10 ጉዳት የሚያስከትሉ ሥርዓቶችን የሚያወጡ፣+
ሁልጊዜ ጨቋኝ ድንጋጌዎችን የሚያረቁ ወዮላቸው!
2 የድሆችን አቤቱታ ላለመስማት፣
በሕዝቤም መካከል የሚገኙትን ምስኪኖች ፍትሕ ለመንፈግ ሕግ የሚያወጡ ወዮላቸው!+
መበለቶችን ይበዘብዛሉ፤
አባት የሌላቸውንም ልጆች ይዘርፋሉ።+
3 በምትመረመሩበት ቀን፣+
ጥፋትም ከሩቅ በሚመጣበት ጊዜ ምን ይውጣችሁ ይሆን?+
እርዳታ ለማግኘት ወደ ማን ትሸሻላችሁ?+
ሀብታችሁንስ የት ትተዉት ይሆን?
4 በእስረኞች መካከል ተኮራምታችሁ ከመቀመጥና
በሞቱ ሰዎች መካከል ከመውደቅ በስተቀር የምታተርፉት ነገር የለም።
ከዚህ ሁሉ የተነሳ ቁጣው አልተመለሰም፤
ይልቁንም እጁ ለመምታት ገና እንደተዘረጋ ነው።+
5 “የቁጣዬ በትር የሆነውንና+
ውግዘቴን የምገልጽበትን ዱላ በእጁ የያዘውን
አሦራዊ+ ተመልከት!
6 ከሃዲ በሆነው ብሔር ላይ፣
እጅግ ባስቆጣኝም ሕዝብ ላይ እልከዋለሁ፤+
ብዙ ምርኮ እንዲወስድ፣ ብዙ ሀብት እንዲዘርፍና
ሕዝቡን በጎዳናዎች ላይ እንዳለ ጭቃ እንዲረጋግጥ አዘዋለሁ።+
7 እሱ ግን እንዲህ ያለ ዝንባሌ አይኖረውም፤
ልቡም እንዲህ ለማድረግ አያቅድም፤
የልቡ ፍላጎት መደምሰስና
ጥቂት ሳይሆን ብዙ ብሔራትን ማጥፋት ነውና።
8 እሱ እንዲህ ይላል፦
‘አለቆች ሆነው የሚያገለግሉኝ ሁሉ ነገሥታት አይደሉም?+
9 ካልኖ+ እንደ ካርከሚሽ+ አይደለችም?
ሃማት+ እንደ አርጳድ+ አይደለችም?
ሰማርያስ+ እንደ ደማስቆ+ አይደለችም?
10 እጄ በኢየሩሳሌምና በሰማርያ ካሉት ይበልጥ በርካታ የተቀረጹ ምስሎች ያሏቸውንና
ከንቱ አማልክት የሚያመልኩትን መንግሥታት ይዟል!+
11 በሰማርያና ከንቱ በሆኑት አማልክቷ ላይ እንዳደረግኩት ሁሉ፣
በኢየሩሳሌምና በጣዖቶቿስ ላይ እንዲሁ አላደርግም?’+
12 “ይሖዋ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም የሚያከናውነውን ሥራ ሁሉ ሲያጠናቅቅ በእብሪተኛ ልቡ፣ በኩራቱና በትዕቢተኛ ዓይኑ የተነሳ የአሦርን ንጉሥ ይቀጣዋል።+ 13 እሱ እንዲህ ይላልና፦
‘በእጄ ብርታትና በጥበቤ
ይህን አደርጋለሁ፤ እኔ ጥበበኛ ነኝና።
የሕዝቦችን ድንበር አስወግዳለሁ፤+
ሀብታቸውንም እዘርፋለሁ፤+
እንደ ኃያል ሰውም ነዋሪዎቹን በቁጥጥር ሥር አውላለሁ።+
14 ሰው እጁን ወደ ወፍ ጎጆ እንደሚሰድ፣
እጄ የሕዝቦችን ሀብት ይይዛል፤
አንድ ሰው የተተዉ እንቁላሎችን እንደሚሰበስብ
እኔም መላውን ምድር እሰበስባለሁ!
ክንፎቹን የሚያራግብ ወይም አፉን የሚከፍት አሊያም የሚጮኽ አይኖርም።’”
15 መጥረቢያ፣ በሚቆርጥበት ሰው ላይ ይኩራራል?
መጋዝ፣ በሚገዘግዝበት ሰው ላይ ራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል?
በትር፣+ የሚያነሳውን ሰው ወዲያና ወዲህ ማንቀሳቀስ ይችላል?
ወይስ ዱላ፣ ከእንጨት ያልተሠራውን ሰው ወደ ላይ ከፍ ማድረግ ይችላል?
16 ስለዚህ እውነተኛው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ
በወፈሩት ሰዎች ላይ ክሳትን ይሰዳል፤+
ከክብሩም በታች እንደ እሳት ነበልባል የሚንቦገቦግ እሳት ያነዳል።+
17 የእስራኤል ብርሃን+ እንደ እሳት፣+
ቅዱስ አምላኩም እንደ ነበልባል ይሆናል፤
አረሙንና ቁጥቋጦውን በአንድ ቀን ያጋየዋል፤ ደግሞም ይበላዋል።
18 አምላክ የደኑንና የፍራፍሬ እርሻውን ክብር ፈጽሞ ያጠፋል፤
ክብሩም እንደታመመ ሰው እየመነመነ ይሄዳል።+
19 በደኑ ውስጥ የሚተርፉት ዛፎች
ጥቂት ከመሆናቸው የተነሳ አንድ ትንሽ ልጅ ቆጥሮ ሊመዘግባቸው ይችላል።
20 በዚያ ቀን ከእስራኤላውያን መካከል የሚቀሩት፣
ከያዕቆብም ቤት የሚተርፉት ሰዎች
ከእንግዲህ ወዲህ፣ በመታቸው ላይ ፈጽሞ አይታመኑም፤+
ከዚህ ይልቅ የእስራኤል ቅዱስ በሆነው በይሖዋ ላይ
በታማኝነት ይደገፋሉ።
21 ጥቂት ቀሪዎች ይኸውም ከያዕቆብ ቤት የሚተርፉት ሰዎች
ወደ ኃያሉ አምላክ ይመለሳሉ።+
22 እስራኤል ሆይ፣
ሕዝብህ እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆንም
ከእነሱ መካከል ጥቂት ቀሪዎች ይመለሳሉ።+
23 አዎ፣ ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ የወሰነው ጥፋት፣
በመላ ምድሪቱ ላይ ይፈጸማል።+
24 ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በጽዮን የምትኖር ሕዝቤ ሆይ፣ በበትር+ ይመታህና ግብፅ እንዳደረገብህ+ ዱላውን በአንተ ላይ ያነሳ የነበረውን አሦርን አትፍራ። 25 ከጥቂት ጊዜ በኋላ ውግዘቱ ያበቃልና፤ ቁጣዬም እስኪጠፉ ድረስ በእነሱ ላይ ይነድዳል።+ 26 የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በኦሬብ ዓለት ምድያምን ድል እንዳደረገ+ ሁሉ ጅራፉን በእሱ ላይ ያወዛውዛል።+ በትሩም በባሕሩ ላይ ይሆናል፤ በግብፅ ላይ እንዳደረገውም በትሩን ያነሳዋል።+
27 “በዚያ ቀን ሸክሙ ከትከሻህ ላይ፣+
ቀንበሩም ከአንገትህ ላይ ይወርዳል፤+
ከዘይቱም የተነሳ ቀንበሩ ይሰበራል።”+
28 በአያት+ ላይ መጥቷል፤
ሚግሮንን አቋርጦ አልፏል፤
በሚክማሽ+ ጓዙን ያስቀምጣል።
29 መልካውን ተሻግረዋል፤
በጌባ+ ያድራሉ፤
ራማ ራደች፤ የሳኦል ከተማ ጊብዓ+ ሸሽታለች።+
30 የጋሊም ሴት ልጅ ሆይ፣ እሪታሽን አቅልጪው!
ላይሻ ሆይ፣ አዳምጪ!
ምስኪኗ አናቶት+ ሆይ፣ ጩኺ!
31 ማድመና ሸሽታለች።
የጌቢም ነዋሪዎች መሸሸጊያ ፈለጉ።
32 በዚሁ ቀን በኖብ+ ያርፋል።
በጽዮን ሴት ልጅ ተራራ፣
በኢየሩሳሌም ኮረብታ ላይ እጁን በዛቻ ያወዛውዛል።
33 እነሆ፣ እውነተኛው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ
ቅርንጫፎችን በታላቅ ኃይል እየቆራረጠ ይጥላል፤+
ረጃጅሞቹ ዛፎች ይገነደሳሉ፤
ከፍ ያሉትም ይዋረዳሉ።
34 በደን ውስጥ ያለውን ጥሻ በብረት መሣሪያ ይቆራርጣል፤
ሊባኖስም በኃያሉ እጅ ይወድቃል።