የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es19 ገጽ 88-97
  • መስከረም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መስከረም
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2019
  • ንዑስ ርዕሶች
  • እሁድ፣ መስከረም 1
  • ሰኞ፣ መስከረም 2
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 3
  • ረቡዕ፣ መስከረም 4
  • ሐሙስ፣ መስከረም 5
  • ዓርብ፣ መስከረም 6
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 7
  • እሁድ፣ መስከረም 8
  • ሰኞ፣ መስከረም 9
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 10
  • ረቡዕ፣ መስከረም 11
  • ሐሙስ፣ መስከረም 12
  • ዓርብ፣ መስከረም 13
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 14
  • እሁድ፣ መስከረም 15
  • ሰኞ፣ መስከረም 16
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 17
  • ረቡዕ፣ መስከረም 18
  • ሐሙስ፣ መስከረም 19
  • ዓርብ፣ መስከረም 20
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 21
  • እሁድ፣ መስከረም 22
  • ሰኞ፣ መስከረም 23
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 24
  • ረቡዕ፣ መስከረም 25
  • ሐሙስ፣ መስከረም 26
  • ዓርብ፣ መስከረም 27
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 28
  • እሁድ፣ መስከረም 29
  • ሰኞ፣ መስከረም 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2019
es19 ገጽ 88-97

መስከረም

እሁድ፣ መስከረም 1

ልጆቻችሁን . . . በይሖዋ ተግሣጽና ምክር አሳድጓቸው።—ኤፌ. 6:4

ልጆችን “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” ማሳደግ ክርስቲያን ወላጆች ካሏቸው ውድ መብቶች አንዱ ነው። (መዝ. 127:3) በጥንቷ እስራኤል የነበሩ ልጆች የተወለዱት ራሱን ለይሖዋ በወሰነ ብሔር ውስጥ ነው፤ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ የሚወለዱ ልጆች ግን በግለሰብ ደረጃ ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰን አለባቸው። ከዚህም በተጨማሪ ወላጆች፣ ለአምላክና ለእውነት ያላቸውን ፍቅር ለልጆቻቸው በውርስ መስጠት አይችሉም። ወላጆች ልጃቸው ራሱን ለይሖዋ ወስኖ በመጠመቅ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንዲሆን፣ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ሊረዱት ይገባል። ከዚህ የበለጠ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ምን ነገር አለ? ደግሞም ማንኛውም ሰው በቅርቡ ከሚመጣው ታላቅ መከራ ለመዳን ምልክት የሚደረግበት በግለሰብ ደረጃ ራሱን ለአምላክ ከወሰነ፣ ከተጠመቀና ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግል ከሆነ ብቻ ነው። (ማቴ. 24:13) እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ራሳቸውን ወስነው የተጠመቁ የይሖዋ አገልጋዮች ሲሆኑ ማየት የሚያስገኘውን ደስታና እርካታ እንድታጣጥሙ ምኞታችን ነው። w18.03 12 አን. 16-17

ሰኞ፣ መስከረም 2

ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ።—1 ጢሞ. 4:16

በቤተሰብም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ቅዱስ ጽሑፋዊ ተግሣጽ የመስጠት ኃላፊነት የተጣለባቸው ሁሉ የክርስቶስን ምሳሌ መከተላቸው ጥበብ ነው። በእርግጥም እንዲህ ማድረጋቸው በአምላክና በልጁ ለመቀረጽ እንደሚፈልጉ ያሳያል። መለኮታዊ ተግሣጽን መቀበል እንዲሁም ለሌሎች ተግሣጽ በምንሰጥበት ጊዜ የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚያስገኛቸውን በረከቶች ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም። ለምሳሌ ቤተሰቦችም ሆኑ ጉባኤዎች ሰላም የሰፈነባቸው ይሆናሉ፤ በተጨማሪም እያንዳንዱ ሰው በሌሎች ዘንድ ተወዳጅና ተፈላጊ እንደሆነ የሚሰማው ከመሆኑም ሌላ ያለምንም ስጋት ተረጋግቶ ይኖራል። ይህ ሁኔታ ወደፊት ለምናገኘው በረከት እንደ ቅምሻ ነው ማለት ይቻላል። (መዝ. 72:7) አዎ፣ የይሖዋ ተግሣጽ በእሱ አባታዊ እንክብካቤ ሥር እንዳለ አንድ ቤተሰብ ለዘላለም በሰላምና በአንድነት የምንኖርበትን መንገድ ያስተምረናል ብንል ማጋነን አይሆንም። (ኢሳ. 11:9) መለኮታዊ ተግሣጽን በዚህ መልኩ የምንመለከተው ከሆነ ለተግሣጽ ትክክለኛውን አመለካከት ማዳበር ቀላል ይሆንልናል፤ በእርግጥም ተግሣጽ አምላክ ለእኛ ያለውን ወደር የለሽ ፍቅር የሚያሳይ ግሩም ማስረጃ ነው። w18.03 26 አን. 15፤ 27 አን. 17, 19

ማክሰኞ፣ መስከረም 3

ኃጢአታቸውን በግልጽ እየተናዘዙ ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በእሱ ይጠመቁ ነበር።—ማቴ. 3:6

ለመጠመቅ ወደ ዮሐንስ የመጡት ሰዎች ይህን ያደረጉት የሙሴን ሕግ በመተላለፍ ለፈጸሙት ኃጢአት ንስሐ መግባታቸውን ለማሳየት ነበር። (ማቴ. 3:1-6) ይሁን እንጂ ዮሐንስ ካከናወናቸው ጥምቀቶች ሁሉ የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጥምቀት፣ ከኃጢአት ንስሐ ከመግባት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ልብ ማለት ያስፈልጋል። ዮሐንስ፣ የአምላክ ልጅ የሆነውን ኢየሱስን የማጥመቅ ልዩ መብት አግኝቷል። (ማቴ. 3:13-17) ፍጹም የሆነው ኢየሱስ ኃጢአት ስላልሠራ ንስሐ መግባት አላስፈለገውም። (1 ጴጥ. 2:22) ኢየሱስ የተጠመቀው የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን ማቅረቡን ለማሳየት ነው። (ዕብ. 10:7) በተጨማሪም ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ያከናውን በነበረበት ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ሰዎችን አጥምቀዋል። (ዮሐ. 3:22፤ 4:1, 2) ዮሐንስ እንዳጠመቃቸው ሰዎች ሁሉ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያጠመቋቸው ሰዎችም የተጠመቁት፣ የሙሴን ሕግ በመተላለፍ ለፈጸሙት ኃጢአት ንስሐ መግባታቸውን ለማሳየት ነበር። ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ግን ተከታዮቹ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች የሚጠመቁበት ምክንያት ከዚህ የተለየ ሆኗል። w18.03 5 አን. 6-7

ረቡዕ፣ መስከረም 4

መንፈሳዊ ሰው ሁሉንም ነገር ይመረምራል።—1 ቆሮ. 2:15

“መንፈሳዊ ሰው” መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? ከዓለማዊ ሰው በተለየ መልኩ መንፈሳዊ ሰው ከአምላክ ጋር ላለው ዝምድና ትልቅ ቦታ ይሰጣል። መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ‘አምላክን ለመምሰል’ ጥረት ያደርጋሉ። (ኤፌ. 5:1) ይህም ሲባል የይሖዋን አስተሳሰብ ለመረዳት ብሎም ነገሮችን እሱ በሚመለከትበት መንገድ ለመመልከት ይጥራሉ ማለት ነው። ለእነዚህ ሰዎች አምላክ እውን ሆኖ ይታያቸዋል። ሥጋዊ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች በተቃራኒ መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች፣ መላ ሕይወታቸውን ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ለመምራት የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። (መዝ. 119:33፤ 143:10) መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው በሥጋ ሥራዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ “የመንፈስ ፍሬ” ለማፍራት ጥረት ያደርጋል። (ገላ. 5:22, 23) ነጥቡን ግልጽ ለማድረግ፦ ነገሮችን ሁልጊዜ በአዎንታዊ መንገድ የሚመለከት ሰው አዎንታዊ አስተሳሰብ አለው ይባላል፤ በተመሳሳይም ለመንፈሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ሰው መንፈሳዊ አስተሳሰብ አለው ሊባል ይችላል። w18.02 19 አን. 3, 6

ሐሙስ፣ መስከረም 5

እጅግ የተወደድክ ዳንኤል ሆይ።—ዳን. 10:11

ዳንኤል በግዞት ይኖርባት የነበረችው የባቢሎን ከተማ በጣዖት አምልኮና በመናፍስታዊ ድርጊቶች የተሞላች ነበረች። በተጨማሪም ባቢሎናውያን አይሁዳውያንን ይንቋቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ በእነሱና በአምላካቸው በይሖዋ ላይ ይሳለቁ ነበር። (መዝ. 137:1, 3) ይህ እንደ ዳንኤል ያሉ ታማኝ አይሁዳውያንን ስሜት ምንኛ ጎድቶት ይሆን! ዳንኤል ከምግብና ከመጠጥ ጋር በተያያዘም ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሞታል፤ ምክንያቱም “በንጉሡ ምርጥ ምግብ ወይም በሚጠጣው የወይን ጠጅ ላለመርከስ” ወስኖ ነበር። (ዳን. 1:5-8, 14-17) ዳንኤል ስውር የሆነ ፈተናም አጋጥሞታል፤ ለየት ያለ ችሎታ ስለነበረው ከፍተኛ ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር። (ዳን. 1:19, 20) ሆኖም ዳንኤል ትዕቢተኛና ግትር ከመሆን ይልቅ ምንጊዜም ክብር የሚገባው ይሖዋ እንደሆነ በመናገር ትሑትና ልኩን የሚያውቅ ሰው እንደሆነ አሳይቷል። (ዳን. 2:30) የሚገርመው ነገር፣ ይሖዋ ዳንኤልን የጽድቅ ምሳሌ አድርጎ ከኖኅና ከኢዮብ ጋር የጠቀሰው ዳንኤል ገና ወጣት ሳለ ነበር። (ሕዝ. 14:14) አምላክ በዳንኤል ላይ ይህን ያህል እምነት መጣሉ ተገቢ ነበር? እንዴታ! ዳንኤል እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ እምነት እንዳለውና ታዛዥ እንደሆነ አሳይቷል። w18.02 5 አን. 11-12

ዓርብ፣ መስከረም 6

ሌዊ በቤቱ ለኢየሱስ ትልቅ ግብዣ አደረገ።—ሉቃስ 5:29

ኢየሱስ፣ ደስታ በሚያስገኙ እንቅስቃሴዎች በመካፈል ረገድ ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው። በአንድ ወቅት ‘በሠርግ ድግስ’ ላይ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌዊ ባዘጋጀው “ትልቅ ግብዣ” ላይ ተገኝቷል። (ዮሐ. 2:1-10) በሠርጉ ድግስ ላይ የወይን ጠጅ ባለቀበት ወቅት ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ በመቀየር ተአምር ፈጽሟል። ይህ ሲባል ግን የኢየሱስ ሕይወት ሥጋዊ ደስታን በማሳደድ ላይ ያተኮረ ነበር ማለት አይደለም። በሕይወቱ ውስጥ ይሖዋን ያስቀደመ ከመሆኑም ሌላ ሰዎችን ለመርዳት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል። በተጨማሪም ብዙዎች ሕይወት እንዲያገኙ ሲል በመከራ እንጨት ላይ ተሠቃይቶ ለመሞት ፈቃደኛ ሆኗል። ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ፣ ስደት ሲያደርሱባችሁና ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲያስወሩባችሁ ደስተኞች ናችሁ። በሰማያት የሚጠብቃችሁ ሽልማት ታላቅ ስለሆነ ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ።” (ማቴ. 5:11, 12) አምላክን ከልባችን የምንወደው ከሆነ እሱን እንደሚያሳዝነው ከምናውቀው ነገር ብቻ ሳይሆን ሊያሳዝነው እንደሚችል ከምናስበው ነገርም ጭምር እንርቃለን።—ማቴ. 22:37, 38፤ w18.01 26 አን. 16-18

ቅዳሜ፣ መስከረም 7

አገልጋይ ከልጅነቱ ጀምሮ ከተሞላቀቀ፣ የኋላ ኋላ ምስጋና ቢስ ይሆናል።—ምሳሌ 29:21

ለይሖዋ የምንሰጠው ስለምንወደውና ላደረገልን ነገሮች አመስጋኝነታችንን መግለጽ ስለምንፈልግ ነው። ይሖዋ ስላደረገልን በጣም ብዙ ነገሮች ስናስብ ልባችን በአድናቆት ይሞላል። ንጉሥ ዳዊት ሁሉንም ያገኘነው ከይሖዋ እንደሆነና ለይሖዋ የምንሰጠው ማንኛውም ነገር እሱ የሰጠን እንደሆነ ገልጿል። (1 ዜና 29:11-14) ለጋስ መሆን መልሶ ይክሳል። ሁልጊዜ ተቀባይ ከመሆን ይልቅ በልግስና መስጠት ጠቃሚ ነው። ወላጆቹ ከሚሰጡት ትንሽ የኪስ ገንዘብ ላይ አጠራቅሞ ለእነሱ ስጦታ የሚሰጥን አንድ ልጅ ለማሰብ ሞክር። ወላጆቹ ስጦታውን በአድናቆት እንደሚመለከቱት መገመት አያዳግትም! ወይም ደግሞ በአቅኚነት እያገለገለ ከወላጆቹ ጋር የሚኖር አንድ ልጅ አንዳንድ የቤት ወጪዎችን ለመሸፈን ትንሽም ቢሆን የገንዘብ ድጋፍ ያደርግ ይሆናል። ምንም እንኳ ወላጆቹ ይህን ከእሱ ባይጠብቁም ልጁ እነሱ ለሚያደርጉለት ነገር ያለውን አድናቆት የሚገልጽበት መንገድ እንደሆነ ስለሚያስቡ ስጦታውን ሊቀበሉ ይችላሉ። በተመሳሳይም ይሖዋ ያሉንን ውድ ነገሮች መስጠታችን እኛኑ እንደሚጠቅመን ያውቃል። w18.01 18 አን. 4, 6

እሁድ፣ መስከረም 8

አንተም ሆንክ ዘሮችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ።—ዘዳ. 30:19

ይሁን እንጂ ልጆቻችሁ ጥበብ እንዲያዳብሩ ለመርዳት፣ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለእነሱ መናገራችሁ ብቻ በቂ አይደለም። ልጆቻችሁ እንደሚከተሉት ባሉ ጥያቄዎች ላይ ቆም ብለው እንዲያስቡ ማድረጋችሁ ተገቢ ነው፦ ‘መጽሐፍ ቅዱስ፣ ማራኪ የሚመስሉ አንዳንድ ነገሮችን እንዳናደርግ የሚከለክለው ለምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ምንጊዜም እንደሚጠቅሙኝ የሚያሳምነኝ ምንድን ነው?’ (ኢሳ. 48:17, 18) ልጃችሁ የመጠመቅ ፍላጎት ካለው በቁም ነገር እንዲያስብበት ልትረዱት የሚገባ ሌላም ጉዳይ አለ፤ ይህም ‘ክርስቲያን መሆን ስለሚያስከትላቸው ኃላፊነቶች ምን አመለካከት አለኝ?’ የሚለው ነው። ክርስቲያን መሆን ምን ጥቅሞች አሉት? ምን መሥዋዕቶችንስ ያስከፍላል? ልጃችሁ የሚያገኘው ጥቅም ከሚከፍለው መሥዋዕት እንደሚልቅ የሚሰማው ለምንድን ነው? (ማር. 10:29, 30) አንድ ሰው ከተጠመቀ በኋላ በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ እንዲያስብ የሚያደርጉ ነገሮች በሕይወቱ ውስጥ ያጋጥሙታል። በመሆኑም ይህን ትልቅ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት እነዚህን ጉዳዮች ሊያጤናቸው ይገባል። ልጆቻችሁ እነዚህን ነገሮች እንዲያመዛዝኑ ከረዳችኋቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ምንጊዜም እንደሚጠቅሟቸው በግለሰብ ደረጃ አምነው መቀበል ቀላል ይሆንላቸዋል። w17.12 21 አን. 14-15

ሰኞ፣ መስከረም 9

ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል።—ኢሳ. 40:26

በከባድ በሽታ የሚሠቃዩ በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አሉ። ሌሎች ደግሞ እነሱ ራሳቸው በዕድሜ ቢገፉም፣ አረጋውያን የሆኑ የቤተሰባቸውን አባላት የመንከባከብ ኃላፊነት አለባቸው። አንዳንድ ክርስቲያኖች ቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ነገር እንኳ ማሟላት ትግል ሆኖባቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ችግሮች የተደራረቡባቸው ብዙ ወንድሞች አሉ። ይሖዋ፣ ሕይወት የሌለውን እያንዳንዱን ፍጥረቱን በሚገባ የሚያውቀው ከሆነ በፍቅር ተነሳስተው ለሚያገለግሉት ሕዝቦቹማ የበለጠ ትኩረት እንደሚሰጥ መገመት አያዳግትም! (መዝ. 19:1, 3, 14) አባታችን የእኛን ማንነት በሚገባ ያውቃል። መጽሐፍ ቅዱስ “የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል” ይላል። (ማቴ. 10:30) መዝሙራዊውም “ይሖዋ ነቀፋ የሌለባቸውን ሰዎች የሕይወት ጎዳና ያውቃል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (መዝ. 37:18) ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ እያጋጠሙን ያሉ ፈተናዎችን የሚመለከት ከመሆኑም በላይ እያንዳንዱን ፈተና ለመወጣት የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል። w18.01 7 አን. 1፤ 8 አን. 4

ማክሰኞ፣ መስከረም 10

ጣቢታ፣ ተነሽ!—ሥራ 9:40

ጴጥሮስ ጣቢታን ከሞት እንድትነሳ የማድረጉ ክንውን ‘ብዙዎች በጌታ እንዲያምኑ’ አስተዋጽኦ አድርጓል። እነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ስለ ኢየሱስ ምሥራቹን መናገር እንዲሁም ይሖዋ ሙታንን የማስነሳት ኃይል እንዳለው ለሌሎች መመሥከር ችለዋል። (ሥራ 9:36-42) በብዙ የዓይን ምሥክሮች ፊት ስለተከናወነ ትንሣኤ የሚገልጽ ዘገባ ደግሞ እንመልከት። በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ በጥሮአስ (አሁን ያለችው በሰሜን ምዕራብ ቱርክ ነው) በሚገኝ አንድ ፎቅ ላይ ከወንድሞች ጋር ተሰብስቦ ነበር። ጳውሎስ ንግግሩን እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ አስረዘመ። አውጤኪስ የሚባል ወጣት መስኮት ላይ ተቀምጦ ንግግሩን እያዳመጠ ሳለ እንቅልፍ ስላሸነፈው ከሁለተኛ ፎቅ ላይ ወደቀ። አውጤኪስ ጋ ቀድሞ በመድረስ ሁኔታውን የተመለከተው ሐኪሙ ሉቃስ ሳይሆን አይቀርም፤ ሉቃስ፣ ወጣቱ ጉዳት እንደደረሰበት ወይም ራሱን እንደሳተ ሳይሆን እንደሞተ ገልጿል። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ከፎቅ ላይ ወርዶ የወጣቱን አስከሬን አቀፈው፤ ከዚያም ወጣቱ ‘በሕይወት እንዳለ’ ተናገረ። በቦታው የነበሩት ሰዎች ይህን ተአምር መመልከታቸው ምን ስሜት አሳድሮባቸው እንደሚሆን መገመት አያዳግትም! እነዚህ ሰዎች ወጣቱ እንደሞተ በገዛ ዓይናቸው ተመልክተዋል፤ በመሆኑም ጳውሎስ ከሞት ሲያስነሳው “እጅግ ተጽናኑ።”—ሥራ 20:7-12፤ w17.12 5 አን. 10-11

ረቡዕ፣ መስከረም 11

ኑና የይሖዋን ሥራዎች እዩ።—መዝ. 46:8

የሰው ልጅ ለረጅም ዘመናት ሲያሠቃዩት ለኖሩት ችግሮች መፍትሔ እያገኘ ነው? የሰው ልጆች ጦርነትን ማስቀረት አልቻሉም። በኮምፒውተር አማካኝነት የሚፈጸም ወንጀል፣ የቤት ውስጥ ጥቃትና ሽብርተኝነት በአስደንጋጭ ፍጥነት እየጨመሩ ነው። እንዲሁም መድኃኒት ያልተገኘላቸው በሽታዎች እስካሁን መስፋፋታቸውን አላቆሙም። በዛሬው ጊዜ ያለውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት የሚቆጣጠሩት ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ጦርነትን፣ ወንጀልን፣ በሽታንና ድህነትን ማስወገድ እንደማይችሉ ግልጽ ነው፤ ይህን ማድረግ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው። ይሖዋ ለሰው ልጆች ምን እንደሚያደርግ እስቲ እንመልከት። ጦርነት፦ የአምላክ መንግሥት ለጦርነት መንስኤ የሚሆኑትን እንደ ራስ ወዳድነት፣ ምግባረ ብልሹነት፣ የብሔርተኝነት ስሜትና የሐሰት ሃይማኖት ያሉ ነገሮች ያስወግዳል፤ አልፎ ተርፎም ሰይጣንን እንኳ ያጠፋዋል። (መዝ. 46:9) ወንጀል፦ የአምላክ መንግሥት በአሁኑ ጊዜም እንኳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በመካከላቸው ፍቅርና መተማመን እንዲኖር እያስተማረ ነው፤ ይህን ማድረግ የሚችል ሌላ መንግሥት የለም። (ኢሳ. 11:9) በሽታ፦ ይሖዋ ለሕዝቡ የተሟላ ጤንነት ይሰጣቸዋል። (ኢሳ. 35:5, 6) ድህነት፦ ይሖዋ ድህነትን ያስወግዳል፤ እንዲሁም ሕዝቡ ደስተኛ ሕይወት እንዲመሩና ከእሱ ጋር የቀረበ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ያደርጋል።—መዝ. 72:12, 13፤ w17.11 23-24 አን. 14-16

ሐሙስ፣ መስከረም 12

በደም ዕዳ ተጠያቂ እንዳትሆን ነው።—ዘዳ. 19:10

የመማጸኛ ከተሞች የተዘጋጁበት ዋነኛ ዓላማ እስራኤላውያን በደም ዕዳ ተጠያቂ እንዳይሆኑ ሲባል ነው። ይሖዋ ለሕይወት ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ሲሆን “ንጹሕ ደም የሚያፈሱ [እጆችን]” ይጠላል። (ምሳሌ 6:16, 17) ይሖዋ ፍትሐዊና ቅዱስ አምላክ ስለሆነ፣ ሳያውቅ የሰው ሕይወት ያጠፋ ግለሰብ እንኳ በቸልታ እንዲታለፍ አይፈቅድም። ከይሖዋ በተለየ መልኩ፣ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ለሕይወት ጨርሶ አክብሮት አልነበራቸውም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ “የእውቀትን ቁልፍ ነጥቃችሁ ወስዳችኋል። እናንተ ራሳችሁ አልገባችሁም፤ ለመግባት የሚሞክሩትንም ትከለክላላችሁ” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 11:52) እነዚህ ሰዎች፣ የእውቀትን ቁልፍ በመጠቀም የአምላክን ቃል ትርጉም ማብራራትና ሌሎች ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ እንዲጓዙ መርዳት ነበረባቸው። እነሱ ግን ሰዎች ‘የሕይወት “ዋና ወኪል”’ ከሆነው ከኢየሱስ እንዲርቁና ወደ ዘላለም ጥፋት በሚወስደው መንገድ ላይ እንዲጓዙ አድርገዋል። (ሥራ 3:15) ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ኩሩና ራስ ወዳድ በመሆናቸው ለሌሎች ሕይወትና ደህንነት ግድ አልነበራቸውም። እነዚህ ሰዎች ምንኛ ጨካኝና ምሕረት የጎደላቸው ነበሩ! w17.11 15 አን. 9-10

ዓርብ፣ መስከረም 13

በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅም . . . ያፍርበታል።—ማር. 8:38

መጀመሪያ ላይ፣ ለቤተሰቦቻችን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደጀመርን አልነገርናቸው ይሆናል። እምነታችን እየጠነከረ ሲሄድ ግን ስለምናምንበት ነገር መናገር እንዳለብን ሊሰማን ይችላል። በዚህ ረገድ ቆራጥ አቋም መያዝህ በአንተና በማያምኑት ቤተሰቦችህ መካከል ችግር እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል፤ ከሆነ ስሜታቸውን ለመረዳት ጥረት አድርግ። እኛ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በመማራችን በጣም እንደምንደሰት የታወቀ ነው፤ ቤተሰቦቻችን ግን እንደተታለልን ወይም የመናፍቃን ቡድን አባል እንደሆንን አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። በዓላትን አብረናቸው ስለማናከብር ለእነሱ ያለን ፍቅር እንደቀነሰ ሊሰማቸው ይችላል። አልፎ ተርፎም በያዝነው አቋም የተነሳ አምላክ እንደሚቀጣን በማሰብ ስጋት ያድርባቸው ይሆናል። በመሆኑም ራሳችንን በእነሱ ቦታ በማስቀመጥ ስሜታቸውን ለመረዳት ጥረት ማድረግ እንዲሁም በእርግጥ ያስጨነቃቸው ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ በትኩረት ማዳመጥ ይኖርብናል። (ምሳሌ 20:5) ሐዋርያው ጳውሎስ “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች” ምሥራቹን ለማካፈል ሲል የእያንዳንዱን ሰው ስሜት ለመረዳት ጥረት ያደርግ ነበር፤ እኛም የእሱን ምሳሌ መከተላችን ጠቃሚ ነው።—1 ቆሮ. 9:19-23፤ w17.10 15 አን. 11-12

ቅዳሜ፣ መስከረም 14

[ለይሖዋ] የውዳሴ መዝሙር ዘምሩለት።—መዝ. 33:2

ከመዘመር ወደኋላ እንድንል የሚያደርገን እንዴት መዘመር እንዳለብን አለማወቃችን ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የመዘመር ችሎታህን ለማሻሻል የሚረዱህ አንዳንድ ነገሮች አሉ። አተነፋፈስህን ማስተካከልህ ድምፅህን ከፍ አድርገህ በግለት ለመዘመር ይረዳሃል። አምፖል እንዲበራ የሚያደርገው የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሆነ ሁሉ እኛም ስንናገር ወይም ስንዘምር ድምፃችን ኃይል እንዲኖረው የሚያደርገው ትንፋሻችን ነው። በምትዘምርበት ወቅት የድምፅህ መጠን፣ ስትናገር ከምትጠቀምበት ማነስ የለበትም፤ እንዲያውም ከዚያ ከፍ ማለት ይኖርበታል። ቅዱሳን መጻሕፍት ከመዝሙር ጋር በተያያዘ የይሖዋ አገልጋዮች ‘እልል እንዲሉ’ በሌላ አባባል ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲዘምሩ የሚያበረታቱበት ጊዜ አለ። (መዝ. 33:1-3) የሚከተሉትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሩ፦ በመዝሙር መጽሐፋችን ላይ ካሉት የምትወዷቸው መዝሙሮች መካከል አንዱን ምረጡ። ስንኞቹን ጮክ ብላችሁና በልበ ሙሉነት አንብቡ። ቀጥሎም የድምፃችሁን መጠን ሳትቀንሱ አንዱን ስንኝ በአንድ ትንፋሽ አንብቡት። ከዚያም ይህንን ስንኝ በዚያው ስሜት ዘምሩት። (ኢሳ. 24:14) በዚህ ጊዜ ስትዘምሩ ድምፃችሁ ይበልጥ ኃይል ይኖረዋል፤ ይህ ደግሞ ጥሩ ነገር ነው። አፍራችሁ ድምፃችሁን ዝቅ ለማድረግ አትሞክሩ። w17.11 5-6 አን. 11-13

እሁድ፣ መስከረም 15

እውነተኛው አምላክ መንፈሳቸውን ያነሳሳው ሰዎች ሁሉ ወጥተው በኢየሩሳሌም የነበረውን የይሖዋን ቤት መልሰው ለመገንባት ተዘጋጁ።—ዕዝራ 1:5

አይሁዳውያኑ በጉዟቸው ላይ ስለ አዲሱ መኖሪያቸው ብዙ አስበው መሆን አለበት። ኢየሩሳሌም በአንድ ወቅት ምን ያህል ውብ ከተማ እንደነበረች ሰምተዋል። ምክንያቱም በመካከላቸው የነበሩት አረጋውያን የቀድሞውን ቤተ መቅደስ ክብር የማየት አጋጣሚ አግኝተዋል። (ዕዝራ 3:12) አንተም ከእነዚህ ሰዎች ጋር አብረህ እየተጓዝክ ቢሆን አዲሷን መኖሪያህን ኢየሩሳሌምን ከሩቅ ስታያት ምን ይሰማህ ነበር? የፈራረሱ ቤቶች አረም በቅሎባቸው፣ የመጠበቂያ ማማዎቿ ተንደውና በሮቿ ወላልቀው ስታይ ታዝን ነበር? የኢየሩሳሌምን የፈራረሱ ግንቦች፣ ግዙፍና ድርብ ከሆነው የባቢሎን ግንብ ጋር ታወዳድር ነበር? ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት አይሁዳውያን በዚያ ባዩት ሁኔታ ተስፋ አልቆረጡም። ምክንያቱም ወደ ኢየሩሳሌም ባደረጉት ረጅም ጉዞ ላይ የይሖዋን የማዳን እጅ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተመልክተዋል። ኢየሩሳሌም እንደደረሱ መጀመሪያ ያደረጉት ነገር የቀድሞው ቤተ መቅደስ በነበረበት ቦታ ላይ መሠዊያ መሥራት ነው፤ ከዚያም በየዕለቱ ለይሖዋ መሥዋዕት ማቅረብ ጀመሩ።—ዕዝራ 3:1, 2፤ w17.10 26-27 አን. 2-3

ሰኞ፣ መስከረም 16

አትፍራ ወይም አትሸበር፤ . . . ይሖዋ አምላክ ከአንተ ጋር ነውና።—1 ዜና 28:20

ሰለሞን ድፍረት ማሳየትን በተመለከተ ከአባቱ ከዳዊት ብዙ ነገር እንደተማረ ምንም ጥርጥር የለውም። ዳዊት ከፍተኛ የጦር ልምድ ያለውን ግዙፍ ሰው ፊት ለፊት በመግጠም አስገራሚ ድፍረት አሳይቷል። ዳዊት አምላክ ስለረዳው በአንዲት ድቡልቡል ድንጋይ ጎልያድን ድል ማድረግ ችሏል። (1 ሳሙ. 17:45, 49, 50) በእርግጥም ዳዊት ሰለሞንን ደፋር እንዲሆንና ቤተ መቅደሱን እንዲገነባ ያበረታታው ለምን እንደሆነ መገመት አያዳግትም! የቤተ መቅደሱ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ይሖዋ ከእሱ ጋር እንደሚሆን በመንገር አበረታቶታል። ሰለሞን አባቱ በሰጠው ምክር ላይ አሰላስሎ መሆን አለበት፤ ይህም ወጣትና ተሞክሮ የሌለው ቢሆንም ደፋር እንዲሆንና ሥራውን እንዲጀምር እንደረዳው ጥርጥር የለውም። ደግሞም ሰለሞን በይሖዋ እርዳታ እጅግ የሚያምረውን ቤተ መቅደስ በሰባት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ሊጨርስ ችሏል። ይሖዋ ሰለሞንን እንደረዳው ሁሉ እኛንም በቤተሰብም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ደፋር እንድንሆንና ሥራችንን እንድናከናውን ሊረዳን ይችላል። (ኢሳ. 41:10, 13) ከይሖዋ አምልኮ ጋር በተያያዘ ድፍረት የሚጠይቁ እርምጃዎችን ስንወስድ አሁንም ሆነ ወደፊት የይሖዋ በረከት እንደማይለየን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። w17.09 28 አን. 3፤ 29 አን. 4፤ 32 አን. 20-21

ማክሰኞ፣ መስከረም 17

የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው።—ዕብ. 4:12

የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን የአምላክ ቃል ማለትም አምላክ ለሰው ልጆች ያስተላለፈው መልእክት “ሕያውና ኃይለኛ” እንደሆነ ሙሉ እምነት አለን። ብዙዎቻችን የምንመራው ሕይወት፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ ነው። አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ከዚህ ቀደም ሌቦች፣ የዕፅ ሱሰኞች ወይም ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት የሚመሩ ነበሩ። ሌሎች ደግሞ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ሁሉ ነገር የተሟላላቸው ቢሆኑም በሕይወታቸው ውስጥ የጎደላቸው ነገር እንዳለ ይሰማቸው ነበር። (መክ. 2:3-11) ምንም ተስፋ ያልነበራቸውና ግራ የተጋቡ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ባለው ሰዎችን የመለወጥ ኃይል በመታገዝ በሕይወት መንገድ ላይ መጓዝ ሲጀምሩ በተደጋጋሚ ተመልክተናል። “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” በሚል ተከታታይ ርዕስ መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡትን እንዲህ ያሉ በርካታ ተሞክሮዎች በማንበብ እንደተደሰትን ግልጽ ነው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቲያኖች እውነትን ከተቀበሉ በኋላም እንኳ ቀጣይ የሆነ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ እንደሚረዳቸው ማስተዋል ችለናል። w17.09 23 አን. 1

ረቡዕ፣ መስከረም 18

ይሖዋ ስለራራለት . . . ይዘው ከከተማዋ አስወጡት።—ዘፍ. 19:16

ሎጥ ያጋጠመው ይህ ሁኔታ፣ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ የሚያሳይ አይደለም? (ኢሳ. 63:7-9፤ ያዕ. 5:11 ግርጌ፤ 2 ጴጥ. 2:9) ይሖዋ ርኅራኄ ማሳየት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለሕዝቦቹ አስተምሯል። የአንድን ሰው ልብስ መያዣ አድርጎ መውሰድን አስመልክቶ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ሕግ እንደ ምሳሌ እንመልከት። (ዘፀ. 22:26, 27) አንድ ጨካኝ የሆነ አበዳሪ፣ መያዣ አድርጎ የወሰደውን ልብስ ለማስቀረት ሊፈተን ይችላል፤ ይህ ደግሞ ተበዳሪው ለብሶ የሚተኛው ልብስ እንዲያጣ ያደርገዋል። ይሁንና ይሖዋ ሕዝቡ እንዲህ ያለውን ርኅራኄ የጎደለው አመለካከት እንዲያስወግዱና ርኅራኄ የጎደለው ድርጊት እንዳይፈጽሙ ነግሯቸዋል። ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ሕዝቡ ርኅራኄ እንዲያሳዩ ይፈልግ ነበር። ከዚህ ሕግ በስተጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት መገንዘባችን እኛንም ለተግባር አያነሳሳንም? ወንድሞቻችን እንዲሞቃቸው ማድረግ ማለትም ችግራቸው ቀለል እንዲልላቸው መርዳት እየቻልን ሲቸገሩ ዝም ብለን ልናያቸው ይገባል?—ቆላ. 3:12፤ ያዕ. 2:15, 16፤ 1 ዮሐ. 3:17፤ w17.09 9 አን. 4-5

ሐሙስ፣ መስከረም 19

አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው።—ሉቃስ 23:34

ኢየሱስ አባቱ ገዳዮቹን ይቅር እንዲላቸው በጸሎት ጠይቋል። በእርግጥም ኢየሱስ ከባድ ሥቃይና መከራ በሚያስከትል ሁኔታም ሥር ገርና ታጋሽ በመሆን ግሩም ምሳሌ ትቶልናል! (1 ጴጥ. 2:21-23) እኛስ ገርነትና ትዕግሥት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይህን ማድረግ ከምንችልባቸው መንገዶች መካከል አንዱን እንደሚከተለው በማለት ገልጿል፦ “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።” (ቆላ. 3:13) ይህን ትእዛዝ ለመፈጸም ገርና ታጋሽ መሆን እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ይቅር ባዮች በመሆን የጉባኤው አንድነት ተጠብቆ እንዲቀጥል አስተዋጽኦ እናደርጋለን። እያንዳንዱ ክርስቲያን ገርነትንና ትዕግሥትን የመልበስ ግዴታ አለበት፤ ይህ ለምርጫ የተተወ ጉዳይ አይደለም። ገርነትንና ትዕግሥትን መልበስ ለመዳን የግድ አስፈላጊ የሆነ ብቃት ነው። (ማቴ. 5:5፤ ያዕ. 1:21) ከሁሉ በላይ ደግሞ እነዚህን ባሕርያት በማንጸባረቅ ይሖዋን ማስከበርና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ እንዲያደርጉ መርዳት እንችላለን።—ገላ. 6:1፤ 2 ጢሞ. 2:24, 25፤ w17.08 25-26 አን. 15-17

ዓርብ፣ መስከረም 20

ይሖዋ፣ ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድን . . . ያውቃል።—2 ጴጥ. 2:9

መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ይሖዋ ያልተጠበቁ ነገሮችን እንዳደረገ የሚያሳዩ በርካታ ዘገባዎችን እናገኛለን። ንጉሥ ሕዝቅያስ የኖረው የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከኢየሩሳሌም በስተቀር ሁሉንም የተመሸጉ የይሁዳ ከተሞች ወርሮ በያዘበት ወቅት ነበር። (2 ነገ. 18:1-3, 13) ከዚያም ሰናክሬም ትኩረቱን ወደ ኢየሩሳሌም አዞረ። ንጉሥ ሕዝቅያስ ይህ አደጋ በተጋረጠበት ወቅት ምን አደረገ? ወደ ይሖዋ የጸለየ ከመሆኑም ሌላ የይሖዋ ነቢይ የሆነውን ኢሳይያስን ምክር ጠይቋል። (2 ነገ. 19:5, 15-20) በተጨማሪም ሕዝቅያስ፣ ሰናክሬም የጣለበትን ቅጣት በመክፈል ምክንያታዊ መሆኑን አሳይቷል። (2 ነገ. 18:14, 15) በኋላም ከተማዋን ለረጅም ጊዜ ከበባ ለማዘጋጀት አንዳንድ እርምጃዎችን ወስዷል። (2 ዜና 32:2-4) ይሁንና ጉዳዩ መፍትሔ ያገኘው እንዴት ነው? ይሖዋ መልአኩን በመላክ በአንድ ሌሊት 185,000 የሚያክሉትን የሰናክሬም ወታደሮች ገደለ። ማንም ሰው ሌላው ቀርቶ ሕዝቅያስም እንኳ እንዲህ ያለ ነገር ይከሰታል ብሎ ሊጠብቅ አይችልም!—2 ነገ. 19:35፤ w17.08 10 አን. 7፤ 11 አን. 12

ቅዳሜ፣ መስከረም 21

ሰዎችን . . . [ያዘዝኳችሁን] ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።—ማቴ. 28:19, 20

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ዝግጅት ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ይሖዋን በሙሉ ጊዜህ በማገልገል ረገድ ስኬታማ እንድትሆን ከምንም ነገር በላይ የሚረዳህ መንፈሳዊ ባሕርያትን ማዳበር ነው። ስለዚህ የአምላክን ቃል በትጋት አጥና፣ ባነበብከው ነገር ላይ በጥልቀት አሰላስል፤ እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እምነትህን ለመግለጽ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ተጠቀምባቸው። በትምህርት ቤት በምታሳልፋቸው ዓመታትም ምሥራቹን የመስበክ ችሎታህን ማሻሻል ትችላለህ። የሰዎችን አመለካከት በዘዴ በመጠየቅና የሚሰጡትን መልስ በጥሞና በማዳመጥ ለሌሎች አሳቢነት ማሳየትን ተማር። ከዚህም ሌላ በጉባኤ ውስጥ አንዳንድ ሥራዎችን ለማከናወን ራስህን ማቅረብ ለምሳሌ የስብሰባ አዳራሹን በማጽዳቱ ወይም በመጠገኑ ሥራ መካፈል ትችላለህ። ይሖዋ ትሑት የሆኑና የፈቃደኝነት መንፈስ ያላቸው ሰዎችን ይጠቀምባቸዋል። (መዝ. 110:3፤ ሥራ 6:1-3) ሐዋርያው ጳውሎስ በሚስዮናዊነት እንዲካፈል ጢሞቴዎስን የጋበዘው በወንድሞች ዘንድ “በመልካም ምግባሩ የተመሠከረለት” ወጣት ስለነበር ነው።—ሥራ 16:1-5፤ w17.07 23 አን. 7፤ 26 አን. 14

እሁድ፣ መስከረም 22

ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤ ምላስም ሁሉ ታማኝ ለመሆን ይምላል።—ኢሳ. 45:23

በይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት ላይ የተነሳው ጥያቄ በሰዎችም ሆነ በመላእክት አእምሮ ውስጥ መጉላላቱን እስከቀጠለ ድረስ በተለያዩ ብሔራት፣ ጎሳዎች፣ ቤተሰቦችና ግለሰቦች መካከል ክፍፍል መኖሩ አይቀርም። የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት ከተረጋገጠ በኋላ ግን ሁሉም ሰዎች ለይሖዋ የጽድቅ አገዛዝ ለዘላለም ይገዛሉ። በዚያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ሰላም ይሰፍናል። (ኤፌ. 1:9, 10) የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክል መሆኑ ይረጋገጣል፤ የሰይጣንና የሰው ልጆች አገዛዝ ደግሞ ከንቱ መሆኑ በገሃድ ይታያል፤ በመጨረሻም ሙሉ በሙሉ ይወገዳል። አምላክ ያቋቋመው መሲሐዊ መንግሥት ከሁሉ የተሻለ መስተዳድር መሆኑ ይረጋገጣል፤ ንጹሕ አቋማቸውን የጠበቁ ሰዎች ደግሞ የሰው ልጆች ከአምላክ አገዛዝ ጎን መቆም እንደሚችሉ ያሳያሉ። (ኢሳ. 45:24) አንተስ ንጹሕ አቋማቸውን በመጠበቅ የይሖዋን ሉዓላዊነት ከሚደግፉ ሰዎች መካከል መቆጠር ትፈልጋለህ? እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ከፈለግን ትኩረታችንን አንገብጋቢ በሆነው ጉዳይ ላይ ማድረግና ይህ ጉዳይ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘብ አለብን። w17.06 23 አን. 4-5

ሰኞ፣ መስከረም 23

እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።—ምሳሌ 17:17

ከሐዘን ለመጽናናት የሚወስደው ጊዜ ከሰው ወደ ሰው ሊለያይ ይችላል። ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ለማጽናናት፣ በርካታ ጓደኞቻቸውና ዘመዶቻቸው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት አብረዋቸው እንደሚሆኑ ግልጽ ነው፤ ሆኖም በዚህ ጊዜ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ሰው ወደ ዕለታዊ ሕይወቱ ከተመለሰ በኋላ ባሉት ወራትም ጭምር እነሱን ለመርዳት ጥረት ማድረጉ አስፈላጊ ነው። ሐዘን የደረሰበት ሰው ለመጽናናት የሚወስድበት ጊዜ ምንም ያህል ቢሆን፣ የእምነት ባልንጀሮቹ ከጎኑ መሆናቸው በእጅጉ ያጽናናዋል። (1 ተሰ. 3:7) የሚወዱትን ሰው በሞት ላጡ ሰዎች አንዳንድ ሙዚቃዎች፣ ፎቶግራፎች ወይም አብረው ያከናውኗቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች ሌላው ቀርቶ አንድ ዓይነት መዓዛ፣ ድምፅ አሊያም ወቅቶች ሲቀያየሩ የሚኖረው ሁኔታ እንኳ ሐዘናቸው በድንገት እንዲያገረሽባቸው ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማስታወሳችን አስፈላጊ ነው። የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣ ሰው፣ አንዳንድ ነገሮችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለብቻው ሲያደርግ ለምሳሌ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ወይም በመታሰቢያው በዓል ላይ ሲገኝ በሐዘን ሊዋጥ ይችላል። ይሁን እንጂ ሐዘን ያጋጠማቸው ሰዎች ማበረታቻ ማግኘት የሚያስፈልጋቸው በአንዳንድ ለየት ያሉ ወቅቶች ብቻ እንዳልሆነ መዘንጋት የለብንም። w17.07 16 አን. 17-19

ማክሰኞ፣ መስከረም 24

ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።—ፊልጵ. 2:4

ለሌሎች ሰዎች ልባዊ አሳቢነት ስናሳይ ራሳችን የሚሰማን አሉታዊ ስሜት እየቀለለን ይሄዳል። ለምሳሌ ያህል ያገቡም ሆኑ ያላገቡ ብዙ እህቶች ምሥራቹን በማወጅ ከአምላክ ጋር አብረው መሥራታቸው ታላቅ ደስታ አስገኝቶላቸዋል። ግባቸው የአምላክን ፈቃድ በማድረግ እሱን ማስከበር ነው። እንዲያውም አንዳንዶች አገልግሎት ለሕመማቸው መድኃኒት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሁላችንም በክልላችንና በጉባኤው ውስጥ ላሉ ሰዎች አሳቢነት ማሳየታችን በጉባኤው ውስጥ ለሚኖረው አንድነት አስተዋጽኦ ለማበርከት ያስችለናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። በተሰሎንቄ ጉባኤ ለነበሩት ሰዎች ‘እንደምታጠባ እናት’ አሳቢነት አሳይቷቸዋል፤ እንዲሁም “አባት ለልጆቹ እንደሚያደርገው” ለወንድሞቹ ማበረታቻና ማጽናኛ ሰጥቷቸዋል። (1 ተሰ. 2:7, 11, 12) ለእውነተኛው አምላክ ፍቅር ያዳበሩና የእሱን ቃል በተግባር የሚያውሉ ልጆች ለቤተሰባቸው የመጽናኛ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህን የሚያደርጉት ወላጆቻቸውን በማክበርና በሌሎች ተግባራዊ መንገዶች ወላጆቻቸውን በመርዳት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለቤተሰቡ መንፈሳዊነት ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ። w17.06 7 አን. 13-14፤ 8 አን. 17

ረቡዕ፣ መስከረም 25

በዓመፅ ሀብት ለራሳችሁ ወዳጆች አፍሩ።—ሉቃስ 16:9

አንዳንዶች ለልጅ ልጆቻቸው የሚተርፍ ሀብት ሲኖራቸው በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ግን በከፋ ድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ የማይካድ ሐቅ ነው። ኢየሱስ፣ አሁን ያለው የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚጠፋው የአምላክ መንግሥት ሲመጣ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። በራእይ 18:3 ላይ የተገለጹት “ነጋዴዎች” የሚያመለክቱት ስግብግብነት የተሞላበትን የንግድ ሥርዓት ነው፤ የሰይጣን ዓለም የንግዱንና የፖለቲካውን ሥርዓት እንዲሁም ሃይማኖትን ያቀፈ ነው። የአምላክ ሕዝቦች ከፖለቲካና ከሐሰት ሃይማኖት ሙሉ በሙሉ ርቀዋል፤ ይሁንና ከአምላክ ሕዝቦች መካከል አብዛኞቹ ከሰይጣን ዓለም የንግድ ሥርዓት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖራቸው ማድረግ አይችሉም። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በዛሬው ጊዜ ላለው የንግድ ሥርዓት ያለንን አመለካከት ለመመርመር እንደሚከተሉት ያሉትን ጥያቄዎች ማጤናችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ያለኝን ቁሳዊ ሀብት ለአምላክ ታማኝ እንደሆንኩ በሚያሳይ መንገድ መጠቀም የምችለው እንዴት ነው? በንግዱ ዓለም ውስጥ ከሚገባው በላይ ላለመጠላለፍ መጠንቀቅ የምችለው እንዴት ነው? በዚህ አስቸጋሪ ሥርዓት ውስጥም እንኳ የአምላክ ሕዝቦች ሙሉ በሙሉ በይሖዋ እንደሚታመኑ የሚያሳዩት የትኞቹ ተሞክሮዎች ናቸው?’ w17.07 7 አን. 1-3

ሐሙስ፣ መስከረም 26

ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።—ሉቃስ 21:34

ኢየሱስ የዚህ ሥርዓት ጭንቀት ምን ያህል ጫና ሊያሳድርብን እንደሚችል በሚገባ ያውቃል። ኢየሱስ፣ ስለ ዘሪው በተናገረው ምሳሌ ላይ አንዳንዶች “የመንግሥቱን ቃል” ተቀብለው እድገት ማድረግ ቢጀምሩም “የዚህ ሥርዓት ጭንቀት እንዲሁም ሀብት ያለው የማታለል ኃይል ቃሉን [እንደሚያንቀው]” ገልጾ ነበር። (ማቴ. 13:19-22፤ ማር. 4:19) በእርግጥም ጠንቃቆች ካልሆንን፣ በሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋቸው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ትኩረታችንን ሊሰርቁትና መንፈሳዊ እንቅስቃሴያችንን ሊያዳክሙት ይችላሉ። ክርስቶስ የሰጠንን ሥራ ከምንም በላይ በማስቀደም ለእሱ ጥልቅ ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። ታዲያ ምንጊዜም ለዚህ ሥራ ቅድሚያ እየሰጠን መሆኑን እንዴት ማወቅ እንችላለን? በየጊዜው ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘በሕይወቴ ውስጥ ከምንም በላይ የምወደው ነገር ምንድን ነው? ይበልጥ የምደሰተው መንፈሳዊ ነገሮችን በማከናወን ነው? ወይስ በሌሎች እንቅስቃሴዎች በመካፈል?’ w17.05 22-23 አን. 3-4

ዓርብ፣ መስከረም 27

ከአንደበታችሁ የሚወጣው ቃል በቀላሉ የሚገባ [ይሁን]።—1 ቆሮ. 14:9

“የባዕድ አገር ሰዎች” የሚኖሩት የእነሱን ቋንቋ ከሚናገሩ የይሖዋ ምሥክሮች ርቀው ከሆነ በአካባቢው በሚነገረው ቋንቋ ወደሚካሄድ ጉባኤ መሄድ ይኖርባቸዋል። (መዝ. 146:9) ይሁንና የአፍ መፍቻ ቋንቋችሁን የሚጠቀም ጉባኤ በአካባቢያችሁ የሚገኝ ከሆነ ‘ቤተሰባችን በየትኛው ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ ቢሄድ የተሻለ ይሆናል?’ የሚል ጥያቄ ይነሳል። የቤተሰቡ ራስ በጉዳዩ ላይ በደንብ ካሰበበትና ከጸለየበት እንዲሁም ከባለቤቱና ከልጆቹ ጋር ከተማከረበት በኋላ ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። (1 ቆሮ. 11:3) ወላጆች፣ ልጆቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሚዛናዊ ሆነው ማጤን ይኖርባቸዋል። እርግጥ ነው፣ አንድ ልጅ የሚገባው ቋንቋ ምንም ይሁን ምን፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በደንብ መረዳት እንዲችል በየሳምንቱ በስብሰባዎች ላይ ለጥቂት ሰዓታት የሚያገኘው መንፈሳዊ ትምህርት ብቻውን በቂ አይደለም። ሆኖም ወላጆች ልትዘነጉት የማይገባ ነገር አለ፦ ልጆቻችሁ፣ በሚገባ በሚረዱት ቋንቋ በሚካሄድ ስብሰባ ላይ በመገኘት ብቻ እናንተ ከምታስቡት በላይ ትምህርት ሊቀስሙ ይችላሉ። ልጆቻችሁ ጉባኤው የሚመራበትን ቋንቋ በደንብ የማይረዱት ከሆነ ግን ብዙም ጥቅም ላያገኙ ይችላሉ።—1 ቆሮ. 14:11፤ w17.05 10 አን. 10-11

ቅዳሜ፣ መስከረም 28

ሕዝቡም ፈቃደኛ ስለሆነ፣ ይሖዋን አወድሱ!—መሳ. 5:2

ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው፦ ‘ያለኝን ነገር ሁሉ የይሖዋን ግልጽ ትእዛዝ ለመፈጸም ለማዋል የሚያስችል እምነትና ድፍረት አለኝ? የተሻለ ኑሮ ለማግኘት ስል ወደ ሌላ ከተማ ወይም አገር ለመዛወር እያቀድኩ ከሆነ፣ ይህ በቤተሰቤና በጉባኤዬ ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ በጸሎት አስቤበታለሁ?’ ይሖዋ ሉዓላዊነቱን በመደገፍ ረገድ የራሳችንን አስተዋጽኦ እንድናበረክት በመፍቀድ እንደሚያከብረን አሳይቷል። ዲያብሎስ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት በማታለል የይሖዋን ሉዓላዊነት እንዲቃወሙና እሱን እንዲደግፉ አድርጓል፤ እኛ ግን የይሖዋን አገዛዝ ስንደግፍ ከማን ጎን እንደቆምን ሰይጣን በግልጽ እንዲያይ እናደርጋለን። እምነትና ታማኝነት ለይሖዋ አገልግሎት ራስህን በፈቃደኝነት እንድታቀርብ ያነሳሳሃል፤ ይህን ማድረግህ ደግሞ ይሖዋን ያስደስተዋል። (ምሳሌ 23:15, 16) ከይሖዋ ጎን ከቆምክ አምላክ እሱን ለሚነቅፈው ለሰይጣን መልስ መስጠት ይችላል። (ምሳሌ 27:11) በመሆኑም ይሖዋን በታማኝነት ስትታዘዘው እሱ ከፍ አድርጎ የሚመለከተውን ነገር እየሰጠኸው ነው ሊባል ይችላል፤ እሱም በዚህ በጣም ይደሰታል። w17.04 32 አን. 15-16

እሁድ፣ መስከረም 29

ለአምላክ ስእለት በምትሳልበት ጊዜ ሁሉ ስእለትህን ለመፈጸም አትዘግይ፤ እሱ በሞኞች አይደሰትምና። ስእለትህን ፈጽም።—መክ. 5:4

የሙሴ ሕግ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው ለይሖዋ ስእለት ቢሳል ወይም . . . በመሐላ ራሱን ግዴታ ውስጥ ቢያስገባ ቃሉን ማጠፍ የለበትም። አደርገዋለሁ ብሎ የማለውን ነገር ሁሉ መፈጸም አለበት።” (ዘኁ. 30:2) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሰለሞን በመንፈስ መሪነት በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ጽፏል። ኢየሱስም ስእለት ወይም መሐላ ምን ያህል በቁም ነገር ሊታይ እንደሚገባ ሲጠቁም እንዲህ ብሏል፦ “በጥንት ዘመን ለነበሩት ‘በከንቱ አትማል፤ ይልቁንም ለይሖዋ የተሳልከውን ፈጽም’ እንደተባለ ሰምታችኋል።” (ማቴ. 5:33) በእርግጥም ለአምላክ የገባነውን ቃል በቁም ነገር ልናየው ይገባል። ቃላችንን መጠበቅ አለመጠበቃችን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ይነካዋል። ዳዊት “ወደ ይሖዋ ተራራ መውጣት የሚችል ማን ነው? በቅዱስ ስፍራውስ ሊቆም የሚችል ማን ነው?” ብሎ ከጠየቀ በኋላ “[በይሖዋ] ሕይወት በሐሰት ያልማለ፣ በማታለልም መሐላ ያልፈጸመ” በማለት መልስ ሰጥቷል።—መዝ. 24:3, 4 ግርጌ፤ w17.04 4 አን. 3-4

ሰኞ፣ መስከረም 30

በአንደበቱ ስም አያጠፋም።—መዝ. 15:3

በጉባኤ ውስጥ ፍትሕ የጎደለው ድርጊት እንደተፈጸመብን ከተሰማን ስለ ጉዳዩ ሐሜት ላለማሰራጨት መጠንቀቅ ይኖርብናል። እርግጥ ነው፣ አንድ የጉባኤው አባል ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ካወቅን የሽማግሌዎችን እርዳታ መጠየቃችንና ስለ ጉዳዩ ለእነሱ መናገራችን ተገቢ ነው። (ዘሌ. 5:1) ይሁንና ብዙውን ጊዜ የሚያጋጥሙን ሁኔታዎች ከባድ ኃጢአት ከመፈጸም ጋር የተያያዙ አይደሉም፤ በዚህ ጊዜ ለማንም ሰው ሌላው ቀርቶ ለጉባኤ ሽማግሌዎችም እንኳ ሳንናገር ችግሩን መፍታት እንችል ይሆናል። (ማቴ. 5:23, 24፤ 18:15) ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ ጉዳዩን በመፍታት ታማኝነት እናሳይ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በደል እንደደረሰብን የተሰማን ሁኔታውን በተሳሳተ መንገድ ስለተረዳነው እንደሆነ እንገነዘብ ይሆናል። ይህን ስናውቅ፣ የእምነት ባልንጀራችንን ስም በማጥፋት ጉዳዩ እንዲባባስ ባለማድረጋችን እንደምንደሰት የታወቀ ነው! ደግሞም የተሰማን ስሜት ትክክል ሆነም አልሆነ፣ ሐሜት ማሰራጨት የተፈጠረውን ሁኔታ ለማስተካከል ሊረዳ እንደማይችል ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። ለይሖዋና ለወንድሞቻችን ያለን ታማኝነት እንዲህ ያለ ስህተት እንዳንሠራ ይጠብቀናል። w17.04 21 አን. 14

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ