ውጥረት “ድምፅ የለሹ ቀሳፊ”
“በመጀመሪያ የተሰማኝ በጣም ከፍተኛ የሆነ የመጫን ስሜት ነበር። ከደረቴ ጀምሮ በፍጥነት ወደ ትከሻዎቼ፣ ወደ አንገቴና ወደ መንጋጋዎቼ ከተዛመተ በኋላ ቁልቁል ወደ እጆቼ ወረደ። ዝሆን ደረቴ ላይ እንደተጫነኝ ያህል ነበር። መተንፈስ አቃተኝ። ያልበኝ ጀመር። ቁርጠት ከጀመረኝ በኋላ በጣም ኃይለኛ የሆነ የማቅለሽለሽ ስሜት ተሰማኝ። . . . ትንሽ ቆየት ብሎ ነርሶች ሆስፒታሉ አልጋ ላይ ሲያወጡኝ በመደነቅ ‘ልብ ድካም ያዘኝ ማለት ነው?’ ስል ትዝ ይለኛል። ዕድሜዬ ገና አርባ አራት ዓመት ነበር።”
ዶክተር ሮበርት ኤስ ኤልየት ይህን የጻፉት ፍሮም ስትሬስ ቱ ስትሬንግዝ (ከውጥረት ወደ ብርታት) በተባለው መጽሐፋቸው ከ20 ዓመታት በፊት ሊሞቱ ተቃርበው በነበሩበት ጊዜ የተሰማቸውን ስሜት ሲገልጹ ነበር። በዚያው ቀን ጠዋት እንዲህ ያለ ሁኔታ ላይ ከመውደቃቸው በፊት በአንድ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገው ነበር። የሚያስገርመው ንግግር ያደረጉት ስለ ልብ ድካም ነበር። የልብ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ኤልየት ራሳቸው እንደተናገሩት በድንገት ‘በሽተኞችን ከማከም ይልቅ ራሳቸው የልብ በሽተኛ ሆነው በልብ መታከሚያ ክፍል ውስጥ ተኙ።’ ይህ ድንገተኛ አደጋ የደረሰባቸው ለምን ነበር? “የነበረብኝ ውጥረት ውስጥ ውስጤን ሲበላው ቆይቶ ነበር” ብለዋል።a
ዶክተር ኤልየት ከደረሰባቸው ሁኔታ መረዳት እንደሚቻለው ውጥረት ለሞት የሚያደርስ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል። እንዲያውም በዩናይትድ ስቴትስ ከዋነኞቹ የሞት ምክንያቶች ጋር የቅርብ ዝምድና እንዳለው ተገልጿል። ውጥረት የሚያስከትለው ጉዳት ምንም ዓይነት ምልክት ሳይሰጥ ለበርካታ ዓመታት ሲጠራቀም ከቆየ በኋላ አላንዳች ማስጠንቀቂያ በድንገት ብቅ ሊል ይችላል። ስለዚህ ውጥረት “ድምፅ የለሽ ቀሳፊ” መባሉ ተገቢ ነው።
በውጥረት ምክንያት በሚመጡ ችግሮች የሚጠቁት በችኩልነታቸው፣ በግልፍተኝነታቸውና ከሌሎች ተሽለው ለመገኘት ባላቸው ከፍተኛ ፍላጎት ተለይተው የሚታወቁት ታይፕ ኤ ባሕርይ ያላቸው ሰዎች ብቻ አለመሆናቸው ያስደንቃል። ረጋ ያሉ የሚመስሉ ሰዎችም፣ በተለይ እርጋታቸው ኃይለኛ እንፋሎት በሚወጣው ድስት ላይ በደንብ ሳይገጠም እንደተቀመጠ ክዳን ለይስሙላ ብቻ ከሆነ፣ ለዚህ አደጋ የተጋለጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ዶክተር ኤልየት ራሳቸው ከነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች የሚመደቡ እንደሆኑ ያምናሉ። ሌሎችን ሲያስጠነቅቁ “ልባችሁ ላይ የታሠረ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ ይዛችሁ መዞር ከጀመራችሁ ብዙ ዓመት እንደሆናችሁ ሳታውቁ ድንገት ልትሞቱ ትችላላችሁ” ይላሉ።
ይሁን እንጂ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ውጥረት የሚያስከትለው ጉዳት የልብ ድካምና ድንገተኛ ሞት ብቻ አይደለም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ውጥረት የልብ ድካም በማምጣት ረገድ አስተዋጽኦ ቢኖረውም አብዛኛውን ጊዜ ምክንያት የሚሆነው የልብ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች መደንደንና መጥበብ ነው። ስለዚህ አንድ ሰው ውጥረት ብቀንስ ይሻለኛል ብሎ የልብ ሕመም ምልክቶችን ችላ ማለት የለበትም። የታኅሣሥ 8, 1996 (የእንግሊዝኛ) ንቁ! ገጽ 3–13 ተመልከት።