የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es19 ገጽ 47-57
  • ግንቦት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ግንቦት
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2019
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 1
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 2
  • ዓርብ፣ ግንቦት 3
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 4
  • እሁድ፣ ግንቦት 5
  • ሰኞ፣ ግንቦት 6
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 7
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 8
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 9
  • ዓርብ፣ ግንቦት 10
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 11
  • እሁድ፣ ግንቦት 12
  • ሰኞ፣ ግንቦት 13
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 14
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 15
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 16
  • ዓርብ፣ ግንቦት 17
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 18
  • እሁድ፣ ግንቦት 19
  • ሰኞ፣ ግንቦት 20
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 21
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 22
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 23
  • ዓርብ፣ ግንቦት 24
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 25
  • እሁድ፣ ግንቦት 26
  • ሰኞ፣ ግንቦት 27
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 28
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 29
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 30
  • ዓርብ፣ ግንቦት 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2019
es19 ገጽ 47-57

ግንቦት

ረቡዕ፣ ግንቦት 1

ተግሣጽን ያዛት፤ አትልቀቃትም። ጠብቃት፤ ሕይወትህ ናትና።—ምሳሌ 4:13

ተግሣጽ ሕመም ሊያስከትል ቢችልም ከዚያ የከፋ ሕመም ሊያስከትልብን የሚችለው ተግሣጹን አለመቀበላችን ነው። (ዕብ. 12:11) የቃየንን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ቃየን አቤልን ወደ መግደል ሊያመራ የሚችል ጥላቻ በውስጡ እያቆጠቆጠ በነበረበት ወቅት አምላክ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቶት ነበር፦ “ለምን ተናደድክ? ለምንስ አዘንክ? መልካም ወደ ማድረግ ብታዘነብል ኖሮ ሞገስ አታገኝም ነበር? መልካም ወደ ማድረግ ካላዘነበልክ ግን ኃጢአት በደጅህ እያደባ ነው፤ ሊቆጣጠርህም ይፈልጋል፤ ታዲያ አንተ ትቆጣጠረው ይሆን?” (ዘፍ. 4:6, 7) ቃየን ግን አልሰማም። በመሆኑም ኃጢአት ተቆጣጠረው። በዚህም የተነሳ ቃየን አላስፈላጊ ሕመምና ሥቃይ በራሱ ላይ አመጣ! (ዘፍ. 4:11, 12) ይሖዋ የሰጠው ተግሣጽ የሚያስከትልበት ሕመም ከዚህ ጋር ሲነጻጸር ምንኛ የተሻለ ነበር! በእርግጥም ይሖዋ እንዲህ ካለው አላስፈላጊ ሥቃይ ሊያድነን ይፈልጋል! (ኢሳ. 48:17, 18) በመሆኑም ‘ተግሣጽን በመስማት ጥበበኞች እንሁን።’—ምሳሌ 8:33፤ w18.03 32 አን. 18-20

ሐሙስ፣ ግንቦት 2

እኔ ዳንኤል [ዓመታቱን] . . . ከመጻሕፍቱ አስተዋልኩ።—ዳን. 9:2

ዳንኤል ይሖዋን ማወቅ የቻለው እንዴት ነው? ዳንኤል ለይሖዋና በጽሑፍ ለሰፈረው የአምላክ ቃል ፍቅር እንዲያዳብር ወላጆቹ ጥሩ ሥልጠና ሰጥተውት እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት እንችላለን። በዚህ መንገድ ያዳበረው ፍቅር እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ አብሮት ዘልቋል። ዕድሜው በጣም በገፋበት ወቅትም እንኳ ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት ያጠና ነበር። ነቢዩ በጸጸት ስሜት ተውጦ ያቀረበው ከልብ የመነጨ ጸሎት በዳንኤል 9:3-19 ላይ ተመዝግቦ የሚገኝ ሲሆን በጸሎቱ ላይ የጠቀሳቸው ነገሮች ስለ አምላክም ሆነ አምላክ ከእስራኤላውያን ጋር ስለነበረው ግንኙነት ጥልቅ እውቀት እንደነበረው ያሳያሉ። ዳንኤል ያቀረበውን ይህን ጸሎት ለማንበብና በዚያ ላይ ለማሰላሰል ለምን ጊዜ አትመድብም? በጣዖት አምልኮ በተሞላችው በባቢሎን መኖር ለአንድ ታማኝ አይሁዳዊ በጣም ተፈታታኝ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ አይሁዳውያኑን “በግዞት ተወስዳችሁ እንድትኖሩባት ላደረግኳት [ከተማ] ሰላምን ፈልጉ” ብሏቸው ነበር። (ኤር. 29:7) በሌላ በኩል ደግሞ እሱን ብቻ እንዲያመልኩት ይጠብቅባቸው ነበር። (ዘፀ. 34:14) ዳንኤል እነዚህን ሁለት ትእዛዛት በመጠበቅ ረገድ ሚዛኑን እንዳይስት የረዳው ምንድን ነው? አምላካዊ ጥበብ፣ ለዓለማዊ ባለሥልጣናት መገዛት ያለበት አንጻራዊ በሆነ መንገድ እንደሆነ እንዲገነዘብ ረድቶታል። ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ይህንኑ መሠረታዊ ሥርዓት አስተምሯል።—ሉቃስ 20:25፤ w18.02 10 አን. 11-12

ዓርብ፣ ግንቦት 3

[በሰዎቹ ግንባር ላይ] ምልክት አድርግ።—ሕዝ. 9:4

እንደ ጤና ማጣት፣ የገንዘብ ችግር ወይም ስደት ካሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር እየታገልክ ነው? በይሖዋ አገልግሎት ደስተኛ ሆኖ መቀጠል ፈታኝ የሚሆንብህ ጊዜ አለ? ከሆነ ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ የተዉት ምሳሌ የብርታት ምንጭ ይሆንሃል። እነዚህ ሰዎች ፍጹማን ያልነበሩ ከመሆናቸውም ሌላ ዛሬ በእኛ ላይ እየደረሱ ያሉትን አብዛኞቹን ፈተናዎች ተጋፍጠዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ፈተናዎች ለሕይወታቸው አስጊ ነበሩ። ያም ሆኖ እስከ መጨረሻው ንጹሕ አቋማቸውን በመጠበቅ በአምላክ ዘንድ የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ ሆነው ለመቆጠር በቅተዋል። (ሕዝ. 14:12-14) ሕዝቅኤል በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የጻፈው በ612 ዓ.ዓ. በባቢሎን ሆኖ ነበር። (ሕዝ. 1:1፤ 8:1) አስቀድሞ በተነገረው መሠረት ከሃዲዋ ኢየሩሳሌም የምትጠፋበት ወቅት ማለትም 607 ዓ.ዓ. በጣም ተቃርቦ ነበር። በዚያን ወቅት እንደ ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ ያለ እምነትና ታዛዥነት የነበራቸው እንዲሁም ከጥፋቱ እንዲተርፉ ምልክት የተደረገባቸው ሰዎች ጥቂት ነበሩ። (ሕዝ. 9:1-5) ዛሬም ቢሆን ይህ ሥርዓት በሚጠፋበት ጊዜ ከጥፋቱ እንዲተርፉ ምልክት የሚደረግባቸው ይሖዋ ከነቀፋ ነፃ እንደሆኑ የሚቆጥራቸው እንደ ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ ያሉ ሰዎች ብቻ ናቸው።—ራእይ 7:9, 14፤ w18.02 3-4 አን. 1-3

ቅዳሜ፣ ግንቦት 4

በወጣትነትህ ጊዜ ታላቁን ፈጣሪህን አስብ።—መክ. 12:1

ወጣት ከሆንክ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምካፈለው ወላጆቼ እንዲህ እንዳደርግ ስለሚጠብቁብኝ ብቻ ነው? ከአምላክ ጋር በግለሰብ ደረጃ ወዳጅነት ለመመሥረትና ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ ጥረት እያደረግኩ ነው?’ እርግጥ ነው፣ መንፈሳዊ ግብ ማውጣት የሚያስፈልጋቸው ወጣቶች ብቻ አይደሉም። የይሖዋ አገልጋዮች የሆንን ሁሉ መንፈሳዊ ግብ ማውጣታችን መንፈሳዊነታችንን ለማጠናከር ይረዳናል። (መክ. 12:13) ማሻሻያ ማድረግ የሚያስፈልገን በየትኞቹ አቅጣጫዎች እንደሆነ ካስተዋልን በኋላ፣ ዛሬ ነገ ሳንል ለውጥ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። መንፈሳዊ ሰው መሆን ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው። እንዲያውም የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው። (ሮም 8:6-8) በመንፈሳዊ መጎልመስ አለብን ሲባል ግን ፍጹም መሆን አለብን ማለት አይደለም። የይሖዋ መንፈስ አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግ እንድንችል ይረዳናል። ያም ቢሆን እኛም የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አስደሳች ሊሆን ቢችልም ልክ እንደ ልብ ወለድ መጻሕፍት አዝናኝ እንዲሆንልን መጠበቅ የለብንም። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ፣ በውስጡ ያሉትን ጠቃሚ መንፈሳዊ ዕንቁዎች ለማግኘት ብርቱ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። w18.02 25 አን. 10-11

እሁድ፣ ግንቦት 5

ታዲያ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነስና ተጠመቅ።—ሥራ 22:16

አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ ወስኖ ከመጠመቁ በፊት ሁሉንም ነገር ማወቅ አለበት ማለት አይደለም። ሁሉም ደቀ መዛሙርት፣ ከተጠመቁ በኋላም ቢሆን ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እያደጉ መሄድ ይኖርባቸዋል። (ቆላ. 1:9, 10) ታዲያ አንድ ሰው ከመጠመቁ በፊት ምን ያህል እውቀት ሊኖረው ይገባል? በመጀመሪያው መቶ ዘመን የሚኖር አንድ ቤተሰብ የወሰደው እርምጃ ለሁላችንም ጥሩ ትምህርት ይዟል። (ሥራ 16:25-33) ጳውሎስ በ50 ዓ.ም. ገደማ በሁለተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ላይ ፊልጵስዩስን ጎብኝቶ ነበር። በዚያ ሳለም እሱና ጓደኛው ሲላስ በሐሰት ተከስሰው ወደ ወህኒ ተጣሉ። ሌሊት ላይ ከባድ የምድር ነውጥ በመከሰቱ የእስር ቤቱ መሠረት ተናጋ፤ በተጨማሪም በሮቹ በሙሉ ተከፈቱ። የእስር ቤቱ ጠባቂ፣ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ለመግደል ሰይፉን መዘዘ፤ በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ድምፁን ከፍ አድርጎ በመጣራት አስቆመው። ከዚያም ጳውሎስና ሲላስ ለጠባቂውና ለቤተሰቡ መሠከሩላቸው። ታዲያ ይህ ቤተሰብ፣ ስለ ኢየሱስ የተማረው እውነት ምን እንዲያደርግ አነሳሳው? ጠባቂውና ቤተሰቡ ወዲያውኑ ተጠመቁ። w18.03 10 አን. 7-8

ሰኞ፣ ግንቦት 6

አምላኩ ይሖዋ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!—መዝ. 144:15

ይሖዋ ደስተኛ አምላክ ነው፤ ሕዝቡም ቢሆን ደስተኛ ነው። ከዚህም ሌላ ራሳቸውን ከሚወዱና ከሌሎች ስለሚያገኙት ነገር ብቻ ከሚያስቡ ሰዎች በተለየ የይሖዋ አገልጋዮች ለሌሎች በመስጠት ደስታ ያገኛሉ። (ሥራ 20:35፤ 2 ጢሞ. 3:2) አምላክን ከራሳችን አስበልጠን እንደምንወደው ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? በፊልጵስዩስ 2:3, 4 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ምክር ልብ እንበል፦ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ እንጂ በጠበኝነት መንፈስ ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ፤ ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።” ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ይህን ምክር በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ አደርጋለሁ? በጉባኤ ውስጥም ሆነ በአገልግሎት ላይ ሌሎችን ለመርዳት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን እፈልጋለሁ?’ እርግጥ ነው፣ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ሌሎችን ለመርዳት ማዋል ሁልጊዜ ቀላል ይሆናል ማለት አይደለም። የራሳችንን ጥቅም መሠዋት ብሎም ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ሊኖርብን ይችላል። ይሁንና የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ገዢ ሞገስ እንዳገኘን ከማወቅ በላይ ምን ሊያስደስተን ይችላል? w18.01 23 አን. 6-7

ማክሰኞ፣ ግንቦት 7

በእምነት ውስጥ መሆናችሁን ለማረጋገጥ ዘወትር ራሳችሁን ፈትሹ።—2 ቆሮ. 13:5

ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም የሚጠቀመው በዚህ ድርጅት ብቻ እንደሆነ ከልቤ አምናለሁ? የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክና ለማስተማር የምችለውን ሁሉ እያደረግኩ ነው? የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንደሆነና የሰይጣን አገዛዝ ፍጻሜው እንደቀረበ በእርግጥ አምናለሁ? አኗኗሬስ ይህን ያሳያል? በይሖዋና በኢየሱስ ላይ ምን ያህል ትምክህት አለኝ? ራሴን በወሰንኩበት ወቅት እንደነበረው ሁሉ አሁንም በእነሱ እተማመናለሁ?’ (ማቴ. 24:14፤ 2 ጢሞ. 3:1፤ ዕብ. 3:14) ለእነዚህ ጥያቄዎች በምንሰጠው መልስ ላይ ማሰላሰላችን፣ ማንነታችንን ለማወቅ ዘወትር ራሳችንን ለመመርመር ያስችለናል። ለመታሰቢያው በዓል መዘጋጀት የምንችልበት አንዱ መንገድ፣ የበዓሉን አስፈላጊነት የሚያጎሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶችን ማንበብና ባነበብነው ላይ ማሰላሰል ነው። (ዮሐ. 3:16፤ 17:3) የዘላለም ሕይወት ማግኘት ከፈለግን ስለ ይሖዋ ‘ማወቃችን’ እንዲሁም በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ‘ማመናችን’ የግድ አስፈላጊ ነው። ወደ ይሖዋና ወደ ኢየሱስ ለመቅረብ የሚረዱ ርዕሶችን መርጠን ማጥናታችን ለመታሰቢያው በዓል ለመዘጋጀት ይረዳናል። w18.01 13 አን. 5-6

ረቡዕ፣ ግንቦት 8

የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም።—ዮሐ. 6:44

አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹን እንዴት እንደረዳቸው የሚገልጹ የሚያበረታቱ ተሞክሮዎችን በመጽሐፍ ቅዱስና በጽሑፎቻችን ላይ አንብበህ እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዳምጠህ ሊሆን ይችላል። ይሁንና በመንፈሳዊ እድገት እያደረግህ ስትሄድ የይሖዋን እጅ በራስህ ሕይወት የተመለከትከው እንዴት እንደሆነ ማስተዋል ያስፈልግሃል። አንተ በግልህ የይሖዋን ጥሩነት ቀምሰህ ያየህባቸው አጋጣሚዎች አሉ? ይሖዋ፣ ሁሉንም ክርስቲያኖች ወደ ራሱና ወደ ልጁ እንዲቀርቡ በመሳብ የእሱን ጥሩነት ልዩ በሆነ መንገድ ቀምሰው እንዲያዩ አድርጓል። ምናልባት አንድ ወጣት ‘ይሖዋ የሳበው ወላጆቼን ነው፤ እኔ እነሱን ተከትዬ ነው የመጣሁት’ ብሎ ያስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ራስህን ለይሖዋ ስትወስንና ስትጠመቅ፣ አንተ ራስህ በግለሰብ ደረጃ ከእሱ ጋር ልዩ ዝምድና እንደመሠረትክ የሚያሳይ እርምጃ ወስደሃል። አሁን በእሱ ዘንድ በሚገባ ታውቀሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ሰው አምላክን የሚወድ ከሆነ በእሱ ዘንድ የታወቀ ነው” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (1 ቆሮ. 8:3) እንግዲያው ይሖዋ በድርጅቱ ውስጥ የሰጠህን ቦታ ምንጊዜም ከፍ አድርገህ ተመልከተው። w17.12 26 አን. 12-13

ሐሙስ፣ ግንቦት 9

ይሖዋ የሚወዳቸውን ይገሥጻል።—ዕብ. 12:6

“ተግሣጽ” የሚለውን ቃል ስትሰማ የምታስበው ስለ ቅጣት ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ተግሣጽ ከዚህ ያለፈ ነገርን ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ አብዛኛውን ጊዜ ተግሣጽን የሚገልጸው አዎንታዊ በሆነ መንገድ ሲሆን ቃሉ ከእውቀት፣ ከጥበብ፣ ከፍቅርና ከሕይወት ጋር ተያይዞ ተጠቅሷል። (ምሳሌ 1:2-7፤ 4:11-13) ደግሞም የአምላክ ተግሣጽ እሱ ለእኛ ያለው ፍቅር መገለጫ ከመሆኑም ሌላ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ያለውን ፍላጎት ያሳያል። (ዕብ. 12:6) አምላክ የሚሰጠን ተግሣጽ ቅጣትን የሚጨምርበት ጊዜ ቢኖርም ቅጣቱ የሚጎዳ ወይም ጭካኔ የተሞላበት አይደለም። እንዲያውም “ተግሣጽ” የሚለው ቃል ዋነኛ ትርጉም ትምህርት ከመስጠት ጋር የተያያዘ ነው፤ ለምሳሌ አንድ ወላጅ ለሚወደው ልጁ የሚሰጠውን ትምህርት ሊያመለክት ይችላል። እኛም የክርስቲያን ጉባኤ አባላት እንደመሆናችን መጠን የአምላክ ቤተሰብ አባላት ነን። (1 ጢሞ. 3:15) በመሆኑም ይሖዋ የምንመራባቸውን መሥፈርቶች የማውጣት እንዲሁም እነዚህን መሥፈርቶች ስንጥስ ፍቅራዊ ተግሣጽ የመስጠት መብት እንዳለው አምነን እንቀበላለን። በተጨማሪም የፈጸምነው የተሳሳተ ድርጊት የሚያስከትልብን መዘዝ በሰማይ ያለውን አባታችንን መስማት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስገነዝበናል፤ ይህም ቢሆን ይሖዋ እኛን የሚገሥጽበት አንዱ መንገድ ነው።—ገላ. 6:7፤ w18.03 23 አን. 1፤ 24 አን. 3

ዓርብ፣ ግንቦት 10

አዋቂ ሰው ንግግሩ ቁጥብ ነው፤ ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰውም የተረጋጋ ነው።—ምሳሌ 17:27

በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ወጣት ከሆንክ ወላጆችህ ስሜትህን እንደማይረዱልህ ወይም በጣም ጥብቅ እንደሆኑብህ ይሰማህ ይሆናል። እንዲያውም በወላጆችህ በጣም ከመበሳጨትህ የተነሳ፣ ይሖዋን ማገልገልህን ብትተው የተሻለ እንደሚሆን ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ በእነሱ ተማርረህ ይሖዋን ማገልገልህን ብታቆም ይዋል ይደር እንጂ፣ ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን ወላጆችህንና የጉባኤህን አባላት ያህል ከልቡ ስለ አንተ የሚያስብ ሰው እንደሌለ መገንዘብህ አይቀርም። እስቲ አስበው፦ ወላጆችህ ምንም ዓይነት እርማት የማይሰጡህ ቢሆን በእርግጥ እንደሚወዱህ ይሰማህ ነበር? (ዕብ. 12:8) ምናልባትም ያስከፋህ ወላጆችህ አንተን የሚገሥጹበት መንገድ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ምክሩ በተሰጠበት መንገድ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ምክንያታቸውን ለማስተዋል ሞክር። ነገሩን በሰከነ መንፈስ ለማሰብና ወላጆችህ ሲገሥጹህ ከመጠን በላይ ላለመበሳጨት ጥረት አድርግ። እርማት ሲሰጥህ ተግሣጹ በተሰጠበት መንገድ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ በተረጋጋ መንፈስ ምክሩን ተቀብለህ በተግባር አውለው፤ ይህም በሳል ሰው ለመሆን ጥረት እንደምታደርግ የሚያሳይ ነው።—ምሳሌ 1:8፤ w17.11 29 አን. 16-17

ቅዳሜ፣ ግንቦት 11

መጀመሪያ ላይ የነበረህን ፍቅር ትተሃል።—ራእይ 2:4

በወጣትነታቸው የተጠመቁ አንዳንዶች ከጊዜ በኋላ፣ ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖር የጥበብ አካሄድ ስለመሆኑ ጥርጣሬ እንዳደረባቸው አስተውላችሁ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም የተወሰኑት እውነትን ትተው ወጥተዋል። በመሆኑም ልጃችሁ በክርስትና ጎዳና ላይ መጓዝ ከጀመረ በኋላ አመለካከቱን እንዳይቀይርና ለእውነት የነበረውን የመጀመሪያ ፍቅር እንዳይተው ስጋት ሊያድርባችሁ ይችላል። ታዲያ እንዲህ ዓይነት ነገር እንዳይከሰት ለመከላከል ብሎም ልጃችሁ “ወደ መዳን ማደግ” እንዲችል ለመርዳት ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? (1 ጴጥ. 2:2) መልሱ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ሐሳብ ላይ ይገኛል፦ “በተማርካቸውና አምነህ በተቀበልካቸው ነገሮች ጸንተህ ኑር፤ ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች እነማን እንዳስተማሩህ ታውቃለህ፤ እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ እንድታገኝ የሚያስችሉህን ቅዱሳን መጻሕፍት [የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት] ከጨቅላነትህ ጀምሮ አውቀሃል።” (2 ጢሞ. 3:14, 15) ጳውሎስ (1) ቅዱሳን መጻሕፍትን ስለማወቅ፣ (2) የተማሩትን ነገር አምኖ ስለመቀበል እንዲሁም (3) በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ ስለማግኘት እንደተናገረ ልብ ማለት ያስፈልጋል። w17.12 18-19 አን. 2-3

እሁድ፣ ግንቦት 12

አገልጋዮቼ ከልባቸው ደስታ የተነሳ እልል ይላሉ፤ እናንተ ግን ከልባችሁ ሐዘን የተነሳ ትጮኻላችሁ።—ኢሳ. 65:14

በርካታ ሃይማኖቶች ስለ ገሃነመ እሳት ስለሚያስተምሩ፣ አባሎቻቸው አሥራት እንዲሰጡ ጫና ስለሚያደርጉ ወይም ፖለቲካ ውስጥ ስለሚገቡ ሰዎች ከአምላክ እንዲርቁ ያደርጋሉ። በመሆኑም ያለሃይማኖት ደስተኛ ሆኖ መኖር እንደሚቻል የሚሰማቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ አያስገርምም! አንድ ሰው የሐሰት ሃይማኖትን ባይከተል ደስተኛ ሊሆን እንደሚችል አይካድም፤ ይሁን እንጂ “ደስተኛው አምላክ” ከተባለው ከይሖዋ ጋር ዝምድና የሌለው ሰው እውነተኛ ደስታ ሊኖረው አይችልም። (1 ጢሞ. 1:11) አምላክ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ሌሎችን የሚጠቅም ነው። አገልጋዮቹም ሌሎችን ለመርዳት ጥረት ስለሚያደርጉ ደስተኞች ናቸው። (ሥራ 20:35) ለምሳሌ ያህል፣ እውነተኛው ሃይማኖት ደስተኛ ቤተሰብ ለመገንባት የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመልከት። እውነተኛው አምልኮ የትዳር ጓደኛሞች እርስ በርስ እንዲከባበሩ፣ የጋብቻ ቃለ መሐላቸውን አክብደው እንዲመለከቱ፣ ከምንዝር እንዲርቁ፣ ልጆቻቸውን ሥርዓታማ አድርገው እንዲያሳድጉ እንዲሁም ለቤተሰባቸው አባላት እውነተኛ ፍቅር እንዲያሳዩ ያበረታታል። በዚህም ምክንያት እውነተኛውን አምልኮ የሚከተሉ ሰዎችን ያቀፉት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጉባኤዎች አንድነት፣ ሰላምና ደስታ የሰፈነባቸው መሆን ችለዋል። w17.11 21 አን. 6-7

ሰኞ፣ ግንቦት 13

እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ!—ሮም 7:24

በርካታ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ይህን ሐሳብ እንደተናገረው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ የተሰማቸው ጊዜ አለ። ሁላችንም ይሖዋን ለማስደሰት ልባዊ ፍላጎት ቢኖረንም ከአዳም በወረስነው ኃጢአት የተነሳ ይሖዋን የሚያሳዝን ድርጊት የምንፈጽምበት ጊዜ ይኖራል፤ በዚህ ወቅት እንደ ጳውሎስ ስሜታችን ሊደቆስ ይችላል። እንዲያውም ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ አምላክ ፈጽሞ ይቅር ሊላቸው እንደማይችል ተሰምቷቸዋል። ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ይሖዋን መጠጊያ ወይም መሸሸጊያ የሚያደርጉ ሰዎች በጥፋተኝነት ስሜት ከመጠን በላይ ሊደቆሱ እንደማይገባ ይናገራሉ። (መዝ. 34:22) ጳውሎስ ይሖዋን ሙሉ በሙሉ መታዘዝ አለመቻሉ የፈጠረበትን ስሜት ከገለጸ በኋላ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚታደገኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን!” ብሏል። (ሮም 7:25) ጳውሎስ፣ ከኃጢአት ምኞቶችና ቀደም ሲል የፈጸመው በደል ከሚያሳድርበት ስሜት ጋር ይታገል ነበር፤ ሆኖም ለፈጸመው ኃጢአት ንስሐ ስለገባ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይሖዋ ይቅር እንዳለው ሙሉ እምነት ነበረው። ኢየሱስ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ስለሰጠን ንጹሕ ሕሊና እንዲሁም ውስጣዊ ሰላም እንድናገኝ ይረዳናል። (ዕብ. 9:13, 14) በተጨማሪም ሊቀ ካህናችን ነው፤ በመሆኑም ለእኛ “ለመማለድ ሁልጊዜ ሕያው ሆኖ ስለሚኖር በእሱ አማካኝነት ወደ አምላክ የሚቀርቡትን ፈጽሞ [ሊያድን] ይችላል።”—ዕብ. 7:24, 25፤ w17.11 8 አን. 1-2፤ 12 አን. 15

ማክሰኞ፣ ግንቦት 14

ለአምላካችሁ ለይሖዋ ተሳሉ፤ ስእለታችሁንም ፈጽሙ።—መዝ. 76:11

ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን እንደምንኖር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ከባድም ሆነ ቀላል ፈተና ሲያጋጥመን የምንወስደው እርምጃ “በየቀኑ” ይሖዋን ለማወደስ የገባነውን ቃል አክብደን እንደምንመለከት የሚያሳይ ሊሆን ይገባል። (መዝ. 61:8) ለምሳሌ ያህል፣ በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት አንድ ሰው ሊያሽኮረምምህ በሚሞክርበት ጊዜ ቆራጥ አቋም በመውሰድ ‘የይሖዋን መንገድ እንደምትወድ’ ታሳያለህ? (ምሳሌ 23:26) አሊያም ደግሞ የምትኖረው ይሖዋን በማያመልክ ቤተሰብ ውስጥ ነው እንበል። ከቤተሰብህ መካከል የይሖዋን መመሪያዎች ለመጠበቅ ጥረት የሚያደርግ ማንም ሰው ባይኖርም ክርስቲያናዊ አቋምህን ጠብቀህ ለመኖር እንዲረዳህ ይሖዋን በጸሎት ትጠይቀዋለህ? በሰማይ ወዳለው አፍቃሪ አባትህ በየቀኑ በመጸለይ ፍቅር ስላሳየህና በእሱ አገዛዝ ሥር እንድትሆን ስላስቻለህ ታመሰግነዋለህ? መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ለማንበብ ጊዜ ትመድባለህ? እስቲ አስበው፤ ራስህን በወሰንክበት ወቅት እነዚህን ነገሮች እንደምታደርግ ቃል ገብተህ የለም? በመሆኑም ይህ የታዛዥነት ጉዳይ ነው። በይሖዋ አምልኮ ሙሉ ተሳትፎ ማድረግህ እሱን እንደምትወደውና ራስህን ለእሱ የወሰንከው ከልብህ እንደሆነ ያሳያል። ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ እንዲሁ በዘልማድ የሚደረግ ሳይሆን መላ ሕይወታችንን የሚነካ ጉዳይ ነው። w17.10 23 አን. 11-12

ረቡዕ፣ ግንቦት 15

ለአምላካችን የውዳሴ መዝሙር መዘመር ጥሩ ነው።—መዝ. 147:1

አንድ ታዋቂ ገጣሚ ‘ቃላት፣ አንድን ሐሳብ በአእምሯችን እንድንሥል ያደርጉናል። ሙዚቃ ወይም መዝሙር ደግሞ የሚተላለፈው ሐሳብ ስሜታችንን እንዲኮረኩረው ያደርጋል’ ብሎ ነበር። በሰማይ ያለውን አባታችንን ይሖዋን ለማወደስና ለእሱ ያለንን ፍቅር በመዝሙር ለመግለጽ ከሚያስችሉ ሐሳቦች የተሻለ ስሜታችንን ሊኮረኩር የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ ጥያቄ የለውም! በእርግጥም፣ ለብቻችንም ይሁን በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሆነን የምንዘምረው መዝሙር በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑ የሚያስገርም አይደለም። አንተስ በጉባኤ ውስጥ ድምፅህን ከፍ አድርገህ መዘመርን በተመለከተ ምን ይሰማሃል? እንዲህ ማድረግ ያሳፍርሃል? በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ውስጥ ወንዶች፣ ሰው በተሰበሰበበት ቦታ መዘመር ያሳፍራቸው ይሆናል። እንዲህ ያለው አመለካከት በመላው ጉባኤ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፤ በተለይ ደግሞ ኃላፊነት ያላቸው ወንዶች፣ ጉባኤ ላይ መዝሙር በሚዘመርበት ወቅት የማይዘምሩ አሊያም በሌሎች እንቅስቃሴዎች የሚጠመዱ ከሆነ ይህ ሌሎችም ከመዘመር ወደኋላ እንዲሉ ሊያደርጋቸው ይችላል። (መዝ. 30:12) መዝሙርን እንደ አምልኳችን ክፍል አድርገን የምንመለከተው ከሆነ መዝሙር ሲዘመር ወደ ውጭ አንወጣም፤ እንዲሁም ይህ የስብሰባው ክፍል እንዳያመልጠን እንጠነቀቃለን። w17.11 3 አን. 1-3

ሐሙስ፣ ግንቦት 16

በምድር ላይ ሰላም ለማስፈን የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ የመጣሁት ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አይደለም።—ማቴ. 10:34

ሁላችንም ከጭንቀት ነፃ የሆነ ሰላማዊ ሕይወት መምራት እንፈልጋለን። በመሆኑም ይሖዋ ከሚረብሹ ሐሳቦችና ከአሉታዊ ስሜቶች የሚጠብቀንን “የአምላክ ሰላም” በመስጠት ውስጣዊ መረጋጋት እንዲኖረን ስለሚረዳን በጣም አመስጋኞች ነን! (ፊልጵ. 4:6, 7) በተጨማሪም ራሳችንን ለይሖዋ ስለወሰንን ‘ከአምላክ ጋር ሰላም’ ሊኖረን ማለትም ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና ልንመሠርት ችለናል። (ሮም 5:1) ይሁንና አምላክ በምድር ላይ ሙሉ በሙሉ ሰላምን የሚያሰፍንበት ጊዜ ገና አልመጣም። የምንኖረው በዓይነቱ ልዩ በሆነውና በግጭት በተሞላው የመጨረሻው ዘመን ውስጥ ስለሆነ በርካታ ሰዎች የጠበኝነት ባሕርይ ማንጸባረቅ ይቀናቸዋል። (2 ጢሞ. 3:1-4) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሰይጣንን እንዲሁም እሱ የሚያስፋፋቸውን የሐሰት ትምህርቶች ለመቃወም መንፈሳዊ ውጊያ ማካሄድ ይኖርብናል። (2 ቆሮ. 10:4, 5) ሰላማችንን የሚያውከው ትልቁ ምክንያት ግን ከማያምኑ ቤተሰቦቻችን የሚመጣው ተቃውሞ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ቤተሰቦቻችን በእምነታችን ሊያፌዙብን፣ ቤተሰብን እንደምንከፋፍል አድርገው ሊናገሩ ወይም እምነታችንን ካልካድን እንደ ቤተሰቡ አባል አድርገው እንደማይቀበሉን ሊገልጹ ይችላሉ። w17.10 12 አን. 1-2

ዓርብ፣ ግንቦት 17

ሕግህን ምንኛ ወደድኩ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ።—መዝ. 119:97

ቋንቋ በጊዜ ሂደት ስለሚለወጥ መጽሐፍ ቅዱስ የተተረጎመባቸው ቋንቋዎችም መለወጣቸው አይቀርም። መጀመሪያ ሲዘጋጅ ለመረዳት ቀላል የነበረ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንኳ ከጊዜ በኋላ ለመረዳት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደ ምሳሌ እንመልከት። ኪንግ ጄምስ ቨርዥን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው በ1611 ነው። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በስፋት ከተሰራጩት የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሶች መካከል አንዱ ሲሆን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ሆኖም ዘመናት እያለፉ ሲሄዱ ኪንግ ጄምስ ቨርዥን ላይ የሚገኙ አንዳንድ አገላለጾች ጊዜ ያለፈባቸው ሆኑ። ከረጅም ጊዜ በፊት ከተዘጋጁ በሌላ ቋንቋ የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም ጋር በተያያዘ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በመሆኑም በዘመናዊ ቋንቋ የተዘጋጀውን አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘታችን የሚያስደስት አይደለም? ይህ ትርጉም ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ከ150 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል፤ በመሆኑም በርካታ ሰዎች ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የማንበብ አጋጣሚ አላቸው። ይህ ትርጉም ቀለል ያሉ ቃላትን ስለሚጠቀም የአምላክ ቃል ወደ ልባችን ዘልቆ እንዲገባ ያደርጋል። w17.09 19 አን. 5-6

ቅዳሜ፣ ግንቦት 18

ልጄ ሆይ . . . ጥበበኛ ሁን፤ ልቤንም ደስ አሰኘው።—ምሳሌ 27:11

ክርስቲያን ወጣቶች ሊያደርጓቸው የሚገቡ አስፈላጊ ውሳኔዎች አሉ። ጥሩ ጓደኞችንና ጤናማ መዝናኛን ከመምረጥ፣ የሥነ ምግባር ንጽሕናን ከመጠበቅ እንዲሁም ራስን ወስኖ ከመጠመቅ ጋር በተያያዘ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ማድረግ ደፋር መሆንን ይጠይቃል። ምክንያቱም እንዲህ ያሉ ውሳኔዎችን የሚያደርጉ ወጣቶች አምላክን የሚነቅፈው ሰይጣን ከሚፈልገው ነገር ጋር የሚቃረን እርምጃ እየወሰዱ ነው። ወጣቶች ከሚያጋጥሟቸው ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ግብ ማውጣት ነው። በአንዳንድ አገሮች ወጣቶች ከፍተኛ ትምህርት እንዲከታተሉና ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ እንዲይዙ ጫና ይደረግባቸዋል። በሌሎች አገሮች ደግሞ፣ ካለው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የተነሳ ወጣቶች ቤተሰባቸውን በቁሳዊ ነገሮች በመደገፍ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ሊሰማቸው ይችላል። ይሖዋ ደፋሮች በመሆን መንፈሳዊ ግቦችን የሚያወጡና በሕይወታቸው ውስጥ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ የሚሰጡ ወጣቶችን ይባርካቸዋል። በተጨማሪም ቤተሰብ ከመሠረቱ በኋላ ቤተሰባቸውን ማስተዳደር እንዲችሉ ይረዳቸዋል። በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶችም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደኖረው እንደ ወጣቱ ጢሞቴዎስ ሁሉ መንፈሳዊ ግቦችን በመከታተል ላይ ትኩረት ማድረግ ይችላሉ።—ፊልጵ. 2:19-22፤ w17.09 29-30 አን. 10-12

እሁድ፣ ግንቦት 19

ይህ የሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ በውስጡ የተጻፈውንም በጥንቃቄ [ፈጽም]፤ . . . እንዲህ ካደረግክ መንገድህ ይቃናልሃል፤ እንዲሁም ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን ትችላለህ።—ኢያሱ 1:8

ክርስቲያኖች በትጋትና ትርጉም ባለው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸው ራስን የመግዛት ባሕርይን ለማዳበር ይረዳቸዋል። እንዴት? መጽሐፍ ቅዱስ፣ የምንወስደው እርምጃ የሚያስገኘውን ጥቅምም ሆነ የሚያስከትለውን ጉዳት በግልጽ የሚያሳዩ ዘገባዎችን ይዟል። ይሖዋ እነዚህ ታሪኮች ተመዝግበው እንዲቆዩ ያደረገው በዓላማ ነው። (ሮም 15:4) እነዚህን ታሪኮች ማንበባችን፣ ማጥናታችንና በእነሱ ላይ ማሰላሰላችን በእርግጥም ጥበብ ነው! እነዚህን ዘገባዎች በግል ሕይወታችሁም ሆነ በቤተሰባችሁ ውስጥ ተግባራዊ ልታደርጓቸው የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክሩ። ይሖዋ በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ እንዲረዳችሁ ጸልዩ። በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር ራሳችሁን መግዛት እንደሚከብዳችሁ ካስተዋላችሁ ይህን አምናችሁ ተቀበሉ። ከዚያም ጉዳዩን አስመልክታችሁ ጸልዩ፤ እንዲሁም ማሻሻያ ማድረግ የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ጥረት አድርጉ። (ያዕ. 1:5) በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን ላይ ምርምር ማድረጋችሁ ራስን የመግዛት ባሕርይን ለማዳበር ሊረዷችሁ የሚችሉ ተጨማሪ ነጥቦችን ለማግኘት እንደሚያስችላችሁ ምንም ጥርጥር የለውም። w17.09 6 አን. 15-16

ሰኞ፣ ግንቦት 20

አዲሱን ስብዕና ልበሱ።—ቆላ. 3:10

‘አዲሱ ስብዕና’ “እንደ አምላክ ፈቃድ [የተፈጠረን]” ስብዕና ያመለክታል። (ኤፌ. 4:24) እንዲህ ያለውን አዲስ ስብዕና ማዳበር ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ የሰው ልጆችን የፈጠረው በራሱ አምሳል ነው፤ በመሆኑም ሁላችንም የእሱን ግሩም ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ አለን። (ዘፍ. 1:26, 27፤ ኤፌ. 5:1) ጳውሎስ አዲሱን ስብዕና እንድንለብስ ማሳሰቢያ ከሰጠ በኋላ የአዲሱ ስብዕና አስፈላጊ ገጽታ የሆነውን ከአድልዎ ነፃ መሆንን አስመልክቶ ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “ግሪካዊ ወይም አይሁዳዊ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ የባዕድ አገር ሰው፣ እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ነፃ ሰው ብሎ ልዩነት የለም።” በጉባኤ ውስጥ በዘር፣ በብሔር አሊያም በኑሮ ደረጃ ምክንያት ልዩነት ሊኖር የማይገባው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች በሙሉ ‘አንድ ናቸው።’ (ቆላ. 3:11፤ ገላ. 3:28) አዲሱን ስብዕና የለበሱ ሰዎች የእምነት ባልንጀሮቻቸውንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን በአክብሮት ይይዛሉ፤ ከየትኛውም ዘር ወይም የኑሮ ደረጃ ለመጡ ሰዎች አክብሮት አላቸው።—ሮም 2:11፤ w17.08 22 አን. 1፤ 23 አን. 3-4

ማክሰኞ፣ ግንቦት 21

ይሖዋ . . . በትዕግሥት ይጠባበቃል።—ኢሳ. 30:18

ይሖዋ እሱ ራሱ የማያደርገውን ነገር እንድናደርግ አልጠየቀንም። በትዕግሥት በመጠበቅ ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ትቶልናል። (2 ጴጥ. 3:9) ይሖዋ በኤደን ገነት ውስጥ በአገዛዙ ላይ የተነሳው ጥያቄ በማያዳግም ሁኔታ ምላሽ እንዲያገኝ ሲል በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በትዕግሥት ሲጠባበቅ ቆይቷል። ስሙ ሙሉ በሙሉ የሚቀደስበትን ጊዜ “በትዕግሥት [በመጠባበቅ]” ላይ ይገኛል። ይህም ‘እሱን በጉጉት ለሚጠባበቁ ሁሉ’ ወደር የሌለው በረከት ያስገኛል። (ኢሳ. 30:18 ግርጌ) ኢየሱስም በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነበር። በምድር ላይ ሳለ የደረሰበትን የታማኝነት ፈተና በተሳካ ሁኔታ የተወጣ እንዲሁም በ33 ዓ.ም. የቤዛውን ዋጋ የከፈለ ቢሆንም መግዛት ለመጀመር እስከ 1914 ድረስ መጠበቅ አስፈልጎታል። (ሥራ 2:33-35፤ ዕብ. 10:12, 13) ጠላቶቹም ቢሆኑ ሙሉ በሙሉ የሚወገዱት በሺህ ዓመት ግዛቱ መጨረሻ ላይ ነው። (1 ቆሮ. 15:25) ይሁንና ኢየሱስ በትዕግሥት በመጠበቁ ፈጽሞ እንደማይቆጭ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። w17.08 7 አን. 16-17

ረቡዕ፣ ግንቦት 22

አምላክ . . . በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል።—2 ቆሮ. 1:3, 4

“ልጃችን ከሞተ በኋላ ወደ አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በጥልቅ ሐዘን ተውጠን ነበር” በማለት ሱሲ የተባለች እህት ተናግራለች። ባለቤቱ በድንገት የሞተችበት አንድ ክርስቲያን ደግሞ “በቃላት ለመግለጽ የሚከብድ አካላዊ ሥቃይ ይሰማው እንደነበር” ተናግሯል። የሚያሳዝነው ሌሎች በርካታ ሰዎችም እንዲህ ዓይነት ሥቃይ አጋጥሟቸዋል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ብዙ ወንድሞችና እህቶች፣ አርማጌዶን ከመምጣቱ በፊት የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ሊያጡ እንደሚችሉ አልጠበቁ ይሆናል። አንተ ራስህ የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ሐዘን የደረሰበት ሰው ታውቅ ይሆናል፤ በመሆኑም ‘ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች መጽናኛ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?’ የሚል ጥያቄ ሊፈጠርብህ ይችላል። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ ሐዘን እየቀነሰ እንደሚመጣ ሲነገር ሰምተህ ይሆናል። ይሁንና ጊዜ ማለፉ ብቻ ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች የተሰበረ ልብ ይጠግነዋል? ባለቤቷን በሞት ያጣች አንዲት ሴት “ሐዘኑ እንዲቀንስልን የሚረዳን፣ ጊዜያችንን የምናሳልፍበት መንገድ ነው ቢባል ይበልጥ ትክክል እንደሆነ ይሰማኛል” ብላለች። አካላዊ ቁስል ተገቢው እንክብካቤ ከተደረገለት ውሎ አድሮ እየዳነ እንደሚሄድ ሁሉ፣ ስሜቱ የተጎዳ ሰውም ተገቢውን እርዳታ ካገኘ ቀስ በቀስ ሥቃዩ እየቀነሰ ይሄዳል። w17.07 12-13 አን. 1-3

ሐሙስ፣ ግንቦት 23

በይሖዋ ሐሴት አድርግ፤ እሱም የልብህን መሻት ይሰጥሃል።—መዝ. 37:4

ይሖዋ የሚያበረታታህ ምን ዓይነት ዕቅድ እንድታወጣ ነው? የሰው ልጆችን የፈጠራቸው፣ ስለ እሱ በማወቅና እሱን በታማኝነት በማገልገል ደስታ እንዲያገኙ አድርጎ ነው። (መዝ. 128:1፤ ማቴ. 5:3) የሰው ልጆች ሕይወት፣ በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም በመራባት ብቻ ረክተው እንዲኖሩ ከተፈጠሩት እንስሳት ሕይወት በእጅጉ የተለየ ነው። አንተም እንስሳትን ከሚያስደስቷቸው ነገሮች የበለጡ ግቦች ላይ ለመድረስ ዕቅድ እንድታወጣ ይሖዋ ይፈልጋል፤ ይህን ማድረግህ በሕይወትህ ደስተኛ ለመሆን ያስችልሃል። ፈጣሪያችን ‘የፍቅር አምላክ’ እንዲሁም ‘ደስተኛ አምላክ’ እንደሆነ ብሎም የሰው ልጆችን “በራሱ መልክ” እንደፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ቆሮ. 13:11፤ 1 ጢሞ. 1:11፤ ዘፍ. 1:27) አፍቃሪ የሆነውን አምላካችንን ለመምሰል ስትጥር ደስተኛ ትሆናለህ። “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” የሚለውን ጥቅስ እውነተኝነት በሕይወትህ ተመልክተህ አታውቅም? (ሥራ 20:35) ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ ይህ የማይታበል ሐቅ ነው። ይሖዋ፣ ለእሱና ለሌሎች ፍቅር በማሳየት ላይ ያተኮረ ዕቅድ እንድታወጣ የሚፈልገው ለዚህ ነው።—ማቴ. 22:36-39፤ w17.07 23 አን. 3

ዓርብ፣ ግንቦት 24

ንጹሕ አቋም ይዘው የሚመላለሱትን ይሖዋ አንዳች መልካም ነገር አይነፍጋቸውም።—መዝ. 84:11

አምላክ አገልጋዮቹን የሚይዛቸው በአክብሮት ነው። እኛ ለራሳችን ከምናስበው በላይ አምላክ ለእኛ ያስብልናል። ይሖዋ ለሕዝቡ አሳቢነት የሚያሳየው በቡድን ደረጃ ብቻ አይደለም። ለእያንዳንዱ ግለሰብም ትኩረት ይሰጣል። እስቲ በጥንት ዘመን የነበረውን ሁኔታ እንመልከት። ይሖዋ ለሦስት መቶ ዘመናት ያህል መሳፍንት በማስነሳት የእስራኤልን ብሔር ይመራ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በጠላቶቻቸው ላይ ድል ያቀዳጃቸው ነበር። ይሁንና ከፍተኛ አለመረጋጋት በነበረበት በዚያ ዘመንም እንኳ ይሖዋ ለሰዎች በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ይሰጥ ነበር። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዷ ሩት የተባለች እስራኤላዊት ያልሆነች ሴት ነች። ሩት የሐሰት አምልኮን ትታ ይሖዋን ለማምለክ ስትል ትልቅ መሥዋዕትነት ከፍላለች። ይሖዋ ሩትን ባልና ወንድ ልጅ በመስጠት ባርኳታል። ይሁንና ያገኘችው በረከት ይህ ብቻ አይደለም። መሲሑ የመጣው በልጇ የዘር ሐረግ በኩል ነው። በተጨማሪም ይሖዋ የሕይወት ታሪኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው በስሟ የተጠራ መጽሐፍ ላይ እንዲሰፍር አድርጓል። ሩት ትንሣኤ በምታገኝበት ወቅት ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ስታውቅ ምን ሊሰማት እንደሚችል አስብ!—ሩት 4:13፤ ማቴ. 1:5, 16፤ w17.06 28-29 አን. 8-9

ቅዳሜ፣ ግንቦት 25

መንፈስ ቅዱስ . . . የነገርኳችሁን ነገር ሁሉ እንድታስታውሱ ያደርጋችኋል።—ዮሐ. 14:26

በ1970፣ ፒተር የተባለ አንድ ወንድም የ19 ዓመት ወጣት በነበረበት ወቅት ብሪታንያ ውስጥ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ማገልገል ጀመረ። ከቤት ወደ ቤት በሚያገለግልበት ወቅት አንድ ጺማም የሆነ ሰው አገኘ። ፒተር ሰውየውን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማወቅ ይፈልግ እንደሆነ ጠየቀው። ሰውየው የአይሁድ ረቢ ስለነበር ይህ ወጣት መጽሐፍ ቅዱስን ሊያስተምረው ማሰቡ አስገረመው። ረቢው ፒተርን ለመፈተን “እሺ የእኔ ልጅ፣ ለመሆኑ የዳንኤል መጽሐፍ የተጻፈው በምን ቋንቋ ነው?” ሲል ጠየቀው። ፒተርም “የተወሰነው ክፍል የተጻፈው በአረማይክ ነው” ብሎ መለሰ። ፒተር እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “ረቢው መልሱን በማወቄ ተገረመ፤ ከእሱ ይበልጥ የተገረምኩት ግን እኔ ነበርኩ! መልሱን ማወቅ የቻልኩት እንዴት ነው? ወደ ቤት ተመልሼ ባለፉት ወራት የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ስመለከት የዳንኤል መጽሐፍ የተወሰነው ክፍል የተጻፈው በአረማይክ እንደሆነ የሚናገር ርዕስ አገኘሁ።” (ዳን. 2:4 ግርጌ) ከዚህ ማየት እንደምንችለው መንፈስ ቅዱስ ከዚህ በፊት ያነበብናቸውን ነገሮች እንድናስታውስ ሊረዳን ይችላል።—ሉቃስ 12:11, 12፤ 21:13-15፤ w17.06 13 አን. 17

እሁድ፣ ግንቦት 26

የሚያገቡ ሰዎች በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል።—1 ቆሮ. 7:28

ሚስት ስታረግዝ ውጥረት የሚያስከትሉ አዳዲስ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። ልጅ ማግኘት በራሱ በጣም የሚያስደስት ነገር ቢሆንም በእርግዝና ወቅት ወይም ከዚያ በኋላ ሊያጋጥም የሚችለውን ከጤና ጋር የተያያዘ ችግር ማሰባቸው ደስታቸውን ሊያደበዝዘው ይችላል። በተጨማሪም ልጅ መውለድ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንደሚያስከትል የታወቀ ነው። ልጁ ከተወለደ በኋላ ባልና ሚስቱ ተጨማሪ ማስተካከያዎች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። እናትየው አብዛኛውን ጊዜዋን የምታሳልፈው ልጇን በመንከባከብ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ባልየው ሚስቱ ትኩረት እንደነፈገችው ሊሰማው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ባልየው ራሱ አባት መሆኑ የሚያስከትልበት ተጨማሪ ኃላፊነት ይኖራል። ለሚስቱ ብቻ ሳይሆን ለልጁም ጭምር እንክብካቤ ማድረግና የሚያስፈልገውን ማሟላት ይጠበቅበታል። አንዳንድ ባለትዳሮች ደግሞ የተለየ ዓይነት መከራ ይደርስባቸዋል። ልጅ ለመውለድ የሚጓጉ ቢሆንም እንኳ መውለድ ሳይችሉ ይቀራሉ። ሚስትየዋ ማርገዝ አለመቻሏ ከባድ የስሜት ሥቃይ ሊያስከትልባት ይችላል። w17.06 4 አን. 1፤ 5 አን. 5-6

ሰኞ፣ ግንቦት 27

የተናገርከው ነገር ለምላሴ እጅግ ጣፋጭ ነው፤ ለአፌም ከማር የበለጠ ይጥማል!—መዝ. 119:103

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እውነትን እንወዳለን፤ እንዲሁም ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ከሁሉ የላቀው የእውነት ምንጭ የአምላክ ቃል ነው። ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ቃልህ እውነት ነው” ብሏል። (ዮሐ. 17:17) በመሆኑም ለእውነት ፍቅር ማዳበር እንድንችል፣ መጀመሪያ ስለ አምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት መቅሰም ያስፈልገናል። (ቆላ. 1:10) ይህ ግን የጭንቅላት እውቀት ከማካበት ያለፈ ነገርን የሚያካትት ነው። መዝሙር 119⁠ን በመንፈስ መሪነት የጻፈው መዝሙራዊ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መውደድ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ገልጿል። (መዝ. 119:97-100) ባነበብናቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ላይ ለማሰላሰል ወይም በጥልቀት ለማሰብ በየዕለቱ ጊዜ እንመድባለን? የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረጋችን ባስገኘልን ጥቅሞች ላይ ስናሰላስል፣ በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኘው እውነት ያለን አድናቆት እየጨመረ ይሄዳል። በተጨማሪም በአምላክ ድርጅት በኩል የምናገኘውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መንፈሳዊ ምግብ እንደ ጣፋጭ ምግብ ማጣጣም እንችላለን። መንፈሳዊውን ምግብ በምሳሌያዊ መንገድ እያጣጣምን መመገባችን፣ የእውነትን “ደስ የሚያሰኙ ቃላት” በሌላ ጊዜ እንድናስታውስና ሌሎችን ለመርዳት እንድንጠቀምበት ያስችለናል።—መክ. 12:10፤ w17.05 19-20 አን. 11-12

ማክሰኞ፣ ግንቦት 28

አምላክ በእርግጥ በመካከላችሁ ነው።—1 ቆሮ. 14:25

የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑትን ጨምሮ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን መርዳት እንፈልጋለን። (ሉቃስ 10:33-37) ይህን ማድረግ የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ደግሞ ለእነዚህ ሰዎች ምሥራቹን መስበክ ነው። በርካታ ስደተኞችን የረዳ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “እኛ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆንን እና ዋነኛ ዓላማችን ሰዎችን በመንፈሳዊ እንጂ በቁሳዊ መርዳት እንዳልሆነ ገና ከጅምሩ ግልጽ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። አለዚያ አንዳንዶች ወደ እኛ የሚመጡት ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ብቻ ሊሆን ይችላል።” ‘ለባዕድ አገር ሰዎች’ ክርስቲያናዊ ፍቅር ማሳየታችን ጥሩ ውጤት ያስገኛል። (መዝ. 146:9) ለምሳሌ፣ የአንዲት እህት ቤተሰቦች ኤርትራ ውስጥ በደረሰባቸው ስደት ምክንያት ወደ ሱዳን ሸሹ። አራት ልጆቿ በረሃ ውስጥ ለስምንት ቀናት ያህል አድካሚ የሆነ ጉዞ ካደረጉ በኋላ ሱዳን ደረሱ። እህት እንዲህ ብላለች፦ “ሱዳን ያሉት ወንድሞች እንደ ቤተሰባቸው አድርገው የተቀበሏቸው ሲሆን ምግብ፣ ልብስና መኖሪያ እንዲሁም ለመጓጓዣ የሚሆን ገንዘብ ሰጧቸው። የሚያመልኩት አምላክ አንድ ስለሆነ ብቻ የባዕድ አገር ሰዎችን ቤታቸው የሚቀበሉ የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው!”—ዮሐ. 13:35፤ w17.05 7 አን. 17, 19-20

ረቡዕ፣ ግንቦት 29

አገልጋዬ ኢዮብ እንዳደረገው ስለ እኔ እውነቱን አልተናገራችሁም።—ኢዮብ 42:8

“ሰው አምላክን ሊጠቅመው ይችላል? ማስተዋል ያለውስ ሰው ምን ይፈይድለታል? ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ አንተ ጻድቅ መሆንህ ግድ ይሰጠዋል? ወይስ በንጹሕ አቋም መመላለስህ እሱን ይጠቅመዋል?” (ኢዮብ 22:1-3) እንደ እነዚህ ያሉ ጥያቄዎች ወደ አእምሮህ መጥተው ያውቃሉ? ቴማናዊው ኤሊፋዝ፣ ኢዮብን እንዲህ ብሎ ሲጠይቀው መልሱ ‘በጭራሽ’ የሚል እንደሚሆን ተማምኖ ነበር። ወዳጁ የሆነው ሹሃዊው በልዳዶስ ደግሞ ሰው በአምላክ ፊት ጻድቅ መሆን እንደማይችል ተናግሯል። (ኢዮብ 25:4) እነዚህ የሐሰት አጽናኞች ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል የምናደርገው ጥረት እሱን ምንም እንደማይጠቅመው እንዲሁም አምላክ ከብል፣ ከእጭ ወይም ከትል አስበልጦ እንደማይመለከተን ለማሳመን እየሞከሩ ነበር። (ኢዮብ 4:19፤ 25:6) ኤሊፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር የተሳሳተ ነገር ስለተናገሩ ይሖዋ እርማት የሰጣቸው መሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አመለካከት ግልጽ ያደርገዋል፤ ኢዮብን ግን “አገልጋዬ” ብሎ በመጥራት በእሱ እንደሚደሰት አሳይቷል። (ኢዮብ 42:7) በእርግጥም “ሰው አምላክን ሊጠቅመው ይችላል።” w17.04 28 አን. 1-2

ሐሙስ፣ ግንቦት 30

በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።—መዝ. 37:11

ሕይወታችንን በሙሉ ያሳለፍነው በዚህ አሮጌ ዓለም ውስጥ ከመሆኑ አንጻር በዓለም ላይ ያሉት ሁኔታዎች ምን ያህል ጭንቀት እንደሚፈጥሩብን ላናስተውል እንችላለን። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ሕዝብ በሚበዛበት የባቡር ጣቢያ አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሁካታውን ይለምዱት ይሆናል፤ በቆሻሻ መጣያ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችም እንዲሁ ሽታው ላይረብሻቸው ይችላል። በአሁኑ ጊዜ ያሉት አስጨናቂ ሁኔታዎች በሙሉ ሲወገዱ እንዴት ያለ እፎይታ እናገኝ ይሆን! በዛሬው ጊዜ የሚሰማን ጭንቀት ሲወገድ ምን ዓይነት ስሜት ይሰማን ይሆን? በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ተስፋ ልብ በል። ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ደስታ እንድናገኝ እንደሚፈልግ ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! እንግዲያው በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ከይሖዋ አምላክና ከድርጅቱ ጋር ተቀራርበህ ለመኖር የምትችለውን ሁሉ አድርግ። ውድ የሆነውን ተስፋህን ከፍ አድርገህ ተመልከተው፤ በተስፋህ ላይ በማሰላሰል እውን ሆኖ እንዲታይህ አድርግ፤ እንዲሁም ስለ ተስፋህ ለሌሎች ተናገር። (1 ጢሞ. 4:15, 16፤ 1 ጴጥ. 3:15) እንዲህ ካደረግህ ከዚህ አሮጌ ዓለም ጋር አብረህ አትጠፋም። ከዚህ ይልቅ በሕይወት ተርፈህ ለዘላለም በደስታ ትኖራለህ! w17.04 13 አን. 16-17

ዓርብ፣ ግንቦት 31

ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሳሳታለን።—ያዕ. 3:2 ግርጌ

ማናችንም ይህን ሐቅ መቀበል አይከብደንም፤ ይሁን እንጂ አንድ ወንድም የፈጸመው ስህተት በግለሰብ ደረጃ የሚነካን ሲሆን ሁኔታው ፈታኝ ሊሆንብን ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ይሖዋ ስለ ፍትሕ ያለውን አመለካከት እናንጸባርቃለን? ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሽማግሌ በተወሰነ መጠንም ቢሆን እንደሚያዳላ የሚጠቁም ሐሳብ ቢሰነዝር ምን ይሰማሃል? አሊያም ደግሞ አንድ ሽማግሌ አንተን የሚጎዳ ወይም የሚያሳዝን ነገር ሳያስበው ቢናገር በዚህ ትደናቀፋለህ? ይህ ወንድም ከዚህ በኋላ ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል ብቁ እንዳልሆነ ቸኩለህ ከመደምደም ይልቅ የጉባኤው ራስ የሆነውን ኢየሱስን በትዕግሥት ትጠባበቃለህ? ይህ ሽማግሌ በሠራው ስህተት ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ለረጅም ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ማገልገሉን ለማስታወስ ትሞክራለህ? አንተን የበደለህ ወንድም በሽምግልና ማገልገሉን ቢቀጥል እንዲያውም ተጨማሪ መብቶች ቢያገኝ አብረኸው ትደሰታለህ? ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆንህ ከፍትሕ ጋር በተያያዘ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንዳለህ ያሳያል።—ማቴ. 6:14, 15፤ w17.04 27 አን. 18

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ