በልጅነታቸው ሥነ ልቦናዊ ችግር የደረሰባቸውን ሰዎች ማጽናናት
በጉባኤው ውስጥ ከፍተኛ አክብሮትን ያተረፉና ተግባቢ የሆኑ ወጣት ባልና ሚስት ናቸው። ሆኖም ባልየው እቤት መጥቶ ሊያነጋግራቸው ይችል እንደሆነ ሽማግሌውን ሲጠይቀው የድምፁ ቃና በጣም እንደተጨነቀና አፋጣኝ እርዳታ እንደሚሻ ያሳይ ነበር፤ እሷም ብትሆን ዓይኖቿ በእንባ ተሞልተው ነበር። በተደጋጋሚ ጊዜያት ወደ አእምሮዋ እየመጣ በሚረብሻት ከባድ የመንፈስ ጭንቀትና ራስን የመጥላት ስሜት ስትሰቃይ የነበረ ከመሆኑም በላይ ራሷን ለመግደል እስከ ማሰብ ደርሳ ነበር። በልጅነቷ በጾታ ተነውራለች። የይሖዋ ድርጅት ምሥጋና ይግባውና እንዲህ ዓይነት ወንጀል የተፈጸመባቸውን ሰዎች እንዴት መርዳት እንደሚቻል የሚጠቁሙ መመሪያዎች የሰጠ በመሆኑ ሽማግሌው ይህን ጉዳይ በተመለከተ ማኅበሩ ለሽማግሌዎች የጻፋቸውን ደብዳቤዎች እንዲሁም በጥቅምት 8, 1991 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት ላይ የወጡትን ርዕሶችና በጥቅምት 1, 1983 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን ርዕስ አጠና። ከእነዚህ ጽሑፎች ላይ የተወሰዱ ጥቂት ጠቃሚ ነጥቦች እነሆ:-
1. አዳምጡ፣ አዳምጡ፣ አዳምጡ። አንድ ልጅ ወድቆ ጉልበቱ ቢቆስል መጀመሪያ የሚታየው ነገር እንዲያባብሉት ወደ እናቱ ወይም ወደ አባቱ መሮጥ ነው። በጾታ የተነወረ ልጅ ግን ይህ ምርጫ አልነበረው ይሆናል። ስለዚህ ትልቅ ሰው ከሆነም በኋላ ይኸው ነገር ያስፈልገው ይሆናል—ራሱን በእሱ ቦታ አስቀምጦ ለሚያዳምጠውና ለሚያጽናናው ሰው ችግሩን አውጥቶ መናገር ይፈልጋል። (ከኢዮብ 10:1 እና 32:20 ጋር አወዳድር።) ሽማግሌው ከላይ የተጠቀሱትን ባልና ሚስት ለማነጋገር በሄደበት ጊዜ ጥቂት ብቻ መናገሩና ለብዙ ሰዓት ማዳመጡ ባልየውን በጣም አስገረመው። ችግሮችን ከተግባራዊ ሁኔታ አንጻር የሚመለከተውና ለመርዳት ዝግጁ የሆነው ይህ ባል ትክክል መስሎ ያልታየውን ስሜት ለማረም በመሞከር ስሜታዊ ችግርን፣ እውነታን ቁልጭ አድርጎ በማስቀመጥ ለመፍታት እየሞከረ እንደነበረ ተረዳ። ሚስቱ ከተግባራዊ መልስ ይበልጥ የሚያስፈልጋት ራሱን በእሷ ቦታ አስቀምጦ ችግሯን የሚረዳላትና ስሜቷን የሚካፈላት ሰው እንደሆነ ተገነዘበ። (ከሮሜ 12:15 ጋር አወዳድር።) እንደዚያ እንዲሰማት ያደረጋት በቂ ምክንያት መኖሩን በጥሞና አዳምጦ የሚረዳላት ሰው ያስፈልጋት ነበር።
2. ያደረባቸው አስተሳሰብ የተሳሳተ እንደሆነ እንዲገነዘቡ እርዷቸው። ልጆች በጾታ በሚነወሩበት ጊዜ እንደረከሱ፣ የሚወዳቸው እንደሌለና ምንም ዋጋ እንደሌላቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ልክ እንደ ሐሰት የሃይማኖት መሠረተ ትምህርቶች ከይሖዋ ጋር ጤናማ የሆነ ዝምድና እንዳይኖር እንቅፋት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ይህ የተሳሳተ አስተሳሰብ እንደሆነና ይህን አስወግደው ትክክለኛ አመለካከት እንዲይዙ ቀስ ብላችሁና ደጋግማችሁ በመንገር በትዕግሥት እርዷቸው። ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሳችሁ አስረዷቸው። (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5) ለምሳሌ ያህል እንዲህ ልትሏቸው ትችላላችሁ:- “እንደረከስክ ሆኖ እንደሚሰማህ ይገባኛል። ይሖዋ ግን ስለ አንተ ምን የሚሰማው ይመስልሃል? ልጁ እንዲሞትና ቤዛ እንዲሆንልህ ያደረገው ቢወድህ አይደለም እንዴ? [ዮሐንስ 3:16] ይህ የማስነወር ድርጊት በይሖዋ ዓይን ርኩስ የሚያደርገው አንተን ነው ወይስ ድርጊቱን የፈጸመውን ሰው? ኢየሱስ ‘ከሰው የሚወጡት ሰውን የሚያረክሱ ናቸው እንጂ ከሰው ውጭ የሚገባውስ ሊያረክሰው የሚችል ምንም የለም’ ብሎ እንደተናገረ አስታውስ። [ማርቆስ 7:15] በዚያን ጊዜ ያንን የማስነወር ወንጀል የመፈጸም ሐሳብ የመነጨው ከአንተ ከትንሹ ልጅ ነው ወይስ ድርጊቱን ከፈጸመው ሰው?”
3. አጽናኗቸው። እያንዳንዱ ሰው ከሌላው የተለየ ነው፤ ስለዚህ ጳውሎስ “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው” ሲል የሰጠው ምክር እንደየሁኔታው በተለያየ መንገድ የሚሠራ ነው። (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW) ይሁን እንጂ ነገሮችን አቅልሎ መናገር ብዙውን ጊዜ አያጽናናም። ለምሳሌ ያህል የማስነወር ድርጊት የተፈጸመበትን ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ እንዲያነብ፣ በስብከቱ ሥራ ይበልጥ እንዲሳተፍ ወይም ደግሞ ‘ሸክሙን በይሖዋ ላይ እንዲጥል ብቻ’ ብንመክረው እንዲህ ዓይነቱ ሐሳብ አንዳንድ ጊዜ ሊጠቅም ቢችልም ብዙውን ጊዜ ውጤት ላያስገኝ ይችላል። (መዝሙር 55:22፤ ከገላትያ 6:2 ጋር አወዳድር።) ብዙዎቹ የተቻላቸውን ያህል እነዚህን ነገሮች ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ይበልጥ ለመሥራት ባለመቻላቸው ራሳቸውን ክፉኛ በመውቀስ ላይ ያሉ ናቸው።—ከ1 ዮሐንስ 3:19, 20 ጋር አወዳድር።
በተመሳሳይም የተነወሩ ሰዎችን ያለፈውን ነገር እንዲሁ እንዲረሱት መንገሩ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። እንደዚያ ማድረግ ቢችሉማ ኖሮ ቀድሞውኑ ያደርጉት ነበር፤ እንዲህ ዓይነት ቀላል መፍትሔ ለማግኘትም እርዳታ አያሻቸውም ነበር።a የደረሰባቸው ሥነ ልቦናዊ ችግር በጣም ከባድ መሆኑን አትዘንጋ። ሁኔታውን ለማነጻጸር ያህል አንድ ሰው የመኪና አደጋ ደርሶበት እያቃሰተ ሳለ ደረስክ እንበል። እንዲሁ ብቻ ‘ሥቃዩን እርሳው፤ ስለ እሱ አታስብ’ ትለዋለህ? ሌላ እርዳታ እንደሚያስፈልገው የታወቀ ነው።
የምትናገረው ነገር የሚያጽናናና የሚጠቅም መሆን አለመሆኑን ከተጠራጠርክ በመንፈስ ጭንቀት እየተሰቃየ ያለውን ግለሰብ ለምን አትጠይቀውም? እውነተኛና ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆነም ምክር እንኳን በትክክለኛው ጊዜ የሚሰጥና ለሁኔታው ተስማሚ መሆን አለበት።—ከምሳሌ 25:11 ጋር አወዳድር።
ሽማግሌው ወንድም ለጥቂት ጊዜያት እየተመላለሰ ካነጋገራቸው በኋላ ከላይ የተጠቀሰችው እህት አመለካከቷ እየተሻሻለ መሄድ ጀመረ፤ ባሏም በችግሯ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ሊረዳት የሚችልበትን ብቃት ሊያገኝ ችሏል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁለቱም ተመሳሳይ ሥነ ልቦናዊ ችግር የደረሰባቸውን ሌሎች ሰዎች ማጽናናት ችለዋል። “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” የሆነው ይሖዋ በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት በቃሉና በሕዝቡ ተጠቅሞ ‘የተሰበሩትን ሲጠግን’ ማየቱ ምንኛ እምነትን የሚያጠነክር ነው።—2 ቆሮንቶስ 1:3፤ ኢሳይያስ 61:1
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እርግጥ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ‘በኋላቸው ያለውን እንዲረሱ’ ምክር ሰጥቷል። ሆኖም ጳውሎስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው ቀደም ሲል ስለነበረው ክብርና ዓለማዊ ስኬት ነው፤ በኋላ ግን ይህን “እንደ ጉድፍ” ቆጥሮታል። ቀደም ሲል የደረሰበትንና በግልጽ የዘረዘረውን መከራ አስመልክቶ መናገሩ አልነበረም።—ፊልጵስዩስ 3:4-6, 8, 13፤ ከ2 ቆሮንቶስ 11:23-27 ጋር አወዳድር።