የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es19 ገጽ 67-77
  • ሐምሌ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሐምሌ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2019
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 1
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 2
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 3
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 4
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 5
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 6
  • እሁድ፣ ሐምሌ 7
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 8
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 9
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 10
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 11
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 12
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 13
  • እሁድ፣ ሐምሌ 14
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 15
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 16
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 17
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 18
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 19
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 20
  • እሁድ፣ ሐምሌ 21
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 22
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 23
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 24
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 25
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 26
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 27
  • እሁድ፣ ሐምሌ 28
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 29
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 30
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2019
es19 ገጽ 67-77

ሐምሌ

ሰኞ፣ ሐምሌ 1

በተገቢው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ።—1 ጴጥ. 5:6

ሸብና ‘በቤቱ ላይ [በሕዝቅያስ ቤት ላይ ሳይሆን አይቀርም] የተሾመ መጋቢ’ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ሥልጣን ነበረው። (ኢሳ. 22:15) የሚያሳዝነው ግን ኩሩ በመሆን ለራሱ ክብር መፈለግ ጀመረ። (ኢሳ. 22:16-18) ሸብና ለራሱ ክብር ማግኘት ስለፈለገ አምላክ ‘ከኃላፊነቱ አባርሮ’ በእሱ ምትክ ኤልያቄምን ሾመው። (ኢሳ. 22:19-21) ይህ ለውጥ የተደረገው የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን ለማጥቃት እያሰበ በነበረበት ወቅት ላይ ነው። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሰናክሬም ሕዝቅያስንም ሆነ አይሁዳውያንን ወኔ እንዲከዳቸውና እጅ እንዲሰጡ ለማድረግ ሲል በብዙ ሠራዊት የታጀቡ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ወደ ኢየሩሳሌም ላከ። (2 ነገ. 18:17-25) እነዚህን ባለሥልጣናት እንዲያነጋግር የተላከው ኤልያቄም ነበር፤ ሆኖም ብቻውን አልነበረም። ሌሎች ሁለት ሰዎች አብረውት የነበሩ ሲሆን ከሁለቱ አንዱ ሸብና ነበር፤ ሸብና በዚህ ወቅት በጸሐፊነት እያገለገለ ነበር። ይህ ሁኔታ ሸብና በተወሰደበት እርምጃ ከመከፋትና ቅር ከመሰኘት ይልቅ የተሰጠውን ከቀድሞው ዝቅ ያለ ኃላፊነት በትሕትና እንደተቀበለ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። w18.03 25 አን. 7-8, 10

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 2

በመንፈስ መመላለሳችሁን ቀጥሉ፤ . . . እንዲህ ካደረጋችሁ የሥጋን ምኞት ከቶ አትፈጽሙም።—ገላ. 5:16

ለቁሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ የመስጠት ወይም በሥጋዊ ምኞቶች ላይ የማተኮር አዝማሚያ እንዳለን ብናስተውል ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን ሳናቋርጥ ከለመንነው አስተሳሰባችንን ማስተካከልና ተገቢ በሆኑ ነገሮች ላይ ማተኮር እንድንችል ይረዳናል። (ሉቃስ 11:13) የሐዋርያው ጴጥሮስን ሁኔታ እናስታውስ። ጴጥሮስ ከአንድ መንፈሳዊ ሰው የማይጠበቁ ነገሮችን ያደረገባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ማቴ. 16:22, 23፤ ሉቃስ 22:34, 54-62፤ ገላ. 2:11-14) ያም ሆኖ ተስፋ አልቆረጠም። ጴጥሮስ በይሖዋ እርዳታ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበር ችሏል። እኛም እንዲህ ማድረግ እንችላለን። ጴጥሮስ ልናዳብራቸው የሚገቡ ባሕርያትን በዝርዝር ጽፏል። (2 ጴጥ. 1:5-8) ራስን መግዛትን፣ ጽናትን፣ ወንድማዊ መዋደድንና የመሳሰሉትን ባሕርያት ለማዳበር “ልባዊ ጥረት” ማድረጋችን መንፈሳዊ አመለካከት ያለን ሰዎች በመሆን ረገድ እድገት እያደረግን ለመሄድ ያስችለናል። እንግዲያው ‘መንፈሳዊነቴን ለማጠናከር በዛሬው ዕለት የትኛውን ባሕርይ ለማዳበር ጥረት ማድረግ እችላለሁ?’ እያልን በየዕለቱ ራሳችንን እንጠይቅ። w18.02 25-26 አን. 12-13

ረቡዕ፣ ሐምሌ 3

የተናገረውን ቃል ከሚጠበቅብኝ በላይ ከፍ አድርጌ ተመልክቻለሁ።—ኢዮብ 23:12

ኢዮብ አምላክ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚገባ መረዳት ችሎ ነበር። ስለ ይሖዋ ትክክለኛ እውቀት የነበረው ሲሆን ከዚህ እውቀት ጋር በሚስማማ መንገድ ተመላልሷል። ለምሳሌ በአንድ በኩል በባልንጀራው ላይ ደግነት የጎደለው ድርጊት እየፈጸመ በሌላ በኩል ደግሞ አምላክን እንደሚወድ መናገር እንደማይችል ተገንዝቦ ነበር። (ኢዮብ 6:14) ራሱን ከሌሎች ከፍ አድርጎ ከመመልከት ይልቅ ሀብታም ድሃ ሳይል ለሁሉም ሰው ወንድማዊ ፍቅር ያሳይ ነበር። “እኔን በማህፀን ውስጥ የሠራኝ እነሱንስ አልሠራም?” በማለት ጠይቋል። (ኢዮብ 31:13-22) በግልጽ ማየት እንደምንችለው ኢዮብ የነበረው ክብርና ሀብት ስለ ራሱም ሆነ ስለ ሌሎች ያለውን አመለካከት እንዲያዛባበት አልፈቀደም። ኢዮብ በዘመናችን ካሉ ከፍተኛ ሥልጣንና ሀብት ያላቸው ሰዎች ምንኛ የተለየ ነበር! ኢዮብ ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ ይርቅ ነበር፤ በልቡም እንኳ እንዲህ ያለውን ነገር ላለማሰብ ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። በሐሰት አምልኮ መካፈልም ሆነ ቁሳዊ ሀብትን ከይሖዋ ማስበለጥ “በላይ ያለውን እውነተኛውን አምላክ መካድ” እንደሆነ ተረድቷል። (ኢዮብ 31:24-28) በተጨማሪም ኢዮብ ጋብቻ፣ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚፈጸም ቅዱስ ጥምረት እንደሆነ ይሰማው ነበር። ሌላው ቀርቶ ድንግሊቷን ሥነ ምግባር በጎደለው መንገድ ላለመመልከት ከዓይኑ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል።—ኢዮብ 31:1፤ w18.02 11 አን. 16, 18፤ 12 አን. 19

ሐሙስ፣ ሐምሌ 4

በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች መካከል [ኖኅ] እንከን የሌለበት ሰው ነበር። ኖኅ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር።—ዘፍ. 6:9

ኖኅ ጥሩ ሰው መሆኑ ብቻ በቂ እንደሆነ አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ ደፋር “የጽድቅ ሰባኪ” በመሆን በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት በይፋ ይናገር ነበር። (2 ጴጥ. 2:5) ሐዋርያው ጳውሎስ ኖኅን አስመልክቶ ሲናገር “በዚህ እምነት አማካኝነትም ዓለምን ኮንኗል” በማለት ጽፏል። (ዕብ. 11:7) ኖኅ በዚህ አቋሙ የተነሳ ፌዝና ተቃውሞ አልፎ ተርፎም የኃይል ጥቃት አጋጥሞታል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው። ያም ሆኖ ‘በሰው ፍርሃት’ አልተሸነፈም። (ምሳሌ 29:25) ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ የሚሰጠው ድፍረት እንደነበረው አሳይቷል። ኖኅ ከ500 ለሚበልጡ ዓመታት ለአምላክ ታማኝ ሆኖ ከኖረ በኋላ ይሖዋ የሰዎችንና የእንስሳትን ሕይወት ለማትረፍ የሚያስችል መርከብ እንዲሠራ ትእዛዝ ሰጠው። (ዘፍ. 5:32፤ 6:14) ይህ ሥራ ለኖኅ ምን ያህል ከባድ እንደነበር መገመት እንችላለን! ሥራውን ተፈታታኝ የሚያደርግበት የግንባታው ክብደት ብቻ አልነበረም። ኖኅ ይህ ሥራ ለተጨማሪ ፌዝና ተቃውሞ እንደሚያጋልጠው ያውቅ ነበር። ያም ቢሆን በእምነት የይሖዋን ትእዛዝ ፈጽሟል። ዘገባው “ልክ እንደዚሁ አደረገ” ይላል።—ዘፍ. 6:22፤ w18.02 4 አን. 4, 6-7

ዓርብ፣ ሐምሌ 5

በአንድነት [አብሮ መኖር] ምንኛ መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!—መዝ. 133:1

አንድነታችን እንዲጠናከር አስተዋጽኦ የምናደርግበት አስፈላጊ መንገድ የፍቅር አምላክ የሆነውን ይሖዋን በመምሰል ፍቅር ማሳየት ነው። (1 ዮሐ. 4:8) ከአንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር በተያያዘ “ወንድሞቼ ስለሆኑ ችያቸው ብኖርም እነሱን መውደድ ግን ይከብደኛል” የሚል አመለካከት ሊኖረን አይገባም። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ በፍቅር በመቻቻል ኑሩ” በማለት ከሰጠው ምክር ጋር ይጋጫል። (ኤፌ. 4:2) ጳውሎስ እንዲሁ ‘ተቻችለን እንድንኖር’ ብቻ ሳይሆን ይህንን “በፍቅር” እንድናደርገው እንደመከረን ልብ ማለት ያስፈልጋል። በሁለቱ ሐሳቦች መካከል ልዩነት አለ። በየጉባኤያችን ውስጥ ይሖዋ ወደ ራሱ የሳባቸው የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ይገኛሉ። (ዮሐ. 6:44) ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ወደ ራሱ ከሳባቸው ወዷቸዋል ማለት ነው። ታዲያ ይሖዋ የሚወደውን የእምነት ባልንጀራችንን እኛስ ልንወደው አይገባም? ይሖዋ ወንድሞቻችንን እንድንወድ የሰጠንን ትእዛዝ ተግባራዊ ከማድረግ ፈጽሞ ወደኋላ ማለት አይኖርብንም!—1 ዮሐ. 4:20, 21፤ w18.01 16 አን. 14

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 6

በወጣትነትህ ጊዜ ታላቁን ፈጣሪህን አስብ።—መክ. 12:1

አንዳንድ ወላጆች፣ ልጃቸው ከመጠመቁ በፊት በትምህርቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢደርስና ጥሩ ሥራ ቢይዝ የተሻለ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ወላጆች እንዲህ ዓይነት ሐሳብ የሚያቀርቡት ለልጃቸው መልካም ስለሚያስቡ ነው፤ ሆኖም እንደሚከተለው ብለው ራሳቸውን መጠየቃቸው ጠቃሚ ነው፦ ‘ይህ አካሄድ ልጄ በሕይወቱ እውነተኛ ስኬት እንዲያገኝ ይረዳዋል? ደግሞስ እንዲህ ያለው አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው ሐሳብ ጋር ይስማማል?’ ዓለምም ሆነ በዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች ከይሖዋ ፈቃድ ጋር እንደሚጋጩ መዘንጋት የለብንም። (ያዕ. 4:7, 8፤ 1 ዮሐ. 2:15-17፤ 5:19) ሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም እንዲሁም ይህ ዓለም የሚያራምደው መጥፎ አስተሳሰብ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ልጃችሁ መቋቋም እንዲችል የሚረዳው ከሁሉ የተሻለው መከላከያ ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረቱ ነው። ወላጆች ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ነገር ትምህርትና ጥሩ ሥራ ከሆነ ግን ልጁ እነዚህ ነገሮች ከይሖዋ ጋር ዝምድና ከመመሥረት ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆኑ ሊሰማው ይችላል፤ ይህ ደግሞ አደገኛ ነው። ደግሞስ አፍቃሪ የሆኑ ክርስቲያን ወላጆች፣ የተሳካ ሕይወት ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ልጃቸው በዓለም ላይ ያለውን አመለካከት እንዲያዳብር ይፈልጋሉ? እውነተኛ ደስታና ስኬት ማግኘት የምንችለው በሕይወታችን ውስጥ ለይሖዋ አንደኛ ቦታ ስንሰጠው ብቻ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም።—መዝ. 1:2, 3፤ w18.03 10-11 አን. 10-11

እሁድ፣ ሐምሌ 7

ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ።—ማቴ. 6:33

ብዙዎች አኗኗራቸውን ቀላል ማድረጋቸው ይበልጥ ደስተኞች ለመሆን ያስቻላቸው ከመሆኑም በላይ ይሖዋን ለማገልገል ተጨማሪ ጊዜ አስገኝቶላቸዋል። ጃክ ከባለቤቱ ጋር በአቅኚነት ለማገልገል ስለፈለገ የነበራቸውን ትልቅ ቤትና ድርጅታቸውን ሸጠ። ጃክ እንዲህ ብሏል፦ “ለዓመታት፣ በሥራ ቦታ በሚያጋጥሙኝ ችግሮች የተነሳ ወደ ቤት የምመለሰው እየተበሳጨሁ ነበር። የዘወትር አቅኚ የሆነችው ባለቤቴ ግን ምንጊዜም ደስተኛ ናት። ‘የእኔ አለቃ ከማንም የተሻለ ነው!’ ትለኝ ነበር። አሁን እኔም አቅኚ ስለሆንኩ ሁለታችንም የምንሠራው ለአንድ አካል ይኸውም ለይሖዋ ነው።” ለገንዘብ ያለን አመለካከት ሚዛናዊ መሆኑን ለማወቅ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በመጠቀም ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመራችን ጠቃሚ ነው፦ ‘መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብን በተመለከተ የሚሰጠውን ምክር ከልቤ አምንበታለሁ? አኗኗሬስ ይህን ያሳያል? በሕይወቴ ውስጥ ከምንም በላይ የሚያሳስበኝ ገንዘብ የማግኘት ጉዳይ ነው? ከይሖዋና ከሰዎች ጋር ካለኝ ወዳጅነት ይበልጥ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ለቁሳዊ ነገሮች ነው? ይሖዋ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች እንደሚያሟላልኝ ሙሉ በሙሉ እተማመናለሁ?’ ይሖዋ እሱን ተስፋ የሚያደርጉትን መቼም ቢሆን እንደማያሳፍራቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። w18.01 25 አን. 12-13

ሰኞ፣ ሐምሌ 8

ሁልጊዜ ታዛዥ እንደሆናችሁ ሁሉ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግታችሁ ሥሩ።—ፊልጵ. 2:12

የራስን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግቶ መሥራት በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ኃላፊነት ነው። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ከሚረዱህ ነገሮች መካከል የአምላክን ቃል ማንበብና ባነበብከው ላይ ማሰላሰል፣ ወደ ይሖዋ መጸለይ እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ የይሖዋን እጅ ያየህባቸውን መንገዶች ቆም ብለህ ማሰብ ይገኙበታል። እነዚህን ነገሮች ማድረግህ ይሖዋ ወዳጅህ መሆኑን እንድትተማመን ይረዳሃል። ይህ ደግሞ ስለምታምንባቸው ነገሮች በድፍረት ለመናገር ያነሳሳሃል። (መዝ. 73:28) ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ የራሱን የመከራ እንጨት ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ።” (ማቴ. 16:24) በእርግጥም የክርስቶስ ተከታይ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ራሱን ለይሖዋ መወሰን እና መጠመቅ ይጠበቅበታል። ይህን ማድረጉ በአሁኑ ጊዜ የተትረፈረፈ በረከት፣ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያስገኝለታል። በእርግጥም የራስህን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግተህ እንድትሠራ የሚያነሳሳ በቂ ምክንያት አለህ! w17.12 27 አን. 18-19

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 9

ትዕግሥትን ልበሱ።—ቆላ. 3:12

ወላጆች፣ ልጆቻቸውን በትዕግሥት የሚያስተምሯቸው ከሆነ ልጆቹ የእውነት ‘ስፋት፣ ርዝመት፣ ከፍታና ጥልቀት ምን ያህል እንደሆነ’ ቀስ በቀስ ማስተዋል ይጀምራሉ። (ኤፌ. 3:18) ዕድሜያቸውንና የመረዳት ችሎታቸውን ባገናዘበ መልኩ ማስተማር ይኖርባችኋል። ልጆቻችሁ የሚማሩትን ነገር እያመኑበት ሲመጡ፣ አብረዋቸው ለሚማሩ ልጆችም ሆነ ለሌሎች ስለ እምነታቸው ማስረዳት ቀላል ይሆንላቸዋል። (1 ጴጥ. 3:15) ለምሳሌ ልጆቻችሁ መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን በተመለከተ ምን ብሎ እንደሚያስተምር ማስረዳት ይችላሉ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ማብራሪያ አሳማኝ እንደሆነ ይሰማቸዋል? እርግጥ ነው፣ የአምላክን ቃል በልጆቻችሁ ውስጥ መቅረጽ ትዕግሥት ይጠይቃል፤ ይሁንና የምታደርጉት ጥረት ፈጽሞ የሚያስቆጭ አይሆንም። (ዘዳ. 6:6, 7) እርግጥ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አምኖ በመቀበል ረገድ እናንተ ራሳችሁ ለልጆቻችሁ ምሳሌ መሆናችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። የሦስት ሴቶች ልጆች እናት የሆነችው ስቴፋኒ እንዲህ ብላለች፦ “ልጆቼ ገና ሕፃናት ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ ራሴን እንዲህ እያልኩ እጠይቅ ነበር፦ ‘ይሖዋ መኖሩን፣ አፍቃሪ መሆኑን እንዲሁም መንገዶቹ ትክክል መሆናቸውን እኔ ራሴ አምኜ የተቀበልኩት ለምን እንደሆነ ለልጆቼ እነግራቸዋለሁ? እኔ ይሖዋን ከልቤ እንደምወደው ልጆቼ በግልፅ መመልከት ይችላሉ?’ እኔ ራሴ አምኜ ያልተቀበልኩትን ነገር ልጆቼ እንዲያምኑበት መጠበቅ አልችልም።” w17.12 20 አን. 8-10

ረቡዕ፣ ሐምሌ 10

ወንድምሽ ይነሳል።—ዮሐ. 11:23

ማርታ ወንድሟ እንደሚነሳ ይህን ያህል እርግጠኛ የሆነችው ለምንድን ነው? በትንሣኤ እንድትተማመን ያደረጋት ኢየሱስ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት ስለተፈጸሙ ተአምራት የነበራት እውቀት ሊሆን ይችላል። ከልጅነቷ ጀምሮ ስለ እነዚህ ተአምራት በቤት ውስጥ እንዲሁም በምኩራብ ተምራለች። በመንፈስ መሪነት በተጻፉት ዘገባዎች ውስጥ የሰፈሩት ስለ ትንሣኤ የሚያወሱ ሦስት ታሪኮች ወደ አእምሯችን ይመጡ ይሆናል። እስቲ የመጀመሪያውን ትንሣኤ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ይህ ትንሣኤ የተከናወነው፣ ነቢዩ ኤልያስ ከአምላክ ባገኘው ኃይል ተአምራት ይፈጽም በነበረበት ወቅት ነው። ኤልያስን፣ የፊንቄ የወደብ ከተማ በሆነችው በሰራፕታ የምትኖር አንዲት ድሃ መበለት አስተናገደችው። አምላክም ለዚህ ቤተሰብ አንድ ተአምር ፈጸመ፤ ይህች ሴትና ልጇ የነበራቸው ዱቄትና ዘይት እንዳያልቅ በማድረግ በረሃብ እንዳይሞቱ ታደጋቸው። (1 ነገ. 17:8-16) ከጊዜ በኋላ ግን የሴትየዋ ልጅ ታምሞ ሞተ። በዚህ ጊዜ ኤልያስ ይህችን ሴት ረዳት። ነቢዩ “አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ የዚህ ልጅ ሕይወት ይመለስለት” በማለት ጸለየ። የጠየቀውም ተፈጸመለት! አምላክ የኤልያስን ጸሎት በመስማት ልጁ ከሞት እንዲነሳ አደረገ። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የምናገኘው የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው። (1 ነገ. 17:17-24) ማርታ ስለዚህ አስደናቂ ክንውን እንደምታውቅ ጥርጥር የለውም። w17.12 3 አን. 1፤ 4 አን. 3, 5-6

ሐሙስ፣ ሐምሌ 11

ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።—ማቴ. 6:24

ብዙ ሰዎች ጥሩ ደሞዝና ማዕረግ በሚያስገኝ የሥራ መስክ መሰማራትን በሕይወታችን ውስጥ ዋነኛ ግባችን እንድናደርገው ያበረታቱን ይሆናል። እንዲህ ያለው የሥራ መስክ ትልቅ ቦታ ላይ ለመድረስ ብሎም ሥልጣንና ሀብት ለማግኘት ያስችል ይሆናል። ብዙዎች የሕይወታቸው ዋነኛ ግብ እንዲህ ባለው የሥራ መስክ መሰማራት በመሆኑ አንድ ክርስቲያንም ተመሳሳይ አመለካከት ሊያድርበት ይችላል። ሥልጣን በሚያስገኝና አንቱ በሚያስብል የሥራ መስክ መሰማራት በእርግጥ ዘላቂ ደስታ ያስገኛል? በፍጹም። ሰይጣን በሌሎች ላይ የመሠልጠንና የመከበር ምኞት እንደነበረው አስታውስ፤ ይሁንና እነዚህን ነገሮች ማግኘቱ ደስተኛ አላደረገውም፤ እንዲያውም በቁጣ ተሞልቷል። (ማቴ. 4:8, 9፤ ራእይ 12:12) ከዚህ በተቃራኒ ግን ሰዎች ስለ አምላክ እንዲያውቁና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ መርዳት ታላቅ ደስታ ያስገኛል። እንዲህ ያለ ደስታ ሊያስገኝ የሚችል ሌላ የሥራ መስክ የለም። ከዚህም ሌላ ይህ ዓለም የፉክክር መንፈስን ያስፋፋል። ሰዎች ከሌሎች ልቀው እንዲገኙ ግፊት የሚደረግባቸው ሲሆን ይህም ቅናት እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ የእነዚህ ሰዎች አካሄድ “ነፋስን እንደማሳደድ” መሆኑን ይገልጻል።—መክ. 4:4፤ w17.11 22-23 አን. 11-13

ዓርብ፣ ሐምሌ 12

የውዳሴ መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄዱ።—ማቴ. 26:30

የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላም ሙዚቃ በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ጉልህ ቦታ ነበረው። በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው ምሽት ላይ ኢየሱስ የጌታ ራት በዓልን ካቋቋመ በኋላ ከሐዋርያቱ ጋር መዝሙር ዘምሯል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በኅብረት ሆነው አምላክን በመዝሙር በማወደስ ረገድ ምሳሌ ትተውልናል። እነዚያ ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ የሚሰበሰቡት በግለሰቦች መኖሪያ ቤት ውስጥ ቢሆንም ይህ መሆኑ ለይሖዋ በግለት እንዳይዘምሩ አላደረጋቸውም። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያን ወንድሞቹን “በመዝሙራት፣ ለአምላክ በሚቀርብ ውዳሴና በአመስጋኝነት መንፈስ በሚዘመሩ መንፈሳዊ ዝማሬዎች ትምህርትና ማበረታቻ መስጠታችሁን ቀጥሉ፤ በልባችሁም ለይሖዋ ዘምሩ” በማለት በመንፈስ መሪነት አበረታቷቸዋል። (ቆላ. 3:16) በመዝሙር መጽሐፋችን ላይ የሚገኙት መዝሙሮችም “በአመስጋኝነት መንፈስ [የሚዘመሩ] መንፈሳዊ ዝማሬዎች” ናቸው። እነዚህ መዝሙሮች “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ክፍል ናቸው።—ማቴ. 24:45፤ w17.11 4 አን. 7-8

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 13

አመቺ የሆኑ የመማጸኛ ከተሞችን ለራሳችሁ ምረጡ።—ዘኁ. 35:11

ስድስቱ የመማጸኛ ከተሞች ወደነበሩበት ቦታ መድረስ አስቸጋሪ አልነበረም። ይሖዋ ሦስቱን የመማጸኛ ከተሞች ከዮርዳኖስ ወዲህ፣ ሦስቱን ከተሞች ደግሞ ከዮርዳኖስ ወዲያ እንዲያደርጓቸው እስራኤላውያንን አዟቸው ነበር። ይህን ያላቸው ለምንድን ነው? ሳያስበው ነፍስ ያጠፋ ማንኛውም ሰው ብዙም ሳይቸገር በፍጥነት ወደ መማጸኛ ከተማ መድረስ እንዲችል ነው። (ዘኁ. 35:12-14) ወደ መማጸኛ ከተሞች የሚወስዱት መንገዶች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዲገኙ ይደረግ ነበር። (ዘዳ. 19:3) በተጨማሪም የአይሁዳውያን የማመሣከሪያ ጽሑፎች እንደሚገልጹት ወደ መማጸኛ ከተሞች የሚሸሹ ሰዎችን ለመርዳት ሲባል በመንገዶቹ ላይ አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶች ይቆሙ ነበር። በእስራኤል ውስጥ የመማጸኛ ከተሞች ስለተዘጋጁ፣ ሳያውቅ ሰው የገደለ ግለሰብ ወደ ሌላ አገር ለመሸሽ የሚገደድበት ምክንያት አይኖርም፤ ግለሰቡ ወደ ባዕድ አገር መሸሽ ቢኖርበት ግን የሐሰት አምልኮን ለመከተል ሊፈተን ይችላል። እስቲ አስበው፦ ሆን ብለው ነፍስ ያጠፉ ግለሰቦች በሞት እንዲቀጡ የሚያዝዝ ሕግ ያወጣው ይሖዋ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሳያውቁ ነፍስ ያጠፉ ሰዎች በርኅራኄ እንዲያዙ እንዲሁም ምሕረትና ጥበቃ የሚያገኙበት አጋጣሚ እንዲያገኙ ዝግጅት ያደረገውም እሱ ራሱ ነው! አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደገለጹት “በተቻለ መጠን ሁሉም ነገር ግልጽ፣ ያልተወሳሰበና ቀላል ተደርጎ ነበር።” ይሖዋ፣ አገልጋዮቹን ለመቅጣት የሚቸኩል ጨካኝ ዳኛ አይደለም። ከዚህ ይልቅ “አምላክ ምሕረቱ ብዙ ነው።”—ኤፌ. 2:4፤ w17.11 14 አን. 4-5

እሁድ፣ ሐምሌ 14

ወደ እኔ ተመለሱ . . . እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ።—ዘካ. 1:3

የሚበር ጥቅልል፣ በመስፈሪያ ውስጥ ያለች አንዲት ሴትና የራዛ ዓይነት ክንፎች ያላቸው በነፋስ መካከል የሚወነጨፉ ሁለት ሴቶች። የዘካርያስ መጽሐፍ እንደነዚህ ያሉ አስደናቂ ራእዮችን ይዟል። (ዘካ. 5:1, 7-9) ለመሆኑ ይሖዋ ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ያሉ ራእዮችን እንዲያይ ያደረገው ለምንድን ነው? ዘካርያስ ያየው ስድስተኛውና ሰባተኛው ራእይ ሐቀኝነት በጎደለው አካሄዳቸው ለሚቀጥሉ ሰዎች ይሖዋ መጥፎ ድርጊትን ችላ ብሎ እንደማያልፍ የሚያስገነዝብ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ይሖዋን በንጹሕ ልቦና የሚያመልኩ አገልጋዮቹ ደግሞ ለክፋት ከፍተኛ ጥላቻ ሊኖራቸው ይገባል። ዘካርያስ ያያቸው ራእዮች ይሖዋ የሰጠንን ፍቅራዊ ማረጋገጫም ይዘዋል። የአምላክ ሞገስና ጥበቃ ያለን ሰዎች ለመሆን ትጋት የተሞላበት ጥረት የምናደርግ ከሆነ ሞትን ከሚያስከትለው እርግማን ማምለጥ እንችላለን። በተጨማሪም የይሖዋን በረከት እናገኛለን። በክፋት በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ ንጹሕ ሆነን ለመኖር የምናደርገው ትግል ፈጽሞ የሚያስቆጭ አይደለም። ደግሞም በይሖዋ እርዳታ እንደሚሳካልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን! w17.10 21 አን. 1፤ 25 አን. 19

ሰኞ፣ ሐምሌ 15

አረጋውያን ሴቶች ለቅዱሳን ሰዎች የሚገባ ባሕርይ ያላቸው . . . ይሁኑ፤ ይህም ወጣት ሴቶችን [እንዲመክሩ ነው]።—ቲቶ 2:3, 4

በዛሬው ጊዜ ነጠላ እህቶች አገልግሎታቸውን ማስፋት የሚችሉባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ፤ በአቅኚነት አገልግሎት መካፈልን፣ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውሮ ማገልገልን፣ በአካባቢ ንድፍና ግንባታ ፕሮግራም መካፈልንና በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት መማርን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። እንዲያውም አንዳንድ እህቶች ጊልያድ ትምህርት ቤት ገብተው የመማር አጋጣሚ አግኝተዋል። በዕድሜ የገፉ እህቶች ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ማድረግ ባይችሉም እንኳ እነሱም ለጉባኤው በረከት ናቸው። እነዚህን እህቶች በጣም እንወዳቸዋለን! አንዳንዶቹ በአምላክ አገልግሎት የቀድሞውን ያህል ብዙ ማከናወን አይችሉ ይሆናል፤ ይሁንና አሁንም ቢሆን ደፋሮች በመሆን የሚሠሩት ሥራ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት አረጋዊት እህት በአለባበስ ረገድ ልከኛ መሆንን በተመለከተ ለአንዲት ወጣት እህት ምክር እንዲሰጡ ሊጠየቁ ይችላሉ፤ በዚህ ጊዜ ደፋር መሆን ያስፈልጋቸዋል። እኚህ እህት ምክር የሚያስፈልጋትን እህት በሚያነጋግሩበት ጊዜ የአለባበስ ምርጫዋን በተመለከተ አይነቅፏትም፤ ከዚህ ይልቅ በዚህ ረገድ የምታደርገው ምርጫ በሌሎች ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል እንድታስብበት ይረዷታል። (1 ጢሞ. 2:9, 10) ፍቅርና አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ የቀረበ እንዲህ ያለ ምክር ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። w17.09 31-32 አን. 17-18

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 16

ስለ አምላክ እውቀት ትቀስማለህ።—ምሳሌ 2:5

ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው አካላት መጽሐፍ ቅዱስ ለተራው ሕዝብ እንዳይደርስ ጥረት ያደረጉባቸው ጊዜያት ነበሩ። ይሁንና ቅን ልብ ያላቸው ግለሰቦች እንዲህ ያለውን ተቃውሞ በድፍረት ተጋፍጠዋል። በ14ኛው መቶ ዘመን የኖረውን ጆን ዊክሊፍ የተባለ የሃይማኖት ምሁር እንደ ምሳሌ እንመልከት። ጆን ዊክሊፍ ሁሉም ሰው የአምላክን ቃል ማንበብ አለበት የሚል ጠንካራ እምነት ነበረው። ሆኖም በእሱ ዘመን፣ እንግሊዝ ውስጥ የሚኖሩ አብዛኞቹ ተራ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት አይችሉም ነበር። በ1382 የዊክሊፍ መጽሐፍ ቅዱስ ተብሎ የሚጠራው የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ተዘጋጀ። ተራው ሕዝብ የአምላክን ቃል እንዲረዳ የማገዝ ፍላጎት የነበራቸው ሎላርድ ተብለው የሚታወቁት ተጓዥ ሰባኪዎች፣ በመላው እንግሊዝ ከአንዱ መንደር ወደ ሌላው በእግር እየተዘዋወሩ ሰብከዋል። ሎላርዶች አብዛኛውን ጊዜ፣ ለሚያገኟቸው ሰዎች ከዊክሊፍ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንዳንድ ጥቅሶችን የሚያነቡላቸው ከመሆኑም ሌላ የዚህን መጽሐፍ ቅዱስ በእጅ የተገለበጡ ቅጂዎች ይሰጧቸው ነበር። ከዚያ በኋላ ባሉት መቶ ዓመታት በአውሮፓም ሆነ በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ተራው ሕዝብ በሚናገረው ቋንቋ እንዲተረጎምና እንዲሰራጭ ማድረግ ጀመሩ። w17.09 20-21 አን. 10-12

ረቡዕ፣ ሐምሌ 17

የሚያገቡ ሰዎች በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል።—1 ቆሮ. 7:28

ልጅ እየፈለጉ መውለድ አለመቻል ራሱ ‘በሥጋ ላይ የሚደርስ መከራ’ ነው። (ምሳሌ 13:12) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን፣ መሃን መሆን እንደሚያሳፍር ነገር ተደርጎ ይቆጠር ነበር። የያዕቆብ ሚስት የሆነችው ራሔል እንደ እህቷ ልጆች መውለድ ባለመቻሏ ምሬቷን ገልጻ ነበር። (ዘፍ. 30:1, 2) ባለትዳሮች ሊደርሱባቸው ከሚችሉ መከራዎች ሌላው ደግሞ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ነው። ብዙዎች የትዳር ጓደኛቸውን በሞት በማጣታቸው ለየት ያለ ፈተና አጋጥሟቸዋል። የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣው ሰው በዚህ ሥርዓት ውስጥ እንዲህ ያለ ፈተና ያጋጥመኛል ብሎ አልጠበቀ ይሆናል። ክርስቲያኖች ኢየሱስ በሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት አላቸው። (ዮሐ. 5:28, 29) የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣ ሰው ይህን ተስፋ ማወቁ ምን ጥቅም ያስገኝለታል? በጣም እንደሚያጽናናው የታወቀ ነው። አፍቃሪ የሆነው አባታችን በቃሉ አማካኝነት እንዲህ ያሉ ተስፋዎችን በመስጠት መከራ የሚደርስባቸውን ሰዎች ያጽናናል። w17.06 4 አን. 1፤ 5 አን. 6፤ 6 አን. 9

ሐሙስ፣ ሐምሌ 18

ይሖዋ፣ ይሖዋ፣ መሐሪና ሩኅሩኅ የሆነ አምላክ።—ዘፀ. 34:6

በአንድ ወቅት አምላክ ራሱን ለሙሴ ሲገልጥ ስሙንና ባሕርያቱን ነግሮታል። መጀመሪያ ላይ የጠቀሳቸው ባሕርያት ደግሞ ምሕረትና ርኅራኄ ናቸው። (ዘፀ. 34:5-7) ይሖዋ ስለ ኃይሉ ወይም ስለ ጥበቡ መናገር ይችል ነበር። ይሁንና ይሖዋ ጎላ አድርጎ የገለጸው አገልጋዮቹን ለመርዳት ፈቃደኛ መሆኑን የሚያሳዩ ባሕርያቱን ነው፤ ምክንያቱም ሙሴ በዚያን ወቅት አምላክ እንደሚደግፈው የሚያሳይ ማረጋገጫ ይፈልግ ነበር። (ዘፀ. 33:13) የተፈጠርነው ርኅራኄ ማሳየት እንድንችል ተደርገን ቢሆንም ከአዳም የወረስነው አለፍጽምና ራስ ወዳዶች መሆን እንዲቀናን ያደርገናል። አንዳንድ ጊዜ ‘ሌሎችን እንርዳ ወይስ የራሳችንን ፍላጎት እናስቀድም’ የሚለውን ጉዳይ መወሰን ከባድ ሊሆንብን ይችላል። አንዳንዶች በውስጣቸው ያለውን የራስ ወዳድነት ስሜት ለማሸነፍ ሁልጊዜ ትግል ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ ርኅራኄን ለማዳበር ምን ማድረግ ይኖርብሃል? በመጀመሪያ፣ ይሖዋ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ሰዎች ርኅራኄ ያሳዩት እንዴት እንደሆነ ጊዜ ወስደህ ለመመርመር ጥረት አድርግ። ከዚያም በዚህ ረገድ የአምላክን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት እንደሆነና ይህን ማድረግህ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልህ ለማሰብ ሞክር። w17.09 8 አን. 1፤ 9 አን. 3

ዓርብ፣ ሐምሌ 19

ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ።—ፊልጵ. 2:3

አዲሱን ስብዕና ለመልበስ ጥረት የምናደርገው ይሖዋን ለማስከበር እንጂ የሰዎችን ውዳሴ ለማግኘት መሆን አይኖርበትም። በአንድ ወቅት ፍጹም የነበረ መንፈሳዊ ፍጡርም እንኳ በውስጡ ኩራት እንዲያድር በመፍቀዱ ኃጢአት እንደሠራ እናስታውስ። (ከሕዝቅኤል 28:17 ጋር አወዳድር።) ኃጢአተኛ ለሆንነው ለእኛ ደግሞ ከኩራትና ከትዕቢት መራቅ ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም! ያም ቢሆን ትሕትናን መልበስ እንችላለን። እንዲህ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል? ምንጊዜም ትሑት መሆን ከፈለግን በየዕለቱ የአምላክን ቃል የምናነብበትና ባነበብነው ላይ የምናሰላስልበት ጊዜ መመደብ ይኖርብናል። (ዘዳ. 17:18-20) በተለይም ደግሞ ኢየሱስ ባስተማራቸው ትምህርቶችና በትሕትና በማገልገል ረገድ በተወው ግሩም ምሳሌ ላይ ጊዜ ወስደን ማሰላሰላችን ይጠቅመናል። (ማቴ. 20:28) ኢየሱስ የሐዋርያቱን እግር እስከማጠብ ድረስ ትሑት መሆኑን አሳይቷል። (ዮሐ. 13:12-17) ትሕትናን ለመልበስ የሚረዳን ሌላው ነገር ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን አዘውትረን መጸለያችን ነው፤ ከሌሎች የተሻልን እንደሆንን በትንሹም እንኳ የሚሰማን ከሆነ የአምላክ መንፈስ ይህን ዝንባሌ ከሥሩ ነቅለን መጣል እንድንችል ይረዳናል።—ገላ. 6:3, 4፤ w17.08 25 አን. 11-12

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 20

ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።—ፊልጵ. 4:6, 7

የአምላክን ቅዱስ መንፈስ አመራር ብንከተልም ነገሮች ባሰብነው መንገድ እየሄዱ እንዳልሆነ የተሰማን ጊዜ ሊኖር ይችላል። በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማድረግን የሚጠይቁ አሊያም ተፈታታኝ የሆኑ አዳዲስ ሁኔታዎች አጋጥመውን ይሆናል። (መክ. 9:11) ታዲያ ስለ ምንም ነገር እንዳንጨነቅ እንዲሁም “የአምላክ ሰላም” እንዲኖረን ምን ሊረዳን ይችላል? ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ የጭንቀት ማርከሻው ጸሎት እንደሆነ ያሳያል። በመሆኑም ምንም ነገር ሲያስጨንቀን ወደ ይሖዋ መጸለይ ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 5:6, 7) ይሖዋ እንደሚያስብልህ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ወደ እሱ ጸልይ። ከይሖዋ ያገኘሃቸውን በረከቶች በማስታወስ ጸሎትህን “ከምስጋና ጋር” አቅርብ። ይሖዋ “ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ” እንደሚችል ማስታወሳችን በእሱ ላይ ያለን እምነት እንዲጠናከር ያደርጋል።—ኤፌ. 3:20፤ w17.08 9 አን. 4, 6፤ 10 አን. 10

እሁድ፣ ሐምሌ 21

መመካከር ከሌለ የታቀደው ነገር ሳይሳካ ይቀራል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል።—ምሳሌ 15:22

በርካታ ክርስቲያኖች በወጣትነታቸው አቅኚዎች ሆነው በማገልገላቸው ደስታ አግኝተዋል። ወጣት ከሆንክ ልታወጣ ያሰብከውን ዕቅድ በተመለከተ እነዚህን ክርስቲያኖች ለምን አታማክራቸውም? እንዲህ ያሉ መንፈሳዊ ሰዎች፣ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በሕይወትህ ሙሉ የሚጠቅምህ ትምህርት እንደሚሰጥህ ይነግሩሃል። ኢየሱስ በሰማይ እያለ ከአባቱ የተማረ ቢሆንም በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅትም መማሩን ቀጥሎ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ምሥራቹን የሰዎችን ልብ በሚነካ መንገድ ማቅረብ እንዲሁም በመከራ ውስጥ ታማኝነትን መጠበቅ ደስታ እንደሚያስገኝ ተምሯል። (ኢሳ. 50:4፤ ዕብ. 5:8፤ 12:2) ኢየሱስ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ብሏል። (ማቴ. 28:19, 20) ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ ለመሰማራት ካቀድክ፣ በሕይወትህ ውስጥ ከሁሉ የላቀ እርካታ የሚያስገኝና አምላክን የሚያስከብር ሥራ መርጠሃል። እርግጥ ነው፣ እንደማንኛውም የሥራ መስክ ሁሉ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራም ውጤታማ ለመሆን ጊዜ ያስፈልግሃል። w17.07 23 አን. 6-7

ሰኞ፣ ሐምሌ 22

ሁልጊዜ አጽናናችኋለሁ።—ኢሳ. 66:13

ከሐዘናችን እንድንጽናና ከማንም በላይ ሊረዳን የሚችለው ሩኅሩኅ የሆነው የሰማዩ አባታችን ይሖዋ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። (2 ቆሮ. 1:3, 4) ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች መጽናኛ ማግኘት የሚችሉበት ሌላው መንገድ ደግሞ የክርስቲያን ጉባኤ ነው። (1 ተሰ. 5:11) “የተደቆሰ መንፈስ” ያላቸውን ሰዎች ማበርታትና ማጽናናት የምትችሉት እንዴት ነው? (ምሳሌ 17:22) “ዝም ለማለት ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው” የሚለውን ጥቅስ አስታውሱ። (መክ. 3:7) ዳሊን የተባለች ባለቤቷን በሞት ያጣች ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን መግለጽ ይፈልጋሉ። በመሆኑም ሐዘን የደረሰበትን ሰው ለማጽናናት ልታደርጉ የምትችሉት በጣም አስፈላጊ ነገር፣ ሐሳቡን ሲገልጽ ሳታቋርጡት ማዳመጥ ነው።” ወንድሟ የራሱን ሕይወት ያጠፋው ዩኒያም አክላ እንዲህ ብላለች፦ “የሚሰማቸውን ሐዘን ሙሉ በሙሉ መረዳት ባትችሉም እንኳ ስሜታቸውን ለመረዳት እንደምትፈልጉ ማሳየታችሁ በራሱ ያጽናናቸዋል።” ሐዘን በሰዎች ላይ የሚፈጥረው ስሜትና ሐዘናቸውን የሚገልጹበት መንገድ የተለያየ እንደሆነም አስታውሱ። w17.07 13 አን. 3፤ 14 አን. 11-13

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 23

ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል እንደሆንክ ሰዎች ይወቁ።—መዝ. 83:18

በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ነገር ገንዘብ ነው። ትኩረታቸው በሙሉ ያረፈው ሀብት በማካበት ላይ ሲሆን ያላቸውን ሀብት ላለማጣት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ሌሎች ደግሞ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለቤተሰባቸው፣ ለጤናቸው ወይም እንደ ስኬት ለሚቆጥሯቸው ነገሮች ነው። ይሁን እንጂ በሁላችንም ፊት የተደቀነው አንገብጋቢ ጉዳይ የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት መረጋገጡ ነው። ይህን አንገብጋቢ ጉዳይ ችላ እንዳንል መጠንቀቅ ይኖርብናል። ለዚህ ሊዳርገን የሚችለው ምንድን ነው? በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከልክ በላይ መጠመዳችን የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት መረጋገጡ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንድንዘነጋ ሊያደርገን ይችላል። ወይም ደግሞ በሚደርሱብን ከባድ ፈተናዎች ተውጠን ለዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት ሳንሰጥ ልንቀር እንችላለን። በሌላ በኩል ግን፣ የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት መረጋገጡ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በተገነዘብን መጠን በዕለታዊ ሕይወታችን የሚገጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በተሻለ ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ይኖረናል። በተጨማሪም ይህን መገንዘባችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ያደርገናል። w17.06 22 አን. 1-2

ረቡዕ፣ ሐምሌ 24

እኔ የክርስቶስን አርዓያ እንደምከተል እናንተም የእኔን አርዓያ ተከተሉ።—1 ቆሮ. 11:1

ይሖዋ ምንጊዜም ሥልጣኑን የሚጠቀመው ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው። የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚወዱ የቤተሰብ ራሶችና የጉባኤ ሽማግሌዎችም የራሳቸው ሉዓላዊነት ያላቸው ይመስል ከሌሎች ብዙ አይጠብቁም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን ለመምሰል ይጥራሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ረገድ የአምላክንና የልጁን ምሳሌ ለመከተል ጥረት አድርጓል። ጳውሎስ ሌሎች እንዲሸማቀቁ ከማድረግ ወይም ትክክል የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ ለማስገደድ ከመሞከር ይልቅ ተማጽኗቸዋል። (ሮም 12:1፤ ኤፌ. 4:1፤ ፊልሞና 8-10) ይሖዋ ሌሎችን የሚይዘው በዚህ መንገድ ነው። በመሆኑም የይሖዋን አገዛዝ የሚወዱና የሚደግፉ ሰዎች የእሱን ምሳሌ መከተል አለባቸው። የይሖዋን አገዛዝ እንደምንደግፍ የምናሳይበት ሌላው መንገድ ይሖዋ ሥልጣን ከሰጣቸው ሰዎች ጋር በመተባበር ነው። አንድ ውሳኔ የተደረገበት ምክንያት ባይገባን ወይም በውሳኔው ባንስማማም እንኳ ቲኦክራሲያዊውን ሥርዓት መደገፍ ይኖርብናል። ዓለም እንዲህ ያለው ነገር አይዋጥለትም፤ በይሖዋ አገዛዝ ሥር ለመኖር ግን ይህን ማድረግ አስፈላጊ ነው።—ኤፌ. 5:22, 23፤ 6:1-3፤ ዕብ. 13:17፤ w17.06 30 አን. 14-15

ሐሙስ፣ ሐምሌ 25

እርስ በርስ እንድትዋደዱ ከአምላክ [ተምራችኋል]።—1 ተሰ. 4:9

በየትኛውም ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ተስፋ የቆረጡ ወይም በመንፈስ ጭንቀት የተዋጡ አሊያም ሌሎች ፈተናዎች ያጋጠሟቸው ወንድሞችና እህቶች ትኩረት፣ ማበረታቻና ማጽናኛ ልንሰጣቸው ይገባል። (ምሳሌ 12:25፤ ቆላ. 4:11) “በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች” በቃልም ሆነ በድርጊት ከልብ እንደምናስብላቸው የምናሳይ ከሆነ ለወንድሞቻችን እውነተኛ ፍቅር እንዳለን እናረጋግጣለን። (ገላ. 6:10) መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ክፉ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀናት’ ራስ ወዳድነትና ስግብግብነት በስፋት እንደሚታይ አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞ. 3:1, 2) በመሆኑም ክርስቲያኖች ለአምላክ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው እውነትና ለወንድሞቻቸው ያላቸውን ፍቅር ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለባቸው። እርግጥ ነው፣ ከእምነት አጋሮቻችን ጋር አለመግባባት የሚያጋጥመን ጊዜ ይኖራል። በዚህ ወቅት በፍቅር ተነሳስተን አለመግባባቱን ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ቶሎ መፍታታችን ለሁሉም የጉባኤው አባላት በረከት ያስገኛል! (ኤፌ. 4:32፤ ቆላ. 3:14) እንግዲያው ለይሖዋ፣ ለቃሉና ለወንድሞቻችን ምንጊዜም ጥልቅ ፍቅር እናሳይ። w17.05 21 አን. 17-18

ዓርብ፣ ሐምሌ 26

“ኃጢአት የለብንም” ብለን የምንናገር ከሆነ ራሳችንን እያታለልን ነው።—1 ዮሐ. 1:8

ክርስቲያኖች ከጉባኤ ውጭ ያሉ ሰዎች ፍትሐዊ ያልሆነ ድርጊት ሊፈጽሙባቸው እንደሚችሉ ይጠብቃሉ። ይሁንና በጉባኤ ውስጥ፣ ፍትሐዊ እንዳልሆነ የሚሰማን ነገር ብንመለከት ወይም በእኛ ላይ ቢፈጸም እምነታችን ሊፈተን ይችላል። አንተስ ጉባኤው ወይም አንድ የእምነት ባልንጀራህ በደል እንደፈጸመብህ ቢሰማህ ምን ታደርጋለህ? ይህ ሁኔታ እንዲያሰናክልህ ትፈቅዳለህ? ሁላችንም ፍጽምና የሚጎድለን ከመሆኑም ሌላ የኃጢአት ዝንባሌ አለን፤ በመሆኑም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም እንኳ ሌሎች ሊበድሉን እንደሚችሉ ወይም እኛ ራሳችን ሌሎችን ልንበድል እንደምንችል የታወቀ ነው። እንዲህ ያለው ነገር እምብዛም የሚያጋጥም ባይሆንም ታማኝ ክርስቲያኖች የፍትሕ መጓደል ቢያጋጥማቸው ነገሩ እንግዳ ሊሆንባቸው ወይም ሊሰናከሉ አይገባም። ይሖዋ የእምነት አጋሮቻችን ቢበድሉን እንኳ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን ለመመላለስ የሚረዳ ጠቃሚ ምክር በቃሉ ውስጥ እንዲካተት አድርጎልናል።—መዝ. 55:12-14፤ w17.04 19 አን. 4-5

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 27

የሚያገቡ ሰዎች በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል።—1 ቆሮ. 7:28

የማያምን የትዳር ጓደኛ ባላቸው ክርስቲያኖች ትዳር ውስጥ የሚፈጠረው ውጥረትና ጭንቀት የከፋ ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን፣ የትዳር ጓደኛችሁ ክርስቶስን ለመከተል ፈቃደኛ አለመሆኑ ብቻውን፣ ለመለያየት ወይም ለፍቺ መሠረት ሊሆን አይችልም። (1 ቆሮ. 7:12-16) አንድ የማያምን ባል ከመንፈሳዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ያለበትን ኃላፊነት ላይወጣ ቢችልም የቤተሰቡ ራስ እንደመሆኑ መጠን ሊከበር ይገባዋል። የማታምን ሚስት ያለው ክርስቲያን ባልም ለሚስቱ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ጥልቅ ፍቅር ሊያሳያት ይገባል። (ኤፌ. 5:22, 23, 28, 29) የትዳር ጓደኛችሁ ለይሖዋ በምታቀርቡት አገልግሎት ላይ ገደብ ለመጣል ቢሞክርስ? ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት እህት ባሏ አገልግሎት መውጣት የምትችለው በተወሰኑ ቀናት ላይ ብቻ እንደሆነ ነግሯት ነበር። እናንተም ተመሳሳይ ሁኔታ ካጋጠማችሁ ራሳችሁን እንደሚከተለው በማለት ጠይቁ፦ ‘የትዳር ጓደኛዬ ጨርሶ ይሖዋን እንዳላመልክ እየከለከለኝ ነው? ካልሆነ እሱ ያቀረበውን ሐሳብ መቀበል እችል ይሆን?’ ምክንያታዊ መሆናችሁ በትዳራችሁ ውስጥ አላስፈላጊ ቅራኔ እንዳይፈጠር ይረዳችኋል።—ፊልጵ. 4:5፤ w17.10 13 አን. 7-8

እሁድ፣ ሐምሌ 28

በልጆችህም ውስጥ ቅረጻቸው።—ዘዳ. 6:7

በትንቢት እንደተነገረው “ከብሔራት ቋንቋዎች ሁሉ የተውጣጡ” ሰዎች ወደ ይሖዋ ድርጅት እየጎረፉ ነው። (ዘካ. 8:23) ይሁንና ልጆቻችሁ የእናንተን ቋንቋ በደንብ የማይረዱ ከሆነ እውነትን ለእነሱ ማስተማር ከባድ ሊሆንባችሁ ይችላል። የላቀ ቦታ የምትሰጧቸው ጥናቶቻችሁ ልጆቻችሁ ናቸው፤ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ደግሞ ይሖዋን “ማወቅ” አለባቸው። (ዮሐ. 17:3) ልጆቻችሁ የይሖዋን ትምህርቶች እንዲያውቁ፣ አመቺ በሆነ ጊዜ ሁሉ ስለ እነዚህ ትምህርቶች ‘መናገር’ ይኖርባችኋል። (ዘዳ. 6:6, 7) ልጆቻችሁ በአካባቢው የሚነገረውን ቋንቋ በትምህርት ቤትና በዙሪያቸው ካሉት ሰዎች መማራቸው አይቀርም፤ የእናንተን ቋንቋ በዋነኝነት መማር የሚችሉት ግን በቋንቋችሁ አዘውትራችሁ የምታነጋግሯቸው ከሆነ ነው። ልጆቻችሁ የእናንተን ቋንቋ ማወቃቸው የልባቸውን አውጥተው እንዲያዋሯችሁ ያስችላል፤ ሌሎች ጥቅሞችም አሉት። ልጆቻችሁ የተለያዩ ቋንቋዎችን መቻላቸው ለአእምሯዊ እድገታቸው አስተዋጽኦ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ከሰዎች ጋር የመግባባት ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ይረዳቸዋል። w17.05 9 አን. 5-6

ሰኞ፣ ሐምሌ 29

ሂድና ወደ ታቦር ተራራ ዝመት፤ [እኔም] ሲሳራን . . . ወደ አንተ አመጣዋለሁ፤ እሱንም በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ።—መሳ. 4:6, 7

እስራኤላውያን በጠላቶቻቸው ላይ ጥቃት ለመሰንዘርም ሆነ ራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችል የጦር መሣሪያ አልነበራቸውም፤ በሌላ በኩል ግን ጠላቶቻቸው የብረት ማጭድ የተገጠመላቸው 900 የጦር ሠረገሎች ነበሯቸው። (መሳ. 4:1-3, 13፤ 5:6-8) ያም ቢሆን ይሖዋ ለባርቅ ከላይ የተገለጸውን መመሪያ ሰጠው። ባርቅ ምንም ጊዜ ሳያጠፋ የይሖዋን መመሪያ በሥራ ላይ አዋለ። (መሳ. 4:14-16) በታአናክ በተካሄደው በዋናው ውጊያ ላይ ድንገት የጣለው ዶፍ ዝናብ አካባቢውን አጨቅይቶት ነበር። በውጊያው ላይ ባርቅ የሲሳራን ሠራዊት 24 ኪሎ ሜትር ርቃ እስከምትገኘው እስከ ሃሮሼትጎይም ድረስ አሳደደ። በዚህ መሃል የሲሳራ ሠረገላ በጭቃ ተያዘ፤ በመሆኑም ሲሳራ፣ በአንድ ወቅት አስፈሪ ከነበረው አሁን ግን ምንም ጥቅም ከሌለው ሠረገላው ላይ ወርዶ ወደ ጻናኒም በእግሩ ሸሸ። ከዚያም ከአሳዳጆቹ ለመደበቅ ሲል የቄናዊው የሄቤር ሚስት ወደሆነችው ወደ ኢያዔል ድንኳን ሄደ፤ ኢያዔልም ሲሳራን ተቀበለችው። ሲሳራ ውጊያው ስላደከመው ድብን ያለ እንቅልፍ ወሰደው። በመሆኑም ኢያዔል እሱን ለመግደል ከወሰደችው ድፍረት የተሞላበት ወሳኝ እርምጃ ራሱን ማዳን አልቻለም። (መሳ. 4:17-21) በዚህ መንገድ እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን ድል አደረጉ! w17.04 29-30 አን. 6-8

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 30

ይሖዋ ከብሔራት ጋር ሙግት [አለው]። . . . ክፉዎችንም ለሰይፍ ይዳርጋል።—ኤር. 25:31

ከአርማጌዶን በኋላ በምድር ላይ የሚቀር ድርጅት ይኖራል? መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ በገባው ቃል መሠረት አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን፤ በእነዚህም ውስጥ ጽድቅ ይሰፍናል” ይላል። (2 ጴጥ. 3:13) አሮጌው ሰማይና ምድር ማለትም ምግባረ ብልሹ መንግሥታትም ሆኑ በእነሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ክፉው ኅብረተሰብ ይወገዳሉ። ከዚያም ‘በአዲስ ሰማያትና በአዲስ ምድር’ ይተካሉ። “አዲስ ሰማያት” የሚለው አገላለጽ አዲስ መንግሥትን የሚያመለክት ሲሆን “አዲስ ምድር” የሚለው አገላለጽ ደግሞ በዚህ መንግሥት የሚተዳደርን በምድር ላይ የሚኖር አዲስ ኅብረተሰብ ያመለክታል። በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው ይህ መንግሥት፣ ሁሉ ነገር በሥርዓት እንዲከናወን የሚፈልገውን የይሖዋ አምላክን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባርቃል። (1 ቆሮ. 14:40) “አዲስ ምድር” የተባለው በምድር ላይ የሚኖረው ኅብረተሰብም በሥርዓት የተደራጀ ይሆናል። በዚህ ኅብረተሰብ ውስጥ የተለያዩ ጉዳዮችን የሚያከናውኑ መልካም ምግባር ያላቸው ወንዶች ይሾማሉ። (መዝ. 45:16) እነዚህን ወንዶች የሚመሯቸው ክርስቶስና ከእሱ ጋር የሚገዙት 144,000ዎች ይሆናሉ። ምግባረ ብልሹ የሆኑ ድርጅቶች በሙሉ ተወግደው መልካም ምግባር ባለው አንድ ድርጅት ሲተኩ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር እስቲ አስበው! w17.04 11 አን. 8-9

ረቡዕ፣ ሐምሌ 31

ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።—ዘፍ. 2:24

አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ከሚገባቸው ቃለ መሐላዎች መካከል ሁለተኛ ቦታ የሚሰጠው የጋብቻ ቃለ መሐላው ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ጋብቻ ቅዱስ ነው። ሙሽራውና ሙሽራይቱ ቃለ መሐላ የሚፈጽሙት በአምላክና በምሥክሮች ፊት ነው። በብዙ የዓለም ክፍሎች አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሲጋቡ፣ ‘ሁለቱም በአምላክ የጋብቻ ሥርዓት ሥር በዚህች ምድር ላይ በሕይወት አብረው እስከኖሩ ድረስ’ አንዳቸው ሌላውን ለመውደድና ለመንከባከብ እንዲሁም እርስ በርስ ለመከባበር ቃል ይገባሉ። ሌሎችም ቢሆኑ በቀጥታ እነዚህን ቃላት በመጠቀም ቃል ባይገቡም በአምላክ ፊት ቃለ መሐላ ፈጽመዋል። ሙሽሮቹ በዚህ መንገድ ቃል ከገቡ በኋላ ባል እና ሚስት ተብለው ይጠራሉ፤ የአምላክ ዓላማ ጋብቻቸው የዕድሜ ልክ ጥምረት እንዲሆን ነው። (1 ቆሮ. 7:39) በመሆኑም ኢየሱስ እንዳለው “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው” ይኸውም ባልም ሆነ ሚስት አሊያም ሌላ ሰው ‘ሊለያየው አይገባም።’ ስለዚህ ትዳር የሚመሠርቱ ሰዎች፣ ፍቺን እንደ አማራጭ ሊመለከቱት እንደማይገባ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። (ማር. 10:9) እርግጥ ነው፣ ፍጹም የሆነ ትዳር የለም። ትዳር ፍጽምና የሚጎድላቸው ሁለት ሰዎች ጥምረት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ያገቡ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ “መከራ” ሊያጋጥማቸው እንደሚችል የሚናገረው ለዚህ ነው።—1 ቆሮ. 7:28፤ w17.04 7 አን. 14-15

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ