“እኛ አቁመናል—አንተም ማቆም ትችላለህ!”
በጃፓን የሚገኝ የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
እንደሚባለው በ1500ዎቹ ዓመታት መገባደጃ ላይ የአውሮፓ መርከቦች በጃፓን ወደቦች መልሕቃቸውን ጥለው ይቆሙ ነበር። በእነዚህ መርከቦች ላይ ከተሳፈሩት ሰዎች መካከል “ሆዳቸው ውስጥ እሳት የሚያነዱ” የሚመስሉ ትምባሆ አጫሾች ነበሩ። ይህ አስገራሚ ሁኔታ የፈጠረው የማወቅ ጉጉት በ1880ዎቹ ዓመታት በጃፓን አገር ትምባሆ የማጨስ ልማድ ሥር እንዲሰድ ምክንያት ሆኗል። የትምባሆ ጭስ ያስገረማቸው የእነዚያ ጃፓናውያን ዝርያዎች ዛሬ በዓለም ከሚገኙ ከባድ አጫሾች መካከል ይፈረጃሉ ብሎ ማን አስቦ ነበር?
“ትልቅ ሰው መሆናችን እንዲሰማን ለማድረግና ትላልቅ ሰዎች የሚሰማቸውን ስሜት ለማወቅ ስለፈለግን ነው።”—አኪዮ፣ ኦሳሙና ዮኮ
“ለመክሳት ስለ ፈለግኩ ነበር።”—ሱያ
“ማጨስ የጀመርኩት የማወቅ ጉጉት ስላደረብኝ ነበር።”—ቶሺሂሮ
“ትምባሆ ምንም ዓይነት ጉዳት የሚያስከትልብን አልመሰለንም ነበር።”—ሪዮሃ፣ ጁኒቺና ያሱሂኮ
“ሁለተኛ ልጄን ባረገዝኩበት ጊዜ ይሰማኝ የነበረውን የማቅለሽለሽ ስሜት ለማስወገድ ስል ማጨስ ጀመርኩ።”—ቺዬኮ
“በመሥሪያ ቤት ስብሰባዎች ወቅት የሚያሳፍሩ ሁኔታዎች ሲገጥሙኝ ይህን ስሜቴን ለመደበቅ ስል ማጨስ ጀመርኩ።”—ቶትሱሂኮ
እነዚህ በዚህ አገር የሚገኙ አንዳንድ ሰዎች ለምን ማጨስ እንደጀመሩ ሲጠየቁ የሰጧቸው መልሶች ናቸው። በተለይ ጃፓን በአንዳንድ ሰዎች የአጫሾች ገነት ተብላ እስከ መጠራት መድረሷን ስንመለከት እነዚህን ምክንያቶች መረዳት ከባድ አይሆንም። ይሁን እንጂ ከላይ ስማቸውን የጠቀስናቸው ሁሉ የትምባሆ ሱሳቸውን እርግፍ አድርገው የተዉ መሆናቸው የሚያስደንቅ ነው። የሚኖሩበት አካባቢ ይፈጥርባቸው የነበረውን መሰናክል ስንመለከት ማጨስ ለማቆም መቻላቸው እንደ ቀላል ነገር የሚቆጠር አይደለም። እንዴት ሊያቆሙ እንደቻሉ ለማወቅ ትፈልጋለህ? በመጀመሪያ በጃፓን አገር ትምባሆ ማጨስ ምን ያህል የተስፋፋ ልማድ እንደሆነ እንመልከት።
የትምባሆ አጫሾች ሁኔታ
ለአካለ መጠን ከደረሱ ጃፓናውያን ወንዶች መካከል 56 በመቶ የሚሆኑት አጫሾች ሲሆኑ በአሜሪካ ግን 15 ዓመትና ከዚያ በላይ ከሆናቸው ወንዶች መካከል የሚያጨሱት 28 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ከጃፓናውያን ሴቶች 22 በመቶ የሚሆኑት 34, 000,000 ከሚደርሱት ጃፓናውያን አጫሾች ጎራ የሚመደቡ ከመሆናቸውም በላይ ብዙዎቹ ገና ወጣቶች ናቸው። የትላልቅ ሰዎች ምሳሌነትና በረቀቀ ዘዴ የሚቀርቡ ማስታወቂያዎች ለወጣት አጫሾች ፈጣን እድገት አስተዋጽኦ አድርገዋል። በቴሌቪዥንና በራዲዮ ሲጋራ ማስተዋወቅ በዩናይትድ ስቴትስ የተከለከለው ከሁለት አሥርተ ዓመታት በፊት ሲሆን በጃፓን ግን የተከለከለው በቅርቡ ነው።
ከዚህም በላይ በጃፓን አገር በየጎዳና ማዕዘናት ከሚገኙ የመሸጫ መሣሪያዎች ሲጋራ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። የሲጋራው ፓኮ እጃቸው ከገባ በኋላ በፓኮዎቹ ላይ የተጻፈውን እምብዛም አሳማኝ ያልሆነ የይስሙላ የማስጠንቀቂያ መልእክት ልብ የሚሉት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። በፓኮዎቹ ላይ የተጻፈው ማስጠንቀቂያ “ብዙ አናጭስ፣ ጉዳት ሊያስከትልብን ይችላል” የሚል ብቻ ሊሆን ይችላል። በትምባሆ ምክንያት የሚመጡት ከባድ መዘዞች በብዛት የማይታወቁ ከመሆናቸው በተጨማሪ የበርካታ እውቅ ሰዎች መጥፎ ምሳሌ መሆን ጃፓናውያን እንዲያጨሱ አደፋፍሯል። ምንም ነገር አይደርስብንም ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል።
የትምባሆ ተቃዋሚዎች ጃፓን ዜጎቿ ማጨስ እንዲያቆሙ በማድረግ ረገድ ግድየለሽ ስለ መሆኗ በምሬት መናገራቸው አያስደንቅም። ይሁን እንጂ የትምህርት ባለሞያዎች ማጨስ በጤንነትና በሕይወት ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት ሰዎችን ማስጠንቀቅ በጣም አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ጀምረዋል። አዎን፣ ጃፓናውያን አጫሾችም በሌሎች አገሮች እንደሚኖሩት አጫሾች የማቅለሽለሽ ስሜት ይሰማቸዋል፣ ትንፋሻቸው እጥር እጥር ይልባቸዋል፣ ያስላቸዋል፣ ሆዳቸውን ያማቸዋል፣ ምግብ ያስጠላቸዋል፣ ጉንፋን ይመላለስባቸዋል፣ ከጊዜ በኋላ ደግሞ በሳንባ ካንሰር፣ በልብ በሽታ ወይም በሌላ ችግር ምክንያት ሕይወታቸው በአጭሩ ይቀጫል።
ከሚያዝያ 1, 1985 ጀምሮ ለበርካታ ዓመታት በመንግሥት ንብረትነት ይንቀሳቀስ የነበረው የትምባሆ ኢንዱስትሪ ወደ ግል ይዞታ ተዛውሯል። ቢሆንም አሁንም ከመንግሥት ጋር የቅርብ ትስስር ስላለው የአጫሾች ቁጥር እንዲቀንስ የሚወሰዱ እርምጃዎች ሁሉ እንቅፋት ያጋጥማቸዋል። ፀረ ትምባሆ ቡድኖች ጃፓንን የአጫሾች ምሽግ ብለው የሚጠሩት በዚህ ምክንያት ነው። በተጨማሪም ዘ ዴይሊ ዮሚዩሪ በዚህ አገር የሚገኙ ዶክተሮች ጃፓን “ማጨስን የምታበረታታ አገር ነች” የሚል ምሬት እንዳሰሙ ሪፖርት ያደረገው በዚህ ምክንያት ነው።
አንዳንዶች እንዴት ሊያቆሙ እንደቻሉ ለመመልከት “እንዴት ለማቆም እንደቻልን” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
ልታቆም የምትችለው እንዴት ነው?
በሣጥኑ ውስጥ እንደተጠቀሱት ያሉ የቀድሞ አጫሾች የሚሰጡት ምክር ሲጠቃለል ማጨስ እንድታቆም የሚገፋፋ ምክንያት ይኑርህ የሚል ነው። ይህን እርምጃ እንድትወስድ ሊገፋፋህ የሚችለው ከሁሉ የተሻለው ነገር ለአምላክ ያለህ ፍቅርና እርሱን ለማስደሰት ያለህ ፍላጎት ነው። ሌላው ጥሩ ምክንያት ለሰዎች ያለህ ፍቅር ነው። አንድ ግብ አውጣና ያንን ግብህን የሙጥኝ ብለህ ያዝ። ማጨስ ለማቆም መወሰንህን አሳውቅ። ለወዳጆችህ ንገራቸው። ቤተሰቦችህ እርዳታ እንዲያደርጉልህ ጠይቅ። ከቻልክ በአንድ ጊዜ አቁም። ከሚጨስበት አካባቢ ለመራቅ የተቻለህን ሁሉ አድርግ።
መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት ላይ ከሆንክ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ብዙ ጊዜ አብረህ ለማሳለፍ ሞክር። ብዙ ጊዜ ከእነርሱ ጋር የምታሳልፍ ከሆነ የማጨስ ፍላጎትህ እየጠፋ ይሄዳል። በሌላ በኩል ደግሞ የይሖዋ ምሥክር ከሆንክና አንድን የሚያጨስ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት ላይ ከሆንክ ተስፋ ቆርጠህ ጥናቱን አታቋርጥ። ከመጥፎ ልማዱ ይበልጥ ይሖዋን እንዲወድ እርዳው።
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
“እንዴት ለማቆም እንደቻልን”
ሚዬኮ:- “ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በጀመርኩበት ጊዜ ማጨስ ለማቆም እንደማልችል እርግጠኛ ነበርኩ። ማጥናት የፈለግኩበት ዓላማ ቢያንስ ልጆቼ ሕይወት የሚያስገኘውን መንገድ እንዲያውቁ ለማስቻል ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ወላጅ ለልጆቹ ጥሩ አርዓያ መሆን እንደሚገባው ስለተገነዘብኩ ይሖዋ እንዲረዳኝ አጥብቄ መጸለይ ጀመርኩ። ከጸሎቴ ጋር የሚስማማ ተግባር ለመፈጸም ከፍተኛ ጥረት ጠይቆብኛል። ለጥቂት ጊዜም በጣም ከብዶኝ ነበር። ይሁን እንጂ በመጨረሻ ከዚህ ቆሻሻ ልማድ ስላቀቅ ንጹሕ ሕሊና በማግኘቴ የተሰማኝን ጥሩ ስሜት ፈጽሞ አልረሳውም።”
ማሳዩኪ:- “በቀን ሦስት ፓኬት ሲጋራ አጨስ የነበርኩት ሰው ብዙ ተደጋጋሚ ሙከራ ካደረግኩ በኋላ የመጨረሻዋን ሲጋራዬን አጥፍቼ ከትምባሆ ጋር ተቆራረጥኩ። ቤተሰቤ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ወዳጆቼና ይሖዋ አምላክ እንዳቆም ረድተውኛል። በምሠራበት ባንክ ማጨስ ማቆሜን ያመነ ሰው አልነበረም። ለደንበኞቻችን ክብር ስንል የባንክ ሥራ በሚከናወንበት አካባቢ የሚሠሩ ሁሉ በሥራ ሰዓት እንዳያጨሱ ሐሳብ አቀረብኩ። ከሠራተኞቹ 80 በመቶ የሚሆኑት አጫሾች ቢሆኑም የሰጠሁት ሐሳብ ተቀባይነት አገኘ። ይህ ልማድ በአሁኑ ጊዜ በባንካችን 260 ቅርንጫፎች እየተሠራበት ነው።”
ኦሳሙ:- “እውነትን የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ መማር ስጀምር ማጨስ ማቆም እንዳለብኝ አወቅኩ። አንድ ዓመት ያህል ፈጅቶብኛል። ካቆምኩ በኋላም ቢሆን ለስድስት ወራት ያህል ከማጨስ ፍላጎቴ ጋር ታግዬአለሁ። ማጨስ የማቆም ልባዊ ፍላጎት ሊኖረኝ እንደሚገባ አውቅ ነበር።”
ቶሺሂሮ:- “በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ልቤ በጣም ተነክቶ ስለነበረ ቢያንስ ማጨስ የማቆም መሥዋዕትነት መክፈል እንደሚኖርብኝ ተሰማኝ።”
ያሱሂኮ:- “ይሖዋ አምላክን ለመታዘዝና ማጨስ ለማቆም ያደረግኩት ውሳኔ ሕይወቴን አትርፎልኛል። አንድ ቀን እሠራበት የነበረው ክፍል ከተቀደደ ቧንቧ በሚወጣ የፕሮፔን ጋዝ ተሞላ። እንደ ድሮው ቢሆን ኖሮ ሲጋራዬን ስለኩስ ከፍተኛ ፍንዳታ ይፈጠር ነበር። ከጥቂት ቀናት በፊት ማጨስ አቁሜ ስለነበረ ግን በሕይወት ቆይቼ ታሪኬን ለመናገር ችያለሁ።”
አኪዮ:- “አልፎ አልፎ የማቅለሽለሽ ስሜት ሲሰማኝ ማጨሴ ጉዳት እያስከተለብኝ እንዳለ ጠረጠርኩ። ቢሆንም አላቆምኩም። ማጨስ ስለሚያስከትለው ጉዳት በሐቅ ላይ የተመሠረተ መረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘሁት ሚስቴ የይሖዋ ምሥክር ከሆነች በኋላ ነበር። ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩና አንድ አጫሽ የሚጎዳው ራሱን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቹን ጭምር እንደሆነ ከመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ተማርኩ። ወዲያው አቆምኩ!”
ሪዮሂ:- “ሲጋራ ትገዛልኝ የነበረችው ባለቤቴ ነበረች። በአንድ ጊዜ 20 ፓኬት ትገዛለች። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ካጠናች በኋላ ግን እንደሚጎዳኝ የምታውቀውን ነገር ልትገዛልኝ ፈቃደኛ አልሆነችም። በዚህ ምክንያት የራሴን የትምባሆ ሱቅ ከፈትኩ። በቀን ሦስት ፓኬት ተኩል አጨስ ነበር። ከጊዜ በኋላ ከምሥክሮቹ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። ወዲያው በመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥሩ ንግግር የመስጠት ችሎታ ለማዳበር ፈለግኩ። በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተካፋይ ለመሆን እንድችል ማጨስ አቆምኩ።”
ጁኒቺ:- “የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ትንሿ ልጄ በሕይወት መቆየቴ በጣም አሳስቧት ነበር። ማጨስ እንደማቆም ቃል እንድገባላት ስላደረገችኝ አቆምኩ።”
ሱያ:- “ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መንግሥት አዳራሽ በሄድኩበት ጊዜ ወዲያው እንደገባሁ የሲጋራ መተርኮሻና ክብሪት እንዲሰጠኝ ጠየቅኩ። በዚያ ቦታ አንድም የሚያጨስ ሰው እንደሌለ ሲነገረኝ በጣም ተደነቅኩ። ማጨስ ማቆም እንዳለብኝ ተረዳሁ። በሆስፒታል ያሳለፍኳቸው ስምንት የሥቃይ ቀናት ዳግመኛ ሲጋራ ማጨስ ብጀምር እንደገና ለማቆም የማደርገው ጥረት ተመሳሳይ ሥቃይ እንደሚያስከትልብኝ እንድገነዘብ አድርገውኛል።”
ዮኮ:- “በመጽሔቶችና በሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎች ላይ ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ የሚወጡትን ጽሑፎች አጠናሁ። ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ሊቸነከር ሲል የተሰጠውን አደንዛዥ ዕፅ አልወስድም እንዳለ ተገነዘብኩ። ንጹሕ የስሙ አወዳሽ ለመሆን እንደምፈልግ ለይሖዋ አምላክ በጸሎት ነገርኩት። ከዚያ ወዲህ አጭሼ አላውቅም። በአካባቢ ያሉ ሰዎች ሲያጨሱ ጭሱን የመሳብ ፍላጎት ያድርብኛል። ሆኖም የማጨስ ፍላጎቴ እንዲያገረሽብኝ ስለማልፈልግ ቶሎ ብዬ ከአካባቢው እርቃለሁ።”
እነዚህ የቀድሞ አጫሾች በሙሉ ሁለተኛ ላለማጨስ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። አንተስ ከዚህ ልማድ ለመላቀቅ የምትፈልግ አጫሽ ነህ?
ሚዬኮ
ኦሳሙ
ያሱሂኮ
አኪዮና ባለቤቱ ሳቺኮ
ጁኒቺና ልጁ መሪ
ዮኮ