በቤት ውስጥ እንዳይከሰት መከላከል
ሞኒክን ማስነወር የጀመረው ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለች ነው። በመጀመሪያ ልብሷን ስታወልቅ እየተደበቀ ያያት ነበር፤ በኋላ ግን ማታ ማታ ወደ ክፍሏ እየመጣ የጾታ ብልቷን መነካካት ጀመረ። እንዲተው ስትነግረው በጣም ይቆጣታል። እንዲያውም አንድ ጊዜ በመዶሻ ከመታት በኋላ ከፎቅ ደረጃ ላይ አንከባልሏታል። “የሚያምነኝ ሰው አልነበረም፤” ስትል ሞኒክ ወደ ኋላ መለስ ብላ ታስታውሳለች፤ እናቷም እንኳ አታምናትም ነበር። ሞኒክን ያስነውር የነበረው እንጀራ አባቷ ነበር።
በልጆች ላይ ትልቅ ሥጋት የሚፈጥረው አድብቶ የሚመጣ ባይተዋር ሰው አይደለም። የቤተሰቡ አባል እንጂ። ልጆችን በጾታ የማስነወር ወንጀል በአብዛኛው የሚፈጸመው እዚያው ቤት ውስጥ ባለ ሰው ነው። እንግዲያው እቤት ውስጥ ልጆችን የማስነወር ድርጊት እንዳይከሰት መከላከል የሚቻለው እንዴት ነው?
የታሪክ ምሁሩ ዶክተር ሳንደር ጄ ብሪነር ስላውተር ኦቭ ዚ ኢኖሰንትስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ በአምስት የጥንት ኅብረተሰቦች ውስጥ ማለትም በግብጽ፣ በቻይና፣ በግሪክ፣ በሮምና በእስራኤል ውስጥ ስለተፈጸመው ልጆችን የማስነወር ድርጊት የሚገልጸውን ማስረጃ ተንትነዋል። በመጨረሻም ምንም እንኳ ልጆችን በጾታ የማስነወር ድርጊት በእስራኤል ውስጥም የነበረ ቢሆንም ከሌሎቹ አራት አገሮች ሕዝቦች ጋር ሲወዳደር በጣም አነስተኛ ነበር ሲሉ ደምድመዋል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? እስራኤላውያን ከሌሎች የጎረቤት አገር ሕዝቦች በተለየ ሁኔታ ሴቶችንና ልጆችን ማክበርን ተምረው ነበር፤ ከቅዱሳን ጽሑፎች ያገኙት የላቀ እውቀት ነበራቸው። እስራኤላውያን የቤተሰብ ኑሮን አስመልክቶ የተሰጠውን መለኮታዊ ሕግ በሥራ ባዋሉ ጊዜ ልጆችን በጾታ የማስነወርን ድርጊት መከላከል ችለው ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉት ቤተሰቦች እነዚህ ንጹህና ውጤታማ የሆኑ መሥፈርቶች ከምንጊዜውም በበለጠ ያስፈልጓቸዋል።
የሥነ ምግባር ሕጎች
ቤተሰብህ የመጽሐፍ ቅዱስን ሕግ ይሠራበታልን? ለምሳሌ ያህል ዘሌዋውያን 18:6 እንዲህ ይላል:- “ከእናንተም ማንም ሰው ኃፍረተ ሥጋውን ይገልጥ ዘንድ ወደ ዘመዱ ሁሉ አይቅረብ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” በተመሳሳይም ዛሬ የክርስቲያን ጉባኤ ማንኛውንም ዓይነት በጾታ የማስነወር ድርጊት የሚያግድ ጠንካራ ሕግ አለው። አንድን ልጅ በጾታ የሚያስነውር ማንኛውም ሰው ከጉባኤው ሊወገድ ይችላል።a—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10
ሁሉም ቤተሰቦች እንዲህ ዓይነቶቹን ሕጎች ማወቅና አንድ ላይ ሆነው መመርመር አለባቸው። ዘዳግም 6:6, 7 እንዲህ ሲል አጥብቆ ያሳስባል:- “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው።” እነዚህን ሕጎች ለልጆች ማስተማር ማለት እንዲሁ አልፎ አልፎ ትምህርት መስጠት ማለት ብቻ አይደለም። በቋሚነት የሚካሄድ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ የሚደረግበት ውይይት ያስፈልጋል። እናትና አባት፣ ሁለቱም አምላክ በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚደረግን የጾታ ግንኙነት አስመልክቶ ያወጣቸውን ሕጎችና ይሖዋ በፍቅር ተገፋፍቶ እነዚህን ሕጎች ያወጣበትን ምክንያት በየጊዜው ለልጆቻቸው ሊገልጹላቸው ይገባል።
በተጨማሪም በጾታ ጉዳዮች ረገድ ማንም ሰው፣ ሌላው ቀርቶ የቅርብ ዘመዶች እንኳን ሊያልፉት የማይገባ ወሰን እንዳለ ልጆችን ለማስገንዘብ የዳዊት ልጆች ስለሆኑት ስለ ትዕማርና አምኖን የሚናገረውን ታሪክ የመሰሉ ታሪኮችን ልትጠቀሙ ትችላላችሁ።—ዘፍጥረት 9:20-29፤ 2 ሳሙኤል 13:10-16
ለእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች አክብሮት እንዳለን በአኗኗራችንም ተግባራዊ በሆነ መንገድ ማሳየት እንችላለን። በሩቅ ምሥራቅ በምትገኝ አንዲት አገር የተካሄደ ጥናት እንደሚያሳየው ብዙውን ጊዜ በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የጾታ ግንኙነት የሚፈጸመው የኢኮኖሚው ሁኔታ የማያስገድድ ሆኖ ሳለ ወላጆችና ልጆች አንድ ላይ በሚተኙባቸው ቤተሰቦች ውስጥ ነው። በተመሳሳይም ተቃራኒ ጾታ ያላቸው ልጆች ዕድሜያቸው ከፍ እያለ ሲሄድ በተቻለ መጠን አንድ አልጋ ላይ ወይም አንድ ክፍል ውስጥ ባይተኙ ጥሩ ነው። በጣም የተጨናነቀ የኑሮ ሁኔታ ባለባቸው አካባቢዎችም እንኳ ወላጆች እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የት መተኛት እንዳለበት በሚወስኑበት ጊዜ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም ይኖርባቸዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ስካር ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ድርጊት ወደ መፈጸም ሊመራ እንደሚችል በመጠቆም ከዚህ ልማድ እንድንርቅ ያዛል። (ምሳሌ 23:29-33) አንድ ጥናት እንደገለጸው ከሆነ በቅርብ ዘመዳሞች መካከል ከተፈጸመው የጾታ ግንኙነት መካከል 60 ወይም 70 በመቶ ገደማ የሚሆኑትን ልጆች ያስነወሩት ወላጆች ድርጊቱን መፈጸም በጀመሩበት ወቅት ሰክረው የነበሩ ናቸው።
አፍቃሪ የቤተሰብ ራስ
በጾታ የማስነወር ወንጀል በብዛት የሚፈጸመው ጨቋኝ የሆኑ ባሎች ባሉባቸው ቤተሰቦች ውስጥ እንደሆነ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች መገንዘብ ችለዋል። ሴቶች የተፈጠሩት የወንዶችን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ ነው የሚለው በብዙዎች ዘንድ የሚታመንበት አመለካከት ቅዱስ ጽሑፋዊ ተቀባይነት የለውም። አንዳንድ ወንዶች ሴቶች ልጆቻቸውን የሚያስነውሩት ከሚስታቸው ማግኘት ያልቻሉትን ነገር ለማግኘት ሲሉ እንደሆነ በመግለጽ ይህን ክርስቲያናዊ ያልሆነ አስተሳሰብ ምክንያት አድርገው ለማቅረብ ይሞክራሉ። እንዲህ ዓይነቱ ጭቆና በዚህ ሁኔታ ሥር የሚገኙ ሴቶች የስሜት ሚዛናቸውን እንዳይጠብቁ ሊያደርጋቸው ይችላል። እንዲያውም ብዙዎቹ ሴቶች የራሳቸውን ልጆች እንዲጠብቁ የሚገፋፋቸው ተፈጥሯዊ ስሜት ይጠፋል። (ከመክብብ 7:7 ጋር አወዳድር።) በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ጥናት እንዳመለከተው የሥራ ሱስ ያለባቸው አባቶች በአብዛኛው ቤት ውስጥ በማይኖሩበት ጊዜ በእናትና በወንድ ልጅ መካከል የሚፈጸም በጾታ የማስነወር ወንጀል እየተስፋፋ ሄዷል።
የአንተስ ቤተሰብ እንዴት ነው? ባል እንደ መሆንህ መጠን የራስነት ድርሻህን በሚገባ ትወጣለህ ወይስ ይህን ድርሻህን ለሚስትህ ትተወዋለህ? (1 ቆሮንቶስ 11:3) ሚስትህን በፍቅር፣ በአክብሮትና በእንክብካቤ ትይዛታለህ? (ኤፌሶን 5:25፤ 1 ጴጥሮስ 3:7) የምትሰጠውን ሐሳብ ትኩረት ሰጥተህ በቁም ነገር ትመለከተዋለህ? (ዘፍጥረት 21:12፤ ምሳሌ 31:26, 28) ልጆችህንስ? ውድ እንደሆኑ አድርገህ ትመለከታቸዋለህ? (መዝሙር 127:3) ወይስ በቀላሉ አግባብ ያልሆነ ነገር ሊፈጸምባቸው የሚችሉ ሸክሞች እንደሆኑ አድርገህ ትቆጥራቸዋለህ? (ከ2 ቆሮንቶስ 12:14 ጋር አወዳድር።) በቤተሰብ ውስጥ ያሉትን የኃላፊነት ድርሻዎች በተመለከተ የተዛቡና ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ አመለካከቶች ከቤትህ እንዲወገዱ አድርግ፤ በዚህ መንገድ ቤተሰብህ በጾታ የማስነወርን ወንጀል ይበልጥ መከላከል እንዲችል ታደርጋለህ።
ስሜታቸው የሚጠበቅበት ቦታ
ሳንዲ (ስሟን ቀይረነዋል) የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች:- “የቤተሰቤ ሁኔታ ራሱ ለወሲባዊ ጥቃት የተመቻቸ ነበር። የቀዘቀዘ መንፈስ የሰፈነበትና እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ራሱን ከሌላው አግልሎ የሚኖርበት ቤት ነበር።” ራስን ማግለል፣ ግትር መሆንና ከሚገባው በላይ ምሥጢራዊ መሆን ጤናማና ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ አመለካከቶች ከመሆናቸውም በላይ አስነዋሪ ድርጊት የሚፈጸምበት ቤተሰብ መለያ ምልክቶች ናቸው። (ከ2 ሳሙኤል 12:12፤ ከምሳሌ 18:1 እና ከፊልጵስዩስ 4:5 ጋር አወዳድር።) የልጆች ስሜት ሊጠበቅበት የሚችል መንፈስ በቤትህ ውስጥ እንዲሰፍን አድርግ። አንድ ቤት፣ ልጆች በራስ የመተማመን መንፈሳቸው የሚገነባበትና የልባቸውን አውጥተው በነፃነት መናገር የሚችሉበት ቦታ መሆን አለበት።
በተጨማሪም ልጆችን በማቀፍ፣ በመደባበስ፣ እጃቸውን በመያዝና በማጫወት አካላዊ የፍቅር መግለጫዎች ማሳየት በጣም አስፈላጊ ነው። በጾታ ለማስነወር ድርጊት ሊያጋልጡ ይችላሉ በሚል አስተሳሰብ እነዚህን የፍቅር መግለጫዎች ማስቀረት የለባችሁም። ግልጽና ሞቅ ያለ የፍቅርና የምስጋና ቃል በመናገር ልጆቻችሁ ዋጋማ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ አድርጉ። ሳንዲ እንዲህ ስትል ወደ ኋላ መለስ ብላ ታስታውሳለች:- “እማዬ ማንኛውንም ሰው ማመስገን ስህተት እንደሆነ አድርጋ ታስብ ነበር። ሰውን ማመስገን ጉረኛ እንዲሆን ያደርገዋል የሚል አመለካከት ነበራት።” ሳንዲ ለማንም ትንፍሽ ሳትል ቢያንስ ቢያንስ ለአሥር ዓመታት ያህል በጾታ ስትነወር ቆይታለች። በሌሎች ዘንድ የሚወደዱ መሆቸውንና ዋጋማነታቸውን የሚጠራጠሩ ልጆች በጾታ የማስነወር ወንጀል የሚፈጽመው ሰው ከፍ ከፍ ሲያደርጋቸው፣ “እንደሚወዳቸው” ሲገልጽላቸው ወይም ደግሞ እሱ ለማድረግ በፈለገው ነገር የማይስማሙ ከሆነ እንደሚጠላቸው ሲዝትባቸው በቀላሉ ሊሸነፉለት ይችላሉ።
ከ40 ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንዶች ልጆችን በጾታ ያስነወረ አንድ ሰው “ከሁሉም ይበልጥ” ለዚህ ጥቃት የሚጋለጡት እንደ እሱ ያለ ጓደኛ የማግኘት ስሜታዊ ፍላጎት ያላቸው ልጆች እንደሆኑ ተናግሯል። ልጃችሁ እንዲህ ዓይነት ስሜታዊ ፍላጎት እንዲያድርበት አታድርጉ።
በጾታ የማስነወርን ዑደት መግታት
ኢዮብ ከባድ ፈተና ውስጥ ወድቆ በነበረበት ጊዜ “ነፍሴ ሕይወቴን ሰለቸቻት፤ የኀዘን እንጉርጉሮዬን እለቅቀዋለሁ፤ በነፍሴም ምሬት እናገራለሁ” ሲል ተናግሮ ነበር። (ኢዮብ 10:1) በተመሳሳይም ብዙ ወላጆች ራሳቸውን በመርዳት ልጆቻቸውን መርዳት እንደሚችሉ ተገንዝበዋል። በቅርቡ ዘ ሃርቫርድ ሜንታል ኸልዝ ሌተር እንደሚከተለው ብሎ ነበር:- “ወንዶች የደረሰባቸውን ሥቃይ እንዳይናገሩ የሚያደርገው ጠንካራ ማኅበረሰባዊ እገዳ በጾታ የማስነወር ዑደት እንዲቀጥል አስተዋጽኦ ያደረገ ይመስላል።” በልጅነታቸው በጾታ መነወራቸውን ትንፍሽ ሳይሉ በሆዳቸው ይዘው የቀሩ ወንዶች ውሎ አድሮ እነሱ ራሳቸው በጾታ የማስነወር ድርጊት ሊፈጽሙ ይችላሉ። ዘ ሴፍ ቻይልድ ቡክ የተባለው መጽሐፍ በልጆች ላይ ወሲባዊ ጥቃት የሚፈጽሙት አብዛኞቹ ሰዎች፣ ራሳቸው በልጅነታቸው በጾታ የተነወሩና ከደረሰባቸው ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ማገገም የሚችሉበት እርዳታ ያላገኙ ናቸው ብሏል። የሕሊና ሥቃያቸውንና ንዴታቸውን የሚገልጹት ሌሎች ልጆችን በማስነወር ነው።b—በተጨማሪም ኢዮብ 7:11ንና 32:20ን ተመልከት።
እናቶች ቀደም ሲል በልጅነታቸው መነወራቸው ያስከተለባቸውን ችግር እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ በማያውቁበት ጊዜ የእነሱም ልጆች ለዚህ አደጋ ይበልጥ የተጋለጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በልጅነታቸው በጾታ የተነወሩ ሴቶች ብዙውን ጊዜ ልጆችን የሚያስነውሩ ወንዶችን እንደሚያገቡ ተመራማሪዎች ሪፖርት አድርገዋል። ከዚህም በላይ አንዲት ሴት በልጅነቷ መነወሯ ያስከተለባትን ችግር እንዴት መቋቋም እንደምትችል ካላወቀች ይህን በጾታ የማስነወር ድርጊት በተመለከተ ከልጆቿ ጋር መወያየት ሊከብዳት እንደሚችል የታወቀ ነው። ልጆቿ በጾታ ቢነወሩ መነወራቸውን ለመረዳትና አዎንታዊ እርምጃ ለመውሰድ ልትቸገር ትችላለች። እናቲቱ እርምጃ ባለመውሰዷ ደግሞ ልጆቹ የከፋ ጉዳት ይደርስባቸዋል።
በጾታ የመነወሩ ሂደት በዚህ መንገድ ከአንዱ ትውልድ ወደ ሌላው ሊሻገር ይችላል። እርግጥ በልጅነታቸው የተፈጸመባቸውን ዘግናኝ ድርጊት ለማንሳት የማይፈልጉ ብዙ ሰዎች ሕይወታቸውን በጥሩ ሁኔታ ለመምራት የቻሉ ይመስላል፤ ይህ የሚደገፍ ነው። ሆኖም ብዙዎቹ የደረሰባቸው ሥነ ልቦናዊ ችግር ሥር የሰደደ ከመሆኑም በላይ በልጅነት ሕይወት የተከሰተውን እንዲህ ዓይነት ከባድ የሕሊና ቁስል ለመፈወስ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ብቃት ያለው ባለሙያ የሚሰጠውን እርዳታ ማግኘትን ጨምሮ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ዓላማቸው ነገሩን እያወጡና እያወረዱ በጭንቀት ስሜት መዋጥ አይደለም። ቤተሰባቸውን የሚያጠቃውን ይህን የሚያሠቃይና ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ልጆችን የማስነወር ዑደት መግታት ይኖርባቸዋል።—የጥቅምት 8, 1991 ንቁ! (የእንግሊዝኛ) መጽሔት ገጽ 3 እስከ 11 ተመልከት።
ልጆችን የማስነወር ድርጊት የሚያከትምበት ጊዜ
ከላይ የቀረበውን ሐሳብ በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ ካዋላችሁት ልጆችን በጾታ የማስነወር ወንጀል በቤታችሁ እንዳይፈጸም ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክትላችሁ ይችላል። ሆኖም ልጆችን የሚያስነውሩ ሰዎች ድርጊቱን በድብቅ እንደሚፈጽሙ፣ የተጣለባቸውን አመኔታ መሣሪያ አድርገው እንደሚጠቀሙና የረቀቀ ዘዴ በመጠቀም ምንም የማያውቁትን ልጆች እንደሚያታልሉ መዘንጋት የለባችሁም። በመሆኑም ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ይህን ጸያፍ ወንጀል ማንም ሳያውቅባቸው በድብቅ እንደሚያከናውኑ ግልጽ ነው።
ይሁን እንጂ የሚያደርጉትን ነገር አምላክ እንደሚመለከተው እርግጠኞች ሁኑ። (ኢዮብ 34:22) ንስሐ ካልገቡና ካልተለወጡ በስተቀር ይህን የብልግና ድርጊታቸውን ፈጽሞ አይረሳውም። እሱ በወሰነው ቀን ሥራቸውን ገሃድ ያወጣዋል። (ከማቴዎስ 10:26 ጋር አወዳድር።) ፍትሃዊ የሆነ ፍርድም ይበይንባቸዋል። ይሖዋ አምላክ እንዲህ ዓይነት ከሃዲ ሰዎች በሙሉ ‘ከምድር ገጽ ተጠርገው የሚጠፉበትና’ አምላክንና ሰውን የሚያፈቅሩ ገርና ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች ብቻ እንዲኖሩ የሚደረግበት ጊዜ እንደሚመጣ ቃል ገብቷል። (ምሳሌ 2:22፤ መዝሙር 37:10, 11, 29፤ 2 ጴጥሮስ 2:9-12) ኢየሱስ ክርስቶስ በከፈለው ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይህን የመሰለ ግሩም የአዲስ ዓለም ተስፋ ተሰጥቶናል። (1 ጢሞቴዎስ 2:6) አዎን፣ ያን ጊዜ ነው፣ ልጆችን የማስነወር ድርጊት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያከትመው።
እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ልጆቻችንን ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን። ልጆቻችን በጣም ውድ ናቸው! አብዛኞቹ ወላጆች ትንንሽ ልጆቻቸውን ለማዳን ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ለመጣል ዝግጁዎች ናቸው። (ከዮሐንስ 15:13 ጋር አወዳድር።) ልጆቻችንን የማንጠብቃቸው ከሆነ መዘዙ በጣም የከፋ ይሆናል። የምንጠብቃቸው ከሆነ ግን ግሩም የሆነ ስጦታ ልናበረክትላቸው እንችላለን—ምንም ጠባሳ የሌለውና ከመከራ ነፃ የሆነ ጥሩ የልጅነት ሕይወት። “እግዚአብሔርን:- አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ፤ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፣ በእርሱም እታመናለሁ” ሲል የጻፈው መዝሙራዊ የተሰማው ዓይነት ስሜት ሊሰማቸው ይችላል።—መዝሙር 91:2
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንድ ልጅ በጾታ ተነወረ የሚባለው አንድ ሰው የራሱን የጾታ ፍላጎት ለማርካት ልጁን መሣሪያ አድርጎ በሚጠቀምበት ጊዜ ነው። ይህ ድርጊት ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ዝሙት ወይም ፖርኒያ ብሎ የሚጠራውን ድርጊት ይጨምራል፤ ይህም የጾታ ብልትን ማሻሸትን፣ የጾታ ግንኙነት መፈጸምንና በአፍ ወይም ደግሞ በፊንጢጣ መገናኘትን ሊጨምር ይችላል። ጡትን መደባበስ፣ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት ለመፈጸም መጠየቅ፣ ዕርቃነ ሥጋን የሚያሳዩ የብልግና ጽሑፎች ለልጅ ማሳየት፣ ተደብቆ የሰውን ዕርቃነ ሥጋ ማየት ወይም ሰዎች የጾታ ግንኙነት ሲፈጽሙ መመልከትና ሆን ብሎ ዕርቃነ ሥጋን ማሳየት የመሳሰሉት አስነዋሪ ድርጊቶች መጽሐፍ ቅዱስ “ነውር” ብሎ ከሚያወግዘው ነገር ጋር የሚወዳደሩ ሊሆኑ ይችላሉ።—ገላትያ 5:19-21 NW፤ በመጋቢት 15, 1983 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 30 ላይ ያለውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
b በልጆች ላይ ወሲባዊ ጥቃት የሚፈጽሙት አብዛኞቹ ሰዎች በልጅነታቸው የተነወሩ ቢሆኑም እንኳ በልጅነታቸው መነወራቸው እነሱም ይህን ድርጊት የሚፈጽሙ ዓይነት ሰዎች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ማለት አይደለም። በልጅነታቸው በጾታ ከተነወሩ ሰዎች መካከል ውሎ አድሮ በልጆች ላይ ወሲባዊ ጥቃት የሚፈጽሙት ቁጥራቸው ከአንድ ሦስተኛ በታች ነው።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከብዙ ዓመታት በፊት በቅርብ ዘመዱ የተነወረ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል:- “በጾታ የማስነወር ድርጊት የልጆችን ቅስም ይሰብራል፤ በሰዎች ላይ የነበራቸውን እምነት ያጠፋዋል፤ በሕይወታቸው ላይ መጥፎ ጠባሳ ይተዋል። ልጆችን መጠበቅ የሚያስፈልገው ለዚህ ነው። እኔ አሁን መላ ሕይወቴን እንደ አዲስ ለመገንባት ተገድጃለሁ። ታዲያ ሌሎች ልጆችም ለምን ሕይወታቸው ይበላሽ?”
እውነትም ለምን ይበላሽ?
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ልጆቹን እመኗቸው!
በቅርቡ ካናዳ ውስጥ በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ግዛት በተደረገ አንድ ጥናት በልጆች ላይ ወሲባዊ ጥቃት በሚፈጽሙ 30 ሰዎች ላይ ምርምር ተካሄዶ ነበር። የተገኘው ውጤት በጣም የሚያስደነግጥ ነው። እነዚህ 30 ሰዎች በጠቅላላው 2,099 ልጆችን አስነውረዋል። ከእነዚህ መካከል ግማሽ የሚሆኑት እምነት እንዲጣልባቸው የሚያደርግ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ያላቸው ናቸው፤ አስተማሪዎች፣ ቄሶች፣ አስተዳዳሪዎችና ልጆችን የሚንከባከቡ ሰዎች ናቸው። በልጆች ላይ ወሲባዊ ጥቃት የሚፈጽም አንድ የ50 ዓመት የጥርስ ሐኪም በ26 ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ 500 የሚጠጉ ልጆችን አስነውሯል።
ይሁን እንጂ በቶሮንቶ እየታተመ የሚወጣው ዘ ግሎብ ኤንድ ሜል የተባለው ጋዜጣ እንዲህ ብሏል:- “ከሚፈጸመው የማስነወር ድርጊት መካከል 80 በመቶ የሚሆነውን አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ የማኅበረሰቡ ክፍሎች (ድርጊቱን የፈጸመውን ሰው ጓደኞች ወይም ባልደረቦች፣ ድርጊቱ የተፈጸመባቸውን ልጆች ቤተሰቦች፣ ሌሎች ልጆችንና ድርጊቱ ከተፈጸመባቸው ልጆች አንዳንዶቹን ጨምሮ) አይቀበሉትም ወይም ደግሞ ድርጊቱን አቅልለው ይመለከቱታል።” “ሪፖርቱ ሰዎች ይህን አምነው አለመቀበላቸው ልጆችን የማስነወር ወንጀል እንዲቀጥል አስተዋጽኦ አድርጓል” ማለቱ ምንም አያስደንቅም።
በጾታ ከተነወሩት ልጆች መካከል አንዳንዶቹ ድርጊቱ እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ “የልጆቹ ወላጆች ልጆቹ የሚነግሯቸውን ነገር አምነው ለመቀበል ፈቃደኞች አይደሉም” በማለት ዘ ግሎብ ኤንድ ሜል ሪፖርቱን በቀጥታ በመጥቀስ ዘግቧል። በተመሳሳይም በጀርመን የሚገኙ አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን በቅርቡ አንድን ሪፖርት በመጥቀስ በጾታ የተነወሩ ልጆች ሰባት ጊዜ ደጋግመው ካልተናገሩ የሚያምናቸው የለም ብለዋል።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልጆች ከፍተኛ የሆነ ወዳጃዊና ፍቅራዊ ትኩረት ያሻቸዋል