የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es17 ገጽ 88-97
  • መስከረም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መስከረም
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2017
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ዓርብ፣ መስከረም 1
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 2
  • እሁድ፣ መስከረም 3
  • ሰኞ፣ መስከረም 4
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 5
  • ረቡዕ፣ መስከረም 6
  • ሐሙስ፣ መስከረም 7
  • ዓርብ፣ መስከረም 8
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 9
  • እሁድ፣ መስከረም 10
  • ሰኞ፣ መስከረም 11
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 12
  • ረቡዕ፣ መስከረም 13
  • ሐሙስ፣ መስከረም 14
  • ዓርብ፣ መስከረም 15
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 16
  • እሁድ፣ መስከረም 17
  • ሰኞ፣ መስከረም 18
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 19
  • ረቡዕ፣ መስከረም 20
  • ሐሙስ፣ መስከረም 21
  • ዓርብ፣ መስከረም 22
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 23
  • እሁድ፣ መስከረም 24
  • ሰኞ፣ መስከረም 25
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 26
  • ረቡዕ፣ መስከረም 27
  • ሐሙስ፣ መስከረም 28
  • ዓርብ፣ መስከረም 29
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2017
es17 ገጽ 88-97

መስከረም

ዓርብ፣ መስከረም 1

[አብርሃም] እውነተኛው አምላክ ወዳሳየው ስፍራ ተጓዘ።​—⁠ዘፍ. 22:3

አብርሃም ከእሱና ከይስሐቅ ጋር ከተጓዙት አገልጋዮቹ ከመለየቱ በፊት “እናንተ አህያውን ይዛችሁ እዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ በመሄድ በአምላክ ፊት ሰግደን ወደ እናንተ እንመለሳለን” ብሏቸዋል። (ዘፍ. 22:⁠5) አብርሃም ምን ማለቱ ነበር? ይስሐቅን መሥዋዕት ሊያደርገው እንደሆነ እያወቀ ከይስሐቅ ጋር እንደሚመለስ ለአገልጋዮቹ ሲናገር እየዋሸ ነበር? በፍጹም። መጽሐፍ ቅዱስ አብርሃም ምን አስቦ እንደነበር ለማወቅ ይረዳናል። (ዕብ. 11:​19) አብርሃም “አምላክ [ይስሐቅን] ከሞት እንኳ ሳይቀር ሊያስነሳው እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር።” አዎ፣ አብርሃም በትንሣኤ ያምን ነበር። እሱም ሆነ ሣራ በስተርጅናቸው ልጅ መውለድ እንዲችሉ ይሖዋ እንደረዳቸው ያውቃል። (ዕብ. 11:​11, 12, 18) አብርሃም በይሖዋ ዘንድ የማይቻል ነገር እንደሌለ ተገንዝቧል። በመሆኑም በዚያ ፈታኝ ወቅት የሚፈጠረው ነገር ምንም ይሁን ምን፣ የሚወደውን ልጁን መልሶ እንደሚያገኘው እርግጠኛ ነበር፤ ምክንያቱም ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች በሙሉ የሚፈጸሙት በይስሐቅ በኩል ነው። በእርግጥም አብርሃም “በእምነታቸው የተነሳ እንደ ጻድቃን ለተቆጠሩት ሁሉ አባት” ተብሎ መጠራቱ ምንም አያስደንቅም!​—ሮም 4:​11፤ w16.02 1:3, 13

ቅዳሜ፣ መስከረም 2

ይሖዋ ስለ ታላቁ ስሙ ሲል ሕዝቡን አይተውም።​—⁠1 ሳሙ. 12:​22

አምላክ ሳኦልን ንጉሥ እንዲሆን የቀባው ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ሳኦል ታዛዥ ሳይሆን በመቅረቱ ይሖዋ ተወው። (1 ሳሙ. 15:​17-23) አምላክ ሳኦልን ከሥልጣኑ ወዲያው ስላላወረደው፣ የእሱ መጥፎ ድርጊት ለተገዢዎቹም ሆነ በቅርቡ ለነበሩት ሰዎች ፈተና ሆኖባቸው ነበር። “በይሖዋ ዙፋን ላይ” የተቀመጠው ንጉሥ የተከተለውን መጥፎ አካሄድ እየተመለከቱ ለአምላክ ታማኝ መሆን ተፈታታኝ ነበር። (1 ዜና 29:​23) ሆኖም የሳኦል ልጅ ዮናታን ለይሖዋ ታማኝ መሆኑን አሳይቷል። እኛም አንዳንድ የበላይ ባለሥልጣናት ክብር ሊሰጣቸው እንደማይገባ ይሰማን ይሆናል፤ ሆኖም አምላክ ባዘዘው መሠረት ሁኔታው በሚፈቅድበት ጊዜ ሁሉ ለእነሱ በመገዛት ለይሖዋ ታማኝ መሆናችንን ማሳየት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ምግባረ ብልሹ ሊሆን ይችላል፤ ያም ሆኖ “ለበላይ ባለሥልጣናት” በአንጻራዊ ሁኔታ መገዛት ስላለብን ሥልጣኑን እናከብራለን። (ሮም 13:1, 2) ሁላችንም ይሖዋ ሥልጣን ለሰጣቸው ሰዎች አክብሮት በማሳየት ለእሱ ታማኝ መሆን እንችላለን።​—⁠1 ቆሮ. 11:3፤ ዕብ. 13:​17፤ w16.02 3:5, 6, 8

እሁድ፣ መስከረም 3

ሕዝብህ በገዛ ፈቃዱ ራሱን ያቀርባል።​—⁠መዝ. 110:3

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ወጣቶችን ጨምሮ የይሖዋ ሕዝብ በአጠቃላይ ለአምላክ አገልግሎት “በገዛ ፈቃዱ ራሱን ያቀርባል።” በመሆኑም ለመጠመቅ የሚያስብ አንድ ሰው ይህን ውሳኔ የሚያደርገው በራሱ ፍላጎት ተነሳስቶ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን አለበት። ይህ ደግሞ ራስህን በጥሞና መመርመር ይጠይቅብህ ይሆናል። ለምን? በወጣትነት ዕድሜህ ያለህበት ሁኔታ ለየት ያለ ሊሆን ስለሚችል ነው። ለምሳሌ ያደግከው እውነት ቤት ውስጥ ሊሆን ይችላል። ባለፉት ዓመታት አንዳንድ እኩዮችህን አልፎ ተርፎም ወንድሞችህንና እህቶችህን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ሲጠመቁ ተመልከተህ ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል? ጥምቀት፣ ይዋል ይደር እንጂ ሁሉም ወጣቶች የሆነ ዕድሜ ላይ ሲደርሱ በዘልማድ ሊወስዱት የሚገባ እርምጃ እንደሆነ አድርገህ እንዳታስብ ተጠንቀቅ። ታዲያ ይሖዋ ስላደረገው የጥምቀት ዝግጅት ተገቢ አመለካከት እንዲኖርህ ምን ይረዳሃል? መጠመቅ በጣም አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ቆም ብሎ ማሰብን ልማድ አድርግ። w16.03 1:11, 12

ሰኞ፣ መስከረም 4

የሚሰማም ሁሉ “ና!” ይበል፤ የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግ ሁሉ የሕይወትን ውኃ በነፃ ይውሰድ።​—⁠ራእይ 22:​17

የክርስቲያን ጉባኤ አባል እንደመሆናችን መጠን ይህን ግብዣ በተሳካ ሁኔታ ማከናወን የምንችለው እንዴት ነው? እንደ አንድ አካል ‘ተገጣጥመንና’ እርስ በርስ ‘ተስማምተን’ የምንሠራ ከሆነ ብቻ ነው። (ኤፌ. 4:​16) የመንግሥቱን ምሥራች በተቻለን መጠን ለብዙ ሰዎች ማካፈል ከፈለግን የስብከቱን ሥራ በተደራጀ መልኩ ማከናወን ይኖርብናል። ለዚህም ሲባል መመሪያዎች ይሰጡናል። በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ጉባኤዎች አማካኝነት የሚሰጠን መመሪያ ጥረታችንን አስተባብረን እንድንሠራ ያስታጥቀናል። የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ካደረግን በኋላ የመንግሥቱን መልእክት ለሰው ሁሉ ለመስበክ እንወጣለን። በአንደበታችንም ሆነ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በማበርከት ለሰዎች ምሥራቹን እናሰራጫለን። አንተስ በልዩ የአገልግሎት ዘመቻዎች እንድንካፈል የሚሰጡንን መመሪያዎች ለመታዘዝ ጥረት ታደርጋለህ? እንዲህ የምታደርግ ከሆነ በራእይ 14:6 ላይ የተገለጸው ‘በሰማይ መካከል የሚበረው መልአክ’ የያዘውን መልእክት ከሚያስተጋቡት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ምሥራቹን በኅብረት ታውጃለህ። w16.03 3:4, 5

ማክሰኞ፣ መስከረም 5

የመጽሐፍ ጥቅልሎችም ተከፈቱ።​—⁠ራእይ 20:​12

በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንዴት መኖር እንዳለብን የሚገልጹ መመሪያዎችን የያዙ ጥቅልሎች እንደሚከፈቱ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ከሞት የሚነሱትን ጨምሮ ሁሉም ሰዎች እነዚህን ጥቅልሎች በማጥናት አምላክ ለእነሱ ያለውን ዓላማ ማወቅ ይችላሉ። ጥቅልሎቹ የይሖዋን አስተሳሰብ ይበልጥ እንድንረዳ እንደሚያስችሉን ጥርጥር የለውም። ምድር ገነት ስትሆን በዚያ የሚኖሩት ሰዎች በመንፈስ መሪነት ስለተጻፈው የአምላክ ቃል ያላቸው እውቀት እየጨመረ ይሄዳል፤ እንዲሁም ከአዳዲሶቹ ጥቅልሎች አዲስ መረጃ ያገኛሉ። በእነዚህ ነገሮች መመራታቸው ሰዎችን በፍቅር፣ በአሳቢነትና በአክብሮት እንዲይዙ ያስችላቸዋል። (ኢሳ. 26:⁠9) በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር የሚኖረው የትምህርት መርሐ ግብር ምን ሊመስል እንደሚችል አስብ! “በጥቅልሎቹ ውስጥ [ለተጻፉት] ነገሮች” ጥሩ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። በመጨረሻው ፈተና ወቅት ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው የሚኖሩ ሰዎችን ስም ይሖዋ ‘በሕይወት መጽሐፍ’ ላይ በማይፋቅ መንገድ ይጽፈዋል። እኛም ይህን በረከት ማግኘት እንችላለን! w16.03 4:19, 20

ረቡዕ፣ መስከረም 6

ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ተስፋዬ ነህ፤ ከልጅነቴ ጀምሮ በአንተ ታምኛለሁ።​—⁠መዝ. 71:5

ተሞክሮ ያላቸው ሽማግሌዎች ለወንድሞች ከልጅነታቸው ማለትም ከአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ አንስቶ በጉባኤ ውስጥ ለዕድሜያቸው የሚመጥን ኃላፊነት በመስጠት ማሠልጠን ጥቅም እንዳለው ይናገራሉ። ልጆች ገና በለጋነታቸው እንዲህ ዓይነት ሥልጠና ማግኘታቸው ትኩረታቸውን የሚሰርቁ ነገሮች በሚዥጎደጎዱባቸው ማለትም በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይም ትኩረታቸውን በመንፈሳዊ ግቦች ላይ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። (መዝ. 71:​17) አንድ ሽማግሌ የተማሪውን የማገልገል ፍላጎት ማነሳሳት የሚችልበት ሌላው ዘዴ ደግሞ ምን ማድረግ እንዳለበት ብቻ ሳይሆን ለምን እንደሚያደርግ መንገር ነው። ሽማግሌው፣ ለተማሪው አንድን ነገር የሚያደርግበትን ምክንያት የሚነግረው ከሆነ ታላቅ አስተማሪ የሆነውን የኢየሱስን ምሳሌ እየተከተለ ነው። ለምሳሌ ኢየሱስ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ለሐዋርያቱ ተልእኮ ከመስጠቱ በፊት ይህን ትእዛዝ መፈጸም ያለባቸው ለምን እንደሆነ ነግሯቸዋል። “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል። ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ” ብሏቸዋል።​—⁠ማቴ. 28:​18, 19፤ w15 4/15 2:5, 6

ሐሙስ፣ መስከረም 7

ጌታ አጠገቤ ቆሞ ኃይል ሰጠኝ፤ ከአንበሳ አፍም ዳንኩ።​—⁠2 ጢሞ. 4:​17

በሮም የክርስትና እምነት ተከታይ መሆን አደገኛ የነበረበት ወቅት ነው። የክርስቶስ ተከታዮች በ64 ዓ.ም. ከተማዋን በእሳት እንዳቃጠሉ የሚገልጽ ወሬ ስለተነዛባቸው ሕዝቡ ለእነሱ ከፍተኛ ጥላቻ ነበረው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሁለተኛ ጊዜ የታሰረው እንዲህ ያለ ያልተረጋጋ ሁኔታ በሰፈነበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። ታዲያ ሌሎች ክርስቲያኖች ሊረዱት ይመጡ ይሆን? ጳውሎስ መጀመሪያ ላይ ይህ ጉዳይ ሳያሳስበው አልቀረም፤ ምክንያቱም ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ “የመጀመሪያ መከላከያዬን ባቀረብኩበት ወቅት ሁሉም ትተውኝ ሄዱ እንጂ ከእኔ ጎን የቆመ ማንም አልነበረም” ብሏል። (2 ጢሞ. 4:​16) ያም ሆኖ ጳውሎስ ምንም እርዳታ አላገኘም ማለት አይደለም። በዚያ ወቅት ያጋጠሙትንም ሆነ ወደፊት የሚደርሱበትን ፈተናዎች በጽናት እንዲወጣ ይሖዋ ሊያጠናክረው እንደሚችል ተማምኗል። እንዲያውም “ጌታ ከክፉ ሥራ ሁሉ ይታደገኛል” በማለት አክሎ ተናግሯል። (2 ጢሞ. 4:​18) በእርግጥም ጳውሎስ፣ ከሰዎች የሚገኘው እርዳታ ውስን በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ይሖዋና ልጁ በሚሰጡን እርዳታ መተማመን እንደሚቻል ተምሯል። w15 4/15 4:1-3

ዓርብ፣ መስከረም 8

እሱ ራስህን ይጨፈልቃል።​—⁠ዘፍ. 3:​15

ኢየሱስ ሲወለድ ሰይጣን ይህ ጨቅላ ሕፃን ሲያድግ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ እንደሚሆን ያውቃል። ሰይጣን አንድን ሕፃን መግደል ዘግናኝ ድርጊት እንደሆነ ይሰማው ይሆን? ዲያብሎስ የሥነ ምግባር ደንብ የለውም። ከሕፃኑ ኢየሱስ ጋር በተያያዘም ሳይውል ሳያድር እርምጃ ወሰደ። እንዴት? ንጉሥ ሄሮድስ፣ ኮከብ ቆጣሪዎች ‘የተወለደውን የአይሁዳውያን ንጉሥ’ በተመለከተ ሲያጠያይቁ በሰማ ጊዜ በጣም ተበሳጨ፤ በመሆኑም ይህን ሕፃን ለመግደል ቆርጦ ተነሳ። (ማቴ. 2:1-3, 13) ሕፃኑ በምንም መንገድ እንዳያመልጥ ሲል በቤተልሔምና በአካባቢዋ የሚገኙ ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆናቸው ወንዶች ልጆች በሙሉ እንዲገደሉ አዘዘ። (ማቴ. 2:​13-18) እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ለማሰብ ከሚከብደው ከዚህ እልቂት ተርፏል፤ ሆኖም ይህ ክንውን ጠላታችን ስለሆነው ስለ ሰይጣን ምን ይጠቁመናል? ዲያብሎስ ለሰው ሕይወት ምንም ደንታ እንደሌለው ግልጽ ነው። ለሕፃናት እንኳ የሚራራ አንጀት የለውም። እውነትም ሰይጣን “እንደሚያገሳ አንበሳ” ነው። (1 ጴጥ. 5:⁠8) ምን ያህል አረመኔ እንደሆነ ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም! w15 5/15 1:10, 12, 13

ቅዳሜ፣ መስከረም 9

የተስፋውን ቃል ፍጻሜ ባያዩም . . . ከሩቅ አይተው በደስታ ተቀበሉት።​—⁠ዕብ. 11:​13

አይተነው የማናውቀውን ነገር በዓይነ ሕሊናችን የመመልከት ችሎታ ከአምላክ ያገኘነው ስጦታ ነው። ይህ ችሎታ ወደፊት የሚፈጸሙ መልካም ነገሮችን በተስፋ እንድንጠባበቅ እንዲሁም አስቀድመን ዕቅድ በማውጣት ችግር ውስጥ ከመግባት እንድንርቅ ይረዳናል። ይሖዋ ወደፊት የሚሆኑ ነገሮችን አስቀድሞ ስለሚያውቅ ስለ እነዚህ ነገሮች በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ብዙ ጊዜ ነግሮናል። እኛም ወደፊት የሚፈጸሙ ነገሮችን በአእምሯችን መሳል እንችል ይሆናል። እንዲያውም እምነት ለማዳበር የሚረዳን የማይታዩ ነገሮችን በምናብ የመመልከት ችሎታችን ነው። (2 ቆሮ. 4:​18) ሐና፣ ልጇ በማደሪያው ድንኳን እንዲያገለግል ወደዚያ ስትወስደው ስለሚኖረው ሁኔታ ብታሰላስል በዓይነ ሕሊናዋ የምትመለከተው ነገር በእውነታ ላይ የተመሠረተ ነው። በአእምሮዋ የምትስለው ነገር በውሳኔዋ ላይ የተመሠረተ ሲሆን እንዲህ ማድረጓ በግቧ ላይ እንድታተኩር ረድቷታል። (1 ሳሙ. 1:​22) እኛም አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎች በዓይነ ሕሊናችን ስንመለከት፣ እያሰላሰልን ያለነው መፈጸሙ በማይቀር ነገር ላይ ነው። (2 ጴጥ. 1:​19-21) በጥንት ዘመን የኖሩ በርካታ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች አምላክ ተስፋ የሰጣቸውን ነገሮች በአእምሯቸው ይስሉ እንደነበር ጥርጥር የለውም። w15 5/15 3:1-3

እሁድ፣ መስከረም 10

ባለጸጋ ሰው [ሀብቱን] . . . ጥበቃ እንደሚያስገኝ ግንብ አድርጎ ይመለከተዋል።​—⁠ምሳሌ 18:​11

ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ግምት ውስጥ ሳናስገባ ሀብት ስለማካበት የምናሰላስል ከሆነ አደገኛ ነው። ኢየሱስ “ለራሱ ሀብት የሚያከማች በአምላክ ዘንድ ግን ሀብታም ያልሆነ ሰው” ያለበትን አሳዛኝ ሁኔታ የሚያሳይ ምሳሌ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:​16-21) ይሖዋ እሱን የሚያስደስት ነገር ስናደርግ ልቡ ሐሴት ያደርጋል። (ምሳሌ 27:​11) ‘በሰማይ ሀብት’ በማከማቸታችን የእሱን ሞገስ ማግኘት ምንኛ የሚያስደስት ነው! (ማቴ. 6:​20) ደግሞም ሊኖረን ከሚችለው ውድ ሀብት ሁሉ የላቀው ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ‘በምድር ላይ ሀብት ለማከማቸት’ የምናደርገው ጥረት ሕይወታችንን ከተቆጣጠረው ይህ ምን ያህል ጭንቀት ሊፈጥርብን እንደሚችል አስበው። (ማቴ. 6:​19) ኢየሱስ፣ አንድ ምሳሌ በመጠቀም “የዚህ ሥርዓት ጭንቀት እንዲሁም ሀብት ያለው የማታለል ኃይል” የመንግሥቱን ቃል ሊያንቀው እንደሚችል ገልጿል።​—⁠ማቴ. 13:​18, 19, 22፤ w15 5/15 4:15, 16

ሰኞ፣ መስከረም 11

ሕዝቡም ዱዳዎች ሲናገሩ፣ ሽባዎች ሲፈወሱ፣ አንካሶች ሲራመዱና ዓይነ ስውሮች ሲያዩ ተመልክተው እጅግ ተደነቁ።​—⁠ማቴ. 15:​31

ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክ ኃይል ተጠቅሞ እጅግ የሚያስገርሙ የተለያዩ ተአምራትን ፈጽሟል። በሥጋ ደዌ የተያዙ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን በሕዝቡ መካከል ያለውን ማንኛውንም ዓይነት በሽታና ማንኛውንም ዓይነት ሕመም ፈውሷል። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት የርኅራኄ ተግባር ለመፈጸም፣ የሰውነት ክፍል የሚለግሱ ሰዎች አላስፈለጉትም። ምክንያቱም የፈወሰው፣ ጉዳት የደረሰባቸውን የአካል ክፍሎች ነው። ከዚህም ሌላ ሰዎችን ወዲያውኑ የፈወሰ ሲሆን አጠገቡ የሌሉ ሕመምተኞችን እንኳ ያዳነበት ጊዜ አለ። (ዮሐ. 4:​46-54) እነዚህ አስደናቂ ዘገባዎች ምን ያስተምሩናል? አሁን በሰማይ ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ዘላቂ ፈውስ ለማምጣት ኃይል ብቻ ሳይሆን ፍላጎትም ጭምር እንዳለው ይጠቁሙናል። ኢየሱስ ሰዎችን የያዘበትን መንገድ ማወቃችን “ለችግረኛውና ለድሃው ያዝናል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንደሚፈጸም እንድንተማመን ያደርገናል። (መዝ. 72:​13) በእርግጥም በዚያን ጊዜ ኢየሱስ የተቸገሩትን ሁሉ የመርዳት ልባዊ ፍላጎቱን ያሳካል። w15 6/15 2:6

ማክሰኞ፣ መስከረም 12

ስምህ ይቀደስ።​—⁠ማቴ. 6:9

ብዙ ሰዎች የጌታን ጸሎት በቃላቸው መድገም ይችላሉ። ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል የአምላክ መንግሥት እውን መስተዳድር እንደሆነና በምድር ላይ አስደናቂ የሆኑ ለውጦችን እንደሚያመጣ ለሰዎች ለማስረዳት ብዙውን ጊዜ ይህን ጸሎት እንጠቅሳለን። አሊያም ደግሞ አምላክ የግል ስም እንዳለውና ይህ ስም መቀደስ ወይም ‘ብሩክ መሆን’ እንዳለበት ለማጉላት በጸሎቱ ላይ ያለውን የመጀመሪያ ልመና አውጥተን እናሳያቸው ይሆናል። (ማቴ. 6:9 የግርጌ ማስታወሻ) ኢየሱስ ይህን ጸሎት ያስተማረን በሕዝበ ክርስትና ውስጥ በርካታ ሰዎች እንደሚያደርጉት በጸለይን ቁጥር ቃል በቃል እንድንደግመው አስቦ ነው? በፍጹም። ኢየሱስ ይህን ናሙና ከማስተማሩ በፊት “በምትጸልዩበት ጊዜ . . . አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ” ብሎ ነበር። (ማቴ. 6:⁠7) ከጊዜ በኋላም ይህን ጸሎት በድጋሚ ሲያስተምር ለየት ያለ አገላለጽ ተጠቅሟል። (ሉቃስ 11:1-4) ኢየሱስ፣ ስለ የትኞቹ ነገሮች መለመን እንዳለብንና በጸሎታችን ላይ ቅድሚያ መስጠት የሚገባን ለምን ነገሮች እንደሆነ አስገንዝቦናል። ይህ ጸሎት፣ የጸሎት ናሙና ተብሎ የሚጠራውም ለዚህ ነው። w15 6/15 4:1, 2

ረቡዕ፣ መስከረም 13

የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።​—⁠1 ቆሮ. 10:​12

ይሖዋ ከፍተኛ ኃይል ያለውን ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት ጥንካሬ እንድናገኝና ፈተናን መቋቋም እንድንችል ይረዳናል። በተጨማሪም አምላክ ልንርቃቸው ስለሚገቡ ሁኔታዎች በቃሉና በጉባኤው አማካኝነት አስቀድሞ ያስጠነቅቀናል፤ ከማስጠንቀቂያዎቹ መካከል እምብዛም አስፈላጊ ባልሆኑ ቁሳዊ ነገሮች ላይ ብዙ ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት ማጥፋትን አስመልክቶ የሚሰጠን ምክር ይገኝበታል። ቀደም ሲል አቅኚ የነበሩት ኢስፔንና ያኒ ሁለት ልጆቻቸውን እያሳደጉ ነው። ኢስፔን እንዲህ ብሏል፦ “ቀደም ሲል እናደርገው እንደነበረው አሁን በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ረዘም ያለ ጊዜ ማሳለፍ አንችልም፤ በመሆኑም ፈተና ውስጥ እንዳንወድቅ አዘውትረን ወደ ይሖዋ እንጸልያለን። መንፈሳዊነታችንንና ለአገልግሎቱ ያለንን ቅንዓት ጠብቀን ለመኖር እንዲረዳን ይሖዋን እንጠይቀዋለን።” በዘመናችን የተስፋፋው ሌላው ፈተና ደግሞ ፖርኖግራፊ ማየት ነው። አንዳንዶች፣ መጥፎ በሆኑ ነገሮች ላይ በማሰላሰላቸው በዚህ ፈተና ወድቀዋል። ሆኖም በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችን እንዳደረጉት እኛም ይህን ፈተና መቋቋም እንችላለን።​—⁠1 ቆሮ. 10:​13፤ w15 6/15 5:15, 16

ሐሙስ፣ መስከረም 14

የምድር ነገሥታት፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የጦር አዛዦች፣ ሀብታሞች፣ ብርቱዎች፣ ባሪያዎች ሁሉና ነፃ ሰዎች ሁሉ በዋሻዎች ውስጥና ተራራ ላይ ባሉ ዓለቶች መካከል ተደበቁ።​—⁠ራእይ 6:​15

የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች ከጠፉ በኋላ ምን ይሆናል? በዚያን ጊዜ የልባችን እውነተኛ ዝንባሌ ይገለጣል። አብዛኛው የሰው ዘር “ተራራ ላይ ባሉ ዓለቶች” የተመሰሉትን ሰብዓዊ ድርጅቶች መሸሸጊያ ለማድረግ ይሞክራል። የአምላክ ሕዝቦች ግን ይሖዋ ወዳዘጋጀው መጠለያ በምሳሌያዊ ሁኔታ ይሸሻሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለተወሰነ ጊዜ ያህል ክፍተት የተገኘው ብዙ አይሁዳውያን ወደ ክርስትና እንዲለወጡ አልነበረም። ከዚህ በተለየ፣ ቀድሞውንም ክርስቲያን የነበሩት ሰዎች በታዛዥነት እርምጃ የሚወስዱበት ጊዜ ነበር። በተመሳሳይም ወደፊት ታላቁ መከራ ለተወሰነ ጊዜ ሲቋረጥ አዳዲስ አማኞች ወደ ክርስትና እንደሚጎርፉ አንጠብቅም። ከዚህ ይልቅ በዚህ ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ ይሖዋን እንደሚወዱና የክርስቶስን ወንድሞች እንደሚደግፉ ለማሳየት አጋጣሚ ያገኛሉ።​—⁠ማቴ. 25:​34-40፤ w15 7/15 2:7

ዓርብ፣ መስከረም 15

አንድ ሰው በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረው ሲል መከራን ችሎ ቢያሳልፍና ግፍ ቢደርስበት ይህ ደስ የሚያሰኝ ነው።​—⁠1 ጴጥ. 2:​19

አስተዳደግህ አሊያም የምትኖርበት አካባቢ ለአገርህ ወይም ለብሔርህ የተለየ ታማኝነት እንዲያድርብህ አድርጎሃል? እንዲህ ዓይነቱ ስሜት አሁንም በውስጥህ አለ? ክርስቲያኖች፣ ብሔራዊ ስሜት ለሌሎች ያላቸውን አመለካከት እንዲያዛባው መፍቀድ አይኖርባቸውም። ይሁንና ከአንተ የተለየ ዜግነት፣ ባሕል፣ ቋንቋ ወይም ዘር ላላቸው ሰዎች አሉታዊ አመለካከት እንዳለህ ብትገነዘብ ምን ማድረግ ያስፈልግሃል? ይሖዋ፣ ስለ ብሔራዊ ስሜትና ስለ ጭፍን ጥላቻ ያለውን አመለካከት ቆም ብለህ ማሰብህ ጠቃሚ ነው። እነዚህ ነገሮች ምርምር ልታደርግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው። በተጨማሪም ይሖዋ በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ የእሱ ዓይነት አመለካከት ለማዳበር እንዲረዳህ በጸሎት ለምነው። (ሮም 12:⁠2) ሁላችንም እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል፤ ምክንያቱም ይዋል ይደር እንጂ ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች በሕሊናቸው ምክንያት በአካባቢያቸው ካሉ ሰዎች ለምሳሌ ከሥራ ባልደረቦቻቸው፣ አብረዋቸው ከሚማሩ ሰዎች፣ ከጎረቤቶቻቸው፣ ከዘመዶቻቸው ወይም ከሌሎች የተለየ አቋም መያዝ የሚያስፈልጋቸው ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም። በዚህ ጊዜ መለየታችን የግድ ነው! w15 7/15 3:14, 15

ቅዳሜ፣ መስከረም 16

ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ አምላኩ ወደ ይሖዋ ጸለየ።​—⁠ዮናስ 2:1

ይሖዋ ልመናችንን ይሰማል፤ እንዲሁም ስሜታችንን ማንም በማይረዳልን ጊዜም እንኳ እሱ የውስጣችንን ያውቃል። ለእኛ ጽኑ ፍቅር እንዳለው ከሚያሳይበት ግሩም መንገድ አንዱ ለጸሎታችን የሚሰጠው ምላሽ ነው። በአምላክ ቃል ውስጥ ከተመዘገቡት ጸሎቶች ብዙ መማር እንችላለን። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ በቤተሰብ አምልኮ ወቅት እንደዚህ ባሉ ጸሎቶች ላይ መወያየታችን በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ጥንት የነበሩት የይሖዋ አገልጋዮች የሚያሳስባቸውን ነገር ለአምላክ በገለጹበት መንገድ ላይ በማሰላሰል የጸሎታችንን ይዘት ማሻሻል እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ዮናስ በአንድ ትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ ሆኖ በጸጸት ስሜት ያቀረበውን ጸሎት መመልከት ትችላላችሁ። (ዮናስ 1:​17 እስከ 2:​10) ሰለሞን የቤተ መቅደሱ ምረቃ ላይ ያቀረበውን ከልብ የመነጨ ጸሎትም መከለስ ይቻላል። (1 ነገ. 8:​22-53) እንዲሁም ኢየሱስ ለእኛ ጥቅም ሲል ባስተማረው የጸሎት ናሙና ላይ ማሰላሰል ትችላላችሁ። (ማቴ. 6:9-13) ከሁሉ በላይ ደግሞ ያለማሰለስ “ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ።” እንዲህ ካደረጋችሁ “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”​—⁠ፊልጵ. 4:6, 7፤ w15 8/15 1:11, 12

እሁድ፣ መስከረም 17

ተገዙ።​—⁠ዕብ. 13:​17

በአዲሱ ዓለም ውስጥ ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠንን አመራር እየተከተልን ምድርን ማስዋብ፣ ከሞት የተነሱ ሰዎችን ማስተማርና አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ፈቃድ መፈጸም ትልቅ ደስታ የሚያመጣ ነገር ይሆናል። ሆኖም ብዙም የማያስደስተንን ሥራ እንድንሠራ መመሪያ ቢሰጠንስ? ይህን መመሪያ አክብረን አቅማችን በፈቀደው መጠን ሥራውን ጥሩ አድርገን ለማከናወንና ከሥራው ደስታ ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን? ብዙዎቻችን ‘አዎ’ ብለን እንመልስ ይሆናል። ይህ ከሆነ ታዲያ ዛሬስ ለቲኦክራሲያዊ መመሪያ እየተገዛን ነው? እንዲህ እያደረግን ከሆነ በይሖዋ አገዛዝ ሥር ለሚኖረው የዘላለም ሕይወት እየተዘጋጀን ነው። በአዲሱ ዓለም ለሚኖረው ሕይወት ለመዘጋጀት በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ ላደረገው ዝግጅት ከመገዛት ባለፈ ባለን ነገር የመርካትና ተባብሮ የመሥራት መንፈስ ማዳበርም ይኖርብናል። በዛሬው ጊዜ አመራር ከሚሰጡት ጋር ተባብረን የምንሠራ፣ ለምሳሌ በሚሰጠን አዲስ የአገልግሎት ምድብ እርካታና ደስታ የምናገኝ ከሆነ በአዲሱ ዓለም ውስጥም እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ይችላል። w15 8/15 3:6, 7

ሰኞ፣ መስከረም 18

[አረማዊ] ሚስቶቹ ልቡ ሌሎች አማልክትን ወደ መከተል እንዲያዘነብል አደረጉት፤ . . . ሰለሞንም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።​—⁠1 ነገ. 11:4, 6

ሰለሞን መጥፎ ጓደኝነት መመሥረቱ፣ የነበረውን ጥበብ እያደር እንዲያጣና ከእውነተኛው አምልኮ እንዲርቅ አድርጎታል። (1 ነገ. 11:1-6) ይሖዋን የማይወድ ሰው ማግባት ለሚያስቡ ክርስቲያኖች ይህ ጥሩ ማስጠንቀቂያ ይሆናቸዋል! አንድ ሰው የአምላክ አገልጋይ የሆነው ከማያምን ሰው ጋር ትዳር ከመሠረተ በኋላ ቢሆንስ? መጽሐፍ ቅዱስ “እናንተ ሚስቶች፣ ለቃሉ የማይታዘዙ ባሎች ካሉ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው ምግባር እንዲማረኩ ለባሎቻችሁ ተገዙ” ይላል። (1 ጴጥ. 3:⁠1) ይህ ሐሳብ የተጻፈው ለክርስቲያን ሚስቶች ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ይሖዋን ማምለክ ለጀመሩና የማያምኑ ሚስቶች ላሏቸው ባሎችም ይሠራል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ግልጽ ነው፦ ጥሩ የትዳር አጋር ሁኑ፤ እንዲሁም አምላክ ለጋብቻ ያወጣቸውን የላቁ መሥፈርቶች ተግባራዊ አድርጉ። በርካታ የማያምኑ ሰዎች፣ የትዳር ጓደኛቸው የአምላክን መመሪያዎች መከተል ከጀመረ በኋላ ምን ያህል ለውጥ እንዳደረገ ሲመለከቱ እነሱም እውነትን ተቀብለዋል። w15 8/15 4:15, 16

ማክሰኞ፣ መስከረም 19

ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል።​—⁠ምሳሌ 14:​15

አንዳንድ የበሽታ ዓይነቶች ፈውስ የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም አንዳንድ የሕክምና ዓይነቶች በጣም ውጤታማ እንደሆኑ ሲወራ ብንሰማና ወሬው እንዲሁ የስሚ ስሚ ቢሆን እንዲህ ያሉትን የሕክምና ዓይነቶች በመጠቀም ረገድ ጥንቃቄ ማድረጋችን የጥበብ አካሄድ ነው። ጳውሎስ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” ሲል በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (ፊልጵ. 4:⁠5) ምክንያታዊ መሆናችን መንፈሳዊ ጉዳዮችን ቸል እስክንል ድረስ ስለ ጤናችን ከሚገባው በላይ ከመጨነቅ እንድንቆጠብ ይረዳናል። የጤንነታችን ጉዳይ በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ ከያዘ ራስ ወዳድ የመሆን አዝማሚያ እየታየብን ሊሆን ይችላል። (ፊልጵ. 2:⁠4) በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊይዝ የሚገባው መንፈሳዊ ነገር ነው፤ በመሆኑም ስለ ጤንነታችን ያለን አመለካከት ምክንያታዊነት የሚንጸባረቅበት ሊሆን ይገባል። (ፊልጵ. 1:​10) ከጤና ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ እያንዳንዳችን የራሳችንን ውሳኔ ለማድረግና የሚያስከትልብንን ኃላፊነት ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ይኖርብናል። w15 9/15 2:8, 10

ረቡዕ፣ መስከረም 20

ብርሃንህንና እውነትህን ላክ። እነሱ ይምሩኝ።​—⁠መዝ. 43:3

ይሖዋ “የእውነት አምላክ” ነው። (መዝ. 31:⁠5) ይሖዋ ልጆቹን የሚወዳቸው ከመሆኑም ሌላ በማንኛውም የሕይወታቸው ዘርፍ በተለይ ደግሞ ከአምልኮ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች መመሪያ እንዲሆናቸው የእውነትን ብርሃን ያበራላቸዋል። ይሖዋ የገለጠልን እውነት ምንድን ነው? ይህስ እሱ እንደሚወደን የሚያሳየው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ የራሱን ማንነት በተመለከተ እውነቱን ገልጦልናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሌሎች ስሞች ሁሉ ይበልጥ በብዛት ተጠቅሶ የሚገኘውን የግል ስሙን አሳውቆናል። ይሖዋ በዚህ መንገድ እሱን እንድናውቀው በማድረግ ወደ እኛ ይቀርባል። (ያዕ. 4:⁠8) በተጨማሪም ይሖዋ ባሕርያቱን በመግለጥ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ አሳውቆናል። ግዑዙ ጽንፈ ዓለም ኃይሉንና ጥበቡን የሚያሳይ ቢሆንም ይሖዋ በቅዱሳን መጻሕፍት አማካኝነት ፍትሑን በተለይ ደግሞ ገደብ የሌለውን ፍቅሩን ገልጦልናል። (ሮም 1:​20) ይሖዋ፣ ኃይልና ጥበብ ብቻ ሳይሆን ፍትሕና ፍቅር ያለው አባት ስለሆነ ልጆቹ ወደ እሱ መቅረብ አይከብዳቸውም። w15 9/15 4:8, 9

ሐሙስ፣ መስከረም 21

የይሖዋም እጅ በአገልጋዮቹ ዘንድ ትታወቃለች።​—⁠ኢሳ. 66:​14

ብዙ ሰዎች እነሱ በሚያደርጉትና አምላክ በሚያደርገው ነገር መካከል ምንም ግንኙነት ያለ አይመስላቸውም። እንዲያውም አንዳንዶች አምላክ በሰዎች ላይ የሚደርሰው ነገር ግድ እንደማይሰጠው ይሰማቸዋል። ኅዳር 2013፣ ሃያን የተባለው ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ መካከለኛውን ፊሊፒንስ ባወደመበት ወቅት የአንድ ትልቅ ከተማ ከንቲባ “አምላክ የሆነ ቦታ ሄዶ መሆን አለበት” ብለዋል። ሌሎች ሰዎች ደግሞ የሚያደርጉትን ነገር አምላክ ማየት የሚችል አይመስላቸውም። (ኢሳ. 26:​10, 11፤ 3 ዮሐ. 11) እነዚህ ሰዎች ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ለአምላክ እውቅና መስጠት ተገቢ መስሎ አልታያቸውም’ ብሎ የገለጻቸው ዓይነት ሰዎች ናቸው። እንዲህ ያሉ ሰዎች “በዓመፅ፣ በኃጢአተኝነት፣ በስግብግብነት፣ በክፋት” የተሞሉ ናቸው። (ሮም 1:​28, 29) ስለ እኛስ ምን ማለት ይቻላል? ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ሰዎች በተለየ ይሖዋ የምናደርገውን ነገር ሁሉ እንደሚመለከት እንገነዘባለን። ይሁንና ትኩረት እንደሚሰጠንና ድጋፍ እንደሚያደርግልንስ ይሰማናል? w15 10/15 1:1-3

ዓርብ፣ መስከረም 22

እምነቴን በሥራ አሳይሃለሁ።—⁠ያዕ. 2:​18

በስብከቱ ሥራ መካፈል እምነታችንን በተግባር የምናሳይበት ግሩም መንገድ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በስብከቱ ሥራ መካፈላችን አምላክ ይህን ሥርዓት ለማጥፋት የወሰነው ጊዜ እንደሚመጣና ‘እንደማይዘገይ!’ እምነት እንዳለን ያሳያል። (ዕን. 2:⁠3) በፈቃደኝነት ተነሳስተን በአገልግሎት ብዙ ለማከናወን የምናደርገው ጥረት እምነታችን የሚለካበት አንዱ መንገድ ነው። ታዲያ የምንችለውን ያህል እያደረግን ምናልባትም በሥራው ያለንን ተሳትፎ ማሳደግ የምንችልባቸውን መንገዶች እየፈለግን ነው? (2 ቆሮ. 13:⁠5) አዎን፣ ‘እምነታችንን በይፋ መናገራችን’ በልባችን ውስጥ እምነት እንዳለ የምናሳይበት አሳማኝ ማስረጃ ነው። (ሮም 10:​10) በተጨማሪም በየዕለቱ ከሚያጋጥሙን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ጋር በምናደርገው ትግል እምነት እንዳለን ማሳየት እንችላለን። ሕመም፣ ተስፋ መቁረጥ፣ የመንፈስ ጭንቀት፣ ድህነት ወይም ሌላ ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመን ይሖዋና ልጁ “እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ” ድጋፍ እንደሚያደርጉልን እርግጠኞች ነን። (ዕብ. 4:​16) ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ነገሮችም እርዳታ ለማግኘት በመጸለይ እንዲህ ዓይነት እምነት እንዳለን እናሳያለን። w15 10/15 2:12-14

ቅዳሜ፣ መስከረም 23

መንፈስ ቅዱስ . . . የነገርኳችሁን ነገር ሁሉ እንድታስታውሱ ያደርጋችኋል።​—⁠ዮሐ. 14:​26

መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት የማትችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ቢችልም ቀደም ሲል በአእምሮህ ባከማቸኸው እውቀት ላይ ማለትም በምትወዳቸው ጥቅሶች ወይም የመዝሙር ስንኞች ላይ እንዳታሰላስል ሊያግድህ የሚችል ሰው የለም። (ሥራ 16:​25) ደግሞም የአምላክ መንፈስ ከዚህ በፊት የተማርካቸውን መልካም ነገሮች እንድታስታውስ ሊረዳህ ይችላል። በመሆኑም ዛሬውኑ የሳምንቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ለማንበብና ለማሰላሰል ጊዜ መድብ። ኢየሱስ በተናገረውና ባደረገው ነገር ላይ ለማሰላሰልም ጊዜ መመደብ አለብህ። ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚገልጹት የወንጌል ዘገባዎች በሰፊው ከሚታወቁት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መካከል እንደሚገኙ ግልጽ ነው። (ሮም 10:​17፤ ዕብ. 12:2፤ 1 ጴጥ. 2:​21) እንዲያውም የአምላክ ሕዝቦች፣ ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈውን ሕይወት በጊዜ ቅደም ተከተል የሚያቀርብ ጽሑፍ አግኝተዋል። በእያንዳንዱ የመጽሐፉ ምዕራፍ ላይ የቀረቡትን ተዛማጅ የወንጌል ዘገባዎች በጥሞና ማንበባችንና በዚያ ላይ ማሰላሰላችን በጣም ይጠቅመናል።​—⁠ዮሐ. 14:6፤ w15 10/15 4:11, 12

እሁድ፣ መስከረም 24

እኔ ግን ከአባቴ የሰማሁትን ነገር ሁሉ ስላሳወቅኳችሁ ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ።​—⁠ዮሐ. 15:​15

ኢየሱስ አፍቃሪና ታማኝ ጓደኛ ነበር። በጥንት ዘመን አንድ ጌታ ሐሳቡንና ስሜቱን አውጥቶ ለባሪያዎቹ ማውራቱ የተለመደ አልነበረም። ኢየሱስ ግን ለታማኝ ሐዋርያቱ ጌታቸው ብቻ ሳይሆን ወዳጃቸውም ነበር። አብሯቸው ጊዜ ያሳልፍ፣ ስሜቱን ያካፍላቸው እንዲሁም የልባቸውን አውጥተው ሲነግሩት በጥሞና ያዳምጣቸው ነበር። (ማር. 6:​30-32) እንዲህ ያለ ፍቅር የተንጸባረቀበት የሐሳብ ልውውጥ በኢየሱስና በሐዋርያቱ መካከል ጠንካራ ወዳጅነት እንዲመሠረት ያደረገ ሲሆን ይህም በአምላክ አገልግሎት ለሚኖራቸው ኃላፊነት አዘጋጅቷቸዋል። ኢየሱስ የሚወዳቸው ደቀ መዛሙርቱና ጓደኞቹ በይሖዋ አገልግሎት ራስን ማስጠመድ የሚያስገኘውን ደስታ እንዲያጣጥሙ ይመኝ ነበር። በመሆኑም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በቅንዓት እንዲካፈሉ አበረታቷቸዋል። በእርግጥም ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በትጋት እንዲያከናውኑ ይፈልግ ነበር! ደግሞም በሥራቸው እንዲሳካላቸው እንደሚረዳቸው የሚገልጽ ፍቅር የተንጸባረቀበት ማበረታቻ ሰጥቷቸዋል።​—⁠ማቴ. 28:​19, 20፤ w15 11/15 2:3, 5

ሰኞ፣ መስከረም 25

ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።​—⁠ማቴ. 22:​39

ፍቅር የይሖዋ አምላክ ዋነኛ ባሕርይ ነው። (1 ዮሐ. 4:​16) የመጀመሪያ የፍጥረት ሥራው ኢየሱስ ነው፤ እሱም ከአባቱ ጋር ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት በሰማይ ሲኖር ፍቅር ስለሚንጸባረቅባቸው የአምላክ መንገዶች ተምሯል። (ቆላ. 1:​15) ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈውን ጊዜ ጨምሮ መላ ሕይወቱ፣ ይሖዋ የፍቅር አምላክ መሆኑን እንደተገነዘበና በዚህ ረገድ እሱን እንደሚመስል ያሳያል። በመሆኑም የይሖዋና የኢየሱስ አገዛዝ ምንጊዜም ፍቅር የሚንጸባረቅበት እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ኢየሱስ ከሕጉ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው እንደሆነ ሲጠየቅ እንዲህ ብሏል፦ “‘አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።’ ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው። ሁለተኛውም ይህንኑ የሚመስል ሲሆን ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል።” (ማቴ. 22:​37-39) ኢየሱስ ይሖዋን ከመውደድ ቀጥሎ ሁለተኛውን ቦታ የሚይዘው ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር መሆኑን እንደገለጸ ልብ በል። ይህም ከሁሉም ሰው ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ፍቅር ማሳየት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያጎላ ነው። w15 11/15 4:1-3

ማክሰኞ፣ መስከረም 26

ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል።​—⁠ሮም 15:4

አምላክ ሐሳቡን ለሰው ልጆች ለመግለጽ ከዕብራይስጥ በተጨማሪ በሌሎች ቋንቋዎች ተጠቅሟል። የአምላክ ሕዝቦች ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ የአንዳንዶቹ የዕለት ተዕለት ቋንቋ አረማይክ ሆነ። ይሖዋ አስቀድሞ ይህን ስለተገነዘበ ሳይሆን አይቀርም፣ ነቢዩ ዳንኤልና ነቢዩ ኤርምያስ እንዲሁም ካህኑ ዕዝራ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ዘገባዎቻቸው ውስጥ የተወሰኑትን ክፍሎች በአረማይክ እንዲጽፉ በመንፈሱ መርቷቸዋል። ከጊዜ በኋላ ታላቁ እስክንድር ከጥንቱ ዓለም አብዛኛውን በቁጥጥሩ ሥር ሲያደርግ ኮይኔ ወይም የጋራ መግባቢያ የነበረው ግሪክኛ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ሆነ። በርካታ አይሁዳውያን ይህን ቋንቋ መናገር ጀመሩ፤ በዚህ የተነሳ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ወደ ግሪክኛ ተተረጎሙ። በ72 ተርጓሚዎች እንደተዘጋጀ የሚታሰበው ይህ ትርጉም ሰብዓ ሊቃናት (ሴፕቱጀንት) በመባል ይታወቃል። ሰብዓ ሊቃናት የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሲሆን ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ትርጉሞች አንዱ ነው። በሥራው የተካፈሉት ተርጓሚዎች ብዙ በመሆናቸው የተጠቀሙበት የአተረጓጎም ስልትም የተለያየ ነው፤ አንዳንዶቹ ቃል በቃል ሲተረጉሙ ሌሎቹ ግን እንዲህ አላደረጉም። ያም ቢሆን ግሪክኛ ተናጋሪ አይሁዳውያን፣ በኋላ ላይ ደግሞ ክርስቲያኖች ሰብዓ ሊቃናትን እንደ አምላክ ቃል አድርገው ተቀብለውታል። w15 12/15 1:4-6

ረቡዕ፣ መስከረም 27

በጣም ሰፊ የሆነን ጫካ በእሳት ለማያያዝ ትንሽ እሳት ብቻ ይበቃል!​—⁠ያዕ. 3:5

ያዕቆብ በዚህ ምሳሌ ላይ ሊያጎላው የፈለገውን ነጥብ ቁጥር 6 ላይ ግልጽ አድርጎታል። ጥቅሱ “ምላስም እሳት ናት” ይላል። ምላስ የሚለው ቃል የመናገር ችሎታችንን ያመለክታል። እንደ እሳት ሁሉ ንግግራችንም ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “አንደበት የሞትና የሕይወት ኃይል አላት” ይላል። (ምሳሌ 18:​21) እርግጥ ነው፣ እሳት የሚያስከትለውን ጉዳት በመፍራት በእሳት መጠቀማችንን እንደማናቆም ሁሉ፣ ጎጂ ነገር እንዳንናገር በመስጋት መናገራችንን እስከ ጭራሹ አናቆምም። ቁልፉ አንደበታችንን መቆጣጠር መቻላችን ላይ ነው። እሳትን በተገቢው መንገድ የምንጠቀምበት ከሆነ ምግባችንን ለማብሰልና ሰውነታችንን ለማሞቅ ሊያገለግለን እንዲሁም ብርሃን ሊሰጠን ይችላል። ምላሳችንንም ከገራነው አምላክን በሚያስከብርና ሌሎችን በሚጠቅም መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን። (መዝ. 19:​14) ድምፅ አውጥተን በመናገርም ይሁን በእጃችን ምልክት በመስጠት ሐሳባችንንና ስሜታችንን የመግለጽ ችሎታ ከአምላክ ያገኘነው ድንቅ ስጦታ ነው። ይሁንና ይህን ስጦታ፣ ለማፍረስ ሳይሆን ለማነጽ ልንጠቀምበት ይገባል።​—⁠ያዕ. 3:9, 10፤ w15 12/15 3:1-3

ሐሙስ፣ መስከረም 28

የተወደደው ሐኪም ሉቃስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል።​—⁠ቆላ. 4:​14

ሉቃስ ለጳውሎስ ከጤና ጋር የተያያዘ ምክር ሰጥቶት ሊሆን እንደሚችል እንዲሁም ለጳውሎስም ሆነ በሚስዮናዊ አገልግሎቱ ወቅት አብረውት ለተጓዙት ሌሎች ሰዎች የሕክምና እርዳታ አድርጎላቸው እንደሚሆን ማሰቡ ምክንያታዊ ነው። ሉቃስ እንዲህ ማድረግ ያስፈለገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ጳውሎስም እንኳ በጉዞው ላይ እያለ ታሞ ነበር። (ገላ. 4:​13) ኢየሱስ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም” ብሎ ከተናገረው ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ ሉቃስም በዚህ ወቅት የሕክምና እርዳታ መስጠት ይችል ነበር። (ሉቃስ 5:​31) ሉቃስ የሕክምና ሥልጠና ያገኘው የት ወይም መቼ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ሲጽፍ ሉቃስ የሕክምና ባለሙያ መሆኑን የጠቀሰው ሉቃስን ስለሚያውቁት ሊሆን ይችላል ተብሎ ይታሰባል። በቆላስይስ አቅራቢያ ባለችው በሎዶቅያ የሕክምና ትምህርት ቤት ነበረ። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ ሉቃስ የሕክምና ባለሙያ እንጂ የሕክምና ችሎታ ሳይኖረው ጤና ነክ ምክር የሚሰጥ ሰው አልነበረም። ሉቃስ የወንጌል ዘገባውንና የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ሲጽፍ የተጠቀመባቸው የሕክምና ቃላት እንዲሁም ኢየሱስ የፈወሳቸው ሰዎች ላለባቸው ሕመም ትኩረት መስጠቱ ይህን ይጠቁማሉ። w15 12/15 4:11, 12

ዓርብ፣ መስከረም 29

በቃላት ሊገለጽ ለማይችለው ነፃ ስጦታው አምላክ የተመሰገነ ይሁን።​—⁠2 ቆሮ. 9:​15

ይሖዋ፣ አንድያ ልጁን ወደ ምድር በመላክ ከሁሉ የላቀውን ስጦታ በፍቅር ተነሳስቶ ሰጥቶናል! (ዮሐ. 3:​16፤ 1 ዮሐ. 4:9, 10) ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን የአምላክ ስጦታ “በቃላት ሊገለጽ [የማይችል] ነፃ ስጦታ” በማለት ገልጾታል። ጳውሎስ፣ አምላክ ቃል የገባቸው አስደናቂ ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጸሙ ዋስትና የሚሆነው የክርስቶስ ፍጹም መሥዋዕት እንደሆነ ስለሚያውቅ ነው። (2 ቆሮ. 1:​20) ‘በቃላት ሊገለጽ የማይችለው ይህ ነፃ ስጦታ’ ይሖዋ በኢየሱስ በኩል የሚያደርግልንን መልካም ነገሮች በሙሉ እንዲሁም የሚያሳየንን ታማኝ ፍቅር ያካትታል። በእርግጥም ስጦታው እጅግ አስደናቂ በመሆኑ የሰው ልጆች ሙሉ በሙሉ በሚረዱት መንገድ መግለጽ አስቸጋሪ ነው። እንዲህ ያለ ልዩ ስጦታ በመቀበላችን ምን ሊሰማን ይገባል? ደግሞስ ከይሖዋ ያገኘነው ስጦታ ምን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል? አኗኗርህን መለስ ብለህ እንድታጤንና ሕይወትህን የምትመራበትን መንገድ እንድትቀይር ያነሳሳህ ይሆን? ይበልጥ ለጋስና አፍቃሪ እንድትሆን እንዲሁም የበደሉህን ይቅር እንድትል ያነሳሳህ ይሆን? ይሖዋ በክርስቶስ አማካኝነት የሰጠን ስጦታ ከየትኛውም ስጦታ በእጅጉ የላቀ ነው።​—⁠1 ጴጥ. 3:​18፤ w16.01 2:1, 2, 4, 5

ቅዳሜ፣ መስከረም 30

ነፋስ ወደፈለገው አቅጣጫ ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ሆኖም ከየት እንደሚመጣና ወዴት እንደሚሄድ አታውቅም። ከመንፈስ የተወለደም ሁሉ እንደዚሁ ነው።​—⁠ዮሐ. 3:8

በዚህ መንገድ ጥሪ የተደረገላቸው ክርስቲያኖች ‘እኔ የተመረጥኩት ለምንድን ነው? ሌሎች ሳይመረጡ እንዴት እኔ ተመረጥኩ?’ የሚል ጥያቄ ይፈጠርባቸው ይሆናል። እንዲያውም ይህን ጥሪ ማግኘት ይገባቸው እንደሆነ ይጠራጠሩ ይሆናል። ይሁንና መጠራታቸውን ፈጽሞ አይጠራጠሩም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ያለ ስጦታ በማግኘታቸው ልባቸው በደስታና በአድናቆት ይሞላል። ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት የሚከተለውን ሐሳብ ሲያሰፍር የነበረው ዓይነት ስሜት አላቸው፦ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይወደስ፤ እሱ በታላቅ ምሕረቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት ለሕያው ተስፋ እንደ አዲስ ወልዶናልና፤ እንዲሁም ለማይበሰብስ፣ ለማይረክስና ለማይጠፋ ርስት ወልዶናል። ይህም በሰማይ ለእናንተ ተጠብቆላችኋል።” (1 ጴጥ. 1:3, 4) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይህን ጥቅስ ሲያነቡ በሰማይ ያለው አባታቸው በግለሰብ ደረጃ እያናገራቸው እንደሆነ ቅንጣት ታክል አይጠራጠሩም። w16.01 3:11, 12

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ