የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es20 ገጽ 47-57
  • ግንቦት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ግንቦት
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2020
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ዓርብ፣ ግንቦት 1
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 2
  • እሁድ፣ ግንቦት 3
  • ሰኞ፣ ግንቦት 4
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 5
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 6
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 7
  • ዓርብ፣ ግንቦት 8
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 9
  • እሁድ፣ ግንቦት 10
  • ሰኞ፣ ግንቦት 11
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 12
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 13
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 14
  • ዓርብ፣ ግንቦት 15
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 16
  • እሁድ፣ ግንቦት 17
  • ሰኞ፣ ግንቦት 18
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 19
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 20
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 21
  • ዓርብ፣ ግንቦት 22
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 23
  • እሁድ፣ ግንቦት 24
  • ሰኞ፣ ግንቦት 25
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 26
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 27
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 28
  • ዓርብ፣ ግንቦት 29
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 30
  • እሁድ፣ ግንቦት 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2020
es20 ገጽ 47-57

ግንቦት

ዓርብ፣ ግንቦት 1

የባዕድ አገሩን ሰው ውደዱ።—ዘዳ. 10:19

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙዎች አገራቸውን ትተው በመሰደድ በሌሎች አገራት ውስጥ ለመኖር ተገድደዋል። ወደምትኖሩበት አካባቢ የመጡ የሌላ አገር ሰዎች በሚናገሩት ቋንቋ ሰላምታ የሚሰጥበትን መንገድ ለመማር ለምን አትሞክሩም? ከሰላምታ በተጨማሪ ከሰዎቹ ጋር ውይይት ለመጀመር የሚያስችሏችሁን አንዳንድ አገላለጾች መማርም ትችላላችሁ። ሰዎቹ ቆም ብለው ሲያናግሯችሁ jw.org የተባለውን ድረ ገጽ ልታስተዋውቋቸው እንዲሁም በቋንቋቸው የሚገኙ የተለያዩ ቪዲዮዎችንና ጽሑፎችን ልታሳዩአቸው ትችላላችሁ። አፍቃሪ የሆነው አባታችን ይሖዋ፣ በአገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን ለመርዳት ሲል የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባን አዘጋጅቶልናል። በዚህ ስብሰባ ላይ የምናገኘው ጠቃሚ ሥልጠና፣ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግና ጥናት ለመምራት ድፍረት እንዲኖረን ብዙዎቻችንን ረድቶናል። ወላጆች፣ ልጆቻችሁ በራሳቸው አባባል ሐሳብ እንዲሰጡ በማሠልጠን እነሱም ብርሃናቸውን እንዲያበሩ እርዷቸው። አንዳንድ አዳዲስ ሰዎች፣ ልጆች የሚሰጡትን ከልብ የመነጨ መልስ መስማታቸው ወደ እውነት እንዲሳቡ አድርጓቸዋል።—1 ቆሮ. 14:25፤ w18.06 22-23 አን. 7-9

ቅዳሜ፣ ግንቦት 2

ክርስቶስ እኛን እንደተቀበለን ሁሉ . . . እናንተም አንዳችሁ ሌላውን ተቀበሉ።—ሮም 15:7

በአንድ ወቅት ሁላችንም “ባዕዳን” ይኸውም ከአምላክ የራቅን እንደነበርን ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። (ኤፌ. 2:12) ይሖዋ ግን ‘በፍቅር ማሰሪያ’ ወደ ራሱ ስቦናል። (ሆሴዕ 11:4፤ ዮሐ. 6:44) ክርስቶስም ቢሆን የአምላክ ቤተሰብ አባላት መሆን የምንችልበትን አጋጣሚ በመክፈት ተቀብሎናል። ፍጽምና የሌለን ቢሆንም ኢየሱስ በደግነት ተቀብሎናል፤ ከዚህ አንጻር ሌሎችን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆን ጨርሶ ልናስበው የማይገባ ነገር ነው! ወደዚህ ክፉ ሥርዓት መጨረሻ እየተጠጋን ስንሄድ፣ ጭፍን አመለካከትና ጥላቻ ይበልጥ እየተስፋፉ እንደሚሄዱ ጥያቄ የለውም። (ገላ. 5:19-21፤ 2 ጢሞ. 3:13) እኛ ግን የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን፣ አድልዎ የሌለበትንና ሰላማዊ የሆነውን ሰማያዊ ጥበብ ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን። (ያዕ. 3:17, 18) ከሌሎች አገሮች ከመጡ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት፣ ባሕላቸውን ማክበር አልፎ ተርፎም ቋንቋቸውን መማር ያስደስተናል። ይህን ስናደርግ በጉባኤያችን ውስጥ ሰላም እንደ ወንዝ፣ ፍትሕ ደግሞ እንደ ባሕር ሞገድ ይሆናል።—ኢሳ. 48:17, 18፤ w18.06 12 አን. 18-19

እሁድ፣ ግንቦት 3

የሰላምን ምሥራች ለማወጅ ዝግጁ በመሆን እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ።—ኤፌ. 6:15

አንድ የሮም ወታደር ጫማውን ካላደረገ ወደ ጦር ሜዳ ለመዝመት ዝግጁ አይደለም። ወታደሩ የሚያደርገው ክፍት ጫማ የሚሠራው ሦስት የቆዳ ንጣፎችን በማነባበር ነው። የጫማው አሠራር ምቹና ጠንካራ እንዲሆን ያደርገዋል። የሮም ወታደሮች ይህን ጫማ የሚያደርጉት ለጦርነት ዝግጁ ለመሆን ነው፤ ክርስቲያኖች ግን ምሳሌያዊውን ጫማ ማድረጋቸው የሰላምን መልእክት ለማድረስ መዘጋጀታቸውን ያመለክታል። (ኢሳ. 52:7፤ ሮም 10:15) እርግጥ ነው፣ አጋጣሚውን በምናገኝበት ጊዜ ምሥራቹን መናገር ድፍረት ይጠይቃል። የ20 ዓመቱ ቦ እንዲህ ብሏል፦ “አብረውኝ ለሚማሩ ልጆች መስበክ ያስፈራኝ ነበር። የምፈራው ምሥራቹን መናገር ስለሚያሳፍረኝ ነበር። መለስ ብዬ ሳስበው ግን ምኑ እንዳሳፈረኝ አይገባኝም። አሁን ለእኩዮቼ መመሥከር ያስደስተኛል።” በርካታ ወጣቶች ምሥራቹን ለመናገር በሚገባ መዘጋጀታቸው መስበክ ይበልጥ ቀላል እንዲሆንላቸው እንደሚያደርግ ይናገራሉ። w18.05 29 አን. 9-11

ሰኞ፣ ግንቦት 4

ብዙ ፍሬ [አፍሩ]።—ዮሐ. 15:8

ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “ሰላሜን እሰጣችኋለሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐ. 14:27) የኢየሱስ ሰላም፣ ፍሬ ለማፍራት የሚረዳን እንዴት ነው? በስብከቱ ሥራ ስንጸና፣ ይሖዋ እና ኢየሱስ እንደሚደሰቱብን ማወቅ የሚያስገኘውን ውስጣዊ ሰላም ማጣጣም እንችላለን። (መዝ. 149:4፤ ሮም 5:3, 4፤ ቆላ. 3:15) ኢየሱስ የሐዋርያቱ “ደስታ የተሟላ እንዲሆን” ያለውን ምኞት ከገለጸ በኋላ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር የማሳየትን አስፈላጊነት ነግሯቸዋል። (ዮሐ. 15:11-13) ቀጥሎም “ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ” ብሏቸዋል። የኢየሱስ ወዳጅ መሆን እንዴት ያለ ትልቅ ስጦታ ነው! ይሁንና ሐዋርያቱ ከኢየሱስ ጋር ያላቸው ወዳጅነት እንዲቀጥል ምን ማድረግ ነበረባቸው? ‘ሄደው ፍሬ ማፍራታቸውን’ እንዲቀጥሉ ተነግሯቸዋል። (ዮሐ. 15:14-16) ኢየሱስ ይህን ከመናገሩ ከሁለት ዓመት በፊት ሐዋርያቱን “በምትሄዱበት ጊዜም ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል’ ብላችሁ ስበኩ” በማለት አዟቸው ነበር። (ማቴ. 10:7) ከመሞቱ በፊት ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት፣ በጀመሩት ሥራ እንዲጸኑ ያበረታታቸው ለዚህ ነው።—ማቴ. 24:13፤ ማር. 3:14፤ w18.05 20-21 አን. 15-16

ማክሰኞ፣ ግንቦት 5

አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።—ገላ. 6:7

ወጣቶች ሕይወታችሁ ይሖዋን በማስደሰትና በመንፈሳዊ ግቦች ላይ ያተኮረ እንዲሆን አድርጉ። ይሁንና እኩዮቻችሁ በመዝናናትና ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ያተኮረ ሕይወት ሲመሩ ትመለከቱ ይሆናል፤ ምናልባት እናንተም ከእነሱ ጋር ጊዜ እንድታሳልፉ ይጋብዟችሁ ይሆናል። ይዋል ይደር እንጂ፣ ግባችሁ ላይ ለመድረስ ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆናችሁ ማሳየት ይጠበቅባችኋል። በመሆኑም የእኩዮቻችሁ ተጽዕኖ ትኩረታችሁን እንዲከፋፍለው አትፍቀዱ። ወጣቶች የእኩዮቻቸውን ተጽዕኖ መቋቋም የሚችሉባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ትክክል ያልሆነውን ነገር ለማድረግ የምትፈተኑበት ሁኔታ ውስጥ ላለመግባት መጠንቀቅ ትችላላችሁ። (ምሳሌ 22:3) ሌሎችን ተከትላችሁ መጥፎ ምግባር መፈጸም የሚያስከትለውን መዘዝ አስቡ። በተጨማሪም የሌሎችን ምክር መስማት እንደሚያስፈልጋችሁ አምናችሁ ተቀበሉ። ትሕትና፣ ወላጆቻችሁም ሆኑ በጉባኤ ውስጥ ያሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖች የሚሰጧችሁን ምክር መቀበል ቀላል እንዲሆንላችሁ ያደርጋል። (1 ጴጥ. 5:5, 6) የሚሰጣችሁን ጥሩ ምክር በትሕትና ትቀበላላችሁ? w18.04 28-29 አን. 14-16

ረቡዕ፣ ግንቦት 6

እኔ እስክመጣ ድረስ ያላችሁን አጥብቃችሁ ያዙ። ደግሞም ድል ለሚነሳና በሥራዬ እስከ መጨረሻ ለሚጸና በብሔራት ላይ ሥልጣን እሰጠዋለሁ።—ራእይ 2:25, 26

ኢየሱስ በትንሿ እስያ ለነበሩ አንዳንድ ጉባኤዎች በላከው መልእክት ላይ ተከታዮቹ ላከናወኑት ሥራ ያለውን አድናቆት ገልጿል። ለምሳሌ ያህል፣ በትያጥሮን ላለው ጉባኤ የላከውን መልእክት የጀመረው በሚከተሉት ቃላት ነው፦ “ሥራህን፣ ፍቅርህን፣ እምነትህን፣ አገልግሎትህንና ጽናትህን አውቃለሁ፤ ደግሞም ከመጀመሪያው ሥራህ ይልቅ የአሁኑ እንደሚበልጥ አውቃለሁ።” (ራእይ 2:19) ኢየሱስ እነዚህ ክርስቲያኖች እንቅስቃሴያቸውን ከፍ እንዳደረጉ በመጥቀስ ብቻ አልተወሰነም፤ ከዚህ ይልቅ ለመልካም ሥራ እንዲነሳሱ ያደረጓቸውን ባሕርያት ጭምር ጠቅሶ አመስግኗቸዋል። ኢየሱስ በትያጥሮን ጉባኤ ላሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ምክር መስጠት ቢያስፈልገውም መልእክቱን የጀመረውም ሆነ የጨረሰው የሚያበረታቱ ሐሳቦችን በመናገር ነው። (ራእይ 2:27, 28) ኢየሱስ የጉባኤዎች ሁሉ ራስ እንደመሆኑ መጠን ምን ያህል ሥልጣን እንዳለው ለማሰብ ሞክር። ለእሱ ስንል ላከናወንናቸው ነገሮች እኛን የማመስገን ግዴታ የለበትም። ያም ቢሆን አድናቆቱን መግለጹ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶታል። ኢየሱስ በዚህ ረገድ ለጉባኤ ሽማግሌዎች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቷል! w19.02 16 አን. 10

ሐሙስ፣ ግንቦት 7

ይሁዳና ሲላስ . . . ብዙ ቃል በመናገር ወንድሞችን አበረታቷቸው፤ እንዲሁም አጠናከሯቸው።—ሥራ 15:32

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል፣ አመራር ለሚሰጡትም ሆነ ለሌሎች ክርስቲያኖች የብርታት ምንጭ እንደሆነ አሳይቷል። እነዚህ ወንድሞች፣ በቅርቡ ክርስቲያን የሆኑት አማኞች መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ይጸልዩላቸው ዘንድ ሁለቱን የበላይ አካል አባላት ማለትም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ልከዋል። (ሥራ 8:5, 14-17) ፊልጶስም ሆነ እሱ ወደ ክርስትና እንዲለወጡ የረዳቸው ሰዎች የበላይ አካሉ ባደረገላቸው በዚህ ድጋፍ ምንኛ ተበረታተው ይሆን! በዛሬው ጊዜ ያለው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካልም ለቤቴል ቤተሰብ አባላት፣ በመስኩ ላይ ለሚያገለግሉ ልዩ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ብሎም በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ለታቀፉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ማበረታቻ ይሰጣል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም በሚያገኙት ማበረታቻ እጅግ ይደሰታሉ! በተጨማሪም በ2015 የበላይ አካሉ ወደ ይሖዋ ተመለስ የሚል ርዕስ ያለውን ብሮሹር አውጥቷል፤ ይህ ብሮሹር በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በርካታ ሰዎች ከፍተኛ የብርታት ምንጭ ሆኗል። w18.04 19 አን. 18-20

ዓርብ፣ ግንቦት 8

እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል።—ዮሐ. 8:32

ብዙዎች የበለጠ ነፃነት ባገኙ መጠን ሕይወታቸውም ይበልጥ እንደሚሻሻል ይሰማቸዋል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ገደብ የሌለው ነፃነት በሁለት በኩል እንደተሳለ ሰይፍ ነው። ምንም ዓይነት ገደብ በሌለበት ዓለም ላይ ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል ማሰቡ እንኳ ይዘገንናል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ ‘በየትኛውም የተደራጀ ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉት ሕግጋት የተወሳሰቡ ናቸው፤ ምክንያቱም እነዚህ ሕግጋት የተዋቀሩት ሰዎች ከተቀመጠላቸው ገደብ ሳያልፉ ነፃነታቸውን መጠቀም እንዲችሉ ለማድረግ በሚያስችል መንገድ ነው።’ በእርግጥም ‘ሕግጋቱ የተወሳሰቡ ናቸው’ መባሉ የሚያስገርም አይደለም። የሰው ልጆች ያወጧቸውን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕግጋት ለዚህ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፤ በዚያ ላይ ደግሞ እነዚህን ሕግጋት ለመተርጎምና ለማስፈጸም እጅግ ብዙ የሕግ ባለሙያዎችና ዳኞች ያስፈልጋሉ። ኢየሱስ እውነተኛ ነፃነት ለማግኘት አስፈላጊ የሆኑ ሁለት ነገሮችን ጠቅሷል፦ የመጀመሪያው እሱ ያስተማረውን እውነት መቀበል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን ነው። እነዚህን ነገሮች ማድረግ እውነተኛ ነፃነት ያስገኛል። ይሁንና ነፃ የምንወጣው ከምንድን ነው? ኢየሱስ እንዲህ በማለት መልሱን ሰጥቶናል፦ “ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው። . . . ወልድ ነፃ ካወጣችሁ፣ በእርግጥ ነፃ ትሆናላችሁ።”—ዮሐ. 8:34, 36፤ w18.04 6-7 አን. 13-14

ቅዳሜ፣ ግንቦት 9

የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ።—1 ጴጥ. 3:8

ስለ እኛ ከሚያስቡና ለስሜታችን ከሚጨነቁ ሰዎች ጋር መሆን ያስደስተናል። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን በእኛ ቦታ በማስቀመጥ ምን እንደሚያሳስበን ወይም ምን እንደሚሰማን ለማስተዋል ይሞክራሉ። አንዳንድ ጊዜ ገና ሳንጠይቃቸው እንኳ ምን ሊያስፈልገን እንደሚችል ተገንዝበው እርዳታ ያደርጉልናል። በእርግጥም ‘ስሜታችንን የሚረዱልንን’ ሰዎች ከልብ እናደንቃለን። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም ርኅራኄ ማሳየት ወይም የሌላውን ስሜት መረዳት እንፈልጋለን። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እንዲህ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ለምን? አንዱ ምክንያት ፍጽምና የጎደለን መሆናችን ነው። (ሮም 3:23) በመሆኑም ስለ ራሳችን ብቻ እንድናስብ የሚገፋፋንን ውስጣዊ ዝንባሌ መዋጋት ይኖርብናል። በተጨማሪም አንዳንዶቻችን በአስተዳደጋችን ወይም ከዚህ በፊት ባጋጠመን ነገር ምክንያት ለሌሎች ርኅራኄ ማሳየት ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። ከዚህም በላይ በዙሪያችን ያሉት ሰዎች ዝንባሌ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል። በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ለሌሎች ስሜት ግድ የላቸውም። ከዚህ ይልቅ “ራሳቸውን የሚወዱ” ናቸው። (2 ጢሞ. 3:1, 2) ሆኖም ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ የተዉትን ምሳሌ የምንከተል ከሆነ የሌሎችን ስሜት በመረዳት ረገድ ይበልጥ እየተሻሻልን መሄድ እንችላለን። w19.03 14 አን. 1-3

እሁድ፣ ግንቦት 10

ልብህን ጠብቅ።—ምሳሌ 4:23

ከአሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ የመጨረሻው መጎምጀትን ወይም የሌላ ሰው የሆነን ነገር መመኘትን ይከለክላል። (ዘዳ. 5:21፤ ሮም 7:7) ይሖዋ ይህን ሕግ የሰጠው አንድ አስፈላጊ ትምህርት ለማስተላለፍ ይኸውም ሕዝቡ ልባቸውን ማለትም አስተሳሰባቸውን፣ ስሜታቸውንና የማመዛዘን ችሎታቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ለማስገንዘብ ነው። ይሖዋ ክፉ ድርጊት የሚመነጨው ከክፉ ሐሳብና ምኞት እንደሆነ ያውቃል። ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊት በዚህ ወጥመድ ውስጥ ወድቋል። በጥቅሉ ሲታይ ዳዊት ጥሩ ሰው ነበር። በአንድ ወቅት ግን የሌላ ሰው ሚስት አይቶ ተመኘ። ይህ ምኞት ደግሞ ኃጢአት ወደመፈጸም መራው። (ያዕ. 1:14, 15) ዳዊት ምንዝር ፈጽሟል፣ የሴትየዋን ባል ለማታለል ሞክሯል፣ ከዚያም ሰውየውን አስገድሎታል። (2 ሳሙ. 11:2-4፤ 12:7-11) ይሖዋ ከውጫዊ ገጽታችን ባሻገር ያለውን ነገር የማየት ችሎታ አለው። ልባችንን ማለትም ውስጣዊ ማንነታችንን ይመለከታል። (1 ሳሙ. 16:7) ከእሱ ሊደበቅ የሚችል ምንም ዓይነት ሐሳብ፣ ስሜት ወይም ድርጊት የለም። ይሖዋ በውስጣችን ያለውን መልካም ነገር ያያል፤ እንዲሁም ያን መልካም ነገር ማሳደግ እንድንችል ይረዳናል። ሆኖም በልባችን ውስጥ ያለ መጥፎ አስተሳሰብ አድጎ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ከመፈጸማችን በፊት ይህን አስተሳሰብ ለይተን እንድናውቀውና እንድንቆጣጠረው ይፈልጋል።—2 ዜና 16:9፤ ማቴ. 5:27-30፤ w19.02 21 አን. 9፤ 22 አን. 11

ሰኞ፣ ግንቦት 11

በምድር ላይ የምትኖሩ የዋሆች ሁሉ ይሖዋን ፈልጉ። . . . የዋህነትን ፈልጉ።—ሶፎ. 2:3

መጽሐፍ ቅዱስ “ሙሴ በምድር ላይ ከነበሩ ሰዎች ሁሉ ይልቅ በጣም የዋህ” እንደነበር ይገልጻል። (ዘኁ. 12:3) ይህ ሲባል ታዲያ ሙሴ ደካማ፣ ወላዋይና የሚያጋጥመውን ተቃውሞ ፊት ለፊት መጋፈጥ የሚፈራ ሰው ነበር ማለት ነው? አንዳንዶች የዋህ የሚለውን ቃል ሲሰሙ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው እንዲህ ዓይነት ሰው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህ ከእውነታው ፈጽሞ የራቀ ነው። ሙሴ ጠንካራ፣ ውሳኔ ማድረግ የማይፈራና ደፋር የአምላክ አገልጋይ ነበር። በይሖዋ እርዳታ፣ ኃያል ከሆነው የግብፅ ገዢ ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጧል፤ ሦስት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን በምድረ በዳ መርቷል፤ እንዲሁም እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን ድል እንዲያደርጉ ረድቷል። እርግጥ ነው፣ እኛ ሙሴን ያጋጠሙት ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች አያጋጥሙን ይሆናል፤ ሆኖም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን፣ የዋህ መሆን ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርጉ ሰዎች ወይም ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ይሁንና ይህን ባሕርይ እንድናዳብር የሚያነሳሳ አጥጋቢ ምክንያት አለን። ይሖዋ “የዋሆች . . . ምድርን ይወርሳሉ” በማለት ቃል ገብቷል። (መዝ. 37:11) የዋህ እንደሆንክ ይሰማሃል? ሌሎችስ ስለ አንተ እንደዚያ ይሰማቸዋል? w19.02 8 አን. 1-2

ማክሰኞ፣ ግንቦት 12

[መጥፎውን] ጥሩ የሚሉ . . . ወዮላቸው።—ኢሳ. 5:20

የሰው ልጆች ሕሊና አላቸው። የመጀመሪያዎቹ ሰዎች የሆኑት አዳምና ሔዋን ሕሊና ነበራቸው። የይሖዋን ትእዛዝ ከጣሱ በኋላ መደበቃቸው ይህን ያሳያል። እነዚህ ባልና ሚስት የተደበቁት ሕሊናቸው ስለወቀሳቸው ነው። ሕሊናቸው በሚገባ ያልሠለጠነ ሰዎች፣ የማይሠራ ኮምፓስ ካለው መርከብ ጋር ይመሳሰላሉ። ኮምፓሱ በትክክል በማይሠራ መርከብ መጓዝ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ነፋስና ሞገድ፣ መርከቡ በቀላሉ አቅጣጫውን እንዲስት ሊያደርጉት ይችላሉ። በሌላ በኩል ግን በትክክል የሚሠራ ኮምፓስ፣ የመርከቡ ነጂ መስመሩን ጠብቆ እንዲጓዝ ሊረዳው ይችላል። ሕሊናችን ከኮምፓስ ጋር ይመሳሰላል። ሕሊና፣ ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ለመለየት የሚረዳንና በትክክለኛው አቅጣጫ የሚመራን ችሎታ ነው። እርግጥ ነው፣ ሕሊናችን በትክክለኛው አቅጣጫ እንዲመራን መሠልጠን አለበት። ሕሊናችን በሚገባ ካልሠለጠነ መጥፎ ነገር እንዳንፈጽም ማስጠንቀቂያ አይሰጠንም። (1 ጢሞ. 4:1, 2) እንዲያውም እንዲህ ያለው ሕሊና ‘መጥፎውን ጥሩ’ አድርገን እንድናስብ ሊገፋፋን ይችላል። w18.06 16 አን. 1-3

ረቡዕ፣ ግንቦት 13

ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ።—ሮም 12:2

እምብዛም ግልጽ ባልሆነ መንገድ የሚመጡ ዓለማዊ አስተሳሰቦችን ማወቃችንና ከእነሱ መራቃችን አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ የዜና ሪፖርቶች አንድን ፖለቲካዊ አመለካከት በሚደግፍ መልኩ ሊቀርቡ ይችላሉ። በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚቀርቡ ዘገባዎች፣ ዓለም ግብን ወይም ስኬትን አስመልክቶ ያለውን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ ፊልሞችና መጻሕፍት “ከራስ በላይ ነፋስ” አሊያም “ቅድሚያ ለቤተሰብ” የሚሉትን ፍልስፍናዎች የሚያበረታቱ ሲሆን እነዚህን አስተሳሰቦች ምክንያታዊ፣ ማራኪ አልፎ ተርፎም ትክክል የሆኑ አስመስለው ያቀርባሉ። እንዲህ ያሉት አስተሳሰቦች እኛም ሆንን ቤተሰባችን እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምንችለው ይሖዋን ከማንም በላይ ስንወድ እንደሆነ ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር የሚቃረኑ ናቸው። (ማቴ. 22:36-39) ይህ ሲባል ግን ጤናማ በሆኑ መዝናኛዎች መካፈል ስህተት ነው ማለት አይደለም። ያም ቢሆን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘ስውር በሆነ መንገድ የሚመጡ ዓለማዊ ትምህርቶችን አስተውላለሁ? አንዳንድ ፕሮግራሞችን ላለመመልከት ወይም ጽሑፎችን ላለማንበብ በእኔም ሆነ በልጆቼ ላይ ገደብ አበጃለሁ? ልጆቼ ዓለማዊ ሐሳቦች በሚያሳድሩት ተጽዕኖ እንዳይሸነፉ የአምላክን አስተሳሰብ እንዲያዳብሩ እረዳቸዋለሁ?’ w18.11 22 አን. 18-19

ሐሙስ፣ ግንቦት 14

እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ።—ኢሳ. 41:10

ይሖዋ ለእኛ ሙሉ ትኩረቱን በመስጠትና ፍቅሩን በመግለጽ ከእኛ ጋር እንደሆነ ያሳያል። ለእኛ ያለውን ስሜት የገለጸው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር። “አንተ በዓይኔ ፊት ውድ ሆነሃልና፤ የተከበርክም ነህ፤ እኔም ወድጄሃለሁ” በማለት ተናግሯል። (ኢሳ. 43:4) ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ፍቅሩን እንዳያሳይ ሊያግድ የሚችል አንዳች ኃይል የለም፤ ለእኛ ያለው ታማኝነት ፈጽሞ አይናወጥም። (ኢሳ. 54:10) ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያስወግድልን ቃል አልገባም፤ ሆኖም የችግር ‘ወንዝ’ እንዲያሰምጠን ወይም የፈተና ‘ነበልባል’ ዘላቂ ጉዳት እንዲያደርስብን እንደማይፈቅድ ቃል ገብቶልናል። ከእኛ ጋር እንደሚሆንና እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ‘እንድናልፍ’ እንደሚረዳን ማረጋገጫ ሰጥቶናል። ሆኖም ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው? ይሖዋ ፍርሃታችንን እንድናሸንፍና እንድንረጋጋ ይረዳናል፤ ይህም ከሞት ጋር ፊት ለፊት በምንፋጠጥበት ጊዜም እንኳ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያስችለናል። (ኢሳ. 41:13፤ 43:2) አምላክ “እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ” በማለት በገባው ቃል ላይ እምነት ማሳደራችን የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በድፍረት እንድንጋፈጥ ይረዳናል። w19.01 3 አን. 4-6

ዓርብ፣ ግንቦት 15

ሰው በልቡ ብዙ ነገር ያቅዳል፤ የሚፈጸመው ግን የይሖዋ ፈቃድ ነው።—ምሳሌ 19:21

ወጣቶች ከሆናችሁ አስተማሪዎች፣ የትምህርት ቤት አማካሪዎች ወይም ሌሎች ሰዎች ከፍተኛ ትምህርት እንድትከታተሉ እንዲሁም ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ እንድትይዙ ሊያበረታቷችሁ ይችላሉ። ይሖዋ ግን ከዚህ የተለየ አካሄድ እንድትከተሉ ይመክራችኋል። እርግጥ ነው፣ ትምህርት ከጨረሳችሁ በኋላ ራሳችሁን ማስተዳደር እንድትችሉ ተማሪ ሳላችሁ ጠንክራችሁ እንድትሠሩ ይጠብቅባችኋል። (ቆላ. 3:23) ሆኖም በሕይወታችሁ ውስጥ ቅድሚያ የምትሰጧቸውን ነገሮች ስትወስኑ እሱ ባወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድትመሩ ይፈልጋል፤ እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች አምላክ በመጨረሻው ዘመን ለምንኖረው ለእኛ ያለውን ዓላማና ፈቃድ ግንዛቤ ውስጥ ያስገቡ ናቸው። (ማቴ. 24:14) ይሖዋ ያለንበት ዓለም ከፊት ለፊቱ ምን እንደሚጠብቀውና መጥፊያው ምን ያህል እንደቀረበ ያውቃል። (ኢሳ. 46:10፤ ማቴ. 24:3, 36) ስለ እኛም ቢሆን የተሟላ እውቀት አለው፤ እውነተኛ እርካታና ደስታ የሚሰጠን እንዲሁም ለሐዘንና ለብስጭት የሚዳርገን ምን እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል። በመሆኑም ሰዎች የሚሰጡት ምክር ምንም ያህል ምክንያታዊ ቢመስል በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እስካልሆነ ድረስ ምክሩ ጥበብ የተንጸባረቀበት ነው ሊባል አይችልም። w18.12 19 አን. 1-2

ቅዳሜ፣ ግንቦት 16

ክፉዎች አይኖሩም።—መዝ. 37:10

“የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።” በተጨማሪም ዳዊት በመንፈስ መሪነት “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” የሚል ትንቢት ተናግሯል። (መዝ. 37:11, 29፤ 2 ሳሙ. 23:2) እነዚህ ተስፋዎች የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ በሚፈልጉ ሰዎች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳደሩባቸው ይመስልሃል? የአምላክ አገልጋዮች፣ ጻድቃን ብቻ በምድር ላይ የሚኖሩ ከሆነ በኤደን የአትክልት ስፍራ የነበረው ዓይነት ገነት መልሶ ይቋቋማል ብለው ተስፋ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ምክንያት ነበራቸው። ሆኖም ይሖዋን እንደሚያገለግሉ ይናገሩ የነበሩት አብዛኞቹ እስራኤላውያን በጊዜ ሂደት ለይሖዋና ለእውነተኛው አምልኮ ጀርባቸውን መስጠት ጀመሩ። በመሆኑም አምላክ ባቢሎናውያን ሕዝቡን እንዲወሩ፣ ምድሪቷን እንዲያጠፉና ብዙዎቹን በግዞት እንዲወስዱ አደረገ። (2 ዜና 36:15-21፤ ኤር. 4:22-27) በዚያ ጊዜም እንኳ የአምላክ ነቢያት፣ ከ70 ዓመታት በኋላ ሕዝቡ ወደ ትውልድ አገሩ እንደሚመለስ ተንብየው ነበር። እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ሆኖም በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛም ትልቅ ትርጉም አላቸው፤ ምድር ገነት እንደምትሆን ማስረጃ ይሆናሉ። w18.12 4 አን. 9-10

እሁድ፣ ግንቦት 17

ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ መንገዴ ከመንገዳችሁ፣ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ ከፍ ያለ ነው።—ኢሳ. 55:9

ይህ ዓለም የሚሰጣቸው ምክሮች አብዛኛውን ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጋጫሉ። ይሁንና ከእነዚህ ምክሮች መካከል አንዳንዶቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይበልጥ ለዘመናችን ተስማሚ ናቸው ሊባል ይችላል? ኢየሱስ “ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 11:19) ዓለም በቴክኖሎጂ ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሰ ቢሆንም እንደ ጦርነት፣ ዘረኝነትና ወንጀል ያሉ ደስታ የሚያሳጡ ከባድ ችግሮችን ማስወገድ አልቻለም። በሥነ ምግባር ረገድ ስላለው ልል አቋምስ ምን ማለት ይቻላል? በርካታ ሰዎች ዓለም የሚያራምደው አቋም ችግሮችን ከማስወገድ ይልቅ እንደ ቤተሰብ መፈራረስና በሽታ ያሉ ሌሎች ችግሮችን እያስከተለ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በሌላ በኩል ግን የአምላክን አስተሳሰብ ለማዳበር ጥረት የሚያደርጉ ክርስቲያኖች ከቤተሰባቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ተሻሽሏል፤ ልቅ በሆነ የሥነ ምግባር አቋም ምክንያት ከሚመጡ የጤና ችግሮች ተጠብቀዋል እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር በሰላም መኖር ችለዋል። (ኢሳ. 2:4፤ ሥራ 10:34, 35፤ 1 ቆሮ. 6:9-11) ታዲያ ይህ፣ የይሖዋ አስተሳሰብ ከዓለም አስተሳሰብ የላቀ መሆኑን የሚያሳይ አይደለም? w18.11 20 አን. 8-10

ሰኞ፣ ግንቦት 18

መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል።—1 ቆሮ. 15:33

ከቤተሰባችን አባላት ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ጥረት ማድረግና እነሱን በደግነት መያዝ ቢኖርብንም እነሱን ለማስደሰት ስንል አቋማችንን እንዳናላላ መጠንቀቅ ይኖርብናል። እርግጥ ከእነሱ ጋር ተስማምተን ለመኖር ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥላለን። ሆኖም የቅርብ ወዳጅነት የምንመሠርተው ይሖዋን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ብቻ ነው። በእውነት ጎዳና ላይ የሚጓዙ ሁሉ ቅዱስ መሆን አለባቸው። (ኢሳ. 35:8፤ 1 ጴጥ. 1:14-16) ሁላችንም ወደ እውነት ቤት ስንመጣ ከመጽሐፍ ቅዱስ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ለመስማማት ስንል ማስተካከያዎች ማድረግ አስፈልጎናል። አንዳንዶች ደግሞ ትላልቅ ለውጦች ማድረግ አስፈልጓቸዋል። ያደረግነው ለውጥ ትንሽም ይሁን ትልቅ፣ አሁን ያለንን ንጹሕና ቅዱስ አቋም በዓለም ውስጥ ባለው በሥነ ምግባር ያዘቀጠ ሕይወት መለወጥ አንፈልግም። የሥነ ምግባር አቋማችንን እንድናበላሽ በሚደርስብን ተጽዕኖ እንዳንሸነፍ ምን ሊረዳን ይችላል? ይሖዋ እኛን ቅዱስ ለማድረግ ሲል በከፈለው ከፍተኛ ዋጋ ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል፤ ይሖዋ ለእኛ ሲል ውድ የሆነውን የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን ደም ከፍሎልናል። (1 ጴጥ. 1:18, 19) በይሖዋ ፊት ያለንን ንጹሕ አቋም ይዘን ለመቀጠል የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ምን ያህል ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ምንጊዜም ማስታወስ ይኖርብናል። w18.11 11 አን. 10-11

ማክሰኞ፣ ግንቦት 19

የሚያድነኝን አምላክ በትዕግሥት እጠብቃለሁ። አምላኬ ይሰማኛል።—ሚክ. 7:7

በርካታ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በአገልግሎት ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ቢኖሩም ሚዛናቸውን እንዳይስቱ እንደረዳቸው ተናግረዋል። የእነዚህ ክርስቲያኖች ምሳሌ እንደሚያሳየው ባለንበት ሁኔታ ሥር አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረጋችንና በሙሉ እምነት ይሖዋን መጠባበቃችን ውስጣዊ ሰላማችንን ጠብቀን ለመኖር ይረዳናል። እንዲያውም ካጋጠመን አዲስ ሁኔታ ጋር ለመላመድ ያደረግነው ጥረት ብዙ መንፈሳዊ ጥቅም እንዳስገኘልን እንገነዘብ ይሆናል። የአገልግሎት ምድብ ለውጥን፣ የጤና ችግርንና ተጨማሪ የቤተሰብ ኃላፊነትን ጨምሮ በሕይወታችሁ ውስጥ ያልተጠበቁ ለውጦች ሲያጋጥሟችሁ ይሖዋ እንደሚንከባከባችሁና በተገቢው ጊዜ እንደሚረዳችሁ እርግጠኞች ሁኑ። (ዕብ. 4:16፤ 1 ጴጥ. 5:6, 7) እስከዚያው ድረስ ግን ባላችሁበት ሁኔታ ሥር አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ጥረት አድርጉ። በጸሎት አማካኝነት በሰማይ ካለው አባታችሁ ጋር ተቀራረቡ፤ እንዲሁም ችግሮቻችሁን ስለ እናንተ በሚያስበው በይሖዋ ላይ መጣልን ተማሩ። እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ እናንተም ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟችሁም ውስጣዊ ሰላማችሁን ጠብቃችሁ መኖር ትችላላችሁ። w18.10 30 አን. 17፤ 31 አን. 19, 22

ረቡዕ፣ ግንቦት 20

[ይሖዋ] እንዴት እንደተሠራን በሚገባ ያውቃልና፤ አፈር መሆናችንን ያስታውሳል።—መዝ. 103:14

ይሖዋ ለአገልጋዮቹ አሳቢነት ያሳየባቸውን በርካታ ምሳሌዎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ በ1 ሳሙኤል 3:1-18 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው አምላክ ብላቴናውን ሳሙኤልን ለሊቀ ካህናቱ ለኤሊ የፍርድ መልእክት እንዲያስተላልፍ በአሳቢነት የረዳው እንዴት እንደሆነ ልብ በሉ። የይሖዋ ሕግ፣ ልጆች በዕድሜ የገፉ ሰዎችን በተለይም የሕዝብ አለቃ የሆኑትን እንዲያከብሩ ያዝዝ ነበር። (ዘፀ. 22:28፤ ዘሌ. 19:32) በመሆኑም ብላቴናው ሳሙኤል በጠዋት ተነስቶ ወደ ኤሊ በመሄድ፣ ይሖዋ የነገረውን አስደንጋጭ የፍርድ መልእክት በድፍረት ለኤሊ ማስተላለፍ ምን ያህል ሊከብደው እንደሚችል መገመት አያዳግትም! እንዲያውም ዘገባው “ሳሙኤል ራእዩን ለኤሊ መንገር ፈርቶ ነበር” ይላል። ሆኖም አምላክ፣ ሳሙኤልን እያነጋገረው ያለው እሱ መሆኑን ኤሊ እንዲያውቅ አደረገ። በዚህም የተነሳ ኤሊ ራሱ ሳሙኤልን ጠርቶ የይሖዋን መልእክት እንዲነግረውና እሱ ከነገረው ነገር ውስጥ “አንዲት ቃል እንኳ” እንዳይደብቀው አዘዘው። ሳሙኤልም በታዘዘው መሠረት ይሖዋ ያለውን “በሙሉ ምንም ሳይደብቅ ነገረው፤” ሳሙኤል የተናገረው መልእክት ቀደም ሲል ለኤሊ ከተነገረው አንድ መልእክት ጋር ተመሳሳይ ነበር። (1 ሳሙ. 2:27-36) ስለ ሳሙኤልና ኤሊ የሚናገረው ታሪክ፣ ይሖዋ ምን ያህል አሳቢና ጥበበኛ እንደሆነ ያሳያል። w18.09 23 አን. 2፤ 24 አን. 4-5

ሐሙስ፣ ግንቦት 21

ይሖዋ ሆይ፣ በድንኳንህ ውስጥ በእንግድነት የሚስተናገድ ማን ነው? . . . በልቡ . . . እውነትን የሚናገር ሰው ነው።—መዝ. 15:1, 2

በዛሬው ጊዜ ባለው ማኅበረሰብ ዘንድ ውሸት የተለመደ ነገር ሆኗል። ዩዲጂት ባተቻርጂ የተባለው ጸሐፊ “የምንዋሸው ለምንድን ነው?” በሚለው ጽሑፉ ላይ እንደገለጸው “ውሸት የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ባሕርይ እንደሆነ ተደርጎ መታየት ጀምሯል።” አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የሚዋሹት ከቅጣት ለማምለጥ አሊያም በሌሎች ዘንድ ጥሩ ግምት ለማትረፍ ሲሉ ነው። በተጨማሪም የሠሩትን ስህተትና የፈጸሙትን መጥፎ ድርጊት ለመሸፋፈን ወይም የገንዘብም ሆነ ሌላ ዓይነት ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ይዋሻሉ። ጽሑፉ እንደሚናገረው አንዳንዶች “ለሚያውቋቸው ሰዎች፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ለጓደኞቻቸው ወይም ለሚወዷቸው ሰዎች ምንም ሳይመስላቸው ቀላልም ሆነ ከባድ በሆኑ ጉዳዮች ይዋሻሉ።” ይህ ሁሉ ውሸት ምን ውጤት አስከትሏል? አለመተማመን እንዲሰፍንና በሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲበላሽ አድርጓል። መዝሙራዊው ዳዊት “ከልብ የመነጨ እውነት ደስ ያሰኝሃል” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። (መዝ. 51:6) ዳዊት ሐቀኝነት የሚመነጨው ከልብ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። እውነተኛ ክርስቲያኖች በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፍ ‘እርስ በርሳቸው እውነትን ይነጋገራሉ።’—ዘካ. 8:16፤ w18.10 7 አን. 4፤ 8 አን. 9-10፤ 10 አን. 19

ዓርብ፣ ግንቦት 22

በአስተማማኝ ሁኔታ መራቸው፤ አንዳች ፍርሃትም አልተሰማቸውም።—መዝ. 78:53

እስራኤላውያን በ1513 ዓ.ዓ. ግብፅን ለቀው ሲወጡ ቁጥራቸው ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሳይሆን አይቀርም። በሕዝቡ መካከል ልጆች፣ አረጋውያን፣ አቅመ ደካሞች እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች እንደሚኖሩ መገመት ይቻላል። እንዲህ ያለውን እጅግ ብዙ ሕዝብ ከግብፅ እየመሩ ለማውጣት አስተዋይና አሳቢ የሆነ መሪ እንደሚያስፈልግ ጥያቄ የለውም። ይሖዋም በሙሴ አማካኝነት ሕዝቡን በመምራት እንዲህ ዓይነት መሪ መሆኑን አሳይቷል። በመሆኑም እስራኤላውያን ዕድሜ ልካቸውን ከኖሩበት አገር ሲወጡ አንዳች ፍርሃት አልተሰማቸውም። (መዝ. 78:52) ይሖዋ፣ ሕዝቡን ያለአንዳች ስጋት እንዲጓዙ የረዳቸው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ከግብፅ ሲወጡ “የጦርነት አሰላለፍ ተከትለው” በተደራጀ መንገድ እንዲጓዙ አድርጎ ነበር። (ዘፀ. 13:18) ይህም ሕዝቡ በእርግጥም እየመራቸው ያለው አምላካቸው መሆኑን እንዲተማመኑ አድርጓቸው መሆን አለበት። በተጨማሪም ይሖዋ “ቀን በደመና፣ ሌሊቱን ሙሉ ደግሞ በእሳት ብርሃን” ሕዝቡን በመምራት አብሯቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ የሚታይ ማስረጃ ሰጥቷቸዋል። (መዝ. 78:14) ይሖዋ “አትፍሩ። አብሬያችሁ ሆኜ እመራችኋለሁ እንዲሁም እጠብቃችኋለሁ” ያላቸው ያህል ነበር። w18.09 26 አን. 11-12

ቅዳሜ፣ ግንቦት 23

ምነው በመቃብር ውስጥ በሰወርከኝ! . . . ቀጠሮም ሰጥተህ ባስታወስከኝ።—ኢዮብ 14:13

በጥንት ዘመን የኖሩ አንዳንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ሁኔታዎች በጣም አስጨናቂ ስለሆኑባቸው ሞትን ተመኝተው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢዮብ ሥቃዩ እጅግ ስለበዛበት “ሕይወቴን ተጸየፍኳት፤ በሕይወት መቀጠል አልፈልግም” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 7:16) ዮናስም በአገልግሎት ምድቡ ያጋጠመው ነገር በጣም ስላበሳጨው “ይሖዋ ሆይ፣ በሕይወት ከመኖር ይልቅ መሞት ስለሚሻለኝ እባክህ ግደለኝ” ብሎ ነበር። (ዮናስ 4:3) ታማኙ ነቢይ ኤልያስም በአንድ ወቅት በጣም ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ “አሁንስ በቅቶኛል! ይሖዋ ሆይ፣ . . . ሕይወቴን ውሰዳት” ብሏል። (1 ነገ. 19:4) ሆኖም ይሖዋ እነዚህን ታማኝ አገልጋዮቹን ይወዳቸው ስለነበር ሕይወታቸውን እንዲያጡ አልፈለገም። ይሖዋ፣ አገልጋዮቹን እንደዚህ ስለተሰማቸው በመንቀፍ ፋንታ ለእነሱ ያለውን ፍቅር በማሳየት አንጿቸዋል፤ ይህም ሞትን ከመመኘት ይልቅ በሕይወት ኖረው እሱን በታማኝነት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ረድቷቸዋል። w18.09 13 አን. 4

እሁድ፣ ግንቦት 24

ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን።—1 ቆሮ. 3:9

ከአምላክ ጋር የሚሠሩ ሰዎች እንግዳ ተቀባይ በመሆናቸው ተለይተው ይታወቃሉ። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “እንግዳ መቀበል” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “ለእንግዶች ደግነት ማሳየት” የሚል ፍቺ አለው። (ዕብ. 13:2 ግርጌ) የአምላክ ቃል እንግዶችን በመቀበል ፍቅር እንድናሳይ የሚያበረታቱ ዘገባዎችን ይዟል። (ዘፍ. 18:1-5) ‘በእምነት የሚዛመዱንን ሰዎችም’ ሆነ ሌሎችን ለመርዳት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ልንጠቀምባቸው ይገባል። (ገላ. 6:10) ጉባኤያችሁን የሚጎበኙ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን በእንግድነት ተቀብላችሁ በማሳረፍ ከአምላክ ጋር መሥራት ትችሉ ይሆን? (3 ዮሐ. 5, 8) እንዲህ ማድረጋችሁ ከእንግዶቻችሁ ጋር ‘እርስ በርስ ለመበረታታት’ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ይከፍትላችኋል። (ሮም 1:11, 12) የአምላክ ቃል በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንዶች፣ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለማገልገልና የበላይ ተመልካችነት ኃላፊነትን ለመሸከም በመጣጣር ከይሖዋ ጋር እንዲሠሩ ያበረታታል። (1 ጢሞ. 3:1, 8, 9፤ 1 ጴጥ. 5:2, 3) እንዲህ የሚያደርጉ ወንድሞች የእምነት አጋሮቻቸውን በመንፈሳዊም ሆነ በሌሎች መንገዶች ይረዳሉ። (ሥራ 6:1-4) አስፈላጊ የሆኑ የጉባኤ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ወንድሞች ሌሎችን መርዳታቸው ታላቅ ደስታ እንዳስገኘላቸው ይናገራሉ። w18.08 24 አን. 6-7፤ 25 አን. 10

ሰኞ፣ ግንቦት 25

ሽማግሌ የሆነውን በኃይለ ቃል አትናገረው። ከዚህ ይልቅ እንደ አባት ቆጥረህ በደግነት ምከረው።—1 ጢሞ. 5:1

ጢሞቴዎስ በዕድሜ ለገፉት ለእነዚህ ወንድሞች መመሪያ ለመስጠት የተወሰነ ሥልጣን ቢኖረውም ወንድሞቹን በደግነትና በአክብሮት መያዝ ይጠበቅበት ነበር። ይሁንና ይህን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ የሚጠበቅብን እስከ ምን ድረስ ነው? ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ሆን ብሎ ኃጢአት የሚሠራ ወይም ይሖዋን የሚያሳዝን አካሄድ የሚከተል ቢሆን ግለሰቡ በዕድሜ ስለገፋ ብቻ በዝምታ ማለፍ እንዳለብን ሊሰማን ይገባል? ይሖዋ የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት አይፈርድም፤ ስለዚህ ሆን ብሎ ኃጢአት የሚሠራን ሰው በዕድሜ ስለገፋ ብቻ በቸልታ አያልፈውም። በኢሳይያስ 65:20 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ልብ እንበል፤ ጥቅሱ “ኃጢአተኛው መቶ ዓመት ቢሞላውም እንኳ ይረገማል” ይላል። ሕዝቅኤል በተመለከተው ራእይ ላይም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል መሠረታዊ ሥርዓት እናገኛለን። (ሕዝ. 9:5-7) በመሆኑም ምንጊዜም ቢሆን በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው ጉዳይ ከዘመናት በፊት ለነበረው ለይሖዋ አምላክ አክብሮት ማሳየታችን ነው። (ዳን. 7:9, 10, 13, 14) ለይሖዋ አክብሮት የምናሳይ ከሆነ አንድ ሰው ዕድሜው ምንም ያህል ቢሆን ምክር በሚያስፈልገው ጊዜ ምክር ከመስጠት ወደኋላ አንልም።—ገላ. 6:1፤ w18.08 11 አን. 13-14

ማክሰኞ፣ ግንቦት 26

ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል።—ምሳሌ 14:15

እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ ያገኘነውን መረጃ ገምግመን ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ የመድረስ ችሎታ ማዳበር ያስፈልገናል። (ምሳሌ 3:21-23፤ 8:4, 5) እንዲህ ያለውን ችሎታ ካላዳበርን ሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም አስተሳሰባችንን በቀላሉ ሊያዛቡት ይችላሉ። (ኤፌ. 5:6፤ ቆላ. 2:8) ደግሞም ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ መድረስ የምንችለው የተሟላ መረጃ ካለን ብቻ ነው። በዛሬው ጊዜ ሰዎች በመረጃ ጎርፍ ተጥለቅልቀዋል ሊባል ይችላል። የኢንተርኔት ድረ ገጾች፣ ቴሌቪዥንና ሌሎች መገናኛ ብዙኃን ስፍር ቁጥር የሌላቸው መረጃዎችን ያቀርባሉ። በተጨማሪም ብዙዎች ከጓደኞቻቸውና ከሚያውቋቸው ሰዎች ኢ-ሜይሎች፣ የጽሑፍ መልእክቶች እንዲሁም የተለያዩ መረጃዎች በየጊዜው ይደርሷቸዋል። እርግጥ ነው፣ መልእክቶቹን የሚልኩት ሰዎች ይህን የሚያደርጉት መረጃ ለማስተላለፍ አስበው ብቻ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ሆን ብለው የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚያሰራጩና መረጃዎችን አዛብተው የሚያቀርቡ ሰዎችም አሉ። በመሆኑም የሚደርሱንን መረጃዎች በጥንቃቄ መገምገም ይኖርብናል። w18.08 3 አን. 1, 3

ረቡዕ፣ ግንቦት 27

በአምላክ ፊት ሞገስ [አግኝተሻል]።—ሉቃስ 1:30

የአምላክ ልጅ ሰው ሆኖ የሚወለድበት ጊዜ ሲደርስ ይሖዋ ማርያም የተባለችን አንዲት ትሑት ድንግል የዚህ ልዩ ልጅ እናት እንድትሆን መረጣት። ማርያም የምትኖረው ከኢየሩሳሌምና ዕፁብ ድንቅ ከሆነው ቤተ መቅደሷ ርቃ በምትገኘውና እምብዛም በማትታወቀው የናዝሬት ከተማ ውስጥ ነበር። (ሉቃስ 1:26-33) ከጊዜ በኋላ ከዘመዷ ከኤልሳቤጥ ጋር ያደረገችው ውይይት እንደሚያሳየው ማርያም ጥልቅ መንፈሳዊነት ያላት ሰው ነበረች። (ሉቃስ 1:46-55) አዎ፣ ይሖዋ ማርያምን ትኩረት ሰጥቶ ይመለከታት የነበረ ሲሆን ላሳየችው ታማኝነት ይህን ያልተጠበቀ መብት ሰጥቷታል። ከጊዜ በኋላ ማርያም ኢየሱስን ስትወልድ ይሖዋ በኢየሩሳሌምና በቤተልሔም የነበሩት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ባለሥልጣናት ወይም ገዢዎች ስለዚህ ጉዳይ እንዲያውቁ አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ከቤተልሔም ውጭ ሜዳ ላይ በጎቻቸውን ሲጠብቁ ለነበሩ እዚህ ግቡ የማይባሉ እረኞች መላእክት ተገለጡላቸው። (ሉቃስ 2:8-14) ከዚያም እነዚህ እረኞች ሄደው አዲስ የተወለደውን ሕፃን አዩት። (ሉቃስ 2:15-17) ማርያምና ዮሴፍ፣ ኢየሱስ ክብር የተሰጠው እንዲህ ባለ መንገድ እንደሆነ ሲያዩ ምንኛ ተደንቀው ይሆን! w18.07 9-10 አን. 11-12

ሐሙስ፣ ግንቦት 28

ይሖዋ በሰለሞን ላይ ተቆጣ።—1 ነገ. 11:9

ይሖዋ በሰለሞን ላይ የተቆጣው ለምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ሰለሞን ሁለት ጊዜ ከተገለጠለት . . . ከይሖዋ ልቡ ስለሸፈተ ይሖዋ በሰለሞን ላይ ተቆጣ፤ ደግሞም ሌሎች አማልክትን እንዳይከተል በማዘዝ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ አስጠንቅቆት ነበር። እሱ ግን ይሖዋ ያዘዘውን ነገር አልጠበቀም።” በዚህም የተነሳ ሰለሞን የአምላክን ሞገስና ድጋፍ አጥቷል። የሰለሞን ዘሮች አንድ በሆነው የእስራኤል መንግሥት ላይ መግዛት ያልቻሉ ከመሆኑም ሌላ ለበርካታ ትውልዶች የሚዘልቅ መከራ ደርሶባቸዋል። (1 ነገ. 11:9-13) ከሰለሞን ሕይወት ማየት እንደሚቻለው መንፈሳዊነታችንን ከባድ አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ነገሮች መካከል አንዱ የይሖዋን መሥፈርቶች ከማያውቁ ወይም ከማያከብሩ ሰዎች ጋር መወዳጀት ነው። አንዳንዶቹ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ቢሆኑም በመንፈሳዊ ደካሞች ሊሆኑ ይችላሉ። ሌሎቹ ደግሞ ይሖዋን የማያመልኩ ዘመዶቻችን፣ ጎረቤቶቻችን፣ የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም አብረውን የሚማሩ ልጆች ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ሆነ ይህ የምንቀርባቸው ሰዎች ለይሖዋ መሥፈርቶች አክብሮት ከሌላቸው በጊዜ ሂደት በአምላክ ፊት ያለንን ጥሩ አቋም ሊያበላሹብን ይችላሉ። w18.07 19 አን. 9-10

ዓርብ፣ ግንቦት 29

መላው ዓለም ግን በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው።—1 ዮሐ. 5:19

ሰይጣን የእሱን አስተሳሰብ ለማስፋፋት ፊልሞችንና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ይጠቀማል። ሰይጣን የሌሎችን ታሪክ መስማት እንደሚያስደስተን ያውቃል፤ በተጨማሪም እነዚህ ታሪኮች እኛን ከማዝናናት ባለፈ አስተሳሰባችንን፣ ስሜታችንንና ድርጊታችንን እንደሚቀርጹት ይገነዘባል። ኢየሱስ ታሪኮችን በመጠቀም ሰዎችን አስተምሯል። ስለ ደጉ ሳምራዊና ስለ አባካኙ ልጅ የተናገራቸውን ታሪኮች እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። (ማቴ. 13:34፤ ሉቃስ 10:29-37፤ 15:11-32) ሆኖም በሰይጣን አስተሳሰብ የተበከሉ ሰዎችም አስተሳሰባችንን ለማበላሸት ይህንኑ ዘዴ ሊጠቀሙ ይችላሉ። በመሆኑም ሚዛናዊ መሆን ያስፈልገናል። አስተሳሰባችንን የማይበክሉ አዝናኝና አስተማሪ ፊልሞች እንዲሁም የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች እንዳሉ የታወቀ ነው። ሆኖም ጠንቃቃ መሆን ይኖርብናል። የምንዝናናባቸውን ፕሮግራሞች ስንመርጥ ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘ይህ ፊልም ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለሥጋ ምኞቶቼ መሸነፍ ምንም ችግር እንደሌለው የሚያስተምር ነው?’ (ገላ. 5:19-21፤ ኤፌ. 2:1-3) አንድ ፕሮግራም ሰይጣናዊ አስተሳሰብን የሚያስፋፋ እንደሆነ ከተገነዘብን ምን ማድረግ ይኖርብናል? እንዲህ ያለውን ፕሮግራም ልክ እንደ ተላላፊ በሽታ በመቁጠር ልንርቀው ይገባል! w19.01 15-16 አን. 6-7

ቅዳሜ፣ ግንቦት 30

የመዳንን የራስ ቁር አድርጉ።—ኤፌ. 6:17

የራስ ቁር የወታደሩን አንጎል ከጉዳት እንደሚጠብቅለት ሁሉ ‘የመዳን ተስፋችንም’ አእምሯችንን ማለትም የማሰብ ችሎታችንን ከጉዳት ይጠብቅልናል። (1 ተሰ. 5:8፤ ምሳሌ 3:21) ሰይጣን የራስ ቁራችንን እንድናወልቅ ሊያደርገን የሚሞክረው በምን መንገድ ነው? ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ ምን እንዳደረገ እንመልከት። ኢየሱስ የሰውን ዘር የመግዛት ተስፋ እንዳለው ሰይጣን አውቆ መሆን አለበት። ሆኖም ኢየሱስ ይህ ተስፋ እንዲፈጸምለት፣ ይሖዋ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ መጠበቅ ይገባዋል። ከዚያ በፊት ደግሞ ተሠቃይቶ መሞት ነበረበት። ሰይጣን ግን የኢየሱስ ተስፋ ቶሎ እንዲፈጸም የሚያደርግ ግብዣ አቀረበ። ሰይጣን፣ ኢየሱስ አንድ ጊዜ ተደፍቶ ቢያመልከው የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ወዲያውኑ እንደሚሰጠው ነገረው። (ሉቃስ 4:5-7) ዛሬም በተመሳሳይ ይሖዋ በአዲሱ ዓለም ብዙ አስደናቂ ነገሮችን እንደሚሰጠን ቃል መግባቱን ሰይጣን ያውቃል። ሆኖም ይህ ተስፋ እስኪፈጸምልን መጠበቅ ያስፈልገናል፤ ያ ጊዜ እስኪደርስ ደግሞ የተለያዩ መከራዎች ያጋጥሙን ይሆናል። ሰይጣን ይህን ስለሚያውቅ በአሁኑ ጊዜ የተመቻቸ የሚባለውን ሕይወት እንድንመራ አጓጊ ግብዣዎች ያቀርብልናል። የምንፈልገውን ነገር ሁሉ አሁኑኑ ለማግኘት ጥረት እንድናደርግ ይፈልጋል። በመሆኑም በሕይወታችን ውስጥ ቁሳዊ ነገሮችን እንድናስቀድምና ለአምላክ መንግሥት ሁለተኛ ቦታ እንድንሰጥ ሊያደርገን ይሞክራል።—ማቴ. 6:31-33፤ w18.05 30-31 አን. 15-17

እሁድ፣ ግንቦት 31

[በወጣትነትህ] ዘመን ልብህ ደስ ይበለው።—መክ. 11:9

በእርግጥም ይሖዋ በወጣትነት ዘመንህ ደስተኛ እንድትሆን ይፈልጋል። በመንፈሳዊ ግቦች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዲሁም ዕቅድ ስታወጣና ውሳኔ ስታደርግ የይሖዋን ምክር መከተል ይኖርብሃል። ከልጅነትህ ጀምሮ ይህን ካደረግህ የይሖዋን አመራር፣ ጥበቃና በረከት ታገኛለህ። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ግሩም ምክሮች በጥሞና አስብባቸው፤ እንዲሁም “በወጣትነትህ ጊዜ ታላቁን ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን ምክር በተግባር አውል። (መክ. 12:1) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ይሖዋን በማገልገል ላይ ያተኮረ ሕይወት ለመምራት ስለቆረጡ ከፍተኛ አድናቆት ይገባቸዋል። ወጣቶች መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረጋቸውና ለስብከቱ ሥራ ቅድሚያ መስጠታቸው በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሕይወት ለመምራት ያስችላቸዋል። ከዚህም ሌላ ይህ ዓለም ትኩረታቸውን እንዳይከፋፍለው ይጠነቀቃሉ። ወጣቶች ልፋታቸው ከንቱ እንደማይሆን መተማመን ይችላሉ። አፍቃሪ የሆኑ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ይደግፏቸዋል፤ ሕይወታቸውን ለይሖዋ አደራ ከሰጡ ዕቅዳቸው ሁሉ ይሳካል። w18.04 29 አን. 17, 19

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ