ታላቅ ያደርጋል፤
ወደ ግዞት ይወስዳቸውም ዘንድ ብሔራትን እንዲስፋፉ ያደርጋቸዋል።
24 የሕዝቡን መሪዎች ማስተዋል ይነሳል፤
መንገድ በሌለበት ጠፍ መሬትም እንዲቅበዘበዙ ያደርጋል።+
25 ብርሃን በሌለበት ጨለማ፣ በዳበሳ ይሄዳሉ፤+
እንደሰከሩ ሰዎች እንዲዳክሩ ያደርጋቸዋል።+