የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es18 ገጽ 7-17
  • ጥር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥር
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2018
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሰኞ፣ ጥር 1
  • ማክሰኞ፣ ጥር 2
  • ረቡዕ፣ ጥር 3
  • ሐሙስ፣ ጥር 4
  • ዓርብ፣ ጥር 5
  • ቅዳሜ፣ ጥር 6
  • እሁድ፣ ጥር 7
  • ሰኞ፣ ጥር 8
  • ማክሰኞ፣ ጥር 9
  • ረቡዕ፣ ጥር 10
  • ሐሙስ፣ ጥር 11
  • ዓርብ፣ ጥር 12
  • ቅዳሜ፣ ጥር 13
  • እሁድ፣ ጥር 14
  • ሰኞ፣ ጥር 15
  • ማክሰኞ፣ ጥር 16
  • ረቡዕ፣ ጥር 17
  • ሐሙስ፣ ጥር 18
  • ዓርብ፣ ጥር 19
  • ቅዳሜ፣ ጥር 20
  • እሁድ፣ ጥር 21
  • ሰኞ፣ ጥር 22
  • ማክሰኞ፣ ጥር 23
  • ረቡዕ፣ ጥር 24
  • ሐሙስ፣ ጥር 25
  • ዓርብ፣ ጥር 26
  • ቅዳሜ፣ ጥር 27
  • እሁድ፣ ጥር 28
  • ሰኞ፣ ጥር 29
  • ማክሰኞ፣ ጥር 30
  • ረቡዕ፣ ጥር 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2018
es18 ገጽ 7-17

ጥር

ሰኞ፣ ጥር 1

ለቅዱሳን ስለተሰጠው እምነት ብርቱ ተጋድሎ [አድርጉ]።—ይሁዳ 3

ወጣቷ የአባቷን መመለስ በጭንቀት ስትጠባበቅ ቆይታለች። አባቷ ድል ተቀዳጅቶ ከጦር ሜዳ በሰላም መመለሱን ስታይ በደስታ ልትቀበለው ወጣች። አባቷ ግን ከእሷ ጋር አብሮ በመደሰትና በመጨፈር ፋንታ ልብሱን ቀዶ “ወዮ፣ ልጄ! ልቤን ሰበርሽው” አላት። ከዚያም ሕይወቷን ለዘለቄታው የሚቀይር ብሎም እንደማንኛውም ሰው የመኖር ምኞቷንና ተስፋዋን የሚያከስም ነገር ተናገረ። እሷ ግን ምንም ሳታመነታ፣ አባቷ ለይሖዋ የገባውን ቃል እንዲፈጽም አበረታታችው። የተናገረችው ነገር ታላቅ እምነት እንዳላት ያሳያል። ይሖዋ የሚጠይቃት ማንኛውም ነገር፣ እሷን የሚጠቅም እንደሆነ እምነት ነበራት። (መሳ. 11:34-37) አባቷም የእሷን ምላሽ ሲሰማ ልቡ በኩራት ተሞላ፤ ምክንያቱም ውሳኔውን በፈቃደኝነት መደገፏ የይሖዋን ሞገስ እንደሚያስገኝ ያውቃል። ዮፍታሔና ልጁ፣ የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ ከባድ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ አምላክ ነገሮችን በሚያከናውንበት መንገድ ላይ እምነት እንዳላቸው አሳይተዋል። የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ሲባል ማንኛውንም መሥዋዕት መክፈል ፈጽሞ እንደማያስቆጭ እርግጠኞች ነበሩ። w16.04 1:1, 2

ማክሰኞ፣ ጥር 2

ስለ ኢዮብ ጽናት ሰምታችኋል፤ በውጤቱም ይሖዋ ያደረገለትን አይታችኋል።—ያዕ. 5:11

አንድ ወዳጅህ ወይም የቤተሰብህ አባል በተናገረው ተስፋ አስቆራጭ ነገር ስሜትህ ተደቁሶ አሊያም በከባድ ሕመም እየተሠቃየህ ወይም የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ከሆነ ኢዮብ ከተወው ምሳሌ ማጽናኛ ማግኘት ትችላለህ። (ኢዮብ 1:18, 19፤ 2:7, 9፤ 19:1-3) ኢዮብ መከራ እንዲደርስበት ያደረገው ማን መሆኑን ባያውቅም እንኳ ተስፋ አልቆረጠም። እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? አንደኛ ነገር “አምላክን የሚፈራ” ሰው ነበር። (ኢዮብ 1:1) ኢዮብ አመቺ በሆነ ወቅትም ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜ ይሖዋን ለማስደሰት ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። በተጨማሪም ይሖዋ፣ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ባከናወናቸው አስደናቂ ነገሮች ላይ እንዲያሰላስል ኢዮብን ረድቶታል። ይህም መከራዎቹን ይሖዋ በትክክለኛው ጊዜ እንደሚያስወግዳቸው ይበልጥ እንዲተማመን አድርጎታል። (ኢዮብ 42:1, 2) ደግሞም የሆነው ይህ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ በኢዮብ ላይ የደረሰው መከራ እንዲያበቃ አደረገ፤ ደግሞም ብልጽግናውን መለሰለት። ይሖዋ ለኢዮብ ቀድሞ የነበረውን እጥፍ አድርጎ ሰጠው” ይላል። ኢዮብም “ሸምግሎና ዕድሜ ጠግቦ ሞተ።”—ኢዮብ 42:10, 17፤ w16.04 2:11, 13

ረቡዕ፣ ጥር 3

እንደ እባብ ጠንቃቆች፣ እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ።—ማቴ. 10:16

አደገኛ ሁኔታዎችን አስቀድመን በማስተዋል ጠንቃቆች መሆናችንን እናሳያለን፤ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ የገለልተኝነት አቋማችንን በመጠበቅ ደግሞ የዋሆች መሆናችንን እናሳያለን። ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሲነሱ ስለምንናገረው ነገር ጠንቃቃ መሆን አለብን። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ስንሰብክ የአንድን መሪ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ፖሊሲዎች፣ ከማወደስም ሆነ ከመንቀፍ መቆጠብ ይኖርብናል። ከሰዎች ጋር ስንነጋገር ትኩረት ማድረግ ያለብን መሠረታዊ በሆነው ችግር ላይ እንጂ በማንኛውም ፖለቲካዊ መፍትሔ ላይ ሊሆን አይገባም፤ በዚህ መንገድ የሚያግባቡንን ነጥቦች ለማንሳት ጥረት ማድረግ አለብን። ከዚያም የአምላክ መንግሥት የሰው ልጆች ያሉባቸውን ችግሮች ለዘለቄታው ጠራርጎ የሚያስወግደው እንዴት እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ እናሳያቸው። በውይይቱ መሃል፣ ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን ጋብቻ ወይም ፅንስ ማስወረድን የመሳሰሉ አወዛጋቢ ጉዳዮች ከተነሱ የአምላክ መሥፈርቶች ምን እንደሆኑ እናስረዳቸው፤ እንዲሁም እነዚህን መሥፈርቶች በሕይወታችን ተግባራዊ ለማድረግ የምንጥረው እንዴት እንደሆነ ልንገልጽላቸው ይገባል። ከእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የየትኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ አቋም ደግፈን መናገር አይኖርብንም። በተጨማሪም አንዳንድ ሕጎች ሊወጡ፣ ሊሻሩ ወይም ሊለወጡ እንደሚገባ የሚገልጽ ሐሳብ ቢሰነዘር እኛ ከየትኛውም ወገን ልንሆን አይገባም፤ ሌሎች የእኛን አመለካከት እንዲቀበሉም ጫና አናሳድርም። w16.04 4:8, 9

ሐሙስ፣ ጥር 4

ስለዚህ ሂዱና . . . ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ።—ማቴ. 28:19

ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ፣ ማጥመቅና ማስተማር ያስፈልገናል፤ ይሁንና በቅድሚያ ሊከናወን የሚገባው ነገር ምንድን ነው? ኢየሱስ “ሂዱ” ብሏል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ይህን ትእዛዝ በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፦ “እያንዳንዱ አማኝ፣ መንገድ ተሻግሮም ይሁን ውቅያኖስ አቋርጦ ‘መሄድ’ አለበት።” (ማቴ. 10:7፤ ሉቃስ 10:3) ኢየሱስ ይህን ትእዛዝ የሰጠው ተከታዮቹ ምሥራቹን በተናጠል እንዲሰብኩ አስቦ ነው? ወይስ በቡድን ተደራጅተው የስብከት ዘመቻ እንዲያካሂዱ? አንድ ግለሰብ ወደ “ሁሉም ብሔራት” መሄድ ስለማይችል ይህ ሥራ መከናወን ያለበት አንድ ላይ በተደራጁ ብዙ ሰዎች ነው። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን “ሰው አጥማጆች” እንዲሆኑ መጋበዙ ይህን ይጠቁማል። (ማቴ. 4:18-22) ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሰው፣ አንድ ሰው ዓሣዎችን ለመያዝ መንጠቆ ላይ ምግብ ካንጠለጠለ በኋላ ዓሣዎቹ መጥተው ምግቡን እስኪወስዱ ድረስ ለብቻው ቁጭ ብሎ የሚጠብቅበትን ዓይነት ዓሣ የማጥመድ ዘዴ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ የተናገረው ብዙ ሰዎች አንድ ላይ ተቀናጅተው መረብ በመጠቀም ስለሚያከናውኑት ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ነው።—ሉቃስ 5:1-11፤ w16.05 2:3, 4

ዓርብ፣ ጥር 5

በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ። በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፤ እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።—ምሳሌ 3:5, 6

የይሖዋን አስተሳሰብ በሚገባ ለማወቅ ለግል ጥናት ትልቅ ቦታ መስጠት ይኖርብናል። የአምላክን ቃል ስናነብ ወይም ስናጠና እንዲህ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው፦ ‘ይህ ሐሳብ ስለ ይሖዋ፣ ነገሮችን ስለሚያከናውንበት መንገድና ስለ እሱ አስተሳሰብ ምን ያስተምረኛል?’ መዝሙራዊው ዳዊት የነበረው ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል፤ እንዲህ በማለት ዘምሯል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ መንገድህን አሳውቀኝ፤ ጎዳናህንም አስተምረኝ። አንተ አዳኝ አምላኬ ስለሆንክ በእውነትህ እንድመላለስ አድርገኝ፤ አስተምረኝም። ቀኑን ሙሉ አንተን ተስፋ አደርጋለሁ።” (መዝ. 25:4, 5) በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ ስናሰላስል እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ይህን ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው? ተግባራዊ ማድረግ የምችለው የት ነው? በቤት ውስጥ? በሥራ ቦታ? በትምህርት ቤት? ወይስ በአገልግሎት?’ ያነበብነውን ነገር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው የት እንደሆነ ካወቅን በሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት እንደሆነ በቀላሉ ማስተዋል እንችላለን። w16.05 3:9, 11

ቅዳሜ፣ ጥር 6

የበላይ ተመልካች የማይነቀፍ . . . ሊሆን ይገባዋል።—1 ጢሞ. 3:2, 4

ይሖዋ ለበላይ ተመልካቾች የሚሆኑ ብቃቶች በዝርዝር እንዲሰፍሩ ማድረጉ፣ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ላቅ ያሉ መሥፈርቶችን እንዲያሟሉ የሚፈልግ መሆኑን ያሳያል። (1 ጢሞ. 3:2-7) ይሖዋ፣ ሽማግሌዎች ጥሩ ምሳሌ እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል፤ እንዲሁም “በገዛ ልጁ ደም የዋጀውን” ጉባኤ የሚይዙበትን መንገድ በተመለከተ ይጠይቃቸዋል። (ሥራ 20:28) አምላክ፣ በተሾሙት የበታች እረኞች እንክብካቤ ሥር ሆነን ያለ ስጋት እንድንኖር ይፈልጋል። (ኢሳ. 32:1, 2) ከእነዚህ ነጥቦች አንጻር፣ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንዲያሟሉ የሚጠበቁባቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች መኖራቸው ይሖዋ ምን ያህል በጥልቅ እንደሚያስብልን እንድንገነዘብ ያደርገናል። ለነገሩ በዚህ ጥቅስ ላይ ከተዘረዘሩት ብቃቶች መካከል አብዛኞቹ፣ ይሖዋ ከሁሉም ክርስቲያኖች የሚጠብቃቸው ስለሆኑ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከዚህ ጥቅስ ትምህርት ሊያገኝ ይችላል። ለምሳሌ፣ ሁላችንም ምክንያታዊ ልንሆንና ጤናማ አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል። (ፊልጵ. 4:5፤ 1 ጴጥ. 4:7) ሽማግሌዎች “ለመንጋው ምሳሌ” ለመሆን ሲጥሩ እኛም ከእነሱ ትምህርት ልንወስድና ‘በእምነታቸው ልንመስላቸው’ ይገባል።—1 ጴጥ. 5:3፤ ዕብ. 13:7፤ w16.05 5:8-10

እሁድ፣ ጥር 7

ከምንም ነገር በላይ ልብህን ጠብቅ።—ምሳሌ 4:23

ልባችንን ሊያደነድኑ የሚችሉትን የትኞቹን ባሕርያት ማስወገድ ይኖርብናል? ከእነዚህ መካከል ተገቢ ያልሆነ ኩራት፣ ኃጢአትን ልማድ ማድረግ እንዲሁም እምነት ማጣት ይገኙበታል። እንደነዚህ ያሉት ዝንባሌዎች ያለመታዘዝና የዓመፀኝነት መንፈስ እንዲኖረን ሊያደርጉ ይችላሉ። (ዳን. 5:1, 20፤ ዕብ. 3:13, 18, 19) የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ዖዝያ ታብዮ ነበር። (2 ዜና 26:3-5, 16-21) ዖዝያ በንግሥናው መጀመሪያ ላይ “በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር” ያደረገ ከመሆኑም ሌላ “አምላክን ይፈልግ ነበር።” አምላክም ዖዝያን አበረታው፤ የሚያሳዝነው ግን “በበረታ ጊዜ ልቡ ታበየ።” እንዲያውም ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ በመግባት ዕጣን ለማጠን ሞከረ፤ ይህ የአሮን ዘሮች ለሆኑት ካህናት ብቻ የተሰጠ መብት ነበር። ካህናቱ ድርጊቱ ትክክል አለመሆኑን ሲነግሩት ደግሞ ትዕቢተኛው ዖዝያ እጅግ ተቆጣ! ይህ ምን አስከተለ? አምላክ ውርደት ያከናነበው ሲሆን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የሥጋ ደዌ በሽተኛ ሆኖ ኖረ። (ምሳሌ 16:18) እኛም የኩራት ዝንባሌ ካደረብን ‘ከሚገባው በላይ ስለ ራሳችን በማሰብ ራሳችንን ከፍ አድርገን’ ልንመለከት አልፎ ተርፎም ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክርን ለመቀበል ፈቃደኞች ላንሆን እንችላለን።—ሮም 12:3፤ ምሳሌ 29:1፤ w16.06 2:3, 4

ሰኞ፣ ጥር 8

እርስ በርሳችሁ በፍቅር በመቻቻል ኑሩ።—ኤፌ. 4:2

ከአንተ የተለየ ባሕል ላላቸው የእምነት ባልንጀሮችህ ምን አመለካከት አለህ? የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው፣ አለባበሳቸው፣ ባሕርያቸው ወይም ምግባቸው አንተ ከለመድከው የተለየ ሊሆን ይችላል። እነዚህን ወንድሞችና እህቶች ትርቃቸዋለህ? አብዛኛውን ጊዜህን የምታሳልፈው የአንተ ዓይነት አስተዳደግና ባሕል ካላቸው ሰዎች ጋር ነው? አሊያም ደግሞ አንተ ባለህበት ጉባኤና ወረዳ ውስጥ ወይም በቅርንጫፍ ቢሮው ሥር ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉት ሽማግሌዎች በዕድሜ ከአንተ የሚያንሱ ወይም የተለየ ባሕልና ዘር ያላቸው ቢሆኑስ? እነዚህ ልዩነቶች በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ሊኖር የሚገባውን አንድነት እንዲያናጉት ትፈቅዳለህ? እንዲህ ዓይነት እንቅፋቶችን ለማስወገድ ምን ሊረዳን ይችላል? የበለጸገች ከተማ በሆነችውና የተለያዩ ዜጎች በሚኖሩባት በኤፌሶን ለነበሩት ክርስቲያኖች ጳውሎስ ከዚህ ጋር በተያያዘ ጠቃሚ ምክር ሰጥቷቸዋል። (ኤፌ. 4:1-3) ጳውሎስ በመጀመሪያ የጠቀሰው እንደ ትሕትና፣ ገርነት፣ ትዕግሥትና ፍቅር ያሉትን ባሕርያት ነው። እነዚህ ባሕርያት አንድን ቤት ጸንቶ እንዲቆም ከሚያደርጉት ዓምዶች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። w16.06 3:17, 18

ማክሰኞ፣ ጥር 9

ተጠንቀቁ፤ ከስግብግብነትም ሁሉ ተጠበቁ።—ሉቃስ 12:15

ሰይጣን ከይሖዋ ይልቅ ለሀብት ባሪያ እንድንሆን ይፈልጋል። (ማቴ. 6:24) ጉልበታቸውን ሁሉ ቁሳዊ ነገሮችን ለማከማቸት የሚያውሉ ሰዎች፣ የራስ ወዳድነት ፍላጎታቸውን በማርካት ላይ ስለሚያተኩሩ ውሎ አድሮ ሕይወታቸው ትርጉም አልባ ይሆናል፤ ከዚያ የከፋው ደግሞ በመንፈሳዊ ባዶ መሆናቸው እንዲሁም ለሐዘንና ለብስጭት መዳረጋቸው ነው። (1 ጢሞ. 6:9, 10፤ ራእይ 3:17) ይህ ሁኔታ ኢየሱስ ስለ ዘሪው በተናገረው ምሳሌ ላይ እንደገለጸው ነው። የመንግሥቱ መልእክት “በእሾህ መካከል” ሲዘራ “የሌሎች ነገሮች ሁሉ ምኞት . . . ቃሉን ያንቀዋል፤ የማያፈራም ይሆናል።” (ማር. 4:14, 18, 19) እኛም የምንኖረው የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በቀረበበት ጊዜ ላይ እንደመሆኑ መጠን አሁን ለራሳችን ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮችን የምናከማችበት ወቅት አይደለም። የቱንም ያህል ከፍ አድርገን የምንመለከታቸው ወይም ውድ የሆኑ ቁሳዊ ንብረቶቻችን ከታላቁ መከራ ይተርፉልናል ብለን መጠበቅ አይኖርብንም።—ምሳሌ 11:4 ግርጌ፤ ማቴ. 24:21, 22፤ w16.07 1:5, 6

ረቡዕ፣ ጥር 10

ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀብለናል።—ዮሐ. 1:16

አንድ የወይን እርሻ ባለቤት፣ በወይን እርሻው ላይ የሚሠሩ ሠራተኞችን ለመቅጠር በጠዋት ተነስቶ ወደ ገበያ ቦታ ሄደ። ያገኛቸው ሰዎች በሚሰጣቸው ክፍያ ስለተስማሙ ወደ እርሻው ቦታ ሄደው መሥራት ጀመሩ። ይሁንና የእርሻው ባለቤት ተጨማሪ ሠራተኞች ስላስፈለጉት በቀኑ ውስጥ በተለያየ ሰዓት ወደ ገበያው ቦታ በመሄድ ሌሎች ሰዎችን ቀጠረ፤ የእርሻው ባለቤት አመሻሹ ላይ ለቀጠራቸው ሰዎችም ተገቢውን ክፍያ እንደሚከፍላቸው ነገራቸው። በመሸም ጊዜ የእርሻው ባለቤት ሠራተኞቹን በመሰብሰብ ደሞዛቸውን ከፈላቸው፤ ለብዙ ሰዓታት ሲለፉ ለዋሉትም ሆነ ለአንድ ሰዓት ብቻ ለሠሩት የሰጣቸው ክፍያ ተመሳሳይ ነው። መጀመሪያ የተቀጠሩት ሠራተኞች ይህን ሲያውቁ ቅሬታቸውን ገለጹ። የወይን እርሻው ባለቤትም ከመካከላቸው ለአንዱ እንዲህ አለው፦ ‘በዚህ ደሞዝ ለመሥራት ተስማምተህ አልነበረም? ለሁሉም ሠራተኞቼ የፈለግኩትን ያህል የመስጠት መብት የለኝም? እኔ ለጋስ በመሆኔ ልትመቀኝ ይገባሃል?’ (ማቴ. 20:1-15 ግርጌ) ኢየሱስ የተናገረው ይህ ምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰውን አንድ የይሖዋ ባሕርይ ያስታውሰናል፤ ይህም የአምላክ “ጸጋ” ነው።—2 ቆሮ. 6:1፤ w16.07 3:1, 2

ሐሙስ፣ ጥር 11

እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ . . . እነዚህ ቃላት አስተማማኝና እውነት ስለሆኑ ጻፍ።—ራእይ 21:5

መጨረሻው እየቀረበ ሲመጣ የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ ተልእኳችንን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል! (ማር. 13:10) ምሥራቹ የይሖዋን ጸጋ አጉልቶ እንደሚያሳይ ምንም ጥርጥር የለውም። በምሥክርነቱ ሥራ ስንካፈል ይህን ልናስታውስ ይገባል። የምንሰብክበት ዋና ዓላማ ለይሖዋ ክብር ማምጣት ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንደምናገኛቸው ቃል የተገቡልን በረከቶች በሙሉ የይሖዋ ጸጋ ግሩም መገለጫዎች እንደሆኑ ለሰዎች በማሳወቅ ነው። ለሌሎች በምንሰብክበት ጊዜ በክርስቶስ አገዛዝ ሥር የሰው ልጆች፣ ከቤዛዊ መሥዋዕቱ የተሟላ ጥቅም እንደሚያገኙና ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና እንደሚደርሱ ልናስረዳቸው እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥቶ የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት ማግኘት ነው።” (ሮም 8:21) ይህ ሊሆን የሚችለው በይሖዋ ጸጋ አማካኝነት ብቻ ነው። w16.07 4:17-19

ዓርብ፣ ጥር 12

ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፤ ሚስትም ብትሆን ለባሏ እንደዚሁ ታድርግለት።—1 ቆሮ. 7:3

መጽሐፍ ቅዱስ በባልና ሚስት መካከል ከሚፈጸም የፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ የፍቅር መግለጫዎች ምን ዓይነት ሊሆኑ እንደሚገባ ወይም እስከ ምን ድረስ መሄድ እንደሚቻል ዝርዝር መመሪያ ባይሰጥም አንዳንድ የፍቅር መግለጫዎችን ይጠቅሳል። (መኃ. 1:2፤ 2:6) ክርስቲያን ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላው አሳቢነት ማሳየት አለባቸው። ለአምላክና ለሌሎች ጥልቅ ፍቅር ካለን ማንኛውም ሰው ወይም ነገር በትዳራችን ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ አንፈቅድም። አንዳንድ ባለትዳሮች የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን (ፖርኖግራፊ) የማየት ወይም የማንበብ ልማድ ስለተጠናወታቸው፣ በትዳራቸው ውስጥ ችግሮች ከመፈጠራቸውም አልፎ ትዳራቸው እስከ መፍረስ ደርሷል። ፖርኖግራፊ የማየት ጉጉትም ሆነ ከትዳር ጓደኛችን ውጭ በማንኛውም መንገድ የፆታ ስሜትን የማርካት ፍላጎት እንዲያድርብን ፈጽሞ መፍቀድ አይኖርብንም። የትዳር ጓደኛችን ያልሆነን ሰው እያሽኮረመምን እንዳለን የሚያስመስል ነገር ማድረግ እንኳ ፍቅር የጎደለው ድርጊት ስለሆነ ልንርቀው ይገባል። አምላክ የምናስበውንም ሆነ የምናደርገውን ነገር ሁሉ እንደሚያውቅ ማስታወሳችን፣ እሱን የሚያሳዝን ነገር ከማድረግ እንድንቆጠብ የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ ያስችለናል።—ማቴ. 5:27, 28፤ ዕብ. 4:13፤ w16.08 2:7-9

ቅዳሜ፣ ጥር 13

[በአምላክ ፈቃድ] ትክክለኛ እውቀት ትሞሉ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለያችንንና መለመናችንን አላቋረጥንም።—ቆላ. 1:9

የቆላስይስ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን ትክክለኛ እውቀት መቅሰማቸው ‘ለይሖዋ በሚገባ ሁኔታ እንዲመላለሱና እሱን ሙሉ በሙሉ እንዲያስደስቱ’ ያስችላቸዋል። ይህም “በመልካም ሥራ ሁሉ” በተለይም ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ‘ፍሬ ማፍራታቸውን’ እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል። (ቆላ. 1:10) አንድ የይሖዋ አገልጋይ በአገልግሎቱ ውጤታማ መሆን ከፈለገ በግሉ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ረገድ ጥሩ ልማድ ሊኖረው ይገባል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይህን እውነታ እንዲገነዘቡ መርዳታችን አስፈላጊ ነው። በቅድሚያ ግን እኛ ራሳችን እንዲህ ዓይነቱን ልማድ ማዳበር ያለውን ጥቅም መገንዘብ ይኖርብናል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን የማጥናት ጥሩ ልማድ ሊኖረን ይገባል። ስለሆነም እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘በአገልግሎት የማገኛቸው ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ ሐሳቦችን ቢጠቅሱ ወይም ከባድ ጥያቄዎችን ቢጠይቁኝ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መልስ መስጠት እችላለሁ?’ መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን በማጥናታችን ምን ያህል እንደተጠቀምን ለሌሎች ከነገርናቸው፣ እነሱም ተመሳሳይ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት ለማጥናት ሊነሳሱ ይችላሉ። w16.08 4:3, 4

እሁድ፣ ጥር 14

የምንታገለው . . . በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው።—ኤፌ. 6:12

በዓለም ላይ ያሉ እንደ “ምሽግ” የሆኑ ነገሮች ተጽዕኖ እንዳያሳድሩብን መታገላችን በጣም አስፈላጊ ነው። ከእነዚህም መካከል ዓለም የሚያስፋፋቸው ትምህርቶችና ፍልስፍናዎች እንዲሁም እንደ ፆታ ብልግና፣ ሲጋራ ማጨስ፣ የአልኮል መጠጥ ከልክ በላይ መጠጣትና ዕፅ መውሰድ የመሳሰሉት ጎጂ ልማዶች ይገኙበታል። በተጨማሪም ካሉብን ድክመቶችና ተስፋ እንድንቆርጥ ከሚያደርጉን ነገሮች ጋር ሁልጊዜ መታገል አለብን። (2 ቆሮ. 10:3-6፤ ቆላ. 3:5-9) እንደነዚህ ያሉትን ኃይለኛ ጠላቶቻችንን በእርግጥ ማሸነፍ እንችላለን? አዎ፣ ግን ያለምንም ትግል እናሸንፋለን ማለት አይደለም። ጳውሎስ፣ በዚያ ዘመን በቡጢ ውድድር ከሚካፈል ሰው ጋር ራሱን በማነጻጸር “ቡጢ የምሰነዝረውም አየር ለመምታት አይደለም” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮ. 9:26) አንድ የቡጢ ተወዳዳሪ ባላጋራው የሚሰነዝርበትን ቡጢ እንደሚመክት ሁሉ እኛም ጠላቶቻችን ከሚሰነዝሩብን ጥቃት ራሳችንን መከላከል አለብን። ይሖዋ ይህን ማድረግ እንድንችል የሚያሠለጥነን ከመሆኑም ሌላ ይረዳናል። በቃሉ በኩል ሕይወት አድን የሆነ መመሪያ ይሰጠናል። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎቻችን እንዲሁም በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች አማካኝነት ይረዳናል። ታዲያ የተማራችሁትን በተግባር እያዋላችሁት ነው? w16.09 2:2, 3

ሰኞ፣ ጥር 15

ክርስቶስ እንኳ ራሱን አላስደሰተም።—ሮም 15:3

ኢየሱስ ከራሱ ምቾት ይልቅ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግና ሌሎችን ለመርዳት ቅድሚያ ይሰጥ ነበር። እኛም ምሥራቹን የምንነግራቸው ሰዎች ጆሯቸውን እንዳይሰጡን የሚያደርጉ ልብሶችንም ሆነ ፋሽኖችን፣ የምንወዳቸው ቢሆኑም እንኳ ልናስወግዳቸው ይገባል። (ሮም 15:2) ክርስቲያን ወላጆች፣ የቤተሰባቸው አባላት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ እንዲያደርጉ የማሠልጠን ኃላፊነት አለባቸው። ይህም ሲባል እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው በአለባበሳቸውና በአጋጌጣቸው ልከኛ በመሆን የአምላክን ልብ ደስ ለማሰኘት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል ማለት ነው። (ምሳሌ 22:6፤ 27:11) ወላጆች ለሚያመልኩት ቅዱስ አምላክ ልጆቻቸው አክብሮት እንዲያዳብሩ ለመርዳት፣ እነሱ ራሳቸው ጥሩ ምሳሌ መሆን እንዲሁም ፍቅር የተንጸባረቀበትና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መመሪያ መስጠት ይኖርባቸዋል። ልጆች ተገቢ የሆነ ልብስ ማግኘት የሚችሉት የትና እንዴት እንደሆነ ወላጆቻቸው ሊያስተምሯቸው ይገባል። ይህም እነሱ የወደዱትን ብቻ ሳይሆን የይሖዋ ምሥክር መሆን የሚያስከትልባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችላቸውንም ልብስ እንዲመርጡ መርዳትን ይጨምራል። w16.09 3:13, 14

ማክሰኞ፣ ጥር 16

ተማሪ ከአስተማሪው አይበልጥም፤ በሚገባ የተማረ ሁሉ ግን እንደ አስተማሪው ይሆናል።—ሉቃስ 6:40

ኢየሱስ ይሖዋን፣ የአምላክን ቃልና ሰዎችን ይወድ ስለነበር የሌሎችን ልብ በሚነካ መንገድ ማስተማር ችሏል። (ሉቃስ 24:32፤ ዮሐ. 7:46) ወላጆችም እንዲህ ዓይነት ፍቅር ካላቸው የልጆቻቸውን ልብ መንካት ይችላሉ። (ዘዳ. 6:5-8፤ ሉቃስ 6:45) ስለሆነም ወላጆች መጽሐፍ ቅዱስንና ጽሑፎቻችንን በትጋት አጥኑ። ለፍጥረት ሥራዎች እንዲሁም በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በጽሑፎቻችን ላይ ለሚወጡ ርዕሶች ትኩረት ስጡ። (ማቴ. 6:26, 28) እንዲህ ማድረጋችሁ ግንዛቤያችሁን የሚያሰፋና ለይሖዋ ያላችሁን አድናቆት የሚያሳድግ ከመሆኑም ሌላ ልጆቻችሁን ለማስተማር ይበልጥ ዝግጁ እንድትሆኑ ይረዳችኋል። የእናንተ ልብ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከተሞላ ያወቃችሁትን ነገር ከቤተሰባችሁ ጋር ለመወያየት ትነሳሳላችሁ። ይህን የምታደርጉት ለጉባኤ ስብሰባዎች ስትዘጋጁ ወይም የቤተሰብ አምልኮ ስታከናውኑ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ሊሆን ይገባል። በተጨማሪም ከልጆቻችሁ ጋር እንዲህ ዓይነት ውይይት የምታደርጉት ይህን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባችሁ ስለሚሰማችሁ ብቻ መሆን የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ በዕለታዊ ጭውውታችሁ ውስጥ ልታካትቱት የሚገባ ነገር ነው። w16.09 5:6, 7

ረቡዕ፣ ጥር 17

ማንኛቸውም የአይሁዳውያንን ቋንቋ መናገር አይችሉም ነበር።—ነህ. 13:24

የአምላክን ቃል በሌላ ቋንቋ መረዳት አለመቻላችን መንፈሳዊነታችን አደጋ ላይ እንዲወድቅ ሊያደርግ ይችላል። በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነህምያ፣ ከባቢሎን ከተመለሱ አይሁዳውያን ልጆች መካከል አንዳንዶቹ ዕብራይስጥ መናገር እንደማይችሉ ሲያውቅ ሁኔታው በጣም አሳስቦት ነበር። እነዚህ ልጆች የአምላክን ቃል ትርጉም ሙሉ በሙሉ መረዳት አለመቻላቸው ከይሖዋና እሱ ከመረጠው ሕዝብ ጋር ባላቸው ዝምድና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ነበረው። (ነህ. 8:2, 8) በውጭ አገር ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉ አንዳንድ ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጆቻቸው ለእውነት ያላቸው ፍላጎት እየቀነሰ እንደሄደ ተገንዝበዋል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? በሌላ ቋንቋ የምናነበው ነገር በራሳችን ቋንቋ የምናነበውን ያህል ልባችንን ላይነካው ይችላል። በተጨማሪም በሌላ ቋንቋ ሐሳባችንን በደንብ መግለጽ አለመቻላችን ውጥረት ሊፈጥርብንና በመንፈሳዊ ሊያዳክመን ይችላል። በመሆኑም በሌላ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ለማገልገል ያለን ፍላጎት ሳይቀዘቅዝ፣ መንፈሳዊነታችንን ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ አለብን።—ማቴ. 4:4፤ w16.10 2:4-6

ሐሙስ፣ ጥር 18

እምነት . . . የምናምንበት ነገር በዓይን የሚታይ ባይሆንም እውን መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።—ዕብ. 11:1

የክርስቲያኖች እምነት ትልቅ ዋጋ ያለው ባሕርይ ነው። እምነት ያላቸው ሁሉም ሰዎች አይደሉም። (2 ተሰ. 3:2) ይሁንና ይሖዋ ለሁሉም አገልጋዮቹ “እምነት” ሰጥቷቸዋል። (ሮም 12:3፤ ገላ. 5:22) አምላክ፣ እምነት ስለሰጠን አመስጋኞች ልንሆን ይገባል! ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በሰማይ ያለው አባቱ ሰዎችን ወደ ራሱ የሚስበው በወልድ አማካኝነት እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐ. 6:44, 65) አንድ ሰው በኢየሱስ ማመኑ ደግሞ የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት ያስችለዋል። ይህም ከይሖዋ ጋር ዘላለማዊ የሆነ ዝምድና ለመመሥረት በር ይከፍታል። (ሮም 6:23) እንዲህ ያለ አስደናቂ በረከት ልናገኝ የቻልነው እንዴት ነው? እንደ ኃጢአታችን ቢሆን የሚገባን ሞት ነበር። (መዝ. 103:10) ይሖዋ ግን ትኩረት ያደረገው በመልካም ጎናችን ላይ ነው። በመሆኑም ምሥራቹን እንድንቀበል በጸጋው ልባችንን ከፈተልን። ስለሆነም በኢየሱስ ላይ እምነት በማዳበር እሱን መከተል ጀመርን፤ ይህ ደግሞ የዘላለም ሕይወት ተስፋ አስገኘልን።—1 ዮሐ. 4:9, 10፤ w16.10 4:1, 2

ዓርብ፣ ጥር 19

[ጳውሎስ] በሚያልፍባቸው ስፍራዎች የሚያገኛቸውን ደቀ መዛሙርት በብዙ ቃል [አበረታታቸው]።—ሥራ 20:2

ጳውሎስ በጻፋቸው ደብዳቤዎች ላይ ለእምነት ባልንጀሮቹ ያለውን አድናቆት ገልጿል። ከአንዳንዶቹ ጋር ለዓመታት አብሮ ስለተጓዘ ያሉባቸውን ድክመቶች እንደሚያውቅ ጥርጥር የለውም፤ ያም ቢሆን ስለ እነሱ መልካም ነገር ተናግሯል። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ ስለ ጢሞቴዎስ ሲናገር ‘በጌታ ልጄ የሆነው የምወደውና ታማኝ የሆነው’ በማለት ገልጾታል፤ በተጨማሪም ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ ለሌሎች ክርስቲያኖች ከልቡ እንደሚያስብ ተናግሯል። (1 ቆሮ. 4:17፤ ፊልጵ. 2:19, 20) ሐዋርያው ስለ ቲቶ ለቆሮንቶስ ጉባኤ ሲጽፍ ደግሞ “ለእናንተ ጥቅም አብሮኝ የሚሠራ ባልደረባዬ” በማለት ለእሱ ያለውን አድናቆት ገልጿል። (2 ቆሮ. 8:23) ጢሞቴዎስና ቲቶ፣ ጳውሎስ ለእነሱ ያለውን አመለካከት ሲያውቁ ምንኛ ተበረታተው ይሆን! ጳውሎስና በርናባስ፣ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል ከዚያ ቀደም ጥቃት ተሰንዝሮባቸው ወደነበሩ ቦታዎች ተመልሰው ሄደዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በልስጥራ ከባድ ተቃውሞ አጋጥሟቸው የነበረ ቢሆንም ወደዚያ ተመልሰው በመሄድ አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ አበረታተዋል። (ሥራ 14:19-22) ጳውሎስ በኤፌሶን በቁጣ የተሞሉ ሰዎች ከተነሱበት በኋላ በዚያ የነበሩትን ደቀ መዛሙርት አበረታቷቸዋል።—ሥራ 20:1፤ w16.11 1:10, 11

ቅዳሜ፣ ጥር 20

በአስተሳሰብም ሆነ በዓላማ ፍጹም አንድነት [ይኑራችሁ]።—1 ቆሮ. 1:10

ይሖዋ በድርጅቱ ምድራዊ ክፍል ውስጥ የሚገኙ አገልጋዮቹን ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ይመራቸዋል እንዲሁም ይመግባቸዋል፤ ይህን ባሪያ የሚመራው ደግሞ ‘የጉባኤው ራስ’ ክርስቶስ ነው። (ማቴ. 24:45-47፤ ኤፌ. 5:23) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው የበላይ አካል ሁሉ ታማኝና ልባም ባሪያም መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈስ መሪነት እንደተጻፈ የአምላክ ቃል ወይም መልእክት አድርጎ የሚቀበለው ከመሆኑም ሌላ ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። (1 ተሰ. 2:13) መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዘውትረን በስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ ያዘናል። (ዕብ. 10:24, 25) እንዲሁም ትምህርታችን አንድ እንዲሆን አጥብቆ ያሳስበናል። የይሖዋ ቃል፣ ከምንም ነገር በላይ የአምላክን መንግሥት እንድናስቀድም ይመክረናል። (ማቴ. 6:33) በተጨማሪም ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ምሥራቹን ከቤት ወደ ቤት፣ በአደባባይና መደበኛ ባልሆነ መንገድ የመስበክ ኃላፊነትና መብት እንደተሰጠን ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሥራ 5:42፤ 17:17፤ 20:20) የአምላክ ቃል፣ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የድርጅቱን ንጽሕና መጠበቅ እንዳለባቸው ይናገራል። (1 ቆሮ. 5:1-5, 13፤ 1 ጢሞ. 5:19-21) ይሖዋ በድርጅቱ ውስጥ ያሉ ሁሉ አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን መጠበቅ እንዳለባቸውም ተናግሯል።—2 ቆሮ. 7:1፤ w16.11 3:7, 8

እሁድ፣ ጥር 21

ሕዝቤ ሆይ፣ . . . ከእሷ ውጡ።—ራእይ 18:4

ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት በነበሩት አሥርተ ዓመታት ቻርልስ ቴዝ ራስልና ተባባሪዎቹ፣ የሕዝበ ክርስትና ድርጅቶች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንደማያስተምሩ ተገንዝበው ነበር። በመሆኑም ከሐሰት ሃይማኖት ለመራቅ ወሰኑ። እነዚህ ወንድሞች የወሰዱትን ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋም በተመለከተ የኅዳር 1879 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ የሚከተለውን ግልጽ ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “የክርስቶስ ሚስት የሆነች ንጽሕት ድንግል መሆኗን የምትናገር ሆኖም ከዓለም (ከአውሬው) ጋር አንድነት ያላትና የዓለምን ድጋፍ የምታገኝ ማንኛዋም ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳን መጻሕፍት መሠረት አመንዝራ ቤተ ክርስቲያን [ታላቂቱ ባቢሎን] በመሆኗ ልናወግዛት ይገባል።” (ራእይ 17:1, 2) በወቅቱ የነበሩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወንዶችና ሴቶች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቁ ነበር። የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶችን እየደገፉ የአምላክን ሞገስ ማግኘት እንደማይችሉ ተገንዝበዋል። በመሆኑም በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የነበሩበትን ቤተ ክርስቲያን መልቀቃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ አዘጋጁ። w16.11 5:2, 3

ሰኞ፣ ጥር 22

እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ . . . አእምሯቸው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው።—ሮም 8:5

በየዓመቱ ከሚከበረው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ጋር በተያያዘ ሮም 8:15-17⁠ን አንብበህ ታውቅ ይሆናል። ይህ ጥቅስ ክርስቲያኖች በመንፈስ መቀባታቸውን የሚያውቁት፣ መንፈስ ቅዱስ ከመንፈሳቸው ጋር ሆኖ ሲመሠክር እንደሆነ ይገልጻል። ይህ ምዕራፍ በዋነኝነት የተጻፈው ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ‘መንፈስን ያገኙ’ ሲሆን ‘ከሥጋዊ አካላቸው ነፃ በመውጣት አምላክ ልጆቹ አድርጎ እንዲወስዳቸው እየተጠባበቁ’ ነው። (ሮም 8:23) የወደፊት ተስፋቸው በሰማይ የአምላክ ልጆች መሆን ነው። ይህ ሊሆን የቻለው ከተጠመቁ በኋላ አምላክ ከቤዛው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ኃጢአታቸውን ይቅር ስላላቸው እንዲሁም እነሱን በማጽደቅ መንፈሳዊ ልጆቹ ስላደረጋቸው ነው። (ሮም 3:23-26፤ 4:25፤ 8:30) ይሁን እንጂ ሮም ምዕራፍ 8 ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ክርስቲያኖችም ትኩረት ይስባል፤ ምክንያቱም አምላክ እነሱንም እንደ ጻድቃን ይመለከታቸዋል። በመሆኑም በዚህ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው ለጻድቃን የተሰጠ ምክር ለእነሱም ጠቃሚ ነው። w16.12 2:1-3

ማክሰኞ፣ ጥር 23

ፈጽሞ አትጨነቁ።—ማቴ. 6:34

ኢየሱስ “ፈጽሞ አትጨነቁ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? አንድ የአምላክ አገልጋይ በሕይወቱ ውስጥ የሚያስጨንቅ ነገር ጨርሶ እንደማይገጥመው መናገሩ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ኢየሱስ ይህን ሲል፣ አላስፈላጊ ወይም ከልክ ያለፈ ጭንቀት ችግሮችን ለመፍታት እንደማይረዳ ለደቀ መዛሙርቱ ማስተማሩ ነበር። እያንዳንዱ ቀን የራሱ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉት፤ በመሆኑም ክርስቲያኖች አሁን ያላቸው ጭንቀት እንዳይበቃቸው፣ ስላለፈው ወይም ስለ ወደፊቱ ጊዜ እያሰቡ መጨነቅ አያስፈልጋቸውም። አንድ ክርስቲያን ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን እያሰበ የሚብሰለሰል ከሆነ ሳያስፈልግ ሊጨነቅ ይችላል። ይሁን እንጂ ስለማታውቀው ሁኔታ እያሰብክ በጭንቀት ወይም በስጋት መዋጥ ምንም ፋይዳ የለውም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ፣ የፈራነውን ያህል መጥፎ ነገር ላይደርስ ይችላል። በተጨማሪም የሚያስጨንቅህን ነገር ሁሉ ልትጥልበት ከምትችለው አምላክ ቁጥጥር ውጪ የሆነ ምንም ነገር የለም። አምላክ ታማኞቹን እንደሚባርክ ብሎም ከቀድሞ ሕይወታቸው እንዲሁም አሁን ካሉበትና ወደፊት ሊያጋጥማቸው ከሚችለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ የሚሰማቸውን ጭንቀት ለመቋቋም እንደሚረዳቸው እርግጠኛ ሁን። w16.12 3:13, 16

ረቡዕ፣ ጥር 24

ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች።—ምሳሌ 11:2

ንጉሥ ሳኦል እስራኤልን መግዛት ሲጀምር ልኩን የሚያውቅና በሌሎች ዘንድ አክብሮት ያተረፈ ሰው ነበር። (1 ሳሙ. 9:1, 2, 21፤ 10:20-24) ሆኖም ንጉሥ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ እብሪተኛ እንደሆነ የሚያሳዩ ድርጊቶችን መፈጸም ጀመረ። በአንድ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን እስራኤልን ለመውጋት መጥተው ነበር። ነቢዩ ሳሙኤል ወደ ጊልጋል መጥቶ ለይሖዋ መሥዋዕት እንደሚያቀርብ ለሳኦል ነግሮት ነበር። ሳሙኤል ግን ባለው ጊዜ ሳይመጣ ቀረ። እስራኤላውያንም ሳኦልን ጥለውት መሸሽ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ሳኦል ትዕግሥቱ ስላለቀ ሳሙኤልን ከመጠበቅ ይልቅ እሱ ራሱ መሥዋዕቱን አቀረበ፤ ሆኖም እንዲህ የማድረግ ሥልጣን አልነበረውም። ይሖዋም ሳኦል ባደረገው ነገር አልተደሰተም። (1 ሳሙ. 13:5-9) ሳሙኤል ወደ ጊልጋል ሲመጣ ሳኦልን ገሠጸው። ሳኦል እርማቱን ከመቀበል ይልቅ ሰበብ አስባብ መደርደር፣ ጥፋቱን በሌሎች ላይ ማላከክ እንዲሁም ድርጊቱን ማቃለል ጀመረ። (1 ሳሙ. 13:10-14) ይህ ድርጊቱና ከዚያ በኋላ የፈጸማቸው ሌሎች ነገሮች የኋላ ኋላ ንግሥናውን አልፎ ተርፎም የይሖዋን ሞገስ እንዲያጣ አድርገውታል። (1 ሳሙ. 15:22, 23) ሳኦል ጅማሬው ጥሩ ቢሆንም ፍጻሜው አሳዛኝ ሆኗል።—1 ሳሙ. 31:1-6፤ w17.01 3:1, 2

ሐሙስ፣ ጥር 25

እንደ ልቤ የሆነውን . . . ዳዊትን አገኘሁ።—ሥራ 13:22

ዳዊት ታማኝ ሰው ነበር። ያም ሆኖ ከባድ ኃጢአት የሠራበት ወቅት ነበር። ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ፈጽሟል። (2 ሳሙ. 11:1-21) ዳዊት የሠራውን ስህተት ወደ ኋላ ተመልሶ ማስተካከልም ሆነ የሠራው ስህተት ከሚያስከትልበት መዘዝ ማምለጥ አይችልም። እንዲያውም አንዳንዶቹ መዘዞች እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ የሚዘልቁ ነበሩ። (2 ሳሙ. 12:10-12, 14) ስለዚህ እምነት ያስፈልገው ነበር። ከልቡ ንስሐ ከገባ ይሖዋ ምሕረት እንደሚያደርግለትና የፈጸመው ስህተት ያስከተለበትን መዘዝ እንዲቋቋም እንደሚረዳው መተማመን ነበረበት። ፍጹማን ስላልሆንን ሁላችንም ኃጢአት እንሠራለን። አንዳንዶቹ ስህተቶች ከሌሎቹ ከበድ ያሉ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ፣ የሠራናቸውን ስህተቶች ወደ ኋላ ተመልሰን ማስተካከል አንችል ይሆናል። በመሆኑም የሠራነው ስህተት የሚያስከትልብንን መዘዝ ተቀብለን ለመኖር እንገደዳለን። (ገላ. 6:7) ያም ቢሆን ይሖዋ ንስሐ እስከገባን ድረስ ችግሮች በሚያጋጥሙን ወቅት እንደሚደግፈን በገባው ቃል ላይ መተማመን እንችላለን፤ ሌላው ቀርቶ ችግር ውስጥ የገባነው በራሳችን ጥፋት ቢሆንም እንኳ ይረዳናል።—ኢሳ. 1:18, 19፤ ሥራ 3:19፤ w17.01 1:10-12

ዓርብ፣ ጥር 26

የሰው ልጆች ከፀሐይ በታች የሚሆነውን ነገር ሁሉ መረዳት [አይችሉም።] ሰዎች የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ ሊረዱት አይችሉም። ይህን ለማወቅ የሚያስችል ጥበብ አለን ቢሉም እንኳ ሊረዱት አይችሉም።—መክ. 8:17

ውሳኔያችን የሚያስከትለውን ውጤት በእርግጠኝነት ማወቅ ወይም መቆጣጠር በማንችልበት ጊዜም እንኳ ልክን ማወቅ ትክክለኛውን ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል ወሰንን እንበል፤ የጤና ችግር ቢያጋጥመንስ? በዕድሜ የገፉ ወላጆቻችን የእኛ እንክብካቤ ቢያስፈልጋቸውስ? ደግሞስ በዕድሜ ከገፋን በኋላ ማን ይንከባከበናል? የቱንም ያህል ብንጸልይ ወይም ምርምር ብናደርግ እንዲህ ላሉት ጥያቄዎች የተሟላ መልስ ማግኘት አንችልም። በይሖዋ ላይ ያለን እምነት የአቅም ገደብ ያለብን መሆኑን እንድናውቅ ብቻ ሳይሆን ይህን አምነን እንድንቀበልም ይረዳናል። ስለ ጉዳዩ ምርምር ካደረግን፣ ሌሎችን ካማከርንና የይሖዋን አመራር ለማግኘት ከጸለይን በኋላ የአምላክ መንፈስ ከሚሰጠን አመራር ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። (መክ. 11:4-6) በዚህ መንገድ ውሳኔ ካደረግን ይሖዋ ውሳኔያችንን ሊባርከው አሊያም ደግሞ በግባችን ላይ ማስተካከያ እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል።—ምሳሌ 16:3, 9፤ w17.01 4:14

ቅዳሜ፣ ጥር 27

ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ . . . አትብላ።—ዘፍ. 2:17

አዳምና ሔዋን ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ሁኔታ ከፊታቸው ተደቀነ። ታዲያ ይሖዋን ይታዘዛሉ ወይስ እባቡ ያላቸውን ያደርጋሉ? አዳምና ሔዋን ይሖዋን ላለመታዘዝ ወሰኑ። (ዘፍ. 3:6-13) በይሖዋ ላይ በማመፃቸው ፍጽምና የጎደላቸው ሆኑ። በተጨማሪም አለመታዘዛቸው ከአምላክ እንዲርቁ አደረጋቸው፤ ምክንያቱም የይሖዋ ዓይኖች “ክፉ የሆነውን ነገር እንዳያዩ እጅግ ንጹሐን ናቸው።” በመሆኑም ‘ክፋትን ዝም ብሎ ማየት አይችልም።’ (ዕን. 1:13) ይሖዋ ክፋትን ዝም ብሎ ቢያይ ኖሮ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ ሕያዋን ፍጥረታት የወደፊት ተስፋ አደጋ ላይ ይወድቅ ነበር። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ በኤደን የተፈጸመውን ኃጢአት በቸልታ ቢያልፈው ኖሮ እምነት የሚጣልበት አምላክ መሆኑ አጠያያቂ ይሆን ነበር። ይሖዋ ግን ላወጣቸው መሥፈርቶች ምንጊዜም ታማኝ ነው፤ መቼም ቢሆን መሥፈርቶቹን አይጥስም። (መዝ. 119:142) አዳምና ሔዋን የመምረጥ ነፃነት ቢኖራቸውም ይሖዋን አለመታዘዛቸው ከሚያስከትለው መዘዝ ማምለጥ አይችሉም። በመሆኑም ውሎ አድሮ መሞታቸውና ወደ አፈር መመለሳቸው አልቀረም።—ዘፍ. 3:19፤ w17.02 1:8, 10, 11

እሁድ፣ ጥር 28

ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም።—ማቴ. 4:4

ኢየሱስ አገልግሎቱን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በቅዱሳን መጻሕፍት ይመራ ነበር። ከመሞቱ በፊት የተናገረው የመጨረሻ ሐሳብ እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መሲሑ የተነገሩ ትንቢቶችን የያዘ ነበር። (ማቴ. 27:46፤ ሉቃስ 23:46) በተቃራኒው በወቅቱ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች፣ የአምላክ ቃል ከራሳቸው ወግ ጋር በሚጋጭበት ጊዜ ቃሉን ችላ ይሉት ነበር። ኢየሱስ ስለ እነዚህ ሰዎች ሲናገር ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ያስነገረውን ትንቢት በመጥቀስ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው። የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው።” (ማቴ. 15:7-9) ኢየሱስ የሚያስተምረውም ትምህርት ቢሆን በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ነበር። ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹ ጥያቄ በሚያነሱበት ጊዜ መልስ ይሰጥ የነበረው የራሱን ጥበብ ወይም ተሞክሮ በመጠቀም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንደ መጨረሻ ባለሥልጣን አድርጎ ይጠቅስ ነበር።—ማቴ. 22:33-40፤ w17.02 3:18, 19

ሰኞ፣ ጥር 29

ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ፤ . . . ንጉሥን አክብሩ።—1 ጴጥ. 2:17

የይሖዋ ምሥክሮች ለመንግሥት ባለሥልጣናት አክብሮት ለማሳየት የተቻላቸውን ጥረት ያደርጋሉ። እርግጥ ነው፣ እያንዳንዱ አገር የየራሱ ባሕል ስላለው አክብሮት በማሳየት ረገድ የሚጠበቅብን ነገር እንደየአገሩ ሊለያይ ይችላል። ያም ቢሆን ባለሥልጣናቱ ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ከእነሱ ጋር ለመተባበር እንጥራለን። በእርግጥ የምናሳየው አክብሮትና ታዛዥነት ገደብ እንዳለው ቅዱሳን መጻሕፍት ይጠቁማሉ። የአምላክን ትእዛዝ እንድንጥስ ወይም ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማችንን እንድናላላ የሚያደርግ ነገር አናደርግም። (1 ጴጥ. 2:13-16) በጥንት ጊዜ የኖሩ የይሖዋ አገልጋዮች ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት አክብሮት በማሳየት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል። የሮም መንግሥት፣ በግዛቱ ውስጥ የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ አዋጅ ባወጣ ጊዜ ዮሴፍና ማርያም ታዘዋል። በወቅቱ ማርያም የበኩር ልጇን የምትወልድበት ጊዜ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ለመመዝገብ ወደ ቤተልሔም ተጉዘዋል። (ሉቃስ 2:1-5) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ጳውሎስ፣ ጥፋት ሠርተሃል ተብሎ በተከሰሰበት ወቅት ትሕትና በተሞላበት መንገድ የመከላከያ ሐሳቡን ያቀረበ ሲሆን ለንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳና በሮም ግዛት ሥር የነበረችው የይሁዳ አገረ ገዢ ለሆነው ለፊስጦስ ተገቢውን አክብሮት አሳይቷል።—ሥራ 25:1-12፤ 26:1-3፤ w17.03 1:9, 10

ማክሰኞ፣ ጥር 30

እነዚህ ነገሮች . . . [የተጻፉት] የሥርዓቶቹ ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅ ነው።—1 ቆሮ. 10:11

እስራኤላውያን የከነአናውያንን የኃጢአት ጎዳና በተከተሉበት ጊዜ ይሖዋ ለእነሱ ጥበቃ ማድረጉን አቁሟል። (መሳ. 2:1-3, 11-15፤ መዝ. 106:40-43) በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት የነበሩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ቤተሰቦች፣ ምንጊዜም ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ መኖር በጣም ፈታኝ እንደሆነባቸው መገመት አያዳግትም! ያም ሆኖ እንደ ዮፍታሔ፣ ሐና፣ ሕልቃና እና ሳሙኤል ያሉ ታማኝ ሰዎች የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ቁርጥ ውሳኔ አድርገው እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። (1 ሳሙ. 1:20-28፤ 2:26) በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች የሚያስቡትና የሚያደርጉት ነገር በጥንት ጊዜ ከነበሩት ከነአናውያን ጋር ይመሳሰላል፤ ለፆታ ምኞት ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ከመሆኑም ሌላ ዓመፀኞች ናቸው፤ እንዲሁም ቁሳዊ ነገሮችን ያሳድዳሉ። ይሖዋ ለእስራኤላውያን እንዳደረገው ሁሉ ለእኛም እንዲህ ካለው የዓለም ተጽዕኖ እንድንርቅ ግልጽ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል። ታዲያ እስራኤላውያን ከፈጸሙት ስህተት ትምህርት አግኝተናል? (1 ቆሮ. 10:6-10) ከነአናውያን የነበራቸው ዓይነት አስተሳሰብ በውስጣችን ፈጽሞ እንዳይኖር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለብን። (ሮም 12:2) እንዲህ ያለ ጥረት በማድረግ ረገድ በይሖዋ ላይ እምነት እያሳየን ነው? w16.04 1:4-6

ረቡዕ፣ ጥር 31

ማስተዋል ያለው ሰውም ጥበብ ያለበትን መመሪያ ይቀበላል።—ምሳሌ 1:5

ከበድ ያሉ ውሳኔዎች ማድረግ ሲያስፈልገን ከሁሉ የተሻለ ምክር የያዘውን መጽሐፍ ቅዱስን መመርመራችን እንዲሁም በጸሎት የይሖዋን ምክር መጠየቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። ደግሞም ይሖዋ ከእሱ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ ውሳኔዎች ለማድረግ የሚረዱ ባሕርያትን እንድናፈራ ያስችለናል። ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘የማደርገው ውሳኔ ይሖዋን እንደምወድ የሚያሳይ ነው? ቤተሰቤ ደስተኛና ሰላማዊ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል? ደግሞስ ታጋሽና ደግ እንደሆንኩ ያሳያል?’ ይሖዋ እሱን እንድንወደውና እንድናገለግለው አያስገድደንም። የመምረጥ ነፃነት ስለሰጠን እሱን ለማገልገልም ሆነ ላለማገልገል የራሳችንን ‘ምርጫ’ የማድረግ መብት አለን፤ ይሖዋ ይህን ኃላፊነታችንንና መብታችንን ያከብርልናል። (ኢያሱ 24:15፤ መክ. 5:4) ይሁን እንጂ እሱ በሚሰጠን መመሪያ ላይ ተመሥርተን የምናደርጋቸውን ውሳኔዎች በተግባር እንድናውል ይጠብቅብናል። ይሖዋ በሚሰጠን መመሪያ ላይ እምነት ካለንና እነዚህን መመሪያዎች በተግባር ካዋልናቸው ያላንዳች መወላወል ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ እንችላለን።—ያዕ. 1:5-8፤ 4:8፤ w17.03 2:17, 18

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ