የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es20 ገጽ 27-37
  • መጋቢት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጋቢት
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2020
  • ንዑስ ርዕሶች
  • እሁድ፣ መጋቢት 1
  • ሰኞ፣ መጋቢት 2
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 3
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 4
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 5
  • ዓርብ፣ መጋቢት 6
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 7
  • እሁድ፣ መጋቢት 8
  • ሰኞ፣ መጋቢት 9
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 10
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 11
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 12
  • ዓርብ፣ መጋቢት 13
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 14
  • እሁድ፣ መጋቢት 15
  • ሰኞ፣ መጋቢት 16
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 17
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 18
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 19
  • ዓርብ፣ መጋቢት 20
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 21
  • እሁድ፣ መጋቢት 22
  • ሰኞ፣ መጋቢት 23
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 24
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 25
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 26
  • ዓርብ፣ መጋቢት 27
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 28
  • እሁድ፣ መጋቢት 29
  • ሰኞ፣ መጋቢት 30
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2020
es20 ገጽ 27-37

መጋቢት

እሁድ፣ መጋቢት 1

አንተ ሁሉንም ነገር ትገዛለህ።—1 ዜና 29:12

የዘፍጥረትን መጽሐፍ የመጀመሪያ ሁለት ምዕራፎች ስናነብ፣ አዳምና ሔዋን በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች የሚመኙት ዓይነት ነፃነት እንደነበራቸው ይኸውም ከድህነት፣ ከፍርሃትና ከጭቆና ነፃ እንደነበሩ እንገነዘባለን። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ስለ ምግብም ሆነ ስለ ሥራ ፈጽሞ አይጨነቁም ነበር፤ ከሕመምና ከሞት ስጋትም ቢሆን ነፃ ነበሩ። (ዘፍ. 1:27-29፤ 2:8, 9, 15) ሆኖም ከነፃነት ጋር በተያያዘ ልንዘነጋው የማይገባ አንድ ወሳኝ ነጥብ አለ፦ ገደብ የለሽ ነፃነት ያለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ የሁሉ ነገር ፈጣሪና የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ስለሆነ ነው። (1 ጢሞ. 1:17፤ ራእይ 4:11) በተቃራኒው ግን በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ ፍጥረታት በሙሉ ያላቸው ነፃነት አንጻራዊ ነው። እነዚህ ፍጥረታት ፍትሐዊ፣ አስፈላጊና ምክንያታዊ የሚባሉት ገደቦች የትኞቹ እንደሆኑ የመወሰን ሥልጣን ያለው ይሖዋ አምላክ ብቻ እንደሆነ አምነው መቀበል አለባቸው። ደግሞም ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ሲፈጥር እንዲህ ዓይነት ገደቦችን አስቀምጧል። w18.04 4 አን. 4, 6

ሰኞ፣ መጋቢት 2

ምሥራች ይዞ የሚመጣ፣ . . . እግሮቹ እንዴት ያማሩ ናቸው!—ኢሳ. 52:7

በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች መቋቋም የቻልነው በይሖዋ እርዳታ ብቻ ነው። (2 ቆሮ. 4:7, 8) ይሁንና ከይሖዋ ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የሌላቸው ሰዎች በዚህ ዓለም ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መቋቋም ምን ያህል ሊከብዳቸው እንደሚችል አስብ። ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም ለእነዚህ ሰዎች እናዝንላቸዋለን፤ ይህም “የተሻለ ነገር እንደሚመጣ [የሚያበስረውን] ምሥራች” እንድናውጅላቸው ያነሳሳናል። በመሆኑም ሰዎችን ስታስተምር ትዕግሥተኛ ሁን። በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ሰዎች እኛ ጠንቅቀን የምናውቃቸውን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ጨርሶ ላያውቁ እንደሚችሉ አስታውስ። በተጨማሪም በርካታ ሰዎች፣ የሚያምኑባቸውን ነገሮች እጅግ ከፍ አድርገው ይመለከቷቸዋል። እምነታቸው ከቤተሰባቸው፣ ከባሕላቸውና ከማኅበረሰቡ ጋር እንደሚያስተሳስራቸው ይሰማቸዋል። ሰዎች “አሮጌውን” እምነታቸውን እንዲተዉ ከመጠየቃችን በፊት አሁን እየተማሯቸው ላሉት “አዲስ” እውነቶች ማለትም ከዚህ በፊት ለማያውቋቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች አድናቆት እንዲያዳብሩ መርዳት ሊያስፈልገን ይችላል። ቀደም ሲል የነበራቸውን አመለካከት ሊተዉ የሚችሉት እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። ሰዎች እንዲህ ያሉ ለውጦችን እንዲያደርጉ መርዳት ጊዜ ሊወስድ ይችላል።—ሮም 12:2፤ w19.03 23-24 አን. 10, 12-13

ማክሰኞ፣ መጋቢት 3

በአንተ ደስ ይለኛል።—ማር. 1:11

ይሖዋ ልጁን እንደሚወደውና ደስ እንደሚሰኝበት በመግለጽ የተወው ግሩም ምሳሌ ሌሎችን የምናበረታታበትን አጋጣሚ መፈለግ እንዳለብን ያስገነዝበናል። (ዮሐ. 5:20) ከፍ አድርገን የምንመለከተው ሰው ለእኛ ያለውን ፍቅር ሲገልጽልንና ላከናወንነው መልካም ነገር ሲያመሰግነን ደስ ይለናል። በተመሳሳይም በጉባኤያችን ያሉ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም የቤተሰባችን አባላት የእኛ ፍቅርና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ለሌሎች አመስጋኝነታችንን መግለጻችን እምነታቸውን ለማጠናከርና ይሖዋን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ለማበረታታት ያስችለናል። በተለይ ወላጆች፣ ልጆቻቸውን ማበረታታት ይኖርባቸዋል። ልጆቻቸውን ከልብ ማመስገናቸውና ፍቅራቸውን መግለጻቸው ልጆቹ ስኬታማ እንዲሆኑ ይረዳል። “በአንተ ደስ ይለኛል” የሚለው አገላለጽ ይሖዋ ልጁ የአባቱን ፈቃድ በታማኝነት እንደሚፈጽም ያለውን እምነት ያሳያል። ይሖዋ በልጁ ይተማመንበታል፤ ስለዚህ እኛም ይሖዋ የሰጣቸውን ተስፋዎች ሁሉ ኢየሱስ በታማኝነት እንደሚያስፈጽም ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን። (2 ቆሮ. 1:20) ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ስንመረምር ከእሱ ለመማርና የእሱን ፈለግ ለመከተል ያለን ቁርጠኝነት ይበልጥ ይጠናከራል።—1 ጴጥ. 2:21፤ w19.03 8 አን. 3፤ 9 አን. 5-6

ረቡዕ፣ መጋቢት 4

ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላላቸው ሰዎች ሕይወት የሚያስገኘው መንፈስ ሕግ፣ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነፃ አውጥቷችኋል።—ሮም 8:2

አንድ ስጦታ ምን ያህል ውድ እንደሆነ መገንዘባችን ለሰጪው አመስጋኝነታችንን ለማሳየት ይበልጥ እንደሚያነሳሳን የታወቀ ነው። እስራኤላውያን፣ ይሖዋ ከግብፅ ባርነት ነፃ በማውጣት ለሰጣቸው ነፃነት አድናቆት አላሳዩም። ነፃ በወጡ በጥቂት ወራት ውስጥ፣ በግብፅ የነበረውን ምግብና መጠጥ መመኘት እንዲሁም ይሖዋ የሰጣቸውን ነገር ማማረር ጀመሩ፤ ይባስ ብሎም ወደ ግብፅ መመለስ ፈለጉ። እስቲ አስበው፣ ‘ዓሣ፣ ኪያር፣ ሐብሐብ፣ ባሮ ሽንኩርት፣ ቀይ ሽንኩርትና ነጭ ሽንኩርት’ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን በነፃነት ከማምለክ መብታቸው በለጠባቸው። ታዲያ ይሖዋ በሕዝቡ እጅግ መቆጣቱ ምን ያስገርማል? (ዘኁ. 11:5, 6, 10፤ 14:3, 4) ይህ ለእኛም ትልቅ ትምህርት ይዞልናል! ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በደግነት የሰጣቸውን ነፃነት አቅልለው እንዳይመለከቱ ሁሉንም ክርስቲያኖች አሳስቧል።—2 ቆሮ. 6:1፤ w18.04 9-10 አን. 6-7

ሐሙስ፣ መጋቢት 5

ጽድቅንና ፍትሕን ይወዳል። ምድር በይሖዋ ታማኝ ፍቅር ተሞልታለች።—መዝ. 33:5

ሁላችንም በሌሎች የመወደድ ፍላጎት አለን። በተጨማሪም ሁላችንም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንድንያዝ እንፈልጋለን። በተደጋጋሚ ፍቅርና ፍትሕ የምንነፈግ ከሆነ ዋጋ ቢስ እንደሆንን ሊሰማንና ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። ይሖዋ ፍቅርና ፍትሕ የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለን ያውቃል። (መዝ. 33:5) አምላካችን በጥልቅ እንደሚወደንና ፍትሕ እንድናገኝ እንደሚፈልግ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ በሙሴ በኩል ለእስራኤል ብሔር የሰጠውን ሕግ መመርመራችን ይህን እውነታ በሚገባ ለመረዳት ያስችለናል። የሙሴን ሕግ ስንመረምር አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደን እንገነዘባለን። (ሮም 13:8-10) ይሖዋ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ ስለሆነ የሙሴ ሕግ የተመሠረተው በፍቅር ላይ ነው ማለት እንችላለን። (1 ዮሐ. 4:8) ይሖዋ ጠቅላላውን የሙሴን ሕግ ያወጣው ‘አምላክህን ውደድ’ እና ‘ባልንጀራህን ውደድ’ በሚሉት ሁለት መሠረታዊ ትእዛዛት ላይ ተመሥርቶ ነው። (ዘሌ. 19:18፤ ዘዳ. 6:5፤ ማቴ. 22:36-40) በሕጉ ውስጥ የተካተቱት ከ600 የሚበልጡ ትእዛዛት በሙሉ የይሖዋን ፍቅር የተለያዩ ገጽታዎች የሚያንጸባርቁ ናቸው። w19.02 20-21 አን. 1-4

ዓርብ፣ መጋቢት 6

ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናልና።—ማቴ. 6:21

ኢዮብ ከተቃራኒ ፆታ ጋር በተያያዘ በሚያሳየው ምግባር ጠንቃቃ ነበር። (ኢዮብ 31:1) የትዳር ጓደኛው ላልሆነች ሴት የፍቅር ስሜት ማሳየት ተገቢ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። እኛም የምንኖርበት ዓለም የፆታ ፍላጎት የሚቀሰቅሱ ነገሮችን ያዥጎደጉድብናል። ልክ እንደ ኢዮብ፣ የትዳር ጓደኛችን ላልሆነ ሰው ተገቢ ያልሆነ ትኩረት ላለመስጠት እንጠነቀቃለን? በተጨማሪም ማንኛውንም ዓይነት የብልግና ምስል ወይም የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ነገር ላለመመልከት ከዓይናችን ጋር ቃል ኪዳን እንገባለን? (ማቴ. 5:28) በዚህ ረገድ በየዕለቱ ራሳችንን የምንገዛ ከሆነ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያደረግነውን ውሳኔ ይበልጥ እናጠናክራለን። ኢዮብ ለቁሳዊ ነገሮች ካለው አመለካከት ጋር በተያያዘም ይሖዋን ታዟል። በቁሳዊ ንብረት መታመን ቅጣት የሚገባው ከባድ በደል እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። (ኢዮብ 31:24, 25, 28) ዛሬ የምንኖረው ለቁሳዊ ነገሮች ከልክ ያለፈ ቦታ በሚሰጥ ዓለም ውስጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር በመከተል ለገንዘብና ለቁሳዊ ንብረት ሚዛናዊ አመለካከት ካዳበርን ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ እናጠናክራለን።—ምሳሌ 30:8, 9፤ ማቴ. 6:19, 20፤ w19.02 6 አን. 13-14

ቅዳሜ፣ መጋቢት 7

አብ እኔን እንደወደደኝ፣ እኔም እናንተን እንዲሁ ወድጃችኋለሁ።—ዮሐ. 15:9

ኢየሱስ ያደረገው ነገር ሁሉ ይሖዋ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባርቃል። (1 ዮሐ. 4:8-10) ኢየሱስ ፍቅሩን ያሳየበት ከሁሉ የላቀው መንገድ ደግሞ ለእኛ ሲል ሕይወቱን መሥዋዕት ማድረጉ ነው። ቅቡዓንም ሆን ‘የሌሎች በጎች’ አባላት ይሖዋና ልጁ በዚህ መሥዋዕት አማካኝነት ካሳዩን ፍቅር ተጠቃሚዎች ነን። (ዮሐ. 10:16፤ 1 ዮሐ. 2:2) ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ በመታሰቢያው በዓል ላይ የተጠቀመበት ነገር እንኳ ለደቀ መዛሙርቱ ያለውን ፍቅርና አሳቢነት ያሳያል። እንዴት? ኢየሱስ የመታሰቢያው በዓል ውስብስብ የሆነ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ሳይሆን ቀለል ያለ ዝግጅት እንዲሆን በማድረግ በመንፈስ ለተቀቡት ተከታዮቹ ያለውን ፍቅር አሳይቷል። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ቅቡዓን ደቀ መዛሙርት የመታሰቢያውን በዓል በየዓመቱ ማክበር የሚኖርባቸው ሲሆን ይህን የሚያደርጉት እስርን ጨምሮ በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር ሆነው ነው። (ራእይ 2:10) ታዲያ የኢየሱስን ትእዛዝ መጠበቅ ችለው ይሆን? እንዴታ! ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር ጥረት አድርገዋል። w19.01 24 አን. 13-15

እሁድ፣ መጋቢት 8

እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል።—ዮሐ. 8:32

ኢየሱስ የጠቀሰው ነፃነት ከሐሰት ሃይማኖት፣ ከመንፈሳዊ ድንቁርናና ከአጉል እምነት ነፃ መውጣትን ይጨምራል። በተጨማሪም ይህ ነፃነት ይሖዋ ወደፊት የሚሰጠንን “የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት” ያካትታል። (ሮም 8:21) በዛሬው ጊዜም እንኳ ‘የክርስቶስን ቃል’ ወይም ትምህርቶች ‘ጠብቀን በመኖር’ ይህን ነፃነት ማጣጣም እንችላለን። (ዮሐ. 8:31) በዚህ መንገድ፣ በትምህርት ብቻ ሳይሆን በሕይወታችን ተግባራዊ በማድረግም ጭምር ‘እውነትን ማወቅ’ እንችላለን። በዚህ አሮጌ ሥርዓት ውስጥ ስኬታማ የሚባለው ሕይወት እንኳ አጭር ከመሆኑም በላይ አስተማማኝ አይደለም። ነገ ምን እንደሚፈጠር አናውቅም። (ያዕ. 4:13, 14) ስለዚህ “እውነተኛ [ወደሆነው] ሕይወት” ማለትም ወደ ዘላለም ሕይወት በሚመራው ጎዳና ላይ መጓዛችንን መቀጠላችን ጥበብ ነው። (1 ጢሞ. 6:19) አምላክ በዚህ ጎዳና ላይ እንድንሄድ እንደማያስገድደን የታወቀ ነው። ምርጫውን ማድረግ ያለብን እኛው ራሳችን ነን። እንግዲያው ወጣቶች፣ ይሖዋን ‘ድርሻችሁ’ አድርጉ። (መዝ. 16:5) እሱ የሰጣችሁን “መልካም ነገሮች” ከፍ አድጋችሁ ተመልከቱ። (መዝ. 103:5) እንዲሁም ይሖዋ ‘ለዘላለም ብዙ ደስታ’ እንደሚሰጣችሁ እምነት ይኑራችሁ።—መዝ. 16:11፤ w18.12 28 አን. 19, 21

ሰኞ፣ መጋቢት 9

ባልም ሚስቱን መተው የለበትም።—1 ቆሮ. 7:11

ሁሉም ክርስቲያኖች የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ለጋብቻ ዝግጅት አክብሮት ለማሳየት ጥረት ማድረግ አለባቸው። ይሁንና የሰው ልጆች ፍጽምና የጎደላቸው ስለሆኑ አንዳንዶች እንዲህ ማድረግ ሊከብዳቸው ይችላል። (ሮም 7:18-23) ከዚህ አንጻር በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች በጋብቻቸው ውስጥ ችግር አጋጥሟቸው የነበረ መሆኑ ሊያስገርመን አይገባም። ጳውሎስ “ሚስት ከባሏ አትለያይ” ሲል ጽፎ ነበር፤ ሆኖም ይህን መመሪያ ተግባራዊ ያላደረጉ ባለትዳሮች ነበሩ። (1 ቆሮ. 7:10) ጳውሎስ እነዚህ ባለትዳሮች የተለያዩት በምን ምክንያት እንደሆነ አልገለጸም። ሆኖም ባልየው የፆታ ብልግና ፈጽሞ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ምክንያቱም ይህ ቢሆን ኖሮ ሚስትየው ለመፋታትና ድጋሚ ለማግባት የሚያስችል መሠረት ይኖራት ነበር። ጳውሎስ ከባሏ ጋር የተለያየች ሚስት ‘ሳታገባ መኖር ወይም ከባሏ ጋር መታረቅ’ እንዳለባት ጽፏል። በመሆኑም ሁለቱ በአምላክ ዓይን አሁንም የተጣመሩ ናቸው ማለት ነው። ጳውሎስ የተፈጠረው ችግር ምንም ይሁን ምን የፆታ ብልግና እስካልተፈጸመ ድረስ የሁለቱ ሰዎች ግብ መታረቅ መሆን እንዳለበት መክሯል። ለዚህ የሚረዳቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለማግኘት የጉባኤ ሽማግሌዎችን ሊጠይቁ ይችላሉ። w18.12 13 አን. 14-15

ማክሰኞ፣ መጋቢት 10

ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ።—ማቴ. 6:33

በዛሬው ጊዜ አምላክ ለሕዝቡ ያለው ፈቃድ፣ ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲመሠርቱና እሱ በሰጣቸው ሥራ የቻሉትን ያህል ሙሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ነው። (ማቴ. 28:19, 20፤ ያዕ. 4:8) አንዳንድ ሰዎች በቅን ልቦና ተነሳስተው ከዚህ የተለየ አካሄድ እንድንከተል ይገፋፉን ይሆናል። ለምሳሌ አሠሪህ ጠቀም ያለ የደሞዝ ጭማሪ የሚያስገኝ እድገት እንደሚሰጥህ ቢነግርህ፣ ሆኖም ይህ ሥራ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችህ ላይ እንቅፋት የሚፈጥርብህ ቢሆን ምን ታደርጋለህ? አሊያም ደግሞ ተማሪ ብትሆንና ከቤተሰቦችህ እንድትርቅ የሚያስገድድ ተጨማሪ የትምህርት ዕድል ብታገኝ ምን ትወስናለህ? በጉዳዩ ላይ ለመጸለይ፣ ምርምር ለማድረግና ሌሎች ሰዎችን ለማማከር የግድ ሁኔታው እስኪያጋጥምህ ድረስ መጠበቅ የለብህም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንዲህ ስላሉ ጉዳዮች ያለውን አመለካከት ለማወቅና የእሱ ዓይነት አስተሳሰብ ለማዳበር አስቀድመህ ጥረት ማድረግህ አስፈላጊ ነው። እንዲህ ካደረግክ፣ የቀረበልህ ግብዣ ያን ያህል ፈታኝ አይሆንብህም። ምክንያቱም ከወዲሁ መንፈሳዊ ግብ ስላወጣህና እዚያ ላይ ለመድረስ ቁርጥ አቋም ስላለህ የሚቀርህ አስቀድመህ ያደረግከውን ውሳኔ ሥራ ላይ ማዋል ብቻ ይሆናል። w18.11 27 አን. 18

ረቡዕ፣ መጋቢት 11

ከምንም ነገር በላይ ልብህን ጠብቅ።—ምሳሌ 4:23

ሰለሞን የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ገና በወጣትነቱ ነበር። በግዛቱ መጀመሪያ አካባቢ ይሖዋ በሕልም ተገልጦ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ጠይቅ” አለው። ሰለሞንም እንዲህ በማለት መለሰ፦ “እኔ ገና አንድ ፍሬ ልጅና ተሞክሮ የሌለኝ [ነኝ]። . . . ስለሆነም አገልጋይህ ሕዝብህን መዳኘት . . . እንዲችል ታዛዥ ልብ ስጠው።” (1 ነገ. 3:5-10) ሰለሞን “ታዛዥ ልብ” እንዲሰጠው መጠየቁ ምን ያህል ልኩን የሚያውቅ ሰው እንደነበር ያሳያል። በእርግጥም ይሖዋ ሰለሞንን ይወደው የነበረ መሆኑ ምንም አያስገርምም! (2 ሳሙ. 12:24) አምላካችን፣ በወጣቱ ንጉሥ መልስ በጣም ስለተደሰተ ለሰለሞን “ጥበበኛና አስተዋይ ልብ” ሰጠው። (1 ነገ. 3:12) ሰለሞን ታማኝ በነበረባቸው ጊዜያት ሁሉ ብዙ በረከቶችን አግኝቷል። “ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ስም” ቤተ መቅደስ የመገንባት ትልቅ መብት ተሰጥቶታል። (1 ነገ. 8:20) በተጨማሪም ከአምላክ ያገኘው ጥበብ በብዙዎች ዘንድ እውቅና አትርፎለታል። ከዚህም ሌላ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተናገራቸው ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ሦስት መጻሕፍት ላይ ተመዝግበዋል። ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል አንዱ የምሳሌ መጽሐፍ ነው። w19.01 14 አን. 1-2

ሐሙስ፣ መጋቢት 12

ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ።—ሮም 12:2

አንዳንድ ሰዎች ማንም አስተሳሰባቸውን እንዲቀርጸው ወይም በአስተሳሰባቸው ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድርባቸው አይፈልጉም። “በራሴ እንጂ በሌላ በማንም አስተሳሰብ መመራት አልፈልግም” ይላሉ። ምናልባትም እንዲህ የሚሉት የራሳቸውን ውሳኔ ራሳቸው ማድረግ ስለሚፈልጉና እንዲህ ማድረጋቸው ትክክል እንደሆነ ስለሚሰማቸው ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች በማንም ቁጥጥር ሥር መሆን ወይም ማንነታቸውን ማጣት አይፈልጉም። ሆኖም አስተሳሰባችንን ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር ማስማማታችን በራሳችን የማሰብ ወይም ሐሳባችንን የመግለጽ ነፃነታችንን እንደማያሳጣን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ሁለተኛ ቆሮንቶስ 3:17 እንደሚናገረው “የይሖዋ መንፈስ ባለበት . . . ነፃነት አለ።” እያንዳንዳችን የየራሳችንን ስብዕና የማዳበርና የምንወደውን ነገር የመምረጥ ነፃነት አለን። ደግሞም ይሖዋ የፈጠረን በዚህ መንገድ ነው። ይሁንና ነፃነታችን ምንም ገደብ የለውም ማለት አይደለም። (1 ጴጥ. 2:16) ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ከመወሰን ጋር በተያያዘ ይሖዋ በእሱ አስተሳሰብ እንድንመራ ይፈልጋል፤ አስተሳሰቡን ደግሞ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል። w18.11 19 አን. 5-6

ዓርብ፣ መጋቢት 13

ዴማስ በአሁኑ ጊዜ ያለውን ሥርዓት ወዶ፣ ትቶኝ ወደ ተሰሎንቄ ሄዷል።—2 ጢሞ. 4:10

እውነትን ስንማር ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ መንፈሳዊ ነገሮችን ማስቀደም እንዳለብን ተገንዝበናል። በእውነት ጎዳና ለመሄድ ስንል ቁሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች ሆነናል። ከጊዜ በኋላ ግን ሌሎች ሰዎች ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ሲገዙ ወይም በገንዘባቸው አንዳንድ ነገሮችን ሲያደርጉ ስንመለከት ብዙ ነገር እንደቀረብን ይሰማን ይሆናል። በመሆኑም ባሉን መሠረታዊ ነገሮች ረክተን ከመኖር ይልቅ ቁሳዊ ሀብት ለማካበት ስንል መንፈሳዊ ነገሮችን ወደ ጎን ገሸሽ ማድረግ ልንጀምር እንችላለን። እንዲህ ያለው አካሄድ የዴማስን ሁኔታ ያስታውሰናል። ዴማስ “በአሁኑ ጊዜ ያለውን ሥርዓት” መውደዱ ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር የማገልገል መብቱን ትቶ እንዲሄድ አድርጎታል። ዴማስ ጳውሎስን ትቶ የሄደው ለምንድን ነው? ከመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ይልቅ ቁሳዊ ነገሮችን ስለወደደ ይሆን? አሊያም ከጳውሎስ ጋር ለማገልገል ሲል መሥዋዕት መክፈሉን ለመቀጠል ፈቃደኛ ስላልሆነ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረው ነገር የለም። ሆኖም ዴማስ ካጋጠመው ሁኔታ የምናገኘው ትምህርት አለ። እኛም ለቁሳዊ ነገሮች ያለን ፍቅር ዳግመኛ እንዳይቀጣጠልና ለእውነት ያለንን ፍቅር እንዳያጠፋብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። w18.11 10 አን. 9

ቅዳሜ፣ መጋቢት 14

መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም።—ዘፍ. 3:4

ሰይጣን የተናገረው ውሸት ከክፋት የመነጨ ነበር፤ ምክንያቱም ሔዋን እሱ የተናገረውን ውሸት አምና ፍሬውን ከበላች መሞቷ እንደማይቀር ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። የሚያሳዝነው በመጀመሪያ ሔዋን በኋላም አዳም የይሖዋን ትእዛዝ የጣሱ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ሕይወታቸውን አጥተዋል። (ዘፍ. 3:6፤ 5:5) ከዚህ የከፋው ደግሞ በእነሱ ኃጢአት ምክንያት “ሞት ለሰው ሁሉ [የተዳረሰ]” መሆኑ ነው። እንዲያውም “አዳም ትእዛዝ በመተላለፍ የሠራውን ዓይነት ኃጢአት ባልሠሩት ላይም እንኳ ሳይቀር” ሞት ነገሠ። (ሮም 5:12, 14) በመሆኑም የሰው ልጆች በአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ መሠረት ፍጹም ሆነው ለዘላለም መኖር አልቻሉም፤ ከዚህ ይልቅ ‘የዕድሜያቸው ርዝማኔ 70 ዓመት፣ ለየት ያለ ጥንካሬ ካላቸው ደግሞ 80 ዓመት’ ገደማ ብቻ ሆነ። በዚያ ላይ ይህ አጭር ሕይወታቸው፣ አብዛኛውን ጊዜ “በችግርና በሐዘን የተሞላ ነው።” (መዝ. 90:10) ሰይጣን የተናገረው ውሸት ያስከተለው መዘዝ ምንኛ አስከፊ ነው! ኢየሱስ የዲያብሎስን ተግባር ሲገልጽ “በእሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም” ብሏል። (ዮሐ. 8:44) አሁንም ቢሆን በሰይጣን ዘንድ እውነት የለም፤ ምክንያቱም ዛሬም ‘መላውን ዓለም ማሳሳቱን’ ቀጥሏል። (ራእይ 12:9) እኛ ዲያብሎስ እንዲያሳስተን እንደማንፈልግ ግልጽ ነው። w18.10 6-7 አን. 1-4

እሁድ፣ መጋቢት 15

ሰላም ፈጣሪዎች ደስተኞች ናቸው፤ የአምላክ ልጆች ይባላሉና።—ማቴ. 5:9

ሰላም ለመፍጠር ቅድሚያውን ወስደው ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች ደስተኞች ይሆናሉ። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “የጽድቅ ፍሬ ሰላም ፈጣሪ ለሆኑ ሰዎች ሰላማዊ በሆኑ ሁኔታዎች ይዘራል” በማለት ጽፏል። (ያዕ. 3:18) ከአንድ የጉባኤያችን ወይም የቤተሰባችን አባል ጋር አለመግባባት ሲያጋጥመን፣ ሰላም ፈጣሪ ለመሆን እንዲረዳን አምላክን ልንለምነው እንችላለን። ይሖዋም በምላሹ ቅዱስ መንፈሱን የሚሰጠን ሲሆን ይህም ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ለማንጸባረቅ ያስችለናል፤ በውጤቱም ይበልጥ ደስተኞች እንሆናለን። ኢየሱስ፣ ቅድሚያውን ወስዶ ሰላም ፈጣሪ መሆን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ሲያጎላ እንዲህ ብሏል፦ “መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ። በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።”—ማቴ. 5:23, 24፤ w18.09 21 አን. 17

ሰኞ፣ መጋቢት 16

እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።—ዮሐ. 13:34

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ ስለ ፍቅር 30 ጊዜ ገደማ ጠቅሷል። ለደቀ መዛሙርቱም “እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” የሚል ቀጥተኛ መመሪያ ሰጥቷቸዋል። (ዮሐ. 15:12, 17) ደቀ መዛሙርቱ አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅር በጉልህ የሚታይ መሆን አለበት፤ እንዲያውም ፍቅራቸው የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች እንደሆኑ በግልጽ የሚያሳይ መለያ ምልክት ይሆናል። (ዮሐ. 13:35) ይሁን እንጂ በመካከላቸው የሚኖረው ፍቅር የስሜት ጉዳይ ብቻ አይደለም። ኢየሱስ የተናገረው የራስን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግ ስለሚያነሳሳ ላቅ ያለ የፍቅር ዓይነት ነው። ኢየሱስ “ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም። የማዛችሁን ነገር የምትፈጽሙ ከሆነ ወዳጆቼ ናችሁ” ብሏል። (ዮሐ. 15:13, 14) በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮችም እውነተኛና የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር በማሳየት እንዲሁም አንድነታቸውን በመጠበቅ ተለይተው ይታወቃሉ። (1 ዮሐ. 3:10, 11) የይሖዋ አገልጋዮች የተለያየ ብሔር፣ ጎሣ፣ ቋንቋ ወይም አስተዳደግና ባሕል ቢኖራቸውም የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር የሚያሳዩ መሆኑ ምንኛ የሚያስደስት ነው! w18.09 12 አን. 1-2

ማክሰኞ፣ መጋቢት 17

አንድ ሰው የራሱ ለሆኑት በተለይ ደግሞ ለቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማያቀርብ ከሆነ እምነትን [ክዷል]።—1 ጢሞ. 5:8

ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ የቤተሰባቸውን አባላት እንዲንከባከቡ ይፈልጋል። ለምሳሌ፣ ብዙ ሰዎች የቤተሰባቸው አባላት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት መሥራት አለባቸው። በርካታ እናቶች፣ ሕፃናት ልጆቻቸውን ለመንከባከብ ሲሉ ቤት ይውላሉ። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ አቅመ ደካማ የሆኑ ወላጆቻቸውን መንከባከብ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። እነዚህ አስፈላጊ የሆኑ ተግባሮች ናቸው። አንተም እንዲህ ያሉ ኃላፊነቶች ካሉብህ በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች የምትፈልገውን ያህል ሰፋ ያለ ጊዜ ማሳለፍ አትችል ይሆናል። ያም ቢሆን ተስፋ አትቁረጥ! የቤተሰብህ አባላት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማቅረብህ ይሖዋን ያስደስተዋል። (1 ቆሮ. 10:31) ከባድ የቤተሰብ ኃላፊነት ከሌለብህ፣ የቤተሰባቸውን አባላት የሚንከባከቡ የእምነት ባልንጀሮችህን እንዲሁም የታመሙ፣ በዕድሜ የገፉ አሊያም በሌላ ምክንያት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ክርስቲያኖችን ማገዝ ትችላለህ። በጉባኤህ ውስጥ እንዲህ ያለ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ይኖሩ ይሆን? እነዚህን ክርስቲያኖች መርዳትህ ይሖዋ ለእነዚህ ሰዎች ጸሎት መልስ ሲሰጥ አብረኸው የመሥራት አጋጣሚ ያስገኝልሃል።—1 ቆሮ. 10:24፤ w18.08 24 አን. 3, 5

ረቡዕ፣ መጋቢት 18

አምላክ ከእሱ ጋር ነበር፤ ከመከራውም ሁሉ ታደገው።—ሥራ 7:9, 10

ዮሴፍ የገዛ ወንድሞቹ በቅናት ተነሳስተው ለባርነት ሲሸጡት ገና 17 ዓመቱ ነበር። አባቱ ከሌሎች ልጆቹ ሁሉ አስበልጦ የሚወደው እሱን ነበር። (ዘፍ. 37:2-4, 23-28) ዮሴፍ ከሚወደው አባቱ ከያዕቆብ ተለይቶ ለ13 ዓመታት ገደማ ግብፅ ውስጥ በባርነትና በእስር ኖሯል። ታዲያ በዚህ ወቅት ተስፋ እንዳይቆርጥና ምሬት እንዳያድርበት የረዳው ምንድን ነው? ዮሴፍ እስር ቤት ውስጥ ይማቅቅ በነበረበት ወቅት፣ ትኩረቱ እንዲያርፍ ያደረገው ይሖዋ እየባረከው እንዳለ በሚያሳዩ ማስረጃዎች ላይ እንደነበር ጥርጥር የለውም። (ዘፍ. 39:21፤ መዝ. 105:17-19) በተጨማሪም ዮሴፍ ልጅ ሳለ ያያቸው ትንቢታዊ ትርጉም ያዘሉ ሕልሞች ይሖዋ ሞገሱን እንዳሳየው እርግጠኛ እንዲሆን አድርገውት መሆን አለበት። (ዘፍ. 37:5-11) ከዚህም ሌላ በተደጋጋሚ ወደ ይሖዋ በመጸለይ ስሜቱን አውጥቶ እንደተናገረ መገመት እንችላለን። (መዝ. 145:18) ይሖዋም በመከራው ሁሉ “ከእሱ ጋር” እንደሚሆን እርግጠኛ እንዲሆን በማድረግ ዮሴፍ ላቀረበው ከልብ የመነጨ ጸሎት ምላሽ ሰጥቷል። w18.10 28 አን. 3-4

ሐሙስ፣ መጋቢት 19

ድሃ በባልንጀሮቹ ዘንድ እንኳ የተጠላ ነው፤ የባለጸጋ ወዳጆች ግን ብዙ ናቸው።—ምሳሌ 14:20

ስለ ሌሎች ባለን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው አንዱ ነገር የሰዎች የኑሮ ደረጃ ነው። አንድ ሰው ባለጸጋ አሊያም ድሃ መሆኑ ለእሱ ባለን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት ነው? ሰለሞን፣ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎችን በተመለከተ በዛሬው የዕለት ጥቅሳችን ላይ የተጠቀሰውን አሳዛኝ እውነታ ጽፏል። ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? እኛም ጥንቃቄ ካላደረግን ሀብታም ከሆኑ ወንድሞች ጋር ወዳጅነት የመመሥረት፣ ድሃ የሆኑ ወንድሞችን ግን ብዙም ያለመቅረብ አዝማሚያ ሊታይብን ይችላል። ለሌሎች የምንሰጠው ቦታ በቁሳዊ ንብረታቸው ላይ የተመሠረተ መሆኑ በጣም አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን በጉባኤ ውስጥ የመደብ ልዩነት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ያለው አመለካከት በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩ አንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ መከፋፈል እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጿል። (ያዕ. 2:1-4) በዛሬው ጊዜም እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በጉባኤያችን ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር መጠንቀቅ እንዲሁም የሰዎችን ውጫዊ ገጽታ አይቶ የመፍረድን ዝንባሌ ማስወገድ ይኖርብናል። w18.08 10 አን. 8-10

ዓርብ፣ መጋቢት 20

አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ።—1 ጴጥ. 4:8

የእምነት ባልንጀሮቻችንን የምንይዝበት መንገድ ከይሖዋ ጋር ለመሠረትነው ልዩ ወዳጅነት አድናቆት እንዳለንና እንደሌለን ያሳያል። እነሱም የይሖዋ ንብረት ናቸው። ሁሌም ይህን ሐቅ የምናስታውስ ከሆነ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ምንጊዜም ደግነትና ፍቅር እናሳያለን። (1 ተሰ. 5:15) ኢየሱስ ተከታዮቹን “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 13:35) ሚልክያስ፣ አገልጋዮቹ እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ ይሖዋ ‘በትኩረት እንደሚያዳምጥ’ ገልጿል። (ሚል. 3:16) በእርግጥም ይሖዋ “የእሱ የሆኑትን ያውቃል።” (2 ጢሞ. 2:19) የምንናገረውንና የምናደርገውን እያንዳንዱን ነገር ጠንቅቆ ያውቃል። (ዕብ. 4:13) የእምነት ባልንጀሮቻችንን ደግነት በጎደለው መንገድ ስንይዛቸው ወይም ስንናገራቸው ይሖዋ ‘በትኩረት ያዳምጣል።’ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳችን ለሌላው ይቅር ባዮች ስንሆን እንዲሁም የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ፣ ልግስናና ደግነት ስናሳይም እንደሚያስተውል እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዕብ. 13:16፤ w18.07 26 አን. 15, 17

ቅዳሜ፣ መጋቢት 21

[ከይሖዋ] ጋር ተጣበቅ።—ዘዳ. 10:20

ከይሖዋ ጋር መጣበቅ ተገቢ ነው። እንደ አምላካችን ያለ ኃያል፣ ጥበበኛና አፍቃሪ አካል የለም! ከመካከላችን ከእሱ ጎን መቆም የማይፈልግ ማን አለ? (መዝ. 96:4-6) ያም ሆኖ ከአምላክ አገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹ ከይሖዋ ጎን መቆም የሚጠይቅ ሁኔታ ባጋጠማቸው ጊዜ እንዲህ ሳያደርጉ ቀርተዋል። የቃየንን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ቃየን የሚያመልከው የሐሰት አማልክትን ሳይሆን ይሖዋን ነበር። ሆኖም አምልኮው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። ምክንያቱም በልቡ ውስጥ የክፋት ሐሳብ እያቆጠቆጠ ነበር። (1 ዮሐ. 3:12) ይሖዋ ቃየንን ሊረዳው ስላሰበ እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጠው፦ “መልካም ወደ ማድረግ ብታዘነብል ኖሮ ሞገስ አታገኝም ነበር? መልካም ወደ ማድረግ ካላዘነበልክ ግን ኃጢአት በደጅህ እያደባ ነው፤ ሊቆጣጠርህም ይፈልጋል፤ ታዲያ አንተ ትቆጣጠረው ይሆን?” (ዘፍ. 4:6, 7) በሌላ አነጋገር ይሖዋ “ንስሐ ከገባህና ከጎኔ ጸንተህ ከቆምክ እኔም ከጎንህ እሆናለሁ” እያለው ነበር። ቃየን ግን ምክሩን አልሰማም። w18.07 17 አን. 1, 3፤ 18 አን. 4

እሁድ፣ መጋቢት 22

ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።—ማቴ. 5:16

ብርሃናችንን ማብራት ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ፣ ምሥራቹን በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መካፈል ነው። (ማቴ. 28:19, 20) ከዚህም በተጨማሪ በምናሳየው ምግባር ይሖዋን ማስከበር እንችላለን። ምሥራቹን የምንሰብክላቸው ሰዎችም ሆነ ስንሰብክ የሚመለከቱን ሌሎች ግለሰቦች የምናሳየውን ባሕርይ ይታዘባሉ። ሰዎችን ስናነጋግር ፈገግ ብለን ወዳጃዊ ስሜት በሚንጸባረቅበት መንገድ ሰላምታ መስጠታችን፣ ሌሎች ለእኛም ሆነ ለምናመልከው አምላክ ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ወደ ቤትም ስትገቡ ቤተሰቡን ሰላም በሉ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 10:12) ኢየሱስና ሐዋርያቱ በሚሰብኩበት አካባቢ፣ ሰዎች ወደ ቤታቸው የመጣን ሰው ባያውቁትም እንኳ ወደ ውስጥ እንዲገባ የመጋበዝ ባሕል ነበራቸው። በዛሬው ጊዜ በብዙ አካባቢዎች እንዲህ ዓይነቱ ልማድ ቀርቷል። ያም ቢሆን ወደ ቤታቸው የመጣንበትን ምክንያት በደግነትና ወዳጃዊ ስሜት በሚንጸባረቅበት መንገድ ካስረዳናቸው የቤቱ ባለቤቶች ሊረጋጉ ይችላሉ። በዚህ ረገድ ፈገግታ ትልቅ ኃይል አለው። በጽሑፍ ጋሪ ተጠቅመን ስንመሠክርም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ሰዎችን ፈገግ ብለን ሰላም ስንላቸው ብዙውን ጊዜ ጥሩ ምላሽ ይሰጣሉ። w18.06 22 አን. 4-5

ሰኞ፣ መጋቢት 23

አምላክ [አያዳላም]።—ሥራ 10:34

ቀደም ሲል ሐዋርያው ጴጥሮስ የሚቀራረበው ከአይሁዳውያን ጋር ብቻ ነበር። ክርስቲያኖች ማዳላት እንደሌለባቸው አምላክ በግልጽ ካሳወቀው በኋላ ግን ጴጥሮስ ሮማዊ ወታደር ለሆነው ለቆርኔሌዎስ ሰብኳል። (ሥራ 10:28, 35) ከዚያ በኋላ ጴጥሮስ ከአሕዛብ ወገን ከሆኑ አማኞች ጋር አብሮ ይመገብና ጊዜ ያሳልፍ ነበር። ከዓመታት በኋላ ግን ጴጥሮስ በአንጾኪያ በነበረበት ወቅት፣ አይሁዳውያን ካልሆኑት ክርስቲያኖች ጋር አብሮ መብላት አቁሞ ራሱን ከእነሱ አገለለ። (ገላ. 2:11-14) በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ለጴጥሮስ ተገቢውን ተግሣጽ የሰጠው ሲሆን ጴጥሮስም እርማቱን ተቀብሏል። ይህን እንዴት እናውቃለን? ጴጥሮስ በትንሿ እስያ ለሚኖሩ አይሁዳውያንና ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ክርስቲያኖች የመጀመሪያ ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት መላውን የወንድማማች ማኅበር መውደድ አስፈላጊ መሆኑን አበክሮ ገልጿል። (1 ጴጥ. 1:1፤ 2:17) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሐዋርያት “ሁሉንም ዓይነት ሰዎች” መውደድ እንዳለባቸው ከኢየሱስ ምሳሌ ተምረዋል። (ዮሐ. 12:32፤ 1 ጢሞ. 4:10) ሐዋርያቱ አመለካከታቸውን ለማስተካከል ጊዜ ቢወስድባቸውም ይህን ማድረግ ችለዋል። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች “አዲሱን ስብዕና” ስለለበሱ፣ ልክ እንደ አምላክ ሁሉንም ሰዎች በእኩል ዓይን ማየት ችለው ነበር።—ቆላ. 3:10, 11፤ w18.06 11 አን. 15-16

ማክሰኞ፣ መጋቢት 24

የጽድቅን ጥሩር ለብሳችሁ ጸንታችሁ ቁሙ።—ኤፌ. 6:14

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የሮም ወታደሮች ከሚጠቀሙባቸው የጥሩር ዓይነቶች መካከል፣ አንዱ በሌላው ላይ በተነባበሩ ጠፍጣፋ ብረቶች የተሠራ ጥሩር ይገኝበታል። እንዲህ ዓይነቱን ጥሩር ያደረገ ወታደር ጥሩሩ ቦታውን እንዳልለቀቀ ሁልጊዜ ማረጋገጥ ይኖርበታል። ይህን ማድረጉ ጠላቱ ልቡንና ሌሎች የሰውነቱን ክፍሎች እንዳይወጋ ለመከላከል ይረዳዋል። ወታደሮቹ የሚለብሱት ጥሩር፣ ምሳሌያዊውን ልባችንን ከጉዳት ከሚጠብቁት የይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ሊመሳሰል ይችላል። (ምሳሌ 4:23) አንድ ወታደር ከብረት የተሠራ ጥሩሩን አውልቆ መናኛ በሆነ ንጥረ ነገር የተሠራ ጥሩር እንደማያደርግ የታወቀ ነው፤ በተመሳሳይ እኛም ትክክል የሆነውን ነገር በተመለከተ የይሖዋን መሥፈርቶች ትተን በራሳችን መሥፈርቶች ለመመራት ፈጽሞ አንፈልግም። የሰው ልጆች፣ ልባችንን ለመጠበቅ የሚያስችል የማመዛዘን ችሎታ ጨርሶ የለንም። (ምሳሌ 3:5, 6) በመሆኑም ይሖዋ የሰጠንን ‘የብረት ጥሩር’ ልባችንን በሚገባ በሚከልል መንገድ መታጠቃችንን አዘውትረን ማረጋገጥ ይኖርብናል። በተጨማሪም ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ይበልጥ ፍቅር ባዳበርን መጠን ‘ጥሩራችንን’ መሸከም ይኸውም በአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች መመራት የበለጠ ቀላል ይሆንልናል።—መዝ. 111:7, 8፤ 1 ዮሐ. 5:3፤ w18.05 28 አን. 3-4, 6-7

ረቡዕ፣ መጋቢት 25

ሕዝቡም . . . ከሙሴ ጋር ተጣላ።—ዘኁ. 20:3

ሙሴ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ እስራኤላውያንን ለረጅም ጊዜ ሲመራ ቆይቷል፤ ሆኖም ሕዝቡ ውኃ በማጣታቸው ብቻ ሳይሆን በሙሴ ምክንያት ውኃ ያጡ ይመስል በእሱ ላይ ጭምር አጉረምርመዋል። (ዘኁ. 20:1-5, 9-11) ሙሴ በጣም ስለተበሳጨ እንደ ወትሮው ገር መሆን ሳይችል ቀረ። በይሖዋ በመታመን ልክ እንደታዘዘው ዓለቱን ከመናገር ይልቅ በምሬት ሕዝቡን የተቆጣ ከመሆኑም ሌላ ተአምሩን የሚፈጽመው እሱ ራሱ እንደሆነ በሚያስመስል መንገድ ተናገረ። ከዚያም ዓለቱን ሁለቴ ሲመታው ውኃው እየተንዶለዶለ ይወጣ ጀመር። ኩራትና ብስጭት፣ ሙሴን አሳዛኝ ስህተት እንዲሠራ አድርገውታል። (መዝ. 106:32, 33) ሙሴ ለተወሰነ ጊዜ ያህል የዋህነት ማሳየት ስላቃተው ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ተከልክሏል። (ዘኁ. 20:12) ከዚህ ታሪክ ትልቅ ትምህርት እናገኛለን። አንደኛ፣ ምንጊዜም የዋህ ሆነን ለመቀጠል ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ አለብን። ለአፍታ እንኳ ከተዘናጋን ወዲያውኑ ኩራት ሊጠናወተንና ሞኝነት የሚንጸባረቅበት ነገር ልንናገር ወይም ልናደርግ እንችላለን። ሁለተኛ፣ ውጥረት ውስጥ ስንሆን የዋህነት ማሳየት ከባድ ሊሆንብን ይችላል፤ ስለዚህ ውጥረት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜም እንኳ የዋህነት ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። w19.02 12-13 አን. 19-21

ሐሙስ፣ መጋቢት 26

ይህ የመንግሥቱ ምሥራች . . . በመላው ምድር ይሰበካል።—ማቴ. 24:14

ኢየሱስ እንድንሰብክ የሰጠን ትእዛዝ ከባድ ሸክም ነው? በጭራሽ። ኢየሱስ ስለ ወይን ተክሉ የሚገልጸውን ምሳሌ ከተናገረ በኋላ የመንግሥቱን መልእክት ስንሰብክ ደስታ እንደምናገኝ ገልጿል። (ዮሐ. 15:11) እንዲያውም ኢየሱስ፣ እሱ ያገኘውን ደስታ እኛም እንደምናገኝ አረጋግጦልናል። ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? ኢየሱስ ራሱን ከወይን ተክል፣ ደቀ መዛሙርቱን ደግሞ ከወይኑ ተክል ቅርንጫፎች ጋር አመሳስሏቸዋል። (ዮሐ. 15:5) ቅርንጫፎቹ ውኃና ሌሎች አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን የሚያገኙት ከወይኑ ተክል ጋር ተጣብቀው እስከቀጠሉ ድረስ ነው። በተመሳሳይ እኛም የክርስቶስን ፈለግ በጥብቅ በመከተል ከእሱ ጋር ተጣብቀን እስከኖርን ድረስ ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ በማድረግ ያገኘውን ዓይነት ደስታ ማጣጣም እንችላለን። (ዮሐ. 4:34፤ 17:13፤ 1 ጴጥ. 2:21) ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለችው ሃኔ “በስብከቱ ሥራ ከተካፈልኩ በኋላ ሁልጊዜ የሚሰማኝ ደስታ በይሖዋ አገልግሎት እንድቀጥል ይገፋፋኛል” ብላለች። በእርግጥም አገልግሎቱ የሚያስገኝልን ጥልቅ ደስታ፣ አስቸጋሪ በሆኑ ክልሎች ውስጥ እንኳ መስበካችንን እንድንቀጥል ብርታት ይሰጠናል።—ማቴ. 5:10-12፤ w18.05 17 አን. 2፤ 20 አን. 14

ዓርብ፣ መጋቢት 27

እምነትንና እውነትን በተመለከተ የአሕዛብ አስተማሪ ሆኜ [ተሹሜያለሁ]።—1 ጢሞ. 2:7

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ወንድሞቹን በማበረታታት ረገድ ከሁሉ የላቀ ሚና የተጫወተው ሐዋርያው ጳውሎስ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ጳውሎስ ግሪካውያንንና ሮማውያንን ጨምሮ የአይሁድ እምነት ተከታይ ላልሆኑ የተለያዩ አማልክትን የሚያመልኩ ሰዎች እንዲሰብክ በመንፈስ ቅዱስ ተልኮ ነበር። (ገላ. 2:7-9) ጳውሎስ በዛሬዋ ቱርክ እንዲሁም በመላው የግሪክና የጣሊያን ግዛት ረጅም ጉዞ በማድረግ አይሁዳዊ ባልሆኑ ሰዎች መካከል የክርስቲያን ጉባኤዎችን አቋቁሟል። እነዚህ አዲስ ክርስቲያኖች ‘በገዛ አገራቸው ሰዎች እጅ መከራ’ ይደርስባቸው ስለነበር ማበረታቻ አስፈልጓቸዋል። (1 ተሰ. 2:14) ጳውሎስ በቅርቡ ለተቋቋመው የተሰሎንቄ ጉባኤ በ50 ዓ.ም. አካባቢ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “ሁላችሁንም በጸሎታችን በጠቀስን ቁጥር ሁልጊዜ አምላክን እናመሰግናለን፤ የእምነት ሥራችሁን፣ ከፍቅር የመነጨ ድካማችሁንና . . . የምታሳዩትን ጽናት . . . ዘወትር እናስባለን።” (1 ተሰ. 1:2, 3) በተጨማሪም “እርስ በርስ ተበረታቱ እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ” በማለት አንዳቸው ለሌላው የብርታት ምንጭ እንዲሆኑ አሳስቧቸዋል።—1 ተሰ. 5:11፤ w18.04 18-19 አን. 16-17

ቅዳሜ፣ መጋቢት 28

አስቀድሞም ምሥራቹ ለብሔራት ሁሉ መሰበክ አለበት።—ማር. 13:10

ይሖዋን በማስደሰት ላይ ያተኮረ ሕይወት የሚመራ ወጣት ለአገልግሎት ቅድሚያ ይሰጣል። የስብከቱ ሥራ በጣም አጣዳፊ ከመሆኑ አንጻር በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ልንሰጠው እንደሚገባ አያጠራጥርም። አንተስ በአገልግሎት ይበልጥ አዘውትረህ የመካፈል ግብ ልታወጣ ትችላለህ? በአቅኚነት ማገልገል ትችል ይሆን? በሌላ በኩል ደግሞ በስብከቱ ሥራ መካፈል ያን ያህል የማያስደስትህ ቢሆን ምን ማድረግ ትችላለህ? ይበልጥ ውጤታማ ሰባኪ መሆን የምትችለውስ እንዴት ነው? ሁለት ነገሮች ሊረዱህ ይችላሉ፦ በሚገባ ተዘጋጅ እንዲሁም የምታውቀውን ለሌሎች ለመናገር በምታደርገው ጥረት ተስፋ አትቁረጥ። እነዚህን እርምጃዎች መውሰድህ በስብከቱ ሥራ ላይ ያልጠበቅከውን ደስታ ለማግኘት ያስችልሃል። ለስብከቱ ሥራ በሚገባ ለመዘጋጀት የሚረዳህ የመጀመሪያው እርምጃ፣ አብረውህ የሚማሩ ልጆች ብዙ ጊዜ ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ ለማግኘት መሞከር ነው። “በአምላክ የምታምነው ለምንድን ነው?” የሚለውን ጥያቄ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ወጣቶች የዚህን ጥያቄ መልስ ለመዘጋጀት የሚረዷቸውን ርዕሶች jw.org በተባለው ድረ ገጻችን ላይ ማግኘት ይችላሉ። ድረ ገጹ ላይ “አምላክ መኖሩን እንዳምን ያደረገኝ ምንድን ነው?” የሚል የመልመጃ ሣጥን ይገኛል። የመልመጃ ሣጥኑ የራስህን መልስ እንድታዘጋጅ ይረዳሃል። w18.04 27 አን. 10-11

እሁድ፣ መጋቢት 29

ብዙ ተባዙ።—ዘፍ. 1:28

አዳምና ሔዋን መጀመሪያ ላይ በተለያዩ አቅጣጫዎች ነፃነት የነበራቸው ቢሆንም አንዳንድ ገደቦችም ተጥለውባቸው ነበር። በእርግጥ አንዳንዶቹ ገደቦች የተፈጥሯቸው ክፍል በመሆናቸው እነዚህን ገደቦች ማክበር የተለየ ጥረት የሚጠይቅ አልነበረም። ለምሳሌ ያህል፣ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በሕይወት ለመቀጠል ከፈለጉ መተንፈስ፣ መብላት፣ መተኛትና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮችን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቁ ነበር። ይህ መሆኑ ታዲያ ነፃነታቸውን ይገድበዋል? በፍጹም፤ ምክንያቱም ይሖዋ የፈጠራቸው እነዚህን ነገሮች በማከናወን ደስታና እርካታ እንዲያገኙ አድርጎ ነው። (መዝ. 104:14, 15፤ መክ. 3:12, 13) ይሖዋ፣ ምድርን እንዲሞሏትና እንዲንከባከቧት አዳምንና ሔዋንን አዟቸው ነበር። ይህ ትእዛዝ ነፃነታቸውን የሚገድብ ነበር? በጭራሽ! ይሖዋ ይህን መመሪያ የሰጣቸው፣ ምድርን ገነት ለማድረግና ፍጹም በሆኑ የሰው ልጆች ለመሙላት ካለው ዓላማ ጋር በተያያዘ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ስለፈለገ ነው። (መዝ. 127:3፤ ኢሳ. 45:18) አዳምና ሔዋን ይሖዋ የሰጣቸውን ትእዛዝ ቢያከብሩ ኖሮ በትዳርና በቤተሰብ ሕይወታቸው እየተደሰቱ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ያገኙ ነበር። w18.04 4-5 አን. 7-8

ሰኞ፣ መጋቢት 30

ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ አማኞች ሆኑ።—ሥራ 13:48

በአገልግሎት ስንካፈል ትዕግሥተኞች ከሆን ሰዎች ከዚህ በፊት ሰምተዋቸው የማያውቋቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ወዲያውኑ እንዲረዱ ወይም እንዲቀበሉ አንጠብቅባቸውም። ለምሳሌ ያህል፣ በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋችንን በተመለከተ ለሰዎች ማስረዳት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። በርካታ ሰዎች ሞት የሁሉም ነገር መጨረሻ እንደሆነ ያምናሉ። አሊያም ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ሊያስቡ ይችላሉ። አንድ ወንድም በዚህ ረገድ ውጤታማ ሆኖ ያገኘውን አቀራረብ ተናግሯል። ለሚያነጋግራቸው ሰዎች በመጀመሪያ ዘፍጥረት 1:28⁠ን ያነብላቸዋል። ከዚያም አምላክ የሰው ልጆችን የፈጠራቸው የትና በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዲኖሩ አስቦ እንደሆነ ይጠይቃቸዋል። አብዛኞቹ ሰዎች “ምድር ላይ አስደሳች ሕይወት እንዲመሩ ነው” በማለት ይመልሳሉ። ከዚያም ወንድም ኢሳይያስ 55:11⁠ን ያነብላቸውና “አምላክ ዓላማውን ይለውጣል?” ብሎ ይጠይቃቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎቹ “አይ፣ አይለውጥም” ብለው ይመልሱለታል። በመጨረሻም ወንድም መዝሙር 37:10, 11⁠ን ካነበበላቸው በኋላ የሰው ልጆች ወደፊት ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚጠብቃቸው ይጠይቃቸዋል። ይህ ወንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በዚህ መንገድ ተጠቅሞ አምላክ አሁንም ጥሩ የሆኑ ሰዎች ለዘላለም ገነት በሆነች ምድር ላይ እንዲኖሩ እንደሚፈልግ በማብራራት በርካታ ሰዎችን መርዳት ችሏል። w19.03 24 አን. 14-15፤ 25 አን. 19

ማክሰኞ፣ መጋቢት 31

እሱን ስሙት።—ማቴ. 17:5

ይሖዋ ልጁ የተናገራቸውን ነገሮች እንድንሰማና እንድንታዘዝ ያለውን ፍላጎት ግልጽ አድርጓል። ኢየሱስ ተከታዮቹ የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ እንዳለባቸው ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ አስተምሯቸዋል፤ እንዲሁም ነቅተው እንዲጠብቁ በተደጋጋሚ አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 24:42፤ 28:19, 20) በተጨማሪም ሕይወት ለማግኘት ከፍተኛ ተጋድሎ እንዲያደርጉ የመከራቸው ከመሆኑም ሌላ ተስፋ እንዳይቆርጡ አበረታቷቸዋል። (ሉቃስ 13:24) ከዚህም በላይ ተከታዮቹ እርስ በርስ መዋደድ፣ አንድነታቸውን መጠበቅና ትእዛዛቱን መፈጸም እንደሚያስፈልጋቸው አጽንኦት ሰጥቶ ተናግሯል። (ዮሐ. 15:10, 12, 13) ይህ ምክር በዚያን ጊዜ ጠቃሚ እንደነበር ሁሉ ዛሬም ጠቃሚ ነው። ኢየሱስ “ከእውነት ጎን የቆመ ሁሉ ቃሌን ይሰማል” ብሏል። (ዮሐ. 18:37) የኢየሱስን ድምፅ እንደምንሰማ የምናሳየው “እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ነው። (ቆላ. 3:13፤ ሉቃስ 17:3, 4) በተጨማሪም “አመቺ በሆነ ጊዜም ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜ” ምሥራቹን በቅንዓት በመስበክ ድምፁን እንደምንሰማ እናሳያለን።—2 ጢሞ. 4:2፤ w19.03 10 አን. 9-10

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ