ነሐሴ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 1
በሁሉም ረገድ ምንም የማይጎድላችሁ ፍጹማንና እንከን የለሽ እንድትሆኑ ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም።—ያዕ. 1:4
ጦርነቱ ተፋፍሟል። በመስፍኑ ጌድዮን የሚመሩት የእስራኤል ወታደሮች፣ ጠላቶቻቸው የሆኑትን ምድያማውያንንና ግብረ አበሮቻቸውን ሌሊቱን ሙሉ ሲያሳድዱ አድረዋል፤ እነሱን እየተከታተሉ ወደ 32 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ መንገድ ስለተጓዙ እጅግ ዝለዋል! እስራኤላውያን ይህ፣ ውጊያውን የሚያቆሙበት ወቅት እንዳልሆነ ያውቃሉ። በመሆኑም “ጠላቶቻቸውን ከማሳደድ ወደኋላ” አላሉም፤ ከዚህ ይልቅ ምድያማውያንን በማሸነፍ እንዲገዙላቸው አደረጉ። (መሳ. 7:22፤ 8:4, 10, 28) እኛም ብንሆን ምንጊዜም ውጊያ ላይ ነን፤ ውጊያው ደግሞ ከባድ ነው። ጠላቶቻችን፣ ሰይጣንና እሱ የሚገዛው ዓለም እንዲሁም የራሳችን አለፍጽምና ናቸው። አንዳንዶቻችን በውጊያው ላይ በርካታ አሥርተ ዓመታት ያሳለፍን ሲሆን በይሖዋ እርዳታ ብዙ ድሎችን ተቀዳጅተናል። አንዳንድ ጊዜ ግን ከጠላቶቻችን ጋር መዋጋትና የዚህን ሥርዓት መጨረሻ መጠባበቅ ሊታክተን ይችላል። ሆኖም በውጊያው ሙሉ በሙሉ እንዳላሸነፍን እናስታውስ። ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት የምንኖር ክርስቲያኖች፣ ከባድ ፈተናዎች ሊያጋጥሙንና ግፍ ሊፈጸምብን እንደሚችል አስጠንቅቆናል፤ በተጨማሪም ድል መቀዳጀታችን የተመካው በመጽናታችን ላይ እንደሆነ ተናግሯል።—ሉቃስ 21:19፤ w16.04 2:1, 2
ሐሙስ፣ ነሐሴ 2
የሐዋርያቱንም ትምህርት በትኩረት መከታተላቸውን ቀጠሉ፤ አንድ ላይ ይሰበሰቡ . . . ነበር።—ሥራ 2:42
በስብሰባዎቻችን ላይ ታላቁ አስተማሪያችን ይሖዋ፣ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት መመሪያ ይሰጠናል። (ኢሳ. 30:20, 21) በስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙ የማያምኑ ሰዎች እንኳ “አምላክ በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” የሚል መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። (1 ቆሮ. 14:23-25) ይሖዋ ስብሰባዎችን በቅዱስ መንፈሱ የሚመራ ሲሆን መንፈሳዊ ትምህርት የሚሰጠን እሱ ነው። በመሆኑም በስብሰባዎቻችን ላይ የይሖዋን ድምፅ የምንሰማ ከመሆኑም ሌላ ፍቅራዊ እንክብካቤ እንደሚያደርግልን እናስተውላለን። ይህም ወደ እሱ እንድንቀርብ ያደርገናል። ኢየሱስ “ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እገኛለሁ” ብሏል። (ማቴ. 18:20) ክርስቶስ የጉባኤው ራስ እንደመሆኑ መጠን የአምላክን ሕዝቦች ባቀፉት ጉባኤዎች ‘መካከል ይመላለሳል።’ (ራእይ 1:20 እስከ 2:1) እስቲ አስበው! ይሖዋና ኢየሱስ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አማካኝነት ያበረታቱናል። ይሖዋ ወደ እሱና ወደ ልጁ ለመቅረብ ምን ያህል እንደምንጓጓ ሲመለከት ምን የሚሰማው ይመስልሃል? w16.04 3:13, 14
ዓርብ፣ ነሐሴ 3
ለቁጣ አትቸኩል።—መክ. 7:9
አንዲት እህት፣ የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች በተገኙበት ግብዣ ላይ የነበሩ ሁለት ወንድሞችን ሰላም አለቻቸው፤ ሆኖም ሰላም ያለችበት መንገድ አንደኛውን ወንድም አላስደሰተውም። ሁለቱ ወንድሞች ብቻቸውን ሲሆኑ፣ በእህት ቅር የተሰኘው ወንድም የተናገረችውን ነገር አንስቶ ይነቅፋት ጀመረ። ሌላኛው ወንድም ግን ይህች እህት ለ40 ዓመታት ያህል በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ይሖዋን በታማኝነት እንዳገለገለች ካስታወሰው በኋላ ይህን ያለችው እሱን ለመጉዳት አስባ እንዳልሆነ አስረግጦ ነገረው። የመጀመሪያው ወንድም ነገሩን ለአፍታ ካሰበበት በኋላ “ልክ ነህ” ብሎ መለሰለት። በመሆኑም ጉዳዩ በዚያው ተቋጨ። ከዚህ ተሞክሮ ምን ትምህርት ማግኘት ይቻላል? ቅር ሊያሰኝህ የሚችል ሁኔታ ሲፈጠር ምላሽ የምትሰጥበት መንገድ ጉዳዩ እንዲባባስ ወይም በአጭሩ እንዲቀጭ ሊያደርግ ይችላል። አፍቃሪ የሆነ ሰው ጥቃቅን ስህተቶችን ችላ ብሎ ያልፋል። (ምሳሌ 10:12፤ 1 ጴጥ. 4:8) ‘በደልን የሚተው’ ሰው በይሖዋ ፊት ‘ውብ’ ነው። (ምሳሌ 19:11) በመሆኑም አንድ ሰው ደግነት ወይም አክብሮት የጎደለው ነገር እንዳደረገብህ ከተሰማህ በቅድሚያ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ጉዳዩን ችላ ብዬ ማለፍ እችላለሁ? ያን ያህል አክብጄ ልመለከተው የሚገባ ነገር ነው?’ w16.05 1:8, 9
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 4
ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ለተግባር እንድትነሳሱ በማድረግ ኃይል የሚሰጣችሁ አምላክ ነው።—ፊልጵ. 2:13
በዛሬው ጊዜ የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበኩ ያሉት እነማን ናቸው? “የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው!” ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን። ይህን ያህል እርግጠኞች መሆን የቻልነው ለምንድን ነው? ትክክለኛውን መልእክት ይኸውም የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበክን ስለሆነ ነው። መልእክቱን ለመስበክ ወደ ሰዎች ስለምንሄድ ትክክለኛውን ዘዴ እየተጠቀምን ነው። በተጨማሪም የስብከቱን ሥራ የምናከናውነው በትክክለኛው ዓላማ ይኸውም በፍቅር ተነሳስተን እንጂ የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ብለን አይደለም። በሁሉም ብሔራት ውስጥ ለሚገኙና የተለያዩ ቋንቋዎች ለሚናገሩ ሰዎች ስለምንሰብክ ሥራችንን በተቻለን መጠን በስፋት እያከናወንን ነው። ከዚህም ሌላ ዓመት አልፎ ዓመት ቢተካም መጨረሻው እስኪመጣ ድረስ ሳንታክት ይህን ሥራ እናከናውናለን። የአምላክ ሕዝቦች አሁን ባለንበት ታሪካዊ ወቅት እያከናወኑ ያሉት ሥራ በእርግጥም በጣም የሚያስደንቅ ነው! ይሁንና ይህ ሁሉ ሊከናወን የቻለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን በመናገር መልሱን ሰጥቶናል። እንግዲያው አፍቃሪው አባታችን በሚሰጠን ኃይል እየታገዝን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረጋችንንና አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸማችንን እንቀጥል።—2 ጢሞ. 4:5፤ w16.05 2:17, 18
እሁድ፣ ነሐሴ 5
ክፉ የሆነውን ተጸየፉ፤ ጥሩ የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ።—ሮም 12:9
በራሳችን ተነሳስተን የአምላክን ፈቃድ ስንፈጽምና ይህን ለማድረግ ከልባችን ስንጥር ለይሖዋ ያለን ፍቅርና እሱን ለማስደሰት ያለን ፍላጎት ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ እናሳያለን። ሉዓላዊነቱን እንደምንደግፍም እናሳያለን። ይሖዋ ሉዓላዊነቱን የሚጠቀምበት መንገድ ትክክል ስለመሆኑ ሰይጣን ጥያቄ አስነስቷል፤ በመሆኑም ደግና አድናቂ የሆነው የሰማዩ አባታችን፣ የእሱን ሉዓላዊነት ለመደገፍ በፈቃዳችን ተነሳስተን ለምናደርገው ከፍተኛ ጥረት ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ጥርጥር የለውም። (ኢዮብ 2:3-5፤ ምሳሌ 27:11) ይሁንና ይሖዋ እሱን ለማስደሰት ስንል ካለብን አለፍጽምና ጋር የምናደርገውን ትግል ሙሉ በሙሉ ቢያስወግድልን ኖሮ ለሉዓላዊነቱ ታማኝ እንደሆንንና ሉዓላዊነቱን እንደምንደግፍ መናገር አንችልም ነበር። በመሆኑም ይሖዋ እሱን የሚያስደስቱ ባሕርያትን ለማዳበር “ልባዊ ጥረት” እንድናደርግ ይመክረናል። (2 ጴጥ. 1:5-7፤ ቆላ. 3:12) አስተሳሰባችንንና ስሜታችንን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እንድናደርግ ይፈልጋል። (ሮም 8:5) በዚህ ረገድ ከልባችን ጥረት ካደረግን በኋላ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አሁንም ሕይወታችንን እየለወጠው እንዳለ ስንገነዘብ ይበልጥ እርካታ እናገኛለን። w16.05 4:12, 13
ሰኞ፣ ነሐሴ 6
ይሖዋ ሆይ፣ . . . አንተም ሠሪያችን ነህ።—ኢሳ. 64:8
ይሖዋ ‘የሸክላውን’ ዓይነትና ጥራት ያውቃል፤ በመሆኑም የሚቀርጸው ይህን መሠረት በማድረግ ነው። (መዝ. 103:10-14) በእርግጥም ይሖዋ የእያንዳንዳችንን ድክመት፣ የአቅም ገደብና መንፈሳዊነት ከግምት በማስገባት በግለሰብ ደረጃ ይቀርጸናል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አባቱ ፍጹም ላልሆኑት አገልጋዮቹ ያለውን አመለካከት አንጸባርቋል። የኢየሱስ ሐዋርያት የተለያየ ድክመት ነበራቸው፤ በተለይ ደግሞ ‘ማን ይበልጣል?’ በሚለው ጉዳይ ብዙ ጊዜ ይከራከሩ ነበር። በሐዋርያቱ መካከል የነበረውን የጦፈ ክርክር ብትመለከት ኖሮ እነዚህን ሰዎች በቀላሉ ሊቀረጽ እንደሚችል የሸክላ ጭቃ አድርገህ ታያቸው ነበር? ኢየሱስ አሉታዊ አመለካከት አልነበረውም። ታማኝ ሐዋርያቱ እሱ በደግነትና በትዕግሥት የሚሰጣቸውን ምክር ተግባራዊ ቢያደርጉ እንዲሁም በትሕትና ረገድ የተወውን ምሳሌ ቢከተሉ ሊለወጡ እንደሚችሉ ያውቅ ነበር። (ማር. 9:33-37፤ 10:37, 41-45፤ ሉቃስ 22:24-27) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ሐዋርያቱ መንፈስ ቅዱስ የወረደባቸው ሲሆን ስለ ሥልጣን ከማሰብ ይልቅ በሰጣቸው ሥራ ላይ ትኩረት አድርገዋል።—ሥራ 5:42፤ w16.06 1:10
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 7
አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ ነው።—ዘዳ. 6:4
እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ብቻ ነው፤ እንደ እሱ ያለ ሌላ አምላክ የለም። (2 ሳሙ. 7:22) በመሆኑም ሙሴ፣ እስራኤላውያን ሊያመልኩ የሚገባው ይሖዋን ብቻ እንደሆነ ማሳሰቡ ነበር። በዙሪያቸው እንዳሉት አሕዛብ፣ ተባዕትና እንስት የሆኑ በርካታ አማልክትን ሊያመልኩ አይገባም። ከእነዚህ የሐሰት አማልክት የተወሰኑት፣ አንዳንድ የተፈጥሮ ኃይሎችን እንደሚቆጣጠሩ ይታመን ነበር። ሌሎቹ ደግሞ የአንድ የሐሰት አምላክ የተለያዩ መገለጫዎች ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ግብፃውያን ራ የተባለውን የፀሐይ አምላክ፣ ነት የተባለችውን የሰማይ አምላክ፣ ጌብ የተባለውን የምድር አምላክ፣ ሃፒ የተባለውን የናይል አምላክና እንደ ቅዱስ የሚታዩ ሌሎች በርካታ እንስሳትን ያመልኩ ነበር። ይሖዋ በአሥሩ መቅሰፍቶች አማካኝነት ከእነዚህ የሐሰት አማልክት አብዛኞቹን አዋርዷቸዋል። ዋነኛው የከነአናውያን አምላክ፣ የመራባት አምላክ የሆነው ባአል ሲሆን ይኸው አምላክ የሰማይ፣ የዝናብና የአውሎ ነፋስ አምላክ እንደሆነም ይታመን ነበር። በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች፣ ባአል ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ይሰማቸው ነበር። (ዘኁ. 25:3) እስራኤላውያን ግን አምላካቸው ይኸውም “እውነተኛው አምላክ” አንድ ይሖዋ መሆኑን ማስታወስ ነበረባቸው።—ዘዳ. 4:35, 39፤ w16.06 3:4, 5
ረቡዕ፣ ነሐሴ 8
ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው። እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።—ማቴ. 28:20
ኢየሱስ በይሖዋና በሕዝቡ መተማመኑ ተገቢ ነበር፤ አሁንም ቢሆን ሁኔታው አልተለወጠም። በእርግጥም ይሖዋ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በአገልጋዮቹ አማካኝነት እያከናወነ ያለው ነገር እጅግ አስደናቂ ነው። ይሖዋ አንድነት ያለውን የክርስቲያን ጉባኤ እየመራው በመሆኑ አገልጋዮቹ እውነትን በዓለም ዙሪያ መስበክ ችለዋል፤ እንዲህ እያደረገ ያለ ሌላ ሕዝብ የለም። ኢሳይያስ 65:14 የአምላክ ሕዝቦች ስላሉበት መንፈሳዊ ሁኔታ ሲገልጽ “እነሆ፣ አገልጋዮቼ ከልባቸው ደስታ የተነሳ እልል ይላሉ” በማለት ይናገራል። ይሖዋ እየመራንና ብዙ መልካም ነገሮችን እንድናከናውን እየረዳን በመሆኑ በጣም ደስተኞች ነን! ከዚህ በተቃራኒ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም በሐዘን ተውጧል፤ ምክንያቱም ሁኔታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ ነው። ምንጊዜም ለይሖዋና ለዝግጅቶቹ ታማኝ መሆን አለብን። w16.06 4:10-12
ሐሙስ፣ ነሐሴ 9
ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።—ማቴ. 25:13
ነቅቶ የመጠበቅን አስፈላጊነት፣ በጥንት ዘመን ከተሞችን ይጠብቁ ከነበሩ ጠባቂዎች መማር እንችላለን። በዚያን ዘመን፣ እንደ ኢየሩሳሌም ያሉ በርካታ ትላልቅ ከተሞች ዙሪያቸው በረጅም ቅጥር ይታጠር ነበር። እንዲህ ያለው ቅጥር ወራሪዎች ከተማዋን እንዳይደፍሯት የሚከላከል ከመሆኑም ሌላ ጠባቂዎቹ ከፍታ ላይ ሆነው አካባቢውን እንዲቃኙ ያስችላቸዋል። በከተማዎቹ ቅጥሮችና በሮች ላይ ሆነው ቀንና ሌሊት የሚጠብቁ ዘቦች ይመደቡ ነበር። እነዚህ ጠባቂዎች ከተማዋ ላይ ጥቃት ሊሰነዘር እንደሆነ የሚጠቁም ነገር ከርቀት ከተመለከቱ የከተማዋን ነዋሪዎች ያስጠነቅቃሉ። (ኢሳ. 62:6) ጠባቂዎቹ ንቁ ሆነው አካባቢውን በትኩረት መከታተላቸው የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነበር። (ሕዝ. 33:6) አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ፣ የሮም ሠራዊት ከኢየሩሳሌም ቅጥር ጋር ተያይዞ የተሠራውን የአንቶኒያን ግንብ በ70 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ሊያውል የቻለው በር ላይ ያሉት ጠባቂዎች ተኝተው ስለነበር እንደሆነ ገልጿል! ሮማውያን በአንቶኒያ ግንብ አልፈው በመግባት ቤተ መቅደሱን በእሳት አጋዩት፤ እንዲሁም ከተማዋን አጠፏት። ይህም በአይሁድ ብሔር ላይ የደረሰው ታላቅ መከራ መደምደሚያ ሆነ። w16.07 2:2, 7, 8
ዓርብ፣ ነሐሴ 10
ሕግ የሚተላለፉ ሰዎች በሚፈጽሙት ስህተት ከእነሱ ጋር ተታልላችሁ እንዳትወሰዱና ጽኑ አቋማችሁ እንዳይናጋ ተጠንቀቁ።—2 ጴጥ. 3:17
የይሖዋ ጸጋ ብዙ በረከቶች የሚያስገኝልን ቢሆንም ይሖዋ የፈለግነውን ብናደርግ በቸልታ እንደሚያልፈን አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። ከጥንቶቹ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ ‘በአምላክ ጸጋ እያሳበቡ ዓይን ያወጣ ምግባር ይፈጽሙ’ ነበር። (ይሁዳ 4) እነዚህ ታማኝ ያልሆኑ ክርስቲያኖች፣ ኃጢአት ቢፈጽሙም ይሖዋ ሁልጊዜ ይቅር እንደሚላቸው ያስቡ የነበረ ይመስላል። ይባስ ብለው ደግሞ ወንድሞቻቸውም የእነሱን አስጸያፊ አካሄድ እንዲከተሉ ይገፋፉ ነበር። ዛሬም ቢሆን እንዲህ የሚያደርግ ማንኛውም ሰው “የጸጋን መንፈስ በንቀት [እያጥላላ]” ነው። (ዕብ. 10:29) በዛሬው ጊዜ ሰይጣን፣ አንዳንድ ክርስቲያኖችን ኃጢአት ቢፈጽሙም አምላክ ምሕረት እንደሚያደርግላቸውና ምንም ቅጣት እንደማይደርስባቸው አድርገው እንዲያስቡ በማድረግ እያታለላቸው ነው። ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር የሚል ቢሆንም እንኳ የኃጢአት ዝንባሌያችንን ለማሸነፍ አጥብቀን እንድንታገል ይጠብቅብናል። w16.07 3:16, 17
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 11
በፆታ ብልግና ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።—ማቴ. 19:9
አንድ ሰው በፆታ ብልግና ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሕጋዊ ፍቺ ቢፈጽምም እንኳ ሌላ ሰው ለማግባት ነፃ አይሆንም። እርግጥ ነው፣ ሆሴዕ የፆታ ብልግና የፈጸመችውን ሚስቱን ጎሜርን ይቅር እንዳላት ሁሉ ክህደት የተፈጸመበት አንድ ባለትዳርም ንስሐ የገባውን የትዳር ጓደኛውን ይቅር ለማለት ሊመርጥ ይችላል። በመንፈሳዊ ሁኔታ ምንዝር የፈጸሙት እስራኤላውያን ንስሐ ሲገቡ ይሖዋ ምሕረት አድርጎላቸዋል። (ሆሴዕ 3:1-5) በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ባለትዳር፣ የትዳር ጓደኛው ምንዝር እንደፈጸመ ካወቀ በኋላም ከእሱ ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸሙን ቢቀጥል እንዲህ ማድረጉ ለበዳዩ ይቅርታ እንዳደረገለት ስለሚቆጠር ከዚያ በኋላ ፍቺ ለመፈጸም የሚያስችል ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት አይኖረውም። ኢየሱስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ከተናገረ በኋላ ነጠላ ሆነው ለመኖር “ስጦታው ያላቸው” ሰዎች እንዳሉ ገልጿል። አክሎም “ይህን ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 19:10-12) ብዙዎች፣ ሐሳባቸው ሳይከፋፈል ይሖዋን ለማገልገል ሲሉ ነጠላ ሆነው ለመኖር መርጠዋል። እንዲህ በማድረጋቸውም አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል። w16.08 1:15, 16
እሁድ፣ ነሐሴ 12
ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም፤ እሱን መጠጊያ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው። . . . እሱን የሚፈሩ የሚያጡት ነገር የለም።—መዝ. 34:8, 9
ወጣቶች በይሖዋ አገልግሎት ብዙ ነገር ለማከናወን የሚያስችል ጉልበት አላቸው። (ምሳሌ 20:29) በቤቴል የሚያገለግሉ አንዳንድ ወጣቶች፣ መጽሐፍ ቅዱሶችንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማተሙና በመጠረዙ ሥራ ይካፈላሉ። ጥቂት የማይባሉ ወጣት ወንድሞችና እህቶች የመንግሥት አዳራሾችን በመገንባትና በማደስ ሥራ ይሳተፋሉ። የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ ወጣቶች፣ ተሞክሮ ካላቸው ወንድሞች ጋር በመሆን በአደጋው ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ ይሰጣሉ። እንዲሁም በርካታ ወጣት አቅኚዎች ምሥራቹን ለመስበክ ሲሉ ሌላ ቋንቋ ይማራሉ፤ ወይም ወደ ሌላ አካባቢ ተዛውረው ያገለግላሉ። መዝሙራዊው “ይሖዋን የሚሹ . . . መልካም ነገር አይጎድልባቸውም” ሲል ዘምሯል። (መዝ. 34:10) በእርግጥም ይሖዋ በቅንዓት የሚያገለግሉትን ፈጽሞ አያሳፍራቸውም። በይሖዋ አገልግሎት የቻልነውን ሁሉ ስናደርግ በግለሰብ ደረጃ፣ ‘ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቀምሰን ማየት’ እንችላለን። አምላክን በሙሉ ነፍሳችን ማገልገላችን ተወዳዳሪ የሌለው ደስታ ያስገኝልናል። w16.08 3:5, 8
ሰኞ፣ ነሐሴ 13
አድናችኋለሁ፤ እናንተም በረከት ትሆናላችሁ። አትፍሩ! እጃችሁን አበርቱ።—ዘካ. 8:13
ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እኛን ለማበርታት ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ አለው። (1 ዜና 29:12) በመሆኑም ሰይጣንና ይህ ክፉ ሥርዓት የሚያመጡብንን ማንኛውንም ፈተና መቋቋም እንድንችል ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን መጠየቃችን ወሳኝ ነገር ነው። (መዝ. 18:39፤ 1 ቆሮ. 10:13) በተጨማሪም በአምላክ ቅዱስ መንፈስ መሪነት የተጻፈው ቃሉ ስላለን እጅግ አመስጋኞች ነን። እስቲ በየወሩ ስለምናገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መንፈሳዊ ምግብም አስቡ። በዘካርያስ 8:9, 13 ላይ የሚገኘው ትንቢት የተነገረው በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ በድጋሚ በሚገነባበት ወቅት ነው፤ በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ማበረታቻ ለእኛም በጣም ጠቃሚ ነው። ከዚህም ሌላ በጉባኤ ስብሰባዎችና በትላልቅ ስብሰባዎች እንዲሁም በቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች አማካኝነት ከሚሰጠን ትምህርት ብርታት እናገኛለን። የምናገኘው ሥልጠና መንፈሳዊ ግቦች እንድናወጣ እንዲሁም ያሉብንን በርካታ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶች እንድንፈጽም ያነሳሳናል። (መዝ. 119:32) አንተስ በዚህ መንገድ ከሚቀርብልን ትምህርት ብርታት ለማግኘት እንደምትጓጓ ታሳያለህ? w16.09 1:10, 11
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 14
ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ [አረጋግጡ]።—ሮም 12:2
አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግ አንድ ግለሰብ ወንድ ይሁን ሴት ለመለየት የሚያስቸግር አለባበስን ይሖዋ አጥብቆ እንደሚጠላ በግልጽ ያሳያል፤ በዛሬው ጊዜ ይህ ዓይነቱ አለባበስ ፋሽን እየሆነ መጥቷል። (ዘዳ. 22:5) አምላክ አለባበስን በተመለከተ ከሰጠው መመሪያ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ወንዶች ሴት እንዲመስሉ፣ ሴቶች ደግሞ ወንድ እንዲመስሉ አሊያም በሁለቱ ፆታዎች መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ አዳጋች እንዲሆን የሚያደርጉ አለባበሶችን አምላክ ይጠላል። የአምላክ ቃል፣ ክርስቲያኖች ከአለባበስ ጋር በተያያዘ ጥሩ ውሳኔ እንዲያደርጉ የሚረዷቸው መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። ክርስቲያኖች የሚኖሩበት ቦታ፣ ባሕላቸው ወይም የአየሩ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የትኛው አለባበስ ተቀባይነት እንዳለውና የትኛው ደግሞ ተገቢ እንዳልሆነ የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ አያስፈልገንም። በቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች የምንመራ ሲሆን እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንም ዓይነት የግል ምርጫ እንዳይኖረን የሚከለክሉ አይደሉም። w16.09 3:3, 4
ረቡዕ፣ ነሐሴ 15
በዚህ ጊዜ ሁሉም ጥለውት ሸሹ።—ማር. 14:50
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የነበራቸውን ድፍረትና ሐቀኝነት እንመልከት። ብዙዎቹ የጥንት ጸሐፊዎች ያሰፈሯቸው ዘገባዎች መሪዎቻቸውን የሚክቡና አገራቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ናቸው። የይሖዋ ነቢያት ግን ምንጊዜም እውነተኛውን ዘገባ ያሰፍሩ ነበር። የሕዝባቸውን ሌላው ቀርቶ የንጉሦቻቸውንም ጭምር ድክመት አስፍረዋል። (2 ዜና 16:9, 10፤ 24:18-22) ከዚህም ሌላ ጸሐፊዎቹ ራሳቸውም ሆኑ ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች የፈጸሟቸውን ስህተቶች ሳይሸሽጉ ዘግበዋል። (2 ሳሙ. 12:1-14) መጽሐፍ ቅዱስ ለሕይወት ጠቃሚ የሆኑ መመሪያዎችን የያዘ በመሆኑ፣ ብዙዎች ይህ መጽሐፍ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መሆኑን እንዲያምኑ አድርጓቸዋል። (መዝ. 19:7-11) የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረጋችን በሐሰት አምልኮ እንዳንካፈል የጠበቀን ከመሆኑም ሌላ ብዙዎችን ባሪያ ካደረጉት አጉል እምነቶች ነፃ አውጥቶናል። (መዝ. 115:3-8) እንደ ዝግመተ ለውጥ ያሉ ትምህርቶች ለይሖዋ ብቻ የሚገባውን የአምላክነት ቦታ ለፍጥረት እንዲሰጥ አድርገዋል። አምላክ የለም የሚሉ ሰዎች የወደፊት ሕልውናችን ሙሉ በሙሉ በሰው ልጆች እጅ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁንና የተሻለ የወደፊት ሕይወት እንደሚኖረን እርግጠኛ የሆነ ተስፋ ሊሰጡን አይችሉም።—መዝ. 146:3, 4፤ w16.09 4:10, 11
ሐሙስ፣ ነሐሴ 16
ትቃርም፤ ምንም እንዳትበድሏት።—ሩት 2:15
ቦዔዝ የሩት ሁኔታ እንዲሁም የባዕድ አገር ሰው በመሆኗ ሊያጋጥማት የሚችለው ችግር አሳስቦት ነበር። ይህን ከሚጠቁሙት ነገሮች አንዱ፣ ማሳ ውስጥ የሚሠሩት ወንዶች እንዳያስቸግሯት ከወጣት ሴት ሠራተኞቹ ሳትርቅ እንድትሠራ የነገራት መሆኑ ነው። ሌላው ቀርቶ እንደ ቅጥር ሠራተኞቹ ሁሉ እሷም በቂ ምግብና ውኃ ማግኘት እንድትችል አድርጎ ነበር። በተጨማሪም ቦዔዝ ሩትን ያነጋገረበት መንገድ ይህችን ድሃ የባዕድ አገር ሴት ዝቅ አድርጎ እንደማይመለከታት የሚያሳይ ነው፤ እንዲያውም አበረታቷታል። (ሩት 2:8-10, 13, 14) ቦዔዝ፣ ሩትን እንዲያደንቃት ያደረገው ለአማቷ ለናኦሚ የነበራት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ብቻ ሳይሆን የይሖዋ አምላኪ ለመሆን መወሰኗም ጭምር ነው። ቦዔዝ፣ ‘በክንፎቹ ሥር ለመጠለል ብላ ወደ እስራኤል አምላክ’ ለመጣችው ለሩት ደግነት ማሳየቱ እንደ ይሖዋ ዓይነት ታማኝ ፍቅር እንደነበረው ይጠቁማል። (ሩት 2:12, 20፤ ምሳሌ 19:17) እኛም በተመሳሳይ ደግነት ማሳየታችን “ሁሉም ዓይነት ሰዎች” እውነትን እንዲያውቁ እንዲሁም ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወዳቸው እንዲገነዘቡ ሊረዳቸው ይችላል።—1 ጢሞ. 2:3, 4፤ w16.10 1:10-12
ዓርብ፣ ነሐሴ 17
ይሖዋን ጠየቅኩት፤ እሱም መለሰልኝ። ከምፈራው ነገር ሁሉ ታደገኝ።—መዝ. 34:4
እኛም ይሖዋ እንደሚሰማንና በደስታ ለመጽናት የሚያስችል ብርታት እንደሚሰጠን ስለምናውቅ የሚያስጨንቀንን ነገር ሁሉ አውጥተን ለእሱ መናገር እንችላለን። አምላክ ለጸሎታችን መልስ ሲሰጠን ደግሞ እምነታችን እየጠነከረ ይሄዳል። (1 ዮሐ. 5:14, 15) እምነት ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ በመሆኑ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ኢየሱስ እንደመከረን ‘ደጋግመን መለመን’ ይኖርብናል። (ሉቃስ 11:9, 13) ይሁን እንጂ የምንጸልየው አምላክ እንዲረዳን ለመጠየቅ ብቻ መሆን የለበትም። ይሖዋን በየዕለቱ እንድናመሰግነውና እንድናወድሰው የሚያነሳሱንን ‘ድንቅ ሥራዎቹን ዘርዝረን መጨረስ አንችልም!’ (መዝ. 40:5) በተጨማሪም ጸሎታችን፣ ‘በእስር ላይ ያሉትን ከእነሱ ጋር ታስረን እንዳለን አድርገን በማሰብ ሁልጊዜ እንደምናስታውሳቸው’ የሚያሳይ መሆን አለበት። ከዚህም ሌላ ለመላው የወንድማማች ማኅበር በተለይም ‘በመካከላችን ሆነው አመራር ለሚሰጡት’ ልንጸልይ ይገባል። ይሖዋ፣ ሁላችንም ለምናቀርበው ጸሎት መልስ እንደሚሰጥ ስንመለከት ልባችን በደስታ ይሞላል!—ዕብ. 13:3, 7፤ w16.10 3:8, 9
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 18
እናንተ የዳናችሁት በእምነት አማካኝነት . . . ነው፤ ይህም እናንተ በራሳችሁ ያገኛችሁት አይደለም፤ ይልቁንም የአምላክ ስጦታ ነው።—ኤፌ. 2:8
በዘመናችን ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች በአምላክ መንግሥት ላይ ያላቸውን እምነት በተግባር አሳይተዋል። ይህም ከስምንት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ያሉትን ዓለም አቀፋዊ መንፈሳዊ ገነት አስገኝቷል። በዚህ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ የአምላክ መንፈስ ፍሬ ጎልቶ ይታያል። (ገላ. 5:22, 23) በእርግጥም መንፈሳዊው ገነት የእውነተኛ እምነትና ፍቅር ታላቅ መገለጫ ነው! ለዚህ ሊመሰገኑ የሚገባቸው ሰዎች ሳይሆኑ አምላካችን ነው። ይህ አስደናቂ ክንውን “የይሖዋ ስም እንዲገን” እያደረገ ነው፤ “እንዲሁም ፈጽሞ የማይጠፋ የዘላለም ምልክት ይሆናል።” (ኢሳ. 55:13) መላዋ ምድር ፍጹም፣ ጻድቅና ደስተኛ በሆኑ የሰው ልጆች እስክትሞላ ድረስ መንፈሳዊ ገነታችን እየሰፋና እየለመለመ ይሄዳል፤ ይህም ለይሖዋ ስም ዘላለማዊ ውዳሴ ያመጣል። እንግዲያው ይሖዋ በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳለን በተግባር ማሳየታችንን እንቀጥል! w16.10 4:18, 19
እሁድ፣ ነሐሴ 19
አንዳንዶች . . . ሥርዓት በጎደለው መንገድ በመካከላችሁ [እየተመላለሱ ነው]።—2 ተሰ. 3:11
ሁላችንም ሽማግሌዎች የሚሰጡንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ አለብን። ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ ሥርዓት በጎደለው መንገድ የሚሄዱ ሰዎችን አስመልክቶ የሰጠውን ምክር እንመልከት። አንዳንድ የጉባኤው አባላት “በማይመለከታቸው ጉዳይ ጣልቃ [ይገቡ]” ነበር። በወቅቱ የነበሩት ሽማግሌዎች ለእነዚህ ክርስቲያኖች ምክር ሳይሰጧቸው አልቀሩም፤ ይሁንና እነዚህ ሰዎች ምክሩን ችላ ብለው በድርጊታቸው ቀጥለዋል። ታዲያ ጉባኤው እንዲህ በሚያደርግ ግለሰብ ላይ ምን እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል? ጳውሎስ “ይህን ሰው ምልክት አድርጉበት፤ . . . ከእሱ ጋር አትግጠሙ” ብሏል። ሆኖም ጳውሎስ፣ ግለሰቡን እንደ ጠላት እንዳይመለከቱት አስጠንቅቋቸዋል። (2 ተሰ. 3:11-15) በዛሬው ጊዜም አንድ ሰው የጉባኤውን መልካም ስም የሚያጎድፍ ጎዳና መከተሉን ለማቆም ፈቃደኛ ባይሆን ለምሳሌ ከማያምን ሰው ጋር መጠናናቱን ቢቀጥል፣ ሽማግሌዎች ይህን በተመለከተ ለጉባኤው የማስጠንቀቂያ ንግግር እንዲቀርብ ሊያደርጉ ይችላሉ። (1 ቆሮ. 7:39) ታዲያ ሽማግሌዎች ለሚሰጡት ምክር ምን ምላሽ ትሰጣለህ? በንግግሩ ላይ የተጠቀሰውን አካሄድ የሚከተለውን ግለሰብ የምታውቀው ከሆነ ከእሱ ጋር ባለህ ቅርርብ ላይ ገደብ ታበጃለህ? በዚህ መንገድ ፍቅር ማሳየትህና ቁርጥ አቋም መውሰድህ፣ ሥርዓት በጎደለው መንገድ የሚሄደው ሰው አቋሙን እንዲያስተካክል ይረዳው ይሆናል። w16.11 2:13
ሰኞ፣ ነሐሴ 20
ከእናንተ መካከል እንኳ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች ይነሳሉ።—ሥራ 20:30
በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተቀየሩ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተቀቡ። እነዚህ አዲስ ክርስቲያኖች “የተመረጠ ዘር፣ ንጉሣዊ ካህናት፣ ቅዱስ ብሔር፣ ልዩ ንብረት እንዲሆን የተለየ ሕዝብ” ሆነዋል። (1 ጴጥ. 2:9, 10) ሐዋርያት በሕይወት እስካሉ ድረስ የአምላክን ሕዝብ ጉባኤ ይጠብቁ ነበር። በተለይ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ግን “ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች [ተነሱ]።” (2 ተሰ. 2:6-8) ከእነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በጉባኤ ውስጥ በበላይ ተመልካችነት የማገልገል ኃላፊነት ነበራቸው፤ ከጊዜ በኋላም “ጳጳሳት” ሆኑ። ኢየሱስ ተከታዮቹን “ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” ያላቸው ቢሆንም በክርስቲያኖች መካከል የቀሳውስት ቡድን ብቅ ማለት ጀመረ። (ማቴ. 23:8) በአርስቶትልና በፕላቶ ፍልስፍና የተማረኩ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች፣ የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶችን ማስተማር የጀመሩ ሲሆን ይህም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ንጹሕ ትምህርት ቀስ በቀስ እየዋጠው ሄደ። w16.11 4:8
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 21
ኃጢአት . . . ሟች በሆነው ሰውነታችሁ ላይ መንገሡን እንዲቀጥል አትፍቀዱ።—ሮም 6:12
ክርስቲያን ከመሆናችን በፊት፣ ድርጊታችን በአምላክ ፊት ምን ያህል መጥፎ እንደሆነ ባለማወቃችን ብዙ ጊዜ ኃጢአት እንሠራ ነበር። “ለርኩሰትና ለክፋት ባሪያዎች” የሆንን ያህል ነበር። በሌላ አባባል “የኃጢአት ባሪያዎች” ነበርን ማለት ይቻላል። (ሮም 6:19, 20) የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ስናውቅ ግን በሕይወታችን ውስጥ ለውጥ አደረግን፤ ከዚያም ራሳችንን ለአምላክ ወስነን ተጠመቅን። በዚህ መንገድ ‘ከኃጢአት ነፃ ወጥተን የጽድቅ ባሪያዎች ሆነናል።’ (ሮም 6:17, 18) ይሁንና ፍጽምና የጎደለው ሰውነታችን እንድናደርግ የሚገፋፋንን ነገሮች በሙሉ የምናደርግ ከሆነ ‘ኃጢአት በሰውነታችን ላይ መንገሡን እንዲቀጥል እየፈቀድን ነው’ ሊባል ይችላል። ኃጢአት እንዲነግሥብን ‘መፍቀድ’ ወይም አለመፍቀድ በእኛ ላይ የተመካ ነው፤ በመሆኑም ሊያሳስበን የሚገባው ጥያቄ ‘የልባችን ፍላጎት ምንድን ነው?’ የሚለው ነው። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ፍጽምና የጎደለው ሰውነቴ ወይም አእምሮዬ ወደተሳሳተ አቅጣጫ እንዲመራኝ በመፍቀድ መጥፎ ድርጊት የምፈጽምበት ጊዜ አለ? ወይስ ለኃጢአት ሞቻለሁ?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ፣ አምላክ እኛን ይቅር በማለት ላሳየን ጸጋ ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆንን የሚያሳይ ነው። w16.12 1:11, 12
ረቡዕ፣ ነሐሴ 22
በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር . . . ሰላም ያስገኛል።—ሮም 8:6
ውስጣዊ ሰላም ካለን ከቤተሰባችንም ሆነ ከጉባኤያችን አባላት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ጥረት እናደርጋለን። ይሁንና እኛም ሆንን ወንድሞቻችን ፍጽምና ይጎድለናል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፤ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን “ከወንድምህ ጋር ታረቅ” የሚለውን የኢየሱስ ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንዳለብን ተምረናል። (ማቴ. 5:24) ወንድሞቻችንም “ሰላም የሚሰጠው አምላክ” አገልጋዮች መሆናቸውን ማስታወሳችን ይህን ማድረግ ቀላል እንዲሆንልን አስተዋጽኦ ያበረክታል። (ሮም 15:33፤ 16:20) በዋጋ ሊተመን የማይችል ሌላም ዓይነት ሰላም አለ። “በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር” ከፈጣሪያችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ያስችለናል። ኢሳይያስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “ሙሉ በሙሉ በአንተ የሚመኩትን ትጠብቃለህ፤ በአንተ ስለሚታመኑ ዘላቂ ሰላም ትሰጣቸዋለህ” ብሎ ነበር፤ ይህ ትንቢት በኢሳይያስ ዘመን ፍጻሜውን ያገኘ ሲሆን በዘመናችንም በላቀ ሁኔታ እየተፈጸመ ነው።—ኢሳ. 26:3፤ ሮም 5:1፤ w16.12 2:5, 18, 19
ሐሙስ፣ ነሐሴ 23
ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ።—ፊልጵ. 4:4
የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ሊጠፋ በተቃረበበትና በጨለማ በተዋጠው በመጨረሻው ቀን ውስጥም እንኳ ይሖዋ ሕዝቡን እየባረከ ነው። እውነተኛ አገልጋዮቹ በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ሐሴት እንዲያደርጉና የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እንዲያገኙ እያደረገ ነው። (ኢሳ. 54:13) ኢየሱስ ቃል በገባው መሠረት፣ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ አፍቃሪ በሆኑ ወንድሞችና እህቶች በተሞላ ዓለም አቀፋዊ መንፈሳዊ ቤተሰብ ውስጥ እንድንታቀፍ በማድረግ ወሮታ ከፍሎናል። (ማር. 10:29, 30) ከዚህም ሌላ አምላክን ከልባቸው የሚፈልጉ ሁሉ የአእምሮ ሰላም፣ እርካታና ደስታ ስላላቸው ወደር የሌለው ሽልማት እያገኙ ነው። (ፊልጵ. 4:5-7) ‘የአምላክን ፈቃድ ከፈጸምክ የተስፋው ቃል ሲፈጸም እንደምታይ’ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ዕብ. 10:35, 36) እንግዲያው እምነታችንን ማጠናከራችንን እና ለይሖዋ እንደምናደርገው በማሰብ በሙሉ ነፍሳችን ማገልገላችንን እንቀጥል። ሽልማታችንን የምናገኘው ከይሖዋ ዘንድ እንደሆነ በማሰብ ይህን ማድረግ እንችላለን።—ቆላ. 3:23, 24፤ w16.12 4:17, 20
ዓርብ፣ ነሐሴ 24
የይሖዋ መንፈስ ባለበት ደግሞ ነፃነት አለ።—2 ቆሮ. 3:17
የመምረጥ ነፃነታችን ገደብ ያለው ከሆነ እውነተኛ ነፃነት አለን ሊባል ይችላል? አዎ፣ ሊባል ይችላል! እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ሰዎች ባላቸው ነፃነት ላይ ገደብ መደረጉ እነሱን ከአደጋ ይጠብቃቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ርቆ ወደሚገኝ አንድ ከተማ መኪና እየነዳህ መሄድ ፈለግክ እንበል። ሆኖም የምትሄድበት መንገድ ምንም ዓይነት የትራፊክ ሕግ የሌለበት እንዲሁም ሁሉም ሰው በፈለገው ፍጥነትና አቅጣጫ የሚነዳበት ቢሆን ምን ይሰማሃል? መቼም የደህንነት ስሜት እንደማይሰማህ የታወቀ ነው። ሁሉም ሰው እውነተኛ ነፃነት የሚያስገኘውን ጥቅም ማጣጣም እንዲችል ከተፈለገ ገደብ ሊኖር ይገባል። የመምረጥ ነፃነታችን ይሖዋ ባወጣቸው መመሪያዎች መገደቡ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ለማየት እስቲ የአዳምን ምሳሌ እንመልከት። አዳም እንዳይበላ ከተከለከለው ፍሬ በመብላት አምላክ ያስቀመጠለትን ገደብ አልፎ መሄድ መረጠ። አዳም የመምረጥ ነፃነቱን እንዲህ ባለ ተገቢ ያልሆነ መንገድ መጠቀሙ በዘሮቹ ላይ ለብዙ ሺህ ዓመታት የዘለቀ ሥቃይና መከራ አስከትሏል። (ሮም 5:12) አዳም እንዲህ ያለ ውሳኔ ማድረጉ ያስከተለውን ውጤት መገንዘባችን፣ የመምረጥ ነፃነታችንን ይሖዋ ካስቀመጠልን ገደብ ሳናልፍ በአግባቡ እንድንጠቀምበት ሊያነሳሳን ይገባል። w17.01 2:6, 8
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 25
እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት።—ሮም 12:3
አንድ አዲስ ኃላፊነት ከመቀበላችን በፊት በጸሎት በመታገዝ ያለንበትን ሁኔታ በሐቀኝነት መመርመራችን አቅማችንን ያላገናዘበ ነገር ከማድረግ እንድንቆጠብ ይረዳናል። ልካችንን ማወቃችን ከአቅማችን በላይ የሆነን ነገር ‘አልችልም’ ማለት እንዲቀለን ያደርጋል። በሌላ በኩል ደግሞ ስለ ጌድዮን ከሚናገረው ዘገባ መመልከት እንደሚቻለው አንድ አዲስ ኃላፊነት ስንቀበል ሊሳካልን የሚችለው የይሖዋን አመራርና በረከት ካገኘን ብቻ ነው። ይሖዋም ቢሆን ‘ልካችንን አውቀን ከእሱ ጋር እንድንሄድ’ ግብዣ አቅርቦልናል። (ሚክ. 6:8) በመሆኑም ምንጊዜም ቢሆን አዲስ ኃላፊነት ስንቀበል ወደ ይሖዋ መጸለይ እንዲሁም እሱ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠንን መመሪያ በጥንቃቄ መመርመር ይኖርብናል። አረማመዳችን ፍጹም ከሆነው የይሖዋ እርምጃ ጋር እንዲስማማ ማድረግን መማር አለብን። ‘ታላቅ የሚያደርገን’ የይሖዋ ትሕትና እንጂ የእኛ ችሎታ እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። (መዝ. 18:35) ልካችንን አውቀን ከአምላክ ጋር መሄዳችን ራሳችንን ከሚገባው በላይ ከፍ አድርገን ወይም በጣም ዝቅ አድርገን እንዳንመለከት ይረዳናል። w17.01 3:17, 18
እሁድ፣ ነሐሴ 26
ከጌታ ጋር በተያያዘ በትጋት የምታከናውኑት ሥራ ከንቱ [አይደለም]።—1 ቆሮ. 15:58
ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱ የሚያበቃበት ጊዜ እንደሚመጣና ሥራውን ሌሎች እንደሚረከቡት ያውቅ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ፍጹም ባይሆኑም እንኳ በእነሱ ላይ ይተማመን ስለነበር ከእሱ የሚበልጥ ሥራ እንደሚያከናውኑ ነግሯቸዋል። (ዮሐ. 14:12) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በሚገባ ያሠለጠናቸው ሲሆን እነሱም በወቅቱ ይታወቅ በነበረው ዓለም ምሥራቹን ከዳር እስከ ዳር አዳርሰዋል። (ቆላ. 1:23) ኢየሱስ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ከሰጠ በኋላ ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ ተመልሷል፤ በዚያም “ከየትኛውም መስተዳድር፣ ሥልጣን፣ ኃይልና ጌትነት . . . እጅግ የላቀ ቦታ [ተሰጥቶታል]።” (ኤፌ. 1:19-21) እኛም አርማጌዶን ከመምጣቱ በፊት ታማኝ ሆነን ከሞትን ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ከሞት እንነሳለን፤ በዚያ ወቅት እያንዳንዳችን የሚያስደስተንን ሥራ እንሠራለን። እስከዚያው ድረስ ግን ሁላችንም የምናከናውነው በጣም አስፈላጊ ሥራ አለ፤ ይህም ምሥራቹን የመስበኩና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ነው። እንግዲያው ወጣቶችም ሆንን በዕድሜ የገፋን፣ ‘ምንጊዜም የጌታ ሥራ የበዛልን እንሁን።’ w17.01 5:17, 18
ሰኞ፣ ነሐሴ 27
እኔ ይሖዋ ነኝና፤ አልለወጥም።—ሚል. 3:6
ቤዛው በድጋሚ መከፈል አያስፈልገውም። (ዕብ. 9:24-26) ቤዛው ከአዳም የወረስነውን ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ይደመስስልናል። የክርስቶስ መሥዋዕት የሰይጣን ዓለም ባሪያ ከመሆን ነፃ አውጥቶናል፤ እንዲሁም ከሞት ፍርሃት እንድንላቀቅ አድርጎናል። (ዕብ. 2:14, 15) አምላክ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም ምንም ጥርጥር የለውም። ይሖዋ ያወጣቸው የተፈጥሮ ሕጎች እንደማይለዋወጡ ሁሉ ይሖዋም አይለወጥም። አምላክ ፈጽሞ አያሳፍረንም። ይሖዋ ለእኛ ሕይወትን በመስጠት ብቻ ሳይወሰን ፍቅሩንም አሳይቶናል። “አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል፤ እንዲሁም አምነናል። አምላክ ፍቅር ነው።” (1 ዮሐ. 4:16) በቅርቡ መላዋ ምድር ውብ ገነት ትሆናለች፤ በምድር ላይ የሚኖሩ ሁሉ አምላክን በመምሰል አንዳቸው ለሌላው ፍቅር ያሳያሉ። በዚያ ጊዜ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ሁሉ እንዲህ ይላሉ፦ “ውዳሴ፣ ግርማ፣ ጥበብ፣ ምስጋና፣ ክብር፣ ኃይልና ብርታት ለዘላለም ለአምላካችን ይሁን። አሜን።”—ራእይ 7:12፤ w17.02 2:16, 17
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 28
ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።—2 ቆሮ. 7:1
በሰኔ 1, 1973 መጠበቂያ ግንብ ላይ “ከትንባሆ ሱስ መላቀቅ ያልቻሉ ሰዎች ለመጠመቅ ብቁ ይሆናሉ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦ ነበር። መልሱ “ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚያሳዩት እንዲህ ያሉ ሰዎች ለመጠመቅ ብቁ አይሆኑም” የሚል ነበር። መጠበቂያ ግንቡ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አንዳንድ ጥቅሶችን ከጠቀሰ በኋላ ንስሐ የማይገቡ አጫሾች ከጉባኤ መወገድ ያለባቸው ለምን እንደሆነ አብራርቷል። (1 ቆሮ. 5:7) መጠበቂያ ግንቡ እንዲህ ይላል፦ “ይህ እንዲሁ በጭፍን የተደረገ ፍትሐዊ ያልሆነ ውሳኔ አይደለም። የዚህ ጥብቅ መመሪያ ምንጭ አምላክ ነው፤ እሱም ሐሳቡን በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ አማካኝነት ገልጾልናል።” በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ ስለ ሃይማኖት የተጻፈ አንድ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “የክርስትና ሃይማኖት መሪዎች፣ በአባሎቻቸውና በብዙኃኑ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን እምነቶችና አመለካከቶች ለማስተናገድ ሲሉ በየጊዜው በትምህርቶቻቸው ላይ ማስተካከያ ያደርጋሉ።” ከይሖዋ ምሥክሮች ሌላ፣ ለአንዳንድ አባላቱ ሊከብድ ቢችልም እንኳ ሙሉ በሙሉ በአምላክ ቃል ለመመራት ጥረት የሚያደርግ ሃይማኖት አለ? w17.02 4:15
ረቡዕ፣ ነሐሴ 29
ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል።—ማቴ. 23:12
ሽማግሌዎች እንደ ዝነኛ ሰዎች እንድንመለከታቸው አይፈልጉም፤ ይህ ደግሞ ትሑት እንደሆኑ የሚያሳይ ነው። በዚህ መንገድ በአሁኑ ጊዜ ካሉትም ሆነ በኢየሱስ ዘመን ከነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ይለያሉ፤ ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “በራት ግብዣ ላይ የክብር ቦታ ማግኘት፣ በምኩራብ ደግሞ ከፊት መቀመጥ ይወዳሉ፤ በገበያ ቦታም ሰዎች እጅ እንዲነሷቸው ይፈልጋሉ።” (ማቴ. 23:6, 7) እውነተኛ ክርስቲያን እረኞች፣ ኢየሱስ የሰጠውን መመሪያ በመታዘዝ ትሑት እንደሆኑ ያሳያሉ፤ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “መምህራችሁ አንድ ስለሆነ ረቢ ተብላችሁ አትጠሩ፤ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ። በተጨማሪም አባታችሁ አንድ እሱም በሰማይ ያለው ብቻ ስለሆነ በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ። እንዲሁም መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ ስለሆነ መሪ ተብላችሁ አትጠሩ። ይልቁንም ከመካከላችሁ ታላቅ የሆነው የእናንተ አገልጋይ መሆን ይገባዋል።” (ማቴ. 23:8-11) በዓለም ዙሪያ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች የወንድሞቻቸውን ፍቅርና አክብሮት ያተረፉት ለምን እንደሆነ መገመት አያዳግትም። w17.03 1:14, 15
ሐሙስ፣ ነሐሴ 30
እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል።—ገላ. 6:5
ውሳኔ ማድረግ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው፤ በተጨማሪም ጥበብ የሚንጸባረቅበትና ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ የምንችለው ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት ሲኖረን ነው። ሌላ ሰው ውሳኔ እንዲያደርግልን ኃላፊነቱን ልንሰጠው አይገባም። ከዚህ ይልቅ በአምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ራሳችን ለይተን ማወቅና ይህን ለመከተል መምረጥ ይኖርብናል። ሌሎች ሰዎች ውሳኔ እንዲያደርጉልን በመፍቀድ አደገኛ የሆነ አካሄድ ልንከተል የምንችለው እንዴት ነው? የእኩዮች ተጽዕኖ መጥፎ ውሳኔዎችን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይችላል። (ምሳሌ 1:10, 15) ሌሎች ሰዎች ምንም ያህል ተጽዕኖ ሊያደርጉብን ቢሞክሩም በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነውን ሕሊናችንን መከተል የእኛ ኃላፊነት ነው። ሌሎች ውሳኔ እንዲያደርጉልን የምንፈቅድ ከሆነ እነሱን ‘ለመከተል’ መርጠናል ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ምርጫ ግን ውጤቱ አስከፊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሌሎች ውሳኔ እንዲያደርጉልን መፍቀድ ያለውን አደጋ በተመለከተ በገላትያ ለነበሩት ክርስቲያኖች ግልጽ የሆነ ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል። (ገላ. 4:17) በጉባኤ ውስጥ የነበሩ አንዳንዶች ለሌሎች ውሳኔ ማድረግ ይፈልጉ ነበር። w17.03 2:8-10
ዓርብ፣ ነሐሴ 31
[ኢዮስያስ] ገና ልጅ ሳለ የአባቱን የዳዊትን አምላክ መፈለግ ጀመረ፤ በ12ኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከፍ ካሉ የማምለኪያ ቦታዎች [እና] ከማምለኪያ ግንዶች . . . አነጻ።—2 ዜና 34:3
ኢዮስያስ አምላክን የሚያስደስተውን ነገር በቅንዓት አከናውኗል። እንደ ኢዮስያስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ልጆችም ከትንሽነታቸው አንስቶ ይሖዋን መፈለግ አለባቸው። ንጉሥ ምናሴ ንስሐ ከገባ በኋላ ኢዮስያስን ስለ አምላክ ምሕረት አስተምሮት ሊሆን ይችላል። ልጆች የሆናችሁ፣ በቤተሰባችሁና በጉባኤያችሁ ውስጥ ካሉ ታማኝ የሆኑ ትላልቅ ወንድሞችና እህቶች ጋር ብትቀራረቡ ይሖዋ ስላደረገላቸው በርካታ መልካም ነገሮች ሊነግሯችሁ ይችላሉ። በተጨማሪም ኢዮስያስ ቅዱሳን መጻሕፍት ምን እንደሚሉ ማወቁ ልቡ እንዲነካና እርምጃ እንዲወስድ እንዳነሳሳው አስታውሱ። እናንተም የአምላክን ቃል ማንበባችሁ ደስታችሁ እንዲጨምር፣ ከአምላክ ጋር ያላችሁ ወዳጅነት እንዲጠናከር እንዲሁም ሌሎች አምላክን እንዲፈልጉ ለመርዳት እንድትነሳሱ ሊያደርግ ይችላል። (2 ዜና 34:18, 19) ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችሁ ለአምላክ በምታቀርቡት አገልግሎት ረገድ ማሻሻያ ማድረግ የምትችሉባቸውን መንገዶች እንድታስተውሉ ይረዳችኋል። ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልጋችሁ ከተሰማችሁ ልክ እንደ ኢዮስያስ ለውጥ ለማድረግ የተቻላችሁን ጥረት አድርጉ። w17.03 3:18, 19