የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es17 ገጽ 37-46
  • ሚያዝያ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሚያዝያ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2017
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 1
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 2
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 3
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 4
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 5
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 6
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 7
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 8
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 9
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 10
  • የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ዕለት
    ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ
    ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 11
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 12
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 13
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 14
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 15
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 16
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 17
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 18
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 19
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 20
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 21
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 22
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 23
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 24
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 25
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 26
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 27
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 28
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 29
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2017
es17 ገጽ 37-46

ሚያዝያ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 1

ንቁ ሆናችሁ ኑሩ! ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል።​—⁠1 ጴጥ. 5:8

በአንድ ወቅት በይሖዋ ፊት ጥሩ አቋም ነበረው። ይሁንና ይህ መንፈሳዊ ፍጡር፣ ሰዎች እንዲያመልኩት መመኘት ጀመረ። ይህን ተገቢ ያልሆነ ምኞት ከማስወገድ ይልቅ ስላሰላሰለበትና እንዲያድግ ስለፈቀደለት ምኞቱ ኃጢአትን ወለደ። (ያዕ. 1:​14, 15) እያወራን ያለነው ‘በእውነት ውስጥ ጸንቶ ስላልቆመው’ ስለ ሰይጣን እንደሆነ የታወቀ ነው። ሰይጣን በይሖዋ ላይ ያመፀ ከመሆኑም ሌላ “የውሸት አባት” ሆነ። (ዮሐ. 8:​44) ሰይጣን ካመፀበት ጊዜ ጀምሮ የይሖዋ ቀንደኛ ጠላት እንደሆነ ታይቷል፤ የሰው ልጆች ወዳጅ ሆኖ እንደማያውቅም ግልጽ ነው። ለሰይጣን የተሰጡት መጠሪያዎች ምን ያህል በክፋት እንደተዘፈቀ ይጠቁማሉ። ሰይጣን የሚለው ቃል “ተቃዋሚ” ማለት ሲሆን ይህ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር የአምላክን ሉዓላዊነት እንደማይደግፍ ያሳያል፤ እንዲያውም የይሖዋን ሉዓላዊ ገዢነት የሚጠላ ከመሆኑም ሌላ አጥብቆ ይቃወመዋል። ሰይጣን ከምንም በላይ የሚፈልገው ነገር የይሖዋ ሉዓላዊ ገዢነት ሲያበቃ ማየት ነው። w15 5/15 1:1, 2

እሁድ፣ ሚያዝያ 2

አንድ ሰው አምላክን የሚወድ ከሆነ በእሱ ዘንድ የታወቀ ነው።​—⁠1 ቆሮ. 8:3

ቅዱሳን መጻሕፍትን ማጥናታችን መንፈሳዊነታችንን ለማሻሻል የሚረዱንን ነገሮች ከመጠቆም ባለፈ ሌላም ጥቅም አለው። ተወዳጅ ስለሆኑት የይሖዋ ባሕርያት ያለን አድናቆት እንዲጨምር የሚረዳን ሲሆን ይህም እሱን ይበልጥ እንድንወደው ያደርጋል። ለአምላክ ያለን ፍቅር እየጨመረ ሲሄድ ደግሞ እሱም በምላሹ ይበልጥ ይወደናል፤ ይህም ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና ያጠናክረዋል። ይሁንና ወደ ይሖዋ ለመቅረብ በትክክለኛ ዓላማ ተነሳስተን ማጥናታችን አስፈላጊ ነው። ዮሐንስ 17:3 “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው” ይላል። እንግዲያው የምናጠናው፣ እውቀት ለመቅሰም ብቻ ሳይሆን የይሖዋን ማንነት በተሻለ መንገድ ‘ለማወቅ’ ሊሆን ይገባል። (ዘፀ. 33:​13፤ መዝ. 25:⁠4) ይሖዋን ይበልጥ እያወቅነው መሄዳችን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ዘገባዎችን ስናነብ ይሖዋ አንድ እርምጃ የወሰደበትን ምክንያት መረዳት ባንችል እንኳ ነገሩ ከሚገባ በላይ እንዳያስጨንቀን ያደርጋል። w15 4/15 3:6-8

ሰኞ፣ ሚያዝያ 3

[ጢሞቴዎስ] በየስፍራው በሚገኙ ጉባኤዎች ሁሉ ሳስተምር የምጠቀምባቸውን ይኸውም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በተያያዘ አገልግሎቴን የማከናውንባቸውን ዘዴዎች ያሳስባችኋል።​—⁠1 ቆሮ. 4:​17

ወንድሞችን በመንፈሳዊ እንዲያድጉ በመርዳት ረገድ የተዋጣላቸው አንዳንድ ሽማግሌዎች ሌሎችን ለማሠልጠን ምን ዓይነት ዘዴ​ዎችን እንደተጠቀሙ በቅርቡ ተጠይቀው ነበር። እነዚህ ሽማግሌዎች ያሉበት ሁኔታ በእጅጉ የተለያየ ቢሆንም የሰጡት ምክር በሚያስገርም ሁኔታ ይመሳሰላል። ይህ ምን ይጠቁማል? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ለተማሪዎች የሚሰጠው ይህ ሥልጠና በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን ብቻ ሳይሆን ዛሬም በሁሉም ‘ስፍራ በሚገኙ ጉባኤዎች’ ውስጥ ይሠራል። አስተማሪዎች ለሥልጠና አመቺ ሁኔታ መፍጠር ይኖርባቸዋል። አንድ ገበሬ ዘር ከመዝራቱ በፊት መሬቱን ማለስለስ እንዳለበት ሁሉ አንድ አስተማሪም ተማሪውን ማሠልጠን ከመጀመሩ በፊት የተማሪውን ልብ ማዘጋጀት ይኖርበታል። ታዲያ አስተማሪዎች ሌሎችን ለማሠልጠን አመቺ ሁኔታ መፍጠር የሚችሉት እንዴት ነው? ሳሙኤል፣ ሳኦል የእስራኤልን ሕዝብ እንዲመራ ሲያዘጋጀው የተጠቀመውን ዘዴ በመከተል ነው።​—⁠1 ሳሙ. 9:​15-27፤ 10:1፤ w15 4/15 1:11, 12

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 4

መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው።​—⁠1 ዮሐ. 5:​19

ይህ ዓለም የሚያስፋፋው አብዛኛው ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር ይጋጫል። እርግጥ ነው፣ በዓለም ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ መጥፎ ነው ማለት አይደለም። ያም ቢሆን ሰይጣን፣ በእሱ ቁጥጥር ሥር ባለው ዓለም ተጠቅሞ ምኞታችንን በማነሳሳት ኃጢአት እንድንፈጽም አሊያም ደግሞ ዓለምን በመውደድ ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ ችላ እንድንል ለማድረግ እንደሚጥር መጠበቅ ይኖርብናል። (1 ዮሐ. 2:​15, 16) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ዓለምን መውደድ ወጥመድ የሆነባቸው ይመስላል። ለምሳሌ “ዴማስ በአሁኑ ጊዜ ያለውን ሥርዓት ወዶ፣ ትቶኝ . . . ሄዷል” በማለት ጳውሎስ ጽፏል። (2 ጢሞ. 4:​10) ዴማስ፣ ጳውሎስን እስከ መተው የደረሰው በዓለም ውስጥ ምን ወዶ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አይናገርም። ዴማስ ከመንፈሳዊ ግቦች በላይ ቁሳዊ ነገሮችን መውደድ ጀምሮ ሊሆን ይችላል። ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ዴማስ ውድ የሆኑ መንፈሳዊ መብቶችን አጥቷል፤ ምን ለማግኘት ሲል? እስቲ አስበው፣ የጳውሎስ ባልደረባ ሆኖ ሲያገለግል ይሖዋ ከሚሰጠው በረከት የላቀ ነገር ዓለም ሊያቀርብለት ይችላል?​—⁠ምሳሌ 10:​22፤ w15 5/15 2:10, 11

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 5

ይሖዋ መሐሪና ሩኅሩኅ . . . ነው።​—⁠መዝ. 103:8

ኢየሱስ፣ እሱ ፈጽሞ ደርሶበት የማያውቅ ሁኔታ ያጋጠማቸውን ጨምሮ የሰዎችን ሥቃይ ይረዳ ነበር። ለምሳሌ ሕዝቡ፣ የሚያታልሏቸውን እንዲሁም በርካታ ሰው ሠራሽ ሕግጋትን የሚጭኑባቸውን የሃይማኖት መሪዎች ይፈሩ ነበር። (ማቴ. 23:4፤ ማር. 7:1-5፤ ዮሐ. 7:​13) ኢየሱስ ፈርቶ ወይም ተታሎ ባያውቅም እሱ ያላለፈበትን ሁኔታ መረዳት ይችላል። በመሆኑም “[ሕዝቡን] ባየ ጊዜ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው ስለነበር እጅግ አዘነላቸው።” (ማቴ. 9:​36) እንደ አባቱ ሁሉ ኢየሱስም አፍቃሪና ሩኅሩኅ ነው። ኢየሱስ ሰዎች ሲሠቃዩ በተመለከተ ጊዜ በፍቅር ተነሳስቶ ረድቷቸዋል። እንዲህ በማድረግ የአባቱን ፍቅር ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። በአንድ ወቅት ኢየሱስና ሐዋርያቱ ለስብከት ረጅም መንገድ ተጉዘው ነበር፤ ከዚያም ገለል ወዳለ አንድ ስፍራ በመሄድ ለማረፍ አሰቡ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ እሱን ለሚጠብቁት ሰዎች ስላዘነላቸው ጊዜ ወስዶ ‘ብዙ ነገር ያስተምራቸው ጀመር።’​—⁠ማር. 6:​30, 31, 34፤ w15 5/15 4:3, 4

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 6

በተለይ . . . በሰው ልጆች እጅግ እደሰት ነበር።​—⁠ምሳሌ 8:​31

ጥልቅ የሆነው የይሖዋ ጥበብ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ የተገለጠው በአምላክ የበኩር ልጅ ላይ ነው። ኢየሱስ በጥበብ የተመሰለ ሲሆን “የተዋጣለት ሠራተኛ” ሆኖ ከአባቱ ጎን ነበር። አባቱ “ሰማያትን ባዘጋጀ” ብሎም “የምድርን መሠረቶች ባቆመ ጊዜ” ኢየሱስ ምን ያህል ተደስቶና ሐሴት አድርጎ እንደሚሆን እስቲ አስበው። ይሁንና የአምላክ የበኩር ልጅ ግዑዛን ነገሮችን ቢያደንቅም ‘በተለይ በሰው ልጆች እጅግ ይደሰት ነበር።’ (ምሳሌ 8:​22-31) በእርግጥም ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊትም ለሰው ልጆች ጥልቅ ፍቅር ነበረው። የአምላክ የበኩር ልጅ ከጊዜ በኋላም ለአባቱ ያለውን ፍቅርና ታማኝነት እንዲሁም ‘ለሰው ልጆች’ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ለማሳየት ሲል በፈቃደኝነት “ራሱን ባዶ በማድረግ” ሰው ሆኖ ወደ ምድር መጥቷል። ይህን ያደረገው “በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት” ነው። (ፊልጵ. 2:5-8፤ ማቴ. 20:​28) በእርግጥም ለሰው ልጆች ታላቅ ፍቅር አለው! w15 6/15 2:1, 2

ዓርብ፣ ሚያዝያ 7

እኛ በእሱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል።​—⁠1 ዮሐ. 4:9

ይሖዋ ላደረገልህ ነገር አድናቆት አለህ? ከሆነ ራስህን ለይሖዋ መወሰንና መጠመቅ ይኖርብሃል። ራስን መወሰን የይሖዋን ፈቃድ በሕይወትህ ውስጥ ከማንኛውም ነገር በላይ በማስቀደም እሱን ለዘላለም ለማገልገል የምትገባው ቃል ኪዳን እንደሆነ አስታውስ። ታዲያ እንዲህ ያለ ከባድ እርምጃ መውሰድ ሊያስፈራህ ይገባል? በፍጹም! ይሖዋ ምንጊዜም በሕይወትህ ደስተኛ እንድትሆን እንደሚፈልግ፣ “ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን” አትርሳ። (ዕብ. 11:⁠6) ራስህን ለይሖዋ መወሰንህና መጠመቅህ ሕይወትህ እንዲበላሽ አያደርግም። ከዚህ በተቃራኒ ይሖዋን ማገልገል የተሻለ ሕይወት እንድትመራ ያስችልሃል። ይሖዋ ከሰይጣን ምንኛ የተለየ ነው! የሰይጣን ፍላጎት አንተን መጠቀሚያ ማድረግ ብቻ ነው። ከእሱ ጎን ለሚቆሙ ሰዎች የሚሰጣቸው ዘላቂ ጥቅም የለም። ታዲያ እሱ ራሱ የሌለውን ነገር እንዴት ሊሰጥህ ይችላል? w16.03 2:16, 18, 19

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 9፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ሉቃስ 19:​29-44

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 8

አባት ሆይ፣ ስለሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። እውነት ነው፣ ሁልጊዜ እንደምትሰማኝአውቃለሁ።​—⁠ዮሐ. 11:​41, 42

ከይሖዋ ጋር ያለህ ግንኙነት ጠንካራ መሆን እንዲችል ስትጸልይ እንደሚሰማህ እርግጠኛ መሆን አለብህ። እስቲ ይህን አስብ፦ ይሖዋ ሰብዓዊ አገልጋዮቹ የሚያቀርቡለትን ጸሎት ሲመልስ ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ተመልክቷል። እሱም በምድር ላይ አገልግሎቱን ሲያከናውን በሰማይ ላለው አባቱ ስሜቱን አውጥቶ ለመግለጽ በጸሎት ተጠቅሟል። እንዲያውም በአንድ ወቅት ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ አድሯል፤ ታዲያ ኢየሱስ፣ ይሖዋ እንደሚሰማው እርግጠኛ ባይሆን ኖሮ እንዲህ ያደርግ ነበር? (ሉቃስ 6:​12፤ 22:​40-46) ጸሎት አእምሮን ከማረጋጋት ያለፈ ጥቅም እንደሌለው ቢሰማው ኖሮ ደቀ መዛሙርቱን እንዲጸልዩ ያስተምራቸው ነበር? ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ጸሎት፣ ከይሖዋ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችል መንገድ እንደሆነ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። እኛም ይሖዋ “ጸሎት ሰሚ” አምላክ እንደሆነ መተማመን እንችላለን።​—⁠መዝ. 65:2፤ w15 4/15 3:11, 13

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 10፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ሉቃስ 19:​45-48፤ ማቴዎስ 21:​18, 19፤ 21:​12, 13

እሁድ፣ ሚያዝያ 9

አባ፣ አባት ሆይ፣ አንተ ሁሉን ነገር ማድረግ ትችላለህ፤ ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ። ሆኖም እኔ የምፈልገው ሳይሆን አንተ የምትፈልገው ይሁን።​—⁠ማር. 14:​36

ከልጆቻችሁ ጋር ሆናችሁ በትሕትና ስትጸልዩ ልጆቻችሁ በይሖዋ መታመንን ይማራሉ። በብራዚል የምትኖረው አና እንዲህ ብላለች፦ “በቤተሰባችን ውስጥ ችግሮች በሚኖሩበት ጊዜ ለምሳሌ አያቶቼ በታመሙበት ወቅት ወላጆቼ ሁኔታውን ለመቋቋም የሚያስችላቸው ጥንካሬና ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳቸው ጥበብ እንዲሰጣቸው ወደ ይሖዋ ይጸልዩ ነበር። በጣም የሚያስጨንቅ ሁኔታ በሚያጋጥማቸው ጊዜም እንኳ ጉዳዩን ለይሖዋ ይተዉት ነበር። ይህም በይሖዋ መታመንን አስተምሮኛል።” ከልጆቻችሁ ጋር ስትጸልዩ ስለ እነሱ ብቻ አትጸልዩ። ይሖዋ እናንተንም እንዲረዳችሁ ጠይቁት፤ ለምሳሌ በትልቅ ስብሰባ ላይ መገኘት እንድትችሉ አሠሪያችሁ ፈቃድ እንዲሰጣችሁ ለማነጋገር ወይም ለጎረቤታችሁ ለመመሥከር ይሖዋ ድፍረት እንዲሰጣችሁ አሊያም በሌሎች ጉዳዮች እንዲረዳችሁ ጸልዩ። ትሑት በመሆን በአምላክ እንደምትታመኑ ካሳያችሁ ልጆቻችሁም ይህን ማድረግ ይማራሉ። w15 11/15 1:7, 8

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 11፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ሉቃስ 20:1-47

ሰኞ፣ ሚያዝያ 10

አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።​—⁠ማቴ. 22:​37

ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ማሳደግ ከምትችልባቸው ከሁሉ የተሻሉ መንገዶች አንዱ ይሖዋ በሰጠን እጅግ የላቀ ስጦታ ማለትም በልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ማሰላሰል ነው። (2 ቆሮ. 5:​14, 15፤ 1 ዮሐ. 4:9, 19) ስለ ቤዛው እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ለአንተ ስላለው ትርጉም ማሰብህ የአድናቆት ስሜት እንዲያድርብህ ያደርጋል። ለቤዛው ስጦታ የምትሰጠውን ምላሽ ለማስረዳት አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ አንድ ሰው ከመስመጥ አዳነህ እንበል። ቤት ሄደህ ሰውነትህን ካደራረቅክ በኋላ የተደረገልህን ነገር በሙሉ ትረሳለህ? በጭራሽ! ከሞት ላዳነህ ሰው ትልቅ ውለታ እንዳለብህ እንደሚሰማህ ጥርጥር የለውም። እንደ እውነቱ ከሆነ ያ ሰው በሕይወት እንድትቀጥል አስችሎሃል! ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ የላቀ ውለታ ውለውልናል። ይሖዋ ባደረገልን በዚህ ታላቅ የፍቅር መግለጫ የተነሳ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ወደር የለሽ ተስፋ ተከፍቶልናል! w16.03 2:16, 17

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 12፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ሉቃስ 22:1-6፤ ማርቆስ 14:1, 2, 10, 11

የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ዕለት
ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 11

ክርስቶስ [ሞቶልናል]።​—⁠ሮም 5:8

ይሖዋ፣ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት ከእሱ ጋር በሰማይ ሲኖር ታማኝነቱን ባሳየው አንድያ ልጁ ሙሉ በሙሉ ይተማመናል። ኢየሱስ በምድር ላይ እጅግ ከባድ የሆነ ፈተና ቢደርስበትም ንጹሕ አቋሙን የጠበቀ ከመሆኑም በላይ የይሖዋን ሉዓላዊነት በመደገፍ ለአባቱ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሆኗል። ከዚህም ሌላ ኢየሱስ በሞቱ አማካኝነት የቤዛውን ዋጋ በመክፈሉ ምንኛ አመስጋኞች ነን! ይህን ማድረጉ የሰው ልጆች የሚቤዡበትና አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉበት መንገድ ከፍቷል። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የአምላክ ፍቅር ከእኛ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በዚህ መንገድ ተገልጧል፤ እኛ በእሱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል። ይህ ፍቅር የተገለጠው በዚህ መንገድ ነው፦ እኛ አምላክን ስለወደድነው ሳይሆን እሱ ስለወደደንና ለኃጢአታችን የማስተሰረያ መሥዋዕት እንዲሆን ልጁን ስለላከ ነው።”​—⁠1 ዮሐ. 4:9, 10፤ w15 11/15 3:13, 14

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 13፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ሉቃስ 22:7-13፤ ማርቆስ 14:​12-16 (ኒሳን 14፦ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች) ሉቃስ 22:​14-65

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 12

ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።​—⁠ሮም 5:​12

የመጀመሪያው ሰው የአዳም ልጆች በመሆናችን ሁላችንም ኃጢአትንና የኃጢአት ደሞዝ የሆነውን ሞትን ወርሰናል። ማናችንም ብንሆን “ቤዛው አያስፈልገኝም” ማለት አንችልም። በጣም ታማኝ የሆነ የአምላክ አገልጋይም እንኳ ይሖዋ በክርስቶስ በኩል ያሳየን ጸጋ የግድ ያስፈልገዋል። ሁላችንም ከፍተኛ ዕዳ እንደተሰረዘልን መገንዘብ ይኖርብናል። ታዲያ የይሖዋ ፍቅርና ምሕረት ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል? በወንድሞቻችን ወይም በእህቶቻችን ላይ ቂም ይዘን ከሆነ “ይቅር ለማለት ዝግጁ” የሆነውን ይሖዋን መምሰል ይኖርብናል። (ነህ. 9:​17፤ መዝ. 86:⁠5) ይሖዋ ከፍተኛ መጠን ያለውን ዕዳችንን በመሰረዝ ላደረገልን ነገር አድናቆት ካለን እኛም ሌሎችን ከልባችን ይቅር ለማለት እንነሳሳለን። ለሌሎች ፍቅርና ምሕረት የማናሳይ ከሆነ አምላክ ሊወደን ወይም ይቅር ሊለን አይችልም። (ማቴ. 6:​14, 15) ይቅር ማለታችን የደረሰብንን በደል ባያስቀረውም በወደፊት ሕይወታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ጥርጥር የለውም። w16.01 2:5, 15-17

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 14፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ሉቃስ 22:​66-71

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 13

እኔን የተከተላችሁኝ እናንተ በ12 ዙፋኖች ላይ ተቀምጣችሁ በ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ።​—⁠ማቴ. 19:​28

ጴጥሮስና ሌሎች ደቀ መዛሙርት የወደፊቱን ጊዜ በአእምሯቸው እንዲስሉ ለመርዳት ኢየሱስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ነገራቸው። እነሱም ምድርን በሚያስተዳድረውና ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች አስደናቂ በረከቶችን በሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ውስጥ በሚኖራቸው ድርሻ ላይ ማሰላሰል ይችሉ ነበር። በየትኛውም ጊዜ በምድር ላይ የኖሩ የአምላክ አገልጋዮች፣ አምላክ ቃል ስለገባቸው ነገሮች ፍጻሜ በማሰባቸው ተጠቅመዋል። አቤል ስለ አምላክ ዓላማ ያወቀው ነገር የተሻለ የወደፊት ሕይወት እንደሚመጣ ለማሰብ፣ እምነት ለማዳበርና አስተማማኝ ተስፋ እንዳለው ለማመን አስችሎታል። አብርሃም ታላቅ እምነት እንዳለው የሚያሳዩ ነገሮችን ያከናወነው፣ ተስፋ ከተሰጠበት “ዘር” ጋር በተያያዘ አምላክ ስለተናገረው ትንቢት ፍጻሜ በዓይነ ሕሊናው በማየቱ ነው። (ዘፍ. 3:​15) ሙሴ “የሚከፈለውን ወሮታ በትኩረት ተመልክቷል”፤ በመሆኑም እምነትና ለይሖዋ ፍቅር ማዳበር ችሏል። (ዕብ. 11:​26) በአምላክ ላይ ያለን እምነትና ለእሱ ያለን ፍቅር ይሖዋ ቃል የገባቸውን ነገሮች በዓይነ ሕሊናችን እንድንመለከት ሊረዳን ይችላል። w15 5/15 3:17, 18

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 15፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 27:​62-66

ዓርብ፣ ሚያዝያ 14

ክርስቶስ . . . የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ [ትቶላችኋል]።​—⁠1 ጴጥ. 2:​21

በመንፈሳዊ እድገት ማድረግ የሚፈልግ ክርስቲያን ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በመከተል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖረው የተቻለውን ጥረት ያደርጋል። ‘ጠንካራ ምግብ ለጎልማሳ ሰዎች’ እንደሆነ በመገንዘብ በየጊዜው ቃሉን በጥልቀት ይቆፍራል። (ዕብ. 5:​14) አንድ ጎልማሳ ክርስቲያን “ስለ አምላክ ልጅ ትክክለኛ እውቀት” መቅሰም እንደሚፈልግ የታወቀ ነው። (ኤፌ. 4:​13) በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን የምታነብበት ፕሮግራም አለህ? የግል ጥናት የምታደርግበትስ ቋሚ ፕሮግራም አለህ? በየሳምንቱ የቤተሰብ አምልኮ ለማድረግ ጊዜ መድበሃል? የአምላክን ቃል ስታጠና የይሖዋን አመለካከትና ስሜት ይበልጥ እንድትረዳ የሚያስችሉህን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማግኘት ጥረት አድርግ። ከዚያም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመሥርተህ ውሳኔ አድርግ፤ እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እየቀረብክ ትሄዳለህ። w15 9/15 1:5, 9, 10

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 16፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ሉቃስ 24:1-12

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 15

[ክርስቶስ] የአምላክ ኃይል . . . ነው።​—⁠1 ቆሮ. 1:​24

ኢየሱስ ስለ ምድር ሥነ ምህዳር በሚገባ ያውቃል። የምድርን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መጠቀም፣ ማስተዳደር እንዲሁም ለነዋሪዎቹ ማዳረስ ይችልበታል። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ የተፈጥሮ ኃይሎችን በመቆጣጠር “የአምላክ ኃይል” መሆኑን አሳይቷል። የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር፦ ክርስቶስ አገልግሎቱን ሲያከናውን በመዋሉ በጣም ደክሞታል። ማዕበሉ ጀልባዋን እያንገላታት ብሎም ጀልባዋ ውስጥ ውኃ ተረጭቶ እየገባ ነው። የማዕበሉ ድምፅ ኃይለኛ ከመሆኑም ሌላ ጀልባዋ እየተናጠች ቢሆንም ኢየሱስ ድብን ያለ እንቅልፍ ወስዶታል። ሰውነቱ በጣም ዝሏል። በፍርሃት የተዋጡት ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን ቀስቅሰው “ማለቃችን እኮ ነው” አሉት። (ማቴ. 8:​25) ኢየሱስ ከእንቅልፉ ተነስቶ ነፋሱንና ባሕሩን “ጸጥ በል! ረጭ በል!” አለው፤ አውሎ ነፋሱም ቆመ። (ማር. 4:​39) ኢየሱስ ነፋሱንና ባሕሩን ረጭ እንዲሉ እያዘዘ ነበር። ውጤቱ ምን ሆነ? መጽሐፍ ቅዱስ “ታላቅ ጸጥታም ሰፈነ” ይላል። ኢየሱስ ምንኛ ታላቅ ኃይል አለው! w15 6/15 1:12-14

እሁድ፣ ሚያዝያ 16

የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን።​—⁠ማቴ. 6:​11

ኢየሱስ ስለ ዕለት ምግባችን ሲጠቅስ በየቀኑ ስለሚያስፈልገን ነገር መናገሩ እንደሆነ ግልጽ ነው። አምላክ፣ አበቦችን እንደሚያለብስ ከገለጸ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም?” ከዚያም “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ” የሚለውን ጠቃሚ ምክር በድጋሚ በመናገር ሐሳቡን ደመደመ። (ማቴ. 6:​30-34) ይህም ለቁሳዊ ነገሮች ፍቅር ከማዳበር ይልቅ መሠረታዊ ስለሆኑት በየዕለቱ የሚያስፈልጉን ነገሮች ብቻ ማሰብ እንዳለብን ያሳያል። ከእነዚህ ፍላጎቶች መካከል ተስማሚ መኖሪያ፣ ቤተሰባችንን ለማስተዳደር የሚያስችለን ሥራ እንዲሁም የጤና ችግሮችን ለመወጣት የሚረዳን ጥበብ ይገኙበታል። ይሁንና የምንጸልየው ከአካላዊ ፍላጎታችን ጋር ስለተያያዙት ስለ እነዚህ ነገሮች ብቻ ከሆነ ይህ ሚዛናዊ እንዳልሆንን የሚጠቁም ነው። ምክንያቱም ከዚህ ይበልጥ ትልቅ ቦታ ልንሰጠው የሚገባ መንፈሳዊ ፍላጎት አለን። ጌታችን “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም” ብሏል። (ማቴ. 4:⁠4) እንግዲያው ይሖዋ በጊዜው መንፈሳዊ ምግብ ማቅረቡን እንዲቀጥል ምንጊዜም ልንጸልይ ይገባል። w15 6/15 5:4, 7, 8

ሰኞ፣ ሚያዝያ 17

ከክፉው አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።​—⁠ማቴ. 6:​13

ፈተና ሲያጋጥመን ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ እንዲረዳን አምላክን አዘውትረን እንለምነዋለን? አስተዳደጋችን ወይም የቀድሞ አኗኗራችን ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች እንድንወድ ተጽዕኖ ያደርግብን ይሆናል። ያም ቢሆን ይሖዋ፣ እሱን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማገልገላችንን እንድንቀጥል የሚያስፈልጉትን ለውጦች ለማድረግ ይረዳናል። ንጉሥ ዳዊት ይህን ተገንዝቦ ነበር። ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ከፈጸመ በኋላ ይሖዋን “ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ በውስጤም ጽኑ የሆነ አዲስ መንፈስ አኑር” በማለት ተማጽኖታል። (መዝ. 51:​10, 12) ደካማው ሥጋችን በኃጢአት ድርጊቶች በቀላሉ ሊማረክ ይችላል፤ ይሁንና ይሖዋ የፈቃደኝነት መንፈስ ይኸውም እሱን የመታዘዝ ፍላጎት በውስጣችን እንዲቀሰቀስ ሊረዳን ይችላል። መጥፎ ምኞቶች በውስጣችን ሥር ሰደው ንጹሕ ሐሳቦችን ገፍተው ለማውጣት ቢሞክሩም እንኳ ይሖዋ የእሱን መመሪያዎች በመታዘዝ በዚያ መሠረት መኖር እንድንችል አካሄዳችንን ይመራልናል። ይሖዋ ማንኛውም ጎጂ ነገር በእኛ ላይ እንዳይሠለጥን ሊከላከልልን ይችላል።​—⁠መዝ. 119:​133፤ w15 6/15 3:5, 6

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 18

በብዙ አማካሪዎችም ድል ይገኛል።​—⁠ምሳሌ 24:6

በመካከላችን ያሉ አንዳንድ አረጋውያን ጉባኤዎች በሽማግሌዎች አካል ሳይሆን በአንድ የጉባኤ አገልጋይ፣ አገሮች ደግሞ በቅርንጫፍ ኮሚቴ ሳይሆን በአንድ የበላይ ተመልካች ይመሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፤ በተጨማሪም መመሪያ የሚተላለፈው በግልጽ በሚታወቀው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አማካኝነት ሳይሆን በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት በኩል እንደነበረም ትዝ ይላቸው ይሆናል። ሥራውን በኃላፊነት የሚመሩት ለአምላክ ያደሩ ወንድሞች፣ ከሌሎች ታማኝ ወንድሞች እገዛ ያገኙ የነበረ ቢሆንም በጉባኤዎች፣ በቅርንጫፍ ቢሮዎችና በዋናው መሥሪያ ቤት ውስጥ ውሳኔ የሚያስተላልፉት ብቻቸውን ነበር። በ1970ዎቹ የተደረጉት ማስተካከያዎች የበላይ ተመልካችነት ኃላፊነትን የሚይዘው አንድ ግለሰብ መሆኑ ቀርቶ የሽማግሌዎች አካል እንዲሆን መንገድ ከፍተዋል። ማስተካከያዎቹ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘውን አሠራር በተመለከተ ባገኘነው ተጨማሪ እውቀት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። አንድ ግለሰብ ብቻ የመወሰን ኃላፊነት ከሚኖረው ይልቅ ይሖዋ “ስጦታ አድርጎ” የሰጠን “ሰዎች” ሁሉ ያላቸው መልካም ችሎታ አንድ ላይ መቀናጀቱ ድርጅቱ እንዲጠቀም አድርጓል።​—⁠ኤፌ. 4:8፤ w15 7/15 1:14, 15

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 19

የዓለም ክፍል አይደሉም።​—⁠ዮሐ. 17:​16

ክርስቲያኖች በጦርነት ጊዜ ብቻ ሳይሆን መቼም ቢሆን ታማኝ የመሆናቸውና የገለልተኝነት አቋማቸውን የመጠበቃቸው ጉዳይ ያሳስባቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሁሉ እሱን ሊወዱት፣ ታማኝ ሊሆኑለትና ሊታዘዙት ቃል ገብተዋል። (1 ዮሐ. 5:⁠3) የምንኖረው የትም ይሁን የት እንዲሁም አስተዳደጋችን፣ ዜግነታችን ወይም ባሕላችን ምንም ይሁን ምን በአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ለመመራት እንፈልጋለን። ለይሖዋና ለመንግሥቱ ያለንን ታማኝነት ለሌላ ለማንኛውም ነገር ካለን ፍቅር እናስበልጣለን። (ማቴ. 6:​33) ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ታማኝነት ለማሳየት በዚህ ዓለም ላይ በሚፈጠር በየትኛውም ግጭት ወይም ውዝግብ ውስጥ ከመግባት መቆጠብ አለባቸው። (ኢሳ. 2:4፤ ዮሐ. 17:​11, 15, 16) የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች ለአገራቸው፣ ለዘራቸው ወይም ለባሕላቸው አልፎ ተርፎም ለብሔራዊ የስፖርት ቡድናቸው ልዩ ታማኝነት ማሳየት እንዳለባቸው ይሰማቸው ይሆናል። እንዲህ ያለው ታማኝነት የውድድርና የፉክክር መንፈስ እንዲኖር ይባስ ብሎም ደም መፋሰስና የጅምላ ጭፍጨፋ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል። እኛም በዓለም ላይ ባሉ ውዝግቦች ረገድ ሳናስበው ከአንዱ ወገን እንቆም እንዲሁም በቀላሉ ውዝግቡ ውስጥ እንገባ ይሆናል። w15 7/15 3:1, 2

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 20

ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት ይሁን።​—⁠1 ቆሮ. 14:​40

አንድ የመንግሥት አዳራሽ ተገንብቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ የምናመልከውን አምላክ ባሕርያትና ማንነት ይኸውም የሥርዓት አምላክ መሆኑን የሚያንጸባርቅ እንዲሆን በንጽሕና መያዝ አለበት። (1 ቆሮ. 14:​33) መጽሐፍ ቅዱስ ቅድስናን እንዲሁም መንፈሳዊ ንጽሕናን ከአካላዊ ንጽሕና ጋር ያያይዘዋል። (ራእይ 19:⁠8) በመሆኑም አንድ ሰው በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ከፈለገ ንጽሕናውንም መጠበቅ አለበት። ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንጻር የአዳራሹ ሁኔታ ከምንሰብከው ምሥራች ጋር የሚስማማ መሆን አለበት፤ ይህም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ምንጊዜም ወደ ስብሰባዎቻችን ለመጋበዝ ነፃነት እንዲሰማን ያደርጋል። የምንጋብዛቸው ሰዎች አምላካችን ቅዱስ እንደሆነ መመልከት እንዲሁም በቅርቡ ምድርን በመለወጥ ከብክለት የጸዳች ገነት እንደሚያደርጋት መገንዘብ ይችላሉ። (ኢሳ. 6:1-3፤ ራእይ 11:​18) በአካባቢው ያለው ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ የመንግሥት አዳራሾቻችን ንጹሕና ሥርዓታማ በመሆን ረገድ አርዓያ ሊሆኑ ይገባል፤ ምክንያቱም የይሖዋ ስም የሚጠራባቸው ከመሆኑም ሌላ የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ናቸው።​—⁠ዘዳ. 23:​14፤ w15 7/15 4:13-15

ዓርብ፣ ሚያዝያ 21

ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።​—⁠ማር. 13:​35

የኢየሱስ ተከታዮች፣ ክርስቶስ ከ1914 አንስቶ በሥልጣኑ ላይ መገኘቱን ስለተገነዘቡ በማንኛውም ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል በማሰብ ዝግጁ ሆነው እየጠበቁ ነው። ይህን የሚያደርጉት የመንግሥቱን የስብከት ሥራ በማጧጧፍ ነው። ኢየሱስ የሚመጣው በኋላ ላይ ይኸውም “ዶሮ ሲጮኽ” አሊያም “ንጋት ላይ” ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል። ይህ ከሆነ ታዲያ ተከታዮቹ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ኢየሱስ “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ” ብሏል። እንግዲያው ረጅም ጊዜ ስለጠበቁ ብቻ መጨረሻውን አርቀው ቢመለከቱ ወይም በተስፋ መጠባበቃቸውን ቢያቆሙ ተገቢ አይሆንም። እስቲ በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንዳለን አድርገን እናስብ፤ ከሥርዓቱ መደምደም ጋር የተያያዙ ትንቢቶች በሙሉ ልክ ይሖዋ እንደተናገረው ተፈጽመዋል። በዚያ ወቅት በእነዚህ ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል፤ እንዲሁም ቃል የገባቸውን ሌሎች ነገሮች እንደሚፈጽም ይበልጥ እንተማመናለን። (ኢያሱ 23:​14) በእርግጥም “ጊዜያትንና ወቅቶችን የመወሰን ሥልጣን ያለው” አምላክ፣ “የሁሉም ነገር መጨረሻ [እንደቀረበ]” እንድንገነዘብና ነቅተን እንድንኖር ለሰጠን ማሳሰቢያ አመስጋኞች እንደምንሆን ጥርጥር የለውም።​—⁠ሥራ 1:7፤ 1 ጴጥ. 4:7፤ w15 8/15 2:10, 11, 14

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 22

የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል።​—⁠2 ጢሞ. 3:​12

ብዙ ሰዎች ለመዝናናት ብለው የሚያዩአቸው ወይም የሚፈጽሟቸው ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ ዓመፅ፣ የፆታ ብልግና፣ መናፍስትነት ወይም ርኩሰት እንደሆኑ የሚገልጻቸው ድርጊቶች ናቸው። ለምሳሌ ኢንተርኔት፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ፊልሞች፣ ልብ ወለድ መጻሕፍትና መጽሔቶች ዓመፅንና የፆታ ብልግናን እንደ መልካም ነገር አድርገው ያቀርባሉ። በአንድ ወቅት ተቀባይነት እንደሌላቸው የሚታዩ ድርጊቶች በአሁኑ ጊዜ ተቀባይነት ከማግኘትም አልፈው በአንዳንድ አገሮች ሕጋዊ ሆነዋል። ይህ መሆኑ ግን እነዚህ ድርጊቶች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ አያደርግም። (ሮም 1:​28-32) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ የኢየሱስ ተከታዮች ርኩስ ከሆነ መዝናኛ ይርቁ ነበር። እንዲህ በማድረጋቸውና አምላካዊ ባሕርያትን በማንጸባረቃቸው መጥፎ ስም ይሰጣቸው እንዲሁም ስደት ይደርስባቸው ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን በመሰለው ያዘቀጠ ወራዳ ሕይወት ከእነሱ ጋር መሮጣችሁን ስለማትቀጥሉ ግራ ይጋባሉ፤ በመሆኑም ይሰድቧችኋል።”​—⁠1 ጴጥ. 4:4፤ w15 8/15 4:2, 3

እሁድ፣ ሚያዝያ 23

እያንዳንዱ የአካል ክፍል በአግባቡ ሥራውን ማከናወኑ አካሉ ራሱን በፍቅር እያነጸ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያበረክታል።​—⁠ኤፌ. 4:​16

አንድ የጎለመሰ የይሖዋ አገልጋይ በጉባኤው ውስጥ አንድነት እንዲሰፍን ይጥራል። (ኤፌ. 4:1-6, 15) የአምላክ ሕዝቦች “እርስ በርስ ተስማምተው” እንዲኖሩና ሁሉም እርስ በርስ እንዲደጋገፉ እንፈልጋለን። የይሖዋ ቃል በሚለው መሠረት ይህ አንድነት እንዲኖር ከተፈለገ ትሕትናን ማዳበር ያስፈልገናል። አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን በሌሎች አለፍጽምና ቢጎዳም እንኳ የጉባኤው አንድነት እንዳይናጋ በትሕትና ጥረት ማድረጉን ይቀጥላል። በጉባኤ ውስጥ የሚገኝ አንድ ክርስቲያን ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያደርግ ብታይ ምን ይሰማሃል? ወይም አንድ የጉባኤህ አባል በግለሰብ ደረጃ አንተን ቢበድልህ ምን ታደርጋለህ? ካስቀየመህ ሰው ጋር ላለመገናኘት ምሳሌያዊ ግንብ መገንባት ይቀናሃል? ወይስ በሁለታችሁ መካከል የተፈጠረው ክፍተት እንዳያራርቃችሁ ድልድይ ለመገንባት ትሞክራለህ? አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ግንብ ሳይሆን ድልድይ ለመገንባት ጥረት ያደርጋል። ለጉባኤው አንድነት የበኩልህን ድርሻ ለማበርከት ጥረት ታደርጋለህ? w15 9/15 1:12, 13

ሰኞ፣ ሚያዝያ 24

ቃልህ እውነት ነው።​—⁠ዮሐ. 17:​17

ኢየሱስ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ የተሻለ የሕይወት መመሪያ እንደሆነ በእርግጠኝነት ያምን ነበር። የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ማንበብ፣ ማጥናትና ባወቅነው ነገር ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስን በጥቅሉ ከማጥናት በተጨማሪ ጥያቄዎች በሚፈጥሩብህ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምርምር አድርግ። ለምሳሌ ያህል፣ የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ መሆኑን የሚያሳየውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ በዝርዝር በማጥናት የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ በእርግጥ እንደቀረበ ያለህን እምነት ማጠናከር ትችላለህ። ከዚህ በፊት ፍጻሜያቸውን ያገኙ በርካታ ትንቢቶችን በማጥናት ገና ፍጻሜያቸውን ባላገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ላይ ያለህን እምነት አጠናክር። መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት እንደሚለውጥ የሚያሳዩ ተሞክሮዎችን በማንበብ የአምላክ ቃል የያዘው ምክር ጠቃሚ መሆኑን በተመለከተ ያለህን እምነት ገንባ። (1 ተሰ. 2:​13) በተጨማሪም ይሖዋ በገባልህ ግሩም ተስፋዎች ላይ በማሰላሰል የኢየሱስን አርዓያ መከተል ትችላለህ። (ዕብ. 12:⁠2) አምላክ የሰጣቸው እነዚህ ተስፋዎች በጥቅሉ ለሰው ልጆች ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ለአንተ እንደተሰጡ አድርገህ አስብ። w15 9/15 3:16, 17

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 25

ባሉህ ውድ ነገሮች . . . ይሖዋን አክብር።​—⁠ምሳሌ 3:9

አምላክን እንደምንወደው ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? በአገራችንም ሆነ በዓለም ዙሪያ የሚካሄደውን የመንግሥቱን ሥራ ባለን ሀብት መደገፍ እንችላለን። በቁሳዊ ረገድ ያለን ብዙም ይሁን ጥቂት ለይሖዋ ያለንን ፍቅር በዚህ መንገድ መግለጽ እንደምንችል የታወቀ ነው። (2 ቆሮ. 8:​12) ይሁን እንጂ ይሖዋን እንደምንወደው ማሳየት የምንችልበት ሌላም መንገድ አለ። ኢየሱስ ለተከታዮቹ ስለ ምግብና ልብስ መጨነቃቸውን ትተው መንግሥቱን እንዲያስቀድሙ ማሳሰቢያ እንደሰጣቸው አስታውስ። ኢየሱስ በሰማይ የሚኖረው አባታችን የሚያስፈልገንን ነገር እንደሚያውቅ ተናግሯል። (ማቴ. 6:​31-33) አምላክ በገባልን በዚህ ቃል ላይ ያለን እምነት ለይሖዋ ያለን ፍቅር ምን ያህል ጥልቀት እንዳለው ያሳያል፤ ምክንያቱም ፍቅርና እምነት የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው። የማናምነውን ሰው ልንወደው አንችልም። (መዝ. 143:⁠8) በመሆኑም ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘የማወጣቸው ግቦችና አኗኗሬ ይሖዋን በእርግጥ እንደምወደው ያሳያሉ? በእያንዳንዱ ቀን የማደርገው ነገር ይሖዋ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ሊያሟላልኝ እንደሚችል እምነት እንዳለኝ ያሳያል?’ w15 9/15 5:7, 8

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 26

ያለ እምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም።​—⁠ዕብ. 11:6

‘ከታላቁ መከራ በሕይወት ተርፈው ወደ አዲሱ ዓለም እንዲገቡ ይሖዋ ከሚፈቅድላቸው ሰዎች መካከል እገኝ ይሆን?’ ብለህ ጠይቀህ ታውቃለህ? ለመዳን ከሚያስፈልጉት ባሕርያት መካከል አንዱ ጠንካራ እምነት ማዳበር ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን፣ ግርማንና ክብርን” ለማግኘት “ተፈትኖ የተረጋገጠ” እምነት እንደሚያስፈልግ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (1 ጴጥ. 1:⁠7) ታላቁ መከራ በፍጥነት እየቀረበ በመሆኑ ክብር የተጎናጸፈው ንጉሣችን በሚገለጥበት ጊዜ በእምነታቸው የተነሳ ከሚያመሰግናቸው ሰዎች መካከል መሆን እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። በእርግጥም፣ “በሕይወት የሚያኖር እምነት” ማዳበር እንፈልጋለን። (ዕብ. 10:​39) ይህን ግብ በአእምሯችን በመያዝ “እምነቴ እንዲጠነክር ደግሞ አንተ እርዳኝ!” ሲል የተማጸነው ሰው ያቀረበው ዓይነት ልመና ማቅረብ እንችላለን። (ማር. 9:​24) አሊያም “እምነት ጨምርልን” እንዳሉት የኢየሱስ ሐዋርያት ለማለት እንገፋፋ ይሆናል።​—⁠ሉቃስ 17:5፤ w15 10/15 2:1, 2

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 27

ማንኛውንም ሸክም . . . ከላያችን አንስተን እንጣል።​—⁠ዕብ. 12:1

ጳውሎስ ‘ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች’ ላይ ትኩረት ያደረገ ከመሆኑም በላይ ወደ ሶርያ፣ ትንሿ እስያ፣ መቄዶንያና ይሁዳ ብዙ ጊዜ በመሄድ አምላክን በትጋት አገልግሏል። ጳውሎስ “ከኋላዬ ያሉትን ነገሮች እየረሳሁ ከፊቴ ወዳሉት ነገሮች እንጠራራለሁ፤ . . . የሰማያዊውን ሕይወት ሽልማት አገኝ ዘንድ ግቡ ላይ ለመድረስ እየተጣጣርኩ ነው” በማለት ጽፏል። (ፊልጵ. 1:​10፤ 3:8, 13, 14) ነጠላ መሆኑ ባስገኘለት አጋጣሚ ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ‘ሐሳቡ ሳይከፋፈል ዘወትር ለጌታ ያደረ’ መሆን ችሏል። (1 ቆሮ. 7:​32-35) እንደ ጳውሎስ ሁሉ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮችም ነጠላ ሆነው ለመኖር ወስነዋል፤ ይህ ደግሞ የቤተሰብ ኃላፊነት እንዳይበዛባቸው ስለሚያደርግ የመንግሥቱን አገልግሎት በቅንዓት ለማከናወን አስችሏቸዋል። (ማቴ. 19:​11, 12) አብዛኛውን ጊዜ ያገቡ ክርስቲያኖች ብዙ የቤተሰብ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል። ይሁንና ያገቡም ሆኑ ያላገቡ ክርስቲያኖች ‘ማንኛውንም ሸክም አንስተው በመጣል’ ብዙ ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች ሳይኖሩባቸው አምላክን ማገልገል ይችላሉ። ይህ ደግሞ ጊዜ የሚያባክኑ ልማዶችን ማስወገድና በአምላክ አገልግሎት የሚያሳልፉትን ጊዜ ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ግብ ማውጣት ይጠይቅባቸው ይሆናል። w15 10/15 3:15, 16

ዓርብ፣ ሚያዝያ 28

ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች . . . በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ።​—⁠2 ጢሞ. 3:​13

“ይሖዋ ሆይ፣ የሰው መንገድ በራሱ እጅ እንዳልሆነ በሚገባ አውቃለሁ። አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ትክክል መሆኑን ታሪክ በበቂ ሁኔታ አረጋግጧል። (ኤር. 10:​23) በእርግጥም ይሖዋ የሰው ልጆችን ሲፈጥር ከእሱ አገዛዝ ርቀው ራሳቸውን ለመምራት የሚያበቃ ችሎታም ሆነ መብት አልሰጣቸውም። አምላክ ክፋት ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀጥል መፍቀዱ የሰዎች አገዛዝ ከንቱ እንደሆነ ከማሳየቱም ባሻገር ዘላቂ ጥቅም አለው። ውጤታማ የሚሆነው የአምላክ አገዛዝ ብቻ እንደሆነ በማያዳግም ሁኔታ ያረጋግጣል። ይሖዋ ክፋትንና ክፉ አድራጊዎችን ካጠፋ በኋላ፣ የእሱ አገዛዝ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ስለመሆኑ ጥያቄ የሚያነሳ አካል ቢኖር አምላክ ይህ ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ጊዜ መስጠት አያስፈልገውም። እንዲህ ያሉት ዓመፀኞች ወዲያውኑ ሊጠፉ እንጂ ክፋትን እንደገና እንዲያስፋፉ ሊፈቀድላቸው እንደማይገባ የሰው ልጆች ታሪክ በቂ ማስረጃ ይሆናል። w15 11/15 3:5, 6

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 29

የሰላም አምላክ ፈቃዱን እንድታደርጉ በመልካም ነገር ሁሉ ያስታጥቃችሁ።​—⁠ዕብ. 13:​20, 21

ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት መናገር ያስደስተው ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚያሳየው ከማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ይበልጥ ስለ አምላክ መንግሥት ብዙ ጊዜ ተናግሯል፤ አገልግሎቱን ሲያከናውን ስለዚህ መንግሥት ከ100 ጊዜ በላይ ጠቅሷል። በእርግጥም ለመንግሥቱ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል። (ማቴ. 12:​34) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ለሚሆኑ ከ500 የሚበልጡ ደቀ መዛሙርት ታይቶ ነበር። (1 ቆሮ. 15:⁠6) የመንግሥቱን መልእክት “ከሁሉም ብሔራት” ለተውጣጡ ሰዎች እንዲያደርሱ ያዘዛቸው በዚያ ወቅት ሳይሆን አይቀርም፤ በወቅቱ ይህን ሥራ ማከናወን ተፈታታኝ ነበር! ኢየሱስ ይህ ታላቅ ሥራ “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ” እንደሚከናወን የተነበየ ሲሆን ይህም እየተፈጸመ ነው። አንተም ይህ ተልእኮና ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ የበኩልህን አስተዋጽኦ እያደረግክ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 28:​19, 20) አምላካችንም ይህን ተልእኮ ለመወጣት በሚረዳን “መልካም ነገር ሁሉ” አስታጥቆናል። w15 11/15 5:1-3

እሁድ፣ ሚያዝያ 30

ይህ ለዘላለም ስሜ ነው።​—⁠ዘፀ. 3:​15

በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎችን (ለምሳሌ የሙት ባሕር ጥቅልሎችን) የሚያጠኑ ምሁራን፣ ቴትራግራማተን በእነዚህ ጽሑፎች ላይ በብዛት የሚገኝ መሆኑ አስገርሟቸዋል። መለኮታዊው ስም፣ በእነዚያ ጥንታዊ የዕብራይስጥ ቅጂዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ከሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. እስከ አንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ በተገለበጡ አንዳንድ የግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት ቅጂዎች ላይም ይገኛል። የአምላክ የግል ስም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መግባት እንዳለበት ግልጽ ማስረጃ ቢኖርም በርካታ ተርጓሚዎች ቅዱስ የሆነውን መለኮታዊ ስም ከትርጉም ሥራዎቻቸው ውስጥ ሙሉ በሙሉ አውጥተውታል። በ1952 ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርዥን የተባለው ትርጉም ወጣ። ይህ ትርጉም በ1901 ከወጣው አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን ላይ ተሻሽሎ የተዘጋጀ ሲሆን የአሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን አዘጋጆች የተከተሉትን ፖሊሲ በመሻር የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አውጥቶታል። ለምን? መቅድሙ እንዲህ ይላል፦ ‘አንድና ብቸኛ የሆነውን አምላክ በተጸውኦ ስም መጥራት ለዓለም አቀፉ የክርስትና እምነት ፈጽሞ ተገቢ አይደለም።’ ከዚያ በኋላ በእንግሊዝኛም ሆነ በሌሎች ቋንቋዎች የተዘጋጁ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን አካሄድ ተከትለዋል። w15 12/15 2:3-5

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ