የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es17 ገጽ 47-57
  • ግንቦት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ግንቦት
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2017
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሰኞ፣ ግንቦት 1
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 2
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 3
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 4
  • ዓርብ፣ ግንቦት 5
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 6
  • እሁድ፣ ግንቦት 7
  • ሰኞ፣ ግንቦት 8
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 9
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 10
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 11
  • ዓርብ፣ ግንቦት 12
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 13
  • እሁድ፣ ግንቦት 14
  • ሰኞ፣ ግንቦት 15
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 16
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 17
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 18
  • ዓርብ፣ ግንቦት 19
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 20
  • እሁድ፣ ግንቦት 21
  • ሰኞ፣ ግንቦት 22
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 23
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 24
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 25
  • ዓርብ፣ ግንቦት 26
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 27
  • እሁድ፣ ግንቦት 28
  • ሰኞ፣ ግንቦት 29
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 30
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2017
es17 ገጽ 47-57

ግንቦት

ሰኞ፣ ግንቦት 1

ከአፉ በሚወጡት የሚማርኩ ቃላት [ተደነቁ]።​—⁠ሉቃስ 4:​22

ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በመከተል ንግግራችን ደግነት፣ አክብሮትና ለሌሎች ስሜት አሳቢነት የሚንጸባረቅበት እንዲሆን ማድረግ እንችላለን። ኢየሱስ ሕዝቡ እሱን ለማዳመጥ ሲሉ ያደረጉትን ጥረት ሲመለከት በጣም ስላዘነላቸው ‘ብዙ ነገር አስተምሯቸዋል።’ (ማር. 6:​34) ኢየሱስ ሌሎች ቢሰድቡትም እንኳ ኃይለ ቃል አልተናገረም። (1 ጴጥ. 2:​23) በጣም የምንቀርበውን ሰው በለሰለሰ አንደበትና ዘዴኛነት በተሞላበት መንገድ ማነጋገር ሊከብደን ይችላል። እንዲያውም የፈለግነውን የመናገር ነፃነት እንዳለን ይሰማን ይሆናል። ለምሳሌ ከቤተሰባችን አባል ወይም በጉባኤ ውስጥ ከምንቀርበው ጓደኛችን ጋር ስናወራ እንዲህ እናደርግ ይሆናል። ይሁንና ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ስለሚቀርባቸው እነሱን በኃይለ ቃል ለመናገር ነፃነት እንዳለው ተሰምቶት ነበር? በፍጹም! የቅርብ ተከታዮቹ ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲከራከሩ ኢየሱስ አንድን ትንሽ ልጅ እንደ ምሳሌ በመጠቀም ደግነት በተሞላበት መንገድ እርማት ሰጥቷቸዋል። (ማር. 9:​33-37) ሽማግሌዎች “በገርነት መንፈስ” ምክር በመስጠት የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ይችላሉ።​—⁠ገላ. 6:1፤ w15 12/15 3:15, 16

ማክሰኞ፣ ግንቦት 2

እርስ በርሳችሁ እንደ ወንድማማች መዋደዳችሁን ቀጥሉ።​—⁠ዕብ. 13:1

እርስ በርሳችን እንደ ወንድማማች መዋደዳችንን መቀጠል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ዋነኛው ምክንያት፣ ይሖዋ አንዳችን ለሌላው የወንድማማች ፍቅር እንድናሳይ የሚጠብቅብን መሆኑ ነው። ወንድሞቻችንን ሳንወድ አምላክን እንወደዋለን ማለት የማይመስል ነገር ነው። (1 ዮሐ. 4:7, 20, 21) በተጨማሪም አንዳችን የሌላው ድጋፍ ያስፈልገናል። በተለይ በአስቸጋሪ ጊዜያት ወንድሞቻችን ይበልጥ ያስፈልጉናል። ጳውሎስ ደብዳቤውን ከጻፈላቸው ዕብራውያን ክርስቲያኖች አንዳንዶቹ ብዙም ሳይቆይ ቤት ንብረታቸውን ጥለው መሸሽ እንደሚኖርባቸው ያውቃል። ይህ ወቅት ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን ኢየሱስ ተናግሯል። (ማር. 13:​14-18፤ ሉቃስ 21:​21-23) በመሆኑም እነዚያ ክርስቲያኖች፣ አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ማጠናከር ይኖርባቸዋል። (ሮም 12:⁠9) እስከ ዛሬ ሆኖ የማያውቀው ታላቅ መከራ የጥፋት ነፋሳት በቅርቡ ይለቀቃሉ። (ማር. 13:​19፤ ራእይ 7:1-3) አዘውትረን መሰብሰባችን ብቻውን በቂ አይደለም። ጳውሎስ እነዚህን አጋጣሚዎች “ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች” እርስ በርስ ለመነቃቃት እንዲጠቀሙባቸው ዕብራውያን ክርስቲያኖችን አሳስቧቸዋል።​—⁠ዕብ. 10:​24, 25፤ w16.01 1:6-8

ረቡዕ፣ ግንቦት 3

ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።​—⁠ሥራ 2:4

ጊዜው በ33 ዓ.ም. የዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ነው። በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ ደርብ ላይ ባለ አንድ ክፍል ውስጥ መቶ ሃያ የሚያህሉ ክርስቲያኖች አንድ ላይ ሆነው “ተግተው ይጸልዩ ነበር።” (ሥራ 1:​13-15) አሁን በእነዚህ ክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸመው ነገር ነቢዩ ኢዩኤል የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል። (ኢዩ. 2:​28-32፤ ሥራ 2:​16-21) ደርብ ላይ በተሰበሰቡት ክርስቲያኖች ላይ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወረደ። (ሥራ 1:⁠8) እነሱም ትንቢት መናገር ይኸውም ስላዩአቸውና ስለሰሟቸው ድንቅ ነገሮች መመሥከር ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ በርካታ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ሐዋርያው ጴጥሮስ በዚያ የተፈጸመው ነገር ምን ትርጉም እንዳለው ለተሰበሰቡት ሰዎች አብራራላቸው። አክሎም አድማጮቹን እንዲህ አላቸው፦ “ንስሐ ግቡ፤ እያንዳንዳችሁም ለኃጢአታችሁ ይቅርታ እንድታገኙ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ነፃ ስጦታ ትቀበላላችሁ።” በዚያ ቀን በአጠቃላይ 3,000 የሚያህሉ ሰዎች የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለው ተጠመቁ፤ እንዲሁም በትንቢት በተነገረው መሠረት መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።​—⁠ሥራ 2:​37, 38, 41፤ w16.01 3:1-3

ሐሙስ፣ ግንቦት 4

የማይገባው ሆኖ ሳለ ከቂጣው የሚበላ ወይም ከጌታ ጽዋ የሚጠጣ ከጌታ አካልና ደም ጋር በተያያዘ ተጠያቂ ይሆናል።​—⁠1 ቆሮ. 11:​27

እዚህ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ሊያጎላው የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው? አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን ከይሖዋ ጋር ያለውን ጥሩ ግንኙነት ጠብቆ ካልተመላለሰ ከቂጣው የሚበላውና ከጽዋው የሚጠጣው ሳይገባው ይሆናል። (ዕብ. 6:4-6፤ 10:​26-29) እንዲህ ያለው ማስጠንቀቂያ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሽልማታቸውን ገና እንዳላገኙ እንዲያስታውሱ ያደርጋል። “አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የሚሰጠውን የሰማያዊውን ሕይወት ሽልማት” ያገኙ ዘንድ ግባቸው ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረጋቸውን መቀጠል አለባቸው። (ፊልጵ. 3:​13-16) ጳውሎስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች “ከተጠራችሁበት ጥሪ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ” በማለት በመንፈስ መሪነት ጽፎላቸዋል። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? ጳውሎስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል፦ “በፍጹም ትሕትናና ገርነት፣ በትዕግሥት እንዲሁም እርስ በርሳችሁ በፍቅር በመቻቻል ኑሩ፤ አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት አድርጉ።” (ኤፌ. 4:1-3) የይሖዋ መንፈስ ኩራትን ሳይሆን ትሕትናን ማዳበርን ያበረታታል።​—⁠ቆላ. 3:​12፤ w16.01 4:5, 6

ዓርብ፣ ግንቦት 5

አምላክ አብርሃምን ፈተነው።​—⁠ዘፍ. 22:1

አንድ አረጋዊ ሰው እያዘገመ ተራራ ሲወጣ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። በሕይወቱ ውስጥ ካደረጋቸው ጉዞዎች ሁሉ ይህ ከባዱ ሳይሆን አይቀርም። ጉዞውን ከባድ ያደረገበት የዕድሜው መግፋት አይደለም። አብርሃም 125 ዓመት ገደማ ቢሆነውም ጉልበቱ አሁንም ጠንካራ ነው። አብሮት የሚጓዘው ወጣት 25 ዓመት ገደማ ይሆነዋል። ይህ ወጣት፣ የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ ሲሆን የማገዶ እንጨት ተሸክሟል። አብርሃም ደግሞ ቢላ እንዲሁም እሳት ለማቀጣጠል የሚያስፈልገውን ነገር ይዟል። አብርሃም የገዛ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ይሖዋ ጠይቆት ነበር! (ዘፍ. 22:1-8) አብርሃም በሕይወቱ ካጋጠሙት ሁሉ ከባድ የሆነ የእምነት ፈተና ተደቅኖበታል። አብርሃም አምላክን የታዘዘው በጭፍን አይደለም። ከዚህ ይልቅ የታዘዘው ነገሮችን በእምነት ዓይን ስለተመለከተ ነው። አብርሃም የእምነት ዓይን ስለነበረው በሰማይ ያለው አባቱ ይሖዋ፣ ታማኝ አገልጋዮቹ ዘላቂ ጉዳት የሚያመጣባቸውን ነገር እንዲፈጽሙ እንደማይጠይቃቸው መመልከት ችሏል። ይሖዋን ከታዘዘ፣ አምላኩ እሱንም ሆነ የሚወደውን ልጁን እንደሚባርካቸው ያውቅ ነበር። ይሁንና ለእምነቱ መሠረት የሆነው ምን ነበር? እውቀትና ተሞክሮ ነው። w16.02 1:3, 4

ቅዳሜ፣ ግንቦት 6

እነሆ፣ እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ! እንደ ቃልህ ይሁንልኝ።​—⁠ሉቃስ 1:​38

ማርያም የአምላክን አንድያ ልጅ እንደምትፀንስ፣ እንደምትወልድና እንደምታሳድግ ተነገራት! ማርያም ባገኘችው አስደናቂ መብት ላይ ትኩረት ስናደርግ፣ ሊያስጨንቋት የሚችሉት ነገሮች ወደ አእምሯችን አይመጡ ይሆናል። የአምላክ መልአክ የሆነው ገብርኤል በተአምራዊ ሁኔታ ይኸውም ከወንድ ጋር ግንኙነት ሳትፈጽም እንደምትፀንስ ነገራት። ገብርኤል፣ ማርያም እንዴት እንዳረገዘች ለቤተሰቧ አባላት ወይም ለጎረቤቶቿ እንደሚያስረዳቸው አልነገራትም። ታዲያ ስለ እሷ ምን ያስቡ ይሆን? ማርያም እጮኛዋ ዮሴፍ ምን ሊሰማው እንደሚችል አሳስቧት መሆን አለበት። እርጉዝ ብትሆንም ለእሱ ያላትን ታማኝነት እንዳላጓደለች ልታሳምነው የምትችለው እንዴት ነው? ከሁሉ በላይ ደግሞ የልዑሉን አምላክ አንድያ ልጅ ተንከባክቦ ማሳደግና ማሠልጠን እንዴት ያለ ከባድ ኃላፊነት ነው! ማርያም፣ ገብርኤል ባናገራት ወቅት አሳስበዋት ሊሆኑ የሚችሉትን ነገሮች ሁሉ ማወቅ አንችልም። ሆኖም ማርያም በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሰፈረውን መልስ እንደሰጠች እናውቃለን።​—⁠ሉቃስ 1:​26-37፤ w16.02 2:13, 14

እሁድ፣ ግንቦት 7

አርካዊው ኩሲ ልብሱን ቀዶና በራሱ ላይ አቧራ ነስንሶ እሱን ለማግኘት በዚያ ይጠባበቅ ነበር።​—⁠2 ሳሙ. 15:​32

ኩሲ የተባለ ሰው ለአምላክ ታማኝ ለመሆን ድፍረት ማሳየት አስፈልጎታል። ኩሲ፣ የንጉሥ ዳዊት ታማኝ ወዳጅ ነበር። ሆኖም የዳዊት ልጅ አቢሴሎም የብዙዎችን ልብ በማሸፈት ኢየሩሳሌምን ለመያዝና ዙፋን ላይ ለመውጣት በሞከረበት ወቅት የኩሲ ታማኝነት ተፈተነ። (2 ሳሙ. 15:​13፤ 16:​15) ዳዊት ከተማዋን ለቆ ሸሸ፤ ታዲያ ኩሲ ምን ያደርግ ይሆን? ታማኝነቱን በማላላት ከአቢሴሎም ጎን ይቆም ይሆን? ወይስ ሕይወቱን ለማትረፍ እየሸሸ ያለውን በዕድሜ የገፋውን ንጉሥ ይከተላል? ኩሲ፣ አምላክ ለሾመው ንጉሥ ታማኝ ለመሆን ስለቆረጠ ዳዊትን ለማግኘት ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጣ። (2 ሳሙ. 15:​30) ዳዊት፣ ኩሲ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለስና የአቢሴሎም ወዳጅ በመምሰል የአኪጦፌልን ምክር እንዲያከሽፍለት ጠየቀው። ኩሲ፣ ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ ዳዊት የጠየቀውን በመፈጸም ለይሖዋ ታማኝ መሆኑን አሳይቷል። ልክ ዳዊት እንደጸለየው፣ ደፋር የሆነው ኩሲ የሰጠው ምክር የአኪጦፌል ምክር ከንቱ እንዲሆን አድርጓል።​—⁠2 ሳሙ. 15:​31፤ 17:​14፤ w16.02 4:15, 16

ሰኞ፣ ግንቦት 8

የአምላክህን የይሖዋን ቃል ከሰማህ እነዚህ ሁሉ በረከቶች ይወርዱልሃል፤ተከታትለውም ይደርሱብሃል።​—⁠ዘዳ. 28:2

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለእስራኤል ብሔር የተሰጠው ሕግ በውስጡ ካካተታቸው መመሪያዎች ጥቅም ማግኘት እንችላለን። እንዴት? ከሕጉ በስተ ጀርባ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ቆም ብለን በመመርመር ነው። በእነዚህ ሕጎች ሥር ባንሆንም እንኳ አብዛኞቹ ከዕለት ተዕለት ሕይወታችንና ለቅዱሱ አምላካችን ለይሖዋ ከምናቀርበው አምልኮ ጋር በተያያዘ አስተማማኝ መመሪያ ይሰጡናል። አምላክ እነዚህ ሕጎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲጻፉ ያደረገው ትምህርት እንድንቀስምባቸውና ከክርስቲያኖች የሚጠበቀውን የላቀ የሥነ ምግባር ደረጃ መገንዘብ እንድንችል ነው። ኢየሱስ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “‘አታመንዝር’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።” በመሆኑም ምንዝር ከመፈጸም መራቅ ብቻ ሳይሆን የፆታ ብልግና የመፈጸም ምኞትንም ማስወገድ ይኖርብናል።​—⁠ማቴ. 5:​27, 28፤ w16.03 4:6, 8

ማክሰኞ፣ ግንቦት 9

በእኛ ላይ ፈራጅ የሚሆን ንጉሥ ሹምልን።​—⁠1 ሳሙ. 8:5

ሳሙኤል የሕዝቡን ጥያቄ ለመፈጸም አመንትቶ ስለነበር ይሖዋ ሕዝቡን እንዲሰማ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ ነግሮታል። (1 ሳሙ. 8:7, 9, 22) ያም ቢሆን ሳሙኤል እሱን በሚተካው ሰው ላይ ጥላቻ ወይም ቅሬታ እንዲያድርበት አልፈቀደም። ይሖዋ ሳኦልን እንዲቀባ ሲነግረው ታዟል፤ ይህን ያደረገው ግዴታ ስለሆነበት ሳይሆን በፍቅር ተነሳስቶና ደስ እያለው ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችም ለሚያሠለጥኗቸው ወንድሞች ልክ እንደ ሳሙኤል ጥሩ መንፈስ ማሳየት አለባቸው። (1 ጴጥ. 5:⁠2) እንዲህ ያሉ ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ያሏቸውን አንዳንድ መብቶች ተማሪዎቹ ሊወስዱባቸው እንደሚችሉ በመፍራት እነሱን ከማሠልጠን ወደኋላ አይሉም። ደጎችና ሌሎችን በደስታ የሚረዱ አስተማሪዎች፣ ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ ተማሪዎችን የሚመለከቷቸው እንደ ተቀናቃኝ ሳይሆን ‘ከእነሱ ጋር አብረው እንደሚሠሩና’ ለጉባኤው ውድ ስጦታ እንደሆኑ አድርገው ነው። (2 ቆሮ. 1:​24፤ ዕብ. 13:​16) ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት ሌሎችን የሚያሠለጥኑ እንዲህ ያሉ አስተማሪዎች፣ ተማሪዎቹ ችሎታቸውን ተጠቅመው ጉባኤውን ሲያገለግሉ ማየታቸው ልዩ የእርካታ ስሜት እንደሚፈጥርላቸው ግልጽ ነው!​—⁠ሥራ 20:​35፤ w15 4/15 1:16, 17

ረቡዕ፣ ግንቦት 10

በተገቢው መጠን እገሥጽሃለሁ።​—⁠ኤር. 30:​11

ንጉሥ አዛርያስ “በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር” አድርጓል። ያም ሆኖ “ይሖዋ ንጉሡን ቀሰፈው፤ እስከ ዕለተ ሞቱም ድረስ የሥጋ ደዌ በሽተኛ ሆኖ ኖረ።” (2 ነገ. 15:1-5) ይሖዋ እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? ይህ ዘገባ ምንም ፍንጭ አይሰጠንም። ታዲያ ይህ ሊረብሸን ይገባል? አሊያም ይሖዋ፣ አዛርያስን የቀጣው ያለ ምንም ምክንያት እንደሆነ ማሰብ ይኖርብናል? ይሖዋ ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ በደንብ የምናውቅ ከሆነ እንዲህ አይሰማንም። ንጉሥ አዛርያስ፣ ንጉሥ ዖዝያ ተብሎም ተጠርቷል። (2 ነገ. 15:7, 32) በ2 ዜና መዋዕል 26:3-5, 16-21 ላይ የሚገኘው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ዘገባ እንደሚገልጸው ዖዝያ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ለተወሰነ ጊዜ አድርጓል፤ ከጊዜ በኋላ ግን “ለጥፋት እስኪዳረግ ድረስ ልቡ ታበየ።” ከቦታው በማለፍ በትዕቢት ተነሳስቶ የክህነት አገልግሎት ለማከናወን ሞከረ። ሰማንያ አንድ ካህናት ዖዝያን ፊት ለፊት በመጋፈጥ እርማት ሰጡት። ታዲያ ዖዝያ ምን ምላሽ ሰጠ? በወቅቱ ያደረገው ነገር ምን ያህል እንደታበየ የሚያሳይ ነው። ዘገባው እንደሚገልጸው ዖዝያ በካህናቱ ላይ “እጅግ ተቆጣ።” በእርግጥም ይሖዋ፣ በሥጋ ደዌ በሽታ የቀሰፈው መሆኑ ምንም አያስገርምም! w15 4/15 3:8, 9

ሐሙስ፣ ግንቦት 11

ታላቁ ዘንዶ ይኸውም መላውን ዓለም እያሳሳተ ያለው ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የጥንቱ እባብ ወደ ታች ተወረወረ።​—⁠ራእይ 12:9

በዕለቱ ጥቅስ ላይ ሰይጣን፣ ዲያብሎስ ተብሎም ተጠርቷል፤ ይህም “ስም አጥፊ” ማለት ነው። ይህ መጠሪያ ሰይጣን፣ ይሖዋን ውሸታም ብሎ በመጥራት ስሙን እንዳጎደፈ ያስታውሰናል። “የጥንቱ እባብ” የሚለው አገላለጽ ሰይጣን፣ ኤደን ውስጥ በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን ያታለለበትን አሳዛኝ ቀን እንድናስብ ያደርገናል። “ታላቁ ዘንዶ” የሚለው አገላለጽ ደግሞ አስፈሪ የሆነን አውሬ በአእምሯችን እንድንስል የሚያደርግ ሲሆን ይህም ሰይጣን በጭካኔ ተነሳስቶ የይሖዋን ዓላማ ለማደናቀፍና ሕዝቦቹን ለማጥፋት የሚያደርገውን ጥረት በሚገባ የሚገልጽ ነው። በግልጽ ለማየት እንደምንችለው ንጹሕ አቋማችንን እንድናጎድፍ ለማድረግ ከተነሱ ጠላቶች ሁሉ ቀንደኛው ሰይጣን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ፤ ንቁ ሆናችሁ ኑሩ! ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል” ብሎ የሚመክረን መሆኑ የተገባ ነው። (1 ጴጥ. 5:⁠8) አንድ የአምላክ አገልጋይ ከባድ ኃጢአት ሲፈጽም ሰይጣን በደስታ እንደሚፈነጥዝ ጥርጥር የለውም። እንዲያውም እነዚህን ድሎች ይሖዋን ለመንቀፍ ሳይጠቀምባቸው አይቀርም።​—⁠ምሳሌ 27:​11፤ w15 5/15 1:3, 4, 10

ዓርብ፣ ግንቦት 12

የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነው።​—⁠1 ጢሞ. 6:​10

ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ውብ መኖሪያ ማዘጋጀቱ ተመችቶን እንድንኖር እንደሚፈልግ በግልጽ ያሳያል። (ዘፍ. 2:⁠9) ይሁንና ሰይጣን “ሀብት [ባለው] የማታለል ኃይል” ተጠቅሞ ተገቢ ያልሆነ ፍላጎት እንዲያድርብን ሊያደርግ ይችላል። (ማቴ. 13:​22) ብዙዎች ገንዘብ ደስታ እንደሚያስገኝላቸው ወይም ለስኬት ቁልፉ ቁሳዊ ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። እንዲህ ብሎ ማሰብ በሰይጣን መታለል ነው፤ እንዲሁም ከምንም በላይ ትልቅ ቦታ የምንሰጠውን ነገር ይኸውም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና እንድናጣ ሊያደርገን ይችላል። ኢየሱስ ተከታዮቹን “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም” በማለት አስጠንቅቋቸዋል። (ማቴ. 6:​24) ለሀብት ብቻ ባሪያ ከሆንን ይሖዋን ማገልገላችንን አቁመናል ማለት ነው፤ ሰይጣን የሚፈልገው ደግሞ ይህንኑ ነው! ገንዘብም ሆነ ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችሉ ነገሮች ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ችላ እንድንል እንዲያደርጉን ፈጽሞ አንፍቀድ። ሰይጣንን ተዋግተን ማሸነፍ እንድንችል ለቁሳዊ ነገሮች ምንጊዜም ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል።​—⁠1 ጢሞ. 6:6-10፤ w15 5/15 2:12

ቅዳሜ፣ ግንቦት 13

አንድ የአካል ክፍል ቢሠቃይ ሌሎቹ የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረውት ይሠቃያሉ።​—⁠1 ቆሮ. 12:​26

የሌሎችን ሥቃይ መረዳት ቀላል የማይሆንበት ጊዜ አለ። ብዙ ሰዎች እኛ ጨርሶ አጋጥሞን የማያውቅ ችግር ይደርስባቸዋል። አንዳንዶች በደረሰባቸው ጉዳት፣ በሕመም ወይም በዕድሜ መግፋት የተነሳ አካላዊ ሥቃይ አለባቸው። ሌሎች ደግሞ ከስሜት ጋር የተያያዙ ፈተናዎች አሉባቸው፤ ከእነዚህም መካከል በመንፈስ ጭንቀት፣ ከመጠን ባለፈ የፍርሃት ስሜት ወይም የደረሰባቸው ጥቃት ባስከተለባቸው ጠባሳ የሚሠቃዩ ሰዎች ይገኙበታል። አንዳንዶች የሚኖሩት በሃይማኖት በተከፋፈለ ወይም በነጠላ ወላጅ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ ይሆናል። ሁሉም ሰው ችግር ያጋጥመዋል፤ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ሌሎች ያሉባቸው ችግሮች እኛ ከሚገጥሙን የተለዩ ይሆናሉ። በዚህ ጊዜ የአምላክን ፍቅር ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው? የሌላውን ሰው ስሜት ቢያንስ በተወሰነ መጠን መረዳት እስክንችል ድረስ ግለሰቡን በጥሞና በማዳመጥ ነው። ይህን ማድረጋችን ግለሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ከግምት አስገብተን እርምጃ በመውሰድ ይሖዋን በፍቅሩ ለመምሰል ያነሳሳናል። እያንዳንዱ ግለሰብ የሚያስፈልገው ነገር የተለያየ ቢሆንም መንፈሳዊ ማበረታቻ ልንሰጠው እንዲሁም በሌሎች መንገዶች የሚያስፈልገውን ነገር ልናደርግለት እንችል ይሆናል።​—⁠ሮም 12:​15፤ 1 ጴጥ. 3:8፤ w15 5/15 4:6, 7

እሁድ፣ ግንቦት 14

[ክርስቶስ] የአምላክ ኃይል . . . ነው።​—⁠1 ቆሮ. 1:​24

ክርስቶስ ኃይል ያገኘው ከይሖዋ ነው፤ በመሆኑም ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የተፈጥሮ ኃይሎችን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር እንደሚችል እርግጠኞች ለመሆን የሚያበቃ ምክንያት አለን። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎች እንመልከት። ከጥፋት ውኃ በፊት ይሖዋ “ከሰባት ቀን በኋላ በምድር ላይ 40 ቀንና 40 ሌሊት ዝናብ አዘንባለሁ” ብሎ ነበር። (ዘፍ. 7:⁠4) በተመሳሳይም ዘፀአት 14:​21 “ይሖዋም ሌሊቱን ሙሉ ኃይለኛ የምሥራቅ ነፋስ በማምጣት ባሕሩ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደረገ” ይላል። በዮናስ 1:4 ላይ ደግሞ “ይሖዋ በባሕሩ ላይ ኃይለኛ ነፋስ አመጣ፤ ከባድ ማዕበል ስለተነሳ መርከቧ ልትሰበር ተቃረበች” የሚል ሐሳብ እናገኛለን። ይሖዋ የተፈጥሮ ኃይሎችን እንደሚቆጣጠር ማወቁ የሚያጽናና ነው። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የፕላኔታችን የወደፊት ዕጣ አስጊ አይደለም። “የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር” ስለሚሆን በተፈጥሮ ኃይሎች ምክንያት የሚሞቱ ወይም የአካል ጉዳተኛ የሚሆኑ ሰዎች እንደማይኖሩ ማወቁ እንዴት ያስደስታል! (ራእይ 21:3, 4) በሺው ዓመት ግዛት ወቅት አምላክ በክርስቶስ በኩል ኃይሉን በመጠቀም የተፈጥሮ ኃይሎችን እንደሚቆጣጠር መተማመን እንችላለን። w15 6/15 1:15, 16

ሰኞ፣ ግንቦት 15

ከእሷ [ሥነ ምግባር ከጎደላት ሴት] ራቅ፤ ወደ ቤቷም ደጃፍ አትቅረብ።​—⁠ምሳሌ 5:8

እንዲህ ያለውን ምክር ችላ ማለት የሚያስከትለው አደጋ በምሳሌ ምዕራፍ 7 ላይ ተገልጿል፤ ምዕራፉ ሥነ ምግባር የጎደላት ሴት በምትኖርበት አካባቢ በእግሩ መንሸራሸር ስለጀመረ አንድ ወጣት ይናገራል። እነዚህ ሰዎች የፆታ ብልግና ፈጸሙ። ወጣቱ ይህች ሴት ወዳለችበት ባይቀርብ ምንኛ የተሻለ ይሆን ነበር! (ምሳሌ 7:6-27) እኛም አንዳንድ ጊዜ ማመዛዘን እንደጎደለን የሚያሳይ ነገር እንፈጽም ምናልባትም መጥፎ ምኞቶች እንዲቀሰቀሱብን በሚያደርግ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንገባ ይሆን? ለምሳሌ ሌሊት ላይ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ በፕሮግራሞቻቸው ላይ ከሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ እምብዛም ቁጥጥር አያደርጉ ይሆናል። እንግዲያው ምን እየተላለፈ እንዳለ ለማየት ብለን ብቻ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን የምንቀያይር ከሆነ አደጋ ውስጥ ልንገባ እንችላለን። በሌላ በኩል ደግሞ ኢንተርኔት ላይ የሚያጋጥሙንን ሊንኮች ወዴት እንደሚመሩን ሳናውቅ የመክፈት ልማድ ይኖረን ይሆናል፤ አሊያም የፖርኖግራፊ ማስታወቂያዎች ወይም ሌላ ዓይነት ከፆታ ብልግና ጋር የተያያዙ ግብዣዎች የሚመጡባቸው ድረ ገጾችን ወይም ቻት ሩሞችን አዘውትረን እንጠቀም ይሆናል። ታዲያ እንዲህ ባሉት ሁኔታዎች ውስጥ መጥፎ ምኞቶችን የሚቀሰቅሱ ወይም ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ የምናደርገውን ትግል የሚያዳክሙ ፈተናዎች ሊያጋጥሙን አይችሉም? w15 6/15 3:8, 9

ማክሰኞ፣ ግንቦት 16

በደላችንን ይቅር በለን።​—⁠ማቴ. 6:​12

ኢየሱስ የተጠቀመበት “በደላችን” ወይም “ኃጢአታችን” የሚለው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “ዕዳችን” ማለት ነው፤ ኢየሱስ “ዕዳ” የሚለውን ቃል የተጠቀመው ለምንድን ነው? (ማቴ. 6:​12፤ ሉቃስ 11:⁠4) ከ60 ዓመት በፊት በመጠበቂያ ግንብ ላይ የሚከተለው ግሩም ማብራሪያ ወጥቶ ነበር፦ “የአምላክን ሕግ ስንተላለፍ የምንፈጽመው ኃጢአት የእሱ ባለዕዳዎች ያደርገናል። . . . አምላክ ለሠራነው ኃጢአት ሕይወታችንን ሊያስከፍለን ይችላል። . . . ሰላሙን ሊወስድብን በሌላ አባባል ከእኛ ጋር ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት ሊያቋርጥ ይችላል። . . . ታዛዥ በመሆን የምንከፍለው የፍቅር ዕዳ አለብን፤ ኃጢአት በፈጸምን ቁጥር ደግሞ ለእሱ ያለብንን የፍቅር ዕዳ ሳንከፍል እንቀራለን፤ ምክንያቱም ኃጢአት መፈጸማችን ለአምላክ ያለን ፍቅር መቀነሱን ያሳያል።” (1 ዮሐ. 5:⁠3) በየዕለቱ ይቅርታ የሚያስፈልገን መሆኑ፣ አምላክ ኃጢአታችንን መሰረዝ የሚችልበት ብቸኛ ሕጋዊ መሠረት ይኸውም የኢየሱስ መሥዋዕት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያጎላል። ይህ ቤዛ የተከፈለው ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ቢሆንም ዛሬ እንደተቀበልነው ስጦታ በአድናቆት ልንመለከተው ይገባል። ለሕይወታችን የተከፈለው “የቤዛ ዋጋ እጅግ ውድ ስለሆነ” ፍጹም ያልሆነ ማንኛውም ሰው ቤዛውን ለመክፈል ምንም ማድረግ አይችልም።​—⁠መዝ. 49:7-9፤ 1 ጴጥ. 1:​18, 19፤ w15 6/15 5:9, 10

ረቡዕ፣ ግንቦት 17

እግሬ የሚያርፍበትንም ስፍራ አከብራለሁ።​—⁠ኢሳ. 60:​13

ተግባራዊ ነጥቦችን የያዙ እንዲሁም ማራኪ በሆነ መንገድ የቀረቡ ጽሑፎችን በአገልግሎት ላይ ማበርከት ምንኛ አስደሳች ነው! ከዚህም ሌላ እውነትን ለማሰራጨት jw.org እንደተባለው ድረ ገጽ ያሉትን ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ስንጠቀም ይሖዋ በየትኛውም ቦታ ያሉ ሰዎች በጣም የሚያስፈልጋቸውን ሆኖም ብዙዎቹ ያላገኙትን መመሪያ ለመስጠት ፍላጎት እንዳለው እናሳያለን። ሌላው ሳይጠቀስ የማይታለፍ ነገር ደግሞ የቤተሰብ አምልኮ ወይም የግል ጥናት ለማድረግ ሰፋ ያለ ጊዜ እንድናገኝ ሲባል የተደረገው ጥበብ የታከለበት ማስተካከያ ነው። ከትላልቅ ስብሰባዎች ጋር በተያያዘ የተደረጉትን ለውጦችም እናደንቃለን። ስብሰባዎቹ ከዓመት ወደ ዓመት እየተሻሻሉ እንደመጡ ብዙውን ጊዜ እንናገራለን። በተጨማሪም ባሉን በርካታ ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች አማካኝነት የሚሰጠው ሥልጠና መጨመሩ ያስደስተናል። በእነዚህ ማስተካከያዎች ሁሉ ላይ የይሖዋ እጅ እንዳለበት በግልጽ መመልከት ይቻላል። ይሖዋ፣ ድርጅቱም ሆነ በአሁኑ ጊዜም እንኳ ያለን መንፈሳዊ ገነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየተዋበ እንዲሄድ አድርጓል! w15 7/15 1:16, 17

ሐሙስ፣ ግንቦት 18

ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።​—⁠ሉቃስ 10:​27

አንድ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለብህ እርግጠኛ ካልሆንክ ‘ኢየሱስ ቢሆን ኖሮ ምን ያደርግ ነበር?’ ብለህ ራስህን መጠየቅህ ጠቃሚ ነው። ኢየሱስ የኖረበት አገር እንደ ይሁዳ፣ ገሊላና ሰማርያ ያሉ የተለያዩ ክልሎችን ያካተተ ነበር። በእነዚህ ክልሎች ውስጥ በሚኖሩት ሰዎች መካከል አለመግባባት እንደነበር የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በግልጽ ያሳያሉ። (ዮሐ. 4:⁠9) በተጨማሪም በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን (ሥራ 23:6-9)፣ በሕዝቡና በቀረጥ ሰብሳቢዎች (ማቴ. 9:​11) እንዲሁም በረቢዎች ትምህርት ቤት በተማሩና ባልተማሩ (ዮሐ. 7:​49) መካከል መከፋፈል ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እስራኤላውያንን የሚገዟቸው ሮማውያን ሲሆኑ ሕዝቡ የሮማውያንን አገዛዝ አምርሮ ይጠላ ነበር። ኢየሱስ ሃይማኖታዊ እውነትን ደግፎ የተናገረ ከመሆኑም ሌላ መዳን የሚጀምረው ከአይሁዳውያን መሆኑን ገልጿል፤ ያም ቢሆን ደቀ መዛሙርቱ በሕዝቡ መካከል ባለው ውዝግብ ውስጥ እንዲገቡ ፈጽሞ አላበረታታም። (ዮሐ. 4:​22) ከዚህ ይልቅ ሰዎችን ሁሉ እንደ ባልንጀራቸው አድርገው እንዲወዱ አሳስቧቸዋል። w15 7/15 3:5

ዓርብ፣ ግንቦት 19

ይሖዋ ከጎኔ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል? ይሖዋ ረዳቴ ሆኖ ከጎኔ አለ።​—⁠መዝ. 118:6, 7

ሰዎች በተፈጥሯችን የመውደድና የመወደድ ፍላጎት አለን። ይህ ፍላጎታችን ሳይሟላ ሲቀር በቀላሉ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፤ እንደማንወደድ እንዲሰማን ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል ያልጠበቅናቸው ሁኔታዎች መከሰታቸው ወይም የጠበቅነው ሳይሆን መቅረቱ፣ ጤና ማጣት፣ የኢኮኖሚ ችግር አሊያም በአገልግሎት ውጤታማ አለመሆን ይገኙበታል። ይሖዋ እንደቀድሞው እንደማይወደን ከተሰማን በእሱ ፊት ውድ እንደሆንን ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው፤ እንዲሁም “ቀኝ እጅህን ይዣለሁ” ስላለን ከጎናችን ይሆናል፤ እርዳታውም አይለየንም። እኛ ለእሱ ታማኝ እስከሆንን ድረስ ይሖዋ መቼም አይረሳንም። (ኢሳ. 41:​13፤ 49:​15) ባሏን በሞት በማጣቷ ምክንያት ሁለት ልጆቿን ብቻዋን ያሳደገች ብሪጀት የተባለች እናት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ሰይጣን በሚቆጣጠረው ሥርዓት ውስጥ ልጆችን ማሳደግ በተለይ ለነጠላ ወላጅ በጣም ከባድ ፈተና ነው። ሆኖም ይሖዋ እንደሚወደኝ እርግጠኛ ነኝ፤ ምክንያቱም ልብ የሚሰብርና የሚያስለቅስ ሁኔታ ባጋጠመኝ ጊዜ ሁሉ የሚያስፈልገኝን መመሪያ ሰጥቶኛል። እንዲሁም መሸከም ከምችለው በላይ እንድፈተን አልተወኝም።”​—⁠1 ቆሮ. 10:​13፤ w15 8/15 1:1-3

ቅዳሜ፣ ግንቦት 20

በተስፋ ጠብቀው!​—⁠ዕን. 2:3

ነቢዩ ዕንባቆም ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ ትንቢት እንዲናገር ታዝዞ ነበር። ዕንባቆም ትንቢት መናገር ሲጀምር፣ በዚህች ከተማ ላይ ስለሚደርሰው ጥፋት ለዓመታት ሲታወጅ ቆይቶ ነበር። ሁኔታዎቹ በጣም ከመክፋታቸው የተነሳ ‘ክፉው ጻድቁን ከብቦት እንዲሁም ፍትሕ ተጣምሞ’ ነበር። በመሆኑም ዕንባቆም “ይሖዋ ሆይ፣ እርዳታ ለማግኘት ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው?” ብሎ መጠየቁ የሚያስገርም አይደለም። ይሖዋ አስቀድሞ የተነገረው ጥፋት ‘እንደማይዘገይ’ ለታማኙ ነቢይ ማረጋገጫ ሰጥቶታል። (ዕን. 1:1-4) ዕንባቆም ተስፋ ቆርጦ እንደሚከተለው ብሎ ቢያስብ ኖሮስ? ‘ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ ለዓመታት ስሰማ ኖሬአለሁ። ጥፋቱ የሚመጣው ገና ወደፊት ቢሆንስ? ከተማዋ በድንገት የምትጠፋ ይመስል ትንቢት መናገሬን መቀጠል ምክንያታዊ አይደለም። ይህን ሥራ ለሌሎች ብተወውስ?’ ዕንባቆም በእንደዚህ ዓይነት ሐሳቦች ላይ ቢያውጠነጥን ኖሮ የይሖዋን ሞገስ ያጣ ነበር፤ ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን ስትጠፋ ደግሞ ሕይወቱን ሊያጣ ይችል ነበር! w15 8/15 2:12, 13

እሁድ፣ ግንቦት 21

መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል።​—⁠1 ቆሮ. 15:​33

መልካሙ አመላችን እንዳይበላሽ ከፈለግን መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች የቅርብ ጓደኞቻችን ሊሆኑ አይገባም። ይህም ሲባል መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙ የማያምኑ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ይሖዋን እናመልካለን እያሉ ሆን ብለው ሕጎቹን የሚጥሱ ሰዎችም ጓደኞቻችን መሆን የለባቸውም ማለት ነው። ክርስቲያን ነን የሚሉ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ከባድ ኃጢአት ፈጽመው ንስሐ የማይገቡ ከሆነ ከእነሱ ጋር ያለን ጓደኝነት መቋረጥ ይኖርበታል። (ሮም 16:​17, 18) የአምላክን ሕግጋት ከማይታዘዙ ሰዎች ጋር ጓደኝነት ከመሠረትን በእነሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስንል እነሱ የሚያደርጉትን ነገር ለመፈጸም ልንገፋፋ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ የፆታ ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎች የቅርብ ጓደኞቻችን ከሆኑ እኛም ብልግና ለመፈጸም ልንፈተን እንችላለን። ራሳቸውን የወሰኑ አንዳንድ ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ደርሶባቸዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ንስሐ ባለመግባታቸው ተወግደዋል። (1 ቆሮ. 5:​11-13) እነዚህ ሰዎች ንስሐ ካልገቡ ጴጥሮስ የገለጸው ዓይነት ሁኔታ ይደርስባቸዋል።​—⁠2 ጴጥ. 2:​20-22፤ w15 8/15 4:4-6

ሰኞ፣ ግንቦት 22

የማዛችሁን ነገር የምትፈጽሙ ከሆነ ወዳጆቼ ናችሁ።​—⁠ዮሐ. 15:​14

ኢየሱስ የቅርብ ወዳጆቹን በመምረጥ ረገድ ጠንቃቃ ነበር። ኢየሱስ እነዚህን ወዳጆቹን የመረጠው እሱን በታማኝነት ከተከተሉትና ይሖዋን በሙሉ ልባቸው ካገለገሉት ሰዎች መካከል ነው። አንተስ የቅርብ ጓደኞችህ እንዲሆኑ የምትመርጠው ራሳቸውን ሳይቆጥቡ ይሖዋን ከሚያገለግሉ ሰዎች መካከል ነው? እንዲህ ማድረግህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን መካከል ያለው ሞቅ ያለ መንፈስ ወደ ጉልምስና እንድታድግ ሊረዳህ ይችላል። በሕይወትህ ምን ማድረግ እንዳለብህ ለመወሰን እያሰብክ ያለህ ወጣት ልትሆን ትችላለህ። ይሖዋን በማገልገል የብዙ ዓመት ተሞክሮ ካላቸውና ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱ የእምነት ባልንጀሮችህ ጋር መቀራረብህ ምንኛ ጥበብ ነው! እነዚህ ክርስቲያኖች ባሳለፏቸው ዓመታት በሕይወታቸው ውስጥ የተለያዩ ውጣ ውረዶች አጋጥመዋቸው ወይም አምላክን ሲያገለግሉ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተጋፍጠው ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ ክርስቲያኖች ከሁሉ የተሻለውን የሕይወት ጎዳና እንድትመርጥ ሊረዱህ ይችላሉ። እንዲህ ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር ሞቅ ያለና የሚያንጽ ወዳጅነት መመሥረትህ አንተም ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች እንድታደርግ የሚረዳህ ከመሆኑም ሌላ ወደ ጉልምስና እንድታድግ ያስችልሃል።​—⁠ዕብ. 5:​14፤ w15 9/15 1:14, 15

ማክሰኞ፣ ግንቦት 23

በእምነት ጸንታችሁ በመቆም [ዲያብሎስን] ተቃወሙት።​—⁠1 ጴጥ. 5:9

ኢየሱስ በቃልም ሆነ በተግባር የደቀ መዛሙርቱን እምነት ገንብቷል። (ማር. 11:​20-24) እኛም የእሱን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል፤ ምክንያቱም ሌሎች እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ ስንረዳ የእኛም እምነት ይጠናከራል። (ምሳሌ 11:​25) በምትሰብኩበትና በምታስተምሩበት ጊዜ አምላክ መኖሩን፣ ለእኛ የሚያስብ መሆኑን እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ቃሉ መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ጎላ አድርጋችሁ ጥቀሱ። በተጨማሪም ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ እርዷቸው። የጥርጣሬ መንፈስ ቢታይባቸው፣ ምናልባትም በተሾሙ ወንድሞች ላይ ማጉረምረም ቢጀምሩ ከእነሱ ለመራቅ አትቸኩሉ። ከዚህ ይልቅ እምነታቸውን መልሰው እንዲያጠናክሩ የሚያስችሏቸውን እርምጃዎች እንዲወስዱ በዘዴ እርዷቸው። (ይሁዳ 22, 23) ተማሪ ከሆንክ ስለ ዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ትምህርት በሚሰጥበት ጊዜ ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ስለመሆኑ ያለህን እምነት በድፍረት ተናገር፤ ይህም ሌሎች ጥሩ ምላሽ እንዲሰጡ ሊያደርግ ይችላል። ይሖዋ በእምነት ጸንተን እንድንቆም ሁላችንንም ይረዳናል። (1 ጴጥ. 5:​10) እምነታችንን ለመገንባት የምናደርገው ጥረት የሚያስቆጭ አይደለም፤ ምክንያቱም እምነት የሚያስገኘው ወሮታ የሚተካከለው ነገር የለም። w15 9/15 3:20, 21

ረቡዕ፣ ግንቦት 24

ሰማያት የአምላክን ክብር ይናገራሉ፤ ጠፈርም የእጆቹን ሥራ ያውጃል።​—⁠መዝ. 19:1

በዛሬው ጊዜ ስለ ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎችና ዓላማው እየተፈጸመ ስላለበት መንገድ ሰፊ እውቀት በማግኘት ተባርከናል። ዓለም ከፍተኛ ትምህርትንና ብዙ መማርን ያበረታታል። ይሁንና የብዙዎች ተሞክሮ እንደሚያሳየው እንዲህ ዓይነቱን ግብ መከታተል አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሰው እምነቱንም ሆነ ለአምላክ ያለውን ፍቅር እንዲያጣ ያደርገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን እውቀትን እንድንወድ ብቻ ሳይሆን ጥበብና ማስተዋልም እንዲኖረን ያበረታታናል። ይህም አምላክ የሰጠንን እውቀት ተግባራዊ በማድረግ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን መጥቀም የምንችልበትን መንገድ ማስተዋል እንደሚገባን ያሳያል። (ምሳሌ 4:5-7) የአምላክ “ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።” (1 ጢሞ. 2:⁠4) ለሰዎች ሁሉ የመንግሥቱን ምሥራች ለመንገርና ሰዎች አምላክ ለሰው ዘር ያለውን ታላቅ ዓላማ እንዲያውቁ ለመርዳት ልባዊ ጥረት ስናደርግ ይሖዋን እንደምንወደው እናሳያለን።​—⁠መዝ. 66:​16, 17፤ w15 9/15 5:10, 11

ሐሙስ፣ ግንቦት 25

ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል።​—⁠ሮም 15:4

ኤልያስ በይሖዋ ላይ ያለውን ከፍተኛ እምነት የሚያሳዩትን ቀጥሎ የቀረቡ ሁኔታዎች ተመልከት። ኤልያስ፣ ይሖዋ ድርቅ ሊያመጣ እንደሆነ ለንጉሥ አክዓብ ሲያሳውቀው “ሕያው በሆነው . . . በይሖዋ እምላለሁ፣ በእኔ ትእዛዝ ካልሆነ በቀር . . . ጠል ወይም ዝናብ አይኖርም!” በማለት በእርግጠኝነት ተናግሯል። (1 ነገ. 17:⁠1) ኤልያስ በድርቁ ወቅት ይሖዋ ለእሱም ሆነ ለሌሎች የሚያስፈልጋቸውን እንደሚያቀርብላቸው እምነት ነበረው። (1 ነገ. 17:4, 5, 13, 14) ኤልያስ፣ ይሖዋ ሞቶ የነበረውን ልጅ ሊያስነሳው እንደሚችልም ጠንካራ እምነት እንዳለው አሳይቷል። (1 ነገ. 17:​21) በተጨማሪም በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ያቀረበውን መሥዋዕት ይሖዋ እሳት ልኮ እንዲበላው እንደሚያደርግ ፈጽሞ አልተጠራጠረም። (1 ነገ. 18:​24, 37) ይሖዋ የድርቁ ወቅት እንዲያበቃ የሚያደርግበት ጊዜ ሲደርስ ዝናብ እንደሚመጣ የሚያሳይ ምንም ምልክት ከመታየቱ በፊት እንኳ ኤልያስ አክዓብን “የከባድ ዝናብ ድምፅ እያጉረመረመ ስለሆነ ሂድ ብላ፤ ጠጣም” ብሎታል። (1 ነገ. 18:​41) እነዚህ ዘገባዎች እንዲህ ያለ ጠንካራ እምነት እንዳለንና እንደሌለን ራሳችንን እንድንመረምር አያደርጉንም? w15 10/15 2:4, 5

ዓርብ፣ ግንቦት 26

በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል።​—⁠1 ጢሞ. 4:​15

የሰዎች ቋንቋ የመማር ችሎታ ከአምላክ የተገኘ ተአምራዊ ስጦታ ነው። (መዝ. 139:​14፤ ራእይ 4:​11) አምላክ የሰጠን አእምሮ ከሌላም አቅጣጫ ሲታይ በጣም ጠቃሚ የሆነ ስጦታ ነው። ከእንስሳት በተለየ ሰዎች የተፈጠሩት “በአምላክ መልክ” ነው። ሰዎች ነፃ ምርጫ ስላላቸው የቋንቋ ችሎታቸውን ተጠቅመው አምላክን ማወደስ ይችላሉ። (ዘፍ. 1:​27) ቋንቋን የፈጠረው አምላክ እሱን ማክበር ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ግሩም የሆነ ስጦታ ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በከፊልም ሆነ በሙሉ ከ2,800 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረውን ሐሳብ ስታነብ የአምላክ ዓይነት አስተሳሰብ ይኖርሃል። (መዝ. 40:5፤ 92:5፤ 139:​17) በዚህ መንገድ “ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ እንድታገኝ” በሚያስችሉህ ነገሮች ላይ ማሰላሰል ትችላለህ። (2 ጢሞ. 3:​14-17) ማሰላሰል ሲባል አእምሮ በአንድ ነገር ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ይኸውም በአንድ ጉዳይ ላይ (ጥሩ ወይም መጥፎ ሊሆን ይችላል) ማውጠንጠን ወይም በተመስጦ ማሰብ ማለት ነው። (መዝ. 77:​12፤ ምሳሌ 24:1, 2) ከምንም ነገር በላይ የሚጠቅመን ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማሰላሰል ነው።​—⁠ዮሐ. 17:3፤ w15 10/15 4:2-4

ቅዳሜ፣ ግንቦት 27

አንድ ሰው የራሱን ቤተሰብ እንዴት እንደሚያስተዳድር ካላወቀ የአምላክን ጉባኤ እንዴት ሊንከባከብ ይችላል?​—⁠1 ጢሞ. 3:5

ኢየሱስ፣ ሌሎችን በትሕትና እንዲያገለግሉ በቃልም ሆነ በድርጊት ደቀ መዛሙርቱን አሠልጥኗቸዋል። (ሉቃስ 22:​27) ሐዋርያቱን፣ በይሖዋ አገልግሎትና ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ እንዲያሳዩ አስተምሯቸዋል። እናንተም በትሕትና የራሳችሁን ጥቅም መሥዋዕት የምታደርጉ ከሆነ ልጆቻችሁ እንዲሁ እንዲያደርጉ ማስተማር ትችላላችሁ። ሁለት ልጆች ያሏት ዴቢ እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ሽማግሌ እንደመሆኑ መጠን ለሌሎች ጊዜ በመስጠቱ ፈጽሞ ቀንቼ አላውቅም። ባለቤቴ፣ እኔም ሆንኩ ልጆቼ በምንፈልገው ጊዜ ሁሉ ትኩረት እንደሚሰጠን አውቃለሁ።” ባለቤቷ ፕራናስ በማከል እንዲህ ብሏል፦ “ከጊዜ በኋላ ልጆቻችን ከትላልቅ ስብሰባዎችና ከሌሎች ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በፈቃደኝነት ያከናውኑ ጀመር። ልጆቻችን ደስተኞች ናቸው፤ ጥሩ ጓደኞችም አፍርተዋል እንዲሁም ከወንድሞቻቸውና ከእህቶቻቸው ጋር መሆን ያስደስታቸዋል!” በአሁኑ ወቅት መላው ቤተሰብ፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈለ ነው። እናንተም ትሕትናንና የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስን ማሳየታችሁ ልጆቻችሁ ሌሎችን እንዴት ማገልገል እንደሚችሉ እንዲማሩ ይረዳቸዋል። w15 11/15 1:9

እሁድ፣ ግንቦት 28

የማይታዩት ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።​—⁠ሮም 1:​20

የይሖዋ ታላቅ ፍቅር በብዙ መንገዶች ታይቷል። አስደናቂ የሆነውን ጽንፈ ዓለም እንደ ምሳሌ እንመልከት። በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ከዋክብትንና ፕላኔቶችን የያዙ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ጋላክሲዎች አሉ። ፍኖተ ሐሊብ በተባለው በእኛ ጋላክሲ ውስጥ ከታቀፉት ከዋክብት መካከል ፀሐይ ትገኝበታለች፤ ፀሐይ ባትኖር ኖሮ በምድር ላይ ያሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕያዋን ፍጥረታት ሕልውና ያከትም ነበር። እነዚህ ሁሉ ፍጥረታት ይሖዋ፣ አምላክ ለመሆኑ እንዲሁም እንደ ኃይል፣ ጥበብና ፍቅር ላሉት ባሕርያቱ ማስረጃ ናቸው። ይሖዋ ምድርን ሲፈጥር በእሷ ላይ እንዲኖሩ ላሰባቸው ሕያዋን ፍጥረታት አስፈላጊ ነገሮችን በሙሉ አብሮ ፈጥሯል። ለሰው ልጆች ውብ የአትክልት ቦታ ያዘጋጀ ሲሆን ለዘላለም መኖር የሚያስችላቸው ፍጹም አእምሮና አካል ሰጥቷቸዋል። (ራእይ 4:​11) በተጨማሪም “ሕይወት ላለው ሁሉ ምግብ ይሰጣል፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና።”​—⁠መዝ. 136:​25፤ w15 11/15 3:7, 8

ሰኞ፣ ግንቦት 29

ከእናንተ ጋር ነኝ።​—⁠ማቴ. 28:​20

ንጉሣችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲቀበሉ ልባቸውን ለማዘጋጀት የሚረዱ የተለያዩ መሣሪያዎችን ባለፉት ዓመታት ሰጥቶናል። ከእነዚህ መሣሪያዎች አንዳንዶቹ ያገለገሉት ለተወሰኑ አሥርተ ዓመታት ሲሆን አንዳንዶቹ ግን አሁንም ጠቃሚ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። ይሁንና ሁሉም መሣሪያዎች ከወንጌላዊነቱ ሥራችን ጋር በተያያዘ በተለያየ መንገድ ችሎታችንን እንድናዳብር ረድተውናል። ብዙዎች አገልግሎት እንዲጀምሩ የረዳቸው አንዱ መሣሪያ የምሥክርነት መስጫ ካርድ ሲሆን የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይህን መሣሪያ መጠቀም የጀመሩት በ1933 ነው። ካርዱ አጠር ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የያዘ ነበር። የምሥክርነት መስጫ ካርድ ብዙ ጥቅሞች ነበሩት። አንዳንድ አስፋፊዎች በስብከቱ ሥራ የመካፈል ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም ዓይናፋር ነበሩ፤ ምን ብለው መናገር እንዳለባቸው አያውቁም። ሌሎች ደግሞ የሚያውቁትን ሁሉ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ለቤቱ ባለቤት መናገር ይችላሉ፤ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ዘዴኛነት ይጎድላቸው ነበር! የምሥክርነት መስጫ ካርዶች ግን በሚገባ የተመረጡ ጥቂት ቃላትን ስለሚጠቀሙ ለአስፋፊዎቹ እንደ “አንደበት ሆነውላቸዋል።” w15 11/15 5:3-6

ማክሰኞ፣ ግንቦት 30

የይሖዋን ስም ያወድሱ።​—⁠መዝ. 148:​13

የአምላክ ስምና የስሙ መቀደስ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ የሚያሳዩ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። (ዘፀ. 3:​15፤ መዝ. 83:​18፤ ኢሳ. 42:8፤ 43:​10፤ ዮሐ. 17:6, 26፤ ሥራ 15:​14) የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነው ይሖዋ አምላክ፣ ጸሐፊዎቹ ስሙን በተደጋጋሚ ጊዜያት እንዲጠቀሙበት በመንፈሱ መርቷቸዋል። (ሕዝ. 38:​23) በጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ውስጥ በሺዎች በሚቆጠሩ ጊዜያት የሚገኘውን ስም ማውጣት ለመጽሐፉ ባለቤት አክብሮት ማጣት ነው። የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የሚጠቁሙት ማስረጃዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል እንጂ አልቀነሱም። በ2013 ተሻሽሎ በወጣው የእንግሊዝኛ አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ የአምላክ ስም 7,216 ጊዜ የሚገኝ ሲሆን ይህ ቁጥር በ1984 በተዘጋጀው እትም ላይ ካለው በ6 ይበልጣል። የአምላክ ስም የገባባቸው አምስት ተጨማሪ ቦታዎች 1 ሳሙኤል 2:​25፤ 6:3፤ 10:​26፤ 23:​14, 16 ናቸው። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የአምላክ ስም ቀድሞ በነበረበት ቦታ እንዲገባ የተደረገበት ዋነኛ ምክንያት፣ ማሶሬቶች ከገለበጡት የዕብራይስጥ ቅጂ 1,000 ዓመት በፊት በተዘጋጁት የሙት ባሕር ጥቅልሎች ላይ ስሙ ስለሚገኝ ነው። ከዚህም ሌላ በጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ላይ በተደረገ ተጨማሪ ጥናት ምክንያት መሳፍንት 19:​18 ላይ የአምላክ ስም እንዲገባ ተደርጓል። w15 12/15 2:5, 6

ረቡዕ፣ ግንቦት 31

እርስ በርሳችሁ እንደ ወንድማማች መዋደዳችሁን ቀጥሉ።​—⁠ዕብ. 13:1

የወንድማማች ፍቅር ከአሁኑ ማዳበራችን አስፈላጊ ነው፤ እንዲህ ማድረጋችን ወደፊት የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተናና መከራ ለመቋቋም ያስችለናል። ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት አሁንም እንኳ ጠንካራ የወንድማማች ፍቅር ማዳበር ያስፈልገናል። በርካታ ወንድሞቻችን በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ በኃይለኛ አውሎ ነፋስ፣ በሱናሚ ወይም በሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች የተነሳ ጉዳት ደርሶባቸዋል። አንዳንድ ወንድሞች ደግሞ ተቃውሞና ስደት እያጋጠማቸው ነው። (ማቴ. 24:​6-9) ይህም እንዳይበቃ፣ ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት በዚህ ሥርዓት ውስጥ ስለምንኖር በየዕለቱ ኢኮኖሚያዊ ጫና ያታግለናል። (ራእይ 6:5, 6) እንዲህ ያሉት ችግሮች እየጨመሩ ሲሄዱ የወንድማማች ፍቅራችንን ጥልቀት ለማሳየት የሚያስችሉን አጋጣሚዎችም ይጨምራሉ። ‘የብዙዎች ፍቅር ቢቀዘቅዝም’ እኛ ግን የወንድማማች ፍቅራችን ምንጊዜም እንዲቀጥል ማድረግ አለብን።​—⁠ማቴ. 24:​12፤ w16.01 1:8, 9

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ