ጥቅምት
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 1
ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና ይሰጣል።—ያዕ. 1:5
ይሖዋ የጥበብ ምንጭ ሲሆን ይህን ጥበብ ለሌሎች በልግስና ይሰጣል። አምላክ የሚሰጠውን ጥበብ ማግኘት የምንችልበት አንዱ መንገድ እሱ የሚሰጠንን ተግሣጽ በመቀበል ነው። ይህ ጥበብ ደግሞ ከሥነ ምግባራዊና ከመንፈሳዊ ጉዳት ይጠብቀናል። (ምሳሌ 2:10-12) ይህም ‘ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ በመኖር’ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ያስችለናል። (ይሁዳ 21) ሆኖም ወደ ኃጢአት ያዘነበለው ሥጋችን፣ አስተዳደጋችንና ሌሎች ምክንያቶች ተግሣጽን መቀበል ወይም ለተግሣጽ ትክክለኛውን አመለካከት መያዝ ተፈታታኝ እንዲሆንብን ሊያደርጉ ይችላሉ። ተግሣጽ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች በገዛ ሕይወታችን ስንመለከት ግን አምላክ ምን ያህል እንደሚወደን እንገነዘባለን፤ ይህም ለተግሣጽ አድናቆት እንድናዳብር ይረዳናል። ምሳሌ 3:11, 12 “ልጄ ሆይ፣ የይሖዋን ተግሣጽ ለመቀበል እንቢተኛ አትሁን፤ . . . ይሖዋም የሚወዳቸውን ይወቅሳልና” ይላል። አዎ፣ ይሖዋ ለእኛ የሚበጀንን ነገር እንደሚያደርግ ፈጽሞ አንዘንጋ። (ዕብ. 12:5-11) ደግሞም አምላክ እኛን በሚገባ ስለሚያውቀን እሱ የሚሰጠን ተግሣጽ ምንጊዜም ትክክለኛና ከተገቢው መጠን የማያልፍ ነው። w18.03 28 አን. 1-2
ረቡዕ፣ ጥቅምት 2
አንዳችሁ ለሌላው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳዩ።—1 ጴጥ. 4:9
ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን ሐሳብ የጻፈው የተለያየ ባሕል ያላቸው ክርስቲያኖችን ላቀፉት በትንሿ እስያ ለሚገኙት ጉባኤዎች ነው። በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ወንድሞች “እንደ እሳት [ያሉ] ከባድ ፈተናዎች” አጋጥመዋቸዋል። ታዲያ በየትኛውም ቦታ የሚገኙ ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉትን አስጨናቂ ነገሮች እንዲቋቋሙ ሊረዳቸው የሚችለው ምንድን ነው? (1 ጴጥ. 1:1፤ 4:4, 7, 12) ጴጥሮስ፣ ክርስቲያን ወንድሞቹንና እህቶቹን ያበረታታቸው ‘አንዳቸው ሌላውን’ በእንግድነት እንዲቀበሉ በሌላ አባባል በደንብ የሚያውቋቸውንና የሚቀርቧቸውን ሰዎች እንዲያስተናግዱ መሆኑን ልብ እንበል። የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየታቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው? እርስ በርስ ያቀራርባቸዋል። አንተስ በግልህ ይህን አልተመለከትክም? ሌሎች ቤታቸው በእንግድነት ጋብዘውህ ያውቃሉ? በዚያ ወቅት ምን ያህል አስደሳች ጊዜ እንዳሳለፋችሁ ታስታውሳለህ? በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የጉባኤህን አባላት አንተ ስትጋብዛቸው ወዳጅነታችሁ አልተጠናከረም? ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በእንግድነት ስንቀበል እነሱን በቅርበት ለማወቅ የተሻለ አጋጣሚ እናገኛለን። በጴጥሮስ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ሁኔታዎች እየተባባሱ ሲሄዱ ይበልጥ መቀራረብ ያስፈልጋቸው ነበር። በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ከሚኖሩ ክርስቲያኖች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።—2 ጢሞ. 3:1፤ w18.03 14-15 አን. 1-3
ሐሙስ፣ ጥቅምት 3
መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና።—ማቴ. 5:3
መንፈሳዊ አስተሳሰብ መያዝን የሚያበረታቱ ሐሳቦችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። ሮም 8:6 መንፈሳዊ አስተሳሰብ ማዳበር ያለውን ጥቅም ሲገልጽ “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሞት ያስከትላልና፤ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ግን ሕይወትና ሰላም ያስገኛል” ይላል። በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት ካደረግን በአሁኑ ጊዜ ከአምላክ ጋር ያለንን ሰላም ጠብቀን መኖርና ውስጣዊ ሰላም ማግኘት እንችላለን፤ ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት እናገኛለን። ይሁንና የምንኖረው አደገኛ በሆነ ዓለም ውስጥ ነው። ሥጋዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ስለምንኖር መንፈሳዊ ሰው ለመሆንና መንፈሳዊነታችንን ጠብቀን ለማቆየት ብርቱ ትግል ማድረግ ያስፈልገናል። አንድ ሰው መንፈሳዊነቱን ካጣ የዚህ ዓለም የተበከለ ‘አየር’ አእምሮውንና አስተሳሰቡን በቀላሉ ይቆጣጠረዋል። አንዳንድ ሰዎች ዓለማዊ አስተሳሰብ ስለተቆጣጠራቸው ጨርሶ ‘መንፈሳዊ እንዳልሆኑ’ ወይም የአምላክ መንፈስ እንደሌላቸው ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ ተናግሯል።—ይሁዳ 18, 19፤ w18.02 19 አን. 5, 7፤ 20 አን. 8
ዓርብ፣ ጥቅምት 4
ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች . . . በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ።—2 ጢሞ. 3:13
በሕክምና መስክ የተሰማሩ በርካታ ባለሙያዎች ተላላፊ በሽታ የያዛቸውን ሰዎች ያክማሉ። እነዚህ ባለሙያዎች ለሕመምተኞቹ እንክብካቤ የሚያደርጉት ሊረዷቸው ስለሚፈልጉ ነው። ይህን ሲያደርጉ ግን በሽታው ወደ እነሱም እንዳይጋባ መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል። በተመሳሳይም ብዙዎቻችን የምንኖረውና የምንሠራው አምላክ የማይወዳቸውን ባሕርያት ከሚያንጸባርቁ ሰዎች ጋር ነው። በመሆኑም የእነዚህ ሰዎች አመለካከትና ዝንባሌ እንዳይጋባብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ከፍተኛ የሥነ ምግባር ውድቀት ይታያል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ ከአምላክ የራቁ ሰዎች ስለሚያሳዩአቸው ባሕርያት ጠቅሷል። (2 ጢሞ. 3:1-5) እንደነዚህ ዓይነት ባሕርያት እየተስፋፉ መሄዳቸው በጣም እንደሚረብሸን የታወቀ ነው፤ ያም ሆኖ እንዲህ ያሉት መጥፎ ባሕርያትና ዝንባሌዎች ወደ እኛም ሊጋቡ እንደሚችሉ ማስታወስ ይኖርብናል። (ምሳሌ 13:20) በመሆኑም ሰዎች አምላክን እንዲያውቁ በምንረዳበት ጊዜ የእነሱ መጥፎ ባሕርይ እንዳይጋባብን መከላከል ያስፈልገናል። w18.01 27 አን. 1-2
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 5
ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም [አጥምቋቸው]።—ማቴ. 28:19
ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ይኸውም በ33 ዓ.ም. ከ500 ለሚበልጡ ወንዶች፣ ሴቶችና ምናልባትም ልጆች ተገልጦ ነበር። ከላይ ያለውን መመሪያ የሰጠው በዚያ ወቅት ሳይሆን አይቀርም። (1 ቆሮ. 15:6) ኢየሱስ፣ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ስለማድረግ መመሪያ በሰጠበት ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተከታዮቹ በቦታው የነበሩ ይመስላል። ኢየሱስ ይህንን መመሪያ መስጠቱ፣ ጥምቀት የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የመሆንን ቀንበር ለመሸከም ከሚፈልጉ ሁሉ የሚጠበቅ ብቃት መሆኑን በግልጽ ያሳያል። (ማቴ. 11:29, 30) አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማገልገል የሚፈልግ ማንኛውም ሰው፣ ኢየሱስ በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ የሚጫወተው ሚና እንዳለ አምኖ መቀበል ይኖርበታል። ግለሰቡ ይህን አምኖ ከተቀበለ መጠመቅ ይችላል። በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የውኃ ጥምቀት ይህ ብቻ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በግልጽ እንደሚያሳየው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አዳዲስ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ጥምቀት አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበው ነበር። ደግሞም የሚጠመቁበትን ጊዜ ሳያስፈልግ አላዘገዩትም።—ሥራ 2:41፤ 9:18፤ 16:14, 15, 32, 33፤ w18.03 5 አን. 8
እሁድ፣ ጥቅምት 6
እጅግ የተወደድክ ዳንኤል ሆይ።—ዳን. 10:11
የምንኖርበት ዓለም “የአጋንንት መኖሪያ” የሆነችውና በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ የምትወክለው ታላቂቱ ባቢሎን በምታሳድረው ተጽዕኖ የተነሳ በሥነ ምግባራዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ የተበላሸ ነው። (ራእይ 18:2) በመሆኑም ከሌሎች ለየት ብለን ልንታይ አልፎ ተርፎም ሰዎች ሊያፌዙብን ይችላሉ። (ማር. 13:13) ስለዚህ ልክ እንደ ዳንኤል አምላካችን ወደሆነው ወደ ይሖዋ መቅረባችን አስፈላጊ ነው። ትሑትና ታዛዥ በመሆን በእሱ የምንታመን ከሆነ ይሖዋ ልክ እንደ ዳንኤል ውድ አድርጎ ይመለከተናል። (ሐጌ 2:7 ግርጌ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆችም የዳንኤል ወላጆች ከተዉት ምሳሌ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። እንዴት? ዳንኤል ልጅ በነበረበት ጊዜ በይሁዳ ውስጥ ክፋት ተስፋፍቶ የነበረ ቢሆንም ዳንኤል ከልጅነቱ ጀምሮ ለአምላክ ፍቅር አዳብሯል። ይህ ወላጆቹ ጥሩ አድርገው እንዳሠለጠኑት የሚያሳይ ነው። (ምሳሌ 22:6) “አምላክ ፈራጄ ነው” የሚል ትርጉም ያለው የዳንኤል ስም ራሱ ወላጆቹ አምላክን የሚፈሩ ሰዎች እንደነበሩ ይጠቁማል። (ዳን. 1:6 ግርጌ) ስለዚህ ወላጆች፣ በልጆቻችሁ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ በትዕግሥት አስተምሯቸው። (ኤፌ. 6:4) በተጨማሪም አብራችኋቸው ጸልዩ፤ ለእነሱም ጸልዩላቸው። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ ለመቅረጽ ጥረት ስታደርጉ የይሖዋ የተትረፈረፈ በረከት እንደማይለያችሁ እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ።—መዝ. 37:5፤ w18.02 5 አን. 12፤ 6 አን. 14-15
ሰኞ፣ ጥቅምት 7
ሁሉም ነገር የተገኘው ከአንተ ነውና፤ የሰጠንህም ከገዛ እጅህ የተቀበልነውን ነው።—1 ዜና 29:14
መስጠት የአምልኳችን አንዱ ክፍል ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በሰማይ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲህ ብለው ሲናገሩ በራእይ ተመልክቷል፦ “ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ እንዲሁም ወደ ሕልውና የመጡትም ሆነ የተፈጠሩት በአንተ ፈቃድ ስለሆነ ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።” (ራእይ 4:11) ይሖዋ ግርማና ክብር የሚገባው አምላክ እንደመሆኑ መጠን ምርጣችንን በመስጠት ልናከብረው ይገባል ቢባል አትስማማም? ይሖዋ በዓመት ሦስት ጊዜ በሚከበሩት በዓላት ወቅት እስራኤላውያን በፊቱ እንዲቀርቡ በሙሴ በኩል አዟቸው ነበር። እስራኤላውያን ይሖዋን ለማምለክ በሚሰበሰቡባቸው በእነዚያ በዓላት ወቅት ‘ባዶ እጃቸውን ይሖዋ ፊት አይቀርቡም’ ነበር። (ዘዳ. 16:16) ዛሬም በተመሳሳይ የይሖዋን ድርጅት ምድራዊ ክፍል ለመደገፍና አድናቆታችንን ለመግለጽ የራሳችንን ጥቅም መሥዕዋት በማድረግ በልግስና እንሰጣለን፤ ይህም የአምልኳችን አንዱ ክፍል ነው። w18.01 18 አን. 4-5
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 8
እረፍት እሰጣችኋለሁ።—ማቴ. 11:28
ኢየሱስ በዕለት ጥቅሱ ላይ ያለውን ሐሳብ ከተናገረ በኋላ “ቀንበሬን ተሸከሙ፤ . . . ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና” ብሏል። (ማቴ. 11:29, 30) ብዙዎቻችን የዚህን አባባል እውነተኝነት በሕይወታችን ተመልክተናል! አንዳንድ ጊዜ ወደ ጉባኤ ስብሰባ ለመሄድ ወይም በመስክ አገልግሎት ለመካፈል ከቤታችን ስንወጣ በጣም ዝለን ሊሆን ይችላል። ወደ ቤታችን የምንመለሰው ግን መንፈሳችን ታድሶ እንዲሁም የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል አግኝተን ነው። በእርግጥም የኢየሱስ ቀንበር ልዝብ ነው! ኬላ የተባለች እህት ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድረም በተባለ ከፍተኛ ድካም የሚያስከትልና አቅም የሚያሳጣ ሕመም፣ በመንፈስ ጭንቀት እንዲሁም በጣም ኃይለኛ በሆነ ራስ ምታት ትሠቃያለች። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይከብዳታል። ይሁንና በአንድ ወቅት እንደምንም ብላ ወደ ስብሰባ በመሄድ የሕዝብ ንግግር ካዳመጠች በኋላ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ንግግሩ ስለ ተስፋ መቁረጥ የሚያወሳ ነበር። ተናጋሪው ንግግሩን ያቀረበው የሌሎችን ችግር እንደሚረዳና እንደሚያስብላቸው በሚያሳይ መንገድ ስለነበር አለቀስኩ። ይህ አጋጣሚ፣ ሁልጊዜ በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዳለብኝ እንዳስታውስ አድርጎኛል።” ኬላ በስብሰባ ላይ ለመገኘት ጥረት በማድረጓ በእጅጉ እንደተደሰተች ጥርጥር የለውም! w18.01 8-9 አን. 6-7
ረቡዕ፣ ጥቅምት 9
እግሮቼ ከመንገድ ሊወጡ ተቃርበው ነበር።—መዝ. 73:2
ልጃችሁ ከተጠመቀ በኋላ ያመነበትን ነገር ውሎ አድሮ መጠራጠር ቢጀምርስ? ለምሳሌ ያህል፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ የተጠመቀ ልጅ በዓለም ላይ ባሉ ነገሮች ይማረክ አሊያም ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መመራት ጠቃሚ መሆኑን ይጠራጠር ይሆናል። (መዝ. 73:1, 3, 12, 13) ወላጆች፣ ልጃችሁ እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ እንዳለው ካስተዋላችሁ፣ እናንተ ጉዳዩን የምትይዙበት መንገድ ይሖዋን ማገልገሉን እንዲቀጥል አሊያም ጨርሶ እንዲያቆም ሊያደርግ እንደሚችል መገንዘብ ይኖርባችኋል። ልጃችሁ በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኝ ቢሆን ከሚያነሳቸው ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከእሱ ጋር ጦርነት ልትከፍቱ አይገባም። ዓላማችሁ ልጃችሁን በፍቅርና በደግነት መርዳት ሊሆን ይገባል። እርግጥ ነው፣ አንድ የተጠመቀ ወጣት ለይሖዋ ራሱን እንደወሰነ ሊዘነጋ አይገባም። ራሱን ሲወስን፣ አምላክን ለመውደድና የእሱን ፈቃድ ከምንም ነገር በላይ ለማስቀደም ቃል ገብቷል። (ማር. 12:30) ይሖዋ፣ አንድ ሰው በዚህ መንገድ የገባውን ቃል አቅልሎ አይመለከተውም፤ በመሆኑም እንዲህ ያለ ቃል የገባ ማንኛውም ሰው ጉዳዩን በቁም ነገር ሊመለከተው ይገባል።—መክ. 5:4, 5፤ w17.12 22 አን. 16-17
ሐሙስ፣ ጥቅምት 10
[ወንድሜ] በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ።—ዮሐ. 11:24
የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች እንደ ማርታ ወደፊት ትንሣኤ እንደሚኖር ያውቁ ነበር። አብርሃም ለረጅም ጊዜ ጠብቆ ያገኘውን ወራሹን ይስሐቅን በተመለከተ ምን ዓይነት ትእዛዝ እንደተሰጠው እስቲ እንመልከት። ይሖዋ፣ አብርሃምን “እባክህ ልጅህን፣ በጣም የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን . . . የሚቃጠል መባ አድርገህ አቅርበው” ብሎት ነበር። (ዘፍ. 22:2) እንዲህ ያለ ትእዛዝ ምን ዓይነት ስሜት ሊያሳድር እንደሚችል እስቲ አስበው። ይሖዋ በአብርሃም ዘር አማካኝነት የምድር ብሔራት ሁሉ እንደሚባረኩ ቃል ገብቷል። (ዘፍ. 13:14-16፤ 18:18፤ ሮም 4:17, 18) ከዚህም በላይ ይሖዋ፣ ይህ ዘር የሚመጣው “በይስሐቅ በኩል” እንደሚሆን ገልጿል። (ዘፍ. 21:12) ይሁን እንጂ አብርሃም ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበው ይህ ተስፋ እንዴት ሊፈጸም ነው? አምላክ ይስሐቅን ከሞት ሊያስነሳው እንደሚችል አብርሃም እምነት እንደነበረው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት አብራርቷል። (ዕብ. 11:17-19) አብርሃም ልጁ መቼ እንደሚነሳ ያውቅ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ አይገልጽም። ሆኖም አብርሃም ይሖዋ ይስሐቅን እንደሚያስነሳው ይተማመን ነበር። w17.12 6 አን. 12-14
ዓርብ፣ ጥቅምት 11
ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ [ነኝ]።—ሥራ 20:26
እኛም እንደ ጳውሎስ ለሕይወት የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ጥረት ማድረግ አለብን። ይሖዋ፣ ሰው “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ” ይፈልጋል። (2 ጴጥ. 3:9) አንተስ እንዲህ ዓይነት ፍላጎት አለህ? ይበልጥ መሐሪ ለመሆንና የርኅራኄ ስሜት ለማዳበር የምንጥር ከሆነ በአገልግሎታችን ይበልጥ በቅንዓት ለመካፈል እንነሳሳለን፤ ይህን ስናደርግ ደግሞ ይበልጥ ደስተኞች እንሆናለን። ስለ ሕይወት የይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንዳለን ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ነገሮችን ለማስወገድ በመጣር ነው። በምናሽከረክርበትም ሆነ ሌሎች ነገሮችን በምንሠራበት ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፤ የአምልኮ ቦታችንን ስንገነባ፣ ስናድስ ወይም ወደ እነዚህ ቦታዎች ስንጓዝም ተመሳሳይ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። ይበልጥ ሊያሳስበን የሚገባው የራሳችንም ሆነ የሌሎች ደህንነትና ጤንነት እንጂ አንድን ነገር በታቀደለት ጊዜ መጨረሳችን፣ ብዙ መሥራት መቻላችን አሊያም የገንዘብ ጉዳይ አይደለም። ፍትሐዊ የሆነው አምላካችን ምንጊዜም የሚያደርገው ትክክልና ተገቢ የሆነውን ነገር ነው። እኛም እሱን መምሰል እንፈልጋለን። በተለይ ሽማግሌዎች የራሳቸውም ሆነ አብረዋቸው የሚሠሩት ሰዎች ደህንነት ለአደጋ እንዳይጋለጥ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። (ምሳሌ 22:3) አንድ ሽማግሌ የደህንነት መመሪያዎችን እንድትከተል ከጠቆመህ ምክሩን ተግባራዊ አድርገው። (ገላ. 6:1) ለሕይወት የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ካዳበርክ “በደም ዕዳ ተጠያቂ [አትሆንም]።”—ዘዳ. 19:10፤ w17.11 15-16 አን. 11-12
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 12
ማንኛውም ሰው ሽልማቱን እንዲያሳጣችሁ አትፍቀዱ።—ቆላ. 2:18
በዛሬው ጊዜ ያሉ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “አምላክ . . . የሚሰጠውን የሰማያዊውን ሕይወት ሽልማት” የማግኘት ግሩም ተስፋ አላቸው። (ፊልጵ. 3:14) ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚነግሡበትን እንዲሁም የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ ለመርዳት ከእሱ ጋር ሆነው የሚሠሩበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። (ራእይ 20:6) አምላክ ለእነዚህ ክርስቲያኖች የሰጣቸው ተስፋ ምንኛ አስደናቂ ነው! ሌሎች በጎች የተባሉት ክርስቲያኖች ደግሞ ከዚህ የተለየ ተስፋ አላቸው። በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ሽልማት ተዘጋጅቶላቸዋል፤ ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ተስፋ ነው! (2 ጴጥ. 3:13) ጳውሎስ እንደ እሱ ቅቡዓን የሆኑት ክርስቲያኖች ታማኝ ሆነው እንዲኖሩና ሽልማቱን ማግኘት እንዲችሉ ለመርዳት ሲል “አእምሯችሁ . . . ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አድርጉ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ቆላ. 3:2) እነዚህ ክርስቲያኖች ውድ በሆነው ሰማያዊ ውርሻቸው ላይ ትኩረት ማድረግ ነበረባቸው። (ቆላ. 1:4, 5) በእርግጥም የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ፣ ይሖዋ ቃል በገባላቸው በረከቶች ላይ ማሰላሰላቸው ዓይናቸው በሽልማታቸው ላይ እንዲያተኩር ይረዳቸዋል።—1 ቆሮ. 9:24፤ w17.11 25 አን. 1-2
እሁድ፣ ጥቅምት 13
ለይሖዋ . . . ዘምሩ።—መዝ. 96:1
ለይሖዋ ‘በደስታ ዘምሩ’ በተባለው የመዝሙር መጽሐፍ ላይ የሚገኙት ብዙዎቹ መዝሙሮች የጸሎት ይዘት አላቸው። በእነዚህ መዝሙሮች አማካኝነት የውስጥ ስሜትህን ለይሖዋ መግለጽ ትችላለህ። ሌሎቹ መዝሙሮች ደግሞ “ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች [ያነቃቁናል]።” (ዕብ. 10:24) የመዝሙሮቹን ዜማ፣ ምት እና ግጥም በደንብ ለማወቅ ጥረት ልናደርግ ይገባል። jw.org ላይ የሚገኘውን በዘማሪዎች ቡድን በእንግሊዝኛ የተዘመረ መዝሙር ማዳመጣችን በዚህ ረገድ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። መዝሙሮቹን ቤታችን ሆነን መለማመዳችን በልበ ሙሉነትና ከልብ በመነጨ ስሜት ለመዘመር ያስችለናል። መዝሙር በአምልኳችን ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንደሆነ አንዘንጋ። ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና አድናቆት ለመግለጽ የሚያስችል ግሩም መንገድ ነው። (ኢሳ. 12:5) ድምፅህን ከፍ አድርገህ ከልብህ ስትዘምር ሌሎችም በልበ ሙሉነት እንዲዘምሩ ታበረታታለህ። በእርግጥም ወጣቶችን፣ አዋቂዎችንና አዲሶችን ጨምሮ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሁሉ በመዝሙር አማካኝነት ለይሖዋ በምናቀርበው አምልኮ መካፈል ይችላሉ። እንግዲያው መዝሙር ከመዘመር ወደኋላ አንበል። አዎን ሁላችንም በደስታ እንዘምር! w17.11 7 አን. 18-19
ሰኞ፣ ጥቅምት 14
እንደ እባብ ጠንቃቆች፣ እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ።—ማቴ. 10:16
በዛሬው ጊዜ ብዙ ስደተኞች የሚመጡት በስብከቱ ሥራችን ላይ ገደብ ከተጣለባቸው አገሮች ነው። ስደተኞችን በሚቀበሉ አገሮች ውስጥ ላሉ ቀናተኛ ምሥክሮች ምስጋና ይግባቸውና፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች “የመንግሥቱን ቃል” ለመጀመሪያ ጊዜ የመስማት አጋጣሚ አግኝተዋል። (ማቴ. 13:19, 23) ‘ሸክማቸው የከበዳቸው’ ብዙ ሰዎች በስብሰባዎቻችን ላይ ተገኝተው መንፈሳዊ እርዳታ በማግኘታቸው “አምላክ በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” ለማለት ችለዋል። (ማቴ. 11:28-30፤ 1 ቆሮ. 14:25) ለስደተኞች የሚሰብኩ ክርስቲያኖች “ጠንቃቆች” አልፎ ተርፎም ‘ብልሆች’ መሆን ይኖርባቸዋል። (ምሳሌ 22:3) የሚያሳስባቸውን ጉዳይ ሲነግሯችሁ በጥሞና ማዳመጥ ያለባችሁ ቢሆንም ስለ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ከመወያየት ተቆጠቡ። ቅርንጫፍ ቢሮውም ሆነ የአካባቢው ባለሥልጣናት የሚሰጧችሁን መመሪያ ተከተሉ፤ ራሳችሁንም ሆነ ሌሎችን ለአደጋ የሚያጋልጥ ምንም ነገር አታድርጉ። ለስደተኞቹ ሃይማኖትና ባሕል አክብሮት እንዳላችሁ አሳዩ። ለምሳሌ ያህል፣ ከአንዳንድ አገሮች የሚመጡ ሰዎች ተገቢ ስለሚባለው የሴቶች አለባበስ የራሳቸው አመለካከት ያላቸው ሲሆን ከዚያ የተለየ አለባበስ ቅር ያሰኛቸዋል። ስለዚህ ለስደተኞች ስትሰብኩ እነሱን ላለማስከፋት በአለባበሳችሁ ረገድ መጠንቀቅ ያስፈልጋችኋል። w17.05 7 አን. 17-18
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 15
ንግግራችሁ ምንጊዜም . . . ለዛ ያለው ይሁን።—ቆላ. 4:6
ከማያምኑ ቤተሰቦቻችን ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን ማንጸባረቅ እንድንችል ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን መጠየቅ እንችላለን። እያንዳንዱን የሐሰት ሃይማኖት ትምህርት እያነሳን ከእነሱ ጋር መከራከር አይኖርብንም። አንዳንድ ጊዜ ቤተሰቦቻችን በንግግራቸው ወይም በድርጊታቸው ሊጎዱን ይችላሉ፤ በዚህ ጊዜ ሐዋርያት የተዉትን ምሳሌ ለመከተል ጥረት እናደርጋለን። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሲሰድቡን እንባርካለን፤ ስደት ሲያደርሱብን በትዕግሥት እናሳልፋለን፤ ስማችንን ሲያጠፉ በለዘበ አንደበት እንመልሳለን።” (1 ቆሮ. 4:12, 13) ተቃዋሚ የሆኑ ቤተሰቦቻችንን በለዘበ አንደበት ማነጋገራችን ከእነሱ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን የሚረዳ ቢሆንም የበለጠ ውጤት የሚያስገኘው ግን የምናሳየው መልካም ምግባር ነው። (1 ጴጥ. 3:1, 2, 16) በመሆኑም ቤተሰቦችህ የይሖዋ ምሥክሮች አስደሳች ትዳር እንዳላቸው፣ ልጆቻቸውን ጥሩ አድርገው እንደሚያሳድጉ፣ ንጹሖችና ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች እንደሆኑ እንዲሁም አርኪ ሕይወት እንደሚመሩ ከግል ሕይወትህ መመልከት እንዲችሉ አድርግ። ቤተሰቦችህ ወደ እውነት ባይመጡ እንኳ ታማኝ በመሆን ይሖዋን እንዳስደሰትከው ማወቅህ እርካታ ይሰጥሃል። w17.10 15 አን. 13-14
ረቡዕ፣ ጥቅምት 16
ተቀባይነት ሊያገኝ እንደሚገባው . . . ሠራተኛ አድርገህ ራስህን በአምላክ ፊት [አቅርብ]።—2 ጢሞ. 2:15
በዘመናችን ያሉ በርካታ ሰዎች የአምላክን ቃል በማጥናት ትልቅ ለውጥ ማድረጋቸው ሊያስገርመን ይገባል? በፍጹም! እንዲህ ያሉ ተሞክሮዎች፣ ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ የነበራቸውን በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ ክርስቲያኖች ያስታውሱናል። (1 ቆሮ. 6:9-11) ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህ ክርስቲያኖች የአምላክን መንግሥት እንዳይወርሱ የሚያደርጓቸውን የተለያዩ ድርጊቶች ከዘረዘረ በኋላ “አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ” በማለት ተናግሯል። ሆኖም እነዚህ ሰዎች በቅዱሳን መጻሕፍትና በአምላክ መንፈስ እርዳታ ለውጥ ማድረግ ችለዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ እውነትን ከተቀበሉ በኋላም ከባድ መንፈሳዊ ችግሮችን ማሸነፍ ነበረባቸው። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንድ ቅቡዕ ወንድም ከክርስቲያን ጉባኤ እንደተወገደና ከጊዜ በኋላ እንደተመለሰ ይናገራል። (1 ቆሮ. 5:1-5፤ 2 ቆሮ. 2:5-8) እነዚህ የእምነት ባልንጀሮቻችን የተለያዩ ችግሮች እንዳጋጠሟቸውና ከአምላክ ቃል ባገኙት እርዳታ እነዚህን ችግሮች እንደተወጡ ማንበባችን የሚያበረታታ አይደለም? በእርግጥም በእጃችን የሚገኘውን ይህን መሣሪያ በጥሩ ሁኔታ ልንጠቀምበት እንፈልጋለን። w17.09 23-24 አን. 2-3
ሐሙስ፣ ጥቅምት 17
በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።—1 ዮሐ. 3:18
ትክክለኛ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተው ፍቅር ማለትም አጋፔ ከይሖዋ የተገኘ ስጦታ ነው። የዚህ ፍቅር ምንጭ ይሖዋ ነው። (1 ዮሐ. 4:7) አጋፔ ከሁሉ የላቀው የፍቅር ዓይነት ነው። ይህ የፍቅር ዓይነት ለአንድ ሰው የሚኖረንን የመውደድ ስሜት የሚያካትት ቢሆንም በዋነኝነት የሚገለጸው ግን ለሌሎች ጥቅም ስንል በምናከናውነው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ተግባር ነው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ፣ አጋፔ የተባለውን የፍቅር ዓይነት “ለይቶ ማወቅ የሚቻለው በሚያከናውነው ተግባር ብቻ ነው” በማለት ገልጿል። ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ለሌሎች ስናሳይ ወይም ሌሎች እንዲህ ያለውን ፍቅር ሲያሳዩን ሕይወታችን አስደሳችና ትርጉም ያለው ይሆናል። ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ከመፍጠሩ በፊትም እንኳ ለሰው ልጆች ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። የሰው ልጆች ዘላለማዊ መኖሪያ የሆነችውን ምድርን የፈጠራት በሕይወት ለመቀጠል የሚያስፈልጉ ነገሮችን ብቻ እንድታሟላ አድርጎ ሳይሆን ሰዎች ደስተኛ ሆነው እንዲኖሩባት በሚያስችል መንገድ ነው። ይሖዋ ይህን ያደረገው ሙሉ በሙሉ ለእኛ ጥቅም በማሰብ እንጂ ለእሱ የሚያስገኝለት ነገር ስላለ አይደለም። በተጨማሪም ይሖዋ በምድር ላይ ያሉ ልጆቹን በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ በመስጠት የባረካቸው ሲሆን በዚህ መንገድ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። w17.10 7 አን. 1-2
ዓርብ፣ ጥቅምት 18
ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።—ያዕ. 2:8
ያዕቆብ “ማዳላታችሁን የማትተዉ ከሆነ . . . ኃጢአት እየሠራችሁ ነው” በማለት አክሎ ተናግሯል። (ያዕ. 2:9) በተቃራኒው ግን ፍቅር በትምህርት ደረጃ፣ በዘር አሊያም በኑሮ ደረጃ አድልዎ ከማድረግ እንድንርቅ ያነሳሳናል። በእርግጥም አድልዎ አለማድረግ እንደ ጭንብል ከላይ የምናጠልቀው ነገር መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ እውነተኛ የስብዕናችን ገጽታ ሊሆን ይገባል። በተጨማሪም ፍቅር “ታጋሽና ደግ ነው” እንዲሁም “አይታበይም።” (1 ቆሮ. 13:4) የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ሰዎች መናገር ትዕግሥት፣ ደግነትና ትሕትና ማሳየትን እንደሚጠይቅ አይካድም። (ማቴ. 28:19) እነዚህን ባሕርያት ማንጸባረቃችን በጉባኤያችን ውስጥ ካሉት ከሁሉም ወንድሞችና እህቶች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረንም ይረዳናል። እንዲህ ያለውን ፍቅር ማሳየት ምን በረከት ያስገኛል? ጉባኤዎቻችን አንድነት እንዲኖራቸውና ይሖዋን የሚያስከብሩ እንዲሆኑ ያስችላል። ይህ ደግሞ አዳዲሶች ወደ ይሖዋ ቤት እንዲሳቡ ያደርጋል። ስለ አዲሱ ስብዕና የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የሚከተለውን ሐሳብ በመናገር የሚደመደም መሆኑ የተገባ ነው፦ “በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ላይ ፍቅርን ልበሱ፤ ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነውና።”—ቆላ. 3:14፤ w17.08 26 አን. 18-19
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 19
ይሖዋ ለሕዝቡ . . . ስለራራ መልእክተኞቹን እየላከ በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃቸው ነበር።—2 ዜና 36:15
እኛም ከኃጢአት መንገዳቸው በመመለስ የአምላክን ሞገስ ሊያገኙ ለሚችሉ ሰዎች ተመሳሳይ ርኅራኄ ልናሳይ አይገባም? ይሖዋ በቅርቡ በሚመጣው የፍርድ ቀን ማንም ሰው እንዲጠፋ አይፈልግም። (2 ጴጥ. 3:9) በመሆኑም ይሖዋ ክፉዎችን ለማጥፋት እርምጃ እስኪወስድ ድረስ የእሱን ርኅራኄ የሚያሳየውን የማስጠንቀቂያ መልእክት ማወጃችንን እንቀጥል። ርኅራኄ በማሳየት ረገድ ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ሕዝቡ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው ስለነበር” እጅግ ራርቶላቸዋል። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ያሉበትን አሳዛኝ ሁኔታ ሲመለከት ምን አደረገ? መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙ [ነገር] ያስተምራቸው ጀመር” ይላል። (ማቴ. 9:36፤ ማር. 6:34) ኢየሱስ ተራውን ሕዝብ የመርዳት አንዳች ፍላጎት ካልነበራቸው ከፈሪሳውያን ፈጽሞ የተለየ አመለካከት ነበረው። (ማቴ. 12:9-14፤ 23:4፤ ዮሐ. 7:49) አንተስ በመንፈሳዊ የተራቡ ሰዎችን የመርዳት ልባዊ ፍላጎት በማሳየት የኢየሱስን ምሳሌ ትከተላለህ? w17.09 9 አን. 6፤ 10 አን. 9
እሁድ፣ ጥቅምት 20
እርምጃ በምወስድበት ጊዜ ሊያግድ የሚችል ማን ነው?—ኢሳ. 43:13
ዮሴፍ ግብፅ ውስጥ እስር ቤት በነበረበት ወቅት፣ ከዚያ ወጥቶ በምድሪቱ ላይ ከፈርዖን ቀጥሎ ከፍተኛ ባለሥልጣን እንደሚሆን ብሎም ይሖዋ ሕዝቡን ከረሃብ ለመታደግ እንደሚጠቀምበት ሊገምት ይችላል? (ዘፍ. 40:15 ግርጌ፤ 41:39-43፤ 50:20) ይሖዋ የወሰደው እርምጃ ዮሴፍ ሊገምት ከሚችለው ሁሉ በላይ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ሣራም ብትሆን በዕድሜ ስለገፋች ይሖዋ የራሷን ልጅ እንደሚሰጣት ልትጠብቅ አትችልም። የይስሐቅ መወለድ፣ ሣራ ልትገምተው ከምትችለው ሁሉ በላይ እንደሚሆን ግልጽ ነው። (ዘፍ. 21:1-3, 6, 7) እርግጥ ነው፣ ቃል የተገባልን አዲስ ዓለም ከመምጣቱ በፊት ይሖዋ ችግሮቻችንን ሁሉ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ያስወግድልናል ብለን አንጠብቅም፤ እንዲሁም ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ አንድ ዓይነት ተአምር እንዲፈጽምልን አንጠይቅም። ይሁንና አምላካችን ይሖዋ አገልጋዮቹን ከዚህ በፊት አስገራሚ በሆነ መንገድ እንደረዳቸውና ዛሬም ቢሆን እንዳልተለወጠ እናውቃለን። (ኢሳ. 43:10-12) ይሖዋ ፈቃዱን በተሟላ መንገድ መፈጸም እንድንችል የሚያስፈልገንን ኃይል ለመስጠት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ እርግጠኞች ነን። (2 ቆሮ. 4:7-9) በእርግጥም ይሖዋ ለእሱ ታማኝ እስከሆንን ድረስ ከአቅማችን በላይ እንደሆኑ የሚሰሙንን ችግሮች መወጣት እንድንችል ይረዳናል። w17.08 11-12 አን. 13-14
ሰኞ፣ ጥቅምት 21
የምታደርገውን ሁሉ ለይሖዋ አደራ ስጥ፤ ዕቅድህም ሁሉ ይሳካል።—ምሳሌ 16:3
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ጋር እንድትቀራረብና ጎልማሳ ክርስቲያን እንድትሆን ይረዳሃል። በተጨማሪም ብዙዎች በወጣትነታቸው ይሖዋን በሙሉ ጊዜያቸው ማገልገላቸው፣ በትዳራቸው ስኬታማ እንዲሆኑ እንደረዳቸው ተገንዝበዋል። ከማግባታቸው በፊት አቅኚነትን የጀመሩ አብዛኞቹ ክርስቲያኖችም፣ ከትዳር አጋራቸው ጋር በዚህ አገልግሎት መካፈላቸውን መቀጠል ችለዋል። (ሮም 16:3, 4) የልብህ ፍላጎት በምታወጣው ዕቅድ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። መዝሙር 20:4 “[ይሖዋ] የልብህን ፍላጎት ያሟላልህ፤ ዕቅድህንም ሁሉ ያሳካልህ” ይላል። እንግዲያው በሕይወትህ ምን ማድረግ እንደምትፈልግ በሚገባ አስብበት። ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ምን እያከናወነ እንዳለ እንዲሁም እሱን ለማገልገል አንተ ምን ማድረግ እንደምትችል አስብ። ከዚያም እሱን የሚያስደስተውን ነገር ለማድረግ ዕቅድ አውጣ። ይሖዋን በሙሉ ጊዜህ ማገልገል ጥልቅ እርካታ ያስገኝልሃል፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለ ሕይወት መምራትህ አምላክን ያስከብራል። ስለዚህ “በይሖዋ ሐሴት አድርግ፤ እሱም የልብህን መሻት ይሰጥሃል።”—መዝ. 37:4፤ w17.07 26 አን. 15-18
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 22
ያህን አወድሱ! . . . እሱን ማወደስ ደስ ያሰኛል፤ ደግሞም ተገቢ ነው።—መዝ. 147:1
አንድ ሰው የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ሲወጣ አሊያም ደግሞ ግሩም ክርስቲያናዊ ባሕርይ ሲያንጸባርቅ ልናመሰግነው እንደሚገባ ግልጽ ነው። ከሰዎች ጋር በተያያዘ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ አምላክንማ እንድናወድስ የሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች እንዳሉን ጥርጥር የለውም! ይሖዋን ድንቅ በሆነው የፍጥረት ሥራው ላይ ስለተንጸባረቀው ታላቅ ኃይሉ አሊያም ልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ለሰው ልጆች በመስጠት ስላሳየው ፍቅሩ ልናወድሰው እንችላለን። የመዝሙር 147 ጸሐፊ ይሖዋን ለማወደስ ተነሳስቷል። በተጨማሪም ሌሎችም አብረውት አምላክን እንዲያወድሱ አበረታትቷል። (መዝ. 147:7, 12) ይህን መዝሙር ማን እንደጻፈው አናውቅም፤ የመዝሙሩ ጸሐፊ የኖረው፣ እስራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ ይሖዋ በረዳቸው ጊዜ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። (መዝ. 147:2) የአምላክ ሕዝብ እውነተኛውን አምልኮ ወደሚያከናውኑበት ቦታ መመለሳቸው መዝሙራዊው፣ ይሖዋን እንዲያወድስ አነሳስቶት መሆን አለበት። አንተስ “ሃሌሉያህ!” ብለህ ከፍ ባለ ድምፅ ይሖዋን እንድታወድስ የሚያነሳሱህ በሕይወትህ ውስጥ የተፈጸሙ ምን ነገሮች አሉ?—መዝ. 147:1 ግርጌ፤ w17.07 17 አን. 1-3
ረቡዕ፣ ጥቅምት 23
በዓመፅ ሀብት ለራሳችሁ ወዳጆች አፍሩ፤ እነሱም የዓመፅ ሀብት ሲያልቅ በዘላለማዊ መኖሪያ ይቀበሏችኋል።—ሉቃስ 16:9
ኢየሱስ፣ አብዛኞቹ ተከታዮቹ ፍትሕ የጎደለው የንግድ ሥርዓት ባለበት በዚህ ዘመን መተዳደሪያ ማግኘት ከባድ ሊሆንባቸው እንደሚችል ያውቃል። ኢየሱስ ቁሳዊ ነገሮችን “የዓመፅ ሀብት” ብሎ የጠራቸው ለምን እንደሆነ ባይናገርም፣ ስግብግብነት የሚንጸባረቅበት የንግድ ሥርዓት በአምላክ ዓላማ ውስጥ እንዳልነበረ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን በኤደን እያሉ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ አትረፍርፎ ሰጥቷቸዋል። (ዘፍ. 2:15, 16) ከጊዜ በኋላ ደግሞ፣ አምላክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቅዱስ መንፈሱን ከሰጣቸው በኋላ የነበረውን ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “አንዳቸውም ቢሆኑ ያላቸው ማንኛውም ንብረት የግላቸው እንደሆነ አድርገው አይቆጥሩም ነበር፤ ከዚህ ይልቅ ያላቸው ነገር ሁሉ የጋራ ነበር።” (ሥራ 4:32) ነቢዩ ኢሳይያስም የሰው ልጆች በሙሉ የምድርን ሀብት በነፃ መጠቀም የሚችሉበት ጊዜ እንደሚመጣ ተንብዮአል። (ኢሳ. 25:6-9፤ 65:21, 22) እስከዚያው ድረስ ግን የኢየሱስ ተከታዮች በዛሬው ጊዜ ያለውን “የዓመፅ ሀብት” በመጠቀም መተዳደሪያ ለማግኘት፣ ‘አርቀው ማሰብ’ ወይም “ብልሆች” መሆን ያስፈልጋቸዋል፤ በእርግጥ ይህን ሲያደርጉ አምላክን ማስደሰት እንዳለባቸውም አይዘነጉም።—ሉቃስ 16:8፤ w17.07 8 አን. 4-6
ሐሙስ፣ ጥቅምት 24
ያለው ነገር ሁሉ በእጅህ ነው።—ኢዮብ 1:12
መጀመሪያ ላይ ከተጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አንዱ የሆነው የኢዮብ መጽሐፍ ‘ኢዮብ ከባድ መከራ ቢደርስበት አምላክን ይክዳል’ በማለት ሰይጣን ክስ እንደሰነዘረ ይናገራል። እንዲያውም ሰይጣን፣ አምላክ ኢዮብ ላይ መከራ እንዲያደርስበት ጥያቄ አቅርቧል። ይሖዋ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም። ይሁንና ሰይጣን ኢዮብን እንዲፈትነው ፈቀደለት። ኢዮብ በአጭር ጊዜ ውስጥ አገልጋዮቹን፣ መተዳደሪያውንና የሚወዳቸውን አሥር ልጆቹን አጣ። ሰይጣን፣ በኢዮብ ላይ መከራ ያመጣው አምላክ ራሱ እንደሆነ ለማስመሰል ሞክሯል። (ኢዮብ 1:13-19) ከዚያም ሰይጣን፣ ኢዮብ አሰቃቂ በሆነ ሕመም እንዲሠቃይ አደረገ። (ኢዮብ 2:7) በዚህ ላይ ደግሞ ሚስቱም ሆነች አጽናኝ መስለው የቀረቡት ሦስት ጓደኞቹ የተናገሩት ተስፋ አስቆራጭ ንግግር ሥቃዩን አባባሰበት። (ኢዮብ 2:9፤ 3:11፤ 16:2) ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? የሰይጣን ክስ ሙሉ በሙሉ ውሸት መሆኑ ተረጋገጠ። ኢዮብ አምላክን ለመካድ ፈቃደኛ አልሆነም።—ኢዮብ 27:5፤ w17.06 24 አን. 9-10
ዓርብ፣ ጥቅምት 25
አንድ ሰው . . . ለቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማያቀርብ ከሆነ እምነትን የካደ [ነው]።—1 ጢሞ. 5:8
በዛሬው ጊዜ ያሉ የቤተሰብ ራሶች ቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር የማሟላት ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። ይህን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ጠንክረው መሥራት ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ በዚህ የመጨረሻ ዘመን ሰብዓዊ ሥራ ብዙውን ጊዜ ውጥረት የሚፈጥር ነገር ሆኗል። በዛሬው ጊዜ ካሉት የሥራ አጋጣሚዎች አንጻር የሠራተኞች ቁጥር ብዙ በመሆኑ ሥራ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው። በርካታ ሠራተኞች ለረጅም ሰዓት ለመሥራት ይገደዳሉ፤ አንዳንድ ጊዜም የሚሰጣቸው ክፍያ አነስተኛ ነው። በተጨማሪም ድርጅቶች ምርታቸውን ከፍ ለማድረግ በሠራተኞቻቸው ላይ ሁልጊዜ የሚያሳድሩት ጫና ሠራተኞቹ በአካላዊ፣ በአእምሯዊና በስሜታዊ ሁኔታ እንዲዝሉ ያደርጋል። አሠሪዎቻቸው የሚጠብቁባቸውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ የማይሆኑ ሠራተኞች ደግሞ ሥራቸውን የማጣት አደጋ ይደቀንባቸዋል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በዋነኝነት ታማኝ መሆን ያለብን ለአምላካችን ለይሖዋ እንጂ ለአሠሪያችን አይደለም። (ሉቃስ 10:27) ሰብዓዊ ሥራ በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ መያዝ የለበትም። የምንሠራው፣ መሠረታዊ ፍላጎታችንን ለማሟላትና አገልግሎታችንን ለማከናወን የሚያስፈልገንን ነገር ለማግኘት ነው። ሆኖም ጥንቃቄ ካላደረግን ሰብዓዊ ሥራ ለአምልኳችን እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። w17.05 23 አን. 5-7
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 26
የወለደህን አባትህን ስማ፤ እናትህንም ስላረጀች አትናቃት።—ምሳሌ 23:22
በእውነት ቤት ብዙም ያልቆዩ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ልጆቻቸውን ስለ ይሖዋ ሲያስተምሩ የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንዲረዷቸው የሚጠይቁበት ጊዜ አለ። አንድ ወላጅ ሌላ ሰው ልጆቹን እንዲያስጠናለት ከወሰነ ልጆቹን የሚያስጠናው ሰው የወላጆቹን ኃላፊነት ለመውሰድ መሞከር የለበትም። (ኤፌ. 6:1-4) የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ወላጆች ያሏቸውን ልጆች የምናስጠናበት ጊዜም ይኖራል። ይህ በሚሆንበት ወቅት፣ ለልጆቹ መንፈሳዊ እርዳታ ስላበረከትን ብቻ የልጆቹ ወላጆች እንደሆንን ሊሰማን አይገባም። በተጨማሪም ልጆቹን ቤታቸው ውስጥ ማስጠናቱ የተሻለ ነው፤ በዚህ ወቅት ቤት ውስጥ ወላጆቻቸው ወይም ሌላ የጎለመሰ የይሖዋ ምሥክር ቢኖር ይመረጣል። አለዚያ ደግሞ ሰዎች በሚገኙበት ሌላ ቦታ ማስጠናታችን ጥበብ ይሆናል። ይህን ማድረጋችን ሌላ ሰው ጉዳዩን በተሳሳተ መንገድ እንዳይረዳው ያደርጋል። ወላጆቻቸው ከጊዜ በኋላ የልጆቻቸውን መንፈሳዊ ፍላጎት በማሟላት አምላክ የሰጣቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ተስፋ እናደርጋለን። w17.06 8 አን. 15-16
እሁድ፣ ጥቅምት 27
አንድ ሰው የሚናገረውን ቋንቋ ትርጉም ካላወቅኩ . . . ለእኔ የባዕድ አገር ሰው ይሆንብኛል።—1 ቆሮ. 14:11
ልጆች የወላጆቻቸው ባሕል ካልገባቸው የእነሱን ቋንቋ እንዲሁም ሃይማኖት መማር አይፈልጉ ይሆናል። ክርስቲያን ወላጆች ከራሳቸው ፍላጎት ይልቅ የልጆቻቸውን መንፈሳዊነት ሊያስቀድሙ ይገባል። (1 ቆሮ. 10:24) ሳሙኤል የተባለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ፣ እውነት የልጆቻችንን ልብ የሚነካው በየትኛው ቋንቋ ሲማሩት እንደሆነ ለማስተዋል ሞከርን፤ እንዲሁም ጥበብ ለማግኘት ጸለይን። . . . ልጆቻችን በእኛ ቋንቋ ከሚመሩ ስብሰባዎች እምብዛም እየተጠቀሙ እንዳልሆነ ስንገነዘብ በአካባቢው ቋንቋ ወደሚካሄድ ጉባኤ ለመዛወር ወሰንን። ከልጆቻችን ጋር ሆነን አዘውትረን በስብሰባዎች ላይ እንገኝ እንዲሁም እናገለግል ነበር። በተጨማሪም የአካባቢውን ወንድሞች ቤታችን እንጋብዛቸው እንዲሁም አብረውን ሽርሽር እንዲሄዱ እናደርግ ነበር። እንዲህ ያለ ጥረት ማድረጋችን ልጆቻችን ከወንድሞች ጋር እንዲቀራረቡ ረድቷቸዋል፤ በተጨማሪም ይሖዋን እንዲያውቁት ብሎም እንደ አምላካቸው ብቻ ሳይሆን እንደ አባታቸውና እንደ ወዳጃቸው እንዲመለከቱት አድርጓል። ይህ፣ የእኛን ቋንቋ ከመቻል የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንደሆነ ይሰማናል።” w17.05 10 አን. 11-13
ሰኞ፣ ጥቅምት 28
ይሖዋን አወድሱ!—መሳ. 5:2
በቅርቡ ምድር ከማንኛውም አገዛዝ በላይ የይሖዋን ሉዓላዊነት በሚደግፉ ሰዎች ትሞላለች። ያን ቀን በጉጉት እንጠባበቃለን! ልክ እንደ ዲቦራና ባርቅ እኛም “ይሖዋ ሆይ፣ ጠላቶችህ ሁሉ ይጥፉ፣ አንተን የሚወዱ ግን ደምቃ እንደምትወጣ ፀሐይ ይሁኑ” ብለን እንዘምራለን። (መሳ. 5:31) ይሖዋ የሰይጣንን ክፉ ዓለም ሲያጠፋ ይህ ልመናችን ምላሽ ያገኛል! የአርማጌዶን ጦርነት በሚጀምርበት ወቅት ከሰው ልጆች መካከል ጠላትን ድል የሚያደርጉ ፈቃደኛ ተዋጊዎች አያስፈልጉም። በዚያ ወቅት “ዝም ብላችሁ ቁሙ፤ ይሖዋ . . . የሚወስደውን የማዳን እርምጃ ተመልከቱ” የሚለውን መመሪያ ከመታዘዝ ሌላ የሚጠበቅብን ነገር አይኖርም። (2 ዜና 20:17) እስከዚያው ድረስ ግን የይሖዋን ዓላማ በድፍረትና በቅንዓት ለመደገፍ የሚያስችሉን ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። ዲቦራና ባርቅ የድል መዝሙራቸውን የጀመሩት ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ ውዳሴ በማቅረብ ነበር። “ሕዝቡም ፈቃደኛ ስለሆነ፣ ይሖዋን አወድሱ!” በማለት ዘምረዋል። (መሳ. 5:1, 2) ዛሬም የምታሳዩት የፈቃደኝነት መንፈስ ሌሎችም ‘ይሖዋን እንዲያወድሱ’ የሚያነሳሳ ይሁን! w17.04 32 አን. 17-18
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 29
አሁንም ቢሆን እዚህ እስር ቤት ውስጥ የጣሉኝ ያለምንም ጥፋት ነው።—ዘፍ. 40:15
ዮሴፍ ለ13 ዓመታት የዘለቀ መከራ በደረሰበት ወቅት የተፈጸመበትን በደል ረስቶታል ማለት ባይሆንም ምሬት እንዲያድርበት አልፈቀደም። (ዘፍ. 45:5-8) ከሁሉ በላይ ደግሞ የሌሎች አለፍጽምና እንዲሁም ያደረሱበት በደል ከይሖዋ እንዲያርቀው አልፈቀደም። ዮሴፍ ታማኝ በመሆኑ ይሖዋ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ሲያስተካክል እንዲሁም እሱንም ሆነ ቤተሰቡን ሲባርክ ለመመልከት በቅቷል። እኛም ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ከፍ አድርገን መመልከትና ዝምድናችን እንዳይበላሽ መጠንቀቅ ይኖርብናል። የወንድሞቻችን አለፍጽምና ከምንወደው አምላካችን ሊለየን እና እሱን ከማምለክ ወደኋላ እንድንል ሊያደርገን አይገባም። (ሮም 8:38, 39) እንዲያውም አንድ የእምነት አጋራችን ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ቢፈጽምብን፣ ልክ እንደ ዮሴፍ ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብና እሱ ለነገሮች ያለው ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ጥረት እናድርግ። ቅዱሳን ጽሑፎች በሚሉት መሠረት ሁኔታውን ለማስተካከል የምንችለውን ሁሉ ካደረግን በኋላ ይሖዋ ጉዳዩን በራሱ ጊዜና መንገድ እንደሚያስተካክል በመተማመን ነገሩን ለእሱ መተው ይኖርብናል። w17.04 20 አን. 12፤ 22 አን. 15-16
ረቡዕ፣ ጥቅምት 30
አገልጋይህን ሳትረሳት ወንድ ልጅ ብትሰጣት በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለይሖዋ እሰጠዋለሁ።—1 ሳሙ. 1:11
ሐና ለአምላክ የገባችውን ስእለት ፈጸመች። ቃሏን ለማጠፍ ጨርሶ አላሰበችም። ሳሙኤልን በሴሎ ባለው የማደሪያ ድንኳን ወደሚያገለግለው ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ኤሊ ይዛው በመሄድ እንዲህ አለችው፦ “ይህን ልጅ እንዲሰጠኝ ጸልዬ ነበር፤ ይሖዋም የለመንኩትን ሰጠኝ። እኔ ደግሞ በበኩሌ ልጁን ለይሖዋ እሰጠዋለሁ። በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ለይሖዋ የተሰጠ ይሆናል።” (1 ሳሙ. 1:24-28) ከዚያ በኋላ ሳሙኤል በማደሪያው ድንኳን ውስጥ መኖር ጀመረ። መጽሐፍ ቅዱስ “ብላቴናው ሳሙኤልም በይሖዋ ፊት እያደገ ሄደ” ይላል። (1 ሳሙ. 2:21) ይሁንና ሐና ስእለቷን መፈጸም ቀላል ሆኖላት ነበር? ሐና ሕፃን ልጇን በጣም እንደምትወደው የታወቀ ነው፤ ከዚያ በኋላ ግን በየቀኑ ልታገኘው አትችልም። ልጇን ማቀፍ፣ ከእሱ ጋር መጫወትና እሱን መንከባከብ ሊያምራት እንደሚችል ጥያቄ የለውም፤ ሐና፣ አንዲት እናት የምትወደውን ልጇን ስታሳድግ የሚኖራት አስደሳች ትዝታ ሁሉ ሊቀርባት ነው። ሆኖም ሐና ለአምላክ የተሳለችውን በመፈጸሟ አልተቆጨችም። “ልቤ በይሖዋ ሐሴት አደረገ” በማለት ተናግራለች።—1 ሳሙ. 2:1, 2፤ መዝ. 61:1, 5, 8፤ w17.04 4-5 አን. 7-8
ሐሙስ፣ ጥቅምት 31
በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ።—2 ጢሞ. 3:1
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የምንኖርበት ጊዜ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” እንደሚሆን ትንቢት ከተናገረ በኋላ “ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች . . . በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ” ሲል በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (2 ጢሞ. 3:2-5, 13) ይህ ትንቢት እየተፈጸመ እንደሆነ አስተውለሃል? ብዙዎቻችን በክፉ ሰዎች ይኸውም በጉልበተኞች፣ ጭፍን ጥላቻ ባላቸው ግለሰቦችና ጨካኝ በሆኑ ወንጀለኞች ጥቃት ደርሶብን ያውቃል። ከእነዚህ አንዳንዶቹ የክፋት ድርጊታቸውን ለመደበቅ እንኳ አይሞክሩም፤ ሌሎች ደግሞ መልካም መስለው በመቅረብ የክፋት ድርጊታቸውን ለመሸፈን የሚሞክሩ አስመሳዮች ናቸው። እንዲህ ያለ ጥቃት ደርሶብን የማያውቅ ቢሆን እንኳ ክፉ ሰዎች በእኛ ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም። ክፉዎች የሚፈጽሟቸውን ዘግናኝ ድርጊቶች ስንሰማ በጣም እናዝናለን። እነዚህ ሰዎች በልጆች፣ በአረጋውያን እንዲሁም አቅመ ደካማ በሆኑ ሌሎች ሰዎች ላይ ግፍ ሲፈጽሙ ስሜታችን በጣም ይረበሻል። ክፉ ሰዎች የሚፈጽሙት ድርጊት ኢሰብዓዊ፣ እንስሳዊና አጋንንታዊ ነው። (ያዕ. 3:15) የሚያስደስተው ነገር የአምላክ ቃል የሚያጽናና ምሥራች ይዟል። w17.04 10 አን. 4