የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es19 ገጽ 26-36
  • መጋቢት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጋቢት
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2019
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ዓርብ፣ መጋቢት 1
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 2
  • እሁድ፣ መጋቢት 3
  • ሰኞ፣ መጋቢት 4
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 5
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 6
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 7
  • ዓርብ፣ መጋቢት 8
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 9
  • እሁድ፣ መጋቢት 10
  • ሰኞ፣ መጋቢት 11
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 12
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 13
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 14
  • ዓርብ፣ መጋቢት 15
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 16
  • እሁድ፣ መጋቢት 17
  • ሰኞ፣ መጋቢት 18
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 19
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 20
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 21
  • ዓርብ፣ መጋቢት 22
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 23
  • እሁድ፣ መጋቢት 24
  • ሰኞ፣ መጋቢት 25
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 26
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 27
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 28
  • ዓርብ፣ መጋቢት 29
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 30
  • እሁድ፣ መጋቢት 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2019
es19 ገጽ 26-36

መጋቢት

ዓርብ፣ መጋቢት 1

ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ።—ፊልጵ. 2:3

በጉባኤያችሁ ውስጥ ባሕርይው ብዙም የማይጥምህ ሰው አለ? ስለ ግለሰቡ ያለህን አሉታዊ አመለካከት ለማስተካከል ምንም ዓይነት ጥረት ካላደረግክ ይህ ስሜትህ ሥር እየሰደደ ሊሄድ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ እንግዳ ተቀባይ መሆን ከሌሎች ጋር እንዲያውም ከጠላቶቻችን ጋር እንኳ ያለንን ግንኙነት ለማሻሻል እንደሚረዳ ይናገራል። (ምሳሌ 25:21, 22) ሌሎችን መጋበዛችን በመካከላችን ያለውን ቅሬታ ለማስወገድና ሰላማዊ ግንኙነት ለመመሥረት ይረዳናል። አንድን ሰው በእንግድነት ማስተናገዳችን፣ ይሖዋ ይህን ግለሰብ ወደ እውነት እንዲስበው ያደረጉትን ግሩም ባሕርያት ለማስተዋል አጋጣሚ ይፈጥርልናል። (ዮሐ. 6:44) በፍቅር ተነሳስተን አንድን ሰው መጋበዛችን ግንኙነታችን ሙሉ በሙሉ እንዲለወጥ ሊያደርግ ይችላል። ወንድሞችህን ለመጋበዝ የሚያነሳሳህ ፍቅር እንዲሆን ምን ማድረግ ትችላለህ? ፍቅር ለማዳበር የሚረዳህ አንዱ መንገድ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በተግባር ማዋል ነው። ወንድሞቻችን ወይም እህቶቻችን ከእኛ የሚበልጡባቸውን መንገዶች ለምሳሌ እምነታቸውን፣ ጽናታቸውን፣ ድፍረታቸውን ወይም ያሏቸውን ሌሎች ክርስቲያናዊ ባሕርያት ለማስተዋል ጥረት ካደረግን ለእነሱ ያለን ፍቅር ይጠናከራል፤ ከልብ ተነሳስተን እነሱን በእንግድነት መቀበልም ቀላል ይሆንልናል። w18.03 17 አን. 18-19

ቅዳሜ፣ መጋቢት 2

ይሖዋ . . . ማንም እንዲጠፋ [አይፈልግም]።—2 ጴጥ. 3:9

አንዳንድ ወላጆች ከተወገደ ልጃቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ታዛዥነት ማሳየት በጣም ተፈታታኝ ሊሆንባቸው ይችላል። የተወገደች ልጇ ከቤት የወጣችን አንዲት እናት ምሳሌ እንመልከት። እናትየዋ እንዲህ ስትል በሐቀኝነት ተናግራለች፦ “ከልጄና ከልጅ ልጄ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ስል በጽሑፎቻችን ላይ ከወጡት ሐሳቦች መካከል ትንሽ ክፍተት የሚሰጠኝ ነገር ለማግኘት እሞክር ነበር።” አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ግን የልጃችን ጉዳይ ከእኛ እጅ እንደወጣና በጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ መግባት እንደሌለብን እንዳስተውል በደግነት ረድቶኛል።” ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ልጃቸው ወደ ጉባኤ ተመለሰች። እናትየዋ እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ አምላክን እንደታዘዝን ስለምታውቅ ለእኛ ጥልቅ አክብሮት አላት።” እናንተም የተወገደ ልጅ ካላችሁ ‘በሙሉ ልባችሁ በይሖዋ ለመታመንና በገዛ ራሳችሁ ማስተዋል ላለመመካት’ ጥረት ታደርጋላችሁ? (ምሳሌ 3:5, 6) ይሖዋ በሚሰጠው ተግሣጽና መመሪያ ላይ እምነት ይኑራችሁ። የይሖዋን ትእዛዝ መፈጸም ከወላጅ አንጻር በጣም ቢከብዳችሁም እንኳ እንዲህ ከማድረግ ወደኋላ አትበሉ። አዎ፣ ከአምላክ ተግሣጽ ጋር የሚስማማ እንጂ የሚቃረን ነገር አታድርጉ። w18.03 31 አን. 12-13

እሁድ፣ መጋቢት 3

ሂዱና . . . ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ።—ማቴ. 28:19

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው በስንት ዓመቱ መጠመቅ እንዳለበት የሚገልጽ መመሪያ አይሰጥም። በማቴዎስ 28:19 ላይ “ደቀ መዛሙርት አድርጉ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል፣ ሰዎችን ተከታይ ወይም ደቀ መዝሙር የማድረግ ግብ ይዞ ማስተማር የሚል መልእክት ያስተላልፋል። ደቀ መዝሙር የሚባለው፣ ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገሮች የተማረና በሚገባ የተረዳ እንዲሁም ያወቀውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚጥር ሰው ነው። በመሆኑም ሁሉም ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጆቻቸውን ከሕፃንነታቸው አንስቶ በማስተማር የተጠመቁ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ የመርዳት ግብ ሊኖራቸው ይገባል። እርግጥ ነው፣ ሕፃናት ለመጠመቅ ብቁ አይሆኑም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው ትናንሽ ልጆችም እንኳ የቅዱሳን መጻሕፍትን እውነት መረዳትና ለተማሩት ነገር አድናቆት ማዳበር ይችላሉ። ለምሳሌ ጢሞቴዎስ፣ ገና በልጅነቱ እውነትን የራሱ ያደረገ ደቀ መዝሙር ነው። ጢሞቴዎስ ጠንካራ እምነት አዳብሯል። (2 ጢሞ. 1:5፤ 3:14, 15) በአሥራዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ወይም በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ አካባቢ እያለ፣ በጉባኤ ውስጥ ልዩ የአገልግሎት መብቶችን ለመቀበል የሚያስፈልገውን ብቃት አሟልቶ ነበር።—ሥራ 16:1-3፤ w18.03 9 አን. 4-5

ሰኞ፣ መጋቢት 4

አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ ይሂድ።—ኤፌ. 4:23

የአምላክ አገልጋዮች ለመሆን ስንል መላ ሕይወታችንን የሚነካ ትልቅ ለውጥ አድርገናል። ከተጠመቅን በኋላም ቢሆን ለውጥ ማድረጋችንን አላቆምንም። ማናችንም ብንሆን ፍጹማን አይደለንም፤ በመሆኑም ለውጥ ማድረጋችንን መቀጠል ያስፈልገናል። (ፊልጵ. 3:12, 13) ወጣትም ሆንን አዋቂ እያንዳንዳችን እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘መንፈሳዊ አስተሳሰብ በማዳበር ረገድ ማሻሻያ እያደረግኩ እንደሆነ ይሰማኛል? ክርስቶስን ይበልጥ እየመሰልኩ ነው? ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ያለኝ አመለካከት እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ ስገኝ የማሳየው ምግባር ስለ መንፈሳዊ አቋሜ ምን ይናገራል? ንግግሬ በሕይወቴ ውስጥ ለማግኘት ስለምመኘው ነገር ምን ያሳያል? የጥናት ልማዴ፣ አለባበሴና አጋጌጤ እንዲሁም ሌሎች ሲመክሩኝ የምሰጠው ምላሽ ስለ እኔ ምን ይጠቁማል? ትክክል ያልሆነ ነገር ለማድረግ ስፈተን ምን እርምጃ እወስዳለሁ? መሠረታዊ ከሆኑ ነገሮች አልፌ ጎልማሳ ክርስቲያን ወደ መሆን ደረጃ ደርሻለሁ?’ (ኤፌ. 4:13) ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ በመንፈሳዊ ምን ያህል እድገት እንዳደረግን ለመገምገም ያስችለናል። w18.02 24 አን. 4-5

ማክሰኞ፣ መጋቢት 5

አምላኩ ይሖዋ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!—መዝ. 144:15

የምንኖረው በሰው ዘር ታሪክ በዓይነቱ ልዩ በሆነ ዘመን ውስጥ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስቀድሞ እንደተነገረው ይሖዋ “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ . . . እጅግ ብዙ ሕዝብ” እየሰበሰበ ነው። ደስተኛ የሆኑት እነዚህ ሰዎች “ቀንና ሌሊት [ለአምላክ] ቅዱስ አገልግሎት እያቀረቡለት” ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ያቀፈ “ኃያል ብሔር” ሆነዋል። (ራእይ 7:9, 15፤ ኢሳ. 60:22) በእርግጥም አምላክንና ባልንጀሮቻቸውን የሚወዱ ብዛት ያላቸው ሰዎች የኖሩበት እንዲህ ያለ ዘመን ታይቶ አያውቅም። በሌላ በኩል ግን ከላይ ከተጠቀሰው በጣም የተለየ ዓይነት ፍቅር የሚያሳዩ ሰዎችም በዚህ ዘመን እንደሚኖሩ ቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድመው ተናግረዋል፤ ከአምላክ የራቁት እነዚህ ሰዎች የሚያሳዩት ፍቅር ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “በመጨረሻዎቹ ቀናት . . . ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ . . . ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞ. 3:1-4) እነዚህ ሰዎች የሚያሳዩት ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ፍቅር ለአምላክ ካለን ፍቅር ጋር ይቃረናል። እንዲያውም እንዲህ ያለው ፍቅር፣ ዓለማችን ራስ ወዳድ በሆኑ ግለሰቦች የተሞላና “ለመቋቋም የሚያስቸግር” እንዲሆን አድርጓል። w18.01 22 አን. 1-2

ረቡዕ፣ መጋቢት 6

ይሖዋን የሚፈልጉ . . . ሁሉን ነገር መረዳት ይችላሉ።—ምሳሌ 28:5

ኖኅ ያገኘው ትክክለኛ እውቀት እምነትና አምላካዊ ጥበብ እንዲያዳብር ረድቶታል፤ ይህም ከተለያዩ አደጋዎች በተለይም ከመንፈሳዊ አደጋ ጠብቆታል። ለምሳሌ ኖኅ “ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ” ስለነበር ፈሪሃ አምላክ ከሌላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነት አልመሠረተም። በወቅቱ የነበሩ እምነት የለሽና ሞኝ ሰዎች ሥጋ የለበሱት አጋንንት በነበራቸው ከሰው በላይ የሆነ ችሎታ ተደምመው እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ምናልባትም አንዳንዶቹ እነዚህን አጋንንት ማምለክ ጀምረው ሊሆን ይችላል። ኖኅ ግን በዚህ ፈጽሞ አልተታለለም። (ዘፍ. 6:1-4, 9) በተጨማሪም ኖኅ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት” የሚለው ትእዛዝ የተሰጠው ለሰው ልጆች እንደሆነ ያውቅ ነበር። (ዘፍ. 1:27, 28) በመሆኑም በሴቶችና ሥጋ በለበሱ መላእክት መካከል የሚደረገው የፆታ ግንኙነት ስህተትና ከተፈጥሮ ውጭ እንደሆነ ሳይገነዘብ አልቀረም። በዚህ መንገድ የተወለዱት ልጆች ከሰው ልጆች በጣም የተለዩ መሆናቸው ደግሞ ተጨማሪ ማረጋገጫ እንደሆነለት ምንም ጥርጥር የለውም። ከጊዜ በኋላ አምላክ ለኖኅ በምድር ላይ የጥፋት ውኃ እንደሚያመጣ የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ሰጠው። ኖኅ በዚህ ማስጠንቀቂያ ላይ እምነት ማሳደሩ መርከቡን እንዲሠራ ያነሳሳው ሲሆን ይህም ቤተሰቡን ለማትረፍ አስችሎታል።—ዕብ. 11:7፤ w18.02 9 አን. 8

ሐሙስ፣ መጋቢት 7

አሁን የሆንኩትን ለመሆን የበቃሁት በአምላክ ጸጋ ነው።—1 ቆሮ. 15:10

ከባድ ኃጢአት ፈጽመህ ከሆነ ይሖዋ ወደ ቀድሞ መንፈሳዊ አቋምህ እንድትመለስ ሊረዳህ ይፈልጋል። ሆኖም በጉባኤው አማካኝነት ባደረገው ዝግጅት መጠቀም ይኖርብሃል። (ምሳሌ 24:16፤ ያዕ. 5:13-15) የዘላለም ሕይወት ማግኘትህ በዚህ ላይ የተመካ ነው፤ እንግዲያው እርምጃ ለመውሰድ አትዘግይ! ይሁንና ይሖዋ ኃጢአትህን ይቅር ካለልህ ከዓመታት በኋላም የጥፋተኝነት ስሜት የሚያሠቃይህ ቢሆን ምን ማድረግ ትችላለህ? ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ቀደም ሲል በፈጸማቸው ስህተቶች ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ሕሊናው ይወቅሰው ነበር። “እኔ የአምላክን ጉባኤ አሳድድ ስለነበር ከሐዋርያት ሁሉ የማንስና ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነኝ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮ. 15:9) ጳውሎስ ቀደም ሲል ስህተት የፈጸመ ቢሆንም ይሖዋ ተቀብሎታል፤ ደግሞም ሐዋርያው ይህን እንዲገነዘብ ይሖዋ ይፈልግ ነበር። አንተም ቀደም ሲል ለፈጸምከው ኃጢአት ከልብህ ንስሐ ከገባህ ብሎም እንደ አስፈላጊነቱ ሽማግሌዎችን ካነጋገርክ፣ ይሖዋ ምሕረት እንደሚያደርግልህ መተማመን ትችላለህ። ይሖዋ ይቅር እንዳለህ አምነህ ተቀበል!—ኢሳ. 55:6, 7፤ w18.01 11 አን. 17-18

ዓርብ፣ መጋቢት 8

ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።—ያዕ. 4:8

ከይሖዋ ጋር የመሠረትከውን ወዳጅነት ይዘህ ለመቀጠል፣ እሱ ሲያናግርህ ማዳመጥ እንዲሁም ሐሳብህን ለእሱ መግለጽ ያስፈልግሃል። ይሖዋ ሲናገር ማዳመጥ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን ማጥናት ነው። ይህም የአምላክን ቃል እና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችንን በማንበብ እንዲሁም ባነበብነው ላይ በማሰላሰል እውቀት መቅሰምን ይጨምራል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንዲሁ የአእምሮ እውቀት ለማካበት ተብሎ የሚደረግ ነገር እንዳልሆነ አስታውስ። ወይም ደግሞ የትምህርት ቤት ፈተና ለማለፍ እንደምታደርገው መረጃዎችን ሸምድዶ የመያዝ ጉዳይ አይደለም። ውጤታማ የሆነ ጥናት፣ አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅ ከሚያስችል አስደሳች ጉዞ ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ እንዲህ ያለው ጥናት ስለ ይሖዋ ማንነት ከዚህ በፊት የማታውቃቸውን ነገሮች ለመገንዘብ ያስችልሃል። ይህ ደግሞ ወደ አምላክ ለመቅረብ ይረዳሃል፤ እሱም በምላሹ ወደ አንተ ይቀርባል። የይሖዋ ድርጅት፣ የጥናት ፕሮግራምህ ውጤታማ እንዲሆን የሚረዱህ የተለያዩ መሣሪያዎችን አዘጋጅቷል። ለምሳሌ፣ jw.org/am ላይ የሚወጡት “ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?” ለተባለው መጽሐፍ የተዘጋጁት የማጥኛ ጽሑፎች፣ የምታምንባቸው ነገሮች በአሳማኝ ማስረጃ ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ያስችሉሃል።—መዝ. 119:105፤ w17.12 25 አን. 8-9

ቅዳሜ፣ መጋቢት 9

በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም።—ኢሳ. 11:9

እንዲህ ያለ የተረጋጋ ሁኔታ የሚኖረው ‘ምድር በይሖዋ እውቀት ስለምትሞላ’ እንደሆነ ልብ እንበል። እንስሳት ስለ ይሖዋ መማር ስለማይችሉ ይህ ትንቢት በምሳሌያዊ ሁኔታ ፍጻሜውን የሚያገኘው በሰዎች ላይ መሆን አለበት። (ኢሳ. 11:6, 7) በአንድ ወቅት እንደ ተኩላ ጨካኞች የነበሩ ብዙ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር ችለዋል። ከእነዚህ መካከል የአንዳንዶቹን ተሞክሮ jw.org/am ላይ “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” በሚሉት ርዕሶች ሥር ማግኘት ይቻላል። ቀደም ሲል ጨካኝ የነበሩና ለውጥ ያደረጉ ሰዎች “እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና [ለብሰዋል]።” (ኤፌ. 4:23, 24) እነዚህ ሰዎች ስለ አምላክ ይበልጥ እያወቁ ሲሄዱ እሱ ያወጣቸውን መሥፈርቶች መከተል እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። በመሆኑም ከሚያምኑባቸው ነገሮች፣ ከአመለካከታቸውና ከምግባራቸው ጋር በተያያዘ ለውጥ ለማድረግ ይነሳሳሉ። እንዲህ ያሉ ለውጦችን ማድረግ ቀላል ባይሆንም የአምላክን ፈቃድ የማድረግ ልባዊ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ይሖዋ በመንፈሱ ይረዳቸዋል። w18.01 31 አን. 15-16

እሁድ፣ መጋቢት 10

ሆኖም እያንዳንዱ በራሱ ተራ [ሕያው] ይሆናል።—1 ቆሮ. 15:23

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰማያዊው ትንሣኤ ስለሚከናወንበት መንገድ ሲናገር “እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል” ይላል። በምድር ላይ ለመኖር ከሞት የሚነሱት ሰዎች ትንሣኤም በተደራጀ መልኩ እንደሚከናወን መተማመን እንችላለን። ይህ በጉጉት የምንጠብቀው ክንውን ነው። የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ከጀመረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ በዘመናችን የሞቱ ሰዎች በቅድሚያ ከሞት ተነስተው ከሚያውቋቸው ሰዎች ጋር ይገናኙ ይሆን? አመራር የመስጠት ችሎታ ያላቸው በጥንት ዘመን የኖሩ ታማኝ አገልጋዮች፣ በአዲሱ ዓለም ውስጥ የአምላክን ሕዝቦች በማደራጀቱ ሥራ እንዲካፈሉ ሲባል በቅድሚያ ከሞት ይነሱ ይሆን? ፈጽሞ ይሖዋን አገልግለው ስለማያውቁ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች የሚነሱት መቼ እና የት ነው? ከዚህ ጋር የተያያዙ በርካታ ጥያቄዎች ይፈጠሩብን ይሆናል። ይሁን እንጂ ስለ እነዚህ ነገሮች አሁን መጨነቅ ያስፈልገናል? እዚያው ደርሰን ይሖዋ እነዚህን ነገሮች እንዴት እንደሚያከናውን እስክናይ መጠበቁ የተሻለ አይሆንም? እስከዚያው ድረስ ግን አምላክ በመታሰቢያ መቃብር ያሉትን ሙታን እንደሚያስነሳቸው ያለንን እምነት ማጠናከር ይኖርብናል፤ ይሖዋ ይህን እንደሚያደርግ በኢየሱስ በኩል አረጋግጦልናል።—ዮሐ. 5:28, 29፤ 11:23፤ w17.12 12 አን. 20-21

ሰኞ፣ መጋቢት 11

ሚስቶች ሆይ፣ የክርስቶስ ተከታዮች ሊያደርጉት የሚገባ ስለሆነ ለባሎቻችሁ ተገዙ። ባሎች ሆይ፣ ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ፤ መራራ ቁጣም አትቆጧቸው። ልጆች ሆይ፣ በሁሉም ነገር ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።—ቆላ. 3:18-20

በዛሬው ጊዜ ያሉ ባሎች፣ ሚስቶችና ልጆችም ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ቢያደርጉ እንደሚጠቀሙ ጥርጥር የለውም። ባሎች “ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ፤ መራራ ቁጣም አትቆጧቸው” የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል። አፍቃሪ የሆነ ባል፣ የሚስቱን ሐሳብ በማዳመጥና የእሷን ሐሳብ ከፍ አድርጎ በመመልከት ሚስቱን እንደሚያከብር ያሳያል። (1 ጴጥ. 3:7) ሚስቱ ያለችውን ሁሉ ይፈጽማል ማለት ባይሆንም ውሳኔ ከማድረጉ በፊት እሷን ማማከሩ የተሻለ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ይረዳዋል። (ምሳሌ 15:22) አፍቃሪ የሆነ ባል፣ ሚስቱ እንድታከብረው ከመጠየቅ ይልቅ በራሷ ተነሳስታ እንድታከብረው በሚያደርግ መንገድ ይይዛታል። አንድ ባል፣ ሚስቱንና ልጆቹን የሚወድ ከሆነ ቤተሰቡ ይሖዋን በደስታ ያገለግላል፤ እንዲሁም የሕይወትን ሽልማት አብረው ይወርሳሉ። w17.11 28 አን. 12፤ 29 አን. 15

ማክሰኞ፣ መጋቢት 12

በዓለም . . . ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።—ቆላ. 2:8

ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ደብዳቤ የጻፈው በሮም ለመጀመሪያ ጊዜ ታስሮ በነበረበት ወቅት ማለትም ከ60-61 ዓ.ም. ገደማ ባለው ጊዜ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ “መንፈሳዊ ግንዛቤ” የማዳበርን ማለትም ነገሮችን ይሖዋ በሚያይበት መንገድ የማየትን አስፈላጊነት ለእምነት ባልንጀሮቹ ጠቁሟቸዋል። (ቆላ. 1:9) አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ይህን የምለው ማንም ሰው አግባብቶ እንዳያታልላችሁ ነው። በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዓለም መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁም በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።” (ቆላ. 2:4, 8) ከዚህም ሌላ ጳውሎስ፣ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው አንዳንድ አስተሳሰቦች ትክክል ያልሆኑበትን ምክንያት እንዲሁም ዓለማዊ አስተሳሰብ ፍጽምና የጎደላቸውን ሰዎች ትኩረት የሚስበው ለምን እንደሆነ አብራርቷል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ዓለማዊ አስተሳሰብ ካለው ጥበበኛ እንደሆነና ከሌሎች እንደሚበልጥ ሊሰማው ይችላል። ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው ወንድሞች፣ ከዓለማዊ አስተሳሰብና ትክክል ካልሆኑ ልማዶች እንዲርቁ ለመርዳት ሲል ነው።—ቆላ. 2:16, 17, 23፤ w17.11 20 አን. 1

ረቡዕ፣ መጋቢት 13

እጅህ ወይም እግርህ ቢያሰናክልህ ቆርጠህ ጣለው።—ማቴ. 18:8

አንድ ክርስቲያን የይሖዋን ምሕረት ላለማጣት የትኞቹን ነገሮች መተው ሊያስፈልገው ይችላል? አንድን ነገር በጣም የሚወደው ቢሆንም እንኳ ወደ ኃጢአት ሊመራው የሚችል ከሆነ ለመተው ፈቃደኛ መሆን አለበት። (ማቴ. 18:9) አንዳንድ ጓደኞችህ ይሖዋን የሚያሳዝን ነገር እንድትፈጽም የሚገፋፉህ ከሆነ ከእነሱ ጋር ያለህን ግንኙነት ታቋርጣለህ? ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ ራስህን ለመግዛት እየታገልክ ከሆነ ከልክ በላይ እንድትጠጣ ሊፈትኑህ ከሚችሉ ሁኔታዎች ትርቃለህ? የብልግና ምኞቶች ወደ አእምሮህ እየመጡ የሚያስቸግሩህ ከሆነ ርኩስ ሐሳቦችን ከሚቀሰቅሱ ፊልሞች፣ ድረ ገጾች ወይም ድርጊቶች በሙሉ ለመራቅ ጥረት ታደርጋለህ? ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ላለማጉደል ስንል ማንኛውንም ዓይነት መሥዋዕት ብንከፍል የሚያስቆጭ አይሆንም። የእሱን ሞገስ እንዳጣን ማሰብ ከሚፈጥረው ስሜት የከፋ ምንም ነገር የለም። በሌላ በኩል ደግሞ የይሖዋን “ዘላለማዊ ታማኝ ፍቅር” ማግኘት ከሚፈጥረው ደስታ የሚበልጥ ነገር የለም።—ኢሳ. 54:7, 8፤ w17.11 11 አን. 12

ሐሙስ፣ መጋቢት 14

ይህ በመላው ምድር ላይ የሚወጣው እርግማን ነው፤ ምክንያቱም የሚሰርቁ ሁሉ . . . አልተቀጡም።—ዘካ. 5:3

ዘካርያስ 5:4 ‘እርግማኑ ወደ ሌባው ቤት ይገባል፤ በዚያም ቤት ውስጥ ይቀመጣል፤ ቤቱንም ይበላዋል’ እንደሚል ልብ በል። የይሖዋን የቅጣት ፍርድ አጥር በማጠር ወይም በር በመቆለፍ መከላከል አይቻልም። ይሖዋ በሕዝቡ መካከል የተፈጸመውን የትኛውንም የተደበቀ ኃጢአት ያጋልጣል። ግለሰቡ የስርቆት ድርጊቱን ከባለሥልጣናት፣ ከአሠሪዎቹ፣ ከሽማግሌዎች ወይም ከወላጆቹ ሊደብቅ ይችል ይሆናል፤ ማንኛውንም ዓይነት ስርቆት ገሃድ እንደሚያወጣ ቃል ከገባው አምላክ ግን ምንም ነገር መደበቅ አይቻልም። (ዕብ. 4:13) በእርግጥም “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር” ጥረት በሚያደርጉ ሰዎች መካከል መሆን በጣም አስደሳች ነው! (ዕብ. 13:18) ይሖዋ ማንኛውንም ዓይነት ስርቆት ይጠላል። እኛም ይሖዋ ካወጣቸው የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖር ትልቅ ክብር እንደሆነ ስለሚሰማን በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ ከሚያመጣ ከማንኛውም ድርጊት እንርቃለን። ደግሞም እንዲህ ማድረጋችን ሆን ብለው የይሖዋን ሕጎች በሚጥሱ ሰዎች ላይ ከሚመጣው የቅጣት ፍርድ እንድንተርፍ ያስችለናል። w17.10 22 አን. 6-7

ዓርብ፣ መጋቢት 15

አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት አድርጉ።—ኤፌ. 4:3

ወንድሞቻችን በተሳሳተ መንገድ እንደተረዱን ወይም እንደበደሉን በሚሰማን ጊዜም እንኳ ከእነሱ ጋር ያለንን ሰላማዊ ግንኙነት ይዘን ለመቀጠል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን። (ሮም 12:17, 18) አንድን ሰው የሚጎዳ ነገር በምንፈጽምበት ጊዜ ይቅርታ መጠየቃችን የግለሰቡን ስሜት ሊጠግነው ይችላል፤ ሆኖም ይቅርታ ስንጠይቅ ከልባችን መሆን አለበት። በተለይ ደግሞ በትዳር ውስጥ ሰላም በጣም አስፈላጊ ነው። አንድ ባልና ሚስት ሰው ፊት ሲሆኑ የሚዋደዱ እየመሰሉ ለብቻቸው በሚሆኑበት ጊዜ ግን የሚኮራረፉ፣ ኃይለ ቃል የሚነጋገሩ አሊያም አንዳቸው ሌላውን የሚማቱ ከሆነ እውነተኛ ፍቅር አላቸው ሊባል አይችልም። አንድ ሰው ሲበድለን በደሉን ይቅር ለማለትና እሱን በተመለከተ የሚሰማንን ቅሬታ ለማስወገድ ፈቃደኞች መሆን አለብን። ከልብ ይቅር ብለናል ሊባል የሚችለው በልባችን ውስጥ ምንም ዓይነት ‘የበደል መዝገብ ከሌለ’ ነው፤ ይህ ደግሞ አስተሳሰባችንን መቆጣጠርን ይጠይቃል። (1 ቆሮ. 13:4, 5) ቅሬታ እንዲያድርብን የምንፈቅድ ወይም ቂም የምንይዝ ከሆነ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድናም አደጋ ላይ ይወድቃል።—ማቴ. 6:14, 15፤ w17.10 10 አን. 14-15

ቅዳሜ፣ መጋቢት 16

እኔን ወደ እናንተ የላከኝ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንደሆነ ታውቃላችሁ።—ዘካ. 6:15

የዘካርያስ መልእክት በዘመኑ በነበሩት አይሁዳውያን ላይ ምን ስሜት አሳድሮባቸው ይሆን? ይሖዋ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸውና ሥራውን የሚያስቆመው ምንም ነገር እንደማይኖር ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። ቤተ መቅደሱ እንደሚገነባ የሰጣቸው ይህ ዋስትና የዛለው ልባቸው በተስፋ እንዲሞላ አድርጎ መሆን አለበት። ይሁንና ጥቂት የሆኑት አይሁዳውያን ይህን ከባድ ሥራ ዳር ማድረስ የሚችሉት እንዴት ነው? ዘካርያስ ቀጥሎ የተናገረው ሐሳብ በውስጣቸው ሊፈጠር የሚችለውን ማንኛውንም ፍርሃት ወይም ጥርጣሬ የሚያስወግድ ነበር። እንደ ሄልዳይ፣ ጦቢያህና የዳያህ ያሉ ታማኝ ሰዎች ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ሰዎች ‘በይሖዋ ቤተ መቅደስ የግንባታ ሥራ እንደሚካፈሉ’ አምላክ ተናግሯል። አይሁዳውያኑ አምላክ እንደሚረዳቸው በመተማመን ወዲያውኑ ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን በፋርስ ንጉሥ የተጣለው እገዳ ቢኖርም ግንባታውን ማከናወናቸውን ቀጠሉ። ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ የተራራ ያህል ግዙፍ የነበረው እንቅፋት ማለትም በግንባታ ሥራው ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ አደረገ፤ በመሆኑም በ515 ዓ.ዓ. የቤተ መቅደሱ ግንባታ ተጠናቀቀ። (ዕዝራ 6:22፤ ዘካ. 4:6, 7) ይሁንና ይሖዋ የገባው ቃል በዘመናችን ከዚህ እጅግ የላቀ ፍጻሜ ያገኛል። w17.10 29 አን. 17

እሁድ፣ መጋቢት 17

ደፋር . . . ሁን፤ ሥራህንም ጀምር።—1 ዜና 28:20

ሰለሞን በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ የመገንባቱን ሥራ በበላይነት የመከታተል ኃላፊነት ተሰጥቶታል፤ ይህ ሥራ በታሪክ ዘመናት ከተከናወኑት የግንባታ ሥራዎች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። ምክንያቱም ሕንፃው “እጅግ የሚያምር ከመሆኑ የተነሳ ዝናውም ሆነ ውበቱ በመላው ምድር የታወቀ ይሆናል።” ከሁሉ በላይ ደግሞ ይህ ሕንፃ “የእውነተኛው አምላክ የይሖዋ ቤት” ነው። ይሖዋ፣ ሰለሞን ይህን የግንባታ ሥራ በበላይነት እንዲከታተል መመሪያ ሰጥቷል። (1 ዜና 22:1, 5, 9-11) ንጉሥ ዳዊት፣ ሰለሞን የአምላክ ድጋፍ እንደማይለየው እርግጠኛ ነበር፤ ሆኖም ሰለሞን “ገና ወጣት” ከመሆኑም ሌላ ‘ተሞክሮ አልነበረውም።’ ታዲያ ደፋር በመሆን ይህን ኃላፊነት ይቀበል ይሆን? ወጣትና ተሞክሮ የሌለው መሆኑ እንቅፋት ይፈጥርበት ይሆን? ሰለሞን እንዲሳካለት ከፈለገ ደፋር መሆንና ሥራውን መጀመር ነበረበት። ሰለሞን ደፋር ካልሆነ በፍርሃት ሊሽመደመድና ሥራውን ከመጀመር ወደኋላ ሊል ይችላል፤ ሥራውን ጨርሶ አለመጀመር ደግሞ ከሁሉ የከፋ ነው፤ ከዚህ ይልቅ ጀምሮ ሳይሳካለት ቢቀር ይሻላል። እኛም ልክ እንደ ሰለሞን ደፋር ለመሆን የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል፤ ይህም እሱ የሰጠንን ሥራ ለማከናወን ያስችለናል። w17.09 28 አን. 1-2፤ 29 አን. 4-5

ሰኞ፣ መጋቢት 18

የአምላካችን ቃል . . . ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።—ኢሳ. 40:8

መጽሐፍ ቅዱስ ባይኖር ሕይወትህ ምን ሊመስል እንደሚችል አስበህ ታውቃለህ? የዕለት ተዕለት ሕይወትህን የምትመራበት አስተማማኝ መመሪያ ልታገኝ አትችልም። አምላክን፣ ሕይወትንና የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ለሚፈጠሩብህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ የምታገኝበት ምንም መንገድ አይኖርም። እንዲሁም ይሖዋ በጥንት ጊዜ ከሰው ልጆች ጋር ስለነበረው ግንኙነት ልታውቅ አትችልም። ደስ የሚለው ነገር እንዲህ ያለ አሳዛኝ ሁኔታ አላጋጠመንም። ምክንያቱም ይሖዋ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። በውስጡ ያለው መልእክት ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖርም ዋስትና ሰጥቶናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ በአንድ ወቅት ኢሳይያስ 40:8⁠ን ጠቅሶ ተናግሮ ነበር። በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው “የይሖዋ ቃል” የሚለው አገላለጽ በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያመለክት ባይሆንም በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን መልእክት ለማመልከት ሊሠራበት ይችላል። (1 ጴጥ. 1:24, 25) ባለፉት መቶ ዘመናት የኖሩ ቅን ልብ ያላቸው ግለሰቦች ብዙ መሥዋዕት ቢያስከፍላቸውም ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲተረጎሙና እንዲሰራጩ አድርገዋል። የእነዚህ ሰዎች ፍላጎት ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ነው፤ የአምላክ ፈቃድ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።”—1 ጢሞ. 2:3, 4፤ w17.09 18 አን. 1-2

ማክሰኞ፣ መጋቢት 19

አንቺ . . . ሚስቱ [ነሽ]። ታዲያ እንዲህ ያለውን እጅግ መጥፎ ድርጊት በመፈጸም በአምላክ ላይ እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?—ዘፍ. 39:9

በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ወጣት ክርስቲያኖች ዮሴፍ የደረሰበት ዓይነት ፈተና ይደርስባቸዋል። (ዘፍ. 39:7) ኪም ያጋጠማትን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። አብረዋት ከሚማሩት ልጆች መካከል አብዛኞቹ የፆታ ግንኙነት ይፈጽሙ ነበር፤ ከሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በኋላ ሲገናኙ አብዛኛውን ጊዜ የሚያወሩት እንዲህ በማድረግ ስላሳለፉት ጊዜ ነው። ኪም ግን በዚህ ረገድ ልትናገረው የምትችለው ምንም ነገር የለም። ከሌሎች የተለየች በመሆኗ አንዳንድ ጊዜ ‘እንደተተወችና ብቸኛ እንደሆነች’ እንደሚሰማት በሐቀኝነት ተናግራለች፤ በተጨማሪም የወንድ ጓደኛ ባለመያዟ እኩዮቿ እንደ ሞኝ እንደሚመለከቷት ገልጻለች። ይሁንና ኪም ወጣቶች የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ የሚደርስባቸው ፈተና ከባድ እንደሆነ ተገንዝባ ነበር። (2 ጢሞ. 2:22) አብረዋት የሚማሩት ልጆች በተደጋጋሚ ‘አሁንም ድንግል ነሽ?’ እያሉ ይጠይቋታል። ይህም የፆታ ግንኙነት የማትፈጽምበትን ምክንያት የምታስረዳበት አጋጣሚ እንድታገኝ አስችሏታል። የፆታ ብልግና እንዲፈጽሙ የሚደረግባቸውን ግፊት ለመቋቋም ቁርጥ ውሳኔ ያደረጉ ወጣቶቻችንን በጣም እንኮራባቸዋለን፤ ይሖዋም ቢሆን እንደሚኮራባቸው ምንም ጥርጥር የለውም! w17.09 4 አን. 8፤ 5 አን. 10

ረቡዕ፣ መጋቢት 20

ተበሳጭተህ ክፉ ነገር አትሥራ።—መዝ. 37:8

በቀላሉ ቱግ የሚሉ ሰዎች ቁጣቸውን የሚገልጹት በስድብ ነው። እንዲህ ያለው ባሕርይ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ደስታን እንደሚያሳጣ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ቁጣን፣ ስድብንና ጩኸትን እንድናስወግድ የሚመክረን አለምክንያት አይደለም። (ኤፌ. 4:31) የሚያሳዝነው እንዲህ ያለው ምግባር አብዛኛውን ጊዜ ወደ ጠብ ይመራል። በምንኖርበት ዓለም ውስጥ በተለያየ መንገድ ቁጣን መግለጽ የተለመደ ነገር እንደሆነ ተደርጎ ይታያል፤ ይሁንና እንዲህ ያለው ምግባር ፈጣሪያችንን አያስከብርም። በመሆኑም በርካታ ሰዎች እነዚህን ጎጂ ልማዶች ማስወገድና አዲሱን ስብዕና መልበስ አስፈልጓቸዋል። (ቆላ. 3:8-10) ከስድብ በተጨማሪ የመዋሸት ልማድም የአሮጌው ስብዕና አንዱ ክፍል ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙ ሰዎች የሚጠበቅባቸውን ግብር ላለመክፈል ወይም ለሠሩት ስህተት ኃላፊነት ላለመውሰድ ሲሉ መዋሸታቸው የተለመደ ነው። ይሖዋ ግን “የእውነት አምላክ” ነው። (መዝ. 31:5) በመሆኑም የእሱ አገልጋይ የሆነ ‘እያንዳንዱ’ ግለሰብ ‘ከባልንጀራው ጋር እውነትን እንዲነጋገር’ እንዲሁም ‘እንዳይዋሽ’ ይጠብቅበታል። (ኤፌ. 4:25፤ ቆላ. 3:9) ስለዚህ ሊያሳፍረን ወይም ከባድ ሊሆንብን ቢችልም እንኳ እውነቱን መናገር ይኖርብናል።—ምሳሌ 6:16-19፤ w17.08 18 አን. 3, 5፤ 20 አን. 12-13, 15

ሐሙስ፣ መጋቢት 21

ቃሉም በፍጥነት ይሮጣል።—መዝ. 147:15

በዛሬው ጊዜ ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ይመራናል። “ቃሉም በፍጥነት ይሮጣል”፤ ይህም ይሖዋ፣ ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ መንፈሳዊ አመራር እንደሚሰጠን ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ፣ “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች በመመርመር፣ JW ብሮድካስቲንግን በመመልከት፣ jw.org ላይ የሚወጡ ነገሮችን በመከታተል፣ የጉባኤ ሽማግሌዎችን በማነጋገር እንዲሁም ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር በመቀራረብ የምታገኘውን ጥቅም እስቲ አስበው። (ማቴ. 24:45) ይሖዋ የሚያስፈልግህን አመራር በፍጥነት እንደሚሰጥህ በሕይወትህ አልተመለከትክም? መዝሙራዊው፣ የጥንቶቹ የይሖዋ ሕዝቦች በአምላክ ዘንድ ልዩ ቦታ እንደነበራቸው ያውቅ ነበር። አምላክ “ቃሉን” እንዲሁም “ሥርዓቱንና ፍርዶቹን” የሰጠው ለእነሱ ብቻ ነው። (መዝ. 147:19, 20) በዛሬው ጊዜም በምድር ላይ ካሉ ሰዎች መካከል፣ በአምላክ ስም የምንጠራው እኛ ብቻ ነን፤ ይህም ታላቅ መብት ነው። ይሖዋን ስለምናውቅ፣ ቃሉ በሕይወታችን ውስጥ ስለሚመራን እንዲሁም ከእሱ ጋር ልዩ ዝምድና መመሥረት ስለቻልን አመስጋኞች ነን። እንደ መዝሙር 147 ጸሐፊ ሁሉ አንተም “ያህን አወድሱ!” እንድትል እንዲሁም ሌሎችም ይህን እንዲያደርጉ እንድታበረታታ የሚያነሳሱ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉህ አይሰማህም? w17.07 20 አን. 15-16፤ 21 አን. 18

ዓርብ፣ መጋቢት 22

ወታደር ሆኖ የሚያገለግል ማንኛውም ሰው ለውትድርና የመለመለውን ሰው ደስ ማሰኘት ስለሚፈልግ ራሱን በንግድ ሥራ አያጠላልፍም።—2 ጢሞ. 2:4

በዛሬው ጊዜ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን ጨምሮ በምድር ላይ ያሉ የኢየሱስ ተከታዮች በሙሉ፣ ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ይጥራሉ። የማስታወቂያው ኢንዱስትሪና በዓለም ላይ ያሉ ሌሎች ነገሮች የሚያሳድሩባቸውን ጫና ይቋቋማሉ፤ እነዚህ ክርስቲያኖች ‘ተበዳሪ የአበዳሪው ባሪያ ነው’ የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት አይዘነጉም። (ምሳሌ 22:7) ሰይጣን፣ እሱ ለሚቆጣጠረው የንግድ ሥርዓት ባሪያ ሆነን ጊዜያችንን እና ጉልበታችንን በሙሉ ስናባክን የማየትን ያህል የሚያስደስተው ነገር የለም። የምናደርጋቸው አንዳንድ ውሳኔዎች ለዓመታት ዕዳ ውስጥ እንድንዘፈቅ ሊያደርጉን ይችላሉ። አንዳንዶች ቤት ወይም መኪና ለመግዛት፣ ከፍተኛ ትምህርት ለመማር ሌላው ቀርቶ ድል ያለ ሠርግ ለመደገስ ሲሉ ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ይገባሉ። አኗኗራችንን ቀላል በማድረግ፣ አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ ባለመግባት እንዲሁም ወጪዎቻችንን በመቀነስ አርቆ አሳቢ መሆናችንን ማሳየት እንችላለን፤ ይህን ስናደርግ ለዚህ ዓለም የንግድ ሥርዓት ሳይሆን ለይሖዋ ባሪያ መሆን እንችላለን።—1 ጢሞ. 6:10፤ w17.07 10 አን. 13

ቅዳሜ፣ መጋቢት 23

የምታስተምረው ትምህርት በሙሉ ትክክል እንደሆነ አምናለሁ፤ የሐሰትን መንገድ ሁሉ እጠላለሁ።—መዝ. 119:128

ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ የመሆን መብት አለው። ሥልጣኑን የሚጠቀምበት ፍጹም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ነው። ይሖዋ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “በምድር ላይ ታማኝ ፍቅር የማሳየው፣ ደግሞም ፍትሕና ጽድቅ የማሰፍነው እኔ ይሖዋ [ነኝ፤] . . . በእነዚህ ነገሮች ደስ እሰኛለሁና።” (ኤር. 9:24) ይሖዋ ትክክልና ፍትሐዊ የሆነውን ነገር ለመለየት ሰዎች ያወጡትን ሕግ መመልከት አያስፈልገውም። ከዚህ ይልቅ ትክክል የሆነውን ነገር ለማወቅ የሚያስችል መሥፈርት ያወጣው እሱ ራሱ ነው። በመሆኑም ፍጹም በሆነው የፍትሕ መሥፈርቱ ላይ የተመሠረተ ሕግ ለሰው ልጆች ሰጥቷል። “ጽድቅና ፍትሕ [የዙፋኑ] መሠረት ናቸው፤” ስለሆነም ሕጎቹ፣ መሠረታዊ ሥርዓቶቹና ውሳኔዎቹ በሙሉ ትክክል እንደሆኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝ. 89:14) ሰይጣን ‘የይሖዋ አገዛዝ ፍትሐዊ አይደለም’ የሚል ክስ ቢሰነዝርም እሱ ራሱ በዓለም ላይ ፍትሕ እንዲሰፍን ማድረግ አልቻለም። w17.06 28 አን. 5

እሁድ፣ መጋቢት 24

ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ . . . ቃልህ እውነት ነው።—2 ሳሙ. 7:28

ይሖዋ የእውነት አምላክ ነው። (መዝ. 31:5) ለጋስ አባት እንደመሆኑ መጠን ለሚፈሩት ሰዎች መለኮታዊ እውነቶችን ይገልጥላቸዋል። እውነትን መጀመሪያ ከሰማንበት ጊዜ አንስቶ ከቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ከክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን፣ እንዲሁም ከትላልቅና ሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን የተለያዩ እውነቶችን ስንማር ቆይተናል። በጊዜ ሂደት ተጨማሪ እውነቶችን እያገኘን ስንሄድ ኢየሱስ የገለጸው ዓይነት አሮጌና አዲስ እውነቶችን የያዘ ‘የከበረ ሀብት ማከማቻ’ ይኖረናል። (ማቴ. 13:52) እነዚህን እውነቶች ልክ እንደተሸሸገ ሀብት የምንፈልጋቸው ከሆነ ይሖዋ ‘የከበረ ሀብት ማከማቻችንን’ ውድ በሆኑ አዳዲስ እውነቶች እንድንሞላ ይረዳናል። (ምሳሌ 2:4-7) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ጥሩ የግል ጥናት ልማድ ማዳበር እንዲሁም በአምላክ ቃልና በጽሑፎቻችን ላይ ጥልቅ ምርምር ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን ከዚህ በፊት የማናውቃቸውን ‘አዳዲስ’ እውነቶች እናገኛለን። (ኢያሱ 1:8, 9፤ መዝ. 1:2, 3) አዎ፣ ‘የከበረ ሀብት ማከማቻችንን’ በመለኮታዊ እውነቶች ለመሙላት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ አለብን። w17.06 12 አን. 13-14

ሰኞ፣ መጋቢት 25

እናንተም ትጠሩኛላችሁ፤ ወደ እኔም ቀርባችሁ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ።—ኤር. 29:12

አንድ ያላገባ ወጣት ወንድም “የሚያገቡ ሰዎች በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል” በሚለው በ1 ቆሮንቶስ 7:28 ላይ በሚገኘው ሐሳብ ላይ ሲያሰላስል በአእምሮው ውስጥ አንዳንድ ጥያቄዎች ተፈጠሩ። በመሆኑም ባለትዳር የሆነን በዕድሜ የገፋ የጉባኤ ሽማግሌ ቀርቦ እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “እዚህ ላይ የተጠቀሰው ‘መከራ’ ምንድን ነው? ደግሞስ ካገባሁ ይህን ‘መከራ’ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?” ሽማግሌው ጥያቄውን ከመመለሱ በፊት ይሖዋ ‘በሚደርስብን መከራ [“ፈተና፣” ግርጌ] ሁሉ የሚያጽናናን የመጽናናት ሁሉ አምላክ’ እንደሆነ የሚገልጸውን ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፈውን ሐሳብ ጠቀሰለት። (2 ቆሮ. 1:3, 4) በእርግጥም ይሖዋ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ የሚያጽናናን አፍቃሪ አባታችን ነው። አንተም ምናልባት በአንድ ወቅት እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ አምላክ በቃሉ አማካኝነት ድጋፍ እና መመሪያ ሰጥቶህ እንደነበረ ታስታውስ ይሆናል። ይሖዋ፣ እንደ ጥንት አገልጋዮቹ ሁሉ እኛም የተሻለውን ነገር እንድናገኝ ይፈልጋል።—ኤር. 29:11፤ w17.06 4 አን. 1-2

ማክሰኞ፣ መጋቢት 26

ይሖዋ የባዕድ አገር ሰዎችን ይጠብቃል።—መዝ. 146:9

ስደተኛ የሆኑ ወንድሞቻችን ከቁሳዊ እርዳታ ይበልጥ የሚያስፈልጋቸው ነገር መንፈሳዊና ስሜታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት ነው። (ማቴ. 4:4) ሽማግሌዎች፣ እነሱ በሚናገሩት ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎችን በመስጠት እንዲሁም የእነሱን ቋንቋ ከሚናገሩ ወንድሞች ጋር በማገናኘት ሊረዷቸው ይችላሉ። በርካታ ስደተኞች በጣም ከሚቀርቧቸው ዘመዶቻቸው፣ ጎረቤቶቻቸውና የጉባኤያቸው አባላት ተለያይተዋል። በመካከላችን ሲሆኑ ይሖዋ እንደሚወዳቸውና እንደሚያስብላቸው እንዲሰማቸው ልናደርግ ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ባሕላቸውንና ያሳለፉትን ሕይወት ከሚያውቁ የማያምኑ ዘመዶቻቸው አሊያም የአገራቸው ሰዎች ጋር ለመቀራረብ ሊፈተኑ ይችላሉ። (1 ቆሮ. 15:33) በጉባኤ ውስጥ የባይተዋርነት ስሜት እንዳይሰማቸው የምናደርግ ከሆነ “የባዕድ አገር ሰዎችን ይጠብቃል” ከተባለለት ከይሖዋ ጋር አብረን የመሥራት መብት እናገኛለን። በስደት ወደ ሌላ አገር የሄዱ አንዳንድ ሰዎች አሳዳጆቻቸው በሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ወደ አገራቸው መመለስ አይችሉ ይሆናል። ከዚህም ሌላ በርካቶች አስከፊ ድርጊቶች ሲፈጸሙ በመመልከታቸው ለከባድ የስሜት ጉዳት ተዳርገዋል። ‘እኔ በእነሱ ቦታ ብሆን ኖሮ ምን እንዲደረግልኝ እፈልግ ነበር?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ።—ማቴ. 7:12፤ w17.05 6-7 አን. 15-16

ረቡዕ፣ መጋቢት 27

ክፋት እየበዛ ስለሚሄድ የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል።—ማቴ. 24:12

በተስፋ መቁረጥ ስሜት ከተሸነፍን እምነታችን ሊዳከምና ለአምላክ ያለን ፍቅር ሊቀዘቅዝ ይችላል። ሰይጣን በሚቆጣጠረው በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ሁላችንም ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎች አልፎ አልፎ ያጋጥሙናል። (1 ዮሐ. 5:19) ምናልባትም ከዕድሜ መግፋት፣ ከጤና መታወክ ወይም ከኢኮኖሚያዊ ችግሮች ጋር እየታገልን ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ ብቃት የለኝም የሚለው ስሜት፣ የጠበቅናቸው ነገሮች አለመፈጸማቸው ወይም የግል ድክመቶቻችን ይረብሹን ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች ወይም ስሜቶች፣ ይሖዋ እንደተወን እንዲሰማን ፈጽሞ ሊያደርጉን አይገባም። እንዲያውም ይሖዋ ለእኛ ስላለው ጽኑ ፍቅር በሚገልጹ ሐሳቦች ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። በመዝሙር 136:23 ላይ የሚገኘው “መንፈሳችን ተደቁሶ በነበረበት ጊዜ አስታወሰን፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” የሚለው ሐሳብ እንዲህ ያለ ማበረታቻ ይሰጠናል። በእርግጥም ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ያለው ታማኝ ፍቅር ምንጊዜም አይለወጥም። በመሆኑም ይሖዋ “እርዳታ ለማግኘት [የምናቀርበውን] ልመና” እንደሚሰማና ምላሽ እንደሚሰጠን እርግጠኛ መሆን እንችላለን።—መዝ. 116:1፤ 136:24-26፤ w17.05 18 አን. 8

ሐሙስ፣ መጋቢት 28

የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላላችሁ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።—ማቴ. 6:15

ገላትያ 2:11-14 ላይ እንደተገለጸው ጴጥሮስ የሰው ፍርሃት ወጥመድ ሆኖበት ነበር። (ምሳሌ 29:25) ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት በሚገባ ቢያውቅም በኢየሩሳሌም ባለው ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ የተገረዙ አይሁዳውያን ምን ይሉኛል የሚል ፍርሃት አደረበት። ሐዋርያው ጳውሎስ በአንጾኪያ ጴጥሮስን በግልጽ የተቃወመው ሲሆን ግብዝነቱንም አጋልጧል። (ሥራ 15:12፤ ገላ. 2:13) ጴጥሮስ፣ ጳውሎስ የሰጠውን እርማት በትሕትና እንደተቀበለ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። ጴጥሮስ መብቶቹን እንዳጣ የሚገልጽ ዘገባ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑ ሁለት ደብዳቤዎችን በመንፈስ መሪነት ጽፏል። የጉባኤው ራስ የሆነው ኢየሱስ በእሱ መጠቀሙን ቀጥሎ ነበር። (ኤፌ. 1:22) በመሆኑም የጉባኤው አባላት ይቅር ባይ በመሆን ኢየሱስንና አባቱን መምሰል የሚችሉበት አጋጣሚ ነበራቸው። ፍጽምና የጎደለው ሰው በሠራው ስህተት ምክንያት፣ ከጉባኤው አባላት መካከል የተሰናከለ እንደማይኖር ተስፋ እናደርጋለን። w17.04 27 አን. 16-18

ዓርብ፣ መጋቢት 29

ፈሪሃ አምላክ ለሌላቸው ሰዎች ለወደፊቱ ምሳሌ እንዲሆኑ [አምላክ] የሰዶምና የገሞራ ከተሞችን አመድ በማድረግ ፈርዶባቸዋል።—2 ጴጥ. 2:6

ይሖዋ ያንን አካባቢ በማጥፋት የወሰደው እርምጃ በዚያ የነበረውን ክፋት ከማስወገዱም ሌላ ዛሬ ባሉት ‘ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች’ ላይ ምን እንደሚያደርግ የሚያሳይ “ምሳሌ” ሆኗል። ይሖዋ በዚያ ወቅት ይፈጸም የነበረውን ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት በሙሉ እንዳስወገደው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያለውን ሥርዓት በማጥፋት ምድርን ከማንኛውም መጥፎ ድርጊት ያጸዳል። ታዲያ መጥፎ ድርጊቶች በምን ይተካሉ? ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የሚኖሩት ሰዎች አስደሳች በሆኑ ሥራዎች ይጠመዳሉ። ይህችን ፕላኔት ወደ ገነትነት መቀየር እንዲሁም ለራሳችንም ሆነ ለምንወዳቸው ሰዎች ቤቶችን መሥራት ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን እስቲ አስበው። በተጨማሪም ከሞት የሚነሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የመቀበልና እነዚህን ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲሁም ለሰው ልጆች ስላደረጋቸው ነገሮች የማስተማር አጋጣሚ ይኖረናል። (ኢሳ. 65:21, 22፤ ሥራ 24:15) በዚያን ጊዜ ለእኛ ደስታ ለይሖዋ ደግሞ ውዳሴ በሚያመጡ ሥራዎች እንጠመዳለን! w17.04 12 አን. 11-12

ቅዳሜ፣ መጋቢት 30

ሊቀበለኝ ከቤቴ በር የሚወጣው ማንኛውም ሰው የይሖዋ ይሆናል።—መሳ. 11:31

ዮፍታሔ ይህን ስእለት ሲሳል እሱን ለመቀበል ከቤቱ የምትወጣው ሴት ልጁም ልትሆን እንደምትችል ሳያውቅ አይቀርም። ይህን አወቀም አላወቀ፣ ስእለቱን ለመፈጸም እሱም ሆነ ልጁ ትልቅ መሥዋዕት መክፈል እንደሚጠይቅባቸው ጥያቄ የለውም። ዮፍታሔ፣ ልጁን ባያት ጊዜ “ልብሱን ቀደደ፤ እንዲህም አለ፦ ‘ወዮ፣ ልጄ! ልቤን ሰበርሽው።’” ልጁም ‘ስለ ድንግልናዋ አለቀሰች።’ እንዲህ የተሰማቸው ለምንድን ነው? ዮፍታሔ ወንድ ልጅ አልነበረውም፤ ያለችው አንዲት ልጅ ደግሞ ከዚያ በኋላ ስለማታገባና ልጅ ስለማትወልድ ዮፍታሔ የልጅ ልጆች ማየት አይችልም። የቤተሰቡን ስም የሚያስጠራ ዘር አይኖርም። ይሁን እንጂ ዮፍታሔና ልጁ ከራሳቸው ስሜት የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንዳለ ተገንዝበው ነበር። ዮፍታሔ “አንዴ ለይሖዋ ቃል ገብቻለሁ፤ ልመልሰውም አልችልም” አለ። ልጁም “የገባኸውን ቃል በእኔ ላይ ፈጽምብኝ” አለችው። (መሳ. 11:35-39) ዮፍታሔና ሴት ልጁ ታማኝ ሰዎች ነበሩ፤ ለሉዓላዊው አምላክ የገቡትን ቃል መፈጸም ከፍተኛ ዋጋ ቢያስከፍላቸውም ቃላቸውን ለማጠፍ ጨርሶ አላሰቡም።—ዘዳ. 23:21, 23፤ መዝ. 15:4፤ w17.04 4 አን. 5-6

እሁድ፣ መጋቢት 31

በትዕግሥት እጠብቃለሁ።—ሚክ. 7:7

ዮሴፍ ከባድ ግፍ ተፈጽሞበታል። በመጀመሪያ፣ ገና የ17 ዓመት ልጅ ሳለ ወንድሞቹ ለባርነት ሸጡት። ከዚያም የጌታውን ሚስት አስገድዶ ለመድፈር ሞክሯል በሚል ተከሶ እስር ቤት ገባ። (ዘፍ. 39:11-20፤ መዝ. 105:17, 18) ዮሴፍ ለፈጸመው የጽድቅ ሥራ ከመባረክ ይልቅ እየተቀጣ ያለ ይመስል ነበር። ከ13 ዓመት በኋላ ግን ሁኔታው በአንዴ ተቀየረ። ከእስር ቤት የተለቀቀ ሲሆን በግብፅ ውስጥ ሁለተኛው ከፍተኛ ባለሥልጣን ሆኖ ተሾመ። (ዘፍ. 41:14, 37-43፤ ሥራ 7:9, 10) ዮሴፍ የተፈጸመበት ግፍ እንዲመረር አድርጎት ነበር? ይሖዋ እንደተወው ተሰምቶት ይሆን? በፍጹም። ዮሴፍ በትዕግሥት እንዲጠባበቅ የረዳው ምንድን ነው? በይሖዋ ላይ የነበረው እምነት ነው። ይሖዋ ሁኔታዎችን እንደሚቆጣጠር እምነት ነበረው። ለወንድሞቹ የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ ዮሴፍ እንዲህ ያለ እምነት እንዳለው ያሳያል፦ “ምንም እንኳ እኔን ለመጉዳት አስባችሁ የነበረ ቢሆንም አምላክ ግን ይኸው ዛሬ እንደምታዩት ነገሩን ለመልካም አደረገው፤ የብዙ ሰዎችንም ሕይወት ለማዳን ተጠቀመበት።” (ዘፍ. 50:19, 20) በመጨረሻም ዮሴፍ በትዕግሥት መጠበቁ የሚያስገኘውን ውጤት ለማየት በቅቷል። w17.08 4 አን. 6፤ 6 አን. 12-13

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ