የካቲት
ሐሙስ፣ የካቲት 1
ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም።—ያዕ. 1:4
ጽናት የሚፈጽመው “ሥራ” ምንድን ነው? ጽናት ‘በሁሉም ረገድ ምንም የማይጎድለን ፍጹማንና እንከን የለሽ እንድንሆን’ ይረዳናል። (ያዕ. 1:4) አብዛኛውን ጊዜ ፈተናዎች፣ ምን ድክመት እንዳለብን እንዲሁም ልናሻሽላቸው የሚገቡን ባሕርያት የትኞቹ እንደሆኑ እንድንገነዘብ ያደርጋሉ። የሚደርሱብንን ፈተናዎች በጽናት የምንወጣ ከሆነ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ይበልጥ በተሟላ መንገድ ማዳበር እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ይበልጥ ታጋሾች፣ አድናቂዎችና ሩኅሩኆች እንድንሆን ሊረዱን ይችላሉ። ጽናት ጥሩ ክርስቲያኖች እንድንሆን በመቅረጽ ረገድ አስፈላጊ የሆነ ሥራ ይፈጽማል፤ በመሆኑም የሚደርሱብንን ፈተናዎች ለማስቆም ስንል ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ከመጣስ ልንቆጠብ ይገባል። ለምሳሌ ያህል፣ ርኩስ የሆኑ ሐሳቦች ወደ አእምሮህ እየመጡ ቢያስቸግሩህ ምን ታደርጋለህ? በፈተናው ከመሸነፍ ይልቅ እነዚህን ምኞቶች ለማስወገድ እንዲረዳህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። እንዲህ በማድረግ፣ ራስን የመግዛት ባሕርይ ታዳብራለህ። ከማያምን የቤተሰብህ አባል ተቃውሞ እየደረሰብህ ነው? በተጽዕኖው ከመሸነፍ ይልቅ በሙሉ ልብህ ይሖዋን ማምለክህን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። የአምላክን ሞገስ ለማግኘት፣ መጽናት እንዳለብን አስታውስ።—ሮም 5:3-5፤ ያዕ. 1:12፤ w16.04 2:15, 16
ዓርብ፣ የካቲት 2
ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ።—ፊልጵ. 2:3
ስለ ዘር፣ ባሕል ወይም አገር ተገቢ ያልሆነ ኩራት ማዳበር ይሖዋ ለሰብዓዊ አገዛዝና ለሰው ዘር ካለው አመለካከት ጋር እንደሚጋጭ እናውቃለን። እርግጥ ነው፣ አምላክ ያደግንበትን ባሕል እንድንተው አይጠብቅብንም። እንዲያውም የተለያዩ ባሕሎች መኖራቸው በሰብዓዊው ቤተሰብ መካከል ያለውን አስደናቂ ልዩነት ያጎላል። ያም ቢሆን በአምላክ ዓይን ሁሉም ሰው እኩል መሆኑን ማስታወስ ይገባናል። (ሮም 10:12) ከትውልድ ቦታችን ጋር በተያያዘ ተገቢ ያልሆነ ኩራት ማዳበር ብሔራዊ ስሜት እንዲያድርብን ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ አቋማችንን ወደማላላት ሊመራን ይችላል። ክርስቲያኖችም ቢሆን እንዲህ ዓይነት ኩራት ወጥመድ ሊሆንባቸው ይችላል፤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው ጉባኤ አንዳንድ አባላት እንኳ ከእነሱ የተለየ ዜግነት ባላቸው ወንድሞቻቸው ላይ አድልዎ ፈጽመዋል። (ሥራ 6:1) ተገቢ ያልሆነ ኩራት በልባችን ውስጥ እያቆጠቆጠ መሆኑን እንዴት ማወቅ እንችላለን? ለምሳሌ የሌላ አገር ዜጋ የሆነ ክርስቲያን አንድ ሐሳብ አቀረበልን እንበል። ‘እኛ ነገሮችን የምናከናውንበት መንገድ የተሻለ ነው’ በማለት ሐሳቡን ወዲያውኑ ውድቅ እናደርገዋለን? የተሻለው አካሄድ ሁላችንም በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን በመንፈስ መሪነት የተሰጠ ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ነው። w16.04 4:12, 13
ቅዳሜ፣ የካቲት 3
የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ።—ሉቃስ 4:43
ኢየሱስ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች” ሰብኳል፤ ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሥራ እንዲሠሩ ይጠብቅባቸዋል። ታዲያ ‘በሁሉም ብሔራት’ ለሚገኙ ሰዎች ይህን መልእክት እየሰበከ ያለው የትኛው ቡድን ነው? (ማቴ. 28:19) መልሱ ግልጽ ነው፤ ይህን ሥራ የሚያከናውኑት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። ለምሳሌ ሚስዮናዊ የሆነ አንድ ቄስ፣ በብዙ አገሮች እንደኖረ ለአንድ ወንድም ከነገረው በኋላ በእያንዳንዱ አገር ያገኛቸውን የይሖዋ ምሥክሮች ‘የምትሰብኩት መልእክት ምንድን ነው?’ ብሎ እንደጠየቃቸው ገለጸለት። ታዲያ ምን ምላሽ አገኘ? ቄሱ “ሁሉም በጣም ሞኞች ከመሆናቸው የተነሳ ‘የአምላክን መንግሥት ምሥራች’ በማለት አንድ ዓይነት መልስ ሰጥተውኛል” ብሏል። እነዚያ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለ መልስ መስጠታቸው ግን “ሞኞች” መሆናቸውን የሚያሳይ ሳይሆን ከእውነተኛ ክርስቲያኖች የሚጠበቀው አንድነት እንዳላቸው የሚጠቁም ነው። (1 ቆሮ. 1:10) በተጨማሪም የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ በተባለው መጽሔት ውስጥ ያለውን መልእክት እንደሚያስተጋቡ የሚያሳይ ነው። ይህ መጽሔት በ254 ቋንቋዎች የሚገኝ ሲሆን እያንዳንዱ እትም በአማካይ ወደ 59 ሚሊዮን በሚጠጉ ቅጂዎች ይታተማል፤ በመሆኑም መጽሔቱ በዓለም ላይ በስፋት በመሰራጨት ረገድ ተወዳዳሪ የለውም። w16.05 2:6
እሁድ፣ የካቲት 4
እያንዳንዱ ሰው . . . በልቡ ያሰበውን ይስጥ።—2 ቆሮ. 9:7
የመንግሥቱ አስፋፊዎች እንደመሆናችን መጠን የዘወትር አቅኚ በመሆን ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መግባት እንፈልግ ይሆናል። ይህን ለማሳካት ስንልም ሕይወታችንን ለማቅለል የሚረዱ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ጀመርን። ሆኖም ‘በጥቂት ነገሮች ተደስቼ መኖር እችል ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስበን ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ‘አቅኚ ሁኑ’ የሚል የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ የለም፤ አስፋፊ ሆነንም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገል እንችላለን። ይሁን እንጂ ለመንግሥቱ ሲሉ መሥዋዕትነት የሚከፍሉ ሰዎች የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያገኙ ኢየሱስ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ሉቃስ 18:29, 30) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ለእሱ ‘በፈቃደኝነት የውዳሴ መባ ስናቀርብና’ እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት ስንል የምንችለውን ሁሉ በደስታ ስናደርግ እንደሚደሰት ቅዱሳን መጻሕፍት ያሳያሉ። (መዝ. 119:108) ታዲያ እነዚህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች በመመርመርና የእሱን አመራር ለማግኘት በመጸለይ የይሖዋን አስተሳሰብ ማወቅ አንችልም? በእነዚህ ነጥቦች ላይ ማሰላሰላችን፣ ከእኛ ሁኔታ ጋር የሚስማማና በሰማይ ያለውን አባታችንን በረከት የሚያስገኝ ውሳኔ ለማድረግ ሊረዳን ይችላል። w16.05 3:13
ሰኞ፣ የካቲት 5
አስጨናቂ የሆኑት ዘመናት ከመምጣታቸው . . . በፊት በወጣትነትህ ጊዜ ታላቁን ፈጣሪህን አስብ።—መክ. 12:1
ለወጣቶች በሚዘጋጁ ጽሑፎች ላይ የሚጠቀሱት አብዛኞቹ ችግሮች ሌሎቻችንንም ያጋጥሙናል። ሁላችንም ለእምነታችን ጥብቅና መቆም፣ ስሜታችንን መቆጣጠር፣ ጎጂ የሆነ የእኩዮች ተጽዕኖን መቋቋም እንዲሁም ከመጥፎ ጓደኛና መዝናኛ መራቅ ይኖርብናል። እነዚህና ሌሎች በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ለወጣቶች በተዘጋጁት ጽሑፎች ላይ ተብራርተዋል። በዕድሜ ከፍ ያሉ ክርስቲያኖች፣ ለወጣቶች የተዘጋጁ ጽሑፎች ለእነሱ እንደማይመጥኑ ሊሰማቸው ይገባል? በፍጹም! ትምህርቱ የተዘጋጀው ወጣቶችን በሚማርክ መልኩ ቢሆንም ምክሩ የተመሠረተው ጊዜ በማይሽራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ነው፤ ስለዚህ ሁላችንም ከዚህ መንፈሳዊ ዝግጅት ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ጽሑፎቻችን ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዲቋቋሙ የሚያግዟቸው ከመሆኑም ሌላ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉና ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ ይረዷቸዋል። በዕድሜ ከፍ ያሉ ክርስቲያኖችም በዚህ ረገድ ጥቅም ማግኘት ይችላሉ።—መክ. 12:13፤ w16.05 5:15, 16
ማክሰኞ፣ የካቲት 6
እስራኤል ሆይ ስማ፣ አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ ነው። አንተም አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ።—ዘዳ. 6:4, 5
“አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ ነው።” ይህ ትልቅ ትርጉም ያዘለ ጥቅስ ነው! ይህ ሐሳብ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡና ምድሪቱን ሲቆጣጠሩ ያጋጠሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ሰጥቷቸዋል። እኛም ይህን ጥቅስ ልብ ማለታችን፣ ከፊታችን የሚጠብቀንን ታላቅ መከራ ለማለፍ የሚያስችል ብርታት እንድናገኝና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለሚኖረው ሰላምና አንድነት አስተዋጽኦ እንድናደርግ ይረዳናል። ይሖዋን በሙሉ ነፍሳችን በመውደድና በማገልገል እንዲሁም በወንድማማች ማኅበራችን መካከል ያለው አንድነት ተጠብቆ እንዲኖር ልባዊ ጥረት በማድረግ፣ እሱን ብቻ ማምለካችንን እንቀጥል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ኢየሱስ በግ እንደሆኑ ለሚፈርድላቸው ሰዎች የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ የሚፈጸምበትን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ እንችላለን፦ “እናንተ አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።”—ማቴ. 25:34፤ w16.06 3:2, 20
ረቡዕ፣ የካቲት 7
ልብ ከምንም ነገር በላይ ከዳተኛ ነው።—ኤር. 17:9
ኩራት ለድርጊታችን ሰበብ እንድንፈጥርና ለመቀረጽ ፈጽሞ የማንመች እንድንሆን ሊያደርገን ይችላል። በአንድ የእምነት ባልንጀራህ ቅር ተሰኝተህ ታውቃለህ? አሊያም አንድን መብት በማጣትህ ስሜትህ ተጎድቶ ያውቃል? ከሆነ ምን አደረግክ? ክብርህ እንደተነካ ተሰማህ? ወይስ በዋነኝነት ያሳሰበህ ከወንድምህ ጋር ሰላም በመፍጠር ለይሖዋ ታማኝ መሆንህ ነው? (መዝ. 119:165፤ ቆላ. 3:13) አንድ ሰው ኃጢአትን ልማድ ካደረገ ምናልባትም በድብቅ ኃጢአት የሚፈጽም ከሆነ መለኮታዊ ምክር ሲሰጠው ለመቀበል ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል። ይህ ደግሞ ኃጢአትን እንደ ቀላል ነገር እንዲመለከት ሊያደርገው ይችላል። የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች የመመልከት ልማድ የነበረው አንድ ወንድም “ሽማግሌዎችን መንቀፍ ጀመርኩ” በማለት ተናግሯል። መጥፎ ልማዱ መንፈሳዊነቱ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነበር። ውሎ አድሮ ይህ ልማዱ ስለታወቀ ሽማግሌዎች እርዳታ ሰጡት። ሁላችንም ፍጽምና እንደሚጎድለን የታወቀ ነው። ሆኖም የአምላክን ምሕረትና እርዳታ ከመሻት ይልቅ ሌሎችን መንቀፍ ወይም ለፈጸምነው ኃጢአት ሰበብ መደርደር ከጀመርን ልባችን ደንድኗል ማለት ነው። w16.06 2:5, 6
ሐሙስ፣ የካቲት 8
ስለ ሕይወታችሁ . . . አትጨነቁ።—ማቴ. 6:25
ኢየሱስን ያዳምጡ የነበሩ ሰዎች፣ ሊያስጨንቃቸው ስለማይገባ ነገር ይጨነቁ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ መጨነቃቸውን እንዲተዉ እያሳሰባቸው ነው፤ ይህን ያለው ያለ ምክንያት አይደለም። ሊያሳስቡን ስለሚገቡ ነገሮችም እንኳ ከልክ በላይ መጨነቅ፣ ትኩረታችን እንዲሰረቅና ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ መንፈሳዊ ነገሮችን ችላ እንድንል ሊያደርገን ይችላል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ከልብ ስለሚያስብ፣ በተራራ ስብከቱ ላይ ይህን አደገኛ ዝንባሌ በተመለከተ አራት ጊዜ ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 6:27, 28, 31, 34) ኢየሱስ ሰዎች በየዕለቱ ምን እንደሚያስፈልጋቸው በሚገባ ያውቃል። ከዚህም በላይ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” በተባለው በዚህ ‘የመጨረሻ ቀን’ ውስጥ የሚኖሩ ተከታዮቹ ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሟቸው ይረዳል። (2 ጢሞ. 3:1) ብዙዎች ከሚያጋጥሟቸው ነገሮች መካከል እንደ ሥራ ማጣት፣ የኑሮ ውድነት፣ የምግብ እጥረትና የከፋ ድህነት ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይገኙበታል። ያም ሆኖ ኢየሱስ ‘ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነት ከልብስ’ እንደሚበልጥ ተገንዝቦ ነበር። w16.07 1:8, 9
ዓርብ፣ የካቲት 9
አምላክ የኃይሉ መግለጫ አድርጎ በሰጠኝ ነፃ ስጦታ ይኸውም በጸጋው አማካኝነት የዚህ ሚስጥር አገልጋይ ሆኛለሁ።—ኤፌ. 3:7
ይሖዋ የሚጠብቅብንን ነገሮች ሙሉ በሙሉ ማሟላት ብንችል ኖሮ እሱ የሚያሳየን ደግነት የሚገባን ነገር ይሆን ነበር። ሆኖም ይህን ማድረግ አንችልም። በመሆኑም ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “ሁልጊዜ ጥሩ ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኃጢአት የማይሠራ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም” በማለት ጽፏል። (መክ. 7:20) ሐዋርያው ጳውሎስም በተመሳሳይ “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል” እንዲሁም “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው” በማለት ጽፏል። (ሮም 3:23፤ 6:23ሀ) እኛም የሚገባን ሞት ነው። ይሁንና ይሖዋ፣ ኃጢአተኛ ለሆኑት የሰው ልጆች ጸጋውን በማሳየት ተወዳዳሪ በሌለው መንገድ ፍቅሩን ገልጿል። ከሁሉ የላቀው የይሖዋ ስጦታ፣ ለእኛ ሲል እንዲሞት ወደ ምድር የላከው “አንድያ ልጁ” ነው። (ዮሐ. 3:16) በመሆኑም ጳውሎስ ኢየሱስን አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እስከ ሞት ድረስ መከራ በመቀበሉ አሁን የክብርና የሞገስ ዘውድ ደፍቶ እናየዋለን፤ እሱ በአምላክ ጸጋ ለሰው ሁሉ ሲል ሞትን ቀምሷል።” (ዕብ. 2:9) በእርግጥም “አምላክ የሚሰጠው ስጦታ . . . በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።”—ሮም 6:23ለ፤ w16.07 3:3, 4
ቅዳሜ፣ የካቲት 10
ማሟያ የምትሆነውን ረዳት እሠራለታለሁ።—ዘፍ. 2:18
ጋብቻ በታሪክ ዘመናት ሁሉ የነበረ ነገር ነው። ጋብቻ እንዴት እንደተጀመረና ዓላማው ምን እንደሆነ መመርመራችን፣ የጋብቻን ጥምረት በተመለከተ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረንና የሚያስገኛቸውን በረከቶች ይበልጥ ማጣጣም እንድንችል ይረዳናል። አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን ከፈጠረ በኋላ ለእንስሳቱ ስም እንዲያወጣላቸው ወደ እሱ አመጣቸው። “ለሰው ግን ማሟያ የሚሆን ረዳት አልነበረውም።” በመሆኑም አምላክ፣ አዳም ከባድ እንቅልፍ እንዲወስደው ካደረገ በኋላ ከጎድን አጥንቶቹ አንዷን ወስዶ ሴት አድርጎ ሠራት፤ ከዚያም ወደ አዳም አመጣት። (ዘፍ. 2:20-24) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው የጋብቻ መሥራች አምላክ ነው። ይሖዋ “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ብሎ ተናግሮ ነበር፤ ኢየሱስም ይህንኑ መሠረታዊ ሥርዓት በድጋሚ ተናግሯል። (ማቴ. 19:4, 5) አምላክ የመጀመሪያዋን ሴት ሔዋንን የፈጠራት ከአዳም የጎድን አጥንት መሆኑ፣ ባልና ሚስት ምን ያህል የጠበቀ ጥምረት እንዳላቸው ለመጀመሪያዎቹ ጥንዶች አስገንዝቧቸው መሆን አለበት። አምላክ፣ ባልና ሚስት እንዲፋቱ ወይም በትዳር ጓደኛቸው ላይ ሌላ ደርበው እንዲያገቡ ዓላማው አልነበረም። w16.08 1:1, 2
እሁድ፣ የካቲት 11
ኢየሱስ . . . በሌሎች ከተሞች ለማስተማርና ለመስበክ ሄደ።—ማቴ. 11:1
ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ከሰዎች ጋር ስለ አምላክ መንግሥት ይወያይ ነበር። ለምሳሌ ሲካር ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የያዕቆብ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ካገኛት ሴት ጋር ደስ የሚልና ፍሬያማ የሆነ ውይይት አድርጓል። (ዮሐ. 4:5-30) በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌዊ ተብሎ የሚጠራውንና ቀረጥ ሰብሳቢ የነበረውን ማቴዎስን አነጋግሮታል። ማቴዎስ የኢየሱስ ተከታይ እንዲሆን የቀረበለትን ግብዣ ተቀብሏል። በማቴዎስ ቤት ውስጥ በተደረገው ግብዣ ላይ ኢየሱስ ሲናገር ማቴዎስና በቦታው የነበሩ ሌሎች ሰዎች አዳምጠዋል። (ማቴ. 9:9፤ ሉቃስ 5:27-39) በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ኢየሱስ፣ ከናዝሬት ለመጡ ሰዎች አሉታዊ አመለካከት የነበረውን ናትናኤልን ወዳጃዊ በሆነ መንገድ አነጋግሮታል። በመሆኑም ናትናኤል አመለካከቱን የቀየረ ሲሆን የናዝሬት ሰው የሆነው ኢየሱስ ስለሚያስተምረው ትምህርት የበለጠ ለማወቅ ወስኗል። (ዮሐ. 1:46-51) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው፣ እኛም አዳዲስ አስፋፊዎች ሰዎችን ወዳጃዊ መንፈስ በሚንጸባረቅበትና ዘና ባለ መንገድ እንዲያነጋግሩ ልናሠለጥናቸው ይገባል። በዚህ መንገድ የምናሠለጥናቸው አስፋፊዎች፣ ለሰዎች ልባዊ አሳቢነትና ደግነት ማሳየታቸው ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች እንደሚማርክ ሲመለከቱ መደሰታቸው አይቀርም። w16.08 4:7-9
ሰኞ፣ የካቲት 12
ሚስት ከባሏ አትለያይ። . . . ባልም ሚስቱን መተው የለበትም።—1 ቆሮ. 7:10, 11
አንድ ባልና ሚስት በትዳራቸው ውስጥ እልባት ያላገኘ ከባድ ችግር በሚኖርበት ጊዜ ከሁለት አንዳቸው አሊያም ሁለቱም ለመለያየት ወይም ለመፋታት ሊያስቡ ይችላሉ። ባለትዳሮች ከትዳር ጓደኛቸው ጋር መለያየትን እንደ ቀላል ነገር ሊያዩት አይገባም። በትዳር ውስጥ ከባድ ችግሮች በሚኖሩበት ጊዜ መለያየት መፍትሔ ቢመስልም እንዲህ ማድረጉ በአብዛኛው ተጨማሪ ችግሮች ያስከትላል። ይሖዋ፣ ሰው አባትና እናቱን ትቶ ከሚስቱ ጋር እንደሚጣበቅ ተናግሯል፤ ኢየሱስም ይህን ሐሳብ በድጋሚ ከተናገረ በኋላ “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” ብሏል። (ማቴ. 19:3-6፤ ዘፍ. 2:24) ይህ ጥቅስ ባልና ሚስት ራሳቸውም ቢሆኑ ‘አምላክ ያጣመረውን መለያየት’ እንደሌለባቸው ያጎላል። በይሖዋ ፊት ጋብቻ የዕድሜ ልክ ጥምረት ነው። (1 ቆሮ. 7:39) ማናችንም ብንሆን በአምላክ ፊት ተጠያቂዎች ነን፤ ባለትዳሮች ይህን ማስታወሳቸው፣ ችግሮች ተባብሰው ከባድ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ዛሬ ነገ ሳይሉ መፍትሔ ለማግኘት ከልባቸው ጥረት እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። w16.08 2:10, 11
ማክሰኞ፣ የካቲት 13
በክፉ አትሸነፍ።—ሮም 12:21
ጠላቶቻችን ጨርሶ ባልጠበቅነው ጊዜ ወይም በተዳከምንበት ወቅት ጥቃት ሊሰነዝሩብን ስለሚችሉ ሁልጊዜ ንቁ መሆን አለብን። “በክፉ አትሸነፍ” የሚለው ሐሳብ ክፉውን ማሸነፍ እንደምንችል ያሳያል። ክፉውን ማሸነፍ የምንችለው በትግሉ ከጸናን ነው። በሌላ በኩል ግን ከተዘናጋንና መታገላችንን ካቆምን በሰይጣን፣ እሱ በሚቆጣጠረው ክፉ ዓለምና ኃጢአተኛ በሆነው ሥጋችን ልንሸነፍ እንችላለን። ሰይጣን፣ ተሸንፋችሁ እጅ እንድትሰጡ እንዲያደርጋችሁ ፈጽሞ አትፍቀዱ! (1 ጴጥ. 5:9) በትግል ላይ ያሉ ሰዎች፣ አሸናፊ መሆን ከፈለጉ እየታገሉ ያሉበትን ዓላማ መዘንጋት የለባቸውም። የአምላክን ሞገስና በረከት ማግኘት እንዲችሉ በዕብራውያን 11:6 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ምንጊዜም በአእምሯቸው መያዝ ይኖርባቸዋል፤ ጥቅሱ “ወደ አምላክ የሚቀርብ ሁሉ እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታል” ይላል። “ከልብ ለሚፈልጉት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ያመለክታል።—ሥራ 15:17፤ w16.09 2:4, 5
ረቡዕ፣ የካቲት 14
ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ።—1 ቆሮ. 10:31
የአምላክ ቃል፣ ይሖዋን የሚያስከብር ጥበብ የተንጸባረቀበት ምርጫ ለማድረግ የሚረዱንን ጠቃሚ መመሪያዎች ይዟል። ያም ቢሆን በአለባበስ ረገድ የራሳችንን ምርጫ ማድረግ እንችላለን። የገንዘብ አቅማችንም ሆነ ምርጫችን ሊለያይ ይችላል። ይሁንና ልብሳችን ምንጊዜም ያልተዝረከረከ፣ ንጹሕ፣ ልከኛና ለሁኔታው የሚስማማ እንዲሁም በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆን ይኖርበታል። ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ የተንጸባረቀበት፣ ማስተዋል የተሞላበትና ሁሉንም ነገሮች ግምት ውስጥ ያስገባ ውሳኔ ማድረግ ቀላል የማይሆንበት ጊዜ እንዳለ እሙን ነው። አብዛኞቹ ሱቆች የሚያቀርቡት በወቅቱ ፋሽን የሆነውን ነገር ስለሆነ ልከኛ የሆነ ቀሚስና የቀሚስ አላባሽ አሊያም በጣም ያልተጣበቀ ሙሉ ልብስ ወይም ሱሪ ለማግኘት ብዙ ጊዜና ጥረት ይጠይቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ ደስ የሚልና ተገቢ የሆነ ልብስ ለማግኘት የምናደርገውን ልባዊ ጥረት የእምነት ባልንጀሮቻችን ማስተዋላቸውና ማድነቃቸው አይቀርም። በተጨማሪም በሰማይ ያለውን አፍቃሪ አባታችንን የሚያስከብር አለባበስ እንዲኖረን ለማድረግ ስንል ምንም ያህል መሥዋዕትነት ብንከፍል የሚያስቆጭ አይደለም። w16.09 3:15, 16
ሐሙስ፣ የካቲት 15
የሰሜኑን ሰማይ በባዶ ስፍራ ላይ ዘርግቷል፤ ምድርንም ያለ ምንም ነገር አንጠልጥሏል።—ኢዮብ 26:7
ልጆች፣ ነገሮችን በዓይነ ሕሊናቸው የመሳል ልዩ ችሎታ አላቸው። ስለሆነም ወላጆች፣ ልጆቻችሁን ስታስተምሩ ብዙ ጊዜ ምሳሌዎችን ተጠቀሙ። ልጃችሁ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት ያለውን እምነት ለማጠናከርም ውጤታማ ምሳሌዎችን መጠቀም ትችላላችሁ። የዛሬውን የዕለት ጥቅስ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህ ጥቅስ በመንፈስ መሪነት እንደተጻፈ ለልጃችሁ ማስረዳት የምትችሉት እንዴት ነው? እውነታውን እንዲሁ ልትነግሩት ትችሉ ይሆናል። ይህን ከማድረግ ይልቅ ልጃችሁ ነገሮችን በዓይነ ሕሊናው ለመሳል እንዲሞክር ለምን አትረዱትም? ኢዮብ የኖረው ቴሌስኮፕና መንኮራኩር ባልተሠራበት ዘመን እንደሆነ ግለጹ። የልጃችሁ ድርሻ፣ በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች እንደ ምድር ያለ ትልቅ ነገር ያለምንም ድጋፍ ይንጠለጠላል ብሎ ማመን ምን ያህል ሊከብዳቸው እንደሚችል ማስረዳት ሊሆን ይችላል። ክብደት ያላቸው ነገሮች የሚደግፋቸው ነገር ሳይኖር በባዶ መንጠልጠል እንደማይችሉ በምሳሌ ለማሳየት አንድ ኳስ ወይም ድንጋይ መጠቀም ይችላል። ልጆችን በዚህ መንገድ ማስተማር የሚከተለውን ሐቅ እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል፦ ሰዎች አንዳንድ ሳይንሳዊ እውነታዎችን ለማረጋገጥ ረጅም ጊዜ ወስዶባቸዋል፤ ይሖዋ ግን ይህ እውነታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍር ያደረገው ጥንት ነው።—ነህ. 9:6፤ w16.09 5:9, 12
ዓርብ፣ የካቲት 16
በልብህ [እመን]።—ሮም 10:9
አንድ ሰው እምነት አለው የሚባለው የአምላክን ዓላማዎች ስላወቀ ብቻ አይደለም። እምነት፣ አንድ ሰው ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲኖር የሚገፋፋ ኃይል ነው። ግለሰቡ አምላክ የሰው ልጆችን ለማዳን ባደረገው ዝግጅት ላይ እምነት ካለው ምሥራቹን ለሌሎች ለማካፈል ይነሳሳል። በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ከፈለግን እምነት ሊኖረን የሚገባ ከመሆኑም በላይ እምነታችን ምንጊዜም ጠንካራ መሆን አለበት። አንድ ተክል እንዳይጠወልግ ውኃ ያስፈልገዋል፤ በተመሳሳይም እምነት ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል። ከሰው ሠራሽ አትክልት በተለየ፣ ሕይወት ያለው ተክል ሁልጊዜ ለውጥ ያደርጋል። ውኃ ካጣ ይጠወልጋል፤ በቋሚነት ውኃ ካገኘ ደግሞ እየለመለመ ይሄዳል። በአንድ ወቅት ጤናማ የነበረ ተክልም እንኳ በቂ ውኃ ካላገኘ ሊደርቅ ይችላል። ከእምነታችን ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እምነታችንን ችላ ካልነው ጠውልጎ መሞቱ አይቀርም። (ሉቃስ 22:32፤ ዕብ. 3:12) ተገቢውን እንክብካቤ ካደረግንለት ግን ጠንካራ ሆኖ ሊቀጥልና “እያደገ” ሊሄድ ይችላል፤ ይህም “በእምነት . . . ጤናሞች” ለመሆን ያስችለናል።—2 ተሰ. 1:3፤ ቲቶ 2:2፤ w16.10 4:4, 5
ቅዳሜ፣ የካቲት 17
ዋናው ባለሥልጣንም ስም አወጣላቸው፤ ዳንኤልን ብልጣሶር . . . ብሎ [ጠራው]።—ዳን. 1:7
ዳንኤልና ጓደኞቹ በግዞት በተወሰዱበት ወቅት ባቢሎናውያን፣ እነዚህን ወጣቶች “የከለዳውያንን . . . ቋንቋ” በማስተማር ከባሕሉ ጋር እንዲዋሃዱ ለማድረግ ሞክረው ነበር። ከዚህም ሌላ እንዲያሠለጥናቸው የተመደበው የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን የባቢሎናውያን ስም አወጣላቸው። (ዳን. 1:3-7) ለዳንኤል የተሰጠው ስም የባቢሎን ዋነኛ አምላክ ከሆነው ከቤል ጋር የተያያዘ ነበር። ንጉሥ ናቡከደነጾር ይህን ያደረገው በዳንኤል አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ይኸውም አምላኩ ይሖዋ፣ ለባቢሎን አምላክ እንደተገዛ ሆኖ እንዲሰማው ለማድረግ ፈልጎ ሊሆን ይችላል። (ዳን. 4:8) ዳንኤል የንጉሡ ምርጥ ምግብ ቢቀርብለትም በዚህ ምግብ “ላለመርከስ በልቡ ቁርጥ ውሳኔ” አድርጓል። (ዳን. 1:8) ዳንኤል ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን’ በአፍ መፍቻ ቋንቋው ያጠና ስለነበር በሌላ አገር ቢኖርም መንፈሳዊነቱን ሊጠብቅ ችሏል። (ዳን. 9:2 ግርጌ) በመሆኑም ወደ ባቢሎን ከተወሰደ ከ70 ዓመታት ገደማ በኋላም እንኳ የሚታወቀው በዕብራይስጥ ስሙ ነበር።—ዳን. 5:13፤ w16.10 2:7, 8
እሁድ፣ የካቲት 18
መንፈሱ ወደመራቸው አቅጣጫ . . . ሁሉ ይሄዳሉ።—ሕዝ. 1:20
ኢየሱስ መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርበው ‘በታማኙ ባሪያ’ በኩል ብቻ ነው። (ማቴ. 24:45-47) ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ተከታዮቹ የአምላክን ቃል እንዲማሩና መመሪያዎቹን እንዲከተሉ ለመርዳት ከ1919 ጀምሮ በዚህ ባሪያ ሲጠቀም ቆይቷል። እኛም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መመሪያዎች በመታዘዝ ለጉባኤው ንጽሕና፣ ሰላምና አንድነት አስተዋጽኦ እናበረክታለን። እያንዳንዳችን ‘ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ምግብ ለሚያቀርብበት መስመር ታማኝ ነኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው። በጽሑፍ የሰፈረው የይሖዋ ቃል ስለ ድርጅቱ ሰማያዊ ክፍል ለማወቅ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ሕዝቅኤል በተመለከተው ራእይ ላይ የአምላክ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል በሠረገላ ተመስሏል። (ሕዝ. 1:4-28) ክርስቶስና ቅዱሳን መላእክት ይህን ክፉ ዓለም የሚያጠፉበት ጊዜ በተቃረበበት በዚህ ዘመን፣ የይሖዋ ሠረገላ የእሱን ስም ለማስቀደስና የሉዓላዊነቱን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እየገሰገሰ ነው! w16.11 3:9, 10
ሰኞ፣ የካቲት 19
እርስ በርስ እንበረታታ፤ ደግሞም ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን እናድርግ።—ዕብ. 10:25
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት የኢየሱስ ተከታዮች ሁሉ እኛም አንድ ላይ የምንሰበሰበው ለመማርና እርስ በርስ ለመበረታታት ነው። (1 ቆሮ. 14:31) ለብዙ ዓመታት ይሖዋን ያገለገሉ ሰዎችም እንኳ ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ኢያሱን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አምላክን ለዓመታት በታማኝነት አገልግሏል። ያም ቢሆን ይሖዋ፣ እንደሚከተለው ብሎ ኢያሱን እንዲያበረታታው ለሙሴ ነግሮታል፦ “በዚህ ሕዝብ ፊት የሚሻገረውም ሆነ አንተ ያየሃትን ምድር እንዲወርሱ የሚያደርገው ኢያሱ ስለሆነ እሱን መሪ አድርገህ ሹመው፤ አደፋፍረው፤ አበረታታውም።” (ዘዳ. 3:27, 28) ኢያሱ፣ እስራኤላውያንን እየመራ ተስፋይቱን ምድር ድል አድርጎ የመቆጣጠር ከባድ ኃላፊነት ሊሰጠው ነው። ወደፊት ተፈታታኝ ሁኔታዎች የሚያጋጥሙት ከመሆኑም ሌላ ቢያንስ አንድ ጊዜ በውጊያ ይሸነፋል። (ኢያሱ 7:1-9) በእርግጥም ኢያሱ መበረታታትና መደፋፈር ያስፈለገው መሆኑ የሚያስገርም አይደለም! እኛም የአምላክን መንጋ ለመንከባከብ ተግተው የሚሠሩትን ሽማግሌዎችና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች እናበረታታቸው።—1 ተሰ. 5:12, 13፤ w16.11 1:12, 13
ማክሰኞ፣ የካቲት 20
በብዙ ውኃዎች ላይ በምትቀመጠው በታላቂቱ አመንዝራ ላይ የተበየነውን ፍርድ አሳይሃለሁ።—ራእይ 17:1
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር በተያያዘ ስለወሰዱት አቋም፣ ለዘመዶቻቸውና ለቅርብ ወዳጆቻቸው እንዲሁም ለነበሩበት ቤተ ክርስቲያን አባላት ብቻ ማሳወቁ በቂ እንደሆነ አልተሰማቸውም። ታላቂቱ ባቢሎን ሃይማኖታዊ አመንዝራ መሆኗን መላው ዓለም ሊያውቅ ይገባል! በመሆኑም በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች “የባቢሎን ውድቀት” የሚል ርዕሰ ጉዳይ የያዘና ሕዝበ ክርስትናን የሚያጋልጥ ትራክት 10,000,000 ቅጂዎች ከታኅሣሥ 1917 እስከ 1918 መጀመሪያ ባለው ጊዜ ውስጥ በቅንዓት አሰራጭተዋል። ይህ የሕዝበ ክርስትናን ቀሳውስት በእጅጉ ያስቆጣቸው መሆኑ ምንም አያስገርምም፤ ያም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ይህን አስፈላጊ ሥራ ከማከናወን ወደኋላ አላሉም። ‘ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያቸው አድርገው ለመታዘዝ’ ቆርጠው ነበር። (ሥራ 5:29) ይህ ምን ያስገነዝበናል? እነዚህ ክርስቲያኖች በጦርነቱ ወቅት በታላቂቱ ባቢሎን ከመማረክ ይልቅ ከተጽዕኖዋ እየተላቀቁና ሌሎች ይህን እንዲያደርጉ እየረዱ ነበር። w16.11 5:2, 4
ረቡዕ፣ የካቲት 21
እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ አእምሯቸው በሥጋዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን አእምሯቸው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው።—ሮም 8:5
አንዳንዶች፣ ጥቅሱ የሚያነጻጽረው እውነት ውስጥ ያሉና የሌሉ በሌላ አባባል ክርስቲያን የሆኑና ያልሆኑ ሰዎችን እንደሆነ ያስቡ ይሆናል። ይሁንና ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው ‘ቅዱሳን እንዲሆኑ ለተጠሩና በአምላክ ለተወደዱ በሮም የሚኖሩ’ ሰዎች ነው። (ሮም 1:7) በመሆኑም ጳውሎስ ያነጻጸረው፣ እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚመላለሱ ክርስቲያኖችን እንደ መንፈስ ፈቃድ ከሚመላለሱ ክርስቲያኖች ጋር ነው። “እንደ ሥጋ ፍላጎት [መኖርን]” በክርስቲያኖች ‘ሰውነት ውስጥ ይሠሩ ከነበሩት የኃጢአት ምኞቶች’ ጋር አያይዞ ጠቅሶታል። (ሮም 7:5) በመሆኑም ጳውሎስ ‘አእምሯቸው በሥጋዊ ነገሮች ላይ ስላተኮረ’ ሰዎች ሲናገር የኃጢአት ምኞቶችና ዝንባሌዎች እንዲመሯቸውና እንዲቆጣጠሯቸው የሚፈቅዱ ወይም በሥጋዊ ፍላጎታቸው ላይ የሚያተኩሩ ሰዎችን ማመልከቱ ነበር። በጥቅሉ ሲታይ እነዚህ ሰዎች ከፆታ ጋር በተያያዘም ይሁን በሌሎች ጉዳዮች ረገድ ምኞታቸውን፣ ፍላጎታቸውንና ስሜታቸውን የሚከተሉ ናቸው። w16.12 2:5, 7
ሐሙስ፣ የካቲት 22
በደሉ ይቅር የተባለለት . . . ሰው ደስተኛ ነው።—መዝ. 32:1
አንዳንዶች ቀደም ሲል ባደረጉት ነገር ወይም በፈጸሙት ስህተት የተነሳ ይጨነቁ ይሆናል። ንጉሥ ዳዊት ‘የፈጸማቸው ስህተቶች በራሱ ላይ እንደሚያንዣብቡ’ የተሰማው ጊዜ ነበር። “በጭንቀት ከተዋጠው ልቤ የተነሳ እጅግ እቃትታለሁ” በማለት ተናግሯል። (መዝ. 38:3, 4, 8, 18) በዚያ ወቅት ጥበብ የሚሆነው ምን ማድረግ ነበር? ዳዊትስ ምን አድርጓል? ይሖዋ ምሕረት እንደሚያደርግለትና ይቅር እንደሚለው ተማምኗል። (መዝ. 32:2, 3, 5) ሌሎችን የሚያስጨንቃቸው ደግሞ አሁን ያሉበት ሁኔታ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ዳዊት መዝሙር 55ን በጻፈበት ወቅት ለሕይወቱ ሰግቶ ነበር። (መዝ. 55:2-5) ያም ቢሆን የነበረበት አስጨናቂ ሁኔታ በይሖዋ እንዳይተማመን እንዲያደርገው አልፈቀደም። ዳዊት ስላጋጠመው ችግር አጥብቆ በመጸለይ ብቻ ሳይወሰን የጭንቀቱን መንስኤ ለማስወገድ እርምጃ ወስዷል። (2 ሳሙ. 15:30-34) አንተም ከዳዊት ትምህርት ማግኘት ትችላለህ። ጭንቀት እንዲቆጣጠርህ ከመፍቀድ ይልቅ ችግሩን ለመፍታት የቻልከውን ያህል ጥረት አድርግ፤ ከዚያም ይሖዋ እንደሚረዳህ በመተማመን ጉዳዩን ለእሱ ተወው። w16.12 3:14, 15
ዓርብ፣ የካቲት 23
በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁ።—2 ሳሙ. 12:13
ዳዊት የይሖዋ ተወካይ የሆነው ነቢዩ ናታን የሰጠውን እርማት ተቀብሏል። በተጨማሪም ዳዊት ወደ ይሖዋ በመጸለይ ኃጢአቱን የተናዘዘ ከመሆኑም ሌላ የይሖዋን ሞገስ መልሶ የማግኘት ልባዊ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል። (መዝ. 51:1-17) ዳዊት የጥፋተኝነት ስሜት እንዲያሽመደምደው ከመፍቀድ ይልቅ ከሠራው ስህተት ተምሯል። ደግሞም እንደዚያ ያሉ ከባድ ኃጢአቶችን ዳግመኛ አልፈጸመም። ከጊዜ በኋላ ዳዊት ታማኝነቱን እንደጠበቀ ሞቷል፤ ይሖዋም ቢሆን ዳዊትን የሚያስታውሰው በዚህ የታማኝነት አቋሙ ነው። (ዕብ. 11:32-34) ዳዊት ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? ከባድ ኃጢአት ከሠራን ከልብ ንስሐ መግባትና የይሖዋን ምሕረት ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ኃጢአታችንን ለእሱ መናዘዝ አለብን። (1 ዮሐ. 1:9) በተጨማሪም መንፈሳዊ እርዳታ ወደሚሰጡን የጉባኤ ሽማግሌዎች መቅረብ ያስፈልገናል። (ያዕ. 5:14-16) ይሖዋ ባደረገልን በእነዚህ ዝግጅቶች መጠቀማችን አምላክ እኛን ለመፈወስና ይቅር ለማለት በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳለን ያሳያል። ከዚያም ከስህተታችን መማርና ይሖዋን በሙሉ ልብ ማገልገላችንን መቀጠል ይኖርብናል።—ዕብ. 12:12, 13፤ w17.01 1:13, 14
ቅዳሜ፣ የካቲት 24
አገልጋይህንም ከእብሪት ድርጊቶች ጠብቀው።—መዝ. 19:13
‘የእብሪት ድርጊት’ የሚባለው ምንድን ነው? ይህ አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት በችኮላ ወይም በማን አለብኝነት ያልተፈቀደ ነገር ማድረግን ለማመልከት ነው። በወረስነው ኃጢአት የተነሳ ሁላችንም እንደ እብሪት ሊቆጠር የሚችል ድርጊት የምንፈጽምበት ጊዜ ይኖራል። ሆኖም ንጉሥ ሳኦል ካጋጠመው ሁኔታ ማየት እንደሚቻለው በእብሪት ድርጊታችን ከገፋንበት ይዋል ይደር እንጂ ከአምላክ ጋር ያለን ግንኙነት አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም። መዝሙር 119:21 ስለ ይሖዋ ሲናገር “እብሪተኛ የሆኑትን . . . ትገሥጻለህ” ይላል። ይሖዋ እንዲህ የሚያደርገው ለምንድን ነው? የእብሪት ድርጊቶች አንድ ሰው ባለማወቅ እንደሚሠራቸው ስህተቶች ቀለል ተደርገው የሚታዩ አይደሉም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ልክን አለማወቅ ለይሖዋ ሉዓላዊነት አክብሮት አለማሳየት ነው። ሁለተኛ፣ ከተሰጠን ሥልጣን አልፈን የምንሄድ ከሆነ ከሌሎች ጋር መጋጨታችን አይቀርም። (ምሳሌ 13:10) በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የእብሪት ድርጊት እንደፈጸምን ሲታወቅ ለኀፍረት አልፎ ተርፎም ለውርደት ልንዳረግ እንችላለን። (ሉቃስ 14:8, 9) የእብሪት ድርጊት ምንጊዜም መጨረሻው አያምርም። ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚናገሩት ልክን ማወቅ ከሁሉ የተሻለው አካሄድ ነው። w17.01 3:4, 5
እሁድ፣ የካቲት 25
ምግባረ ብልሹ የሆኑት እነሱ ናቸው። ልጆቹ አይደሉም፤ ጉድለቱ የራሳቸው ነው።—ዘዳ. 32:5
አዳም ፍጽምና ስለጎደለው የአምላክን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ ማንጸባረቅ አልቻለም። አዳም ሊያገኝ ይችል የነበረውን አስደናቂ ሕይወት ከማጣቱም ሌላ ለልጆቹ አለፍጽምናን፣ ኃጢአትንና ሞትን አውርሷል። (ሮም 5:12) ዘሮቹ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኗል። ከዚህም ሌላ አዳምና ሔዋንም ሆኑ ዘሮቻቸው ፍጹም የሆኑ ልጆች ሊወልዱ አይችሉም። ሰይጣን ዲያብሎስ የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን በአምላክ ላይ እንዲያምፁ ከማድረግም አልፎ በታሪክ ዘመናት በሙሉ የሰው ልጆችን ለማሳት ጥረት ማድረጉን ቀጥሏል። (ዮሐ. 8:44) አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ግን አልቀነሰም። አዳምና ሔዋን ቢያምፁም ይሖዋ፣ የሰው ልጆች ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖራቸው ይፈልጋል። ማንም ሰው እንዲጠፋ አይፈልግም። (2 ጴጥ. 3:9) ስለዚህ አዳምና ሔዋን ካመፁ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አምላክ የሰው ልጆች ከእሱ ጋር የነበራቸውን ዝምድና መልሰው እንዲያገኙ የሚያስችል ዝግጅት አደረገ፤ እርግጥ ይህን ያደረገው የጽድቅ መሥፈርቶቹን ሳያላላ ነው።—ዮሐ. 3:16፤ w17.02 1:12-14
ሰኞ፣ የካቲት 26
ምክር በሚሹ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች።—ምሳሌ 13:10
ልክ እንደ ይሖዋ ሌሎች ባላቸው አዎንታዊ ጎን ላይ ማተኮራችን በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ለተሰጠን ቦታ ያለን አድናቆት እንዲጨምር ያደርጋል። የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ወይም በሌሎች ላይ ለመሠልጠን ከመሞከር ይልቅ ልካችንን በማወቅ የሌሎችን ምክር እንጠይቃለን፤ እንዲሁም የሚሰጡንን ሐሳብ እንቀበላለን። ወንድሞቻችን መብት ሲያገኙ አብረናቸው እንደሰታለን። በተጨማሪም ይሖዋ ‘በዓለም ዙሪያ በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያሉትን ወንድሞቻችንን’ እንደባረካቸው ስናይ እሱን ለማወደስ እንገፋፋለን። (1 ጴጥ. 5:9) ልካችንን በማወቅ ነገሮችን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ለመመልከት ጥረት ማድረጋችን አምላክን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን ለማድረግም ይረዳናል። አዘውትረን በማጥናት፣ በመጸለይ እንዲሁም የተማርነውን ተግባራዊ በማድረግ ሕሊናችንን ቀስ በቀስ ማሠልጠን እንችላለን። (1 ጢሞ. 1:5) በተጨማሪም ለሌሎች ቅድሚያ መስጠትን እንማራለን። እኛ ድርሻችንን ከተወጣን ይሖዋ ልክን ማወቅንና ሌሎች አምላካዊ ባሕርያትን እንድናዳብር በመርዳት ‘ሥልጠናችን እንዲጠናቀቅ’ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።—1 ጴጥ. 5:10፤ w17.01 4:17, 18
ማክሰኞ፣ የካቲት 27
በመልካም ሁኔታ የሚያስተዳድሩ በተለይ ደግሞ በመናገርና በማስተማር ተግተው የሚሠሩ ሽማግሌዎች እጥፍ ክብር ሊሰጣቸው ይገባል።—1 ጢሞ. 5:17
በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች አክብሮት ማሳየት እንዳለብን ግልጽ ነው። በተለይ ደግሞ በመካከላችን ሆነው አመራር ለሚሰጡን ሽማግሌዎች ይህን ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። እነዚህ ወንድሞች ብሔራቸው፣ የትምህርት ደረጃቸው፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ቦታ ወይም የኑሮ ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን አክብሮት እናሳያቸዋለን። መጽሐፍ ቅዱስ ሽማግሌዎች “ስጦታ” እንደሆኑ የሚናገር ሲሆን እነዚህ ወንድሞች፣ አምላክ ለአገልጋዮቹ የሚያስፈልገውን ለማሟላት ባደረገው ዝግጅት ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። (ኤፌ. 4:8) የጉባኤ ሽማግሌዎችን፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችን፣ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም የበላይ አካል አባላትን እስቲ እናስብ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች እንዳደረጉት ሁሉ እኛም አመራር የሚሰጡንን የተሾሙ ወንድሞች ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን። እርግጥ ነው፣ የክርስቲያን ጉባኤን ወክለው ለሚያገለግሉ የታወቁ ወንድሞች አምልኮ አከል ክብር አንሰጣቸውም፤ ወይም ደግሞ መልአክ ያየን ይመስል ለእነሱ የተለየ ቦታ ለመስጠት አንሞክርም። ይሁንና እነዚህ ወንድሞች ሥራቸውን በትጋት ስለሚያከናውኑና ትሑት ስለሆኑ አክብሮት እናሳያቸዋለን።—2 ቆሮ. 1:24፤ ራእይ 19:10፤ w17.03 1:13
ረቡዕ፣ የካቲት 28
ለምን ጥሩ ብለህ ትጠራኛለህ? ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም።—ማር. 10:18
ኢየሱስ የይሁዳ ንጉሥ ከሆነው ከቀዳማዊ ሄሮድስ አግሪጳ ምንኛ የተለየ ነበር! ሄሮድስ በአንድ ልዩ ዝግጅት ላይ “ልብሰ መንግሥቱን” ለብሶ ነበር። በአድናቆት የተዋጠው ሕዝብ “ይህ የአምላክ ድምፅ ነው እንጂ የሰው አይደለም!” እያለ ጮኸ። ሄሮድስ የሕዝቡ ውዳሴ ሳያስደስተው አልቀረም። በዚህ ጊዜ “ለአምላክ ክብር ባለመስጠቱ ወዲያውኑ የይሖዋ መልአክ ቀሰፈው፤ በትል ተበልቶም ሞተ።” (ሥራ 12:21-23) ይህን የተመለከተ ማንኛውም ሰው ሄሮድስ በይሖዋ የተመረጠ መሪ አለመሆኑን መገንዘቡ አይቀርም። በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ በአምላክ የተሾመ መሪ መሆኑን በግልጽ ማየት ይቻል ነበር፤ ኢየሱስ ከሁሉ የላቀው የአምላክ ሕዝቦች መሪ ይሖዋ እንደሆነ ሌሎች እንዲገነዘቡ በማድረግ ምንጊዜም ለእሱ ክብር ይሰጥ ነበር። ኢየሱስ መሪ የሚሆነው ለጥቂት ዓመታት ብቻ አይደለም። ከሞት ከተነሳ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል። . . . እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”—ማቴ. 28:18-20፤ w17.02 3:20, 21