ውጥረት “ቀስ በቀስ የሚጎዳ መርዝ”
“ሰዎች ‘ራስህን ብዙ አታስጨንቅ፣ በሽታ ላይ ትወድቃለህ’ ሲሉ ብዙ ጊዜ እንሰማለን። ይህ አባባላቸው የተረጋገጠ ባዮሎጂያዊ መሠረት እንዳለው አይገነዘቡ ይሆናል።”—ዶክተር ዴቪድ ፌልተን
ጉርምስና ዕድሜ ላይ የደረሰ ልጅ አለ አባት የምታሳድገው ጂል በባንክ የነበራት ገንዘብ እየተሟጠጠ በመሄዱና ከወላጆቿ ጋር የነበራት ዝምድና በመሻከሩ ከፍተኛ ውጥረት አጋጥሟታል። በድንገት ክንዷ ላይ የሚያሳክክ ሽፍ ያለ ነገር ወጣባት። አንቲባዮቲኮች፣ ኮርቲዞን ያላቸውን ቅባቶች፣ የአለርጂ መድኃኒቶችን ሁሉ ሞከረች፣ ግን አንዱም አልረዳትም። እንዲያውም ሽፍታው ወደ ሌላ የሰውነቷ ክፍሎች በሙሉ ተዛምቶ ፊቷን ጭምር አበላሸው። የነበረባት ውጥረት ቃል በቃል ቆዳዋ ውስጥ ገባ።
ጂል የበሽተኞችን ውስጣዊ ስሜት በሚመረምር የቆዳ ክሊኒክ እንድትታከም ተደረገ። የክሊኒኩ ተባባሪ መሥራች የሆኑት ዶክተር ቶማስ ግራግ “በሕይወታቸው ውስጥ ያጋጠማቸውን ነገር ለማወቅ እንሞክራለን” ይላሉ። አልድን ብሎ ያስቸገረ የቆዳ ችግር ያላቸው ሰዎች ከሕክምና በተጨማሪ ያለባቸውን ጭንቀትና ውጥረት እንዲቋቋሙ የሚያስችላቸው እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ዶክተር ግራግ “አስተሳሰብህ ወይም የምታደርገው ነገር የቆዳ በሽታ ያመጣል ማለት ችግሩን አለ አግባብ አቅልሎ መመልከት ይሆናል” ካሉ በኋላ “ይሁን እንጂ የአንድ ሰው ስሜታዊ ሁኔታ ከቆዳ በሽታ ጋር ከፍተኛ ዝምድና ሊኖረው ይችላል ለማለት እንችላለን። ስለዚህ ሰውዬው በኑሮው ውስጥ ያጋጠመውን ውጥረት መቋቋም እንዲችል ሳንረዳው የስቴሮይድ ቅባት ብቻ አዝዘን መሸኘት የለብንም” ብለዋል።
ጂል ያለባትን ውጥረት እንዴት እንደምትቋቋም ማወቋ ቆዳዋን እንዳዳነላት ይሰማታል። “አሁንም ሽፍታው ቱግ የሚልበት ጊዜ አለ። ቢሆንም እንደበፊቱ ሆኖብኝ አያውቅም” ትላለች። የርሷ ሁኔታ ያልተለመደ ነውን? በፍጹም አይደለም። ውጥረት እንደ እንድብድብ፣ ሶርያሲስ፣ ብጉርና ችፌ ያሉትን ጨምሮ ለበርካታ የቆዳ ችግሮች ምክንያት እንደሚሆን ብዙ ዶክተሮች ያምናሉ። ይሁን እንጂ ውጥረት የሚጎዳው ቆዳችሁን ብቻ አይደለም።
ውጥረትና በሽታ የመከላከል አቅም
ውጥረት በሽታ የመከላከል አቅምን በማመናመን ለበርካታ የኢንፌክሽን በሽታዎች ሊያጋልጥ እንደሚችል በቅርቡ የተደረጉ ምርምሮች ያመለክታሉ። “ውጥረት ራሱ አያሳምምም” ይላሉ የቫይሮሎጂ ሊቅ የሆኑት ሮናልድ ግላሰር። “ነገር ግን የሰውነታችሁን በሽታ የመከላከል አቅም ስለሚያዳክም በበሽታ የመያዝ ዕድላችሁ በጣም ከፍተኛ እንዲሆን ያደርጋል።” በተለይ ውጥረት ከጉንፋን፣ ከኢንፍሉዌንዛና ኸርፒዝ ከተባለው የቆዳ በሽታ ጋር ዝምድና እንዳለው የሚያረጋግጥ አሳማኝ ማስረጃ አለ። ምን ጊዜም ለእነዚህ ቫይረሶች የተጋለጥን ብንሆንም የሰውነታችን በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ተዋግተው ያስወግዷቸዋል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሊቃውንት እንደሚሉት አንድ ሰው ስሜታዊ ጭንቀት በሚያጋጥመው ጊዜ እነዚህ ሕዋሳት የመከላከል አቅማቸውን ሊያጡ ይችላሉ።
ይህ የሚሆንበት ባዮሎጂያዊ ምክንያት እስካሁን ሙሉ በሙሉ ሊታወቅ ባይችልም አንዳንዶች ውጥረት ሲያጋጥማችሁ በሰውነታችሁ ውስጥ የሚለቀቁ ሆርሞኖች በደማችሁ ውስጥ በሚዘዋወሩበት ጊዜ በሽታ ተከላካይ ሕዋሶቻችሁ ተግባራቸውን እንዳያከናውኑ ያግዳሉ የሚል መላ ምት ያቀርባሉ። እነዚህ ሆርሞኖች አብዛኛውን ጊዜ ያላቸው ተልእኮ ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ በመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ይህ ሁኔታ አሳሳቢ አይሆንም። ይሁን እንጂ አንድ ሰው የማያቋርጥና ከፍተኛ የሆነ ውጥረት የሚደርስበት ከሆነ የሰውነቱ በሽታ የመከላከል አቅም በጣም ተዳክሞ ለተለያዩ በሽታዎች በቀላሉ ወደሚጋለጥበት ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል የሚናገሩ ሊቃውንት አሉ።
ካናዳውያን ዶክተሮች እንደሚገምቱት ለሕክምና ከሚመጡ በሽተኞቻቸው መካከል ከ50 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት ከውጥረት ጋር ግንኙነት ባላቸው እንደ ራስ ምታት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ድካምና የሆድ ዕቃ ችግር ባሉት ሕመሞች የሚሰቃዩት በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በዩናይትድ ስቴትስ ይህ ቁጥር ከ75 በመቶ እስከ 90 በመቶ እንደሚደርስ ይገመታል። ዶክተር ጂን ኪንግ “ሥር የሰደደ ውጥረት ቀስ በቀስ እንደሚጎዳ መርዝ ነው” ብለው መናገራቸው ከሚገባ በላይ ማጋነናቸው እንዳልሆነ ይሰማቸዋል።
ብቸኛ ምክንያትም ሆነ ብቸኛ መፍትሔ አይደለም
ከላይ የተመለከትነው እውነት ቢሆንም ውጥረት ብቻውን በሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም ላይ የጤና ችግር ሊያስከትል በሚችል መጠን ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ሳይንቲስቶች እርግጠኛ አይደሉም። ስለዚህ ውጥረት ያለበት ሰው ሁሉ፣ ውጥረቱ ሥር የሰደደ እንኳን ቢሆን መታመሙ አይቀርም ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። በሌላ በኩል ደግሞ የውጥረት አለመኖር ብቻውን ለጥሩ ጤና ዋስትና ስለማይሆን ብሩሕና ትክክለኛ አስተሳሰብ በመያዝ ብቻ ማንኛውንም በሽታ ላስወግድ እችላለሁ ብሎ በማሰብ ሕክምናን ቸል ማለት ተገቢ አይደለም። ዶክተር ዳንኤል ጎልማን እንደሚከተለው በማለት ያስጠነቅቃሉ:- “አመለካከትን ማስተካከል ማንኛውንም በሽታ ያድናል የሚለው አስተሳሰብ አእምሮ በበሽታ ላይ ስለሚያሳድረው ተጽእኖ ብዙ ግራ መጋባትና ዝብርቅ እንዲፈጠር ከማድረጉም በላይ አንዳንድ ጊዜ በሽታ የአንድ ዓይነት ሥነ ምግባር ወይም መንፈሳዊ ጉድለት ምልክት የሆነ ይመስል ሰዎች የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል።”
ስለዚህ ለበሽታ አንድ የተወሰነ ምክንያት ብቻ ለይቶ መጠቆም እንደማይቻል መገንዘብ ይገባል። ቢሆንም በበሽታና በውጥረት መካከል ዝምድና መኖሩ በሚቻልበት ጊዜ ሁሉ ይህን “ቀስ በቀስ የሚጎዳ መርዝ” እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል ማወቅ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዝባል።
ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ከማየታችን በፊት ግን የውጥረት ባሕርይ ምን እንደሆነና በአንዳንድ ሁኔታዎች ውጥረት እንዴት ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል እንመለከታለን።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከውጥረት ጋር ዝምድና ያላቸው አንዳንድ ሕመሞች
• አለርጂ
• አርትራይትስ
• አስም
• የወገብ፣ የአንገትና የትከሻ ሕመም
• ጉንፋን
• ድባቴ (depression)
• ተቅማጥ
• ኢንፍሉዌንዛ
• የሆድ ዕቃ ችግር
• ራስ ምታት
• የልብ ችግር
• እንቅልፍ እጦት
• ገሚስ ራስምታት (migraine)
• የጨጓራ ቁስለት
• የወሲብ ስሜት መዛባት
• የቆዳ ችግር
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብዛኞቹ ሰዎች ወደ ሐኪሞች የሚሄዱት ከውጥረት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ነው