ሚያዝያ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 1
[ኢየሱስ] ጴጥሮስን “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ ሰይጣን! የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ [አታስብም]” አለው።—ማቴ. 16:23
ስለ እኛስ ምን ማለት ይቻላል? የምናንጸባርቀው የአምላክን አስተሳሰብ ነው ወይስ የዚህን ዓለም? እርግጥ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ምግባራችንን አምላክ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር እንዳስማማን ግልጽ ነው። ሆኖም አስተሳሰባችንስ እንዴት ነው? አስተሳሰባችንና አመለካከታችን ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር እንዲስማማ እያደረግን ነው? ይህ የታሰበበት ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። በሌላ በኩል ግን የዓለምን አስተሳሰብ መቀበል ያን ያህል ጥረት አይጠይቅም፤ እንዲያውም በጣም ቀላል ነው። ምክንያቱም ዙሪያችንን የከበበን የዓለም መንፈስ ነው። (ኤፌ. 2:2) ከዚህም በተጨማሪ የዓለም አስተሳሰብ በአብዛኛው ለራሳችን ፍላጎት ቅድሚያ እንድንሰጥ ስለሚያበረታታ በቀላሉ ሊማርከን ይችላል። አዎ፣ የይሖዋን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ ተፈታታኝ ቢሆንም የዓለምን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ ግን በጣም ቀላል ነው። ይሁንና ዓለም አስተሳሰባችንን እንዲቀርጸው የምንፈቅድ ከሆነ በራስ የመመራት ዝንባሌ ሊጠናወተንና ራስ ወዳዶች ልንሆን እንችላለን። (ማር. 7:21, 22) ስለዚህ “የሰውን” ሳይሆን “የአምላክን ሐሳብ” ለማዳበር ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። w18.11 18 አን. 1፤ 19 አን. 3-4
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 2
በጣም የምደሰትበት የምወደው ልጄ ይህ ነው።—ማቴ. 3:17
ኢየሱስ በሦስት የተለያዩ ወቅቶች ይሖዋ በቀጥታ ከሰማይ በመናገር እውቅና ሲሰጠው ምንኛ ተበረታቶ ይሆን! ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ተጠምቆ እንደወጣ ይሖዋ ከላይ ያለውን ሐሳብ ተናገረ። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ከኢየሱስ ሌላ ይህን የሰማው መጥምቁ ዮሐንስ ብቻ ነው። ከዚያም ኢየሱስ ከመሞቱ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ይሖዋ ኢየሱስን አስመልክቶ “በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት” በማለት የተናገረ ሲሆን ይህንንም ሦስት ሐዋርያቱ ሰምተዋል። (ማቴ. 17:5) በመጨረሻም ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ቀናት በፊት ይሖዋ በድጋሚ ልጁን ከሰማይ አነጋግሮታል። (ዮሐ. 12:28) ኢየሱስ አምላክን ሰድቧል በሚል የሐሰት ክስ ተወንጅሎ የውርደት ሞት እንደሚሞት ቢያውቅም የእሱ ሳይሆን የይሖዋ ፈቃድ እንዲፈጸም ጸልዮአል። (ማቴ. 26:39, 42) እውቅና ማግኘት የሚፈልገው ከዓለም ሳይሆን ከአባቱ ብቻ ስለነበር “የሚደርስበትን ውርደት ከምንም ሳይቆጥር በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ጸንቷል።”—ዕብ. 12:2፤ w18.07 10-11 አን. 15-16
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 9፦ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች) ማርቆስ 14:3-9
ዓርብ፣ ሚያዝያ 3
አባት ሆይ፣ ፈቃድህ ከሆነ ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ።—ሉቃስ 22:42
ኢየሱስ የጌታ ራት በዓልን ካቋቋመ ብዙም ሳይቆይ አስደናቂ ድፍረት አሳይቷል። እንዴት? አባቱ ለእሱ ያለውን ፈቃድ መፈጸሙ አምላክን ሰድቧል በሚል አሳፋሪ ወንጀል እንደሚያስከስሰውና እንደሚያስገድለው ቢያውቅም የአባቱን ፈቃድ ከመፈጸም ወደኋላ አላለም። (ማቴ. 26:65, 66) ኢየሱስ የይሖዋን ስም ለማክበር፣ የአምላክን ሉዓላዊነት ለመደገፍና ንስሐ የሚገቡ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን በር ለመክፈት ሲል ንጹሕ አቋሙን ፍጹም በሆነ መንገድ ጠብቋል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ተከታዮቹን በቅርቡ ለሚጠብቃቸው ነገር አዘጋጅቷቸዋል። በተጨማሪም ኢየሱስ በወቅቱ ተሰምቶት ሊሆን በሚችለው ጭንቀት ላይ ከማተኮር ይልቅ ታማኝ ሐዋርያቱ በሚያስፈልጋቸው ነገር ላይ ትኩረት በማድረግ ድፍረት እንዳለው አሳይቷል። ይሁዳ እንዲወጣ ካደረገ በኋላ ያቋቋመው ቀለል ያለ በዓል ወደፊት በመንፈስ ለሚቀቡ ተከታዮቹ፣ የአዲሱ ቃል ኪዳን ተካፋይ መሆናቸው ያስገኘላቸውን መብትና የፈሰሰው ደሙ ያስገኘላቸውን ጥቅም ያስታውሳቸዋል።—1 ቆሮ. 10:16, 17፤ w19.01 22 አን. 7-8
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 9፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማርቆስ 11:1-11
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 4
አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው።—ዮሐ. 12:28
በምላሹም የኢየሱስ አባት “ስሜን አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ” በማለት ከሰማይ ተናገረ። ኢየሱስ እስከ መጨረሻው ለይሖዋ ታማኝ የመሆኑ ጉዳይ በጣም አስጨንቆት ነበር። ኃይለኛ ግርፋት እንደሚጠብቀውና በአሰቃቂ ሁኔታ እንደሚገደል ያውቃል። (ማቴ. 26:38) ከምንም በላይ ኢየሱስ የአባቱን ስም ማስከበር ይፈልግ ነበር። ኢየሱስ ‘አምላክን ሰድቧል’ በሚል ወንጀል ተከስሶ መገደሉ በአምላክ ስም ላይ ነቀፋ እንዳያመጣ ፈርቶ ነበር። ልክ እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም በይሖዋ ስም ላይ የሚደርሰው ነቀፋ ሊያሳስበን ይችላል። ምናልባትም እንደ ኢየሱስ ኢፍትሐዊ ድርጊት ተፈጽሞብን ይሆናል። አሊያም ተቃዋሚዎች ስለ እኛ በሚያሰራጩት የሐሰት ወሬ ምክንያት ተረብሸን ሊሆን ይችላል። እነዚህ ወሬዎች በይሖዋ ስም ላይ የሚያስከትሉትን ነቀፋ እያሰብን ልንጨነቅ እንችላለን። እንዲህ ባሉ ጊዜያት፣ ይሖዋ የተናገራቸውን ቃላት ማስታወሳችን በእጅጉ ያጽናናናል። ይሖዋ በምንም ዓይነት ስሙን ሳያስከብር አይቀርም።—መዝ. 94:22, 23፤ ኢሳ. 65:17፤ w19.03 11-12 አን. 14-16
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 10፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማርቆስ 11:12-19
እሁድ፣ ሚያዝያ 5
ኢየሱስ . . . ከባድ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ እንደሚገባው . . . ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጽላቸው ጀመር።—ማቴ. 16:21
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጆሯቸውን ማመን አቅቷቸዋል። የእስራኤልን መንግሥት መልሶ ያቋቁማል ብለው ያሰቡት ኢየሱስ በቅርቡ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚገደል ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ቀድሞ ምላሽ የሰጠው ሐዋርያው ጴጥሮስ ነው። “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን” በማለት ተናገረ። አክሎም “በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” አለው። ኢየሱስም “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ ሰይጣን! የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ ስለማታስብ እንቅፋት ሆነህብኛል” በማለት መለሰለት። (ማቴ. 16:22, 23፤ ሥራ 1:6) ኢየሱስ የተናገረው ይህ ሐሳብ በአምላክ አስተሳሰብና በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው ዓለም አስተሳሰብ መካከል ግልጽ ልዩነት እንዳለ ይጠቁማል። (1 ዮሐ. 5:19) ጴጥሮስ በዓለም ላይ የሚታየውን ለራስ የመሳሳት ዝንባሌ እያንጸባረቀ ነበር። ኢየሱስ ግን የአባቱ አስተሳሰብ ከዚህ የተለየ እንደሆነ ያውቃል። ለጴጥሮስ የሰጠው መልስ እንደሚያሳየው ኢየሱስ የዓለምን አስተሳሰብ በግልጽ በመቃወም በይሖዋ አስተሳሰብ ለመመራት መርጧል። w18.11 18 አን. 1-2
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 11፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማርቆስ 11:20 እስከ 12:27, 41-44
ሰኞ፣ ሚያዝያ 6
ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን ታውጃላችሁ።—1 ቆሮ. 11:26
ይሖዋ በዓለም ዙሪያ በጌታ ራት ላይ የተገኙትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲመለከት ምን ላይ እንደሚያተኩር ለማሰብ ሞክር። በዝግጅቱ ላይ የተገኙትን በርካታ ሰዎች በጥቅሉ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ይመለከታል። ለምሳሌ ያህል፣ በየዓመቱ በታማኝነት በዚህ ስብሰባ ላይ የሚገኙትን ሰዎች ያያል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በስብሰባው ላይ የሚገኙት፣ የሚደርስባቸውን ከባድ ስደት ተቋቁመው ሊሆን ይችላል። ሌሎች ደግሞ በሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው ባይገኙም በመታሰቢያው በዓል ላይ የግድ መገኘት እንዳለባቸው ስለሚሰማቸው ፈጽሞ አይቀሩም። በተጨማሪም ይሖዋ በመታሰቢያው በዓል ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኙ ሰዎችንም ያያል፤ ምናልባትም እነዚህ ሰዎች በበዓሉ ላይ የተገኙት ምን እንደሚከናወን ለማወቅ ፈልገው ሊሆን ይችላል። ይሖዋ በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙትን በርካታ ሰዎች ሲያይ እንደሚደሰት ምንም ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 22:19) ሆኖም በዋነኝነት ትኩረት የሚያደርገው ሰዎቹን በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ባነሳሳቸው ምክንያት ላይ ነው። በይሖዋ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሰዎቹ ይህን እርምጃ ለመውሰድ የተነሳሱበት ውስጣዊ ግፊት ነው። ከይሖዋና እሱ እየተጠቀመበት ካለው ድርጅት ለመማር ከፍተኛ ጉጉት አለን?—ኢሳ. 30:20፤ ዮሐ. 6:45፤ w19.01 26 አን. 1-3
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 12፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማርቆስ 14:1, 2, 10, 11፤ ማቴዎስ 26:1-5, 14-16
የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ዕለት
ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 7
ክርስቶስ [ሞቶልናል]።—ሮም 5:8
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠት ባለፈ በእያንዳንዱ ቀን ከራሱ ፍላጎት ይልቅ ለእነሱ ፍላጎት ቅድሚያ ይሰጥ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በጣም ደክሞት ወይም ተጨንቆ በነበረበት ጊዜ እንኳ ከተከታዮቹ ጋር ጊዜ አሳልፏል። (ሉቃስ 22:39-46) በተጨማሪም ትኩረት ያደረገው ከሌሎች በሚያገኘው ነገር ላይ ሳይሆን ለሌሎች በሚሰጠው ነገር ላይ ነበር። (ማቴ. 20:28) በዓለም ላይ ያለው ብቸኛውና እውነተኛው የወንድማማች ማኅበር አባል እንደመሆናችን መጠን አዲሶች ከእኛ ጋር በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ አቅማችን የፈቀደውን ያህል ብዙ ሰዓት ማሳለፋችን ያስደስተናል። ሆኖም ይበልጥ ትኩረት የምናደርገው ‘በእምነት የሚዛመዱንን’ የቀዘቀዙ አስፋፊዎች በመርዳት ላይ ነው። (ገላ. 6:10) እነዚህን አስፋፊዎች በስብሰባዎች በተለይ ደግሞ በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ በማበረታታት ለእነሱ ያለንን ፍቅር እናሳያለን። ልክ እንደ ይሖዋና እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም አንድ የቀዘቀዘ ክርስቲያን ወደ ይሖዋ ሲመለስ እጅግ ደስ ይለናል።—ማቴ. 18:14፤ w19.01 29 አን. 12, 14፤ 30 አን. 15
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 13፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማርቆስ 14:12-16፤ ማቴዎስ 26:17-19 (ኒሳን 14፦ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች) ማርቆስ 14:17-72
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 8
ይህ ሥጋዬን ያመለክታል። . . . ይህ . . . “የቃል ኪዳን ደሜን” ያመለክታል።—ማቴ. 26:26-28
ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ሲያቋቁም የተጠቀመው፣ ከፋሲካው ማዕድ የተረፈውን ቂጣና ወይን ብቻ ነው። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ እነዚህ ሁለት ነገሮች በቅርቡ ለእነሱ ሲል መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበውን ፍጹም የሆነውን ሥጋውንና ደሙን እንደሚያመለክቱ ነገራቸው። ሐዋርያቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ይህ አዲስ ዝግጅት፣ ቀለል ያለ መሆኑ ያን ያህል አላስገረማቸው ይሆናል። ለምን? ኢየሱስ ከተወሰኑ ወራት በፊት የቅርብ ጓደኞቹ ወደሆኑት ወደ አልዓዛር፣ ማርታና ማርያም ቤት ሄዶ ማስተማር ጀመረ። ማርታም በቦታው ነበረች፤ ሆኖም ቤቷ ለተገኘው ለዚህ የተከበረ እንግዳ ትልቅ ግብዣ በማዘጋጀት ተጠምዳ ስለነበር ትኩረቷ ተከፋፍሏል። ኢየሱስ ይህን ስላስተዋለ ለማርታ በደግነት ምክር ሰጣት፤ ምክሩ ትልቅ ግብዣ ማዘጋጀት የግድ አስፈላጊ እንዳልሆነ እንድታስተውል የሚረዳ ነበር። (ሉቃስ 10:40-42) ኢየሱስ ለማርታ የሰጣትን ይህንኑ ምክር፣ ከጊዜ በኋላ መሥዋዕት ሆኖ ከመሞቱ ከጥቂት ሰዓታት በፊት እሱ ራሱ ተግባራዊ አድርጎታል። ለመታሰቢያ በዓሉ የተጠቀመበት ማዕድ ቀለል ያለ እንዲሆን አድርጓል። w19.01 20-21 አን. 3-4
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 14፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማርቆስ 15:1-47
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 9
አባት ሆይ . . . በጎንህ ሆኜ ክብር እንደነበረኝ ሁሉ አሁንም በጎንህ አድርገህ አክብረኝ።—ዮሐ. 17:5
ይሖዋ ኢየሱስን ፈጽሞ ባልተጠበቀ መንገድ አክብሮታል፤ ከሞት ካስነሳው በኋላ “የላቀ ቦታ [የሰጠው]” ከመሆኑም ሌላ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ለማንም ተሰጥቶ የማያውቅ የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት እንዲያገኝ አድርጓል! (ፊልጵ. 2:9፤ 1 ጢሞ. 6:16) በእርግጥም ኢየሱስ ለተከተለው የታማኝነት ጎዳና አስደናቂ በሆነ መንገድ እውቅና አግኝቷል! በዚህ ዓለም ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት እንዳንጣጣር ምን ሊረዳን ይችላል? ይሖዋ ምንጊዜም ለታማኝ አገልጋዮቹ እውቅና እንደሚሰጥና አብዛኛውን ጊዜም እንዲህ የሚያደርገው ባልተጠበቀ መንገድ እንደሆነ እናስታውስ። ወደፊትስ ቢሆን ይሖዋ ያልጠበቅናቸውን በረከቶች አዘጋጅቶልን እንደሆነ ማን ያውቃል? እስከዚያው ድረስ ግን ይህ ክፉ ዓለም እንደሚያልፍ በማስታወስ የሚደርስብንን ማንኛውንም ችግርና ፈተና በጽናት እንቋቋም። (1 ዮሐ. 2:17) አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ ‘የምናከናውነውን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳየነውን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።’—ዕብ. 6:10፤ w18.07 11 አን. 17-18
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 15፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማቴዎስ 27:62-66 (ኒሳን 16፦ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች) ማርቆስ 16:1
ዓርብ፣ ሚያዝያ 10
የምለምንህ . . . ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው።—ዮሐ. 17:20, 21
ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት፣ በመካከላቸው ያለው አንድነት እንደሚያሳስበው የሚያሳይ ሐሳብ ተናግሯል። ከሐዋርያቱ ጋር ሆኖ ባቀረበው ጸሎት ላይ፣ እሱና አባቱ አንድ እንደሆኑ ሁሉ ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ አንድ እንዲሆኑ ያለውን ፍላጎት ገልጿል። በደቀ መዛሙርቱ መካከል የሚኖረው አንድነት፣ የአምላክን ፈቃድ እንዲያደርግ ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው ይሖዋ መሆኑን የሚመሠክር ግልጽ ማስረጃ ይሆናል። ፍቅር የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ተለይተው የሚታወቁበት ባሕርይ ሲሆን እንዲህ ያለው ፍቅር ለአንድነታቸው አስተዋጽኦ ያበረክታል። (ዮሐ. 13:34, 35) ኢየሱስ የአንድነትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የገለጸው ሐዋርያቱ በዚህ ረገድ ድክመት እንዳላቸው ስላስተዋለ ሊሆን ይችላል። ሐዋርያቱ ከዚያ ቀደም እንዳደረጉት ሁሉ ከኢየሱስ ጋር ባሳለፉት የመጨረሻ ምሽትም “ከመካከላችን ታላቅ የሆነው ማን ነው?” በሚለው ጉዳይ ላይ ተከራክረው ነበር። (ሉቃስ 22:24-27፤ ማር. 9:33, 34) በሌላ ጊዜ ደግሞ ያዕቆብና ዮሐንስ፣ ኢየሱስ በመንግሥቱ ሲመጣ የተሻለውን ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀውታል።—ማር. 10:35-40፤ w18.06 8 አን. 1-2
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ኒሳን 16፦ ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች) ማርቆስ 16:2-8
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 11
ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል። ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።—ዘፍ. 2:24
ይሖዋ ባለትዳሮች ዕድሜ ልካቸውን የሚዘልቅ ጠንካራ ፍቅር እንዲያዳብሩ ይፈልጋል። (ማቴ. 19:3-6) ምንዝር አንድ ሰው ሊፈጽም ከሚችላቸው እጅግ አስከፊ የሆኑና ፍቅር የጎደላቸው ድርጊቶች መካከል አንዱ ነው። በእርግጥም ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል ሰባተኛው “አታመንዝር” የሚል መሆኑ ተገቢ ነው። (ዘዳ. 5:18) ምንዝር “በአምላክ ላይ” የሚፈጸም ኃጢአትና በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸም የጭካኔ ድርጊት ነው። (ዘፍ. 39:7-9) ምንዝር የተፈጸመበት ግለሰብ በሚወደው ሰው በመከዳቱ ምክንያት ከባድ የስሜት ቁስል የሚደርስበት ሲሆን ይህ ቁስል ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ላይሽር ይችላል። በተጨማሪም ይሖዋ ለልጆች ደህንነት ከልብ ያስባል። ይሖዋ ወላጆች የልጆቻቸውን ቁሳዊ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ፍላጎት ጭምር እንዲያሟሉ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። ወላጆች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመው ልጆቻቸው የይሖዋን ሕግ እንዲያውቁና ከፍ አድርገው እንዲመለከቱ እንዲሁም ይሖዋን እንዲወዱ ማስተማር ነበረባቸው። (ዘዳ. 6:6-9፤ 7:13) ወላጆች ልጆቻቸውን ሊመለከቷቸው የሚገባው ችላ ሊሉት ወይም የፈለጉትን ነገር ሊያደርጉበት እንደሚችሉት ንብረት አድርገው ሳይሆን በጥንቃቄ ሊይዙት እንደሚገባ ከይሖዋ የተገኘ ውርሻ አድርገው ነው።—መዝ. 127:3፤ w19.02 21 አን. 5, 7
እሁድ፣ ሚያዝያ 12
አምላክ . . . ንጹሕ አቋም እንዳለኝ ይገነዘባል።—ኢዮብ 31:6
ኢዮብ፣ አምላክ በሚከፍለው ወሮታ ላይ ትኩረት ማድረጉ ንጹሕ አቋሙን እንዲጠብቅ ረድቶታል። ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ለመጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት አምላክ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እምነት ነበረው። ከባድ ፈተና ቢደርስበትም ይሖዋ በመጨረሻ ወሮታውን እንደሚከፍለው እርግጠኛ ነበር። በአምላክ ላይ ያለው ይህ ትምክህት ንጹሕ አቋሙን ለመጠበቅ እንደረዳው ምንም ጥርጥር የለውም። ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቁ ይሖዋ በጣም ተደስቷል፤ በመሆኑም ጉድለቶች እያሉበትም እንኳ የተትረፈረፈ በረከት አፍስሶለታል! (ኢዮብ 42:12-17፤ ያዕ. 5:11) ወደፊት ደግሞ ከዚህ እጅግ የላቀ ሽልማት ይጠብቀዋል። አምላካችን አልተለወጠም። (ሚል. 3:6) ይሖዋ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት የምናስታውስ ከሆነ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ያለን ተስፋ ምንጊዜም ብሩሕ ሆኖ ይታየናል። (1 ተሰ. 5:8, 9) አንዳንድ ጊዜ በታማኝነት ጎዳና ላይ ብቻህን እየተጓዝክ እንዳለህ ሊሰማህ ይችላል፤ ሆኖም ፈጽሞ ብቻህን አይደለህም። በዓለም ዙሪያ በታማኝነት ንጹሕ አቋማቸውን እየጠበቁ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች አሉ። በጥንት ዘመንም ቢሆን ሞትን መጋፈጥ ቢጠይቅባቸው እንኳ ንጹሕ አቋማቸውን የጠበቁ በርካታ የእምነት ሰዎች ነበሩ። ንጹሕ አቋምህን መጠበቅህ ከእነሱ እንደ አንዱ ለመቆጠር ያስችልሃል።—ዕብ. 11:36-38፤ 12:1፤ w19.02 7 አን. 15-16
ሰኞ፣ ሚያዝያ 13
የአስተሳሰብ አንድነት ይኑራችሁ፤ የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ፤ የወንድማማች መዋደድ ይኑራችሁ፤ ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ ትሑታን ሁኑ።—1 ጴጥ. 3:8
የጌታ ራትን የምናከብርበት ወቅት ካለፈ በኋላም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው፦ ‘ፍቅር በማሳየት ረገድ ኢየሱስን ይበልጥ መምሰል የምችለው እንዴት ነው? ከራሴ ፍላጎት ይልቅ ለእምነት ባልንጀሮቼ ፍላጎት ቅድሚያ እሰጣለሁ? ወንድሞቼና እህቶቼ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር እንዲያደርጉ እጠብቃለሁ ወይስ የአቅም ገደብ እንዳለባቸው እገነዘባለሁ?’ ምንጊዜም ኢየሱስን ለመምሰልና “የሌላውን ስሜት [ለመረዳት]” ጥረት እናድርግ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ክርስቲያኖች የጌታ ራትን እንዲያከብሩ የተሰጣቸውን ትእዛዝ መጠበቅ አያስፈልጋቸውም። ኢየሱስ በታላቁ መከራ ወቅት ‘ሲመጣ’ ምድር ላይ የቀሩትን “የተመረጡ” ቅቡዓን ወደ ሰማይ ይሰበስባል፤ ከዚያ በኋላ የመታሰቢያውን በዓል ማክበር እናቆማለን። (1 ቆሮ. 11:26፤ ማቴ. 24:31) የመታሰቢያው በዓል በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከሁሉ የላቀ ትሕትና፣ ድፍረትና ፍቅር የታየበት ዝግጅት ነው፤ የይሖዋ ሕዝቦች የመታሰቢያው በዓል መከበሩን ካቆመ በኋላም እንኳ ይህን ቀለል ያለ ዝግጅት በደስታ እንደሚያስታውሱት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። w19.01 25 አን. 17-19
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 14
ከልብ የመነጨ እውነት ደስ ያሰኝሃል፤ ልቤን እውነተኛ ጥበብ አስተምረው።—መዝ. 51:6
ውስጣዊ ማንነታችንን መጠበቅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለመረዳት አካላዊ ጤንነታችንን እንደ ምሳሌ አድርገን መውሰድ እንችላለን። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሰውነታችን ጤናማ እንዲሆን ከፈለግን የተመጣጠነ ምግብ መመገብና አዘውትረን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርብናል። በተመሳሳይም መንፈሳዊ ጤንነታችንን መጠበቅ ከፈለግን የተመጣጠነ መንፈሳዊ ምግብ መመገብና በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት አዘውትረን በተግባር ማሳየት ይኖርብናል። እምነታችንን በተግባር ማሳየት፣ የተማርናቸውን ነገሮች ተግባራዊ ማድረግንና ስለምናምንባቸው ነገሮች ለሌሎች መናገርን ይጨምራል። (ሮም 10:8-10፤ ያዕ. 2:26) በሁለተኛ ደረጃ፣ ውስጣችን በበሽታ ቢጠቃም ከውጫዊ ገጽታችን በመነሳት ጤናማ የሆንን ሊመስለን ይችላል። በተመሳሳይም በውስጣችን የተሳሳተ ምኞት እያቆጠቆጠ ቢሆንም በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ስለምንካፈል ብቻ ጠንካራ እምነት ያለን ሊመስለን ይችላል። (1 ቆሮ. 10:12፤ ያዕ. 1:14, 15) ሰይጣን በእሱ አስተሳሰብ ሊበክለን እንደሚሞክር መዘንጋት አይኖርብንም። w19.01 15 አን. 4-5
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 15
አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ።—ሉቃስ 10:37
እንደሚከተለው ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘እኔስ እንደ ደጉ ሳምራዊ ርኅራኄ አሳያለሁ?’ (ሉቃስ 10:30-35) ‘ችግር ለደረሰባቸው ሰዎች ምሕረት በማሳየትና በደግነት እነሱን በመርዳት ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እችል ይሆን? ለምሳሌ፣ በዕድሜ ለገፉ ክርስቲያኖች፣ ለመበለቶች እንዲሁም በመንፈሳዊ ሁኔታ ወላጅ አልባ ለሆኑ ልጆች የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ መስጠት እችላለሁ? “የተጨነቁትን ለማጽናናት” ቅድሚያውን ወስጄ ጥረት አደርጋለሁ?’ (1 ተሰ. 5:14፤ ያዕ. 1:27) ለሌሎች ምሕረት ስናሳይ፣ መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ እናጣጥማለን። በተጨማሪም ይሖዋን እያስደሰትን እንደሆነ ስለምናውቅ ደስተኞች እንሆናለን። (ሥራ 20:35፤ ዕብ. 13:16) ንጉሥ ዳዊት፣ ለሌሎች አሳቢነት የሚያሳይን ሰው በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ይጠብቀዋል፤ በሕይወትም ያኖረዋል። በምድር ላይ ደስተኛ ይባላል።” (መዝ. 41:1, 2) ምሕረትና ርኅራኄ የምናሳይ ከሆነ ይሖዋም ምሕረት ያሳየናል፤ ይህ ደግሞ ለዘላለም ደስተኞች ለመሆን ያስችለናል።—ያዕ. 2:13፤ w18.09 19 አን. 11-12
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 16
እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ። እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ።—ኢሳ. 41:10
ዮሺኮ የተባለች አንዲት ታማኝ እህት አሳዛኝ ነገር ተነገራት። ዮሺኮ በጥቂት ወራት ውስጥ እንደምትሞት ሐኪሟ ገለጸችላት። በዚህ ወቅት ምን ተሰማት? በጣም የምትወደው አንድ ጥቅስ ትዝ አላት፤ ጥቅሱ የዛሬው የዕለት ጥቅስ ነው። ከዚያም ለሐኪሟ ይሖዋ እጇን እንደያዛት ስለሚሰማት ምንም እንደማትፈራ ነገረቻት። በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው የሚያጽናና መልእክት እህታችን በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ እንድትታመን ረድቷታል። ይህ ጥቅስ እኛም ከባድ ፈተና በሚያጋጥመን ወቅት መረጋጋት እንድንችል ይረዳናል። ይሖዋ በኢሳይያስ አማካኝነት እነዚህን ቃላት ያጻፈው፣ ከጊዜ በኋላ በግዞት ወደ ባቢሎን የሚወሰዱትን አይሁዳውያን ለማጽናናት ነበር። ሆኖም ይሖዋ አይሁዳውያን ግዞተኞች ብቻ ሳይሆኑ ከዚያ በኋላ የሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦቹም እንዲጠቀሙበት ሲል ይህ መልእክት እስከ ዘመናችን ድረስ እንዲቆይ አድርጓል። (ኢሳ. 40:8፤ ሮም 15:4) ዛሬ የምንኖረው “ለመቋቋም [በሚያስቸግር] በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ እንደመሆኑ መጠን በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ማበረታቻ ከምንጊዜውም ይበልጥ ያስፈልገናል።—2 ጢሞ. 3:1፤ w19.01 2 አን. 1-2
ዓርብ፣ ሚያዝያ 17
አማኝ ያልሆነው ወገን ለመለየት ከመረጠ ይለይ።—1 ቆሮ. 7:15
አንድ ባልና ሚስት እንዲህ ባለ ምክንያት ቢለያዩም ይህ ትዳራቸውን አያፈርሰውም፤ እንዲሁም ተለያይተው ቢኖሩም ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ባለትዳሮች አብረው መኖራቸውን እንዲቀጥሉ የሚያነሳሳ ምክንያት ጠቅሷል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አማኝ ያልሆነ ባል ከሚስቱ ጋር ባለው ዝምድና የተነሳ ተቀድሷል . . . አማኝ ያልሆነች ሚስትም ከወንድም ጋር ባላት ዝምድና የተነሳ ተቀድሳለች፤ እንዲህ ባይሆን ኖሮ ልጆቻችሁ ርኩሳን በሆኑ ነበር፤ አሁን ግን ቅዱሳን ናቸው።” (1 ቆሮ. 7:14) የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላቸው በርካታ ታማኝ ክርስቲያኖች በጣም ተፈታታኝ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ላለመለያየት ወስነዋል። ከእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ፣ ባሳዩት ጽናት የተነሳ የትዳር ጓደኛቸው የኋላ ኋላ ይሖዋን ማምለክ እንደጀመረ ተመልክተዋል፤ ይህም ባደረጉት ውሳኔ ይበልጥ ደስተኞች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። (1 ቆሮ. 7:16፤ 1 ጴጥ. 3:1, 2) በዓለም ዙሪያ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ ስኬታማ ትዳር ያላቸው በርካታ ክርስቲያኖች አሉ። በጉባኤያችሁ ውስጥም እንዲህ ያሉ ባለትዳሮች እንደሚኖሩ ግልጽ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው ባሎች ታማኞችና ሚስቶቻቸውን የሚወዱ ስለሆኑ ሚስቶችም አፍቃሪና ባሎቻቸውን የሚያከብሩ ስለሆኑ ነው። እነዚህ ጥንዶች ለጋብቻ ዝግጅት አክብሮት ማሳየት እንደሚቻል ያረጋግጣሉ።—ዕብ. 13:4፤ w18.12 14 አን. 18-19
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 18
ይሖዋ አምላክ . . . በኤደን የአትክልት ስፍራ ተከለ፤ የሠራውንም ሰው በዚያ አስቀመጠው።—ዘፍ. 2:8
ኤደን የሚለው ቃል “ደስታ” የሚል ትርጉም አለው፤ በእርግጥም ያ የአትክልት ስፍራ በጣም አስደሳች ነበር። የተትረፈረፈ ምግብና ውብ መልክዓ ምድር ያለው ሲሆን ሰዎች ከእንስሳት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ነበራቸው። (ዘፍ. 1:29-31) “የአትክልት ስፍራ” ተብሎ ለተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል አቻ ሆኖ የገባው የግሪክኛ ቃል ፓራዲሶስ የሚለው ነው። በማክሊንቶክና ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ የግሪክኛውን ፓራዲሶስ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “አንድ ግሪካዊ ተጓዥ ይህን ቃል ሲሰማ በአእምሮው ውስጥ የሚስለው እንደሚከተለው ያለውን ቦታ ነበር፦ ጉዳት እንዳይደርስበት የታጠረ ሰፊና የተንጣለለ መናፈሻ፣ ምንም ያልተነካ የተፈጥሮ ውበት ያለው፣ ግርማ ሞገስ የተላበሱና ፍሬያማ የሆኑ ዛፎች የሞሉበት፣ ኩልል ያሉ ወንዞች የሚያጠጡት እንዲሁም በወንዞቹ ዳርቻ የድኩላ ወይም የበግ መንጋ የተሰማራበት ስፍራ።” (ከዘፍጥረት 2:15, 16 ጋር አወዳድር።) አምላክ አዳምና ሔዋንን እንዲህ ባለ ገነት ውስጥ እንዲኖሩ አድርጓቸው ነበር፤ ሆኖም የአምላክን ትእዛዝ በመጣስ በዚያ ለመኖር የሚያስችላቸውን ብቃት አጓደሉ። በመሆኑም እነሱም ሆኑ ዘሮቻቸው በገነት ውስጥ የመኖር መብታቸውን አጡ። (ዘፍ. 3:23, 24) የአትክልት ስፍራው ከዚያ በኋላ ማንም ሰው ባይኖርበትም እስከ ኖኅ የጥፋት ውኃ ድረስ የቆየ ይመስላል። w18.12 3-4 አን. 3-5
እሁድ፣ ሚያዝያ 19
የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ . . . እኔ ይሖዋ [ነኝ]።—ኢሳ. 48:17
ወላጆች በልጆቻቸው ውስጥ መልካም እሴቶችን ለመቅረጽ ጥረት ያደርጋሉ። ልጆቹ ወላጆቻቸው ባስተማሯቸው እሴቶች ለመመራት ከመረጡ በአብዛኛው የኋላ ኋላ የማይቆጩባቸውን ውሳኔዎች ያደርጋሉ። በመሆኑም በራሳቸው ላይ አላስፈላጊ ችግርና ጭንቀት ከማምጣት ይድናሉ። ይሖዋም ልክ እንደ አንድ ጥሩ ወላጅ፣ ልጆቹ ከሁሉ የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ ይፈልጋል። (ኢሳ. 48:18) ስለዚህ ከሥነ ምግባርና ከሌሎች ጋር ካለን ግንኙነት ጋር በተያያዘ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሰጥቶናል። እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ረገድ የእሱን አመለካከት እንድናዳብርና በዚያ መሠረት እንድንኖር ግብዣ አቅርቦልናል። ይህ መፈናፈኛ የሚያሳጣ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የማሰብ ችሎታችን እንዲሰፋ፣ እንዲዳብርና የላቀ እንዲሆን ያደርጋል። (መዝ. 92:5፤ ምሳሌ 2:1-5፤ ኢሳ. 55:9) በግለሰብ ደረጃ ማንነታችንን ሳናጣ ደስተኛ ሕይወት ለመምራት የሚያስችሉ ምርጫዎችን እንድናደርግ ይረዳናል። (መዝ. 1:2, 3) በእርግጥም በይሖዋ አስተሳሰብ መመራት ጠቃሚና አስደሳች ነው! w18.11 19-20 አን. 7-8
ሰኞ፣ ሚያዝያ 20
ይሰድቧችኋል።—1 ጴጥ. 4:4
በእውነት ውስጥ መመላለሳችንን ለመቀጠል ሌሎች በሚያሳድሩብን ተጽዕኖ እንዳንሸነፍ መጠንቀቅ ይኖርብናል። በእውነት ጎዳና መጓዝ ስንጀምር የይሖዋ ምሥክር ካልሆኑ ጓደኞቻችንና የቤተሰባችን አባላት ጋር ያለን ግንኙነት ተቀይሯል። አንዳንዶቹ ለምናምንባቸው ነገሮች አክብሮት ቢያሳዩም ሌሎቹ ግን ተቃዋሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ። የቤተሰባችን አባላት፣ የሥራ ባልደረቦቻችንና አብረውን የሚማሩ ልጆች በሚያከብሯቸው በዓላት ላይ እንድንካፈል ተጽዕኖ ያደርጉብን ይሆናል። ይሖዋን በማያስከብሩ ባሕሎችና በዓላት ላይ እንድንካፈል የሚደርስብንን ተጽዕኖ መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ እንዲህ ላሉት ልማዶች ያለውን አመለካከት ማስታወሳችን ይረዳናል። ታዋቂ የሆኑ ክብረ በዓላትን አመጣጥ አስመልክቶ በጽሑፎቻችን ላይ የወጡ ሐሳቦችን መከለስ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በእነዚህ በዓላት ላይ የማንካፈልባቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች ማስታወሳችን “በጌታ ዘንድ ተቀባይነት” ባለው መንገድ እየተጓዝን እንዳለ እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል። (ኤፌ. 5:10) በይሖዋና እውነት በሆነው ቃሉ ላይ እምነት ማሳደራችን ‘ሰውን በመፍራት ወጥመድ’ እንዳንያዝ ይጠብቀናል።—ምሳሌ 29:25፤ w18.11 11 አን. 10, 12
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 21
ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር ስለነበር . . . የሚያደርገውን ነገር ሁሉ [ያሳካለት ነበር]።—ዘፍ. 39:23
ድንገተኛ ለውጥ ሲያጋጥመን፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚሰማን ጭንቀት በቀላሉ ሊያሽመደምደን ይችላል። ዮሴፍ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊያጋጥመው ይችል ነበር። እሱ ግን ባለበት ሁኔታ ሥር አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ያደረገ ሲሆን ይህም የይሖዋን በረከት አስገኝቶለታል። ዮሴፍ በጶጢፋር ቤት ውስጥ ያደርግ እንደነበረው ሁሉ እስር ቤት ውስጥ ሳለም የእስር ቤቱ አለቃ ያዘዘውን ማንኛውንም ሥራ በትጋት ያከናውን ነበር። (ዘፍ. 39:21, 22) እኛም እንደ ዮሴፍ ከቁጥጥራችን ውጭ የሆኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙን ይሆናል። በዚህ ጊዜ ታጋሾች ለመሆንና ባለንበት ሁኔታ ሥር አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ጥረት እናድርግ፤ ይህም የይሖዋን በረከት ያስገኝልናል። (መዝ. 37:5) እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ‘ግራ እንጋባ’ ይሆናል፤ ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ፈጽሞ “ተስፋ አንቆርጥም።” (2 ቆሮ. 4:8 ግርጌ) በተለይ በአገልግሎታችን ላይ ትኩረት የምናደርግ ከሆነ ጳውሎስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት በእኛ ላይ ሲፈጸሙ ማየት እንችላለን። w18.10 29 አን. 11, 13
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 22
አምላክ . . . የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።—ዕብ. 6:10
አንድ የምታውቁትና የምታከብሩት ሰው ስማችሁን ቢረሳው፣ ይባስ ብሎ ደግሞ ማን እንደሆናችሁ እንኳ ቢዘነጋ ምን ይሰማችኋል? እንዲህ ያለው ሁኔታ በጣም ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል። ለምን? ምክንያቱም ሁላችንም በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ተፈጥሯዊ ፍላጎት አለን። ሰዎች እንዲሁ በስም እንዲያውቁን ብቻ ሳይሆን ለማንነታችንና ላከናወንናቸው ነገሮች እውቅና እንዲሰጡን ጭምር እንፈልጋለን። (ዘኁ. 11:16፤ ኢዮብ 31:6) እንደ ሌሎች ተፈጥሯዊ ፍላጎቶቻችን ሁሉ በሌሎች ዘንድ ለመታወቅ ያለን ፍላጎትም በአለፍጽምናችን ምክንያት ሊዛባና ሚዛኑን ሊስት ይችላል። በመሆኑም ሰዎች ተገቢ ያልሆነ እውቅና እንዲሰጡን መፈለግ ልንጀምር እንችላለን። የሰይጣን ዓለም ዝነኛ የመሆንና በሌሎች ዘንድ እውቅና የማግኘት ፍላጎት በውስጣችን እንዲቀጣጠል ያደርጋል፤ ይህም በእርግጥ እውቅና ሊሰጠውና ሊመለክ ለሚገባው አካል ማለትም በሰማይ ላለው አባታችን ለይሖዋ አምላክ ትኩረት እንዳንሰጥ እንቅፋት ይሆንብናል።—ራእይ 4:11፤ w18.07 7 አን. 1-2
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 23
መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው።—1 ዮሐ. 5:19
ሰይጣንና አጋንንቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ሰዎች ‘ውሸት እንዲናገሩ’ ተጽዕኖ የሚያሳድሩባቸው መሆኑ የሚያስገርም አይደለም። (1 ጢሞ. 4:1, 2) የሐሰት ትምህርቶችን የሚያስተምሩ የሃይማኖት መሪዎች ከሁሉ ይበልጥ ተጠያቂ ናቸው፤ ምክንያቱም እነሱ የሚያስተምሩትን ውሸት የሚያምኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ተስፋቸው አደጋ ላይ ይወድቃል። አንድ ሰው በሐሰት ትምህርቶች ተታሎ አምላክ የሚጠላውን ነገር ቢያደርግ የዘላለም ሕይወት ተስፋውን ሊያጣ ይችላል። (ሆሴዕ 4:9) ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች በዚህ ረገድ ተጠያቂዎች እንደሆኑ ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ፊት ለፊት እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ አንድን ሰው ወደ ይሁዲነት ለመለወጥ በባሕርና በየብስ ስለምትጓዙና ሰውየው በተለወጠ ጊዜ ከእናንተ ይባስ ሁለት እጥፍ ለገሃነም [ለዘላለማዊ ጥፋት] የተገባ እንዲሆን ስለምታደርጉት ወዮላችሁ!” (ማቴ. 23:15) ኢየሱስ ጠንከር ያሉ ቃላትን ተጠቅሞ እነዚህን የሃይማኖት መሪዎች አውግዟቸዋል። በእርግጥም እነዚህ ሰዎች “ነፍሰ ገዳይ” ከሆነው ‘ከአባታቸው ከዲያብሎስ ናቸው።’—ዮሐ. 8:44፤ w18.10 7 አን. 5-6
ዓርብ፣ ሚያዝያ 24
በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ [እንዲሁም] ስደት ሲያደርሱባችሁ . . . ደስተኞች ናችሁ።—ማቴ. 5:11
ኢየሱስ እንዲህ ያለው ለምን ነበር? “በሰማያት የሚጠብቃችሁ ሽልማት ታላቅ ስለሆነ ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ ስደት አድርሰውባቸው ነበርና” በማለት መልሱን ሰጥቷል። (ማቴ. 5:12) ሐዋርያት የተገረፉና መስበካቸውን እንዲያቆሙ የታዘዙ ቢሆንም ከሳንሄድሪን ሸንጎ የወጡት “ደስ እያላቸው” ነበር። እርግጥ ነው፣ ሐዋርያትን ያስደሰታቸው ግርፋቱ አይደለም። የተደሰቱት “ስለ [ኢየሱስ ስም] ውርደት ለመቀበል ብቁ ሆነው በመቆጠራቸው” ነው። (ሥራ 5:41) በዛሬው ጊዜ ያለን የይሖዋ አገልጋዮችም ስለ ኢየሱስ ስም ውርደት ሲደርስብን ወይም ሌሎች ፈተናዎች ሲያጋጥሙን በደስታ እንጸናለን። (ያዕ. 1:2-4) እንደ ሐዋርያቱ ሁሉ እኛም የሚያስደስተን መከራ መቀበላችን አይደለም። ሆኖም ፈተና ሲያጋጥመን ታማኝነታችንን ከጠበቅን ይሖዋ እንድንጸና እንዲሁም ደስታችንን እንዳናጣ ይረዳናል። ‘ደስተኛ አምላክ’ የሆነውን የይሖዋን ሞገስ እንዳገኘን ማወቃችን፣ ስደት ወይም የቤተሰብ ተቃውሞ ቢያጋጥመን አሊያም ብንታመም ወይም ዕድሜያችን ቢገፋም ደስተኛ ለመሆን ይረዳናል።—1 ጢሞ. 1:11፤ w18.09 21 አን. 18-20
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 25
ይህም በችግርና በሐዘን የተሞላ ነው።—መዝ. 90:10
“ለመቋቋም የሚያስቸግር” በተባለው በዚህ ዘመን የሚኖሩ ብዙ ሰዎች በጭንቀት ይዋጣሉ፤ በርካቶች ሕይወት ተስፋ አስቆራጭ ስለሆነባቸው ቢሞቱ እንደሚሻል ይሰማቸዋል። (2 ጢሞ. 3:1-5) በየዓመቱ ከ800,000 በላይ ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት እንደሚያጠፉ አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ፤ ይህም በየ40 ሴኮንዱ አንድ ሰው ሕይወቱን ያጠፋል ማለት ነው። የሚያሳዝነው አንዳንድ ክርስቲያኖችም እንኳ የሚሰማቸውን ጭንቀት መቋቋም ስላቃታቸው ሕይወታቸውን አጥፍተዋል። እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተስፋ ቆርጠው ‘ሕይወት በቅቶኛል’ እስከማለት አይደርሱ ይሆናል፤ ይሁንና በርካታ አስጨናቂ ሁኔታዎች ስለሚያጋጥሟቸው ፍቅር በማሳየት ልናንጻቸው ይገባል። አንዳንዶች ስደትና ፌዝ ይደርስባቸዋል። ሌሎች በሥራ ቦታቸው የሚሰነዘርባቸው ነቀፋ እንዲሁም የሥራ ባልደረቦቻቸው ሐሜት ስሜታቸውን ይጎዳዋል። አሊያም ደግሞ ተጨማሪ ሰዓት መሥራታቸው ወይም ከአቅማቸው በላይ እንዲሠሩ የሚጠበቅባቸው መሆኑ ውጥረት ይፈጥርባቸዋል። አንዳንዶች መንፈሳቸውን የሚደቁስ የቤተሰብ ችግር ያጋጥማቸዋል፤ ለምሳሌ የማያምን የትዳር ጓደኛቸው ነጋ ጠባ ይተቻቸው ይሆናል። በጉባኤያችን ያሉ በርካታ ክርስቲያኖች እንደነዚህ ያሉ ችግሮች ስለሚደራረቡባቸው ይዝላሉ። w18.09 13 አን. 3, 5
እሁድ፣ ሚያዝያ 26
ልጆቼ በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የበለጠ ደስታ የለኝም።—3 ዮሐ. 4
ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጆቻቸው መንፈሳዊ ግቦችን እንዲያወጡ በመርዳት ከይሖዋ ጋር ተባብረው መሥራት ይችላሉ። በርካታ ወላጆች እንዲህ አድርገዋል፤ በመሆኑም ልጆቻቸው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል የወሰኑ ሲሆን አንዳንዶቹ ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች እንኳ ሄደው ለማገልገል ፈቃደኞች ሆነዋል። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ሚስዮናውያን ወይም ቤቴላውያን ሆነው ያገለግላሉ፤ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች በአቅኚነት የሚያገለግሉም አሉ። ልጆቹ ከቤት ርቀው ስለሚያገለግሉ የቤተሰቡ አባላት የሚፈልጉትን ያህል አዘውትረው መገናኘት አይችሉ ይሆናል። ያም ቢሆን የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉ ወላጆች፣ ልጆቻቸውን በተመደቡበት ቦታ በጽናት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ያበረታቷቸዋል። ለምን? ልጆቻቸው የአምላክን መንግሥት እያስቀደሙ መሆናቸው ታላቅ ደስታና እርካታ ስለሚያስገኝላቸው ነው። እንዲህ ያሉት ወላጆች፣ ሳሙኤልን ለይሖዋ ‘እንዳዋሰችው’ አድርጋ እንደተናገረችው እንደ ሐና ዓይነት ስሜት ይኖራቸው ይሆናል። ወላጆች በዚህ መንገድ ከይሖዋ ጋር አብረው መሥራታቸውን እንደ ታላቅ ክብር ይቆጥሩታል። ይህን መብታቸውን በምንም ነገር መለወጥ አይፈልጉም።—1 ሳሙ. 1:28 ግርጌ፤ w18.08 24 አን. 4
ሰኞ፣ ሚያዝያ 27
ሀብታም ሰው ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት እጅግ አስቸጋሪ ይሆንበታል።—ማቴ. 19:23
ኢየሱስ ሀብታም ሰው ጨርሶ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም እንዳላለ ልብ ማለት ያስፈልጋል። በተጨማሪም ኢየሱስ “እናንተ ድሆች የሆናችሁ ደስተኞች ናችሁ፤ የአምላክ መንግሥት የእናንተ ነውና” ብሏል። (ሉቃስ 6:20) ይህ ሲባል ግን ድሃ የሆኑ ሰዎች በሙሉ የተለየ በረከት አግኝተዋል ወይም የኢየሱስን ትምህርት ተቀብለዋል ማለት አይደለም። ድሃ የሆኑ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን አልተቀበሉትም። ነጥቡ ግልጽ ነው፦ የአንድን ሰው ቁሳዊ ንብረት በመመልከት ግለሰቡ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና መገምገም አንችልም። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሀብታም አሊያም ድሃ የሆኑ በርካታ ወንድሞችና እህቶች አሉ፤ ሁሉም ይሖዋን የሚወዱ ከመሆኑም ሌላ በሙሉ ልባቸው ያገለግሉታል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሀብታም የሆኑ ክርስቲያኖች “ተስፋቸውን አስተማማኝነት በሌለው ሀብት ላይ ሳይሆን . . . [በአምላክ] ላይ እንዲጥሉ” ይመክራል። (1 ጢሞ. 6:17-19) በሌላ በኩል ደግሞ የአምላክ ቃል፣ ሀብታም ድሃ ሳይል ሁሉም ክርስቲያኖች የገንዘብ ፍቅር እንዳይጠናወታቸው መጠንቀቅ እንዳለባቸው ያሳስባል። (1 ጢሞ. 6:9, 10) በእርግጥም ለወንድሞቻችን የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ካለን በኑሮ ደረጃቸው ላይ ተመሥርተን በእነሱ ላይ አንፈርድም። w18.08 10-11 አን. 11-12
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 28
ራሳችሁን ለአምላክ አስገዙ።—ያዕ. 4:7
ይሖዋ ሕዝቡ አድርጎ በመቁጠር ስላከበረን አመስጋኝነታችንን ማሳየት እንደምንፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። በፈቃደኝነት ራሳችንን በመወሰን የእሱ ንብረት መሆናችንን አምነን መቀበላችን የጥበብ አካሄድ እንደሆነ እንገነዘባለን። ክፋትን አጥብቀን እንቃወማለን። በተጨማሪም የእምነት ባልንጀሮቻችንም የይሖዋ ንብረት እንደሆኑ ስለምንገነዘብ ለእነሱ ፍቅርና አክብሮት እናሳያለን። (ሮም 12:10) መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ ሕዝቡን አይጥልም” በማለት ቃል ይገባልናል። (መዝ. 94:14) ይህ አስተማማኝ ዋስትና ነው፤ በማንኛውም ዓይነት መከራ ውስጥ ብንሆን ይሖዋ ከጎናችን ይሆናል። ሌላው ቀርቶ ሞትም እንኳ ይሖዋ ለእኛ ካለው ፍቅር ሊነጥለን አይችልም። (ሮም 8:38, 39) “ብንኖርም ሆነ ብንሞት የይሖዋ ነን።” (ሮም 14:8) በእርግጥም ይሖዋ በሞት ያንቀላፉትን ታማኝ ወዳጆቹን በሙሉ ዳግመኛ ሕያው የሚያደርግበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። (ማቴ. 22:32) በአሁኑ ጊዜም እንኳ የተትረፈረፉ በረከቶችን እያገኘን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ይሖዋ አምላኩ የሆነ ብሔር፣ የራሱ ንብረት አድርጎ የመረጠው ሕዝብ ደስተኛ ነው።”—መዝ. 33:12፤ w18.07 26 አን. 18-19
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 29
ሁሉም ነገር ተፈቅዷል፤ ሆኖም ሁሉም ነገር ይጠቅማል ማለት አይደለም። ሁሉም ነገር ተፈቅዷል፤ ሆኖም ሁሉም ነገር ያንጻል ማለት አይደለም።—1 ቆሮ. 10:23
አንዳንዶች እንደ ትምህርትና ሥራ ያሉት ጉዳዮች የግል ውሳኔ ከመሆናቸው አንጻር ሕሊናቸው እስካልወቀሳቸው ድረስ የፈለጉትን የማድረግ ነፃነት እንዳላቸው ይሰማቸዋል። ይህን የሚሉት ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሲጽፍ የተናገረውን “ነፃነቴ በሌላው ሰው ሕሊና ለምን ይፈረድበት?” የሚለውን ሐሳብ በአእምሯቸው ይዘው ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮ. 10:29) እንዲህ ባሉት ጉዳዮች ላይ የራሳችንን ምርጫ የማድረግ ነፃነት እንዳለን የታወቀ ነው፤ ሆኖም ነፃነታችን አንጻራዊ እንደሆነና የምናደርጋቸው ውሳኔዎች በሙሉ የሚያስከትሉት ውጤት እንዳለ ማስታወስ ይኖርብናል። ጳውሎስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ የጻፈው ለዚህ ነው። (1 ቆሮ. 10:23) ይህ ጥቅስ፣ በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ነፃነታችንን ከምንጠቀምበት መንገድ ጋር በተያያዘ ከግል ምርጫችን ይበልጥ ግምት ውስጥ ልናስገባቸው የሚገቡ አስፈላጊ ነገሮች መኖራቸውን እንድናስተውል ይረዳናል። w18.04 10 አን. 10
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 30
ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ።—ሚል. 3:7
በዛሬው ጊዜ ያለ አንድ ክርስቲያን ይሖዋን እንደሚያመልክ እየተናገረ የተሳሳተ አካሄድ ሊከተል ይችላል። (ይሁዳ 11) ለምሳሌ የብልግና ምኞቶችን ሊያውጠነጥን፣ የስግብግብነት ሐሳብ በውስጡ እንዲያቆጠቁጥ ሊፈቅድ አሊያም ለእምነት ባልንጀራው ጥላቻ ሊያዳብር ይችላል። (1 ዮሐ. 2:15-17፤ 3:15) እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የኃጢአት ድርጊት ወደመፈጸም ሊመራ ይችላል። አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ሐሳብ በውስጡ እያውጠነጠነም በአገልግሎት ንቁ ተሳትፎ ያደርግ እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ ይገኝ ይሆናል። ሌሎች ሰዎች አስተሳሰባችንንና ምግባራችንን መመልከት ባይችሉም ይሖዋ ግን ሁሉንም ነገር ማየት ስለሚችል በሙሉ ልብ ከእሱ ጎን መቆም አለመቆማችንን ማወቅ ይችላል። (ኤር. 17:9, 10) ያም ቢሆን ይሖዋ በእኛ ላይ ቶሎ ተስፋ አይቆርጥም። ከአምላክ የሚያርቀንን አካሄድ መከተል ስንጀምር ይሖዋ “ወደ እኔ ተመለሱ” በማለት አጥብቆ ያሳስበናል። ይሖዋ በተለይም ከድክመቶቻችን ጋር በምንታገልበት ወቅት ክፋትን አጥብቀን እንድንቃወም ይፈልጋል። (ኢሳ. 55:7) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ እሱም የኃጢአት ዝንባሌያችንን ‘እንድንቆጣጠር’ የሚያስችለንን መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና አካላዊ ጥንካሬ በመስጠት ከጎናችን እንደሆነ ያሳያል።—ዘፍ. 4:7፤ w18.07 18 አን. 5-6