ከዕፅ ጋር የሚደረገውን ውጊያ በድል አድራጊነት ማጠናቀቅ ይቻል ይሆን?
ከዕፅ ጋር የሚካሄደውን ጦርነት በድል አድራጊነት መወጣት በጣም ክቡር የሆነ ዓላማ ቢሆንም ቀላል አይደለም። የተከለከሉ ዕፆችን ባቡር የሚያንቀሳቅሱት ሁለት ኃይለኛ ሞተሮች ናቸው። እነርሱም አቅርቦትና ተፈላጊነት ናቸው። የፖሊስ ሠራዊትና መንግሥታት የዕፆችን አቅርቦት ለመግታት ሲጣጣሩ አንድ መቶ ዓመት ሊሞላ ምንም ያህል አልቀረም። ግምታቸው በጣም ቀላል ነበር:- ዕፆች ካልኖሩ የዕፅ ሱሰኞች አይኖሩም።
በአቅርቦቱ ላይ ጥቃት መሰንዘር
ይህን ዓላማ ለማሳካት ፀረ ዕፅ የፖሊስ ኃይሎች በርካታ የዕፅ ጭነቶችን ለመውረስ ችለዋል። በአገሮች መካከል በተፈጠረው ትብብር እውቅ የዕፅ አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል። ይሁን እንጂ የፖሊሶች ቁጥጥር አንዳንድ የዕፅ አዘዋዋሪዎች የነበሩበትን አካባቢ እንዲለውጡ ወይም ሌሎች ገበያዎችን እንዲፈልጉ ወይም ደግሞ አዳዲስ ዘዴዎችን እንዲፈልጉ ያስገድዳቸው እንደሆነ እንጂ ፈጽሞ ሊያስቆማቸው አልቻለም። አንድ የናርኮቲክ ኤክስፐርት “የዕፅ አዘዋዋሪዎች ገደብ የሌለው ገንዘብ እስከኖራቸውና እኛ ደግሞ ባጀት ለማስጨመር ከፍተኛ ትግል ማድረግ እስካለብን ድረስ ፈጽሞ ልንቋቋማቸው አንችልም” ብለዋል።
በጅብራልታር ፖሊስ ሠራዊት የወንጀል መከላከል መኮንን የሆኑት ጆ ዴ ላ ሮሳ በአፍሪካና በአይቤሪያ ባሕረ ገብ መሬት መካከል የሚደረገውን ዕፅ የማዘዋወር እንቅስቃሴ መቆጣጠር ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ለንቁ! ዘጋቢ ተናግረዋል። “በ1997 ወደ 400 ኪሎ የሚያክል የካናቢስ ሙጫ ለመያዝ ችለናል። ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ከዕፅ አዘዋዋሪዎች በቀጥታ ተይዞ የተወረሰ ሳይሆን ባሕር ላይ ብቻውን ሲንሳፈፍ ወይም በባሕር ሞገድ ተወስዶ በባሕር ዳርቻዎች ላይ የተገኘ ነው። በየዓመቱ በጅብራልታር የባሕር ወሽመጥ የሚያልፈው የዕፅ መጠን ምን ያህል ብዙ እንደሆነ ከዚህ መረዳት ትችላለህ። ለመያዝ የቻልነው የተራራውን ጫፍ ብቻ ነው። ከአፍሪካ ወደ ስፔይን የሚያጓጉዙት ዕፅ ጫኞች የኮንትሮባንድ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣኖች ካሏቸው ጀልባዎች በጣም የሚፈጥኑ ጀልባዎች አሏቸው። ሊያመልጡ እንደማይችሉ ከተሰማቸው ደግሞ ዕፆቹን ወደ ባሕር ስለሚጥሉ እነርሱን ለመክሰስ የሚያስችል ማስረጃ ማግኘት ያቅተናል።”
በሌሎች የዓለም ክፍሎችም ፖሊሶች ተመሳሳይ ችግር ያጋጥማቸዋል። ተራ መንገደኞች መስለው የሚታዩ ሰዎች፣ ቀላል ክብደት ብቻ ለማመላለስ የሚያገለግሉ አውሮፕላኖች፣ የመርከብ ላይ ኮንቴይነሮች፣ ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች ሳይቀሩ ዕፆችን ውቅያኖስ አቋርጠው ወይም ከድንበር ወደ ድንበር አስርገው ያስገባሉ። አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንዳሰላው “ዕፅ የማዘዋወርን ሥራ አትራፊነት በበቂ መጠን ለመቀነስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚጓጓዘው ዕፅ ቢያንስ 75 በመቶ የሚሆነውን መያዝ ያስፈልጋል።” ባሁኑ ደረጃ በኮኬይን ረገድ መያዝ የተቻለው 30 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ሲሆን በሌሎች ዕፆች ረገድ ደግሞ አኃዙ ከዚህ በጣም ያነሰ ነው።
ታዲያ መንግሥታት የካናቢስ ተክሎችን፣ የኦፒየም ፖፒዎችንና የኮካ ቁጥቋጦዎችን ባሉበት በማውደም ችግሩን ከመነሻው የማይቀጩት ለምንድን ነው? የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቅርቡ እንዲህ ያለ እርምጃ እንዲወሰድ ቢያሳስብም ይህን ማድረግ ቀላል ሆኖ አልተገኘም። ካናቢስ በማንኛውም ሰው ጓሮ ሊበቅል ይችላል። በአንዲዝ ተራራዎች የሚገኝ አንድ ዋነኛ የኮካ አብቃይ አካባቢ “ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ የሆነ አካባቢ” እንደሆነ ተገልጿል። ዋነኛ የኦፒየምና የሄሮይን ምንጭ በሆኑት በአፍጋኒስታንና በበርማ ሩቅ አካባቢዎችም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው።
ከዚህም ሌላ የዕፅ አዘዋዋሪዎች ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ወደሄደው ሰው ሠራሽ ዕፆች ዞር ሊሉ መቻላቸው ሁኔታውን ይበልጥ አስቸጋሪ አድርጎታል። በማንኛውም የዓለም ክፍል በኅቡዕ የተቋቋሙ ቤተ ሙከራዎች እነዚህን ሰው ሠራሽ ዕፆች በቀላሉ ማምረት ይችላሉ።
የፖሊስ ቁጥጥር በማጠናከርና የእሥራት ቅጣት በመጨመር የዕፁን ንግድ መግታት ይቻል ይሆን? የዕፅ አስተላላፊዎችና የዕፅ ሱሰኞች ቁጥር በጣም ከፍተኛ ሲሆን የፖሊሶች ቁጥር ግን በጣም አነስተኛ በመሆኑ ይህ ዘዴ ውጤት ሊያስገኝ አልቻለም። ለምሳሌ ያህል ዩናይትድ ስቴትስ ሁለት ሚልዮን የሚያክሉ እሥረኞች ሲኖሯት የብዙዎቹ ወንጀል ከዕፅ ጋር የተያያዘ ነው። ቢሆንም ልታሠር እችላለሁ የሚለው ስጋት ሰዎች ዕፅ ከመውሰድ እንዲታቀቡ አላደረጋቸውም። የዕፅ ሽያጭ በጣም በደራባቸው በርካታ ታዳጊ አገሮች በቁጥር አነስተኛ የሆኑትና ዝቅተኛ ደመወዝ የሚከፈላቸው ፖሊሶች ንግዱን ሊቆጣጠሩ አልቻሉም።
ዕፆች ያላቸውን ተፈላጊነት መቀነስ ይቻል ይሆን?
የዕፆችን አቅርቦት ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት ሁሉ ከንቱ ከሆነ ያላቸውን ተፈላጊነት ስለ መቀነስስ ምን ለማለት ይቻላል? ታይም መጽሔት “በዕፅ ላይ የሚካሄደው ጦርነት የሰዎችን ልብና አእምሮ ለመማረክ የሚደረግ ትግል እንጂ በፖሊሶች፣ በፍርድ ቤቶችና በወህኒ ቤቶች ብቻ የሚፈታ ነገር አይደለም” ብሏል።
ቀደም ብለን የጠቀስናቸው ጆ ዴ ላ ሮዛም የተከለከሉ ዕፆችን ለመዋጋት የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ትምህርት እንደሆነ ያምናሉ። “የዕፅ ሱሰኛነት በኅብረተሰቡ የሚፈጠር ማህበራዊ ችግር በመሆኑ ኅብረተሰቡን መለወጥ ወይም ቢያንስ የሰዎችን አስተሳሰብ መለወጥ ይኖርብናል” ይላሉ። “ሁሉም አደገኛ ሁኔታ መኖሩን፣ ዕፆች በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ መሆናቸውንና ልጆቻቸው የዕፅ ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገነዘቡ ዘንድ ትምህርት ቤቶችን፣ ወላጆችንና አስተማሪዎችን ለማሳተፍ እየሞከርን ነው።”
የይሖዋ ምሥክሮች ምን አድርገዋል?
የይሖዋ ምሥክሮች ለበርካታ ዓመታት ሰዎች ከዕፅ እንዲርቁ በትጋት ሲያስተምሩ ቆይተዋል። ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ዕፅ አደገኛነት እንዲያስተምሩ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጁ ጽሑፎች አሉ።a ከዚህም በላይ የሚያካሂዱት አገልግሎት የብዙ የዕፅ ሱሰኞችንና አዘዋዋሪዎችን ሕይወት በማስተካከል ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በፊተኛው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው አና እህቷ የይሖዋ ምሥክሮች የዕፅ ሱሰኞች ከሱሳቸው እንዲላቀቁ በመርዳት ረገድ እንደተሳካላቸው ሰምታ ስለነበረ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንድትተዋወቅ ተደረገ። አና ለመጽሐፍ ቅዱስ ብዙም ፍላጎት ያልነበራት ብትሆንም ምሥክሮቹ አድርገውት ወደነበረ ትልቅ ስብሰባ እያመነታች ሄደች። በስብሰባው ቦታ አንድ የታወቀ የዕፅ አዘዋዋሪ በቁመናውም ሆነ በአኗኗሩ ፈጽሞ ተለውጦ አገኘችው። አና “እሱ ከተለወጠ እኔም መለወጥ እችላለሁ ብዬ አሰብኩ” አለች። “የእርሱ መለወጥ የቀረበልኝን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የመጀመር ግብዣ እንድቀበል አደረገኝ።
“ከመጀመሪያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ጀምሮ ከቤቴ ላለመውጣት ወሰንኩ። ምክንያቱም ከቤት ከወጣሁ ሌሎች ዕፅ ወሳጆችን ስለማገኝ ዕፅ ወደ መውሰድ እንደምመለስ አውቅ ነበር። ዕፅ መውሰድ ስህተት እንደሆነና አምላክም ይህን ልማድ እንደማይደግፍ አውቄያለሁ። በተጨማሪም ዕፅ በሰዎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳትና እኔም በቤተሰቤ ላይ ያደረስኩትን ጉዳት ተመልክቻለሁ። ቢሆንም ከዕፅ እሥረኝነት ነጻ ለመውጣት መንፈሳዊ ጥንካሬ ያስፈልገኝ ነበር። ዕፁ ከሰውነቴ እስኪወጣ ከፍተኛ ሥቃይ ደረሰብኝ። ዕፁ ያሳደረብኝ ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ እስኪጠፋ ድረስ ቀኑን ሙሉ መተኛት ነበረብኝ። ይሁን እንጂ ባገኘሁት ውጤት ተክሼያለሁ።”
እውነተኛ ተስፋና ትርጉም
በፊተኛው ርዕስ የተጠቀሰው የአና ባለቤት ፔትሮም በተመሳሳይ መንገድ ከዕፅ ሱስ መላቀቅ ችሏል። “አንድ ቀን ወንድሜ ቤት ሐሺሽ እያጨስኩ ሳለሁ የማወቅ ጉጉቴን የቀሰቀሰ ርዕስ ያለው መጽሐፍ ተመለከትኩ” በማለት ፔትሮ ያስታውሳል። “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የሚል ርዕስ ነበረው። ወደ ቤቴ ወሰድኩና ጥቅሶቹን አውጥቼ እየተመለከትኩ አነበብኩት። እውነትን እንዳገኘሁ እርግጠኛ ሆንኩ።
“መጽሐፍ ቅዱስ ማንበቤና የምማረውን ለሰዎች መናገሬ ስለ ራሴ ጥሩ ስሜት እንዲኖረኝ ከማድረጉም በላይ ለዕፅ የነበረኝ ፍላጎት ቀንሶልኛል። አንድ የነዳጅ ጣቢያ ለመዝረፍ ያወጣሁትን ዕቅድ ለመሰረዝ ወሰንኩ። አንድ ጓደኛዬ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያጠና ስለነበረ ወዲያው እኔም የእርሱን አርዓያ ተከተልኩ። በዘጠኝ ወር ውስጥ አኗኗሬን ለውጬ ተጠመቅኩ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ የቀድሞ ጓደኞቼ የዕፅ ግብዣ አቅርበውልኝ ነበር። እኔ ግን ወዲያው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መናገር እጀምራለሁ። አንዳንዶች ተቀብለውኛል። እንዲያውም አንደኛው ሱሱን እስከማሸነፍ ደርሷል።
“የዕፅን ሱስ ለማሸነፍ ተስፋ ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ዓይነቱን ተስፋ ሰጥቶኛል። ሕይወቴ ትርጉም ያለው እንዲሆን ረድቶኛል። አምላክ ስለ ዕፅና ዓመፅ ያለውን አመለካከት በግልጽ አሳይቶኛል። ሁሉን ስለሚችለው አምላክ ባወቅኩ መጠን መንፈሴ እንደሚነቃቃ አስተዋልኩ። እንዲህ ዓይነቱ መነቃቃት ምንም የሚያስከትለው ጉዳት የለም። በኋላም በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ ንጹሕ ኑሮ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ለመወዳጀት መቻሌ በዚሁ መንገድ እንድቀጥል ረድቶኛል።”
ከዕፅ አዘዋዋሪነት ወደ ግንበኛነት
በፊተኛው ርዕስ የተጠቀሰው ዕፅ አዘዋዋሪው ሆሴ አሁን እንደገና ግንበኛ ሆኗል። ትርፍ ያጋብስበት የነበረውን ንግዱን መተው ቀላል ሆኖ አላገኘውም። እንዲህ ይላል:- “ዕፅ ብዙ ገንዘብ ያስገኛል። ግን ጥሩ ዓይነት የገንዘብ ማግኛ አይደለም። ሽጉጥና የተብለጨለጩ መኪኖች የያዙ ወጣት ልጆች አያለሁ። ቤተሰቦች ይፈራርሳሉ። በየጎዳናው ከባድ ወንጀሎች ይፈጸማሉ። ብዙ ሱሰኞች ለዕፅ መግዣ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት መኪኖችን ሰብረው ይሰርቃሉ፣ ሱቆችን ይዘርፋሉ፣ ወይም ሰዎችን ይቀማሉ። ብዙዎች በሐሺሽ ይጀምሩና ወደ ኤክስታሲ ወይም ወደ ሌሎች እንክብሎች ይሸጋገራሉ። ከዚያም ኮኬይን አልፎ ተርፎም ሄሮይን እስከመሞከር ይደርሳሉ። ብዙዎች ወደዚህ ቀለበት እንዲገቡ የበኩሌን አስተዋጽኦ እንዳደረግኩ ይሰማኛል።
“ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የማደርገውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በቀጠልኩ መጠን በዕፅ አዘዋዋሪነት ሥራ መካፈሌ ስህተት መሆኑን ይበልጥ እያመንኩበት ሄድኩ። ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረኝ ፈለግኩ። እንደኔ ታጠና የነበረችው ባለቤቴም ተመሳሳይ ፍላጎት ነበራት። እርግጥ ነው፣ ዕፅ መሸጥ ማቆም ቀላል ነገር አልነበረም። ለደንበኞቼና ለዕፅ አዘዋዋሪዎቼ መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት ላይ እንደሆንኩና የዕፅ ንግድ እንደተውኩ ገለጽኩላቸው። በመጀመሪያ ሊያምኑኝ አልቻሉም ነበር። አንዳንዶቹ እስካሁን ድረስም አያምኑም። ቢሆንም ከተውኩ ሁለት ዓመት ያህል ሆኖኛል። ለአንድ አፍታ እንኳን ቆጭቶኝ አያውቅም።
“ያለፈውን ዓመት ያሳለፍኩት በግንበኝነት ሙያዬ ላይ ተሠማርቼ ነው። ባሁኑ ጊዜ በወር የማገኘው ገንዘብ በዕፅ ንግድ በአንድ ቀን አገኝ የነበረውን ሩብ ያህል ነው። ይሁን እንጂ ይህ የተሻለ አኗኗር ስለሆነ ደስ ብሎኛል።”
ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ዓለም አቀፍ መፍትሔ
ጥቂት የዕፅ አዘዋዋሪዎች ይህን ንግዳቸውን በቆራጥነት ትተዋል። በሺህ የሚቆጠሩ ዕፅ ወሳጆችም የተለያየ መልክ ባላቸው የተሐድሶ ፕሮግራሞች ተረድተው ከሱሳቸው ተላቅቀዋል። ይሁን እንጂ ወርልድ ድራግ ሪፖርት እንደሚለው “ለረዥም ጊዜ ዕፅ ሲወስዱ ከቆዩ ከባድ ሱሰኞች መካከል እስከ ዘለቄታው ዕፅ መውሰድ የሚያቆሙት ጥቂቶች ብቻ ናቸው።” በተጨማሪም ከዕፅ ሱሰኝነት በሚገላገል አንድ ሰው እግር ብዙ አዳዲስ ሱሰኞች ይተካሉ። አቅርቦቱና ተፈላጊነቱ አለማቋረጥ ያድጋል።
በዕፅ ላይ የሚደረገው ውጊያ በድል አድራጊነት እንዲደመደም ከተፈለገ መላውን ምድር የሚያቅፍ መፍትሔ መገኘት ይኖርበታል። ምክንያቱም ችግሩ መላውን ምድር የሚያቅፍ ሆኗል። በዚህ ረገድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የናርኮቲክ መድኃኒቶች ኮሚሽን እንዲህ ብሏል:- “ዕፆችን መውሰድ፣ ማዘዋወርና በዚሁ ሳቢያ የሚፈጸሙት ወንጀሎች ከፍተኛ ሥጋት እንደሚያስከትሉ በአብዛኞቹ አገሮች ግንዛቤ ያገኘ ቢሆንም ተራው ሕዝብ የተከለከሉ ዕፆች በብሔራት የተናጠል ጥረት ብቻ ሊወገድ የማይችል ምድር አቀፍ ችግር እንዳስከተሉ እምብዛም አልተገነዘበም።”
ይሁን እንጂ መንግሥታት ጥረታቸውን አስተባብረው ይህን ዓለም አቀፍ ችግር ያስወግዱ ይሆን? እስካሁን የታዩት ውጤቶች የሚያበረታቱ አይደሉም። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ለዚህ ችግር እርግጠኛው መፍትሔ በብሔራዊ ድንበሮች የማይገደብ ሰማያዊ መንግሥት እንደሆነ ይጠቁማል። በኢየሱስ ክርስቶስ የሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት “ከዘላለም እስከ ዘላለም” እንደሚኖር መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጣል። (ራእይ 11:15) ስለዚህ በአምላክ መንግሥት ሥር የሚሰጠው መለኮታዊ ትምህርት ሰዎች ለዕፅ ያላቸው ፍላጎት ፈጽሞ እንዲጠፋ ያደርጋል። (ኢሳይያስ 54:13) ባሁኑ ጊዜ ለዕፅ ሱሰኝነት መስፋፋት አመቺ ሁኔታ የፈጠሩት ማህበራዊና ስሜታዊ ችግሮችም ለዘላለም ይጠፋሉ።—መዝሙር 55:22፤ 72:12፤ ሚክያስ 4:4
እርዳታ ትሻለህን?
በአሁኑ ጊዜም እንኳ ሰዎች በክርስቶስ በሚመራው የአምላክ መንግሥት ተስፋ ማድረጋቸው ዕፅ ከመውሰድ እንዲታቀቡ አድርጓቸዋል። ተጨማሪ መረጃ ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ እባክህ በአካባቢህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን አነጋግር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በታተመው ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መልሶቻቸው በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 34 ላይ የሚገኘውን “አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ እምቢ መባል የሚኖርበት ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዕፅ ሲያዝ
[ምንጭ]
K. Sklute/SuperStock
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፔትሮና ሚስቱ አና ከልጆቻቸው ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ሲያጠኑ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፔትሮ የአደጋ ማስጠንቀቂያ መሣሪያዎች ሲተክል