የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 7/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የተበከለ ደም?
  • ከግልፍተኛ አሽከርካሪዎች መራቅ
  • ሙዚቃን በማስጮህ ማምለጫ አድርጎ መጠቀም
  • ሕፃን ልጅዎን ያነጋግሩ
  • ማጨስ በቢልዮን ዶላር የሚቆጠር ኪሳራ ያስከትላል
  • ዝቅተኛ የወሊድ ቁጥር የሚያስከትለው ውጤት
  • ድንገተኛ አደጋ እንጂ ዕድል አይደለም
  • የምትናገረውን አድማጭ ጆሮ እንዲያገኝ አድርግ
  • የቋንቋ መሞት
  • ልብህን ጠብቅ
  • የመምረጥ መብት አለህ
    ደም ሕይወትህን ሊያድን የሚችለው እንዴት ነው?
  • ጤናማ ያልሆነ የአኗኗር ዘይቤ ኪሣራው ምን ያህል ነው?
    ንቁ!—1998
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—1996
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—1998
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 7/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

የተበከለ ደም?

በኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ እየታተሙ የሚወጡ ዘጠኝ ጋዜጦች “ከጥር 1991 እስከ ታኅሣሥ 1996 ባለው ጊዜ ውስጥ በኒው ዮርክ/ኒው ጀርሲ ሆስፒታል ደም ለወሰዱ ሁሉ” በሚል ርዕስ በቅርቡ አንድ ማስታወቂያ ይዘው ወጥተው ነበር። ማስታወቂያውን ያወጣው የኒው ዮርክ የደም ማዕከል የማስታወቂያው ዓላማ በ1990ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ደም የወሰዱ ሰዎች የወሰዱት ደም ንጹሕ መሆኑን እንዲገነዘቡ ለማድረግ እንደሆነ ቢናገርም ማስታወቂያው የፈጠረው ስሜት ግን የተገላቢጦሽ ሳይሆን አይቀርም። ለምን? አንዱ ምክንያት በማስታወቂያው ላይ የሰፈረው የሚከተለው ማስጠንቀቂያ ነው:- “በዚያ ወቅት ደም የወሰዱ ሰዎች እንደ ኤች አይ ቪና ሄፐታይተስ ባሉ በደም በሚተላለፉ በሽታዎች ሊለከፉ ይችላሉ።”

ከግልፍተኛ አሽከርካሪዎች መራቅ

“ግልፍተኛ አሽከርካሪዎችን አቅልሎ መመልከት አይገባም” በማለት አንድ የቀድሞ የመኪና እሽቅድምድም ተወዳዳሪ ፍሊት ሜንቴናንስ ኤንድ ሴፍቲ ሪፖርት ለተባለ መጽሔት አስተያየቱን ሰጥቷል። ረጋ ያለ መንፈስ መያዝና ጉዳት ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ሁኔታዎች መራቅ ግልፍተኛ አሽከርካሪዎች ሊፈጥሩት ከሚችሉት አደጋ ራስን ለመጠበቅ ሊረዳ ይችላል። ራስን ከአደጋ እንዴት መከላከል እንደሚቻል ሐሳብ የሚለግሱ ሰዎች የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥተዋል:-

◼ በምታሽከረክርበት ጊዜ የጨዋ ባሕርይ ይኑርህ።

◼ ግልፍተኛ አሽከርካሪ ሲያጋጥምህ ለአደጋ የማያጋልጥህ ከሆነ መንገድ ልቀቅለት።

◼ በጣም ተጠግተህ በማሽከርከር ወይም ለመሽቀዳደም በመሞከር እልህ አትጋባ።

◼ ለዛቻ ወይም ለስድብ ምንም ምላሽ አትስጥ እንዲሁም የተሳሳተ ግምት የሚያሳድር የሰውነት እንቅስቃሴ አታሳይ።

◼ ቁጡ አሽከርካሪን አለማየቱ ይመረጣል።

◼ መኪናህን አቁመህ ከሌላ አሽከርካሪ ጋር አተካራ አትግጠም።

ሙዚቃን በማስጮህ ማምለጫ አድርጎ መጠቀም

ዶክተሮች ሙዚቃን ከልክ በላይ ማስጮህ “በመላው ሰውነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር” ቢያስጠነቅቁም ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ብዙ ወጣቶች አለ ዎክማን ለመኖር የተቸገሩ ይመስላሉ ሲል ፕቺያቹካ የተባለው ሳምንታዊ የፖላንድ ጋዜጣ ዘግቧል። ይህ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው? አንዳንዶች ዎክማን የሚጠቀሙት “ራሳቸውን ከአካባቢያቸው ለማግለል ነው። ድምፀ ራስ (headphones) ያደረገ ወጣት የወላጆቹን ንዝንዝ አይሰማም ወይም ደግሞ ወላጆቹ አንድ ነገር እንዲያደርግ በሚጠይቁት ጊዜ መልስ አይሰጥም” ይላል ጋዜጣው። በተጨማሪም ፕቺያቹካ ሙዚቃን ከልክ በላይ ማስጮህ “ድካም፣ ራስ ምታት፣ ሐሳብን የማሰባሰብ ችግር ወይም የእንቅልፍ እጦት” ሊያስከትል እንደሚችል በመግለጽ ወላጆች ልጆቻቸው ዎክማን እንዳይጠቀሙ ከመከልከል ይልቅ በልክ እንዲያደርጉት ሊያስተምሯቸው እንደሚገባ ይመክራል። “አልፎ አልፎ ዎክማኑን ከልጆቻችሁ ተውሳችሁ ውሰዱ” ይላል ጋዜጣው። “እንዲህ ማድረጋችሁ ልጆቻችሁ ከድምፀ ራሱ ዕረፍት እንዲያገኙ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ የልጆቻችሁን ዓለም ለማወቅ ያስችላችኋል።”

ሕፃን ልጅዎን ያነጋግሩ

ሕፃን ልጆችን በየቀኑ ለ30 ደቂቃ ያክል ማነጋገር የማሰብና የቋንቋ ችሎታቸውን በእጅጉ ያሻሽለዋል በማለት የለንደኑ ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቧል። ተመራማሪዎች የዘጠኝ ወር ዕድሜ ባላቸው በ140 ሕፃናት ላይ ጥናት አድርገው ነበር። ጥናቱ ከተካሄደባቸው ሕፃናት ወላጆች መካከል ግማሽ ያህሉ ልጆቻቸውን ማነጋገር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተነግሯቸው ነበር። የተቀሩት ወላጆች ግን ምንም አልተነገራቸውም። ከሰባት ዓመት በኋላ “ልጆቻቸውን [እንዲያነጋግሩ] ሐሳብ የቀረበላቸው ወላጆች ልጆች አማካይ የማሰብ ችሎታቸው ከተቀሩት ወላጆች ልጆች በአንድ ዓመት ከሦስት ወር ልቆ የተገኘ ሲሆን” የቋንቋ ችሎታቸውም “በሚያስደንቅ ሁኔታ በልጦ እንደተገኘ” ሪፖርቱ ገልጿል። በደረሰው ማኅበራዊ ለውጥ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ ያሉት ወላጆች ልጆቻቸውን በማነጋገር የሚያሳልፉት ጊዜ በድሮ ጊዜ ከነበሩት ወላጆች በጣም ያነሰ እንደሆነ ዶክተር ሳሊ ዋርድ የተባሉት ተመራማሪ ገልጸዋል። ለምሳሌ ያህል በርካታ ቁጥር ያላቸው እናቶች ተቀጥረው የሚሠሩ ከመሆናቸውም በላይ በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ እርስ በርስ መነጋገር ቀርቶ በምትኩ የቪዲዮ ፊልም መድረኩን ይዟል።

ማጨስ በቢልዮን ዶላር የሚቆጠር ኪሳራ ያስከትላል

በብዙ አገሮች የአጫሾች ቁጥር በመቀነስ ላይ የሚገኝ ቢሆንም በስዊዘርላድ ግን ምንም ዓይነት የመቀነስ አዝማሚያ እንደማይታይበት በርን ኦበርላንድ የተባለ ጋዜጣ ገልጿል። አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የስዊዘርላንድ ሕዝብ ያጨሳል። ማጨስ በሚያስከትለው ጠንቅ ሳቢያ በየዓመቱ ከ8,000 የሚበልጡ ሰዎች የሚሞቱ ሲሆን በኤድስ፣ በሄሮይን፣ በኮኬይን፣ በአልኮል መጠጥ፣ በእሳት አደጋ፣ በመኪና አደጋ፣ በነፍስ ግድያና ራስን በራስ በማጥፋት የሚሞቱት ሰዎች አንድ ላይ ቢደመሩ እዚህ አኃዝ ላይ አይደርሱም። ስዊዘርላንድ ውስጥ በሚገኝ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ፌደራል ክፍል የቀረበ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በ1995 ለትምባሆ ፍጆታ የወጣው ማኅበራዊ ወጪ አሥር ቢልዮን የስዊስ ፍራንክ ሲሆን ይህም ከስድስት ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር የሚበልጥ ነው። ጥናቱ ለሕክምናና በሐኪም ቤት ለሚሰጥ እንክብካቤ የወጣውን ወጭ፣ በሥራ ቦታ የደረሰውን ኪሣራ፣ አጫሽ ህሙማንና እነርሱ የሚያስተዳድሯቸው ሰዎች የደረሰባቸውን ጉስቁልናና የሟች ቤተሰብ አባላት የሚደርስባቸውን ሥቃይ በገንዘብ ለመተመን ሞክሯል።

ዝቅተኛ የወሊድ ቁጥር የሚያስከትለው ውጤት

‘በአሁኑ ጊዜ በኢንዱስትሪ በበለጸገው ዓለም ውስጥ ዝቅተኛ የወሊድ ቁጥር ስጋት እየፈጠረ ነው’ ሲል በፓሪስ እየታተመ የሚወጣው ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪብዩን ዘግቧል። ለምን? ምክንያቱም ይህ ሁኔታ ውሎ አድሮ በዕድሜ የገፉ ሰዎችን የሚጦሩ በቂ ወጣቶች እንዳይኖሩ የሚያደርግ በመሆኑ ነው። ለምሳሌ ያህል በበርካታ የአውሮፓ አገሮች ከ60 ዓመት በላይ የሆነው ሕዝብ ቁጥር ከ20 ዓመት በታች ከሆኑት ወጣቶች ቁጥር የሚበልጥበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የትዳር ጓደኛሞች አገር ለመጎብኘት፣ በሥራ መስክ ዕድገት ለማግኘት ወይም ትምህርታቸውን ለማሻሻል ሲሉ ልጆች የሚወልዱበትን ጊዜ የሚያራዝሙ መሆኑ በዕድሜ ለገፉ ሰዎች ቁጥር መብዛት እንደ ምክንያት ከተጠቀሱት ነገሮች አንዱ ነው። ሌሎቹ የተጠቀሱት ምክንያቶች ደግሞ ልጆች መውለድ “ሸክም” እንዲሆን ወይም “አስቸጋሪ ሁኔታ” እንዲፈጥር የሚያደርጉ የኢኮኖሚ ተጽዕኖዎች መኖራቸውና ሰዎች ከቀድሞ በበለጠ ረጅም ዕድሜ መኖር መቻላቸው ነው።

ድንገተኛ አደጋ እንጂ ዕድል አይደለም

ብራዚል ውስጥ በየዓመቱ ቢያንስ ቢያንስ 22,000 የሚሆኑ ሕፃናትና በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በድንገተኛ አደጋዎች ሳቢያ ይሞታሉ ሲል የብራዚል የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት አድርጓል። የአብዛኞቹን ሕይወት የሚቀጥፉት የትራፊክ አደጋዎች ናቸው። ይሁን እንጂ የብራዚል የሕፃናት ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ሊንኮን ፍሬሪ “ድንገተኛ አደጋዎች እንደ ዕድል መታየታቸው ቀርቶ ሊወገዱ የሚችሉ ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ብሔራዊ የአደጋ መከላከል ዘመቻ አስተባባሪ የሆኑት ቴሬዛ ኮስታ ‘ባለፉት 15 ዓመታት መንግሥት በወሰዳቸው እርምጃዎች የተነሳ በተቅማጥ፣ በመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽኖችና በሌሎች ተላላፊ በሽታዎች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር የቀነሰ’ በመሆኑ የአደጋ መከላከል እርምጃዎችም የብዙዎችን ሕይወት ሊታደጉ እንደሚችሉ አመልክተዋል።

የምትናገረውን አድማጭ ጆሮ እንዲያገኝ አድርግ

የምትናገረው ምንም ያክል ቁም ነገር ያዘለ ቢሆን አነጋገርህ ለሰዎች የማይጥም ከሆነ በርካታ ሰዎች ለማዳመጥ አይገፋፉም በማለት የድምፅ ሊቅ የሆኑት ዶክተር ሊሊያን ግላስ ይናገራሉ። በደቡብ አፍሪካ እየታተመ የሚወጣው ዘ ሲትዝን የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ማጉተምተም፣ የሰዋስው ግድፈት፣ አንድ ዓይነት የድምፅ ቃና፣ በጣም በፍጥነት መናገር፣ ጸያፍ አነጋገርና እኔ ብቻ ካልተናገርኩ የሚል መንፈስ አድማጭን ያርቃል። በሌላው በኩል ደግሞ አድማጮችን ዘና ለማድረግ ፈገግታ የምታሳይ፣ በግልጽና በዝግታ የምትናገር፣ የአድማጮችን ዓይን እያየህ የምትናገርና አድማጮች አስተያየታቸውን ሲሰነዝሩ ሳታቋርጣቸው በጥንቃቄ የምታዳምጥ ከሆነ የምትናገረውን ማዳመጣቸው አይቀርም። “ከመናገርህ በፊት አስብ” ሲል ጽሑፉ አክሎ ይገልጻል፤ “እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ልትናገር የፈለግከውን ነገር በልበ ሙሉነት መናገር ትችላለህ።”

የቋንቋ መሞት

ባሉበት ማኅበረሰብ ውስጥ ኢያክ የተባለው የአላስካ ቋንቋ የመጨረሻ ተናጋሪ የሆኑት ቺፍ ማሪያ ስሚዝ ጆንስ “ቋንቋውን ለልጆቼ ሳላስተምር በመቅረቴ አንዳንድ ጊዜ በራሴ በጣም እናደዳለሁ” በማለት ተናግረዋል። በዓለም ዙሪያ ከሚነገሩት 6,000 ከሚያክሉት ቋንቋዎች መካከል ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚሆኑት በሚቀጥለው ምዕተ ዓመት ከምድር ገጽ ሊጠፉ እንደሚችሉ በአሁኑ ጊዜ ያለው አዝማሚያ ያሳያል። በአንድ ወቅት 250 ቋንቋዎች ይነገርባት በነበረችው በአውስትራሊያ በአሁኑ ወቅት ያሉት ቋንቋዎች ከ20 አይበልጡም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ኒውስዊክ መጽሔት በሰጠው አስተያየት መሠረት “እንግሊዝኛና ሌሎች ‘ብዙ ተናጋሪ ያላቸው’ ቋንቋዎች እየተስፋፉ በመምጣታቸው” ሌሎች ቋንቋዎች እየተረሱ ነው። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት የታተመው አትላስ ኦቭ ዘ ዎርልድስ ላንጉዌጅስ ኢን ዴንጀር ኦቭ ዲስአፒሪንግ የተባለው መጽሐፍ አዘጋጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ስቴፈን ቩርም “ለምንም ነገር ስለማይጠቅሙህ ጥቂት ተናጋሪ ያላቸውን ‘አናሳ ቋንቋዎች’ መርሳት አለብህ የሚል በሰፊው የተዛመተ አመለካከት አለ” በማለት ተናግረዋል።

ልብህን ጠብቅ

“ሞቃታማ የአየር ጠባይ ለልብ ድካም በሽታ እንደሚያጋልጥ ካወቅን ሰነባብተናል። ይሁን እንጂ በአሁን ወቅት ቀዝቃዛ የአየር ጠባይም ለተመሳሳይ አደጋ እንደሚያጋልጥ ተገንዝበናል” በማለት የልብ ሕክምና ባለሙያና ኦንታሪዮ ካናዳ የሚገኘው የልብና የስትሮክ ተቋም ቃል አቀባይ የሆኑት ዶክተር አንቶኒ ግራሃም ይናገራሉ። ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ፈረንሳይ ውስጥ በሚኖሩ 250,000 ወንዶች ላይ የተደረገ አሥር ዓመት የፈጀ አንድ ጥናት እንዳመለከተው አማካዩ የሙቀት መጠን አሥር ዲግሪ ሲጨምር ወይም ሲቀንስ “ልብ ድካም ለመጀመሪያ ጊዜ ሊከሰት የሚችልበት አጋጣሚ 13 በመቶ ይጨምራል።” የሙቀት መጠን ሲቀንስ ደም በውስጡ ያከማቸውን የሙቀት መጠን ጠብቆ ለማቆየት ሲል ከቆዳ ወደ ውስጠኛ የሰውነት ክፍሎች ስለሚሄድ የልብ ሥራ ከባድና ፍጥነት የሚጠይቅ ይሆናል። በተለይ ደግሞ ሰዎች በሥራ ሲወጠሩ ወይም ተገቢ ልብስ ሳይለብሱ ሲቀሩ ለአደጋው ይበልጥ የተጋለጡ ይሆናሉ። ዶክተር ግራሃም ሲያስጠነቅቁ “አምስት ወር ሙሉ ቤትህ ውስጥ ተጀቡነህ ከሰነበትህ በኋላ ድንገት ተነስተህ በረዶ መዛቅ ካልጀመርኩ ማለት አትችልም። በመጀመሪያ ቀስ በቀስ ራስህን ማለማመድ ይኖርብሃል።”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ