ሰኔ
ዓርብ፣ ሰኔ 1
እኔም የሚቃጠል መባ አድርጌ አቀርበዋለሁ።—መሳ. 11:31
ዮፍታሔ ሌላ ልጅ ስላልነበረው የዘር ሐረጉ እንዲቀጥል የሚያደርግም ሆነ ርስቱን የሚወርስ ልጅ ማግኘት የሚችለው በሴት ልጁ በኩል ብቻ ነበር። (መሳ. 11:34) ያም ሆኖ መሳፍንት 11:35 እንደሚገልጸው ዮፍታሔ “አንዴ ለይሖዋ ቃል ገብቻለሁ፤ ልመልሰውም አልችልም” በማለት ተናገረ። ከፍተኛ መሥዋዕት ቢያስከፍለውም በይሖዋ ላይ እምነት እንዳለው ማሳየቱ የአምላክን ሞገስና በረከት አስገኝቶለታል። አንተ ብትሆን እንዲህ ታደርግ ነበር? ሕይወታችንን ለይሖዋ ስንወስን ራሳችንን ምንም ሳንቆጥብ የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም ተስለናል። ይህን ቃል መጠበቅ የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ እንደሚጠይቅብን እናውቃለን። ይሁንና የማንወደውን ነገር እንድናደርግ ስንጠየቅ፣ የፈቃደኝነት መንፈስ ያለን መሆን አለመሆኑ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። የተጠየቅነውን በማድረግና መሥዋዕትነት በመክፈል ከለመድነው ብሎም ከሚመቸን በተለየ መንገድ አምላክን ስናገለግል እምነት እንዳለን እናሳያለን። የምንከፍለው መሥዋዕት የቱንም ያህል ከባድ ቢሆን፣ ከምናገኘው የላቀ በረከት ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም።—ሚል. 3:10፤ w16.04 1:11, 14, 15
ቅዳሜ፣ ሰኔ 2
መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።—ራእይ 2:7
ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤን የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው። ፈተናዎችን ለመቋቋም፣ ለአገልግሎት የሚያስፈልገንን ድፍረትና ሥልጠና ለማግኘት እንዲሁም ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልገናል። እንግዲያው የጉባኤ ስብሰባዎችን ጨምሮ፣ ይህን መንፈስ ማግኘት የምንችልበት ማንኛውም አጋጣሚ እንዲያመልጠን አንፍቀድ። በብዙዎቹ ስብሰባዎቻችን ላይ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች ፍጻሜ እንመረምራለን። ይህ ደግሞ ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሰጣቸው ተስፋዎችም እንደሚፈጸሙ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። እርግጥ ነው፣ ማበረታቻ የምናገኘው ከመድረክ ከሚቀርበው ትምህርት ብቻ አይደለም። በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ የሚሰጡና ከልባቸው የሚዘምሩ የእምነት ባልንጀሮቻችንም ያንጹናል። (1 ቆሮ. 14:26) በተጨማሪም ከስብሰባዎቻችን በፊትና በኋላ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ስንጨዋወት፣ ከልብ የሚወዱን ወዳጆች እንዳሉን ስለምንገነዘብ መንፈሳችን ይታደሳል።—1 ቆሮ. 16:17, 18፤ w16.04 3:6, 7
እሁድ፣ ሰኔ 3
ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ።—ማቴ. 28:19
ኢየሱስ ምሥራቹ “በመላው ምድር” እንደሚሰበክ ሲናገር ሥራው ምን ያህል ስፋት እንደሚኖረው ገልጿል። (ማቴ. 24:14) ተከታዮቹ፣ ደቀ መዛሙርት የሚያደርጉት “ከሁሉም ብሔራት” የተውጣጡ ሰዎችን ነው። በመሆኑም ሥራው መካሄድ ያለበት በዓለም አቀፍ ደረጃ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የስብከቱ ሥራ ከሚከናወንበት ስፋት ጋር በተያያዘ ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት እንዴት እንደፈጸሙ መረዳት እንድንችል አንዳንድ ነጥቦችን እስቲ እንመልከት። በዩናይትድ ስቴትስ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ውስጥ ወደ 600,000 የሚጠጉ ቀሳውስት አሉ፤ በዚህች አገር 1,200,000 ገደማ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ። የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዙሪያ ያሏት ቀሳውስት ከ400,000 ብዙም አይበልጡም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን የመንግሥቱን ስብከት ሥራ የሚያከናውኑት የይሖዋ ምሥክሮች ምን ያህል እንደሆኑ ደግሞ እንመልከት። በዓለም ዙሪያ በ240 አገሮች የሚገኙ ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ፈቃደኛ አገልጋዮች ለሰዎች ምሥራቹን ይሰብካሉ። እንዴት ያለ አስደናቂ ሥራ እያከናወኑ ነው! ይህም ለይሖዋ ውዳሴና ክብር ያመጣል።—መዝ. 34:1፤ 51:15፤ w16.05 2:13, 14
ሰኞ፣ ሰኔ 4
በቀላሉ የሚቆጣ ሰው ጠብ ያስነሳል፤ ግልፍተኛ የሆነም ብዙ በደል ይፈጽማል።—ምሳሌ 29:22
በራስ የመመራት መንፈስ ሰዎች የኩራት፣ የራስ ወዳድነትና የፉክክር መንፈስ እንዲያሳዩ ያደርጋል፤ ይህ ዓለም የተሞላው ደግሞ እንዲህ ባሉ ሰዎች ነው። በዚህ መንፈስ መመራት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው፣ አንድ ግለሰብ የሚያደርገው ነገር በሌሎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምንም ይሁን ምን የራሱን ፍላጎት ብቻ ማርካቱ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጸውን የሰይጣንን ሐሳብ በተዘዋዋሪ መንገድ እየደገፈ ነው። (ዘፍ. 3:1-5) ይህ ዓይነቱ የራስ ወዳድነት አካሄድ ጠብ እንዲፈጠር ያደርጋል። ከዚህ በተቃራኒ ኢየሱስ፣ የግል ጥቅማቸውን የሚነካ ቢሆንም እንኳ ሰላምን እንዲፈልጉ ሰዎችን አስተምሯል። ኢየሱስ አለመግባባቶችን ወይም ግጭት ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን መፍታት ስለሚቻልበት መንገድ በተራራው ስብከቱ ላይ ግሩም ምክር ሰጥቷል። ለምሳሌ ደቀ መዛሙርቱ ገሮችና ሰላም ፈጣሪዎች እንዲሆኑ፣ ተቆጥተው እንዳይቆዩ፣ አለመግባባቶችን ቶሎ እንዲፈቱ እንዲሁም ጠላቶቻቸውን እንዲወዱ አሳስቧቸዋል።—ማቴ. 5:5, 9, 22, 25, 44፤ w16.05 1:4, 5
ማክሰኞ፣ ሰኔ 5
መልካም የሆነውን ነገር የማድረግ ፍላጎት እንጂ የመፈጸም ችሎታ የለኝም።—ሮም 7:18
ብዙዎቻችን ከመጠመቃችን በፊት ሕይወታችንን መሠረታዊ ከሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር ለማስማማት ጉልህ የሆኑ ለውጦችን ማድረግ አስፈልጎናል። ከተጠመቅን በኋላ ደግሞ አምላክንና ክርስቶስን በቅርብ መከተል እንድንችል አንዳንድ ለውጦችን ማድረጋችንን መቀጠል እንደሚያስፈልገን ተገንዝበናል፤ እነዚህ ለውጦች ያን ያህል ጎልተው የማይታዩ ሊሆኑ ይችላሉ። (ኤፌ. 5:1, 2፤ 1 ጴጥ. 2:21) ለምሳሌ ነቃፊዎች እንደሆንን፣ ሰዎችን እንደምንፈራ፣ የሐሜት ልማድ እንዳለን አሊያም ሌላ ድክመት እንዳለብን አስተውለን ይሆናል። ከእነዚህ ድክመቶች ጋር በተያያዘ ለውጥ ማድረግ ከጠበቅነው በላይ ከባድ ሆኖብናል? አሁንም ፍጹማን አይደለንም። (ቆላ. 3:9, 10) በመሆኑም ከተጠመቅን ሌላው ቀርቶ በእውነት ውስጥ በርካታ ዓመታት ካስቆጠርን በኋላ እንኳ ፈጽመን ስህተት እንደማንሠራ፣ ድክመታችን ሊያሸንፈን እንደማይችል ወይም መጥፎ ስሜትና ዝንባሌ እንደማያስቸግረን ማሰቡ ምክንያታዊ አይሆንም። አንዳንድ ድክመቶችን ለማሸነፍ ለዓመታት መታገል ሊያስፈልገን ይችላል።—ያዕ. 3:2፤ w16.05 4:3-5
ረቡዕ፣ ሰኔ 6
ይሖዋ የሚወዳቸውን ይገሥጻልና፤ እንዲያውም እንደ ልጁ አድርጎ የሚቀበለውን ሁሉ ይቀጣል።—ዕብ. 12:6
አንዳንዶች ‘ወላጆቼ ለምን ተግሣጽ ይሰጡኝ እንደነበር የገባኝ የራሴን ልጆች ስወልድ ነው’ ሲሉ ሰምተህ ታውቅ ይሆናል። ትልቅ ሰው ስንሆን ለተግሣጽ ያለን አመለካከት ይቀየራል፤ በሌላ አባባል ተግሣጽን ይሖዋ በሚያየው መንገድ ይኸውም የፍቅር መግለጫ እንደሆነ አድርገን መመልከት እንጀምራለን። (ዕብ. 12:5, 11) በእርግጥም ይሖዋ እንደ ልጆቹ አድርጎ ስለሚያየንና ስለሚወደን በትዕግሥት ይቀርጸናል። ጥበበኞችና ደስተኞች እንድንሆን እንዲሁም እሱን እንድንወደው ይፈልጋል። (ምሳሌ 23:15) ይሖዋ እንድንሠቃይም ሆነ ከአዳም በወረስነው ኃጢአት ምክንያት “የቁጣ ልጆች” ሆነን እንድንሞት አይፈልግም። (ኤፌ. 2:2, 3) በአንድ ወቅት “የቁጣ ልጆች” ስለነበርን አምላክን የሚያሳዝኑ ብዙ ባሕርያት ነበሩን፤ እንዲያውም አንዳንዶቻችን የአውሬ ዓይነት ባሕርይ ነበረን። ሆኖም ይሖዋ እየቀረጸን በመሆኑ ተለውጠን የበግ ዓይነት ባሕርይ ማሳየት ጀምረናል።—ኢሳ. 11:6-8፤ ቆላ. 3:9, 10፤ w16.06 1:7, 8
ሐሙስ፣ ሰኔ 7
በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጠው እንደዚህ ትንሽ ልጅ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው።—ማቴ. 18:4
አብዛኛውን ጊዜ ልጆች የማወቅ ጉጉት ያላቸው ከመሆኑም ሌላ ትሑቶች ናቸው። (ማቴ. 18:1-3) በመሆኑም ጥበበኛ ወላጆች የእውነትን እውቀት በልጆቻቸው ልብና አእምሮ ውስጥ ለመቅረጽ እንዲሁም ልጆቻቸው ለእውነት ፍቅር እንዲያድርባቸው ለመርዳት ይጥራሉ። (2 ጢሞ. 3:14, 15) እርግጥ ነው፣ ወላጆች በዚህ ረገድ እንዲሳካላቸው በቅድሚያ እውነትን በራሳቸው ልብ ውስጥ መቅረጽና በአኗኗራቸው ማሳየት ይኖርባቸዋል። ወላጆች እውነትን በቃል ከመናገር አልፈው በሕይወታቸው ተግባራዊ የሚያደርጉት ከሆነ ልጆቻቸው እውነትን መውደድ ቀላል ይሆንላቸዋል። በተጨማሪም ወላጆቻቸው ተግሣጽ የሚሰጧቸው ስለሚወዷቸው እንደሆነና እንዲህ ያለው ተግሣጽ ይሖዋ ለእነሱ ያለውን ፍቅር እንደሚያሳይ ይገነዘባሉ። እኛም ትሑቶችና ምንጊዜም ይሖዋን የምንታዘዝ ከሆንን ልክ እንደ ነቢዩ ዳንኤል በይሖዋ ፊት የተወደድን እንሆናለን። (ዳን. 10:11, 19) ከዚህም በላይ ይሖዋ በቃሉ፣ በመንፈሱና በድርጅቱ አማካኝነት ሁልጊዜ ይቀርጸናል። w16.06 2:14, 17
ዓርብ፣ ሰኔ 8
እንደ ልቤ የሆነውን የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ።—ሥራ 13:22
ይሖዋ ዳዊትን ይወደው የነበረ ሲሆን “እንደ ልቤ የሆነ” ሲል ጠርቶታል። (1 ሳሙ. 13:13, 14) ሆኖም ዳዊት ከጊዜ በኋላ ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር በመፈጸሙ ቤርሳቤህ አረገዘች። በዚህ ጊዜ ባለቤቷ ኦርዮ ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፎ በውጊያ ላይ ነበር። ዳዊት፣ ኦርዮ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ቤት በተመለሰበት ወቅት ከቤርሳቤህ ጋር እንዲተኛ ለማድረግ ሞከረ፤ ይህን ያደረገው ቤርሳቤህ የፀነሰችው ከኦርዮ እንደሆነ ተደርጎ እንዲታሰብ ብሎ ነው። ኦርዮ ግን ከቤርሳቤህ ጋር አላደረም፤ በመሆኑም ዳዊት፣ ኦርዮ በጦርነቱ እንዲገደል መመሪያ አስተላለፈ። ዳዊት በፈጸመው ወንጀል ምክንያት ከባድ ቅጣት ደርሶበታል፤ በራሱም ሆነ በቤተሰቡ ላይ መከራ አምጥቷል። (2 ሳሙ. 12:9-12) ይሁን እንጂ በጥቅሉ ሲታይ ዳዊት በአምላክ ፊት “በንጹሕ ልብና በቅንነት” ስለተመላለሰ ይሖዋ ምሕረት አድርጎለታል። (1 ነገ. 9:4) በዚያ ዘመን የምትኖር የአምላክ አገልጋይ ብትሆን ኖሮ ይህን ሁኔታ ስታይ ምን ይሰማህ ነበር? ዳዊት በፈጸመው ኃጢአት የተነሳ ትሰናከል ነበር? w16.06 4:7
ቅዳሜ፣ ሰኔ 9
የተወሰነው ጊዜ መቼ እንደሆነ ስለማታውቁ ምንጊዜም በንቃት ተከታተሉ፤ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።—ማር. 13:33
እኛ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ኢየሱስ የሰጠውን ይህን ማስጠንቀቂያ በቁም ነገር እንመለከተዋለን። የምንኖረው ‘በፍጻሜው ዘመን’ ውስጥ እንደሆነና ‘ታላቁ መከራ’ ሊጀምር የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን እናውቃለን። (ዳን. 12:4፤ ማቴ. 24:21) በተለያዩ የዓለም ክፍሎች አሰቃቂ ጦርነቶች እንደሚካሄዱ እንዲሁም የምግብ እጥረት፣ ቸነፈርና የምድር ነውጥ እንደሚከሰት እናውቃለን፤ ከዚህም በላይ የሥነ ምግባር ብልግና እንዲሁም ሕገ ወጥነት እየተስፋፋ ሲሆን ብዙዎች በሃይማኖት ግራ ተጋብተዋል። በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች ስለ አምላክ መንግሥት በስፋት እየሰበኩ ነው። (ማቴ. 24:7, 11, 12, 14፤ ሉቃስ 21:11) እኛም ኢየሱስ የሚመጣበትንና የአምላክን ዓላማ የሚያስፈጽምበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። (ማር. 13:26, 27) ከታላቁ መከራ ጋር በተያያዘ ግን የቱንም ያህል ጥረት ብናደርግ ይህ ክንውን የሚጀምርበትን ቀንና ሰዓት ቀርቶ ዓመቱን እንኳ ማወቅ አንችልም። w16.07 2:2-4
እሁድ፣ ሰኔ 10
ያለ ምንም ፍርሃት ወደ ጸጋው ዙፋን እንቅረብ።—ዕብ. 4:16
ይሖዋ በሰማይ ወዳለው ዙፋኑ በጸሎት የመቅረብን መብት በጸጋው ሰጥቶናል። ይህን መብት የዘረጋልን በልጁ በኩል ነው፤ “በእሱም አማካኝነት ይህ የመናገር ነፃነት አለን፤ በክርስቶስ ላይ ባለን እምነት አማካኝነትም በልበ ሙሉነት ወደ አምላክ በነፃነት መቅረብ እንችላለን።” (ኤፌ. 3:12) በእርግጥም ይሖዋ በጸሎት አማካኝነት በነፃነት ወደ እሱ እንድንቀርብ መፍቀዱ አስደናቂ የሆነ የጸጋው መገለጫ ነው። ጳውሎስ “እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ምሕረትና ጸጋ እናገኝ ዘንድ” ወደ ይሖዋ በነፃነት እንድንጸልይ አበረታቶናል። (ዕብ. 4:16ሀ) በሕይወታችን ውስጥ መከራ ወይም አስጨናቂ ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜ ሁሉ ይሖዋ በምሕረቱ እንዲረዳን ወደ እሱ መጮኽ እንችላለን። እርዳታው የማይገባን ብንሆንም እንኳ ይሖዋ ልመናችንን ሰምቶ ብዙውን ጊዜ በእምነት ባልንጀሮቻችን በኩል ምላሽ ይሰጠናል፤ በመሆኑም “በሙሉ ልብ ‘ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?’ እንላለን።”—ዕብ. 13:6፤ w16.07 3:12, 13
ሰኞ፣ ሰኔ 11
ሣራም አብርሃምን ጌታዬ እያለች በመጥራት ትታዘዘው ነበር። እናንተም . . . ልጆቿ ናችሁ።—1 ጴጥ. 3:6
ኖኅና ሦስቱ ወንዶች ልጆቹ ከአንድ በላይ ባያገቡም በጥንት ዘመን ብዙ ሚስቶችን ማግባት የተለመደ ነበር። በብዙ ባሕሎች ውስጥ የፆታ ብልግና በጣም የተስፋፋ ከመሆንም አልፎ በአንዳንድ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ውስጥ እንኳ ተካትቶ ነበር። አብራም (አብርሃም) እና ሚስቱ ሦራ (ሣራ) አምላክ በሰጣቸው መመሪያ መሠረት ወደ ከነዓን በሄዱበት ወቅት የጋብቻ ዝግጅትን የሚያቃልሉ ልማዶች በዚያ አካባቢ ተስፋፍተው ነበር። የሰዶምና የገሞራ ነዋሪዎች ልቅ የሆነ የፆታ ብልግና ይፈጽሙ ወይም እንዲህ ያለውን ድርጊት በቸልታ ያልፉ ስለነበር ይሖዋ እነዚህ ከተሞች እንዲጠፉ ወሰነ። አብርሃም በቤተሰቡ ላይ የራስነት ሥልጣኑን በአግባቡ ይጠቀምበት የነበረ ሲሆን ሣራም ለባሏ በመገዛት ረገድ ግሩም ምሳሌ ነች። (1 ጴጥ. 3:3-5) አብርሃም፣ ልጁ ይስሐቅ ይሖዋን የምታመልክ ሴት እንዲያገባ አድርጓል። ይስሐቅም ለልጁ ለያዕቆብ እንዲህ ያደረገ ሲሆን ከጊዜ በኋላ 12ቱ የእስራኤል ነገዶች የተገኙት ከያዕቆብ ወንዶች ልጆች ነው። w16.08 1:10
ማክሰኞ፣ ሰኔ 12
ጥቂት የሆነው ሺህ፣ ትንሽ የሆነውም ኃያል ብሔር ይሆናል።—ኢሳ. 60:22
ይህ ትንቢት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ፍጻሜውን እያገኘ ነው። በ2015 የአገልግሎት ዓመት 8,220,105 የመንግሥቱ አስፋፊዎች በዓለም ዙሪያ በቅንዓት ምሥራቹን መስበካቸው ይህን ያሳያል! የትንቢቱ የመጨረሻ ክፍል፣ ሁሉንም ክርስቲያኖች በግለሰብ ደረጃ ይመለከታል፤ ምክንያቱም ሰማያዊ አባታችን “እኔ ይሖዋ፣ ይህን በራሱ ጊዜ አፋጥነዋለሁ” ብሏል። አንድ መኪና ፍጥነቱን እየጨመረ ሲሄድ ተሳፋሪዎቹ ይህን እንደሚያስተውሉ ሁሉ እኛም ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ይበልጥ እየተጧጧፈ እንደሆነ ማስተዋላችን አይቀርም። ታዲያ በዚህ ረገድ ምን እያደረግን ነው? የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት ለመስበክ የቻልነውን ያህል እየጣርን ነው? ብዙ ወንድሞችና እህቶች በዘወትር ወይም በረዳት አቅኚነት እያገለገሉ ነው። ሌሎች ደግሞ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውረን እንድናገለግል ወይም በሌሎች ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች እንድንካፈል ለሚቀርበው ጥሪ ምላሽ እየሰጡ ነው፤ ታዲያ ይህ የሚያስደስት አይደለም? ወንድሞችም ሆንን እህቶች ‘ከጌታ ሥራ’ ጋር በተያያዘ ልናከናውነው የምንችለው ብዙ ነገር አለ።—1 ቆሮ. 15:58፤ w16.08 3:1, 2
ረቡዕ፣ ሰኔ 13
የይሖዋ እጅ ማዳን ይሳናት ዘንድ አላጠረችም።—ኢሳ. 59:1
እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት በተአምራዊ መንገድ ነፃ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ አማሌቃውያን ጥቃት ሰነዘሩባቸው። ደፋር የሆነው ኢያሱ የሙሴን አመራር በመከተል እስራኤላውያንን እየመራ ለጦርነት ዘመተ። በዚህ ጊዜ ሙሴ፣ ከአሮንና ከሁር ጋር በመሆን በአቅራቢያው ወደሚገኝና ጦር ሜዳውን ለማየት ወደሚያስችል ኮረብታ ወጣ። ሙሴ ይህን ያደረገው እስራኤላውያን ድል እንዲቀዳጁ የሚያስችላቸውን ስልት ለመጠቀም ስላሰበ ነው። በመሆኑም ሙሴ የእውነተኛውን አምላክ በትር በእጆቹ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ያዘ። እሱ እጆቹን እስካላወረደ ድረስ እስራኤላውያን በአማሌቃውያን ላይ እንዲያይሉና ድል እንዲያደርጓቸው ይሖዋ ይረዳቸው ነበር። ይሁንና ሙሴ እጆቹ ሲዝሉ ወደ ታች ያወርዳቸው ነበር፤ በዚህ ጊዜ አማሌቃውያን ያይሉባቸዋል። አሮንና ሁር ይህን ሲመለከቱ ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ “ድንጋይ ወስደው [ከሙሴ ሥር] አስቀመጡለት፤ እሱም በድንጋዩ ላይ ተቀመጠ። ከዚያም አሮንና ሁር አንዱ በአንደኛው በኩል፣ ሌላው ደግሞ በሌላኛው በኩል ሆነው እጆቹን ደገፉለት፤ በመሆኑም ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ እጆቹ ባሉበት ጸኑ።” እስራኤላውያን፣ አምላክ በኃያል እጁ ስለደገፋቸው በውጊያው ድል አደረጉ።—ዘፀ. 17:8-13፤ w16.09 1:5-7
ሐሙስ፣ ሰኔ 14
ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው።—ሮም 7:21
ጳውሎስ፣ በይሖዋ በመታመን ወደ እሱ ከጸለየና በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ካዳበረ በውስጡ ያለውን ይህን ትግል ማሸነፍ እንደሚችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር። እኛም ካሉብን ድክመቶች ጋር በምናደርገው ትግል አሸናፊዎች መሆን እንችላለን። እንዴት? የጳውሎስን ምሳሌ በመከተል፣ ድክመቶቻችንን በራሳችን ኃይል ለማሸነፍ ከመታገል ይልቅ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ በመታመን እንዲሁም በቤዛው ላይ እምነት በማሳደር ነው። አምላክ አንድ ጉዳይ ምን ያህል እንዳሳሰበን እንድናሳይ የሚፈልግበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ እኛ ራሳችን (ወይም አንድ የቤተሰባችን አባል) በጠና ብንታመም አሊያም ግፍ ቢፈጸምብን ምን እናደርጋለን? ይሖዋ፣ በታማኝነት ለመቀጠል ብሎም ደስታችንንና መንፈሳዊ ሚዛናችንን ጠብቀን ለመኖር የሚያስችለንን ብርታት እንዲሰጠን አዘውትረን በመለመን በእሱ ሙሉ በሙሉ እንደምንታመን እናሳያለን። (ፊልጵ. 4:13) በጳውሎስ ዘመንም ሆነ በዚህ ዘመን የኖሩ የብዙ ክርስቲያኖች ተሞክሮ እንደሚያሳየው ጸሎት ኃይላችን እንዲታደስና ለመጽናት የሚያስችል ድፍረት እንድናገኝ ይረዳናል። w16.09 2:14, 15
ዓርብ፣ ሰኔ 15
ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ አይሁዳውያን . . . ዕብራይስጥ ተናጋሪ በሆኑት አይሁዳውያን ላይ ቅሬታ ማሰማት ጀመሩ።—ሥራ 6:1
የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ እያደገ ሲሄድ መድልዎ እንዳለ የሚጠቁም ሁኔታ መታየት ጀመረ። ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ አይሁዳውያን መበለቶቻቸው ቸል ስለተባሉባቸው ቅሬታ አሰሙ። ሐዋርያት ይህን ችግር ለመፍታትና ማንም ቸል እንዳይባል ለማድረግ ሲሉ ሰባት ወንዶች ሾሙ። ሰባቱም ወንዶች የግሪክኛ ስም ያላቸው መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው፤ ምናልባትም ሐዋርያት ይህን ያደረጉት በዜግነት ምክንያት በጥንቶቹ ክርስቲያኖች መካከል ሊፈጠር የሚችለውን አለመግባባት ለማብረድ አስበው ሊሆን ይችላል። (ሥራ 6:2-6) ሁላችንም፣ አናስተውለው ይሆናል እንጂ ያደግንበት ባሕል ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርግብናል። (ሮም 12:2) በተጨማሪም ጎረቤቶቻችን አሊያም አብረውን የሚሠሩ ወይም የሚማሩ ሰዎች ከእኛ የተለየ ዜግነት፣ ዘርና የቆዳ ቀለም ያላቸውን ሰዎች የሚያንቋሽሽ ነገር ሲናገሩ እንሰማ ይሆናል። ታዲያ እንዲህ ያለው የተዛባ አመለካከት ተጽዕኖ እያደረገብን ይሆን? አንድ ሰው በባሕላችን ውስጥ ያለን አንድ ነገር አጋንኖ በማቅረብ በትውልድ አገራችን ላይ ቢቀልድ ምን ይሰማናል? w16.10 1:7, 8
ቅዳሜ፣ ሰኔ 16
[የአምላክ] የማይታዩት ባሕርያቱ . . . በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።—ሮም 1:20
“ማስተዋል” ሲባል በቀላሉ የማይታይን ወይም ግልጽ ያልሆነን ነገር መረዳት ወይም መገንዘብ ማለት ነው። (ዕብ. 11:3) በመሆኑም አስተዋይ የሆኑ ሰዎች በሚያዩትና በሚሰሙት ነገር ብቻ ከመወሰን ይልቅ አእምሯቸውን ወይም የማመዛዘን ችሎታቸውን ይጠቀማሉ። የይሖዋ ድርጅት በዚህ ረገድ እኛን ለመርዳት ሲል ጥሩ ምርምር የተደረገባቸው ብዙ መርጃ መሣሪያዎች አቅርቦልናል። በእነዚህ መሣሪያዎች መጠቀማችን ፈጣሪያችንን በእምነት ዓይናችን ‘ለማየት’ ያስችለናል። (ዕብ. 11:27) ከእነዚህ መሣሪያዎች መካከል አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች የአምላክን ክብር ይገልጣሉ የተባለው ቪዲዮ (እንግሊዝኛ) እንዲሁም ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? እና የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የተባሉት ብሮሹሮች እና ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ይገኙበታል። ብዙውን ጊዜ ንቁ! መጽሔት፣ በአምላክ እንዲያምኑ ያደረጋቸው ምን እንደሆነ ከገለጹ የሳይንስ ሊቃውንትና ሌሎች ሰዎች ጋር የተደረጉ ቃለ ምልልሶችን ይዞ ይወጣል። “ንድፍ አውጪ አለው?” በሚል ዓምድ ሥር የሚወጡት የተለያዩ ርዕሶች ደግሞ በፍጥረት ላይ የሚታየውን አስደናቂ ንድፍ ያጎላሉ። የሳይንስ ሊቃውንት እነዚህን አስደናቂ ንድፎች ለመኮረጅ ብዙ ጊዜ ጥረት ያደርጋሉ። w16.09 4:4, 5
እሁድ፣ ሰኔ 17
በእምነታቸው ምክንያት በመልካም [ተመሥክሮላቸዋል]።—ዕብ. 11:39
በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ የተዘረዘሩት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በሞት ያንቀላፉት፣ ተስፋ የተሰጠበት “ዘር” ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ ሕይወት ለማግኘት የሚያስችል መንገድ ከመክፈቱ በፊት ነው። (ገላ. 3:16) ያም ቢሆን ከሞት ተነስተው ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ፤ በዚያም ፍጹም ሕይወት ያገኛሉ። (መዝ. 37:11፤ ኢሳ. 26:19፤ ሆሴዕ 13:14) ዕብራውያን 11:13 በቅድመ ክርስትና ዘመን ስለኖሩ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “እነዚህ ሁሉ የተስፋውን ቃል ፍጻሜ ባያዩም እምነታቸውን እንደጠበቁ ሞቱ፤ ሆኖም ከሩቅ አይተው በደስታ ተቀበሉት።” ከእነዚህ መካከል አንዱ አብርሃም ነው። ይሁንና አብርሃም፣ ተስፋ የተሰጠበት “ዘር” በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖረው አስደሳች ሕይወት በአእምሮው ቁልጭ ብሎ ይታየው ነበር? ኢየሱስ ለተቃዋሚዎቹ የተናገረው ሐሳብ ለዚህ ጥያቄ ግልጽ መልስ ይሰጠናል፤ “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን እንደሚያይ ተስፋ በማድረግ እጅግ ተደሰተ፤ አይቶትም ደስ ተሰኘ” ብሎ ነበር። (ዮሐ. 8:56) ሣራ፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ሌሎች በርካታ የአምላክ አገልጋዮችም “አምላክ ንድፍ ያወጣላትንና የገነባትን” ከተማ ይኸውም ወደፊት የሚቋቋመውን የአምላክ መንግሥት በጉጉት ይጠባበቁ ነበር።—ዕብ. 11:8-11፤ w16.10 3:4, 5
ሰኞ፣ ሰኔ 18
በማንኛውም ጊዜ . . . መጸለያችሁን ቀጥሉ።—ኤፌ. 6:18
ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እውነትን ስለገለጠልንና በምሥራቹ እንድናምን ስላስቻለን ምንኛ አመስጋኞች ነን! (ሉቃስ 10:21) ይሖዋ፣ “የእምነታችን ዋና ወኪል እና ፍጹም አድራጊ” በሆነው በልጁ በኩል ወደ ራሱ ስለሳበን ምንጊዜም ልናመሰግነው ይገባል። (ዕብ. 12:2) እንዲህ ላለው ጸጋ ያለንን አመስጋኝነት ለማሳየት በጸሎትና የአምላክን ቃል በማጥናት እምነታችንን ማጠናከራችንን መቀጠል ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 2:2) ይሖዋ ቃል በገባቸው ተስፋዎች ላይ እምነት እንዳለን ምንጊዜም ማሳየት ይኖርብናል። ይህንንም የምናደርገው ሌሎች በግልጽ ሊያዩት በሚችሉት መንገድ ሊሆን ይገባል። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ሁልጊዜ እንሳተፋለን። በተጨማሪም “ለሁሉም፣ በተለይ ደግሞ በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች መልካም” ማድረጋችንን አናቋርጥም። (ገላ. 6:10) ከዚህም ሌላ ‘አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፍፈን ለመጣል’ ብርቱ ጥረት እናደርጋለን።—ቆላ. 3:5, 8-10፤ w16.10 4:11, 12
ማክሰኞ፣ ሰኔ 19
[ይሖዋ] ሰማያትን በጥበብ ሠራ።—መዝ. 136:5
ጽንፈ ዓለም የተደራጀው በእርግጥም አስገራሚ በሆነ መንገድ ነው። ከዚህ አንጻር ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ በሚገባ የተደራጁ እንዲሆኑ መፈለጉ የሚያስገርም አይደለም። እንዲያውም ይህን ማድረግ እንድንችል አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። የአምላክ ድርጅት የሚሰጠንን መመሪያዎችና የይሖዋን መሥፈርቶች ችላ ማለት ሕይወታችን ደስታ የራቀውና በመከራ የተሞላ እንዲሆን ያደርጋል። የጥንቶቹ እስራኤላውያን፣ በመደራጀት ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። ለአብነት ያህል፣ በሙሴ ሕግ ሥር “በተደራጀ መልክ [የሚያገለግሉ] ሴት አገልጋዮች” ነበሩ። (ዘፀ. 38:8) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ንጉሥ ዳዊት ሌዋውያኑንና ካህናቱን ሥራቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን በሚያስችል ሁኔታ አደራጅቷቸዋል። (1 ዜና 23:1-6፤ 24:1-3) በአንደኛው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ የተደራጀ ነበር፤ መጀመሪያ ላይ በሐዋርያት የተዋቀረው የበላይ አካል ለጉባኤው አመራር ይሰጥ ነበር። (ሥራ 6:1-6) ለጉባኤዎች ምክርና መመሪያ የሚተላለፈው በመንፈስ መሪነት በተጻፉ ደብዳቤዎች አማካኝነት ነበር።—1 ጢሞ. 3:1-13፤ ቲቶ 1:5-9፤ w16.11 2:3, 6, 8, 9
ረቡዕ፣ ሰኔ 20
በምርኮ መወሰድ የሚገባው ሁሉ . . . ተማርኮ ይወሰድ!—ኤር. 15:2
በ607 ዓ.ዓ በዳግማዊ ናቡከደነጾር የሚመራ ግዙፍ የባቢሎናውያን ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ወረረ። በዚያ ወቅት የነበረውን ደም መፋሰስ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “[ናቡከደነጾር] ወጣቶቻቸውን በቤተ መቅደሳቸው ውስጥ በሰይፍ ገደለ፤ ለወጣቱም ሆነ ለድንግሊቱ፣ ለሽማግሌውም ሆነ ለአቅመ ደካማው አልራራም። . . . የእውነተኛውን አምላክ ቤት አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፈረሰ፤ የማይደፈሩ ማማዎቿን ሁሉ በእሳት አቃጠለ፤ እንዲሁም ውድ የሆኑትን ዕቃዎች በሙሉ አወደመ።” (2 ዜና 36:17, 19) የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች፣ ከተማዋ መጥፋቷ ሊያስደነግጣቸው አይገባም ነበር። አይሁዳውያን የአምላክን ሕግ ችላ ማለታቸውን ከቀጠሉ ይሖዋ ለባቢሎናውያን አሳልፎ እንደሚሰጣቸው የአምላክ ነቢያት ለዓመታት ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። በርካታ አይሁዳውያን በሰይፍ ስለት እንደሚሞቱና ከሞት የተረፉት ደግሞ ቀሪ ሕይወታቸውን ባቢሎን ውስጥ በግዞት እንደሚያሳልፉ ትንቢት ተነግሮ ነበር። w16.11 4:1, 2
ሐሙስ፣ ሰኔ 21
በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ።—ሮም 5:12
ኃጢአትና ሞት “ወደ ዓለም” እንዲገባ ምክንያት የሆነው “አንድ ሰው” ሲሆን እሱም አዳም ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በአንድ ሰው በደል የተነሳ ሞት” እንደነገሠ የሚናገረው ለዚህ ነው። ጳውሎስ “የአምላክን የተትረፈረፈ ጸጋ” ማግኘት የሚቻለው “በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት” እንደሆነ ተናግሯል። (ሮም 5:12, 15, 17) ይህ ጸጋ የሰውን ዘር በሙሉ ጠቅሟል። ጳውሎስ “በአንዱ ሰው [በኢየሱስ] መታዘዝም ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ” ብሏል። በመሆኑም የአምላክ ጸጋ “በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የዘላለም ሕይወት” ያስገኛል። (ሮም 5:19, 21) ይሖዋ፣ ልጁ ወደ ምድር መጥቶ ቤዛውን እንዲከፍል የማድረግ ግዴታ አልነበረበትም። ይሖዋና ኢየሱስ፣ ኃጢአተኛ የሆኑት የሰው ልጆች በቤዛው አማካኝነት ይቅርታ ማግኘት የሚችሉበትን ዝግጅት ያደረጉት የሰው ልጆች ይህን ለማግኘት የሚበቁ ወይም የሚገባቸው ስለሆኑ አይደለም። በመሆኑም የኃጢአት ይቅርታ እና የዘላለም ሕይወት ተስፋ ማግኘታችን ይገባናል የማንለው ደግነት ወይም ጸጋ ነው። እንግዲያው የአምላክን የደግነት ስጦታ ይኸውም ጸጋውን ከፍ አድርገን ልንመለከተውና ይህንንም በአኗኗራችን ልናሳይ ይገባል። w16.12 1:1, 6, 7
ዓርብ፣ ሰኔ 22
ሥጋ ለአምላክ ሕግ ስለማይገዛ . . . በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር የአምላክ ጠላት ያደርጋል።—ሮም 8:7
ራሳችንን መመርመራችን አስፈላጊ ነው። ለምን? ጳውሎስ “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሞት ያስከትላል” ሲል ጽፏል። (ሮም 8:6) ይህ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፤ በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር በአሁኑ ጊዜ መንፈሳዊ ሞት የሚያስከትል ሲሆን ወደፊት ደግሞ ቃል በቃል ሕይወታችንን ያሳጣናል። ሆኖም ጳውሎስ፣ አንድ ሰው “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር” ስለጀመረ ብቻ መጨረሻው ሞት እንደሚሆን መናገሩ አልነበረም። ለውጥ ማድረግ ይቻላል። በቆሮንቶስ ይኖር የነበረውን የሥነ ምግባር ብልግና የፈጸመ ሰው እንደ ምሳሌ እንውሰድ፦ ይህ ሰው “በሥጋዊ ነገሮች” ላይ በማተኮሩ ከጉባኤ ተወግዷል። ያም ቢሆን ለውጥ ማድረግ ይችል ነበር፤ ደግሞም ለውጥ አድርጓል። ግለሰቡ ሥጋዊ ነገሮችን መከተሉን ትቶ ወደ ትክክለኛው ጎዳና ተመልሷል። (2 ቆሮ. 2:6-8) ይህ ሰው ለውጥ ማድረግ ከቻለ በዛሬው ጊዜ የሚገኝ ክርስቲያንም ለውጥ ማድረግ ይችላል፤ በተለይ ደግሞ በቆሮንቶስ የነበረውን ሰው ያህል ሥጋዊ ነገሮችን በመከተል ረገድ የከፋ ጎዳና ያልተከተለ ሰው መቀየር ላይከብደው ይችላል። በእርግጥም ጳውሎስ “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር” የሚያስከትለውን መዘዝ በተመለከተ የሰጠው ማስጠንቀቂያ፣ ክርስቲያኖች አስፈላጊ የሆነውን ማንኛውንም ለውጥ እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይገባል! w16.12 2:5, 12, 13
ቅዳሜ፣ ሰኔ 23
ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል።—መዝ. 55:22
ይሖዋ ‘እንደሚደግፈን’ ተማምነን ‘ሸክማችንን በእሱ ላይ መጣል’ መቻላችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! አምላክ “ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ” እንደሚያደርግልን ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን። (ኤፌ. 3:20) እስቲ አስበው፤ ይሖዋ የሚያደርግልን “አብልጦ” ወይም “እጅግ አብልጦ” ብቻ ሳይሆን ከምናስበው ሁሉ “በላይ እጅግ አብልጦ” ነው! ሽልማታችንን ማግኘት ከፈለግን በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት ማሳደር እንዲሁም መመሪያዎቹን መታዘዝ ይኖርብናል። ሙሴ የእስራኤልን ብሔር እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርገህ እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር ላይ ይሖዋ [ይባርክሃል]፤ . . . ይህ የሚሆነው ግን የአምላክህን የይሖዋን ቃል በትኩረት የምትሰማና እኔ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዛት በሙሉ በጥንቃቄ የምትፈጽም ከሆነ ነው። አምላክህ ይሖዋ በገባልህ ቃል መሠረት ይባርክሃል።” (ዘዳ. 15:4-6) ይሖዋ፣ በታማኝነት እስካገለገልከው ድረስ እንደሚባርክህ ሙሉ በሙሉ ትተማመናለህ? ይህን ለማድረግ በቂ ምክንያት አለህ። w16.12 4:8, 9
እሁድ፣ ሰኔ 24
ይሖዋ . . . አንተን የራሱ ሕዝብ፣ ልዩ ንብረቱ እንድትሆን መርጦሃል።—ዘዳ. 7:6
ይሖዋ ይህን ምርጫ ያደረገው እንዲሁ ደስ ስላለው አይደለም። ይሖዋ ይህን ውሳኔ ያደረገው ከብዙ ዘመናት በፊት ለወዳጁ ለአብርሃም የገባውን ቃል ለመፈጸም ሲል ነው። (ዘፍ. 22:15-18) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ምንጊዜም ነፃነቱን የሚጠቀመው ከፍቅሩና ከፍትሑ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው። በተደጋጋሚ ከእውነተኛው አምልኮ ዘወር ይሉ ለነበሩት እስራኤላውያን እርማት የሰጠበት መንገድ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው። እስራኤላውያን ከልባቸው ንስሐ ገብተው ወደ እሱ እስከተመለሱ ድረስ ፍቅሩንና ምሕረቱን ሊያሳያቸው ፈቃደኛ ነበር፤ “ከዳተኛነታቸውን እፈውሳለሁ። በገዛ ፈቃዴ እወዳቸዋለሁ” ብሏል። (ሆሴዕ 14:4) ይሖዋ፣ የመምረጥ ነፃነቱን ለሌሎች መልካም ነገር ለማድረግ ተጠቅሞበታል፤ በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል! ይሖዋ የፍጥረት ሥራውን ሲጀምር የማሰብ ችሎታ ላላቸው ፍጥረታቱ በፍቅር ተነሳስቶ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷቸዋል። ይህ ስጦታ መጀመሪያ የተሰጠው “የማይታየው አምላክ አምሳል” ለሆነው ለይሖዋ የበኩር ልጅ ነው። (ቆላ. 1:15) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትም እንኳ ምንጊዜም ለአባቱ ታማኝ ለመሆን እንዲሁም ሰይጣን ባስነሳው ዓመፅ ላለመተባበር መርጧል። w17.01 2:3, 4
ሰኞ፣ ሰኔ 25
[አምላክ] የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።—ዕብ. 6:10
በሕይወታችን ውስጥ የሚከሰቱት ለውጦች፣ በይሖዋ ሥራ የምናደርገው ተሳትፎ እንዲጨምር ወይም እንዲቀንስ ሊያደርጉ ይችላል። ወጣት ነህ ወይስ በዕድሜ የገፋህ? የጤንነትህ ሁኔታስ እንዴት ነው? ይሖዋ እያንዳንዳችን በእሱ አገልግሎት ውስጥ የተሻለ አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችልበትን አቅጣጫ ምንጊዜም ያስባል። ይሖዋ ከእኛ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ነው፤ እንዲሁም የምናደርገውን ነገር ሁሉ ከፍ አድርጎ ይመለከታል። ኢየሱስ በተሰጠው የሥራ ምድብ ሁሉ ደስተኛ ነበር፤ እኛም ደስተኛ መሆን እንችላለን። (ምሳሌ 8:30, 31) ልኩን የሚያውቅ ሰው በተሰጠው ሥራ ወይም ኃላፊነት ረክቶ ይኖራል። መብት ስለማግኘት አይጨነቅም፤ ወይም ሌሎች ባገኙት መብት ላይ አያተኩርም። ከዚህ ይልቅ አሁን ያለውን ኃላፊነት ከይሖዋ እንዳገኘው አድርጎ ስለሚመለከተው ከሥራው ደስታና እርካታ ለማግኘት ጥረት ያደርጋል። እንዲሁም ሌሎች ከይሖዋ ለተቀበሉት መብት ወይም ኃላፊነት ከልብ የመነጨ አክብሮት እንዳለው ያሳያል። ልካችንን ማወቃችን ለሌሎች የሚገባቸውን ክብርና ድጋፍ በመስጠት ደስታ እንድናገኝ ይረዳናል።—ሮም 12:10፤ w17.01 3:13, 14
ማክሰኞ፣ ሰኔ 26
ከአባቱ ጋር እንደሚሠራ ልጅ ምሥራቹን በማስፋፋቱ ሥራ ከእኔ ጋር እንደ ባሪያ [አገልግሏል]።—ፊልጵ. 2:22
አንዳንድ ወጣት ወንድሞች፣ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችም የሚሳተፉበትን ሥራ የማስተባበር ኃላፊነት ተቀብለው ይሆናል። እነዚህ ወንድሞች አሁን ይህን ኃላፊነት ቢረከቡም ውሳኔ ከማድረጋቸው በፊት ጥበብና ተሞክሮ ያላቸውን በዕድሜ የገፉ ወንድሞች ማማከራቸው ጠቃሚ ነው። ወጣቱ ጢሞቴዎስ ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር ለበርካታ ዓመታት አብሮ ሠርቷል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል፦ “በጌታ ልጄ የሆነውን የምወደውንና ታማኝ የሆነውን ጢሞቴዎስን የምልክላችሁ ለዚህ ነው። እሱም . . . ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በተያያዘ አገልግሎቴን የማከናውንባቸውን ዘዴዎች ያሳስባችኋል።” (1 ቆሮ. 4:17) ይህ አጭር መግለጫ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ ምን ያህል ተባብረው ይሠሩ እንደነበር በግልጽ ያሳያል። ጳውሎስ ‘አገልግሎቱን የሚያከናውንባቸውን ዘዴዎች’ ጊዜ ወስዶ ለጢሞቴዎስ አስተምሮታል። ጢሞቴዎስም የተሰጠውን ሥልጠና በሚገባ የተቀበለ ሲሆን በጳውሎስ ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፏል፤ ጢሞቴዎስ በቆሮንቶስ ያሉትን ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት እንደሚችል ጳውሎስ ተማምኖበት ነበር። ጳውሎስ፣ በዛሬው ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ወንድሞችን ለኃላፊነት ብቁ እንዲሆኑ ለሚያሠለጥኑ ሽማግሌዎች ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። w17.01 5:13, 14
ረቡዕ፣ ሰኔ 27
ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት [ይነሳሉ]።—ሥራ 24:15
ይሖዋ፣ ሰዎች በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ እንዲሞቱ አይፈልግም። የሕይወት ምንጭ እንደመሆኑ መጠን ከሞት ለተነሱ ሁሉ አባት ይሆንላቸዋል። (መዝ. 36:9) ከዚህ አንጻር ኢየሱስ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ” ብለን እንድንጸልይ ማስተማሩ ተገቢ ነው። (ማቴ. 6:9) ይሖዋ ሙታንን ከማስነሳት ጋር በተያያዘ ኢየሱስ ትልቅ ሚና እንዲኖረው አድርጓል። (ዮሐ. 6:40, 44) ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት” እንደሆነ የተናገረው ቃል በገነት ውስጥ ፍጻሜውን ያገኛል። (ዮሐ. 11:25) ይሖዋ የቤተሰቡ አባላት እንዲሆኑ የጋበዘው የተመረጡ ጥቂት ሰዎችን ብቻ አይደለም፤ ኢየሱስ “የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ ለእኔ ወንድሜ፣ እህቴና እናቴ ነው” በማለት መናገሩ ይህን ያሳያል። (ማር. 3:35) የአምላክ ፈቃድ ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡና ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” አገልጋዮቹ እንዲሆኑ ነው። በክርስቶስ ቤዛ ላይ እምነት እንዳላቸው የሚያሳዩና የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ ሁሉ “መዳን ያገኘነው በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከአምላካችን እንዲሁም ከበጉ ነው” በማለት በታላቅ ድምፅ ከሚጮኹት ሰዎች መካከል የመሆን አጋጣሚ አላቸው።—ራእይ 7:9, 10፤ w17.02 2:10, 11
ሐሙስ፣ ሰኔ 28
በመካከላችሁ ሆነው አመራር የሚሰጡትን አስቡ።—ዕብ. 13:7
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በተለያዩ ቋንቋዎች ለማሰራጨት ሲባል ዛየንስ ዎች ታወር ትራክት ሶሳይቲ የተባለው ማኅበር በ1884 ተቋቋመ፤ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ቻርልስ ቴዝ ራስል ነበር። ወንድም ራስል መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ያጠና የነበረ ሲሆን አምላክ ሥላሴ እንደሆነና ነፍስ እንደማትሞት የሚገልጹት ትምህርቶች ሐሰት መሆናቸውን በድፍረት አጋልጧል። ክርስቶስ የሚመለሰው በማይታይ ሁኔታ እንደሆነ እንዲሁም “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” በ1914 እንደሚያበቁ ተገንዝቦ ነበር። (ሉቃስ 21:24) ወንድም ራስል ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ገንዘቡን ምንም ሳይቆጥብ እነዚህን እውነቶች ለሌሎች አካፍሏል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋና የጉባኤው ራስ የሆነው ኢየሱስ በዚያ ወሳኝ ወቅት ወንድም ራስልን ተጠቅመውበታል። ወንድም ራስል ከሰዎች ክብር ለማግኘት አልሞከረም። በ1896 እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለእኛም ሆነ ለምናዘጋጃቸው ጽሑፎች ሙገሳና ውዳሴ መቀበል አንፈልግም፤ ‘አባ’ ወይም ‘ረቢ’ ተብለን መጠራት አንፈልግም። ማንም ሰው በእኛ ስም እንዲጠራም አንፈልግም።” አክሎም “ይህ የአምላክ እንጂ የሰው ሥራ አይደለም” ብሏል። w17.02 4:8, 9
ዓርብ፣ ሰኔ 29
ብልህ ሰው የሚሄድበትን መንገድ በጥበብ ያስተውላል።—ምሳሌ 14:8
ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ የተለያዩ ምርጫዎችንና ውሳኔዎችን ማድረግ ይኖርብናል። ሁሉም ውሳኔዎቻችን የሕይወትና የሞት ጉዳይ ናቸው ማለት ላይሆን ይችላል። ይሁንና የምናደርጋቸው ብዙዎቹ ምርጫዎች ወይም ውሳኔዎች በሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያስከትሉ ይችላሉ። ጥሩ ውሳኔዎችን ካደረግን በአንጻራዊ ሁኔታ የተረጋጋና ሰላማዊ ሕይወት መኖር እንችላለን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተሳሳቱ ውሳኔዎች ካደረግን ሕይወታችን በችግርና በብስጭት የተሞላ ሊሆን ይችላል። ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል? በአምላክ ላይ እምነት ሊኖረን ይኸውም ጥበበኞች እንድንሆን እኛን ለመርዳት ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው እንዳለው ልንተማመን ይገባል። በተጨማሪም በይሖዋ ቃልና ነገሮችን በሚያከናውንበት መንገድ ላይ እምነት ማዳበር አለብን፤ በሌላ አባባል በመንፈሱ መሪነት ባስጻፈው ቃሉ ውስጥ በሚገኘው ምክር መተማመን ይኖርብናል። (ያዕ. 1:5-8) ወደ እሱ እየቀረብንና ለቃሉ ያለን ፍቅር እየጨመረ ሲሄድ እሱ በሚሰጠን ምክር ይበልጥ እንተማመናለን። በመሆኑም ውሳኔዎችን ከማድረጋችን በፊት የአምላክን ቃል የመመርመር ልማድ እናዳብራለን። w17.03 2:2, 3
ቅዳሜ፣ ሰኔ 30
ዓይኖቻችን ወደ አንተ ይመለከታሉ።—2 ዜና 20:12
እንደ አባቱ እንደ አሳ ሁሉ ኢዮሳፍጥም አስፈሪ የሆነ የጠላት ሠራዊት በመጣበት ጊዜም እንኳ ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ያደረ መሆኑን አሳይቷል። (2 ዜና 20:2-4) ኢዮሳፍጥ ፈርቶ ስለነበር “[ይሖዋን] ለመፈለግ ቆርጦ ተነሳ።” እሱም ሆነ ሕዝቡ “ይህን ታላቅ ሠራዊት ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል” እንደሌላቸው በመግለጽ ትሕትና የተሞላበት ጸሎት አቅርቧል፤ አክሎም “ምን ማድረግ እንዳለብንም አናውቅም” ሲል ተናግሯል። በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ መናገሩም በይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንደሚታመን ያሳያል። ልክ እንደ ኢዮሳፍጥ ሁሉ እኛም አንዳንድ ጊዜ፣ ችግር ሲያጋጥመን ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ እንጋባ ምናልባትም በፍርሃት እንዋጥ ይሆናል። (2 ቆሮ. 4:8, 9) በዚህ ጊዜ፣ ኢዮሳፍጥ ምን እንዳደረገ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው፤ እሱም ሆነ የይሁዳ ሰዎች ጠላቶቻቸውን የመቋቋም አቅም እንደሌላቸው በሕዝቡ ፊት ባቀረበው ጸሎት ላይ ገልጿል። (2 ዜና 20:5) የቤተሰብ ራሶች ችግር በሚያጋጥማቸው ጊዜ ይሖዋ አስፈላጊውን መመሪያና ሁኔታውን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንዲሰጣቸው በመለመን የኢዮሳፍጥን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። በቤተሰብህ ፊት እንዲህ ዓይነት ልመና ማቅረብ ሊያሳፍርህ አይገባም። የቤተሰብህ አባላት እንዲህ ያለ ጸሎት ስታቀርብ መስማታቸው በይሖዋ እንደምትታመን እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል። አምላክ ኢዮሳፍጥን እንደረዳው ሁሉ አንተንም ይረዳሃል። w17.03 3:12, 13