የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es17 ገጽ 98-108
  • ጥቅምት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥቅምት
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2017
  • ንዑስ ርዕሶች
  • እሁድ፣ ጥቅምት 1
  • ሰኞ፣ ጥቅምት 2
  • ማክሰኞ፣ ጥቅምት 3
  • ረቡዕ፣ ጥቅምት 4
  • ሐሙስ፣ ጥቅምት 5
  • ዓርብ፣ ጥቅምት 6
  • ቅዳሜ፣ ጥቅምት 7
  • እሁድ፣ ጥቅምት 8
  • ሰኞ፣ ጥቅምት 9
  • ማክሰኞ፣ ጥቅምት 10
  • ረቡዕ፣ ጥቅምት 11
  • ሐሙስ፣ ጥቅምት 12
  • ዓርብ፣ ጥቅምት 13
  • ቅዳሜ፣ ጥቅምት 14
  • እሁድ፣ ጥቅምት 15
  • ሰኞ፣ ጥቅምት 16
  • ማክሰኞ፣ ጥቅምት 17
  • ረቡዕ፣ ጥቅምት 18
  • ሐሙስ፣ ጥቅምት 19
  • ዓርብ፣ ጥቅምት 20
  • ቅዳሜ፣ ጥቅምት 21
  • እሁድ፣ ጥቅምት 22
  • ሰኞ፣ ጥቅምት 23
  • ማክሰኞ፣ ጥቅምት 24
  • ረቡዕ፣ ጥቅምት 25
  • ሐሙስ፣ ጥቅምት 26
  • ዓርብ፣ ጥቅምት 27
  • ቅዳሜ፣ ጥቅምት 28
  • እሁድ፣ ጥቅምት 29
  • ሰኞ፣ ጥቅምት 30
  • ማክሰኞ፣ ጥቅምት 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2017
es17 ገጽ 98-108

ጥቅምት

እሁድ፣ ጥቅምት 1

አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህን ጠራቸው።​—⁠ሮም 8:​30

ይሖዋ ቅቡዓንን መምረጥ የጀመረው ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ነው፤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ አባላት በሙሉ ቅቡዓን ሳይሆኑ አይቀሩም። ከመጀመሪያው መቶ ዘመን በኋላ እስከ መጨረሻዎቹ ቀናት መባቻ ባለው ጊዜ ውስጥ፣ የክርስቶስ ተከታዮች ነን ይሉ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ነበሩ፤ ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች ‘ከእንክርዳድ’ ጋር አመሳስሏቸዋል። ያም ሆኖ ይሖዋ በዚያ ጊዜ ውስጥ ታማኝ የሆኑ አንዳንዶችን መቀባቱን የቀጠለ ሲሆን እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ እንደጠቀሰው “ስንዴ” ሆነው ተገኝተዋል። (ማቴ. 13:​24-30) በመጨረሻዎቹ ቀናትም ይሖዋ የ144,000ዎቹን አባላት መቀባቱን ቀጥሏል። ይሖዋ ለዚህ መብት ብቁ የሚሆኑ አንዳንድ ሰዎችን ለመምረጥ እስከ መጨረሻዎቹ ቀናት መገባደጃ ለመቆየት ከፈለገ በእሱ ጥበብ ላይ ጥያቄ ለማንሳት እኛ ማን ነን? (ኢሳ. 45:9፤ ዳን. 4:​35፤ ሮም 9:​11, 16) በ11ኛው ሰዓት ለተቀጠሩት ሠራተኞች ጌታው ባደረገው ነገር ቅር ተሰኝተው እንዳጉረመረሙት ሰዎች እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን።​—⁠ማቴ. 20:8-15፤ w16.01 4:15

ሰኞ፣ ጥቅምት 2

እባክህ ልጅህን፣ በጣም የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ በዚያም እኔ በማሳይህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መባ አድርገህ አቅርበው።​—⁠ዘፍ. 22:2

በዛሬው ጊዜ አምላክ እንዲህ ያለ ጥያቄ አያቀርብልንም። ሆኖም ትእዛዛቱን መፈጸም ከባድ በሚሆንብን ወይም አንድ ዓይነት መመሪያ የተሰጠበትን ምክንያት ሙሉ በሙሉ በማንረዳበት ጊዜም እንኳ እንድንታዘዘው ይጠብቅብናል። ከአምላክ ትእዛዛት መካከል ለመታዘዝ የሚከብድህ አለ? አንዳንዶች የስብከቱ ሥራ ከባድ ይሆንባቸዋል። ዓይናፋር በመሆናቸው ለማያውቁት ሰው ምሥራቹን መንገር ይጨንቃቸው ይሆናል። ሌሎች ደግሞ በትምህርት ቤት አሊያም በሥራ ቦታ አብረዋቸው ካሉት ሰዎች የተለዩ መሆን ተፈታታኝ ሊሆንባቸው ይችላል። (ዘፀ. 23:2፤ 1 ተሰ. 2:⁠2) አንተም ልክ እንደ አብርሃም የሞሪያን ተራራ እየወጣህ ያለ ያህል፣ የተሰጠህ ሥራ ከአቅምህ በላይ እንደሆነ ይሰማሃል? ከሆነ ስለ አብርሃምና ስላሳየው እምነት ማሰብህ ደፋር እንድትሆን ይረዳሃል! ታማኝ ወንዶችና ሴቶች በተዉት ምሳሌ ላይ ማሰላሰላችን እነሱን ለመምሰልና ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖረን ለማድረግ ያነሳሳናል።​—⁠ዕብ. 12:1, 2፤ w16.02 1:3, 14

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 3

ሳኦል፣ ዳዊት እንዲገደል ማሰቡን ለልጁ ለዮናታንና ለአገልጋዮቹ በሙሉ ነገራቸው።​—⁠1 ሳሙ. 19:1

ሳኦል ዳዊትን ለመግደል ቆርጦ ስለተነሳ ዮናታን ለማን ታማኝ መሆን እንዳለበት ግራ ተጋብቶ ነበር። ዮናታን ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን የተጋባ ቢሆንም ለአባቱም ታዛዥ ነበር። ሆኖም ዮናታን፣ አምላክ ከዳዊት እንጂ ከሳኦል ጋር እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። በመሆኑም ዮናታን ከሳኦል ይበልጥ ለዳዊት ታማኝ ሆኗል። ዳዊትን እንዲደበቅ ካስጠነቀቀው በኋላ ስለ እሱ ለአባቱ መልካም ነገር ተናግሯል። (1 ሳሙ. 19:1-6) እኛም ካልተጠነቀቅን ለአንድ አገር፣ ትምህርት ቤት ወይም የስፖርት ቡድን ያለን ታማኝነት ቀስ በቀስ ለአምላክ ካለን ታማኝነት ሊበልጥብን ይችላል። ቼዝ መጫወት ይወድ የነበረውን የሄንሪን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ትምህርት ቤቱ በቼዝ ውድድር ሁልጊዜ ያሸንፍ ስለነበር እሱም ለማሸነፍ የተቻለውን ጥረት ማድረግ እንዳለበት ይሰማው ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ለትምህርት ቤቴ የማሳየው ታማኝነት ለአምላክ ከማሳየው ታማኝነት ቀስ በቀስ እየበለጠ ሄደ። ቅዳሜና እሁድ የሚደረጉት የቼዝ ጨዋታዎች ለመንግሥቱ አገልግሎት የማውለውን ጊዜ እየተሻሙብኝ መጡ። በመሆኑም ከቼዝ ቡድኑ ለመውጣት ወሰንኩ።”​—⁠ማቴ. 6:​33፤ w16.02 3:10, 12

ረቡዕ፣ ጥቅምት 4

ሕዝብህ በገዛ ፈቃዱ ራሱን ያቀርባል።​—⁠መዝ. 110:3

ወጣት እንደመሆንህ መጠን ለመጠመቅ ውሳኔ ያደረግከው ከልብህ ተነሳስተህ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ የምትችልባቸው መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ይሖዋን ለማገልገል ያለህ ልባዊ ፍላጎት በምታቀርበው ጸሎት ላይ ሊታይ ይችላል። በተደጋጋሚ መጸለይህና በጸሎትህ ላይ አንዳንድ ነገሮችን ለይተህ መጥቀስህ ከይሖዋ ጋር ምን ያህል የጠበቀ ዝምድና እንዳለህ ሊያሳይ ይችላል። (መዝ. 25:⁠4) ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጥበት አንዱ ወሳኝ መንገድ ቃሉ ላይ ትኩረት እንድናደርግ መርዳት ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የምናደርገው ጥረት ወደ ይሖዋ ለመቅረብና እሱን ከልብ ለማገልገል እንደምንፈልግ የሚታይበት ሌላ መንገድ ነው። (ኢያሱ 1:⁠8) ስለዚህ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘የሚያሳስቡኝን ነገሮች ለይቼ በመጥቀስ የመጸለይ ልማድ አለኝ? በግሌ መጽሐፍ ቅዱስን የማጠናበት ቋሚ ፕሮግራም አለኝ?’ ቤተሰብህ፣ የቤተሰብ አምልኮ የሚያደርግ ከሆነ ደግሞ ‘ቤተሰባችን በሚያደርገው በዚህ ፕሮግራም ላይ በደስታ እሳተፋለሁ?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ ለመጠመቅ የወሰንከው በራስህ ፍላጎት ተነሳስተህ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ይረዳሃል። w16.03 1:11, 13

ሐሙስ፣ ጥቅምት 5

በእሱ አማካኝነት የአካል ክፍሎች ሁሉ . . . እርስ በርስ ተስማምተው ተገጣጥመዋል።​—⁠ኤፌ. 4:​16

የምናከናውነው ሥራ ያለውን ድምር ውጤት በዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ላይ ማንበብ ምንኛ ያስደስታል! በተጨማሪም በክልል፣ በብሔራት አቀፍ ስብሰባ እንዲሁም በልዩ የክልል ስብሰባ ላይ የሚኖረንን አንድነት ለማሰብ ሞክር። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ስሜት የሚቀሰቅሱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮች የምናዳምጥ ከመሆኑም ባሻገር ድራማዎችና ሠርቶ ማሳያዎች እንመለከታለን። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ክፍሎች አምላክ በሙሉ ነፍሳችን እንድናገለግለው ያቀረበልንን ፍቅራዊ ግብዣ ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓልም በመካከላችን አንድነት እንዲኖር ያደርጋል። ለአምላክ ጸጋ አድናቆት ስላለን እንዲሁም ለኢየሱስ መመሪያ ታዛዥ ስለሆንን ኒሳን 14 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ሁላችንም ይህን ዓመታዊ በዓል ለማክበር እንሰበሰባለን። (1 ቆሮ. 11:​23-26) በተጨማሪም የመታሰቢያው በዓል ከሚከበርበት ቀን በፊት ባሉት ሳምንታት የቻልነውን ያህል የጉባኤያችንን ክልል በመሸፈን ሌሎችም ትልቅ ቦታ በሚሰጠው በዚህ በዓል ላይ አብረውን እንዲገኙ እንጋብዛለን። በግለሰብ ደረጃ የምናደርገው ጥረት እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ያለው ላይመስል ይችላል። በኅብረት ስንሠራ ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ውዳሴና ክብር ለሚገባው ለይሖዋ ትኩረት እንዲሰጡ እናደርጋለን! w16.03 3:4, 6, 7

ዓርብ፣ ጥቅምት 6

በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው።​—⁠ማቴ. 3:​17

በጉባኤ ውስጥ ለማገልገል እየሠለጠኑ ያሉ ወንድሞች ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር እንዲያስቡ መማር ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሽማግሌ የመንግሥት አዳራሹን መግቢያ ለእይታ ማራኪ እንዲያደርግና እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን ከአካባቢው እንዲያስወግድ አንድን ወንድም ይጠይቀዋል። በዚህ ጊዜ ቲቶ 2:​10ን በመጥቀስ ወንድም በመንግሥት አዳራሹ የተሰጠውን ይህን ኃላፊነት መወጣቱ “አዳኛችን የሆነው አምላክ ትምህርት በሁሉም መንገድ ውበት እንዲጎናጸፍ” የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ ይገልጽለታል። በተጨማሪም ተማሪው የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣቱ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን አረጋውያን የሚጠቅመው እንዴት እንደሆነ ሊነግረው ይችላል። ከተማሪው ጋር እንዲህ ያለ ውይይት ማድረጉ ሕግ በመፈጸም ላይ ሳይሆን ለሰዎች በማሰብ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ያሠለጥነዋል። እሱ የሚያከናውነው አገልግሎት በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችንና እህቶችን ምን ያህል እየጠቀማቸው እንደሆነ ሲመለከት ይደሰታል። በተጨማሪም ሽማግሌው ተማሪው የተሰጠውን ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ሲጥር ማመስገን እንዳለበት መርሳት አይኖርበትም። አንድ አትክልት ውኃ ማግኘቱ እንዲለመልም እንደሚያደርገው ሁሉ ተማሪውም ልባዊ ምስጋና ማግኘቱ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ይረዳዋል። w15 4/15 2:7, 8

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 7

ጌታ ከክፉ ሥራ ሁሉ ይታደገኛል።​—⁠2 ጢሞ. 4:​18

አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ባጋጠሙህ ጊዜ ማንም የሚረዳህ እንደሌለ ተሰምቶህ ያውቃል? ሥራ አጥተህ ወይም በትምህርት ቤት ተጽዕኖ ደርሶብህ አሊያም የጤና እክል ወይም ሌላ የሚያስጨንቅ ሁኔታ አጋጥሞህ ይሆናል። ምናልባትም እርዳታ ጠይቀህ ሌሎች የሚያስፈልግህን ድጋፍ ሊሰጡህ ባለመቻላቸው አዝነህ ይሆናል። ለነገሩ አንዳንድ ችግሮች ከሰው ልጆች አቅም በላይ ናቸው። ታዲያ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? መጽሐፍ ቅዱስ “በይሖዋ ታመን” የሚል ምክር ይሰጣል። (ምሳሌ 3:5, 6) ሆኖም ይሖዋ እንደሚረዳህ መተማመን ትችላለህ? እንዴታ! መለኮታዊ እርዳታ እንደምናገኝ እርግጠኞች መሆን እንደምንችል የሚያሳዩ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች አሉ። እንግዲያው ሰዎች ብዙም ስላልረዱህ ቅር ከመሰኘት ይልቅ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ አንተም እነዚህን ሁኔታዎች በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ ለመታመን እና የእሱን ፍቅራዊ እንክብካቤ ለማየት እንደሚያስችሉህ አጋጣሚዎች አድርገህ ተመልከታቸው። እንዲህ ማድረግህ በእሱ ይበልጥ እንድትተማመንና ከእሱ ጋር ያለህ ዝምድና እንዲጠናከር ያደርጋል። w15 4/15 4:3-5

እሁድ፣ ጥቅምት 8

የዚህ ሥርዓት አምላክ የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ አሳውሯል።​—⁠2 ቆሮ. 4:4

ሰዎች አፍቃሪ አምላክ ከሆነው ከይሖዋ የሚርቁት በሰይጣን ሲታለሉ ብቻ ነው። (1 ዮሐ. 4:⁠8) ሰይጣን የሚጠቀምበት ማታለያ ሰዎች “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ” እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል። (ማቴ. 5:3 የግርጌ ማስታወሻ) በዚህ መንገድ ሰይጣን፣ “የአምላክ አምሳል ስለሆነው ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውና ክብራማ የሆነው ምሥራች የሚፈነጥቀው ብርሃን በእነሱ ላይ እንዳያበራ . . . የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ አሳውሯል።” ሰይጣን በዋነኝነት ከሚጠቀምባቸው ማታለያዎች አንዱ የሐሰት ሃይማኖት ነው። ሰዎች የቀድሞ አባቶቻቸውን አሊያም የፍጥረት ሥራዎችን ወይም እንስሳትን በሌላ አባባል ‘እሱ ብቻ እንዲመለክ ከሚፈልገው’ ከይሖዋ ውጪ ማንኛውንም አካል ወይም ግዑዝ ነገር ሲያመልኩ ሰይጣን በጣም ይደሰታል። (ዘፀ. 20:⁠5) አምላክን በትክክለኛው መንገድ እያመለኩ እንዳሉ የሚሰማቸው ብዙ ሰዎች እንኳ በሐሰት እምነቶችና ትርጉም የለሽ በሆኑ የአምልኮ ሥርዓቶች ተተብትበዋል። ያሉበት አሳዛኝ ሁኔታ ይሖዋ እንደሚከተለው በማለት ከለመናቸው ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ነው፦ “እርካታ ለማያስገኝ ነገርስ ለምን ገቢያችሁን ታባክናላችሁ? እኔን በጥሞና አዳምጡ፤ . . . ምርጥ ምግብ በመብላትም ሐሴት ታደርጋላችሁ።”​—⁠ኢሳ. 55:2፤ w15 5/15 1:14, 15

ሰኞ፣ ጥቅምት 9

እሱ ራስህን ይጨፈልቃል፤ አንተም ተረከዙን ታቆስላለህ።​—⁠ዘፍ. 3:​15

አቤል በዚህ ተስፋ ላይ ብዙ ጊዜ አሰላስሎ እንዲሁም አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከመሥራታቸው በፊት የነበራቸው ዓይነት የፍጽምና ደረጃ ላይ የሰው ዘር መድረስ እንዲችል አንድ ሰው ‘ተረከዙ እንደሚቆስል’ ተገንዝቦ ሊሆን ይችላል። አቤል አምላክ የሰጠው ተስፋ እንደሚፈጸም እምነት ነበረው፤ በመሆኑም ይሖዋ መሥዋዕቱን ተቀብሎታል። (ዘፍ. 4:3-5፤ ዕብ. 11:⁠4) ኖኅ ከጥፋት ውኃው ሊተርፍ የቻለው እምነት ስለነበረው ነው። (ዕብ. 11:⁠7) ከጥፋት ውኃው በኋላም እምነቱ የእንስሳት መሥዋዕት እንዲያቀርብ አነሳስቶታል። (ዘፍ. 8:​20) እንደ አቤል ሁሉ ኖኅም፣ ውሎ አድሮ የሰው ልጅ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ እንደሚወጣ እምነት ነበረው። ከጥፋቱ በኋላ ናምሩድ በይሖዋ ላይ ባመፀበት ጊዜ በነበረው ብሩህ ነገር የማይታይበት ወቅትም እንኳ ኖኅ እምነቱንና ተስፋውን አላጣም። (ዘፍ. 10:8-12) ኖኅ፣ የሰው ዘር ከጨቋኝ አገዛዝ፣ ከወረሰው ኃጢአትና ከሞት ነፃ ስለሚወጣበት ጊዜ ማሰቡ ልቡን በደስታ እንደሚሞላው የታወቀ ነው። እኛም እንዲህ ያለውን አስደናቂ ጊዜ በዓይነ ሕሊናችን ማየት እንችላለን፤ ደግሞም ይህ ጊዜ በጣም ቀርቧል!​—⁠ሮም 6:​23፤ w15 5/15 3:4, 6

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 10

በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።​—⁠ምሳሌ 12:​25

የሚያስጨንቁንን ሐሳቦች ካልተቆጣጠርናቸው በአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ ጉዳት ሊያደርሱብን ይችላሉ። በመሆኑም በይሖዋ መታመን ይኖርብናል፤ እንዲሁም በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የተገለጸውን ሐሳብ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። ስሜታችንን የሚረዳልን ሰው የሚሰጠን ማበረታቻ ልባችን በደስታ እንዲሞላ ያደርጋል። ነገሮችን በአምላክ ዓይን መመልከት ለሚችል ሰው ለምሳሌ ለወላጆቻችን፣ ለትዳር ጓደኛችን ወይም ለምናምነው ወዳጃችን የውስጣችንን አውጥተን መናገራችን ጭንቀታችን እንዲቀለን ሊረዳን ይችላል። ከይሖዋ የበለጠ ጭንቀታችንን ሊረዳልን የሚችል ማንም የለም። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።” (ፊልጵ. 4:6, 7) እንግዲያው የሚያስጨንቅ ነገር ሲያጋጥመን ከመንፈሳዊ ጉዳት የሚጠብቁንን አካላት ይኸውም የእምነት ባልንጀሮቻችንን፣ ሽማግሌዎችን፣ ታማኙን ባሪያ፣ መላእክትን፣ ኢየሱስንና ይሖዋን ለማሰብ እንሞክር። w15 5/15 4:16, 17

ረቡዕ፣ ጥቅምት 11

በዚያም ለ38 ዓመት ሕመምተኛ ሆኖ የኖረ አንድ ሰው ነበር።​—⁠ዮሐ. 5:5

በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ቤተ መቅደስ በስተ ሰሜን ቤተዛታ የሚባል የውኃ ገንዳ ይገኛል። የታመሙ በርካታ ሰዎች በተአምር እንደሚፈወሱ ተስፋ በማድረግ በዚያ ይሰበሰቡ ነበር። ኢየሱስ፣ በርኅራኄ ስሜት ተገፋፍቶ እሱ በምድር ላይ ከኖረበት ለሚበልጡ ዓመታት ታሞ ወደ ቆየ አንድ ሰው ቀረበ። (ዮሐ. 5:6-9) ኢየሱስ፣ ሰውየውን መዳን ይፈልግ እንደሆነ ጠየቀው። ሰውየው ወዲያውኑ ምላሽ ሰጠው። ሕመምተኛው መዳን ቢፈልግም እንኳ ገንዳው ውስጥ ለመግባት የሚረዳው ሰው ስለሌለ ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ እንደገባው ገለጸ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ ሰውየውን ለማመን የሚከብድ ነገር እንዲያደርግ ይኸውም ምንጣፉን ተሸክሞ እንዲሄድ አዘዘው። ሰውየውም ኢየሱስ ያለውን በማመን ምንጣፉን አንስቶ መሄድ ጀመረ። ይህ ኢየሱስ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለሚያደርገው ነገር ናሙና የሚሆን እንዴት ያለ አስደሳች ድርጊት ነው! ይህ ተአምር ኢየሱስ ሩኅሩኅ መሆኑንም ያሳያል። እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ፈልጎ ያገኝ ነበር። የኢየሱስ ምሳሌ እኛም በክልላችን ውስጥ ያሉ በዚህ ዓለም በሚፈጸሙት መጥፎ ነገሮች ያዘኑ ሰዎችን መፈለጋችንን እንድንቀጥል ሊያነሳሳን ይገባል። w15 6/15 2:8-10

ሐሙስ፣ ጥቅምት 12

እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ።​—⁠ማቴ. 6:9

በጸሎት ናሙናው ላይ “አባቴ ሆይ” ሳይሆን “አባታችን ሆይ” መባሉ እርስ በርስ ከልብ በሚዋደድ “የወንድማማች ማኅበር” ውስጥ እንደታቀፍን ያስታውሰናል። (1 ጴጥ. 2:​17) ይህ እንዴት ያለ ውድ መብት ነው! አምላክ እንደ ልጆቹ አድርጎ የወሰዳቸውና ሰማያዊ ሕይወት የሚያገኙ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይሖዋን “አባት” ብለው የመጥራት ልዩ የሆነ መብት አላቸው። (ሮም 8:​15-17) በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም ቢሆኑ ይሖዋን “አባት” ብለው መጥራት ይችላሉ። ይሖዋ ሕይወት ሰጪያቸው ከመሆኑም ሌላ ለሁሉም እውነተኛ አምላኪዎቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በፍቅር ተነሳስቶ ያቀርብላቸዋል። ምድራዊ ተስፋ ያላቸው እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ፍጽምና ደረጃ ላይ ከደረሱና በመጨረሻው ፈተና ታማኝ መሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ “የአምላክ ልጆች” ተብለው ይጠራሉ። (ሮም 8:​21፤ ራእይ 20:7, 8) ወላጆች ልጆቻቸውን መጸለይ ሲያስተምሯቸውና ይሖዋን እንደ አፍቃሪ ሰማያዊ አባታቸው አድርገው እንዲመለከቱት ሲረዷቸው ትልቅ ስጦታ እየሰጧቸው ነው። ወላጆች፣ ለልጆቻቸው ሊሰጧቸው ከሚችሉት ስጦታ ሁሉ የላቀው ከይሖዋ ጋር የቀረበና የጠበቀ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ መርዳት ነው። w15 6/15 4:4-6

ዓርብ፣ ጥቅምት 13

ከክፉው አድነን።​—⁠ማቴ. 6:​13

“ከክፉው አድነን” ከሚለው ልመና ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ከፈለግን፣ የሰይጣን ‘ዓለም ክፍል ላለመሆን’ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፤ እንዲሁም የሰይጣንን ‘ዓለምም ሆነ በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች መውደድ’ የለብንም። (ዮሐ. 15:​19፤ 1 ዮሐ. 2:​15-17) ይህን ለማድረግ ቀጣይነት ያለው ትግል ይጠይቃል። ይሖዋ፣ ሰይጣንንም ሆነ የእሱን ክፉ ዓለም በማጥፋት ለዚህ ልመና ምላሽ ሲሰጠን እንዴት ያለ እፎይታ እናገኛለን! ይሁንና ሰይጣን ከሰማይ ሲወረወር፣ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው አውቆ እንደነበር ማስታወስ አለብን። በቁጣ የተሞላው ሰይጣን ንጹሕ አቋማችንን እንድናጎድፍ ለማድረግ የተቻለውን ያህል ይፍጨረጨራል። እንግዲያው ይሖዋ ከእሱ እንዲያድነን ሁልጊዜ መጸለይ ይኖርብናል። (ራእይ 12:​12, 17) እንዲህ ባለው አስደሳች ጊዜ መኖር ትፈልጋለህ? እንግዲያው የአምላክ መንግሥት፣ የእሱን ስም እንዲያስቀድስና ፈቃዱን በምድር ላይ እንዲፈጽም መጸለይህን ቀጥል። መንፈሳዊና ቁሳዊ ፍላጎትህን እንዲያሟላልህ ይሖዋን ጠይቀው። አዎን፣ ከጸሎት ናሙናው ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።​—⁠ማቴ. 6:9-13፤ w15 6/15 5:12, 17, 18

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 14

ታላቅ መከራ ይከሰታል።​—⁠ማቴ. 24:​21

በዚያ የፈተና ወቅት የሚፈጸሙትን ሁሉንም ነገሮች ሙሉ በሙሉ ባንረዳም እንኳ በተወሰነ መጠን መሥዋዕት የሚያስከፍለን ነገር እንደሚኖር እንጠብቃለን። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ ንብረታቸውን ትተው መሄድ እንዲሁም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ መኖር አስፈልጓቸው ነበር። (ማር. 13:​15-18) እኛስ ታማኝነታችንን ለመጠበቅ ስንል ቁሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች እንሆናለን? ለይሖዋ ታማኝ መሆናችንን ለማሳየት ስንል የሚጠበቅብንን ነገር ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንሆናለን? እስቲ አስበው! በጥንት ጊዜ የነበረውን የዳንኤልን ምሳሌ በመከተል፣ ምንም መጣ ምን በዚያ ጊዜ አምላካችንን ማገልገላችንን የምንቀጥለው እኛ ብቻ እንሆናለን። (ዳን. 6:​10, 11) ይህ ጊዜ “የመንግሥቱ ምሥራች” የሚሰበክበት አይደለም። በዚህ ወቅት ምሥራቹን የምንሰብክበት ጊዜ አልፏል። “መጨረሻው” በቅርቡ ይመጣል! (ማቴ. 24:​14) የአምላክ ሕዝቦች ኃይለኛ የሆነ የፍርድ መልእክት እንደሚያውጁ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ መልእክት የሰይጣን ክፉ ዓለም ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ እንደሆነ ማወጅን ይጨምር ይሆናል። w15 7/15 2:3, 8, 9

እሁድ፣ ጥቅምት 15

እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም።​—⁠ዮሐ. 17:​16

ዓለም ባለን የገለልተኝነት አቋም የተነሳ ቢጠላን መገረም አይኖርብንም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ይህ እንደሚሆን አስጠንቅቆናል። አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች ከክርስቲያናዊ ገለልተኝነት ጋር የተያያዙት ጉዳዮች ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንዳላቸው አይገነዘቡም። እኛ ግን ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ጉዳይ ነው። ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ከፈለግን ዛቻ ቢሰነዘርብንም መጽናት ይኖርብናል። (ዳን. 3:​16-18) የሰው ፍርሃት በሁሉም ዕድሜ ባሉ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ቢሆንም በተለይ ታዳጊዎች ከሌሎች የተለዩ መሆን ይከብዳቸው ይሆናል። ልጆቻችሁ ለባንዲራ ሰላምታ ከመስጠት ወይም ከብሔራዊ በዓላት ጋር በተያያዘ አቋማቸውን የሚፈትን ሁኔታ እያጋጠማቸው ከሆነ እርዳታ ልታደርጉላቸው ይገባል። ልጆቻችሁ ጉዳዩ ምን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነ እንዲገነዘቡ በቤተሰብ አምልኳችሁ ወቅት ለመርዳት ጥረት አድርጉ፤ ይህም የሚያጋጥማቸውን ፈተና በድፍረት ለመወጣት ያስችላቸዋል። የሚያምኑበትን ነገር በግልጽና አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ እንዲናገሩ እርዷቸው። (ሮም 1:​16) አስፈላጊ ከሆነ ከመምህሮቻቸው ጋር ስለ እነዚህ ጉዳዮች ተነጋገሩ። w15 7/15 3:15, 16

ሰኞ፣ ጥቅምት 16

አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ . . . አንድያ ልጁን ሰጥቷል።​—⁠ዮሐ. 3:​16

አምላክ በጸጋው የሰጠን የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት “ሕይወት ማግኘት እንድንችል” መንገድ ከፍቶልናል። (1 ዮሐ. 4:⁠9) ሐዋርያው ጳውሎስ ከሁሉ የላቀውን ይህን የአምላክ ፍቅር መግለጫ አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ክርስቶስ አስቀድሞ የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ለኃጢአተኞች ሞቷልና። ለጻድቅ ሰው የሚሞት ማግኘት በጣም አዳጋች ነው፤ ለጥሩ ሰው ለመሞት የሚደፍር ግን ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ሆኖም አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ እንዲሞትልን በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል።” (ሮም 5:6-8) ይህ ታላቅ የአምላክ ፍቅር መገለጫ፣ መላው የሰው ዘር በይሖዋ ፊት ሞገስ እንዲያገኝ አጋጣሚ ከፍቷል። ይሖዋ ለመላው የሰው ዘር ያለውን ፍቅር በቤዛው አማካኝነት አሳይቷል። በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የምናደርግ እንዲሁም ይሖዋን ምንጊዜም በታማኝነት የምናገለግል ከሆነ በአዲሱ ዓለም አስደሳች ሕይወት እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንግዲያው የቤዛውን ዝግጅት፣ ከሁሉ የላቀ የአምላክ ጽኑ ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አድርገን መመልከታችን ምንኛ የተገባ ነው! w15 8/15 1:13, 15

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 17

አትዘኑ።​—⁠ነህ. 8:​10

በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር የመኖር መብት ለማግኘት ስንል ከይሖዋ ድርጅት ጋር ለመተባበርና ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶችን ለመወጣት ማንኛውንም ጥረት ብናደርግ የሚያስቆጭ አይሆንም። እርግጥ ነው፣ ያለንበት ሁኔታ ሊለወጥ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ የዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል ቤተሰብ አባላት መስክ ላይ እንዲያገለግሉ ተመድበዋል፤ አሁን በሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች እየተካፈሉ በመሆናቸው የተትረፈረፈ በረከት አግኝተዋል። ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆነው ያገለግሉ የነበሩ አንዳንድ ወንድሞች ደግሞ በዕድሜ መግፋት ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በአሁኑ ጊዜ ልዩ አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ ተመድበዋል። ባለን ነገር የምንረካ፣ የአምላክን እርዳታ ለማግኘት የምንጸልይና በእሱ አገልግሎት የቻልነውን ያህል ለማድረግ የምንጥር ከሆነ በዚህ አስጨናቂ ዘመንም ቢሆን ደስታና ብዙ በረከት ማግኘት እንችላለን። (ምሳሌ 10:​22) ወደፊትስ ምን ይጠብቀናል? በአዲሱ ዓለም ውስጥ መኖሪያችን እንዲሆን የምንመርጠው ቦታ ሊኖር ቢችልም ወደ ሌላ አካባቢ እንድንሄድ እንጠየቅ ይሆናል። በዚያን ጊዜ የምናገለግለው የትም ይሁን የት እንዲሁም የምንሠራው ሥራ ምንም ይሁን ምን በደስታ እየተፍለቀለቅን፣ በአመስጋኝነትና በእርካታ ስሜት ተሞልተን እንደምንኖር እርግጠኛ መሆን እንችላለን። w15 8/15 3:8

ረቡዕ፣ ጥቅምት 18

[ኖኅ] በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች መካከል . . . እንከን የሌለበት ሰው ነበር።​—⁠ዘፍ. 6:9

ኖኅ በክፋት በተሞላ ዓለም ውስጥ ይኖር ነበር፤ ሆኖም ኖኅ በዘመኑ የነበሩ ሰዎችን የቅርብ ጓደኞቹ አላደረገም። ኖኅ፣ ፈሪሃ አምላክ ከሌላቸው ሰዎች ጋር ፈጽሞ ወዳጅነት አልመሠረተም። እሱም ሆነ ሰባቱ የቤተሰቡ አባላት መርከብ መሥራትን ጨምሮ አምላክ የሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣት ላይ ትኩረት አድርገው ነበር። በተጨማሪም ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” ነበር። (2 ጴጥ. 2:⁠5) ኖኅ መስበኩ፣ መርከብ መሥራቱና ከቤተሰቡ ጋር የነበረው ቅርርብ አምላክ የሚደሰትባቸውን መልካም ነገሮች በማከናወን እንዲጠመድ አስችሎታል። በዚህም የተነሳ ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃው መትረፍ ችለዋል። በዛሬው ጊዜ ያለን በሙሉ የእነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች ዘሮች ነን፤ ታማኙ ኖኅ፣ ሚስቱ፣ ልጆቹና ሚስቶቻቸው ባለውለታችን ናቸው። በተመሳሳይም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ታማኝና ታዛዥ ክርስቲያኖች አምላካዊ ፍርሃት ከሌላቸው ሰዎች በመራቃቸው በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምና የአይሁድ ሥርዓት ሲጠፉ መትረፍ ችለዋል።​—⁠ሉቃስ 21:​20-22፤ w15 8/15 4:17, 18

ሐሙስ፣ ጥቅምት 19

ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ . . . ለጭፈራም ጊዜ አለው።​—⁠መክ. 3:4

ማንኛውም ዓይነት ጊዜ ማሳለፊያ ጠቃሚ እንዲሁም አእምሮንና ሰውነትን የሚያድስ ነው ማለት አይደለም፤ በተጨማሪም ረዘም ያለ ሰዓት በመዝናኛ ማጥፋት አሊያም ብዙ ጊዜ ለመዝናኛ መመደብ ጥሩ አይደለም። ሕሊናችን ገንቢ በሆነ መዝናኛ እንድንደሰትና ከመዝናኛ ጥቅም እንድናገኝ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “የሥጋ ሥራዎች” ብሎ ከሚጠራቸው አንዳንድ ምግባሮች እንድንርቅ ያስጠነቅቀናል። የሥጋ ሥራዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦ “የፆታ ብልግና፣ ርኩሰት፣ ዓይን ያወጣ ምግባር፣ ጣዖት አምልኮ፣ መናፍስታዊ ድርጊት፣ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ በቁጣ መገንፈል፣ ጭቅጭቅ፣ መከፋፈል፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ ሰካራምነት፣ መረን የለቀቀ ፈንጠዝያና እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው።” ጳውሎስ “እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽሙ የአምላክን መንግሥት አይወርሱም” ሲል ጽፏል። (ገላ. 5:​19-21) በመሆኑም ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው፦ ‘ሕሊናዬ ጠበኝነት፣ ከፍተኛ ፉክክር፣ ብሔራዊ ስሜት ወይም ጭካኔ ከሚንጸባረቅበት ስፖርት እንድርቅ ይገፋፋኛል? ደግሞስ የብልግና ምስሎች የሚታዩበት አሊያም ብልሹ ምግባርን፣ ስካርን ወይም መናፍስታዊ ድርጊትን እንደ ጥሩ ነገር አድርጎ የሚያቀርብ ፊልም ለማየት ስፈተን ያስጠነቅቀኛል?’ w15 9/15 2:11, 12

ዓርብ፣ ጥቅምት 20

ይሖዋ ሆይ፣ የሰው መንገድ በራሱ እጅ እንዳልሆነ በሚገባ አውቃለሁ። አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም።​—⁠ኤር. 10:​23

ሰዎች ያለ አምላክ እርዳታ ራሳቸውን በራሳቸው መምራት እንደማይችሉ እንዲሁም ይህን መሠረታዊ እውነት ችላ ማለት አሳዛኝ መዘዝ እንደሚያስከትል ከመጽሐፍ ቅዱስ መረዳት ችለናል። ይህ ለደህንነታችን ወሳኝ ነገር ነው። ሰላምና አንድነት ሊኖረን የሚችለው ለአምላክ ሥልጣን እውቅና የምንሰጥ ከሆነ ብቻ ነው። ይሖዋ ይህን አስፈላጊ እውነት ለእኛ መግለጡ ታላቅ ፍቅሩን የሚያሳይ አይደለም? አንድ አፍቃሪ አባት ልጆቹ ትርጉምና ዓላማ ያለው ሕይወት እንዲመሩ ስለሚፈልግ የእነሱ የወደፊት ሕይወት በጥልቅ ያሳስበዋል። የሚያሳዝነው ግን አብዛኞቹ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ አመለካከት የላቸውም፤ አሊያም ሕይወታቸውን የሚያሳልፉት ዘላቂ ጥቅም የሌላቸውን ግቦች በማሳደድ ነው። (መዝ. 90:​10) እኛ ግን የአምላክ ልጆች እንደመሆናችን መጠን ይሖዋ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ግሩም ተስፋ ስለሰጠን በእርግጥ እንደሚወደን ይሰማናል። ይህ ደግሞ እውነተኛ ትርጉምና ዓላማ ያለው ሕይወት እንድንመራ ያስችለናል። w15 9/15 4:10, 11

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 21

በእኔ ትእዛዝ ካልሆነ በቀር . . . ጠል ወይም ዝናብ አይኖርም!​—⁠1 ነገ. 17:1

በጥንት ጊዜ አምላክ፣ ከእስራኤላውያን ጋር በነበረው ግንኙነት ለሕዝቡ ያደረገውን ነገር ሰዎች የማየትና የመስማት አጋጣሚ ነበራቸው። ይሖዋ ሕዝቡን ከግብጽ በተአምር ያወጣቸው ከመሆኑም በላይ የተዋጓቸውን ነገሥታት ሁሉ አንድ በአንድ ድል እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። (ኢያሱ 9:3, 9, 10) የእስራኤላውያን ጠላቶች አምላክ ለእስራኤላውያን እየተዋጋላቸው እንደሆነ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ለሽንፈት ተዳርገዋል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ክፉው ንጉሥ አክዓብ የአምላክ እጅ ያከናወናቸውን ነገሮች ማየት የሚችልበት ሰፊ አጋጣሚ ነበረው። አክዓብ፣ ኤልያስ እሳት ከሰማይ ወርዶ መሥዋዕቱን እንዲበላው ያቀረበው ጸሎት መልስ ሲያገኝ ተመልክቷል። እንዲሁም ኤልያስ “ዝናቡ እንዳያግድህ ወደዚያ ውረድ!” በማለት ለአክዓብ የነገረው ነገር ይሖዋ በዚያ ጊዜ የተከሰተውን የድርቅ ወቅት እንዲያበቃ የሚያደርግ መሆኑን ይጠቁም ነበር። (1 ነገ. 18:​22-45) አክዓብ ግን እነዚህ ነገሮች ሁሉ ሲፈጸሙ ቢመለከትም የአምላክ ታላቅ ኃይል መግለጫ መሆናቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። ይህም ሆነ ሌሎች ምሳሌዎች አንድ ትልቅ ቁም ነገር ማለትም የይሖዋ እጅ የሚያከናውነውን ነገር ለማስተዋል ንቁ መሆን እንዳለብን ያስተምሩናል። w15 10/15 1:4, 5

እሁድ፣ ጥቅምት 22

ጻድቅ በእምነት ይኖራል።​—⁠ገላ. 3:​11

የአምላክን አመራር ከተከተልን ጥሩ ውጤት እንደምናገኝ ፈጽሞ መጠራጠር የለብንም። ሊረዳን በሚችለው አምላክ ላይ እምነት መጣላችን ወሳኝ ነገር ነው። ጳውሎስ፣ አምላክ “በእኛ ውስጥ ከሚሠራው ኃይሉ ጋር በሚስማማ ሁኔታ፣ ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ” እንደሚችል አስገንዝቦናል። (ኤፌ. 3:​20) የይሖዋ አገልጋዮች የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ይሁንና የአቅም ገደብ እንዳለባቸው ስለሚገነዘቡ ጥረታቸውን እንዲባርክላቸው ወደ ይሖዋ ዘወር ይላሉ። ታዲያ አምላካችን ከእኛ ጋር መሆኑ የሚያስደስት አይደለም? እኛስ እምነት እንዲጨመርልን የምናቀርበው ልመና መልስ እንደሚያገኝ መጠበቅ እንችላለን? መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ’ መልስ እንደምናገኝ ማረጋገጫ ይሰጠናል። (1 ዮሐ. 5:​14) ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደምንችለው ይሖዋ በእሱ ሙሉ በሙሉ በሚታመኑ ሰዎች ይደሰታል። ይሖዋ እምነት እንዲጨመርልን ለምናቀርበው ልመና መልስ የሚሰጥ በመሆኑ እምነታችን እጅግ እያደገ ሄዶ ‘ለአምላክ መንግሥት ብቁ ሆነን እንድንቆጠር ሊያደርገን’ ይችላል።​—⁠2 ተሰ. 1:3, 5፤ w15 10/15 2:16-18

ሰኞ፣ ጥቅምት 23

ቀስ በቀስ እንዳንወሰድ።​—⁠ዕብ. 2:1

በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማሰላሰል አንድ ሰው ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና እንዲደርስ ይረዳዋል። (ዕብ. 5:​14፤ 6:⁠1) ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ለማሰላሰል በቂ ጊዜ የማይሰጥ ሰው ጠንካራ እምነት ሊኖረው አይችልም። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ቀስ በቀስ የመወሰድ ወይም ከእውነት የመራቅ አደጋ ተደቅኖበታል። (ዕብ. 3:​12) ኢየሱስ የአምላክን ቃል “በመልካምና በጥሩ ልብ” የማንሰማ ወይም የማንቀበል ከሆነ ቃሉን ‘በውስጣችን ማኖር’ እንደማንችል ተናግሯል። ከዚህ ይልቅ ‘የዚህ ዓለም የኑሮ ጭንቀት፣ ሀብትና ሥጋዊ ደስታ ትኩረታችንን ሊከፋፍልብንና ለፍሬ እንዳንበቃ’ ሊያደርገን ይችላል። (ሉቃስ 8:​14, 15) በመሆኑም በአምላክ ቃል ላይ ዘወትር እናሰላስል። ይህ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸውን የይሖዋን ክብርና ባሕርይ ለማንጸባረቅ ያነሳሳናል። (2 ቆሮ. 3:​18) ደግሞስ ከዚህ የበለጠ ምን እንፈልጋለን? በአምላክ እውቀት ማደግና የእሱን ክብር ማንጸባረቅ መቻል ግሩም መብት ከመሆኑም ሌላ በሰማይ የሚኖረውን አፍቃሪ አባታችንን እንዴት መምሰል እንደምንችል በተማርን መጠን ክብሩን ማንጸባረቃችንን እንቀጥላለን።​—⁠መክ. 3:​11፤ w15 10/15 4:13, 14

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 24

ጥበብ ለአንተ መልካም እንደሆነ እወቅ። ጥበብን ብታገኝ የወደፊት ሕይወትህ የተሳካ ይሆናል።​—⁠ምሳሌ 24:​14

ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁ በመንፈሳዊ ጤናማ ሆነው እንዲቀጥሉ ትፈልጋላችሁ። አምላክም ልጆቻችሁን “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” እንድታሳድጓቸው ይፈልጋል። (ኤፌ. 6:⁠4) በመሆኑም አምላክ የሰጣችሁን ኃላፊነት ለመወጣት ቋሚ የሆነ መንፈሳዊ ፕሮግራም እንዲኖራችሁ አድርጉ። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ልጆቻችሁ ትምህርት መቅሰማቸው አስፈላጊ እንደሆነ ስለምታውቁና የመማር ፍቅር እንዲያዳብሩ ስለምትፈልጉ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ታደርጋላችሁ። በተመሳሳይም አፍቃሪ ወላጆች፣ ልጆቻቸው በጉባኤ ስብሰባዎችና በሌሎች መንፈሳዊ ፕሮግራሞች አማካኝነት ከሚቀርበው ‘የይሖዋ ተግሣጽ’ እንዲጠቀሙ ጥረት ያደርጋሉ። መለኮታዊ ትምህርት በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ልጆቻችሁ ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍቅር እንዲያድርባቸውና ጥበብን እንዲወዱ ለመርዳት ትጥራላችሁ። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዳደረገው ሁሉ እናንተም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁ የአምላክን ቃል የማስተማር ፍቅር እንዲያድርባቸውና በመስክ አገልግሎት ዘወትር እንዲካፈሉ በማገዝ በአገልግሎታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ መርዳት ትችላላችሁ። w15 11/15 2:6

ረቡዕ፣ ጥቅምት 25

የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስ ራስ ደግሞ አምላክ እንደሆነ እንድታውቁ እወዳለሁ።​—⁠1 ቆሮ. 11:3

አምላክ ከማንኛውም ዝግጅት ጋር በተያያዘ የራስነት ሥርዓት እንዲኖር አድርጓል፤ በዚህም የተነሳ ፍቅር በጣም አስፈላጊ ነው። ያም ሆኖ የራስነት ሥልጣን አምባገነናዊ በሆነ መንገድ ሊሠራበት አይገባም። ባል የሚስቱ ራስ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ሚስቱን ‘እንዲያከብራት’ ያዛል። (1 ጴጥ. 3:⁠7) ባሎች ለሚስቶቻቸው አክብሮት ማሳየት ከሚችሉባቸው መንገዶች አንዱ፣ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባትና በአንዳንድ ጉዳዮች ረገድ የእነሱን ምርጫ ማስቀደም ነው። ደግሞም የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደና ራሱን ለጉባኤው አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ እናንተም ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ።” (ኤፌ. 5:​25) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሕይወቱን ሳይቀር ሰጥቷል። አንድ ባል እንደ ኢየሱስ የራስነት ሥልጣኑን በፍቅር የሚጠቀምበት ከሆነ ሚስቱ እሱን መውደድና ማክበር እንዲሁም ለእሱ መገዛት ይበልጥ ቀላል ይሆንላታል።​—⁠ቲቶ 2:3-5፤ w15 11/15 4:6, 7

ሐሙስ፣ ጥቅምት 26

ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ አይሁዳውያን . . . ዕብራይስጥ ተናጋሪ በሆኑት አይሁዳውያን ላይ ቅሬታ ማሰማት ጀመሩ።​—⁠ሥራ 6:1

ክርስትና እየተስፋፋ ሲሄድ ክርስቲያኖች በአብዛኛው የሚነጋገሩት በግሪክኛ ነበር። እንዲያውም ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ያስተማረውንና ያደረገውን ነገር በተመለከተ በመንፈስ መሪነት ያሰፈሯቸው የወንጌል ዘገባዎች በስፋት የተሰራጩት በግሪክኛ ነው። በመሆኑም አብዛኞቹ ደቀ መዛሙርት የሚጠቀሙት በዕብራይስጥ ሳይሆን በግሪክኛ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፋቸው ደብዳቤዎችና በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ሌሎች መጻሕፍትም የተሰራጩት በግሪክኛ ነው። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች፣ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ሲጠቅሱ በአብዛኛው የሚጠቀሙት ሰብዓ ሊቃናትን መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ከዕብራይስጡ ጽሑፍ በተወሰነ መጠን የሚለዩት እነዚህ ጥቅሶች በአሁኑ ጊዜ፣ በመንፈስ መሪነት የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ሆነዋል። በመሆኑም ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች የትርጉም ሥራ በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ክፍል ሆነ፤ ይህም አምላክ አንዱን ባሕል ወይም ቋንቋ ከሌላው እንደማያበላልጥ ያሳያል።​—⁠ሥራ 10:​34፤ w15 12/15 1:8, 9

ዓርብ፣ ጥቅምት 27

ይሖዋ ሆይ፣ አፌ ምስጋናህን እንዲያውጅ ከንፈሮቼን ክፈት።​—⁠መዝ. 51:​15

መናገር፣ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ክፍል ቢሆንም ሁልጊዜ ማውራት አለብን ማለት አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ዝም ለማለት ጊዜ አለው” ይላል። (መክ. 3:⁠7) ሌሎች ሲናገሩ ዝም ማለት አክብሮት እንዳለን ያሳያል። (ኢዮብ 6:​24) ሚስጥር ከሆኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አንደበታችንን በመቆጣጠር ዝም ማለታችን ደግሞ የማስተዋልና የማመዛዘን ችሎታ እንዳለን ይጠቁማል። (ምሳሌ 20:​19) የሚያስቆጣ ነገር ሲያጋጥመን አንደበታችንን መግታትም የጥበብ እርምጃ ነው። (መዝ. 4:⁠4) በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ “ለመናገርም ጊዜ አለው” ይላል። (መክ. 3:⁠7) አንድ ጓደኛህ የሚያምር ስጦታ ቢሰጥህ ማንም የማያየው ቦታ አታስቀምጠውም። ከዚህ ይልቅ በስጦታው በተገቢው መንገድ በመጠቀም አድናቆትህን ታሳያለህ። በተመሳሳይም ከይሖዋ ባገኘነው የመናገር ስጦታ በጥበብ በመጠቀም አመስጋኝነታችንን እናሳያለን። ይህም ስሜታችንን መግለጽን፣ የሚያስፈልገንን ነገር መናገርን፣ ሌሎችን ማበረታታትንና አምላክን ማወደስን ሊጨምር ይችላል። w15 12/15 3:4, 5

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 28

ከእንግዲህ ውኃ አትጠጣ፤ ከዚህ ይልቅ ለሆድህና በተደጋጋሚ ለሚነሳብህ ሕመም ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ።​—⁠1 ጢሞ. 5:​23

በዛሬው ጊዜ አንድ ክርስቲያን ‘በመፈወስ ስጦታ’ ተጠቅሞ ከሕመማችን ሊያድነን አይችልም። (1 ቆሮ. 12:⁠9) ይሁንና አንዳንድ ወንድሞች ምክር ባንጠይቃቸውም እንኳ በአሳቢነት ተነሳስተው ከጤና ጋር የተያያዙ አስተያየቶችን ይሰጣሉ። በእርግጥ አንዳንዶች የሚሰጡት ሐሳብ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ጢሞቴዎስ በአካባቢው ያለው ውኃ በመበከሉ የተነሳ ሳይሆን አይቀርም፣ ሆዱን ባመመው ጊዜ ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት ምክር ሰጥቶታል። ይህ ግን የእምነት ባልንጀራችን፣ አንዳንድ ዕፀዋትን ወይም መድኃኒቶችን እንዲወስድ አሊያም አንድን የአመጋገብ ሥርዓት እንዲከተል ለማሳመን ከመሞከር በጣም የተለየ ነው፤ ምናልባትም ይህ ዓይነቱ ሕክምና ውጤታማ ላይሆን እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የጤና ምክር የሚሰጡ ሰዎች ‘አንድ ዘመዴ እንዲህ ዓይነት ሕመም ነበረበት፤ . . . ሲወስድ ግን ተሻለው’ እንደሚለው ዓይነት ሐሳብ ሲሰነዝሩ ይሰማል። ምክሩ የተሰጠው በአሳቢነት ሊሆን ይችላል፤ ያም ቢሆን በሰፊው የሚሠራበት መድኃኒትም ሆነ የሕክምና ዓይነት እንኳ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ማስታወስ ይኖርብናል።​—⁠ምሳሌ 27:​12፤ w15 12/15 4:13

እሁድ፣ ጥቅምት 29

ጻድቅ የሆነው ክርስቶስ . . . ለዓመፀኞች ሲል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመሞት ከኃጢአት ነፃ አውጥቷቸዋል።​—⁠1 ጴጥ. 3:​18

በወረስነው ኃጢአት የተነሳ ሁላችንም የሞት ቅጣት ይጠብቀናል። (ሮም 5:​12) አፍቃሪ የሆነው ይሖዋ ግን ኢየሱስ ወደ ምድር እንዲመጣና “ለሰው ሁሉ ሲል ሞትን” እንዲቀምስ ዝግጅት አድርጓል። (ዕብ. 2:⁠9) ይሖዋ ይህን በማድረጉ ከሞት የታደገን ከመሆኑም ባሻገር ለሞት መንስኤ የሆነውን ነገር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የሚያስችለውን መሠረት ጥሏል። (ኢሳ. 25:7, 8፤ 1 ቆሮ. 15:​22, 26) በኢየሱስ ላይ እምነት ያላቸው ሁሉ በክርስቶስ በሚመራው የአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በምድር ላይ በሰላምና በደስታ ለዘላለም የሚኖሩ ሲሆን ቅቡዓኑ ደግሞ በዚህ መንግሥት ውስጥ ተባባሪ ገዢዎች ይሆናሉ። (ሮም 6:​23፤ ራእይ 5:9, 10) ይሖዋ የሰጠን ይህ ስጦታ የሚያስገኛቸው ሌሎች በረከቶችስ አሉ? ከይሖዋ ያገኘነው ስጦታ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል ማንኛውም በሽታ ሙሉ በሙሉ መወገዱ፣ ምድራችን ወደ ገነትነት መለወጧ እንዲሁም የሞቱ ሰዎች መነሳታቸው ይገኙበታል። (ኢሳ. 33:​24፤ 35:5, 6፤ ዮሐ. 5:​28, 29) ይሖዋና ውድ ልጁ ‘በቃላት ሊገለጽ የማይችል ነፃ ስጦታ’ ስለሰጡን እንደምንወዳቸው ጥያቄ የለውም።​—⁠2 ቆሮ. 9:​15፤ w16.01 2:5, 6

ሰኞ፣ ጥቅምት 30

ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ።​—⁠ዮሐ. 3:7

የተቀቡ ክርስቲያኖች የአምላክ መንፈስ በግለሰብ ደረጃ ሳይመሠክርላቸው በፊት፣ በምድር ላይ የመኖር ተስፋን ከፍ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ይሖዋ ይህችን ምድር የሚያጸዳበትን ጊዜ ለማየት ይጓጉ እንዲሁም በዚያ ከሚገኘው በረከት መካፈል ይፈልጉ ነበር። ምናልባትም በሞት የተለዩአቸው የሚወዷቸው ሰዎች ትንሣኤ ሲያገኙና እነሱን ሲቀበሉ በዓይነ ሕሊናቸው ያዩ ነበር። ራሳቸው በሠሩት ቤት ውስጥ ለመኖርና የተከሏቸውን ዛፎች ፍሬ ለመብላት ይጓጉ ነበር። (ኢሳ. 65:​21-23) ታዲያ አመለካከታቸው የተለወጠው ለምንድን ነው? በዚህ ተስፋ ስላልረኩ አይደለም። አስተሳሰባቸው የተለወጠው ጭንቀት ወይም መከራ ስለበዛባቸው አይደለም። በምድር ላይ ለዘላለም መኖር አሰልቺ እንደሆነና ደስታ እንደማያስገኝ ተሰምቷቸው በድንገት ሐሳባቸውን ስለቀየሩም አይደለም፤ አሊያም በሰማይ መኖር ምን ሊመስል እንደሚችል ለማወቅ ስለፈለጉ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አመለካከታቸው የተቀየረው የአምላክ መንፈስ ስለጠራቸው አልፎ ተርፎም አስተሳሰባቸውንና ተስፋቸውን ስለለወጠው ነው። w16.01 3:11, 13

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 31

ከእሱ ጋር አብረን የምንሠራ እንደመሆናችን መጠን የአምላክን ጸጋ ከተቀበላችሁ በኋላ ዓላማውን እንዳትስቱ እናሳስባችኋለን።​—⁠2 ቆሮ. 6:1

ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ነው፤ የሁሉም ነገር ፈጣሪ እንዲሁም ተወዳዳሪ የሌለው ጥበብና ኃይል ያለው አምላክ ነው። ኢዮብ ይህን እውነታ ተገንዝቧል። ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎቹን በተመለከተ ለኢዮብ ጥያቄ ካቀረበለት በኋላ ኢዮብ “አንተ ሁሉን ነገር ማድረግ እንደምትችል፣ ደግሞም ያሰብከውን ነገር ሁሉ ማድረግ እንደማይሳንህ አሁን አወቅኩ” በማለት መልሷል። (ኢዮብ 42:⁠2) ይሖዋ፣ ያሰበውን ለማከናወን የማንም እገዛ የማያስፈልገው ቢሆንም ዓላማውን ዳር በማድረስ ረገድ ሌሎችም አብረውት እንዲሠሩ ገና ከጅምሩ በመጋበዝ ፍቅሩን አሳይቷል። የአምላክ የመጀመሪያ ፍጥረት፣ መንፈሳዊ አካል የሆነው አንድያ ልጁ ነው። ይሖዋ ከዚያ በኋላ ሕይወት ያላቸውንና የሌላቸውን ነገሮች በሙሉ ሲፈጥር ልጁ አብሮት እንዲሠራ አድርጓል። (ዮሐ. 1:1-3, 18) በመሆኑም ይሖዋ አንድያ ልጁ በፍጥረት ሥራው እንዲካፈል በማድረግ እንዲሁም ኢየሱስ የተጫወተውን ቁልፍ ሚና ለሌሎች በመግለጽ ልጁን አክብሮታል።​—⁠ቆላ. 1:​15-17፤ w16.01 5:1, 2

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ