የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 11/8 ገጽ 25-29
  • ኩላሊት ለሕይወትህ የግድ አስፈላጊ የሆነ ማጣሪያ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኩላሊት ለሕይወትህ የግድ አስፈላጊ የሆነ ማጣሪያ
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በኩላሊቶችህ ውስጥ ያለው ነገር ምንድን ነው?
  • ደምህ የሚጣራባቸው ሁለት ደረጃዎች
  • ቆሻሻዎችን ከሰውነት ማስወገድ
  • ኩላሊቶችህን ተንከባከብ!
  • ውኃ ምትክ የማይገኝለት ፈሳሽ
    ንቁ!—2003
  • እጅግ አስደናቂ የሆነው የደም ዝውውር ሥርዓት
    ንቁ!—2001
  • አምላክ ስለ ደም ያለውን አመለካከት ተቀበልኩ
    ንቁ!—2004
ንቁ!—1998
g98 11/8 ገጽ 25-29

ኩላሊት ለሕይወትህ የግድ አስፈላጊ የሆነ ማጣሪያ

አየርላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

መሬትና የሰው አካል የጋራ የሆነ ባሕርይ አላቸው:- ሕይወትን ጠብቆ ለማቆየት ሁለቱም ማጣሪያ ያስፈልጋቸዋል። መሬት ያለማቋረጥ ከፀሐይ የሚመጡትን ጎጂ ጨረሮች የሚከላከል ነገር ያስፈልጋታል። በከባቢ አየራችን ውስጥ የሚገኘው የኦዞን ንብር እነዚህን ጨረሮች አጣርቶ በማስቀረት ለሕይወት አስፈላጊ የሆነው ብርሃን ወደ መሬት እንዲያልፍ ያደርጋል። ሰውነትህስ? በሰውነትህ ውስጥ የሚካሄዱት አብዛኞቹ ኬሚካላዊ ሂደቶች መርዛማ የሆኑ ንጥረ ነገሮችና መወገድ ያለባቸው ሌሎች ነገሮች ወደ ደምህ እንዲገቡ ያደርጋሉ። እነዚህ ነገሮች ካልተወገዱ ከባድ ችግር አልፎ ተርፎም ሞት ሊያስከትሉብህ ይችላሉ። ዘወትር መጣራትና መወገድ አለባቸው።

ይህ የማጣራት ሥራ ኩላሊቶችህ ከሚያከናውኗቸው ዋና ዋና ተግባሮች አንዱ ነው። ሆኖም እነዚህ ትንንሽ የሰውነት ክፍሎች ጎጂ ንጥረ ነገሮችን ማወቅ፣ መለየትና ማስወገድ፣ በዚያው ጊዜ ደግሞ አስፈላጊ የሆኑት ንጥረ ነገሮች አካልህን ይመግቡና ያዳብሩ ዘንድ እዚያው እንዲቀሩ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? በተጨማሪም ኩላሊቶችህ ዘወትር ጤንነትህን እንዲጠብቁልህ የበኩልህን አስተዋጽኦ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

በኩላሊቶችህ ውስጥ ያለው ነገር ምንድን ነው?

ሁሉም ሰዎች ማለት ይቻላል፣ በጀርባቸው በኩል ከታች ከአከርካሪያቸው ግራና ቀኝ የተቀመጡ ሁለት ኩላሊቶች አሏቸው። እያንዳንዳቸው 10 ሴንቲ ሜትር ርዝመት፣ 5 ሴንቲ ሜትር ስፋትና 2.5 ሴንቲ ሜትር ውፍረት ያላቸው ሲሆን ከ110–170 ግራም ይመዝናሉ። ኩላሊት ከላይ እስከ ታች ለሁለት ሲከፈል ከዚህ ርዕስ ጋር ተያይዘው በወጡት ሥዕላዊ መግለጫዎች ላይ እንደሚታየው በርካታ ገጽታዎች ቁልጭ ብለው ይታያሉ።

ኩላሊት እንዴት ሥራውን እንደሚያከናውን በዓይነ ሕሊናህ መመልከት እንድትችል አንድ ጨዋታ ወይም ዝግጅት ለማየት ወደ ስታድየም እየጎረፉ ያሉ በሺህ የሚቆጠሩ ተመልካቾችን ወደ አእምሮህ ለማምጣት ሞክር። በመጀመሪያ ሰዎቹ ተከፋፍለው በርካታ ትናንሽ ሰልፎች መሥራት አለባቸው። ከዚያም በጥበቃ በሮቹ በኩል አንድ በአንድ እንዲገቡ ይደረጋል። በዚህ ጊዜ ትኬት ያልያዙት እንዲመለሱ ይደረጋል። ትኬት የያዙ ተመልካቾች ወደ ተመደቡላቸው መቀመጫዎች እንዲያልፉ ይደረጋል።

በተመሳሳይም በደምህ ውስጥ ያሉ በርካታ ንጥረ ነገሮች በመላ ሰውነትህ ውስጥ መዘዋወር አለባቸው። ይሁን እንጂ ይህን ሂደት በሚያከናውኑበት ወቅት ከሁለቱም ኩላሊቶች ጋር በተገናኙ ኩላሊታዊ ደም ወሳጅ ተብለው በሚጠሩ ትልልቅ የደም ስሮች አማካኝነት በተደጋጋሚ ጊዜያት በኩላሊቶችህ ውስጥ ማለፍ አለባቸው። (በገጽ 26 ላይ የሚገኘውን ሥዕል ተመልከት።) ኩላሊት ውስጥ ከገቡ በኋላ ኩላሊታዊ ደም ወሳጁ በኩላሊት የውስጥና የውጭ ንብሮች ላይ ወደሚገኙት ትንንሽ ደም ሥሮች ያሰራጫቸዋል። በደምህ ውስጥ የሚገኙት የተለያዩ ንጥረ ነገሮች በዚህ መንገድ ይበልጥ ሊስተናገዱ ወደሚችሉባቸው ትንንሽ “ሰልፎች” እንዲተላለፉ ይደረጋል።

በመጨረሻ ደሙ እያንዳንዳቸው 40 የሚሆኑ በጣም የተሳሰሩ ትንንሽ የደም ስሮች ወደሚገኙባቸው አነስተኛ የደም ስር ክምችቶች ጋር ይደርሳል። እያንዳንዱ ክምችት ችፍርግ (glomerulus) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ቦውማን ስርጉድa ተብሎ በሚጠራ ባለ ሁለት ንብር ገለፈት የተከበበ ነው። ችፍርጉና ቦውማን ስርጉዱ አንድ ላይ በመሆን ኩሊቴ (nephron) ተብሎ የሚጠራውን የመጀመሪያውን የኩላሊትህን ‘የጥበቃ በር’ ይፈጥራሉ፤ ይህ ክፍል የኩላሊትህ ዋነኛ ማጣሪያ ነው። በእያንዳንዱ ኩላሊት ውስጥ ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ኩሊቴዎች አሉ። ሆኖም በጣም አነስተኛ በመሆናቸው አንዱን ለመመልከት አጉሊ መነጽር መጠቀም ያስፈልጋል!—በገጽ 27 ላይ የሚገኘውን በትልቁ ጎልቶ የቀረበውን የአንድ ኩሊቴ ሥዕላዊ መግለጫ ተመልከት።

ደምህ የሚጣራባቸው ሁለት ደረጃዎች

በደምህ ውስጥ ያሉት የደም ሕዋሳትና ፕሮቲኖች እጅግ አስፈላጊ ናቸው። ለሰውነትህ የኦክስጅን አቅርቦትን፣ መከላከያንና ጥገናን የመሳሰሉ ወሳኝ የሆኑ ግልጋሎቶች ይሰጣሉ። የደም ሕዋሳትና ፕሮቲኖች ከሰውነት እንዳይወገዱ ለማድረግ የመጀመሪያው የማጣራት ሂደት ከሌሎቹ ንጥረ ነገሮች ሁሉ ይለያቸዋል። ይህን ልዩ ተግባር የሚያከናውኑት ቦውማን ስርጉዶች ናቸው። ግን እንዴት?

ችፍርግ ውስጥ የገቡ የደም ስሮች ይከፈሉና በጣም ቀጫጭን ግድግዳዎች ያሏቸው ትንንሽ ፀጉሮዎች (capillaries) ይሆናሉ። ይህም በመሆኑ የደም ግፊት የተወሰነ ውኃና ሌሎች ትንንሽ ሞሊኪውሎችን ከደም ውስጥ በማስወጣት ጥቃቅን በሆኑት የፀጉሮዎቹ ገለፈቶች በኩል ወደ ቦውማን ስርጉድና ከስርጉዱ ጋር ወደተያያዙት ጥቅል ቱቦዎች እንዲገቡ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ቱቦ ጥምዝማዥ ቱቦ (convoluted tubule) በመባል ይታወቃል። ተለቅ ተለቅ ያሉት የፕሮቲን ሞሊኪውሎችና ሁሉም የደም ሴሎች እዚያው ደም ውስጥ ይቀሩና በፀጉሮዎቹ ውስጥ መፍሰሳቸውን ይቀጥላሉ።

አሁን የማጣራት ሂደቱ ይበልጥ ይጠናከራል። ኩላሊትህ ለሰውነትህ ጠቃሚ የሆነ ምንም ነገር እንዳይወጣ መቆጣጠር ይኖርበታል! በዚህ ወቅት በቱቦው ውስጥ የሚፈሰው ፈሳሽ ጠቃሚ የሆኑ የሟሙ ሞሊኪውሎችን እንዲሁም ቆሻሻዎችንና አስፈላጊ ያልሆኑ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ውኃማ ድብልቅ ነው። በቱቦው የውስጠኛ ግድግዳ ላይ የሚገኙት በዚህ ተግባር የተካኑ ሕዋሳት እንደ ውኃ፣ ጨው፣ ስኳር፣ ማዕድናት፣ ቪታሚኖች፣ ሆርሞኖችና አሚኖ አሲድ ያሉትን ጠቃሚ ሞሊኪውሎች ለይተው ያውቃሉ። እነዚህ ነገሮች እንደገና ወደ ቱቦው ግድግዳ ገብተው በዙሪያው ባሉት ፀጉሮዎች ያልፉና ዳግመኛ ወደ ደምህ ይገባሉ። ፀጉሮዎቹ ተጣምረው ትንንሽ ደም መላሽ የደም ስሮች ይሆኑና እነዚህ የደም ሥሮች ደግሞ ጥምረት ፈጥረው ኩላሊታዊ ደም መላሽ የተባለውን ትልቅ የደም ሥር ያስገኛሉ። የተጣራው ደምህ በዚህ የደም ሥር አማካኝነት ከኩላሊትህ ይወጣና ሰውነትህ ሕያው ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ማድረጉን ይቀጥላል።

ቆሻሻዎችን ከሰውነት ማስወገድ

ይሁን እንጂ በቱቦው ውስጥ የሚቀረው ፈሳሽስ? ይህ ፈሳሽ ለሰውነትህ አስፈላጊ ያልሆኑ ንጥረ ነገሮችን እንደያዘ ግልጽ ነው። ፈሳሹ በቱቦው ውስጥ አድርጎ ኮሌክቲንግ ቲዩቢዩል ወይም ኮሌክቲንግ ዳክት ወደሚባለው ትልቅ ቱቦ ሲፈስ በቱቦው ግድግዳ ላይ ያሉት ሌሎቹ ሕዋሳት እንደ አሞኒያ፣ ፖታሲየም፣ ዩሪያና ዩሪክ አሲድ ያሉትን ነገሮች እንዲሁም ትርፍ የሆነውን ውኃ በመልቀቅ ከፈሳሹ ጋር እንዲቀላቀል ያደርጋሉ። የመጨረሻው ውጤት ሽንት ይሆናል ማለት ነው።

በተለያዩ ኩሊቴዎች ውስጥ ያሉት ኮሌክቲንግ ዳክቶች ጥምረት ይፈጥሩና ሽንቱ በትርሽሜ (pyramid) ጫፎች ላይ በሚገኙ ቀዳዳዎች በኩል እንዲወጣ ያደርጋሉ። ሽንቱ ወደ ኩላ ገንዳ (renal pelvis) ይገባና ኩላሊትንና ፊኛን በሚያገናኘው ቱቦ ማለትም በቦየፊኛ (ureter) በኩል ይወጣል። ሽንቱ ከሰውነትህ ከመወገዱ በፊት ፊኛህ ውስጥ ተከማችቶ ይቆያል።

በኩላሊትህ ውስጥ የሚገኙት ከሁለት ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ኩሊቴዎች ያለ አጉሊ መነጽር የማይታዩ ቢሆንም እንኳ የሚያከናውኑት ተግባር እጅግ የሚያስደንቅ ነው። ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ኩሊቴዎች . . . ወደ አምስት ሊትር የሚጠጋ የውኃ ይዘት ያለውን መላውን ደም በየ45 ደቂቃው ያጣራሉ።” የተለያዩ ንጥረ ነገሮች እንደገና ወደ ሰውነት እንዲገቡ ከተደረገና ብዙዎቹ ሂደቶች ከተጠናቀቁ በኋላ አንድ ጤናማ የሆነ አካል በየ24 ሰዓቱ 2 ሊትር ገደማ የሚሆን ቆሻሻ በሽንት መልክ ሊያስወግድ ይችላል። እንዴት ያለ ጥራት ያለውና የተሟላ የማጣራት ሂደት ነው!

ኩላሊቶችህን ተንከባከብ!

ኩላሊትህ ለረጅም ጊዜ የመሥራት ብቃት ያለው ራሱን በራሱ የሚያጸዳና የሚጠብቅ የአካል ክፍል ነው። ይሁን እንጂ ሥራቸውን በሚገባ እንዲያከናውኑ በመርዳት ረገድ አንተም የምታበረክተው ድርሻ ይኖራል። ሰውነትህ ጤናማ እንዲሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ በኩላሊቶችህ ማለፍ መቻል አለበት። እንዲያውም በቂ ውኃ መጠጣት የኩላሊት ኢንፌክሽን እንዲሁም የኩላሊት ጠጠር እንዳይፈጠር ለመከላከል የሚረዳ ዋነኛ መንገድ እንደሆነ ይታመናል።b በተጨማሪም ውኃ መጠጣት ለምግብ መፈጨትና ለስርአተ ልብ ወቧንቧ (cardiovascular systems) እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ በኒው ዮርክ ሎንግ አይላንድ ኮሌጅ ሆስፒታል ውስጥ የዩሮሎጂ ክፍል ሊቀ መንበር የሆኑት ዶክተር ሲ ጎዴክ አመልክተዋል።

ምን ያህል ውኃ መጠጣት ያስፈልጋል? ዶክተር ጎዴክና ሌሎች ብዙ ዶክተሮች እያንዳንዱ ሰው በሌሎች ምግቦችና ፈሳሾች ከሚወስደው ውኃ በተጨማሪ በየቀኑ ቢያንስ ቢያንስ ሁለት ሊትር ውኃ መጠጣት እንዳለበት ይናገራሉ። “አብዛኞቹ ሰዎች በሰውነታቸው ውስጥ በቂ ውኃ አይኖርም” ሲሉ ዶክተር ጎዴክ ለንቁ! መጽሔት ተናግረዋል። ልብህ ወይም ኩላሊትህ የጤና ችግር እስከሌለባቸው ድረስ ውኃ እጅግ ይጠቅማቸዋል በማለት ገልጸዋል። “ሆኖም በቂ ውኃ መጠጣት አለብህ፤ አብዛኞቹ ሰዎች በቂ ውኃ አይጠጡም” ሲሉ ተናግረዋል።

አንዳንዶች ውኃ ውስጥ እንደ ሎሚ ያለ ትንሽ ማጣፈጫ ጨምሮ መጠጣት ደስ ይላቸዋል። ሌሎች ደግሞ የምንጭ ውኃ ወይም ደግሞ በከሰል የተጣራ ውኃ መጠጣት ይመርጣሉ። በዚያም ሆነ በዚህ ምንም ያልተቀላቀለበት ወይም ደግሞ በጣም አነስተኛ የሆነ ማጣፈጫ የገባበት ውኃ ከሌላ መጠጥ ይበልጥ ለኩላሊቶችህ ተስማሚ ነው። እንዲያውም በፍራፍሬ ጭማቂዎችና በጣፋጭ መጠጦች ውስጥ ያለው ስኳር የሰውነታችንን የውኃ ፍላጎት ይጨምረዋል። አልኮል ወይም ካፌይን ያለባቸው መጠጦች ሰውነታችን ብዙ ውኃ እንዲያወጣ ያደርጉታል።

በየቀኑ ሁለት ሊትር ውኃ የመጠጣት ልማድ ማዳበሩ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው። አንደኛ ነገር፣ ብዙ ሰዎች ከወትሮው የበለጠ አሁንም አሁንም ወደ መጸዳጃ ቤት መመላለሱ አመቺ ሆኖ አያገኙትም ወይም ያሳፍራቸዋል። ሆኖም ይህን ተጨማሪ ጥረት ማድረግህ ለሰውነትህ እጅግ ጠቃሚ ነው። በተጨማሪም በቂ ውኃ መጠጣት ጤናህን ለመጠበቅ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ውበት ሊጨምርልህ ይችላል። ዶክተሮች ጥሩ ያመጋገብ ሥርዓት መከተልና ከፍተኛ መጠን ያለው ፈሳሽ መውሰድ ከማንኛውም የቆዳ ቅባት ይበልጥ የቆዳን ውበት ለመጠበቅ እንደሚረዳ ይናገራሉ።

ክፋቱ፣ የውኃ ጥም እንዲሰማን የሚያደርገው የሰውነታችን ሂደት ፍጹም ካለመሆኑም ሌላ ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ ጉድለቱ እየከፋ ይሄዳል። ስለዚህ ሲጠማን ብቻ መጠጣታችን በቂ ነው ብለን እርግጠኛ ልንሆን አንችልም። በቂ ውኃ ስለመጠጣትህ እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? አንዳንዶች ገና በጠዋቱ ሁለት ብርጭቆ ውኃ ይጠጡና በተወሰነ ጊዜ ልዩነት ተጨማሪ ብርጭቆ ውኃ ይጠጣሉ። ሌሎች ደግሞ ውኃውን በሚያሳይ ዕቃ ቀድተው አጠገባቸው በማስቀመጥ ቀኑን ሙሉ ፉት ሲሉ ይውላሉ። የትኛውንም ዘዴ በመጠቀም ንጹሕ ውኃ በብዛት መጠጣትህ ለሕይወትህ እጅግ አስፈላጊ ለሆነው ዕጹብ ድንቅ ማጣሪያ ማለትም ለኩላሊት አድናቆት እንዳለህ የምታሳይበት ጥሩ መንገድ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በ1840ዎቹ መጀመሪያ ላይ ይህን አነስተኛ የሆነ ስርጉድና ተግባሩን የገለጸው እንግሊዛዊው ቀዶ ሐኪምና ሂስቶሎጂስት ዊልያም ቦውማን ነበር። በመሆኑም ስርጉዱ በእሱ ስም ሊሰየም ችሏል።

b የነሐሴ 22, 1993 ገጽ 20–2 እና የመጋቢት 8, 1986 ገጽ 18 ንቁ! (እንግሊዝኛ) እትሞችን ተመልከት።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ኩሊቴ ዋነኛው ማጣሪያ ክፍል

በእያንዳንዱ ኩላሊት ውስጥ ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ኩሊቴዎች አሉ። በአንድ ነጠላ ኩሊቴ ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ ቱቦ በአማካይ 3.05 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ሲኖረው ስፋቱ ደግሞ 0.05 ሴንቲ ሜትር ብቻ ነው። ሆኖም በአንድ ኩላሊት ውስጥ የሚገኙትን ሁሉንም ቱቦዎች መዘርጋት ቢቻል ኖሮ 30 ኪሎ ሜትር ገደማ ይሆኑ ነበር!

ቦውማን ስርጉድ ኩሊቴ ውስጥ ባለው ጥምዝማዥ ቱቦ ጫፍ ላይ የሚገኝ ነው። ይህ ቱቦ ፀጉሮዎች ተብለው በሚጠሩ የተጠላለፉ እጅግ አነስተኛ የደም ስሮች የተከበበ ነው። ቱቦው በኩሊቴ ተጣርተው የተለዩትን ቆሻሻዎችና መርዛም የሆኑ ንጥረ ነገሮች ወደሚ​ያስወግደው ኮሌክቲንግ ዳክት የተባለ ትልቅ ቱቦ ውስጥ ይገባል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኩላሊታዊ ደም መላሽ የተጣራ ደም ወደ ሰውነት መልሶ ያስገባል

ኩላሊታዊ ደም ወሳጅ ያልተጣራ ደም ወደ ኩላሊት ይወስዳል

ኩላሊታዊ ትርሽሜ ሽንትን ወደ ኩላ ገንዳ የሚወስዱ ሾጣጣ መዋቅሮች ናቸው

ልህፅ (cortex) የእያንዳንዱን ኩሊቴ ችፍርግ የያዘ ነው

ኩላ ገንዳ ሽንትን በማጠ ራቀም ወደ ቦየፊኛ የሚያሻግር ማስተላለፊያ ነው

ቦየፊኛ ሽንትን ከኩላሊት ወደ ፊኛ ይወስዳል

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኩሊቴዎች፣ ሁለት ሚልዮን ገደማ የሆኑ የቱቦ ዓይነት ቅርጽ ያላቸው ያለ አጉሊ መነጽር የማይታዩ ማጣሪያዎች ሲሆኑ ደምን ያጣራሉ

ቦውማን ስርጉድ

ችፍርግ

ሽንት ወደ ጥምዝማዥ ቱቦ ከገባ በኋላ ወደ ፊኛ ይሄዳል

ፀጉሮዎች

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ