የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es17 ገጽ 77-87
  • ነሐሴ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ነሐሴ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2017
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 1
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 2
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 3
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 4
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 5
  • እሁድ፣ ነሐሴ 6
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 7
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 8
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 9
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 10
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 11
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 12
  • እሁድ፣ ነሐሴ 13
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 14
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 15
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 16
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 17
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 18
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 19
  • እሁድ፣ ነሐሴ 20
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 21
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 22
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 23
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 24
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 25
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 26
  • እሁድ፣ ነሐሴ 27
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 28
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 29
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 30
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2017
es17 ገጽ 77-87

ነሐሴ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 1

የምድር ሁሉ ዳኛ ትክክል የሆነውን ነገር አያደርግም?​—⁠ዘፍ. 18:​25

አብርሃም፣ ትናንሽ በሚመስሉ ጉዳዮች እንኳ ይሖዋን የመታዘዝ ልማድ ስለነበረው ከአምላክ ጋር ያለው ወዳጅነት ይበልጥ እየጠነከረ እንዲሄድ ማድረግ ችሏል። የልቡን አውጥቶ ለይሖዋ ለመናገር ነፃነት ይሰማው ነበር፤ ከበድ ያሉ ጥያቄዎች ሲፈጠሩበትም ይሖዋን ከመጠየቅ ወደኋላ አላለም። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ሰዶምንና ገሞራን ሊያጠፋቸው እንደሆነ አብርሃም ሲያውቅ ‘ጻድቃን ከክፉዎች ጋር አብረው ይጠፉ ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ አሳስቦት ነበር። ምናልባትም አብርሃም በወቅቱ በሰዶም ይኖር የነበረው የወንድሙ ልጅ የሎጥና የቤተሰቡ ሁኔታ አስጨንቆት ይሆናል። አብርሃም “የምድር ሁሉ ዳኛ” ለሆነው አምላክ ጥያቄዎቹን ያቀረበው በታላቅ ትሕትና ሲሆን በእሱም ይተማመን ነበር። ይሖዋም ምን ያህል መሐሪ አምላክ እንደሆነ አብርሃም እንዲገነዘብ በትዕግሥት ረድቶታል፤ የፍርድ እርምጃ በሚወስድበት ጊዜም እንኳ ከጥፋቱ የሚተርፉ ጻድቃንን ለማግኘት የእያንዳንዱን ሰው ልብ እንደሚመረምር ለአብርሃም አስገንዝቦታል። (ዘፍ. 18:​22-33) አብርሃም ያካበተው እውቀትና ተሞክሮ በሙሉ ከይሖዋ ጋር ያለውን የጠበቀ ወዳጅነት ለማጠናከር እንደረዳው ምንም ጥርጥር የለውም። w16.02 1:11, 12

ረቡዕ፣ ነሐሴ 2

ይሖዋ በእኔና በአንተ፣ በዘሮቼና በዘሮችህ መካከል ለዘላለም ይሁን።​—⁠1 ሳሙ. 20:​42

ታማኝነት ሁሉም ሰው የሚያደንቀው ባሕርይ ነው ማለት ይቻላል። ይሁንና ዮናታን ለአምላክ ያለውን ታማኝነት ከግምት ሳናስገባ ለዳዊት ያሳየውን ታማኝነት ብቻ አድንቀን ብናልፍ አንድ ጠቃሚ ትምህርት ያመልጠናል። ዮናታን ዳዊትን እንደ ተቀናቃኙ ሳይሆን እንደ ወዳጁ የተመለከተው ለምንድን ነው? ዮናታን ቅድሚያ የሰጠው ለአምላክ ያለውን ታማኝነት ነው። በእርግጥም ዮናታን ለዳዊት ታማኝ እንዲሆን ያነሳሳው ዋናው ነገር ለይሖዋ ታማኝ መሆኑ ነው። ሁለቱም ሰዎች በመሐላ የገቡትን ቃል ጠብቀው ኖረዋል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን፣ የሌሎችን ታማኝነት ከማድነቅ ባለፈ እኛ ራሳችን ለቤተሰባችን አባላት፣ ለወዳጆቻችን እንዲሁም ለእምነት አጋሮቻችን ታማኝነት እናሳያለን። (1 ተሰ. 2:​10, 11) ይሁንና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ለማን ያለን ታማኝነት ነው? ከማንም በላይ ታማኝ ልንሆን የሚገባው ሕይወት ለሰጠን አምላክ እንደሆነ ጥርጥር የለውም! (ራእይ 4:​11) ምንጊዜም እንዲህ ያለውን ታማኝነት ማሳየታችን እውነተኛ ደስታና እርካታ ያመጣልናል። ሆኖም ለአምላክ ታማኝ ለመሆን ከፈለግን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንኳ ከእሱ ጋር መጣበቅ አለብን። w16.02 3:3, 4

ሐሙስ፣ ነሐሴ 3

ዳንኤል . . . ላለመርከስ በልቡ ቁርጥ ውሳኔ አደረገ።​—⁠ዳን. 1:8

አንድ የጎለመሰ ወጣት ያመነበትን ነገር አጥብቆ ይይዛል። በመንግሥት አዳራሽ የአምላክ ወዳጅ፣ በትምህርት ቤት ደግሞ የዓለም ወዳጅ መስሎ ለመታየት አይሞክርም። የእምነት ፈተና በሚያጋጥመው ጊዜ እንኳ ከአቋሙ ፍንክች አይልም። (ኤፌ. 4:​14, 15) እርግጥ ነው፣ ፍጹም የሆነ ሰው የለም፤ ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች አልፎ አልፎ ስህተት ይሠራሉ። (መክ. 7:​20) ሆኖም ለመጠመቅ እያሰብክ እንደመሆኑ መጠን የይሖዋን መሥፈርቶች ለመጠበቅ ምን ያህል ቁርጥ አቋም እንዳለህ መገምገምህ ጥበብ ነው። ‘አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች በጥብቅ በመከተል ረገድ ምን ዓይነት አቋም አለኝ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። በቅርቡ ላጋጠሙህ የእምነት ፈተናዎች ምን ምላሽ እንደሰጠህ ቆም ብለህ አስብ። ክፉን ከደጉ ለመለየት የሚያስችል ማስተዋል እንዳለህ አሳይተሃል? አንተስ ዳንኤል እንዳጋጠመው ሁሉ በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያለ ሰው ልዩ ቦታ ቢሰጥህ ምን ይሰማሃል? የአምላክ ፈቃድ፣ ለአንተ ፈተና ከሆነብህ ነገር ጋር በሚጋጭበት ጊዜም “የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ [ማስተዋል]” ትችላለህ?​—⁠ኤፌ. 5:​17፤ w16.03 1:7-9

ዓርብ፣ ነሐሴ 4

በእነዚያ ቀናት ከአምላክ የፍጥረት ሥራ መጀመሪያ አንስቶ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሆኖ የማያውቅ . . . መከራ ይከሰታል።​—⁠ማር. 13:​19

የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ብሎ በሚጠራው ዘመን ውስጥ ነው፤ በቅርቡ ደግሞ ፈጽሞ ተከስቶ የማያውቅ መከራ ይጀምራል። (2 ጢሞ. 3:⁠1) በተጨማሪም ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ ተባረው በምድር አካባቢ እንዲወሰኑ ተደርገዋል፤ ይህም በምድር ነዋሪዎች ላይ ከባድ ወዮታ አስከትሏል። (ራእይ 12:9, 12) እኛ ደግሞ ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ ስፋት ለብሔራትና የተለያየ ቋንቋ ለሚናገሩ ሕዝቦች ምሥራቹን የማዳረስ ታሪካዊና ተወዳዳሪ የሌለው ተልእኮ ተሰጥቶናል! የአምላክ በረከት እንዳይቋረጥብን ከፈለግን በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ለሚሰጡን መመሪያዎች ትኩረት መስጠት አለብን። በአሁኑ ጊዜ የታዛዥነት መንፈስ ካለን የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት የሚያስወግደው ‘ታላቁ መከራ’ በሚጀምርበት ወቅት መመሪያዎችን መከተል ቀላል ይሆንልናል። (ማቴ. 24:​21) ከዚያ በኋላ በአዲሱ ምድር ውስጥ አዳዲስ መመሪያዎች ያስፈልጉናል። w16.03 4:16, 18

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 5

ከጭሱም አንበጦች [ወጡ]።​—⁠ራእይ 9:3

በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. መደምደሚያ አካባቢ ሐዋርያው ዮሐንስ ሰባት መላእክትን በራእይ የተመለከተ ሲሆን እያንዳንዳቸው መለከት ይነፉ ነበር። አምስተኛው መልአክ መለከቱን ሲነፋ ዮሐንስ ከሰማይ ወደ ምድር የወደቀ አንድ “ኮከብ” አየ። “ኮከቡ” በእጁ ቁልፍ ይዞ ነበር፤ በዚያም የጥልቁን መግቢያ ከፈተው። በዚህ ጊዜ ጥቁር ጭስ ተትጎለጎለ፤ ከጭሱም የአንበጣ መንጋ ወጣ። እነዚህ ምሳሌያዊ አንበጦች ዕፀዋትን ከመጉዳት ይልቅ “የአምላክ ማኅተም በግንባራቸው ላይ የሌላቸውን ሰዎች” አጠቁ። (ራእይ 9:1-4) ዮሐንስ የአንበጣ መንጋ ምን ያህል አውዳሚ እንደሆነ እንደሚያውቅ ጥርጥር የለውም። በሙሴ ዘመን አንበጦች በጥንቷ ግብፅ ላይ ውድመት አስከትለው አልነበረም? (ዘፀ. 10:​12-15) ዮሐንስ የተመለከተው ምሳሌያዊ የአንበጣ መንጋ የይሖዋን ኃይለኛ የፍርድ መልእክት የሚያውጁትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። ምድራዊ ተስፋ ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ከቅቡዓኑ ጋር አብረው እየሠሩ ነው። በእርግጥም በኅብረት የምናከናውነው የስብከት ሥራ ሰይጣን በዓለም አቀፉ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ላይ ያለውን ሥልጣን የሚያዳክም መሆኑ ምንም አያስገርምም! w16.03 3:3

እሁድ፣ ነሐሴ 6

በሕግህ ውስጥ ያሉትን አስደናቂ ነገሮች አጥርቼ እንዳይ ዓይኖቼን ክፈት።​—⁠መዝ. 119:​18

አንድ ሽማግሌ፣ ብዙ ተሞክሮ በሌለው ወንድም አስተሳሰብና ድርጊት ላይ የመንግሥቱ እውነት ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳሳደረ ለማወቅ እንዲህ ብሎ ሊጠይቀው ይችላል፦ ‘ራስህን ለይሖዋ መወሰንህ ሕይወትህን በምትመራበት መንገድ ላይ ምን ለውጥ አስከትሏል?’ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማንሳት ቅዱስ አገልግሎታችንን በሙሉ ነፍስ ማቅረብ ስለሚቻልበት መንገድ ትርጉም ያለው ውይይት ለመጀመር በር ይከፍታል። (ማር. 12:​29, 30) ከውይይቱ በኋላ ይሖዋ ለወንድም መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠው ሽማግሌው ሊጸልይ ይችላል፤ ይህም ሥልጠናው ግቡን እንዲመታ ይረዳል። ወንድም ስለ እሱ ከልብ የመነጨ ጸሎት ሽማግሌው ሲያቀርብ መስማቱ እንደሚያበረታታው ጥርጥር የለውም! አንድ ሽማግሌ ተማሪው ለማገልገል ፈቃደኛ፣ እምነት የሚጣልበትና ትሑት መሆኑ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያስገነዝቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን በሥልጠናው የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ መጥቀስ ይችላል። (1 ነገ. 19:​19-21፤ ነህ. 7:2፤ 13:​13፤ ሥራ 18:​24-26) አልሚ ንጥረ ነገሮች ለአፈር ወሳኝ እንደሆኑ ሁሉ እንዲህ ያሉ ባሕርያትም ተማሪውን ይጠቅሙታል። መንፈሳዊ እድገቱን ያፋጥኑታል፤ እንዲሁም ‘ዓይኖቹ’ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን “አስደናቂ ነገሮች” ማየት እንዲችል ይረዱታል። w15 4/15 2:3, 4

ሰኞ፣ ነሐሴ 7

ወደ አምላክ ቅረቡ።​—⁠ያዕ. 4:8

ወደ ይሖዋ ለመቅረብ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ከእሱ ጋር አዘውትረን የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ነው። ለመሆኑ ከአምላክ ጋር መነጋገር የምትችለው እንዴት ነው? ይሖዋን የምታነጋግረው ወደ እሱ አዘውትረህ በመጸለይ ነው። (መዝ. 142:⁠2) በተጨማሪም በጽሑፍ የሰፈረውን የአምላክ ቃል ዘወትር በማንበብና ባነበብከው ላይ በማሰላሰል ይሖዋ ሲያነጋግርህ ማዳመጥ ትችላለህ። (ኢሳ. 30:​20, 21) ስትጸልይ የምትፈልገውን ነገር ለይተህ የምትጠቅስ ከሆነ ይሖዋ የሚሰጥህ ምላሽ በግልጽ የሚታይ ባይሆንም እንኳ አንተ ለጸሎትህ መልስ እንዳገኘህ በቀላሉ ታስተውላለህ። ጸሎትህ ምላሽ ማግኘቱ ደግሞ ይሖዋ ይበልጥ እውን እንዲሆንልህ ያደርጋል። በተጨማሪም የሚያሳስቡህን ነገሮች ለይሖዋ ግልጥልጥ አድርገህ በነገርከው መጠን እሱ ወደ አንተ ይበልጥ እየቀረበ ይሄዳል። ከይሖዋ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲኖረን የምናደርገው ጥረት በሕይወታችን ሙሉ የሚቀጥል ነው። ይሖዋ ወደ እኛ እንዲቀርብ የምንፈልግ ከሆነ እኛም ወደ እሱ ለመቅረብ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። እንግዲያው በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና በጸሎት አማካኝነት ከአምላካችን ጋር አዘውትረን የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋችንን እንቀጥል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ከይሖዋ ጋር ያለን ግንኙነት እየተጠናከረ ስለሚሄድ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ለመወጣት ያስችለናል። w15 4/15 3:3, 14, 16

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 8

ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል።​—⁠1 ጴጥ. 5:8

የዕለት ጥቅሱ የሰይጣንን አረመኔያዊ መንፈስ ጥሩ አድርጎ ይገልጻል! መላው ዓለም በቁጥጥሩ ሥር ቢሆንም ሰይጣን ተጨማሪ ሰለ​ባዎች ይፈልጋል። የሰይጣን ዓላማ የይሖዋን ሕዝቦች መዋጥ ነው። ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አንስቶ እስከ አሁን ድረስ በኢየሱስ ተከታዮች ላይ ያመጣው የስደት ማዕበል አረመኔ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። የተራበ አንበሳ ለሚያድነው እንስሳ ምንም ዓይነት አዘኔታ የለውም። እንስሳውን ከመግደሉ በፊት ርኅራኄ አይሰማውም፤ ከበላው በኋላም ቢሆን በድርጊቱ አይጸጸትም። በተመሳሳይም ዲያብሎስ ሊውጣቸው ለሚሞክር ሰዎች ፈጽም አዘኔታ አያሳይም። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን እንደ ፆታ ብልግና እና ስግብግብነት ባሉት ኃጢአቶች እንዲወድቁ ለማድረግ ሰይጣን ዲያብሎስ ምን ያህል አድፍጦ ሲጠባበቅ እንደነበር አስብ። ዚምሪ በፆታ ብልግና፣ ግያዝ ደግሞ በስግብግብነት መሸነፋቸው ያስከተለባቸውን አሳዛኝ መዘዝ በምታነብበት ጊዜ፣ የሚያገሳው አንበሳ ባገኘው ድል ሲፈነጥዝ ይታይሃል?​—⁠ዘኁ. 25:6-8, 14, 15፤ 2 ነገ. 5:​20-27፤ w15 5/15 1:8, 9

ረቡዕ፣ ነሐሴ 9

ዲያብሎስን . . . ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል።​—⁠ያዕ. 4:7

ከሰይጣን ጋር ተዋግተን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ከጸናችሁ ሕይወታችሁን ታተርፋላችሁ” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 21:​19) ሰዎች የሚያደርጉት ማንኛውም ነገር ዘላቂ ጉዳት አያስከትልብንም። እኛ ራሳችን ካልሆንን በቀር ማንም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሽብን አይችልም። (ሮም 8:​38, 39) የይሖዋ አገልጋዮች ቢሞቱ እንኳ ሰይጣን አሸነፈ ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ከሞት እንደሚያስነሳቸው ጥርጥር የለውም! (ዮሐ. 5:​28, 29) በሌላ በኩል ግን የሰይጣን የወደፊት ተስፋ የጨለመ ነው። ፈሪሃ አምላክ የሌለው የሰይጣን ሥርዓት ከጠፋ በኋላ ሰይጣን ለ1,000 ዓመት ወደ ጥልቁ ይወረወራል። (ራእይ 20:1-3) የኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ሲጠናቀቅ ሰይጣን ለአጭር ጊዜ “ከእስራቱ ይፈታል”፤ በዚህ ጊዜ ፍጹም የሆኑ የሰው ልጆችን ለማሳት የመጨረሻ ሙከራ ያደርጋል። ከዚያ በኋላ ዲያብሎስ ይጠፋል። (ራእይ 20:7-10) ሰይጣን ወደፊት የመኖር ተስፋ የለውም፤ አንተ ግን ተስፋ አለህ! በእምነት ጸንተህ በመቆም ሰይጣንን ተቃወመው። (1 ጴጥ. 5:⁠9) ተዋግተህ ልታሸንፈው ትችላለህ! w15 5/15 2:1, 18

ሐሙስ፣ ነሐሴ 10

ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል፤ ተሞክሮ የሌለው ግን ዝም ብሎ ይሄዳል፤ መዘዙንም ይቀበላል።​—⁠ምሳሌ 22:3

ብልህ ሰው፣ ማሰላሰል እንደ እሳት እንደሆነ ይገነዘባል። እሳት በተገቢው መንገድ ከተሠራበት ጠቃሚ ነው፤ ለምሳሌ ምግባችንን ለማብሰል ይረዳናል። እሳት ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ ግን ቤት ሊያቃጥልና የነዋሪዎቹን ሕይወት ሊያጠፋ ስለሚችል አደገኛ ነው። በተመሳሳይም ማሰላሰል ይሖዋን እንድንመስል የሚረዳን ከሆነ ጠቃሚ ነው። የብልግና ምኞቶች እንዲፈጠሩብን የሚያደርግ ከሆነ ግን አደገኛ ነው። ለምሳሌ፣ በኃጢአት ድርጊቶች ላይ የማውጠንጠን ልማድ ካለን ይህ፣ የተመኘነውን ነገር ወደመፈጸም ሊመራን ይችላል። በእርግጥም በብልግና ድርጊቶች ላይ ማሰላሰል በመንፈሳዊ ሁኔታ ሞት ሊያስከትልብን ይችላል። (ያዕ. 1:​14, 15) ኢየሱስ ስለ ሥነ ምግባር ብልግና ማውጠንጠን ተገቢ እንዳልሆነ አስጠንቅቋል። “አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል” በማለት ተናግሯል።​—⁠ማቴ. 5:​28፤ w15 5/15 4:11, 12, 14

ዓርብ፣ ነሐሴ 11

በተለይ . . . በሰው ልጆች እጅግ እደሰት ነበር።​—⁠ምሳሌ 8:​31

ኢየሱስ ከቦታ ቦታ እየተጓዘ መስበኩን የሚገልጹትን ዘገባዎች ስንመረምር ለሰው ዘር ቤተሰብ ከልብ እንደሚያስብ የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች እናገኛለን። በአንድ ወቅት ኢየሱስ አንድ የሚያሳዝን ነገር ተመለከተ። (ማር. 1:​39, 40) በሥጋ ደዌ በሽታ የተያዘ አንድ ሰው አየ፤ ይህ የሚያስፈራ በሽታ ነው። ሐኪሙ ሉቃስ ስለ ሰውየው ሲናገር “መላ ሰውነቱን የሥጋ ደዌ የወረሰው ሰው” ማለቱ ሕመሙ የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን ይጠቁማል። (ሉቃስ 5:​12) በሥጋ ደዌ የተያዘው ሰው “ኢየሱስን ባየው ጊዜ በግንባሩ ተደፍቶ ‘ጌታ ሆይ፣ ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ’ ሲል ለመነው።” ሰውየው፣ ኢየሱስ እሱን የመፈወስ ኃይል እንዳለው አልተጠራጠረም፤ ሆኖም እሱን ለመፈወስ ፍላጎት ያለው መሆኑን ማወቅ ፈልጓል። ታዲያ ኢየሱስ ለዚህ አሳዛኝ ልመና ምን ምላሽ ሰጠ? ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ሕመምተኛውን ሰው ከዳሰሰው በኋላ “እፈልጋለሁ! ንጻ” አለው፤ የድምፁ ቃና እርግጠኝነትና አሳቢነት የሚንጸባረቅበት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ሰውየው “ወዲያውኑ የሥጋ ደዌው ለቀቀው።” (ሉቃስ 5:​13) በእርግጥም ኢየሱስ ሰዎችን ምን ያህል እንደሚወድ አሳይቷል።​—⁠ሉቃስ 5:​17፤ w15 6/15 2:3-5

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 12

ራሱን የሚያገል ሰው ሁሉ . . . ጥበብንም ሁሉ ይቃወማል።​—⁠ምሳሌ 18:1

ድክመቶቻችንን ለአንድ የጎለመሰ ክርስቲያን በድፍረት መናገራችን በደግነት ከሚሰጠን ምክር ለመጠቀም ስለሚያስችለን መጥፎ ምኞቶችን ከማስተናገድ እንድንርቅ ይረዳናል። (ዕብ. 3:​12, 13) ጎልማሳ ከሆነና መንፈሳዊ ብቃት ካለው ክርስቲያን ጋር ስለ ድክመቶቻችን ማውራታችን ያላስተዋልናቸውን ክፍተቶች ለመመልከት ያስችለናል። ይህም ከይሖዋ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር የሚያስፈልጉንን ማስተካከያዎች ለማድረግ ይረዳናል። ክርስቲያን ሽማግሌዎች እኛን ለመርዳት ብቃት አላቸው። (ያዕ. 5:​13-15) የብልግና ምኞቶች በውስጣችን የተፈጠሩት ፖርኖግራፊ የመመልከት ርኩስ ልማድ ስለተጠናወተን ከሆነ እርዳታ መጠየቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። እርዳታ ሳንጠይቅ በቆየን መጠን ርኩስ ምኞቶች በውስጣችን ‘ፀንሰው ኃጢአትን የመውለዳቸው’ አጋጣሚ ይበልጥ ሰፊ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ሌሎችን የሚጎዳ ከመሆኑም ሌላ በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ ያመጣል። ብዙ የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋን ለማስደሰትና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለመኖር ያላቸው ፍላጎት የሽማግሌዎችን እርዳታ እንዲጠይቁ ብሎም የሚሰጣቸውን ፍቅራዊ እርዳታ ለመቀበል ፈቃደኞች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።​—⁠ያዕ. 1:​15፤ መዝ. 141:5፤ ዕብ. 12:5, 6፤ w15 6/15 3:15-17

እሁድ፣ ነሐሴ 13

በዚያ ቀን እያንዳንዱ ነቢይ ትንቢት በሚናገርበት ጊዜ ሁሉ በገዛ ራእዩ ያፍራል፤ ሰዎችንም ለማታለል የነቢያት ዓይነት ፀጉራም ልብስ አይለብስም።​—⁠ዘካ. 13:4

በታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ የተካተቱት ሃይማኖቶች ይጠፋሉ ሲባል የእነዚህ ሃይማኖቶች አባላት የነበሩ ሁሉ አብረው ይጠፋሉ ማለት ነው? ላይሆን ይችላል። አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ሃይማኖታቸውን የሚተዉ ከመሆኑም ሌላ የሐሰት ሃይማኖት አባል የነበሩ መሆናቸውን ይክዳሉ። (ዘካ. 13:5, 6) ታዲያ የአምላክ ሕዝቦች በዚህ ጊዜ ምን ይሆናሉ? ኢየሱስ “ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ባልዳነ ነበር፤ ሆኖም ለተመረጡት ሲባል ቀኖቹ ያጥራሉ” ብሏል። (ማቴ. 24:​22) በ66 ዓ.ም. መከራው ‘አጥሮ’ ነበር። ይህም ‘የተመረጡት’ ማለትም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ኢየሩሳሌምንና አካባቢዋን ለቀው ለመሸሽ አጋጣሚ እንዲያገኙ አድርጓል። በተመሳሳይም ወደፊት የሚመጣው ታላቅ መከራ የመጀመሪያ ምዕራፍ “ለተመረጡት” ሲባል ‘ያጥራል።’ ፖለቲካዊ ኃይሎችን የሚያመለክቱት “አሥር ቀንዶች” የአምላክን ሕዝቦች እንዲያጠፉ አይፈቀድላቸውም። (ራእይ 17:​16) ከዚህ ይልቅ መከራው ለአጭር ጊዜ ጋብ ይላል። w15 7/15 2:5, 6

ሰኞ፣ ነሐሴ 14

ፈታኙም [ቀረበ]።​—⁠ማቴ. 4:3

እያንዳንዱ ግለሰብ ፈተና ውስጥ መግባት አለመግባቱ በራሱ ላይ የተመካ ነው። (ማቴ. 6:​13፤ ያዕ. 1:​13-15) ኢየሱስ፣ ሰይጣን ያቀረበለትን እያንዳንዱን ፈተና ከአምላክ ቃል ውስጥ ተስማሚ ጥቅስ በመጥቀስ ወዲያውኑ ተቃውሟል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ የአምላክን ሉዓላዊነት ደግፏል። ሰይጣን ግን ተስፋ አልቆረጠም። “ሌላ አመቺ ጊዜ እስኪያገኝ ድረስ” ጠበቀ። (ሉቃስ 4:​13) ኢየሱስም ቢሆን ንጹሕ አቋሙን እንዲያጎድፍ ሰይጣን ባደረገበት ተጽዕኖ አልተሸነፈም። ያም ቢሆን ሰይጣን አንተን ጨምሮ የኢየሱስን ተከታዮች ለማጥመድ ጥረት ያደርጋል። ከአምላክ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄ መልስ ስላላገኘ ፈታኙ በዚህ ዓለም ተጠቅሞ እንዲፈትነን ይሖዋ ፈቅዶለታል። ወደ ፈተና የሚያስገባን አምላክ አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ በእኛ የሚተማመን ከመሆኑም ሌላ ሊረዳን ይፈልጋል። ይሁንና ይሖዋ የመምረጥ ነፃነታችንን ሊጋፋ ስለማይፈልግ ወደ ፈተና እንዳንገባ አይከለክለንም። እኛ ሁለት ነገሮችን ማድረግ ይኸውም በመንፈሳዊ ንቁ መሆንና በጸሎት መጽናት አለብን። w15 6/15 5:13, 14

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 15

አገልግሎታችን እንከን እንዳይገኝበት በምንም መንገድ ማሰናከያ እንዲኖር አናደርግም።​—⁠2 ቆሮ. 6:3

ክርስቲያኖች ከገለልተኝነት ጋር የተያያዘ ጉዳይ ሲነሳ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት አእምሯቸውንና ሕሊናቸውን ማሠልጠን ይኖርባቸዋል። (ሮም 14:​19) በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ክልል ውስጥ የምትኖረውን ሚሪዬታን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ያደገችው ሰርቦችን በሚጠላ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው። ይሖዋ የማያዳላ አምላክ እንደሆነና በዘር ልዩነት ምክንያት ለሚፈጠሩ ችግሮች ተጠያቂው ሰይጣን መሆኑን ስታውቅ ብሔራዊ ስሜትን ከውስጧ ለማጥፋት ትግል ማድረግ ጀመረች። በአካባቢዋ ከዘር ጋር የተያያዘ ግጭት ሲቀሰቀስ ግን ቀደም ሲል ለሰርቦች የነበራት ጥላቻ ማገርሸት ጀመረ፤ በመሆኑም ለሰርቦች መስበክ ከበዳት። ይሁንና እንዲህ ያለው ተገቢ ያልሆነ ስሜት በራሱ እንደሚጠፋ በማሰብ እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም። ይሖዋ ይህንን ችግሯን ለመወጣት እንዲረዳት በጸሎት ለመነችው። ሚሪዬታ እንዲህ ብላለች፦ “ከሁሉ በላይ የረዳኝ በአገልግሎቱ ላይ ትኩረት ማድረጌ ነው። በአገልግሎት ላይ የይሖዋን ፍቅር ለማንጸባረቅ እጥራለሁ፤ ይህም አሉታዊ ስሜትን ለማስወገድ ረድቶኛል።” w15 7/15 3:11-13

ረቡዕ፣ ነሐሴ 16

በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን ያሳይ ዘንድ የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመላለሳሉ።​—⁠2 ዜና 16:9

የይሁዳ ንጉሥ የነበረውን የኢዮሳፍጥን ሁኔታ ተመልከት። በአንድ ወቅት የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ፣ አብሮት እንዲሄድ ለኢዮሳፍጥ ጥያቄ አቀረበለት፤ እሱም ተስማማ። ይህ ግን ጥበብ የጎደለው ውሳኔ ነበር። ምንም እንኳ 400 የሚያህሉ የሐሰት ነቢያት ክፉው አክዓብ ድል እንደሚያደርግ ቢናገሩም አክዓብ መሸነፉ እንደማይቀር እውነተኛው የይሖዋ ነቢይ ሚካያህ ተንብዮ ነበር። አክዓብ በጦርነቱ የሞተ ሲሆን ኢዮሳፍጥም ሕይወቱ የተረፈው ለጥቂት ነው። ኢዮሳፍጥ ከአክዓብ ጋር ጥምረት በመፍጠሩ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ ተግሣጽ ተሰጥቶታል። ያም ሆኖ ባለ ራእዩ የሃናኒ ልጅ ኢዩ፣ ኢዮሳፍጥን “መልካም ነገር ተገኝቶብሃል” ብሎታል። (2 ዜና 18:4, 5, 18-22, 33, 34፤ 19:1-3) በእርግጥ ኢዮሳፍጥ የሞኝነት ድርጊት ፈጽሟል፤ ሆኖም ቀደም ሲል ያከናወናቸውን መልካም ነገሮች ይሖዋ አልረሳም። (2 ዜና 17:3-10) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፣ ፍጹማን ባንሆንም እንኳ ይሖዋን ለማስደሰት በሙሉ ልባችን የምንጥር ከሆነ እሱም ለእኛ ጽኑ ፍቅር እንደሚኖረው ያስታውሰናል። w15 8/15 1:8, 9

ሐሙስ፣ ነሐሴ 17

መልካም ነገር እንዲያደርጉ . . . ምከራቸው፤ እውነተኛ የሆነውን ሕይወት አጥብቀው መያዝ ይችሉ ዘንድ . . . ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆን መልካም መሠረት መጣላቸውን ይቀጥሉ።​—⁠1 ጢሞ. 6:​18, 19

አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለሚኖረው ሕይወት አሁን መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ ያህል፣ ወደ ሌላ አገር ለመዛወር አስበናል እንበል። እዚያ ስንሄድ ለሚያጋጥመን ለውጥ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? መጀመሪያ፣ የዚያ አገር ሰዎች የሚናገሩትን ቋንቋ እንማር ይሆናል። ስለ ባሕላቸው ለማወቅ ጥረት ማድረጉ ጠቃሚ ነው። አንዳንድ ምግቦቻቸውንም እንሞክር ይሆናል። በተወሰነ መጠን፣ የዚያ አገር ነዋሪ ስንሆን በምንኖርበት መንገድ ሕይወታችንን መምራት እንጀምራለን። ደግሞም እዚያ ከደረስን በኋላ የምንኖረው በዚህ መንገድ ነው። በተመሳሳይም በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንደምንኖር በምናስበው መንገድ በአሁኑ ጊዜ ሕይወታችንን በመምራት በዚያ ወቅት ለሚኖረው ሕይወት መዘጋጀት እንችላለን። አንዳንዶች በራስ መንገድ መሄድና እንደምንም ብሎ የግል ምርጫ እንዲከበር ማድረግ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ይሰማቸዋል፤ ሆኖም ይህ ምን አስከትሏል? የአምላክን አመራር አለመቀበል መከራና ጉስቁልና አልፎ ተርፎም ከባድ ሥቃይ አምጥቷል። (ኤር. 10:​23) የሰው ዘር በሙሉ፣ ፍቅራዊ የሆነውን የይሖዋ ሉዓላዊ አገዛዝ የሚቀበልበትን ጊዜ ምንኛ በጉጉት እንጠባበቃለን! w15 8/15 3:4, 5

ዓርብ፣ ነሐሴ 18

ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ።​—⁠2 ቆሮ. 6:​14

ማግባት የሚፈልጉ ክርስቲያኖች ጓደኝነትን በተመለከተ ይበልጥ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የትዳር ጓደኛ የሚፈልጉ የአምላክ አገልጋዮች “በጌታ ብቻ” እንዲያገቡ ይኸውም ራሱን ወስኖ የተጠመቀና በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች የሚመራ የይሖዋ አገልጋይ ብቻ እንዲያገቡ ይመክራል። (1 ቆሮ. 7:​39) ክርስቲያኖች ከእምነት ባልንጀራቸው ጋር በትዳር ሲጣመሩ፣ ራሱን ለይሖዋ የወሰነና ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው እንዲመላለሱ የሚያግዛቸው አጋር ያገኛሉ። ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የተሻለው ነገር ምን እንደሆነ ያውቃል፤ በተጨማሪም ጋብቻን በተመለከተ ያለው አመለካከት ምንጊዜም አይለወጥም። በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን የሰጠውን የማያሻማ መመሪያ እንመልከት። እስራኤላውያን፣ በዙሪያቸው ያሉ ሕዝቦችን ይኸውም ይሖዋን የማያገለግሉ ሰዎችን በተመለከተ የሚከተለው መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር፦ “ከእነሱ ጋር በጋብቻ አትዛመድ። . . . ምክንያቱም ልጆችህ ሌሎች አማልክትን ያገለግሉ ዘንድ እኔን ከመከተል ዞር እንዲሉ ያደርጓቸዋል።”​—⁠ዘዳ. 7:3, 4፤ w15 8/15 4:12, 13

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 19

ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ በማወቅ . . . እንከን የማይገኝባችሁ [እንዲሁም ሌሎችን የማታሰናክሉ ሁኑ]።​—⁠ፊልጵ. 1:​10

ሕሊናችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው? ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰልና ያገኘነውን እውቀት በሥራ ላይ ማዋል ይህን ለማድረግ የሚያስችሉን ቁልፍ ነገሮች ናቸው። ይህ ሲባል ግን መረጃዎችን መሰብሰብና ደንቦችን ማጥናት ማለት ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን ስለ ይሖዋ፣ ስለ ማንነቱ፣ ስለ ባሕርያቱ እንዲሁም ስለሚወዳቸውና ስለሚጠላቸው ነገሮች ያለን ግንዛቤ ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ እንዲሄድ ሊረዳን ይገባል። እንዲህ ከሆነ ሕሊናችን ይሖዋ አምላክ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ ይሆናል። ይህ ደግሞ ይበልጥ እሱን እየመሰልን እንድንሄድ ያነሳሳናል። ይሁንና አንድ የእምነት ባልንጀራችን በሕሊናው ተመርቶ ያደረገው የግል ውሳኔ ባይገባን ቸኩለን በእሱ ላይ መፍረድም ሆነ አስተሳሰቡን እንዲለውጥ መጫን አይገባንም። ምናልባት ሕሊናው አሁንም “ደካማ” ሊሆንና ተጨማሪ ሥልጠና ሊያስፈልገው ይችላል፤ አሊያም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በጣም ጥብቅ ሊሆን ይችላል።​—⁠1 ቆሮ. 8:​11, 12፤ w15 9/15 2:4, 8, 10

እሁድ፣ ነሐሴ 20

ምድርን . . . ለሰው ልጆች ሰጣት።​—⁠መዝ. 115:​16

አምላክ ከፈጠራቸው ነገሮች ሁሉ ምድር በዓይነቷ ልዩ ነች። እስቲ አስበው፣ በፍኖተ ሐሊብና ከዚያ ውጭ ከሚገኙት ቁጥራቸው በውል ከማይታወቅ ፕላኔቶች መካከል ይሖዋ ምድርን መኖሪያ እንድትሆን ብቻ ሳይሆን ለፈጠራቸው ሰዎች ምቹ፣ ውብና ተስማሚ መኖሪያ አድርጎ አዘጋጅቷታል! (ኢሳ. 45:​18) ይህም ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደን ያሳያል። (ኢዮብ 38:4, 7፤ መዝ. 8:3-5) ይሖዋ ግሩም የሆነ መኖሪያ የፈጠረልን ቢሆንም እንኳ ደስታና እርካታ አግኝተን እንድንኖር ከቁሳዊ ነገር ይበልጥ የሚያስፈልገን ሌላ ነገር እንዳለ ያውቃል። አንድ ልጅ ወላጆቹ እንደሚወዱትና እንደሚንከባከቡት ሲያውቅ ይረጋጋል። ይሖዋ ሰዎችን በራሱ መልክ ሲፈጥር በውስጣቸው መንፈሳዊ ፍላጎት ቀርጾባቸዋል፤ ይህም የሚያሳያቸውን ፍቅርም ሆነ የሚያደርግላቸውን እንክብካቤ መገንዘብና ምላሽ መስጠት ያስችላቸዋል። (ዘፍ. 1:​27) ኢየሱስም “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴ. 5:⁠3) ይሖዋ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ “የሚያስደስቱንን ነገሮች ሁሉ አትረፍርፎ [ይሰጠናል]።”​—⁠1 ጢሞ. 6:​17፤ መዝ. 145:​16፤ w15 9/15 4:6, 7

ሰኞ፣ ነሐሴ 21

ለሰው ትክክለኛ መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ይመራል።​—⁠ምሳሌ 14:​12

መዝሙራዊው “አምላክን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤ እሱን እንደ ታላቅ አዳኜ አድርጌ ገና አወድሰዋለሁና። አምላኬ ሆይ፣ ተስፋ ቆርጫለሁ። . . . የማስብህ ለዚህ ነው” ብሎ በጻፈ ጊዜ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ እንዳለው አሳይቷል። (መዝ. 42:5, 6) ለይሖዋ ያለውን ልዩ ስሜትና ፍቅር የሚገልጽ እንዴት ያለ ግሩም ሐሳብ ነው! በሰማይ ለሚኖረው አባታችን እንዲህ ዓይነት ፍቅር አለህ? በእሱስ ትታመናለህ? አዎ የሚል መልስ ብትሰጥም እንኳ ከሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ አንጻር በእሱ ላይ ያለህ እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄድ እንዳለበት ማስተዋል ይኖርብሃል፦ “በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ። በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፤ እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።” (ምሳሌ 3:5, 6) ይሖዋ እኛን አስቀድሞ በመውደድ እሱን መውደድ የምንችልበትን መንገድ አሳይቶናል። (1 ዮሐ. 4:​19) እሱ የተወልንን የላቀ ምሳሌ ምንጊዜም እናስታውስ። እንዲሁም እሱን ‘በሙሉ ልባችን፣ በሙሉ ነፍሳችን፣ በሙሉ አእምሯችንና በሙሉ ኃይላችን’ በመውደድ ለእሱ ያለን ፍቅር ምንጊዜም እየጨመረ ይሂድ!​—⁠ማር. 12:​30፤ w15 9/15 5:17-19

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 22

እኔና ቤተሰቤ ግን ይሖዋን እናገለግላለን።​—⁠ኢያሱ 24:​15

በመስክ አገልግሎት ስንካፈል ሌሎች እምነት እንዲያዳብሩ ከመርዳታችን በተጨማሪ የራሳችንም እምነት እያደገ ይሄዳል። እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት እናዳብራለን፤ እንዲሁም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ በድፍረት መናገር እንችላለን። (ሥራ 4:​17-20፤ 13:​46) ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ እንዴት እንደሚረዳንና ለጸሎታችን እንዴት መልስ እንደሚሰጥ ስንመለከት እምነታችን ያድጋል። የካሌብና የኢያሱ ሁኔታ ይህን ያሳያል። ተስፋይቱን ምድር በሰለሉበት ወቅት በይሖዋ ላይ እምነት እንዳላቸው አሳይተዋል። ይሁንና ከዚያ በኋላ በእያንዳንዱ የሕይወታቸው ክፍል የይሖዋን አመራር ሲመለከቱ እምነታቸው ይበልጥ እያደገ ሄዷል። ኢያሱ “አምላካችሁ ይሖዋ ከገባላችሁ መልካም ቃል ሁሉ አንዲቷም እንኳ ሳትፈጸም [አልቀረችም]” በማለት ለእስራኤላውያን በእርግጠኝነት መናገሩ የሚያስገርም አይደለም። ከጊዜ በኋላም “ስለዚህ ይሖዋን ፍሩ፤ በንጹሕ አቋምና በታማኝነትም አገልግሉት” ብሏቸዋል። (ኢያሱ 23:​14፤ 24:​14) እኛም የይሖዋን ጥሩነት ስንቀምስ እንዲህ ዓይነት የጸና እምነት ማዳበር እንችላለን።​—⁠መዝ. 34:8፤ w15 10/15 2:10, 11

ረቡዕ፣ ነሐሴ 23

ዕዝራ . . . ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።​—⁠ዕዝራ 7:​10

በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ ንግግር ሲሰጥ ማስታወሻ ትይዛለህ? የያዝከውን ማስታወሻ መከለስህ ከአምላክ ቃልም ሆነ ከድርጅቱ በተማርካቸው ነገሮች ላይ ለማሰላሰል ግሩም አጋጣሚ ይከፍትልሃል። በተጨማሪም በየወሩ የሚወጡት የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት እትሞች እንዲሁም በክልል ስብሰባ ላይ የሚወጡ አዳዲስ ጽሑፎች የምናነባቸውና የምናሰላስልባቸው መረጃዎች ይዘዋል። የዓመት መጽሐፍ በምታነብበት ጊዜ ቆም ብለህ ማሰብህ እንዲሁም ባነበብካቸው ተሞክሮዎች ላይ ማሰላሰልህና ልብህ እንዲነካ ማድረግህ ጠቃሚ ነው። ተመላልሶ መጠየቅ ወይም የእረኝነት ጉብኝት ለማድረግ አሊያም ንግግር ለመስጠት በምትዘጋጅበት ጊዜ ቁልፍ በሆኑ ሐሳቦች ላይ ማስመርህ ወይም በኅዳጉ ላይ ማስታወሻ መያዝህ ይጠቅምሃል። ከሁሉ በላይ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ስታነብ አልፎ አልፎ ቆም እያልክ ማሰላሰልህ ትምህርቱ ወደ ልብህ ዘልቆ እንዲገባና ለተማርከው መልካም ነገር ይሖዋን በጸሎት እንድታመሰግን አጋጣሚ ይሰጥሃል። w15 10/15 4:9, 10

ሐሙስ፣ ነሐሴ 24

ኢየሱስም በአካልና በጥበብ እያደገ እንዲሁም በአምላክና በሰው ፊት ይበልጥ ሞገስ እያገኘ ሄደ።​—⁠ሉቃስ 2:​52

ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጆቻቸው ሲጠመቁ ማየት በጣም እንደሚያስደስታቸው የታወቀ ነው። አራቱም ልጆቿ 14 ዓመት ሳይሞላቸው የተጠመቁላት ቤረኒሲ እንዲህ ብላለች፦ “የተደበላለቀ ስሜት ተሰምቶን ነበር። ልጆቻችን ይሖዋን ለማገልገል መፈለጋቸው እንዳስደሰተን ጥያቄ የለውም። ይሁንና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በመሆናቸው ብዙ ተፈታታኝ ነገሮች እንደሚያጋጥሟቸው ተገንዝበን ነበር።” ስለ ልጆች ሥነ ልቦና የሚያጠኑ አንድ ባለሙያ፣ ወላጆች በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻቸው እንዳበዱ ወይም ብስለት እንደጎደላቸው አድርገው ሊያስቡ እንደማይገባ ተናግረዋል። ከዚህ ይልቅ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻቸው፣ በዚህ ጊዜ የፈጠራ ችሎታቸው እንደሚዳብር፣ ከጓደኞቻቸው ጋር ጊዜ ለማሳለፍ እንደሚፈልጉ እንዲሁም ለነገሮች ጠንካራ ስሜት እንደሚኖራቸውና ስሜታቸውን መግለጽ እንደሚፈልጉ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ልጆቻችሁ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያሉ ከይሖዋ ጋር ይበልጥ ትርጉም ያለው ወዳጅነት መመሥረት፣ ለአገልግሎታቸው ግብ ማውጣትና እዚያ ላይ ለመድረስ መሥራት እንዲሁም ራሳቸውን መወሰን ብሎም ከውሳኔያቸው ጋር ተስማምተው ለመኖር ጥረት ማድረግ ይችላሉ። ልክ እንደ ኢየሱስ ሁሉ ለእነሱም ይህ ዕድሜ በመንፈሳዊ እድገት የሚያደርጉበት አስደሳች ጊዜ ሊሆንላቸው ይችላል። w15 11/15 2:1, 2

ዓርብ፣ ነሐሴ 25

መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም።​—⁠ማቴ. 6:​10

አምላክ መሲሐዊውን መንግሥት ማቋቋሙ የሰው ልጆችን እንደሚወድ ያረጋግጣል። ይሖዋ ይህን መንግሥት ለልጁ ሰጥቶታል፤ ኢየሱስ የሰው ልጆችን የሚወድ ከመሆኑም ሌላ እነሱን ለመግዛት የላቀ ብቃት አለው። (ምሳሌ 8:​31) ከኢየሱስ ጋር ሰማያዊ ውርሻ የሚያገኙት 144,000ዎች ከሞት ከተነሱ በኋላ፣ ሰው ሆነው ሲኖሩ ያካበቱትን ልምድ ይጠቀሙበታል። (ራእይ 14:⁠1) የኢየሱስ ስብከት ዋና ጭብጥ የአምላክ መንግሥት ሲሆን ደቀ መዛሙርቱንም ስለ መንግሥቱም ሆነ ስለሚያመጣቸው በረከቶች እን​ዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚያሳየው በ1914 ክርስቶስ በሥልጣኑ ሲገኝ የአምላክ መንግሥት በሰማይ መግዛት ጀምሯል። ከዚያ ጊዜ ወዲህ፣ ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የሚገዙት ቅቡዓን ቀሪዎችና ከዚህ ሥርዓት ጥፋት ተርፈው ወደ አዲሱ ዓለም የሚገቡት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” እየተሰበሰቡ ነው።​—⁠ራእይ 7:9, 13, 14፤ w15 11/15 3:16, 18

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 26

እባክህ ስማኝ፤ እኔም እናገራለሁ።​—⁠ኢዮብ 42:4

ሐዋርያው ዮሐንስ፣ መጀመሪያ ከአምላክ ጋር የነበረውን አካል “ቃል” እንዲሁም ‘የአምላክ ፍጥረት መጀመሪያ’ ሲል ጠርቶታል። (ዮሐ. 1:1፤ ራእይ 3:​14) ይሖዋ አምላክ ሐሳቡንና ስሜቱን ለዚህ የበኩር ልጁ አካፍሎታል። (ዮሐ. 1:​14, 17፤ ቆላ. 1:​15) ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ስለ “መላእክት ልሳን” ተናግሯል፤ ይህም ከሰው ልጆች ቋንቋ እጅግ የሚልቅና በሰማይ ያሉ አካላት የሚግባቡበት ልሳን ነው። (1 ቆሮ. 13:⁠1) ይሖዋ በምድርም ሆነ በሰማይ ስላሉት በቢሊዮን የሚቆጠሩ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት በሚገባ ያውቃል። ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች በተመሳሳይ ጊዜ ላይ በበርካታ ቋንቋዎች ወደ እሱ ይጸልዩ ይሆናል። ይሖዋ እነዚህን ሁሉ ጸሎቶች የሚሰማ ከመሆኑም ሌላ በዚያው ቅጽበት ለመላእክት መመሪያ ይሰጣል እንዲሁም ከእነሱ ጋር ይነጋገራል። ይህን ሁሉ ለማከናወን እንዲችል ሐሳቡ፣ ቋንቋውና ከሌሎች ጋር የሚግባባበት መንገድ ከሰው ልጆች በእጅጉ የላቀ ሊሆን ይገባል። (ኢሳ. 55:8, 9) በግልጽ ማየት እንደምንችለው ይሖዋ ለሰው ልጆች ሐሳቡን የሚያስተላልፈው እነሱ ሊረዱት በሚችሉ ቀለል ያለ መንገድ ነው። w15 12/15 1:1, 2

እሁድ፣ ነሐሴ 27

ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን ምድርም በይሖዋ እውቀት ትሞላለች።​—⁠ኢሳ. 11:9

በብዙ አገሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ዋጋ ውድ ከመሆኑም በላይ በቀላሉ አይገኝም፤ ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት በራሱ በረከት ነው። ከሩዋንዳ የተላከ አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “ወንድሞች መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስጠኗቸው ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለሌላቸው ለረጅም ጊዜ እድገት ሳያደርጉ ቆይተዋል። በአካባቢያቸው የሚገኘው ቤተ ክርስቲያን የሚያዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ውድ ስለሆነ ለመግዛት አቅማቸው አይፈቅድላቸውም። በዚያ ላይ ደግሞ ብዙውን ጊዜ የአንዳንድ ጥቅሶችን ትርጉም መረዳት ይከብዳቸዋል፤ ይህም ለእድገታቸው እንቅፋት ሆኗል።” አዲስ ዓለም ትርጉም በአካባቢያቸው በሚነገረው ቋንቋ ሲዘጋጅ ግን ሁኔታዎች ይለወጣሉ። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ አራት ልጆች ያሏቸው በሩዋንዳ የሚኖሩ የአንድ ቤተሰብ አባላት እንዲህ ብለዋል፦ “ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ስለሰጡን ይሖዋን እንዲሁም ታማኝና ልባም ባሪያን በእጅጉ እናመሰግናቸዋለን። በጣም ድሆች ስለሆንን ለእያንዳንዱ የቤተሰባችን አባል መጽሐፍ ቅዱስ ለመግዛት ገንዘብ የለንም። አሁን ግን ሁላችንም የየራሳችን መጽሐፍ ቅዱስ አለን። አመስጋኝነታችንን ለይሖዋ ለመግለጽ መጽሐፍ ቅዱስን በቤተሰብ ሆነን በየዕለቱ እናነባለን።” w15 12/15 2:15, 16

ሰኞ፣ ነሐሴ 28

ይሖዋ ሆይ፣ ሞገስ አሳየኝ።በአንተ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁና ፈውሰኝ።​—⁠መዝ. 41:4

ዳዊት ይህን የጻፈው እሱ በታመመበትና ሁኔታዎችን መቆጣጠር ባልቻለበት ወቅት አቤሴሎም ዙፋኑን ለመቀማት የተነሳበትን ጊዜ በማሰብ ሊሆን ይችላል። ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ለፈጸመው ኃጢአት አምላክ ይቅር ቢለውም እሱ ግን በደሉንና ያስከተላቸውን መዘዞች አልረሳም። (2 ሳሙ. 12:7-14) ያም ቢሆን ንጉሡ ታሞ በአልጋ ላይ ተኝቶ ሳለ አምላክ እንደሚደግፈው እርግጠኛ ነበር። ዳዊት የጸለየው ይሖዋ በተአምራዊ መንገድ እንዲፈውሰው አይደለም። በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ መረዳት እንደምንችለው ዳዊት ይሖዋን የጠየቀው፣ ለተቸገረ ሰው አሳቢነት ለሚያሳይ ግለሰብ የሚያደርገውን ነገር ለእሱም እንዲያደርግለት ነው። ይህም “ታሞ በአልጋ ላይ ተኝቶ ሳለ” አምላክ የሚሰጠውን ድጋፍ ይጨምራል። (መዝ. 41:⁠3) ዳዊት ኃጢአቱ ይቅር ስለተባለለት፣ አምላክ እንዲያጽናናውና እንዲደግፈው እንዲሁም ሰውነቱ በሽታውን ተቋቁሞ እንዲያገግም መጠየቅ ይችላል። (መዝ. 103:⁠3) እኛም እንዲህ ዓይነት ጸሎት ማቅረብ እንችላለን። w15 12/15 4:8, 9

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 29

አምላክ ልጆቹ አድርጎ እንዲወስዳችሁ የሚያስችል መንፈስ አግኝታችኋል፤ ይህም መንፈስ “አባ፣ አባት!” ብለን እንድንጣራ ይገፋፋናል።​—⁠ሮም 8:​15

ከአምላክ እንዲህ ያለ ልዩ ጥሪ ያገኙ ግለሰቦች ይህን የሚያረጋግጥላቸው ሌላ ምሥክር አይፈልጉም። ለመቀባታቸው ማስተማመኛ የሚሰጣቸው ሌላ አካል አያስፈልጋቸውም። ይሖዋ ስለዚህ ጉዳይ በልባቸው ውስጥ አንዳች ጥርጣሬ እንዳያድር ያደርጋል። ሐዋርያው ዮሐንስ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን “እናንተ ግን ቅዱስ ከሆነው ከእሱ የመንፈስ ቅብዓት አግኝታችኋል፤ ደግሞም ሁላችሁም እውቀት አላችሁ” ብሏቸዋል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ ግን ከእሱ የተቀበላችሁት የመንፈስ ቅብዓት በውስጣችሁ ይኖራል፤ በመሆኑም ማንም እንዲያስተምራችሁ አያስፈልግም፤ ከዚህ ይልቅ ከእሱ ያገኛችሁት ይህ ቅብዓት ስለ ሁሉም ነገር እያስተማራችሁ ነው፤ ደግሞም እውነት እንጂ ውሸት አይደለም። ይህ ቅብዓት ባስተማራችሁ መሠረት ከእሱ ጋር ያላችሁን አንድነት ጠብቃችሁ ኑሩ።” (1 ዮሐ. 2:​20, 27) እነዚህ ቅቡዓን እንደ ማንኛውም ሰው መንፈሳዊ ትምህርት ማግኘት አለባቸው። ይሁንና መቀባታቸውን ሌላ አካል እንዲያጸድቅላቸው አያስፈልግም። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያለው ከሁሉ የላቀ ኃይል ይህን ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል! w16.01 3:9, 10

ረቡዕ፣ ነሐሴ 30

ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ።​—⁠ዕብ. 13:5

ባለን ነገር እውነተኛ እርካታ የምናገኘው በይሖዋ የምንታመን ከሆነ ነው። ባለን ነገር ረክተን መኖር ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት ለማዳበር ያስችለናል። (1 ጢሞ. 6:6-8) እንዲሁም ከይሖዋና ከወንድሞቻችን ጋር ያለን ግንኙነት፣ ገንዘብ ሊገዛው ከሚችለው ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ባለው ነገር ረክቶ የሚኖር ሰው አያጉረመርምም፣ አያማርርም እንዲሁም ስህተት አይፈላልግም፤ ከምቀኝነትና ከስግብግብነት ይርቃል፤ እንዲህ ያሉት ባሕርያት የወንድማማች ፍቅር እንዳያድግ እንቅፋት ይሆናሉ። ባለን ነገር ረክተን መኖር ግን የልግስና መንፈስ እንድናዳብር ይረዳናል። (1 ጢሞ. 6:​17-19) በተጨማሪም በይሖዋ መታመናችን ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ድፍረት እንድናገኝ ያስችለናል። (ዕብ. 13:⁠6) ይህ ዓይነቱ ድፍረት ደግሞ አዎንታዊ አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል፤ እንዲሁም የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለማነጽና ለማበረታታት ያስችለናል። (1 ተሰ. 5:​14, 15) በታላቁ መከራ ወቅት እንኳ መዳናችን እንደቀረበ ስለምናውቅ “ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ቀና አድርጉ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ እናደርጋለን።​—⁠ሉቃስ 21:​25-28፤ w16.01 1:16, 17

ሐሙስ፣ ነሐሴ 31

ይሖዋ የእሱ የሆኑትን ያውቃል።​—⁠2 ጢሞ. 2:​19

በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር ለበርካታ አሥርተ ዓመታት እየቀነሰ ሲሄድ ተመልክተናል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ ቁጥር እየጨመረ ነው። ታዲያ ቁጥሩ መጨመሩ ሊያሳስበን ይገባል? አይገባም። በዚህ ረገድ በአእምሯችን ልንይዛቸው የሚገቡ አንዳንድ ነጥቦችን ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን። በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱ ሰዎችን የሚቆጥሩት ወንድሞች፣ በእርግጥ ሰማያዊ ተስፋ ያለው ማን እንደሆነ ማወቅ አይችሉም። ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱት ሰዎች ቁጥር፣ ቅቡዓን ነን ብለው በስህተት የሚያስቡ ሰዎችንም ይጨምራል። በአንድ ወቅት ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ይወስዱ የነበሩ አንዳንዶች ከጊዜ በኋላ አቁመዋል። ሌሎች ደግሞ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ እንደሚገዙ አድርገው የሚያስቡት ከአእምሮ ወይም ከስሜት ጋር የተያያዘ ችግር ስላለባቸው ሊሆን ይችላል። ስለሆነም በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር፣ በምድር ላይ የቀሩትን ቅቡዓን ትክክለኛ ቁጥር አያመለክትም። በተጨማሪም ታላቁ መከራ ሲጀምር በምድር ላይ ምን ያህል ቅቡዓን እንደሚኖሩ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር የለም። w16.01 4:12-14

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ