የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es18 ገጽ 88-97
  • መስከረም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መስከረም
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2018
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 1
  • እሁድ፣ መስከረም 2
  • ሰኞ፣ መስከረም 3
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 4
  • ረቡዕ፣ መስከረም 5
  • ሐሙስ፣ መስከረም 6
  • ዓርብ፣ መስከረም 7
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 8
  • እሁድ፣ መስከረም 9
  • ሰኞ፣ መስከረም 10
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 11
  • ረቡዕ፣ መስከረም 12
  • ሐሙስ፣ መስከረም 13
  • ዓርብ፣ መስከረም 14
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 15
  • እሁድ፣ መስከረም 16
  • ሰኞ፣ መስከረም 17
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 18
  • ረቡዕ፣ መስከረም 19
  • ሐሙስ፣ መስከረም 20
  • ዓርብ፣ መስከረም 21
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 22
  • እሁድ፣ መስከረም 23
  • ሰኞ፣ መስከረም 24
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 25
  • ረቡዕ፣ መስከረም 26
  • ሐሙስ፣ መስከረም 27
  • ዓርብ፣ መስከረም 28
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 29
  • እሁድ፣ መስከረም 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2018
es18 ገጽ 88-97

መስከረም

ቅዳሜ፣ መስከረም 1

ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም።—ያዕ. 1:4

መጽናት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት፣ ፈተናዎችን ወይም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ከመቋቋም የበለጠ ነገርን ለማመልከት ነው። ጽናት ከአስተሳሰባችንና ከስሜታችን ማለትም መከራ ሲደርስብን ከምናደርገው ነገር ጋር የተያያዘ ነው። የሚጸና ሰው ድፍረትና ትዕግሥት እንዳለው እንዲሁም ከአቋሙ ፍንክች እንደማይል ያሳያል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ጽናት “አንድን ነገር ምርጫ ስለሌለን ብቻ መቀበልን ሳይሆን ብሩህ ተስፋ ይዞ የመቻልን መንፈስ ያመለክታል።” ይኸው ጽሑፍ አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ጽናት፣ አንድ ሰው ወደ እሱ የሚነፍሰውን ነፋስ ፊት ለፊት ተጋፍጦ ሳይንገዳገድ እንዲቆም የሚያስችለው ባሕርይ ነው። ከሥቃዩ ባሻገር ያለውን ግብ ለመመልከት ስለሚረዳ ከባዱን መከራ ወደ ክብር መለወጥ የሚያስችል ግሩም ባሕርይ ነው።” ክርስቲያኖች እንዲጸኑ የሚያነሳሳቸው ፍቅር ነው። (1 ቆሮ. 13:4, 7) ለይሖዋ ያለን ፍቅር፣ እሱ የሚፈቅደውን ማንኛውንም ነገር በጽናት እንድንወጣ ያነሳሳናል። (ሉቃስ 22:41, 42) ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር፣ ፍጹማን ባለመሆናቸው ያለባቸውን ድክመት ችለን እንድናልፍ ይረዳናል። (1 ጴጥ. 4:8) ለትዳር ጓደኛችን ያለን ፍቅር ደግሞ ደስተኛ ባለትዳሮች እንኳ የሚያጋጥማቸውን “መከራ” በጽናት እንድናሳልፍና የትዳር ጥምረታችንን እንድናጠናክር ያደርገናል።—1 ቆሮ. 7:28፤ w16.04 2:3, 4

እሁድ፣ መስከረም 2

በአንድ ልብ ሆነው በቤተ መቅደሱ አዘውትረው ይገኙ ነበር።—ሥራ 2:46

“አዘውትረው ይገኙ ነበር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ሐሳብ በአንድ ነገር መጽናትን የሚያመለክት ሲሆን ይህም ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል። በሮም አገዛዝ ሥር ለሚኖሩትና በጊዜው ከነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ተቃውሞ ለሚደርስባቸው ለጥንቶቹ ክርስቲያኖች በስብሰባዎች ላይ መገኘት ቀላል አልነበረም። ያም ቢሆን በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው ይገኙ ነበር። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ጥልቅ አድናቆት እንዳላቸው አሳይተዋል። ከ22 ለሚበልጡ ዓመታት የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም ጆርጅ ጋንጋስ እንዲህ ብሏል፦ “ከወንድሞች ጋር መሰብሰብ ማለት ለእኔ፣ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ደስታና ማበረታቻ ከሚሰጡኝ ነገሮች አንዱ ነው።” አክሎም “የእኔም የዘወትር ሐሳብና ፍላጎት በስብሰባዎች ላይ መገኘት ነው” ብሏል። አንተስ ይሖዋን ለማምለክ አንድ ላይ ስለ መሰብሰብ እንዲህ ይሰማሃል? ከሆነ በስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ ለመገኘት የምታደርገውን ልባዊ ጥረት ግፋበት። በዚህ መንገድ የንጉሥ ዳዊት ዓይነት ስሜት እንዳለህ ታሳያለህ፤ ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ የምትኖርበትን ቤት . . . እወዳለሁ።”—መዝ. 26:8፤ w16.04 3:16-18

ሰኞ፣ መስከረም 3

በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ።—ማቴ. 5:24

አንድ ወንድም፣ አንተ በተናገርከው ወይም ባደረግከው ነገር ቅር እንደተሰኘ ብታውቅ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ከወንድምህ ጋር መነጋገር ይኖርብሃል። ግብህ ምን እንደሆነ አትርሳ። ዓላማህ ወንድምህም ጥፋት እንዳለበት ማሳመን ሳይሆን ስህተትህን አምነህ በመቀበል ሰላም መፍጠር ነው። ከሁሉ በላይ ሊያሳስበን የሚገባው ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ማድረግ ነው። አብርሃምንና የወንድሙ ልጅ የሆነውን ሎጥን እንመልከት። ሁለቱም ሰዎች ከብቶች ነበሯቸው፤ በግጦሽ መሬት ምክንያት ሳይሆን አይቀርም በእረኞቻቸው መካከል ጠብ ተነሳ። ሆኖም አብርሃም የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ሲል፣ ሎጥ ለእሱና ለቤተሰቡ መኖሪያ የሚሆነውን ቦታ መርጦ እንዲወስድ ቅድሚያውን ሰጠው። (ዘፍ. 13:1, 2, 5-9) እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! አብርሃም የራሱን ፍላጎት ወደ ጎን በመተው ሰላም የሚሰፍንበትን መንገድ ፈልጓል። እንዲህ ያለ ደግነት በማሳየቱ ተጎድቷል? በፍጹም። ይህ ሁኔታ ከተፈጠረ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ታላቅ በረከት እንደሚያፈስለት ቃል ገብቶለታል። (ዘፍ. 13:14-17) አምላክ፣ አገልጋዮቹ ከመለኮታዊ መመሪያዎች ጋር የሚስማማ እርምጃ ለመውሰድና አለመግባባቶችን በፍቅር ለመፍታት ጥረት በማድረጋቸው ምክንያት ዘላቂ ጉዳት እንዲደርስባቸው ፈጽሞ አይፈቅድም። w16.05 1:11, 12

ማክሰኞ፣ መስከረም 4

የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ።—ኤፌ. 5:17

ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ቀጥተኛ የሆኑ በርካታ መመሪያዎችን ሰጥቶናል። ለምሳሌ የፆታ ብልግናን፣ የጣዖት አምልኮን፣ ስርቆትንና ስካርን ያወግዛል። (1 ቆሮ. 6:9, 10) በተጨማሪም የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለደቀ መዛሙርቱ የሚከተለውን ከባድ ሆኖም አስደሳች ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው። እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴ. 28:19, 20) በእርግጥም መለኮታዊ ሕጎችና ትእዛዛት ለእኛ ጥበቃ ሆነውልናል! እነዚህን መመሪያዎች መታዘዛችን ለራሳችን ያለን አክብሮት እንዲጨምር፣ ጥሩ ጤንነት እንዲኖረንና ቤተሰባችን ይበልጥ ደስተኛ እንዲሆን አድርጓል። በስብከቱ ሥራ እንድንካፈል የተሰጠንን ትእዛዝ ጨምሮ የይሖዋን መመሪያዎች በሙሉ በታማኝነት መታዘዛችን ከሁሉም በላይ የእሱን ሞገስና በረከት አስገኝቶልናል። w16.05 3:1

ረቡዕ፣ መስከረም 5

አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።—ሮም 12:2

የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንዲመራን ስንፈቅድ እንዲሁም በአምላክ ቃል ውስጥ ከሰፈረው የይሖዋ አመለካከት ጋር የሚስማማ አመለካከት ስናዳብር አስተሳሰባችን፣ ንግግራችንና ድርጊታችን አምላክን የሚያስደስት ይሆናል። (ሉቃስ 11:13፤ ገላ. 5:22, 23) እርግጥ ነው፣ እንዲህ እያደረግንም ቢሆን በድክመቶቻችን ላለመሸነፍ መጠንቀቅ ያስፈልገናል። (ምሳሌ 4:23) መንፈሳዊ እድገትህ አዝጋሚ እንደሆነ ከተሰማህ እንዲህ ያለ እድገት ማድረግ ጊዜ እንደሚወስድ ማስታወስህ ጠቃሚ ነው። መንፈሳዊ ባሕርያትን ማዳበር ቀጣይነት ያለው ሂደት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ምንጊዜም በሕይወታችን ውስጥ ጠቃሚ ለውጦች ለማድረግ እንዲረዳን ስንጥር ትዕግሥተኞች መሆን አለብን። ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚስማማ ነገር ለማድረግ መጀመሪያ ላይ ራሳችንን መገሠጽ ያስፈልገን ይሆናል። ውሎ አድሮ በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን ይሖዋ አምላክን መምሰል ስንችል ግን አምላክን በሚያስደስት መንገድ ማሰብና መመላለስ ይበልጥ ቀላል ሊሆንልን ይችላል።—መዝ. 37:31፤ ምሳሌ 23:12፤ ገላ. 5:16, 17፤ w16.05 4:14, 16

ሐሙስ፣ መስከረም 6

በይሖዋ ሕግ ደስ ይለዋል፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት በለሆሳስ ያነበዋል።—መዝ. 1:2

ይሖዋ በዛሬው ጊዜ አገልጋዮቹን በዋነኝነት የሚቀርጻቸው በቃሉ፣ በመንፈስ ቅዱስና በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲቀርጸን የምንፈልግ ከሆነ፣ ቃሉን በግብ ማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል እንዲሁም ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ እንድንችል ይሖዋ እንዲረዳን መጠየቅ ይኖርብናል። ዳዊት “መኝታዬ ላይ ሆኜ አንተን አስታውሳለሁ፤ ሌሊት ስለ አንተ አሰላስላለሁ” በማለት ጽፏል። (መዝ. 63:6) በተጨማሪም “ምክር የሰጠኝን ይሖዋን አወድሳለሁ። በሌሊትም እንኳ በውስጤ ያለው ሐሳብ ያርመኛል” ሲል ጽፏል። (መዝ. 16:7) በእርግጥም ዳዊት አምላክ የሚሰጠው ምክር ከባድ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ምክሩ ወደ ልቡ ዘልቆ እንዲገባ እንዲሁም ውስጣዊ ሐሳቡንና ስሜቱን እንዲቀርጸው ፈቅዷል። (2 ሳሙ. 12:1-13) ዳዊት ትሑትና ታዛዥ በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል! አንተስ በአምላክ ቃል ላይ በማሰላሰል ምክሩ ወደ ውስጥህ ዘልቆ እንዲገባ ትፈቅዳለህ? በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባህ ይሰማሃል?—መዝ. 1:3፤ w16.06 1:11

ዓርብ፣ መስከረም 7

ለቁጣ አትቸኩል።—መክ. 7:9

የሰው ልጅ ከፍጽምና ከራቀ 6,000 ያህል ዓመታት እንዳለፉ ማስታወስ ይኖርብናል። ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ስህተት መሥራታቸው አይቀርም። በመሆኑም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ብዙ መጠበቅ የለብንም፤ በተጨማሪም እነሱ የሚፈጽሙት ስህተት፣ በዚህ የመጨረሻ ዘመን ካሉት የአምላክ ሕዝቦች መካከል መሆናችን የሚያስገኝልንን ደስታ እንዲያሳጣን መፍቀድ አይኖርብንም። ሌሎች በፈጸሙት ስህተት ተሰናክለን የይሖዋን ድርጅት ብንተው ደግሞ ከዚህ የከፋ ይሆናል። እንዲህ ብናደርግ ይሖዋን የማገልገል መብታችንን ብቻ ሳይሆን አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋችንንም እናጣለን። ደስታችንንና ተስፋችንን ጠብቀን ለመኖር ከፈለግን ይሖዋ የገባውን የሚከተለውን የሚያጽናና ቃል ምንጊዜም ማስታወስ ይኖርብናል፦ “እነሆ፣ አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እየፈጠርኩ ነውና፤ የቀድሞዎቹ ነገሮች አይታሰቡም፤ ወደ ልብም አይገቡም።” (ኢሳ. 65:17፤ 2 ጴጥ. 3:13) ሌሎች የሚፈጽሙት ስህተት ይህን በረከት እንዳታገኝ እንቅፋት እንዲሆንብህ አትፍቀድ! w16.06 4:13, 14

ቅዳሜ፣ መስከረም 8

አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ ነው።—ዘዳ. 6:4

“አንድ” የሚለው ቃል፣ አንድነትን እንዲሁም በዓላማና በድርጊት አንድ መሆንንም ያመለክታል። ይሖዋ በየጊዜው የሚለዋወጥ አምላክ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ታማኝ፣ እምነት የሚጣልበትና እውነተኛ አምላክ ነው። ይሖዋ ለአብርሃም፣ ዘሮቹ ተስፋይቱን ምድር እንደሚወርሱ ቃል የገባለት ሲሆን ይህን ቃሉን ለመጠበቅ አስደናቂ ነገሮችን አከናውኗል። በዚህ መሃል 430 ዓመታት ቢያልፉም ይሖዋ ቃሉን አልለወጠም። (ዘፍ. 12:1, 2, 7፤ ዘፀ. 12:40, 41) ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ምሥክሮቹ እንደሆኑ በተናገረበት ወቅት እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እኔ ምንጊዜም ያው [ነኝ] . . . ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤ ከእኔም በኋላ የለም።” ይሖዋ ዓላማው እንደማይለዋወጥ ለማጉላት ሲል “እኔ ምንጊዜም ያው ነኝ” በማለት አስረግጦ ተናግሯል። (ኢሳ. 43:10, 13፤ 44:6፤ 48:12) በእርግጥም እኛም ሆንን እስራኤላውያን፣ ምንጊዜም የማይለዋወጠውና ታማኝ የሆነው አምላክ አገልጋዮች መሆናችን ምንኛ ታላቅ መብት ነው!—ሚል. 3:6፤ ያዕ. 1:17፤ w16.06 3:6, 7

እሁድ፣ መስከረም 9

የተወሰነው ጊዜ መቼ እንደሆነ ስለማታውቁ ምንጊዜም በንቃት ተከታተሉ፤ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።—ማር. 13:33

በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ አገሮች በወታደሮችና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በሚታገዙ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች አማካኝነት ድንበራቸውን ያስጠብቃሉ። ወታደሮቹ ወደ ክልላቸው ሰርገው የሚገቡ ሰዎችን ወይም ብሔራዊ ደህንነታቸውን ስጋት ላይ የሚጥሉ ጠላቶችን ነቅተው ይጠባበቃሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ጠባቂዎች ማየት የሚችሉት ከሰብዓዊ መንግሥታት ወይም ከሌሎች ሰዎች የሚሰነዘረውን ጥቃት ብቻ ነው። ጠባቂዎቹ በክርስቶስ የሚመራ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት መኖሩን እንዲሁም ይህ መንግሥት የሚያከናውነውን ሥራም ሆነ በቅርቡ በመንግሥታት ሁሉ ላይ የሚወስደውን የፍርድ እርምጃ ማስተዋል አይችሉም። (ኢሳ. 9:6, 7 ግርጌ፤ 56:10፤ ዳን. 2:44) እኛ ግን ምንጊዜም በመንፈሳዊ ንቁ ከሆንን ይህ የፍርድ ቀን ሲመጣ ዝግጁ ሆነን እንገኛለን። (መዝ. 130:6) ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እየተቃረብን ስንመጣ ነቅቶ መጠበቅ ይበልጥ ተፈታታኝ ይሆንብናል። በዚህ ጊዜ እንቅልፍ ቢጥለን እንዴት የሚያሳዝን ይሆናል! w16.07 2:2, 9, 10

ሰኞ፣ መስከረም 10

አምላክ ለእኔ ያሳየው [ጸጋ] ከንቱ ሆኖ አልቀረም።—1 ቆሮ. 15:10

ጳውሎስ ቀደም ሲል ክርስቲያኖችን ያሳድድ ስለነበር፣ አምላክ ለእሱ ያሳየው ታላቅ ምሕረት ይገባኛል የሚለው ነገር እንዳልሆነ አሳምሮ ያውቅ ነበር። ጳውሎስ በሕይወቱ መገባደጃ ላይ አብሮት ለሚያገለግለው ለጢሞቴዎስ እንደሚከተለው በማለት ጽፎለታል፦ “ለአገልግሎቱ በመሾም ታማኝ አድርጎ ስለቆጠረኝ ኃይል የሰጠኝን ጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስን አመሰግናለሁ።” (1 ጢሞ. 1:12-14) ይህ አገልግሎት ምን ነበር? ጳውሎስ በኤፌሶን ጉባኤ ለነበሩት ሽማግሌዎች ይህ አገልግሎት ምን እንደሚያካትት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ሩጫዬን እስካጠናቀቅኩ እንዲሁም ስለ አምላክ ጸጋ የሚገልጸውን ምሥራች በተሟላ ሁኔታ በመመሥከር ከጌታ ኢየሱስ የተቀበልኩትን አገልግሎት እስከፈጸምኩ ድረስ ሕይወቴ ምንም አያሳሳኝም።” (ሥራ 20:24) ጳውሎስ አገልግሎቱን ሲያከናውን የነበረው ቅንዓት በአሁኑ ጊዜ ላለን ክርስቲያኖች ግሩም አርዓያ ከመሆኑም ሌላ አምላክ ለእሱ ያሳየው ጸጋ “ከንቱ” ሆኖ እንዳልቀረ አሳይቷል። w16.07 4:1-3

ማክሰኞ፣ መስከረም 11

[አምላክን] በትዕግሥት እጠብቃለሁ።—ሚክ. 7:7

ይሖዋ፣ ታማኝ አገልጋዮቹ አንዳንድ መብቶችን እስኪያገኙ አሊያም ደግሞ ያሉበት ሁኔታ እስኪስተካከልላቸው ድረስ የተወሰነ ጊዜ እንዲያልፍ ሊፈቅድ ቢችልም ምንጊዜም እነሱን ከመደገፍ ወደኋላ አይልም። ይሖዋ፣ ለአብርሃም ወንድ ልጅ እንደሚሰጠው ቃል ቢገባለትም ይህ የአምላክ አገልጋይ በእምነትና በትዕግሥት መጠበቅ አስፈልጎታል። (ዕብ. 6:12-15) ይስሐቅ እስኪወለድ ድረስ ዓመታት ቢያልፉም አብርሃም ተስፋ አልቆረጠም፤ ይሖዋም አላሳፈረውም። (ዘፍ. 15:3, 4፤ 21:5) እርግጥ ነው፣ በትዕግሥት መጠበቅ ቀላል አይደለም። (ምሳሌ 13:12) የጠበቅነው ነገር አለመሳካቱን እያሰብን የምንብሰለሰል ከሆነ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። ከዚህ ይልቅ ጊዜያችንን መንፈሳዊ ብቃቶችን ለማዳበር ብንጠቀምበት ጥበብ ይሆናል። የአምላክን ቃል በማንበብና ባነበብነው ላይ በማሰላሰል ጥበብን፣ ጥልቅ ማስተዋልን፣ እውቀትን፣ የማመዛዘን ችሎታንና ጤናማ አስተሳሰብን ማዳበር እንችላለን። መዝናኛን፣ አለባበስንና አጋጌጥን፣ የገንዘብ አያያዝን እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት በተመለከተ ውሳኔ የሚጠይቁ ነገሮች በየዕለቱ ያጋጥሙናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርነውን ነገር በተግባር በማዋል ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን ማድረግ እንችላለን። w16.08 3:9-11

ረቡዕ፣ መስከረም 12

ኃይል የሚሰጣችሁ አምላክ ነው።—ፊልጵ. 2:13

ይሖዋ፣ አማሌቃውያንን እና ኢትዮጵያውያንን ድል እንዲያደርጉ እስራኤላውያንን ረድቷቸዋል፤ ለነህምያና አብረውት ለነበሩት አይሁዳውያንም የከተማዋን ቅጥር እንደገና ገንብተው ለማጠናቀቅ የሚያስችል ኃይል ሰጥቷቸዋል። ዛሬም በተመሳሳይ የሚያጋጥመንን ተቃውሞ፣ የሰዎችን ግዴለሽነትና ያለብንን ጭንቀት ተቋቁመን የስብከቱን ሥራ ማከናወን እንድንችል ብርታት ይሰጠናል። (1 ጴጥ. 5:10) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ተአምር ይፈጽምልናል ብለን መጠበቅ የለብንም። ከዚህ ይልቅ እኛ የበኩላችንን ማድረግ ይኖርብናል። ይህም የአምላክን ቃል በየዕለቱ ማንበብን፣ ለሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን መዘጋጀትንና በስብሰባዎች ላይ መገኘትን፣ በግል ጥናትና በቤተሰብ አምልኮ አማካኝነት በመንፈሳዊ ራሳችንን መመገብን እንዲሁም በይሖዋ በመታመን አዘውትረን ወደ እሱ መጸለይን ይጨምራል። ሌሎች እንቅስቃሴዎች፣ ይሖዋ እኛን ለማበርታትና ለማጠናከር ባደረጋቸው ዝግጅቶች እንዳንጠቀም እንቅፋት እንዲሆኑብን ፈጽሞ መፍቀድ አይኖርብንም። ከላይ ከተጠቀሰው ከየትኛውም ዝግጅት ጋር በተያያዘ እጃችሁ እንደዛለ ከተሰማችሁ አምላክ እንዲረዳችሁ ጸልዩ። ከዚያም መንፈሱ “ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ለተግባር እንድትነሳሱ በማድረግ ኃይል የሚሰጣችሁ” እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክሩ። w16.09 1:12

ሐሙስ፣ መስከረም 13

የፆታ ብልግና ስለተስፋፋ እያንዳንዱ ወንድ የራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዷም ሴት የራሷ ባል ይኑራት።—1 ቆሮ. 7:2

ሐዋርያው ጳውሎስ የነጠላነት ሕይወትን ያበረታታ ቢሆንም ከላይ ያለውን ተናግሯል። አክሎም “ራሳቸውን መግዛት ካቃታቸው . . . ያግቡ፤ በፍትወት ከመቃጠል ማግባት ይሻላልና” ብሏል። አንድ ሰው ትዳር መመሥረቱ፣ እንደ ማስተርቤሽን ወይም እንደ ፆታ ብልግና ያሉ ድርጊቶችን ከመፈጸም እንዲርቅ ሊረዳው ይችላል። እርግጥ ነው፣ ያላገቡ ሰዎች ዕድሜያቸው ለትዳር መድረሱን ሊያስቡበት ይገባል፤ ሐዋርያው እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ሰው ሳያገባ ቀርቶ ራሱን መቆጣጠር እንደተሳነው ከተሰማው፣ በተለይ ደግሞ አፍላ የጉርምስና ዕድሜን ያለፈ ከሆነና ማግባቱ የሚመረጥ ከሆነ የፈለገውን ያድርግ፤ ኃጢአት አይሆንበትም። እንዲህ ያሉ ሰዎች ያግቡ።” (1 ቆሮ. 7:9, 36፤ 1 ጢሞ. 4:1-3) አንድ ሰው በወጣትነት ዕድሜ በሚኖረው ከፍተኛ የፆታ ስሜት ተገፋፍቶ ለማግባት መወሰን የለበትም። ምክንያቱም እንዲህ ያለው ሰው፣ ትዳር የሚያስከትለውን ኃላፊነት ለመሸከም የሚያስፈልገው ብስለት ላይኖረው ይችላል። w16.08 1:17

ዓርብ፣ መስከረም 14

በሁሉም ነገር ራሳችንን ብቁ የአምላክ አገልጋዮች አድርገን እናቀርባለን።—2 ቆሮ. 6:4

ብዙ ሰዎች እኛን የሚመዝኑን ‘ውጫዊ ገጽታችንን’ ተመልክተው ነው። (1 ሳሙ. 16:7) በመሆኑም የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ለእኛ የሚመቸንንና የምንወደውን ነገር ከመልበስ ባለፈ ልናስብበት የሚገባ ነገር አለ። በአምላክ ቃል ውስጥ የሰፈሩት መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ ሰውነት ላይ የሚጣበቅና ገላን የሚያጋልጥ ወይም የፆታ ስሜት የሚያነሳሳ ልብስ ከመልበስ እንድንቆጠብ ይገፋፉናል። ይህም ሲባል እርቃንን የሚያጋልጡ ወይም የሰውነትን ቅርጽ አጉልተው የሚያሳዩ ልብሶችን ማስወገድ አለብን ማለት ነው። አለባበሳችን ሌሎችን የሚያሸማቅቅ ወይም ዓይናቸውን የት እንደሚያሳርፉ እንዲጨንቃቸው የሚያደርግ መሆን የለበትም። ሥርዓታማ፣ ንጹሕና ልከኛ አለባበስ ካለን ሰዎች ያከብሩናል፤ እንዲሁም ወደምናመልከው አምላክ ለመቅረብ ይነሳሳሉ። ተገቢ የሆነ አለባበስ ለይሖዋ ድርጅትም ክብር ያመጣል። ይህም ሰዎች ለምንነግራቸው ሕይወት አድን መልእክት ጆሮ እንዲሰጡ ሊያደርግ ይችላል። w16.09 3:5, 6

ቅዳሜ፣ መስከረም 15

ለሰው ሁሉ ገርነትን በተሟላ ሁኔታ እንዲያንጸባርቁ አሳስባቸው።—ቲቶ 3:2

የምታነጋግሩት ሰው ምን ብሎ እንደሚያምን እንደምታውቁ አድርጋችሁ አታስቡ። አንዳንዶች በዝግመተ ለውጥ እንደሚያምኑ ቢናገሩም አምላክ እንዳለም ያስባሉ። አምላክ፣ ሕይወት ያላቸውን የተለያዩ ነገሮች ለመፍጠር ዝግመተ ለውጥን እንደተጠቀመ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ በዝግመተ ለውጥ እንደሚያምኑ የሚናገሩት ‘ይህ ጽንሰ ሐሳብ እውነት ባይሆን ኖሮ በትምህርት ቤት አንማረውም ነበር’ ብለው ስለሚያስቡ ነው። አንዳንዶች በአምላክ ማመን ያቆሙት በሃይማኖት ውስጥ የሚፈጸመው ነገር ቅር ስላሰኛቸው ነው። በመሆኑም ስለ ሕይወት አመጣጥ ከአንድ ሰው ጋር ስትወያዩ በቅድሚያ ጥያቄ መጠየቁ የተሻለ ነው። ግለሰቡ ምን ብሎ እንደሚያምን ለማወቅ ጥረት አድርጉ። ምክንያታዊ ብሎም ለማዳመጥ ፈቃደኛ ከሆናችሁ ግለሰቡም እናንተ የምትናገሩትን ለማዳመጥ ሊነሳሳ ይችላል። አንድ ሰው በፍጥረት በማመናችሁ እየተቻችሁ እንዳለ ከተሰማችሁ፣ ፈጣሪ ሳይኖር ሕይወት እንዴት ሊገኝ እንደቻለ እንዲያስረዳችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። የመጀመሪያው ሕይወት ያለው ነገር በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ወደ ሌላ ሕያው ነገር መለወጥ እንዲችል መራባት ማለትም ራሱን ማባዛት መቻል አለበት። አንድ የኬሚስትሪ ፕሮፌሰር እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ሰው፣ ሕይወት ካላቸው ነገሮች መካከል ውስብስብ የማይባለው እንኳ ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ ሲመለከት በጣም መገረሙ አይቀርም።” w16.09 4:12, 13

እሁድ፣ መስከረም 16

ቤዛ ተከፍሎላቸው ነፃ መሆን [አልፈለጉም]፤ ይህን ያደረጉት የተሻለ ትንሣኤ ለማግኘት ሲሉ ነው።—ዕብ. 11:35

ጳውሎስ ይህን የተናገረው እነማንን በአእምሮው ይዞ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ባንችልም አምላክን በመታዘዛቸውና የእሱን ፈቃድ በመፈጸማቸው በድንጋይ ተወግረው ስለሞቱት ስለ ናቡቴ እና ስለ ዘካርያስ መናገሩ ሊሆን ይችላል። (1 ነገ. 21:3, 15፤ 2 ዜና 24:20, 21) ዳንኤልና ጓደኞቹም ንጹሕ አቋማቸውን ቢያላሉ “ነፃ መሆን” የሚችሉበት አጋጣሚ ነበራቸው። እነዚህ ወጣቶች በአምላክ ኃይል ላይ እምነት ስለነበራቸው “የአንበሶችን አፍ ዘግተዋል” እንዲሁም “የእሳትን ኃይል አጥፍተዋል” ሊባልላቸው ችሏል። (ዕብ. 11:33, 34፤ ዳን. 3:16-18, 20, 28፤ 6:13, 16, 21-23) እንደ ሚካያህ እና ኤርምያስ ያሉት ነቢያት ‘መዘባበቻ በመሆንና ወህኒ ቤት በመጣል ፈተና ቢደርስባቸውም’ እምነት ስለነበራቸው ተቋቁመውታል። እንደ ኤልያስ ያሉ ሌሎች ደግሞ “በየበረሃው፣ በየተራራው፣ በየዋሻውና በምድር ውስጥ ባሉ ጉድጓዶች ተቅበዝብዘዋል።” ሁሉም መጽናት የቻሉት “ተስፋ የተደረጉትን ነገሮች በእርግጠኝነት [ይጠብቁ]” ስለነበር ነው።—ዕብ. 11:1, 36-38፤ 1 ነገ. 18:13፤ 22:24-27፤ ኤር. 20:1, 2፤ 28:10, 11፤ 32:2፤ w16.10 3:10, 11

ሰኞ፣ መስከረም 17

ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ።—ፊልጵ. 2:3

የውጭ አገር ሰዎች ወደ መንግሥት አዳራሻችን መጀመሪያ ሲመጡ ሞቅ አድርገን በመቀበል ደግነት ልናሳያቸው እንችላለን። እኛ ወደምንኖርበት አገር በቅርቡ የመጡ የሌላ አገር ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ዓይናፋርነት እንደሚታይባቸውና ከሌሎች ጋር መቀላቀል እንደሚከብዳቸው አስተውለን ይሆናል። በአስተዳደጋቸው ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ቦታ የተነሳ ሌላ ዘር ወይም ዜግነት ካላቸው ሰዎች እንደሚያንሱ ሊሰማቸው ይችላል። በመሆኑም ቅድሚያውን ወስደን ሞቅ አድርገን ልንቀበላቸውና ልባዊ አሳቢነት ልናሳያቸው ይገባል። JW Language (ጄ ደብልዩ ላንግዌጅ) የተባለው አፕሊኬሽን በቋንቋህ የሚገኝ ከሆነ ከሌላ አገር ለመጡ ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሰላምታ ለመስጠት ይረዳሃል። (ፊልጵ. 2:4) ከአንተ የተለየ ባሕል ካላቸው ሰዎች ጋር መጨዋወት ይከብድህ ይሆናል። እንዲህ ያለውን ስሜት ለማሸነፍ ስለ ራስህ አንዳንድ ነገሮች ልትነግራቸው ትችላለህ። ይህን ስታደርግ ከልዩነቶቻችሁ ይልቅ የሚያመሳስሏችሁ ነገሮች እንደሚበዙ ትገነዘብ ይሆናል፤ በተጨማሪም እያንዳንዱ ባሕል የራሱ የሆነ ጥሩም ሆነ መጥፎ ጎን እንዳለው ትረዳለህ። w16.10 1:13, 14

ማክሰኞ፣ መስከረም 18

በመካከላችሁ ዝሙት እንደተፈጸመ ይወራል፤ እንዲህ ዓይነቱ ዝሙት ደግሞ በአሕዛብ መካከል እንኳ ታይቶ አይታወቅም።—1 ቆሮ. 5:1

በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መመሪያ በመከተል ለጉባኤው መንፈሳዊ ንጽሕና የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን። በጥንቷ ቆሮንቶስ የነበረውን ሁኔታ እንመልከት። ጳውሎስ በዚህች ከተማ ራሱን ሳይቆጥብ ሰብኳል፤ እንዲሁም በዚያ የሚኖሩትን “ቅዱሳን” ይወዳቸው ነበር። (1 ቆሮ. 1:1, 2) በመሆኑም በዚያ በነበረው ጉባኤ ውስጥ በቸልታ የታለፈውን የፆታ ብልግና አስመልክቶ ሲጽፍ ምንኛ አዝኖ ይሆን! ጳውሎስ፣ ሽማግሌዎቹ የፆታ ብልግና የፈጸመውን ሰው ለሰይጣን አሳልፈው እንዲሰጡት በሌላ አባባል እንዲያስወግዱት መመሪያ ሰጠ። የጉባኤውን ንጽሕና ለመጠበቅ ከፈለጉ በመካከላቸው የነበረውን “እርሾ” ማጽዳት ነበረባቸው። (1 ቆሮ. 5:5-7, 12) እኛም ሽማግሌዎች ንስሐ የማይገባ ኃጢአተኛን ለማስወገድ ያደረጉትን ውሳኔ ስንደግፍ የጉባኤው ንጽሕና እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ እናደርጋለን፤ በተጨማሪም እንዲህ ማድረጋችን ግለሰቡ ንስሐ እንዲገባና የይሖዋን ይቅርታ እንዲፈልግ ያነሳሳው ይሆናል። w16.11 2:14

ረቡዕ፣ መስከረም 19

ሕዝቡን የሚያበረታታ የምትናገሩት ቃል ካላችሁ ተናገሩ።—ሥራ 13:15

ማበረታቻ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። ሩቤን የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “አልረባም ከሚል ስሜት ጋር ለበርካታ ዓመታት ስታገል ኖሬያለሁ። አንድ ቀን፣ የጉባኤ ሽማግሌ ከሆነ አንድ ወንድም ጋር እያገለገልኩ ሳለ ወንድም እንደከፋኝ አስተዋለ። ምን እንደሚሰማኝ ስነግረው ርኅራኄ በሚንጸባረቅበት መንገድ አዳመጠኝ። ከዚያም እያከናወንኩ ያለሁትን መልካም ነገር ጠቀሰልኝ። በተጨማሪም እያንዳንዳችን ከብዙ ድንቢጦች እንደምንበልጥ ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ አስታወሰኝ። ይህ ጥቅስ ብዙ ጊዜ ወደ አእምሮዬ የሚመጣ ሲሆን ባስታወስኩት ቁጥር ልቤ ይነካል። ወንድም የተናገረው ነገር በአመለካከቴ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።” (ማቴ. 10:31) መጽሐፍ ቅዱስ አዘውትሮ ማበረታቻ የመስጠትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የሚገልጽ መሆኑ ሊያስገርመን አይገባም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ከእናንተ መካከል አንዳችሁም ኃጢአት ባለው የማታለል ኃይል እንዳትደነድኑ . . . በየዕለቱ እርስ በርሳችሁ ተበረታቱ።” (ዕብ. 3:13) አንድ ሰው በተናገረው ሐሳብ መንፈሳችሁ የታደሰበትን ጊዜ ታስታውሳላችሁ? ከሆነ እርስ በርስ እንድንበረታታ የተሰጠን ትእዛዝ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘባችሁ አይቀርም። w16.11 1:2, 3

ሐሙስ፣ መስከረም 20

ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች ይነሳሉ።—ሥራ 20:30

በ313 ዓ.ም. አረማዊው ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ለክህደት ክርስትና ሕጋዊ እውቅና ሰጠው። የኒቂያ ጉባኤ ከተካሄደ በኋላ በጉባኤው ላይ ተገኝቶ የነበረው ቆስጠንጢኖስ፣ ‘ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው’ የሚለውን ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነውን አርዮስ የተባለ ቄስ በግዞት እንዲቀመጥ አድርጎታል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ በቀዳማዊ ንጉሥ ቲዮዶሸስ (379-395 ዓ.ም.) የግዛት ዘመን፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን (ለክህደት ክርስትና የተሰጠው መጠሪያ) ሮም ውስጥ የመንግሥት ሃይማኖት ሆነ። የታሪክ ምሁራን፣ አረማዊ የነበረው የሮም መንግሥት በአራተኛው መቶ ዘመን “ክርስትናን” እንደተቀበለ ይናገራሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በዚህ ወቅት የክህደት ክርስትና፣ በሮም ግዛት ሥር ከነበሩት የአረማውያን ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ጋር በመዋሃድ የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል ሆኖ ነበር። በስንዴ የተመሰሉት ጥቂት ቁጥር ያላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች በወቅቱ አምላክን ለማገልገል የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነበር።—ማቴ. 13:24, 25, 37-39፤ w16.11 4:8, 9

ዓርብ፣ መስከረም 21

የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ [በይሖዋ] ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።—1 ጴጥ. 5:7

የምንኖረው በጣም አስጨናቂ በሆነ ዘመን ውስጥ ነው። በቁጣ የተሞላው ሰይጣን ዲያብሎስ “የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል።” (1 ጴጥ. 5:8፤ ራእይ 12:17) በመሆኑም የአምላክ አገልጋዮችም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ጭንቀት ቢሰማቸው የሚያስገርም አይደለም። እንደ ንጉሥ ዳዊት ያሉ በጥንት ጊዜ የኖሩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው የይሖዋ አገልጋዮች ‘በጭንቀት የተዋጡበት’ ወቅት ነበር። (መዝ. 13:2) ሐዋርያው ጳውሎስም “የሚያስጨንቀኝ የጉባኤዎች ሁሉ ሐሳብ ነው” እንዳለ ታስታውስ ይሆናል። (2 ቆሮ. 11:28) ታዲያ በጭንቀት ስንዋጥ ምን ማድረግ እንችላለን? በሰማይ የሚኖረው አፍቃሪ አባታችን፣ በጥንት ዘመን የኖሩ አገልጋዮቹን ረድቷቸዋል፤ እኛም በጭንቀት በምንዋጥበት ወይም በምንረበሽበት ጊዜ ሊያሳርፈን ይችላል። የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት (1) ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረብ፣ (2) የአምላክን ቃል ማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል፣ (3) ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን መጠየቅ፣ (4) ጭንቀታችንን ለምንቀርበው ሰው ማካፈል ይኖርብናል። w16.12 3:1, 2

ቅዳሜ፣ መስከረም 22

የእነዚህ ነገሮች መጨረሻ ሞት ነው።—ሮም 6:21

የይሖዋ ሕዝቦች ስለ አምላክ ከማወቃቸው፣ ለእሱ ፍቅር ከማዳበራቸውና እሱን ማገልገል ከመጀመራቸው በፊት ‘ያፈሯቸው የነበሩትን ፍሬዎች’ አስወግደዋል። ቀድሞ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን ‘አሁን ያፍሩባቸዋል’፤ ደግሞም “የእነዚህ ነገሮች መጨረሻ ሞት ነው።” (ሮም 6:21) ይሖዋን ሲያውቁ ግን አኗኗራቸውን ቀየሩ። ጳውሎስ ደብዳቤውን ከጻፈላቸው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ብዙዎቹ እንዲህ ዓይነት ሕይወት ነበራቸው። አንዳንዶቹ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ግብረ ሰዶማውያን፣ ሌቦች፣ ሰካራሞች እና እንደነዚህ ያሉትን ኃጢአቶች የሚፈጽሙ ሰዎች ነበሩ። ይሁንና ‘ታጥበው ነጽተዋል’ እንዲሁም ‘ተቀድሰዋል።’ (1 ቆሮ. 6:9-11) የሮም ጉባኤ አባላት የሆኑ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሁኔታም ተመሳሳይ ነበር። ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል፦ “ሰውነታችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፤ ከዚህ ይልቅ ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ሰውነታችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለአምላክ አቅርቡ።” (ሮም 6:13) ጳውሎስ፣ እነዚህ ክርስቲያኖች ምንጊዜም መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን ከጠበቁ ከአምላክ ጸጋ ጥቅም ማግኘታቸውን መቀጠል እንደሚችሉ እርግጠኛ ነበር። w16.12 1:13

እሁድ፣ መስከረም 23

በይሖዋ ታመን።—መዝ. 37:3

ይሖዋ፣ የሰው ልጆችን የፈጠረው አስደናቂ ችሎታዎች እንዲኖሯቸው አድርጎ ነው። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማቀድና ለችግሮቻችን መፍትሔ ማበጀት እንድንችል የማመዛዘን ችሎታ ሰጥቶናል። (ምሳሌ 2:11) ደግሞም ያቀድነውን ነገር ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል ስለሰጠን ግባችን ላይ መድረስ እንችላለን። (ፊልጵ. 2:13) በተጨማሪም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት የምንችልበት ሕሊና ሰጥቶናል፤ ይህ በተፈጥሮ ያገኘነው ችሎታ ከመጥፎ ድርጊቶች እንድንርቅ እንዲሁም የሠራናቸውን ስህተቶች እንድናርም ይረዳናል። (ሮም 2:15) ይሖዋ፣ ችሎታዎቻችንን መልካም ነገር ለማድረግ ልንጠቀምባቸው እንደሚገባ በቃሉ አማካኝነት በተደጋጋሚ አሳስቦናል። ለምሳሌ ያህል፣ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚከተሉት ሐሳቦች ይገኛሉ፦ “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል” እንዲሁም “እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኃይልህ አከናውን።” (ምሳሌ 21:5፤ መክ. 9:10) በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ደግሞ “አጋጣሚ እስካገኘን ድረስ ለሁሉም . . . መልካም እናድርግ” እንዲሁም “እያንዳንዳችሁ በተቀበላችሁት ስጦታ መሠረት የተሰጣችሁን ስጦታ አንዳችሁ ሌላውን ለማገልገል ተጠቀሙበት” የሚሉ ምክሮች ይገኛሉ። (ገላ. 6:10፤ 1 ጴጥ. 4:10) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ይሖዋ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን የሚጠቅም ነገር እንድናደርግ ይፈልጋል። w17.01 1:1, 2

ሰኞ፣ መስከረም 24

እነዚህ ነገሮች ምሳሌ ይሆኑ ዘንድ በእነሱ ላይ ደረሱ፤ የተጻፉትም የሥርዓቶቹ ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅ ነው።—1 ቆሮ. 10:11

የአዳምና የሔዋን ዘሮች ታዛዥ ሳይሆኑ ከቀሩት ወላጆቻቸው አለፍጽምናንና ሞትን ወርሰዋል። ሆኖም የመምረጥ ነፃነታቸውን አላጡም። አምላክ የእስራኤልን ብሔር የያዘበት መንገድ ይህን ያሳያል። ይሖዋ፣ እስራኤላውያን የእሱ ልዩ ንብረት ለመሆን ወይም ላለመሆን መምረጥ እንደሚችሉ በአገልጋዩ በሙሴ አማካኝነት ገልጾላቸው ነበር። (ዘፀ. 19:3-6) ታዲያ እስራኤላውያን ምን ምላሽ ሰጡ? በአንድ ድምፅ “ይሖዋ የተናገረውን ሁሉ ለመፈጸም ፈቃደኞች ነን” በማለት ለስሙ የተመረጠ ሕዝብ መሆን የሚያስከትለውን ኃላፊነት ለመቀበል መረጡ። (ዘፀ. 19:8) ከጊዜ በኋላ ግን፣ የመምረጥ ነፃነታቸውን ያለአግባብ በመጠቀም የገቡትን ቃል አፈረሱ። ከዚህ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን፤ ከይሖዋ ጋር ተጣብቀን በመኖርና የጽድቅ መሥፈርቶቹን በመታዘዝ የመምረጥ ነፃነታችንን ምንጊዜም በአድናቆት እንደምንመለከት እናሳይ። w17.01 2:9

ማክሰኞ፣ መስከረም 25

ልክህን አውቀህ ከአምላክህ ጋር [ሂድ]!—ሚክ. 6:8

ኢዮርብዓም ንጉሥ በነበረበት ዘመን ይሖዋ ለዚህ ከሃዲ ንጉሥ ከባድ የፍርድ መልእክት እንዲያስተላልፍ አንድ ነቢይ ከይሁዳ ላከ። ትሑት የነበረው ይህ ነቢይ የይሖዋን መልእክት በታማኝነት ያደረሰ ሲሆን ይሖዋም አገልጋዩን ከንጉሡ አስፈሪ ቁጣ ጠብቆታል። (1 ነገ. 13:1-10) ነቢዩ ወደ ቤቱ ሲመለስ በቤቴል አቅራቢያ ከሚኖር አንድ አረጋዊ ሰው ጋር በድንገት ተገናኘ። አረጋዊው ሰው የይሖዋ ነቢይ እንደሆነ ተናገረ። ሰውዬው፣ ወጣቱን ነቢይ በማታለል በእስራኤል ‘ምግብ እንዳይበላና ውኃ እንዳይጠጣ’ እንዲሁም ‘በመጣበት መንገድ እንዳይመለስ’ ይሖዋ የሰጠውን ግልጽ መመሪያ እንዲጥስ አደረገው። ይሖዋ በዚህ አልተደሰተም። ይህ የይሖዋ ነቢይ ወደ ቤቱ ሲመለስ አንድ አንበሳ መንገድ ላይ አገኘውና ገደለው። (1 ነገ. 13:11-24) በአንድ ወቅት ልኩን ያውቅ የነበረው ይህ ነቢይ የዚያን አታላይ አረጋዊ ቃል በመስማት እንዲህ ያለ የእብሪት እርምጃ የወሰደው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረው ነገር የለም። ሆኖም ይህ ነቢይ ‘ልኩን አውቆ ከአምላክ ጋር መሄድ’ እንዳለበት ጨርሶ የዘነጋ ይመስላል። w17.01 4:1-3

ረቡዕ፣ መስከረም 26

ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም እፈጽመዋለሁ። ይህን ለማድረግ አስቤአለሁ፤ አደርገዋለሁም።—ኢሳ. 46:11

“በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ።” በመጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ላይ የሰፈሩት እነዚህ ቃላት ትልቅ ትርጉም ያዘሉ ናቸው። (ዘፍ. 1:1) በእርግጥ አምላክ ስለፈጠራቸው ነገሮች ያለን እውቀት ውስን ነው፤ እንደ ጠፈር፣ ብርሃን እና የስበት ኃይል ያሉትን ነገሮች በዚህ ረገድ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፤ ከአጽናፈ ዓለም ጋር በተያያዘም ቢሆን ማየት የቻልነው በጣም ትንሹን ክፍል እንደሆነ የታወቀ ነው። (መክ. 3:11) ያም ቢሆን ይሖዋ፣ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ገልጾልናል። ዓላማው፣ ምድር በእሱ አምሳል ለተፈጠሩ ሰዎች ተስማሚ መኖሪያ እንድትሆን ነበር። (ዘፍ. 1:26) የይሖዋ ዓላማ እነዚህ ሰዎች ልጆቹ እንዲሆኑ፣ እሱ ደግሞ አባታቸው እንዲሆን ነበር። ሆኖም በዘፍጥረት ምዕራፍ ሦስት ላይ እንደተገለጸው የይሖዋን ዓላማ ሊያስተጓጉል የሚችል ነገር ተፈጠረ። (ዘፍ. 3:1-7) የተፈጠረው ሁኔታ ግን ሊስተካከል የማይችል አይደለም። ይሖዋ ዓላማውን እንዳይፈጽም ሊያግደው የሚችል የለም። (ኢሳ. 46:10፤ 55:11) በመሆኑም ይሖዋ መጀመሪያ ላይ የነበረው ዓላማ እሱ ባሰበው ጊዜ እንደሚፈጸም እርግጠኞች መሆን እንችላለን! w17.02 1:1, 2

ሐሙስ፣ መስከረም 27

[በሙሴ] ውስጥ ቅዱስ መንፈሱን ያኖረው . . . የት አለ?—ኢሳ. 63:11

መንፈስ ቅዱስ የማይታይ ኃይል ከመሆኑ አንጻር እስራኤላውያን በሙሴ ላይ እየሠራ ያለው የአምላክ መንፈስ መሆኑን ማወቅ የሚችሉት እንዴት ነበር? መንፈስ ቅዱስ፣ ሙሴ ተአምራትን እንዲፈጽምና የአምላክን ስም ለፈርዖን እንዲያሳውቅ ረድቶታል። (ዘፀ. 7:1-3) በተጨማሪም ሙሴ እንደ ፍቅር፣ የዋህነትና ትዕግሥት ያሉትን ግሩም ባሕርያት እንዲያፈራ መንፈስ ቅዱስ ረድቶታል፤ እነዚህ ባሕርያት ደግሞ እስራኤላውያንን ለመምራት ብቁ እንዲሆን አስችለውታል። ይሖዋ ሕዝቡን እንዲመራ ሙሴን እንደመረጠው በግልጽ ማየት ይቻል ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ይሖዋ ሕዝቡን እንዲመሩ ለሾማቸው ሌሎች ሰዎች በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ኃይል ሰጥቷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “የነዌ ልጅ ኢያሱ . . . የጥበብ መንፈስ ተሞልቶ ነበር።” (ዘዳ. 34:9) “የይሖዋም መንፈስ በጌድዮን ላይ ወረደ።” (መሳ. 6:34) እንዲሁም “የይሖዋ መንፈስ ለዳዊት ኃይል ሰጠው።” (1 ሳሙ. 16:13) እነዚህን ሰዎች የረዳቸው መንፈስ ቅዱስ ሲሆን ይህ መንፈስ በራሳቸው ሊያከናውኑ የማይችሉትን አስደናቂ ነገር መሥራት እንዲችሉ ኃይል ሰጥቷቸዋል።—ኢያሱ 11:16, 17፤ መሳ. 7:7, 22፤ 1 ሳሙ. 17:37, 50፤ w17.02 3:3-5

ዓርብ፣ መስከረም 28

ጸንታችሁ የቆማችሁት በራሳችሁ እምነት ስለሆነ እኛ ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን እንጂ በእምነታችሁ ላይ የምናዝ አይደለንም።—2 ቆሮ. 1:24

ሁላችንም ጳውሎስ ከተወው ጥሩ ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን፤ ጳውሎስ፣ ወንድሞቹ የራሳቸውን ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳላቸው በመገንዘብ ይህን መብታቸውን አክብሮላቸዋል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችም ከግል ምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ ምክር ሲሰጡ የእሱን ምሳሌ ሊከተሉ ይገባል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መመሪያዎችን ለመንጋው አባላት ለማካፈል ፈቃደኞች ናቸው። ያም ሆኖ ሽማግሌዎች፣ ውሳኔ የማድረጉን ኃላፊነት ለእያንዳንዱ ግለሰብ መተው ይኖርባቸዋል። እንዲህ ማድረጋቸው ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ውሳኔው የሚያስከትለውን ውጤት የሚቀበለው ራሱ ነው። በመሆኑም ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የምናገኘው አንድ ጠቃሚ ትምህርት አለ፦ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን ወይም ምክሮችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ሌሎችን ልንረዳቸው እንችላለን። ያም ሆኖ ሌሎች የራሳቸውን ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳላቸው እንዲሁም ይህ የእነሱ ኃላፊነት እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። እነዚህ ሰዎች ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ሲያደርጉ እንደሚጠቀሙ ጥርጥር የለውም። በግልጽ ለመረዳት እንደምንችለው፣ ለሌሎች ወንድሞችና እህቶች ውሳኔ የማድረግ ሥልጣን እንዳለን አድርገን ፈጽሞ ልናስብ አይገባም። w17.03 2:11

ቅዳሜ፣ መስከረም 29

በመካከላችሁ ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ።—ዕብ. 13:17

ታማኙ ባሪያ የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት በማስፋፋትና በማዳረስ ታላቅ እምነት እንዳለው አሳይቷል። አንተስ በዚህ አስፈላጊ ሥራ በመካፈል ቅቡዓኑን እየደገፍክ ነው? ከሆነ መሪያችን ኢየሱስ “ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል” ብሎ በሚናገርበት ጊዜ እንደምትደሰት ጥርጥር የለውም። (ማቴ. 25:34-40) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲመለስ ተከታዮቹን አልረሳቸውም። (ማቴ. 28:20) ምድር ላይ ሆኖ አመራር ይሰጥ በነበረበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ፣ መላእክትና የአምላክ ቃል ምን ያህል እንደረዱት ያውቃል። በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ታማኙን ባሪያ በእነዚህ ሦስት መንገዶች እየረዳው ነው። የዚህ ባሪያ አባላት የሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ምንጊዜም በጉ በሄደበት ሁሉ ይከተሉታል።” (ራእይ 14:4) እኛም የእነሱን መመሪያ ከተከተልን መሪያችን የሆነውን ኢየሱስን እየተከተልን ነው። በቅርቡ ደግሞ በእሱ አመራር ሥር የዘላለም ሕይወት እናገኛለን። (ራእይ 7:14-17) የትኛውም ሰብዓዊ መሪ እንዲህ ዓይነት ተስፋ ሊሰጠን አይችልም! w17.02 4:17-19

እሁድ፣ መስከረም 30

መንገድህን ለይሖዋ አደራ ስጥ፤ በእሱ ታመን፤ እሱም ለአንተ ሲል እርምጃ ይወስዳል።—መዝ. 37:5

አንድ ችግር ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ሲሰማን በይሖዋ መታመን እንደሚያስፈልገን ስለምናውቅ የእሱን እርዳታ መጠየቃችን አይቀርም። ይሁንና በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከሚያጋጥሙን ትናንሽ የሚመስሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘስ ምን እናደርጋለን? ጉዳዩን በራሳችን ለመፍታት በመሞከር በሰብዓዊ አስተሳሰብ እንደምንመራ እናሳያለን? ወይስ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመመርመርና ተግባራዊ በማድረግ በይሖዋ እንደምንታመን እናሳያለን? ለምሳሌ ያህል፣ በጉባኤ ወይም በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ መገኘትህ ከቤተሰብህ ተቃውሞ ያስነሳብህ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ትክክለኛውን እርምጃ መውሰድ እንድትችል ይሖዋ እንዲረዳህ ትጠይቀዋለህ። በሌላ በኩል ደግሞ ከሥራህ ብትፈናቀልና ሌላ ሥራ ለማግኘት ብትቸገርስ? ሥራ በምታገኝበት ጊዜ ለአዲሱ ቀጣሪህ በየሳምንቱ የምትገኝበት የጉባኤ ስብሰባ እንዳለህ አስቀድመህ ታሳውቀዋለህ? የገጠመን ችግር ምንም ይሁን ምን በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የተናገረው መዝሙራዊ የሰጠውን ምክር መከተላችን ጠቃሚ ነው። w17.03 4:6

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ