የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es17 ገጽ 26-36
  • መጋቢት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጋቢት
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2017
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 1
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 2
  • ዓርብ፣ መጋቢት 3
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 4
  • እሁድ፣ መጋቢት 5
  • ሰኞ፣ መጋቢት 6
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 7
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 8
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 9
  • ዓርብ፣ መጋቢት 10
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 11
  • እሁድ፣ መጋቢት 12
  • ሰኞ፣ መጋቢት 13
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 14
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 15
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 16
  • ዓርብ፣ መጋቢት 17
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 18
  • እሁድ፣ መጋቢት 19
  • ሰኞ፣ መጋቢት 20
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 21
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 22
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 23
  • ዓርብ፣ መጋቢት 24
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 25
  • እሁድ፣ መጋቢት 26
  • ሰኞ፣ መጋቢት 27
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 28
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 29
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 30
  • ዓርብ፣ መጋቢት 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2017
es17 ገጽ 26-36

መጋቢት

ረቡዕ፣ መጋቢት 1

ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን እንኳ አታውቁም።​—⁠ያዕ. 4:​14

አርቀው የሚመለከቱ ሽማግሌዎች፣ ያካበቱትን ተሞክሮ ከእነሱ በዕድሜ ለሚያንሱ ወንድሞች በማካፈል ጊዜያቸውን በአግባቡ ይጠቀማሉ። (መዝ 71:​17, 18) ሽማግሌዎች ሌሎችን ማሠልጠናቸው ጥቅም ያስገኛል። የጉባኤው መንፈሳዊነት ይጠናከራል። እንዴት? ሽማግሌዎች ሌሎችን ለማሠልጠን ጥረት ማድረጋቸው ጉባኤውን የሚረዱ ብዙ ወንድሞች እንዲገኙ ያደርጋል፤ እነዚህ ወንድሞች ደግሞ ጉባኤው በአሁኑ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በተለይ በታላቁ መከራ ወቅት ጸንቶ እንዲቆምና አንድነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። (ሕዝ. 38:​10-12፤ ሚክ. 5:5, 6) በመሆኑም ውድ ሽማግሌዎች፣ የሥራችሁ አንዱ ክፍል እንደሆነ አድርጋችሁ በመቁጠር ከዛሬ ጀምሮ ሌሎችን እንድታሠለጥኑ እንለምናችኋለን። በጉባኤ ውስጥ ያሉ አስፈላጊ የሆኑ ኃላፊነቶችን መወጣት በራሱ ጊዜያችሁን ሊወስድባችሁ እንደሚችል እንረዳለን። ያም ቢሆን ከዚህ ጊዜ ላይ የተወሰነውን በመውሰድ ሌሎችን ለማሠልጠን መጠቀም ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። (መክ. 3:⁠1) እንዲህ ማድረጋችሁ ጊዜያችሁን በአግባቡ እንደምትጠቀሙ የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ ጉባኤውን ይጠቅማል። w15 4/15 1:8-10

ሐሙስ፣ መጋቢት 2

ጆሮህ ከኋላህ “መንገዱ ይህ ነው። በእሱ ሂድ” የሚል ድምፅ ይሰማል።​—⁠ኢሳ. 30:​21

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ለመላው የሰው ዘር የላከውን መልእክት የያዘ መሆኑን እንደምታምን ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንተ በግልህ ወደ ይሖዋ እንዴት መቅረብ እንደምትችል የሚገልጽ ሐሳብስ ይዟል? በሚገባ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ ስታነብና ስታጠና፣ ለመልእክቱ ምን ምላሽ እንደምትሰጥና እንዴት ተግባራዊ እንደምታደርገው ቆም ብለህ አስብ፤ ይህን ማድረግህ ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት እንዲያነጋግርህ እንደፈቀድክ ያሳያል። ይህ ደግሞ ከእሱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖርህ ያደርጋል። (ዕብ. 4:​12፤ ያዕ. 1:​23-25) ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ “በምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ” በማለት የሰጠውን ምክር ካነበብክ በኋላ አሰላስልበት። አሁንም ቢሆን ሕይወትህ ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ከሆነ ይሖዋ እንደሚደሰትብህ ይሰማሃል። በሌላ በኩል ግን ሕይወትህን ቀላል ማድረግና ከመንግሥቱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ይበልጥ ማተኮር እንደሚያስፈልግህ ከተሰማህ፣ ይሖዋ ወደ እሱ መቅረብ እንድትችል በግለሰብ ደረጃ ልትሠራበት የሚገባውን ነገር እንደጠቆመህ አድርገህ ልትወስደው ይገባል።​—⁠ማቴ. 6:​19, 20፤ w15 4/15 3:3-5

ዓርብ፣ መጋቢት 3

የስብከቱ ሥራ በእኔ አማካኝነት ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸምና ብሔራት ሁሉ እንዲሰሙት ጌታ አጠገቤ ቆሞ ኃይል ሰጠኝ፤ ከአንበሳ አፍም ዳንኩ።​—⁠2 ጢሞ. 4:​17

እኛም እንደ ጳውሎስ በስብከቱ ሥራ ከተጠመድን ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ሌሎች ነገሮች በሙሉ ‘እንደሚሰጠን’ መተማመን እንችላለን። (ማቴ. 6:​33) የመንግሥቱ ሰባኪዎች እንደመሆናችን መጠን “ምሥራቹን በአደራ” ተቀብለናል፤ እንዲሁም ይሖዋ ከእሱ ጋር “አብረን የምንሠራ” እንደሆንን አድርጎ ይመለከተናል። (1 ተሰ. 2:4፤ 1 ቆሮ. 3:⁠9) በአምላክ ሥራ በተቻለን መጠን ንቁ ተሳትፎ ማድረጋችን ችግሮቻችን እስኪቃለሉ ድረስ መጠበቅ ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል። እንግዲያው የቀረውን ጊዜ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ለማጠናከር እንጠቀምበት። የሚያስጨንቀን ሁኔታ ሲያጋጥመን ይህን ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ እንደሚያስችል አጋጣሚ አድርገን እንመልከተው። በእርግጥም፣ የአምላክን ቃል በጥልቀት የምናጠና፣ አዘውትረን የምንጸልይ እንዲሁም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምንጠመድ ከሆነ ይሖዋ አሁን ያሉብንንም ሆነ ወደፊት ሊያጋጥሙን የሚችሉትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንድንወጣ ሊረዳን እንደሚችልና ይህንንም እንደሚያደርግ መተማመን እንችላለን። w15 4/15 4:17, 18

ቅዳሜ፣ መጋቢት 4

በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው?​—⁠ያዕ. 4:1

ኩራት የጉባኤን ሰላም ሊያደፈርስ ይችላል። ሥር የሰደደ የጥላቻና የበላይነት ስሜት በንግግራችንና በተግባራችን ሊንጸባረቅ ይችላል፤ ይህም በሌሎች ላይ ከባድ ጉዳት ያደርሳል። (ምሳሌ 12:​18) ከሌሎች እንደምትበልጥ የሚሰማህ ከሆነ “ይሖዋ ኩሩ ልብ ያለውን ሁሉ ይጸየፋል” የሚለውን ጥቅስ ማስታወስ ይኖርብሃል። (ምሳሌ 16:⁠5) ከዚህም ሌላ ከእኛ የተለየ ዘር፣ ዜግነት ወይም ባሕል ላላቸው ሰዎች ያለንን አመለካከት መመርመራችን ጠቃሚ ነው። በዘራችን ወይም በአገራችን የመኩራት ዝንባሌ ካለን አምላክ “የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ” የሚለውን እውነታ ዘንግተናል ማለት ነው። (ሥራ 17:​26) ከዚህ ጥቅስ አንጻር፣ የሰው ልጆች ሁሉ ቅደመ አያት አዳም በመሆኑ በዓለም ላይ ያለው ዘር አንድ ብቻ ነው። እንግዲያው አንዳንድ ዘሮች ከሌሎች የበለጡ ወይም ያነሱ እንደሆኑ ማሰብ ምንኛ ሞኝነት ነው! እንዲህ ያለው አመለካከት ሰይጣን ክርስቲያናዊ ፍቅራችንንና አንድነታችንን እንዲያናጋ መንገድ ይከፍታል። (ዮሐ. 13:​35) ሰይጣንን ተዋግተን ለማሸነፍ ማንኛውንም ተገቢ ያልሆነ ኩራት ማስወገድ ይኖርብናል።​—⁠ምሳሌ 16:​18፤ w15 5/15 2:8, 9

እሁድ፣ መጋቢት 5

አምላክን የምትመስሉ ሁኑ።—⁠ኤፌ. 5:1

አምላክ ታማኝ ለሆኑት ቅቡዓን በሰማይ የማይሞት ሕይወት፣ ታማኝ ለሆኑት የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ደግሞ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጣቸው ቃል መግባቱ እንደሚያስደስተን ምንም ጥርጥር የለውም። (ዮሐ. 10:​16፤ 17:3፤ 1 ቆሮ. 15:​53) በሰማይ የማይሞት ሕይወት የሚሰጣቸውም ሆነ በምድር ላይ ዘላለማዊ ሕይወት የሚያገኙት ሰዎች በዛሬው ጊዜ ያሉት መከራዎች ወደፊት እንደማይደርሱባቸው የታወቀ ነው። ይሖዋ፣ እስራኤላውያን በግብፅ በባርነት እያሉ ሥቃያቸውን እንደተረዳላቸው ሁሉ እኛም የሚያጋጥመንን መከራ በሚገባ ያውቃል። በእርግጥም ከእስራኤላውያን ጋር በተያያዘ “በጭንቃቸው ሁሉ እሱ ተጨነቀ” ተብሎ ነበር። (ኢሳ. 63:⁠9) ከዘመናት በኋላ ደግሞ አይሁዳውያን ቤተ መቅደሱን እንደገና ሲገነቡ ጠላቶቻቸው በሰነዘሩባቸው ተቃውሞ የተነሳ ፈርተው ነበር፤ ይሁንና አምላክ “እናንተን የሚነካ ሁሉ የዓይኔን ብሌን ይነካል” ብሏቸዋል። (ዘካ. 2:⁠8) አንዲት እናት ለሕፃን ልጇ ጥልቅ ፍቅር እንዳላት ሁሉ ይሖዋም ለሕዝቡ ያለው ፍቅር ለእነሱ ሲል እርምጃ እንዲወስድ ይገፋፋዋል። (ኢሳ. 49:​15) በሌላ አባባል ይሖዋ ራሱን በሌሎች ቦታ አድርጎ መመልከት ይችላል፤ ይህንን ችሎታ ለእኛም ሰጥቶናል።​—⁠መዝ. 103:​13, 14፤ w15 5/15 4:2

ሰኞ፣ መጋቢት 6

ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው።​—⁠ማቴ. 26:​11

ኢየሱስ ይህን ሲል በምድር ላይ ምንጊዜም ቢሆን ድሆች እንደሚኖሩ መናገሩ ነበር? አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ይህ ብልሹ ሥርዓት እስካልጠፋ ድረስ ድሆች መኖራቸው እንደማይቀር መግለጹ ነው። በዛሬው ጊዜ፣ በግፍ በተሞላው ሰብዓዊ አገዛዝ የተነሳ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መሠረታዊ ፍላጎት ሊሟላ አልቻለም። ሆኖም እፎይታ የምናገኝበት ጊዜ ሩቅ አይደለም! (መዝ. 72:​16) የኢየሱስ ተአምራት፣ ሥልጣኑን እኛን በሚጠቅም መንገድ ለማዋል ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ እንዳለው እንድንተማመን ያደርጉናል። (ማቴ. 14:​14-21) እኛም ተአምራት መፈጸም ባንችልም እንኳ ሰዎች በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ በግለት ልንረዳቸው እንችላለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ያረጋግጡልናል። ታዲያ ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንዲህ ያለ ልዩ እውቀት ያለን ራሳችንን የወሰንን የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን፣ ለሰዎች ዕዳ እንዳለብን ሊሰማን አይገባም? (ሮም 1:​14, 15) በዚህ ጉዳይ ላይ ማሰላሰላችን ለሌሎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመናገር ያነሳሳናል።​—⁠መዝ. 45:1፤ 49:3፤ w15 6/15 1:7, 10, 11

ማክሰኞ፣ መጋቢት 7

እጆቻችሁን አንጹ፤ . . . ልባችሁን አጥሩ።​—⁠ያዕ. 4:8

ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ከፍ አድርገን የምንመለከት ከሆነ የምናስባቸውን ነገሮች ጨምሮ በመላ ሕይወታችን አምላክን ለማስደሰት ጥረት እናደርጋለን። አእምሯችን ንጹሕና በጎ በሆኑ እንዲሁም ምስጋና በሚገባቸው ነገሮች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ “ንጹሕ ልብ” እንዲኖረን እንደምንፈልግ እናሳያለን። (መዝ. 24:3, 4፤ 51:6፤ ፊልጵ. 4:⁠8) ይሖዋ ፍጽምና የሚጎድለን መሆኑን ከግምት እንደሚያስገባ ጥያቄ የለውም። ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶች በቀላሉ ሊያድሩብን እንደሚችሉ ያውቃል። ያም ቢሆን መጥፎ ሐሳቦችን ለማስወገድ የምንችለውን ያህል ጥረት ከማድረግ ይልቅ የምናሰላስልባቸው ከሆነ ይሖዋ እንደሚያዝን እንገነዘባለን። (ዘፍ. 6:5, 6) በዚህ እውነታ ላይ ማተኮራችን ሐሳባችን ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆን ይበልጥ ጥረት ለማድረግ ያነሳሳናል። በይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንደምንታመን ከምናሳይባቸው መንገዶች አንዱ ርኩስ ሐሳቦችን ለማስወገድ በምናደርገው ትግል እሱ እንዲረዳን መጸለይ ነው። በጸሎት አማካኝነት ወደ ይሖዋ ስንቀርብ እሱም ወደ እኛ ይቀርባል። ቅዱስ መንፈሱን በልግስና ስለሚሰጠን የብልግና ሐሳቦችን ለማስወገድና ንጹሕ ሆነን ለመኖር ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል። w15 6/15 3:4, 5

ረቡዕ፣ መጋቢት 8

የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን።—⁠ማቴ. 6:​11

ይህን ልመና ስናቀርብ የዕለት “ምግቤን” ብቻ ሳይሆን የዕለት “ምግባችንን” ማለት እንዳለብን ልብ በል። በአፍሪካ የሚያገለግል ቪክቶር የተባለ የወረዳ የበላይ ተመልካች ስለዚህ ጉዳይ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ የምንበላውን ምግብ ከየት እንደምናገኝ ወይም የቤት ኪራይ ማን እንደሚከፍልልን መጨነቅ ስለማያስፈልገን ይሖዋን ብዙ ጊዜ ከልቤ አመሰግነዋለሁ። ወንድሞቻችን የሚያስፈልገንን ነገር በየዕለቱ በደግነት ይሰጡናል። በሌላ በኩል ደግሞ እኛን የሚንከባከቡን ወንድሞች የሚያጋጥሟቸውን የኢኮኖሚ ችግሮች መቋቋም እንዲችሉ ይሖዋ እንዲረዳቸው እጸልያለሁ።” እኛም ለብዙ ቀን የሚሆን ምግብ ይኖረን ይሆናል፤ ያም ቢሆን ድሃ የሆኑ ወይም አደጋ በደረሰበት አካባቢ የሚኖሩ ወንድሞቻችንን ማሰብ አለብን። ስለ እነሱ ከመጸለይም አልፈን ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ለምሳሌ፣ ያለንን ነገር እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የእምነት ባልንጀሮቻችን ማካፈል እንችላለን። በተጨማሪም ለዓለም አቀፉ ሥራ የምናደርገው መዋጮ እንደማይባክን እርግጠኛ በመሆን አዘውትረን የገንዘብ መዋጮ የማድረግ አጋጣሚ አለን።​—⁠1 ዮሐ. 3:​17፤ w15 6/15 5:4-6

ሐሙስ፣ መጋቢት 9

ይህ አምላክ፣ ለዘላለም አምላካችን ነውና። እስከ ወዲያኛው ይመራናል።​—⁠መዝ. 48:​14

ከይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ጋር በተያያዘ አስደናቂ የሆነ ለውጥ እንደሚኖር በኢሳይያስ 60:​17 ላይ አስቀድሞ ተነግሯል። ወጣቶች ወይም በእውነት ቤት ብዙ ያልቆዩ ክርስቲያኖች ስለ እነዚህ ለውጦች አንብበው አሊያም ሌሎች ሲናገሩ ሰምተው ሊሆን ይችላል። ይህን ለውጥ በዓይናቸው የተመለከቱ ወንድሞችና እህቶችማ እንዴት ያለ ትልቅ መብት አግኝተዋል! ይሖዋ በሾመው ንጉሡ አማካኝነት ለድርጅቱ ትምህርትና አመራር እየሰጠ መሆኑን እርግጠኞች መሆናቸው የሚገርም አይደለም። በአምላክ መተማመናቸው የተገባ እንደሆነ ያውቃሉ፤ ሁላችንም ብንሆን እንዲህ ያለ የመተማመን ስሜት አለን። እነዚህ ወንድሞች ከልብ በመነጨ ስሜት ሐሳባቸውን ሲገልጹ መስማት እምነትህን ያጠናክረዋል፤ እንዲሁም በይሖዋ ይበልጥ እንድትታመን ያደርግሃል። በእውነት ቤት የቆየንበት ጊዜ ምንም ያህል ቢሆን ለሌሎች ስለ ይሖዋ ድርጅት ማውራት ይኖርብናል። በዚህ ክፉ፣ ምግባረ ብልሹና ፍቅር የጎደለው ዓለም ውስጥ መንፈሳዊ ገነት መኖር መቻሉ በእርግጥም በዘመናችን የተፈጸመ ተአምር ነው! w15 7/15 1:12, 13

ዓርብ፣ መጋቢት 10

ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው።​—⁠ራእይ 16:​16

የአርማጌዶን ጦርነት የይሖዋ ቅዱስ ስም እንዲከበር ያደርጋል። በፍየል የተመሰሉት ሰዎች በሙሉ በዚያ ወቅት “ወደ ዘላለም ጥፋት” ይሄዳሉ። (ማቴ. 25:​31-33, 46) በመጨረሻም ማንኛውም ዓይነት ክፋት ከምድር ላይ ይወገዳል፤ እጅግ ብዙ ሕዝብም የታላቁን መከራ የመጨረሻ ምዕራፍ በሕይወት ያልፋሉ። ከፊታችን እንዲህ ያሉ አስደናቂ ነገሮች የሚጠብቁን ከመሆኑ አንጻር በአሁኑ ጊዜ እያንዳንዳችን ምን ልናደርግ ይገባል? ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚቀልጡ ከሆነ ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ ያደራችሁ መሆናችሁን የሚያሳዩ ተግባሮች በመፈጸም ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል! . . . የይሖዋን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና በአእምሯችሁ አቅርባችሁ እየተመለከታችሁ ልትኖሩ ይገባል! ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እነዚህን ነገሮች እየተጠባበቃችሁ ስለሆነ በመጨረሻ በእሱ ፊት ቆሻሻና እድፍ ሳይኖርባችሁ በሰላም እንድትገኙ የተቻላችሁን ጥረት አድርጉ።” (2 ጴጥ. 3:​11, 12, 14) እንግዲያው ቁርጥ አቋማችን የሰላሙን ንጉሥ መደገፍና ምንጊዜም በመንፈሳዊ ንጹሕ ሆኖ መኖር ይሁን። w15 7/15 2:17, 18

ቅዳሜ፣ መጋቢት 11

ይሖዋ ቤትን ካልሠራ፣ ሠራተኞቹ የሚደክሙት በከንቱ ነው።​—⁠መዝ. 127:1

የይሖዋ ድርጅት፣ ብዙ ወጪ የማያስወጡና መጠነኛ የሆኑ የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባት እንዲሁም ለእነዚህ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ጉባኤዎች ከኅዳር 1, 1999 ወዲህ ከ28,000 በላይ ውብ የሆኑ አዳዲስ የአምልኮ ማዕከሎች ተገንብተዋል። በሌላ አባባል በ15 ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ በአማካይ በቀን አምስት አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች ተሠርተዋል። የመንግሥት አዳራሾች በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ሁሉ እንዲገነቡ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። ፍቅር የሚንጸባረቅበት ይህ ዝግጅት የአንዳንዶች ትርፍ የሌሎችን ጉድለት እንዲሸፍን ማድረግን በሚያበረታታው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ይህም “ሸክሙን እኩል [ለመጋራት] ያስችላል።” (2 ቆሮ. 8:​13-15) በመሆኑም የገንዘብ ድጋፍ ባያገኙ ኖሮ በራሳቸው የመንግሥት አዳራሽ የመገንባት አቅም ለሌላቸው ጉባኤዎች ለንጹሕ አምልኮ የሚውሉ ውብ አዳራሾች ተገንብተውላቸዋል። w15 7/15 4:9-11

እሁድ፣ መጋቢት 12

በተስፋ ጠብቀው!​—⁠ዕን. 2:3

የተለያዩ ገጽታዎች ያሉት የክርስቶስ መገኘት ምልክት ዓላማውን እንዲመታ፣ ኢየሱስ “ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት የሰጠውን ምክር ለሚታዘዙት ሰዎች የምልክቱ ፍጻሜ ግልጽ መሆን መቻል አለበት። (ማቴ. 24:​27, 42) ይህም ከ1914 ጀምሮ እየታየ ያለ ነገር ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የምልክቱ ገጽታዎች ፍጻሜያቸውን እያገኙ ነው። አሁን የምንኖረው “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” በተባለው ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ይህ አጭር ጊዜ ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ የሚያመራ ሲሆን ያለንበት ክፉ ሥርዓት ሲጠፋ ይደመደማል። (ማቴ. 24:⁠3) ታዲያ ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች በተስፋ መጠባበቅ የሚገባቸው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝ ስንል በተስፋ እንጠባበቃለን። በተጨማሪም የመገኘቱን ምልክት እናስተውላለን። በተስፋ የምንጠባበቀው በየዋህነት ሁሉንም ነገር ስለምናምን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ንቁ እንድንሆንና እንዳንዘናጋ እንዲሁም የዚህን ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ በተስፋ እንድንጠባበቅ የሚያነሳሱ አሳማኝ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎች ስላሉን ነው። w15 8/15 2:8, 9

ሰኞ፣ መጋቢት 13

አንተ . . . የሕያዋን [ፍጥረታትን] ሁሉ ፍላጎት ታሟላለህ።—⁠መዝ. 145:​16

አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የምንወዳቸውንና የሚያስደስቱንን ነገሮች ለማከናወን አጋጣሚ እናገኛለን። ደግሞም ይሖዋ እነዚህን ፍላጎቶች እንድናሟላ ባይፈልግ ኖሮ በሥራችን የመርካትና ጤናማ በሆኑ መዝናኛዎች የመደሰት ፍላጎት በውስጣችን ይፈጥር ነበር? (መክ. 2:​24) በዚህም ሆነ በሌሎች መንገዶች ይሖዋ ምንጊዜም ‘የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት ያሟላል።’ እረፍትና መዝናኛ የራሳቸው ቦታ አላቸው፤ ሆኖም ከእነዚህ ነገሮች የበለጠ ደስታ ማግኘት የምንችለው ከይሖዋ ጋር ላለን ግንኙነት ቅድሚያ ስንሰጥ ነው። ምድር ገነት ስትሆንም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እንግዲያው አስቀድመን መንግሥቱን በመፈለግና የይሖዋ ሕዝቦች አሁን በሚያገኟቸው መንፈሳዊ በረከቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ለግል ፍላጎቶቻችን ሁለተኛ ቦታ መስጠትን መልመዳችን ምንኛ ጥበብ ነው! (ማቴ. 6:​33) ምድር ገነት ስትሆን ከዚህ በፊት አይተን በማናውቀው መጠን ደስታ እናገኛለን። ለእውነተኛው ሕይወት ከአሁኑ በመዘጋጀት ይህን ሕይወት ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለን እናሳይ። w15 8/15 3:17, 18

ማክሰኞ፣ መጋቢት 14

እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና መልበስ ይኖርባችኋል።​—⁠ኤፌ. 4:​24

ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ ምድር ላይ ባሳለፈው ሕይወት ፍጽምና ከሚጎድላቸው ሰዎች ጋር ኖሯል። ያሳደጉት ወላጆቹ ፍጹም አልነበሩም፤ እንዲሁም ፍጽምና ከሚጎድላቸው ዘመዶቹ ጋር ለብዙ ዓመታት አብሮ ኖሯል። የቅርብ ተከታዮቹ እንኳ ሳይቀር በብዙዎች ዘንድ የሚታየው ሥልጣን የማግኘት ፍላጎትና የራስ ወዳድነት መንፈስ ተጋብቶባቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት “‘ከመካከላችን ታላቅ የሆነው ማን ነው?’ በሚል በመካከላቸው የጦፈ ክርክር ተነሳ።” (ሉቃስ 22:​24) ይሁንና ኢየሱስ ፍጽምና የሚጎድላቸው ተከታዮቹ መንፈሳዊ እድገት እንደሚያደርጉና አንድነት ያለው ጉባኤ መመሥረት እንደሚችሉ እርግጠኛ ነበር። ኢየሱስ ሐዋርያቱ አንድነት እንዲኖራቸው በዚያው ዕለት ምሽት በሰማይ ለሚኖረው አባቱ እንዲህ ሲል ጸልዮአል፦ “ይህን ልመና የማቀርበውም ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ ይኸውም . . . አባት ሆይ፣ አንተ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለህና እኔም ከአንተ ጋር አንድነት እንዳለኝ ሁሉ እነሱም ከእኛ ጋር አንድነት እንዲኖራቸው ነው። እኛ አንድ እንደሆንን ሁሉ እነሱም አንድ እንዲሆኑ [ነው]።”​—⁠ዮሐ. 17:​21, 22፤ w15 9/15 1:10, 11

ረቡዕ፣ መጋቢት 15

እሱም “ና!” አለው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከጀልባው ላይ ወርዶ በውኃው ላይ እየተራመደ ወደ ኢየሱስ አመራ።​—⁠ማቴ. 14:​29

ጴጥሮስ በውኃው ላይ ሲራመድ በዙሪያው የነበረው ነፋስና ማዕበል ክርስቲያኖች ከሚያጋጥሟቸው ፈተናዎችና መከራዎች ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ፈተናውና መከራው እጅግ ከባድ ቢሆንም እንኳ በይሖዋ እርዳታ ጸንተን መቆም እንችላለን። ጴጥሮስ መስመጥ የጀመረው ከኃይለኛ ነፋሱ ወይም ሞገዱ የተነሳ አለመሆኑን አስታውስ። የተከሰተውን ሁኔታ በቅደም ተከተል ለማሰብ ሞክር፤ ጴጥሮስ “አውሎ ነፋሱን ሲያይ ፈራ።” (ማቴ. 14:​24-32) ጴጥሮስ ትኩረቱን በኢየሱስ ላይ ማድረግ ባቃተው ጊዜ እምነቱ ተናወጠ። እኛም ‘አውሎ ነፋሱን ማየት’ ከጀመርን በሌላ አባባል በማዕበሉ ኃይለኝነት ላይ ካተኮርንና ይሖዋ እንደሚደግፈን ከተጠራጠርን መስመጥ ልንጀምር እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ የእምነት መዳከምን ወይም እምነት ማጣትን ‘በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘን ኃጢአት’ ብሎ ይጠራዋል፤ ይህም እምነታችንን ሊያዳክም የሚችልን የትኛውንም ሁኔታ አቅልለን ማየት እንደሌለብን ያስገነዝበናል። (ዕብ. 12:⁠1) ጴጥሮስ ከደረሰበት ሁኔታ ማየት እንደሚቻለው ትኩረታችን በተሳሳተ ነገር ላይ ካረፈ እምነታችን በቀላሉ ሊዳከም ይችላል። w15 9/15 3:1, 6, 7

ሐሙስ፣ መጋቢት 16

መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ ከላይ ነው፤ ይህ የሚወርደው ከሰማይ ብርሃናት አባት [ነው]።​—⁠ያዕ. 1:​17

ስጦታ ሲሰጥህ ምን ታደርጋለህ? መቼም አድናቆትህን በሆነ መንገድ መግለጽህ አይቀርም። በተጨማሪም ስጦታውን በአግባቡ በመጠቀም እንደ ተራ ነገር እንደማትቆጥረው ታሳያለህ። ይሖዋ ለመኖር የሚያስፈልጉንንና ለደስታችን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ነገሮችን ምንም ሳያጓድል ይሰጠናል። ይህ ታዲያ እኛም በአጸፋው እንድንወደው አያነሳሳንም? ይሖዋ እስራኤላውያንን ለበርካታ መቶ ዓመታት በፍቅር የተንከባከባቸው ሲሆን የተትረፈረፈ ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ በረከት አፍስሶላቸዋል። (ዘዳ. 4:7, 8) ይሁንና እነዚህን በረከቶች በቀጣይነት ማግኘታቸው የተመካው ምድሪቱ ያፈራችውን “መጀመሪያ የደረሰውን ምርጥ ፍሬ” ዘወትር ለይሖዋ መስጠትን የሚያዘውን ሕግ ጨምሮ መላውን የአምላክ ሕግ በመታዘዛቸው ላይ ነበር። (ዘፀ. 23:​19) እስራኤላውያን እንዲህ በማድረግ የይሖዋን ፍቅርና በረከት አቅልለው እንደማይመለከቱ ማሳየት ይችላሉ።​—⁠ዘዳ. 8:7-11፤ w15 9/15 5:5, 6

ዓርብ፣ መጋቢት 17

ልባቸው ንጹሕ የሆነ ደስተኞች ናቸው፤ አምላክን ያያሉና።​—⁠ማቴ. 5:8

በሕይወታችን የይሖዋን እጅ ማየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? እስቲ ይህን አስብ፦ ምናልባት እውነትን የሰማህበት መንገድ በቀጥታ የአምላክ እጅ እንዳለበት እንድታምን ያደርግህ ይሆናል። በጉባኤ ስብሰባ ላይ አንድ ክፍል ሲቀርብ አዳምጠህ “ይሄ በቀጥታ እኔን የሚመለከት ነው” ያልክበት ጊዜ አለ? ወይም ደግሞ ስለ አንድ ጉዳይ ጸልየህ መልስ አግኝተህ ይሆናል። ምናልባትም አገልግሎትህን ለማስፋት ከወሰንክ በኋላ ይሖዋ ነገሮችን እንዴት እንዳሳካልህ ስታይ ተገርመህ ሊሆን ይችላል። አሊያም ለመንፈሳዊ ነገሮች ስትል ሥራህን ከለቀቅክ በኋላ አምላክ “በምንም ዓይነት አልጥልህም” ሲል የገባው ቃል ሲፈጸም ተመልክተህ ይሆን? (ዕብ. 13:⁠5) እንግዲያው በመንፈሳዊ ንቁ ከሆንንና ‘ልባችን ንጹሕ ከሆነ’ ይሖዋ እኛን በተለያዩ መንገዶች እንዴት እየረዳን እንዳለ መገንዘብ እንችላለን። ‘ልበ ንጹሕ’ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ውስጣችንን ንጹሕ በማድረግና ማንኛውንም መጥፎ ምግባር በማስወገድ ነው። (2 ቆሮ. 4:⁠2) መንፈሳዊነታችን ይበልጥ እየተጠናከረ ሲሄድና ትክክለኛ ምግባር ስናሳይ አምላክን ማየት ከሚችሉ ሰዎች መካከል እንሆናለን። w15 10/15 1:17, 19

ቅዳሜ፣ መጋቢት 18

የሚያገለግለኝንም ሁሉ አብ ያከብረዋል።​—⁠ዮሐ. 12:​26

በኢየሩሳሌም ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል ወደ ይሁዲነት የተለወጡ አንዳንድ ግሪካውያን ኢየሱስ ባደረገው ነገር በጣም ተደንቀው እንደነበር መገመት እንችላለን፤ ምክንያቱም ከኢየሱስ ጋር እንዲያገናኛቸው ሐዋርያው ፊልጶስን ጠይቀውት ነበር። ኢየሱስ ግን ከፊቱ ከሚጠብቀው ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ትኩረቱ እንዲሰረቅ አልፈለገም። በአምላክ ጠላቶች እጅ መሥዋዕታዊ ሞት ላለመሞት ሲል በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅነት ለማትረፍ አልሞከረም። በመሆኑም በቅርቡ እንደሚገደል ከገለጸ በኋላ እንድርያስንና ፊልጶስን እንዲህ አላቸው፦ “ሕይወቱን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ሁሉ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል።” ኢየሱስ የእነዚህን ግሪካውያን ስሜት ከማስተናገድ ይልቅ እሱ ያሳየውን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ማንጸባረቅ የተሻለ እንደሆነ ከገለጸ በኋላ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ተናገረ። ፊልጶስ ይህን አበረታች መልእክት ሄዶ ለግሪካውያኑ እንደነገራቸው ምንም ጥርጥር የለውም። (ዮሐ. 12:​20-25) ምንም እንኳ ኢየሱስ ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ በስብከቱ ሥራ ላይ ያደረገ ቢሆንም ሁልጊዜ ስለ ሥራ ብቻ ያስብ ነበር ማለት አይደለም። w15 10/15 3:13, 14

እሁድ፣ መጋቢት 19

እኔ፣ የምወዳቸውን ሁሉ እወቅሳለሁ እንዲሁም እገሥጻለሁ።​—⁠ራእይ 3:​19

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይከራከሩ የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ ተስፋ አልቆረጠባቸውም። የሰጣቸውን ምክር እንዳልሠሩበት ሲያይም ሁኔታውን በቸልታ አላለፈውም። ኢየሱስ አመቺ ጊዜና ቦታ መርጦ በፍቅርና በደግነት እርማት ሰጥቷቸዋል። (ማር. 9:​33-37) እናንተም ለልጆቻችሁ ተግሣጽ በመስጠት እንደምትወዷቸው አሳዩአቸው። አንዳንድ ጊዜ፣ አንድ ድርጊት ትክክል ወይም ስህተት የሆነበትን ምክንያት ማስረዳቱ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። በእርግጥ ልጆቻችሁ የነገራችኋቸውን ተግባራዊ ሳያደርጉ የሚቀሩበት ጊዜ ይኖራል። (ምሳሌ 22:​15) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ። ተስማሚ ጊዜና ቦታ መርጣችሁ ልጆቻችሁን ገሥጿቸው፤ ይህን የምታደርጉት በፍቅር፣ በደግነት ብሎም በትዕግሥት መመሪያ፣ ሥልጠናና እርማት በመስጠት ነው። በደቡብ አፍሪካ የምትኖር ኢሌን የተባለች እህት “ወላጆቼ በቁጣ ወይም ምክንያቱን ሳያስረዱኝ ተግሣጽ ሰጥተውኝ አያውቁም” ብላለች። “ይህም ሳልፈራ ተረጋግቼ እንድኖር አድርጎኛል። ማለፍ የሌለብኝ ገደብ ምን እንደሆነ እንዲሁም ከእኔ ምን እንደሚጠበቅ አውቃለሁ።” w15 11/15 1:5, 6

ሰኞ፣ መጋቢት 20

አምላክ ፍቅር ነው።​—⁠1 ዮሐ. 4:​16

አምላክ ለሰው ልጆች ፍቅር ባይኖረው የወደፊት ሕይወታችን ምን ሊመስል እንደሚችል እስቲ አስበው። ሰይጣን ዲያብሎስ አምላክ የሆነለት ብሎም በሰብዓዊ አገዛዝ የሚመራው ይህ ዓለም ያስመዘገበውን አሰቃቂ ታሪክ መመልከቱ ብቻ በቂ ነው፤ ሰይጣን ፍቅር የሌለው ከመሆኑም ሌላ በቁጣ ተሞልቷል። (2 ቆሮ. 4:4፤ 1 ዮሐ. 5:​19፤ ራእይ 12:9, 12) አፍቃሪ የሆነው አምላክ አመራር ባይኖር ኖሮ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያሉ ፍጥረታት የወደፊት ሕይወት ምን ያህል አስከፊ ሊሆን እንደሚችል ከዚህ መረዳት ይቻላል። ዲያብሎስ በይሖዋ አገዛዝ ላይ ባመፀበት ጊዜ የአምላክ ጽንፈ ዓለማዊ አገዛዝ ትክክለኛና ጽድቅ የሰፈነበት ስለመሆኑ ጥያቄ አንስቷል። በሌላ አባባል ሰይጣን የእሱ አገዛዝ ከፈጣሪ አገዛዝ የተሻለ እንደሚሆን መናገሩ ነበር። (ዘፍ. 3:1-5) ሰይጣን ያነሳው ጥያቄ ትክክል መሆኑን ለማሳየት እንዲሞክር ይሖዋ ጊዜ የሰጠው ቢሆንም ይህ ጊዜ ገደብ አለው። ይሖዋ ከእሱ በቀር ሌሎች አገዛዞች በሙሉ ብቃት እንደሌላቸው በማያሻማ መንገድ መረጋገጥ እንዲችል በቂ ጊዜ በመስጠት ታላቅ ጥበቡን አሳይቷል። አሳዛኝ የሆነው የሰው ዘር ታሪክ እንደሚያሳየው የሰው ልጆችም ሆኑ ሰይጣን መልካም አገዛዝ እንዲሰፍን ማድረግ አይችሉም። w15 11/15 3:3, 4

ማክሰኞ፣ መጋቢት 21

ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ [ስጡ] . . . ይህን ስታደርጉ ግን በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት ይሁን።​—⁠1 ጴጥ. 3:​15

የይሖዋ ሕዝቦች ትሕትና የሚያዳብሩ ከሆነ ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ የተናገረውን አስፈላጊ መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ያደርጋሉ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “‘ባልንጀራህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ፤ ይህን ብታደርጉ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤ እሱ በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣልና፤ በጻድቃንም ሆነ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ዝናብ ያዘንባል።” (ማቴ. 5:​43-45) በእርግጥም የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን፣ ሰዎች ለእኛ ያላቸው አመለካከት ምንም ይሁን ምን ‘ጠላቶቻችንን መውደድን’ መማር አለብን። የይሖዋ ሕዝቦች እሱንና ባልንጀራቸውን እንደሚወዱ በአመለካከታቸውም ሆነ በድርጊታቸው፣ በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፎች ማሳየት ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የመንግሥቱን መልእክት የማይቀበሉ ሰዎችም እንኳ በሚቸገሩበት ጊዜ ፍቅር እናሳያቸዋለን። w15 11/15 4:17, 19, 20

ረቡዕ፣ መጋቢት 22

የተነገራቸውን ቃል ተረድተውት ነበር።​—⁠ነህ. 8:​12

የአምላክ ሕዝቦች የመናገር ይኸውም በቋንቋ የመጠቀም ችሎታቸውን ምንጊዜም ይሖዋን ለማወደስና ፈቃዱን ለሰዎች ለማሳወቅ ያውሉታል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በቋንቋ አማካኝነት ንጹሑን አምልኮ ማስፋፋት የተቻለበት ዋነኛ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ቢኖሩም በበኩረ ጽሑፉ ላይ የሚገኘውን መልእክት በታማኝነት የሚያስተላልፉት ግን ሁሉም አይደሉም። በ1940ዎቹ ዓመታት የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መሠረት ሆነው የሚያገለግሉ መመሪያዎችን አዘጋጀ፤ እነዚህን መመሪያዎች ከ130 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተግባራዊ አድርገናል። መመሪያዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም (1) የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቀድሞ በነበረበት ትክክለኛ ቦታ ላይ መልሶ እንዲገባ በማድረግ የአምላክን ስም ያስቀድሳል። (ማቴ. 6:⁠9) (2) የቋንቋው ሥርዓት እስከፈቀደለት ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ውስጥ ለሚገኘው ሐሳብ ቀጥተኛ ፍቺ ይሰጣል፤ ቃል በቃል መተርጎም ሊተላለፍ የተፈለገውን መልእክት የሚያዛባ ከሆነ ግን የቃሉን ወይም የሐረጉን ትክክለኛ መንፈስ ለማስተላለፍ ይጥራል። (3) ለማንበብ የሚማርክና ለመረዳት የማያስቸግር ቋንቋ ይጠቀማል።​—⁠ነህ. 8:8፤ w15 12/15 2:1, 2

ሐሙስ፣ መጋቢት 23

መለከት ለመለየት የሚያስቸግር ድምፅ ቢያሰማ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል?​—⁠1 ቆሮ. 14:8

በግልጽ ያልሆነ የመለከት ድምፅ በዘመቻ ላይ ያለን ሠራዊት ለአደጋ ሊያጋልጠው ይችላል። በተመሳሳይም የምንናገረው ነገር የተድበሰበሰ ወይም ዙሪያ ጥምጥም ከሆነ ሰሚዎቹን ግራ ሊያጋባና ሊያሳስት ይችላል። (1 ቆሮ. 14:⁠9) እርግጥ ነው፣ ንግግራችን ግልጽ ይሁን ሲባል አክብሮትና ዘዴኛነት የጎደለው ይሆናል ማለት አይደለም። ኢየሱስ ተገቢ ቃላትን መርጦ በመጠቀም ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ከማ​ቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን አጭር ሆኖም ኃይለኛ መልእክት የያዘ ንግግሩን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ የተራቀቁ ወይም አሻሚ ቃላትን አልተጠቀመም፤ ንግግሩ ኃይለ ቃል ያዘለ ወይም ጎጂ አልነበረም። የአድማጮቹን ልብ ለመንካት ሲል ግልጽና ቀላል የሆኑ አገላለጾችን ተጠቅሟል። ለአብነት ያህል፣ ሕዝቡ ስለ ዕለታዊ ምግባቸው እንዳይጨነቁ ለመርዳት ሲል ይሖዋ የሰማይ ወፎችን የሚመግብበትን መንገድ እንደ ምሳሌ ጠቅሷል። ከዚያም አድማጮቹን ከወፎች ጋር በማወዳደር “ታዲያ እናንተ ከእነሱ አትበልጡም?” ብሎ ጠየቃቸው። (ማቴ. 6:​26) ቀላል፣ ለመረዳት የማይከብዱና ልብ የሚነኩ ቃላትን በመጠቀም ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ የቀረበ እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ነው! w15 12/15 3:13, 14

ዓርብ፣ መጋቢት 24

እርስ በርሳችሁ እንደ ወንድማማች መዋደዳችሁን ቀጥሉ።​—⁠ዕብ. 13:1

እንደ ወንድማማች እንዋደዳለን ሲባል ምን ማለት ነው? ጳውሎስ የተጠቀመበት ፊላደልፊያ የሚለው የግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ፍቺ፣ ‘አንድ ሰው ለወንድሙ ያለውን ፍቅር’ ያመለክታል። የወንድማማች መዋደድ የሚለው አገላለጽ ለቤተሰባችን አባል ወይም ለቅርብ ወዳጃችን የሚኖረንን ዓይነት ጠንካራ፣ የጠበቀና ጥልቅ ፍቅር ያመለክታል። (ዮሐ. 11:​36) እንዲህ ዓይነት ፍቅር እናሳያለን ሲባል ወንድማማችና እህትማማች መስለን ለመታየት እንሞክራለን ማለት አይደለም፤ ወንድማማችና እህትማማች ነን። (ማቴ. 23:⁠8) የሚከተለው ጥቅስ በመካከላችን ያለውን የጠበቀ ወዳጅነት በሚገባ ይገልጸዋል፦ “በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።” (ሮም 12:​10) በመሠረታዊ ሥርዓት በሚመራው አጋፔ በተባለው ፍቅር ላይ የወንድማማች መዋደድ ሲጨመር በአምላክ ሕዝቦች መካከል የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖር ያደርጋል። ለክርስቲያኖች ዜግነት ለውጥ አያመጣም፤ ሁሉም አማኞች ወንድማማች ናቸው። (ሮም 10:​12) ወንድማማች እንደመሆናችን መጠን ይሖዋ አንዳችን ለሌላው የወንድማማች ፍቅር እንዲኖረን አስተምሮናል።​—⁠1 ተሰ. 4:9፤ w16.01 1:5, 6

ቅዳሜ፣ መጋቢት 25

ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናል።​—⁠2 ቆሮ. 5:​14

ለኢየሱስ ያለን ፍቅር በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በሙሉ ነፍሳችን እንድንካፈል ሊያነሳሳን ይገባል። (ማቴ. 28:​19, 20፤ ሉቃስ 4:​43) በመታሰቢያው በዓል ወቅት በረዳት አቅኚነት በማገልገል በስብከቱ ሥራ 30 ወይም 50 ሰዓት ለማሳለፍ አጋጣሚ እናገኛለን። አንተስ ሁኔታህን አመቻችተህ እንዲህ ማድረግ ትችላለህ? ባለቤታቸውን በሞት ያጡ አንድ የ84 ዓመት አረጋዊ፣ ዕድሜያቸውና ጤናቸው በረዳት አቅኚነት ለማገልገል እንደማይፈቅድላቸው ተሰምቷቸው ነበር። ይሁንና በአካባቢው የሚገኙ አቅኚዎች እኚህን ወንድም ለመርዳት ፈለጉ። አቅኚዎቹ እኚህን ወንድም በመኪና ይወስዷቸው የነበረ ሲሆን እሳቸው ሊያገለግሉበት የሚችሉ ጥሩ ክልል መረጡላቸው፤ በመሆኑም ወንድም የ30 ሰዓት ግባቸው ላይ መድረስ ቻሉ። አንተስ አንድ ክርስቲያን በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ረዳት አቅኚ ሆኖ በማገልገል የሚገኘውን ደስታ እንዲያጣጥም ልታግዘው ትችላለህ? እርግጥ ነው፣ ረዳት አቅኚ ሆነን ማገልገል የምንችለው ሁላችንም አይደለንም። ያም ቢሆን ያለንን ጊዜና ጉልበት ተጠቅመን ለይሖዋ የምናቀርበውን የውዳሴ መሥዋዕት መጠን ከፍ ማድረግ እንችላለን። w16.01 2:7, 11

እሁድ፣ መጋቢት 26

አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን።​—⁠ዘካ. 8:​23

የሌሎች በጎች አባላት በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ያሉትን የሁሉንም የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት ስም ማወቅ የማይችሉ ከሆነ ከእነሱ ጋር ‘መሄድ’ የሚችሉት እንዴት ነው? በዘካርያስ ላይ የሚገኘው ትንቢት ምሳሌያዊዎቹን አሥር ሰዎች በተመለከተ ምን እንደሚል ልብ በል። እነዚህ ሰዎች “የአንድን አይሁዳዊ ልብስ አጥብቀው በመያዝ ‘አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን’ ይላሉ።” እዚህ ላይ የተጠቀሰው አይሁዳዊ አንድ ብቻ ቢሆንም “እናንተ” ከሚለው ተውላጠ ስም ማየት እንደሚቻለው ሐሳቡ የሚያመለክተው ብዙ ሰዎችን ነው። እንግዲያው እዚህ ላይ የተገለጸው አይሁዳዊ አንድን ሰው ሳይሆን አንድን ቡድን የሚያመለክት ነው! በመሆኑም አይሁዳዊ ተብለው የተገለጹትን ቅቡዓን በግለሰብ ደረጃ አውቀን ከእያንዳንዳቸው ጋር መሄድ አያስፈልገንም። ከዚህ ይልቅ እነዚህን ሰዎች ያቀፈውን ቡድን ለይተን ማወቅና መደገፍ ይኖርብናል። ቅዱሳን መጻሕፍት አንድን ግለሰብ እንድንከተል ፈጽሞ አያበረታቱንም። ምክንያቱም መሪያችን ኢየሱስ ነው።​—⁠ማቴ. 23:​10፤ w16.01 4:4

ሰኞ፣ መጋቢት 27

እስራኤል ሆይ፣ አንተ . . . አገልጋዬ ነህ፤ ያዕቆብ ሆይ፣ አንተን መርጬሃለሁ፤የወዳጄ የአብርሃም ዘር ነህ።—⁠ኢሳ. 41:8

ከተወለድንበት ጊዜ ጀምሮ እስከምንሞትበት ጊዜ ድረስ ፍቅር ማግኘት እንፈልጋለን። በእርግጥም እኛ የሰው ልጆች ፍቅር ያስፈልገናል፤ እንዲያውም ፍቅር እንደ ምግብ ይርበናል። ይህን ስንል በተቃራኒ ፆታዎች መካከል ያለውን ፍቅር ብቻ ማለታችን አይደለም። ሁላችንም ከሌሎች ጋር ወዳጅነት የመመሥረትና የመቀራረብ ከፍተኛ ፍላጎት አለን። ይሁንና ከሁሉ በላይ የሚያስፈልገን የይሖዋን ፍቅር ማግኘት ነው። ብዙ ሰዎች፣ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር በፍቅር ላይ የተመሠረተ የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ይቻላል ብሎ ማሰብ ይከብዳቸዋል። እኛስ እንዲህ ዓይነት ጥርጣሬ አለን? በፍጹም! መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች የአምላክ ወዳጆች መሆን እንደቻሉ ይናገራል። በእነዚህ ሰዎች ታሪክ ላይ ማሰላሰላችን ጠቃሚ ነው፤ ምክንያቱም በሕይወታችን ውስጥ ሊኖሩን ከሚችሉት ግቦች ሁሉ የላቀው ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ነው። እንዲህ ዓይነት ወዳጅነት ከመሠረቱ ሰዎች መካከል አብርሃም በምሳሌነቱ የሚጠቀስ ነው። (ያዕ. 2:​23) አብርሃም ከይሖዋ ጋር ይህን ያህል የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት የቻለው እንዴት ነው? ለወዳጅነታቸው ቁልፍ ሚና የተጫወተው እምነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አብርሃም “በእምነታቸው የተነሳ እንደ ጻድቃን ለተቆጠሩት ሁሉ አባት” እንደሆነ ይናገራል።​—⁠ሮም 4:​11፤ w16.02 1:1, 2

ማክሰኞ፣ መጋቢት 28

እንደ እሱ ያለ አልተገኘም።​—⁠2 ነገ. 18:5

ሕዝቅያስ፣ በጣም መጥፎ ከሆኑት የይሁዳ ነገሥታት መካከል የአንዱ ልጅ ቢሆንም በጣም ጥሩ ንጉሥ መሆን ችሏል። (2 ነገ. 18:⁠6) ሕዝቅያስ አባቱ የፈጸማቸውን መጥፎ ነገሮች ለማስተካከል እርምጃ ወስዷል። ይህንንም ያደረገው ቤተ መቅደሱን በማንጻት፣ ለሕዝቡ ኃጢአት ማስተሰረያ በማቅረብ እንዲሁም የአረማውያንን ጣዖታት ለማጥፋት ቅንዓት የተንጸባረቀበት ሰፊ ዘመቻ በማካሄድ ነው። (2 ዜና 29:1-11, 18-24፤ 31:⁠1) ሕዝቅያስ፣ ከባድ ፈተናዎች ባጋጠሙት ጊዜ ለምሳሌ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በሞከረበት ወቅት ታላቅ ድፍረትና እምነት እንዳለው አሳይቷል። አምላክ እንደሚያድነው የተማመነ ከመሆኑም ሌላ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ ሕዝቡን አበረታቷል። (2 ዜና 32:7, 8) ከጊዜ በኋላ ሕዝቅያስ ልቡ በመታበዩ እርማት ሲሰጠው ራሱን ዝቅ በማድረግ ንስሐ ገብቷል። (2 ዜና 32:​24-26) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሕዝቅያስ፣ ያለፈው ሕይወቱ የአሁኑን ሕይወቱን እንዲያበላሽበት ወይም ጥሩ የወደፊት ሕይወት እንዳይኖረው እንቅፋት እንዲሆንበት አልፈቀደም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋ ወዳጅ በመሆን እኛም ልንከተለው የሚገባ ጥሩ ምሳሌ ትቷል። w16.02 2:11

ረቡዕ፣ መጋቢት 29

አንድ ሰው ሳያውቅ የተሳሳተ ጎዳና ቢከተል መንፈሳዊ ብቃት ያላችሁ እናንተ እንዲህ ዓይነቱን ሰው በገርነት መንፈስ ለማስተካከል ጥረት አድርጉ።​—⁠ገላ. 6:1

አንዳንድ ጊዜ ለማን ታማኝ መሆን እንዳለብህ ግራ ስትጋባ ደግነት ሊረዳህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የእምነት ባልንጀራህ ከባድ ኃጢአት እንደሠራ በእርግጠኝነት ታውቃለህ እንበል። ይህ ሰው በተለይ የቅርብ ወዳጅህ ወይም ዘመድህ ከሆነ ለእሱ ታማኝ መሆን እንዳለብህ ይሰማህ ይሆናል። ይሁንና ኃጢአቱን የምትደብቅለት ከሆነ ለአምላክ ያለህን ታማኝነት እያጓደልክ ነው። ከማንም በላይ ታማኝ መሆን ያለብህ ለይሖዋ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። ደግ ሆኖም ደፋር ልትሆን ይገባል። ጓደኛህ ወይም ዘመድህ የሽማግሌዎችን እርዳታ እንዲጠይቅ አበረታታው። በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ይህን ካላደረገ ግን ለአምላክ ያለህ ታማኝነት፣ ጉዳዩን ለሽማግሌዎች እንድታሳውቅ ሊያነሳሳህ ይገባል። እንዲህ ስታደርግ ለይሖዋ ታማኝነት፣ ለወዳጅህ ወይም ለዘመድህ ደግሞ ደግነት ታሳያለህ፤ ምክንያቱም ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንዲህ ያለውን ሰው በገርነት ለማስተካከል ይጥራሉ።​—⁠ዘሌ. 5:1፤ w16.02 4:14

ሐሙስ፣ መጋቢት 30

ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ ያደራችሁ መሆናችሁን የሚያሳዩ ተግባሮች በመፈጸም ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል!​—⁠2 ጴጥ. 3:​11

‘ለአምላክ ያደሩ መሆንን የሚያሳዩ ተግባሮች’ በጉባኤ ውስጥ የምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሲሆኑ አዘውትሮ በስብሰባ ላይ መገኘትንና በአገልግሎት መካፈልን ያካትታሉ። በግልህ እንደምታቀርበው ጸሎትና የግል ጥናት የመሳሰሉ ሰዎች የማያዩአቸው መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችም በዚህ ውስጥ ይጠቃለላሉ። ራሱን ለይሖዋ የወሰነ ግለሰብ እነዚህን ነገሮች እንደ አድካሚ ሥራ አይመለከታቸውም። ከዚህ ይልቅ ንጉሥ ዳዊት የገለጸው የሚከተለው አመለካከት ይኖረዋል፦ “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው።” (መዝ. 40:⁠8) ራስህን የወሰንክና የተጠመቅክ ክርስቲያን ስትሆን በይሖዋ ፊት የምትቆመው ራስህን ችለህ እንደሆነ አስታውስ። ለእሱ የምታቀርበው አገልግሎት በማንም ላይ ሌላው ቀርቶ በወላጆችህ ላይ የተመካ መሆን የለበትም። ቅዱስ ሥነ ምግባር መያዝህ እንዲሁም ለአምላክ ያደርክ መሆንህን የሚያሳይ ተግባር መፈጸምህ እውነትን የራስህ እንዳደረግክና ለመጠመቅ ብቃቱን እያሟላህ እንደሆነ ያሳያል። w16.03 2:10, 12, 15

ዓርብ፣ መጋቢት 31

እምነት ከመምጣቱ በፊት፣ . . . በሕግ ጥበቃ ሥር እስረኞች እንድንሆን አልፈን ተሰጥተናል። በመሆኑም . . . ሕጉ ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ሞግዚታችን ሆኗል።​—⁠ገላ. 3:​23, 24

የሙሴ ሕግ እስራኤላውያንን፣ ሌሎች ብሔራት ይከተሉት ከነበረው ያዘቀጠ የሥነ ምግባርና የሃይማኖት ልማድ እንደሚጠብቅ ግድግዳ ሆኖ አገልግሏል። እስራኤላውያን የአምላክን መመሪያ ሲታዘዙ ብሔሩ የእሱን በረከት ያገኝ ነበር። መመሪያውን ችላ ሲሉ ደግሞ አስከፊ መዘዝ ደርሶባቸዋል። (ዘዳ. 28:1, 2, 15) በወቅቱ መመሪያዎች አስፈላጊ የነበሩበት ሌላም ምክንያት አለ። ሕጉ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በተያያዘ አንድ ትልቅ ክንውን እንደሚኖር ይጠቁም ነበር። ይህም የመሲሑ የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ነው። ሕጉ እስራኤላውያን ፍጹማን እንዳልሆኑ ምንም በማያሻማ መንገድ አሳይቷል። በተጨማሪም ቤዛ ማለትም ኃጢአታቸውን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍን ፍጹም የሆነ መሥዋዕት እንደሚያስፈልጋቸው አስገንዝቧቸዋል። (ገላ. 3:​19፤ ዕብ. 10:1-10) ከዚህም ሌላ የመሲሑ የዘር ሐረግ እንዲጠበቅ አድርጓል፤ እንዲሁም መሲሑ ሲመጣ በቀላሉ ተለይቶ እንዲታወቅ አስችሏል። በእርግጥም ሕጉ ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ጊዜያዊ አስተማሪ ወይም ‘ሞግዚት’ ሆኖ አገልግሏል። w16.03 4:6, 7

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ