ሐምሌ
እሁድ፣ ሐምሌ 1
የገባኸውን ቃል በእኔ ላይ ፈጽምብኝ።—መሳ. 11:36
የዮፍታሔ ልጅ ንጹሑን አምልኮ ለመደገፍ ስትል፣ ባል የማግባትና ልጅ የመወለድ ተፈጥሯዊ ፍላጎቷን መሥዋዕት አድርጋለች። እሷ ያሳየችውን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች፣ ይሖዋን በተሟላ መንገድ ለማገልገል ሲሉ ትዳር የመመሥረት አሊያም ልጆች የመውለድ አጋጣሚያቸውን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በፈቃደኝነት መሥዋዕት አድርገዋል። በጉልምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ክርስቲያኖችም ቢሆኑ በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ወይም በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ለመካፈል አሊያም የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ለማገልገል ሲሉ ከልጆቻቸውና ከልጅ ልጆቻቸው ጋር ሊያሳልፉ የሚችሉትን ጊዜ መሥዋዕት አድርገዋል። ሌሎች ደግሞ በአገልግሎት ዘመቻዎች ላይ ለመካፈል ሲሉ የግል ጉዳዮቻቸውን ለመተው ፈቃደኛ ሆነዋል። እንዲህ ያለው በሙሉ ልብ የሚቀርብ አገልግሎት ይሖዋን በጣም ያስደስተዋል፤ ይሖዋም ሥራቸውንና ለእሱ ያሳዩትን ፍቅር ፈጽሞ አይረሳም። (ዕብ. 6:10-12) አንተስ ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ መንገድ ለማገልገል ስትል ተጨማሪ መሥዋዕት መክፈል ትችል ይሆን? w16.04 1:16, 17
ሰኞ፣ ሐምሌ 2
ሁሉም አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ አንድ እረኛም ይኖራቸዋል።—ዮሐ. 10:16
ኢየሱስ ራሱን ከእረኛ፣ ተከታዮቹን ደግሞ ከበግ መንጋ ጋር አመሳስሏል። አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ሁለት በጎች አንድ ኮረብታ ላይ፣ ሌሎች ሁለት በጎች ሸለቆ ውስጥ፣ አንድ ሌላ በግ ደግሞ ብቻውን ነጠል ብሎ ሲግጥ ብታይ እነዚህ አምስት በጎች አንድ መንጋ እንደሆኑ ታስባለህ? በተለምዶ አንድ መንጋ የሚባሉት፣ በእረኛቸው ሥር አንድ ላይ ያሉ በጎች ናቸው። በተመሳሳይ እኛም ሆን ብለን ራሳችንን ከመንጋው የምናገልል ከሆነ እረኛችንን መከተል አንችልም። ‘በአንድ እረኛ’ ሥር ያለው “አንድ መንጋ” አባላት መሆን ከፈለግን ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር መሰብሰብ ይኖርብናል። በስብሰባ ላይ ስንገኝ ለወንድማማች ማኅበራችን አንድነት አስተዋጽኦ እናደርጋለን። (መዝ. 133:1) አንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻችንን፣ ወላጆቻቸው ወይም ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው አግልለዋቸዋል። ያም ሆኖ ኢየሱስ፣ የሚወዳቸውና የሚንከባከባቸው መንፈሳዊ ቤተሰብ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል። (ማር. 10:29, 30) አዘውትረን በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ለእነዚህ ውድ ክርስቲያኖች እንደ አባት፣ እናት፣ ወንድም ወይም እህት መሆን እንችላለን! ታዲያ ይህን ማወቃችን በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የምንችለውን ያህል ጥረት እንድናደርግ አያነሳሳንም? w16.04 3:9, 10
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 3
በሰማያት ያለው አባታችሁ በደላችሁን ይቅር እንዲላችሁ እናንተም ለመጸለይ በምትቆሙበት ጊዜ በማንም ሰው ላይ ያላችሁን ቅሬታ ሁሉ ይቅር በሉ።—ማር. 11:25
ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር ፈቃደኞች ካልሆንን መጸለያችን፣ መሰብሰባችን፣ ማገልገላችንም ሆነ በሌሎች የአምልኮ እንቅስቃሴዎች መካፈላችን ከንቱ ነው። ሌሎች የፈጸሙብንን በደል ይቅር ለማለት ፈቃደኞች ካልሆንን የአምላክ ወዳጆች መሆን አንችልም። (ሉቃስ 11:4፤ ኤፌ. 4:32) እያንዳንዱ ክርስቲያን ሌሎችን ይቅር ስለ ማለትም ሆነ ከሌሎች ጋር ስላለው ሰላማዊ ግንኙነት በቁም ነገር ሊያስብበት ይገባል፤ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በሐቀኝነት ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል፦ የእምነት ባልንጀሮቼን በነፃ ይቅር እላለሁ? ከእነሱ ጋር መሆን ያስደስተኛል? ይሖዋ አገልጋዮቹ ሌሎችን ይቅር እንዲሉ ይጠብቅባቸዋል። በመሆኑም ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብህ ሕሊናህ የሚነግርህ ከሆነ በዚህ ረገድ እንዲረዳህ ይሖዋን በጸሎት ጠይቀው። የሰማዩ አባታችን በትሕትና የቀረቡ እንዲህ ያሉ ጸሎቶችን ሰምቶ ምላሽ ይሰጣል።—1 ዮሐ. 5:14, 15፤ w16.05 1:6, 7
ረቡዕ፣ ሐምሌ 4
ይህ የመንግሥቱ ምሥራች . . . ይሰበካል።—ማቴ. 24:14
አስቀድሞ የተነገረው የስብከት ሥራ የሚቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው? ኢየሱስ ይህ ዓለም አቀፋዊ የስብከት ሥራ በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥም እንደሚከናወንና ‘ከዚያም መጨረሻው እንደሚመጣ’ ተናግሯል። ታሪካዊ በሆኑት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ምሥራቹን እየሰበከ ያለ ሌላ ሃይማኖታዊ ቡድን አለ? በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው አንዳንድ ሰዎች “መንፈስ ቅዱስ ያለን እኛ ነን፤ ሥራውን የምታከናውኑት ግን እናንተ ናችሁ” ይሉናል። ይሁን እንጂ በሥራው በጽናት መቀጠላችን የአምላክ መንፈስ እንዳለን የሚያሳይ ማስረጃ አይደለም? (ሥራ 1:8፤ 1 ጴጥ. 4:14) አንዳንድ ሃይማኖታዊ ቡድኖች የይሖዋ ምሥክሮች አዘውትረው የሚያከናውኑትን ሥራ ለመሥራት የሞከሩባቸው ጊዜያት አሉ፤ ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ ጥረታቸው ውጤታማ አልሆነም። ሌሎች ደግሞ በሚስዮናዊነት ሥራ ለተወሰነ ጊዜ ቢሳተፉም ብዙም ሳይቆይ ወደ ወትሮው ኑሯቸው ይመለሳሉ። ከቤት ወደ ቤት ለመሄድ የሚሞክሩም አሉ፤ ሆኖም የሚሰብኩት ስለ ምንድን ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ እነዚህ ሰዎች ክርስቶስ የጀመረውን ሥራ እያከናወኑ እንዳልሆኑ በግልጽ ያሳያል። w16.05 2:13, 16
ሐሙስ፣ ሐምሌ 5
ወንድሞች፣ መደሰታችሁን፣ መስተካከላችሁን፣ ማጽናኛ መቀበላችሁን፣ በሐሳብ መስማማታችሁንና በሰላም መኖራችሁን ቀጥሉ።—2 ቆሮ. 13:11
‘ለመስተካከል’ እና “አዲሱን ስብዕና” ለመልበስ ሁልጊዜ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ጳውሎስ ለእምነት አጋሮቹ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥቷል፦ “ከቀድሞ አኗኗራችሁ ጋር የሚስማማውንና አታላይ በሆነው ምኞቱ እየተበላሸ የሚሄደውን አሮጌውን ስብዕናችሁን አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል። ደግሞም አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ ይሂድ፤ እንዲሁም እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና መልበስ ይኖርባችኋል።” (ኤፌ. 4:22-24) “እየታደሰ ይሂድ” የሚለው አገላለጽ አዲሱን ስብዕና መልበስ ቀጣይነት ያለው ሂደት መሆኑን ይጠቁማል። ይህን ማወቅ የሚያበረታታ ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋን በማገልገል ያሳለፍነው ጊዜ ምንም ያህል ቢሆን፣ አዲሱን ስብዕና ለመልበስ የሚረዱንን ክርስቲያናዊ ባሕርያት ምንጊዜም እያዳበርንና እያሻሻልን መሄድ እንደምንችል ማረጋገጫ ይሰጠናል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ምንጊዜም ለውጥ ማምጣት ይችላል። w16.05 4:8, 9
ዓርብ፣ ሐምሌ 6
[ይሖዋ] የሚወዳቸውን ይወቅሳል።—ምሳሌ 3:12
በአሁኑ ጊዜ የምንኖረው ይሖዋ እኛን ለመቅረጽ ሲል ባዘጋጀው መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ነው። (ኢሳ. 64:8) በዙሪያችን ያለው ዓለም በክፋት የተሞላ ቢሆንም ያለ ስጋት ተረጋግተን እንኖራለን። ይሖዋን ማወቅና የእሱን አባታዊ ፍቅር ማጣጣም ችለናል። (ያዕ. 4:8) በአዲሱ ዓለም ውስጥ ስንኖር ደግሞ መንፈሳዊው ገነት ከሚያስገኛቸው በረከቶች የተሟላ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ በዚያ ወቅት በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች። ዓለም አቀፍ ተሃድሶ በሚኖርበት በዚያ ጊዜ፣ ይሖዋ የምድርን ነዋሪዎች መቅረጹን የሚቀጥል ሲሆን ከእሱ የሚያገኙት ትምህርት ከምንገምተው በላይ ይሆናል። (ኢሳ. 11:9) በተጨማሪም እሱ የሚሰጠንን ትምህርት መቀበልና ፈቃዱን ሙሉ በሙሉ መፈጸም እንድንችል ይሖዋ አእምሯችንንና አካላችንን ፍጹም ያደርግልናል። እንግዲያው ለይሖዋ መገዛታችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ ይህን ስናደርግ ይሖዋ የሚቀርጸን ስለሚወደን መሆኑን እንደተገነዘብን እናሳያለን። w16.06 1:8, 9
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 7
እስራኤል ሆይ ስማ፣ አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ ነው።—ዘዳ. 6:4
ሙሴ በዚህ ጥቅስ ላይ ያሉትን ቃላት የተናገረው በ1473 ዓ.ዓ. በሞዓብ ሜዳ ላይ ተሰብስቦ ለነበረው የእስራኤል ብሔር የስንብት ንግግር ባቀረበበት ወቅት ነው። ብሔሩ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚገባበት ጊዜ ተቃርቧል። (ዘዳ. 6:1) ላለፉት 40 ዓመታት እስራኤልን ሲመራ የቆየው ሙሴ፣ ሕዝቡ ከፊቱ የሚጠብቀውን ተፈታታኝ ሁኔታ በድፍረት እንዲጋፈጥ እያበረታታ ነው። እስራኤላውያን በይሖዋ መታመንና አምላካቸው እንደመሆኑ መጠን ለእሱ ታማኝ መሆን ያስፈልጋቸዋል። የሙሴ የመሰናበቻ ንግግር በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮ ሊሆን እንደሚችል ጥያቄ የለውም። ሙሴ፣ ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን አሥርቱን ትእዛዛትና ሌሎች ሕግጋት ከጠቀሰ በኋላ በዘዳግም 6:4, 5 ላይ የሚገኘውን ማሳሰቢያ ተናገረ። በዚያ ወቅት የተሰበሰቡት እስራኤላውያን አምላካቸው ይሖዋ “አንድ ይሖዋ” መሆኑን ያውቁ እንደነበር ጥርጥር የለውም። ታማኝ የሆኑ እስራኤላውያን የሚያውቁትም ሆነ የሚያመልኩት አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ እሱም የአባቶቻቸው ማለትም የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ የሆነው ይሖዋ ነው። w16.06 3:2, 3
እሁድ፣ ሐምሌ 8
ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም።—ማቴ. 24:36
ኢየሱስ ከላይ ያለውን የተናገረው ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ነው። ይሁንና ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ በሰይጣን ዓለም ላይ ጦርነት እንዲያውጅ ሥልጣን ተሰጥቶታል። (ራእይ 19:11-16) በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ኢየሱስ፣ አርማጌዶን የሚጀምርበትን ጊዜ ያውቃል ብለን ማሰባችን ምክንያታዊ ነው። እኛ ግን ይህ ቀን መቼ እንደሚመጣ አናውቅም። እንግዲያው ታላቁ መከራ የሚመጣበትን ጊዜ በንቃት መጠባበቃችን የግድ ነው። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ይህ ክንውን መቼ እንደሚፈጸም ምንጊዜም ቢሆን ያውቃል። መጨረሻው የሚመጣበትን ትክክለኛ ጊዜ ወስኗል። ታላቁ መከራ የሚጀምርበት ጊዜ ከቀን ወደ ቀን እየቀረበ ሲሆን ይህ ጊዜ ፈጽሞ “አይዘገይም!” (ዕን. 2:1-3) ይህን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ይሖዋ ያስነገራቸው ትንቢቶች ምንጊዜም ቢሆን ልክ በተባለው ጊዜ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል! እኛም ከታላቁ መከራ በሕይወት እንደምንተርፍ ይሖዋ የገባልን ቃል እንደሚፈጸም እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሁንና ይህ ሥርዓት ሲጠፋ በሕይወት መትረፍ ከፈለግን ምንጊዜም ነቅተን መጠበቅ አለብን። w16.07 2:4-6
ሰኞ፣ ሐምሌ 9
ጴጥሮስ “ሌሎቹ ሁሉ ቢሰናከሉ እንኳ እኔ አልሰናከልም” አለው።—ማር. 14:29
ሐዋርያቱ ወሳኝ በሆነ ጊዜ ላይ ኢየሱስን ጥለውት ሸሽተዋል። ቀደም ሲል ጴጥሮስ፣ ሌሎቹ ኢየሱስን ቢተዉት እንኳ እሱ እንደማይተወው ተናግሮ ነበር። (ማር. 14:27-31, 50) የሚያሳዝነው ግን ኢየሱስ ሲያዝ፣ ጴጥሮስን ጨምሮ ሐዋርያቱ ሁሉ ጥለውት ሸሹ። ጴጥሮስ ኢየሱስን ጨርሶ እንደማያውቀው በመግለጽ በተደጋጋሚ ጊዜ ካደው። (ማር. 14:53, 54, 66-72) ያም ሆኖ ጴጥሮስ በመጸጸቱ ይሖዋ ከዚያም በኋላ ተጠቅሞበታል። በዚያን ጊዜ የምትኖር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ብትሆን ኖሮ የጴጥሮስ ድርጊት ይሖዋን በታማኝነት እንዳታገለግል እንቅፋት ይሆንብህ ነበር? በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ስህተት የሠሩ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ ጊዜ እንደሚሰጣቸው እንዲሁም የተፈጸመውን ስህተት ውሎ አድሮ እንደሚያስተካክለውና ትክክለኛውን እርምጃ እንደሚወስድ ትተማመናለህ? በሌላ በኩል ደግሞ ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ አንዳንድ ሰዎች ንስሐ ገብተው የይሖዋን ምሕረት ለማግኘት ጥረት ላያደርጉ ይችላሉ። ታዲያ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር ይሖዋ በተገቢው ጊዜ እነዚህን ኃጢአተኞች እንደሚፈርድባቸው ምናልባትም ከጉባኤው እንደሚያስወግዳቸው እምነት አለህ? w16.06 4:8, 9
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 10
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንዲሁም . . . አባታችን የሆነው አምላክ ልባችሁን ያጽናኑ፤ እንዲሁም . . . ያበርቷችሁ።—2 ተሰ. 2:16, 17 ግርጌ
ይሖዋ በጸጋው ከሰጠን ግሩም በረከቶች አንዱ ልባችን ሲጨነቅ ማጽናኛ ማግኘት መቻላችን ነው። (መዝ. 51:17) ጳውሎስ ስደት እየደረሰባቸው ለነበሩት በተሰሎንቄ የሚገኙ ክርስቲያኖች በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ጽፏል። ይሖዋ በልግስና በሰጠን ጸጋ አማካኝነት በፍቅር እንደሚንከባከበን ማወቁ እንዴት ያበረታታል! ኃጢአተኞች በመሆናችን፣ ይሖዋ ባይረዳን ኖሮ ተስፋ አይኖረንም ነበር። (መዝ. 49:7, 8) ይሁንና ይሖዋ አስደናቂ ተስፋ ሰጥቶናል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “የአባቴ ፈቃድ ወልድን የሚያውቅና በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 6:40) በእርግጥም የዘላለም ሕይወት ተስፋ፣ የአምላክ ጸጋ የተገለጸበት ግሩም ስጦታ ነው። ለዚህ ስጦታ አድናቆት የነበረው ጳውሎስ “የአምላክ ጸጋ ተገልጧልና፤ ጸጋው ለሁሉም ዓይነት ሰዎች መዳን ያስገኛል” ብሏል።—ቲቶ 2:11፤ w16.07 3:14, 15
ረቡዕ፣ ሐምሌ 11
በወጣትነት ሚስታችሁም ላይ ክህደት አትፈጽሙ።—ሚል. 2:15
በዛሬው ጊዜ ባሉት የይሖዋ ሕዝቦች ዘንድ በትዳር ጓደኛ ላይ ክህደት መፈጸም በቸልታ የሚታለፍ ነገር አይደለም። ለምሳሌ፣ ራሱን ለአምላክ ወስኖ የተጠመቀ አንድ ባለትዳር ከሌላ ሰው የትዳር ጓደኛ ጋር ኮበለለ እንበል። ግለሰቡ የቀድሞ ትዳሩን በፍቺ ካፈረሰ በኋላ ይህችኛዋን ሴት ቢያገባ ንስሐ እስካልገባ ድረስ ከክርስቲያን ጉባኤ ይወገዳል፤ እንዲህ ዓይነት እርምጃ የሚወሰደው የጉባኤውን መንፈሳዊ ንጽሕና ለመጠበቅ ሲባል ነው። (1 ቆሮ. 5:11-13) እንዲህ ያለው ሰው ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ለመመለስ ከፈለገ “ለንስሐ የሚገባ ፍሬ” ማፍራት ይጠበቅበታል። (ሉቃስ 3:8፤ 2 ቆሮ. 2:5-10) የተወገደው ግለሰብ ወደ ጉባኤው እስኪመለስ ድረስ ምን ያህል ጊዜ ማለፍ እንዳለበት የተደነገገ ሕግ ባይኖርም እንዲህ ያለው የክህደት ድርጊት በቀላሉ የሚታይ ነገር አይደለም። ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ ከልቡ ንስሐ መግባቱን ለማየት ረዘም ያለ ጊዜ ምናልባትም አንድ ዓመት ወይም ከዚያ የበለጠ ጊዜ ማለፍ ይኖርበት ይሆናል። ግለሰቡ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ቢመለስም እንኳ ከልቡ ንስሐ ስለመግባቱ “በአምላክ የፍርድ ወንበር ፊት” ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያለው ሁኔታ በአምላክ ሕዝቦች መካከል ብዙ ጊዜ ያጋጥማል ማለት አይደለም።—ሮም 14:10-12፤ w16.08 1:12, 13
ሐሙስ፣ ሐምሌ 12
የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣር ሰው መልካም ሥራን ይመኛል።—1 ጢሞ. 3:1
እዚህ ላይ ‘መጣጣር’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ፣ አንድን ነገር ምናልባትም በቀላሉ የማይደረስበትን ነገር ለመያዝ መንጠራራት የሚል መልእክት ያስተላልፋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ቃል የተጠቀመው መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ጥረት እንደሚጠይቅ ለማጉላት ነው። በጉባኤው ውስጥ ወደፊት ሊያከናውን ስለሚችለው ነገር እያሰበ ያለን አንድ ወንድም ወደ አእምሯችን እናምጣ። በአሁኑ ጊዜ የጉባኤ አገልጋይ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ክርስቲያናዊ ባሕርያት ማዳበር እንዳለበት ይገነዘባል። መጀመሪያ፣ የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ለማሟላት ይጥራል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ለማሟላት ግብ ያወጣል። ይህ ወንድም፣ የጉባኤ አገልጋይም ሆነ ሽማግሌ ለመሆን ጥረት በሚያደርግበት ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነት ለመሸከም የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ለማሟላት ተግቶ ይሠራል። በተመሳሳይም አቅኚ፣ ቤቴላዊ እንዲሁም የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው ማገልገል የሚፈልጉ ወንድሞችና እህቶች፣ ግባቸው ላይ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው። w16.08 3:3, 4
ዓርብ፣ ሐምሌ 13
እነሱ በታላቅ ኃይልህና በብርቱ እጅህ የዋጀሃቸው አገልጋዮችህና ሕዝቦችህ ናቸው።—ነህ. 1:10
ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም በሄደበት ጊዜ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል አስበው። ከተማዋ ለጥቃት የተጋለጠች ነበረች፤ በዚያ የሚኖሩት አይሁዳውያንም በጣም ተስፋ ቆርጠዋል። የባዕድ አገር ዜጎች የሆኑት ተቃዋሚዎቻቸው በሚሰነዝሩባቸው ዛቻ የተነሳ እጃቸው በመዛሉ የኢየሩሳሌምን ቅጥር መልሰው መገንባታቸውን አቁመው ነበር። ታዲያ ነህምያስ በዚህ ሁኔታ ተስፋ ቆርጦ እጆቹ እንዲዝሉ ፈቅዶ ይሆን? በጭራሽ! ልክ እንደ ሙሴ፣ አሳና ሌሎች ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ሁሉ ነህምያም ወደ ይሖዋ የመጸለይ ልማድ ነበረው፤ ይህም በእሱ እንደሚታመን የሚያሳይ ነው። (ዘፀ. 17:8-13፤ 2 ዜና 14:8-13) በዚህ ወቅትም ያደረገው ይህንኑ ነው። አይሁዳውያኑ ከአቅማቸው በላይ የሆነ መሰናክል እንደተጋረጠባቸው ተሰምቷቸው ነበር፤ ይሖዋ ግን ነህምያ ላቀረበው ልባዊ ጸሎት ምላሽ በመስጠት ‘በታላቅ ኃይሉ’ እና ‘በብርቱ እጁ’ ተጠቅሞ የዛሉትን የአይሁዳውያኑን እጆች አበረታ። (ነህ. 2:17-20፤ 6:9) በዛሬው ጊዜስ ይሖዋ ‘በታላቅ ኃይሉ’ እና ‘በብርቱ እጁ’ ተጠቅሞ አገልጋዮቹን እንደሚያበረታ እምነት አለህ? w16.09 1:9
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 14
ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ።—1 ቆሮ. 10:31
አንድ የደች ጋዜጣ፣ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ባደረጉት ስብሰባ ላይ የነበረውን ሁኔታ አስመልክቶ ሲዘግብ እንዲህ ብሏል፦ “አየሩ ሞቃት በመሆኑ የብዙዎቹ አለባበስ በመዝናኛ ቦታ እንደሚታየው ዓይነት ነው።” ጋዜጣው አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው።” በእርግጥም የይሖዋ ምሥክሮች ‘ልከኝነትና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ’ የሚንጸባረቅበት እንዲሁም ‘የሚያስከብርና ለአምላክ ያደርን ነን’ ለሚሉ ሰዎች የሚገባ አለባበስ ስላላቸው ብዙዎች ያደንቋቸዋል። (1 ጢሞ. 2:9, 10 ግርጌ) ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን የጻፈው ስለ ሴቶች ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ለክርስቲያን ወንዶችም ይሠራል። የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ተገቢ አለባበስ ያለን መሆኑ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ሲሆን የምናመልከው አምላክም ቢሆን ይህን ጉዳይ ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። (ዘፍ. 3:21) ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ አለባበስና አጋጌጥ የያዙት ሐሳብ፣ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ እውነተኛ አገልጋዮቹ በአለባበስ ረገድ የላቀ መሥፈርት እንዲከተሉ እንደሚፈልግ በግልጽ ያሳያል። በመሆኑም ከአለባበስና ከአጋጌጥ ጋር በተያያዘ የምናደርገው ምርጫ ሉዓላዊውን ጌታ ይሖዋን የሚያስደስተውን ነገር ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን ይኖርበታል። w16.09 3:1, 2
እሁድ፣ ሐምሌ 15
ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው ተናገሩ።—2 ጴጥ. 1:21
አንዳንዶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሰፈሩት ትንቢቶች ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ፣ ከአርኪኦሎጂና ከሳይንስ አንጻር ትክክል ስለመሆኑ ለማጥናት ግብ አውጥተዋል። ምርምር ልታደርጉባቸው ከምትችሏቸው ትኩረት የሚስቡ ትንቢቶች አንዱ በዘፍጥረት 3:15 ላይ ይገኛል። ይህ ጥቅስ የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ጭብጥ ምን እንደሆነ ይኸውም በአምላክ መንግሥት አማካኝነት የይሖዋ አገዛዝ ትክክለኛነት እንደሚረጋገጥና ስሙ እንደሚቀደስ ይጠቁመናል። በምሳሌያዊ አነጋገር የተቀመጠው ይህ ጥቅስ፣ ከኤደን ጀምሮ በሰው ልጆች ላይ የደረሱትን መከራዎች በሙሉ ይሖዋ እንዴት እንደሚያስወግድ ይገልጻል። ታዲያ በዘፍጥረት 3:15 ላይ ምርምር ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምትችሉበት አንዱ መንገድ ክንውኖቹን በዘመን ቅደም ተከተል ማስፈር ሊሆን ይችላል። አምላክ፣ በዚህ ጥቅስ ላይ ከተገለጸው ዝግጅትና ከተጠቀሱት ግለሰቦች ጋር የተያያዙ እውነታዎችን ቀስ በቀስ እንዴት እንደገለጠ የሚጠቁሙ እንዲሁም ትንቢቱ እንዴት እንደሚፈጸም የሚያሳዩ ቁልፍ ጥቅሶችን በቅደም ተከተል ማስፈር ትችላላችሁ። ከዚያም ጥቅሶቹን አንድ ላይ ስትመለከቷቸው እርስ በርሱ የሚስማማ መልእክት እንደሚያስተላልፉ ታስተውላላችሁ፤ ይህን ስታዩ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያትና ጸሐፊዎች ሐሳቡን ያሰፈሩት “በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው” እንደሆነ መገንዘባችሁ አይቀርም። w16.09 4:8
ሰኞ፣ ሐምሌ 16
አንተን ከሌላው የተለየህ እንድትሆን ያደረገህ ማን ነው?—1 ቆሮ. 4:7
ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ አይሁዳዊ ላልሆኑ ሰዎች መሠረተ ቢስ ጥላቻ ነበረው፤ ውሎ አድሮ ግን እንዲህ ያለውን አሉታዊ አመለካከት ማስወገድ ችሏል። (ሥራ 10:28, 34, 35፤ ገላ. 2:11-14) እኛም በተመሳሳይ ለሌሎች መሠረተ ቢስ ጥላቻ እንዳለን ወይም በዘራችን የመኩራት ዝንባሌ በውስጣችን እያቆጠቆጠ እንደሆነ ካስተዋልን፣ ይህን አመለካከት ከሥሩ ነቅለን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለብን። (1 ጴጥ. 1:22) ሁላችንም ለመዳን የማንበቃ ሰዎች መሆናችንን እንዲሁም ዜግነታችን ምንም ይሁን ምን ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደሆንን ማስታወስ ይኖርብናል። (ሮም 3:9, 10, 21-24) ታዲያ ከሌሎች እንደምንበልጥ እንዲሰማን የሚያደርግ ምን ምክንያት አለን? ይልቁንም ሐዋርያው ጳውሎስ የነበረው ዓይነት አመለካከት ልናዳብር ይገባል፤ ጳውሎስ እንደ እሱ ቅቡዓን የሆኑትን የእምነት ባልንጀሮቹን “ከዚህ በኋላ እንግዶችና ባዕዳን አይደላችሁም፤ ከዚህ ይልቅ . . . የአምላክ ቤተሰብ አባላት ናችሁ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ኤፌ. 2:19) ለሌላ አገር ሰዎች መሠረተ ቢስ ጥላቻ እንዳይኖረን ልባዊ ጥረት ማድረጋችን አዲሱን ስብዕና ለመልበስ ይረዳናል።—ቆላ. 3:10, 11፤ w16.10 1:9
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 17
ሕጉንም በቀንና በሌሊት በለሆሳስ ያነበዋል።—መዝ. 1:2
ይሖዋ፣ እምነታችን ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን እኛን ለመርዳት ሲል ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በደግነት ሰጥቶናል። “ደስተኛ” እና ‘ስኬታማ’ ለመሆን ከፈለግን የአምላክን ቃል አዘውትረን ከተቻለም በየዕለቱ ማንበብ አለብን። (መዝ. 1:1-3፤ ሥራ 17:11) በተጨማሪም በቅድመ ክርስትና ዘመን እንደኖሩት የይሖዋ አገልጋዮች፣ አምላክ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰል እንዲሁም የእሱን ትእዛዛት መጠበቅ አለብን። ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ይሰጠናል። (ማቴ. 24:45) ይሖዋ ከሚያቀርብልን መንፈሳዊ ማዕድ የምንመገብ ከሆነ የመንግሥቱን ተስፋ ‘በእርግጠኝነት እንደጠበቁት’ በጥንት ዘመን የኖሩ የእምነት ምሳሌዎች እንሆናለን። (ዕብ. 11:1) በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ የአምላክ ምሥክሮች እምነታቸው ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን የረዳቸው ሌላው ነገር ደግሞ ጸሎት ነው። አምላክ ለጸሎታቸው የሚሰጠውን መልስ መመልከታቸው እምነታቸውን አጠናክሮታል።—ነህ. 1:4, 11፤ መዝ. 34:4, 15, 17፤ ዳን. 9:19-21፤ w16.10 3:7, 8
ረቡዕ፣ ሐምሌ 18
ተራራን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚያስችል እምነት ቢኖረኝ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።—1 ቆሮ. 13:2
ኢየሱስ “ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው?” ለሚለው ጥያቄ የሰጠው መልስ ለአምላክ ያለን ፍቅር በጣም አስፈላጊ ባሕርይ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ያሳያል። (ማቴ. 22:35-40) እምነትም ሆነ ፍቅር አስፈላጊ ባሕርያት በመሆናቸው ክርስቲያን የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እነዚህን ሁለት ባሕርያት በተደጋጋሚ ጊዜያት፣ አብዛኛውን ጊዜም በአንድ ዓረፍተ ነገር ወይም ሐረግ ውስጥ ጎላ አድርገው ገልጸዋቸዋል። ጳውሎስ “የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር እንልበስ” በማለት ወንድሞቹን አሳስቧቸዋል። (1 ተሰ. 5:8) ዮሐንስም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በእርግጥም [የአምላክ ትእዛዝ] ይህ ነው፦ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንድናምንና እሱ ባዘዘን መሠረት እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ነው።” (1 ዮሐ. 3:23) እምነት አስፈላጊ ባሕርይ ቢሆንም አምላክ ቃል የገባቸው ነገሮች ከተፈጸሙና ክርስቲያኖች ተስፋ የሚያደርጓቸው ነገሮች እውን ከሆኑ በኋላ በእነዚህ ተስፋዎች ላይ እምነት ማሳደር አያስፈልገንም። ለአምላክና ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር ግን ምንጊዜም እያደገ መሄድ ይኖርበታል። ጳውሎስ “እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ እነዚህ ሦስቱ ይቀጥላሉ፤ ከእነዚህ መካከል የሚበልጠው ግን ፍቅር ነው” ብሎ የጻፈው ለዚህ ነው።—1 ቆሮ. 13:13፤ w16.10 4:15-17
ሐሙስ፣ ሐምሌ 19
ጉባኤዎቹም በእምነት እየጠነከሩ . . . ሄዱ።—ሥራ 16:5
የበላይ አካሉን ወክለው የሚሄዱ ወንድሞች “በኢየሩሳሌም ያሉት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች” ለጉባኤዎች ያሳውቁ ነበር። (ሥራ 16:4) ጉባኤዎች እነዚህን ውሳኔዎች ሲታዘዙ ደግሞ “በእምነት እየጠነከሩና ከዕለት ወደ ዕለት በቁጥር እየጨመሩ” ይሄዱ ነበር። እኛስ ከአምላክ ድርጅት መመሪያ ሲደርሰን ምን ልናደርግ ይገባል? የአምላክ መጽሐፍ ሁላችንም መታዘዝና መገዛት እንዳለብን ይናገራል። (ዘዳ. 30:16፤ ዕብ. 13:7, 17) ነቃፊነት ወይም የዓመፀኝነት መንፈስ በአምላክ ድርጅት ውስጥ ቦታ የላቸውም፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ዝንባሌ በጉባኤያችን ውስጥ ያለውን ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት ያናጋል። እርግጥ ማንኛውም ታማኝ ክርስቲያን፣ ዲዮጥራጢስ የነበረው ዓይነት መንፈስ ማሳየት አይፈልግም፤ ዲዮጥራጢስ አክብሮትና ታማኝነት የጎደለው ሰው ነበር። (3 ዮሐ. 9, 10) እንግዲያው እንደሚከተለው ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘በዙሪያዬ ያሉትን ሰዎች መንፈሳዊነት ለማጠናከር አስተዋጽኦ አደርጋለሁ? ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የሚሰጡትን መመሪያ ለመቀበልና ለመደገፍ ፈጣን ነኝ?’ w16.11 2:10, 11
ዓርብ፣ ሐምሌ 20
በግዞት ተወስዳችሁ እንድትኖሩባት ላደረግኳት ከተማም ሰላምን ፈልጉ።—ኤር. 29:7
የአምላክን ፈቃድ የተቀበሉት አይሁዳውያን በባቢሎን የነበራቸው ሕይወት መጥፎ አልነበረም ማለት ይቻላል። ባቢሎናውያኑ፣ በተወሰነ መጠንም ቢሆን የራሳቸውን ጉዳዮች እንዲያስተዳድሩ ፈቅደውላቸው ነበር። ምርኮኞቹ በአገሪቱ ውስጥ የመዘዋወር ነፃነትም ጭምር ነበራቸው። ባቢሎን የጥንቱ ዓለም የንግድ መዲና ነበረች፤ በርካታ አይሁዳውያን የንግድ ሙያ እንደተማሩ፣ ሌሎች ደግሞ የተዋጣላቸው የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች እንደሆኑ በቁፋሮ የተገኙ ሰነዶች ያሳያሉ። እንዲያውም አንዳንድ አይሁዳውያን ባለጸጎች ሆነው ነበር። እስራኤላውያን በባቢሎን በግዞት ያሳለፉት ሕይወት፣ ከበርካታ ዘመናት በፊት በግብፅ ካሳለፉት የባርነት ሕይወት ጋር ጨርሶ አይወዳደርም። (ዘፀ. 2:23-25) ይሁንና እስራኤላውያን እንደቀድሟቸው አምላክን ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ባለው መንገድ ማምለክ የሚችሉበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? በወቅቱ ይህ የሚሆን አይመስልም ነበር። ባቢሎናውያን በምርኮ የወሰዷቸውን ሰዎች ፈጽሞ አይለቁም ነበር። ያም ሆኖ ይሖዋ፣ ሕዝቡ ነፃ እንደሚወጡ ቃል ገብቶ ነበር፤ ያለውም ተፈጽሟል። አምላክ ቃል የገባው ነገር መቼም ቢሆን መፈጸሙ አይቀርም።—ኢሳ. 55:11፤ w16.11 4:3, 5
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 21
ለኃጢአት ሞተናል።—ሮም 6:2
እነዚህ ክርስቲያኖች በወቅቱ በምድር ላይ በሕይወት እየኖሩ ነበር፤ ታዲያ ‘ለኃጢአት ሞተዋል’ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? ጳውሎስና በእሱ ዘመን የኖሩ ሌሎች ሰዎች ከቤዛው ተጠቃሚ እንዲሆኑ አምላክ ዝግጅት አድርጓል። በመሆኑም ይሖዋ ኃጢአታቸውን ይቅር ብሏቸዋል፤ በመንፈስ ቅዱስ ቀብቷቸዋል እንዲሁም መንፈሳዊ ልጆቹ እንዲሆኑ ጠርቷቸዋል። በዚህም ምክንያት በሰማይ የመኖር ተስፋ አግኝተዋል። በታማኝነት ከጸኑ ደግሞ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የመኖርና ከእሱ ጋር የመግዛት መብት ያገኛሉ። እነዚህ ሰዎች በምድር ላይ በሕይወት ያሉ ቢሆንም እንኳ ጳውሎስ ‘ለኃጢአት እንደሞቱ’ ገልጿል። ጳውሎስ፣ ሰው ሆኖ የሞተውንና ከሞት ከተነሳ በኋላ የማይሞት ሕይወት ተላብሶ በሰማይ የሚኖረውን የኢየሱስን ምሳሌ ጠቅሷል። ሞት በኢየሱስ ላይ ጌታ መሆኑ አብቅቷል። ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ እነዚህ ክርስቲያኖች “ለኃጢአት [እንደሞቱ] ሆኖም በክርስቶስ ኢየሱስ ለአምላክ [እንደሚኖሩ]” አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። (ሮም 6:9, 11) ቀድሞ የነበራቸው ሕይወት ተለውጧል። ከዚህ በኋላ የኃጢአት ምኞታቸው እንዲመራቸው ወይም እንዲቆጣጠራቸው አይፈቅዱም። ለቀድሞ ሕይወታቸው ሞተዋል። w16.12 1:9, 10
እሁድ፣ ሐምሌ 22
በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር . . . ሕይወትና ሰላም ያስገኛል።—ሮም 8:6
ይህ ሲባል አንድ ሰው የሚያስበውም ሆነ የሚናገረው ነገር ሁሉ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ለአምላክ ስላለው ፍቅር አሊያም ስለ ወደፊት ተስፋው ብቻ መሆን አለበት ማለት አይደለም። ጳውሎስና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ አምላክን ያስደሰቱ ሌሎች ክርስቲያኖች ሕይወታቸው በብዙ መንገዶች እንደሌላው ሰው እንደነበረ እናስታውስ። እንደ ማንኛውም ሰው ይበሉና ይጠጡ ነበር። ብዙዎቹ ትዳር መሥርተው ልጆች ወልደዋል፤ እንዲሁም የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ይሠሩ ነበር። (ማር. 6:3፤ 1 ተሰ. 2:9) ይሁንና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች፣ እንደነዚህ ያሉት የተለመዱ እንቅስቃሴዎች በሕይወታቸው ውስጥ ዋነኛውን ቦታ እንዲይዙ አልፈቀዱም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጳውሎስ ድንኳን በመሥራት ይተዳደር እንደነበር ይገልጻል፤ ሆኖም ሕይወቱ በዋነኝነት ያተኮረው በክርስቲያናዊው የስብከትና የማስተማር ሥራ ላይ እንደነበር ዘገባው ይጠቁማል። (ሥራ 18:2-4፤ 20:20, 21, 34, 35) በሮም የነበሩ ወንድሞቹንና እህቶቹንም በዚህ ሥራ እንዲካፈሉ አበረታቷቸዋል። በእርግጥም በጳውሎስ ሕይወት ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዙት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ነበሩ። የሮም ክርስቲያኖች የእሱን ምሳሌ ሊከተሉ ይገባ ነበር፤ እኛም ብንሆን ይህን ማድረግ አለብን።—ሮም 15:15, 16፤ w16.12 2:5, 15, 16
ሰኞ፣ ሐምሌ 23
ለችግረኛ ሞገስ የሚያሳይ ለይሖዋ ያበድራል፤ ላደረገውም ነገር ብድራት ይከፍለዋል።—ምሳሌ 19:17
ይሖዋ፣ እሱን ለማገልገል የምናደርገውን ማንኛውንም ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በራስ ያለመተማመን ስሜት ሊያድርብን እንደሚችል ያውቃል። ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ችግሮች ቢያስጨንቁን አሊያም የጤና ወይም የስሜት መቃወስ ቅዱስ አገልግሎታችንን ቢገድቡብን ይሖዋ ይራራልናል። ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ለእሱ ታማኝ ለመሆን ሲሉ የሚያደርጓቸውን ነገሮች ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን። (ዕብ. 6:10, 11) በተጨማሪም ‘ጸሎት ሰሚ የሆነው’ አምላክ የሚያሳስቡንን ነገሮች ስንነግረው እንደሚሰማን በመተማመን ወደ እሱ መቅረብ እንችላለን። (መዝ. 65:2) “ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ” የሚያስፈልገንን ስሜታዊና መንፈሳዊ ድጋፍ አትረፍርፎ ይሰጠናል፤ ይህን የሚያደርገውም በእምነት ባልንጀሮቻችን አማካኝነት ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮ. 1:3 ግርጌ) ለሌሎች ርኅራኄ ስናሳይ የይሖዋን ልብ እናስደስታለን። (ማቴ. 6:3, 4) በተጨማሪም ይሖዋ ለደግነታችን ወሮታውን እንደሚከፍለን ቃል ገብቷል። w16.12 4:13, 14
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 24
የይሖዋ መንፈስ ባለበት ደግሞ ነፃነት አለ።—2 ቆሮ. 3:17
ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣ በኋላም የመምረጥ ነፃነቱን በሚገባ ተጠቅሞበታል፤ የአምላክ ቀንደኛ ጠላት እሱን ለመፈተን ሲል ያቀረበለትን ግብዣ አልተቀበለም። (ማቴ. 4:10) ኢየሱስ፣ ከመሞቱ በፊት ባለው ምሽት ላይ ያቀረበው ከልብ የመነጨ ጸሎት የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ያለው ቁርጠኝነት እንዳልተቀየረ የሚያረጋግጥ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “አባት ሆይ፣ ፈቃድህ ከሆነ ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ። ይሁንና የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም።” (ሉቃስ 22:42) እኛም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል፣ የመምረጥ ነፃነታችንን ለይሖዋ ክብር ለማምጣትና የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም እንጠቀምበት። ይሁንና እንዲህ ማድረግ ይቻላል? አዎ፣ የክርስቶስን ምሳሌ መከተል እንችላለን፤ ምክንያቱም ልክ እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም የተሠራነው በአምላክ መልክና አምሳል ነው። (ዘፍ. 1:26) ይህ ሲባል ግን እንደ ይሖዋ ገደብ የለሽ ነፃነት አለን ማለት አይደለም። የአምላክ ቃል፣ ነፃነታችን ገደብ እንዳለው እንዲሁም ይሖዋ ይህን ምክንያታዊ ገደብ አክብረን እንድንኖር እንደሚጠብቅብን ይናገራል። ከዚህም በተጨማሪ ሚስቶች ለባሎቻቸው፣ ልጆች ደግሞ ለወላጆቻቸው መገዛት አለባቸው።—ኤፌ. 5:22፤ 6:1፤ w17.01 2:4, 5
ረቡዕ፣ ሐምሌ 25
እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት።—ሮም 12:3
የምንኖረው አስደሳች ክንውኖች እየተፈጸሙ ባሉበት ወቅት ነው። የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል በብዙ አቅጣጫዎች እድገት እያደረገ ነው፤ ይህ ደግሞ አንዳንድ ለውጦች ማድረግን ይጠይቃል። ለውጡ እኛን የሚነካ በሚሆንበት ጊዜ ትሑት በመሆን ከራሳችን ይልቅ በይሖዋ ፈቃድ ላይ ትኩረት እናድርግ። እንዲህ ማድረጋችን አንድነታችንን ያጠናክረዋል። ጳውሎስ በሮም ላሉ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአንድ አካል ላይ ብዙ የአካል ክፍሎች አሉን፤ ደግሞም ሁሉም የአካል ክፍሎች አንድ ዓይነት ተግባር አያከናውኑም፤ ልክ እንደዚሁ እኛም ብዙ ብንሆንም እንኳ ከክርስቶስ ጋር ባለን አንድነት አንድ አካል ነን።” (ሮም 12:4, 5) እንግዲያው ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ የይሖዋን መንግሥት ፈቃድ ለመፈጸም ጠንክረን እንሥራ። እናንት በዕድሜ የገፋችሁ ወንድሞች፣ እየሠራችሁት ያለውን ሥራ መረከብ እንዲችሉ ወጣቶችን አሠልጥኑ። እናንት ወጣቶች፣ ኃላፊነት ለመቀበል ራሳችሁን አቅርቡ፤ ትሑት ሁኑ፤ እንዲሁም በዕድሜ ለገፉ ወንድሞች ምንጊዜም አክብሮት ይኑራችሁ። እናንት ሚስቶች፣ የአቂላን ሚስት የጵርስቅላን ምሳሌ ተከተሉ፤ ጵርስቅላ እሷና ባለቤቷ በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ ባጋጠማቸው ጊዜም ባለቤቷን በታማኝነት ደግፋለች።—ሥራ 18:2፤ w17.01 5:15, 16
ሐሙስ፣ ሐምሌ 26
[እኔ] እዚህ ግባ የምባል አይደለሁም።—መሳ. 6:15
ጌድዮን ያን ያህል ቦታ የሚሰጠው ሰው እንዳልሆነና የተሰጠውን ተልእኮ ለመቀበል ብቃት እንደሌለው ተናግሯል። ይሖዋ የሰጠውን ኃላፊነት ከተቀበለ በኋላ ደግሞ ሥራው ምን ነገሮችን እንደሚያካትት በሚገባ ለመረዳት እንዲሁም የይሖዋን አመራር ለማግኘት ጥረት አድርጓል። (መሳ. 6:36-40) ጌድዮን ደፋርና ቆራጥ የነበረ ቢሆንም ማንኛውንም ነገር የሚያከናውነው በጥንቃቄና በማስተዋል ነበር። (መሳ. 6:11, 27) የተሰጠውን ተልእኮ ለራሱ ክብር ለማግኘት አልተጠቀመበትም። ከዚህ ይልቅ ተልእኮውን እንዳጠናቀቀ በደስታ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመልሷል። (መሳ. 8:22, 23, 29) ልካችንን ማወቅ አለብን ሲባል ተጨማሪ መብቶች ለማግኘት መጣጣርም ሆነ መብቶች ሲሰጡን መቀበል አይኖርብንም ማለት አይደለም። ቅዱሳን መጻሕፍት ሁላችንም እድገት ለማድረግ እንድንጣጣር ያበረታታሉ። (1 ጢሞ. 4:13-15) ታዲያ አንድ ሰው እድገት አደረገ የሚባለው አዲስ ኃላፊነት ሲቀበል ብቻ ነው? እንዲህ ብሎ መደምደም ምክንያታዊ አይደለም። አሁን ያለን የአገልግሎት መብት ምንም ይሁን ምን፣ የይሖዋን በረከት እስካገኘን ድረስ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ እንችላለን። ምንጊዜም ቢሆን ይሖዋ የሰጠንን ችሎታዎች ማሻሻል እንዲሁም መልካም ሥራዎችን በማከናወን ረገድ ተጨማሪ አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። w17.01 3:15, 16
ዓርብ፣ ሐምሌ 27
እኛ በእሱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል።—1 ዮሐ. 4:9
ይሖዋ ቤዛውን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ዋጋ መክፈል አስፈልጎታል። (1 ጴጥ. 1:19) የሰው ልጆችን ሕይወት ከፍ አድርጎ ስለሚመለከት አንድያ ልጁ ለእኛ ሲል እንዲሞት አድርጓል። ኢየሱስ በአዳም ምትክ አባታችን ሆኗል። (1 ቆሮ. 15:45) በዚህ መንገድ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችልበትን አጋጣሚ ያስገኘልን ከመሆኑም ሌላ ከጊዜ በኋላ እንደገና የአምላክ ቤተሰብ አባል መሆን የምንችልበትን መንገድ ከፍቶልናል። ኢየሱስ ሕይወቱን መሥዋዕት ስላደረገ ይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶቹን ሳይጥስ የሰው ልጆችን እንደገና የቤተሰቡ አባል አድርጎ መቀበል ይችላል። ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ፍጹማን ሲሆኑ ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን እስቲ አስበው! በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ ፍጥረታት በሙሉ አንድ ቤተሰብ ይሆናሉ። በዚያ ጊዜ ሁላችንም የአምላክ ልጆች እንሆናለን። (ሮም 8:21) ለቤዛው ያለን አድናቆት ሌሎችም ከዚህ ውድ ስጦታ እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ ለመናገር የተቻለንን ሁሉ ጥረት እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል። w17.02 1:17, 19
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 28
ታማኝና ልባም ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?—ማቴ. 24:45
የሐምሌ 15, 2013 መጠበቂያ ግንብ “ታማኝና ልባም ባሪያ”፣ የበላይ አካል ሆነው የሚያገለግሉትን ጥቂት ቁጥር ያላቸው የተቀቡ ወንድሞች እንደሚያመለክት ገልጾ ነበር። የበላይ አካሉ አባላት ትላልቅ ውሳኔዎችን የሚያደርጉት በቡድን ሆነው ነው። አባላቱ በሳምንት አንድ ጊዜ ይሰበሰባሉ፤ ይህም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለመመካከር የሚያስችላቸው ከመሆኑም ሌላ አንድነት እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ ያደርጋል። (ምሳሌ 20:18) የበላይ አካሉ አባላት በሙሉ፣ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ሊቀ መንበር ሆነው የማገልገል ኃላፊነት በየዓመቱ በዙር ይደርሳቸዋል፤ አባላቱ አንዳቸው ከሌላው እንደሚበልጡ አድርገው አያስቡም። (1 ጴጥ. 5:1) በበላይ አካሉ ሥር ያሉት ስድስት ኮሚቴዎች አባላትም ልክ እንደዚሁ በዙር ሊቀ መንበር ሆነው ያገለግላሉ። ማንኛውም የበላይ አካል አባል በወንድሞቹ ላይ መሪ እንደሆነ አድርጎ ራሱን አይቆጥርም፤ ከዚህ ይልቅ በግለሰብ ደረጃ ‘ከቤተሰቦቹ’ አንዱ እንደሆነ አድርጎ ያስባል፤ በመሆኑም ታማኙ ባሪያ የሚያቀርበውን ምግብ ይመገባል እንዲሁም የባሪያውን አመራር ይከተላል። የበላይ አካሉ መለኮታዊ ራእይ አይገለጥለትም፤ ደግሞም ጨርሶ ስህተት አይሠራም ማለት አይደለም። በመሆኑም ከመሠረተ ትምህርቶች ወይም ከድርጅታዊ አሠራር ጋር በተያያዘ አንዳንድ ስህተቶች ሊሠራ ይችላል። w17.02 4:10-12
እሁድ፣ ሐምሌ 29
[አምላክ] ለገዛ ልጁ እንኳ [አልሳሳም] . . . ከዚህ ይልቅ ለእኛ ለሁላችን አሳልፎ [ሰጠው]።—ሮም 8:32
በቤዛው በማመን ራሳችንን ለይሖዋ ወስነን ስንጠመቅ ለቤዛው አድናቆት እንዳለን እናሳያለን። መጠመቃችን ‘የይሖዋ እንደሆንን’ ያሳያል። (ሮም 14:8) ይሖዋ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ ስለሆነ አገልጋዮቹ በሙሉ የእሱ ዓይነት ፍቅር እንዲያሳዩ ይፈልጋል። (1 ዮሐ. 4:8-11) ባልንጀራችንን የምንወድ ከሆነ “በሰማያት ላለው [አባታችን] ልጆች” መሆን እንደምንፈልግ እናሳያለን። (ማቴ. 5:43-48) ከሁሉ ከሚበልጡት ሁለት ትእዛዛት የመጀመሪያው ይሖዋን እንድንወድ የሚያዘው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ባልንጀራችንን መውደድ እንዳለብን ይገልጻል። (ማቴ. 22:37-40) የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንድንሰብክ የተሰጠንን ትእዛዝ በመፈጸም ለባልንጀራችን እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። ለሰዎች ፍቅር ስናሳይ የአምላክን ክብር እናንጸባርቃለን። እንዲያውም ሌሎችን በተለይ ደግሞ ወንድሞቻችንን እንድንወድ የተሰጠንን መመሪያ ስንታዘዝ ለአምላክ ያለን ፍቅር “ፍጹም ይሆናል።”—1 ዮሐ. 4:12, 20፤ w17.02 2:13, 14
ሰኞ፣ ሐምሌ 30
እውነተኛው አምላክ፣ ይሖዋ ከሆነ እሱን ተከተሉ፤ ባአል ከሆነ ደግሞ እሱን ተከተሉ!—1 ነገ. 18:21
ሕዝቡ የተደቀነባቸው ውሳኔ ቀላል እንደነበር ታስብ ይሆናል፤ ምክንያቱም ይሖዋን ማገልገል ምንጊዜም ቢሆን ጠቃሚና ጥበብ የሚንጸባረቅበት አካሄድ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። በእርግጥም አስተዋይ የሆነ ማንኛውም ሰው ባአልን ለማምለክ ሊመርጥ አይችልም። እስራኤላውያን ግን “በሁለት ሐሳብ [እያነከሱ]” ነበር። ኤልያስ ከሁሉ የላቀውን አምልኮ ይኸውም የይሖዋን አምልኮ እንዲመርጡ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። እስራኤላውያን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ ያን ያህል የከበዳቸው ለምን ሊሆን ይችላል? አንደኛው ምክንያት በይሖዋ ላይ እምነት ማጣታቸውና እሱን መስማት አለመፈለጋቸው ነው። ትክክለኛ እውቀት ወይም አምላካዊ ጥበብ ለማግኘት ጥረት አላደረጉም፤ እንዲሁም በይሖዋ አልታመኑም። ትክክለኛ እውቀት ቢኖራቸው ኖሮ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ማድረግ ይችሉ ነበር። (መዝ. 25:12) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሌሎች ተጽዕኖ እንዲያደርጉባቸው አልፎ ተርፎም ውሳኔ እንዲያደርጉላቸው ፈቅደዋል። እስራኤላውያን፣ በዙሪያቸው የነበሩ ይሖዋን የማያመልኩ ሰዎች በአስተሳሰባቸው ላይ ተጽዕኖ ስላሳደሩባቸው እነዚያን ጣዖት አምላኪዎች መከተል ጀመሩ። ይሖዋ ይህ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል አስቀድሞ አስጠንቅቋቸው ነበር።—ዘፀ. 23:2፤ w17.03 2:6, 7
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 31
[ሕዝቅያስ] ሙሴ ሠርቶት የነበረውን የመዳብ እባብ አደቀቀ።—2 ነገ. 18:4
ሕዝቅያስ በተወው ምሳሌ ላይ ስናሰላስል፣ ከይሖዋ ጋር ባለን ዝምድና ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ ወይም ለእውነተኛው አምልኮ ሙሉ ትኩረት እንዳንሰጥ እንቅፋት እየሆኑብን ያሉ ነገሮች እንዳሉ ይሰማን ይሆናል። ለምሳሌ በዛሬው ጊዜ ብዙዎች፣ ታዋቂ ሰዎችን እንደ ጣዖት አድርገው ይመለከቷቸዋል፤ በማኅበራዊ ድረ ገጾች አማካኝነት የእነዚህን ሰዎች ሕይወት ለመከታተል ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከቤተሰባቸው አባላት ወይም ከጓደኞቻቸው ጋር ለመገናኘት በማኅበራዊ ድረ ገጾች ይጠቀሙ ይሆናል። ይሁንና በዓለም ላይ ብዙዎች በማኅበራዊ ድረ ገጾች ከልክ በላይ ሲጠቀሙ ይታያሉ፤ በእነዚህ ድረ ገጾች አማካኝነት የማያውቋቸውን ሰዎች ሕይወት እንኳ ይከታተላሉ። የታዋቂ ሰዎችን ፎቶግራፎች በማየት ወይም ስለ እነሱ በማንበብ ብዙ ጊዜ ያጠፋሉ። እንዲህ ዓይነቱ ልማድ እርባና በሌላቸው ነገሮች እንድንጠመድ ሊያደርገን ይችላል። ሌላው ቀርቶ አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ያስቀመጧቸውን ፎቶግራፎች ብዙዎች ስለወደዱላቸው (ላይክ ስላደረጉላቸው) ይኩራሩ ይሆናል፤ ይባስ ብሎም በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ሰዎች እነሱን “መከተል” በማቆማቸው ቅር የሚሰኙም አሉ። ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ሰዎችን እንደ ጣዖት የመመልከት ዝንባሌ እንዳላዳብር ወይም ያን ያህል ጥቅም የሌላቸው ነገሮችን በማከናወን ውድ የሆነውን ጊዜዬን እንዳላጠፋ እጠነቀቃለሁ?’—ኤፌ. 5:15, 16፤ w17.03 3:14, 17