ጥቅምት
ሰኞ፣ ጥቅምት 1
የሚፈሩትን ሰዎች ፍላጎት ያረካል፤ እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትንም ጩኸት ይሰማል፤ ደግሞም ይታደጋቸዋል።—መዝ. 145:19
ይሖዋ “ጽናትንና መጽናኛን [የሚሰጥ] አምላክ” ነው። (ሮም 15:5) የሚያጋጥሙንን ችግሮች ብቻ ሳይሆን ያለንበት ሁኔታ፣ ስሜታችን እንዲሁም ተፈጥሯችን የሚያስከትሉብንን ጫና ሙሉ በሙሉ ሊረዳልን የሚችለው እሱ ብቻ ነው። በመሆኑም እንድንጸና ከማንም በተሻለ ሊረዳን የሚችለው ይሖዋ ነው። ታዲያ አምላክ ለመጽናት የሚያስችል ብርታት እንዲሰጠን ስንጸልይ መልስ የሚሰጠን እንዴት ነው? ይሖዋ የደረሰብንን መከራ መወጣት እንድንችል ስንጠይቀው ‘መውጫ መንገዱን ያዘጋጅልናል።’ (1 ቆሮ. 10:13) ይህ ሲባል ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ መከራውን ያስወግደዋል ማለት ነው? አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ሊያደርግ ይችላል። ብዙ ጊዜ ግን መውጫ መንገዱን የሚያዘጋጅልን “ፈተናውን በጽናት መቋቋም” እንድንችል በመርዳት ነው። ይሖዋ “በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት [እንድንቋቋም]” የሚያስፈልገንን ብርታት ይሰጠናል። (ቆላ. 1:11) ደግሞም ይሖዋ ከአካላችን፣ ከአእምሯችንና ከስሜታችን ጋር በተያያዘ አቅማችን ምን ያህል እንደሆነ በሚገባ ስለሚያውቅ ታማኝነታችንን መጠበቅ እስኪያቅተን ድረስ እንድንፈተን አይፈቅድም። w16.04 2:5, 6
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 2
የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ።—ማቴ. 22:21
የአምላክ ቃል ለሰብዓዊ መንግሥታት እንድንታዘዝ ያስተምረናል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከሰው ይልቅ አምላክን መታዘዝ እንዳለብን ይገልጻል። (ሥራ 5:29፤ ቲቶ 3:1) ታዲያ እነዚህ ሐሳቦች እርስ በርስ ይጋጫሉ? በጭራሽ! በአንጻራዊ ሁኔታ ስለመገዛት የሚገልጸው መሠረታዊ ሥርዓት እነዚህን ትእዛዛት ለመረዳትና ለመፈጸም ያስችለናል። ኢየሱስ የዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ሲናገር ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል። የምንኖርበት አገር መንግሥት የሚያወጣቸውን ሕጎች በመታዘዝ፣ ባለሥልጣናቱን በማክበር እንዲሁም ቀረጥ በመክፈል ለመንግሥት ሥልጣን እንገዛለን። (ሮም 13:7) ይሁንና የመንግሥት ባለሥልጣናት የአምላክን ትእዛዝ እንድንጥስ ቢያዙን ይህን እንደማናደርግ በአክብሮት እንገልጻለን። በዚህ ዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ የገለልተኝነት አቋም እንይዛለን። (ኢሳ. 2:4) ሰብዓዊ መንግሥታት ሥልጣን እንዲይዙ የፈቀደላቸው ይሖዋ ስለሆነ አንቃወማቸውም፤ ብሔራዊ ስሜት የሚንጸባረቅባቸው እንቅስቃሴዎችንም አናካሂድም። (ሮም 13:1, 2) በፖለቲካ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር አንሞክርም፤ በምርጫ አንካፈልም ወይም ፖለቲካዊ ሥልጣን አንይዝም፤ አሊያም ደግሞ መንግሥት ለመለወጥ ጥረት አናደርግም። w16.04 4:1, 2
ረቡዕ፣ ጥቅምት 3
እንደ አሕዛብ . . . አድርገህ ቁጠረው።—ማቴ. 18:17
በክርስቲያኖች መካከል የሚፈጠሩ አብዛኞቹ አለመግባባቶች በራሳቸው በግለሰቦቹ ብቻ መፈታት ይችላሉ፤ ደግሞም እንዲህ መደረግ አለበት። ይሁንና ኢየሱስ እንደተናገረው አንዳንድ ጉዳዮችን ለጉባኤው መንገር ሊያስፈልግ ይችላል። (ማቴ. 18:15-17) አንድ ግለሰብ የበደለውን ወንድም፣ ምሥክሮችን እንዲሁም ጉባኤውን ለመስማት ፈቃደኛ ባይሆንስ? ይህ ሰው “እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ” መቆጠር ይኖርበታል። ይህም በዛሬው ጊዜ ውገዳ ብለን የምንጠራው እርምጃ ነው። እንዲህ ዓይነት ከባድ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑ የተፈጸመው ‘በደል’ ቀላል አለመግባባት ብቻ እንዳልሆነ ያሳያል። ከዚህ ይልቅ ጉዳዩ (1) የሚመለከታቸው ግለሰቦች ከተስማሙ እነሱ ራሳቸው ሊፈቱት የሚችሉ (2) ካልፈቱት ግን ለውገዳ የሚያበቃ ከባድ በደል መሆን አለበት። እንዲህ ያለው በደል፣ ከማጭበርበር ወይም የአንድን ሰው ስም ሆን ብሎ ከማጥፋት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ በማቴዎስ 18:15-17 ላይ የጠቀሳቸው ሦስቱም እርምጃዎች ተግባራዊ የሚደረጉት ከላይ ያሉት ሁለት ሁኔታዎች ከተሟሉ ብቻ ነው። w16.05 1:14
ሐሙስ፣ ጥቅምት 4
የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ።—ኤፌ. 5:17
መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥተኛ መመሪያ የማይሰጥባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ፣ ለክርስቲያኖች ተገቢ የሆነው አለባበስ ምን ዓይነት እንደሆነ የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ይህ የይሖዋን ጥበብ የሚያሳይ ነው የምንለው ለምንድን ነው? ሰዎች ከአለባበስ ጋር በተያያዘ ያላቸው ባሕል ከቦታ ወደ ቦታ ይለያያል፤ እንዲሁም በየጊዜው ይለዋወጣል። መጽሐፍ ቅዱስ ተገቢውን አለባበስና አጋጌጥ በተመለከተ ዝርዝር መመሪያዎችን ይዞ ቢሆን ኖሮ እነዚህ መመሪያዎች አሁን ጊዜ ያለፈባቸው ይሆኑ ነበር። በተመሳሳይም የአምላክ ቃል አንድ ክርስቲያን ከሥራ፣ ከጤና አጠባበቅና ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ የሚያደርጋቸውን ምርጫዎች በተመለከተ ዝርዝር መመሪያዎችን የማይሰጠው ለዚህ ነው። ቀጥተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ያልተሰጠባቸው ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ምን ማድረግ ይኖርብናል? በዚህ ጊዜ ውሳኔ የምናደርገው በግል ምርጫችን ላይ ብቻ ተመሥርተን መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱን ነገር በመመርመር በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል፤ ይህ ደግሞ የእሱን በረከት ያስገኝልናል።—መዝ. 37:5፤ w16.05 3:2, 6
ዓርብ፣ ጥቅምት 5
እንደ ሰው ቃል ሳይሆን እንደ አምላክ ቃል አድርጋችሁ ተቀብላችሁታል፤ ደግሞም የአምላክ ቃል ነው።—1 ተሰ. 2:13
እያንዳንዳችን የምንወደው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይኖረናል። አንዳንዶች፣ በአምላክ ልጅ በኩል የተገለጡትን የይሖዋን ማራኪ ባሕርያት ግሩም አድርገው የሚያሳዩትን የወንጌል መጻሕፍት በጣም ይወዷቸዋል። (ዮሐ. 14:9) ሌሎች ደግሞ ትንቢቶችን የያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ምናልባትም “በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች” የሚገልጸውን የራእይ መጽሐፍን ማንበብ ያስደስታቸዋል። (ራእይ 1:1) ከመዝሙር መጽሐፍ መጽናኛ ወይም ከምሳሌ መጽሐፍ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ትምህርቶችን ያላገኘ ማን አለ? በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ስለምንወድ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችንንም እንወዳለን። ለምሳሌ በመጻሕፍት፣ በብሮሹሮች፣ በመጽሔቶችና በሌሎች መንገዶች ለሚቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ አድናቆት አለን። ይሖዋ ያደረገልን እነዚህ ዝግጅቶች በመንፈሳዊ ምንጊዜም ንቁ እንድንሆን፣ በሚገባ እንድንመገብ እንዲሁም “በእምነት . . . ጤናሞች” እንድንሆን እንደሚረዱን እናውቃለን።—ቲቶ 2:2፤ w16.05 5:1-3
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 6
የመንፈስ ፍሬ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚከለክል ሕግ የለም።—ገላ. 5:22, 23
መንፈስ ቅዱስ በተለያዩ መንገዶች ሊቀርጸን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የክርስቶስን ዓይነት ባሕርያት እንድናዳብር ይረዳናል፤ ከእነዚህ ባሕርያት መካከል የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች ይገኙበታል። ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ ፍቅር ነው። አምላክን እንወደዋለን፤ እንዲሁም የአምላክ ትእዛዛት ከባዶች እንዳልሆኑ ስለምንገነዘብ እሱን መታዘዝና በእሱ መቀረጽ እንፈልጋለን። በተጨማሪም ይህ ዓለምም ሆነ የሚያሳድረው መጥፎ መንፈስ እንዳይቀርጸን የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልገናል። (ኤፌ. 2:2) ሐዋርያው ጳውሎስ ወጣት በነበረበት ጊዜ የሃይማኖት መሪዎቹ የትዕቢት ዝንባሌ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮበት ነበር፤ ይሁንና መንፈስ ቅዱስ አመለካከቱን እንዲለውጥ ረድቶታል፤ ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ” ሲል ጽፏል። (ፊልጵ. 4:13) እኛም እንደ ጳውሎስ፣ ይሖዋ መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠን አዘውትረን እንጠይቀው። ይሖዋ የዋሆች የሚያቀርቡትን ልባዊ ልመና ይሰማል።—መዝ. 10:17፤ w16.06 1:12
እሁድ፣ ጥቅምት 7
ይሖዋ አምላካችን፣ . . . ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።—ራእይ 4:11
አምላካችን፣ ይሖዋ ብቻ ነው፤ በመሆኑም እሱን ብቻ ልናመልክ ይገባል። እሱን እያመለክን ሌሎች አማልክትንም ማምለክ አሊያም ለእሱ በምናቀርበው አምልኮ ውስጥ የሐሰት ትምህርቶችንና ልማዶችን መቀላቀል አንችልም። ይሖዋን በዓለም ላይ ካሉ በርካታ አማልክት አንዱ እንደሆነ አሊያም ከሌሎች አማልክት ሁሉ የበላይና ኃያል እንደሆነ ብቻ አድርገን ልንመለከተው አይገባም። ሊመለክ የሚገባው ይሖዋ ብቻ ነው። ይሖዋን ብቻ ማምለክ ከፈለግን በሕይወታችን ውስጥ ለእሱ ብቻ ልንሰጠው የሚገባውን ቦታ ሌላ ነገር እንዲወስደው ሌላው ቀርቶ እንዲጋራው እንኳ ልንፈቅድ አይገባም። የይሖዋን ቦታ ሊይዙብን የሚችሉት ነገሮች ምንድን ናቸው? ይሖዋ ለእስራኤላውያን አሥርቱን ትእዛዛት ሲሰጥ፣ ከእሱ በቀር ሌሎች አማልክትን እንዳያመልኩና ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ እንዲርቁ አዟቸው ነበር። (ዘዳ. 5:6-10) በዘመናችን እንደ ጣዖት የሚመለኩ ብዙ ነገሮች አሉ፤ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች እነዚህን ነገሮች እንደ ጣዖት እያመለኳቸው እንዳሉ እንኳ ላይገነዘቡ ይችላሉ። የይሖዋ መመሪያዎች ግን አልተለወጡም፤ እሱ አሁንም “አንድ ይሖዋ ነው።”—ማር. 12:29፤ w16.06 3:10, 12
ሰኞ፣ ጥቅምት 8
የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላችሁ በሰማይ ያለው አባታችሁ ይቅር ይላችኋል።—ማቴ. 6:14
ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “እስከ ሰባት ጊዜ ይቅር [ማለት]” ይኖርበት እንደሆነ ሲጠይቀው ኢየሱስ “እስከ 77 ጊዜ እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ ይህን የተናገረው ምንጊዜም ይቅር ለማለት ፈቃደኞች መሆን እንዳለብን ለማጉላት ነው፤ ሌሎችን ይቅር ማለት የሚቀናን ዓይነት ሰዎች መሆን አለብን። (ማቴ. 6:15፤ 18:21, 22) ሁላችንም ስህተት ስለምንሠራ እኛም ሌሎችን ልንበድል እንደምንችል ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። የበደልነው ሰው እንዳለ ከተገነዘብን የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ በመከተል ወደ ግለሰቡ ሄደን እርቅ ለማውረድ ጥረት ማድረግ አለብን። (ማቴ. 5:23, 24) ሌሎች የፈጸምነውን በደል ይቅር ሲሉን ደስ ይለናል፤ እኛም እነሱ ሲበድሉን እንዲሁ ማድረግ ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 13:5፤ ቆላ. 3:13) ሌሎችን ይቅር የምንል ከሆነ ይሖዋም ይቅር ይለናል። በእርግጥም እኛ ስህተት ስንሠራ በሰማይ ያለው አባታችን ይቅር እንደሚለን ሁሉ እኛም ሌሎች ስህተት በሚሠሩበት ጊዜ ይቅር ባዮች ልንሆን ይገባል።—መዝ. 103:12-14፤ w16.06 4:15, 17
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 9
እኔ በምሥራቹ አላፍርምና፤ እንዲያውም ለሚያምን ሁሉ . . . ምሥራቹ መዳን የሚያስገኝ የአምላክ ኃይል ነው።—ሮም 1:16
በዚህ የፍጻሜ ዘመን የይሖዋ ሕዝቦች ‘ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን የመንግሥቱን ምሥራች በመላው ምድር’ የመስበክ ተልእኮ ተሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 24:14) የምናውጀው መልእክት “ስለ አምላክ ጸጋ [የሚገልጽ] ምሥራች” እንደሆነም ተገልጿል። እንዲህ የተባለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በረከቶች እንደምናገኝ ተስፋ ሊኖረን የቻለው፣ በክርስቶስ በኩል በተገለጸው የይሖዋ ጸጋ አማካኝነት ነው። (ሥራ 20:24፤ ኤፌ. 1:3) እኛስ በአገልግሎት በቅንዓት በመካፈል ልክ እንደ ጳውሎስ ይሖዋ ላሳየን ጸጋ አመስጋኝነታችንን እንገልጻለን? (ሮም 1:14, 15) ኃጢአተኞች የሆንነው የሰው ልጆች፣ በተለያዩ መንገዶች ከተገለጸው የይሖዋ ጸጋ ጥቅም አግኝተናል። በመሆኑም ይሖዋ ፍቅሩን የገለጸባቸውን መንገዶች እንዲሁም ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ከዚህ ጥቅም ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ለሰው ሁሉ ለማሳወቅ አቅማችን የፈቀደውን በሙሉ የማድረግ ኃላፊነት አለብን። w16.07 4:4, 5
ረቡዕ፣ ጥቅምት 10
የሰው ልጅ ይመጣል ብላችሁ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሆናችሁ ጠብቁ።—ሉቃስ 12:40
ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ደቀ መዛሙርቱን “የዚህ ዓለም ገዢ” ስለሆነው ስለ ዲያብሎስ ሦስት ጊዜ አስጠንቅቋቸዋል። (ዮሐ. 12:31፤ 14:30፤ 16:11) ኢየሱስ፣ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች እንዳያስተውሉና መጨረሻው መቅረቡን እንዳይገነዘቡ በማድረግ ዲያብሎስ አእምሯቸውን እንደሚያጨልም ያውቅ ነበር። (ሶፎ. 1:14) ሰይጣን በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን ተጠቅሞ የሰዎችን አእምሮ እያሳወረ ነው። ሰዎችን ስታነጋግሩ ምን ምላሽ እንደሚሰጡ አስተውላችኋል? የዚህ ሥርዓት መጨረሻ መቅረቡንም ሆነ ክርስቶስ በአሁኑ ጊዜ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ እየገዛ መሆኑን ማስተዋል እንዳይችሉ ዲያብሎስ ‘የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ እንዳሳወረ’ እየተመለከትን አይደለም? (2 ቆሮ. 4:3-6) አብዛኞቹ ሰዎች ይህ ዓለም ወዴት እያመራ እንደሆነ ልንነግራቸው ስንሞክር ይህ ጉዳይ ብዙም ግድ እንደማይሰጣቸው እንመለከታለን። የሰዎች ግድየለሽነት ተስፋ እንዲያስቆርጣችሁ ወይም ነቅታችሁ ከመጠበቅ እንዲያዘናጋችሁ አትፍቀዱ። ነቅተን መጠበቅ ያለብን ለምን እንደሆነ እናውቃለን። w16.07 2:11, 12
ሐሙስ፣ ጥቅምት 11
ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ . . . ሚስት ባሏን በጥልቅ ታክብር።—ኤፌ. 5:33
አንዲት ሙሽራ በሠርጓ ዕለት አምራና ደምቃ ከሙሽራው ጋር በምትገናኝበት ጊዜ ሁለቱም የሚሰማቸውን ደስታ በቃላት መግለጽ ያስቸግራል። ጋብቻን ያቋቋመው አፍቃሪ አምላክ፣ ሁሉም ባለትዳሮች በትዳር ሕይወታቸው ደስተኛ እንዲሆኑና ጋብቻቸው እንዲሰምር ስለሚፈልግ ማግባት የሚፈልጉ ሁሉ እንዲመሩበት ሲል በቃሉ ውስጥ ጥበብ ያዘለ ምክር አስፍሯል። (ምሳሌ 18:22) ያም ቢሆን ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ፍጹም ያልሆኑ ባለትዳሮች ‘በሥጋቸው ላይ መከራ እንደሚደርስባቸው’ በግልጽ ይናገራሉ። (1 ቆሮ. 7:28) እንዲህ ያለውን መከራ ለመቀነስ ምን ማድረግ ይቻላል? ክርስቲያኖች ትዳራቸው እንዲሰምር ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፍቅር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ባልና ሚስት በትዳራቸው ውስጥ ሊያሳዩአቸው የሚገቡ የተለያዩ የፍቅር ዓይነቶች አሉ። ለምሳሌ፣ አንዳቸው ሌላውን መውደድ (በግሪክኛ ፊሊያ) ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም በተቃራኒ ፆታዎች መካከል የሚኖረውን ዓይነት ፍቅር (ኤሮስ) ማሳየታቸው ደስታ ያስገኝላቸዋል። ልጆች ከወለዱ ደግሞ በቤተሰብ አባላት መካከል የሚኖረውን ፍቅር (ስቶርጌ) ማንጸባረቃቸው አስፈላጊ ነው። ይሁንና ትዳራቸው የሰመረ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርገው በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራው ፍቅር (አጋፔ) ነው። w16.08 2:1, 2
ዓርብ፣ ጥቅምት 12
ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ።—1 ጢሞ. 4:16
በወቅቱ ጢሞቴዎስ ተሞክሮ ያለው የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ነበር። ሆኖም በአገልግሎቱ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ለሚያስተምረው ትምህርት ‘ምንጊዜም ትኩረት ከሰጠ’ ብቻ ነው። አዘውትሮ በሚጠቀምበት መንገድ መስበኩን ቢቀጥል፣ ሰዎች ሁልጊዜ ጥሩ ምላሽ እንደሚሰጡት መጠበቅ አይችልም። የሰዎችን ልብ መንካት እንዲችል የማስተማር ዘዴዎቹን እንደ ሰዎቹ ሁኔታ መቀያየር ነበረበት። እኛም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንደመሆናችን መጠን ተመሳሳይ ነገር ማድረግ አለብን። ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ብዙ ጊዜ ሰዎችን ቤታቸው አናገኛቸውም። ወደ አፓርታማዎች ወይም ወደ አንዳንድ የታጠሩ መኖሪያ ሰፈሮች መግባት አስቸጋሪ የሚሆንባቸው አካባቢዎች አሉ። አንተም በክልልህ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚያጋጥምህ ከሆነ ምሥራቹን ለመስበክ ለምን የተለያዩ ዘዴዎችን አትሞክርም? ምሥራቹን ከምናዳርስባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ የአደባባይ ምሥክርነት ነው። ብዙ አስፋፊዎች ይህን የአገልግሎት ዘዴ ውጤታማና አስደሳች ሆኖ አግኝተውታል። በባቡርና በአውቶቡስ ፌርማታዎች፣ በገበያ ቦታዎች፣ በመናፈሻዎችና ሰዎች በሚገኙባቸው ሌሎች ቦታዎች ምሥራቹን ለመስበክ ጥረት ያደርጋሉ። w16.08 3:14-16
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 13
የዛሉትን እጆችና የተብረከረኩትን ጉልበቶች አበርቱ።—ዕብ. 12:12
ይሖዋ፣ ማበረታቻ ሊሰጡን የሚችሉ አሳቢ የሆኑ ወንድሞች የሚገኙበት ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር ሰጥቶናል። (ዕብ. 12:12, 13) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ በርካታ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ መንፈሳዊ ማበረታቻ አግኝተዋል። በዛሬው ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ታዲያ እኛ ምን ማድረግ እንችላለን? አሮን እና ሁር በውጊያው ወቅት ቃል በቃል የሙሴን እጅ ደግፈውለት እንደነበር አስታውሱ። (ዘፀ. 17:8-13) እኛም ሌሎችን መደገፍና መርዳት የምንችልባቸውን መንገዶች መፈለግ እንችላለን። ማንን መርዳት እንችላለን? የዕድሜ መግፋት፣ የጤና እክል፣ የቤተሰብ ተቃውሞ፣ ብቸኝነት ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ከሚያስከትለው ተፈታታኝ ሁኔታ ጋር እየታገሉ ያሉ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መርዳት እንችላለን። በተጨማሪም መጥፎ ነገር እንዲሠሩ ወይም በዚህ ሥርዓት በትምህርትም ይሁን በሙያቸው ጥሩ ደረጃ የሚባለው ቦታ ላይ እንዲደርሱ አሊያም ሀብት እንዲያሳድዱ ከፍተኛ ጫና የሚደርስባቸውን ወጣቶች ማበረታታት እንችላለን። (1 ተሰ. 3:1-3፤ 5:11, 14) ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር በመንግሥት አዳራሽ ውስጥም ሆነ በአገልግሎት ላይ ስትሆኑ አሊያም አብራችሁ ስትመገቡ ወይም በስልክ ስታወሩ ልባዊ አሳቢነት ልታሳዩ የምትችሉባቸውን መንገዶች ለማሰብ ሞክሩ። w16.09 1:13, 14
እሁድ፣ ጥቅምት 14
ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ።—1 ቆሮ. 10:31
ቅዱስ ለሆነው አምላካችን፣ ለመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም በክልላችን ላሉ ሰዎች ያለን አክብሮት ለምንሰብከው መልእክትም ሆነ ለይሖዋ ክብር የሚያመጣ አለባበስ እንዲኖረን ያነሳሳናል። (ሮም 13:8-10) በተለይ ደግሞ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ስንካፈል ለምሳሌ፣ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ወይም ምሥራቹን ስንሰብክ ለአለባበሳችን ትኩረት መስጠት ይኖርብናል። አለባበሳችን “ለአምላክ ያደርን ነን” ለሚሉ ሰዎች የሚገባ መሆን ይኖርበታል። (1 ጢሞ. 2:10) እርግጥ ነው፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ተገቢ የሚባለው አለባበስ በሌሎች አካባቢዎች ተገቢ ላይሆን ይችላል። በመሆኑም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች ሌሎችን ቅር ላለማሰኘት ሲሉ የአካባቢውን ባሕል ግምት ውስጥ ያስገባሉ። በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ አለባበሳችን በዓለም ላይ የተለመደውን ወጣ ያለ ፋሽን የሚያንጸባርቅ ሳይሆን ተገቢና ልከኛ ሊሆን ይገባል። እንዲህ ካደረግን የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ለመናገር አንሸማቀቅም። ለመመሥከር የሚያስችል አጋጣሚ ካገኘንም ነፃነት ተሰምቶን እንመሠክራለን። w16.09 3:7, 8
ሰኞ፣ ጥቅምት 15
እያንዳንዱ ቤት ሠሪ እንዳለው የታወቀ ነው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው።—ዕብ. 3:4
ጳውሎስ የሰጠው ይህ ማብራሪያ ምክንያታዊነት የሚንጸባረቅበት ከመሆኑም ሌላ ውጤታማ ነው! በእርግጥም ውስብስብ የሆነ ንድፍ ሊያወጣ የሚችለው የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ከሚጠራጠር ሰው ጋር ስትወያዩም ይህን ዘዴ መጠቀም ትችላላችሁ። ግለሰቡ ምን ብሎ እንደሚያምንና ትኩረቱን የሚስቡት ርዕሰ ጉዳዮች የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ ጥረት አድርጉ። (ምሳሌ 18:13) ሳይንሳዊ ነገሮች ትኩረቱን የሚስቡት ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ አንጻር ትክክል መሆኑን የሚያሳዩ ነጥቦችን ብትጠቅሱለት ጥሩ ምላሽ ይሰጥ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶችንና ትክክለኛ ታሪኮችን እንደያዘ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን መመልከታቸው ልባቸውን ይነካው ይሆናል። አሊያም በተራራው ስብከት ላይ እንደሚገኙት ያሉ ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን መጥቀስ ትችላላችሁ። ግባችሁ የሰውየውን ልብ መንካት እንጂ ተከራክሮ መርታት አለመሆኑን አስታውሱ። ስለዚህ ግለሰቡ ሲናገር በጥሞና አዳምጡት። በቅንነት ጥያቄዎችን አቅርቡለት፤ በተለይ በዕድሜ የሚበልጧችሁን ሰዎች ገርነትና አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ ለማነጋገር ጥረት አድርጉ። እንዲህ ካደረጋችሁ አመለካከታችሁን ይበልጥ ሊያከብሩላችሁ ይችላሉ። w16.09 4:14-16
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 16
አንዳችሁ ሌላውን ተቀበሉ።—ሮም 15:7
የሌላ አገር ሰዎች ወደ ጉባኤያችን ሲመጡ እንግድነት እንዳይሰማቸው መርዳት እንድንችል ‘እኔ ወደ ሌላ አገር ብሄድ ሰዎች ምን እንዲያደርጉልኝ እፈልጋለሁ?’ ብለን ራሳችንን በሐቀኝነት መጠየቃችን ጠቃሚ ነው። (ማቴ. 7:12) ከሌላ አገር መጥተው ከአዲስ ባሕል ጋር ለመላመድ ለሚጥሩ ሰዎች ትዕግሥት አሳዩ። መጀመሪያ ላይ፣ የሚያስቡበትን ወይም አንዳንድ ነገሮችን የሚያደርጉበትን መንገድ ሙሉ በሙሉ መረዳት ይከብደን ይሆናል። ይሁን እንጂ እነሱ አመለካከታቸውን ቀይረው የእኛን ባሕል እንዲቀበሉ ከመጠበቅ ይልቅ እነሱንም ሆነ ባሕላቸውን ለመቀበል ለምን ጥረት አናደርግም? ስለ ባሕላቸውና ስለ አገራቸው ለማወቅ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ከእነሱ ጋር መነጋገር ቀላል ይሆንልናል። በጉባኤያችን ወይም በክልላችን ውስጥ ስለሚገኙ የውጭ አገር ዜጎች ብዙም የማናውቅ ከሆነ በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ስለ እነዚህ ሰዎች ባሕል ምርምር ለማድረግ ጊዜ መመደብ እንችላለን። ከባዕድ አገር ከመጡ ሰዎች ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ የሚረዳን ሌላው ነገር ደግሞ ቤታችን መጋበዝ ነው። ይሖዋ “ለአሕዛብ የእምነትን በር [ከከፈተላቸው]” እኛስ “በእምነት ለሚዛመዱን” የውጭ አገር ሰዎች ቤታችንን ክፍት ልናደርግላቸው አይገባም?—ሥራ 14:27፤ ገላ. 6:10፤ ኢዮብ 31:32፤ w16.10 1:15, 16
ረቡዕ፣ ጥቅምት 17
ኃጢአተኞች . . . የሚያሰሙትን እንዲህ ዓይነቱን የተቃውሞ ንግግር በጽናት የተቋቋመውን እሱን በጥሞና አስቡ።—ዕብ. 12:3
ጳውሎስ የእምነት ምሳሌ የሚሆኑ የተለያዩ ወንዶችንና ሴቶችን ከዘረዘረ በኋላ ከሁሉ የላቀ አርዓያ ስለሆነው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል። ዕብራውያን 12:2 “ከፊቱ ለሚጠብቀው ደስታ ሲል፣ የሚደርስበትን ውርደት ከምንም ሳይቆጥር በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ጸንቷል፤ እንዲሁም በአምላክ ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል” ይላል። በእርግጥም፣ ኢየሱስ በጣም ከባድ ፈተናዎችን በመቋቋም የተወውን የእምነት ምሳሌ ‘በጥሞና ማሰብ’ ይኖርብናል። እንደ አንቲጳስ ያሉ በጥንት ዘመን የነበሩና ሰማዕት የሆኑ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በንጹሕ አቋማቸው ጸንተዋል። (ራእይ 2:13) በመሆኑም እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች የላቀ ትንሣኤ ያገኛሉ፤ ይኸውም ከሞት ተነስተው በሰማይ ይኖራሉ፤ ይህ ደግሞ የጥንቶቹ የእምነት ሰዎች ተስፋ ያደርጉት ከነበረው “የተሻለ ትንሣኤ” እንኳ የበለጠ ነው። (ዕብ. 11:35) በሞት አንቀላፍተው የነበሩት ታማኝ ቅቡዓን በሙሉ፣ የአምላክ መንግሥት በ1914 ከተወለደ ብዙም ሳይቆይ ከሞት ተነስተው መንፈሳዊ ሕይወት ተቀብለዋል፤ እነዚህ ቅቡዓን ከኢየሱስ ጋር ሆነው በሰው ልጆች ላይ ይገዛሉ።—ራእይ 20:4፤ w16.10 3:12
ሐሙስ፣ ጥቅምት 18
በየዕለቱ እርስ በርሳችሁ ተበረታቱ።—ዕብ. 3:13
አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን የማያደንቁት፣ የራሳቸው ወላጆች ምንም ዓይነት ማበረታቻ ሰጥተዋቸው ስለማያውቁ ነው። በሥራው ዓለም ያሉ በርካታ ሰዎችም በሥራ ቦታቸው ጨርሶ ማበረታቻ እንደማያገኙ በምሬት ይናገራሉ። ማበረታቻ መስጠት አንድ ሰው ላደረገው መልካም ነገር ማመስገንን ይጨምራል። በተጨማሪም ሰዎች ያሏቸውን ጥሩ ባሕርያት በማድነቅ ወይም ‘ተስፋ የቆረጡትን የሚያጽናና’ ነገር በመናገር ሌሎችን ማበረታታት ይቻላል። (1 ተሰ. 5:14 ግርጌ) አብዛኛውን ጊዜ “ማበረታቻ” ተብሎ የሚተረጎመው የግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ፍቺ “ከጎኔ ሁን” የሚል ነው። ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ስናገለግል እነሱን የሚያበረታታ ነገር ለመናገር አጋጣሚዎች ማግኘታችን አይቀርም። (መክ. 4:9, 10) ታዲያ አመቺ አጋጣሚዎችን ተጠቅመን፣ ሌሎችን እንድንወዳቸውና እንድናደንቃቸው የሚያደርጉንን ምክንያቶች እንነግራቸዋለን? ለዚህ ጥያቄ መልስ ከመስጠታችን በፊት “በትክክለኛው ጊዜ የተነገረ ቃል . . . ምንኛ መልካም ነው!” በሚለው ጥቅስ ላይ ማሰላሰላችን ጠቃሚ ነው።—ምሳሌ 15:23፤ w16.11 1:3-5
ዓርብ፣ ጥቅምት 19
እነሆ፣ ወንድሞች በአንድነት አብረው ቢኖሩ ምንኛ መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!—መዝ. 133:1
አምላክ፣ ሕዝቡ ወደፊት የሚኖረውን ሁኔታ አስመልክቶ ሲናገር “በጉረኖ ውስጥ እንዳለ በግ . . . በአንድነት አኖራቸዋለሁ” ብሏል። (ሚክ. 2:12) በተጨማሪም ይሖዋ በነቢዩ ሶፎንያስ በኩል እንዲህ ሲል ተንብዮአል፦ “በዚያን ጊዜ ሰዎች ሁሉ የይሖዋን ስም እንዲጠሩና እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲያገለግሉት [ወይም “በአንድነት እንዲያመልኩት፣” ግርጌ] ቋንቋቸውን ለውጬ ንጹሕ ቋንቋ [የቅዱሳን መጻሕፍትን እውነት] እሰጣቸዋለሁ።” (ሶፎ. 3:9) ይሖዋን በአንድነት የማምለክ መብት በማግኘታችን ምንኛ አመስጋኞች ነን! በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ምክር፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የነበሩ ክርስቲያኖች የጉባኤያቸውን ንጽሕና፣ ሰላምና አንድነት ለመጠበቅ እንደረዳቸው ግልጽ ነው። (1 ቆሮ. 1:10፤ ኤፌ. 4:11-13፤ 1 ጴጥ. 3:8) ዛሬም ቢሆን አንድነት ያለው የአምላክ ድርጅት አባላት ምሥራቹን ስለሚሰብኩ አስደናቂ የሆነው የአምላክ ዓላማ በምድር ዙሪያ ሊታወቅ ችሏል። w16.11 2:16, 18
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 20
እናንተ . . . ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእሱን “ድንቅ ባሕርያት በየቦታው እንድታውጁ . . . ንጉሣዊ ካህናት፣ ቅዱስ ብሔር፣ ልዩ ንብረት እንዲሆን የተለየ ሕዝብ” ናችሁ።—1 ጴጥ. 2:9
ከክርስቶስ ልደት በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት መቶ ዓመታት ውስጥ በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በግሪክኛ ወይም በላቲን ማንበብ ይችሉ ነበር። በመሆኑም በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን ትምህርት ከቤተ ክርስቲያኗ ትምህርት ጋር የማወዳደር አጋጣሚ ነበራቸው። አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ካነበቡት ነገር በመነሳት የቤተ ክርስቲያኗ ትምህርቶች ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የላቸውም የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ፤ እርግጥ ይህን አመለካከታቸውን በግልጽ መናገር አደገኛ አልፎ ተርፎም ለሞት የሚዳርግ ነበር። ውሎ አድሮ ግን አብዛኛው ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስ በሚገኝባቸው ቋንቋዎች መጠቀም እየተወ ሄደ፤ ቤተ ክርስቲያኗ ደግሞ የአምላክን ቃል ሕዝቡ ወደሚጠቀምበት ቋንቋ ለመተርጎም የተደረጉትን ጥረቶች ተቃወመች። ቤተ ክርስቲያኗ የምታስተምረውን ነገር የሚቃወም ማንኛውም ሰው ከፍተኛ ቅጣት ይበየንበት ነበር። በመሆኑም ታማኝ የሆኑ የአምላክ ቅቡዕ አገልጋዮች በትናንሽ ቡድኖች ሆነው ለመሰብሰብ ተገደዱ፤ ያውም መሰብሰብ ከቻሉ ነው። “ንጉሣዊ ካህናት” የሆኑት ቅቡዓን በተደራጀ መልኩ ሥራቸውን ማከናወን አልቻሉም። ታላቂቱ ባቢሎን ሕዝቡን ተብትባ ይዛው ነበር! w16.11 4:8, 10, 11
እሁድ፣ ጥቅምት 21
ዓመፀኞች የአምላክን መንግሥት [አይወርሱም]።—1 ቆሮ. 6:9
በዛሬው ጊዜ የምንኖር ክርስቲያኖች በቆሮንቶስ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ይፈጽሟቸው የነበሩ ከባድ ኃጢአቶችን ከመፈጸም መራቅ እንዳለብን ግልጽ ነው። የአምላክን ጸጋ እንደተቀበልንና ‘ኃጢአት በእኛ ላይ ጌታ እንዳልሆነ’ መናገር የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ከከባድ ኃጢአቶች ብቻ ሳይሆን አንዳንዶች እንደ ቀላል ከሚመለከቷቸው ኃጢአቶችም ለመራቅ የምንችለውን ሁሉ በማድረግ አምላክን ‘ከልብ ለመታዘዝ’ ቆርጠናል? (ሮም 6:14, 17) ሐዋርያው ጳውሎስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 6:9-11 ላይ የተጠቀሱትን ዓይነት ከባድ ኃጢአቶች እየፈጸመ እንዳልነበረ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ያም ቢሆን ኃጢአተኛ መሆኑን ገልጿል። ጳውሎስ ስለ ራሱ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ለኃጢአት የተሸጥኩ ሥጋዊ ነኝ። ለምን እንዲህ እንደማደርግ አላውቅም። ለማድረግ የምፈልገውን ነገር አላደርግምና፤ ከዚህ ይልቅ የማደርገው የምጠላውን ነገር ነው።” (ሮም 7:14, 15) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ እንደ ኃጢአት አድርጎ የሚቆጥራቸው ሌሎች ነገሮች ነበሩ፤ እንዲህ ያሉትን ኃጢአቶች ለማስወገድ እየታገለ ነበር። (ሮም 7:21-23) እኛም ‘ከልብ ለመታዘዝ’ ጥረት በማድረግ የጳውሎስን ምሳሌ እንከተል። w16.12 1:15, 16
ሰኞ፣ ጥቅምት 22
ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል።—መዝ. 55:22
የሚረብሽ፣ የሚያስፈራ ወይም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥምህ በሰማይ ላለው አፍቃሪ አባትህ የልብህን አውጥተህ ንገረው። አንድን ችግር ለመፍታት የቻልከውን ያህል ጥረት ካደረግህ በኋላ፣ የተሻለ የሚሆነው ስለ ጉዳዩ መጨነቅ ሳይሆን ወደ ይሖዋ ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረብ ነው። (መዝ. 94:18, 19) በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ደጋግመን ለምናቀርበው ከልብ የመነጨ ምልጃ ምላሽ ይሰጣል። እንዴት? አእምሯችንንና ልባችንን፣ ከሚረብሹ ስሜቶች የሚያሳርፍ ውስጣዊ ሰላም በመስጠት ነው። በርካታ ሰዎች ይህን በሕይወታቸው ተመልክተዋል። አምላክ ጭንቀታቸውና ስጋታቸው ተወግዶ፣ ከመረዳት ችሎታ በላይ የሆነ ውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። አንተም እንዲህ ዓይነት ሰላምና መረጋጋት ልታገኝ ትችላለህ። “የአምላክ ሰላም” የሚያጋጥምህን ማንኛውንም ተፈታታኝ ሁኔታ መቋቋም እንድትችል ይረዳሃል። ይሖዋ “እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ” በማለት በገባልን ርኅራኄ የተንጸባረቀበት ቃል ላይ ሙሉ በሙሉ መተማመን ትችላለህ።—ኢሳ. 41:10፤ w16.12 3:3, 4
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 23
ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ ተብሎ ለመጠራት በእምነት እንቢ አለ።—ዕብ. 11:24
ሙሴ “በኃጢአት ከሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ከአምላክ ሕዝብ ጋር መንገላታትን” በመምረጥ ‘በግብፅ የሚገኘውን ውድ ሀብት’ ለመተው ፈቃደኛ ሆኗል። (ዕብ. 11:25, 26) እኛም የመምረጥ ነፃነታችንን በአድናቆት በመመልከት እንዲሁም ይህን ነፃነታችንን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ በመጠቀም በጥንት ዘመን የኖሩ እንዲህ ያሉ የእምነት ሰዎች የተዉትን ምሳሌ እንከተል። ሌላ ሰው እንዲወስንልን ማድረግ ቀላል ሊመስል ቢችልም እንዲህ ማድረግ የመምረጥ ነፃነታችንን መጠቀም ከሚያስገኝልን በረከቶች መካከል አንዱን ያሳጣናል። ይህ በረከት በዘዳግም 30:19, 20 ላይ ተገልጿል። ቁጥር 19፣ አምላክ ለእስራኤላውያን ምርጫ እንደሰጣቸው ይናገራል። ቁጥር 20 ደግሞ እስራኤላውያን በልባቸው ውስጥ ያለውን ነገር ማሳየት የሚችሉበት ግሩም አጋጣሚ ይሖዋ እንደሰጣቸው ይገልጻል። እኛም ይሖዋን ለማምለክ መምረጥ እንችላለን። የመምረጥ ነፃነታችንን ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ለማሳየትና ለእሱ ክብር ለማምጣት ልንጠቀምበት እንችላለን፤ ደግሞም አምላክ የሰጠንን የመምረጥ ነፃነት በአግባቡ እንድንጠቀምበት የሚያነሳሳ ከዚህ የተሻለ ምክንያት ሊኖር አይችልም! w17.01 2:10, 11
ረቡዕ፣ ጥቅምት 24
በይሖዋ ታመን፤ መልካም የሆነውንም አድርግ፤ . . . ለሰዎችም ታማኝ ሁን።—መዝ. 37:3
ይሖዋ እሱ የሰጠንን ችሎታዎች በጥሩ ሁኔታ እንድንጠቀምባቸው ይፈልጋል። ለምን? ምክንያቱም እኛን ይወደናል፤ እንዲሁም ያሉንን ችሎታዎች በዚህ መንገድ መጠቀማችን ደስታና እርካታ እንደሚያስገኝልን ያውቃል። ይሁንና ይሖዋ፣ የሰው ልጆች የአቅም ገደብ እንዳለባቸው ያውቃል። በራሳችን ጥረት አለፍጽምናን፣ ኃጢአትንና ሞትን ማስወገድ አንችልም፤ በተጨማሪም እያንዳንዱ ሰው የመምረጥ ነፃነት ስላለው ሌሎች የሚያደርጉትን ነገር መቆጣጠር አንችልም። (1 ነገ. 8:46) ከዚህም ሌላ የቱንም ያህል እውቀትና ተሞክሮ ያካበትን ብንሆን ከይሖዋ አንጻር ስንታይ ምንጊዜም ሕፃናት ነን። (ኢሳ. 55:9) ይሖዋ እንደሚደግፈንና እኛ ማድረግ የማንችለውን ነገር ለእኛ ሲል እንደሚያደርግልን በመተማመን ምንጊዜም የእሱን መመሪያዎች መፈለግ ይኖርብናል። በሌላ በኩል ደግሞ እጃችንን አጣጥፈን ከመቀመጥ ይልቅ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመፍታትና ሌሎችን ለመርዳት አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። በሌላ አባባል ‘በይሖዋ መታመን’ እና ‘መልካም የሆነውን ማድረግ’ ያስፈልገናል። w17.01 1:2-4
ሐሙስ፣ ጥቅምት 25
አብረኸኝ ተሻገር፤ እኔም በኢየሩሳሌም ቀለብ እሰጥሃለሁ።—2 ሳሙ. 19:33
ቤርዜሊ የቀረበለትን ግብዣ አልተቀበለም። ለምን? ምክንያቱም ዕድሜው ገፍቶ ስለነበር ለንጉሡ ሸክም መሆን አልፈለገም። ስለዚህ ቤርዜሊ በእሱ ምትክ ኪምሃም (ልጁ ሳይሆን አይቀርም) እንዲሄድ ሐሳብ አቀረበ። (2 ሳሙ. 19:31-37) ቤርዜሊ ጥሩ ውሳኔ እንዲያደርግ የረዳው ልኩን ማወቁ ነው። የዳዊትን ግብዣ ያልተቀበለው ተጨማሪ ኃላፊነት ለመሸከም ብቁ እንዳልሆነ ስለተሰማው አሊያም የጡረታ ዘመኑን ዘና ብሎ ማሳለፍ ስለፈለገ አልነበረም። ይህን ያደረገው ያለበት ሁኔታ እንደተቀየረና የአቅም ገደብ እንዳለበት አምኖ ስለተቀበለ ነው። ከአቅሙ በላይ የሆነ የኃላፊነት ሸክም መሸከም አልፈለገም። (ገላ. 6:4, 5) ሥልጣን፣ ኃላፊነት ወይም እውቅና በማግኘት ላይ ትኩረት ካደረግን በውስጣችን የራስ ወዳድነትና የፉክክር መንፈስ ሊያቆጠቁጥ ይችላል፤ ይህም የኋላ ኋላ ለሐዘን ይዳርገናል። (ገላ. 5:26) ከዚህ በተቃራኒ ግን ልካችንን ማወቃችን ከወንድሞቻችን ጋር ተባብረን በመሥራት፣ ችሎታችንንና አቅማችንን ለአምላክ ክብር ለማምጣትና ሌሎችን ለመርዳት እንድንጠቀምበት ያነሳሳናል።—1 ቆሮ. 10:31፤ w17.01 4:5, 6
ዓርብ፣ ጥቅምት 26
አምላክ የሠራውን እያንዳንዱን ነገር ተመለከተ፤ እነሆ፣ እጅግ መልካም ነበር!—ዘፍ. 1:31
ይሖዋ በጣም አስደናቂ የሆነ ፈጣሪ ነው። የፍጥረት ሥራዎቹ በሙሉ ተወዳዳሪ አይገኝላቸውም። (ኤር. 10:12) ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ለሁሉም የፍጥረት ሥራዎቹ ገደብ አበጅቷል። ሁሉም ነገር እርስ በርስ ተቀናጅቶ መሥራት እንዲችል የተፈጥሮ ሕጎችንና የሥነ ምግባር ደንቦችን አውጥቷል። (መዝ. 19:7-9) በመሆኑም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች በሙሉ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የየራሳቸው ቦታና ድርሻ አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ የስበት ሕግ ከባቢ አየር ምንጊዜም በምድር ዙሪያ እንዲኖር ያደርጋል፤ እንዲሁም የባሕር ሞገድንና ውቅያኖሶችን ይቆጣጠራል። የስበት ኃይል ባይኖር ኖሮ በምድር ላይ ሕይወት አይኖርም ነበር። ይሖዋ ለፍጥረት ሥራዎቹ ያወጣቸው ገደቦች በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ፍጹም የሆነ ሥርዓት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ አድርገዋል። እንዲህ ያለ ሥርዓት መኖሩ አምላክ ምድርንም ሆነ የሰውን ዘር ሲፈጥር ዓላማ እንዳለው በግልጽ ያሳያል። በአገልግሎታችን ላይ የምናገኛቸውን ሰዎች፣ ይህን አስደናቂ አጽናፈ ዓለም የፈጠረውን አምላክ እንዲያውቁ ልንረዳቸው እንችላለን።—ራእይ 4:11፤ w17.02 1:4, 5
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 27
ሙሴን አምላክ በቁጥቋጦው ውስጥ በተገለጠለት መልአክ አማካኝነት ገዢና ነፃ አውጪ አድርጎ ላከው።—ሥራ 7:35
ሙሴን ተክቶ የእስራኤል መሪ የሆነው ኢያሱ፣ የአምላክን ሕዝቦች እየመራ ከከነዓናውያን ጋር በተዋጋበት ወቅት “የይሖዋ ሠራዊት አለቃ” ረድቶታል። (ኢያሱ 5:13-15፤ 6:2, 21) ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ደግሞ ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ ኢየሩሳሌምን ሊወር ከመጣው አስፈሪ የአሦራውያን ሠራዊት ጋር ተፋጥጦ ነበር። በዚህ ጊዜ “የይሖዋ መልአክ ወጥቶ በአሦራውያን ሰፈር የነበሩትን 185,000 ሰዎች [በአንድ ሌሊት] ገደለ።” (2 ነገ. 19:35) እርግጥ ነው፣ መላእክቱ ፍጹማን ቢሆኑም የእነሱን እርዳታ ያገኙት ሰዎች ፍጹማን አልነበሩም። ለምሳሌ፣ ሙሴ በአንድ ወቅት ለይሖዋ ክብር ሳይሰጥ ቀርቷል። (ዘኁ. 20:12) ኢያሱ የአምላክን መመሪያ ሳይጠይቅ ከገባኦናውያን ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል። (ኢያሱ 9:14, 15) ሕዝቅያስም ቢሆን በአንድ ወቅት “ልቡ ታብዮ” ነበር። (2 ዜና 32:25, 26) እነዚህ ሰዎች ፍጽምና የጎደላቸው ቢሆኑም እንኳ እስራኤላውያን የእነሱን አመራር መከተል ይጠበቅባቸው ነበር። ይሖዋ፣ በመላእክቱ ተጠቅሞ እነዚህን ሰዎች ደግፏቸዋል። በእርግጥም ሕዝቡን የሚመራው ይሖዋ ነበር። w17.02 3:7-9
እሁድ፣ ጥቅምት 28
በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ለበጉ በረከት፣ ክብር፣ ግርማና ኃይል ለዘላለም ይሁን።—ራእይ 5:13
አንድን ሰው ማክበር ሲባል ለዚያ ሰው የተለየ ትኩረትና ከፍ ያለ ግምት መስጠት ማለት ነው። ትልቅ ግምት የሚሰጠው ሥራ ያከናወኑ ወይም ለየት ያለ የኃላፊነት ቦታ ያላቸው ሰዎች እንዲህ ያለ ክብር እንደሚሰጣቸው የታወቀ ነው። በመሆኑም በዚህ ርዕስ ውስጥ አክብሮት ማሳየት ያለብን ለማን እንደሆነና እንዲህ ዓይነቱን ክብር መስጠታችን ተገቢ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመረምራለን። ራእይ 5:13 ‘በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውና በጉ’ ክብር እንደሚገባቸው ይናገራል። በዚሁ መጽሐፍ ምዕራፍ 4 ላይ ደግሞ ይሖዋ ክብር ይገባዋል እንድንል ከሚያደርጉን ምክንያቶች አንዱ ተገልጿል። በሰማይ ያሉ መንፈሳዊ ፍጥረታት ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ “ለዘላለም የሚኖረውን” ይሖዋን እንዲህ እያሉ ያወድሱታል፦ “ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ እንዲሁም ወደ ሕልውና የመጡትም ሆነ የተፈጠሩት በአንተ ፈቃድ ስለሆነ ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።”—ራእይ 4:9-11፤ w17.03 1:1, 2
ሰኞ፣ ጥቅምት 29
በገዛ ልቡ የሚታመን ሁሉ ሞኝ ነው።—ምሳሌ 28:26
ብዙ ሰዎች ‘ልብህ የሚልህን አድርግ’ ሲሉ ይሰማሉ። እንዲህ ማድረግ ግን አደገኛ ሊሆን ይችላል። ደግሞም ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፍጹም ያልሆነውን ልባችንን ተከትለን ወይም በስሜት ተገፋፍተን ውሳኔ እንዳናደርግ ያሳስበናል። ልባችን የሚለንን መከተል የሚያመጣውን አስከፊ መዘዝ የሚያሳዩ ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው እናገኛለን። ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን ልባችንን ማመን አንችልም፤ ምክንያቱም “ልብ ከምንም ነገር በላይ ከዳተኛ ነው፤ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ አይመለስም።” (ኤር. 3:17፤ 13:10፤ 17:9፤ 1 ነገ. 11:9) ውሳኔ ስናደርግ ልባችን የሚለንን በመከተል ስሜታችን በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ብንፈቅድ ውጤቱ ምን ይሆናል? ለምሳሌ ያህል፣ በተበሳጨንበት ወቅት ውሳኔ ብናደርግ ምን ሊፈጠር ይችላል? ከዚህ ቀደም በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ውሳኔ አድርገን ከነበረ መልሱ አይጠፋንም። (ምሳሌ 14:17፤ 29:22) ተስፋ በቆረጥንበት ጊዜም ቢሆን ጥሩ ውሳኔ ማድረግ እንደማንችል የታወቀ ነው። (ዘኁ. 32:6-12፤ ምሳሌ 24:10) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎችን ስናደርግ ስሜታችን እንዲቆጣጠረን ከፈቀድን በቀላሉ ልንሳሳት እንችላለን። w17.03 2:12, 13
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 30
እባክህ ይሖዋ ሆይ፣ በታማኝነትና በሙሉ ልብ በፊትህ እንዴት እንደተመላለስኩ [አስታውስ]።—2 ነገ. 20:3
ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን ብዙ ጊዜ ስህተት እንሠራለን። ደስ የሚለው ነገር ግን፣ ንስሐ እስከገባንና በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን በትሕትና ምሕረት እስከጠየቅን ድረስ ይሖዋ ‘እንደ ኃጢአታችን አያደርግብንም።’ (መዝ. 103:10) ያም ቢሆን ዳዊት ለሰለሞን እንደነገረው በየዕለቱ ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ተቀባይነት እንዲያገኝ እሱን ‘በሙሉ ልብ ማገልገል’ ይኖርብናል። (1 ዜና 28:9) አምላክን “በሙሉ ልብ” ማገልገል ሲባል ምንጊዜም ለእሱ ሙሉ በሙሉ ያደሩ መሆንን ያካትታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ልብ” የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው የአንድን ሰው ውስጣዊ ማንነት ነው። ይህም ምኞቱን፣ አስተሳሰቡን፣ ዝንባሌውን፣ አመለካከቱን፣ ችሎታውን፣ ግቦቹንና አንድን ነገር ለማድረግ የሚገፋፋውን ስሜት ያጠቃልላል። በመሆኑም ይሖዋን በሙሉ ልቡ የሚያገለግል ሰው ግብዝ አይደለም። ይሖዋን የሚያመልከው ለይስሙላ አይደለም። እኛም ፍጽምና የጎደለን ሰዎች ብንሆንም እንኳ ከግብዝነት በመራቅ ምንጊዜም ለአምላክ ሙሉ በሙሉ ያደርን ከሆንን በሙሉ ልባችን ልናገለግለው እንችላለን።—2 ዜና 19:9፤ w17.03 3:1, 3
ረቡዕ፣ ጥቅምት 31
[ይሖዋ] ትሑት የሆነውን ሰው ይመለከታል፤ ትዕቢተኛውን ግን ወደ እሱ እንዲቀርብ አይፈቅድም።—መዝ. 138:6
ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ስናከናውን ወይም ሌሎች ሲያመሰግኑን ምን እናደርጋለን? በዚህ ጊዜ ይሖዋ ‘እኛን ለመፈተንና በልባችን ያለው እንዲታወቅ ለማድረግ ሲል ይተወን’ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድም በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ የሚያቀርበውን ንግግር ለመዘጋጀት ብዙ ለፍቷል እንበል። ታዲያ ላቀረበው ንግግር ብዙዎች ሲያመሰግኑት ምን ይሰማዋል? ሌሎች ሲያመሰግኑን ኢየሱስ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ጠቃሚ ነው፦ “እናንተም የተሰጣችሁን ሥራ ሁሉ ባከናወናችሁ ጊዜ ‘ምንም የማንጠቅም ባሪያዎች ነን። ያደረግነው ልናደርገው የሚገባንን ነገር ነው’ በሉ።” (ሉቃስ 17:10) ሕዝቅያስ ከሠራው ስህተት ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ሕዝቅያስ ልቡ ስለታበየ “ለተደረገለት መልካም ነገር አድናቆት ሳያሳይ [ቀርቷል]።” (2 ዜና 32:24-27, 31) ይሖዋ ባደረገልን በርካታ መልካም ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን እሱ የሚጠላውን ዝንባሌ እንድናስወግድ ይረዳናል። በታማኝነት ለሕዝቡ ድጋፍ ስለሚያደርገው ስለ ይሖዋ ለሌሎች በአድናቆት መናገራችን ጠቃሚ ነው። w17.03 4:12-14