ግንቦት
ማክሰኞ፣ ግንቦት 1
አሞናውያን ለእስራኤላውያን ተገዙ።—መሳ. 11:33
ዮፍታሔ እስራኤላውያንን ከአሞናውያን እጅ ነፃ ለማውጣት የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ያውቅ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ ድል ካቀዳጀው፣ ከጦርነት ሲመለስ ሊቀበለው መጀመሪያ የሚወጣውን ሰው ለይሖዋ “የሚቃጠል መባ” አድርጎ እንደሚያቀርብ ቃል ገባ። (መሳ. 11:30, 31) ዮፍታሔ የገባው ቃል ምን ትርጉም አለው? ሰውን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ በይሖዋ ዘንድ አስጸያፊ ድርጊት ነው። በመሆኑም ዮፍታሔ ማንንም ሰው ቃል በቃል መሥዋዕት ለማድረግ እንዳላሰበ ግልጽ ነው። (ዘዳ. 18:9, 10) በሙሴ ሕግ መሠረት የሚቃጠል መባ ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ የሚቀርብ መሥዋዕት ነው፤ ስለሆነም ዮፍታሔ፣ ግለሰቡን ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ አገልግሎት እንደሚሰጥ መናገሩ መሆን አለበት። ዮፍታሔ የገባው ቃል፣ ግለሰቡ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በማደሪያው ድንኳን ውስጥ እንዲያገለግል መስጠትን ያመለክታል። ይሖዋ የዮፍታሔን ስእለት የተቀበለው ሲሆን በምላሹም ታላቅ ድል እንዲቀዳጅ አደረገው። (መሳ. 11:32) ዮፍታሔ ከጦርነት ሲመለስ እሱን ለመቀበል የወጣችው የሚወዳት አንድያ ልጁ ነበረች! እንግዲህ ፈተናው እዚህ ላይ ነው። ዮፍታሔ ቃሉን ይጠብቅ ይሆን? w16.04 1:11-13
ረቡዕ፣ ግንቦት 2
የተነበበውን ነገር ማስተዋል እንዲችል ሕዝቡን ይረዱት ነበር።—ነህ. 8:8
ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለው መጽሐፍ በአብዛኞቹ ጉባኤዎች ውስጥ ወደ ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ተጠንቷል። በዚህ ዝግጅት አማካኝነት የአምላክን ባሕርያት ማጥናታችን እንዲሁም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሰጧቸውን ከልብ የመነጩ ሐሳቦች መስማታችን በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን ይበልጥ እንድንወደው አላደረገንም? በተጨማሪም በጉባኤ ለሚቀርቡ ንግግሮችና ሠርቶ ማሳያዎች እንዲሁም ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባቡ ትኩረት መስጠታችን ስለ አምላክ ቃል ያለን እውቀት እንዲጨምር ያደርጋል። በስብሰባዎች ላይ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን። (1 ተሰ. 4:9, 10) ለምሳሌ ያህል፣ የመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕሶች የሚዘጋጁት የአምላክ ሕዝቦች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ግቦችህን መለስ ብለህ እንድትገመግም፣ የእምነት ባልንጀሮችህን ይቅር እንድትል ወይም የጸሎትህን ይዘት እንድታሻሽል ያነሳሳህ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት አለ? በሳምንቱ መሃል በሚደረገው ስብሰባ ላይ ለአገልግሎታችን ሥልጠና እናገኛለን። ምሥራቹን መስበክና ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተማር የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን።—ማቴ. 28:19, 20፤ w16.04 3:4, 5
ሐሙስ፣ ግንቦት 3
ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል።—ሮም 15:4
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ስለሚገኙት በግለሰቦች መካከል ስለተፈጠሩ ግጭቶች አስበህ ታውቃለህ? እስቲ በዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች ላይ የተገለጹትን ብቻ እንመልከት። ቃየን አቤልን ገድሎታል (ዘፍ. 4:3-8)፤ ላሜህም የመታውን አንድ ወጣት ገድሏል (ዘፍ. 4:23)፤ በአብርሃም (በአብራም) እና በሎጥ እረኞች መካከል ጠብ ተፈጥሯል (ዘፍ. 13:5-7)፤ ሣራ (ሦራ) አጋር ስለናቀቻት በአብርሃም ላይ ተቆጥታለች (ዘፍ. 16:3-6)፤ እስማኤል ባገኘው ሰው ሁሉ ላይ እጁን ያነሳል፤ ያገኘውም ሰው ሁሉ እጁን ያነሳበታል። (ዘፍ. 16:12) እነዚህ ግጭቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩት ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ፍጽምና የሚጎድላቸው የሰው ልጆች፣ በመካከላቸው ያለው ሰላም እንዳይደፈርስ መጠንቀቅ ያለባቸው ለምን እንደሆነ እንዲማሩ ለመርዳት ነው። በተጨማሪም ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስገነዝበናል። በገሃዱ ዓለም የነበሩ ሰዎች ስለገጠሟቸው ችግሮች የሚያወሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን በማንበብ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ያጋጠሟቸውን ችግሮች ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ያስገኘላቸውን ውጤት መመልከታችን እኛም በሕይወታችን ውስጥ ተመሳሳይ ሁኔታ ሲያጋጥመን የእነሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል። በእርግጥም እነዚህ ዘገባዎች እንዲህ ያሉ ችግሮች ሲያጋጥሙን ምን ማድረግ እንዳለብንና እንደሌለብን ለመወሰን ይረዱናል። w16.05 1:1, 2
ዓርብ፣ ግንቦት 4
አስቀድሞም ምሥራቹ ለብሔራት ሁሉ መሰበክ አለበት።—ማር. 13:10
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ምሥራቹን ለመስበክ የትኞቹን ዘዴዎች ተጠቅመዋል? ምሥራቹን ለማድረስ፣ ሰዎች በብዛት ወደሚገኙባቸው ቦታዎችና ከቤት ወደ ቤት ሄደዋል። የስብከቱ ሥራ፣ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ መልእክቱን መስማት የሚገባውን ሰው መፈለግን ይጨምራል። (ማቴ. 10:11፤ ሉቃስ 8:1፤ ሥራ 5:42፤ 20:20) እንዲህ ያለው የተደራጀ አሠራር ያለ አድልዎ ለመመሥከር ያስችላል። የይሖዋ ምሥክሮችስ በዚህ ረገድ ምን ታሪክ አስመዝግበዋል? ኢየሱስ ከ1914 ጀምሮ ንጉሥ ሆኖ እየገዛ መሆኑን የሚሰብኩት እነሱ ብቻ ናቸው። ኢየሱስ ባዘዘው መሠረት ለስብከቱ ሥራ ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። ፒለርስ ኦቭ ፌዝ—አሜሪካን ኮንግርጌሽንስ ኤንድ ዜር ፓርትነርስ የተባለው መጽሐፍ “የይሖዋ ምሥክሮች . . . ተቀዳሚ ሥራቸው፣ ስለ መጪው የዓለም ፍጻሜና ለመዳን ስለሚያስፈልገው ነገር የሚገልጸውን መንፈሳዊ መልእክት ማዳረስ መሆኑን ፈጽሞ አይዘነጉም” ብሏል። የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የተጠቀሙባቸውን ዘዴዎች በመከተል ይህን መልእክት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል። w16.05 2:10, 12
ቅዳሜ፣ ግንቦት 5
ይሖዋን መፍራት ምን ማለት እንደሆነ ትረዳለህ።—ምሳሌ 2:5
በይሖዋ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ስናደርግ ይበልጥ ወደ እሱ እንቀርባለን። (ያዕ. 4:8) የእሱን ሞገስና በረከት እናገኛለን። ይህ ደግሞ በሰማይ ባለው አባታችን ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። እንግዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች አምላክ ስለ አንድ ጉዳይ ያለውን አመለካከት እንድናውቅ ስለሚረዱን በእነሱ ለመመራት ጥረት እናድርግ። እርግጥ ነው፣ ምንጊዜም ስለ ይሖዋ የምንማራቸው አዳዲስ ነገሮች ይኖራሉ። (ኢዮብ 26:14) ያም ቢሆን ትጋት የተሞላበት ጥረት በማድረግ በዛሬው ጊዜም እንኳ ጥሩ ውሳኔ ለመወሰን የሚረዳንን ጥበብ፣ እውቀትና ማስተዋል ማግኘት እንችላለን። (ምሳሌ 2:1-5) ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች የሚያመነጯቸው ሐሳቦችና የሚያወጧቸው ዕቅዶች በየጊዜው ይለዋወጣሉ፤ ከዚህ በተቃራኒ መዝሙራዊው “የይሖዋ ውሳኔዎች ለዘላለም ይጸናሉ፤ የልቡ ሐሳብ ከትውልድ እስከ ትውልድ ጸንቶ ይኖራል” በማለት ተናግሯል። (መዝ. 33:11) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አስተሳሰባችንና ድርጊታችን፣ እጅግ ጥበበኛ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ አስተሳሰብ ጋር የሚስማማ ከሆነ ከሁሉ የተሻለ ውሳኔ ማድረግ እንችላለን። w16.05 3:17
እሁድ፣ ግንቦት 6
ይሖዋ ግን የሚያየው ልብን ነው።—1 ሳሙ. 16:7
ይሖዋ ልብን የማንበብና እሱ የመረጣቸውን ወደ ራሱ የመሳብ ችሎታ እንዳለው ማመናችን፣ በክልላችን ውስጥም ሆነ በጉባኤ ባሉ ሰዎች ላይ ከመፍረድ እንድንቆጠብ ሊያደርገን ይገባል። (ዮሐ. 6:44) ይሖዋ እንደ ሸክላ ሠሪ እንደሚቀርጸን መገንዘባችን ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ባለን አመለካከት ላይም ተጽዕኖ ያሳድራል። (ኢሳ. 64:8) ለወንድሞችህና ለእህቶችህ የአምላክ ዓይነት አመለካከት አለህ? ገና በመቀረጽ ላይ እንዳሉ አድርገህ ትመለከታቸዋለህ? ይሖዋ የአንድን ሰው ውስጣዊ ማንነት ይመለከታል፤ እንዲሁም በእሱ የተካኑ እጆች ቢቀረጽ ምን ዓይነት ሰው ሊወጣው እንደሚችል ያውቃል። በመሆኑም ይሖዋ ሰዎችን ሲመለከት አዎንታዊ ጎናቸው ላይ እንጂ ጉድለታቸው ላይ አያተኩርም፤ ያለባቸው ጉድለት ወደፊት እንደሚወገድ ያውቃል። (መዝ. 130:3) እኛም የወንድሞቻችንን አዎንታዊ ጎን በመመልከት እሱን መምሰል እንችላለን። እንዲያውም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ሲጥሩ አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ከታላቁ ሸክላ ሠሪ ጋር መተባበር እንችላለን። (1 ተሰ. 5:14, 15) “ስጦታ” የሆኑት ሽማግሌዎች በዚህ ረገድ ቅድሚያውን መውሰድ ይኖርባቸዋል።—ኤፌ. 4:8, 11-13፤ w16.06 1:4-6
ሰኞ፣ ግንቦት 7
የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።—1 ቆሮ. 10:12
ምሥራቹን ለሰዎች መስበክ ትሕትናን እንዲሁም የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን ማዳበር እንድንችል ይረዳናል። (ገላ. 5:22, 23) ከዚህም ሌላ የክርስቶስ ዓይነት ባሕርያት ስናንጸባርቅ መልእክታችንን እናስውባለን፤ ይህ ደግሞ የአንዳንድ ሰዎች አመለካከት እንዲለወጥ ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ በአውስትራሊያ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች፣ ለአንዲት ሴት ሊመሠክሩላት ሲሉ ሥርዓት የጎደለው ምላሽ ሰጠቻቸው፤ እነሱ ግን ስትናገር በአክብሮት አዳመጧት። ይሁንና በኋላ ላይ ሴትየዋ በድርጊቷ ስለተጸጸተች ለቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ ጻፈች። ደብዳቤው በከፊል እንዲህ ይላል፦ “እነዚያን በጣም ታጋሽና ትሑት ሰዎች፣ ራሴን በማመጻደቅና እነሱን ዝቅ በማድረግ ስላናገርኳቸው ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ። የአምላክን ቃል የሚናገሩ ሰዎችን በዚያ መንገድ ማባረሬ ሞኝነት እንደሆነ ተሰምቶኛል።” አስፋፊዎቹ በትንሹም እንኳ እንደተናደዱ የሚያሳይ ነገር አድርገው ቢሆን ኖሮ ሴትየዋ እንዲህ ዓይነት ደብዳቤ ትጽፍ ነበር? ላትጽፍ ትችላለች። በእርግጥም አገልግሎታችን ለእኛም ሆነ ለምንሰብክላቸው ሰዎች ጠቃሚ ነው! w16.06 2:12, 13
ማክሰኞ፣ ግንቦት 8
ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።—ማቴ. 22:39
ሁላችንም ፍጽምና ይጎድለናል። (ሮም 5:12, 19) ስለሆነም አልፎ አልፎ አንዳንድ ወንድሞች ስሜታችንን የሚጎዳ ነገር ይናገሩ ወይም ያደርጉ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ለይሖዋና ለሕዝቡ ያለን ፍቅር ሊፈተን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ምን እናደርጋለን? ለምሳሌ ያህል፣ ሊቀ ካህናቱ ኤሊ የይሖዋን ሕግ የማያከብሩ ሁለት ልጆች ነበሩት። መጽሐፍ ቅዱስ “የኤሊ ወንዶች ልጆች ምግባረ ብልሹ ነበሩ፤ ለይሖዋ አክብሮት አልነበራቸውም” ይላል። (1 ሳሙ. 2:12) ኤሊ እውነተኛውን አምልኮ በማራመድ ረገድ ትልቅ ቦታ የነበረው ቢሆንም ሁለቱ ልጆቹ ከባድ ኃጢአት ይፈጽሙ ነበር። ኤሊ ይህን ጉዳይ ስለሚያውቅ ተግሣጽ ሊሰጣቸው ይገባ ነበር፤ እሱ ግን ልል ነበር። በመሆኑም አምላክ ኤሊንም ሆነ ልጆቹን ቀጥቷቸዋል። (1 ሳሙ. 3:10-14) ውሎ አድሮ ዘሮቹም እንኳ ሊቀ ካህናት ሆነው የማገልገል መብት አጥተዋል። በኤሊ ዘመን ብትኖር ኖሮ ኤሊ የልጆቹን ኃጢአት በቸልታ ሲያልፍ ምን ይሰማህ ነበር? በዚህ ተሰናክለህ አምላክን ማገልገልህን ታቆም ነበር? w16.06 4:5, 6
ረቡዕ፣ ግንቦት 9
እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።—ማቴ. 6:33
ኢየሱስ ከላይ ያለውን የተናገረው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ቀደም ባለው ቁጥር ላይ “በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ [ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች] ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል” በማለት ተናግሯል። ይሖዋ እያንዳንዳችን የሚያስፈልገንን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ከራሳችን እንኳ አስቀድሞ ያውቃል። (ፊልጵ. 4:19) የትኛው ልብሳችን እያለቀ እንደሆነ፣ ምን ዓይነት ምግብ እንደሚያስፈልገን እንዲሁም ለቤተሰባችን የሚበቃው ምን ዓይነት መጠለያ እንደሆነ ያውቃል። ደግሞም የሚያስፈልገንን ነገር ማግኘት አለማግኘታችንን በትኩረት ይከታተላል። በመሆኑም የሚጠበቅብንን ነገር የምናደርግ ይኸውም በሕይወታችን ውስጥ መንፈሳዊ ነገሮችን የምናስቀድም ከሆነ ይሖዋ ጥሩ የሆነውን ነገር እንደማይነፍገን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። “ለአምላክ ያደርን መሆናችን” የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮች ይኸውም “ምግብና ልብስ” እንዲሁም “መጠለያ” በማግኘታችን ረክተን እንድንኖር ሊያደርገን ይገባል።—1 ጢሞ. 6:6-8 ግርጌ፤ w16.07 1:17, 18
ሐሙስ፣ ግንቦት 10
ጠላቶች ሆነን ሳለን በልጁ ሞት አማካኝነት ከአምላክ ጋር [ታረቅን]።—ሮም 5:10
እርቅ መፍጠራችን ከይሖዋ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ለመመሥረት አስችሎናል። ጳውሎስ ለቅቡዓን ወንድሞቹ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ከይሖዋ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት የመመሥረት መብት ማግኘታችንን ከይሖዋ ጸጋ ጋር አያይዞ ገልጾታል፦ “አሁን በእምነት አማካኝነት ጻድቃን ናችሁ ስለተባልን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከአምላክ ጋር ያለንን ሰላም ጠብቀን እንኑር፤ ደግሞም በኢየሱስ አማካኝነት የአምላክን ጸጋ ለማግኘት በእምነት ወደ እሱ መቅረብ የቻልን ሲሆን ይህን ጸጋ አሁን አግኝተናል።” (ሮም 5:1, 2) ይህ እንዴት ያለ በረከት ነው! ሁላችንም ስንወለድ ጀምሮ ከጽድቅ ጎዳና የራቅን ነበርን። ይሁንና ነቢዩ ዳንኤል፣ በፍጻሜው ዘመን “ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው” ይኸውም ቅቡዓን ቀሪዎች “የጽድቅን ጎዳና እንዲከተሉ ብዙ ሰዎችን [እንደሚረዱ]” ትንቢት ተናግሯል። (ዳን. 12:3) ቅቡዓን፣ በሚያከናውኑት የስብከትና የማስተማር ሥራ አማካኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ “ሌሎች በጎች” በይሖዋ ፊት የጽድቅ አቋም እንዲኖራቸው ረድተዋል። (ዮሐ. 10:16) ይህ ሊሳካ የቻለው ግን በይሖዋ ጸጋ ነው።—ሮም 3:23, 24፤ w16.07 3:10, 11
ዓርብ፣ ግንቦት 11
የመረጧቸውን ሁሉ ለራሳቸው ሚስቶች አድርገው ወሰዱ።—ዘፍ. 6:2
እንዲህ ያለው ጥምረት ከተፈጥሮ ውጭ ነበር፤ ሥጋ የለበሱት መላእክትና የሰው ሴቶች ልጆች፣ ኔፍሊም ተብለው የተጠሩ ዓመፀኛ ልጆች ወለዱ። በወቅቱ “የሰው ልጅ ክፋት በምድር ላይ” በዝቶ ነበር። (ዘፍ. 6:1-5) ይሖዋ ክፉዎችን ለማጥፋት ሲል በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ አመጣ። በወቅቱ የነበሩት ሰዎች፣ ትዳርን ጨምሮ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ከሚገባው በላይ ተጠምደው ስለነበር ‘የጽድቅ ሰባኪ የነበረው ኖኅ’ ስለሚመጣው ጥፋት የሚናገረውን መልእክት በቁም ነገር አልተመለከቱትም። (2 ጴጥ. 2:5) ኢየሱስ በኖኅ ዘመን የነበረውን ሁኔታ በዘመናችን ካለው ሁኔታ ጋር አመሳስሎታል። (ማቴ. 24:37-39) በዛሬው ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች፣ ይህ ክፉ ሥርዓት ከመጥፋቱ በፊት ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር እየተሰበከ ያለውን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስማት አሻፈረን ብለዋል። እኛም እንደ ትዳርና ልጆችን እንደ ማሳደግ የመሳሰሉት የቤተሰብ ጉዳዮችም እንኳ የይሖዋን ቀን በጥድፊያ ስሜት እንዳንጠባበቅ እንቅፋት እንዲሆኑብን ልንፈቅድ አይገባም። w16.08 1:8, 9
ቅዳሜ፣ ግንቦት 12
የቀረው ጊዜ አጭር [ነው]። . . . ከእንግዲህ ወዲህ ሚስት ያላቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፤ . . . በዓለም የሚጠቀሙ ሰዎች ሙሉ በሙሉ እንደማይጠቀሙበት ይሁኑ።—1 ቆሮ. 7:29-31
የምንኖረው ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ እየተገባደዱ ባሉበት ጊዜ ላይ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጊዜ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” በማለት ገልጾታል። (2 ጢሞ. 3:1-5) ያም ቢሆን ምንጊዜም በመንፈሳዊ ጠንካሮች መሆናችን የዚህን ዓለም መጥፎ ተጽዕኖ እንድናሸንፍ ኃይል ይሰጠናል። ጳውሎስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሲል ያገቡ ክርስቲያኖች፣ ትዳር የሚያስከትላቸውን ኃላፊነቶች ቸል እንዲሉ መምከሩ አይደለም። ሆኖም የቀረው ጊዜ አጭር በመሆኑ ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ነው። (ማቴ. 6:33) የምንኖረው በጣም ተፈታታኝ በሆነ ዘመን ውስጥ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ትዳሮች ሲፈርሱ እንመለከታለን፤ ያም ቢሆን ትዳራችን ደስታ የሰፈነበትና ስኬታማ እንዲሆን ማድረግ እንችላለን። በእርግጥም ከይሖዋና ከሕዝቡ ጋር ተቀራርበው የሚኖሩ፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን ተግባራዊ የሚያደርጉ እንዲሁም የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እንዲመራቸው የሚፈቅዱ ያገቡ ክርስቲያኖች “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” የሚለውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ይችላሉ።—ማር. 10:9፤ w16.08 2:17, 18
እሁድ፣ ግንቦት 13
የአምላክን መንጋ እንደ እረኛ ጠብቁ።—1 ጴጥ. 5:2
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እረኛ ሆነው የሚያገለግሉ ብዙ ወንዶች ያስፈልጋሉ፤ በመሆኑም ወደፊት ይህን ኃላፊነት የሚቀበሉት ወንድሞች ቀጣይ የሆነ ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንዲህ ብሎታል፦ “ከእኔ የሰማኸውንና ብዙዎች የመሠከሩለትን ነገር፣ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ፤ እነሱም በበኩላቸው ሌሎችን ለማስተማር ብቃቱን ያሟላሉ።” (2 ጢሞ. 2:1, 2) ጢሞቴዎስ ሥልጠና ያገኘው በዕድሜ ከሚበልጠው ሐዋርያ ጋር አብሮ በማገልገል ነው። ከዚያም ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ የተማረውን ነገር በስብከቱና በሌሎች የቅዱስ አገልግሎት ዘርፎች ተግባራዊ አድርጓል። (2 ጢሞ. 3:10-12) ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን በራሱ ይሠልጥን ብሎ አልተወውም። ከዚህ ይልቅ ይህ ወጣት አብሮት እንዲሠራ አድርጓል። (ሥራ 16:1-5) ሽማግሌዎችም እረኝነት ሲያደርጉ፣ ጥሩ ችሎታ ያላቸውን የጉባኤ አገልጋዮች ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ይዘዋቸው በመሄድ የጳውሎስን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። ሽማግሌዎች እንዲህ ማድረጋቸው፣ የጉባኤ አገልጋዮች ከክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የሚጠበቁትን ባሕርያት ይኸውም የማስተማር ችሎታን፣ እምነትን፣ ትዕግሥትንና ፍቅርን እንዴት ማንጸባረቅ እንደሚቻል ለማየት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ይህም ወደፊት ‘የአምላክ መንጋ’ እረኞች የሚሆኑት ወንድሞች ተገቢውን ሥልጠና ማግኘት እንዲችሉ አስተዋጽኦ ያበረክታል። w16.08 4:16, 17
ሰኞ፣ ግንቦት 14
[እጆቻችሁ] አይዛሉ።—ሶፎ. 3:16
አንድ ሰው ተስፋ መቁረጡን ለማመልከት እጆቹ እንደዛሉ ተደርጎ የተገለጸበት ጊዜ አለ። (2 ዜና 15:7 ግርጌ፤ ዕብ. 12:12) በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያለ ሰው፣ ሁሉ ነገር ይጨልምበታል። ክፉ የሆነው የሰይጣን ዓለም ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድርብን ሲሆን ይህም ጭንቀት ሊፈጥርብንና ከባድ ሸክም የተጫነን ያህል እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል። የሚሰማን ጭንቀት አንዲትን መርከብ ወዴትም እንዳትንቀሳቀስ ወጥሮ ከሚይዛት መልሕቅ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። (ምሳሌ 12:25) እንዲህ እንዲሰማህ የሚያደርግህ ምን ሊሆን ይችላል? የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ወይም በከባድ ሕመም እየተሠቃየህ ይሆናል፤ አሊያም ኑሮ በተወደደበት በዚህ ዘመን ለቤተሰብህ የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ እየታገልክ ወይም ደግሞ ስደት እየደረሰብህ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለው ውጥረት፣ ውሎ አድሮ ኃይልህን ያሟጥጠዋል፤ አልፎ ተርፎም ደስታህን ያሳጣሃል። ይሁንና አምላክ አንተን ለመርዳት እጁን እንደሚዘረጋልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—ኢሳ. 41:10, 13፤ w16.09 1:2, 4
ማክሰኞ፣ ግንቦት 15
የትእዛዛትህን መንገድ በጉጉት እከተላለሁ።—መዝ. 119:32
ብዙዎች ከሚታገሏቸው ነገሮች አንዱ የሥጋ ድክመት ነው። ሌሎች ደግሞ ለአገልግሎቱ አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አስፈልጓቸዋል። አንተም ካለብህ የጤና እክል ወይም ከብቸኝነት ስሜት ጋር እየታገልክ ይሆናል። ያስቀየማቸውን ወይም ከባድ በደል የፈጸመባቸውን ሰው ይቅር ለማለት የሚታገሉም አሉ። በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍነው ጊዜ ምንም ያህል ቢሆን ሁላችንም፣ ለታማኞቹ ወሮታ ከፋይ የሆነውን አምላክ ማገልገል አስቸጋሪ እንዲሆንብን ከሚያደርጉ ነገሮች ጋር መታገል አለብን። ልባችሁ መጥፎ ተጽዕኖ እያሳደረባችሁ እንደሆነ ከተሰማችሁ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት አጥብቃችሁ ጸልዩ። መጸለያችሁና መንፈስ ቅዱስን ማግኘታችሁ፣ ትክክለኛውንና የይሖዋን በረከት የሚያስገኝላችሁን አካሄድ ለመከተል ብርታት ይሰጣችኋል። በተጨማሪም ከጸሎታችሁ ጋር የሚስማማ እርምጃ ውሰዱ። በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ጥረት አድርጉ፤ እንዲሁም የግል ጥናትና ቋሚ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ይኑራችሁ።—መዝ. 119:32፤ w16.09 2:10, 11
ረቡዕ፣ ግንቦት 16
እምነት . . . የምናምንበት ነገር በዓይን የሚታይ ባይሆንም እውን መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።—ዕብ. 11:1
ሰዎች፣ ‘አምላክ አለ’ የሚለው ሐሳብ በእምነት ላይ የተመሠረተ፣ ዝግመተ ለውጥ ግን በሳይንስ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ሲናገሩ ሰምተህ ታውቃለህ? ብዙዎች እንዲህ ያለ አመለካከት አላቸው። ይሁንና ልንዘነጋው የማይገባ አንድ ሐቅ አለ፦ አምላክ እንዳለ ለመቀበልም ሆነ ዝግመተ ለውጥን ለማመን እምነት ያስፈልጋል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ማንኛችንም ብንሆን አምላክን አይተን አሊያም አንድ ነገር ሲፈጠር ተመልክተን አናውቅም። (ዮሐ. 1:18) በሌላ በኩል ደግሞ ሕይወት ያለው አንድ ነገር በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ወደ ሌላ ሕያው ነገር ሲቀየር ተመልክቶ የሚያውቅ የሳይንስ ሊቅም ሆነ ሌላ ሰው የለም። ለምሳሌ፣ በደረቱ የሚሳብ እንስሳ ወደ አጥቢ እንስሳ ሲቀየር ተመልክቶ የሚያውቅ ሰው የለም። (ኢዮብ 38:1, 4) በመሆኑም ሁላችንም ብንሆን ያሉትን ማስረጃዎች መመርመርና በማመዛዘን ችሎታችን ተጠቅመን ምክንያታዊ የሆነ መደምደሚያ ላይ መድረስ ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ አምላክ የፍጥረት ሥራዎች ሲናገር እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የማይታዩት ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል፤ ስለሆነም የሚያመካኙበት ነገር የላቸውም።”—ሮም 1:20፤ w16.09 4:4
ሐሙስ፣ ግንቦት 17
ለእንግዶች ደግነት ማሳየትን አትርሱ።—ዕብ. 13:2 ግርጌ
ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ በእስራኤል ይኖሩ ለነበሩ የባዕድ አገር ሰዎች እንደ ቃርሚያ ዝግጅት ያሉ አንዳንድ ዝግጅቶችን አድርጎላቸው ነበር። (ዘሌ. 19:9, 10) ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ለባዕድ አገር ሰው አክብሮት እንዲያሳዩ ከማዘዝ ይልቅ ራሳቸውን በእነሱ ቦታ አድርገው እንዲያስቡ አበረታቷቸዋል። (ዘፀ. 23:9) እስራኤላውያን “የባዕድ አገር ሰው መሆን ምን ስሜት እንደሚያሳድር” ያውቃሉ። ዕብራውያኑ፣ ባሪያ ከመሆናቸው በፊትም እንኳ በዘራቸው ወይም በሃይማኖታቸው ምክንያት ግብፃውያኑ ያገልሏቸው ነበር። (ዘፍ. 43:32፤ 46:34፤ ዘፀ. 1:11-14) እስራኤላውያን በግብፅ የባዕድ አገር ሰው እያሉ ሕይወት መራራ ሆኖባቸው ነበር፤ በመሆኑም ይሖዋ የባዕድ አገር ሰዎችን ‘እንደ አገራቸው ተወላጅ’ አድርገው እንዲመለከቱ ነግሯቸዋል። (ዘሌ. 19:33, 34) ይሖዋ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ለሚገኙ የሌላ አገር ሰዎችም በጥንት ጊዜ ያሳየው ዓይነት አሳቢነት እንደሚያሳያቸው መተማመን እንችላለን። (ዘዳ. 10:17-19፤ ሚል. 3:5, 6) እነዚህ ሰዎች መድልዎ ሊደርስባቸው እንደሚችል ወይም የአገሩን ቋንቋ ባለመቻላቸው እንደሚቸገሩ አሊያም ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ ካሰብን ለእነሱ ደግነት ለማሳየትና ስሜታቸውን ለመረዳት እንጥራለን።—1 ጴጥ. 3:8፤ w16.10 1:3-5
ዓርብ፣ ግንቦት 18
አካል ያለ መንፈስ የሞተ እንደሆነ ሁሉ እምነትም ያለ ሥራ የሞተ ነው።—ያዕ. 2:26
የያዕቆብ ደብዳቤ፣ ክርስቲያኖች ያላቸው እውነተኛ እምነት፣ ተግባርንም እንደሚጨምር ይገልጻል። ያዕቆብ “እምነትህን ከሥራ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔ ደግሞ እምነቴን በሥራ አሳይሃለሁ” በማለት ጽፏል። (ያዕ. 2:18) ያዕቆብ ቀጥሎ የተናገረው ሐሳብ አንድን ነገር እንዲሁ አምኖ በመቀበልና እምነትን በተግባር በማሳየት መካከል ትልቅ ልዩነት እንዳለ ይጠቁማል። ለምሳሌ አጋንንት አምላክ እንዳለ ያምናሉ፤ ሆኖም እውነተኛ እምነት አላቸው ሊባል አይችልም። እንዲያውም የአምላክ ዓላማዎች እንዳይፈጸሙ ለማድረግ የሚጥሩ መሆኑ እምነት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው። (ያዕ. 2:19, 20) ያዕቆብ አክሎም በጥንት ዘመን የኖረን የእምነት ሰው በመጥቀስ እንዲህ ብሏል፦ “አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያ ላይ ካቀረበ በኋላ የጸደቀው በሥራ አይደለም? እምነቱ ከሥራው ጋር አብሮ ይሠራ እንደነበረና ሥራው እምነቱን ፍጹም እንዳደረገው ትገነዘባለህ።” (ያዕ. 2:21-23) ከዚያም ያዕቆብ እምነት በሥራ መገለጽ እንዳለበት ለማሳየት በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ተናግሯል። w16.10 4:8
ቅዳሜ፣ ግንቦት 19
ዘላለማዊነትን በልባቸው ውስጥ አኑሯል።—መክ. 3:11
ሳይንስ ስለ ጽንፈ ዓለምና ስለ ምድር ብዙ ነገር ያሳወቀን ከመሆኑም ሌላ በተለያዩ የሕይወታችን ዘርፎች ጥቅም አስገኝቶልናል። ይሁንና ሳይንስ የማይመልሳቸው በርካታ ጥያቄዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ጽንፈ ዓለም ወደ ሕልውና የመጣው እንዴት እንደሆነ ወይም የሰው ልጆችም ሆኑ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ሕያዋን ፍጥረታት በምድር ላይ ሊኖሩ የቻሉት ለምን እንደሆነ ሊነግሩን አይችሉም። በተጨማሪም የሰው ልጆች ለዘላለም የመኖር ጉጉት እንዲኖራቸው ያደረገው ምን እንደሆነ አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም። በጣም አስፈላጊ ቢሆኑም መልስ ያላገኙ በርካታ ጥያቄዎች ሊኖሩ የቻሉት ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት፣ ብዙ የሳይንስ ሊቃውንትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ‘አምላክ የለም’ የሚለውን አስተሳሰብና የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ ስለሚያራምዱ ነው። ይሖዋ ግን በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ ለሚፈጠሩት ጥያቄዎች በቃሉ ይኸውም እሱ ባስጻፈው መጽሐፍ አማካኝነት መልስ ሰጥቷል። ይሖዋ ካወጣቸው የማይለዋወጡና አስተማማኝ የተፈጥሮ ሕግጋት ውጭ ሕይወታችንን መምራት አንችልም። የኤሌክትሪክና የቧንቧ ሠራተኞች፣ መሐንዲሶች፣ አውሮፕላን አብራሪዎችና የቀዶ ጥገና ሐኪሞች ሥራቸውን የሚያከናውኑት በተፈጥሮ ሕጎች ተማምነው ነው። w16.11 2:4, 5
እሁድ፣ ግንቦት 20
ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው [በአምላክ] ነው።—ሥራ 17:28
ይሖዋን እንድናመሰግነው የሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች አሉን! ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው። ውድ የሆነ ስጦታ ይኸውም ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። በተሰሎንቄ እንደነበሩት ክርስቲያኖች እኛም የይሖዋን መልእክት እንደ አምላክ ቃል አድርገን በመቀበል አድናቆታችንን እናሳያለን። (1 ተሰ. 2:13) በጽሑፍ የሰፈረው የአምላክ ቃል በእጃችን ስላለ ወደ ይሖዋ መቅረብ ችለናል፤ እሱም ወደ እኛ ቀርቧል። (ያዕ. 4:8) በሰማይ ያለው አባታችን የድርጅቱ አባል የመሆን ውድ መብት ሰጥቶናል። ከይሖዋ ያገኘናቸውን እንዲህ ያሉ በረከቶች በጣም እናደንቃለን! “ይሖዋ ጥሩ ስለሆነ ምስጋና አቅርቡለት፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” በማለት እንደዘመረው መዝሙራዊ ይሰማናል። (መዝ. 136:1) መዝሙር 136 ላይ “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” የሚለው አገላለጽ 26 ጊዜ ተጠቅሷል። ለይሖዋና ለድርጅቱ ታማኝ ከሆንን የዘላለም ሕይወት ስለምናገኝ የእነዚህን ቃላት እውነተኝነት እንመለከታለን! w16.11 3:18, 19
ሰኞ፣ ግንቦት 21
በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።—ሮም 5:12
ይህ ጥቅስ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ላይ በተደጋጋሚ ተጠቅሶ ይገኛል። ከዚህ መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 3, 5 እና 6ን ለልጆችህ ወይም ለሌሎች ስታስጠና ሮም 5:12ን ማንበብህ አይቀርም፤ እነዚህ ምዕራፎች አምላክ ለምድር ስላለው ዓላማ፣ ስለ ቤዛውና የሞቱ ሰዎች ስላሉበት ሁኔታ የሚያብራሩ ናቸው። ይሁንና ሮም 5:12 በይሖዋ ዘንድ ካለህ አቋም፣ ከአኗኗርህ እንዲሁም ከወደፊት ተስፋህ ጋር እንደሚያያዝስ አስበህ ታውቃለህ? ሁላችንም ኃጢአተኞች መሆናችንን መዘንጋት አይኖርብንም። በየዕለቱ ስህተቶች እንሠራለን። ሆኖም አምላክ፣ አፈር መሆናችንን እንደሚያውቅና ምሕረት ሊያሳየን እንደሚፈልግ እርግጠኞች ነን። (መዝ. 103:13, 14) ኢየሱስ በጸሎት ናሙናው ላይ “ኃጢአታችንን ይቅር በለን” ብለን እንድንጸልይ አስተምሮናል። (ሉቃስ 11:2-4) በመሆኑም አምላክ አንድ ጊዜ ይቅር ካለን በኋላ፣ ስለሠራናቸው ስህተቶች እያሰብን የምንብሰለሰልበት ምንም ምክንያት የለም። ያም ቢሆን አምላክ፣ ኃጢአታችንን ይቅር ለማለት ስላደረገው ዝግጅት ማሰባችን ይጠቅመናል። w16.12 1:1-3
ማክሰኞ፣ ግንቦት 22
እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ አእምሯቸው በሥጋዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው።—ሮም 8:5
በሮም የነበሩት ክርስቲያኖች ሕይወታቸው ያተኮረው በምን ላይ እንደሆነ መመርመራቸው አስፈላጊ ነበር። ሕይወታቸውን የሚቆጣጠሩት ወይም በሕይወታቸው ውስጥ ዋነኛውን ቦታ የያዙት “ሥጋዊ ነገሮች” ነበሩ? እኛም በዚህ ጥያቄ ላይ ማሰላሰላችን ተገቢ ነው። ትልቅ ቦታ የምንሰጠውና አዘውትረን የምናወራው ነገር ምንድን ነው? ነጋ ጠባ የሚያሳስበን ጉዳይስ ምንድን ነው? የአንዳንዶች ሕይወት ያተኮረው የወይን ጠጅ ዓይነቶችን በመቅመስ፣ ቤታቸውን በማሳመር፣ አዳዲስ ፋሽኖችን በመከታተል፣ ገንዘባቸውን የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ በማዋል፣ ወደተለያዩ ቦታዎች ሄደው በመዝናናት እና በመሳሰሉት ነገሮች ላይ ነው። እንደነዚህ ያሉት ነገሮች በራሳቸው ስህተት ናቸው ማለት አይደለም፤ ማንኛችንም በሕይወታችን ውስጥ እነዚህን ነገሮች እናደርግ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በአንድ የሠርግ ድግስ ላይ ተጋባዦቹ የወይን ጠጅ እንዲያገኙ አድርጓል፤ ጳውሎስም “ጥቂት የወይን ጠጅ” እንዲጠጣ ጢሞቴዎስን መክሮታል። (1 ጢሞ. 5:23፤ ዮሐ. 2:3-11) ይሁን እንጂ ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ ከወይን ጠጅ ጋር የተያያዘ ጉዳይ በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲይዝ አድርገው ነበር? ወሬያቸው ሁሉ ስለ ወይን ጠጅ ነበር? በፍጹም። እኛስ በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ነገር ምንድን ነው? w16.12 2:5, 10, 11
ረቡዕ፣ ግንቦት 23
ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም።—ዕብ. 13:5
ይሖዋ የገባው ይህ ቃል፣ ኢየሱስ የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን ካስቀደምን ይሖዋ እንደሚባርከን በተናገረው ሐሳብ እንድንተማመን ያደርገናል። (ማቴ. 6:33) በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስን “እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ የምናገኘው ምን ይሆን?” በማለት ጠይቆት ነበር። (ማቴ. 19:27) ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ይህን ጥያቄ በማቅረቡ ተግሣጽ ከመስጠት ይልቅ ደቀ መዛሙርቱ ለከፈሉት መሥዋዕት ወሮታ እንደሚያገኙ ተናገረ። ታማኝ ሐዋርያቱን ጨምሮ ሌሎች ተከታዮቹ ከእሱ ጋር በሰማይ ይገዛሉ። ይሁንና በዚህ ዘመንም ቢሆን የሚያገኙት ወሮታ አለ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ስሜ ሲል ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለም ሕይወትም ይወርሳል።” (ማቴ. 19:29) ደቀ መዛሙርቱ በሕይወታቸው ውስጥ መሥዋዕት ካደረጉት ከየትኛውም ነገር እጅግ የላቀ በረከት ያገኛሉ። መንፈሳዊ አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞች፣ እህቶች ወይም ልጆች ማግኘታችን ለመንግሥቱ ስንል ከተውነው ከማንኛውም ነገር አይበልጥም? w16.12 4:4, 5
ሐሙስ፣ ግንቦት 24
እምነት ተስፋ የተደረጉትን ነገሮች በእርግጠኝነት መጠበቅ ማለት ነው።—ዕብ. 11:1
እውነተኛ ክርስቲያኖች የተዘረጋላቸው ተስፋ ምንኛ ግሩም ነው! ቅቡዓንም ሆንን “ሌሎች በጎች” ሁላችንም የአምላክ ዓላማ ሲፈጸምና የይሖዋ ስም ሲቀደስ ለማየት እንጓጓለን። (ዮሐ. 10:16፤ ማቴ. 6:9, 10) ይህ፣ ማንኛውም ሰው ሊኖረው ከሚችለው ሁሉ የላቀ ተስፋ ነው። በተጨማሪም አምላክ ቃል የገባው “አዲስ ሰማያት” ወይም “አዲስ ምድር” ክፍል ሆነን የዘላለም ሕይወት ለማግኘት እንጠባበቃለን። (2 ጴጥ. 3:13) እስከዚያው ድረስ ደግሞ የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ ይበልጥ እየበለጸጉ ሲሄዱ ለማየት እንናፍቃለን። የሰይጣን ዓለም ክፍል የሆኑ ሰዎችም ተስፋ የሚያደርጓቸው ነገሮች አሉ፤ ሆኖም ተስፋቸው መፈጸም መቻሉን ይጠራጠሩ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቁማርተኞች ሎተሪ እንደሚያሸንፉ ተስፋ ያደርጋሉ፤ ይሁንና ማሸነፋቸውን እርግጠኞች መሆን አይችሉም። በሌላ በኩል ግን እውነተኛ እምነት ሲባል ለክርስቲያኖች የተሰጠውን ተስፋ “በእርግጠኝነት መጠበቅ” ማለት ነው። w16.10 3:1, 2
ዓርብ፣ ግንቦት 25
እያንዳንዳችሁ በተቀበላችሁት ስጦታ መሠረት የተሰጣችሁን ስጦታ አንዳችሁ ሌላውን ለማገልገል ተጠቀሙበት።—1 ጴጥ. 4:10
ይሖዋ በጸጋው ለሁላችንም የተለያየ ስጦታ፣ ችሎታ ወይም ተሰጥኦ ለግሶናል። ይሖዋ የሰጠንን ስጦታ፣ ችሎታ ወይም ተሰጥኦ እሱን ለማስከበርና ሌሎችን ለመጥቀም ልናውለው እንችላለን። (ሮም 12:4-8) ይሖዋ የመጋቢነት ኃላፊነት በአደራ ሰጥቶናል፤ ይህ አደራ ይሖዋ እንደሚያከብረንና እምነት እንደሚጥልብን የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ ኃላፊነት ያስከትልብናል። ይሁንና በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ያለን ቦታ ሁልጊዜ ቋሚ አይደለም። በጊዜ ሂደት ሊለወጥ ይችላል። እስቲ የኢየሱስን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። መጀመሪያ ላይ ከይሖዋ ጋር ብቻውን ነበር። (ምሳሌ 8:22) በኋላም መንፈሳዊ ፍጥረታት፣ ግዑዙ ጽንፈ ዓለምና በመጨረሻም የሰው ልጆች ሲፈጠሩ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል። (ቆላ. 1:16) ከዚያም ወደ ምድር እንዲመጣ ተደርጓል፤ በዚህ ወቅት መጀመሪያ ላይ የሌሎች እርዳታ የሚያስፈልገው ሕፃን የነበረ ሲሆን በኋላም አድጎ አዋቂ ሰው ሆኗል። (ፊልጵ. 2:7) ሕይወቱን ለሌሎች መሥዋዕት በማድረግ ከሞተ በኋላ ደግሞ መንፈሳዊ አካል ለብሶ ወደ ሰማይ ተመልሷል። ከዚያም በ1914 የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኗል። (ዕብ. 2:9) ኢየሱስ ለአንድ ሺህ ዓመት ከገዛ በኋላ “አምላክ ለሁሉም ሁሉንም ነገር እንዲሆን” መንግሥቱን ለይሖዋ ያስረክባል።—1 ቆሮ. 15:28፤ w17.01 3:11, 12
ቅዳሜ፣ ግንቦት 26
የምታገለግሉትን ዛሬውኑ ምረጡ።—ኢያሱ 24:15
አንዲት ሴት የግል ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ሁኔታ ባጋጠማት ወቅት ለጓደኛዋ እንዲህ ብላዋለች፦ “ራሴ አስቤ እንድወስን ከምትጠብቅብኝ ይልቅ ‘እንዲህ አድርጊ’ ብትለኝ ይቀለኛል።” ይህች ሴት ፈጣሪዋ የሰጣትን ውድ ስጦታ ይኸውም የመምረጥ ነፃነቷን ከመጠቀም ይልቅ፣ ማድረግ ያለባትን ሌላ ሰው እንዲነግራት ፈልጋለች። አንተስ የራስህን ውሳኔ ታደርጋለህ ወይስ ሌሎች እንዲወስኑልህ ትፈልጋለህ? የመምረጥ ነፃነትን የምትመለከተው እንዴት ነው? ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ለዘመናት ሲወዛገቡ ቆይተዋል። አንዳንዶች፣ አምላክ የምናደርገውን ነገር ሁሉ አስቀድሞ ስለወሰነው የመምረጥ ነፃነት የሚባል ነገር እንደሌለን ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ‘የመምረጥ ነፃነት አለን ሊባል የሚችለው ነፃነታችን ምንም ገደብ የሌለው ከሆነ ብቻ ነው’ ይላሉ። ስለዚህ ጉዳይ ትክክለኛ ግንዛቤ ልናገኝ የምንችለው የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ሲፈጥረን የመምረጥ ነፃነት ይኸውም የማሰብ ችሎታችንን በመጠቀም የራሳችንን ምርጫ የማድረግ ችሎታና ነፃነት እንደሰጠን ይናገራል። w17.01 2:1, 2
እሁድ፣ ግንቦት 27
ልጄ ሰለሞን ገና ወጣት ነው፤ ተሞክሮም የለውም፤ . . . ስለዚህ የሚያስፈልገውን ነገር አዘጋጅለታለሁ።—1 ዜና 22:5
ዳዊት ልጁ ሰለሞን እንዲህ ያለውን ከባድ ሥራ ማለትም የአምላክን ቤት የመገንባቱን ሥራ ለመምራት ብቁ እንዳልሆነ ሊያስብ ይችል ነበር። ምክንያቱም ቤተ መቅደሱ “እጅግ የሚያምር” መሆን ይኖርበታል፤ ሰለሞን ደግሞ በዚያ ወቅት ‘ገና ወጣትና ተሞክሮ የሌለው’ ነበር። ሆኖም ዳዊት፣ ሰለሞን የተሰጠውን ሥራ መወጣት እንዲችል ይሖዋ እንደሚረዳው ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ግንባታውን ለመደገፍ ማከናወን በሚችለው ነገር ላይ ትኩረት በማድረግ ለግንባታው የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ በብዛት ማሰባሰብ ጀመረ። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በዕድሜ የገፉ ወንድሞች ኃላፊነታቸውን ለወጣት ወንድሞች ሲያስረክቡ ቅር ሊሰኙ አይገባም። ምክንያቱም ወጣቶች ኃላፊነት ለመሸከም ብቁ እንዲሆኑ መሠልጠናቸው ሥራው በተሻለ መንገድ እንዲከናወን ያስችላል። የተሾሙ ወንድሞች፣ እነሱ ያሠለጠኗቸው ወጣት ወንድሞች የእነሱን ሥራ ለመረከብ ብቁ ሆነው ሲገኙ ከፍተኛ እርካታ ሊሰማቸው ይገባል። w17.01 5:8, 9
ሰኞ፣ ግንቦት 28
በአንተና በሴቲቱ መካከል እንዲሁም በዘርህና በዘሯ መካከል ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ፤ እሱ ራስህን ይጨፈልቃል።—ዘፍ. 3:15
የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ የእባቡን ራስ ይጨፈልቃል፤ እንዲሁም ሰይጣን ያስነሳው ዓመፅ ያስከተላቸውን ችግሮች በሙሉ ያስወግዳል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት፣ ደቀ መዛሙርቱ የአምላክ መንግሥት ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንዳለው እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያውኑ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች” በስፋት ማወጅ ጀምሯል። (ሉቃስ 4:43) ወደ ሰማይ ከመመለሱ በፊት ደቀ መዛሙርቱን ለመጨረሻ ጊዜ ባነጋገራቸው ወቅት “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ምሥክሮቹ እንዲሆኑ አዟቸዋል። (ሥራ 1:6-8) በመላው ምድር የሚኖሩ ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት በሚገልጸው የስብከት ሥራ አማካኝነት ስለ ቤዛው መማርና የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች መሆን የሚችሉበት አጋጣሚ ያገኛሉ። በዛሬው ጊዜ የመንግሥቱን ምሥራች በዓለም ዙሪያ እንድንሰብክ የተሰጠንን ተልዕኮ በመወጣት በምድር ያሉትን የክርስቶስ ወንድሞች ስንረዳ መንግሥቱን እንደምንደግፍ እናሳያለን።—ማቴ. 24:14፤ 25:40፤ w17.02 2:7, 8
ማክሰኞ፣ ግንቦት 29
[ክርስቶስ] አንዳንዶቹን ሐዋርያት . . . አድርጎ ሰጠ።—ኤፌ. 4:11
የበላይ አካሉ አባላት በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው ጉባኤ ላይ ሥልጣን ቢኖራቸውም መሪያቸው ኢየሱስ መሆኑን ያውቁ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ “በሁሉም ነገር ወደ እሱ ይኸውም የአካሉ ራስ ወደሆነው ወደ ክርስቶስ በፍቅር እንደግ” ሲል ጽፏል። (ኤፌ. 4:15) ደቀ መዛሙርቱ በአንድ ታዋቂ ሐዋርያ ስም ከመጠራት ይልቅ ‘በመለኮታዊ አመራር ክርስቲያኖች ተብለው ተጠርተዋል።’ (ሥራ 11:26) እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ሐዋርያትና አመራር የሚሰጡ ሌሎች ወንዶች ያስተላለፏቸውን “ወጎች” ወይም በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረቱ ልማዶች ‘አጥብቆ መያዝ’ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሟል። ይሁንና “[እያንዳንዱን የበላይ አካል አባል ጨምሮ] የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ . . . የክርስቶስ ራስ ደግሞ አምላክ እንደሆነ እንድታውቁ እወዳለሁ” በማለት አክሎ ተናግሯል። (1 ቆሮ. 11:2, 3) በሰማይ ያለውና ክብር የተጎናጸፈው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ በይሖዋ አምላክ ሥር ሆኖ ጉባኤውን እየመራ ነበር። w17.02 4:7
ረቡዕ፣ ግንቦት 30
በመልካም ሁኔታ የሚያስተዳድሩ . . . ሽማግሌዎች እጥፍ ክብር ሊሰጣቸው ይገባል።—1 ጢሞ. 5:17
ክብር ለሚገባቸው ክብር መስጠታችን በራሳችን ላይ ብቻ እንዳናተኩር ያደርገናል። ሰዎች አክብሮት ሲያሳዩን ለራሳችን የተጋነነ አመለካከት እንዳናዳብር ይረዳናል። በተጨማሪም ለእምነት አጋሮቻችንም ሆነ ለማያምኑ ሰዎች ከልክ ያለፈና ተገቢ ያልሆነ አክብሮት ባለመስጠት የይሖዋ ድርጅት ያለው ዓይነት አቋም እንዲኖረን ያስችለናል። ከዚህም ሌላ ለሌሎች ተገቢውን አክብሮት መስጠታችን፣ እናከብረው የነበረ አንድ ሰው ያልጠበቅነው ነገር ቢያደርግ እንዳንደናቀፍ ስለሚረዳን ጥበቃ ይሆንልናል። ክብር ለሚገባው ክብር መስጠታችን ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች ሁሉ የላቀው፣ ይህን ማድረጋችን አምላክን የሚያስደስት መሆኑ ነው። በዚህ መንገድ አምላክ የሚጠብቅብንን የምናደርግ ከመሆኑም ሌላ ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ እንሆናለን። ይህም ይሖዋን ለሚነቅፍ ሁሉ መልስ ለመስጠት ያስችለናል። (ምሳሌ 27:11) በዚህ ዓለም ላይ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች ለሌሎች ክብር በማሳየት ረገድ ያላቸው አመለካከት የተዛባ ነው። እኛ ግን ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ ለሌሎች እንዴት ክብር ማሳየት እንደምንችል ማወቃችን አመስጋኝ እንድንሆን ያነሳሳናል። w17.03 1:13, 20, 21
ሐሙስ፣ ግንቦት 31
[ኢዮሳፍጥ] በይሖዋም ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።—2 ዜና 20:32
ኢዮሳፍጥ ልክ እንደ አባቱ እንደ አሳ ሕዝቡ ይሖዋን እንዲፈልግ አበረታቷል። “የይሖዋን ሕግ መጽሐፍ” የሚያስተምሩ ሰዎችን ወደ ይሁዳ ከተሞች ልኳል። (2 ዜና 17:7-10) ከዚህም በላይ ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት በሚያስተዳድረው ክልል ይኸውም በተራራማው የኤፍሬም ምድር የሚኖረውን ሕዝብ እንኳ ‘ወደ ይሖዋ ለመመለስ’ እዚያ ድረስ ሄዷል። (2 ዜና 19:4) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ታላቅ የማስተማር ዘመቻ እያካሄደ ሲሆን ሁላችንም በዚህ ሥራ መካፈል እንችላለን። በየወሩ ሌሎችን ስለ አምላክ ቃል በማስተማር ይሖዋን ለማገልገል እንዲነሳሱ የመርዳት ግብ አለህ? አንተ በምታደርገው ጥረት ላይ የይሖዋ በረከት ታክሎበት ሰዎችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ትችል ይሆናል። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ወደ ይሖዋ ትጸልያለህ? ከራስህ ጊዜ ላይ የተወሰነውን መሥዋዕት አድርገህም እንኳ ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ፈቃደኛ ነህ? ኢዮሳፍጥ፣ ሕዝቡን ወደ እውነተኛው አምልኮ ለመመለስ ወደ ኤፍሬም ክልል እንደሄደ ሁሉ እኛም ከጉባኤ የራቁትን ለመርዳት ጥረት ማድረግ እንችላለን። w17.03 3:10, 11