ነሐሴ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 1
እንደ እኔ ፈቃድ ሳይሆን እንደ አንተ ፈቃድ ይሁን።—ማቴ. 26:39
ጥሩ አስተማሪ ለመሆን በመጀመሪያ ጥሩ ተማሪ መሆን ያስፈልጋል። (1 ጢሞ. 4:15, 16) በመሆኑም አምላክ ተግሣጽ የመስጠት ኃላፊነት የሰጣቸው ሰዎች እነሱ ራሳቸው ለይሖዋ አመራር በፈቃደኝነት መገዛታቸውን መቀጠል አለባቸው። በዚህ መልኩ በትሕትና መገዛታቸው በሌሎች ዘንድ አክብሮት እንዲያተርፉ የሚያስችላቸው ከመሆኑም ሌላ ለሌሎች ሥልጠና ወይም እርማት በሚሰጡበት ጊዜ የመናገር ነፃነት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል። ኢየሱስ በዚህ ረገድ የተወውን ምሳሌ እስቲ እንመልከት። ኢየሱስ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ ምንጊዜም አባቱን ይታዘዝ ነበር። በተጨማሪም የነበረው ጥበብም ሆነ የሚያስተምረው ትምህርት ምንጭ አባቱ እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐ. 5:19, 30) ኢየሱስ ትሑትና ታዛዥ መሆኑ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ እሱ እንዲሳቡ አድርጓል፤ እንዲሁም ሩኅሩኅና ደግ አስተማሪ እንዲሆን አስችሎታል። (ማቴ. 11:29) የሚናገራቸው ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ቃላት፣ በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደተቀጠቀጠ ሸንበቆ ወይም ሊጠፋ እንደተቃረበ የጧፍ ክር ያሉ ሰዎችን አበረታተዋል። (ማቴ. 12:20) ኢየሱስ ትዕግሥቱን የሚፈትን ሁኔታ ባጋጠመው ጊዜም እንኳ ደግና አፍቃሪ መሆኑን አሳይቷል። ሐዋርያቱ የራስ ወዳድነት መንፈስና ከፍ ያለ ቦታ የማግኘት ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳይ ነገር ባደረጉበት ወቅት ለእነሱ እርማት የሰጠበት መንገድ ይህን በግልጽ ያሳያል።—ማር. 9:33-37፤ ሉቃስ 22:24-27፤ w18.03 26-27 አን. 15-16
ዓርብ፣ ነሐሴ 2
አሁንም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነው ጥምቀት . . . እናንተን እያዳናችሁ ነው።—1 ጴጥ. 3:21
ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ኖኅ መርከብ መሥራቱን ጠቅሷል። መርከቡ፣ ኖኅ የአምላክን ፈቃድ የመፈጸም ልባዊ ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነበር። ኖኅ ይሖዋ የሰጠውን ሥራ በታማኝነት አከናውኗል። በእርግጥም ኖኅና ቤተሰቡ እምነታቸውን በተግባር ማሳየታቸው ከጥፋት ውኃው ለመትረፍ አስችሏቸዋል። መርከቡ፣ ኖኅ በአምላክ ላይ እምነት እንዳለው የሚጠቁም ማስረጃ ነበር። በተመሳሳይም አንድ ሰው በሕዝብ ፊት መጠመቁ የሚያሳየው ነገር አለ። ጥምቀት፣ ግለሰቡ በክርስቶስ ላይ እምነት በማሳደር ራሱን ለይሖዋ መወሰኑን ያሳያል። ኖኅ እንዳደረገው ሁሉ፣ ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ደቀ መዛሙርትም አምላክ የሰጣቸውን ሥራ በታዛዥነት ያከናውናሉ። ኖኅ ከጥፋት ውኃው እንደተረፈ ሁሉ ታማኝ የሆኑ የተጠመቁ ክርስቲያኖችም ይህ ክፉ ዓለም በሚጠፋበት ጊዜ በሕይወት ይተርፋሉ። (ማር. 13:10፤ ራእይ 7:9, 10) ራስን መወሰን እንዲሁም መጠመቅ በጣም አስፈላጊ እርምጃ የሆነው ለዚህ ነው። ለመጠመቅ ዛሬ ነገ የሚል ሰው የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ሊያጣ ይችላል። w18.03 4 አን. 3-4
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 3
ሞኝነት በልጅ ልብ ውስጥ ታስሯል።—ምሳሌ 22:15
አንዳንድ ወላጆች ‘ልጄ እስካልተጠመቀ ድረስ ሊወገድ አይችልም’ ብለው ያስቡ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ያለው አስተሳሰብ አታላይ ነው፤ ለምን? (ያዕ. 1:22) ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጃቸው ተቀባይነት ባለው መንገድ ራሱን ለመወሰን የሚያስችል ብስለት ላይ ሳይደርስ እንዲጠመቅ አለመፈለጋቸው ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ልጅ እስካልተጠመቀ ድረስ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ አይደለም ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። ለምን? አንድ ሰው በይሖዋ ዘንድ ተጠያቂ የሚሆነው ስለተጠመቀ ብቻ አይደለም። አንድ ልጅ በይሖዋ ፊት ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር እስካወቀ ድረስ ከተጠያቂነት አያመልጥም። (ያዕ. 4:17) ስለሆነም ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ልጃቸውን ሳይጠመቅ እንዲቆይ አይመክሩትም። ከዚህ ይልቅ ከሕፃንነቱ ጀምሮ በማስተማር ለይሖዋ የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ልባዊ አድናቆት እንዲያዳብር ይረዱታል፤ እንዲሁም እነሱ ራሳቸው ጥሩ ምሳሌ ለመሆን ይጥራሉ። (ሉቃስ 6:40) ልጃችሁ ኃጢአት ከመፈጸም እንዲቆጠብ የሚረዳው ከሁሉ የተሻለው ነገር እንዲህ ዓይነት አድናቆት ማዳበሩ ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው አድናቆት የይሖዋን የጽድቅ ጎዳና እንዲከተል ያነሳሳዋል።—ኢሳ. 35:8፤ w18.03 11 አን. 12-13
እሁድ፣ ነሐሴ 4
ኖኅ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር።—ዘፍ. 6:9
ኖህ ከጥፋት ውኃው በኋላም ለ350 ዓመታት ያህል በዚህ አቋሙ ቀጥሏል። (ዘፍ. 9:28) እንዴት ያለ የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ ነው! እኛም የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች በመደገፍ፣ የሰይጣን ዓለም ክፍል ባለመሆንና ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት ኖኅ የተወውን የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ መከተል እንችላለን። (ማቴ. 6:33፤ ዮሐ. 15:19) እርግጥ ነው፣ የመረጥነው የሕይወት ጎዳና በዓለም ዘንድ ተቀባይነት እንደማያስገኝልን የታወቀ ነው። እንዲያውም እንደ ጋብቻና የፆታ ሥነ ምግባር ካሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አምላክ ያወጣቸውን ሕጎች ለመጠበቅ በወሰድነው ቁርጥ አቋም የተነሳ በአንዳንድ አገሮች ያሉ መገናኛ ብዙኃን መጥፎ ስም ሰጥተውናል። (ሚል. 3:17, 18) ሆኖም እኛም ልክ እንደ ኖኅ ይሖዋን እንጂ ሰዎችን አንፈራም። የዘላለም ሕይወት ሊሰጠን የሚችለው እሱ ብቻ እንደሆነ እናውቃለን። (ሉቃስ 12:4, 5) አንተስ በግለሰብ ደረጃ የኖኅን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው? ሌሎች በሚያሾፉብህ ወይም በሚነቅፉህ ጊዜም ‘ከአምላክ ጋር መሄድህን’ ትቀጥላለህ? የኢኮኖሚ ችግር ቢያጋጥምህም ይሖዋ የሚያስፈልግህን ነገር እንደሚያሟላልህ ትተማመናለህ? ኖኅ የተወውን የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ የምትከተል ከሆነ ይሖዋ እንደሚንከባከብህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—ፊልጵ. 4:6, 7፤ w18.02 4 አን. 4, 8፤ 5 አን. 9-10
ሰኞ፣ ነሐሴ 5
ዓለማዊ ሰው . . . ከአምላክ መንፈስ የሆኑትን ነገሮች አይቀበልም።—1 ቆሮ. 2:14
በዓለም ላይ ባሉ በብዙዎች ዘንድ የሚንጸባረቀው አስተሳሰብ ሥጋዊ ፍላጎትን በማርካት ላይ ያተኮረ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ “በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን ተጽዕኖ እያሳደረ ያለ መንፈስ” በማለት ገልጾታል። (ኤፌ. 2:2) ይህ መንፈስ አብዛኞቹ ሰዎች፣ የብዙኃኑን አካሄድ እንዲከተሉ ያደርጋቸዋል። በመሆኑም የሚያደርጉት ለራሳቸው ትክክል መስሎ የታያቸውን ነገር ሲሆን አምላክ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር ፈጽሞ ጥረት አያደርጉም። ዓለማዊ የሆነ ሰው ለራሱ ክብር ማግኘትና ቁሳዊ ነገሮችን ማካበት በሕይወቱ ውስጥ ከምንም ነገር በላይ ያሳስበዋል፤ በተጨማሪም መብቴ ነው ብሎ ለሚያስበው ነገር ትልቅ ቦታ ይሰጣል። ዓለማዊ የሆኑ ሰዎች “የሥጋ ሥራዎች” ተብለው የተገለጹትን ነገሮች ይፈጽማሉ። (ገላ. 5:19-21) ሥጋዊ አስተሳሰብ ከሚንጸባረቅባቸው ነገሮች መካከል ክፍፍልና አለመግባባት መፍጠር፣ ወገንተኝነት፣ እርስ በርስ በፍርድ ቤት መካሰስ፣ ለራስነት ሥልጣን አክብሮት አለማሳየት እንዲሁም ከልክ በላይ መብላትና መጠጣት ይገኙበታል። ሥጋዊ አመለካከት ያለው ሰው፣ ትክክል ያልሆነ ነገር ለማድረግ ሲፈተን በቀላሉ ይሸነፋል።—ምሳሌ 7:21, 22፤ w18.02 19 አን. 3-5
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 6
ሰዎች . . . ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ።—2 ጢሞ. 3:2, 4
በሚያስደስቱን እንቅስቃሴዎች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መካፈልም ምንም ስህተት የለውም። ይሖዋ የሚፈልገው የመናኞች ዓይነት ሕይወት እንድንመራ ወይም ደስታ በሚያስገኙ ጤናማ እንቅስቃሴዎች ከመካፈል እንድንርቅ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሂድ፣ ምግብህን በደስታ ብላ፤ ልብህም ደስ ብሎት ወይንህን ጠጣ” በማለት የአምላክን አገልጋዮች ይመክራል። (መክ. 9:7) ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:4 ሥጋዊ ደስታን በማሳደድ ተጠምደው በሕይወታቸው ውስጥ ለአምላክ ቦታ ስለማይሰጡ ሰዎች ይገልጻል። ጥቅሱ የሚናገረው ሰዎች ‘ከአምላክ ይበልጥ ሥጋዊ ደስታን እንደሚወዱ’ አለመሆኑን ልብ እንበል፤ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ሰዎች በተወሰነ መጠንም ቢሆን ለአምላክ ፍቅር እንዳላቸው የሚጠቁም ይሆን ነበር። ጳውሎስ የተናገረው ‘ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን እንደሚወዱ’ ነው። አንድ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ [ጥቅስ] ሰዎቹ በተወሰነ ደረጃ አምላክን እንደሚወዱ የሚገልጽ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክን ፈጽሞ እንደማይወዱት የሚያመለክት ነው።” ሥጋዊ ደስታን ከመጠን በላይ የሚወዱ ሰዎች ይህን ነጥብ በቁም ነገር ሊያስቡበት ይገባል! “ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ” የተባሉት ‘በዚህ ዓለም ሥጋዊ ደስታ ትኩረታቸው የተከፋፈለ’ ሰዎች እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል።—ሉቃስ 8:14፤ w18.01 25 አን. 14-15
ረቡዕ፣ ነሐሴ 7
ባሉህ ውድ ነገሮች . . . ይሖዋን አክብር።—ምሳሌ 3:9
ይሖዋ ለጋስ አምላክ ነው። ያለንን ማንኛውም ነገር ያገኘነው ከእሱ ነው። ወርቅንና ብርን ጨምሮ በምድር ላይ ያለው ማንኛውም የተፈጥሮ ሀብት የእሱ ነው፤ እነዚህን የተፈጥሮ ሀብቶች ደግሞ በምድር ላይ ያለ ሕይወት እንዲቀጥል ለማድረግ ይጠቀምባቸዋል። (መዝ. 104:13-15፤ ሐጌ 2:8) እስራኤላውያን በምድረ በዳ በተጓዙበት ወቅት ይሖዋ ለ40 ዓመታት ያህል መና እና ውኃ በማቅረብ መግቧቸዋል። (ዘፀ. 16:35፤ ነህ. 9:20, 21) ይሖዋ በነቢዩ ኤልሳዕ አማካኝነት አንዲት ታማኝ መበለት የነበራት ዘይት በተአምራዊ ሁኔታ እንዲበዛ አድርጓል። ይህ የአምላክ ስጦታ ይህች መበለት የነበረባትን ዕዳ እንድትከፍል አልፎ ተርፎም ለእሷና ለልጆቿ የሚሆን መተዳደሪያ እንድታገኝ አስችሏታል። (2 ነገ. 4:1-7) ኢየሱስም ይሖዋ በሰጠው ኃይል ተጠቅሞ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ሰዎችን መመገብ ችሏል፤ አስፈላጊ በሆነበት ወቅት ደግሞ ገንዘብ እንዲያገኙ አድርጓል። (ማቴ. 15:35-38፤ 17:27) ይሖዋ በምድር ላይ የሚገኙ ፍጥረታቱን በሕይወት ለማኖር የሚያስችል ብዙ ነገር አለው። ሆኖም አገልጋዮቹ ድርጅቱ የሚያከናውነውን ሥራ ለመደገፍ፣ ያላቸውን ቁሳዊ ነገር እንዲሰጡ ግብዣ አቅርቦላቸዋል።—ዘፀ. 36:3-7፤ w18.01 17 አን. 1-3
ሐሙስ፣ ነሐሴ 8
ይሖዋ ሆይ፣ . . . ሕይወቴን ውሰዳት።—1 ነገ. 19:4
በጥንት ዘመን የኖሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችም አቅማቸው እንደተሟጠጠ የተናገሩበት ጊዜ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ኢዮብ 7:7) ይሁንና ባጋጠማቸው ሁኔታ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ይሖዋን ብርታት እንዲሰጣቸው ጠይቀውታል። እሱም ቢሆን አላሳፈራቸውም። አምላካችን “ለደከመው ኃይል . . . ይሰጣል።” (ኢሳ. 40:29) የሚያሳዝነው ግን በዘመናችን ያሉ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች በሕይወታቸው ውስጥ ጫና ሲደራረብባቸው ‘ትንሽ ፋታ እስኪያገኙ ድረስ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን ማቆሙ’ የተሻለ እንደሆነ ሲናገሩ ይሰማል፤ እንዲህ ያለው አመለካከት ግን ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች በረከት ከማስገኘት ይልቅ ሸክም እንደሆኑ የመናገር ያህል ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች የአምላክን ቃል ማንበብ፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና በመስክ አገልግሎት መካፈል ያቆማሉ፤ ሰይጣንም የሚፈልገው ይህንኑ ነው። ዲያብሎስ፣ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ መጠመዳችን ብርታት እንደሚሰጠን ጠንቅቆ ያውቃል፤ ይህ እንዲሆን ደግሞ አይፈልግም። እንግዲያው ኃይላችሁ እንደተሟጠጠና እንደዛላችሁ በሚሰማችሁ ጊዜ ከይሖዋ አትራቁ። እንዲያውም ይበልጥ ወደ እሱ ቅረቡ፤ እሱም “ጽኑ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፤ ደግሞም ያጠነክራችኋል።”—1 ጴጥ. 5:10፤ ያዕ. 4:8፤ w18.01 7-8 አን. 2-3
ዓርብ፣ ነሐሴ 9
ይሖዋ . . . ወደ መቃብር ያወርዳል፤ ከዚያም ያወጣል።—1 ሳሙ. 2:6
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የምናገኘውን ሁለተኛውን ትንሣኤ ያከናወነው ነቢዩ ኤልሳዕ ነው። በሹነም የምትኖር አንዲት ታዋቂ እስራኤላዊት ለኤልሳዕ ታላቅ ደግነት አሳየችው። አምላክ በነቢዩ አማካኝነት በገባው ቃል መሠረት፣ ልጅ የሌላትን ይህችን ሴትና በዕድሜ የገፋውን ባለቤቷን ስለባረካቸው ልጅ መውለድ ቻሉ። የሚያሳዝነው ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ልጃቸው ሞተ። እናትየው ምን ያህል በሐዘን እንደምትደቆስ መገመት አያዳግትም። ሴትየዋ፣ ወደ ኤልሳዕ እንደምትሄድ ለባሏ ከነገረችው በኋላ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ የነበረውን ይህን ነቢይ ለማግኘት 30 ኪሎ ሜትር ያህል ተጓዘች። ነቢዩም አገልጋዩን ግያዝን ወደ ሹነም ቀድሟቸው እንዲሄድ ላከው። ሆኖም ግያዝ የሞተውን ልጅ ሊያስነሳው አልቻለም። ብዙም ሳይቆይ፣ ልጇን ያጣችው እናትና ኤልሳዕ ሹነም ደረሱ። (2 ነገ. 4:8-31) በዚያም ኤልሳዕ የልጁ አስከሬን ወዳለበት ክፍል ገብቶ መጸለይ ጀመረ። የሞተውም ልጅ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ሕያው ሆነ! እናትየው ልጇን ስታገኝ በደስታ ፈነደቀች። (2 ነገ. 4:32-37) አምላክ፣ በሹነም የነበረው ልጅ ዳግመኛ ሕያው እንዲሆን ማድረጉ ሙታንን የማስነሳት ኃይል እንዳለው የሚያረጋግጥ ነው። w17.12 4-5 አን. 7-8
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 10
ሞኝነት በልጅ ልብ ውስጥ ታስሯል።—ምሳሌ 22:15
የሞኝነት ተቃራኒ የሆነው ጥበብ የጉልምስና መገለጫ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ነው ማለት ይቻላል። የአንድ ሰው መንፈሳዊ ጉልምስና በዋነኝነት የሚለካው በዕድሜው ሳይሆን ለይሖዋ ባለው ጤናማ ፍርሃት እንዲሁም ትእዛዞቹን ለማክበር ምንጊዜም ዝግጁ በመሆኑ ነው። (መዝ. 111:10) በመንፈሳዊ ጎልማሳ ለመሆን የሚጥሩ ወጣቶች ‘በማዕበል የሚነዱ ይመስል’ በራሳቸው ምኞት አሊያም በእኩዮቻቸው ተጽዕኖ ተሸንፈው ‘ወዲያና ወዲህ አይሉም።’ (ኤፌ. 4:14) ከዚህ ይልቅ “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት” ለማሠልጠን ጥረት ያደርጋሉ። (ዕብ. 5:14) እነዚህ ወጣቶች ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ውሳኔዎች ያደርጋሉ፤ ይህም ወደ ጉልምስና እያደጉ መሆናቸውን ያሳያል። መዳን ለማግኘት እንዲህ ዓይነቱ ጥበብ አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 24:14) በመሆኑም ልጆቻችሁ የምትመሩባቸውን መሥፈርቶች በግልጽ እንዲያውቁ አድርጉ። ሕይወታችሁን የምትመሩት በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት መሥፈርቶች መሠረት እንደሆነ በንግግራችሁም ሆነ በድርጊታችሁ አሳዩ።—ሮም 2:21-23፤ w17.12 20-21 አን. 12-13
እሁድ፣ ነሐሴ 11
በውጭ ካሉት ጋር ባላችሁ ግንኙነት በጥበብ መመላለሳችሁን ቀጥሉ። ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ [እወቁ]።—ቆላ. 4:5, 6
“በዓለም ላይ ያሉትን ችግሮች የሰው ልጆች በራሳቸው መፍታት ይችላሉ” የሚለው ዓለማዊ አስተሳሰብ ብዙዎችን የሚማርከው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይህ ሐሳብ ትክክል ከሆነ ‘የሰው ልጆች የአምላክ አመራር አያስፈልጋቸውም እንዲሁም የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ’ ማለት ነው። ይህ ሐሳብ አሳማኝ እንዲመስል የሚያደርገው ሌላም ምክንያት አለ፤ ጦርነት፣ ወንጀል፣ በሽታና ድህነት እየቀነሱ እንደሆነ የሚገልጹ ጥናቶች አሉ። አንድ ዘገባ “የሰው ልጆች ሕይወት እየተሻሻለ የመጣው፣ ሰዎች ዓለማችንን የተሻለች ቦታ ለማድረግ ቆርጠው በመነሳታቸው ነው” ብሏል። ሰዎች፣ አንተ ከምታምንበት ነገር ጋር የሚጋጭ ዓለማዊ ሐሳብ ሲሰነዝሩ ከሰማህ በጉዳዩ ላይ የአምላክ ቃል ምን እንደሚል ምርምር አድርግ፤ እንዲሁም ከአንድ የጎለመሰ የእምነት ባልንጀራህ ጋር ተወያዩበት። እንዲህ ያለው ዓለማዊ አስተሳሰብ የብዙዎችን ትኩረት የሚስበው ለምን እንደሆነ፣ ስህተት የሆነበትን ምክንያትና ይህን እንዴት ማስረዳት እንደምትችል ቆም ብለህ አስብ። በእርግጥም ሁላችንም ጳውሎስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ካደረግን ዓለማዊ አስተሳሰብ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን መከላከል እንችላለን። w17.11 23 አን. 14፤ 24 አን. 17
ሰኞ፣ ነሐሴ 12
አምላክ ሆይ፣ እንደ ሌላው ሰው . . . ስላልሆንኩ አመሰግንሃለሁ።—ሉቃስ 18:11
ፈሪሳውያን ምሕረት ማሳየት ይህን ያህል የሚከብዳቸው ለምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው “ሌሎችን በንቀት ዓይን [ይመለከቱ]” ስለነበር ነው። (ሉቃስ 18:9-14) ፈሪሳውያንን ሳይሆን ይሖዋን ለመምሰል ጥረት አድርጉ። ርኅራኄና ምሕረት አሳዩ። (ቆላ. 3:13) እነዚህን ባሕርያት ማሳየት የምትችሉበት አንዱ መንገድ፣ ሌሎች እናንተን ይቅርታ መጠየቅ ከባድ እንዳይሆንባቸው በማድረግ ነው። (ሉቃስ 17:3, 4) እንደሚከተለው በማለት ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘የበደሉኝን ሰዎች ሌላው ቀርቶ በተደጋጋሚ ያስከፉኝንም እንኳ ቶሎ ይቅር እላለሁ? ከበደለኝ ወይም ከጎዳኝ ሰው ጋር ሰላም ለመፍጠር የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ?’ እንደ እውነቱ ከሆነ ይቅር ባይነት፣ ትሕትናችን የሚፈተንበት ጉዳይ ነው። ፈሪሳውያን ሌሎችን ዝቅ አድርገው ይመለከቱ ስለነበር ይህን ፈተና አላለፉም። ክርስቲያኖች ግን “ሌሎች [ከእኛ] እንደሚበልጡ በትሕትና” ልናስብና በነፃ ይቅር ልንላቸው ይገባል። (ፊልጵ. 2:3) አንተስ ይሖዋን በመምሰል ትሕትና ታሳያለህ? የበደሉህ ሰዎች አንተን ይቅርታ ለመጠየቅ ሲመጡ “መንገዱ” አመቺ እንዲሆንላቸው በሌላ አባባል ይቅርታ መጠየቅ ቀላል እንዲሆንላቸው አድርግ። ምሕረት ለማሳየት ፈጣን ሁን፤ እንዲሁም ለቁጣ አትቸኩል።—መክ. 7:8, 9፤ w17.11 14-15 አን. 6-8
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 13
ለአምላካችን የውዳሴ መዝሙር መዘመር ጥሩ ነው።—መዝ. 147:1
የሌሎች ሰዎችን ድምፅ ከራስህ ድምፅ ጋር ስታወዳድር ብቃት እንደሌለህ ሊሰማህ ይችላል። ሆኖም ይህ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ከመዘመር ወደኋላ እንድትል ሊያደርግህ አይገባም። ሁላችንም ለይሖዋ የመዘመር ኃላፊነት አለብን። ስለዚህ የመዝሙር መጽሐፍህን ከፍ አድርገህ በመያዝና ራስህን ቀና በማድረግ ከልብ በመነጨ ስሜት ዘምር! (ዕዝራ 3:11) በአሁኑ ጊዜ በብዙ የስብሰባ አዳራሾቻችን ውስጥ የመዝሙሮቹ ግጥሞች በስክሪኖች ላይ ይታያሉ፤ ይህም ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለመዘመር ይረዳናል። በተጨማሪም ለሽማግሌዎች የሚዘጋጀው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት፣ የመንግሥቱን መዝሙሮች መዘመርን የሚያካትት መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ይህም ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ በመዘመር ረገድ ቅድሚያውን መውሰድ እንዳለባቸው ይጠቁማል። አንዳንዶች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዳይዘምሩ እንቅፋት ከሚሆኑባቸው ነገሮች አንዱ ፍርሃት ነው። ‘ድምፄ ለጆሮ ደስ የማይል ሊሆን ይችላል’ ብለው ይፈሩ ይሆናል። ይሁንና በንግግራችን “ሁላችንም ብዙ ጊዜ [እንደምንሰናከል]” እናስታውስ። (ያዕ. 3:2) ታዲያ በዚህ ምክንያት ከመናገር እንቆጠባለን? እንግዲያው በጣም ጥሩ የሚባል ድምፅ ባይኖረንም እንኳ ይሖዋን በመዝሙር ከማወደስ ወደኋላ ልንል አይገባም። w17.11 4-5 አን. 9-10
ረቡዕ፣ ነሐሴ 14
የአምላካችሁን የይሖዋን ቃል ብትሰሙ ይህ ይሆናል።—ዘካ. 6:15
ዘካርያስ ሰባተኛውን ራእይ ካየ በኋላ ብዙ ነገር ሳያሳስበው አልቀረም። ይሖዋ ሐቀኛ ያልሆኑ ሰዎችን በፈጸሙት ክፉ ድርጊት የተነሳ እንደሚቀጣቸው ዋስትና ሰጥቶ ነበር። ይሖዋ የገባው ይህ ቃል ዘካርያስን አበረታቶት መሆን አለበት። ሆኖም ምንም የተለወጠ ነገር የለም። ሰዎቹ አሁንም ሐቀኝነት የጎደለው ነገር ማድረጋቸውንና ሌሎች ክፉ ድርጊቶች መፈጸማቸውን አላቆሙም። በኢየሩሳሌም የሚገኘው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ግንባታም ገና ብዙ ይቀረዋል። ለመሆኑ አይሁዳውያኑ ይሖዋ የሰጣቸውን ሥራ እንዲህ በፍጥነት እርግፍ አድርገው የተዉት ለምን ይሆን? ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱት የግል ጉዳያቸውን ለማከናወን ብለው ነበር? ይሖዋ ሕዝቡ በዚያ ወቅት ምን እንደሚያስፈልገው ያውቅ ነበር። አምላክ ለዘካርያስ በገለጠለት የመጨረሻ ራእይ አማካኝነት ለአይሁዳውያኑ ያለውን ፍቅር እንዲሁም እስከዚያ ጊዜ ድረስ ላከናወኑት ነገር ያለውን አድናቆት ገልጿል፤ በተጨማሪም ሕዝቦቹ ወደ ሥራው ከተመለሱ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። ይሖዋ ከቤተ መቅደሱ ዳግመኛ መገንባት ጋር በተያያዘም በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በመናገር ቃል ገብቶላቸዋል። w17.10 26 አን. 1፤ 27 አን. 5
ሐሙስ፣ ነሐሴ 15
ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ለተግባር እንድትነሳሱ በማድረግ ኃይል የሚሰጣችሁ አምላክ ነው።—ፊልጵ. 2:13
ተጨማሪ ኃላፊነት ለመቀበል ፈቃደኞች የሆኑ ደፋር ወንዶች ለጉባኤው በረከት ናቸው። (1 ጢሞ. 3:1) አንዳንድ ወንድሞች ግን ኃላፊነት ላይ ለመድረስ ከመጣጣር ወደኋላ ሊሉ ይችላሉ። ምናልባትም አንዳንዶች ከዚህ በፊት በፈጸሙት ኃጢአት ምክንያት የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆነው ለማገልገል ብቁ እንዳልሆኑ ሊሰማቸው ይችላል። ሌሎች ደግሞ አንድን ኃላፊነት ለመወጣት ችሎታው እንደሌላቸው ይሰማቸው ይሆናል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ይሖዋ ድፍረት እንድታዳብር ሊረዳህ ይችላል። (ፊልጵ. 4:13) ሙሴም የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ብቁ እንዳልሆነ የተሰማው ወቅት እንደነበር አስታውስ። (ዘፀ. 3:11) ይሁንና ይሖዋ የረዳው ሲሆን ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስፈልገውን ድፍረት በጊዜ ሂደት ማዳበር ችሏል። አንድ የተጠመቀ ወንድምም የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ልባዊ ጸሎት በማቅረብና በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ተመሳሳይ ድፍረት ማዳበር ይችላል። ድፍረት ስላሳዩ ሰዎች በሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ላይ ማሰላሰሉም ሊረዳው ይችላል። በተጨማሪም ሽማግሌዎች እንዲያሠለጥኑት በትሕትና መጠየቁና በተመደበበት ቦታ ሁሉ ለማገልገል ራሱን ማቅረቡ ጠቃሚ ነው። w17.09 32 አን. 19
ዓርብ፣ ነሐሴ 16
የአምላካችን ቃል . . . ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።—ኢሳ. 40:8
በዘመናችን ያሉ ክርስቲያኖች የሰብዓ ሊቃናት ትርጉምን፣ የዊክሊፍ መጽሐፍ ቅዱስንና ኪንግ ጄምስ ቨርዥንን ጨምሮ የትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በቀጥታ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተዘጋጀ እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። ይሁንና የእነዚህን ትርጉሞች ጨምሮ ለሕትመት የበቁ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ታሪክ ስንመለከት አንድ ሐቅ እንገነዘባለን፦ ይሖዋ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ቃሉ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። ታዲያ ይህን ማወቅህ ይሖዋ ቃል የገባቸው ሌሎች ተስፋዎችም አንድም ሳይቀር እንደሚፈጸሙ ያለህን እምነት አያጠናክረውም? (ኢያሱ 23:14) መጽሐፍ ቅዱስ ለዘመናት ጸንቶ የኖረው እንዴት እንደሆነ መመርመራችን እምነታችን እንዲጠናከርና ለይሖዋ ያለን ፍቅር እንዲያድግ ያደርጋል። አምላክ መጀመሪያውኑም ቢሆን ቃሉን የሰጠን ለምንድን ነው? ቃሉ ጸንቶ እንደሚኖር ማረጋገጫ የሰጠንስ ለምንድን ነው? ይህን ያደረገው ስለሚወደንና የሚጠቅመንን ነገር ሊያስተምረን ስለሚፈልግ ነው። (ኢሳ. 48:17, 18) ይሖዋ ያሳየን ፍቅር እኛም እሱን እንድንወደውና ትእዛዛቱን እንድንፈጽም ሊያነሳሳን ይገባል።—1 ዮሐ. 4:19፤ 5:3፤ w17.09 21-22 አን. 13-14
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 17
አባትህንና እናትህን አክብር።—ኤፌ. 6:2
የማያምን የትዳር ጓደኛ ካላችሁ ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ እንዲታዘዙ ልጆችን ከማሠልጠን ጋር በተያያዘ ተፈታታኝ ሁኔታ ሊያጋጥማችሁ ይችላል። የትዳር ጓደኛችሁን በማክበር ምሳሌ ሁኑ። የትዳር ጓደኛችሁ ባሉት ጥሩ ጎኖች ላይ ትኩረት አድርጉ፤ እንዲሁም ለትዳር ጓደኛችሁ ያላችሁን አድናቆት ግለጹ። በልጆቻችሁ ፊት ስለ ትዳር ጓደኛችሁ አሉታዊ ነገሮችን ከመናገር ተቆጠቡ። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ሰው ይሖዋን ለማምለክም ሆነ ላለማምለክ የመምረጥ ነፃነት እንዳለው አስረዷቸው። ልጆቹ የሚያሳዩት መልካም ምግባር የማያምነው የትዳር ጓደኛችሁ ወደ እውነተኛው አምልኮ እንዲሳብ ሊያደርግ ይችላል። አንዳንድ ባሎች ክርስቲያን ሚስቶቻቸው ለልጆቹ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያስተምሩ ወይም ልጆቹን ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይዘው እንዳይሄዱ ሊከለክሉ ይችላሉ። ያም ቢሆን አንዲት ክርስቲያን ሚስት ለልጆቿ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማስተማር የቻለችውን ሁሉ ጥረት ማድረግ ይኖርባታል። (ሥራ 16:1፤ 2 ጢሞ. 3:14, 15) በዚህ ጊዜ እህት የባሏን ውሳኔ ብታከብርም ያገኘችውን አጋጣሚ ተጠቅማ ለልጆቿ ስለምታምንበት ነገር ለመናገር ጥረት ታደርጋለች፤ እንዲህ በማድረግ ልጆቿ ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው ማሠልጠንና ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ መርዳት ትችላለች።—ሥራ 4:19, 20፤ w17.10 14 አን. 9-10
እሁድ፣ ነሐሴ 18
የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ።—ኤፌ. 5:1
ሰዎች የተፈጠሩት በአምላክ መልክ ነው። ይሖዋ ሩኅሩኅ በመሆኑ የሰው ልጆችም በተፈጥሯቸው ርኅራኄ የማሳየት ችሎታ አላቸው። እውነተኛውን አምላክ የማያውቁ ሰዎችም ጭምር የሌሎች ደህንነት ያሳስባቸዋል። (ዘፍ. 1:27) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ ርኅራኄ ስላሳዩ ሰዎች የሚናገሩ በርካታ ዘገባዎች ይገኛሉ። በሰለሞን ፊት ቆመው የልጁን እውነተኛ ወላጅ ማንነት በተመለከተ ስለተካሰሱ ሁለት ዝሙት አዳሪዎች የሚናገረውን ዘገባ ለማሰብ ሞክር። ሰለሞን ትክክለኛዋን እናት ለማወቅ ሲል ልጁ ለሁለት እንዲሰነጠቅ ትእዛዝ ሰጠ፤ በዚህ ወቅት የልጁ እናት አንጀቷ ተላወሰ። ይህም ከባድ እርምጃ እንድትወስድ ማለትም ልጇን ለሌላኛዋ ሴት ለመስጠት እንድትስማማ አድርጓታል። (1 ነገ. 3:23-27) የሕፃኑን የሙሴን ሕይወት ያተረፈችውን የፈርዖንን ልጅ ታሪክም መጥቀስ እንችላለን። ሙሴ የዕብራውያን ልጅ እንደሆነና ሊገደል እንደሚገባው የምታውቅ ቢሆንም ‘ለሕፃኑ ስላዘነችለት’ ወይም ስለራራችለት እንደ ራሷ ልጅ አድርጋ ልታሳድገው ወሰነች።—ዘፀ. 2:5, 6፤ w17.09 8-9 አን. 2-3
ሰኞ፣ ነሐሴ 19
ይሖዋ . . . እናንተን [ታግሷል]።—2 ጴጥ. 3:9
ትሕትና ከእያንዳንዱ የአምላክ አገልጋይ የሚጠበቅ ብቃት ሲሆን ይህን ባሕርይ ማዳበር ብዙ በረከት ያስገኛል። (ምሳሌ 22:4) ትሕትና በጉባኤ ውስጥ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ያደርጋል። በተጨማሪም ትሕትናን ማዳበራችን የአምላክን ጸጋ ለማግኘት ያስችለናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል፦ “እርስ በርስ ባላችሁ ግንኙነት ሁላችሁም ትሕትናን ልበሱ፤ ምክንያቱም አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።” (1 ጴጥ. 5:5) በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ገርና ታጋሽ የሆኑ ሰዎች ደካማ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠራሉ። ይህ አስተሳሰብ ምንኛ ከእውነት የራቀ ነው! የእነዚህ ግሩም ባሕርያት ምንጭ በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ከሁሉ የላቀ ኃይል ያለው አካል ነው። ይሖዋ አምላክ ገርነትን እና ትዕግሥትን በማንጸባረቅ ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ነው። አብርሃምና ሎጥ ጥያቄ ባቀረቡለት ወቅት ወኪሎቹ በሆኑት መላእክት አማካኝነት ምላሽ የሰጠበትን መንገድ እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። (ዘፍ. 18:22-33፤ 19:18-21) በተጨማሪም ይሖዋ ወላዋይ የሆነውን የእስራኤልን ብሔር ከ1,500 ለሚበልጡ ዓመታት ታግሷል።—ሕዝ. 33:11፤ w17.08 25 አን. 13-14
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 20
ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።—ፊልጵ. 4:7
ወደ ይሖዋ ከጸለይን የአምላክን ሰላም እናገኛለን። ይሁንና የአምላክ ሰላም “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ” እንደሆነ ልብ በል። ይህ ምን ማለት ነው? አንዳንድ ተርጓሚዎች ይህን አገላለጽ “ከምናልመው ሁሉ በላይ” አሊያም “ከሰዎች ግምት ሁሉ የላቀ” ብለው ተርጉመውታል። ጳውሎስ “የአምላክ ሰላም” በአእምሯችን ልናስበው ከምንችለው ሁሉ በላይ አስገራሚ እንደሆነ መናገሩ ነበር። በመሆኑም በሰብዓዊ አመለካከት ሲታይ ችግሮቻችንን መወጣት የምንችልበት ምንም መንገድ የሌለ ቢመስልም ይሖዋ ግን መውጫ መንገዱን የሚያውቅ ከመሆኑም ሌላ ፈጽሞ ያልጠበቅነውን ነገር ሊያደርግ ይችላል። (2 ጴጥ. 2:9) በሕይወታችን ውስጥ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም ‘የአምላክን ሰላም’ ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? ከአምላካችን ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ጥሩ ዝምድና ጠብቀን በመኖር ነው። እንዲህ ያለ ዝምድና ሊኖረን የሚችለው ለእኛ ሲል ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በሰጠው “በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት” ብቻ ነው። የቤዛው ዝግጅት አባታችን ይሖዋ ካከናወናቸው አስገራሚ ነገሮች መካከል አንዱ ነው። ይሖዋ በቤዛው አማካኝነት ኃጢአታችንን ይሸፍንልናል፤ ይህም ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረንና ወደ እሱ እንድንቀርብ ያስችለናል።—ዮሐ. 14:6፤ ያዕ. 4:8፤ 1 ጴጥ. 3:21፤ w17.08 10 አን. 7፤ 12 አን. 15
ረቡዕ፣ ነሐሴ 21
ልብ የራሱን ምሬት ያውቃል፤ ደስታውንም ሌላ ሰው ሊጋራው አይችልም።—ምሳሌ 14:10
አንዳንድ ጊዜ፣ የሚወደውን ሰው በሞት ያጣ ሰው የሚሰማውን የስሜት ሥቃይ ሙሉ በሙሉ የሚያውቀው ግለሰቡ ብቻ ሊሆን ይችላል፤ እንዲሁም ውስጡ የታመቀውን ስሜት በቃላት መግለጽ ይከብደው ይሆናል። ሐዘን የደረሰበት ሰው ሐሳቡን ቢገልጽም እንኳ ምን ለማለት እንደፈለገ መረዳት ቀላል የማይሆንባቸው ጊዜያት አሉ። በሐዘን የተዋጠን ሰው ለማጽናናት ምን ማለት እንዳለብን ማወቅ ከባድ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው። አብዛኛውን ጊዜ፣ ያዘኑ ሰዎችን ማጽናናት የምትችሉበት ዋነኛው መንገድ “ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ነው። (ሮም 12:15) ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ቀርባችሁ ማነጋገር ከከበዳችሁ በካርድ፣ በኢሜይል፣ በሞባይል አጭር መልእክት ወይም በደብዳቤ አማካኝነት የሚያጽናኑ ሐሳቦችን ጽፋችሁ ልትልኩላቸው ትችላላችሁ። አንድ የሚያጽናና ጥቅስ፣ ከሞተው ግለሰብ ጋር በተያያዘ የምታደንቁትን ወይም የምታስታውሱትን ባሕርይ አሊያም አብራችሁ ያሳለፋችሁትን አስደሳች ጊዜ ጠቅሳችሁ መጻፍ ትችላላችሁ። በተጨማሪም ሐዘን ከደረሰበት የእምነት ባልንጀራችሁ ጋር አብራችሁ ስትሆኑ አልፎ ተርፎም እሱ በሌለበት ስለ እሱ ጠቅሳችሁ መጸለያችሁ ትልቅ ጥቅም እንዳለው አትርሱ። w17.07 14-16 አን. 13-16
ሐሙስ፣ ነሐሴ 22
አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።—ማቴ. 19:6
የትዳር ሕይወት ከጠበቃችሁት በላይ ተፈታታኝ ቢሆንባችሁ አልፎ ተርፎም ከባድ ችግሮች ቢያጋጥሟችሁ ምን ታደርጋላችሁ? ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረውን ግንኙነት መለስ ብላችሁ አስቡ። ይሖዋ ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር እንደ ባል ሆኖላቸው እንደነበር ተናግሯል። (ኢሳ. 54:5፤ 62:4) ይሁንና እስራኤላውያን ይሖዋን በተደጋጋሚ አሳዝነውት ነበር። ከእነሱ ጋር የነበረው ግንኙነት ሰላም እንዳጣ ትዳር ሆኖ ነበር። ሆኖም ተስፋ ቆርጦ ይህን “ትዳር” ለማፍረስ አልቸኮለም። በተደጋጋሚ ምሕረት ያሳያቸው ሲሆን ከእነሱ ጋር ለገባው ቃል ኪዳን ታማኝ ሆኗል። (መዝ. 106:43-45) ይሖዋ እንዲህ ያለ ታማኝ ፍቅር ማሳየቱ ይበልጥ ወደ እሱ እንድንቀርብ አያነሳሳንም? የይሖዋን መንገድ የሚወዱ ባለትዳሮችም እሱን ለመምሰል ጥረት ያደርጋሉ። የትዳር ሕይወት ተፈታታኝ ሲሆንባቸው ከትዳሩ ለመገላገል ሲሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ መንገዶችን አይፈላልጉም። ይሖዋ እንዳጣመራቸውና እርስ በርስ ‘ተጣብቀው’ እንዲኖሩ እንደሚፈልግ ይገነዘባሉ። አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን ፈቶ ሌላ ሰው ማግባት የሚችልበት ብቸኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት የፆታ ብልግና ነው። (ማቴ. 19:5, 9) ክርስቲያኖች ትዳራቸው ስኬታማ እንዲሆን የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት በማድረግ የይሖዋን የጽድቅ አገዛዝ እንደሚደግፉ ማሳየት ይችላሉ። w17.06 31 አን. 17-18
ዓርብ፣ ነሐሴ 23
ዓይኖቻችሁ [ይገለጣሉ] . . . እንደ አምላክ [ትሆናላችሁ]።—ዘፍ. 3:5
ሰይጣን ዲያብሎስ በይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ አንስቷል። ሰይጣን ‘የአምላክ አገዛዝ ትክክል አይደለም፤ ፍጥረታቱንም ጥሩ ነገር ይነፍጋቸዋል’ የሚል ክስ ሰንዝሯል። እንደ ዲያብሎስ አስተሳሰብ ከሆነ ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩ የተሻለ ሕይወት መምራትና ይበልጥ ደስተኞች መሆን ይችላሉ። (ዘፍ. 3:1-4) በተጨማሪም ሰይጣን ‘የትኛውም ሰው ከባድ ችግር ቢያጋጥመው የይሖዋን አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረኝ ይላል’ ያለ ያህል ነው። (ኢዮብ 2:4, 5) ይሖዋ ሰዎች ከአምላክ የጽድቅ አገዛዝ ቢያፈነግጡ ሕይወታቸው ምን ሊመስል እንደሚችል እንዲታይ ሲል የተወሰነ ጊዜ ፈቅዷል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ የሰይጣን ክሶች ውሸት እንደሆኑ ያውቃል። ታዲያ አምላክ፣ ሰይጣን ለክሱ ማስረጃ ማቅረብ እንዲችል ጊዜ የሰጠውና ይህ ጉዳይ እልባት ሳያገኝ እንዲቆይ ያደረገው ለምንድን ነው? ጥያቄው የማሰብ ችሎታ ያላቸውን ፍጥረታት ሁሉ የሚመለከት ስለሆነ ነው። (መዝ. 83:18) የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት የይሖዋን አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረን እንዳሉ አስታውስ፤ ከእነሱ በኋላ የኖሩ ብዙ ሰዎችም እንዲሁ አድርገዋል። ይህም አንዳንዶች ሰይጣን ያነሳው ክስ ትክክል ሳይሆን አይቀርም ብለው እንዲያስቡ ሊያደርግ ይችላል። w17.06 22-23 አን. 3-4
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 24
ሂዱና . . . ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ።—ማቴ. 28:19
ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ጥሩ የሥራ ልማድ፣ ከሌሎች ጋር የመግባባት ችሎታ፣ በራስ የመተማመን መንፈስና ዘዴኝነትን እንድታዳብር የሚረዳ ሥልጠና ይሰጥሃል። (ምሳሌ 21:5፤ 2 ጢሞ. 2:24 ግርጌ) ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ይበልጥ አስደሳች የሚያደርገው ሌላም ምክንያት አለ፤ ለእምነትህ መሠረት የሆኑህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በደንብ ማወቅ እንድትችል ይረዳሃል። በተጨማሪም ከይሖዋ ጋር አብረህ መሥራትን ትማራለህ። (1 ቆሮ. 3:9) በምታገለግልበት ክልል ውስጥ ምሥራቹን የሚቀበሉ ሰዎች ጥቂት ቢሆኑም እንኳ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መደሰት ትችላለህ። ደቀ መዛሙርት ማድረግ በቡድን የምናከናውነው ሥራ ነው። ቅን የሆኑ ሰዎችን በመፈለጉ ሥራ መላው ጉባኤ ይካፈላል። ከጊዜ በኋላ ደቀ መዝሙር የሆነውን ሰው ያገኙት አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ብቻ ቢሆኑም እንኳ፣ ቅን ልብ ያላቸውን በመፈለጉ ሥራ መላው ጉባኤ ስለተሳተፈ ሁሉም የደስታው ተካፋዮች ይሆናሉ። ብራንደንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ብራንደን፣ ሰዎች ምሥራቹን በማይቀበሉበት ክልል ውስጥ ለዘጠኝ ዓመት ያህል በአቅኚነት አገልግሏል። እንዲህ ብሏል፦ “ባለሁበት ክልል ውስጥ ያስጠናኋቸው ሰዎች እድገት አድርገው ሲጠመቁ የማየት አጋጣሚ ባላገኝም ሌሎች በዚህ ረገድ ሲሳካላቸው አይቻለሁ። ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በተሟላ ሁኔታ ለመካፈል ዕቅድ በማውጣቴ ደስተኛ ነኝ።”—መክ. 11:6፤ w17.07 23 አን. 7፤ 24 አን. 9-10
እሁድ፣ ነሐሴ 25
ዳግመኛም በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።—1 ሳሙ. 1:18
ሐና መሃን የነበረች ሲሆን ጣውንቷ ፍናና ግን ብዙ ልጆች ነበሯት። (1 ሳሙ. 1:4-7) በዚህ ምክንያት ፍናና “በየዓመቱ” ሐናን ታበሳጫት ነበር። ይህም በሐና ላይ ከፍተኛ መከራና ሐዘን አስከትሎባት ነበር። ጉዳዩን ለይሖዋ በመግለጽ እፎይታ እንዲሰጣት ለመነች። (1 ሳሙ. 1:12) ይሖዋ ልጅ እንደሚሰጣት አለዚያም በሌላ መንገድ እንደሚያጽናናት ተማምና ነበር። እኛም ፍጽምና የጎደለን እንዲሁም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው በዚህ ሥርዓት ውስጥ የምንኖር እንደመሆናችን መጠን ፈተናና መከራ ይደርስብናል። (1 ዮሐ. 5:19) ይሁንና ይሖዋ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” መሆኑን ማወቃችን ምንኛ የሚያስደስት ነው! (2 ቆሮ. 1:3) የሚደርሱብንን ፈተናዎች ወይም መከራዎች ለመቋቋም የሚያስችለንን እርዳታ የምናገኝበት አንዱ መንገድ ጸሎት ነው። ሐና ልቧን አፍስሳ ወደ ይሖዋ ጸልያለች። እኛም በተመሳሳይ፣ መከራ በሚደርስብን ጊዜ የገጠመንን ችግር በጸሎታችን ላይ እንዲሁ ከመጥቀስ ያለፈ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። ለይሖዋ ምልጃ ማቅረብ ይኸውም ስሜታችንን ሁሉ አውጥተን በመግለጽ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ይገባናል።—ፊልጵ. 4:6, 7፤ w17.06 6 አን. 10-11
ሰኞ፣ ነሐሴ 26
የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ ከእነዚህ አስበልጠህ ትወደኛለህ?—ዮሐ. 21:15
ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ዓሣ ለማጥመድ ቢሞክሩም አንድም ዓሣ እንዳልያዙ ስላወቀ “‘መረቡን ከጀልባዋ በስተ ቀኝ ጣሉት፤ ዓሣ ታገኛላችሁ’ አላቸው። እነሱም መረቡን ጣሉ፤ ከዓሣውም ብዛት የተነሳ መረቡን መጎተት አቃታቸው።” (ዮሐ. 21:1-6) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ቁርስ ካበላቸው በኋላ ወደ ስምዖን ጴጥሮስ ዘወር ብሎ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ጥያቄ ጠየቀው። ኢየሱስ “ከእነዚህ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? ጴጥሮስ ዓሣ የማጥመድ ሥራውን በጣም ይወደው ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ይበልጥ የሚወደው ማንን እንደሆነ ጴጥሮስን እየጠየቀው ይመስላል። ጴጥሮስ፣ ለዓሣዎቹና ዓሣ ለማጥመድ ሥራው የነበረው ፍቅር ከኢየሱስና እሱ ካስተማራቸው ነገሮች ይበልጥበት ይሆን? ጴጥሮስ “አዎ፣ ጌታ ሆይ፣ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” ሲል መልሷል። (ዮሐ. 21:15) ደግሞም ጴጥሮስ ከተናገረው ነገር ጋር በሚስማማ መንገድ ኖሯል። ከዚያ ጊዜ አንስቶ፣ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በመጠመድና በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንደ ዓምድ በመሆን ክርስቶስን እንደሚወደው አሳይቷል። w17.05 22 አን. 1-2
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 27
ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?—ዕብ. 13:6
ጳውሎስ በይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ ላይ ጠንካራ እምነት የነበረው መሆኑ በሕይወቱ ውስጥ ችግሮች ሲያጋጥሙት እጅ እንዳይሰጥ ረድቶታል። ያጋጠሙት አስቸጋሪ ሁኔታዎች በይሖዋ እንዳይተማመን አላደረጉትም። ይህን ለማድረግ የሚያስችል ብርታት የሰጠው ምንድን ነው? ‘በሚደርስብን መከራ ሁሉ በሚያጽናናን’ እና “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” በሆነው በይሖዋ መታመኑ ነው። (2 ቆሮ. 1:3, 4) በጸሎት አማካኝነት ለይሖዋ ሐሳባችንን መግለጻችን ከእሱ ጋር የቀረበ ወዳጅነት እንዲኖረን የሚያስችል መሠረት ነው። (መዝ. 86:3፤ 1 ተሰ. 5:17፤ ሮም 12:12) ጊዜ መድበን ለይሖዋ የውስጣችንን አውጥተን የምንነግረውና ስሜታችንን የምንገልጽለት ከሆነ “ጸሎት ሰሚ” ወደሆነው የሰማዩ አባታችን ይበልጥ መቅረባችን አይቀርም። (መዝ. 65:2) በተጨማሪም ይሖዋ ለጸሎታችን ምላሽ እንደሰጠን ስንመለከት ለእሱ ያለን ፍቅር ያድጋል። “ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ . . . ቅርብ” መሆኑን ይበልጥ እየተገነዘብን እንሄዳለን። (መዝ. 145:18) ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ በሚያደርግልን ድጋፍ ላይ መተማመናችን ደግሞ የሚያጋጥሙንን ሌሎች የእምነት ፈተናዎች ለመወጣት ይረዳናል። w17.05 19 አን. 9-10
ረቡዕ፣ ነሐሴ 28
ይሖዋ . . . የሚያየው ልብን ነው።—1 ሳሙ. 16:7
ሽማግሌዎች፣ ምክንያቱ ግልጽ ያልሆነልህ ምናልባትም የማትስማማበት አንድ ውሳኔ ቢያስተላልፉ ምን ታደርጋለህ? እንደዚህ ያለው ሁኔታ በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ያለን እምነት እንዲፈተን ሊያደርግ ይችላል። እንዲህ ያለ ፈተና ቢያጋጥምህ ትሕትና ጥበቃ የሚሆንልህ እንዴት ነው? ሁለት መንገዶችን እንመልከት። በመጀመሪያ፣ ትሕትና የማናውቀው ነገር ሊኖር እንደሚችል አምነን እንድንቀበል ይረዳናል። ስለ አንድ ሁኔታ በደንብ እንደምናውቅ ቢሰማንም እንኳ የሰዎችን ልብ ማንበብ የሚችለው ይሖዋ ብቻ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ይህን እውነታ መገንዘባችን ትሑት እንድንሆን፣ የማናውቀው ነገር ሊኖር እንደሚችል አምነን እንድንቀበል እንዲሁም አመለካከታችንን እንድናስተካክል ያነሳሳናል። ሁለተኛ፣ ፍትሕ የጎደለው ነገር በሚፈጸምብን ወይም በምንመለከትበት ጊዜ ትሑት መሆናችን፣ ይሖዋ ነገሮችን ለማስተካከል እርምጃ እስኪወስድ በትዕግሥት እንድንጠብቅና ታዛዥ እንድንሆን ይረዳናል። ጠቢቡ ሰለሞን “ክፉ ሰው . . . የኋላ ኋላ መልካም አይሆንለትም፤ . . . የሕይወት ዘመኑንም ማራዘም አይችልም” ብሏል። (መክ. 8:12, 13) በእርግጥም ትሑት ከሆንን ራሳችንንም ሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሁሉ እንጠቅማለን።—1 ጴጥ. 5:5፤ w17.04 25-26 አን. 10-11
ሐሙስ፣ ነሐሴ 29
በመሠረቱ እኔ ከዕብራውያን ምድር ወደዚህ የመጣሁት ተገድጄ ነው፤ አሁንም ቢሆን እዚህ እስር ቤት ውስጥ የጣሉኝ ያለምንም ጥፋት ነው።—ዘፍ. 40:15
ዮሴፍ ግፍ እንደተፈጸመበት ምንም ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም ዮሴፍ የታሰረው ያለጥፋቱ እንደሆነ ተናግሯል። በመሆኑም ጉዳዩን ለፈርዖን እንዲነግርለት የመጠጥ አሳላፊውን ጠየቀው። ዓላማው ምን ነበር? “ከዚህ እስር ቤት እንዲያስፈታኝም ስለ እኔ ለፈርዖን ንገረው” ብሎታል። (ዘፍ. 40:14) ዮሴፍ ከተናገረው ነገር መመልከት እንደሚቻለው፣ ያለበትን ሁኔታ ዝም ብሎ ከመቀበል ይልቅ ሁኔታውን ለማስተካከል እርምጃ ወስዷል። ይህ ወጣት ብዙ በደል ተፈጽሞበታል። ዮሴፍ፣ የመጠጥ አሳላፊው እርዳታ ሊያደርግለት እንደሚችል ስለተሰማው የደረሰበትን በደል በግልጽ አስረድቶታል። ይሁን እንጂ ዮሴፍ፣ ወደ ባዕድ አገር የሸጡት ወንድሞቹ መሆናቸውን ለማንም ሰው ሌላው ቀርቶ ለፈርዖን እንኳ እንደተናገረ የሚገልጽ ሐሳብ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አይገኝም። እንዲያውም የዮሴፍ ወንድሞች ወደ ግብፅ መጥተው ከዮሴፍ ጋር ከታረቁ በኋላ ፈርዖን ጥሩ አድርጎ ተቀብሏቸዋል፤ በተጨማሪም “በግብፅ ምድር ያለ ምርጥ ነገር ሁሉ የእናንተው ነው” በማለት በዚያ እንዲኖሩ ጋብዟቸዋል።—ዘፍ. 45:16-20፤ w17.04 20-21 አን. 12-13
ዓርብ፣ ነሐሴ 30
የአምላክ ብልጽግና፣ ጥበብና እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው!—ሮም 11:33
ይሖዋ ሉዓላዊ ገዢ የመሆን መብት አለው የምንልበት አንዱ ምክንያት ጽንፈ ዓለሙን ለማስተዳደር የሚያስችል እውቀትና ጥበብ ስላለው ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ልጁ ወደ ምድር በመጣበት ወቅት ሐኪሞች ሊያድኗቸው ያልቻሏቸውን ሕመምተኞች እንዲፈውስ አስችሎታል። (ማቴ. 4:23, 24፤ ማር. 5:25-29) ይህ ለእኛ ተአምር ቢሆንም ለይሖዋ ግን ተአምር አይደለም። የሰውነታችንን አሠራር በሚገባ ያውቃል፤ እንዲሁም የደረሰብንን ማንኛውንም ዓይነት ጉዳት መፈወስ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ የሞቱትን የማስነሳትና የተፈጥሮ አደጋዎች እንዳይደርሱ የመከላከል ችሎታ አለው። በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም የእርስ በርስ ግጭቶችንም ሆነ በብሔራት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ማስወገድ አልቻለም። ዓለም አቀፍ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ጥበብ ያለው ይሖዋ ብቻ ነው። (ኢሳ. 2:3, 4፤ 54:13) እኛም ስለ ይሖዋ እውቀትና ጥበብ ይበልጥ ባወቅን መጠን በመንፈስ አነሳሽነት በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ እንደጻፈው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት ስሜት ይሰማናል። w17.06 28 አን. 6-7
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 31
አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።—ማር. 10:9
በዓለም ላይ ያሉ በርካታ ሰዎች በትዳራቸው ውስጥ ችግር ሲያጋጥማቸው ችግሩን ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ የትዳር ጓደኛቸውን ትተው ይሄዳሉ። ክርስቲያኖች ግን እንዲህ ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው አይገባም። (1 ቆሮ. 7:27) የጋብቻ ቃለ መሐላን ማፍረስ አምላክን ከመዋሸት ተለይቶ አይታይም፤ አምላክ ደግሞ ውሸታሞችን ይጠላል! (ዘሌ. 19:12፤ ምሳሌ 6:16-19) ይሖዋ፣ የትዳር ጓደኛን በማታለል የሚፈጸም ፍቺንም ይጠላል። (ሚል. 2:13-16) ኢየሱስ እንደገለጸው በቅዱሳን መጻሕፍት መሠረት ፍቺ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው፣ ታማኝ የሆነው የትዳር አጋር፣ ምንዝር የፈጸመ የትዳር ጓደኛውን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ካልሆነ ብቻ ነው። (ማቴ. 19:9፤ ዕብ. 13:4) ስለመለያየትስ ምን ማለት ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድም ግልጽ ሐሳብ ይዟል። (1 ቆሮ. 7:10, 11) ባልና ሚስት ለመለያየት የሚያበቃቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ ምክንያት የለም። ይሁንና አንዳንድ ያገቡ ክርስቲያኖች ከትዳር ጓደኛቸው ጋር እንዲለያዩ የሚያደርጓቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ተሰምቷቸዋል፤ ለምሳሌ አካላዊ ጥቃት ከሚፈጽም ወይም ከሃዲ ከሆነ የትዳር ጓደኛ ጋር መኖር ለሕይወታቸው አሊያም ለመንፈሳዊነታቸው በጣም አስጊ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። w17.04 7 አን. 14-16