ሐምሌ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 1
እንግዳ መቀበልን አትርሱ።—ዕብ. 13:2
“እንግዳ መቀበል” ተብሎ የተተረጎመው ሐረግ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “ለእንግዶች ደግነት ማሳየት” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ይህ ሐረግ የአብርሃምንና የሎጥን ታሪክ ያስታውሰን ይሆናል። ሁለቱም ሰዎች ለማያውቋቸው እንግዶች ደግነት አሳይተዋል። እነዚህ እንግዶች መላእክት መሆናቸውን በኋላ ላይ ተገነዘቡ። (ዘፍ. 18:2-5፤ 19:1-3) እኛስ ሌሎችን ቤታችን ጠርተን ምግብ በመጋበዝ ወይም የሚያንጽ ጭውውት በማድረግ እንግዳ ተቀባይ መሆናችንን እናሳያለን? እንግዳ ተቀባይ መሆን ሲባል ሰፊ ወይም ብዙ ወጪ የሚያስወጣ ግብዣ ማድረግ ያስፈልገናል ማለት አይደለም፤ በሌላ በኩል ደግሞ የምንጋብዘው፣ ብድር ሊመልሱልን የሚችሉ ሰዎችን ብቻ መሆን የለበትም። (ሉቃስ 10:42፤ 14:12-14) ዋናው ግባችን ወንድሞቻችንን ማስደመም ሳይሆን ማበረታታት ነው! የወረዳ የበላይ ተመልካቻችንን እና ባለቤቱን ባንግባባቸውም እንኳ ደስ ብሎን በእንግድነት እንቀበላቸዋለን? (3 ዮሐ. 5-8) ሕይወታችን በሩጫ የተሞላ ከመሆኑም ሌላ ከዕለት ተዕለት ሕይወታችን ጋር በተያያዘ በሚያጋጥመን ጭንቀት የተነሳ ‘እንግዳ መቀበልን እንዳንረሳ’ መጠንቀቃችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! w16.01 1:11, 12
እሁድ፣ ሐምሌ 2
ቃል በተገባው መንፈስ ቅዱስ ታትማችኋል፤ ይህም . . . ለውርሻችን አስቀድሞ የተሰጠ ማረጋገጫ ነው።—ኤፌ. 1:13, 14
ቅቡዓን በዚህ መንገድ በመንፈስ ቅዱስ መቀባታቸው፣ እንደ ቀብድ አሊያም ወደፊት ለሚመጣው ነገር እንደ ዋስትና (ወይም መያዣ) ነው። አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን ይህን ማረጋገጫ ስላገኘ መቀባቱን ይተማመናል። (2 ቆሮ. 1:21, 22፤ 5:5) ግለሰቡ ጥሪውን እንደተቀበለ እርግጠኛ ነው። ሆኖም በሰማይ ሽልማቱን ማግኘት አለማግኘቱ የተመካው ለጥሪው ታማኝ ሆኖ በመገኘቱ ላይ ነው። ጴጥሮስ ነጥቡን እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “በመሆኑም ወንድሞች፣ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን አስተማማኝ ለማድረግ ከበፊቱ ይበልጥ ትጉ፤ እነዚህን ነገሮች የምታደርጉ ከሆነ ፈጽሞ አትወድቁምና። እንዲያውም በእጅጉ ትባረካላችሁ፤ ጌታችንና አዳኛችን ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥትም ትገባላችሁ።” (2 ጴጥ. 1:10, 11) እንግዲያው እያንዳንዱ ቅቡዕ ክርስቲያን ታማኝነቱን ለመጠበቅ መታገል አለበት። ታማኝ ካልሆነ ግን ሰማያዊ ጥሪ ወይም ግብዣ ማግኘቱ ምንም አይጠቅመውም።—ዕብ. 3:1፤ ራእይ 2:10፤ w16.01 3:6, 7
ሰኞ፣ ሐምሌ 3
ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል።—ማቴ. 23:12
አንድ ሰው የክርስቶስ ቅቡዕ ወንድም ቢሆንም እንኳ ለዚህ ግለሰብ ልዩ አክብሮት መስጠት ስህተት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አመራር የሚሰጡትን ክርስቲያን ሽማግሌዎች በእምነታቸው እንድንመስላቸው ያበረታታናል፤ ይሁንና ማንኛውንም ሰው እንደ መሪያችን በማየት ከፍ ከፍ እንድናደርግ ጨርሶ አያዘንም። (ዕብ. 13:7) እውነት ነው፣ ቅዱሳን መጻሕፍት አንዳንዶች “እጥፍ ክብር ሊሰጣቸው” እንደሚገባ ይናገራሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች ክብር ሊሰጣቸው የሚገባው ግን ቅቡዓን ስለሆኑ ሳይሆን “በመልካም ሁኔታ የሚያስተዳድሩ” እንዲሁም “በመናገርና በማስተማር ተግተው የሚሠሩ” በመሆናቸው ነው። (1 ጢሞ. 5:17) ሰማያዊ ጥሪ ያላቸው ክርስቲያኖች፣ ሌሎች አላስፈላጊ አድናቆት ወይም ትኩረት የሚሰጧቸው ከሆነ ይጨንቃቸዋል። ከዚህ የባሰው ደግሞ እንዲህ ያለው ለየት ያለ ትኩረት፣ ትሑት መሆን እንዲከብዳቸው ሊያደርግ ይችላል። (ሮም 12:3) ማናችንም ብንሆን ለክርስቶስ ወንድሞች ማሰናከያ መሆን አንፈልግም!—ሉቃስ 17:2፤ w16.01 4:9
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 4
እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው።—ምሳሌ 17:17
ወዳጅነት እንደ ውድ ሀብት ሊቆጠር ይችላል። ይሁንና ወዳጅነት፣ አንዴ ከገዛነው በኋላ የሆነ ቦታ አስቀምጠነው የአቧራ መከማቻ እንደሚሆን ዕቃ አይደለም። ወዳጅነት፣ እየፋፋና እየተመቸው እንዲሄድ እንክብካቤና ምግብ እንደሚሻ ሕይወት ያለው ነገር ነው። አብርሃም ከይሖዋ ጋር ያለውን ወዳጅነት ይንከባከበው እንዲሁም ወዳጅነቱ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ይጥር ነበር። ይህን ያደረገው እንዴት ነው? አብርሃም፣ ፈሪሃ አምላክና ታዛዥነት በማሳየት ረገድ ቀደም ሲል ያስመዘገበው ታሪክ በቂ እንደሆነ ፈጽሞ ተሰምቶት አያውቅም። ሰፊ የሆነውን ቤተሰቡን ይዞ ወደ ከነአን ሲጓዝ ቀላልም ይሁን ከባድ ውሳኔዎች ማድረግ አስፈልጎታል፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ ይሖዋ እንዲመራው ፈቅዷል። ይስሐቅ ከመወለዱ ከአንድ ዓመት በፊት ይኸውም አብርሃም የ99 ዓመት ሰው እያለ ይሖዋ በቤተሰቡ ውስጥ ያሉትን ወንዶች ሁሉ እንዲገርዝ አብርሃምን አዘዘው። አብርሃም በዚህ ትእዛዝ ላይ ጥያቄ አንስቶ ነበር? አሊያም ላለመታዘዝ ሰበብ ፈልጎ ይሆን? በፍጹም፤ በአምላክ በመታመን የታዘዘውን “በዚያኑ ዕለት” ፈጽሟል።—ዘፍ. 17:10-14, 23፤ w16.02 1:9, 10
ረቡዕ፣ ሐምሌ 5
ሕፃን እንኳ ባሕርይው ንጹሕና ትክክል መሆኑ በአድራጎቱ ይታወቃል።—ምሳሌ 20:11
በዕድሜ ትንሽ ሊባል የሚችል ልጅ እንኳ ትክክለኛውን ነገር ማድረግና ራሱን ለፈጣሪው መወሰን ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ሊገነዘብ ይችላል። በመሆኑም አንድ ወጣት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከጎለመሰና ራሱን ለይሖዋ ከወሰነ መጠመቁ አስፈላጊ ብሎም ተገቢ እርምጃ ነው። (ምሳሌ 20:7) አንድ ሰው ጎለመሰ ሲባል ምን ማለት ነው? ጉልምስና ሲባል አካላዊ እድገት ማድረግ ማለት ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የጎለመሱ ሰዎች “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት [አሠልጥነዋል]።” (ዕብ. 5:14) በመሆኑም የጎለመሱ ሰዎች በይሖዋ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር የሚያውቁ ከመሆኑም በላይ እነዚህን ነገሮች ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። ስለዚህ ስህተት የሆነውን ነገር ለማድረግ በቀላሉ አይፈተኑም፤ እንዲሁም ትክክል የሆነውን ነገር ለመፈጸም ሁልጊዜ ጉትጎታ አያስፈልጋቸውም። በእርግጥም አንድ የተጠመቀ ወጣት ወላጆቹ ወይም ሌሎች አዋቂዎች በሌሉበት እንኳ የአምላክን መሥፈርቶች ይጠብቃል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው።—ፊልጵ. 2:12፤ w16.03 1:4, 5
ሐሙስ፣ ሐምሌ 6
አትፍራ፤ አንተ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆናለህ፤ እኔ ደግሞ ከአንተ ቀጥዬ ሁለተኛ ሰው እሆናለሁ።—1 ሳሙ. 23:17
ወጣቱ ዳዊት ግዙፉን ጎልያድን የተጋፈጠበት መንገድ ዮናታንን በጣም አስገርሞት መሆን አለበት። አሁን ዳዊት “የፍልስጤማዊውን ራስ በእጁ እንደያዘ” የእስራኤል ንጉሥና የዮናታን አባት በሆነው በሳኦል ፊት ቆሟል። (1 ሳሙ. 17:57) ዮናታን ዳዊትን እንዲያደንቅ ያደረገው ድፍረቱ ሳይሆን አይቀርም። አምላክ ከዳዊት ጋር እንደሆነ በግልጽ ማየት ችሏል፤ በመሆኑም “ዮናታንና ዳዊት የጠበቀ ወዳጅነት መሠረቱ። . . . ዮናታንም ዳዊትን እንደ ራሱ ስለወደደው ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን ተጋቡ።” (1 ሳሙ. 18:1-3) ዮናታን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለዳዊት ታማኝ ሆኗል። አምላክ ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የመረጠው ዳዊትን ቢሆንም ዮናታን ከዳዊት ጋር ያለው ወዳጅነት ቀጥሏል። ሳኦል ዳዊትን ለመግደል ይፈልገው በነበረበት ወቅት ዮናታን ስለ ዳዊት ተጨንቆ ነበር። በመሆኑም በይሁዳ ምድረ በዳ በሚገኘው በሆሬሽ የነበረውን ወዳጁን ዳዊትን ለማበረታታት ወደዚያ ሄደ። በዚያም በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ በመናገር “በይሖዋ ላይ ያለው ትምክህት እንዲጠናከር [ዳዊትን] ረዳው።”—1 ሳሙ. 23:16፤ w16.02 3:1, 2
ዓርብ፣ ሐምሌ 7
የተዋጣለት ሠራተኛ ሆኜ [ከይሖዋ ጎን] ነበርኩ። በየዕለቱ በእኔ የተነሳ ልዩ ደስታ ይሰማው ነበር።—ምሳሌ 8:30
ከፍጥረት መጀመሪያ አንስቶ የዓላማ አንድነት በግልጽ ሲታይ ቆይቷል። አባትና ልጅ አንድ ላይ በመሥራት ዛሬ የምናያቸውን ልዩ ልዩ ፍጥረታት አስገኝተዋል። የአምላክ ፍጥረታትም እርስ በርስ ባላቸው የትብብር መንፈስ ይታወቃሉ። ኖኅና ቤተሰቡ መርከብ ሲሠሩ፣ በምድረ በዳ ይጓዝ የነበረው የአምላክ ሕዝብ የማደሪያውን ድንኳን ሲተክል፣ ሲያፈርስና ከቦታ ቦታ ሲያጓጉዝ አልፎ ተርፎም መዘምራን በይሖዋ ቤተ መቅደስ በሙዚቃ መሣሪያዎች ታጅበው በኅብረት እየዘመሩ እሱን ሲያወድሱ አገልጋዮቹ አንድነት እንዳላቸው ታይቷል። የእነዚህ ሁሉ ሥራዎች መሳካት በሰዎቹ መተባበር ላይ የተመካ ነበር። (ዘፍ. 6:14-16, 22፤ ዘኁ. 4:4-32፤ 1 ዜና 25:1-8) በኢየሱስ ክርስቶስ ራስነት ሥር የነበረው የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤም በኅብረት በመሥራት ይታወቅ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች በግለሰብ ደረጃ “ልዩ ልዩ ስጦታዎች” የነበሯቸው ከመሆኑም ሌላ “ልዩ ልዩ አገልግሎቶች” እና “ልዩ ልዩ ሥራዎች” በማከናወን ይሳተፉ ነበር፤ ይሁንና ሁሉም ‘የአንድ አካል’ ክፍል ነበሩ።—1 ቆሮ. 12:4-6, 12፤ w16.03 3:1, 2
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 8
ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ።—ማቴ. 28:19
ኢየሱስ ለተከታዮቹ ስለሰጣቸው የስብከት ሥራ አስብ። ምሥራቹን የሚሰብኩበት ዘዴም ሆነ ሥራውን የሚያከናውኑበት ስፋት በዓይነቱ የተለየ ነው። ከዚያ በፊት በነበሩት ዘመናት፣ እስራኤላውያን የሌላ ብሔር ሰዎች ይሖዋን ለማምለክ ወደ እስራኤል ሲመጡ በደስታ ይቀበሏቸው ነበር። (1 ነገ. 8:41-43) እንዲህ ያደርጉ የነበረው ኢየሱስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ትእዛዝ ከመስጠቱ በፊት ነው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ግን ወደ ብሔራት ሁሉ “ሂዱ” የሚል መመሪያ ተሰጣቸው። በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ይሖዋ አዲስ ዓይነት አሠራር መጠቀም እንደጀመረ የሚጠቁም ማስረጃ ታየ፤ ይህም ዓለም አቀፍ የወንጌላዊነት ሥራ ነው። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የአዲሱ ጉባኤ አባል ለሆኑት 120 ደቀ መዛሙርት ኃይል ስለሰጣቸው በተአምር ባገኙት ችሎታ ለአይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት ለተቀየሩ ሰዎች በየቋንቋቸው መስበክ ጀመሩ። (ሥራ 2:4-11) ከዚያም ክልላቸው ሰፍቶ ሳምራውያንን አካተተ። በኋላም በ36 ዓ.ም. ክልላቸው ይበልጥ በመስፋቱ ላልተገረዙ አሕዛብ መስበክ ጀመሩ። የስብከቱ መስክ አይሁዳውያንን ካቀፈ “ኩሬ” ተነስቶ የሰውን ዘር ወዳቀፈ “ውቅያኖስ” አደገ ሊባል ይችላል። w16.03 4:12
እሁድ፣ ሐምሌ 9
ከእኔ የሰማኸውን . . . ነገር፣ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ።—2 ጢሞ. 2:2
የአምላክ አገልጋዮች ሌሎችን ማሠልጠን ለስኬት እንደሚያበቃ ከጥንት ጀምሮ ተገንዝበዋል። ለምሳሌ አብራም ሎጥን ለማዳን ‘የሠለጠኑ አገልጋዮቹን ሰብስቦ’ ይዞ ሄዶ ነበር፤ ይህም ለስኬት አብቅቶታል። (ዘፍ. 14:14-16) በንጉሥ ዳዊት ዘመን በአምላክ ቤት የነበሩት መዘምራን “ለይሖዋ በሚቀርበው መዝሙር የሠለጠኑ” ነበሩ፤ ይህም ለአምላክ ውዳሴ አምጥቷል። (1 ዜና 25:7) ዛሬ ደግሞ ከሰይጣንና ከተከታዮቹ ጋር መንፈሳዊ ውጊያ እያካሄድን ነው። (ኤፌ. 6:11-13) በተጨማሪም ለይሖዋ ውዳሴ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው። (ዕብ. 13:15, 16) በመሆኑም እንደ ጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች ስኬታማ መሆን ከፈለግን ሥልጠና ማግኘት ይኖርብናል። ይሖዋ በጉባኤ ውስጥ ሌሎችን የማሠልጠን ኃላፊነት ለሽማግሌዎች በአደራ ሰጥቷል። አንድ ሽማግሌ፣ ብዙ ተሞክሮ ለሌለው አንድ ወንድም ሥልጠና ለመስጠት ከመነሳቱ በፊት የተማሪው ልብ ለሥልጠናው ዝግጁ እንዲሆን የሚረዱ ገንቢ የሆኑ አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችን ማካፈል አስፈላጊ እንደሆነ ይገነዘብ ይሆናል።—1 ጢሞ. 4:6፤ w15 4/15 2:1, 2
ሰኞ፣ ሐምሌ 10
[ኢየሱስ] ለሞት የመዳረግ አቅም ያለውን ዲያብሎስን በሞቱ አማካኝነት እንዳልነበረ [ያደርገዋል]።—ዕብ. 2:14
ይህ ሲባል ዲያብሎስ ሁሉንም ሰው በቀጥታ ይገድላል ማለት አይደለም። ሆኖም እሱ የሚያንጸባርቀው የነፍሰ ገዳይነት መንፈስ በመላው ዓለም ላይ ተስፋፍቷል። በተጨማሪም ሔዋን የሰይጣንን ውሸት በማመኗ እንዲሁም አዳም የአምላክን ትእዛዝ በመጣሱ ኃጢአትና ሞት ለሰው ዘር በሙሉ ተዳርሷል። (ሮም 5:12) ከዚህ አንጻር ዲያብሎስ “ለሞት የመዳረግ አቅም” እንዳለው ሊገለጽ ይችላል። ኢየሱስ እንደተናገረው ሰይጣን “ነፍሰ ገዳይ” ነው። (ዮሐ. 8:44) በእርግጥም ሰይጣን ኃያል ጠላታችን ነው! ዲያብሎስን ስንቃወም፣ እሱ ብቻ ሳይሆን የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ገዢነት በሚመለከት በተነሳው ጥያቄ ረገድ ከእሱ ጋር የወገኑት ሁሉ ጠላቶቻችን ይሆናሉ። ከእነዚህም መካከል ብዛት ያላቸው ሌሎች ዓመፀኛ መንፈሳዊ ፍጥረታት ወይም አጋንንት ይገኙበታል። (ራእይ 12:3, 4) አጋንንት፣ በቁጥጥራቸው ሥር ያሉትን ሰዎች ለከፍተኛ ሥቃይ በመዳረግ ከሰው በላይ ኃይል እንዳላቸው በተደጋጋሚ አሳይተዋል። (ማቴ. 8:28-32፤ ማር. 5:1-5) እንግዲያው የእነዚህን ክፉ መላእክትም ሆነ ‘የአጋንንት አለቃ’ የሆነውን የሰይጣንን ኃይል ፈጽሞ አቅልላችሁ አትመልከቱ። (ማቴ. 9:34) የይሖዋን ድጋፍ ካላገኘን በቀር ከዲያብሎስ ጋር በምናደርገው ውጊያ በጭራሽ ማሸነፍ አንችልም። w15 5/15 1:6, 7
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 11
ሴሰኞችም ሆኑ ጣዖት አምላኪዎች ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ግብረ ሰዶማውያን ወይም ሌቦች ወይም ስግብግቦች ወይም ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ቀማኞች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።—1 ቆሮ. 6:9, 10
የፆታ ብልግና ለመፈጸም የምትፈተን ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ድክመት እንዳለብህ አምነህ ተቀበል። (ሮም 7:22, 23) አምላክ ጥንካሬ እንዲሰጥህ ጸልይ። (ፊልጵ. 4:6, 7, 13) የሥነ ምግባር ብልግና ወደመፈጸም ሊመሩህ ከሚችሉ ሁኔታዎች ራቅ። (ምሳሌ 22:3) እንዲሁም ፈተና ሲያጋጥምህ ከፆታ ብልግና በመሸሽ ወዲያውኑ እርምጃ ውሰድ። (ዘፍ. 39:12) ኢየሱስ ፈተናን በመቃወም ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። በሰይጣን ማማለያዎች አልተታለለም፤ እንዲሁም በቀረበለት ግብዣ ላይ ማሰብ ብሎም ጥቅምና ጉዳቱን ማመዛዘን አላስፈለገውም። ከዚህ ይልቅ “ተብሎ ተጽፏል” በማለት ወዲያውኑ ምላሽ ሰጠ። (ማቴ. 4:4-10) ኢየሱስ የአምላክን ቃል ያውቅ ስለነበር ፈተና ሲያጋጥመው ፈጣን እርምጃ መውሰድና ከቅዱሳን መጻሕፍት ጠቅሶ መልስ መስጠት ችሏል። እኛም ከሰይጣን ጋር ተዋግተን ማሸነፍ እንድንችል የፆታ ብልግና ፈተና እንዲሆንብን መፍቀድ የለብንም። w15 5/15 2:15, 16
ረቡዕ፣ ሐምሌ 12
አምላክን የምትመስሉ ሁኑ።—ኤፌ. 5:1
እኛ ያላለፍንበትን ሁኔታ መረዳት መቻላችን የይሖዋን ጥበብ እንድናንጸባርቅና የምናደርጋቸው ነገሮች ሊያስከትሉ የሚችሉትን ውጤት አስቀድመን እንድናስብ ይረዳናል። ይሖዋ ከፈለገ አንዳንድ ድርጊቶች የሚያስከትሉትን ውጤት በሙሉ አስቀድሞ ማወቅ ይችላል። የሰው ልጆች የወደፊቱን ጊዜ የማወቅ ችሎታ ባይኖረንም ልንወስደው ያሰብነው እርምጃ ምን ውጤት እንደሚያስከትል አስቀድመን ማሰባችን ተገቢ ነው። አምላክን በጥበቡ መምሰል ከፈለግን ድርጊታችን የሚያስከትለውን ውጤት ማሰብ አልፎ ተርፎም በዓይነ ሕሊናችን ለመሳል መሞከር ይኖርብናል። ለምሳሌ፣ እየተጠናናን ከሆነ በዚህ ወቅት የፆታ ስሜት ምን ያህል ሊያይል እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልገናል። ከይሖዋ ጋር ያለን ውድ ዝምድና አደጋ ላይ እንዲወድቅ ሊያደርግ የሚችል ዕቅድ ላለማውጣት ወይም ምንም ዓይነት ነገር ላለማድረግ እንጠንቀቅ! በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የሚከተለውን ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ እንጣር፦ “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል፤ ተሞክሮ የሌለው ግን ዝም ብሎ ይሄዳል፤ መዘዙንም ይቀበላል።”—ምሳሌ 22:3፤ w15 5/15 4:10, 11
ሐሙስ፣ ሐምሌ 13
አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።—ማቴ. 5:28
ንጉሥ ዳዊት ምን እንዳጋጠመው አትዘንጋ። ዳዊት “በሰገነቱ ላይ ሳለ . . . አንዲት ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ።” (2 ሳሙ. 11:2) ዳዊት ወዲያውኑ ዘወር በማለት ትኩረቱን በሌላ ነገር ላይ ከማድረግ ይልቅ ሴትየዋን መመልከቱን ቀጠለ። ይህም የሌላን ሰው ሚስት እንዲመኝ ያደረገው ሲሆን ይህ ደግሞ ከእሷ ጋር ምንዝር ወደ መፈጸም መራው። የብልግና ምኞቶችን ለማስወገድ ታማኙ ኢዮብ እንዳደረገው ‘ከዓይናችን ጋር ቃል ኪዳን መግባት’ ይኖርብናል። (ኢዮብ 31:1, 7, 9) ዓይናችንን ለመቆጣጠርና አንድን ሰው በፍትወት ስሜት ከመመልከት ለመቆጠብ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ያስፈልገናል። ይህም በኮምፒውተር፣ በመጽሔት፣ በተሰቀለ ማስታወቂያ ወይም በማንኛውም ቦታ ላይ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ምስል ካጋጠመን ዞር በማለት ትኩረታችንን በሌላ ነገር ላይ ማድረግን ይጨምራል። መጥፎ ምኞቶችን ለማስወገድ በመታገል ረገድ ወዲያውኑ እርምጃ ውሰድ። ታዛዥ በመሆን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ አድርግ፤ ይህም መጥፎ ድርጊቶችን ለማስወገድና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናህን ጠብቀህ ለመኖር ይረዳሃል።—ያዕ. 1:21-25፤ w15 6/15 3:12-14
ዓርብ፣ ሐምሌ 14
ወደ ፈተና አታግባን።—ማቴ. 6:13
ኢየሱስ ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ ያጋጠመውን ነገር መመልከታችን “ወደ ፈተና አታግባን” ብለን መጸለይ አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል። የአምላክ መንፈስ ኢየሱስን ወደ ምድረ በዳ መራው። ለምን? ጥቅሱ “ዲያብሎስ ይፈትነው ዘንድ” ይላል። (ማቴ. 4:1) ይህ ሊያስገርመን ይገባል? አምላክ፣ ልጁን ወደ ምድር የላከበትን ዋነኛ ምክንያት ካወቅን ይህ አያስገርመንም። ኢየሱስ ወደ ምድር የተላከው አዳምና ሔዋን በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ ሲያምፁ ለተነሳው ጥያቄ እልባት ለመስጠት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ሰይጣን እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች አስነስቷል፦ አምላክ ሰውን ሲፈጥረው ጉድለት ነበረው? ፍጹም የሆነ ሰው፣ “ክፉው” ተጽዕኖ ቢያሳድርበትም እንኳ የአምላክን ሉዓላዊነት መደገፍ ይችል ነበር? ደግሞስ ሰይጣን እንዳለው የሰው ዘር ከአምላክ አገዛዝ ውጭ የተሻለ ሕይወት መምራት ይችላል? (ዘፍ. 3:4, 5) እንዲህ ያሉት ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ ጊዜ ያስፈልጋል፤ ሆኖም ጥያቄዎቹ መልስ ማግኘታቸው የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት በሙሉ አምላክ ሉዓላዊነቱን ጠቃሚ በሆነ መንገድ እንደሚጠቀምበት ማየት እንዲችሉ ያደርጋል። w15 6/15 5:12
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 15
ታላቅ መከራ ይከሰታል።—ማቴ. 24:21
ታላቁ መከራ የሚጀምረው እንዴት ነው? በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ስለ “ታላቂቱ ባቢሎን” ጥፋት የሚገልጸው ዘገባ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። (ራእይ 17:5-7) የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ ከአመንዝራ ጋር መመሳሰላቸው ምንኛ ተገቢ ነው! ቀሳውስት ከዚህ ክፉ ዓለም መሪዎች ጋር አመንዝረዋል። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስንና መንግሥቱን በታማኝነት ከመደገፍ ይልቅ በፖለቲካው ዓለም ተደማጭነት ለማግኘት ሲሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ችላ ብለዋል። የተከተሉት ጎዳና፣ ንጹሕ ከሆኑትና በደናግል ከተመሰሉት የአምላክ ቅቡዓን በእጅጉ የተለየ ነው። (2 ቆሮ. 11:2፤ ያዕ. 1:27፤ ራእይ 14:4) ሆኖም በዝሙት አዳሪ የተመሰለችውን ድርጅት የሚያጠፋት ማን ነው? ይሖዋ “ደማቅ ቀይ” በሆነው አውሬ “አሥር ቀንዶች” ልብ ውስጥ “ሐሳቡን” ያኖራል። እነዚህ ቀንዶች፣ ‘በደማቅ ቀይ አውሬ’ ለተመሰለው ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ የሚሰጡትን በአሁኑ ጊዜ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ይወክላሉ።—ራእይ 17:3, 16-18፤ w15 7/15 2:3, 4
እሁድ፣ ሐምሌ 16
እያንዳንዳችሁ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፣” “እኔ ግን የአጵሎስ ነኝ፣” “እኔ ደግሞ የኬፋ ነኝ፣” “እኔ የክርስቶስ ነኝ” ትላላችሁ።—1 ቆሮ. 1:12
እንዲህ ያለውን ክፍፍል የሚፈጥር አመለካከት ለማስወገድ መፍትሔው ምንድን ነው? ጳውሎስ ለክርስቲያኖች የሚከተለውን ምክር ሰጥቷቸዋል፦ “ወንድሞች፣ ሁላችሁም ንግግራችሁ አንድ እንዲሆንና በመካከላችሁ መከፋፈል እንዳይኖር፣ ከዚህ ይልቅ በአስተሳሰብም ሆነ በዓላማ ፍጹም አንድነት እንዲኖራችሁ . . . አጥብቄ አሳስባችኋለሁ።” (1 ቆሮ. 1:10, 11, 13) ዛሬም ቢሆን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ምንም ዓይነት መከፋፈል ሊኖር አይገባም። (ሮም 16:17, 18) ጳውሎስ፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በምድር ባሉ ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ዜግነታቸው በሰማይ መሆኑን እንዲያስታውሱ አሳስቧቸዋል። (ፊልጵ. 3:17-20) እነዚህ ክርስቲያኖች ክርስቶስን ተክተው የሚሠሩ አምባሳደሮች ናቸው። አምባሳደሮች ደግሞ በተመደቡባቸው አገራት ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ አይገቡም። ታማኝ መሆን ያለባቸው ለሌላ መንግሥት ነው። (2 ቆሮ. 5:20) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች በመሆናቸው በዚህ ዓለም ላይ ባሉ ውዝግቦች ረገድ ከማንም ወገን አለመቆማቸው ተገቢ ነው። w15 7/15 3:9, 10
ሰኞ፣ ሐምሌ 17
እሱ . . . መሐሪ ነው፤በደላቸውን ይቅር ይል ነበር፤ደግሞም አላጠፋቸውም። ቁጣውን ሁሉ ከመቀስቀስ ይልቅ ብዙ ጊዜ ስሜቱን ይገታ ነበር።—መዝ. 78:38
በዚህ ጥቅስ ላይ ማሰላሰልህ ይሖዋ ስለ አንተ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብና እንደሚወድህ እንድትገነዘብ ሊያደርግህ ይችላል። በይሖዋ ፊት ውድ እንደሆንክ እርግጠኛ ሁን። (1 ጴጥ. 5:6, 7) አምላክ እኛን ለማነጋገር በዋነኝነት የሚጠቀመው በመጽሐፍ ቅዱስ ስለሆነ ለቃሉ ጥልቅ አክብሮት ሊኖረን ይገባል። ወላጆችም ሆኑ ልጆች አንዳቸው ለሌላው ፍቅር እንዳላቸው እንዲሰማቸው እንዲሁም በመካከላቸው የመተማመን ስሜት እንዲኖር፣ ትርጉም ያለውና ደግነት የሚንጸባረቅበት የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋቸው ወሳኝ ነው። ከይሖዋ ጋር በተያያዘስ ምን መጠበቅ ይኖርብናል? ይሖዋን አይተነውም ሆነ ድምፁን ሰምተን ባናውቅም እንኳ በመንፈስ መሪነት ባስጻፈው ቃሉ አማካኝነት “ያነጋግረናል”፤ እኛም ልናዳምጠው ይገባል። (ኢሳ. 30:20, 21) ራሳችንን ለእሱ የወሰንን ሕዝቦቹ በመሆናችን ይሖዋ ሊመራን እንዲሁም ከጉዳት ሊጠብቀን ይፈልጋል። በተጨማሪም እንድናውቀውና እንድንተማመንበት ይሻል።—መዝ. 19:7-11፤ ምሳሌ 1:33፤ w15 8/15 1:6, 7
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 18
ወደ አምላክ ቅረቡ፤እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።—ያዕ. 4:8
በአዲሱ ዓለም ውስጥ ምድር ገነት ስትሆን ለማየት የምንጓጓ ቢሆንም በዚያ የምናገኛቸው መንፈሳዊ በረከቶች ትልቁን ቦታ ይይዛሉ። የይሖዋ ስም እንደተቀደሰና ሉዓላዊነቱ እንደተረጋገጠ ማወቃችን እንዴት ያለ ጥልቅ ደስታ ያመጣልናል! (ማቴ. 6:9, 10) ይሖዋ ለሰዎችም ሆነ ለምድር ከመጀመሪያው የነበረው ዓላማ ሲፈጸም ስናይ እጅግ እንደሰታለን። ከዚህም ሌላ ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና ስንደርስ ወደ ይሖዋ መቅረብ ምን ያህል ቀላል እንደሚሆንልን አስበው! (መዝ. 73:28) ኢየሱስ “በአምላክ ዘንድ . . . ሁሉ ነገር ይቻላል” የሚል ማረጋገጫ ስለሰጠን እነዚህን በረከቶች እንደምናገኝ ጥያቄ የለውም። (ማቴ. 19:25, 26) ይሁንና በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር፣ ብሎም ከክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ባሻገር በሕይወት ለመቀጠል ተስፋ የምናደርግ ከሆነ የዘላለምን ሕይወት ‘አጥብቀን ለመያዝ’ እርምጃ መውሰድ ያለብን ዛሬ ነው። (1 ጢሞ. 6:19) የዚህን ክፉ ዓለም ፍጻሜ እየተጠባበቅን መኖር ያለብን ከመሆኑም ሌላ በአዲሱ ዓለም ለሚኖረው ሕይወት ለመዘጋጀት የሚረዱንን እርምጃዎች አሁኑኑ መውሰድ ያስፈልገናል። w15 8/15 3:2, 3
ረቡዕ፣ ሐምሌ 19
የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው።—ዮሐ. 17:3
የዚህ ዓለም የመገናኛ ብዙኃንና የመዝናኛው ኢንዱስትሪ የሚያቀርቧቸው አብዛኞቹ ነገሮች የክርስቲያኖችን መንፈሳዊነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው። እነዚህ ነገሮች በይሖዋና እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት እንድናዳብር አይረዱንም። ከዚህ በተቃራኒ ሰዎች በሰይጣን ክፉ ዓለም እንዲታመኑ የሚያበረታቱ ናቸው። በመሆኑም የምናየው፣ የምናነበው ወይም የምንሰማው ነገር “ዓለማዊ ምኞቶችን” የሚቀሰቅስ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። (ቲቶ 2:12) ከዚህ ዓለም በተቃራኒ የይሖዋ ድርጅት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ያደረገልን ዝግጅቶች የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝልን ምግባር እንድንከተል ያበረታቱናል። እውነተኛውን አምልኮ የሚያስፋፉ መጽሔቶች፣ ብሮሹሮች፣ መጻሕፍት፣ ቪዲዮዎች እንዲሁም ድረ ገጾች ያሉን በመሆኑ ምንኛ ተባርከናል! በተጨማሪም የአምላክ ድርጅት በዓለም ዙሪያ ከ110,000 በሚበልጡ ጉባኤዎች አማካኝነት ቋሚ የሆኑ ስብሰባዎች እንዲኖሩን ዝግጅት አድርጎልናል። በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ በአምላክ እንዲሁም እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት እንድናዳብር የሚረዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች ይቀርባሉ።—ዕብ. 10:24, 25፤ w15 8/15 4:9, 11
ሐሙስ፣ ሐምሌ 20
ሕሊናቸው ከእነሱ ጋር ሆኖ [ይመሠክራል]።—ሮም 2:15
የይሖዋ አገልጋዮች ሕሊናቸውን ለማሠልጠን ጥረት ያደርጋሉ። ሕሊናቸው የሚነግራቸው ነገር የአምላክ ቃል ትክክልና ስህተት እንዲሁም ጥሩና መጥፎ የሆነውን በተመለከተ ከያዘው መሥፈርት ጋር የሚስማማ እንዲሆን ይፈልጋሉ። በአግባቡ የሠለጠነ ሕሊና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይሁንና ክርስቲያናዊ ሕሊናን ማሠልጠንና በዚያ መጠቀም አእምሮን የማሠራት ጉዳይ ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ሕሊናን ከእምነትና ከፍቅር ጋር ያያይዘዋል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የዚህ ትእዛዝ ዓላማ ከንጹሕ ልብ፣ ከጥሩ ሕሊናና ግብዝነት ከሌለበት እምነት የሚመነጭ ፍቅር እንዲኖረን ነው።” (1 ጢሞ. 1:5) ሕሊናችንን ካሠለጠንነውና የሚነግረንን ነገር ከሰማን ለይሖዋ ያለን ፍቅር እያደገ ይሄዳል፤ እምነታችንም ይጠናከራል። ደግሞም ሕሊናችንን የምንጠቀምበት መንገድ የመንፈሳዊነታችንን ጥልቀት፣ የልባችንን ጥሩነትና ይሖዋን ለማስደሰት ያለንን ብርቱ ፍላጎት ያሳያል። በእርግጥም ሕሊናችን የሚያሰማው ድምፅ እውነተኛ ማንነታችንን በሚገባ ያሳያል። w15 9/15 2:2, 3
ዓርብ፣ ሐምሌ 21
አብ ምን ያህል ታላቅ ፍቅር እንዳሳየን ተመልከቱ!—1 ዮሐ. 3:1
ይሖዋ የሰው ልጆች ሁሉ ፈጣሪ ነው። (መዝ. 100:3-5) ከዚህም የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ አዳምን “የአምላክ ልጅ” ብሎ ይጠራዋል፤ ኢየሱስ ደግሞ ተከታዮቹን ወደ አምላክ ሲጸልዩ “በሰማያት የምትኖር አባታችን” ብለው እንዲጠሩት አስተምሯቸዋል። (ሉቃስ 3:38፤ ማቴ. 6:9) ይሖዋ ሕይወት ሰጪ ስለሆነ አባታችን ነው፤ በእኛና በእሱ መካከል ያለው ዝምድና በአንድ አባትና በልጆቹ መካከል ካለው ዝምድና ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በአጭር አነጋገር አንድ ጥሩ አባት ልጆቹን እንደሚወድ ሁሉ ይሖዋም እኛን ይወደናል። እርግጥ ሰብዓዊ አባቶች ፍጹም አይደሉም። የፈለጉትን ያህል ጥረት ቢያደርጉም እንኳ ይሖዋ አባታዊ ፍቅሩን ያሳየበትን መንገድ ሙሉ በሙሉ ማንጸባረቅ አይችሉም። እንዲያውም አንዳንዶች ልጅ ሳሉ በቤተሰባቸው ውስጥ ካጋጠማቸው ሁኔታ የተነሳ በስሜታቸው ወይም በአእምሯቸው ላይ የማይሽር ጠባሳ የተወ መጥፎ ትዝታ አላቸው። ይህ ስሜታቸውን ጎድቶትና አሳዛኝ ሁኔታ አስከትሎባቸው ሊሆን ይችላል። ይሖዋ እንዲህ ዓይነት አባት እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። (መዝ. 27:10) ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደንና እንዴት እንደሚንከባከበን ማወቃችን ወደ እሱ እንድንቀርብ እንደሚያደርገን የታወቀ ነው።—ያዕ. 4:8፤ w15 9/15 4:3, 4
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 22
እሱ ደስ ለሚሰኝበት ነገር ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ለተግባር እንድትነሳሱ በማድረግ ኃይል የሚሰጣችሁ አምላክ ነው።—ፊልጵ. 2:13
የአምላክን ፈቃድ ግምት ውስጥ ሳናስገባ ውሳኔ የምናደርግ ከሆነ ፍቅርና እምነት እንደሚጎድለን ያሳያል። በሳሙኤል ዘመን በአንድ ወቅት እስራኤላውያን ከፍልስጥኤማውያን ጋር ባደረጉት ውጊያ ከባድ ሽንፈት ደርሶባቸው ነበር። በዚህ ጊዜ አምላክ እንዲረዳቸውና እንዲጠብቃቸው ፈልገው ነበር። ታዲያ ምን አደረጉ? “አብሮን እንዲሆንና ከጠላቶቻችን እጅ እንዲያድነን የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ከሴሎ ይዘነው እንሂድ” አሉ። ውጤቱስ ምን ሆነ? “በጣም ብዙ ሕዝብ አለቀ፤ ከእስራኤላውያንም ወገን 30,000 እግረኛ ወታደር ሞተ። የአምላክም ታቦት ተማረከ።” (1 ሳሙ. 4:2-4, 10, 11) እስራኤላውያን ታቦቱን ይዘው መሄዳቸው ይሖዋ እንዲረዳቸው የፈለጉ ሊመስል ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ጥረት አላደረጉም፤ ከዚህ ይልቅ በራሳቸው አመለካከት በመመራታቸው ለከፋ ጥፋት ተዳርገዋል።—ምሳሌ 14:12፤ w15 9/15 5:16, 17
እሁድ፣ ሐምሌ 23
እምነት ጨምርልን።—ሉቃስ 17:5
ጠንካራ እምነት ለመገንባትና ጠብቀህ ለማቆየት ማድረግ የምትችለው ነገር ምንድን ነው? እስክትጠመቅ ድረስ ባገኘኸው እውቀት ረክተህ አትኑር። (ዕብ. 6:1, 2) ፍጻሜያቸውን ስላገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መማርህን ቀጥል፤ ምክንያቱም እነዚህ ትንቢቶች እምነትህን እንድትገነባ የሚያስችሉ በቂ ማስረጃዎች እንድታገኝ ያደርጉሃል። ከዚህ በተጨማሪ ጠንካራ እምነት ካላቸው ሰዎች መካከል የሚያስቆጥረን እምነት ያለህ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ የአምላክን ቃል እንደ መለኪያ አድርገህ መጠቀም ትችላለህ። (ያዕ. 1:25፤ 2:24, 26) ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን ‘እኔ በእናንተ እምነት እናንተም በእኔ እምነት እርስ በርሳችን እንበረታታ’ ብሏቸው ነበር። (ሮም 1:12) ከእምነት ባልንጀሮቻችን፣ በተለይ ደግሞ “ተፈትኖ የተረጋገጠ” እምነት እንዳላቸው ካሳዩ ወንድሞቻችን ጋር ስንሆን አንዳችን የሌላውን እምነት መገንባት እንችላለን። (ያዕ. 1:3) መጥፎ ባልንጀርነት እምነት ያጠፋል፤ በአንጻሩ ግን ጥሩ ባልንጀርነት እምነት ይገነባል። (1 ቆሮ. 15:33) ‘መሰብሰባችንን ቸል እንዳንል’ ከዚህ ይልቅ ‘እርስ በርስ እንድንበረታታ’ የተመከርንበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።—ዕብ. 10:24, 25፤ w15 10/15 2:2, 8, 9
ሰኞ፣ ሐምሌ 24
በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ ይሁን።—1 ጢሞ. 4:15
አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ስንዘጋጅ የምናሰላስልበት ጊዜ ያስፈልገናል። እያንዳንዱን ተማሪ በአእምሯችን በመያዝ የምንዘጋጅ ከሆነ ተማሪው እድገት እንዲያደርግ ለመርዳት ምን ዓይነት የአመለካከት ጥያቄ ብንጠይቀው ወይም የትኛውን ምሳሌ ብንጠቀም የተሻለ እንደሆነ ልናስብ እንችላለን። እንዲህ በማድረግ የምናሳልፈው ጊዜ አስደሳች ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም በእነዚህ ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን የእኛን እምነት ያጠናክራል፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችንን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድና በቅንዓት ለማስጠናት ያስችለናል። ወደ መስክ አገልግሎት ለመውጣት ልባችንን በምናዘጋጅበት ጊዜም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። (ዕዝራ 7:10) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሆነው ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ አንድ ምዕራፍ ማንበባችን ለአገልግሎት ያለን ‘ቅንዓት’ እንዲቀጣጠል ያደርጋል። በዚያን ዕለት ልንጠቀምበት ባሰብነው ጥቅስና ጽሑፍ ላይ ማሰላሰላችን አገልግሎታችንን በቅንዓት እንድናከናውን ይረዳናል። (2 ጢሞ. 1:6) በክልልህ ስላሉ ሰዎችና ፍላጎታቸውን ለመቀስቀስ ማድረግ ስለምትችለው ነገር አስብ። እንዲህ ያለ ዝግጅት ማድረጋችን ከአምላክ ቃል በሚገኘው “መንፈስና ኃይል” ተጠቅመን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድንሰብክ ያነሳሳናል።—1 ቆሮ. 2:4፤ w15 10/15 4:9
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 25
ቀኝ ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው።—ማቴ. 5:29
ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘ልጄ የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ለማየት እንዲፈተን የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? እነዚህ ነገሮች በጣም አደገኛ የሆኑበትን ምክንያት ያውቃል? እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ለማየት ቢፈተን መጥቶ ሊያነጋግረኝ እንዲችል በቀላሉ የምቀረብ ነኝ?’ ልጆቻችሁ ገና ትናንሽ እያሉም እንኳ እንዲህ ልትሏቸው ትችላላችሁ፦ “ሳታስበው የብልግና ድረ ገጽ ብትከፍትና ለማየት ብትፈተን መጥተህ ንገረኝ። ፈጽሞ ልታፍር አይገባም። የእኔ ፍላጎት አንተን መርዳት ነው።” አስተዋይ መሆናችሁ የራሳችሁን መዝናኛም በጥንቃቄ ለመምረጥ ያስችላችኋል። ፕራናስ የተባለ አንድ አባት እንዲህ ብሏል፦ “እኛ ወላጆች ከሙዚቃ፣ ከፊልሞች ወይም ከመጻሕፍት ጋር በተያያዘ የምናደርገው ምርጫ ለቤተሰባችን ምሳሌ ይሆናል። ስለተለያዩ ነገሮች ለልጆቻችሁ ብዙ ነገር ትነግሯቸው ይሆናል፤ ልጆቻችሁ የሚያደርጉት ግን እናንተ ስታደርጉ የሚያዩትን ነው።” እናንተ ተጠንቅቃችሁ ጥሩ መዝናኛ ስትመርጡ ልጆቻችሁ ካዩ እነሱም ተመሳሳይ ምርጫ ያደርጉ ይሆናል።—ሮም 2:21-24፤ w15 11/15 1:12-14
ረቡዕ፣ ሐምሌ 26
ጥልቅ ማስተዋል እሰጥሃለሁ፤ ልትሄድበት የሚገባውንም መንገድ አስተምርሃለሁ።—መዝ. 32:8
በአሁኑ ጊዜ በአውቶቡስ ማቆሚያዎች፣ በባቡር ጣቢያዎች፣ በመኪና ማቆሚያዎች እንዲሁም ሕዝብ በሚበዛባቸውና በገበያ ቦታዎች ለሚከናወነው የአደባባይ ምሥክርነት ትልቅ ትኩረት እየተሰጠ ነው። ከእነዚህ የአገልግሎት መስኮች መካከል በአንዳንዶቹ መካፈል የሚያስፈራህ ከሆነ ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልይ፤ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ያገለገለው አንጄሎ መኔራ (ጁኒየር) የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ በቁም ነገር አስብበት፤ እንዲህ ብሏል፦ “አዳዲስ የአገልግሎት ዘርፎችን የምንመለከታቸው ይሖዋን ለማገልገልና ለእሱ ታማኝ መሆናችንን ለማሳየት እንደሚያስችል አዲስ አጋጣሚ አድርገን ነበር፤ በተጨማሪም ንጹሕ አቋማችን የሚፈተንበት ሌላ አጋጣሚ እንደሆነ እናስብ ነበር፤ ይሖዋ በጠየቀን በማንኛውም መንገድ እሱን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆናችንን ለማሳየት ጓጉተን ነበር።” በአዲስ ምናልባትም ከለመድነው በተለየ የአገልግሎት ዘርፍ መካፈል በይሖዋ ይበልጥ ለመተማመን ይረዳናል፤ ይህ ደግሞ መንፈሳዊነታችንን ያሳድጋል። (2 ቆሮ. 12:9, 10) በርካታ አስፋፊዎች፣ ሰዎች jw.org የተባለውን ድረ ገጻችንን እንዲቃኙ ይጋብዛሉ። ድረ ገጻችን ርቀው በሚገኙ ቦታዎች ለሚኖሩ ሰዎች ጭምር ምሥራቹ እንዲደርስ እያደረገ ነው። w15 11/15 5:12, 13, 15
ሐሙስ፣ ሐምሌ 27
ብረት ብረትን እንደሚስል ሁሉ ሰውም ጓደኛውን ይስለዋል።—ምሳሌ 27:17
አንዳንድ የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንደሚያደርጉት ሁሉ የእንግሊዝኛው አዲስ ዓለም ትርጉምም “ሲኦል” የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል እንደ መክብብ 9:10 ባሉ ጥቅሶች ላይ ይጠቀም ነበር። በመሆኑም ጥቅሱ “አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራም ሆነ ዕቅድ፣ እውቀትም ሆነ ጥበብ የለም” ይል ነበር። ይህም ወደ ሌሎች ቋንቋዎች የሚተረጉሙ ተርጓሚዎች እንዲቸገሩ ያደርጋል፤ ምክንያቱም “ሲኦል” የሚለውን ቃል አንባቢዎች ቢያውቁትም የሥቃይና የመከራ ቦታ እንደሆነ አድርገው ያስቡታል። ስለሆነም በ2013 ተሻሽሎ በወጣው አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ “ሲኦል” የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል እና “ሐዲስ” የሚለውን ተመሳሳይ ፍቺ ያለው የግሪክኛ ቃል “መቃብር” ብሎ በትክክል በመተርጎም መልእክቱን ግልጽ ለማድረግ ተወስኗል። ስለሆነም ጊዜ ያለፈባቸው የእንግሊዝኛ አባባሎች ተለውጠዋል፤ እንዲሁም ትክክለኛው መልእክት ሳይቀየር ጽሑፉን ግልጽና ለመረዳት ቀላል በሆነ መንገድ ለማስቀመጥ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ሌሎች ቋንቋዎች ሲተረጎሙ የተገኘውን ተሞክሮ በተግባር በማዋል የእንግሊዝኛውን ጽሑፍ ‘መሳል’ ወይም የተሻለ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል። w15 12/15 2:10, 12
ዓርብ፣ ሐምሌ 28
ለተቸገረ ሰው የሚያስብ ደስተኛ ነው፤በመከራ ቀን ይሖዋ ይታደገዋል። ይሖዋ ይጠብቀዋል፤ በሕይወትም ያኖረዋል።—መዝ. 41:1, 2
ጥንት የነበሩ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች እንዳደረጉት እኛም በምንታመምበት ጊዜ መጽናኛ፣ ጥበብና ድጋፍ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዞር ማለት እንችላለን። እርግጥ ነው፣ ዳዊት ይህን ሲል በዚያ ዘመን የኖረ ለተቸገረ የሚያስብ አንድ ሰው፣ ሞትን ፈጽሞ አያይም ማለቱ እንዳልነበረ እናውቃለን። በመሆኑም ዳዊት፣ በዕለቱ ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ሲጽፍ ለተቸገረ የሚያስብ ሰው በተአምራዊ ሁኔታ ሕይወቱ እንደሚቀጥልና ለዘላለም እንደሚኖር መናገሩ አይደለም። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ሐሳብ አምላክ፣ ታማኝና ለሌሎች አሳቢ የሆኑ ሰዎችን እንደሚረዳ የሚጠቁም ነው። የሚረዳቸው እንዴት ነው? ዳዊት ይህን ሲያብራራ “ታሞ በአልጋ ላይ ተኝቶ ሳለ ይሖዋ ይደግፈዋል፤ በታመመበት ወቅት መኝታውን ሙሉ በሙሉ ትቀይርለታለህ” ብሏል። (መዝ. 41:3) ለተቸገረ አሳቢነት ያሳየ ሰው፣ አምላክ እሱንም ሆነ የታማኝነት አካሄዱን እንደማይረሳ እርግጠኛ መሆን ይችላል። በተጨማሪም አምላክ፣ ሰውነታችን ራሱን በራሱ የመጠገን ችሎታ እንዲኖረው አድርጎ ስለፈጠረን ግለሰቡ ከበሽታው ሊያገግም ይችላል። w15 12/15 4:7
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 29
በእስር ላይ ያሉትን . . . ሁልጊዜ አስታውሷቸው።—ዕብ. 13:3
እዚህ ላይ ጳውሎስ በአጠቃላይ እስር ላይ ስላሉ ሰዎች መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በእምነታቸው ምክንያት እስር ቤት ስለገቡ ወንድሞች መናገሩ ነበር። ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ይህን ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት እሱ ራሱ ከታሰረ አራት ዓመት ያህል ሆኖታል። (ፊልጵ. 1:12-14) ሐዋርያው ‘በእስር ላይ ላሉት ስለራሩላቸው’ ዕብራውያን ክርስቲያኖችን አመስግኗቸዋል። (ዕብ. 10:34) እነዚህ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ከጳውሎስ በአካል ርቀው ነበር። ታዲያ እነዚህ ወንድሞች ሁልጊዜ ሊያስታውሱት የሚችሉት እንዴት ነው? ስለ እሱ ከልብ የመነጨ ጸሎት በማቅረብ ነው። (ዕብ. 13:18, 19) ዛሬም የምንኖረው እስር ቤት ካሉ ወንድሞቻችን ርቀን ይሆናል። በወኅኒ ቤቱ አቅራቢያ የሚኖሩ ወንድሞች እንደሚያደርጉት እስር ላይ ያሉት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማሟላት አንችል ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህን ታማኝ ወንድሞች ሁልጊዜ በማስታወስ፣ እነሱን በጸሎታችን ላይ በመጥቀስ እንዲሁም እነሱን አስመልክተን ይሖዋን በመማጸን ርኅራኄና የወንድማማች ፍቅር ልናሳይ እንችላለን። w16.01 1:13, 14
እሁድ፣ ሐምሌ 30
የአምላክ ልጆች መሆናችንን ይህ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሠክራል።—ሮም 8:16
አምላክ መጀመሪያ ላይ ለሰው ዘሮች የነበረው ዓላማ በዚህ ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው። (ዘፍ. 1:28፤ መዝ. 37:29) አንዳንዶች ወደ ሰማይ ሄደው ነገሥታትና ካህናት እንዲሆኑ መመረጣቸው ከተለመደው ወጣ ያለ ነገር ነው። ይህ ለየት ያለ ዝግጅት ነው። አንድ ሰው እንዲህ ላለው ሕይወት መጠራቱ በአስተሳሰቡ፣ በአመለካከቱና በተስፋው ላይ ትልቅ ለውጥ ያስከትላል። (ኤፌ. 1:18) ይሁንና አንድ ሰው ለሰማያዊ ሕይወት እንደተጠራ ይኸውም ይህን ልዩ ማረጋገጫ እንደተቀበለ እንዴት ያውቃል? ጳውሎስ ‘ቅዱሳን እንዲሆኑ ለተጠሩት’ በሮም ላሉት ቅቡዓን ወንድሞች የጻፈው ደብዳቤ ለዚህ ግልጽ መልስ ይሆናል። እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ዳግመኛ ለፍርሃት የሚዳርጋችሁን የባርነት መንፈስ አልተቀበላችሁም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ልጆቹ አድርጎ እንዲወስዳችሁ የሚያስችል መንፈስ አግኝታችኋል፤ ይህም መንፈስ ‘አባ፣ አባት!’ ብለን እንድንጣራ ይገፋፋናል።” (ሮም 1:7፤ 8:15) በአጭር አነጋገር፣ ግለሰቡ ወደፊት የአምላክ መንግሥት ወራሽ እንዲሆን መጠራቱን ይሖዋ በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ግልጽ ያደርግለታል።—1 ተሰ. 2:12፤ w16.01 3:8, 9
ሰኞ፣ ሐምሌ 31
በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ ላለመግባት . . . ተጣጣሩ።—1 ተሰ. 4:11
ይሖዋ በመንፈስ ለሚቀባቸው ሰዎች ተገቢውን አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ከመቀባታቸው ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ልንጠይቃቸው አይገባም። በዚህ መንገድ በማይመለከተን ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንቆጠባለን። (2 ተሰ. 3:11) በመንፈስ የተቀባው ግለሰብ ወላጆች፣ የትዳር ጓደኛ ወይም ሌሎች ዘመዶችም ቅቡዕ እንደሚሆኑ አድርገን ልናስብ አይገባም። በመንፈስ መቀባት በዝምድና ወይም በጋብቻ የሚገኝ ነገር አይደለም። (1 ተሰ. 2:12) ከዚህም ሌላ የቅቡዓን የትዳር ጓደኛ የሆኑ ክርስቲያኖች፣ ወደፊት ምድር ገነት ስትሆን ከትዳር ጓደኛቸው ጋር እንደማይኖሩ ሲያስቡ ምን እንደሚሰማቸው ልንጠይቃቸው አይገባም። ሌሎች እንዲያዝኑ ሊያደርጉ የሚችሉ ጥያቄዎች ከማንሳት ይልቅ ይሖዋ እጁን እንደሚዘረጋና “የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት” እንደሚያሟላ ሁላችንም ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን። (መዝ. 145:16) ለቅቡዓን ተገቢው አመለካከት ያላቸው ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከአደጋ ይጠብቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሐሰተኛ ወንድሞች” ወደ ጉባኤው ሾልከው ሊገቡ እንደሚችሉ ይናገራል።—ገላ. 2:4, 5፤ 1 ዮሐ. 2:19፤ w16.01 4:10, 11