የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es18 ገጽ 26-36
  • መጋቢት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጋቢት
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2018
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 1
  • ዓርብ፣ መጋቢት 2
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 3
  • እሁድ፣ መጋቢት 4
  • ሰኞ፣ መጋቢት 5
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 6
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 7
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 8
  • ዓርብ፣ መጋቢት 9
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 10
  • እሁድ፣ መጋቢት 11
  • ሰኞ፣ መጋቢት 12
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 13
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 14
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 15
  • ዓርብ፣ መጋቢት 16
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 17
  • እሁድ፣ መጋቢት 18
  • ሰኞ፣ መጋቢት 19
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 20
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 21
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 22
  • ዓርብ፣ መጋቢት 23
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 24
  • እሁድ፣ መጋቢት 25
  • ሰኞ፣ መጋቢት 26
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 27
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 28
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 29
  • ዓርብ፣ መጋቢት 30
  • የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ዕለት
    ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ
    ቅዳሜ፣ መጋቢት 31
  • የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 13፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 26:17-19፤ ማርቆስ 14:12-16፤ ሉቃስ 22:7-13 (ኒሳን 14፦ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች) ዮሐንስ 13:1-5፤ 14:1-3
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2018
es18 ገጽ 26-36

መጋቢት

ሐሙስ፣ መጋቢት 1

ዮፍታሔን . . . አባረሩት።—መሳ. 11:2

በቅንዓትና በጥላቻ የተሞሉት የዮፍታሔ ወንድሞች የበኩር ልጅ በመሆኑ ሊያገኝ የሚገባውን መብት በመከልከል ከአባቱ ቤት አባረውታል። (መሳ. 11:1-3) ይሁንና ዮፍታሔ፣ እንዲረዳቸው ያቀረቡትን ልመና ሰምቶ ረድቷቸዋል። (መሳ. 11:4-11) ዮፍታሔ ከሌሎች ሰዎች ጋር ከተፈጠረው ግጭት ይልቅ ትልቅ ቦታ የሰጠው የይሖዋን ስም ለማስከበር ሲል ለሚያደርገው ውጊያ ነው። ምንጊዜም በይሖዋ ለመታመን ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር፤ ይህ ደግሞ ለእሱም ሆነ ለሌሎች በረከት አምጥቷል። (ዕብ. 11:32, 33) ዮፍታሔ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? ምናልባት አንዳንድ ወንድሞች ቅር አሰኝተውን ወይም ተገቢ ያልሆነ ነገር አድርገውብን ይሆናል። በዚህ ጊዜ፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘት ወይም ከጉባኤው ጋር ሙሉ በሙሉ ከመተባበርና ይሖዋን ከማገልገል ወደኋላ ማለት አይኖርብንም። እኛም እንደ ዮፍታሔ፣ እንዲህ ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለማሸነፍና መልካም ነገር ማድረጋችንን ለመቀጠል የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተል ይኖርብናል።—ሮም 12:20, 21፤ ቆላ. 3:13፤ w16.04 1:7, 9, 10

ዓርብ፣ መጋቢት 2

ተስፋ አንቆርጥም።—2 ቆሮ. 4:1

መጽናት የሚያስፈልገን ለጊዜው ብቻ ሳይሆን እስከ መጨረሻው ነው። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት፣ አደጋ የደረሰባትን መርከብ እንውሰድ። ተሳፋሪዎቹ በሕይወት ለመትረፍ ከፈለጉ እየዋኙ ወደ ዳርቻው መሄድ አለባቸው። ወደ ዳርቻው ለመድረስ ጥቂት ሲቀረውም ሆነ ገና መሃል ላይ እያለ ተስፋ የቆረጠ ተሳፋሪ የሚያጋጥማቸው ነገር ተመሳሳይ ነው። እኛም ብንሆን ወደ አዲሱ ዓለም እስክንገባ ድረስ ለመጽናት ቆርጠናል። ሕይወት ማግኘታችን የተመካው በመጽናታችን ላይ ነው። “ተስፋ አንቆርጥም” በማለት ሁለት ጊዜ እንደተናገረው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት አመለካከት አለን። (2 ቆሮ. 4:16) ይሖዋ እስከ መጨረሻው ድረስ መጽናት እንድንችል እንደሚረዳን ፈጽሞ አንጠራጠርም። በሮም 8:37-39 ላይ ጳውሎስ የተናገረውን ሐሳብ እንጋራለን፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “በወደደን በእሱ አማካኝነት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ በድል አድራጊነት እንወጣለን። ምክንያቱም ሞትም ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ መንግሥታትም ቢሆኑ፣ አሁን ያሉት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ወደፊት የሚመጡት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ማንኛውም ኃይል ቢሆን፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ሌላ ማንኛውም ፍጥረት ቢሆን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ከተገለጸው የአምላክ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ።” w16.04 2:17, 18

ቅዳሜ፣ መጋቢት 3

ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ . . . ይህም ሰው ይሰጠዋል።—ያዕ. 1:5

ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማችንን እንድናላላ ሊያደርጉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ማስተዋልና ማሸነፍ እንድንችል የሚያስፈልገውን ጥበብ እንዲሰጠን ይሖዋን እንጠይቅ። ለእውነተኛው አምልኮ ቆራጥ አቋም በመያዛችን ምክንያት ብንታሰር ወይም ሌላ ዓይነት ቅጣት ቢደርስብን ደግሞ እምነታችንን በድፍረት ለማስረዳትና የሚመጣብንን ማንኛውንም ስደት በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንዲሰጠን ወደ ይሖዋ እንጸልይ። (ሥራ 4:27-31) ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ሊያበረታህ ይችላል። ፈተና ሲያጋጥምህ የገለልተኝነት አቋምህን ለመጠበቅ ሊረዱህ በሚችሉ ጥቅሶች ላይ አሰላስል። መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት የማትችልበት አጋጣሚ ቢፈጠር ከእነዚህ ጥቅሶች ማበረታቻ ማግኘት እንድትችል ጥቅሶቹን በቃልህ ለመያዝ ሞክር። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ መንግሥት ወደፊት ስለሚያመጣቸው በረከቶች ያለን ተስፋ እውን ሆኖ እንዲታየን ይረዳናል። ስደት ሲደርስብን መጽናት እንድንችል ይህ ተስፋ ያስፈልገናል። (ሮም 8:25) ስለምትጓጓላቸው በረከቶች በሚገልጹ ጥቅሶች ላይ አሰላስል፤ በገነት ውስጥ እነዚህን በረከቶች ስታገኝ የሚኖረውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። w16.04 4:14, 15

እሁድ፣ መጋቢት 4

በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ።—ማቴ. 10:8

የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ስለ አምላክ መንግሥት እየሰበኩ አይደሉም። ስለ መንግሥቱ ቢናገሩ እንኳ ብዙዎቹ፣ በክርስቲያኖች ልብ ውስጥ ያለ ስሜት ወይም ሁኔታ እንደሆነ አድርገው ይገልጹታል። (ሉቃስ 17:21) የአምላክ መንግሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ የተሾመበት በሰማይ የሚገኝ መስተዳድር እንደሆነ፣ ለሰው ልጆች ችግሮች በሙሉ መፍትሔ እንደሚያመጣ እንዲሁም በቅርቡ ክፋትን ሁሉ ከምድር እንደሚያስወግድ ሰዎች እንዲገነዘቡ አያደርጉም። (ራእይ 19:11-21) ከዚህ ይልቅ ኢየሱስን የሚያስታውሱት በገና እና በፋሲካ በዓል ወቅት ነው። ኢየሱስ የምድር ንጉሥ ሲሆን ምን እንደሚያከናውን የሚያውቁት ነገር ያለ አይመስልም። እነዚህ ቀሳውስት የስብከቱን ሥራ እንዲያከናውኑ የሚያነሳሳቸው ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚገባም አያውቁም። ዓላማው ገንዘብ መሰብሰብና የተንቆጠቆጡ ሕንፃዎችን መገንባት መሆን የለበትም። በአምላክ ቃል ሊነገድ አይገባም። (2 ቆሮ. 2:17 ግርጌ) መልእክቱን የሚሰብኩ ሰዎች ከሚያከናውኑት ሥራ የግል ጥቅም ለማግኘት መሞከር የለባቸውም።—ሥራ 20:33-35፤ w16.05 2:7, 8

ሰኞ፣ መጋቢት 5

እያንዳንዱ ሰው ምንጊዜም የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ።—1 ቆሮ. 10:24

አንድ ልብስ መልበስ ፈለጋችሁ እንበል፤ ልብሱ የጉባኤውን አባላት ቅር የሚያሰኝ ሊሆን ይችል ይሆናል። ሆኖም ይህን ልብስ እንዳትለብሱ የሚከለክል ቀጥተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ እንደሌለ ታውቃላችሁ። ታዲያ ይሖዋ በዚህ ረገድ ያለውን አመለካከት ማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “ሴቶች ፀጉር በመሸረብና በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም ደግሞ በጣም ውድ በሆነ ልብስ ሳይሆን በልከኝነትና በማስተዋል ተገቢ በሆነ ልብስ ራሳቸውን ያስውቡ፤ ለአምላክ ያደርን ነን የሚሉ ሴቶች ሊያደርጉት እንደሚገባ በመልካም ሥራ ይዋቡ።” (1 ጢሞ. 2:9, 10) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ለክርስቲያን ወንዶችም በእኩል ደረጃ ይሠራል። ለይሖዋ ያደርን እንደመሆናችን መጠን የራሳችን ምርጫ ብቻ ሳይሆን አለባበሳችንና አጋጌጣችን በሌሎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖም ያሳስበናል። ልከኛ ከሆንንና ለሰዎች ፍቅር ካለን፣ የእምነት ባልንጀሮቻችንን አመለካከት ግምት ውስጥ በማስገባት እነሱን ሊረብሽ ወይም ቅር ሊያሰኝ የሚችል ልብስ ከመልበስ እንቆጠባለን።—1 ቆሮ. 10:23፤ ፊልጵ. 3:17፤ w16.05 3:14

ማክሰኞ፣ መጋቢት 6

ይሖዋ ሆይ፣ አንተ አባታችን ነህ። እኛ ሸክላ ነን፤ አንተም ሠሪያችን ነህ፤ ሁላችንም የእጅህ ሥራ ነን።—ኢሳ. 64:8

አዳም በፈጣሪው ላይ በማመፁ የልጅነት መብቱን አጣ። ይሁንና ባለፉት በርካታ ዘመናት የኖሩ እንደ “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” የሆኑ የአዳም ዘሮች የአምላክን ሉዓላዊነት መደገፍ መርጠዋል። (ዕብ. 12:1) እነዚህ ሰዎች ለፈጣሪያቸው በትሕትና በመገዛት፣ ከሰይጣን ይልቅ ይሖዋ እንደ ሸክላ ሠሪ እንዲቀርጻቸው እንዲሁም አባታቸው እንዲሆን እንደሚፈልጉ በተግባር አሳይተዋል። (ዮሐ. 8:44) ለአምላክ ያላቸው ታማኝነት፣ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ያስታውሰናል። በዛሬው ጊዜ ይሖዋን በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩ ሁሉ እንዲህ ዓይነት የትሕትናና የታዛዥነት መንፈስ ለማሳየት ይጥራሉ። ይሖዋን፣ አባታችን ብለው መጥራትና እሱን እንደ ሸክላ ሠሪያቸው ቆጥረው ለእሱ መገዛትን እንደ ታላቅ መብት ይመለከቱታል። አንተስ በአምላክ እጅ ውስጥ እንዳለ ለስላሳ የሸክላ ጭቃ እንደሆንክ ይሰማሃል? በእሱ ፊት ውድ ዕቃ ሆነህ ለመቀረጽ ፈቃደኛ ነህ? መንፈሳዊ ወንድሞችህንና እህቶችህን አምላክ ገና እየቀረጻቸው እንዳለ ትገነዘባለህ? w16.06 1:2, 3

ረቡዕ፣ መጋቢት 7

በእምነት ውስጥ መሆናችሁን ለማረጋገጥ ዘወትር ራሳችሁን ፈትሹ።—2 ቆሮ. 13:5

ወደ አዲሱ ዓለም የምንገባበት ጊዜ እየተቃረበ ባለበት በአሁኑ ወቅት የእኛም እምነት እየተፈተነ ነው። በመሆኑም የእምነታችንን ጥንካሬ መመርመራችን የተገባ ነው። ለምሳሌ ኢየሱስ በማቴዎስ 6:33 ላይ የተናገረውን ሐሳብ በተመለከተ ያለንን አመለካከት መመርመራችን ጠቃሚ ነው። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ቅድሚያ የምሰጣቸው ነገሮችና የማደርጋቸው ውሳኔዎች ኢየሱስ በተናገረው ሐሳብ ከልቤ እንደማምን ያሳያሉ? ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ስል ከስብሰባ ወይም ከአገልግሎት እቀራለሁ? ሥራዬ ጊዜዬን በጣም የሚሻማና ኃይሌን የሚያሟጥጥ ቢሆን ምን አደርጋለሁ? ዓለም እንዲቀርጸኝ እፈቅዳለሁ? ምናልባትም በዚህ ዓለም ተጽዕኖ ተሸንፌ እውነትን እስከመተው እደርስ ይሆን?’ በሌላ በኩል ደግሞ ‘ከጓደኛ ምርጫ፣ ከውገዳ ወይም ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች ለመታዘዝ አመነታለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው። ልባችንን ሊያደነድን የሚችል እንዲህ ያለ ዝንባሌ እንዳለን ካስተዋልን ዛሬ ነገ ሳንል እምነታችንን መመርመራችን አስፈላጊ ነው! በአምላክ ቃል በመጠቀም አዘውትረን ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመርና አስተሳሰባችንን ማስተካከል ያስፈልገናል። w16.06 2:8, 9

ሐሙስ፣ መጋቢት 8

ጥቂት የሆነው ሺህ፣ ትንሽ የሆነውም ኃያል ብሔር ይሆናል።—ኢሳ. 60:22

በምድር ላይ ያሉ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮችን ወይም ምሥክሮቹን ያቀፈ አንድ ልዩ ድርጅት አለ። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሰዎች ፍጽምና የጎደላቸው በመሆናቸው ስህተት ይሠራሉ። ያም ሆኖ አምላክ፣ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ዓለም አቀፉን ጉባኤ በመባረክ እያደገና እየተጠናከረ እንዲሄድ አድርጓል። የዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት በ1914 ሲጀምሩ በምድር ላይ የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች በአንጻራዊ ሁኔታ ትንሽ ነበሩ። ይሁንና ይሖዋ የስብከቱን ሥራቸውን ባርኮታል። በቀጣዮቹ አሥርተ ዓመታት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተምረው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። ይሖዋ ይህን አስደናቂ እድገት በተመለከተ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ከተናገረ በኋላ “እኔ ይሖዋ፣ ይህን በራሱ ጊዜ አፋጥነዋለሁ” ብሏል። ይህ ትንቢት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ፍጻሜውን እንዳገኘ በግልጽ ማየት ይቻላል። የይሖዋ ሕዝቦች እንደ አንድ ታላቅ ብሔር ሆነዋል፤ እንዲያውም በአሁኑ ወቅት፣ በምድር ላይ ካሉት የአምላክ ሕዝቦች አጠቃላይ ቁጥር ያነሰ የሕዝብ ብዛት ያላቸው በርካታ አገራት አሉ። w16.06 4:1, 2

ዓርብ፣ መጋቢት 9

ታዲያ እናንተ [ከሰማይ ወፎች] አትበልጡም?—ማቴ. 6:26

ኢየሱስ፣ በሰማይ ያለው አባቱ ለወፎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር እያሟላ የሰው ልጆችን መሠረታዊ ፍላጎት ችላ ይላል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይመስል ነገር እንደሆነ ተሰምቶታል። (1 ጴጥ. 5:6, 7) እርግጥ ነው፣ አምላክ ምግቡን አፋችን ላይ አያደርግልንም፤ ምግባችንን ለማግኘት ማረስ አሊያም እህሉን ለመግዛት የሚያስችለንን ገንዘብ ለማግኘት መሥራት ይኖርብናል፤ ይሖዋም የምናደርገውን ጥረት ይባርክልናል። ከተቸገርን ደግሞ ሌሎች ያላቸውን እንዲያካፍሉን ሊያነሳሳቸው ይችላል። ኢየሱስ የሰማይ ወፎች መጠለያ ስለሚያገኙበት መንገድ ባይጠቅስም ይሖዋ፣ ጎጇቸውን ለመሥራት የሚያስችላቸውን ችሎታና የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ሰጥቷቸዋል። ይሖዋ፣ እኛም በተመሳሳይ ቤተሰባችንን የምናስጠልልበት ጎጆ እንድናገኝ ይረዳናል። ኢየሱስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን የተናገረው፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሕይወቱን ለሰው ልጆች አሳልፎ እንደሚሰጥ በአእምሮው ይዞ መሆን አለበት። (ከሉቃስ 12:6, 7 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ የሞተው ለሰማይ ወፎች ሳይሆን እኛ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ነው።—ማቴ. 20:28፤ w16.07 1:11-13

ቅዳሜ፣ መጋቢት 10

በጸጋ ሥር እንጂ በሕግ ሥር ስላልሆናችሁ ኃጢአት በእናንተ ላይ ጌታ ሊሆን አይገባም።—ሮም 6:14

የሰው ልጆች በሙሉ የኃጢአትንና የሞትን እርግማን የወረሱት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “በአንድ ሰው [በአዳም] በደል የተነሳ ሞት” በአዳም ዘሮች ላይ እንደነገሠ ይናገራል። (ሮም 5:12, 14, 17) ደስ የሚለው ግን የኃጢአት ተገዢዎች ወይም ባሪያዎች ላለመሆን መምረጥ እንችላለን። በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን፣ የይሖዋ ጸጋ በእኛ ላይ እንዲነግሥ እንደምንፈልግ እናሳያለን። (ሮም 5:20, 21) ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳ ኃጢአት ሕይወታችንን እንዲቆጣጠረው ከመፍቀድ ሌላ አማራጭ እንደሌለን አድርገን ልናስብ አይገባም። ኃጢአት ስንሠራ ይሖዋ ይቅር እንዲለን መለመን እንችላለን። በመሆኑም በእኛ ላይ የሚገዛው የአምላክ ጸጋ ነው። ይህ ምን ውጤት ያስገኛል? ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት አብራርቶታል፦ “የአምላክ ጸጋ . . . ፈሪሃ አምላክ በጎደለው መንገድ መኖርና ዓለማዊ ምኞቶችን መከተል ትተን አሁን ባለው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ፣ በጽድቅና ለአምላክ በማደር እንድንኖር ያሠለጥነናል።”—ቲቶ 2:11, 12፤ w16.07 3:5, 6

እሁድ፣ መጋቢት 11

[አምላክ ሴቲቱን] ወደ ሰውየው አመጣት።—ዘፍ. 2:22

አዳምና ሔዋን የመምረጥ ነፃነታቸውን አላግባብ ስለተጠቀሙበት ይኸውም በይሖዋ ላይ ስላመፁ የመጀመሪያው ጋብቻ ችግር አጋጠመው። “የጥንቱ እባብ” የተባለው ሰይጣን ዲያብሎስ፣ ሔዋን “ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ” ፍሬ ብትበላ ልዩ እውቀት እንደምታገኝና መልካም ወይም ክፉ የሆነውን ነገር ራሷ የመወሰን ችሎታ እንደሚኖራት እንድታምን በማድረግ አታለላት። ሔዋን ስለ ጉዳዩ ባሏን አለማማከሯ ለእሱ የራስነት ሥልጣን አክብሮት እንደሌላት የሚያሳይ ነው። አዳምም ቢሆን አምላክን ከመታዘዝ ይልቅ ሔዋን የሰጠችውን ፍሬ ተቀብሎ በላ። (ራእይ 12:9፤ ዘፍ. 2:9, 16, 17፤ 3:1-6) አዳም የሠራውን ኃጢአት በተመለከተ አምላክ ሲጠይቀው ጥፋቱን በሚስቱ ላይ አላከከ። ሔዋን ደግሞ እባብ እንዳታለላት በመግለጽ ጥፋቷን በእሱ አሳበበች። (ዘፍ. 3:12, 13) ይህ አሳማኝ ያልሆነ ሰንካላ ምክንያት ነው! የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ሳይታዘዙ በመቅረታቸው ይሖዋ በእነዚህ ዓመፀኞች ላይ ፍርድ አስተላለፈ። ይህ ለእኛ ትልቅ ማስጠንቀቂያ ነው! ትዳር የሰመረ እንዲሆን ሁለቱም ተጋቢዎች ለድርጊታቸው ኃላፊነቱን መውሰድና ይሖዋን መታዘዝ አለባቸው። w16.08 1:1, 4, 5

ሰኞ፣ መጋቢት 12

አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።—ማቴ. 19:6

በትዳር ውስጥ ለሚፈጠሩ ችግሮች መንስኤው የትዳር ጓደኛሞች ከእውነታው የራቁ ነገሮችን መጠበቃቸው ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው ትዳሩ አስደሳች እንደሚሆን ተስፋ አድርጎ ይህ እውን ሳይሆን ሲቀር እርካታ ሊያጣ፣ እንደተታለለ ሊሰማው አልፎ ተርፎም በምሬት ሊዋጥ ይችላል። ባልና ሚስት ስሜታቸውን የሚገልጹበት መንገድ ተመሳሳይ አለመሆኑ ወይም በመካከላቸው የአስተዳደግ ልዩነት መኖሩ ችግሮች እንዲከሰቱ ሊያደርግ ይችላል፤ አሊያም ደግሞ ከገንዘብ፣ ከአማቶች ወይም ከልጅ አስተዳደግ ጋር በተያያዘ አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል። ይሁንና አብዛኞቹ ክርስቲያን ባለትዳሮች የአምላክን መመሪያ ስለሚከተሉ፣ ለእነዚህ ችግሮች ሁለቱንም ወገኖች የሚያስማሙ መፍትሔዎችን ማግኘት ችለዋል፤ ይህም የሚያስመሰግናቸው ነው። በትዳራቸው ውስጥ ከባድ ችግር ያጋጠማቸው ባለትዳሮች፣ ሽማግሌዎች እንዲረዷቸው መጠየቅ አለባቸው። ተሞክሮ ያላቸው እነዚህ ወንድሞች፣ ባለትዳሮች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ እንዲያደርጉ ሊረዷቸው ይችላሉ። በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ስንጥር፣ ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ለማዋልና የመንፈስ ፍሬ ለማፍራት እንዲረዳን መጸለይም ይኖርብናል።—ገላ. 5:22, 23፤ w16.08 2:11-13

ማክሰኞ፣ መጋቢት 13

ከአሁን ጀምሮ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ።—ሉቃስ 5:10

ኢየሱስ አገልግሎቱን ለማከናወን ያለው ጊዜ ውስን ነበር። ሆኖም ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ የሰጡ ሰዎችን ፍላጎት ለማሳደግ ጊዜ መድቧል። ኢየሱስ አንድ ጀልባ ላይ ሆኖ ተሰብስበው የነበሩ ሰዎችን ያስተማረበትን ወቅት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በዚያ ወቅት ጴጥሮስን በተአምራዊ መንገድ ብዙ ዓሣ እንዲያጠምድ ከረዳው በኋላ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ነግሮታል። ኢየሱስ የተናገረው ነገርና ድርጊቱ ምን ውጤት አስገኘ? ጴጥሮስና አብረውት የነበሩት ሰዎች “ሁሉን ነገር ትተው [ኢየሱስን] ተከተሉት።” (ሉቃስ 5:1-11) የሳንሄድሪን ሸንጎ አባል የነበረው ኒቆዲሞስ ኢየሱስ የሚያስተምረው ትምህርት ትኩረቱን ስቦት ነበር። ተጨማሪ እውቀት ማግኘት ቢፈልግም በአደባባይ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገር ቢታይ ሰዎች ምን እንደሚሉት በማሰብ ፈርቶ ነበር። ኢየሱስ፣ ሰዎችን በሚመቻቸው ጊዜ ለማነጋገርና ጊዜውን ሳይሰስት ለመስጠት ፈቃደኛ ስለነበር ማታ ላይ ሰው በሌለበት ኒቆዲሞስን አነጋገረው። (ዮሐ. 3:1, 2) የአምላክ ልጅ የሰዎችን እምነት ለመገንባት ጊዜ መድቧል። እኛስ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት ረገድ ትጉዎች መሆን አይኖርብንም? w16.08 4:10, 11

ረቡዕ፣ መጋቢት 14

ልክህን አውቀህ ከአምላክህ ጋር [ሂድ]።—ሚክ. 6:8

ልክን ማወቅ ሲባል ይሖዋ ንጹሕና ቅዱስ መሆኑን እንዲሁም እሱ ያወጣቸው መሥፈርቶች ከሁሉ የላቁ መሆናቸውን መገንዘብን ይጨምራል። ትሑቶችና ልካችንን የምናውቅ ከሆንን በሕይወታችን ውስጥ የእሱን መሥፈርቶች እንከተላለን። ልክን ማወቅ የሌሎችን ስሜትና አመለካከት ማክበርንም ይጨምራል። እንግዲያው ከይሖዋ የላቁ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን በመኖር እንዲሁም የሌሎችን ስሜት በማክበር ‘ልካችንን አውቀን ከአምላክ ጋር እንደምንሄድ’ እናሳይ። አለባበሳችን ሰዎች የይሖዋ አገልጋዮች መሆናችንን እንዲጠራጠሩ የሚያደርግ መሆን የለበትም። ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ጻድቅ የሆነውን አምላካችንን ለመወከል እንደምንበቃ ሊሰማቸው ይገባል። ይሖዋ የላቁ መሥፈርቶች አሉት፤ እኛም እነዚህን መሥፈርቶች ደስ እያለን በሕይወታችን ተግባራዊ እናደርጋለን። ግሩም አለባበስና ምግባር ያላቸው ወንድሞችና እህቶች፣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ሕይወት አድን የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት እንዲቀበሉ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋን ያስከብራሉ እንዲሁም ያስደስታሉ፤ ለዚህም ሊመሰገኑ ይገባል። w16.09 3:18-20

ሐሙስ፣ መጋቢት 15

ከአምላክም ሆነ ከሰዎች ጋር ታግለህ በመጨረሻ አሸንፈሃል።—ዘፍ. 32:28

ያዕቆብ በትግሉ ላለመሸነፍ ቆርጦ ነበር፤ እስከ መጨረሻው ድረስ በፍልሚያው ጸንቷል! (ዘፍ. 32:24-26) ደግሞም በመጽናቱ ሽልማቱን አግኝቷል። በእርግጥም፣ እስራኤል የሚል ስም የተሰጠው መሆኑ ተገቢ ነው፤ እስራኤል “ከአምላክ ጋር የታገለ [በጽናት የተጣበቀ]” ወይም “አምላክ ይታገላል” የሚል ትርጉም አለው። ያዕቆብ እኛም የምንጓጓለትን አስደናቂ ሽልማት ይኸውም የይሖዋን ሞገስና በረከት አግኝቷል። የያዕቆብ ሚስት የሆነችው ራሔል ይሖዋ በገባው ቃል አማካኝነት የባሏን ዘር እንዴት እንደሚባርክ ለማየት ትጓጓ ነበር። ይሁንና ራሔል ልጅ አልነበራትም። በዚያ ዘመን ደግሞ ይህ እንደ ከባድ መከራ የሚታይ ነገር ነበር። ታዲያ ራሔል ተስፋ አስቆራጭና ከቁጥጥሯ ውጭ የሆኑ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟትም በትግሉ ለመቀጠል የሚያስችላትን ስሜታዊም ሆነ አካላዊ ጥንካሬ ያገኘችው እንዴት ነው? ተስፋ ቆርጣ እጅ አልሰጠችም። ከዚህ ይልቅ አጥብቃ በመጸለይ መታገሏን ቀጠለች። ይሖዋም ራሔል ያቀረበችውን ምልጃ የሰማ ሲሆን ውሎ አድሮ ልጆች በመስጠት ባርኳታል።—ዘፍ. 30:8, 20-24፤ w16.09 2:6, 7

ዓርብ፣ መጋቢት 16

የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ከየትኛውም ሰይፍ የበለጠ ስለታም ነው።—ዕብ. 4:12

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ ልጆቻችሁ እንዲገነዘቡ መርዳታችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። (መዝ. 1:1-3) ይህን ማድረግ የሚቻልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ፣ ልጆቻችሁ ራቅ ብሎ በሚገኝ ደሴት ላይ ሊኖሩ እንዳሰቡ አድርገው በዓይነ ሕሊናቸው እንዲስሉ ጠይቋቸው፤ በደሴቱ ላይ አብረዋቸው የሚኖሩትን ሰዎች መምረጥ እንዳለባቸው ንገሯቸው። “የደሴቷ ነዋሪዎች በሙሉ እርስ በርስ ተስማምተው በሰላም እንዲኖሩ፣ እያንዳንዱ ሰው ምን ዓይነት ባሕርይ ሊኖረው የሚገባ ይመስላችኋል?” ብላችሁ ጠይቋቸው። ከዚያም ይሖዋ በአዲስ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ የሚፈልጋቸው ሰዎች ምን ዓይነት እንደሆኑ ለማሳየት ገላትያ 5:19-23⁠ን ልታነቡ ትችላላችሁ። ይህን ምሳሌ መጠቀማችሁ ሁለት አስፈላጊ ትምህርቶችን ለማስተማር ይረዳችኋል። አንደኛ፣ አምላክ ያወጣቸው መመሪያዎች እውነተኛ ሰላምና አንድነት እንዲኖር ያደርጋሉ። ሁለተኛ፣ ይሖዋ አሁን የሚሰጠን ትምህርት በአዲሱ ዓለም ለሚኖረው ሕይወት ያዘጋጀናል። (ኢሳ. 54:13፤ ዮሐ. 17:3) በጽሑፎቻችን ላይ የሚገኙ ተሞክሮዎችን በመጥቀስ ነጥቡን ይበልጥ ማጉላት ትችላላችሁ። “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” በሚለው የመጠበቂያ ግንብ ዓምድ ሥር የሚወጡ ተሞክሮዎችን መጠቀም ትችሉ ይሆናል። w16.09 5:13, 14

ቅዳሜ፣ መጋቢት 17

ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።—ኤፌ. 5:16

ጊዜያችን የተጣበበ ቢሆንም ሁላችንም ለግል ጥናትና ለቤተሰብ አምልኮ ጊዜ መመደብ ይኖርብናል። (ኤፌ. 5:15) ይሁንና ግባችን በጥናቱ ወቅት የተወሰኑ ገጾችን መሸፈን ወይም በስብሰባዎች ላይ የምንሰጠውን ሐሳብ መዘጋጀት ብቻ መሆን የለበትም። የአምላክ ቃል ልባችንን እንዲነካውና እምነታችንን እንዲያጠናክረው ማድረግ እንፈልጋለን። በመሆኑም በምናጠናበት ጊዜ ሌሎች ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ብቻ ሳይሆን እኛ ራሳችን ስለሚያስፈልገን ነገር ማሰብ አለብን። (ፊልጵ. 1:9, 10) ለአገልግሎት፣ ለስብሰባዎች ወይም ንግግር ለማቅረብ ስንዘጋጅ ትምህርቱን እኛ ራሳችን እንዴት ተግባራዊ እንደምናደርገው ላናስብ እንችላለን። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፦ የምግብ ዝግጅት ባለሙያ የሆነ ሰው ምግቡን ለሌሎች ከማቅረቡ በፊት መቅመስ ቢኖርበትም በዚህ ብቻ መኖር አይችልም። ጤናማ መሆን ከፈለገ ለራሱም ገንቢ ምግብ ማዘጋጀት ይኖርበታል። በተመሳሳይ እኛም መንፈሳዊ ፍላጎታችንን የሚያረካ ምግብ ለመመገብ ጥረት ማድረግ አለብን። w16.10 2:10, 11

እሁድ፣ መጋቢት 18

ሥርዓቶቹ የተቋቋሙት በአምላክ ቃል መሆኑን የምንረዳው በእምነት ነው፤ በመሆኑም የሚታየው ነገር ወደ ሕልውና የመጣው ከማይታዩ ነገሮች ነው።—ዕብ. 11:3

መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ምን እንደሆነ በዕብራውያን 11:1 ላይ ያብራራል። እምነት፣ ልናያቸው በማንችላቸው ሁለት ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው፦ (1) ‘ተስፋ የተደረጉት ነገሮች።’ ይህም ወደፊት እንደሚፈጸሙ ተስፋ የተሰጠባቸው ሆኖም ገና ያልተፈጸሙ ነገሮችን፣ ለምሳሌ ክፋት ሁሉ እንደሚወገድና አዲስ ዓለም እንደሚመጣ የተሰጠንን ተስፋ ይጨምራል። (2) ‘በዓይን ባይታዩም እውን የሆኑ ነገሮች።’ እዚህ ጥቅስ ላይ “ተጨባጭ ማስረጃ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አንድ ነገር በዓይን ባይታይም እውን መሆኑን የሚያሳይ ማረጋገጫን ያመለክታል፤ ለምሳሌ ይሖዋ አምላክን፣ ኢየሱስ ክርስቶስንና መላእክትን በዓይን ማየት ባንችልም እውን መሆናቸውን እናውቃለን፤ በሰማይ ያለው የአምላክ መንግሥት ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ታዲያ ተስፋችን እንደሚፈጸም እርግጠኛ እንደሆንን እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተስፋ በተሰጠባቸው የማይታዩ ነገሮች እንደምናምን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በንግግራችንና በድርጊታችን ነው፤ አለዚያ እምነታችን የተሟላ አይሆንም። w16.10 4:6

ሰኞ፣ መጋቢት 19

በየዕለቱ እርስ በርሳችሁ ተበረታቱ።—ዕብ. 3:13

ባለንበት ሁኔታ የተነሳ፣ የመንግሥቱን ሥራ ለመደገፍ ማከናወን የምንችለው ነገርና የምናደርገው መዋጮ ውስን ሊሆን ይችላል፤ ያም ቢሆን ይሖዋና ኢየሱስ ሁላችንም በዚህ ረገድ የምናደርገውን ጥረት በጣም ያደንቃሉ። (ሉቃስ 21:1-4፤ 2 ቆሮ. 8:12) በዕድሜ ከገፉ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መካከል አንዳንዶቹ በስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና ተሳትፎ ለማድረግ እንዲሁም በአገልግሎት አዘውትረው ለመካፈል ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ። ታዲያ እነዚህን ክርስቲያኖች እንደምናደንቃቸው ልንገልጽላቸውና ልናበረታታቸው አይገባም? አዎ፣ ሌሎችን ለማበረታታት የሚያስችሏችሁን አጋጣሚዎች ፈልጉ። ወንድሞቻችንን እንድናደንቅ የሚያደርግ ነገር ካስተዋልን ይህን ከማድረግ ወደኋላ የምንልበት ምን ምክንያት አለ? ጳውሎስና በርናባስ፣ በጵስድያ በምትገኘው አንጾኪያ በነበሩበት ጊዜ ያጋጠማቸውን ነገር እንመልከት። በዚያ የነበረው ምኩራብ አለቆች “ወንድሞች ሆይ፣ ሕዝቡን የሚያበረታታ የምትናገሩት ቃል ካላችሁ ተናገሩ” አሏቸው። በምላሹም ጳውሎስ ግሩም ንግግር ሰጣቸው። (ሥራ 13:13-16, 42-44) እኛም ሌሎችን የሚያበረታታ ነገር መናገር የምንችል ከሆነ ለምን ዝም እንላለን? ሌሎችን የማበረታታት ልማድ ካለን እነሱም በምላሹ ያበረታቱናል።—ሉቃስ 6:38፤ w16.11 1:3, 15, 16

ማክሰኞ፣ መጋቢት 20

የይሖዋ ዓይኖች በሁሉም ቦታ ናቸው፤ ክፉዎችንም ሆነ ጥሩ ሰዎችን ይመለከታሉ።—ምሳሌ 15:3

የይሖዋ ድርጅት አባል መሆን ምንኛ መታደል ነው! እርግጥ ነው፣ የአምላክን መሥፈርቶች እንዲሁም እሱ የሚጠብቅብንን ነገሮች ማወቃችን፣ ትክክል የሆነውን ነገር የማድረግና የእሱን ሉዓላዊነት የመደገፍ ኃላፊነት ያስከትልብናል። ይህ ዓለም በሥነ ምግባር እያዘቀጠ ሲሄድ እኛ ግን አምላክን በመምሰል “ክፉ የሆነውን ነገር [መጥላት]” ይኖርብናል። (መዝ. 97:10) “ጥሩውን መጥፎ፣ መጥፎውንም ጥሩ የሚሉ” ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎችን ከመከተል እንርቃለን። (ኢሳ. 5:20) አምላክን ማስደሰት ስለምንፈልግ አካላዊ፣ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ እንጥራለን። (1 ቆሮ. 6:9-11) ይሖዋን እንወደዋለን፤ በእሱም እንታመናለን፤ በመሆኑም ውድ በሆነው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት በግልጽ የሰፈሩ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን በመኖር ለእሱ ያለንን ታማኝነት እናሳያለን። በቤት፣ በጉባኤ፣ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤትም ሆነ በየትኛውም ቦታ እነዚህን መሥፈርቶች ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። w16.11 3:13

ረቡዕ፣ መጋቢት 21

ሰው ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ።—ሮም 13:1

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ቅን ልብ ቢኖራቸውም እንኳ ከ1914 እስከ 1919 ባሉት ዓመታት ውስጥ ለሰብዓዊ መንግሥታት ስለመገዛት ትክክለኛ አመለካከት ያልያዙበት ወቅት ነበር። በመሆኑም በቡድን ደረጃ ሲታይ ከጦርነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኞች ያልነበሩባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ግንቦት 30, 1918 ስለ ሰላም የሚጸለይበት ቀን እንዲሆን ሲያውጁ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹም በዚህ ሥነ ሥርዓት እንዲካፈሉ የሚያበረታታ ሐሳብ መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቶ ነበር። አንዳንድ ወንድሞች ለጦርነቱ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ሲሉ ቦንዶችን የገዙ ሲሆን ጥቂቶች ደግሞ መሣሪያ ታጥቀው ወደ ጦርነቱ ዘምተዋል። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በታላቂቱ ባቢሎን የተማረኩት፣ እርማትና ተግሣጽ ስላስፈለጋቸው እንደሆነ መደምደም ስህተት ነው። እነዚህ ወንድሞች ከሐሰት ሃይማኖት መለየት እንዳለባቸው ተገንዝበው ነበር፤ እንዲያውም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከባቢሎን ሙሉ በሙሉ ነፃ ለመውጣት ተቃርበው ነበር።—ሉቃስ 12:47, 48፤ w16.11 5:9

ሐሙስ፣ መጋቢት 22

እንደ ሥጋ ፈቃድ ሳይሆን እንደ መንፈስ ፈቃድ [እንመላለሳለን]።—ሮም 8:4

ጳውሎስ “እንደ ሥጋ ፈቃድ [መኖር]” የሚያስከትለውን አደጋ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች መጥቀስ ያስፈለገው ለምንድን ነው? አምላክ እንደ ወዳጆቹ አድርጎ የተቀበላቸውና እንደ ጻድቃን የሚቆጥራቸው በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ክርስቲያኖችስ ተመሳሳይ አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል? የሚያሳዝን ቢሆንም የትኛውም ክርስቲያን በኃጢአተኛ ሥጋው ምኞት መመራት ሊጀምር ይችላል። ለምሳሌ፣ ጳውሎስ በሮም ከነበሩት ወንድሞች መካከል አንዳንዶቹ “ለራሳቸው ፍላጎት ባሪያዎች” እንደነበሩ ጽፏል፤ ይህም የፆታ ፍላጎትን አሊያም የምግብ፣ የመጠጥ ወይም ሌላ ዓይነት ፍላጎትን ሊጨምር ይችላል። አንዳንዶቹ “የየዋሆችን ልብ [እያታለሉ]” ነበር። (ሮም 16:17, 18፤ ፊልጵ. 3:18, 19፤ ይሁዳ 4, 8, 12) በቆሮንቶስ ጉባኤ፣ ለተወሰነ ጊዜ ያህል “ከአባቱ ሚስት ጋር የሚኖር” ወንድም እንደነበረም እናስታውስ። (1 ቆሮ. 5:1) እንግዲያው አምላክ፣ ክርስቲያኖች “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር” እንደሌለባቸው በጳውሎስ በኩል ማሳሰቢያ መስጠቱ የሚያስገርም አይደለም። (ሮም 8:5, 6) ይህ ማስጠንቀቂያ ዛሬም ቢሆን ይሠራል። w16.12 2:5, 8, 9

ዓርብ፣ መጋቢት 23

በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።—ምሳሌ 12:25

ለምትቀርበው ሰው ስሜትህን አውጥተህ መናገርህ ጭንቀትህን ለማቅለል ይረዳሃል። ለትዳር ጓደኛህ፣ ለቅርብ ወዳጅህ አሊያም ለጉባኤህ ሽማግሌ ስሜትህን መናገርህ ስላለህበት ሁኔታ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖርህ ሊረዳህ ይችላል። ስሜትህን በግልጽና በሐቀኝነት መናገርህ ያለህበትን ሁኔታ ለመረዳትና መፍትሔ ለመፈለግ በእጅጉ ይረዳሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “መመካከር ከሌለ የታቀደው ነገር ሳይሳካ ይቀራል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል” ይላል። (ምሳሌ 15:22) ይሖዋ፣ በየሳምንቱ በሚደረጉት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አማካኝነትም አገልጋዮቹ ጭንቀትን መቋቋም እንዲችሉ ይረዳቸዋል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ፣ ስለ አንተ ከሚያስቡና ሊያበረታቱህ ከሚፈልጉ የእምነት ባልንጀሮችህ ጋር መገናኘት ትችላለህ። (ዕብ. 10:24, 25) በዚህ መንገድ ‘እርስ በርስ መበረታታታችሁ’ በመንፈሳዊ የሚያጠነክርህ ከመሆኑም በላይ ያለብህን ማንኛውንም ጭንቀት መቋቋም ቀላል እንዲሆንልህ ያደርጋል።—ሮም 1:12፤ w16.12 3:17, 18

ቅዳሜ፣ መጋቢት 24

[ሐና] ወደ ይሖዋ ትጸልይ ጀመር።—1 ሳሙ. 1:10

የጤና ችግርን ጨምሮ ከቁጥጥራችን ውጭ የሆኑ ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይሖዋ እንደሚያስብልን በመተማመን የሚያስጨንቀንን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ መጣል ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 5:6, 7) በተጨማሪም ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና ከሌሎች መንፈሳዊ ዝግጅቶች ጥቅም ለማግኘት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናድርግ። (ዕብ. 10:24, 25) ከእውነት ቤት የወጡ ልጆች ስላሏቸው ታማኝ ወላጆችስ ምን ማለት ይቻላል? አረጋዊው ሳሙኤል ትላልቅ የሆኑ ልጆቹ እሱ ያስተማራቸውን የጽድቅ መሥፈርቶች እንዲጠብቁ ማስገደድ አይችልም ነበር። (1 ሳሙ. 8:1-3) ሳሙኤል ጉዳዩን ለይሖዋ ከመተው በቀር ምንም አማራጭ አልነበረውም። ሆኖም ንጹሕ አቋሙን ይዞ በመቀጠል የሰማይ አባቱን ማስደሰት ይችላል። (ምሳሌ 27:11) በዛሬው ጊዜም እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ክርስቲያን ወላጆች አሉ። ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞች ወደ እሱ የሚመለሱበትን ጊዜ በጉጉት እንደሚጠባበቅ ይተማመናሉ። (ሉቃስ 15:20) በሌላ በኩል ደግሞ የእነሱ ታማኝነት ልጃቸው ወደ ይሖዋ እንዲመለስ እንደሚረዳው በመተማመን ምንጊዜም ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። w17.01 1:15, 16

እሁድ፣ መጋቢት 25

ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ።—ፊልጵ. 2:3

በጥቅሉ ሲታይ ትሑት ሰው፣ ልኩን የሚያውቅ ማለትም ስለ ችሎታውና ስላከናወነው ነገር ሚዛናዊ አመለካከት ያለው ሰው ነው፤ እንዲህ ዓይነቱ ግለሰብ ስህተቱን አምኖ መቀበልም ሆነ የሌሎችን ሐሳብ ማስተናገድ አይከብደውም። ትሕትና ይሖዋን በጣም ያስደስተዋል። ልክን ማወቅ የሚለውም አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት ስለ ራስ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝን እንዲሁም አቅምን ማወቅን ለማመልከት ነው። አንድ ሰው አቅሙን ማወቁ በሚያሳየው ባሕርይ ላይ ለውጥ ያመጣል፤ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ይህ አገላለጽ በዋነኝነት የሚያመለክተው ይህን ሳይሆን አይቀርም። አንድ ሰው ሳይታወቀው፣ በአስተሳሰቡም ሆነ በድርጊቱ ልኩን የማወቅ ችግር እንዳለበት የሚጠቁሙ ነገሮችን ማድረግ ሊጀምር ይችላል፤ ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? ይህን የሚጠቁሙ አንዳንድ ምልክቶችን እስቲ እንመልከት። ለራሳችንም ሆነ ላገኘናቸው መብቶች ከልክ ያለፈ ቦታ እንሰጥ ይሆናል። (ሮም 12:16) ምናልባትም ወደ ራሳችን ተገቢ ያልሆነ ትኩረት መሳብ ጀምረን ሊሆን ይችላል። (1 ጢሞ. 2:9, 10) አሊያም ደግሞ ያለንን ቦታ፣ ኃላፊነት ካላቸው ሰዎች ጋር ያለንን ቅርርብ ወይም የግል አመለካከታችንን መሠረት በማድረግ ሌሎች የእኛን አቋም እንዲቀበሉ ለመጫን እንፈተን ይሆናል፤ እንዲህ ስናደርግ ልካችንን ማወቅ ተስኖን እብሪተኛ ወደ መሆን እየሄድን እንደሆነ እንኳ ላይታወቀን ይችላል።—1 ቆሮ. 4:6፤ w17.01 3:6-8

ሰኞ፣ መጋቢት 26

የወጣቶች ክብር ጉልበታቸው ነው፤ የአረጋውያንም ግርማ ሽበታቸው ነው።—ምሳሌ 20:29

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የይሖዋ ሕዝቦች የሚያከናውኑት ሥራ ስፋት እየጨመረ መጥቷል። የይሖዋ ድርጅት፣ ምሥራቹን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እየተጠቀመ ነው። አንዳንድ በዕድሜ የገፉ ወንድሞች እንዲህ ካለው ለውጥ ጋር እኩል መራመድ ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። (ሉቃስ 5:39) ይህን ብንተወው እንኳ፣ ወጣቶች በዕድሜ ከገፉት አንጻር ሲታይ የተሻለ ኃይልና ጥንካሬ እንዳላቸው የታወቀ ነው። በመሆኑም በዕድሜ የገፉ ወንድሞች፣ ወጣቶች ተጨማሪ ኃላፊነት እንዲቀበሉ ማዘጋጀታቸው ፍቅር የሚንጸባረቅበትና ምክንያታዊ ነው። (መዝ. 71:18) በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ወንድሞች፣ ለወጣቶች ኃላፊነት መስጠት ሊከብዳቸው ይችላል። አንዳንዶች የሚወዱትን መብት እንዳያጡ ይሰጋሉ። ሌሎች ደግሞ እነሱ ካልተቆጣጠሩት ሥራው በትክክል እንደማይሠራ ያስባሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሌላ ሰው የሚያሠለጥኑበት ጊዜ እንደሌላቸው ይሰማቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቶች ተጨማሪ ኃላፊነት ሳይሰጣቸው ሲቀር ትዕግሥት እንዳያጡ መጠንቀቅ አለባቸው። w17.01 5:3, 4

ማክሰኞ፣ መጋቢት 27

አንድ የጽድቅ ድርጊትም ሁሉም ዓይነት ሰዎች ጻድቃን ናችሁ ተብለው ለሕይወት እንዲበቁ ያስችላል።—ሮም 5:18

አዳም ኃጢአት ከመሥራቱ በፊት እንደነበረው ሁሉ ኢየሱስም ፍጹም ሰው ሆነ። (ዮሐ. 1:14) ይሁንና ኢየሱስ ከአዳም በተለየ መልኩ፣ ይሖዋ ፍጹም ከሆነ ሰው የሚጠብቀውን መሥፈርት ሳያጓድል መኖር ችሏል። በጣም ከባድ ፈተና ቢደርስበትም እንኳ ኃጢአት አልፈጸመም፤ እንዲሁም ከአምላክ ሕጎች መካከል አንዱንም አልጣሰም። ኢየሱስ ፍጹም ሰው እንደመሆኑ መጠን በሰው ልጆች ምትክ በመሞት ከኃጢአትና ከሞት ሊታደጋቸው ይችላል። ኢየሱስ እንደ አዳም ፍጹም ሰው በመሆኑ ተመጣጣኝ ዋጋ መክፈል ችሏል። ፍጹም ከሆነ ሰው እንደሚጠበቀው ሁሉ ለአምላክ ሙሉ በሙሉ ታማኝና ታዛዥ ሆኗል። (1 ጢሞ. 2:6) ኢየሱስ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በመስጠት “ብዙ ሰዎች” መጨረሻ የሌለው ሕይወት ማግኘት የሚችሉበት አጋጣሚ ከፍቷል። (ማቴ. 20:28) በእርግጥም ቤዛው አምላክ መጀመሪያ ላይ የነበረው ዓላማ እንዲፈጸም ቁልፍ ሚና ይጫወታል። (2 ቆሮ. 1:19, 20) ቤዛው ታማኝ የሆኑ ሰዎች በሙሉ የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲያገኙ አስችሏል። w17.02 1:15, 16

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 9፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ዮሐንስ 12:12-19፤ ማርቆስ 11:1-11

ረቡዕ፣ መጋቢት 28

ከፊቱ ለሚጠብቀው ደስታ ሲል . . . ጸንቷል።—ዕብ. 12:2

ያለኸው ረጅምና ጨለማ በሆነ መተላለፊያ ዋሻ ውስጥ ነው እንበል። ዋሻው ውስጥ ሆነህ ‘ከዚህ በኋላ ብርሃን አይ ይሆን?’ የሚል ስጋት ያድርብህ ይሆናል። በተመሳሳይም የሚያጋጥሙህ ችግሮች ከአቅምህ በላይ እንደሆኑ የሚሰማህ ጊዜ ይኖር ይሆናል። ኢየሱስም እንኳ እንዲህ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ‘ኃጢአተኞች የተቃውሞ ንግግር’ የሰነዘሩበትና ውርደት የደረሰበት ከመሆኑም ሌላ “በመከራ እንጨት” ላይ ተሰቅሎ ተሠቃይቶ ሞቷል፤ ይህ ወቅት በሕይወቱ ውስጥ የጨለማ ጊዜ እንደነበር ጥያቄ የለውም! (ዕብ. 12:3) ያም ሆኖ ኢየሱስ ይህን ሁሉ በጽናት ተቋቁሟል። ጽናቱ በሚያስገኝለት ሽልማት፣ በተለይ ደግሞ ለአምላክ ስም መቀደስና ለይሖዋ ሉዓላዊነት መረጋገጥ በሚያደርገው አስተዋጽኦ ላይ ትኩረት አድርጎ ነበር። ኢየሱስ በመከራ ውስጥ ሆኖ ያሳለፈው የጨለማ ወቅት ጊዜያዊ ሲሆን እንደ ብርሃን የሆነለት በሰማይ የሚያገኘው ሽልማት ግን ዘላለማዊ ነው። በዛሬው ጊዜ አንተም ሥቃይ የሚያስከትሉና የሚደቁሱ መከራዎች ያጋጥሙህ ይሆናል። ይሁንና ወደ ዘላለም ሕይወት በሚመራው ጎዳና ላይ የሚያጋጥሙህ መከራዎች ጊዜያዊ እንደሆኑ አስታውስ። w16.04 2:10

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 10፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ዮሐንስ 12:20-50

ሐሙስ፣ መጋቢት 29

በልጁ [በኢየሱስ] ደም አማካኝነት ቤዛውን በመክፈሉ ነፃ ወጥተናል፤ አዎ፣ ለበደላችን ይቅርታ አግኝተናል።—ኤፌ. 1:7

በሥነ ምግባር ልቅ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ ኃጢአት አስነዋሪ ነገር መሆኑ እየቀረ ነው፤ በመሆኑም ብዙዎች ለኃጢአታቸው ቤዛ እንደሚያስፈልጋቸው አይገነዘቡም። ብዙዎች ኃጢአት ምን እንደሆነ፣ በእኛ ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እንዲሁም ከኃጢአት ባርነት ነፃ ለመውጣት ምን ማድረግ እንዳለብን አያውቁም። ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች ኃጢአት ምን እንደሆነ ሲገነዘቡ እንዲሁም ይሖዋ በታላቅ ፍቅሩና በጸጋው ተነሳስቶ ልጁን ወደ ምድር በመላክ ከኃጢአትና የኃጢአት ውጤት ከሆነው ከሞት እንደዋጀን ሲያውቁ በጣም ይደሰታሉ። (1 ዮሐ. 4:9, 10) የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት፣ አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር የገለጸበት ከሁሉ የላቀ ስጦታ ከመሆኑም ሌላ የይሖዋ ጸጋ የተትረፈረፈ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ላይ እምነት ካሳደርን፣ የኃጢአት ይቅርታ እንዲሁም ንጹሕ ሕሊና እንደምናገኝ ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! (ዕብ. 9:14) ይህ በእርግጥም ለሌሎች ልናካፍለው የሚገባ ምሥራች ነው! w16.07 4:6, 7

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 11፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ሉቃስ 21:1-36

ዓርብ፣ መጋቢት 30

[ክርስቶስ] ለእኛ ዘላለማዊ መዳን አስገኘልን።—ዕብ. 9:12

ይሖዋ ኃጢአታችንን ሙሉ በሙሉ ይቅር የሚለን በቤዛው ላይ እምነት ካለን ነው። የአምላክ ቃል ኃጢአታችን ‘ሊደመሰስ’ እንደሚችል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ሥራ 3:19-21) ይሖዋ በመንፈስ የተቀቡ አገልጋዮቹን በቤዛው አማካኝነት ልጆቹ አድርጎ ተቀብሏቸዋል። (ሮም 8:15-17) ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆንነውን ደግሞ እንደ ልጆቹ አድርጎ ለመቀበል የሚያስችል፣ ስማችን የተጻፈበት የምሥክር ወረቀት ያዘጋጀልን ያህል ነው። ወደ ፍጽምና ደረጃ ከደረስንና የመጨረሻውን ፈተና ካለፍን በኋላ ይሖዋ በምሳሌያዊ አነጋገር በምሥክር ወረቀቱ ላይ በመፈረም ምድራዊ ልጆቹ አድርጎ ይቀበለናል። (ሮም 8:20, 21፤ ራእይ 20:7-9) ይሖዋ ውድ ለሆኑት ልጆቹ ያለው ፍቅር ዘላለማዊ ነው። ቤዛው የሚያስገኛቸው ጥቅሞችም ቢሆኑ ዘላለማዊ ናቸው። ይህ ስጦታ መቼም ቢሆን ዋጋው አይቀንስም። ማንኛውም ሰውም ሆነ ኃይል ይህን ስጦታ ሊወስድብን አይችልም። w17.02 2:15, 16

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 12፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 26:1-5, 14-16፤ ሉቃስ 22:1-6

የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ዕለት
ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ
ቅዳሜ፣ መጋቢት 31

ማንም ኃጢአት ቢሠራ ግን በአብ ዘንድ ረዳት አለን፤ እሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።—1 ዮሐ. 2:1

ይሖዋ ወደ ራሱ የሳበን የትኞቹ የኃጢአት ዝንባሌዎች ይበልጥ እንደሚያስቸግሩን በሚገባ እያወቀ ነው። አልፎ አልፎ እንደምንሳሳትም ይገነዘባል። ይሁንና ይሖዋ ይህንን ሁሉ እያወቀ ወዳጆቹ እንድንሆን ጋብዞናል። አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ እጅግ ውድ ስጦታ ይኸውም የሚወደውን ልጁን ቤዛ አድርጎ ሰጥቶናል። (ዮሐ. 3:16) ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ንስሐ ከገባንና በዋጋ ሊተመን የማይችለውን ይህን ዝግጅት መሠረት በማድረግ ይቅር እንዲለን ይሖዋን ከጠየቅነው፣ ፍጹም ባንሆንም እንኳ ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት እንደሚቀጥል እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—1 ጢሞ. 1:15፤ w16.05 4:6, 7

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 13፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 26:17-19፤ ማርቆስ 14:12-16፤ ሉቃስ 22:7-13 (ኒሳን 14፦ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች) ዮሐንስ 13:1-5፤ 14:1-3

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ