የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es19 ገጽ 37-46
  • ሚያዝያ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሚያዝያ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2019
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 1
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 2
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 3
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 4
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 5
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 6
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 7
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 8
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 9
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 10
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 11
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 12
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 13
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 14
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 15
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 16
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 17
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 18
  • የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ዕለት
    ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ
    ዓርብ፣ ሚያዝያ 19
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 20
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 21
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 22
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 23
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 24
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 25
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 26
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 27
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 28
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 29
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2019
es19 ገጽ 37-46

ሚያዝያ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 1

ሰዎችንም ስጦታ አድርጎ ሰጠ።—ኤፌ. 4:8

ውድ ስጦታ ከሆኑት ሽማግሌዎች ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ እነሱን በእምነታቸው በመምሰልና መልካም ምሳሌያቸውን በመከተል ነው። ሌላው መንገድ ደግሞ የሚሰጡንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በመቀበል ነው። (ዕብ. 13:7, 17) ሽማግሌዎች እንደሚወዱንና መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ እንደሚፈልጉ አትርሱ። ለምሳሌ ያህል፣ ከስብሰባዎች መቅረት እንደጀመርን ወይም ቅንዓታችን እየቀዘቀዘ እንደሆነ ካስተዋሉ ወዲያውኑ እኛን ለመርዳት ጥረት እንደሚያደርጉ የታወቀ ነው። ሐሳባችንን ስንገልጽ የሚያዳምጡን ከመሆኑም ሌላ ፍቅራዊ ማበረታቻና አስፈላጊውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በመስጠት በመንፈሳዊ ሊያጠናክሩን ይሞክራሉ። እንዲህ ያለው ማበረታቻ ይሖዋ ለአንተ ያለውን ፍቅር የሚያሳይ እንደሆነ ይሰማሃል? ወደ እኛ ቀርቦ አስፈላጊውን ምክር መስጠት ለሽማግሌዎች ቀላል እንደማይሆን ማስታወስ አለብን። ታዲያ በጉባኤህ ውስጥ ያሉትን ሽማግሌዎች ሸክም ማቅለል የምትችለው እንዴት ነው? ትሑት፣ በቀላሉ የምትቀረብና አመስጋኝ ሁን። እነሱ የሚሰጡህን እርዳታ አምላክ ለአንተ ያለው ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አድርገህ ተመልከተው። እንዲህ ማድረግህ ራስህን የሚጠቅምህ ከመሆኑም በላይ እነሱም ሥራቸውን በደስታ እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል። w18.03 31 አን. 15-16

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 2

ልጄ ሆይ፣ ለሚነቅፈኝ መልስ መስጠት እችል ዘንድ ጥበበኛ ሁን፤ ልቤንም ደስ አሰኘው።—ምሳሌ 27:11

ሁሉም ልጆች የተለያዩ እንደሆኑ ማስታወስ ያስፈልጋል፤ እድገት የሚያደርጉበት ፍጥነት ተመሳሳይ አይደለም። አንዳንዶች በትንሽነታቸው አእምሯዊና ስሜታዊ ብስለት ያዳብራሉ፤ በመሆኑም ገና ልጆች እያሉ መጠመቅ እንደሚፈልጉ ይገልጻሉ። ሌሎች ደግሞ ለመጠመቅ ዝግጁ የሚሆኑት ከፍ ካሉ በኋላ ሊሆን ይችላል። ከዚህ አንጻር፣ አስተዋይ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው እንዲጠመቁ ጫና አያደርጉም። ይልቁንም እያንዳንዱን ልጅ በራሱ ፍጥነት መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ይረዱታል። ወላጆች ልጆቻቸው በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ እንደተጠቀሰው ጥበብ የሚንጸባረቅበት እርምጃ ሲወስዱ ይደሰታሉ። ያም ቢሆን ግባቸው፣ ልጆቻቸው የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት መሆኑን ሊዘነጉ አይገባም። ስለሆነም ወላጆች ‘ልጄ ራሱን ለአምላክ ለመወሰንና ለመጠመቅ የሚያስችል በቂ እውቀት አለው?’ ብለው ራሳቸውን መጠየቃቸው አስፈላጊ ነው። w18.03 9 አን. 6

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 3

ጉዳት ላይ ሊጥለው ቢችልም እንኳ ቃሉን አያጥፍም።—መዝ. 15:4

የቀረበልንን ግብዣ ከተቀበልን ያለበቂ ምክንያት ቃላችንን ማጠፍ የለብንም። የጋበዘን ሰው እኛን ለማስተናገድ ብዙ ዝግጅት አድርጎ ሊሆን ይችላል፤ በመሆኑም ግብዣውን ከሰረዝን ልፋቱ ሁሉ መና ይቀራል። (ማቴ. 5:37) አንዳንዶች፣ የተሻለ እንደሆነ ያሰቡት ግብዣ ላይ ለመገኘት ሲሉ ቀደም ሲል የተቀበሉትን ግብዣ ይሰርዛሉ። ይህ ለወንድሞቻችን ፍቅርና አክብሮት እንዳለን ያሳያል? የጋበዘን ሰው የሚያቀርብልን ምንም ይሁን ምን ለግብዣው ልባዊ አድናቆት ማሳየት ይኖርብናል። (ሉቃስ 10:7) ከአቅማችን በላይ የሆነ ሁኔታ አጋጥሞን ግብዣውን ለመሰረዝ ከተገደድን ደግሞ ለጋበዘን ሰው እንደማንመጣ ወዲያውኑ በማሳወቅ ፍቅርና አሳቢነት እናሳይ። በእንግድነት በምንጋበዝበት ጊዜ የአካባቢውን ባሕል ማክበራችንም አስፈላጊ ነው። በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ ሳይጋበዙ ሰው ቤት መሄድ ምንም ችግር የለውም፤ በሌሎች ባሕሎች ግን አስቀድሞ ፕሮግራም መያዝ ይመረጣል። በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ እንግዶች የሚቀርብላቸውን ግብዣ ወዲያውኑ ከመቀበል ይልቅ ትንሽ መግደርደራቸው ተገቢ እንደሆነ ይታሰባል፤ ግብዣን ወዲያው አለመቀበል አክብሮት አለማሳየት እንደሆነ ተደርጎ የሚቆጠርባቸው ባሕሎችም አሉ። እንግዲያው የጋበዙንን ሰዎች ለማስደሰት የምንችለውን ሁሉ እናድርግ። w18.03 18 አን. 20-21

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 4

ወደ ጉልምስና ለመድረስ እንጣጣር።—ዕብ. 6:1

መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው ለመሆን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ብቻ በቂ እንዳልሆነ ማስታወስ ያስፈልጋል። (1 ነገ. 4:29, 30፤ 11:4-6) ታዲያ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ባለፈ ሌላ ምን የሚያስፈልገን ነገር አለ? መንፈሳዊ እድገት ማድረጋችንን መቀጠል ያስፈልገናል። (ቆላ. 2:6, 7) ይህን ለማድረግ ከሚረዱን ጠቃሚ እርምጃዎች አንዱ ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለውን መጽሐፍ ማጥናት ነው። ይህን መጽሐፍ አጥንተን መጨረሳችን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን ውስጥ እንዴት በሥራ ላይ ልናውላቸው እንደምንችል ለማስተዋል ይረዳናል። ይህን መጽሐፍ አጥንተን ከሆነ ደግሞ በእምነት ጸንተን ለመኖር የሚረዱ ሌሎች ጽሑፎችን ማጥናት እንችላለን። (ቆላ. 1:23) ከዚህም ሌላ ባጠናነው ነገር ላይ ማሰላሰል እንዲሁም ትምህርቱን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል ለማስተዋል እንዲረዳን ወደ ይሖዋ መጸለይ ያስፈልገናል። የምናጠናበትና የምናሰላስልበት ዓላማ፣ ይሖዋን የማስደሰትና ሕጎቹን የመታዘዝ ልባዊ ፍላጎት ማዳበር መሆን እንዳለበት ልንዘነጋ አይገባም። (መዝ. 40:8፤ 119:97) በተጨማሪም መንፈሳዊ እድገታችንን ሊገቱ ከሚችሉ ነገሮች ለመራቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል።—ቲቶ 2:11, 12፤ w18.02 24-25 አን. 7-9

ዓርብ፣ ሚያዝያ 5

[ኖኅ] በእምነት የሚገኘውን ጽድቅ ለመውረስ በቅቷል።—ዕብ. 11:7

እንደ ኖኅ በአምላክ ላይ እምነት ለማዳበር ትጉ የአምላክ ቃል ተማሪዎች መሆን፣ የተማርነው ነገር ወደ ልባችን ዘልቆ እንዲገባ ማድረግ እንዲሁም ያገኘነው እውቀት እንዲቀርጸንና እንዲመራን መፍቀድ ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 1:13-15) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ እምነትና አምላካዊ ጥበብ የምናገኝ ሲሆን ይህም ሰይጣን በሚሸርባቸው የተንኮል ዘዴዎችና በዚህ ዓለም ክፉ መንፈስ እንዳንታለል ጥበቃ ይሆነናል። (2 ቆሮ. 2:11) የዓለም መንፈስ ሰዎች ዓመፅንና የሥነ ምግባር ብልግናን እንዲወዱ እንዲሁም በሥጋ ምኞቶች ላይ እንዲያተኩሩ ያበረታታል። (1 ዮሐ. 2:15, 16) ሌላው ቀርቶ በመንፈሳዊ ደካማ የሆኑ ሰዎች ታላቁ የአምላክ ቀን መቅረቡን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ችላ እንዲሉ ሊያደርግ ይችላል። ኢየሱስ እኛ ያለንበትን ዘመን ከኖኅ ዘመን ጋር ሲያነጻጽር ትኩረት ያደረገው በዓመፅና በሥነ ምግባር ብልግና ላይ ሳይሆን መንፈሳዊ ነገሮችን ችላ ማለት በሚያስከትለው አደጋ ላይ እንደሆነ ልብ ማለት ይኖርብናል። (ማቴ. 24:36-39) በመሆኑም ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘አኗኗሬ ይሖዋን በትክክል እንደማውቀው ያሳያል? በአምላክ ላይ ያለኝ እምነት ከጽድቅ መሥፈርቶቹ ጋር ተስማምቶ ከመኖር ባለፈ ስለ እነዚህ መሥፈርቶች ለሌሎች እንድናገር ይገፋፋኛል?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ ‘ከእውነተኛው አምላክ ጋር እየሄድን’ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ይረዳናል።—ዘፍ. 6:9፤ w18.02 9-10 አን. 8-10

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 6

ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።—2 ጢሞ. 3:5

መጥፎ ባሕርያት ካላቸው ሰዎች ጨርሶ መራቅ እንደማንችል የታወቀ ነው። እንደነዚህ ካሉት ሰዎች ጋር በሥራ ቦታና በትምህርት ቤት መገናኘታችን አይቀርም፤ አሊያም አብረናቸው እንኖር ይሆናል። ሆኖም የእነሱ አስተሳሰብ እንዳይጋባብንና ባሕርያቸውን መኮረጅ እንዳንጀምር መጠንቀቅ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና ይሖዋን ከሚያገለግሉ ሰዎች ጋር በመቀራረብ መንፈሳዊነታችንን ማጠናከራችን ይህን ለማድረግ ይረዳናል። በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች አምላክን እንዲያውቁ መርዳት ይኖርብናል። ምሥራቹን ለመስበክ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን እንፈልግ፤ በተጨማሪም እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ በምናገኝበት ጊዜ የሰዎችን ልብ የሚነካ ነገር ለመናገር እንዲረዳን ይሖዋን እንጠይቀው። የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ሌሎች ሰዎች እንዲያውቁ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ ካደረግን መልካም ምግባራችን ለራሳችን ሳይሆን ለአምላክ ክብር ያመጣል። ይሖዋ “ፈሪሃ አምላክ በጎደለው መንገድ መኖርና ዓለማዊ ምኞቶችን መከተል ትተን አሁን ባለው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ፣ በጽድቅና ለአምላክ በማደር እንድንኖር” አሠልጥኖናል። (ቲቶ 2:11-14) አምላክን የሚያስደስቱ ባሕርያትን የምናንጸባርቅ ከሆነ ሌሎች ሰዎች ምግባራችንን ማስተዋላቸው አይቀርም፤ እንዲያውም አንዳንዶች “አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን” ሊሉ ይችላሉ።—ዘካ. 8:23፤ w18.01 31 አን. 17-18

እሁድ፣ ሚያዝያ 7

ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ [ይሆናሉ]።—2 ጢሞ. 3:2

ራስን መውደድ ስህተት ነው ማለት ነው? አይደለም፤ እንዲያውም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ራስን መውደድ፣ ተገቢ ከመሆኑም በላይ አስፈላጊ ነው። ይሖዋ የፈጠረን እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዲኖረን አድርጎ ነው። ኢየሱስም “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ብሏል። (ማር. 12:31) ራሳችንን የማንወድ ከሆነ ባልንጀራችንን መውደድ አንችልም። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል። ሚስቱን የሚወድ ሰው ራሱን ይወዳል፤ የገዛ አካሉን የሚጠላ ማንም ሰው የለምና፤ ከዚህ ይልቅ ይመግበዋል እንዲሁም ይሳሳለታል።” (ኤፌ. 5:28, 29) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው በተገቢው መጠን ራሳችንን ልንወድ ይገባል። በ2 ጢሞቴዎስ 3:2 ላይ የተጠቀሰው ዓይነት ፍቅር ተገቢ ከሆነው ፍቅር የተለየ ነው። ጳውሎስ የተናገረው ራሳቸውን ከመጠን በላይ ስለሚወዱ ሰዎች ነው። እንዲህ ያሉት ራስ ወዳድ ሰዎች ከሚገባው በላይ ስለ ራሳቸው ያስባሉ። (ሮም 12:3) በሕይወታቸው ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚሰጡት ለራሳቸው ስለሆነ ለሌሎች ያን ያህል ግድ የላቸውም። የሆነ ስህተት ሲፈጠር ጥፋታቸውን ከማመን ይልቅ በሌሎች ላይ ማሳበብ ይቀናቸዋል። ስለ ራሳቸው ብቻ የሚያስቡ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች እውነተኛ ደስታ የላቸውም። w18.01 23 አን. 4-5

ሰኞ፣ ሚያዝያ 8

አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ።—ቆላ. 3:15

የግል ጥናት ይሖዋ ሲያናግረን የምናዳምጥበት መንገድ ሲሆን ጸሎት ደግሞ ሐሳባችንን ለእሱ ለመግለጽ ያስችለናል። አንድ ክርስቲያን ጸሎት፣ አንድን ጉዳይ ለማሳካት የሚረዳ ምትሃታዊ ኃይል እንዳለው ሊያስብ አይገባም፤ አሊያም ጸሎትን በዘልማድ እንደሚከናወን የአምልኮ ሥርዓት አድርጎ ማየት የለበትም። ጸሎት ለፈጣሪያችን የልባችንን አውጥተን የምንገልጽበት መንገድ ነው። ይሖዋ ሐሳብህን ስትገልጽ መስማት ይፈልጋል። (ፊልጵ. 4:6) የሚያስጨንቅ ሁኔታ በሚያጋጥምህ ጊዜስ ምን ማድረግ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል” የሚል ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጥሃል። (መዝ. 55:22) ይህን ምክር መከተል በእርግጥ ጠቃሚ እንደሆነ ይሰማሃል? በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች በመጸለያቸው እንደተጠቀሙ ሊያረጋግጡልህ ይችላሉ። ጸሎት አንተንም ሊረዳህ ይችላል! ጸሎት፣ የይሖዋን እርዳታ ለመለመን እንደሚያስችል ዝግጅት ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም። አንዳንድ ጊዜ፣ አእምሯችን ባጋጠሙን ችግሮች ከመወጠሩ የተነሳ ያሉንን ብዙ በረከቶች ማስተዋል ሊሳነን ይችላል። በእያንዳንዱ ቀን አመስጋኝ ለመሆን የሚያነሳሱህን ቢያንስ ሦስት ነገሮች ቆም ብለህ ለማሰብ ለምን ግብ አታወጣም? ከዚያም ለእነዚህ በረከቶች ይሖዋን አመስግነው። w17.12 25-26 አን. 10-11

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 9

ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ እንድታገኝ የሚያስችሉህን ቅዱሳን መጻሕፍት ከጨቅላነትህ ጀምሮ አውቀሃል።—2 ጢሞ. 3:15

በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለይሖዋ ራሳቸውን ወስነው ይጠመቃሉ። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ በእውነት ቤት ያደጉና ከሁሉ በተሻለው የሕይወት ጎዳና ላይ ለመጓዝ የመረጡ ወጣቶች ናቸው። (መዝ. 1:1-3) ክርስቲያን ወላጆች ከሆናችሁ እናንተም ልጆቻችሁ የሚጠመቁበትን ቀን በጉጉት እንደምትጠባበቁ ጥርጥር የለውም። (ከ3 ዮሐንስ 4 ጋር አወዳድር።) ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ እንዲያውቁ እንደምትፈልጉ ጥርጥር የለውም። ቅዱሳን መጻሕፍት የሚለው አገላለጽ በዛሬው ጊዜ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትንና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ያጠቃልላል። ትናንሽ ልጆችም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱት ሰዎችና ክንውኖች መሠረታዊ የሆነ እውቀት መቅሰም ይችላሉ። የይሖዋ ድርጅት፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ የተለያዩ መሣሪያዎችን አዘጋጅቷል። ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ዝምድና ለመመሥረት ቁልፉ የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት እንደሆነ አስታውሱ። w17.12 18 አን. 1፤ 19 አን. 4

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 10

[ባል] የሚስቱ ራስ ነው።—ኤፌ. 5:23

ባለቤትሽ የማያምን ቢሆንና በተገቢው መንገድ እንደማይዝሽ ቢሰማሽ ምን ማድረግ ትችያለሽ? በዚህ ተበሳጭተሽ ከእሱ ጋር ብትጨቃጨቂ ሁኔታው ሊሻሻል ይችላል? በዚህ መንገድ፣ የምትፈልጊውን ነገር እንዲፈጽም ማድረግ ብትችዪ እንኳ ባለቤትሽ በአንቺ ምግባር ተማርኮ ወደ እውነት የመምጣቱ አጋጣሚ ጠባብ ይሆናል። በሌላ በኩል ግን የባልሽን የራስነት ሥልጣን ብታከብሪ፣ በቤተሰባችሁ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍንና ይሖዋ እንዲከበር የበኩልሽን አስተዋጽኦ ታበረክቻለሽ፤ አልፎ ተርፎም ባለቤትሽ በአንቺ ምግባር ተማርኮ እውነተኛውን አምልኮ ሊቀበልና ሽልማቱን አብራችሁ ልታገኙ ትችላላችሁ። (1 ጴጥ. 3:1, 2) ባለቤትህ የማታምን ብትሆንና እንደማታከብርህ ቢሰማህ ምን ማድረግ ትችላለህ? በእሷ ላይ በመጮኽ የቤቱ አዛዥ ማን እንደሆነ ለማሳየት ብትሞክር አንተን ለማክበር የምትነሳሳ ይመስልሃል? በጭራሽ! አምላክ የራስነት ሥልጣንህን ልክ እንደ ኢየሱስ ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ እንድትጠቀምበት ይጠብቅብሃል። የጉባኤው ራስ የሆነው ኢየሱስ የራስነት ሥልጣኑን የተጠቀመበት በፍቅርና በትዕግሥት ነው። (ሉቃስ 9:46-48) አንድ ባል የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተል ከሆነ ሚስቱ በእሱ ምግባር ተማርካ እውነተኛውን አምልኮ እንድትቀበል ሊረዳት ይችላል። w17.11 28-29 አን. 13-14

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 11

ሁሉን ነገር የሠራው . . . አምላክ ነው።—ዕብ. 3:4

ዓለማዊ አስተሳሰብ፣ ሰዎች የይሖዋን መመሪያዎች ችላ እንዲሉ ወይም አቅልለው እንዲመለከቱ የሚያደርግ ሲሆን ይህ አስተሳሰብ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ደግሞ ቀስ በቀስ እምነታችንን ሊያዳክመው ይችላል። ሁላችንም በቴሌቪዥንና በኢንተርኔት አማካኝነት አሊያም በሥራ ቦታችን ወይም በትምህርት ቤት እንዲህ ላለው አስተሳሰብ እንጋለጣለን። በብዙ አገሮች ውስጥ ሰዎች በአምላክ እንደማያምኑ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፤ እነዚህ ሰዎች ሃይማኖታዊ ዝንባሌ እንደሌላቸው ይገልጻሉ። እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት ‘አምላክ አለ?’ የሚለውን ጉዳይ በቁም ነገር አስበውበት ላይሆን ይችላል፤ ከዚህ ይልቅ ተጠያቂነት ሳይኖርባቸው ያሻቸውን ነገር ማድረግ ስለሚፈልጉ ሊሆን ይችላል። (መዝ. 10:4) ሌሎች ደግሞ “በአምላክ ማመን ሳያስፈልገኝ ላቅ ባሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መመራት እችላለሁ” ብለው ሲናገሩ አዋቂ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። በአምላክ የማያምኑ ሰዎች፣ ፈጣሪ እንደሌለ የሚናገሩት በማስረጃ ላይ ተመሥርተው ነው? አንድ ሰው “ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ሳይንሳዊ ማስረጃዎችን ቢመረምር የሚያገኘው ግራ የሚያጋቡ መረጃዎችን ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን መልሱ ቀላል ነው። አንድ ቤት፣ የሚሠራው ሳይኖር በራሱ ሊገኝ እንደማይችል የታወቀ ነው፤ ታዲያ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ያለ ሠሪ እንዴት በራሳቸው ሊገኙ ይችላሉ? w17.11 20-21 አን. 2-4

ዓርብ፣ ሚያዝያ 12

ይሖዋንም ለሚፈሩና በስሙ ላይ ለሚያሰላስሉ በፊቱ የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ።—ሚል. 3:16

በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት፣ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ክፍል ስለሆነ ነው። ይሖዋ እና ኢየሱስ በዓመት ውስጥ ካሉን ስብሰባዎች ሁሉ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው በዚህ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እያንዳንዳችን የምናደርገውን ጥረት እንደሚመለከቱ ጥርጥር የለውም። አቅማችንና ያለንበት ሁኔታ ካላገደን በቀር በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘታችን እንደሚያስደስታቸው የታወቀ ነው። ለስብሰባዎቻችን ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ በተግባር ማሳየታችን፣ ስማችን ይሖዋ ካዘጋጀው “የመታሰቢያ መጽሐፍ” ይኸውም ‘ከሕይወት መጽሐፍ’ ላይ እንዳይፋቅ ከሚያደርጉት በርካታ ምክንያቶች አንዱ ነው፤ ይህ መጽሐፍ ይሖዋ የዘላለም ሕይወት ሊሰጣቸው ያሰባቸውን ሰዎች ስም የያዘ ነው። (ራእይ 20:15) ከመታሰቢያው በዓል በፊት ባሉት ሳምንታት፣ ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ በቁም ነገር ማሰባችንና ስለ ጉዳዩ መጸለያችን ጠቃሚ ነው።—2 ቆሮ. 13:5፤ w18.01 13 አን. 4-5

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 13

ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ [ይሽሽ]።—ኢያሱ 20:4

ወደ መማጸኛ ከተማ ሸሽቶ የሄደው ግለሰብ እዚያ ከደረሰ በኋላ ያለስጋት መኖር ይችላል። ይሖዋ ስለ እነዚያ ከተሞች ሲናገር “መሸሸጊያ ሆነው ያገለግሏችኋል” ብሏል። (ኢያሱ 20:2, 3) ይሖዋ፣ ነፍስ ያጠፋው ግለሰብ በዚያ ጉዳይ እንደገና ለፍርድ ሊቀርብ እንደሚችል የሚጠቁም ነገር አልተናገረም፤ ደም ተበቃዩም ቢሆን ወደ መማጸኛው ከተማ ገብቶ፣ ሳያውቅ ነፍስ ያጠፋውን ግለሰብ እንዲገድለው አይፈቀድለትም። በመሆኑም ሸሽቶ የሄደው ሰው፣ የበቀል እርምጃ ይወሰድብኛል ብሎ አይፈራም። በዚያ ከተማ ውስጥ እስካለ ድረስ ይሖዋ ጥበቃ ስለሚያደርግለት ያለስጋት መኖር ይችላል። የመማጸኛ ከተማ እስር ቤት አይደለም። በከተማዋ ውስጥ ሆኖ መሥራት፣ ሌሎችን መርዳት እንዲሁም ይሖዋን በሰላም ማገልገል ይችላል። በእርግጥም አስደሳችና የሚያረካ ሕይወት መምራት ይችላል! ከባድ ኃጢአት ከፈጸሙ በኋላ ንስሐ የገቡ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች፣ በደላቸው “ተብትቦ እንደያዛቸው” ይባስ ብሎም ይሖዋ ምንጊዜም በኃጢአት እንደቆሸሹ አድርጎ እንደሚመለከታቸው ይሰማቸዋል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ይሖዋ ይቅር ሲል፣ ሙሉ በሙሉ ምሕረት እንደሚያደርግ መተማመን ትችላለህ! w17.11 9 አን. 6፤ 11 አን. 13-14

እሁድ፣ ሚያዝያ 14

በአንድነት [አብሮ መኖር] ምንኛ መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!—መዝ. 133:1

አንድነታችንን ለማጠናከር አስተዋጽኦ እንድናደርግ የሚያግዘን አንዱ ነገር፣ በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚቀርቡት ቂጣና የወይን ጠጅ ባላቸው ትርጉም ላይ ማሰላሰላችን ነው። ያልቦካው ቂጣና ቀዩ ወይን ስላላቸው ትርጉም ከመታሰቢያው በዓል በፊት ባሉት ጊዜያት በተለይም በዚያ ልዩ ምሽት ላይ በቁም ነገር ልናስብ ይገባል። (1 ቆሮ. 11:23-25) ቂጣው፣ ኢየሱስ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበውን ኃጢአት የሌለበትን ሥጋውን፣ ወይኑ ደግሞ የፈሰሰውን ደሙን ያመለክታል። የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት፣ ይሖዋና ኢየሱስ ታላቅ ፍቅር ያሳዩበት ዝግጅት እንደሆነ እናስታውስ፤ ይሖዋ ለእኛ ሲል ልጁን በመስጠት፣ ኢየሱስ ደግሞ እኛን ለማዳን ሕይወቱን በፈቃደኝነት መሥዋዕት በማድረግ ፍቅራቸውን አሳይተውናል። ይሖዋና ኢየሱስ ባሳዩን ፍቅር ላይ ማሰላሰላችን እኛም በምላሹ እንድንወዳቸው ያነሳሳናል። እኛም ሆንን የእምነት ባልንጀሮቻችን ለይሖዋ ያለን ፍቅር ደግሞ እርስ በርስ የሚያስተሳስረን ከመሆኑም ሌላ አንድነታችንን ያጠናክረዋል። w18.01 15 አን. 11

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 9፦ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 26:6-13

ሰኞ፣ ሚያዝያ 15

የአምላክ ፍቅር ከእኛ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በዚህ መንገድ ተገልጧል፤ እኛ በእሱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል።—1 ዮሐ. 4:9

ይሖዋ የሰው ልጆችን ከልቡ ይወዳል። እንዲያውም በእሱ ፊት በጣም ውድ ስለሆንን ዘላለማዊ መዳን እንድናገኝ ለማድረግ ሲል ልጁን ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። (ዮሐ. 3:16) ይሖዋ ለሰው ልጆች የገባውን ቃል ሳይፈጽም ቢቀር ዲያብሎስ ‘አምላክ ውሸታምና ተገዢዎቹን ጥሩ ነገር የሚነፍግ ኢፍትሐዊ ገዢ ነው’ በማለት የሰነዘረው ክስ እውነት ይሆን ነበር። እንዲሁም “‘እገኛለሁ’ ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች በሞት ካንቀላፉበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉም ነገር ከፍጥረት መጀመሪያ አንስቶ እንዳለ ይቀጥላል” ብለው የሚያፌዙ ሰዎች ትክክል ይሆኑ ነበር። (2 ጴጥ. 3:3, 4) በመሆኑም ይሖዋ፣ የሉዓላዊነቱ ትክክለኛነት መረጋገጥ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆችም መዳን እንዲያስገኝ ያደርጋል። (ኢሳ. 55:10, 11) ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ ሉዓላዊነት በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው። ስለሆነም ምንጊዜም ቢሆን ታማኝ አገልጋዮቹን እንደሚወዳቸው፣ እንደሚያደንቃቸውና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዘፀ. 34:6፤ w17.06 23 አን. 7

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 9፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 21:1-11, 14-17

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 16

[አምላክ] ስለወደደንና ለኃጢአታችን የማስተሰረያ መሥዋዕት እንዲሆን ልጁን ስለላከ ነው።—1 ዮሐ. 4:10

ይሖዋ ቤዛውን እንደሚያዘጋጅ በዘፍጥረት 3:15 ላይ ቃል ከገባበት ጊዜ አንስቶ የቤዛው መሥዋዕት እንደተከፈለ አድርጎ ቆጥሮታል። ከዚያም ከ4,000 ዓመታት ገደማ በኋላ ይሖዋ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍለው ቢሆንም አንድያ ልጁን ለሰው ልጆች መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል። (ዮሐ. 3:16) ይሖዋ ላሳየን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ምንኛ አመስጋኞች ነን! አምላክ የፈጠረን በራሱ አምሳል ስለሆነ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር የማሳየት ችሎታ አለን። አቤል፣ ካለው ነገር ምርጡን ለአምላክ በመስጠት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። (ዘፍ. 4:3, 4) ኖኅ የአምላክን መልእክት የሚሰብክላቸው ሰዎች ምንም ምላሽ ባይሰጡም ለአሥርተ ዓመታት በጽናት በመስበክ ለሰዎች ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። (2 ጴጥ. 2:5) አብርሃም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት እንዲያደርግ በተጠየቀ ጊዜ አምላክን ከምንም ነገር በላይ አስበልጦ እንደሚወድ አሳይቷል። (ያዕ. 2:21) እኛም ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም ልክ እንደ እነዚህ ታማኝ ሰዎች ፍቅር ማሳየት እንፈልጋለን። w17.10 7-8 አን. 3-4

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 10፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 21:18, 19፤ 21:12, 13፤ ዮሐንስ 12:20-50

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 17

ያለን ሊቀ ካህናት በድካማችን ሊራራልን የማይችል አይደለምና፤ ከዚህ ይልቅ እንደ እኛው በሁሉም ረገድ የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁንና እሱ ኃጢአት የለበትም።—ዕብ. 4:15

ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ የሚያቀርበው አገልግሎት “እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ምሕረትና ጸጋ እናገኝ ዘንድ ያለምንም ፍርሃት ወደ ጸጋው ዙፋን [ለመቅረብ]” ይበልጥ እንደሚረዳንና ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንደሚልልን መተማመን እንችላለን። (ዕብ. 4:16) እንግዲያው በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ እምነት ይኑርህ። ቤዛው በግለሰብ ደረጃ አንተን እንደሚጠቅምህ እምነት ይኑርህ። (ገላ. 2:20, 21) አንተም የኃጢአት ይቅርታ እንድታገኝ መሠረት የሚሆነው ቤዛው እንደሆነ እምነት ይኑርህ። ቤዛው አንተም የዘላለም ሕይወት እንድታገኝ መንገድ እንደከፈተልህ እምነት ይኑርህ። የኢየሱስ መሥዋዕት ይሖዋ ለአንተ የሰጠህ ስጦታ ነው። ይሖዋ አንድ ጊዜ ይቅር ካለን በኋላ፣ ያንን ኃጢአት እንደ አዲስ አንስቶ በእኛ ላይ ለመፍረድ ምክንያት እንደሚፈልግ በማሰብ ልንሰጋ አይገባም። (መዝ. 103:8-12) አዎ፣ ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ይቅር እንደሚለን መተማመን እንችላለን። w17.11 11-12 አን. 14-17

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 11፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 21:33-41፤ 22:15-22፤ 23:1-12፤ 24:1-3

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 18

የምለምንህ . . . በእነሱ ቃል አማካኝነት በእኔ ለሚያምኑ ጭምር ነው፤ ይህን ልመና የማቀርበውም . . . አንተ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለህ . . . ሁሉ እነሱም . . . አንድነት እንዲኖራቸው ነው።—ዮሐ. 17:20, 21

የመጀመሪያው የጌታ ራት በተከበረበት ምሽት ላይ ኢየሱስ ለየት ያለ ጸሎት አቅርቦ ነበር፤ እሱና አባቱ ያላቸው ዓይነት አንድነት በተከታዮቹም መካከል እንዲኖር አባቱን ለምኗል። ይሖዋም ውድ ልጁ ላቀረበው ለዚህ ልመና መልስ ሰጥቷል። የአምላክ ሕዝቦች የሚያደርጓቸው በርካታ ስብሰባዎች ቢኖሩም በመካከላቸው ያለው አንድነት ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው በመታሰቢያው በዓል ላይ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች ለአምልኮ አንድ ላይ መሰብሰባቸው ያልተለመደ ነው፤ እንዲያውም አንዳንዶች ይህ ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ይሖዋና ኢየሱስ ግን እንዲህ ያለውን አንድነት ሲያዩ በጣም ይደሰታሉ! የይሖዋ ሕዝቦች በመካከላቸው እንዲህ ዓይነት አንድነት መኖሩ ያን ያህል አያስገርማቸውም። ይሖዋ ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ ትንቢት አስነግሯል።—ሕዝ. 37:15-17፤ ዘካ. 8:23፤ w18.01 14 አን. 7-9

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 12፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 26:1-5, 14-16፤ ሉቃስ 22:1-6

የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ዕለት
ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ
ዓርብ፣ ሚያዝያ 19

ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የማዕዘን ራስ ድንጋይ ሆነ።—መዝ. 118:22

“ግንበኞች” የተባሉት የአይሁድ መሪዎች መሲሑን እንደናቁት አሳይተዋል። ይህን ያደረጉት፣ ኢየሱስን ለመስማት ወይም ደግሞ ክርስቶስ መሆኑን ለመቀበል አሻፈረን በማለታቸው ብቻ አይደለም። በርካታ አይሁዳውያን ኢየሱስ እንዲገደል ከፍተኛ ግፊት በማድረግ ንቀታቸውን ገልጸዋል። (ሉቃስ 23:18-23) በእርግጥም እነዚህ አይሁዳውያን በኢየሱስ ሞት እጃቸው አለበት። ይሁንና ኢየሱስ ከተናቀና ከተገደለ “የማዕዘን ራስ ድንጋይ” እንደሚሆን የተነገረው ትንቢት የሚፈጸመው እንዴት ነው? ትንቢቱ ሊፈጸም የሚችለው ኢየሱስ ከሞት የሚነሳ ከሆነ ብቻ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ እነዚህ ሰዎች ‘በእንጨት ላይ ስለሰቀሉት ሆኖም አምላክ ከሞት ስላስነሳው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ’ ተናግሯል። (ሥራ 3:15፤ 4:5-11፤ 1 ጴጥ. 2:5-7) ከሞት የተነሳው ኢየሱስ፣ የሰው ልጆች መዳን የሚያገኙበት ብቸኛው መንገድ ሆኗል፤ መጽሐፍ ቅዱስ “ልንድንበት የምንችል ከሰማይ በታች ለሰዎች የተሰጠ ሌላ ስም የለም” የሚለው ለዚህ ነው።—ሥራ 4:12፤ ኤፌ. 1:20፤ w17.12 9-10 አን. 6-9

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 13፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 26:17-19፤ ሉቃስ 22:7-13 (ኒሳን 14፦ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 26:20-56

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 20

ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን ታውጃላችሁ።—1 ቆሮ. 11:26

ኢየሱስ በቅርቡ የሚመጣውን ታላቅ መከራ በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “የሰው ልጅም በኃይልና በታላቅ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል። [ኢየሱስም] መላእክቱን በታላቅ የመለከት ድምፅ ይልካል፤ እነሱም . . . ለእሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።” (ማቴ. 24:29-31) ኢየሱስ “ለእሱ የተመረጡትን” የሚሰበስበው በምድር ላይ የቀሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን በሙሉ ወደ ሰማይ ሲወስዳቸው ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ የታላቁ መከራ የመጀመሪያ ምዕራፍ ካለፈ በኋላ ሆኖም የአርማጌዶን ጦርነት ከመፈንዳቱ በፊት ነው። ከዚያም 144,000ዎቹ በሙሉ ከኢየሱስ ጋር ሆነው የምድርን ነገሥታት ድል ያደርጋሉ። (ራእይ 17:12-14) ኢየሱስ ምድር ላይ የቀሩትን ቅቡዓን ለመሰብሰብ ‘ከመምጣቱ’ በፊት የሚከበረው የመታሰቢያ በዓል የመጨረሻው ይሆናል። w18.01 16 አን. 15

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 14፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 27:1, 2, 27-37

እሁድ፣ ሚያዝያ 21

ይህን ኢየሱስን አምላክ ከሞት አስነሳው።—ሥራ 2:32

ኢየሱስ በሰማይ “ለዘላለም” የሚኖር ሲሆን መበስበስን ጨርሶ አያይም። (ራእይ 1:5, 18፤ ሮም 6:9፤ ቆላ. 1:18፤ 1 ጴጥ. 3:18) ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱም በሰማይ ከእሱ ጋር እንደሚገዙ ቃል ገብቶላቸዋል። (ሉቃስ 22:28-30) ጳውሎስ “ክርስቶስ በሞት ካንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሞት ተነስቷል” ሲል ጽፏል። በተጨማሪም ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሌሎችም እንዳሉ ሲጠቁም እንዲህ ብሏል፦ “እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፦ ክርስቶስ በኩራት ነው፤ በመቀጠል ደግሞ ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ የእሱ የሆኑት ሕያዋን ይሆናሉ።” (1 ቆሮ. 15:20, 23) ኢየሱስ ‘የሚገኝበት ጊዜ’ የጀመረው በ1914 ነው። አሁንም የምንኖረው በዚህ ጊዜ ውስጥ ሲሆን የዚህ ክፉ ሥርዓት ማብቂያ ደግሞ በጣም ተቃርቧል። w17.12 10 አን. 11፤ 11 አን. 14-16

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 15፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 27:62-66 (ኒሳን 16፦ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 28:2-4

ሰኞ፣ ሚያዝያ 22

የማጽናናችሁ እኔ ራሴ ነኝ።—ኢሳ. 51:12

የምሕረት አባት የሆነው ይሖዋ እንደ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ፣ ሙሴና ንጉሥ ዳዊት ያሉ ወዳጆቹ በሞቱበት ወቅት፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ምን ያህል ከባድ ሐዘን እንደሚያስከትል ተመልክቷል። (ዘኁ. 12:6-8፤ ማቴ. 22:31, 32፤ ሥራ 13:22) ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ከሞት የሚያስነሳበትን ጊዜ እንደሚናፍቅና በጉጉት እንደሚጠብቅ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢዮብ 14:14, 15) በዚያ ወቅት እነዚህ ሰዎች ደስተኞችና ፍጹም ጤናማ ይሆናሉ። አምላክ፣ ልጁን በጣም የሚወደው ከመሆኑም ሌላ “በየዕለቱ [በእሱ] የተነሳ ልዩ ደስታ ይሰማው” እንደነበር የአምላክ ቃል ይናገራል፤ በመሆኑም ይህ ልጁ ተሠቃይቶ ሲሞት ይሖዋ ምን ተሰምቶት እንደሚሆን ማሰብ እንችላለን። (ምሳሌ 8:22, 30) በዚያ ወቅት ይሖዋ የተሰማውን ሐዘን በቃላት መግለጽ ያዳግታል። (ዮሐ. 5:20፤ 10:17) ሐዘን ሲደርስብን ይሖዋ እንደሚያጽናናን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በመሆኑም ከደረሰብን ሐዘን ጋር በተያያዘ የልባችንን አውጥተን ለእሱ ከመናገር ወደኋላ ልንል አይገባም። ይሖዋ ሥቃያችንን እንደሚረዳልንና በጣም የሚያስፈልገንን መጽናኛ እንደሚሰጠን ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው!—2 ቆሮ. 1:3, 4፤ w17.07 13 አን. 3-5

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 16፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 28:1, 5-15

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 23

አምላክ . . . የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።—ዕብ. 6:10

በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያሏቸውን “ውድ ነገሮች” ማለትም ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጥሪታቸውን በፈቃደኝነት በመስጠት ለታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ድጋፍ እያደረጉ ነው። (ምሳሌ 3:9) ይሖዋ እኛ የምናከናውነውን ሥራ እንዲሁም ለእሱ የምናሳየውን ፍቅር ፈጽሞ አይረሳም። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዘ እየተከናወኑ ያሉት ነገሮች የይሖዋ በረከት እንዳልተለየንና በክርስቶስ አመራር ሥር እንደሆንን የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው። የታቀፍነው አስተማማኝ፣ የይሖዋ ጥበቃ ባለውና ዘላለማዊ በሆነ ድርጅት ውስጥ ነው። በመሆኑም በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለንን ቦታ በአድናቆት እንመልከት፤ እንዲሁም ‘የአምላካችንን የይሖዋን ቃል እንስማ።’ (ዘካ. 6:15) ይህም የንጉሣችንንና የሊቀ ካህናታችንን ጥበቃ ያስገኝልናል። እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናድርግ። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይህ ሥርዓት ሊደመደም በቀሩት ጥቂት ቀናት ውስጥም ሆነ ለዘላለም፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ጥበቃ እንደሚያደርግልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን! w17.10 30 አን. 18-19

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 24

በዓመፅ ሀብት ለራሳችሁ ወዳጆች አፍሩ፤ እነሱም የዓመፅ ሀብት ሲያልቅ በዘላለማዊ መኖሪያ ይቀበሏችኋል።—ሉቃስ 16:9

በቅርቡ ፖለቲካን፣ ሃይማኖትንና የንግዱን ዓለም ያቀፈው መላው የሰይጣን ሥርዓት ድምጥማጡ ይጠፋል። ነቢዩ ሕዝቅኤል እና ነቢዩ ሶፎንያስ፣ በንግዱ ዓለም ውስጥ ለዘመናት ትልቅ ቦታ ሲሰጣቸው የኖሩት ወርቅና ብር በዚያን ጊዜ ዋጋ ቢስ እንደሚሆኑ ተንብየዋል። (ሕዝ. 7:19፤ ሶፎ. 1:18) በሕይወታችን ማብቂያ ላይ ስንደርስ፣ የዚህን ዓለም “የዓመፅ ሀብት” በብዛት ለማካበት ስንል እውነተኛ የሆነውን ሀብት መሥዋዕት እንዳደረግን ብንገነዘብ ምን ይሰማናል? ሁኔታው፣ ብዛት ያለው ገንዘብ ለማከማቸት ሕይወቱን ሙሉ ሲለፋ ቆይቶ፣ ያከማቸው ነገር የሐሰት ገንዘብ እንደሆነ ከተገነዘበ ሰው ጋር ይመሳሰላል። (ምሳሌ 18:11) በእርግጥም የዓመፅ ሀብት ውሎ አድሮ ማለቁ አይቀርም፤ ስለዚህ በዚህ ሀብት ተጠቅመን በሰማይ ‘ወዳጆች የማፍራት’ አጋጣሚ አያምልጠን። የይሖዋን መንግሥት ለመደገፍ የምናደርገው ማንኛውም ነገር መንፈሳዊ ሀብት ያስገኝልናል። w17.07 11 አን. 16

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 25

የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ፤ ክርስቶስ እንደወደደንና . . . ራሱን ስለ እኛ . . . እንደሰጠ ሁሉ እናንተም በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ።—ኤፌ. 5:1, 2

ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከኀፍረት ለመሸሽ አሊያም ሌሎችን ላለማሳዘን ሲሉ የፈጸሙትን ኃጢአት ለመደበቅ ይሞክራሉ። (ምሳሌ 28:13) ሆኖም እንዲህ ያለው አካሄድ ፍቅር የጎደለው ነው፤ ምክንያቱም ይህ ድርጊት ኃጢአት የፈጸመውን ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ይጎዳል። የአምላክ መንፈስ በነፃነት እንዳይሠራ የሚያግድ ከመሆኑም ሌላ የመላውን ጉባኤ ሰላም አደጋ ላይ ይጥላል። (ኤፌ. 4:30) ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ክርስቲያኖች እውነተኛ ፍቅር ካላቸው ሽማግሌዎችን በማነጋገር አስፈላጊውን እርዳታ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። (ያዕ. 5:14, 15) ፍቅር ከሁሉ የላቀ ባሕርይ ነው። (1 ቆሮ. 13:13) የኢየሱስ ተከታዮች መሆናችን የሚታወቀውና የፍቅር ምንጭ የሆነውን ይሖዋን እንደምንመስል የሚታየው ፍቅር ካለን ነው። ጳውሎስ “ፍቅር . . . ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 13:2) እንግዲያው ፍቅራችንን “በቃል” ብቻ ሳይሆን “በተግባርና በእውነት” ጭምር ለመግለጽ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—1 ዮሐ. 3:18፤ w17.10 11 አን. 17-18

ዓርብ፣ ሚያዝያ 26

ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል።—ሥራ 5:29

ዮሴፍ፣ የጶጢፋር ሚስት የፆታ ብልግና እንዲፈጽም በወተወተችው ጊዜ ያሳየውን ድፍረት እንደ ምሳሌ እንመልከት። የእሷን ጥያቄ አለመቀበሉ ከባድ መዘዝ እንደሚያስከትልበት ተገንዝቦ መሆን አለበት። ያም ቢሆን ለእሷ ውትወታ እጅ ከመስጠት ይልቅ ደፋር በመሆን ቆራጥ እርምጃ ወስዷል። (ዘፍ. 39:10, 12) ረዓብም ድፍረት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትሆነናለች። እስራኤላውያን ሰላዮች በኢያሪኮ ወዳለው ቤቷ በመጡ ጊዜ በይሖዋ በመታመን ሁለቱን ሰዎች ቤቷ የደበቀቻቸው ከመሆኑም ሌላ በሰላም ከከተማው እንዲወጡ ረድታቸዋለች፤ በዚህ መንገድ ደፋር መሆኗን አሳይታለች። (ኢያሱ 2:4, 5, 9, 12-16) ኢየሱስ ያሳየውን ድፍረት በገዛ ዓይናቸው የመመልከት አጋጣሚ ያገኙት ታማኝ የሆኑት ሐዋርያትም ሰዱቃውያን ከፍተኛ ተቃውሞ ቢያደርሱባቸውም በኢየሱስ ስም ከማስተማር ወደኋላ አላሉም። (ሥራ 5:17, 18, 27-29) ዮሴፍ፣ ረዓብ፣ ኢየሱስና ሐዋርያቱ መልካም ሥራ ለመሥራት የሚያነሳሳ ውስጣዊ ጥንካሬ እንዳላቸው አሳይተዋል። ደፋሮች የሆኑት ከልክ በላይ በራሳቸው ስለተማመኑ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ስለታመኑ ነው። እኛም ደፋር መሆንን የሚጠይቁ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። በእነዚህ ጊዜያት በራሳችን ከመተማመን ይልቅ በይሖዋ ልንታመን ይገባል።—2 ጢሞ. 1:7፤ w17.09 29 አን. 6-9

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 27

አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፋችሁ ጣሉ።—ቆላ. 3:9

አንድ ሰው በራሱ ጥንካሬ አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፎ መጣል አይችልም። መጥፎ ልማዶቻቸውን ያስወገዱ አብዛኞቹ ሰዎች ይህን ለማድረግ ከፍተኛ ትግል ጠይቆባቸዋል። በትግሉ ሊያሸንፉ የቻሉት የአምላክ ቃልና የቅዱስ መንፈሱ ኃይል በሕይወታቸው ውስጥ እንዲሠራ በመፍቀዳቸው ነው። (ሉቃስ 11:13፤ ዕብ. 4:12) ከአምላክ ቃልና ከቅዱስ መንፈሱ ከሚገኘው ኃይል ተጠቃሚ ለመሆን መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ፣ ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለንን ጥበብና ጥንካሬ እንዲሰጠን ወደ ይሖዋ አዘውትረን መጸለይ ይኖርብናል። (ኢያሱ 1:8፤ መዝ. 119:97፤ 1 ተሰ. 5:17) በተጨማሪም ጥሩ ዝግጅት አድርገን በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ከአምላክ ቃልና ከቅዱስ መንፈሱ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። (ዕብ. 10:24, 25) እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች በተለያየ መልኩ ከሚቀርበው መንፈሳዊ ምግብ በሚገባ መጠቀም ይኖርብናል። (ሉቃስ 12:42) ይሁን እንጂ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት አሮጌውን ስብዕና ገፎ መጣል ብቻ በቂ አይደለም። አዲሱን ስብዕና መልበስም ያስፈልጋል።—ቆላ. 3:10፤ w17.08 21 አን. 16-17

እሁድ፣ ሚያዝያ 28

እኔ በበኩሌ በታማኝ ፍቅርህ እታመናለሁ፤ ልቤ በማዳን ሥራህ ሐሴት ያደርጋል።—መዝ. 13:5

ንጉሥ ዳዊት ብዙ ግፍ ተፈጽሞበታል። ይሖዋ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የቀባው ገና በልጅነቱ ቢሆንም በራሱ ነገድ ላይ ንጉሥ ሆኖ መግዛት የጀመረው ከ15 ዓመት ገደማ በኋላ ነው። (2 ሳሙ. 2:3, 4) በእነዚያ ዓመታት ውስጥ፣ ታማኝ ያልነበረው ንጉሥ ሳኦል ሊገድለው ያሳድደው ነበር። በመሆኑም ዳዊት በየአገሩ በመንከራተትና በየዋሻው በመደበቅ በስደት ለመኖር ተገዷል። ሳኦል በውጊያ ከተገደለ በኋላም እንኳ ዳዊት በመላው የእስራኤል ብሔር ላይ ንጉሥ ሆኖ ለመግዛት ተጨማሪ ሰባት ዓመታት ገደማ መጠበቅ አስፈልጎታል። (2 ሳሙ. 5:4, 5) ዳዊት በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ የነበረው ለምንድን ነው? ዳዊት በይሖዋ ታማኝ ፍቅር ታምኗል። ይሖዋ እሱን ለማዳን እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ በደስታ ይጠባበቅ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ እንዴት እንደካሰው ያሰላስል ነበር። (መዝ. 13:6) አዎ፣ ዳዊት በትዕግሥት መጠበቁ ፈጽሞ እንደማያስቆጨው ያውቅ ነበር። w17.08 6-7 አን. 14-15

ሰኞ፣ ሚያዝያ 29

አምላክ [አያዳላም]።—ሥራ 10:34

ቋንቋ በጊዜ ሂደት ይለወጣል። በመሆኑም በአንድ ቋንቋ ውስጥ ያሉ ቃላትና አገላለጾች ቀደም ሲል ከነበራቸው ፈጽሞ የተለየ ትርጉም ሊኖራቸው ይችላል። አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከተጻፈባቸው ከዕብራይስጥና ከግሪክኛ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይነገር የነበረው ዕብራይስጥና ግሪክኛ በዛሬው ጊዜ ከሚነገረው ፈጽሞ የተለየ ነው። ስለዚህ በዛሬው ጊዜ የሚነገረውን ዕብራይስጥና ግሪክኛ የሚያውቁትን ጨምሮ ማንኛውም ሰው የአምላክን ቃል መረዳት ከፈለገ በዘመናዊ ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ሊያነብ ይገባል። አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስን መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ለማንበብ የጥንቱን ዕብራይስጥና ግሪክኛ መማር እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። ሆኖም ይህ የሚያስቡትን ያህል ውጤታማ ላይሆን ይችላል። ደስ የሚለው ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ከ3,200 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ይሖዋ “በምድር ላይ [የሚኖር] ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ” ከቃሉ ተጠቃሚ እንዲሆን ይፈልጋል። (ራእይ 14:6) ይህን ማወቅህ የማያዳላና አፍቃሪ አምላክ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ አያደርግህም? w17.09 19 አን. 4

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 30

አዋቂ ሰው ንግግሩ ቁጥብ ነው፤ ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰውም የተረጋጋ ነው።—ምሳሌ 17:27

ከክርስቲያን ጉባኤ የተወገዱ ዘመዶች ካሉህ ከእነሱ ጋር አላስፈላጊ ቅርርብ ላለመፍጠር ራስህን መግዛት ሊያስፈልግህ ይችላል። እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ሥር ስንሆን፣ ራስን መግዛት የአምላክን ምሳሌ ለመከተልና እሱ የሰጠንን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችለን መገንዘባችን ሊረዳን ይችላል። ከንጉሥ ዳዊት ግሩም ትምህርት እናገኛለን። ዳዊት ኃያል ሰው የነበረ ቢሆንም ሳኦልና ሺምአይ የሚያበሳጭ ነገር ባደረጉበት ጊዜ በቁጣ ተነሳስቶ የኃይል እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቧል። (1 ሳሙ. 26:9-11፤ 2 ሳሙ. 16:5-10) ይህ ሲባል ግን ዳዊት ሁልጊዜ ራሱን የሚቆጣጠር ሰው ነበር ማለት አይደለም፤ ከቤርሳቤህ ጋር የፈጸመው ኃጢአት እንዲሁም ናባል ያደረገውን ሲሰማ የሰጠው ምላሽ ዳዊት ራሱን መቆጣጠር የተሳነው ጊዜ እንደነበር ይጠቁማሉ። (1 ሳሙ. 25:10-13፤ 2 ሳሙ. 11:2-4) ያም ቢሆን ከዳዊት ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። በመጀመሪያ ደረጃ፣ በአምላክ ሕዝቦች መካከል የሚገኙ የበላይ ተመልካቾች ሥልጣናቸውን አላግባብ እንዳይጠቀሙበት ራሳቸውን መግዛታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ማንም ሰው በዚህ ረገድ ችግር ሊያጋጥመኝ አይችልም ብሎ በማሰብ መዘናጋት አይኖርበትም።—1 ቆሮ. 10:12፤ w17.09 5-6 አን. 12-13

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ