የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 11/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኢንፌክሽን በሆስፒታል
  • በአፍሪካ ያሉ ቀሳውስት የሚፈጽሙት ነውር
  • የሐሰት መድኃኒት
  • ዝንጉ የሆኑ ሰዎች
  • የሚፈጸምባቸውን በደል የሸሹ የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች
  • ሽጉጥ የታጠቁ ሰባኪዎች
  • አንተ ያለህበት ሰልፍ የሚንቀራፈፍ የሚመስለው ለምንድን ነው?
  • የጾታ ንግድ ሰለባዎች
  • በዓለም ረጅሙ ተንጠልጣይ ድልድይ
  • በብዙ መንገዶች ተወዳዳሪ የማይገኝለት ግን ሙት የሆነ ባሕር!
    ንቁ!—2008
  • እየተመናመነ የሚገኘው የምድር የተፈጥሮ ሀብት
    ንቁ!—2005
  • መድኃኒቶችን በአግባቡ ተጠቀምባቸው
    ንቁ!—1997
  • የሰው ልጅ በገዛ እጁ ጉሮሮውን እየዘጋ ነውን?
    ንቁ!—2001
ንቁ!—1998
g98 11/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

ኢንፌክሽን በሆስፒታል

“አንድ ሰው በሆስፒታል ውስጥ ቀዶ ሕክምናም ሆነ ሌላ ዓይነት ሕክምና ከተደረገለት በኋላ በኢንፌክሽን መለከፉ አሳሳቢ የጤና ችግር እንዳለ የሚያመለክት ነው” ሲል ለ ፊጋሮ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ ዘግቧል። በፈረንሳይ ብቻ በየዓመቱ 800,000 ሰዎች በኢንፌክሽን የሚለከፉ ሲሆን በዚህ ሳቢያ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ደግሞ 10,000 እንደሚደርስ ይገመታል። ሕሙማኑን ለኢንፌክሽን የሚያጋልጡትን ሁኔታዎች ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል:- እያንዳንዱ አዲስ ታካሚ አልጋ ከመያዙ በፊት ክፍሉን በጀርም ማጥፊያ መድኃኒት ማጽዳት፣ የሕክምና መሣሪያዎችን ከጀርም የማጽዳት ዘዴ መጠቀምና እያንዳንዱን ታካሚ ከማከም በፊት እጅን በሚገባ መታጠብ። ብዙውን ጊዜ ከእነዚህ ልማዶች መካከል ብዙዎቹ ችላ የሚባሉ ይመስላል። ፓሪስ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል የተካሄደ ጥናት እንደሚያመለክተው በሆስፒታሉ ውስጥ ከሚገኙት ረዳት የሕክምና ሠራተኞች መካከል፣ ከእያንዳንዱ ታካሚ ጋር በተነካኩ ቁጥር እጃቸውን በደንብ እንደሚታጠቡ የተናገሩት 72 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው። ከእነዚህ መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ጀርሞችን ለማጥፋት የሚፈለገውን ያህል አይታጠቡም። እንዲህ ዓይነቶቹ አሳዛኝ መረጃዎች “ገና ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ ያሳያሉ” ሲል ጋዜጣው ደምድሟል።

በአፍሪካ ያሉ ቀሳውስት የሚፈጽሙት ነውር

“ቀሳውስት የሚፈጽሙት በጾታ የማስነወር ድርጊት በአፍሪካ ውስጥም መታየት ጀምሯል” ሲል ካተሊክ ኢንተርናሽናል የተባለው መጽሔት ዘግቧል። እንዲህ ዓይነቱን የማስነወር ድርጊት ለመከላከል አንዳንድ የካቶሊክ ጳጳሳት ይበልጥ ጥብቅ የሆነ ምርመራ እንዲካሄድና ዕጩ ቀሳውስት ጥሩ ሥልጠና እንዲሰጣቸው ሐሳብ እያቀረቡ ነው። የአፍሪካ ጳጳሳት የሚያሳስባቸው ሌላው ነገር ቀሳውስቱ “አልኮልን አላግባብ በመጠቀም እንዲሁም በቅስና አገልግሎት ላይ ለተሰማራ ሰው ተገቢ ባልሆኑና ከቅስና ሙያ ጋር በማይጣጣሙ እንደ ንግድና ፖለቲካ ባሉ እንቅስቃሴዎች መሳተፋቸው” ነው። እነዚህ ነገሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይፋ ሊወጡ የቻሉት ለምንድን ነው? “የነፃ ፕሬስ መብት በመገኘቱና ቤተ ክርስቲያን በመገናኛ ብዙሃን ላይ የነበራት ሥልጣን እየተዳከመ በመምጣቱ ነው” ሲል ካተሊክ ኢንተርናሽናል ገልጿል። አክሎም “በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣናት ስማቸውን የሚያጎድፉ ዜናዎችን ለማገድ ያደረጉት ጥረት . . . ሳይሳካ ቀርቷል” ብሏል።

የሐሰት መድኃኒት

“በመላው ዓለም ገበያ ላይ ከሚውሉት መድኃኒቶች ውስጥ ወደ 8 በመቶ የሚሆኑት የሐሰት መድኃኒቶች መሆናቸውን” ለ ፊጋሮ ማጋዚን ገልጿል። በዓለም ጤና ድርጅት ዘገባ መሠረት በብራዚል 30 ከመቶ የሚሆነው መድኃኒት የሐሰት መድኃኒት ሲሆን በናይጄሪያ ደግሞ ያስደነግጣል፤ 60 ከመቶ የሚሆነው የሐሰት መድኃኒት ነው። የሐሰት መድኃኒቶች ሽያጭ 300 ቢልዮን ዶላር ካፒታል ያለው ንግድ እንደሆነ የተዘገበ ሲሆን በዚህ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት የተደራጀ ወንጀል የሚፈጽሙ ድርጅቶች ናቸው። መድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ይህ ንግድ እንዲገታ የቱንም ያህል ቢጥሩም ፖሊስም ሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለችግሩ መፍትሄ አላገኙለትም። የሐሰት መድኃኒት እንዲሁ የስነ ልቦና ዕረፍት ይሰጥ እንደሆነ እንጂ ምንም ጥቅም የለውም፤ እንዲያውም ሊገድል ይችላል። “የሐሰት መድኃኒት በበሽተኛ ሕይወት ቁማር ይጫወታል” ሲል ለ ፊጋሮ ማጋዚን አስተያየቱን ሰጥቷል።

ዝንጉ የሆኑ ሰዎች

በኢጣሊያ በ1,600 አዋቂዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት 77 ከመቶ የሚሆኑት የመዘንጋት ችግር እንዳለባቸው ማመልከቱን ላ ሬፑብሊካ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። ጥናቱ ከተካሄደባቸው ሰዎች መካከል ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት ከዚያ ቀደም ብሎ በነበረው ዓመት ውስጥ የተከበረ አንድ ትልቅ ክብረ በዓል ዘንግተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ጥናቱ ከተካሄደባቸው ሰዎች መካከል 42 ከመቶ የሚሆኑት በተደጋጋሚ ጊዜያት መኪናቸውን የት እንዳቆሙ ዘንግተዋል፣ 30 ከመቶ በላይ የሚሆኑት የቤታቸውን ቁልፍ ዘንግተዋል፣ 25 ከመቶ በላይ የሚሆኑት የገንዘብ ቦርሳቸውን የዘነጉ ሲሆን ጭራሽ የሚገርመው ደግሞ 1.2 ከመቶ የሚሆኑት ስማቸውንና የአባታቸውን ስም ዘንግተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ 28 በመቶ የሚሆኑት ኢጣሊያውያን ተማሪዎች በነበሩበት ጊዜ በቃላቸው ካጠኗቸው ግጥሞች ውስጥ አሁን ቢያንስ አንዱን እንደሚያስታውሱ ይናገራሉ። የማስታወስ ችሎታህን እንዴት ማሻሻል ትችላለህ? አንድ የሥነ ልቦና ጠበብት ለማስታወስ የሚፈለገውን ነገር ከሌላ ነገር ጋር ለማዛመድ መሞከር፣ ማስታወሻ መጻፍና የተጻፈውን መከለስ እንዲሁም የስልክ ቁጥሮችን፣ የሙዚቃ ዜማዎችንና የታርጋ ቁጥሮችን ጭምር ሳይቀር ለማስታወስ በመሞከር አእምሮን ማሠልጠን ጠቃሚ እንደሆነ ይናገራሉ።

የሚፈጸምባቸውን በደል የሸሹ የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች

“ዘጠና ከመቶ የሚሆኑት የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች ቤተሰብ ያላቸው ናቸው። [ከእነዚህ የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች መካከል] 90 ከመቶ ገደማ የሚሆኑት የወላጆቻቸውን ዱላ ሸሽተው የወጡ ሲሆኑ ለወንጀል ድርጊቶችና ለዕፅ ሱሰኝነት ከመጋለጣቸውም በላይ የጾታ ብልግና መጠቀሚያ ይሆናሉ” ሲሉ በደል ለሚፈጸምባቸው ልጆች ተቆርቋሪ የሆነው ክልላዊ ማዕከል (Crami) አስተባባሪ የሆኑት ኢንዛ ማታር ገልጸዋል። ማታር “ድንገተኛ የሆነ የባሕርይ ለውጥን፣ ራስን የማግለል ዝንባሌንና በአካል ላይ የሚታዩ ምልክቶችን” ጨምሮ በልጆች ላይ በደል እየተፈጸመ እንዳለ ለሚጠቁሙ ምልክቶች ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ የሕክምና ባለሙያዎችንና አስተማሪዎችን ማሳሰባቸውን ኦ ኢስታዶ ደ ኤስ ፓውሉ የተባለው የብራዚል ጋዜጣ ጠቅሷል። ክራሚ (Crami) እርዳታ ካደረገላቸው ልጆች መካከል ራሳቸው እርዳታ የጠየቁት 5 ከመቶ ብቻ ስለሆኑ ልጆቹ እርዳታ እስኪጠይቁ ድረስ መጠበቅ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። በልጆቻቸው ላይ በደል የሚፈጽሙ ወላጆች አብዛኛውን ጊዜ የሌላ እርዳታ አይፈልጉም። ለምን? የክራሚ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዣኡን ሮቤርቶ ስኮንፓሪን “ልጆቻቸውን በኃይል የሚያንገላቱ ወላጆች እነሱ ራሳቸው ባደጉበት መንገድ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ ናቸው፤ ደግሞም ልጆቻቸውን እያስተማሯቸው እንዳሉ ይሰማቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ሽጉጥ የታጠቁ ሰባኪዎች

በዩ ኤስ ኤ፣ ኬንታኪ የሚገኙ ፓስተሮች መሣሪያዎችን በስውር የመያዝ ፈቃድ እስካላቸው ድረስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በስውር ሽጉጥ መያዝ የሚያስችል ፈቃድ ይሰጣቸው ዘንድ በቅርቡ የግዛቲቱ ሕግ እንደተሻሻለ ሮይተርስ የዜና አገልግሎት ዘግቧል። ቀደም ሲል ገዳይ የሆኑ መሣሪያዎችን በስውር የመያዝ ፈቃድ የነበራቸው ፓስተሮች በግዛቲቱ ውስጥ በሚገኙ የአምልኮ ሥፍራዎች ውስጥ መሣሪያዎቹን ይዘው መገኘት አይችሉም ነበር። በ1997 አንዳንድ የኬንታኪ አብያተ ክርስቲያናት የሰበሰቡት የመዋጮ ገንዘብ በመሣሪያ ተገደው ተዘርፎባቸዋል። በወቅቱ የተጎዳ ሰው ባይኖርም “በገጠራማ ቦታ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ያሉ አገልጋዮችና ቄሶች ሽጉጥ በስውር መያዝ እንዲችሉ እንዲፈቅዱላቸው በሕግ አውጪዎች ላይ ግፊት አሳድረዋል” ሲል ዘገባው ይገልጻል። ይህ ማሻሻያ እንዲደረግ የሚፈልጉት ግን ሁሉም የቤተ ክህነት ሰዎች አይደሉም። የኬንታኪ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ዋና ዲሬክተር የሆኑት ናንሲ ጆ ኬምፐር የሚከተለውን ጥያቄ አቅርበዋል:- “ልጆቻችን፣ የሰላምና የዕርቅ መልእክተኞች መሆን ያለባቸው አገልጋዮች ሳይቀሩ ሕይወት ሊያጠፉ የሚችሉ መሣሪያዎችን ይዘው የሚመለከቱ ከሆነ ጠመንጃ ችግሮችን ሊፈታ እንደማይችል ይማራሉ ብለን እንዴት ልንጠብቅ እንችላለን?”

አንተ ያለህበት ሰልፍ የሚንቀራፈፍ የሚመስለው ለምንድን ነው?

ገበያ በወጣህ ቁጥር ቀርፋፋ በሆነው መስመር ላይ እንደምትሰለፍ የሚሰማህ ከሆነ የአጋጣሚ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ዲ ዛይት የተባለው የጀርመን ጋዜጣ እንዳመለከተው በአጠገብህ ካሉት ሁለት ሰልፎች መካከል አንደኛው አንተ ካለህበት ሰልፍ ሊፈጥን የሚችልበት አጋጣሚ ሁለት ሦስተኛ ነው። የሰልፎቹ መደዳ በበዛ ቁጥር አንተ ያለህበት ሰልፍ ሊፈጥን የሚችልበት አጋጣሚ የዚያኑ ያህል ይቀንሳል። ተመራማሪዎች እንደደረሱበት ከሆነ ሰዎች የሚበሳጩት ብዙ ስለጠበቁ ሳይሆን “ጊዜያቸውን በከንቱ እንዳባከኑ ሆኖ ስለሚሰማቸው ነው።” አንዳንድ ሆቴሎች አሳንሱር የሚጠብቁ ሰዎች እንዳይበሳጩ ለማድረግ አሳንሱር በሚጠብቁባቸው ቦታዎች ላይ መስተዋቶች ሰቅለዋል። ይህም ሰዎቹ ፀጉራቸውን እያበጠሩም ሆነ ክራቫታቸውን እያስተካከሉ አሳንሱሩን እንዲጠብቁ ይረዳቸዋል። ሰዎቹ ምን ያህል ጊዜ መጠበቅ እንደሚያስፈልጋቸው ማሳወቁም ሊረዳ ይችላል። በመሆኑም አንዳንድ የምድር ውስጥ የባቡር መስመሮች የሚቀጥለው ባቡር እስከሚነሳ ድረስ ያሉትን ደቂቃዎች የሚያሳውቁ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች አሏቸው።

የጾታ ንግድ ሰለባዎች

በአንድ የዩክሬን ጋዜጣ ላይ የወጣ ማስታወቂያ እንዲህ ይላል:- “ልጃገረዶች:- ያላገቡና በጣም ቆንጆ መሆን አለባቸው። ወጣትና ሎጋ። ሞዴሎች፣ ጸሐፊዎች፣ ተወዛዋዦች፣ የዳንስ ስልት አውጪዎችና የጂምናስቲክ ስፖርተኞች ሆናችሁ እንድትሠሩ ተጋብዛችኋል።” ይህ ማስታወቂያ ሕገ ወጥ የጾታ ንግድ የሚያካሂዱ ሰዎች ምንም የማያውቁ ወጣት ሴቶችን አጥምደው በዝሙት አዳሪነት እንዲሰማሩ ለማድረግ የሚጠቀሙበትን ዘዴ የሚያሳይ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው ሲል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የዩክሬንና የሩስያ ሴቶች በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ሕይወታቸውን ለማሻሻል ሲሉ ወደ ውጭ አገር ይሄዳሉ። ሆኖም ወደሚሄዱበት አገር እንደደረሱ አንዳንዶቹ ወንጀለኛ በሆኑ “አለቆች” ፓስፖርቶቻቸውን ተነጥቀው በዝሙት አዳሪነት እንዲሠሩ ይደረጋል። አሻፈረኝ ካሉ ይደበደባሉ፣ ተገድደው ይደፈራሉ እንዲሁም አሰቃቂ በሆነ መንገድ ይገደላሉ። ከእንዲህ ዓይነቱ ባርነት ላመለጡ ሴቶች ምክር የለገሱ ሊዩድሚላ ቢሩክ የተባሉ ዩክሬናዊት የሥነ ልቦና ባለሙያ እንዲህ ብለዋል:- “አንድ ነገር ከመጠን በላይ ጥሩና ማራኪ መስሎ ከቀረበ ብዙውን ጊዜ ውሸት እንደሚሆን ለእነዚህ ልጆች ልትነግሯቸው ይገባል።”

በዓለም ረጅሙ ተንጠልጣይ ድልድይ

በጃፓን የሚገኘው አዋጂ ደሴትን ከኮቤ ከተማ የሚያገናኘው አካሺ ካይኪዮ የተባለው ድልድይ በሚያዝያ ተመርቆ የተከፈተ ሲሆን በዓለም ላይ እጅግ በጣም ረጅሙ ተንጠልጣይ ድልድይ በመሆን ወዲያው ተመዝግቧል። “በሁለቱ ዓምዶች መካከል ብቻ 1,991 ሜትር ርዝመት ያለውን ይህን ድልድይ ለመሥራት አሥር ዓመት እንደፈጀና 7.7 ቢልዮን ዶላር እንደፈሰሰበት” ታይም መጽሔት ዘግቧል። “የእያንዳንዱ አምድ ቁመት 90 ፎቅ ካለው ሕንፃ የሚበልጥ ሲሆን 20 የንዝረት መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች ተገጥመውለታል፤ ድልድዩን ኃይለኛ ንፋስ ካወዛወዘው አምዶቹን ገትረው የሚይዙ ፔንዱለሞች አሉ።” በተጨማሪም ድልድዩ በሬክተር ስኬል ሲለካ እስከ 8.0 የሚደርስ የመሬት መንቀጥቀጥ እንዲቋቋም ሆኖ የተሠራ ነው። ለድልድዩ ያገለገለው ካቦ ቀጥታ ቢዘረጋ ምድርን ሰባት ጊዜ እንደ መቀነት ሊጠመጠምባት ይችላል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ