ሰኔ
ቅዳሜ፣ ሰኔ 1
አምላክ ፍቅር ነው።—1 ዮሐ. 4:16
ይሖዋ ስለሚወደን ከእሱ ፍቅር ሳንወጣ እንድንኖርና በሕይወት ጎዳና ላይ መጓዛችንን እንድንቀጥል ሲል እርማት፣ ትምህርትና ሥልጠና ይሰጠናል። አንዳንድ ጊዜ ግን ተግሣጽ በቃል ከሚሰጥ ምክር ወይም እርማት ያለፈ ነገርን ሊጨምር ይችላል። አንድ ሰው ከበድ ያለ ኃጢአት ከሠራ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን መብቶች ሊያጣ ይችላል። እንዲህ ያለው ተግሣጽም ቢሆን አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳያል። ለምሳሌ አንድ ሰው መብቶቹን ማጣቱ ለግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ለማሰላሰልና ለጸሎት ይበልጥ ትኩረት መስጠቱ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘብ ሊያደርገው ይችላል። ይህ ደግሞ በመንፈሳዊ እንዲጠናከር ይረዳዋል። (መዝ. 19:7) ከጊዜ በኋላ ግለሰቡ መብቶቹን መልሶ ሊያገኝ ይችላል። ሌላው ቀርቶ ኃጢአተኛው ከጉባኤ እንዲወገድ መደረጉም እንኳ የይሖዋን ፍቅር ያንጸባርቃል፤ ምክንያቱም ይህ እርምጃ መወሰዱ ጉባኤውን ከመጥፎ ተጽዕኖ ይጠብቃል። (1 ቆሮ. 5:6, 7, 11) ደግሞም አምላክ የሚገሥጸው በተገቢው መጠን ስለሆነ የውገዳ ዝግጅት፣ መጥፎ ድርጊት የፈጸመው ሰው ኃጢአቱ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እንዲገነዘብና ንስሐ ለመግባት እንዲነሳሳ ሊያደርገው ይችላል።—ሥራ 3:19፤ w18.03 24 አን. 5-6
እሁድ፣ ሰኔ 2
እሱና መላው ቤተሰቡ ወዲያውኑ ተጠመቁ።—ሥራ 16:33
የእስር ቤቱ ጠባቂ የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት አልነበረውም። ስለዚህ ክርስቲያን ለመሆን፣ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን መማርና አምላክ ከአገልጋዮቹ ምን እንደሚጠብቅ መረዳት እንዲሁም የኢየሱስን ትምህርት ለመታዘዝ ፈቃደኛ መሆን ነበረበት። መሠረታዊ ስለሆኑ የቅዱሳን መጻሕፍት እውነቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ያገኘው እውቀት ብሎም ለተማረው ነገር ያደረበት አድናቆት ለመጠመቅ አነሳስቶታል። (ሥራ 16:25-33) ይህ ሰው ከተጠመቀ በኋላም እውቀት መቅሰሙን እንደቀጠለ ጥያቄ የለውም። ወላጆች ከዚህ ታሪክ ትምህርት ማግኘት ትችላላችሁ፤ ልጃችሁ መሠረታዊ የሆኑ የቅዱሳን መጻሕፍት ትምህርቶችን በሚገባ ስለተረዳ እንዲሁም ራስን መወሰንና ጥምቀት ምን ትርጉም እንዳላቸው ስለተገነዘበ መጠመቅ እንደሚፈልግ ቢነግራችሁ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? ልጃችሁ ለመጠመቅ የሚያስፈልገውን ብቃት ማሟላቱን ለማወቅ የጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲያነጋግሩት ዝግጅት ማድረግ ትችላላችሁ። እንደ ማንኛውም የተጠመቀ ደቀ መዝሙር ሁሉ ልጃችሁም በመላ ሕይወቱ እንዲያውም ለዘላለም ስለ ይሖዋ ዓላማዎች እውቀት መቅሰሙን ይቀጥላል።—ሮም 11:33, 34፤ w18.03 10 አን. 8-9
ሰኞ፣ ሰኔ 3
ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ [ይኑራችሁ]።—ሮም 15:5
መንፈሳዊነታችንን ለማጠናከር የምንጥር ከሆነ መንፈስ ቅዱስ በአስተሳሰባችን ላይ ለውጥ ለማድረግ ይረዳናል። መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን እርዳታ በአስተሳሰባችን ይበልጥ ክርስቶስን እየመሰልን እንድንሄድ ያደርገናል። ከዚህም ሌላ፣ ሥጋዊ ምኞቶችን እንድናስወግድና አምላክን የሚያስደስቱ ባሕርያትን እንድናዳብር ይረዳናል። የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበራችን በንግግራችን፣ በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት በሚኖረን ምግባር እንዲሁም በየዕለቱ በምናደርገው ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። የምናደርጋቸው ውሳኔዎች የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆን እንደምንጥር የሚያሳዩ ይሆናሉ። መንፈሳዊ ሰዎች ስለሆንን፣ ከሰማዩ አባታችን ጋር ያለንን ዝምድና ምንም ነገር እንዲያበላሽብን አንፈቅድም። የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ፣ ትክክል ያልሆነ ነገር ለማድረግ በምንፈተንበት ጊዜ ፈተናውን ለመወጣት ያስችለናል። ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ቆም ብለን እናስባለን፦ ‘ከጉዳዩ ጋር የሚያያዙት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው? ክርስቶስ በእኔ ቦታ ቢሆን ኖሮ ምን ዓይነት ውሳኔ ያደርግ ነበር? ይሖዋን የሚያስደስተው ምን ዓይነት ውሳኔ ነው?’ w18.02 25 አን. 12፤ 26 አን. 14
ማክሰኞ፣ ሰኔ 4
ኖኅ . . . በይሖዋ ፊት ሞገስ አገኘ።—ዘፍ. 6:8
የኖኅ ቅድመ አያት በሆነው በሄኖክ ዘመን የነበሩት ሰዎች ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ነበሩ። ሌላው ቀርቶ በይሖዋ ላይ “ክፉ ቃል” ይናገሩ ነበር። (ይሁዳ 14, 15) ዓመፅ ከዕለት ወደ ዕለት እየተስፋፋ ነበር። እንዲያውም በኖኅ ዘመን ምድር “በዓመፅ ተሞልታ ነበር።” ክፉ መላእክት ሥጋ ለብሰው ወደ ምድር በመምጣት የሰውን ሴቶች ልጆች ያገቡ ሲሆን ጨካኝ የሆኑ የሰውና የመላእክት ዲቃላዎችን ወለዱ። (ዘፍ. 6:2-4, 11, 12) ኖኅ ግን በዘመኑ ካሉት ሰዎች የተለየ አቋም ነበረው። “በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች መካከል እሱ እንከን የሌለበት ሰው ነበር። ኖኅ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር።” (ዘፍ. 6:9) እስቲ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኖኅ ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው በዓመፅ የተሞላ ዓለም ውስጥ ከአምላክ ጋር የሄደው በዛሬው ጊዜ ያለውን የሰው ልጅ ዕድሜ ያህል ማለትም ለ70 ወይም ለ80 ዓመት ብቻ አልነበረም። በዚያ ዓለም ውስጥ ለ600 ዓመታት ያህል ኖሯል! (ዘፍ. 7:11) በተጨማሪም ኖኅ ልክ እንደ እኛ የሚደግፉትና የሚያበረታቱት የእምነት ባልንጀሮች አልነበሩትም፤ ከሁኔታዎች መረዳት እንደምንችለው የገዛ ወንድሞቹና እህቶቹም እንኳ መንፈሳዊ ድጋፍ አላደረጉለትም። w18.02 4 አን. 4-5
ረቡዕ፣ ሰኔ 5
ሰዎች . . . ገንዘብ የሚወዱ [ይሆናሉ]።—2 ጢሞ. 3:2
ገንዘብን የሚወዱ ሰዎች ምንጊዜም ተጨማሪ ለማግኘት ይጥራሉ እንጂ በቃኝ አይሉም፤ ይህ ደግሞ “ብዙ ሥቃይ” ያስከትልባቸዋል። (1 ጢሞ. 6:9, 10፤ መክ. 5:10) ሁላችንም ገንዘብ እንደሚያስፈልገን የታወቀ ነው። ገንዘብ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ጥበቃ ያስገኛል። (መክ. 7:12) ይሁን እንጂ ለመሠረታዊ ፍላጎቶቹ ብቻ የሚበቃ ገንዘብ ያለው ሰው እውነተኛ ደስታ ማግኘት ይችላል? አዎ ይችላል! (መክ. 5:12) የያቄ ልጅ አጉር “ድሃም ሆነ ባለጸጋ አታድርገኝ። ብቻ የሚያስፈልገኝን ቀለብ አታሳጣኝ” ሲል ጽፏል። አጉር በድህነት መቆራመድ ያልፈለገበትን ምክንያት መረዳት አይከብደንም። ቀጥሎ እንደተናገረው ድህነት ወደ ስርቆት ሊመራው ይችላል፤ ይህ ደግሞ የአምላክን ስም ያሰድባል። አጉር “ባለጸጋ አታድርገኝ” በማለት የጸለየውስ ለምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “አለዚያ እጠግብና እክድሃለሁ፤ ከዚያም ‘ይሖዋ ማን ነው?’ እላለሁ።” (ምሳሌ 30:8, 9) ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።”—ማቴ. 6:24፤ w18.01 24 አን. 9-11
ሐሙስ፣ ሰኔ 6
እናንተም እያንዳንዳችሁ ወንድማችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ በሰማይ ያለው አባቴ እንደዚሁ ያደርግባችኋል።—ማቴ. 18:35
ሌሎችን በነፃ ይቅር ስንል፣ አንድነታችን እንዲጠናከር አስተዋጽኦ እናደርጋለን። የበደሉንን ሰዎች ይቅር ስንል የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላስገኘልን የኃጢአት ይቅርታ አድናቆት እንዳለን እናሳያለን። በማቴዎስ 18:23-34 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ የተናገረውን ምሳሌ ካነበብን በኋላ ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን እንጠይቅ፦ ‘ኢየሱስ ያስተማረውን ነገር ተግባራዊ አደርጋለሁ? የእምነት ባልንጀሮቼን እታገሣቸዋለሁ? ስሜታቸውንስ እረዳላቸዋለሁ? የበደሉኝን ሰዎች ይቅር ለማለት ዝግጁ ነኝ?’ እርግጥ ነው፣ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ቅር የሚያሰኙንን ነገሮች በሙሉ በእኩል ደረጃ እንመለከታቸዋለን ማለት አይደለም፤ ፍጹማን ባለመሆናችን አንዳንዶቹን በደሎች ይቅር ማለት በጣም ይከብደን ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ፣ ይሖዋ ምን እንደሚጠብቅብን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ወንድሞቻችን ላደረሱብን በደል ከልባቸው እንደተጸጸቱ እያወቅን ይቅር የማንላቸው ከሆነ ይሖዋም ኃጢአታችንን ይቅር እንደማይለን ኢየሱስ በግልጽ ተናግሯል። ይህ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ኢየሱስ እንዳስተማረን ሌሎችን ይቅር የምንል ከሆነ አንድነታችንን ጠብቀን ማቆየትና ይበልጥ ማጠናከር እንችላለን። w18.01 15 አን. 12
ዓርብ፣ ሰኔ 7
ንጉሥ ሆይ፣ ለ30 ቀናት ያህል ለአንተ ካልሆነ በስተቀር ለአምላክም ሆነ ለሰው ልመና የሚያቀርብ ማንኛውም ግለሰብ ወደ አንበሶች ጉድጓድ [ይወርወር]።—ዳን. 6:7
ዳንኤል ሕይወቱን አደጋ ላይ መጣል የሚጠይቅበት ቢሆንም ለአምላክ በሚያቀርበው አምልኮ ረገድ አቋሙን እንዳላላ የሚያስመስል ነገርም እንኳ ላለማድረግ ወስኗል። ይሖዋ ዳንኤልን ከተፈረደበት አሰቃቂ ሞት ተአምራዊ በሆነ መንገድ በማዳን ዳንኤል የወሰደውን በሚገባ የታሰበበትና ድፍረት የተሞላበት እርምጃ እንደባረከው አሳይቷል። በዚህ የተነሳ በሜዶ ፋርስ ግዛት ውስጥ ባሉ ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች ሳይቀር ስለ ይሖዋ አስደናቂ ምሥክርነት ሊሰጥ ችሏል! (ዳን. 6:25-27) እንደ ዳንኤል በአምላክ ላይ እምነት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ጠንካራ እምነት ለማዳበር የአምላክን ቃል ማንበብ ብቻውን በቂ አይደለም፤ የምናነበውን ነገር ‘ማስተዋልም’ ያስፈልጋል። (ማቴ. 13:23) በተጨማሪም የይሖዋን አስተሳሰብ መረዳት እንፈልጋለን፤ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መገንዘብን ይጠይቃል። በመሆኑም በምናነበው ነገር ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። በተጨማሪም አዘውትረን ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ያስፈልገናል፤ በተለይ ደግሞ መከራ ወይም ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን እንዲህ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። አምላክ ጥበብና ብርታት እንዲሰጠን በእምነት የምንጠይቀው ከሆነ በልግስና እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ያዕ. 1:5፤ w18.02 10-11 አን. 13-15
ቅዳሜ፣ ሰኔ 8
ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም።—መዝ. 34:8
የተጠመቅክ ወጣት የአምላክ አገልጋይ ከሆንክ የምታምንባቸውን ነገሮች ለሌሎች ስትናገር ይሖዋ እንዴት እንደሚደግፍህ በመመልከት የይሖዋን ጥሩነት መቅመስ ትችላለህ። በአገልግሎት ስትካፈል አሊያም በትምህርት ቤትህ ስትመሠክር የይሖዋን እጅ ማየት ትችላለህ። አንዳንዶች በትምህርት ቤት ለእኩዮቻቸው መስበክ ተፈታታኝ ይሆንባቸዋል። ለምን እንዲህ እንደሚሰማቸው አንተም መረዳት አይከብድህ ይሆናል። አብረውህ የሚማሩት ልጆች ምሥራቹን ስትነግራቸው ምን ዓይነት ምላሽ እንደሚሰጡህ አስቀድመህ ማወቅ አትችልም። ብዙ ተማሪዎች ሰብሰብ ባሉበት መናገር ደግሞ ለአንድ የክፍል ጓደኛህ ከመስበክ ይበልጥ ከባድ ሊሆንብህ ይችላል። ታዲያ ድፍረት ለማግኘት ምን ይረዳሃል? በቅድሚያ፣ የምታምንባቸው ነገሮች ትክክል ስለመሆናቸው እርግጠኛ የሆንከው ለምን እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። በjw.org/am ላይ የሚገኙትን የማጥኛ ጽሑፎች በሚገባ ተጠቀምባቸው። እነዚህ የማጥኛ ጽሑፎች ስለምታምንባቸው ነገሮች፣ ለምን እንዳመንክባቸው እንዲሁም እነዚህን ነገሮች ለሌሎች ማስረዳት የምትችልበትን መንገድ ቆም ብለህ እንድታስብ ለመርዳት ተብለው የተዘጋጁ ናቸው። የምታምንባቸው ነገሮች ትክክል መሆናቸውን ማረጋገጥህና ጥሩ ዝግጅት ማድረግህ ስለ ይሖዋ ስም ለመመሥከር ይገፋፋሃል።—ኤር. 20:8, 9፤ w17.12 26 አን. 12, 14-15
እሁድ፣ ሰኔ 9
በተማርካቸውና አምነህ በተቀበልካቸው ነገሮች ጸንተህ ኑር።—2 ጢሞ. 3:14
ለልጆች መንፈሳዊ ነገሮችን ማስተማር ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱ ግለሰቦችና ክንውኖች እንዲያውቁ ከመርዳት ያለፈ ነገር ማድረግን ይጨምራል። ጢሞቴዎስ የተማራቸውን ነገሮች ‘አምኖ መቀበል’ እንዳስፈለገው እናስታውስ። ‘አምኖ መቀበል’ የሚለው ሐረግ በግሪክኛ “አንድ ነገር እውነት መሆኑን ተረድቶ ማመንና እርግጠኛ መሆን” የሚል ትርጉም አለው። ጢሞቴዎስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ከጨቅላነቱ ጀምሮ ያውቅ ነበር። መሲሑ፣ ኢየሱስ መሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ሲያገኝ ደግሞ ይህን አምኖ ተቀበለ። እናንተስ ልጆቻችሁ የተማሩትን ነገር ልክ እንደ ጢሞቴዎስ አምነው እንዲቀበሉ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ታጋሽ መሆን ያስፈልጋችኋል። አንድን ነገር ተረድቶ ለማመን ጊዜ ይወስዳል፤ በሌላ በኩል ደግሞ እናንተ አንድን ነገር አምናችሁ ስለተቀበላችሁት ብቻ ልጆቻችሁም ያምኑበታል ማለት አይደለም። እያንዳንዱ ልጅ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አምኖ ለመቀበል ‘የማሰብ ችሎታውን’ መጠቀም አለበት። (ሮም 12:1) ልጆች ይህን እንዲያደርጉ በመርዳት ረገድ ወላጆች ቁልፍ ሚና ይኖራችኋል፤ በተለይ ደግሞ ጥያቄዎች በሚጠይቋችሁ ወቅት ይህን ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ታገኛላችሁ። w17.12 19 አን. 3, 5-6
ሰኞ፣ ሰኔ 10
በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ።—ዮሐ. 11:24
የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅና ተከታይ የሆነችው ማርታ በሐዘን ተውጣለች። ወንድሟ አልዓዛር በሞት አንቀላፍቷል። በሐዘን የተሰበረ ልቧን ሊጠግንላት የሚችል ነገር ይኖር ይሆን? ኢየሱስ “ወንድምሽ ይነሳል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷታል። (ዮሐ. 11:20-23) ማርታ ወደፊት ትንሣኤ እንደሚኖር እርግጠኛ ነበረች። ኢየሱስ ግን በዚያው ቀን አንድ ተአምር ፈጸመ። ዓይናቸው እያየ አልዓዛርን ከሞት አስነሳው። ኢየሱስም ሆነ አባቱ በዛሬው ጊዜ እንዲህ ያለ ተአምር ይፈጽሙልናል ብለን እንድንጠብቅ የሚያደርግ መሠረት የለንም። ይሁን እንጂ በሞት ያጣሃቸው ሰዎች ወደፊት ትንሣኤ እንደሚኖራቸው አንተም የማርታን ያህል እርግጠኛ ነህ? ምናልባትም የትዳር ጓደኛህን፣ እናትህን፣ አባትህን አሊያም አያትህን በሞት አጥተህ ይሆናል። ወይም ደግሞ ሞት ልጅህን ነጥቆህ ሊሆን ይችላል። የሞተብህን ሰው እቅፍ ለማድረግ እንዲሁም ከእሱ ጋር ለመጫወትና ለመሳቅ ትናፍቅ ይሆናል። ደስ የሚለው ነገር፣ ‘በሞት ያጣሁት ሰው በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ’ በማለት አንተም እንደ ማርታ አፍህን ሞልተህ መናገር ትችላለህ። ያም ቢሆን እያንዳንዱ ክርስቲያን እንዲህ ብሎ በልበ ሙሉነት መናገር የሚችለው ለምን እንደሆነ ቆም ብሎ ማሰቡ ጠቃሚ ነው። w17.12 3 አን. 1-2
ማክሰኞ፣ ሰኔ 11
አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው።—መዝ. 40:8
ኢየሱስ የሙሴን ሕግ ይወደው ነበር። ይህም የሚያስገርም አይደለም! ይህን ሕግ ያወጣው በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው አካል ማለትም አባቱ ይሖዋ ነው። በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘው ትንቢታዊ ሐሳብ ኢየሱስ ለአምላክ ሕግ የነበረውን ጥልቅ ፍቅር የሚገልጽ ነው። ኢየሱስ የአምላክ ሕግ ፍጹምና ጠቃሚ እንደሆነ ብሎም መፈጸሙ እንደማይቀር በንግግሩና በተግባሩ አሳይቷል። (ማቴ. 5:17-19) ከዚህ አንጻር ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ ሰዎች ስለ ሕጉ የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸው ሲያደርጉ ኢየሱስ ምንኛ አዝኖ ይሆን! ጸሐፍትና ፈሪሳውያን በሕጉ ውስጥ የተካተቱትን አንዳንድ ጥቃቅን ነገሮች ምንም ሳያዛንፉ ይታዘዙ ነበር፤ ክርስቶስ “ከኮሰረት፣ ከእንስላልና ከከሙን አሥራት” እንደሚሰጡ ተናግሯል። ታዲያ ችግሩ ምን ነበር? ኢየሱስ አክሎ “በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን እንደ ፍትሕ፣ ምሕረትና ታማኝነት ያሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ችላ ትላላችሁ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 23:23) ከእነዚህ ተመጻዳቂ ሰዎች በተለየ ክርስቶስ፣ ሕጉ የወጣበትን ዓላማ እንዲሁም በእያንዳንዱ ትእዛዝ ላይ የተንጸባረቁትን የይሖዋ ባሕርያት ተገንዝቦ ነበር። w17.11 13 አን. 1-2
ረቡዕ፣ ሰኔ 12
የአምላክ ፈቃድ እንድትቀደሱና ከፆታ ብልግና እንድትርቁ ነው።—1 ተሰ. 4:3
አንዳንድ ሰዎች “በሕይወታችን መደሰት አለብን። ከጋብቻ ውጭ የፆታ ግንኙነት መፈጸም የሚወገዘው ለምንድን ነው?” ይሉን ይሆናል። ይሁንና “ክርስቲያኖች የፆታ ብልግናን ማውገዝ የለባቸውም” የሚለው አመለካከት ስህተት ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የአምላክ ቃል የፆታ ብልግናን ያወግዛል። (1 ተሰ. 4:4-8) ይሖዋ ፈጣሪያችን ስለሆነ የምንመራባቸውን ሕጎች የማውጣት ሥልጣን አለው። ጋብቻን ያቋቋመው አምላክ ሲሆን የፆታ ግንኙነት እንዲፈጸም የፈቀደው በባልና ሚስት መካከል ብቻ ነው። አምላክ ሕጎችን ያስቀመጠልን ስለሚወደን ነው። እነዚህን ሕጎች መታዘዛችን ይጠቅመናል። ቤተሰቦች የአምላክን ሕጎች የሚታዘዙ ከሆነ በመካከላቸው ፍቅርና መከባበር ይኖራል፤ እንዲሁም ያለስጋት መኖር ይችላሉ። አምላክ፣ ሕጎቹን ሆን ብለው የሚጥሱ ሰዎችን በቸልታ አይመለከትም። (ዕብ. 13:4) የአምላክ ቃል ከፆታ ብልግና መራቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል። ከፆታ ብልግና መራቅ የምንችልበት አንዱ መንገድ በምንመለከታቸው ነገሮች ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ ነው። (ማቴ. 5:28, 29) በመሆኑም አንድ ክርስቲያን የብልግና ምስሎችን ከመመልከት ወይም የፆታ ብልግናን የሚያበረታቱ ሙዚቃዎችን ከማዳመጥ መቆጠብ ይኖርበታል።—ኤፌ. 5:3-5፤ w17.11 22 አን. 9-10
ሐሙስ፣ ሰኔ 13
ለአምላካችን የውዳሴ መዝሙር መዘመር ጥሩ ነው።—መዝ. 147:1
ከጥንት ጊዜ አንስቶ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ይሖዋን በሙዚቃ ያወድሱ ነበር። የጥንቶቹ እስራኤላውያን ይሖዋን በታማኝነት ያገለግሉ በነበረበት ዘመን፣ መዝሙር በአምልኳቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ ይሰጠው የነበረ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ ዳዊት በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለሚካሄደው አገልግሎት ዝግጅት ሲያደርግ በመዝሙር ለይሖዋ ውዳሴ የሚያቀርቡ 4,000 ሌዋውያንን አደራጅቶ ነበር። ከእነዚህም መካከል “ለይሖዋ በሚቀርበው መዝሙር የሠለጠኑ . . . ይኸውም በዚህ የተካኑ” 288 ሌዋውያን ነበሩ። (1 ዜና 23:5፤ 25:7) በቤተ መቅደሱ ምረቃ ወቅት፣ ሙዚቃ ትልቅ ሚና ነበረው። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “መለከት ነፊዎቹና ዘማሪዎቹ በኅብረት ይሖዋን ባወደሱና ባመሰገኑ ጊዜ እንዲሁም . . . ይሖዋን በማወደስ የመለከቱን፣ የሲምባሉንና የሌሎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች ድምፅ ባሰሙ ጊዜ . . . የይሖዋ ክብር የእውነተኛውን አምላክ ቤት [ሞላው]።” ይህ ምንኛ እምነትን የሚያጠናክር እንደሆነ መገመት ይቻላል!—2 ዜና 5:13, 14፤ 7:6፤ w17.11 4 አን. 4-5
ዓርብ፣ ሰኔ 14
በምድር ላይ ሰላም ለማስፈን የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ የመጣሁት ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አይደለም።—ማቴ. 10:34
ኢየሱስ እሱ የሚያስተምረው ትምህርት በሰዎች መካከል ክፍፍል እንደሚፈጥር እንዲሁም ተከታዮቹ የሚያጋጥማቸውን ተቃውሞ ተቋቁመው እሱን መከተላቸውን ለመቀጠል ድፍረት እንደሚያስፈልጋቸው ያውቅ ነበር። የኢየሱስ ዓላማ የአምላክን የእውነት መልእክት ማወጅ እንጂ በሰዎች መካከል ቅራኔ መፍጠር አልነበረም። (ዮሐ. 18:37) ያም ቢሆን የአንድ ሰው የቅርብ ወዳጆች ወይም ቤተሰቦች እውነትን ለመቀበል ፈቃደኞች ካልሆኑ ይህ ሰው የክርስቶስን ትምህርቶች በታማኝነት መከተል ከባድ ሊሆንበት ይችላል። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የእሱ ተከታዮች ለመሆን ሲሉ ከቤተሰቦቻቸው የሚሰነዘርባቸውን ፌዝ ተቋቁመው መጽናት አስፈልጓቸዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ በቤተሰቦቻቸው እስከመገለል ደርሰዋል። ያም ቢሆን ያገኙት በረከት የክርስቶስ ተከታዮች በመሆናቸው ካጡት ነገር በእጅጉ የላቀ ነው። (ማር. 10:29, 30) ቤተሰቦቻችን ይሖዋን ለማምለክ የምናደርገውን ጥረት ቢቃወሙም ይህ ለእነሱ ያለንን ፍቅር አይቀንሰውም፤ ይሁንና ለአምላክና ለክርስቶስ ያለን ፍቅር ለማንኛውም ሰው ካለን ፍቅር ሊበልጥ እንደሚገባ መዘንጋት አይኖርብንም። (ማቴ. 10:37) በተጨማሪም ሰይጣን ለቤተሰባችን ያለንን ፍቅር ተጠቅሞ ንጹሕ አቋማችንን እንድናላላ ለማድረግ እንደሚሞክር ልንገነዘብ ይገባል። w17.10 13 አን. 3-6
ቅዳሜ፣ ሰኔ 15
[ክፋትን] የኢፍ መስፈሪያዋ ውስጥ መልሶ ጣላት፤ ቀጥሎም ከእርሳስ የተሠራውን ከባዱን መክደኛ መስፈሪያዋ አፍ ላይ ገጠመው።—ዘካ. 5:8
ይህ ራእይ እንደሚያሳየው ይሖዋ በሕዝቡ መካከል የሚፈጸምን ማንኛውንም ክፋት በቸልታ አያልፍም። ከዚህ ይልቅ በቁጥጥር ሥር እንዲውልና በፍጥነት እንዲወገድ ያደርጋል። (1 ቆሮ. 5:13) መልአኩ ከእርሳስ የተሠራውን መክደኛ በመስፈሪያው አፍ ላይ መግጠሙ ይህን ያረጋግጥልናል። ይሖዋ ንጹሑን አምልኮ ከክፋት እንደሚጠብቅ ዋስትና የሚሰጠው ይህ ራእይ በዘካርያስ ዘመን ለነበሩት እስራኤላውያን በእርግጥም ትልቅ እፎይታ አምጥቶላቸው መሆን አለበት! በተጨማሪም ይህ ራእይ አይሁዳውያኑ፣ የሚያቀርቡት አምልኮ ከክፋት የጸዳ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝቧቸዋል። ክፋት በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ሰርጎ እንዲገባና በመካከላቸው እንዲኖር እንደማይፈቀድለት ደግሞም ሊፈቀድለት እንደማይገባ ግልጽ ነው። ጥበቃና ፍቅራዊ እንክብካቤ በምናገኝበት እንዲሁም ንጹሕ በሆነው የአምላክ ድርጅት ውስጥ የታቀፍን እንደመሆናችን መጠን ይህ ንጽሕና ተጠብቆ እንዲቀጥል የማድረግ ኃላፊነት አለብን። ታዲያ የይሖዋ ድርጅት ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆን የማድረግ ተነሳሽነት አለን? በመንፈሳዊ ገነታችን ውስጥ ማንኛውም ዓይነት ክፋት ቦታ የለውም። w17.10 24 አን. 14-15፤ 25 አን. 17-18
እሁድ፣ ሰኔ 16
ሕግህን . . . እወዳለሁ።—መዝ. 119:163
የመጀመሪያዎቹን 39 የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የጻፉት፣ እስራኤላውያን ወይም አይሁዳውያን ናቸው። “የአምላክ ቅዱስ ቃል” መጀመሪያ ላይ “በአደራ” የተሰጠው ለእነሱ ነበር። (ሮም 3:1, 2) ሆኖም በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በርካታ አይሁዳውያን ዕብራይስጥ አይችሉም ነበር። ለምን? ታላቁ እስክንድር በርካታ አካባቢዎችን በቁጥጥሩ ሥር በማዋል የግሪክ ግዛት እንዲስፋፋ አድርጎ ነበር። (ዳን. 8:5-7, 20, 21) ግዛቱ እየተስፋፋ ሲሄድ በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው ይኖሩ የነበሩትን አይሁዳውያን ጨምሮ አብዛኞቹ ተገዢዎች የሚግባቡበት የጋራ ቋንቋ ግሪክኛ ሆነ። በመሆኑም በርካታ አይሁዳውያን የሚናገሩት ግሪክኛ ነበር፤ ይህም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን መረዳት አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው አድርጓል። ታዲያ መፍትሔው ምን ይሆን? የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክኛ የመተርጎሙ ሥራ በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ተጠናቀቀ። የእነዚህ ቅዱሳን መጻሕፍት ስብስብ የግሪክ ሰብዓ ሊቃናት ተብሎ መጠራት ጀመረ። እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ሙሉውን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የያዘ የመጀመሪያው የትርጉም ሥራ ነው። w17.09 20 አን. 7-9
ሰኞ፣ ሰኔ 17
ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም።—ዕብ. 13:5
አሠሪህ ማታ ማታ እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ትርፍ ሰዓት እንድትሠራ በተደጋጋሚ ይጠይቅህ ይሆናል፤ እነዚህ ጊዜያት ደግሞ የቤተሰብ አምልኮ የምታደርግባቸው፣ በመስክ አገልግሎት የምትካፈልባቸውና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የምትገኝባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። አሠሪህ በተደጋጋሚ የሚያቀርብልህን እንዲህ ያለ ጥያቄ ላለመቀበልና በዚህ ረገድ ለልጆችህ ጥሩ ምሳሌ ሆነህ ለመገኘት ደፋር መሆን ያስፈልግሃል። ወላጆች፣ ልጆቻቸው መንፈሳዊ ግቦች እንዲያወጡና ግቦቻቸው ላይ እንዲደርሱ ለመርዳትም ደፋር መሆን ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን አቅኚ እንዲሆኑ፣ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው እንዲያገለግሉ፣ ቤቴል እንዲገቡ ወይም በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዲካፈሉ ከማበረታታት ወደኋላ ሊሉ ይችላሉ። እነዚህ ወላጆች እንዲህ ከማድረግ ወደኋላ የሚሉት፣ ሲያረጁ የሚጦራቸው እንደሚያጡ ስለሚሰማቸው አሊያም ልጆቻቸው ወደፊት ራሳቸውን መደገፍ ይከብዳቸዋል የሚል ስጋት ስለሚያድርባቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ደፋሮች በመሆን ይሖዋ በገባው ቃል ላይ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ያሳያሉ። (መዝ. 37:25) ወላጆች በዚህ መንገድ በይሖዋ የሚታመኑና ደፋሮች እንደሆኑ የሚያሳዩ ከሆነ ልጆቻቸውም በይሖዋ ላይ ተመሳሳይ እምነት ለመጣል ይነሳሳሉ።—1 ሳሙ. 1:27, 28፤ 2 ጢሞ. 3:14, 15፤ w17.09 30 አን. 14-15
ማክሰኞ፣ ሰኔ 18
የመንፈስ ፍሬ . . . ራስን መግዛት ነው።—ገላ. 5:22, 23
እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ራስን የመግዛት ባሕርይን እንዲያዳብሩ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው? ልጆች እንዲሁ በተፈጥሯቸው ራሳቸውን የሚገዙ እንደማይሆኑ መገንዘብ ይኖርባችኋል። በተጨማሪም ልክ እንደ ሌሎች ባሕርያት ሁሉ ልጆቻችሁ ራስን የመግዛት ባሕርይን እንዲያዳብሩ ከፈለጋችሁ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይጠበቅባችኋል። (ኤፌ. 6:4) በመሆኑም ልጆቻችሁ ስሜታቸውን መቆጣጠር እንደሚከብዳቸው ካስተዋላችሁ ‘በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ሆኛቸዋለሁ?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። በመስክ አገልግሎትና በጉባኤ ስብሰባዎች አዘውትራችሁ መካፈላችሁ እንዲሁም ቋሚ የቤተሰብ አምልኮ ማድረጋችሁ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አቅልላችሁ አትመልከቱ። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ልጆቻችሁ ለሚያቀርቡት ጥያቄ ‘አይሆንም’ ብላችሁ ከመመለስ ወደኋላ አትበሉ! ይሖዋ በአዳምና በሔዋን ላይ ገደብ አድርጎባቸው ነበር፤ ይህ ገደብ፣ ለእሱ ሥልጣን ተገቢ አክብሮት እንዲኖራቸው የሚረዳ ነበር። በተመሳሳይም ወላጆች ልጆቻቸውን መገሠጻቸውና ለእነሱ ጥሩ ምሳሌ መሆናቸው ልጆቻቸው ራሳቸውን መቆጣጠር እንዲችሉ ያሠለጥናቸዋል። ልጆቻችሁ ለይሖዋ ሥልጣን ፍቅር እንዲኖራቸውና እሱ ላወጣቸው መሥፈርቶች አክብሮት እንዲያዳብሩ ለመርዳት ጥረት አድርጉ፤ እነዚህ እሴቶች በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ ልትቀርጹ ከምትችሏቸው እጅግ ውድ የሆኑ ነገሮች መካከል ይገኙበታል።—ምሳሌ 1:5, 7, 8፤ w17.09 7 አን. 17
ረቡዕ፣ ሰኔ 19
በአካል መካከል ክፍፍል [አይኑር]፣ ከዚህ ይልቅ የአካል ክፍሎች በእኩል ደረጃ አንዳቸው ለሌላው አሳቢነት [ያሳዩ]።—1 ቆሮ. 12:25
የሰይጣን ዓለም እስካለ ድረስ ሁላችንም መከራ ይደርስብናል። ሥራ ልናጣ፣ በጠና ልንታመም፣ ስደት ሊደርስብን፣ የተፈጥሮ አደጋ ሊያጋጥመን፣ በወንጀል ምክንያት ንብረታችንን ልናጣ አሊያም ሌሎች ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። መከራ ወይም ችግር ሲያጋጥመን እርስ በርሳችን ለመረዳዳት፣ አንዳችን ለሌላው ከልብ የመነጨ ርኅራኄ ሊኖረን ይገባል። ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ካለን ለሌሎች ደግነት ለማሳየት እንነሳሳለን። (ኤፌ. 4:32) እነዚህ የአዲሱ ስብዕና ገጽታዎች አምላክን በመምሰል ሌሎችን ማጽናናት እንድንችል ይረዱናል። (2 ቆሮ. 1:3, 4) ከሌላ አገር ለመጡ አሊያም በሌሎች ዘንድ ዝቅ ተደርገው ለሚታዩ ሰዎች ለየት ያለ አሳቢነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? እነዚህን ሰዎች ልንቀርባቸው እንዲሁም በጉባኤው ውስጥ ተፈላጊ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ልንረዳቸው ይገባል። (1 ቆሮ. 12:22) በተጨማሪም በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ለስደተኞች ባላቸው ርኅራኄ ተነሳስተው አዲስ ቋንቋ ለመማር ጥረት እያደረጉ ነው። (1 ቆሮ. 9:23) ይህም የተትረፈረፈ በረከት አስገኝቷል። w17.08 23-24 አን. 7-9
ሐሙስ፣ ሰኔ 20
ይሖዋ ድርሻዬ ነው . . . እሱን በትዕግሥት የምጠባበቀው ለዚህ ነው።—ሰቆ. 3:24
ይሖዋ ታጋሾች እንድንሆን ወይም በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኞች እንድንሆን ይፈልጋል። ይሁንና በዚህ ረገድ ምን ሊረዳን ይችላል? የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት መጸለይ ይኖርብናል። ትዕግሥት የመንፈስ ፍሬ ገጽታ እንደሆነ እናስታውስ። (ኤፌ. 3:16፤ 6:18፤ 1 ተሰ. 5:17-19) በመሆኑም በትዕግሥት ለመጽናት እንዲረዳን ይሖዋን አጥብቀን እንለምን። በተጨማሪም አብርሃም፣ ዮሴፍና ዳዊት ይሖዋ የገባላቸውን ቃል ፍጻሜ በትዕግሥት እንዲጠብቁ የረዳቸው ምን እንደሆነ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። እነሱን የረዳቸው በይሖዋና እሱ ነገሮችን በሚይዝበት መንገድ ላይ የነበራቸው ጠንካራ እምነት ነው። በራሳቸውም ሆነ በግል ምቾታቸው ላይ አላተኮሩም። እነዚህ ሰዎች በመጨረሻ ምን በረከት እንዳገኙ ማሰላሰላችን በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ እንድናሳይ ያበረታታናል። እንግዲያው የተለያየ ፈተናና መከራ ቢደርስብንም “በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ” ለማሳየት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እርግጥ ነው፣ “ይሖዋ ሆይ፣ እስከ መቼ ነው?” የምንልበት ጊዜ ይኖር ይሆናል። (ኢሳ. 6:11) ይሁንና የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በሚሰጠን ብርታት በመታገዝ ልክ እንደ ኤርምያስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ መናገር እንችላለን። w17.08 7 አን. 18-20
ዓርብ፣ ሰኔ 21
አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል።—መዝ. 40:8
ኢየሱስ ልጅ እያለ ይጫወትና ጥሩ ጊዜ ያሳልፍ እንደነበር ጥያቄ የለውም። የአምላክ ቃል “ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ . . . ለጭፈራም ጊዜ አለው” ይላል። (መክ. 3:4) ኢየሱስ፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጥናት ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ይጥር ነበር። የ12 ዓመት ልጅ በነበረበት ወቅት፣ የቤተ መቅደሱ መምህራን ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ባለው ‘የመረዳት ችሎታና በመልሱ ተደንቀው’ ነበር። (ሉቃስ 2:42, 46, 47) ኢየሱስ አዋቂ ከሆነ በኋላም ደስተኛ ነበር። ደስተኛ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደረገው ምንድን ነው? አምላክ የሰጠው ተልዕኮ ‘ለድሆች ምሥራች መናገርን እንዲሁም ለታወሩት ማየትን ማወጅን’ እንደሚጨምር ያውቅ ነበር። (ሉቃስ 4:18) ኢየሱስ፣ አምላክ የሰጠውን ተልዕኮ መወጣቱ ደስተኛ እንዲሆን አድርጎታል። ኢየሱስ በሰማይ ስላለው አባቱ ለሰዎች ማስተማር ያስደስተው ነበር። (ሉቃስ 10:21) በአንድ ወቅት ስለ እውነተኛው አምልኮ ለአንዲት ሴት ሲያስተምር ከቆየ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና እንዳከናውነው የሰጠኝን ሥራ መፈጸም ነው” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 4:31-34) ኢየሱስ ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር ማሳየቱ ደስተኛ እንዲሆን አድርጎታል። አንተም እንዲህ ካደረግህ ደስተኛ ትሆናለህ። w17.07 23 አን. 4-5
ቅዳሜ፣ ሰኔ 22
የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።—ፊልጵ. 4:7
የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት፣ እንደ ርኅራኄና የሌሎችን ስሜት መረዳት ያሉትን የይሖዋን ባሕርያት በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ ፍጹም በሆነ መልኩ አንጸባርቋል። (ዮሐ. 5:19) ኢየሱስ ወደ ምድር የተላከው “ልባቸው የተሰበረውን” እና “የሚያለቅሱትንም ሁሉ” እንዲያጽናና ነው። (ኢሳ. 61:1, 2፤ ሉቃስ 4:17-21) በመሆኑም ጥልቅ የሆነ የርኅራኄ ስሜት ያሳይ ነበር፤ የሌሎችን ሥቃይ የሚረዳ ከመሆኑም ሌላ ሥቃያቸውን ለማስታገስ ከልቡ ይፈልግ ነበር። (ዕብ. 2:17) ቅዱሳን መጻሕፍት “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትም፣ ዛሬም፣ ለዘላለምም ያው ነው” የሚል ማረጋገጫ ይሰጡናል። (ዕብ. 13:8) ‘የሕይወት ዋና ወኪል’ የሆነው ኢየሱስ፣ ሐዘን ምን ስሜት እንደሚፈጥር ከራሱ ተሞክሮ ስለሚያውቅ “በፈተና ላይ ላሉት ሊደርስላቸው ይችላል።” (ሥራ 3:15፤ ዕብ. 2:10, 18) ክርስቶስ የሌሎች ሐዘን በጥልቅ ይሰማዋል፤ ስሜታቸውን ይረዳላቸዋል እንዲሁም ‘በሚያስፈልጋቸው ጊዜ’ ያጽናናቸዋል።—ዕብ. 4:15, 16፤ w17.07 13 አን. 6-7፤ 14 አን. 10
እሁድ፣ ሰኔ 23
ሀብታችሁ ባለበት ልባችሁም በዚያ ይሆናል።—ሉቃስ 12:34
ሰይጣንም ሆነ በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም ይሖዋ ለሰጠን መንፈሳዊ ሀብቶች ያለን አድናቆት እንዲቀንስ ወይም እንዲጠፋ ለማድረግ ያለማሰለስ ጥረት ያደርጋሉ። እኛም ካልተጠነቀቅን በዚህ ተጽዕኖ ልንሸነፍ እንችላለን። ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ፣ የተንደላቀቀ ሕይወት የመኖር ሕልም ወይም ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ ወጥመድ ሊሆንብን ይችላል። ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ይህ ዓለምም ሆነ ምኞቱ እንደሚያልፉ ተናግሯል። (1 ዮሐ. 2:15-17) በመሆኑም ላገኘናቸው መንፈሳዊ ሀብቶች ምንጊዜም አመስጋኝ መሆን እንዲሁም እነዚህን ሀብቶች መጠበቅ ይኖርብናል። ለአምላክ መንግሥት ያላችሁ ፍቅር እንዲቀንስ ሊያደርግ የሚችልን ማንኛውንም ነገር ለማስወገድ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። በቅንዓት መስበካችሁን ቀጥሉ፤ ሕይወት አድን ለሆነው አገልግሎታችን ያላችሁ ፍቅር እንዲቀዘቅዝ አትፍቀዱ። መለኮታዊ እውነቶችን በትጋት መፈለጋችሁን ቀጥሉ። እንዲህ ካደረጋችሁ “ሌባ በማይደርስበት፣ ብልም ሊበላው በማይችልበት በሰማያት ለራሳችሁ የማያልቅ ውድ ሀብት [ታከማቻላችሁ]።”—ሉቃስ 12:33, 34፤ w17.06 13 አን. 19-20
ሰኞ፣ ሰኔ 24
በሌላ ቦታ አንድ ሺህ ቀን ከመኖር በቅጥር ግቢዎችህ አንዲት ቀን መዋል ይሻላል።—መዝ. 84:10
የይሖዋ አገዛዝ ጭቆና ያለበት ወይም የማያፈናፍን አይደለም። አገዛዙ ለሰዎች ነፃነት የሚሰጥና ደስታ የሚያስገኝ ነው። (2 ቆሮ. 3:17) ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “ሞገስና ግርማ [በአምላክ ፊት] ናቸው፤ ብርታትና ደስታ እሱ በሚኖርበት ስፍራ ይገኛሉ።” (1 ዜና 16:7, 27) በተመሳሳይም መዝሙራዊው ኤታን እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እልልታ የሚያውቁ ሰዎች ደስተኞች ናቸው። ይሖዋ ሆይ፣ እንዲህ ያሉ ሰዎች በፊትህ ብርሃን ይመላለሳሉ። በስምህ ቀኑን ሙሉ ሐሴት ያደርጋሉ፤ በጽድቅህም ከፍ ከፍ ይላሉ።” (መዝ. 89:15, 16) በይሖዋ ጥሩነት ላይ አዘውትረን ማሰላሰላችን የእሱ አገዛዝ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን እውነተኛ ደስታ የሚያስገኝልን ነገር ምን እንደሆነ ያውቃል፤ ይህንንም አትረፍርፎ ይሰጠናል። ይሖዋ ያወጣቸው መሥፈርቶች በሙሉ እኛን የሚጠቅሙ ናቸው። ይሖዋ የሚጠብቅብንን ነገር ማድረግ አንዳንድ መሥዋዕትነት መክፈል ቢጠይቅብንም እንኳ እሱን መታዘዛችን ደስታ ያስገኝልናል።—ኢሳ. 48:17፤ w17.06 29 አን. 10-11
ማክሰኞ፣ ሰኔ 25
የዘገየ ተስፋ ልብን ያሳምማል።—ምሳሌ 13:12
በእንግሊዝ አገር የምትኖር አንዲት እህት ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት፤ ልጅ መውለድ በጣም ትፈልግ የነበረ ቢሆንም እንኳ ምኞቷ እውን ሊሆንላት አልቻለም። ይህ ፍላጎቷ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሊሳካ እንደማይችል ስታውቅ በጣም አዝና እንደነበር ተናግራለች። በኋላም እሷና ባለቤቷ የማደጎ ልጅ ለማሳደግ ወሰኑ። ይሁንና እንዲህ ብላለች፦ “ያኔም ቢሆን ሙሉ በሙሉ አልተጽናናሁም። የማደጎ ልጅ ማሳደግ የራሴን ልጅ እንደ መውለድ ሊሆንልኝ እንደማይችል ታውቆኝ ነበር።” መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ክርስቲያን ሴቶች ሲናገር “ልጅ በመውለድ ደህንነቷ ተጠብቆ ትኖራለች” ይላል። (1 ጢሞ. 2:15) ይህ ማለት ግን ልጆች መውለድ ወይም ማሳደግ የዘላለም ሕይወት ያስገኛል ማለት አይደለም። ታዲያ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነው? አንዲት ሴት ልጆች በማሳደግና በሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎች መጠመዷ ከሐሜትና በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንድትቆጠብ ሊያደርጋት እንደሚችል መግለጹ ነው።—1 ጢሞ. 5:13፤ w17.06 5-6 አን. 6-8
ረቡዕ፣ ሰኔ 26
[ለአምላክ] ምን ትጨምርለታለህ? ከአንተ እጅ ምን ይቀበላል?—ኢዮብ 35:7
ኤሊሁ፣ አምላክን ለማገልገል የምናደርገው ጥረት ዋጋ የለውም ማለቱ ነበር? በፍጹም። ኤሊሁ፣ ይሖዋ እኛ ባናመልከውም ምንም የሚጎድልበት ነገር እንደሌለ መግለጹ ነው። ይሖዋ በራሱ ምሉዕ ነው። እኛ የምናደርገው ማንኛውም ነገር ለይሖዋ ብልጽግና ወይም ኃይል ሊጨምርለት አይችልም። እንዲያውም ያለንን ማንኛውም መልካም ባሕርይ፣ ተሰጥኦ ወይም ችሎታ ያገኘነው ከይሖዋ ነው፤ እሱም ይህን እንዴት እንደምንጠቀምበት በትኩረት ይመለከታል። ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ታማኝ ፍቅር ስናሳይ ይህን ለእሱ እንዳደረግንለት ይቆጥረዋል። ምሳሌ 19:17 “ለችግረኛ ሞገስ የሚያሳይ ለይሖዋ ያበድራል፤ ላደረገውም ነገር ብድራት ይከፍለዋል” ይላል። ይህ ጥቅስ ይሖዋ ለችግረኛ ሰው የሚደረግን ማንኛውንም የደግነት ተግባር እንደሚመለከት የሚያሳይ ነው? የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ ደግነት ለሚያሳዩ ሰዎች ባለዕዳ እንደሆነ ይሰማዋል ማለት ነው? ደግሞስ እንዲህ ያለውን ልግስና የሚያደርጉ ሰዎችን ለእሱ እንዳበደሩት በመቁጠር ሞገሱንና በረከቱን ይሰጣቸዋል ብለን መደምደም እንችላለን? አዎ፣ የአምላክ ልጅ ራሱ ይህንን አረጋግጦልናል።—ሉቃስ 14:13, 14፤ w17.04 29 አን. 3-4
ሐሙስ፣ ሰኔ 27
በይሖዋ ሕግ ደስ ይለዋል፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት በለሆሳስ ያነበዋል።—መዝ. 1:2
የአምላክን ቃል እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ከማንበብ ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው እውነት ጥልቅ ፍቅር ለማዳበር ምን ሊረዳን ይችላል? በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን በመገኘት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው እውነት ያለን ፍቅር እንዲያድግ ማድረግ እንችላለን። በስብሰባዎች ላይ ትምህርት ከምናገኝባቸው መንገዶች ዋነኛው በመጠበቂያ ግንብ አማካኝነት በየሳምንቱ የምናደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነው። የሚጠናውን ርዕሰ ጉዳይ በደንብ መረዳት እንድንችል እያንዳንዱን የመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕስ በሚገባ መዘጋጀት ይኖርብናል። ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ፣ ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን ጥቅሶች በሙሉ አውጥተን ማንበብ ነው። በአሁኑ ወቅት የመጠበቂያ ግንብ መጽሔትን በብዙ ቋንቋዎች ከjw.org ድረ ገጽ ላይ ማውረድ ወይም JW Library በተባለው አፕሊኬሽን አማካኝነት ማግኘት ይቻላል። በእነዚህ ዝግጅቶች አማካኝነት መጽሔቶችን ስናወርድ በእያንዳንዱ የጥናት ርዕስ ላይ የሚገኙትን ጥቅሶች በቀላሉ አውጥተን ማየት እንችላለን። መጽሔቱን የምናገኝበት መንገድ ምንም ይሁን ምን፣ ጥቅሶቹን በሚገባ ማንበባችንና በጥቅሶቹ ላይ ማሰላሰላችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው እውነት ያለንን ፍቅር ያሳድግልናል። w17.05 20 አን. 14
ዓርብ፣ ሰኔ 28
እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንሰጣለን።—ሮም 14:12
ከተጠመቅንበት ጊዜ አንስቶ አምላክን በታማኝነት በማገልገል ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን መኖር ይገባናል። የገባነውን ቃል ማጠፍ የምንችልበት ምንም መንገድ የለም። አንድ ሰው ይሖዋን ማገልገል ወይም በክርስቲያናዊ መንገድ ሕይወቱን መምራት ቢታክተው፣ ራሱን ለአምላክ የወሰነው ከልቡ እንዳልሆነና ጥምቀቱም ሊጸና እንደማይችል በመግለጽ ወደኋላ ማለት አይችልም። ይህ ግለሰብ ሲጠመቅ፣ ራሱን ሙሉ በሙሉ ለአምላክ እንደወሰነ አድርጎ አቅርቧል። በመሆኑም ማንኛውንም ከባድ ኃጢአት ቢፈጽም በይሖዋም ሆነ በጉባኤው ፊት ተጠያቂ ይሆናል። ማናችንም ብንሆን “መጀመሪያ ላይ የነበረህን ፍቅር ትተሃል” መባል አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ “ሥራህን፣ ፍቅርህን፣ እምነትህን፣ አገልግሎትህንና ጽናትህን አውቃለሁ፤ ደግሞም ከመጀመሪያው ሥራህ ይልቅ የአሁኑ እንደሚበልጥ አውቃለሁ” ብሎ ስለ እኛ እንዲናገር እንፈልጋለን። (ራእይ 2:4, 19) ሁላችንም ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን በመኖር ይሖዋን እናስደስት። w17.04 6-7 አን. 12-13
ቅዳሜ፣ ሰኔ 29
እሱ ዓለት፣ የሚያደርገውም ነገር ሁሉ ፍጹም ነው፤ መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸውና።—ዘዳ. 32:4
“የምድር ሁሉ ዳኛ ትክክል የሆነውን ነገር አያደርግም?” (ዘፍ. 18:25) አብርሃም ይህን ጥያቄ ሲያነሳ፣ ይሖዋ ከሰዶምና ከገሞራ ጋር በተያያዘ ፍጹም ፍትሐዊ የሆነ ፍርድ እንደሚያስተላልፍ ያለውን እምነት መግለጹ ነበር። ይሖዋ “ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አንድ ላይ [በመግደል]” ፍትሕ እንደማያዛባ አብርሃም እርግጠኛ ነበር። አብርሃም እንዲህ ያለው ድርጊት “ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር” እንደሆነ ገልጿል። አብርሃም፣ ይሖዋን በተመለከተ እንዲህ ያለ የመተማመን ስሜት ሊኖረው የቻለው ፍትሕንና ጽድቅን በማንጸባረቅ ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ይሖዋ ስለሆነ ነው። “ፍትሕ” እና “ጽድቅ” ተብለው የሚተረጎሙት የዕብራይስጥ ቃላት በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ብዙ ጊዜ አብረው ይጠቀሳሉ። በመሠረቱ፣ ፍትሐዊ በሆነው ነገርና ትክክል ወይም ጽድቅ በሆነው ነገር መካከል ልዩነት የለም። ደግሞም የይሖዋ መሥፈርቶች ምንጊዜም ትክክለኛ ወይም ጽድቅ የሚንጸባረቅባቸው በመሆናቸው አንድን ጉዳይ አስመልክቶ የሚያስተላልፈው ፍርድ ሁልጊዜ ፍትሐዊ ነው። በተጨማሪም ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ይሖዋ “ጽድቅንና ፍትሕን ይወዳል።”—መዝ. 33:5፤ w17.04 18 አን. 1-2
እሁድ፣ ሰኔ 30
ልጆቼ በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የበለጠ ደስታ የለኝም።—3 ዮሐ. 4
ወላጆች፣ እናንተ የምትተዉት ምሳሌ ልጆቻችሁ ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ መጓዝ እንዲጀምሩ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ልጆቻችሁ “ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት” እንደምትፈልጉ ሲመለከቱ በየዕለቱ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማግኘት በይሖዋ መታመንን ይማራሉ። (ማቴ. 6:33, 34) ስለዚህ አኗኗራችሁን ቀላል አድርጉት። ለቁሳዊ ነገሮች ስትሉ መንፈሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት ከማድረግ ይልቅ መንፈሳዊ ነገሮችን አስቀድሙ። ዕዳ ውስጥ ላለመግባት ተጠንቀቁ። ‘በሰማይ ውድ ሀብት’ ይኸውም የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት እንጂ ቁሳዊ ብልጽግናን ወይም “ከሰው የሚገኘውን ክብር” ለማትረፍ አትድከሙ። (ማር. 10:21, 22፤ ዮሐ. 12:43) ለልጆቻችሁ ጊዜ እስክታጡ ድረስ በሌሎች ነገሮች አትጠመዱ። በተጨማሪም ልጆቻችሁ ለራሳቸው ወይም ለእናንተ ሲሉ ሀብትንና ዝናን ከማሳደድ ይልቅ ይሖዋን ለማስቀደም በመወሰናቸው እንደምትኮሩባቸው እንዲያውቁ አድርጉ። ወላጆች፣ እናንተ የተመቻቸ ሕይወት እንድትመሩ ማድረግ የልጆቻችሁ ኃላፊነት እንደሆነ አድርጋችሁ ማሰብ የለባችሁም። “ለልጆቻቸው ሀብት ማከማቸት የሚጠበቅባቸው ወላጆች ናቸው እንጂ ልጆች ለወላጆቻቸው አያከማቹም” የሚለውን ጥቅስ አስታውሱ።—2 ቆሮ. 12:14፤ w17.05 8-9 አን. 3-4