የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es17 ገጽ 57-67
  • ሰኔ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሰኔ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2017
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 1
  • ዓርብ፣ ሰኔ 2
  • ቅዳሜ፣ ሰኔ 3
  • እሁድ፣ ሰኔ 4
  • ሰኞ፣ ሰኔ 5
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 6
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 7
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 8
  • ዓርብ፣ ሰኔ 9
  • ቅዳሜ፣ ሰኔ 10
  • እሁድ፣ ሰኔ 11
  • ሰኞ፣ ሰኔ 12
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 13
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 14
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 15
  • ዓርብ፣ ሰኔ 16
  • ቅዳሜ፣ ሰኔ 17
  • እሁድ፣ ሰኔ 18
  • ሰኞ፣ ሰኔ 19
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 20
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 21
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 22
  • ዓርብ፣ ሰኔ 23
  • ቅዳሜ፣ ሰኔ 24
  • እሁድ፣ ሰኔ 25
  • ሰኞ፣ ሰኔ 26
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 27
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 28
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 29
  • ዓርብ፣ ሰኔ 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2017
es17 ገጽ 57-67

ሰኔ

ሐሙስ፣ ሰኔ 1

[ለስላሳ] አንደበት አጥንትን ይሰብራል።​—⁠ምሳሌ 25:​15

አንድ ሰው ቅር የሚያሰኝ ነገር በሚናገርበት ጊዜም እንኳ የለዘበ መልስ መስጠት ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። (ምሳሌ 15:⁠1) አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ የአንዲት ነጠላ እህት ልጅ ሁለት ዓይነት ሕይወት እየመራ ነበር። አንዲት ሌላ እህት ይህችን እናት “ልጅሽን በማሠልጠን ረገድ ሳይሳካልሽ መቅረቱ በጣም ያሳዝናል” አለቻት፤ ይህን ያለችው ስላዘነችላት ነው። እናትየው ቆም ብላ ካሰበች በኋላ እንዲህ በማለት መለሰችላት፦ “ነገሮች በትክክለኛው አቅጣጫ እየሄዱ እንዳልሆነ አልክድም፤ ሆኖም ልጄ ሥልጠናውን ገና አልጨረሰም። እርግጠኛ መሆን የምንችለው ከአርማጌዶን በኋላ ነው።” ይህች እናት የሰጠችው የለዘበ መልስ በሁለቱ እህቶች መካከል ያለው ሰላም እንዳይደፈርስ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ ጭውውታቸውን ይሰማ የነበረውን የእህትን ልጅ አበረታቶታል። ልጁ፣ እናቱ በእሱ ተስፋ እንዳልቆረጠች ተገነዘበ። ይህም ከመጥፎ ጓደኞች እንዲርቅ አነሳሳው። ከጊዜ በኋላ የተጠመቀ ሲሆን ውሎ አድሮም ቤቴል ገባ። ከወንድሞቻችን፣ ከቤተሰባችን አባላት ወይም ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር ስንሆን ንግግራችን ምንጊዜም “በጨው የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው” ሊሆን ይገባል።​—⁠ቆላ. 4:6፤ w15 12/15 3:15, 17

ዓርብ፣ ሰኔ 2

የእሳት ምላሶች የሚመስሉ . . . [ተከፋፍለው] በእያንዳንዳቸው ላይ አረፉ።​—⁠ሥራ 2:3

ይህ ነገር ካጋጠማቸው ደቀ መዛሙርት አንዱ ብትሆን በዚያ ዕለት የተከናወነውን ነገር መቼም አትረሳውም። በመንፈስ ቅዱስ መቀባትህን ፈጽሞ አትጠራጠርም፤ በተለይ ደግሞ በማታውቀው ቋንቋ የመናገር ተአምራዊ ስጦታም ተሰጥቶህ ከሆነ መቀባትህን እርግጠኛ ትሆናለህ። (ሥራ 2:6-12) ይሁንና በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ሁሉ፣ የተቀቡት ልክ እንደ መጀመሪያዎቹ 120 ደቀ መዛሙርት አስደናቂ በሆነ መንገድ ነው? አይደለም። በኢየሩሳሌም በዚያን ዕለት የነበሩት ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ የተቀቡት ሲጠመቁ ነው። (ሥራ 2:​38) የእሳት ምላሶች የሚመስሉ ነገሮች ጭንቅላታቸው ላይ አላረፉም። በሌላ በኩል ደግሞ በተጠመቁበት ወቅት በመንፈስ የተቀቡት ሁሉም ክርስቲያኖች አይደሉም። ሳምራውያን በመንፈስ የተቀቡት ከተጠመቁ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነው። (ሥራ 8:​14-17) ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ የተቀቡበት መንገድም ለየት ያለ ነው፤ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡት ገና ከመጠመቃቸው በፊት ነው።​—⁠ሥራ 10:​44-48፤ w16.01 3:3, 5

ቅዳሜ፣ ሰኔ 3

አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት አድርጉ።​—⁠ኤፌ. 4:3

ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ምድራዊ ተስፋ ካላቸው የበለጠ መንፈስ ቅዱስ እንዳልተቀበሉ በመገንዘብ ትሕትና ያሳያሉ። ልዩ እውቀት እንዳላቸው ወይም ራእይ እንደሚገለጥላቸው አይናገሩም፤ አሊያም በሆነ መንገድ ከሌሎች እንደሚበልጡ ለማሳየት አይሞክሩም። ከዚህም በተጨማሪ ለማንም ሰው፣ በመንፈስ እንደተቀባና ከምሳሌያዊው ቂጣና የወይን ጠጅ መውሰድ እንደሚገባው የሚገልጽ ሐሳብ ፈጽሞ አይሰነዝሩም፤ ከዚህ ይልቅ ቅቡዓንን የሚጠራው ይሖዋ እንደሆነ በትሕትና አምነው ይቀበላሉ። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሌሎች የተለየ ክብር እንዲሰጧቸው አይጠብቁም። (ኤፌ. 1:​18, 19፤ ፊልጵ. 2:2, 3) የይሖዋ መንፈስ የመሠከረላቸው በግለሰብ ደረጃ ነው። ለሌሎች ሰዎች የተነገረ ማስታወቂያ የለም። በመሆኑም አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን፣ በእርግጥ በመንፈስ ቅዱስ መቀባቱን አንዳንዶች ቢጠራጠሩ ሊገረም አይገባም። እንዲያውም ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ከአምላክ ልዩ ሹመት እንዳገኘ የሚናገርን ሰው ቶሎ ማመንን አያበረታቱም።​—⁠ራእይ 2:2፤ w16.01 4:6, 7

እሁድ፣ ሰኔ 4

የአምላክ ብልጽግና፣ ጥበብና እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው!​—⁠ሮም 11:​33

ይሖዋ በተደጋጋሚ ጊዜ ጣልቃ በመግባት ለአብርሃምና ለሣራ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ጥበቃ አድርጎላቸዋል። (ዘፍ. 12:​10-20፤ 20:2-7, 10-12, 17, 18) እነዚህ ተሞክሮዎች የአብርሃምን እምነት አጠናክረውለታል። እኛስ የይሖዋ ወዳጆች መሆን እንችላለን? እንዴታ! ይህን ለማድረግ የሚያስፈልገንን እውቀትና ተሞክሮ በቀላሉ ማግኘት እንችላለን። በአሁኑ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ማለቂያ የሌለው ጥበብ ውስጥ አብርሃም ያገኘው በጣም ጥቂቱን ብቻ ነበር። (ዳን. 12:⁠4) የአምላክ ቃል ‘ሰማይንና ምድርን ስለሠራው’ አምላክ ያለን እውቀት ጥልቀት እንዲኖረው እንዲሁም ለእሱ አክብሮትና ፍቅር እንድናዳብር በሚረዳን ውድ ሀብት የተሞላ ነው። (ዘፍ. 14:​22) እንዲህ ያለው አክብሮትና ፍቅር አምላክን እንድንታዘዝ ያነሳሳናል፤ እሱን መታዘዝ የሚያስገኘውን ውጤት ስናይ ደግሞ ተሞክሮ እናገኛለን። ይሖዋ የሚሰጠን ምክር ጥበቃ እንደሚሆንልን በሕይወታችን እንመለከታለን፤ እንዲሁም አምላክ እንደሚባርከንና እንደሚያጠነክረን እንገነዘባለን። አምላክን በሙሉ ልብ ማገልገል እርካታ፣ ሰላምና ደስታ እንደሚያስገኝ እንረዳለን። (መዝ. 34:8፤ ምሳሌ 10:​22) እውቀታችንና ተሞክሯችን በዚህ መንገድ እየጨመረ ሲሄድ በይሖዋ ላይ ያለን እምነትና ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነትም እየተጠናከረ ይሄዳል። w16.02 1:7, 8

ሰኞ፣ ሰኔ 5

እስራኤልን ረድቷል፤ ይህን ያደረገው ለአባቶቻችን በገባው ቃል መሠረት [ነው]።​—⁠ሉቃስ 1:​54, 55

እነዚህ ሐሳቦች ማርያም በመንፈስ መሪነት የተጻፉትን ቅዱሳን መጻሕፍት በሚገባ እንደምታውቅ ይጠቁማል። የማርያም ሐሳብ፣ የነቢዩ ሳሙኤል እናት የሆነችው ሐና ከተናገረችው ነገር ጋር በተወሰነ መጠን ይመሳሰላል። (1 ሳሙ. 2:1-10) ማርያም 20 ጊዜ ያህል ከቅዱሳን መጻሕፍት ጠቅሳ እንደተናገረች ይገመታል። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ስለ መንፈሳዊ ነገሮች መናገር የምትወድ ሴት ነበረች። ማርያም በልቧ ካስቀመጠችው ውድ ሀብት ይኸውም ከታላቁ ወዳጇ ከይሖዋ አምላክ በተማረቻቸው ውድ እውነቶች ከተሞላው ጎተራ እያወጣች የተናገረች ያህል ነው። እንደ ማርያም ሁሉ እኛም አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ የሚሰጠን ኃላፊነት ከባድ ሊመስለን ይችላል። ልክ እንደ እሷ፣ ይሖዋ የሚጠቅመንን ነገር እንደሚያደርግልን በመተማመን የሚሰጠንን ኃላፊነት በትሕትና እንቀበል። ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ የምንማረውን ነገር በጥሞና በማዳመጥ፣ በመንፈሳዊ እውነቶች ላይ በማሰላሰል እንዲሁም የተማርናቸውን ነገሮች ለሌሎች በደስታ በማካፈል ማርያምን በእምነቷ መምሰል እንችላለን።​—⁠መዝ. 77:​11, 12፤ ሉቃስ 8:​18፤ ሮም 10:​15፤ w16.02 2:17, 18

ማክሰኞ፣ ሰኔ 6

ከእናንተ መካከል፣ ግንብ ለመገንባት ፈልጎ ለመጨረስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዳለው ለማወቅ በመጀመሪያ ተቀምጦ ወጪውን የማያሰላ ማን ነው?​—⁠ሉቃስ 14:​28

በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ይጠመቃሉ። (መክ. 12:⁠1) ክርስቲያን ወላጆችና የጉባኤ ሽማግሌዎች እነዚህ ወጣቶች ለመጠመቅ የወሰኑት በራሳቸው ተነሳሽነት መሆኑን ብቻ ሳይሆን በሚገባ አስበውበት ጭምር መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ። አንድ ክርስቲያን ራሱን ወስኖ በሚጠመቅበት ጊዜ በሕይወቱ ውስጥ የይሖዋን በረከት እንደሚያገኝ ብቻ ሳይሆን ከሰይጣን ዲያብሎስ ተቃውሞ እንደሚደርስበትም መጠበቅ ይኖርበታል። (ምሳሌ 10:​22፤ 1 ጴጥ. 5:⁠8) በመሆኑም ክርስቲያን ወላጆች የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ጊዜ ወስደው ልጆቻቸውን ያስተምራሉ። ወላጆቻቸው የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ወጣቶችን ደግሞ የጉባኤው ሽማግሌዎች የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ምን ወጪ እንደሚያስከፍላቸው እንዲያሰሉ በፍቅር ይረዷቸዋል። (ሉቃስ 14:​27-30) አንድን ሕንፃ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ማውጣት እንደሚጠይቅ ሁሉ ይሖዋን በታማኝነት “እስከ መጨረሻው” ለማገልገልም ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል።​—⁠ማቴ. 24:​13፤ w16.03 1:1, 2

ረቡዕ፣ ሰኔ 7

አምላክ [አያዳላም] . . . ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።​—⁠ሥራ 10:​34, 35

የሙሴ ሕግ የተሰጠው ለአንድ ብሔር ይኸውም ለሥጋዊ እስራኤላውያን ነበር። በአንጻሩ ግን መንፈሳዊ እስራኤል የተለያየ ብሔርና አኗኗር ከነበራቸው ሰዎች የተውጣጣ ነው። ሥጋዊ እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር በነበሩበት ጊዜ ይጠቀሙበት የነበረው የሙሴ ሕግ የተቀረጸው በድንጋይ ላይ ነበር። በሌላ በኩል መንፈሳዊ እስራኤላውያን የሚመሩበት ‘የክርስቶስ ሕግ’ በዋነኝነት የተመሠረተው በልብ ላይ በተቀረጹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ነው። ክርስቲያኖች የሚኖሩት የትም ይሁን የት ‘በክርስቶስ ሕግ’ ሥር ናቸው፤ ከሕጉም ጥቅም አግኝተዋል። (ገላ. 6:⁠2) መንፈሳዊ እስራኤላውያን አምላክ በልጁ በኩል ከሚሰጠው አመራር በእጅጉ ይጠቀማሉ። አዲሱ ቃል ኪዳን ከመቋቋሙ በፊት ኢየሱስ ከፍተኛ ትርጉም ያላቸው ሁለት ትእዛዛት ሰጠ። አንዱ ከስብከቱ ሥራ ጋር የተያያዘ ነው። ሌላኛው ደግሞ የኢየሱስ ተከታዮች ከሚያሳዩት ምግባርና የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ከሚይዙበት መንገድ ጋር የሚያያዝ ነው። እነዚህ መመሪያዎች የተሰጡት ለሁሉም ክርስቲያኖች ስለሆነ ተስፋቸው በሰማይ መኖርም ይሁን በምድር በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮችን በሙሉ ይመለከታሉ። w16.03 4:10, 11

ሐሙስ፣ ሰኔ 8

አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።​—⁠ሮም 12:​10

አንድ ሽማግሌ ለአንድ ወንድም ሥልጠና ከመጀመሩ በፊት ዘና ያለ ሁኔታ እንዲኖርና ከእሱ ጋር ጥሩ ወዳጅነት ለመመሥረት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ሽማግሌዎች የሚወስዷቸው እርምጃዎች እንደ አካባቢው ሁኔታና ባሕል ሊለያዩ ይችላሉ። ይሁንና የምትኖረው የትም ይሁን የት እንዲሁም ምንም ያህል ሥራ የሚበዛብህ ሽማግሌ ብትሆን ከተማሪው ጋር ጊዜ ማሳለፍህ ‘በእኔ ዘንድ ትልቅ ቦታ አለህ’ የሚል መልእክት ያስተላልፋል። በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ለመማር ፈቃደኛ የሆነ ተማሪ ይህን መልእክት በሚገባ እንደሚያስተውልና በጥልቅ እንደሚነካው ጥርጥር የለውም። አንድ አስተማሪ ውጤታማ የሚባለው ሌሎችን የማሠልጠን ፍቅር ስላለው ብቻ ሳይሆን ለሚያሠለጥነው ሰው ጭምር ፍቅር ሲኖረው ነው። (ከዮሐንስ 5:​20 ጋር አወዳድር።) አንድ አስተማሪ ለተማሪው ፍቅር ካለው ተማሪው ይህን በቀላሉ ሊያስተውል ይችላል፤ እንዲሁም ለሥልጠናው ጥሩ ምላሽ እንዲሰጥ ያነሳሳዋል። በመሆኑም ውድ ሽማግሌዎች፣ ሌሎችን ስታሠለጥኑ አስተማሪ ብቻ ሳይሆን ጓደኛም ሁኗቸው።​—⁠ምሳሌ 17:​17፤ ዮሐ. 15:​15፤ w15 4/15 1:19, 20

ዓርብ፣ ሰኔ 9

ይሖዋ ንጉሡን ቀሰፈው፤ እስከ ዕለተ ሞቱም ድረስ የሥጋ ደዌ በሽተኛ ሆኖ ኖረ።​—⁠2 ነገ. 15:5

ከአንዳንድ አጫጭር የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ጋር በተያያዘ እንደሚያጋጥመን ሁሉ ስለ ንጉሥ አዛርያስ (ንጉሥ ዖዝያ) ነጥቡን ግልጽ የሚያደርግ ተጨማሪ ሐሳብ በአምላክ ቃል ውስጥ ባይካተት ኖሮ ምን ይሰማህ ነበር? (2 ነገ. 15:7, 32፤ 2 ዜና 26:3-5, 16-21) የአምላክን ጽድቅ ትጠራጠር ነበር? ወይስ ይሖዋ ምንጊዜም ትክክል የሆነውን እንደሚያደርግ እንዲያውም ትክክል ወይም ስህተት ለሆነው ነገር መመዘኛው እሱ እንደሆነ የሚያረጋግጥልን በቂ መረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሚገኝ ይሰማህ ነበር? (ዘዳ. 32:⁠4) የይሖዋን ማንነት ይበልጥ እያወቅን ስንሄድ ለእሱ ያለን ፍቅርና ነገሮችን ለሚያከናውንበት መንገድ ያለን አድናቆት ስለሚጨምር እሱ ለሚያደርገው ለእያንዳንዱ ነገር ማብራሪያ አያስፈልገንም። አምላክ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ በኩል የሚነግርህን ነገር ባጠናህና በዚያ ላይ ባሰላሰልክ መጠን አድናቆትህም የዚያኑ ያህል እንደሚጨምር እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (መዝ. 77:​12, 13) ይህ ደግሞ ይሖዋ ይበልጥ እውን እንዲሆንልህ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ወደ እሱ የበለጠ ትቀርባለህ። w15 4/15 3:8, 10

ቅዳሜ፣ ሰኔ 10

ትእዛዛቱን በማክበር ቃሉን የምትፈጽሙ፣ እናንተ ብርቱዎችና ኃያላን መላእክቱ ሁሉ፣ ይሖዋን አወድሱ።​—⁠መዝ. 103:​20

መላእክት ተብለው የሚጠሩት መንፈሳዊ ፍጥረታት “ብርቱዎችና ኃያላን” ናቸው። መላእክት ከሰው ልጆች የላቁ ፍጥረታት በመሆናቸው በማሰብ ችሎታቸውም ሆነ በጥንካሬያቸው ከእኛ ይበልጣሉ። በእርግጥ ታማኝ የሆኑ መላእክት ኃይላቸውን የሚጠቀሙበት ለበጎ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የይሖዋ መልአክ የጠላት ወታደሮች የሆኑ 185,000 አሦራውያንን በአንድ ሌሊት ገድሏል፤ ይህን ማድረግ ለአንድ ሰው ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው፤ ሙሉ ሠራዊትም ቢሆን እንዲህ ያለ ጀብዱ ማከናወን ሊከብደው ይችላል። (2 ነገ. 19:​35) በሌላ ወቅት ደግሞ አንድ የይሖዋ መልአክ ከሰው በላይ በሆነው ኃይሉና ብልሃቱ በመጠቀም የኢየሱስን ሐዋርያት ከወህኒ አስወጥቷቸዋል። ይህ መንፈሳዊ ፍጡር፣ ጠባቂዎቹን አልፎና የተቆለፉትን በሮች ከፍቶ ሐዋርያቱን ካስወጣ በኋላ በሮቹን መልሶ ቆለፈ፤ ይህን ሁሉ ሲያደርግ ጠባቂዎቹ በሩ ላይ ቆመው ነበር! (ሥራ 5:​18-23) ታማኝ የሆኑ መንፈሳዊ ፍጥረታት ኃይላቸውን የሚጠቀሙበት መልካም ነገር ለማድረግ ነው፤ በተቃራኒው ግን ዲያብሎስ ኃይሉን የሚጠቀመው ለክፋት ነው። ደግሞም ከፍተኛ ኃይል ብሎም ተጽዕኖ የማሳደር ችሎታ አለው! ቅዱሳን መጻሕፍት ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዢ” ብለው ጠርተውታል።​—⁠ዮሐ. 12:​31፤ w15 5/15 1:5, 6

እሁድ፣ ሰኔ 11

ከእናንተ መካከል አንዳችሁም ኃጢአት ባለው የማታለል ኃይል እንዳትደነድኑ።​—⁠ዕብ. 3:​13

ያገባንም እንሁን ያላገባን ከማንኛውም ዓይነት የፆታ ብልግና ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። ይሁንና ትግሉ ቀላል ነው? በፍጹም! ለምሳሌ ወጣት ከሆንክ አብረውህ የሚማሩት ልጆች ከተለያዩ ሰዎች ጋር የፆታ ግንኙነት ስለመፈጸም ወይም የብልግና መልእክቶችን በሞባይል ስልክ ስለመላላክ በኩራት ሲናገሩ ትሰማ ይሆናል፤ በአንዳንድ አገሮች እንዲህ ያሉ መልእክቶችን መላላክ ልጆች ያሉበት ፖርኖግራፊ ከማሰራጨት ተለይቶ አይታይም። መጽሐፍ ቅዱስ “ዝሙት የሚፈጽም ሁሉ . . . በራሱ አካል ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው” ይላል። (1 ቆሮ. 6:​18) የአባለዘር በሽታዎች መስፋፋት ሥቃይና ሞት እያስከተለ ነው። ከዚህም ሌላ ሳያገቡ የፆታ ግንኙነት የፈጸሙ አብዛኞቹ ወጣቶች ይህን በማድረጋቸው እንደተጸጸቱ ይገልጻሉ። የፆታ ብልግና የሚያስከትለው መዘዝ የመዝናኛው ዓለም ከሚገልጸው ነገር ፈጽሞ የተለየ ነው፤ ዓለም የአምላክን ሕግ መጣስ ምንም ጉዳት እንደሌለው ሊያሳምነን ይሞክራል። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ሰዎች “ኃጢአት ባለው የማታለል ኃይል” እንዲወድቁ ያደርጋል። w15 5/15 2:14

ሰኞ፣ ሰኔ 12

ልዑሉ አምላክ . . . ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ደግ ነው።​—⁠ሉቃስ 6:​35

ኢየሱስ አምላክን በደግነቱ መስሎታል። ይህን እንዲያደርግ የረዳው ምንድን ነው? የሚናገረውም ሆነ የሚያደርገው ነገር የሌላውን ግለሰብ ስሜት እንዴት ሊነካ እንደሚችል አስቀድሞ በማሰብ ሰዎችን በደግነት ይይዝ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በኃጢአተኝነቷ የምትታወቅን አንዲት ሴት እንዴት እንደያዛት እንመልከት፤ ሴትየዋ ወደ ኢየሱስ በመቅረብ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመር። ኢየሱስ ሴትየዋ ንስሐ እንደገባች የተገነዘበ ሲሆን ደግነት በጎደለው መንገድ ቢያባርራት ስሜቷ ምን ያህል ሊጎዳ እንደሚችል ተረዳ። በመሆኑም ላደረገችው መልካም ነገር ያመሰገናት ከመሆኑም ሌላ ኃጢአቷን ይቅር አላት። አንድ ፈሪሳዊ፣ ኢየሱስ ያደረገውን ነገር ባወገዘ ጊዜ ለእሱም ቢሆን በደግነት መልስ ሰጥቶታል። (ሉቃስ 7:​36-48) አምላክን በደግነቱ መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “የጌታ ባሪያ ሊጣላ አይገባውም” ካለ በኋላ “ከሰው ጋር ባለው ግንኙነት ዘዴኛ” መሆን እንደሚገባው ገልጿል። (2 ጢሞ. 2:​24 ግርጌ) ራሳችንን በሌሎች ቦታ ማስቀመጣችንና የምንናገረው ነገር እንዴት ሊነካቸው እንደሚችል አስቀድመን ማሰባችን በንግግራችን ብሎም በድርጊታችን የይሖዋን ደግነት ለማንጸባረቅ ያስችለናል።​—⁠ምሳሌ 15:​28፤ w15 5/15 4:8, 9

ማክሰኞ፣ ሰኔ 13

ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችል አቅም ካለህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አትበል።​—⁠ምሳሌ 3:​27

ወንድሞቻችን መከራ ሲደርስባቸው ቁሳዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ድጋፍ ልናደርግላቸው እንዲሁም ልናጽናናቸው እንችላለን። (ምሳሌ 17:​17) ለምሳሌ፣ ከተፈጥሮ አደጋ በኋላ እንደገና እንዲቋቋሙ ልንረዳቸው እንችላለን። ባሏ የሞተባት አንዲት እህት ኃይለኛ ወጀብ ቤቷን አፈራርሶባት ነበር፤ የተደረገላትን እርዳታ አስመልክታ እንደሚከተለው በማለት ምስጋናዋን ገልጻለች፦ “በይሖዋ ድርጅት ውስጥ በመሆኔ ለተደረገልኝ ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ድጋፍም እጅግ በጣም አመስጋኝ ነኝ።” አንዲት ያላገባች እህት ደግሞ ዝናብ የቀላቀለ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ በቤቷ ላይ ያደረሰውን ጉዳት ስትመለከት ግራ ተጋብታና በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተውጣ ነበር። ይህች እህት እርዳታ ካገኘች በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “ምን እንደሚሰማኝ መግለጽ አልችልም! ስሜቴን ሙሉ በሙሉ ለመግለጽ ቃላት ያጥሩኛል። . . . ይሖዋ አመሰግንሃለሁ!” በእርግጥም ሌሎች ለሚያስፈልጋቸው ነገር እውነተኛ አሳቢነት በሚያሳይ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ መታቀፋችን ያስደስተናል። ይበልጥ የሚያስደስተን ደግሞ ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ ለአምላክ ሕዝቦች በጥልቅ ማሰባቸው ነው። w15 6/15 1:17

ረቡዕ፣ ሰኔ 14

አሮጊቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት ሴቶችን ደግሞ እንደ እህቶች አድርገህ በፍጹም ንጽሕና ያዛቸው።​—⁠1 ጢሞ. 5:2

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት ምክር በመስጠት ከመጥፎ ምኞቶች እንድንርቅ እርዳታ ያበረክትልናል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር ከማሽኮርመም መራቅ እንዳለብን በግልጽ ያሳያል። አንዳንዶች ከአንድ ሰው ጋር እስካልተነካኩ ድረስ፣ የፍቅር ስሜት እንዳላቸው የሚጠቁም አካላዊ መግለጫ ማሳየት ወይም በፍቅር ስሜት መተያየት ምንም ጉዳት እንደሌለው ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ማሽኮርመምም ሆነ መሽ​ኮርመም ርኩስ የሆኑ ሐሳቦች እንዲቀሰቀሱ ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ይህም የብልግና ድርጊቶችን ወደመፈጸም ሊመራ ይችላል። እንዲህ ያለው ሁኔታ ከአሁን በፊት አጋጥሟል፤ ወደፊትም ሊያጋጥም ይችላል። በዚህ ረገድ ዮሴፍ ጥበብ የተንጸባረቀበት እርምጃ ወስዷል። የጌታው የጶጢፋር ሚስት አብሯት እንዲተኛ ለማድረግ በሞከረች ጊዜ ዮሴፍ አልተሸነፈም። እሷ ግን ተስፋ አልቆረጠችም። አብሯት እንዲሆን ነጋ ጠባ ትወተውተው ነበር። (ዘፍ. 39:7, 8, 10) ዮሴፍ ግን እሱን ለማማለል የምታደርገውን ጥረት እንድትቀጥልበት ላለማበረታታት ሌላው ቀርቶ በዝምታ ላለማለፍ ቆርጦ ነበር። ይህ ደግሞ ምንም ዓይነት መጥፎ ምኞት በልቡ ውስጥ ሥር እንዳይሰድ ረድቶታል። w15 6/15 3:10, 11

ሐሙስ፣ ሰኔ 15

የበደሉንን ይቅር እንዳልን በደላችንን ይቅር በለን።​—⁠ማቴ. 6:​12

ይሖዋ ስለ ራሳችን መንፈሳዊ ደህንነት ብቻ ሳይሆን እንደበደሉን የሚሰማንን ሰዎች ጨምሮ ስለ ሌሎች መንፈሳዊ ፍላጎትም እንድናስብ ይፈልጋል። በእርግጥ ብዙውን ጊዜ የሚደርሱብን በደሎች ቀላል ናቸው፤ ሆኖም ወንድሞቻችንን ይቅር ስንላቸው፣ ከልብ እንደምንወዳቸውና መሐሪው አምላክ ይቅር እንዳለን ሁሉ እኛም እነሱን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆንን እናሳያለን። (ቆላ. 3:​13) የሚያሳዝነው ነገር፣ ፍጽምና የጎደለን ሰዎች በመሆናችን አንዳንድ ጊዜ በሌሎች ላይ ቂም እንይዝ ይሆናል። (ዘሌ. 19:​18) ስለ ጉዳዩ ለሌሎች የምናወራ ከሆነ አንዳንዶች ከእኛ ጋር እንዲወግኑና በጉባኤ ውስጥ መከፋፈል እንዲፈጠር እናደርጋለን። እንዲህ ያለው ሁኔታ እንዲቀጥል የምንፈቅድ ከሆነ ደግሞ ለአምላክ ምሕረትና ለቤዛው አድናቆት እንደጎደለን እናሳያለን። የይቅር ባይነት መንፈስ የማናሳይ ከሆነ አባታችን በልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት መሠረት እኛን ይቅር ማለቱን ይተዋል። (ማቴ. 18:​35) ኢየሱስ የጸሎት ናሙናውን ካስተማረ በኋላ ወዲያውኑ ስለዚህ ጉዳይ ማብራሪያ ሰጥቷል። (ማቴ. 6:​14, 15) በመጨረሻም አምላክ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን፣ በኃጢአት ጎዳና ላለመመላለስ ጥረት ማድረግ አለብን።​—⁠1 ዮሐ. 3:4, 6፤ w15 6/15 5:9-11

ዓርብ፣ ሰኔ 16

ንጉሥ አስተውሎ በሚሠራ አገልጋይ ደስ ይሰኛል።​—⁠ምሳሌ 14:​35

ይሖዋ ለመንፈሳዊ ገነታችን ውበት አስተዋጽኦ እንድናበረክት የፈቀደልን መሆኑ ትልቅ መብት ነው። የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት በመስበክና ተጨማሪ ደቀ መዛሙርት በማፍራት መንፈሳዊውን ገነት ይበልጥ እናስውበዋለን። አንድ ሰው ራሱን ወስኖ ክርስቲያን እንዲሆን በረዳን ቁጥር የመንፈሳዊው ገነት ወሰን እንዲሰፋ እያደረግን ነው ሊባል ይችላል። (ኢሳ. 26:​15፤ 54:⁠2) ክርስቲያናዊ ባሕርያችንን በየጊዜው በማሻሻልም መንፈሳዊው ገነት ይበልጥ ማራኪ እንዲሆን ማድረግ እንችላለን። በዚህ መንገድ መንፈሳዊው ገነት ለሚመለከቱት ሰዎች ይበልጥ ውብ እንዲሆን እናደርጋለን። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች መጀመሪያ ወደ ድርጅቱ እንዲሳቡ እንዲሁም ወደ አምላክና ወደ ክርስቶስ እንዲቀርቡ የሚያነሳሳቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ይበልጥ የእኛ ንጹሕና ሰላማዊ ምግባር ነው። ይሖዋና ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ያለንን ውብ መንፈሳዊ ገነት ሲመለከቱ ምንኛ ይደሰቱ ይሆን! በአሁኑ ጊዜ መንፈሳዊ ገነታችንን ይበልጥ ከማስዋብ የምናገኘው ደስታ ወደፊት ምድርን ቃል በቃል ወደ ገነትነት ስንለውጥ ለምናገኘው እርካታ ቅምሻ ነው። w15 7/15 1:18-20

ቅዳሜ፣ ሰኔ 17

መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ [ትሆናላችሁ]።​—⁠ዘፍ. 3:5

በዛሬው ጊዜ ሁሉም ሰው፣ ‘አምላክ ነገሮችን የሚያከናውንበት መንገድ ከሰይጣን የላቀ ነው ወይስ የሰይጣን መንገድ ይሻላል?’ በሚለው ጉዳይ ረገድ አቋም መውሰድ አስፈልጎታል። በራስህ መንገድ ነገሮችን ከማከናወን ይልቅ ከይሖዋ ጎን በመቆም የእሱን ሕግጋትና መሥፈርቶች እየታዘዝክ እንደሆነ በሐቀኝነት መናገር ትችላለህ? በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሱ መከራዎች ብቸኛው መፍትሔ የእሱ መንግሥት እንደሆነ ታምናለህ? ወይስ የሰው ዘር ራሱን ማስተዳደር እንደሚችል ይሰማሃል? ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ፣ ሰዎች አከራካሪ በሆኑ ጉዳዮች ረገድ አመለካከትህን ሲጠይቁህ ከምትሰጠው መልስ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው። ፖለቲከኞችና የለውጥ አራማጆች በሰዎች መካከል መከፋፈል ለሚፈጥሩ ጉዳዮች እልባት ለማስገኘት ሲጥሩ ቆይተዋል። ይህን የሚያደርጉት በቅን ልቦና ተነሳስተው ሊሆን ይችላል። ይሁንና ክርስቲያኖች፣ የሰው ልጆችን ችግሮች ሊያስወግድና እውነተኛ ፍትሕ ሊያሰፍን የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ያውቃሉ። በመሆኑም ነገሩን ለይሖዋ መተው ይኖርብናል። ደግሞስ እያንዳንዱ ክርስቲያን የተሻለ እንደሆነ የሚያስበውን የመፍትሔ ሐሳብ የሚያራምድ ቢሆን ብዙም ሳይቆይ በጉባኤዎቻችን ውስጥ መከፋፈል አይፈጠርም? w15 7/15 3:7, 8

እሁድ፣ ሰኔ 18

በሥራዎችህም ሁሉ ላይ አሰላስላለሁ።​—⁠መዝ. 77:​12

ይሖዋ የፈጠራቸውን ነገሮች በማየት ለእኛ ጽኑ ፍቅር እንዳለው ማወቅ እንችላለን? አዎ እንችላለን፤ ምክንያቱም ይሖዋ ለመፍጠር መነሳሳቱ በራሱ ፍቅሩን ይገልጻል። (ሮም 1:​20) ምድርን ሲፈጥር ሕይወት ያለምንም ስጋት እንዲቀጥል የሚያስችል ሥነ ምህዳር እንዲኖራት አድርጓል። ያም ቢሆን በሕይወት ከመኖር ባለፈ እንድናገኝ የሚፈልገው ነገር አለ። ለምሳሌ በሕይወት ለመቀጠል መብላት ይኖርብናል። ይሖዋ ምድርን ሲፈጥር ለጤና ተስማሚ የሆነ ምግብ ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዕፀዋትን እንድታፈራ አድርጓታል። ሌላው ቀርቶ ምግብ መመገብ በራሱ አስደሳችና አርኪ እንዲሆንልን አድርጓል! (መክ. 9:⁠7) ይሖዋ ሲፈጥረን፣ ትርጉም ያለውና ውጤታማ ሥራ የማከናወን ችሎታ ሰጥቶናል፤ ይህ ደግሞ በሕይወታችን እንድንደሰት ተጨማሪ አስተዋጽኦ ያደርጋል። (መክ. 2:​24) የይሖዋ ዓላማ ሰዎች ምድርን እንዲሞሏት፣ እንዲገዟት እንዲሁም በዓሣዎች፣ በወፎች ብሎም ሕይወት ባላቸው ሌሎች ነገሮች ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው ነው። (ዘፍ. 1:​26-28) ይሖዋ፣ እሱን ለመምሰል የሚያስችሉን ባሕርያት እንዲኖሩን አድርጎ የፈጠረን መሆኑም ምን ያህል አፍቃሪ እንደሆነ ያሳያል!​—⁠ኤፌ. 5:1፤ w15 8/15 1:4, 5

ሰኞ፣ ሰኔ 19

ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ያ ቀን ድንገት ሳታስቡት እንደ ወጥመድ ይመጣባችኋል።​—⁠ሉቃስ 21:​34, 35

በዚህ ምድር ላይ የሚታዩት ክንውኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ እንዳለ እንዲሁም ይህ ክፉ ሥርዓት በቅርቡ መጥፋቱ አይቀሬ እንደሆነ በግልጽ ይጠቁማሉ። በመሆኑም በራእይ 17:​16 ላይ የተጠቀሱት “አሥሩ ቀንዶችና አውሬው” በዓለም ላይ ካሉት ሁኔታዎች የተነሳ በታላቂቱ ባቢሎን (የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ ታመለክታለች) ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንዲነሳሱ ረጅም ጊዜ ያስፈልጋል ብለን ማሰብ አይኖርብንም። መንግሥታት ይህን እርምጃ እንዲወስዱ ሐሳቡን ‘በልባቸው የሚያኖረው’ አምላክ እንደሆነና ይህም በቅጽበት እንዲሁም በማንኛውም ሰዓት ሊከሰት እንደሚችል ምንጊዜም እናስታውስ! (ራእይ 17:​17) ይህ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ የሚጠፋበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። በመሆኑም በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ለሚገኘው የኢየሱስ ማስጠንቀቂያ ትኩረት መስጠታችን የተገባ ነው። (ራእይ 16:​15) እንግዲያው ይሖዋ “እሱን በተስፋ ለሚጠባበቁት ሲል እርምጃ” እንደሚወስድ በመተማመን በጥድፊያ ስሜት ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።​—⁠ኢሳ. 64:4፤ w15 8/15 2:17

ማክሰኞ፣ ሰኔ 20

የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ ለእኔ ወንድሜ፣ እህቴና እናቴ ነው።​—⁠ማር. 3:​35

የአምላክን ሕግ ለማይከተሉ ሰዎች እንኳ ደግነት ማሳየት ቢገባንም ከእነሱ ጋር ወዳጅነት ልንመሠርት ወይም የቅርብ ጓደኛችን ልናደርጋቸው አይገባም። በመሆኑም አንድ ያላገባ የይሖዋ ምሥክር፣ ራሱን ለአምላክ ካልወሰነና ለይሖዋ ታማኝ ካልሆነ እንዲሁም የአምላክን የላቁ መሥፈርቶች ከማያከብር ሰው ጋር የፍቅር ጓደኝነት መመሥረቱ ስህተት ይሆናል። በይሖዋ ሕግጋት በማይመሩ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ከማግኘት ይበልጥ ትልቅ ቦታ ልንሰጠው የሚገባው ነገር፣ ክርስቲያናዊ አቋማችንን ይዘን መቀጠላችን ነው። የቅርብ ወዳጆቻችን ሊሆኑ የሚገባው የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎች ናቸው። መጥፎ ጓደኝነት የሚያስከትለው አስከፊ መዘዝ በእስራኤላውያን ላይ ደርሷል። (ዘፀ. 23:​24, 25፤ መዝ. 106:​35-39) ለአምላክ ታማኝ ባለመሆናቸው ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ “እነሆ፣ ቤታችሁ ለእናንተ የተተወ ይሆናል” ብሏቸዋል። (ማቴ. 23:​38) በመሆኑም ይሖዋ እስራኤላውያንን ትቶ በረከቱን አዲስ በተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ ላይ አደረገ።​—⁠ሥራ 2:1-4፤ w15 8/15 4:7, 8

ረቡዕ፣ ሰኔ 21

የዚህ ትእዛዝ ዓላማ ከንጹሕ ልብ፣ ከጥሩ ሕሊና . . . የሚመነጭ ፍቅር እንዲኖረን ነው።​—⁠1 ጢሞ. 1:5

ይሖዋ አምላክ ሰዎችን የፈጠረው ነፃ ምርጫ ማለትም የፈለጉትን የመምረጥ ነፃነት እንዲኖራቸው አድርጎ ነው። አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት እንዲሁም ለዘሮቻቸው ትክክለኛ ምርጫ እንዲያደርጉ የሚረዳ መሪ ማለትም ሕሊና ሰጥቷቸዋል፤ ይህም ትክክልና ስህተት የሆኑ ነገሮችን መለየት የሚያስችል ውስጣዊ ዳኛ ነው። ሕሊናችንን በአግባቡ ከተጠቀምንበት ጥሩ ነገር እንድናደርግና ስህተት ከመሥራት እንድንርቅ ሊረዳን ይችላል። በመሆኑም ሕሊናችን አምላክ እንደሚወደንና ሰዎች ሁሉ መልካም በማድረግ አንድነት እንዲኖራቸው ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ዛሬም ቢሆን ሰዎች ሕሊና አላቸው። (ሮም 2:​14, 15) ምንም እንኳ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከያዘው የሥነ ምግባር መሥፈርት እጅግ የራቁ ቢሆኑም ጥሩ ነገር የሚያደርጉና መጥፎ ነገር የሚጠሉ አንዳንድ ግለሰቦች ያጋጥሙናል። ብዙ ሰዎች የለየለት መጥፎ ድርጊት ከመፈጸም እንዲቆጠቡ የሚያደርገው ሕሊና ነው። ሰው ሁሉ ሕሊና ባይኖረው ኖሮ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ ምን ያህል የከፋ ይሆን እንደነበር መገመት ትችላለህ! አምላክ ለሰዎች ሕሊና በመስጠቱ ምንኛ አመስጋኞች ነን! w15 9/15 2:1, 2

ሐሙስ፣ ሰኔ 22

አብ ምን ያህል ታላቅ ፍቅር እንዳሳየን ተመልከቱ!​—⁠1 ዮሐ. 3:1

ሐዋርያው ዮሐንስ ያሰፈረውን ይህን ሐሳብ በጥልቀትና በአድናቆት ልናስብበት ይገባል። ዮሐንስ “አብ ምን ያህል ታላቅ ፍቅር እንዳሳየን ተመልከቱ” ሲል ክርስቲያኖች አምላክ ለእነሱ ያለው ፍቅር ምን ያህል ጥልቅና ሰፊ እንደሆነ እንዲሁም ፍቅሩን ያሳየበትን መንገድ እንዲያስቡ ማበረታታቱ ነበር። ከዚህ አንጻር የይሖዋን ፍቅር መረዳት ከቻልን ለእሱ ያለን ፍቅር ያድጋል፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር ያለን ዝምድና ይጠናከራል። ይሁንና አንዳንዶች አምላክ ሰዎችን ይወዳል የሚለው ሐሳብ አይዋጥላቸውም። አምላክ፣ ሰዎች እንዲፈሩትና እንዲታዘዙት ብቻ የሚፈልግ አካል እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። አሊያም በውስጣቸው ሥር ከሰደደ የተሳሳተ ትምህርት የተነሳ ሊሆን ይችላል አምላክ አፍቃሪ እንዳልሆነና እነሱም ሊወዱት እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። በአንጻሩ ደግሞ የፈለጉትን ነገር ቢያደርጉም ወይም የሚጠበቅባቸውን ነገር ሳያደርጉ ቢቀሩም እንኳ አምላክ እንደሚወዳቸው የሚያምኑ ሰዎች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ፍቅር የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ እንደሆነና ለእኛ ሲል ልጁን ቤዛ አድርጎ እንዲሰጥ ያነሳሳውም ፍቅር መሆኑን ተምረሃል።​—⁠ዮሐ. 3:​16፤ 1 ዮሐ. 4:8፤ w15 9/15 4:1, 2

ዓርብ፣ ሰኔ 23

ተግሣጽ . . . ያስከፋል።​—⁠ዕብ. 12:​11

ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ሲናገር የተግሣጽን አስፈላጊነት ወይም ዋጋማነት ማቃለሉ አልነበረም፤ ምክንያቱም ከዚያ በመቀጠል “በኋላ ግን በተግሣጽ ሥልጠና ላገኙ ሰዎች የጽድቅን ሰላማዊ ፍሬ ያፈራላቸዋል” ብሏል። ይሖዋን የምንወደው ከሆነ ምክር ሲሰጠን ሰምተን እንዳልሰማን ከመሆን ወይም ቅር ከመሰኘት እንቆጠባለን። ዛሬ ባለው ራስ ወዳድና እኔ ልቅደም ባይ በሆነ ትውልድ ውስጥ ምክርና ተግሣጽ መቀበል ይቅርና ስለ እነዚህ ነገሮች ማንሳት በራሱ አስቸጋሪ ነው። አንዳንዶች ደግሞ ምክር ወይም ተግሣጽ ሲሰጣቸው ቢቀበሉም እንኳ ይህን የሚያደርጉት እያጉረመረሙ ነው። ክርስቲያኖች ግን “ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ” የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል። ከዚህ ይልቅ “ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ” መገንዘብና መፈጸም ይኖርብናል። (ሮም 12:⁠2) ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት የተለያየ ወቅታዊ ምክር ይሰጠናል፤ ለምሳሌ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት፣ ስለ ጓደኛ ምርጫና ስለ መዝናኛ ምክር እናገኛለን። እንዲህ ያለውን መመሪያ በፈቃደኝነት በመቀበልና ተግባራዊ በማድረግ አመስጋኝ መሆናችንን እንዲሁም ይሖዋን ከልባችን እንደምንወደው እናሳያለን።​—⁠ዮሐ. 14:​31፤ ሮም 6:​17፤ w15 9/15 5:13, 15

ቅዳሜ፣ ሰኔ 24

እምነቴ እንዲጠነክር ደግሞ አንተ እርዳኝ።​—⁠ማር. 9:​24

በራሳችን ጥረት ብቻ እምነት ማዳበር አንችልም። እምነት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ አንድ ገጽታ ነው። (ገላ. 5:​22) በመሆኑም ኢየሱስ ተጨማሪ መንፈስ ለማግኘት እንድንጸልይ የሰጠውን ምክር መስማታችን ጥበብ ነው፤ ምክንያቱም አብ “ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን” እንደሚሰጥ ኢየሱስ በእርግጠኝነት ነግሮናል። (ሉቃስ 11:​13) እምነታችንን ከገነባን በኋላ ጠብቀን ለማቆየት ቀጣይ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እምነታችን ከሚነድ እሳት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። እሳት ስናቀጣጥል መጀመሪያ ላይ ቦግ ብሎ ሊነድ ይችላል። ይሁን እንጂ ዝም ብለን ከተውነው እሳቱ ከስሞ ፍም ብቻ ይቀራል፤ ቀስ በቀስ ደግሞ ሙቀት የሌለው አመድ ይሆናል። ይሁንና በየጊዜው እሳቱ ውስጥ እንጨት የምንጨምር ከሆነ መቀጣጠሉን ይቀጥላል። በተመሳሳይም የአምላክን ቃል አዘውትረን የምንመገብ ከሆነ እምነታችን ሕያው ሆኖ ይኖራል። መጽሐፍ ቅዱስን በቀጣይነት በማጥናት ለቃሉና ለቃሉ ባለቤት ጥልቅ ፍቅር ማዳበር እንችላለን፤ ይህ ደግሞ እምነታችን እያደገ እንዲሄድ የሚያስችል መሠረት ይሆነናል። w15 10/15 2:6, 7

እሁድ፣ ሰኔ 25

በሥራዎችህም ሁሉ ላይ አሰላስላለሁ።​—⁠መዝ. 77:​12

ጮክ ብሎ ማንበብ ያነበቡትን ነገር በቀላሉ ለማስታወስ እንደሚረዳ ሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶች አረጋግጠዋል። አእምሯችንን የፈጠረው አምላክ ደግሞ ይህን ያውቃል። በመሆኑም ኢያሱን የሕጉን መጽሐፍ “በለሆሳስ አንብበው” በማለት አዞታል። (ኢያሱ 1:⁠8) መጽሐፍ ቅዱስን ዝቅ ባለ ድምፅ ወይም በለሆሳስ ማንበብ የምታነበው ነገር አእምሮህ ላይ በሚገባ እንዲቀረጽ ያደርጋል። ይህም በተሻለ ሁኔታ አእምሮህን መሰብሰብ እንድትችል ይረዳሃል። ማንበብ ብዙ ጥረት የሚጠይቅ ባይሆንም ማሰላሰል ግን ትኩረትን ማሰባሰብ ይጠይቃል። ፍጽምና የሚጎድለው የሰው አእምሮ ብዙ ማሰብ በማይጠይቁና እምብዛም አድካሚ ባልሆኑ ሥራዎች በቀላሉ የመወሰድ አዝማሚያ ያለው ከዚህ የተነሳ ነው። በመሆኑም ለማሰላሰል ይበልጥ አመቺ የሆነው ጊዜ ዘና የምትልበት እንዲሁም ትኩረትህን የሚሰርቁና የሚያስጨንቁ ነገሮች የሌሉበት ወቅት ነው። መዝሙራዊው፣ ሌሊት ከእንቅልፉ የሚነቃበት ጊዜ ለማሰላሰል ጥሩ ሰዓት እንደሆነ ተረድቷል። (መዝ. 63:⁠6) ፍጹም አእምሮ የነበረው ኢየሱስ ጸጥ ባለ ቦታ ማሰላሰልና መጸለይ ምን ያህል ጥቅም እንዳለው ተገንዝቦ ነበር።​—⁠ሉቃስ 6:​12፤ w15 10/15 4:4, 6, 7

ሰኞ፣ ሰኔ 26

በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ [ነበር]።​—⁠ዮሐ. 2:​25

በአንድ ወቅት በገሊላ ሲያስተምር ካዳመጡት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ኢየሱስን ለመከተል ጉጉት ያላቸው ይመስል ነበር። (ዮሐ. 6:​22-24) ኢየሱስ ግን ልብ ማንበብ ስለሚችል ሰዎቹ ይበልጥ ያጓጓቸው ምግብ ማግኘታቸው እንጂ ትምህርቱ እንዳልነበረ አስተዋለ። ስህተታቸው ምን እንደሆነ በመገንዘብ በትዕግሥት እርማት ሰጣቸው፤ እንዲሁም ማሻሻያ ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ነገራቸው። (ዮሐ. 6:​25-27) የልጆቻችሁን ልብ ማንበብ ባትችሉም አስተዋዮች ከሆናችሁ ልጆቻችሁ ለአገልግሎት ምን አመለካከት እንዳላቸው መገንዘብ ትችላላችሁ። በርካታ ወላጆች በአገልግሎት መሃል ልጆቻቸው ትንሽ አረፍ እንዲሉ ሻይ ይጋብዟቸዋል። ሆኖም ‘ልጄን የሚያስደስተው አገልግሎት ነው ወይስ እረፍቱ?’ ብላችሁ ራሳችሁን በመጠየቅ ስሜታቸውን ለማስተዋል ጥረት አድርጉ። ልጆቻችሁ፣ አገልግሎት አስደሳችና የሚክስ እንዲሆንላቸው እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ካስተዋላችሁ ግብ እንዲያወጡ አግዟቸው። አብረዋችሁ ሲያገለግሉ በስብከቱ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለመርዳት ምን ማድረግ እንደምትችሉ አስቡ። w15 11/15 1:10, 11

ማክሰኞ፣ ሰኔ 27

ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።​—⁠ራእይ 21:4

አፍቃሪው አምላካችን ምንጊዜም ለታማኝ አገልጋዮቹ ከሁሉ የተሻለውን ነገር ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።” የይሖዋን ፍቅር ከልባቸው የሚያደንቁና እንደ ገዢያቸው አድርገው የሚታዘዙት ሁሉ ከፊታቸው እጅግ ግሩም ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል! የይሖዋ ቃል እንዲህ ይላል፦ “ነቀፋ የሌለበትን ሰው ልብ በል፤ ቀና የሆነውንም ሰው በትኩረት ተመልከት፤ የዚህ ሰው የወደፊት ሕይወት ሰላማዊ ይሆናልና። ኃጢአተኞች ሁሉ ግን ይጠፋሉ።” (መዝ. 37:​37, 38) “ነቀፋ የሌለበት” ሰው ይሖዋንና ልጁን ያውቃል፤ እንዲሁም ታዛዥ በመሆን የአምላክን ፈቃድ ይፈጽማል። (ዮሐ. 17:⁠3) እንዲህ ያለው ሰው በ1 ዮሐንስ 2:​17 ላይ የሚገኘውን “ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” የሚለውን ሐሳብ በቁም ነገር ይመለከተዋል። ይህ ዓለም የሚጠፋበት ጊዜ እየተቃረበ በመሆኑ “ይሖዋን ተስፋ አድርግ፤ መንገዱንም ተከተል” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን አጣዳፊ ነው።​—⁠መዝ. 37:​34፤ w15 11/15 3:11, 12

ረቡዕ፣ ሰኔ 28

አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው።​—⁠ማቴ. 9:​37

የአምላክ ሕዝቦች በተቻለ መጠን ምሥራቹን ለብዙ ሰዎች ለማድረስ የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅመዋል። በተለይ ‘ሠራተኞቹ ጥቂት’ በነበሩበት ወቅት ይህ በጣም አስፈላጊ ነበር። በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ አካባቢ የይሖዋ ሕዝቦች ቁጥር ጥቂት በሆነባቸው ቦታዎች ምሥራቹን ለብዙ ሰዎች ለማድረስ ጋዜጦች ጥቅም ላይ ውለዋል። ወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስል፣ ስብከቶቹን ለአንድ የጋዜጣ ድርጅት በየሳምንቱ ይልክ ነበር። ድርጅቱም ስብከቶቹን በዩናይትድ ስቴትስ፣ በካናዳና በአውሮፓ ባሉ ጋዜጦች ላይ እንዲወጡ በቴሌግራፍ ይልካል። በ1913 የወንድም ራስል ስብከቶች በ2,000 ጋዜጦች ላይ ይታተሙ የነበረ ሲሆን 15,000,000 የሚያህሉ አንባቢዎች ዘንድ ይደርሱ እንደነበር ይገመታል። ወንድም ራስል ከሞተ በኋላ ምሥራቹን ለማዳረስ የሚያስችል ሌላ ውጤታማ ዘዴ ጥቅም ላይ ዋለ። ሚያዝያ 16, 1922 ወንድም ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ በሬዲዮ የሚተላለፍ ንግግር አቀረበ፤ ወንድም ራዘርፎርድ በሬዲዮ ካስተላለፋቸው የመጀመሪያ ንግግሮች አንዱ የሆነውን ይህን ንግግር 50,000 ያህል ሰዎች እንዳዳመጡት ይገመታል። ከዚያም የካቲት 24, 1924 የድርጅቱ የመጀመሪያ የሬዲዮ ጣቢያ ይኸውም ደብልዩ ቢ ቢ አር ስርጭት ጀመረ። w15 11/15 5:10, 11

ሐሙስ፣ ሰኔ 29

መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ።​—⁠ዘፀ. 3:​14

ይሖዋ፣ ፍጥረታቱ እሱ የሚፈልገውን እንዲሆኑም ያደርጋል። አምላክ ከስሙ ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ ኖኅን መርከብ ሠሪ፣ ባስልኤልን የተዋጣለት የእጅ ጥበብ ባለሙያ፣ ጌድዮንን ኃያል ተዋጊ እንዲሁም ጳውሎስን የአሕዛብ ሐዋርያ አድርጓቸዋል። በእርግጥም የአምላክ ሕዝቦች መለኮታዊው ስም ትልቅ ትርጉም እንዳለው ይገነዘባሉ። የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴም ቢሆን መለኮታዊውን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማውጣት ለአምላክ ስም አክብሮት እንደጎደለው የሚያሳይ ድርጊት አይፈጽምም። ከ130 በሚበልጡ ቋንቋዎች የተዘጋጁ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱሶች የአምላክ ስም በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ በትክክለኛው ቦታ ላይ እንዲገባ በማድረግ ለስሙ አክብሮት አሳይተዋል። (ሚል. 3:​16) ከዚህ በተቃራኒ በአሁኑ ጊዜ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች መለኮታዊውን ስም በማውጣት በምትኩ “ጌታ” የሚለውን ማዕረግ ወይም በአካባቢው የሚታወቀውን አምላክ መጠሪያ የማስገባት ልማድ አላቸው። የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል፣ የአምላክን ስም የሚያስከብር የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች እንዲደርስ ለማድረግ ቅድሚያ የሰጠበት ዋነኛ ምክንያት ይህ ነው። w15 12/15 2:7-9

ዓርብ፣ ሰኔ 30

በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው “ታምሜአለሁ” አይልም።​—⁠ኢሳ. 33:​24

አምላክ የግለሰቦችን ጤንነት የሚነካ እርምጃ መውሰድ እንደሚችል ጥያቄ የለውም። እንዲህ የማድረግ ኃይል እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል። ለምሳሌ በአብርሃም ዘመን የነበረውን ፈርዖንን እና ከጊዜ በኋላ ደግሞ የሙሴን እህት ሚርያምን እንዲታመሙ በማድረግ ቀጥቷቸዋል። (ዘፍ. 12:​17፤ ዘኁ. 12:9, 10፤ 2 ሳሙ. 24:​15) እስራኤላውያን ታማኝ ካልሆኑ “በሽታዎችን ወይም መቅሰፍቶችን ሁሉ” በማምጣት እንደሚቀጣቸው አምላክ አስጠንቅቋቸው ነበር። (ዘዳ. 28:​58-61) በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ በሽታን ማስወገድ ወይም ሕዝቡ እንዳይታመሙ ጥበቃ ማድረግ ይችላል። (ዘፀ. 23:​25፤ ዘዳ. 7:​15) በተጨማሪም ሰዎችን መፈወስ ይችላል። ኢዮብ ሞትን እስኪመኝ ድረስ በጠና ታሞ የነበረ ቢሆንም አምላክ ፈውሶታል! (ኢዮብ 2:7፤ 3:​11-13፤ 42:​10, 16) አምላክ የታመመን ሰው የመፈወስ ኃይል እንዳለው ጥርጥር የለውም። ልጁም ተመሳሳይ ኃይል አለው። ኢየሱስ የሥጋ ደዌ ወይም የሚጥል በሽታ ያለባቸውን እንዲሁም ዓይነ ስውር አሊያም ሽባ የሆኑ ሰዎችን በተአምራዊ መንገድ እንደፈወሰ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ማቴ. 4:​23, 24፤ ዮሐ. 9:1-7) ኢየሱስ ያከናወናቸው ፈውሶች በአዲሱ ዓለም በላቀ ሁኔታ ለሚያከናውነው ነገር ቅምሻ እንደሆኑ ማወቅ ምንኛ ያበረታታል። w15 12/15 4:3, 4

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ