የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es18 ገጽ 37-46
  • ሚያዝያ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሚያዝያ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2018
  • ንዑስ ርዕሶች
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 1
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 2
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 3
  • የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 16፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ዮሐንስ 20:2-18
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 4
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 5
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 6
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 7
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 8
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 9
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 10
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 11
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 12
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 13
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 14
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 15
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 16
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 17
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 18
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 19
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 20
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 21
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 22
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 23
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 24
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 25
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 26
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 27
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 28
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 29
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2018
es18 ገጽ 37-46

ሚያዝያ

እሁድ፣ ሚያዝያ 1

እናንተ በአንድ ወቅት አእምሯችሁ በክፉ ሥራዎች ላይ ያተኮረ ስለነበር ከአምላክ የራቃችሁና ጠላቶች ነበራችሁ፤ አሁን ግን . . . ራሱን ለሞት አሳልፎ በሰጠው ሰው ሥጋዊ አካል አማካኝነት ከራሱ ጋር አስታርቋችኋል።—ቆላ. 1:21, 22

ሰዎች ከፈጣሪያቸው ጋር ወዳጅነት መመሥረት እንደሚችሉ የማሳወቅ ኃላፊነት አለብን። የሰው ልጆች በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ እምነት ከሌላቸው አምላክ እንደ ጠላቶቹ ይመለከታቸዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በወልድ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ወልድን የማይታዘዝ ግን የአምላክ ቁጣ በላዩ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” (ዮሐ. 3:36) ደስ የሚለው ነገር፣ የክርስቶስ መሥዋዕት ከአምላክ ጋር እርቅ ለመፍጠር የሚያስችል መንገድ ከፍቷል። (2 ቆሮ. 5:18-20) ለሰዎች መንፈሳዊውን እውነት እናስተምራለን፤ እንዲሁም ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ እንረዳለን። ይህም የስብከቱ ሥራችን አብይ ገጽታ ነው። w16.07 4:8-10

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 14፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ዮሐንስ 19:1-42

ሰኞ፣ ሚያዝያ 2

ስምህ ይቀደስ።—ማቴ. 6:9

ኢየሱስ በጸሎት ናሙናው ላይ ያቀረበው የመጀመሪያው ልመና ከአምላክ ስም መቀደስ ጋር የተያያዘ ነው። ይሖዋ ቅዱስ ስለሆነ እሱ የሚያወጣቸው መመሪያዎችና ሕጎች በሙሉ ቅዱስ ናቸው። ይሁንና ሰይጣን በኤደን የአትክልት ስፍራ፣ አምላክ ለሰው ልጆች ሕግ ለማውጣት ባለው መብት ላይ ጥያቄ አንስቷል። ሰይጣን ስለ ይሖዋ ውሸት በመናገር የአምላክን ቅዱስ ስም አጥፍቷል። (ዘፍ. 3:1-5) በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ የይሖዋን ስም ከልቡ ይወደዋል። (ዮሐ. 17:25, 26) ኢየሱስ፣ መለኮታዊው ስም እንዲቀደስ አስተዋጽኦ አበርክቷል። (መዝ. 40:8-10) እንዴት? ኢየሱስ በአኗኗሩና ባስተማራቸው ነገሮች፣ ይሖዋ የሚያወጣቸው መሥፈርቶች ትክክለኛ እንደሆኑና ማንኛውንም መመሪያ የሚሰጠን ለራሳችን ጥቅም መሆኑን ሰዎች እንዲገነዘቡ አድርጓል። ኢየሱስ በሰማይ ላለው አባቱ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ መሆኑ፣ አንድ ፍጹም ሰው አምላክ ላወጣቸው የጽድቅ መሥፈርቶች ሙሉ በሙሉ ታዛዥ መሆን እንደሚችል አረጋግጧል። w17.02 2:2-4

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 15፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 27:62-66 (ኒሳን 16፦ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች) ዮሐንስ 20:1

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 3

ለበጉ . . . ክብር፣ ግርማና ኃይል ለዘላለም ይሁን።—ራእይ 5:13

በጉ የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ኢየሱስ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የአምላክ በግ” ተብሎ ተገልጿል። (ዮሐ. 1:29) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ እስካሁን በምድር ላይ ከገዙትም ሆነ እየገዙ ካሉት ነገሥታት ሁሉ የላቀ እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “እሱ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ነው፤ ያለመሞትን ባሕርይ የተላበሰው እሱ ብቻ ነው፤ ሊቀረብ በማይችል ብርሃን ውስጥ ይኖራል፤ እሱን ያየ ወይም ሊያየው የሚችል አንድም ሰው የለም።” (1 ጢሞ. 6:14-16) በእርግጥም ከነገሥታት መካከል ለኃጢአታችን ሲል ሕይወቱን በፈቃደኝነት ቤዛ አድርጎ የሰጠ ማን አለ? አንተስ በሰማይ ከሚገኙት እልፍ አእላፍ ፍጥረታት ጋር በመሆን በጉን ለማወደስ አትገፋፋም? እነሱ እንዲህ ብለዋል፦ “ታርዶ የነበረው በግ ኃይል፣ ብልጽግና፣ ጥበብ፣ ብርታት፣ ክብር፣ ግርማና በረከት ሊቀበል ይገባዋል።” (ራእይ 5:12) ይሖዋንና ክርስቶስን ማክበር ለምርጫ የተተወ ጉዳይ አይደለም። የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን የተመካው ይህን በማድረጋችን ላይ ነው።—መዝ. 2:11, 12፤ ዮሐ. 5:23፤ w17.03 1:3, 4

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 16፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ዮሐንስ 20:2-18

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 4

ወደዚያ ብትመልሱኝ . . . በእርግጥ እኔ መሪያችሁ እሆናለሁ!—መሳ. 11:9

ዮፍታሔ ስለ እስራኤላውያን ታሪክ በሚገባ ማወቁ፣ በይሖዋ ዓይን ትክክል ስለሆነውና ስህተት ስለሆነው ነገር ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረው አድርጓል። (መሳ. 11:12-27) በሙሴ ሕግ ውስጥ የሚገኙት አምላክ ያወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች በዮፍታሔ አስተሳሰብና ስሜት ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ይሖዋ ቂም መያዝን ይጠላል፤ ሕዝቦቹም እርስ በርስ እንዲዋደዱ ይፈልጋል፤ ዮፍታሔ ይህን ያውቅ ነበር። በተጨማሪም አንድ ሰው ‘የሚጠሉት’ ሰዎች እንኳ ችግር ላይ ሲወድቁ ዝም ብሎ ማለፉ ተገቢ አለመሆኑን ሕጉ እንደሚያስተምር ያውቃል። (ዘፀ. 23:5፤ ዘሌ. 19:17, 18) እንደ ዮሴፍ ያሉ የእምነት ምሳሌዎችም በዮፍታሔ አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ሳያሳድሩ አልቀሩም፤ ዮሴፍ ወንድሞቹ ‘ቢጠሉትም’ ምሕረት አሳይቷቸዋል። (ዘፍ. 37:4፤ 45:4, 5) ዮፍታሔ እንዲህ ያሉ ሰዎች በተዉት ምሳሌ ላይ ማሰላሰሉ፣ ይሖዋን የሚያስደስት እርምጃ እንዲወስድ ረድቶታል። ወንድሞቹ ያደረጉት ነገር በጣም እንደጎዳው ግልጽ ነው፤ ይሁንና ይህ ሁኔታ ይሖዋንና ሕዝቦቹን ከማገልገል ወደኋላ እንዲል አላደረገውም።—መሳ. 11:1-3፤ w16.04 1:8, 9

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 5

አንድ ላይ ይሰበሰቡ . . . ነበር።—ሥራ 2:42

ከጥንት ዘመን ጀምሮ የይሖዋ ሕዝቦች አንድ ላይ የሚሰበሰቡባቸውን አጋጣሚዎች ከፍ አድርገው ይመለከቷቸዋል። የክርስቲያን ጉባኤ እንደተቋቋመ የኢየሱስ ተከታዮች ‘አንድ ላይ መሰብሰብ’ ጀምረዋል። አንተም ብትሆን ልክ እንደ እነሱ አዘውትረህ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። ያም ቢሆን ሁሉም ክርስቲያኖች እንቅፋቶች ያጋጥሟቸዋል። በሰብዓዊ ሥራችን፣ ፕሮግራማችን የተጣበበ በመሆኑ አሊያም በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችን የተነሳ በመዛላችን በስብሰባዎች ላይ መገኘት አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል። የስብሰባዎችን ጥቅም መገንዘባችን እነዚህን እንቅፋቶች አሸንፈን በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን የመገኘት ልማድ ለማዳበር ሊረዳን ይችላል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻችን፣ ከባድ ሕመምን የመሳሰሉ ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ችግሮች ስላሉባቸው አዘውትረው በስብሰባዎች ላይ መገኘት አይችሉም። ሽማግሌዎች፣ አቅማቸው ውስን የሆነው እነዚህ ክርስቲያኖች በስብሰባዎች ላይ ከሚቀርቡት መንፈሳዊ ፕሮግራሞች እንዲጠቀሙ ለመርዳት ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ለምሳሌ፣ ስብሰባውን በስልክ እንዲከታተሉ ወይም ተቀድቶ እንዲያዳምጡት ማድረግ ይቻላል። w16.04 3:3

ዓርብ፣ ሚያዝያ 6

አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።—ዮሐ. 16:33

ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች የተዉት ምሳሌ ለመጽናት የሚያስፈልገንን ጥበብና ብርታት ይሰጠናል። ለምሳሌ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የባቢሎንን መንግሥት የሚወክለውን ምስል ለማምለክ ፈቃደኞች አልሆኑም። (ዳን. 3:16-18) በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህ ወጣቶች ስለወሰዱት ቆራጥ እርምጃ በማንበባቸው፣ ለሚኖሩበት አገር ባንዲራ አምልኮ አናቀርብም ለማለት የሚያስችላቸውን ድፍረት አግኝተዋል። ኢየሱስም ቢሆን በዓለም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ግጭቶች ውስጥ ፈጽሞ ጣልቃ አልገባም። የእሱ ምሳሌ ሌሎችን ሊጠቅም እንደሚችል ስለተገነዘበ ደቀ መዛሙርቱን “አይዟችሁ!” ብሏቸዋል። በጉባኤህ ያሉ ወንድሞችና እህቶችም ድጋፍ ሊሰጡህ ይችላሉ። የጉባኤው አባላት የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ካወቁ ሊያበረታቱህ ይችላሉ። ስለ አንተ እንዲጸልዩ ጠይቃቸው። እርግጥ ነው፣ ወንድሞቻችን እንዲያበረታቱንና እንዲጸልዩልን የምንፈልግ ከሆነ እኛም ለእነሱ እንዲሁ ልናደርግላቸው ይገባል።—ማቴ. 7:12፤ w16.04 4:16, 18

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 7

ሕዝብህ በገዛ ፈቃዱ ራሱን ያቀርባል።—መዝ. 110:3

የገንዘብ መዋጮ ከመሰብሰብ ጋር በተያያዘ የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ምን ይመስላል? ሥራቸው የሚደገፈው በፈቃደኝነት በሚደረግ መዋጮ ነው። (2 ቆሮ. 9:7) በመንግሥት አዳራሾቻቸውም ሆነ በትላልቅ ስብሰባዎቻቸው ላይ ሙዳየ ምጽዋት አይዞርም። ያም ቢሆን ግን በ2015 ብቻ የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን በመስበክ 1.93 ቢሊዮን ሰዓት አሳልፈዋል፤ እንዲሁም በየወሩ ከዘጠኝ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን በነፃ መጽሐፍ ቅዱስን ያስተምራሉ። የሚያስገርመው ደግሞ ለሥራቸው ደሞዝ የማይከፈላቸው ከመሆኑም ሌላ ወጪያቸውን የሚሸፍኑት ራሳቸው ናቸው፤ ይህን የሚያደርጉትም በደስታ ነው። አንድ ምሁር፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑትን ሥራ በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፦ “ዋናው ግባቸው መስበክና ማስተማር ነው። . . . ቀሳውስት የሏቸውም፤ ይህም ወጪያቸውን በእጅጉ ይቀንሰዋል።” ታዲያ ይህን ሥራ ለማከናወን የሚያነሳሳን ምክንያት ምንድን ነው? በአጭር አነጋገር፣ ይህን ሥራ በፈቃዳችን የምናከናውነው ይሖዋንና ሰዎችን ስለምንወድ ነው። እንዲህ ያለ የፈቃደኝነት መንፈስ በማሳየት በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለው ትንቢት እንዲፈጸም እናደርጋለን። w16.05 2:9

እሁድ፣ ሚያዝያ 8

ከሰማይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት . . . ነው።—ያዕ. 3:17

ይህን ማሳሰቢያ ልብ ማለታችን ንጹሕ ያልሆኑ ሐሳቦችና ዝንባሌዎች በውስጣችን እንዲቀሰቀሱ ከሚያደርጉ መዝናኛዎች እንድንርቅ ይረዳናል። አስተዋይ የሆኑ ክርስቲያኖች ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች በሚያንጸባርቁ መጻሕፍት፣ ፊልሞች ወይም ጌሞች መዝናናት ተገቢ ስለመሆኑ ጥያቄ አይፈጠርባቸውም። ምክንያቱም ይሖዋ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው አመለካከት በቃሉ ውስጥ በግልጽ ሰፍሯል። ከአንድ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ይሖዋን የሚያስደስቱ የተለያዩ ውሳኔዎች ማድረግ ይቻላል። ከባድ ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ ነገሮች ሲያጋጥሙን ግን የሽማግሌዎችን ወይም ተሞክሮ ያላቸውን ክርስቲያኖች ምክር መጠየቁ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። (ቲቶ 2:3-5፤ ያዕ. 5:13-15) እርግጥ ነው፣ ሌሎች ለእኛ እንዲወስኑልን መጠየቁ ተገቢ አይደለም። ክርስቲያኖች የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት ማሠልጠን ይኖርባቸዋል። (ዕብ. 5:14) ጳውሎስ “እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል” በማለት በመንፈስ መሪነት ከጻፈው ሐሳብ ጋር ሁላችንም ተስማምተን መኖር ይገባናል።—ገላ. 6:5፤ w16.05 3:15, 16

ሰኞ፣ ሚያዝያ 9

ቀደም ሲል አምላክን የምሳደብ፣ አሳዳጅና እብሪተኛ [ነበርኩ]።—1 ጢሞ. 1:13

ይሖዋ ሰዎችን ሲመለከት ትኩረት የሚሰጠው ለውጫዊ ገጽታቸው አይደለም። ከዚህ ይልቅ ልባቸውን ይኸውም ውስጣዊ ማንነታቸውን ይመረምራል። (1 ሳሙ. 16:7ለ) አምላክ የክርስቲያን ጉባኤን ሲያቋቁም ያደረገው ነገር ይህን በግልጽ ያሳያል። ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር እምብዛም የማይፈለጉ የሚመስሉ ብዙ ሰዎችን ወደ ራሱና ወደ ልጁ ስቧል። (ዮሐ. 6:44) ሳኦል የተባለን ፈሪሳዊ እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል። ‘ልብን የሚመረምረው’ አምላክ ሳኦልን ዋጋ እንደሌለው ሸክላ አድርጎ አልቆጠረውም። (ምሳሌ 17:3) ከዚህ ይልቅ ውድ ዕቃ ተደርጎ ሊቀረጽ እንደሚችል የሸክላ አፈር አድርጎ ተመልክቶታል፤ እንዲያውም “በአሕዛብ እንዲሁም በነገሥታትና በእስራኤል ልጆች ፊት” የሚመሠክር “የተመረጠ ዕቃ” ተብሎ ተጠርቷል። (ሥራ 9:15) በተጨማሪም አምላክ ቀደም ሲል ሰካራሞች፣ የፆታ ብልግና የሚፈጽሙና ሌቦች የነበሩ አንዳንድ ሰዎችን “ክቡር ለሆነ አገልግሎት” ሊውሉ እንደሚችሉ ዕቃዎች አድርጎ ተመልክቷቸዋል። (ሮም 9:21፤ 1 ቆሮ. 6:9-11) እነዚህ ሰዎች ከአምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት እየቀሰሙና እምነታቸው እያደገ ሲሄድ በይሖዋ ለመቀረጽ ፈቃደኞች ሆነዋል። w16.06 1:4

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 10

እነሆ፣ በሸክላ ሠሪ እጅ እንዳለ ጭቃ፣ እናንተም በእኔ እጅ እንዲሁ ናችሁ።—ኤር. 18:6

አምላክ፣ ምንጊዜም በቀላሉ እንደሚቀረጽ የሸክላ ጭቃ እንድንሆን እኛን ለመርዳት ካደረጋቸው ዝግጅቶች መካከል ቃሉ፣ የክርስቲያን ጉባኤና አገልግሎት ይገኙበታል። የሸክላ ጭቃ እንዲለሰልስ ውኃ እንደሚያስፈልገው ሁሉ እኛም በይሖዋ እጅ በቀላሉ መቀረጽ እንድንችል መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብና ማሰላሰል ይኖርብናል። የእስራኤል ነገሥታት የአምላክን ሕግ ቅጂ ለራሳቸው እንዲጽፉና በየዕለቱ እንዲያነቡት ይሖዋ ይጠብቅባቸው ነበር። (ዘዳ. 17:18, 19) ሐዋርያትም ቅዱሳን መጻሕፍትን ማንበባቸውና ባነበቡት ላይ ማሰላሰላቸው ለአገልግሎታቸው እንደሚጠቅማቸው ተገንዝበው ነበር። በጻፏቸው መጻሕፍት ላይ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በተደጋጋሚ ጊዜያት የጠቀሱ ከመሆኑም ሌላ የሚሰብኩላቸውን ሰዎችም ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዲያነቡ ያበረታቷቸው ነበር። (ሥራ 17:11) እኛም የአምላክን ቃል በየዕለቱ የማንበብንና የማሰላሰልን አስፈላጊነት እንገነዘባለን። (1 ጢሞ. 4:15) ይህን ማድረጋችን በይሖዋ ፊት ምንጊዜም ትሑትና በቀላሉ የምንቀረጽ እንድንሆን ይረዳናል። w16.06 2:10

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 11

እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።—ዮሐ. 13:35

ብሔራት ዘግናኝ ጦርነቶችን ባካሄዱበት በዚህ ዘመን፣ የይሖዋ አገልጋዮች አንዳቸው ለሌላው ፍቅር ማሳየታቸው በጣም አስፈላጊ ነበር። ለምሳሌ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ብቻ 55 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች አልቀዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ግን በዚህ ዓለም አቀፋዊ ጦርነት አልተካፈሉም። (ሚክ. 4:1, 3) በመሆኑም “ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ” መሆን ችለዋል። (ሥራ 20:26) የአምላክ ሕዝቦች እድገት እያደረጉ ያሉት በጥላቻ በተሞላ ዓለም ውስጥ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህ ዓለም “የዚህ ሥርዓት አምላክ” በሆነው በሰይጣን ቁጥጥር ሥር እንደሆነ ይናገራል። (2 ቆሮ. 4:4) ሰይጣን የዚህን ዓለም የፖለቲካ ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙኃን ይቆጣጠራል። ምሥራቹ እንዳይሰበክ ማገድ ግን አይችልም። ይሁንና ሰይጣን የቀረው ጊዜ በጣም አጭር እንደሆነ ስለሚያውቅ ሰዎችን ከእውነተኛው አምልኮ እንዲርቁ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም።—ራእይ 12:12፤ w16.06 4:3, 4

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 12

እስቲ የሜዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ።—ማቴ. 6:28

ኢየሱስ አሁን ትኩረታችንን በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ እንድናደርግ አበረታቶናል። “የሜዳ አበቦች” ካላቸው ውበት የምንማረው ብዙ ነገር አለ። ምናልባትም ኢየሱስ፣ ‘መሸ ደህና እደሩ’ እንደሚባለው አበባ ያሉ የተለያዩ አበቦችን በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል፤ ሁሉም የየራሳቸው ውበት አላቸው። እነዚህ ፍጥረታት ራሳቸውን ለማልበስ መፍተል፣ መስፋት ወይም መሸመን አያስፈልጋቸውም። ይሁንና አብበው ሲታዩ በጣም ውብ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰለሞን እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዷ አላጌጠም” ይላል። ኢየሱስ ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልእክት ልብ በሉ፤ “አምላክ ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ ምድጃ የሚጣለውን የሜዳ ተክል እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም?” (ማቴ. 6:29, 30) ያለ ምንም ጥርጥር ያለብሳቸዋል! ይሁንና የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እምነት ጎድሏቸው ነበር። (ማቴ. 8:26፤ 14:31፤ 16:8፤ 17:20) ጠንካራ እምነት ማዳበርና በይሖዋ መታመን ያስፈልጋቸው ነበር። እኛስ? ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ለማሟላት ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው እንዳለው ሙሉ እምነት አለን? w16.07 1:15, 16

ዓርብ፣ ሚያዝያ 13

የአምላክ ጸጋ መልካም መጋቢዎች እንደመሆናችሁ መጠን፣ እያንዳንዳችሁ በተቀበላችሁት ስጦታ መሠረት የተሰጣችሁን ስጦታ አንዳችሁ ሌላውን ለማገልገል ተጠቀሙበት።—1 ጴጥ. 4:10

በሕይወታችን ውስጥ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ይሖዋ ያንን ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል። (1 ጴጥ. 1:6) የይሖዋ ጸጋ በልዩ ልዩ መንገዶች በመገለጹ ብዙ በረከቶች ማግኘት ችለናል። ከእነዚህ በረከቶች አንዱ የኃጢአት ይቅርታ ነው። የይሖዋ ጸጋ የኃጢአት ይቅርታ እንድናገኝ መንገድ ከፍቶልናል፤ ይህ የሚሆነው ግን ንስሐ ከገባንና የኃጢአት ዝንባሌዎቻችንን ለማሸነፍ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋችንን ከቀጠልን ነው። (1 ዮሐ. 1:8, 9) የአምላክ ምሕረት፣ ልባችን በአመስጋኝነት እንዲሞላና እሱን ለማክበር እንድንነሳሳ ሊያደርገን ይገባል። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “[ይሖዋ] ከጨለማው ሥልጣን ታድጎን ወደሚወደው ልጁ መንግሥት አሻግሮናል፤ ልጁም ቤዛውን በመክፈል ነፃ እንድንወጣ ይኸውም የኃጢአት ይቅርታ እንድናገኝ አድርጎናል።” (ቆላ. 1:13, 14) የኃጢአት ይቅርታ ማግኘታችን ሌሎች አስደናቂ በረከቶችን እንድናገኝ አጋጣሚውን ከፍቶልናል። w16.07 3:7-9

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 14

እሱ ራስህን ይጨፈልቃል።—ዘፍ. 3:15

ሰይጣን በኤደን ውስጥ ችግር እንዲፈጠር ቢያደርግም ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የመጀመሪያውን ትንቢት በመናገር ለሰው ዘር ተስፋ ፈነጠቀ። አምላክ ዲያብሎስን ‘በመጨፍለቅ’ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ያጡትን ነገር ይኸውም በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዲያገኙ የሚያስችል ዘር አዘጋጀ፤ ይህም የመጀመሪያው የይሖዋ ዓላማ እንዲፈጸም ያደርጋል። (ዮሐ. 3:16) አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ማመፃቸው በራሳቸው ትዳርም ሆነ ከዚያ በኋላ በተመሠረቱ ሌሎች ጋብቻዎች ሁሉ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ አሳድሯል። ለምሳሌ፣ ሔዋንና ዘሮቿ የሆኑት ሴቶች በእርግዝናቸው ወቅት ከባድ ሕመም የሚኖራቸው ሲሆን የሚወልዱትም በሥቃይ ይሆናል። ሴቶች ምኞታቸው በሙሉ ወደ ባሎቻቸው ይሆናል፤ ባሎች ግን በሚስቶቻቸው ላይ ገዢ ከመሆንም አልፈው በዛሬው ጊዜ በብዙ ትዳሮች ውስጥ እንደሚታየው በሚስቶቻቸው ላይ ጥቃት ይፈጽማሉ። (ዘፍ. 3:16) መጽሐፍ ቅዱስ ባሎች የራስነት ሥልጣናቸውን ፍቅር በተሞላበት መንገድ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ይገልጻል። ሚስቶች ደግሞ ለባሎቻቸው የራስነት ሥልጣን መገዛት አለባቸው። (ኤፌ. 5:33) ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ባልና ሚስት፣ እርስ በርስ ስለሚደጋገፉ በመካከላቸው ሊፈጠር የሚችለውን ግጭት መቀነስ ወይም ጨርሶ ማስቀረት ይችላሉ። w16.08 1:6, 7

እሁድ፣ ሚያዝያ 15

አንቺ ሚስት፣ ባልሽን ታድኚው እንደሆነ ምን ታውቂያለሽ? ወይስ አንተ ባል፣ ሚስትህን ታድን እንደሆነ ምን ታውቃለህ?—1 ቆሮ. 7:16

አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ የትዳር ጓደኛ ይኖራቸው ይሆናል። ሁኔታው እንዲህ ቢሆንም እንኳ አብረው መኖራቸው የተሻለ የሚሆንባቸው ምክንያቶች እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ቆሮ. 7:12-14) የይሖዋ አምላኪ ያልሆነው የትዳር ጓደኛ ቢገነዘበውም ባይገነዘበውም፣ አማኝ በሆነው የትዳር ጓደኛው የተነሳ “ተቀድሷል።” ልጆቻቸውም ቢሆኑ “ቅዱሳን” እንደሆኑ ተደርገው የሚቆጠሩ ሲሆን መለኮታዊ ጥበቃ ያገኛሉ። በሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ማለት ይቻላል ለትዳር ጓደኛቸው ‘መዳን’ ምክንያት የሆኑ ክርስቲያን ባለትዳሮች አሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ክርስቲያን ሚስቶች ለባሎቻቸው እንዲገዙ ምክር ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “ለቃሉ የማይታዘዙ ባሎች ካሉ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው ምግባር እንዲማረኩ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ሊማረኩ የሚችሉትም ንጹሕ ምግባራችሁንና የምታሳዩትን ጥልቅ አክብሮት ሲመለከቱ ነው።”—1 ጴጥ. 3:1-4፤ w16.08 2:14, 15

ሰኞ፣ ሚያዝያ 16

እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ።—1 ጴጥ. 1:22

የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች “የወንድማማች መዋደድ” ሊኖረን እንደሚገባና አንዳችን ሌላውን ማገልገል እንዳለብን ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። (ሉቃስ 22:24-27) የአምላክ ልጅ፣ ሌሎችን ለማገልገል ሲል ሕይወቱን ጨምሮ ሁሉ ነገሩን ሰጥቷል። (ማቴ. 20:28) ዶርቃ “መልካም በማድረግና ምጽዋት በመስጠት የምትታወቅ” ሴት ነበረች። (ሥራ 9:36, 39) በሮም ትገኝ የነበረችው ማርያም የተባለች እህትም ለጉባኤው ‘ብዙ ደክማለች።’ (ሮም 16:6) ታዲያ አዲሶች፣ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን መርዳት አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘቡ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የጎለመሱ ክርስቲያኖች፣ የታመሙና በዕድሜ የገፉ ሰዎችን በሚጠይቁበት ወቅት አብረዋቸው እንዲሄዱ አዲሶችን ሊጋብዟቸው ይችላሉ። ወላጆችም እንዲህ ያሉትን ወንድሞች ለመጠየቅ ሲሄዱ፣ ተገቢ እንደሆነ ከተሰማቸው ልጆቻቸውን ይዘው መሄድ ይችላሉ። ሽማግሌዎች፣ በዕድሜ የገፉ ውድ ወንድሞቻችን ተስማሚ ምግብ እንዲያገኙና ቤታቸው በሚገባ እንዲያዝ ዝግጅት በሚያደርጉበት ጊዜ ሌሎች እንዲያግዟቸው መጠየቅ ይችላሉ። በዚህ መልኩ ወጣቶችና አዲሶች ለሌሎች ደግነት እንዲሁም ለሁሉም የጉባኤ አባላት ፍቅር ማሳየት ስለሚቻልባቸው መንገዶች ይማራሉ።—ሮም 12:10፤ w16.08 4:13, 14

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 17

በጥሩ አፈር ላይ የተዘራው ደግሞ ቃሉን የሚሰማና የሚያስተውል ነው፤ ፍሬም ያፈራል።—ማቴ. 13:23

በፈረንሳይ የምትኖር አንዲት ወጣት እህት “በትምህርት ቤታችን ያሉ አስተማሪዎች በዛሬው ጊዜም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑ ተማሪዎች እንዳሉ ሲያውቁ በጣም ይገረማሉ” ብላለች። አንተም ይሖዋን የምታገለግል አሊያም ስለ እሱ እየተማርክ ያለህ ወጣት ልትሆን ትችላለህ፤ ታዲያ የብዙኃኑን አመለካከት እንድትቀበል፣ ለምሳሌ በፈጣሪ ሳይሆን በዝግመተ ለውጥ እንድታምን ጫና እየተደረገብህ እንዳለ ይሰማሃል? ከሆነ እምነትህን ለማጠናከርና ምንጊዜም ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ልትወስዳቸው የምትችላቸው እርምጃዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ አምላክ የሰጠህን የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም ነው፤ የማመዛዘን ችሎታህ “ምንጊዜም ይጠብቅሃል።” ይህ ችሎታ እምነትህን ሊያጠፉ የሚችሉ ዓለማዊ ፍልስፍናዎች ተጽዕኖ እንዳያሳድሩብህ ይከላከልልሃል። (ምሳሌ 2:10-12) እውነተኛ እምነት ለመገንባት ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ማዳበር ያስፈልጋል። (1 ጢሞ. 2:4) እንግዲያው የአምላክን ቃል ወይም ክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችንን በምታጠናበት ጊዜ ሐሳቡን ገረፍ ገረፍ አድርገህ አትለፈው። ያነበብከውን ነገር ‘ማስተዋል’ እንድትችል የማመዛዘን ችሎታህን ተጠቀም። w16.09 4:1-3

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 18

ክፉውን በመልካም አሸንፍ።—ሮም 12:21

አስተዳደጋችን ጥሩ ባይሆን ወይም አሁን ያለንበት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ቢመስልም እንኳ በጽናት መታገላችንን መቀጠል ያስፈልገናል። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ እንደሚባርከን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዘፍ. 39:21-23) እስቲ በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠመህንና ፈተና የሆነብህን አንድ ሁኔታ ለማሰብ ሞክር። ምናልባትም ግፍና ጭፍን ጥላቻ እየደረሰብህ አሊያም ሰዎች እያፌዙብህ ይሆናል። ወይም አንድ ሰው በቅናት ተነሳስቶ በሐሰት እየወነጀለህ ሊሆን ይችላል። ተስፋ ቆርጠህ እጅ ከመስጠት ይልቅ ያዕቆብ፣ ራሔልና ዮሴፍ ይሖዋን በደስታ ማገልገላቸውን ለመቀጠል የረዳቸው ምን እንደሆነ አስታውስ። እነዚህ ሰዎች ለመንፈሳዊ ነገሮች ከፍተኛ አድናቆት ስለነበራቸው አምላክ ብርታት ሰጥቷቸዋል እንዲሁም ባርኳቸዋል። መታገላቸውን የቀጠሉ ከመሆኑም ሌላ ካቀረቡት ልባዊ ጸሎት ጋር የሚስማማ እርምጃ ይወስዱ ነበር። የምንኖረው የዚህ ክፉ ሥርዓት መጨረሻ በተቃረበበት ወቅት በመሆኑ፣ ከፊታችን የተዘረጋልንን አስተማማኝ ተስፋ አጥብቀን መያዛችን በጣም አስፈላጊ ነው! አንተስ፣ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ስትል ለመታገል ፈቃደኛ ነህ? w16.09 2:8, 9

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 19

የመንፈስ ፍሬ . . . እምነት [ነው]።—ገላ. 5:22

ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን በይሖዋ ላይ እምነት በማሳደር ረገድ እናንተ ራሳችሁ ምሳሌ ሆናችሁ መገኘታችሁ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ልጆቻችሁ የምታደርጉትን ነገር ያስተውላሉ፤ ይህም በእነሱ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ጥርጥር የለውም። ስለዚህ ወላጆች የራሳችሁን እምነት መገንባታችሁን ቀጥሉ። ልጆቻችሁ ይሖዋ ለእናንተ ምን ያህል እውን እንደሆነ እንዲመለከቱ አድርጉ። በቤርሙዳ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት፣ የሚያስጨንቅ ሁኔታ በሚያጋጥማቸው ወቅት ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጣቸው ከልጆቻቸው ጋር ሆነው የሚጸልዩ ሲሆን ልጆቻቸውንም እንዲጸልዩ ያበረታቷቸዋል። “በተጨማሪም ትልቋ ልጃችንን ‘ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ታመኚ፤ ራስሽን በአገልግሎት አስጠምጂ እንዲሁም ከልክ በላይ አትጨነቂ’ እንላታለን። እንዲህ ማድረግ የሚያስገኘውን ውጤት ስትመለከት ይሖዋ እየረዳን እንዳለ ትገነዘባለች። ይህም በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላት እምነት እንዲጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል” በማለት ተናግረዋል። እርግጥ ነው፣ እናንተ ምንም ያህል ጥረት ብታደርጉም እምነት ማዳበር ያለባቸው ልጆቹ ራሳቸው ናቸው። የእናንተ ድርሻ መትከልና ውኃ ማጠጣት ነው። ሊያሳድገው የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። (1 ቆሮ. 3:6) እንግዲያው ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጣችሁ ጸልዩ፤ እንዲሁም ውድ የሆኑ ልጆቻችሁን ለማስተማር ከፍተኛ ጥረት አድርጉ፤ ይህን ካደረጋችሁ ይሖዋ ይባርካችኋል።—ኤፌ. 6:4፤ w16.09 5:16-18

ዓርብ፣ ሚያዝያ 20

[እነዚህን ትእዛዛት በልጆችህ] ውስጥ ቅረጻቸው።—ዘዳ. 6:7

ሰርዥ እና ባለቤቱ ሚውሪዬል በሌላ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ከሦስት ዓመት በላይ ካገለገሉ በኋላ፣ የ17 ዓመት ልጃቸው በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል እንደማያስደስተው አስተዋሉ። ሰርዥ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ሁኔታ ልጃችን መንፈሳዊ እድገት እንዳያደርግ እንቅፋት እንደሆነበት ስናስተውል ወደ ቀድሞ ጉባኤያችን ለመመለስ ወሰንን።” ወላጆች ወደ ቀድሞ ጉባኤያቸው ለመመለስ እንዲወስኑ የሚያደርጋቸው ምን ሊሆን ይችላል? በመጀመሪያ ደረጃ፣ በአንድ በኩል ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱ እየረዱ በሌላ በኩል ደግሞ ለልጆቻቸው አዲስ ቋንቋ ለማስተማር የሚያስፈልገው ጊዜና ኃይል ያላቸው መሆኑን መመርመር ይኖርባቸዋል። ሁለተኛ፣ ልጆቻቸው ለመንፈሳዊ ነገሮች ያላቸው ጉጉት እንደቀነሰ አሊያም በሌላ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ለማገልገል ፍላጎት እንደሌላቸው ይገነዘቡ ይሆናል። ክርስቲያን ወላጆች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካስተዋሉ፣ ልጆቻቸው እውነትን አጥብቀው እስኪይዙ ድረስ ልጆቹ በደንብ በሚረዱት ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ ለመመለስ ሊወስኑ ይችላሉ።—ዘዳ. 6:5-7፤ w16.10 2:14, 15

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 21

ኖኅ ገና ስላልታዩት ነገሮች መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ከተቀበለ በኋላ አምላካዊ ፍርሃት ያሳየውና ቤተሰቡን ለማዳን መርከብ የሠራው በእምነት ነበር።—ዕብ. 11:7

የኖኅ ጎረቤቶች፣ ኖኅ ይህን የሚያህል ግዙፍ መርከብ የሚሠራው ለምን እንደሆነ ጠይቀውት መሆን አለበት። ታዲያ ኖኅ ለጥያቄያቸው መልስ ከመስጠት ተቆጥቦ ወይም ጉዳዩ እንደማይመለከታቸው ነግሯቸው ይሆን? በፍጹም! ኖኅ የነበረው እምነት፣ በድፍረት እንዲመሠክርና በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች አምላክ ስለሚያመጣው ፍርድ እንዲያስጠነቅቅ አነሳስቶታል። ይሖዋ የነገረውን የሚከተለውን መልእክት ቃል በቃል ሳይደግምላቸው አልቀረም፦ “በእነሱ የተነሳ ምድር በዓመፅ ስለተሞላች ሥጋ ለባሽ የሆነውን ሁሉ ለማጥፋት ወስኛለሁ፤ . . . ከሰማያት በታች የሕይወት እስትንፋስ ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃ አመጣለሁ። በምድር ላይ ያለ ነገር ሁሉ ይጠፋል።” በተጨማሪም ኖኅ መዳን የሚችሉበትን ብቸኛ መንገድ ገልጾላቸው እንደሚሆን ጥያቄ የለውም፤ “ወደ መርከቡ መግባት ይኖርባችኋል” የሚለውን የይሖዋን ትእዛዝ ደግሞላቸዋል። ስለዚህ ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” በመሆንም እምነቱን በተግባር አሳይቷል።—ዘፍ. 6:13, 17, 18፤ 2 ጴጥ. 2:5፤ w16.10 4:7

እሁድ፣ ሚያዝያ 22

[ሰው] አካሄዱን . . . በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም።—ኤር. 10:23

ክርስቲያን ወላጆች በአምላክ ቃል መሠረት ልጆቻቸውን በማሠልጠን ለይሖዋ ታማኝ እንደሆኑ ያሳያሉ። ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች፣ የሚኖሩበት ማኅበረሰብ ስለ ልጆች አስተዳደግ ያለው አመለካከት ተጽዕኖ እንዳያደርግባቸው ይጠነቀቃሉ። የዓለም መንፈስ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ቦታ የለውም። (ኤፌ. 2:2) አንድ ክርስቲያን አባት ‘በእኛ አገር ልጆችን የሚያሠለጥኑት እናቶች ናቸው’ ብሎ ሊያስብ አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን የማያሻማ መመሪያ ይሰጣል፦ “አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን . . . በይሖዋ ተግሣጽና ምክር [ትምህርት፤ መመሪያ] አሳድጓቸው።” (ኤፌ. 6:4 ግርጌ) አምላክን የሚፈሩ አባቶችና እናቶች፣ ልጆቻቸው እንደ ሳሙኤል እንዲሆኑ ይፈልጋሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ “ሳሙኤል እያደገ ሄደ፤ ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበር” ይላል። (1 ሳሙ. 3:19) የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ግምት ውስጥ ሳናስገባ ከቤተሰባችን አሊያም ከሥራ ምርጫችን ጋር የተያያዙ አስፈላጊ ውሳኔዎችን ማድረግ ጥበብ ይሆናል? በፍጹም! አካሄዳችንን አቃንተን መምራት ስለማንችል የሰማዩ አባታችን እርዳታ ያስፈልገናል። w16.11 3:14, 15

ሰኞ፣ ሚያዝያ 23

የጣቶችህን ሥራ ሰማያትን፣ አንተ የሠራሃቸውን ጨረቃንና ከዋክብትን ስመለከት፣ ታስበው ዘንድ ሟች ሰው ምንድን ነው?—መዝ. 8:3, 4

አምላክ ወደር የማይገኝለት አደራጅ መሆኑን የፍጥረት ሥራው ያረጋግጣል። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ በጥበብ ምድርን መሠረተ። በማስተዋል ሰማያትን አጸና” ይላል። (ምሳሌ 3:19) እኛ የምናውቀው የአምላክን ‘መንገድ ዳር ዳር’ ብቻ ነው፤ “ስለ እሱ የሰማነው የሹክሹክታ ያህል ብቻ ነው!” (ኢዮብ 26:14) ስለ ፕላኔቶች፣ ከዋክብትና ጋላክሲዎች ያለን ውስን እውቀት እንኳ አጽናፈ ዓለም አስደናቂ በሆነ መንገድ እንደተደራጀ እንድንገነዘብ ያደርገናል። ጋላክሲዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከዋክብትን ያቀፉ ሲሆን ሁሉም በሕዋ ውስጥ በተደራጀ መንገድ ይንቀሳቀሳሉ። በእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ያሉ ፕላኔቶች፣ የትራፊክ ሕግ አክብረው እንደሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ምሕዋራቸውን ጠብቀው በፀሐይ ዙሪያ ይሽከረከራሉ! በጽንፈ ዓለም ውስጥ የሚታየው አስደናቂ ሥርዓት “ሰማያትን” እና ምድርን ‘በጥበብ የሠራውን’ ይሖዋን ልናወድሰው፣ ታማኝ ልንሆንለት እንዲሁም ልናመልከው እንደሚገባ ያሳያል።—መዝ. 136:1, 5-9፤ w16.11 2:3

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 24

[ይሖዋ] በጽድቅ መባ የሚያቀርብ ሕዝብ ይኖረዋል።—ሚል. 3:3

ሚልክያስ 3:1-3 የተቀቡት ‘የሌዊ ልጆች ስለሚነጹበት’ ጊዜ (ከ1914 እስከ 1919 መጀመሪያ አካባቢ) ይናገራል። በዚህ ጊዜ፣ “እውነተኛው ጌታ” ይኸውም ይሖዋ አምላክና “የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ” ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚያገለግሉትን ለመመርመር መጡ። የይሖዋ ሕዝቦች አስፈላጊው እርማት ከተሰጣቸው በኋላ ስለነጹ ተጨማሪ የአገልግሎት ኃላፊነት ለመቀበል ዝግጁ ሆኑ። በ1919 ለእምነት ቤተሰቡ መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርብ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ተሾመ። (ማቴ. 24:45) አሁን የአምላክ ሕዝቦች ከታላቂቱ ባቢሎን ተጽዕኖ ነፃ ወጡ። ለይሖዋ ጸጋ ምስጋና ይግባውና፣ ሕዝቡ ስለ አምላክ ፈቃድ ያላቸው እውቀትና በሰማይ ለሚኖረው አባታቸው ያላቸው ፍቅር ከዚያ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ መጥቷል። ለዚህ በረከት ምንኛ አመስጋኞች ነን! w16.11 5:14

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 25

የሰማያትን መስኮቶች ከፍቼ ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የተትረፈረፈ በረከት ባላፈስላችሁ፣ እስቲ በዚህ ፈትኑኝ።—ሚል. 3:10

ይሖዋ “አስቀድሞ ስለወደደን” እኛም እንወደዋለን። (1 ዮሐ. 4:19) ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ጥልቅ ፍቅር እንዳለው የሚያሳይበት አንዱ መንገድ የሚባርካቸው መሆኑ ነው። ለይሖዋ ያለን ፍቅር እያደገ በሄደ መጠን አምላክ መኖሩንና ለሚወዳቸው ወሮታ ከፋይ መሆኑን ይበልጥ እርግጠኛ ስለምንሆን እምነታችን እየጠነከረ ይሄዳል። (ዕብ. 11:6) ወሮታ ከፋይ መሆን የይሖዋ ማንነትና የመንገዶቹ አቢይ ገጽታ ነው። አምላክ ከልብ ለሚፈልጉት ወሮታ ከፋይ መሆኑን እርግጠኞች ካልሆንን እምነታችን ሙሉ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም “እምነት ተስፋ የተደረጉትን ነገሮች በእርግጠኝነት መጠበቅ ማለት ነው።” (ዕብ. 11:1) በእርግጥም እምነት ማለት ይሖዋ ቃል የገባቸው በረከቶች መፈጸማቸው እንደማይቀር ሙሉ በሙሉ መተማመን ነው። በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ የእሱን በረከት እንድናገኝ ግብዣ አቅርቦልናል። ይሖዋ እንድንፈትነው ያቀረበውን ግብዣ በመቀበል አድናቆታችንንና አመስጋኝነታችንን እናሳያለን። w16.12 4:1-3

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 26

በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሞት ያስከትላል።—ሮም 8:6

አምላክን ለበርካታ ዓመታት ያገለገለ ክርስቲያንም እንኳ በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሊጀምር ይችላል። ጳውሎስ ይህን ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ስለ ምግብ፣ ስለ ሥራ፣ ስለ መዝናኛ እንዲሁም ስለ ፍቅር ግንኙነት ጨርሶ ማሰብ እንደሌለብን መግለጹ አልነበረም። ማንኛውም የአምላክ አገልጋይ በሕይወቱ ውስጥ ስለ እነዚህ ነገሮች ማሰቡ አይቀርም። ኢየሱስ በምግብ ይደሰት የነበረ ሲሆን ሌሎችንም መግቧል። መዝናኛም ቢሆን አስፈላጊ መሆኑን ያውቅ ነበር። ጳውሎስም በትዳር ውስጥ ፍቅርን መግለጽ ተገቢ መሆኑን በደብዳቤው ላይ ገልጿል። ጳውሎስ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል “አእምሮን ወይም ልብን በአንድ ነገር ላይ ማሳረፍ፣ የታሰበበት ግብ ለማውጣት የማመዛዘን ችሎታን መጠቀም” የሚል ትርጉም አለው። እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ ሰዎች የኃጢአት ዝንባሌዎቻቸው ሕይወታቸውን እንዲመሩት ይፈቅዳሉ። አንድ ምሁር በሮም 8:5 ላይ ስለተጠቀሱት ሰዎች ሲናገሩ “ትኩረታቸውን የሚስበው ማለትም ከምንም በላይ የሚማርካቸው፣ አዘውትረው የሚያወሩትና የሚሠሩት እንዲሁም የሚያስደስታቸው ሥጋዊ ነገር ነው” ብለዋል። w16.12 2:5, 9, 10

ዓርብ፣ ሚያዝያ 27

በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?—ያዕ. 4:12

ማንኛውም ሰው ለጊዜውም ቢሆን በሥጋዊ ምኞቶች ከተሸነፈ ከልኩ አልፎ ሊሄድ ይችላል። ለራስ ክብር እንደ መፈለግ፣ ቅናትና ግልፍተኝነት ያሉት ባሕርያት በርካታ ሰዎችን የእብሪት ድርጊት ወደ መፈጸም መርተዋቸዋል። እንደ አቢሴሎም፣ ዖዝያና ናቡከደነጾር ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች እንዲህ ባሉት የሥጋ ሥራዎች የተሸነፉ ሲሆን ይሖዋም የእብሪት ድርጊት በመፈጸማቸው እንዲዋረዱ አድርጓል። (2 ሳሙ. 15:1-6፤ 18:9-17፤ 2 ዜና 26:16-21፤ ዳን. 5:18-21) ይሁንና አንድ ሰው ልኩን እንደማያውቅ የሚያሳይ ድርጊት እንዲፈጽም የሚያደርጉት ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። እስቲ በዘፍጥረት 20:2-7 እና በማቴዎስ 26:31-35 ላይ የሚገኙትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እንደ ምሳሌ እንመልከት። አቢሜሌክ እና ጴጥሮስ የፈጸሙት ድርጊት እብሪተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው? ወይስ በዘገባው ላይ የተጠቀሰውን ድርጊት የፈጸሙት ስለ ጉዳዩ ሙሉ መረጃ ስላልነበራቸው አሊያም ስለተዘናጉ ይሆን? ማናችንም ብንሆን የሰውን ልብ ማንበብ አንችልም፤ በመሆኑም ሰዎች አንድን ነገር ለማድረግ የተነሳሱበትን ውስጣዊ ግፊት በተመለከተ ፍርድ ከመስጠት መቆጠባችን ጥበብ ከመሆኑም ሌላ ለእነዚህ ሰዎች ፍቅር እንዳለን ያሳያል። w17.01 3:9, 10

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 28

እሷ ግን በድሃ አቅሟ ያላትን መተዳደሪያ ሁሉ ሰጥታለች።—ሉቃስ 21:4

ልክ እንደ ድሃዋ መበለት በዘመናችን የሚገኙ በርካታ ክርስቲያኖችም መንግሥቱን እስካስቀደሙ ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚያሟላላቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። (ማቴ. 6:33) የወንድም ማልኮምን ተሞክሮ እስቲ እንመልከት። እሱና ባለቤቱ ይሖዋን ባገለገሉባቸው አሥርተ ዓመታት የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል። ወንድም ማልኮም እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ ያልጠበቅናቸው አልፎ ተርፎም አስጨናቂ የሆኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በእሱ የሚታመኑ ሰዎችን ይባርካቸዋል።” ታዲያ ወንድም ማልኮም ምን ምክር ሰጥቷል? “በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ውጤታማ እና ሥራ የበዛልን ለመሆን መጸለይ ይኖርብናል። ትኩረት የምናደርገው ልናከናውነው በማንችለው ነገር ላይ ሳይሆን ማከናወን በምንችለው ነገር ላይ መሆን አለበት።” ይህ ሥርዓት ‘በክፋት ላይ ክፋት እየጨመረ’ በመሄድ ላይ ነው፤ በመሆኑም ችግሮች እየተባባሱ እንደሚሄዱ እንጠብቃለን። (2 ጢሞ. 3:1, 13) ሆኖም እነዚህ ችግሮች እንዲያሽመደምዱን መፍቀድ የለብንም። ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር አለብን፤ እንዲሁም አቅማችን እስከፈቀደው ድረስ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። w17.01 1:17-19

እሁድ፣ ሚያዝያ 29

ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም።—1 ዜና 17:4

ዳዊት ለይሖዋ አገልግሎት የሚውል “ቤት” ወይም ቤተ መቅደስ አለመኖሩ ስላሳሰበው ቤተ መቅደስ ለመሥራት ፈለገ። ሆኖም የዛሬው የዕለት ጥቅስ እንደሚለው ይሖዋ ከዚህ የተለየ መመሪያ አስተላለፈ። “የምኖርበትን ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም” ብሎ ለዳዊት እንዲነግረው ናታንን አዘዘው። ይሖዋ ዳዊትን መባረኩን እንደሚቀጥል ቃል የገባለት ቢሆንም ቤተ መቅደሱን የሚገነባው ግን እሱ ሳይሆን ልጁ ሰለሞን እንደሆነ ገለጸለት። በዚህ ጊዜ ዳዊት ምን ምላሽ ሰጠ? (1 ዜና 17:1-4, 8, 11, 12፤ 29:1) ዳዊት ለቤተ መቅደሱ ግንባታ የሚመሰገነው እሱ እንደማይሆን ቢያውቅም ለግንባታው ድጋፍ ከመስጠት ወደኋላ አላለም። ደግሞም ሕንፃው የተጠራው የዳዊት ሳይሆን የሰለሞን ቤተ መቅደስ ተብሎ ነው። ዳዊት የልቡን ፍላጎት ማሳካት ባለመቻሉ አዝኖ ሊሆን ቢችልም የግንባታ ሥራውን ሙሉ በሙሉ ደግፏል። በራሱ ተነሳሽነት ግንባታውን የሚያከናውኑ ሠራተኞችን ያደራጀ ሲሆን ለግንባታው የሚሆን ብረት፣ መዳብ፣ ብር፣ ወርቅ እንዲሁም የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎችን አከማችቷል። በተጨማሪም ሰለሞንን እንዲህ በማለት አበረታቶታል፦ “አሁንም ልጄ ሆይ፣ ይሖዋ ከአንተ ጋር ይሁን፤ . . . ተሳክቶልህ የአምላክህን የይሖዋን ቤት ለመሥራት ያብቃህ።”—1 ዜና 22:11, 14-16፤ w17.01 5:6, 7

ሰኞ፣ ሚያዝያ 30

ለስምህም ስትል ታደገን፤ ኃጢአታችንንም ይቅር በለን።—መዝ. 79:9

ስደት ቢደርስብንም እንኳ የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶችና ሕጎች ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። የይሖዋን መመሪያዎች በሕይወታችን ውስጥ በሥራ ላይ በማዋል ብርሃናችን በሰው ፊት እንዲበራ እናደርጋለን፤ ይህ ደግሞ ለይሖዋ ስም ክብር ያመጣል። (ማቴ. 5:14-16) የአምላክ ቅዱስ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን፣ የይሖዋ ሕጎች ትክክለኛ መሆናቸውንና የሰይጣን ክስ ሐሰት መሆኑን በአኗኗራችን እናሳያለን። እርግጥ ነው፣ እንደ ማንኛውም ሰው ስህተት መሥራታችን አይቀርም፤ በዚህ ጊዜ ከልባችን ንስሐ በመግባት ይሖዋን ከሚያስነቅፉ ድርጊቶች እንርቃለን። ይሖዋ በክርስቶስ መሥዋዕት ላይ እምነት ካለን ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል። ራሳቸውን ለእሱ የወሰኑ ሰዎችን አገልጋዮቹ አድርጎ ይቀበላቸዋል። ይሖዋ፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ልጆቹ አድርጎ በመቀበል ጻድቃን ብሎ ጠርቷቸዋል፤ ‘ሌሎች በጎችን’ ደግሞ ወዳጆቹ አድርጎ በመቀበል እንደ ጻድቃን ይቆጥራቸዋል። (ዮሐ. 10:16፤ ሮም 5:1, 2፤ ያዕ. 2:21-25) በመሆኑም በአሁኑ ጊዜም እንኳ ቤዛው፣ በሰማዩ አባታችን ዘንድ የጽድቅ አቋም እንዲኖረንና ስሙን በማስቀደስ ረገድ የበኩላችንን ድርሻ እንድናበረክት አስችሎናል። w17.02 2:5, 6

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ